EBS TV
Kanalga Telegram’da o‘tish
4 586
Obunachilar
-124 soatlar
-57 kun
+3730 kun
Postlar arxiv
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
+1
🚗
በአዲስ አበባ በአንድ ቀን ውስጥ በደረሱ ሦስት የትራፊክ አደጋዎች የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና በ12 ሰዎች ላይ ደግሞ አካል ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
አደጋዎቹ የደረሱት በአዲስ አበባ ን/ስ/ላ/ክ/ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ነው።
1. ጀሞ ቅዱስ ሚካኤል መብራት ከቀኑ 9፡30 አካባቢ የጉዞ አቅጣጫውን ከአየር ጤና ወደ ጀርመን አደባባይ ያደረገ የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 3-08136 ኢት ሲኖትራክ ተሽከርካሪ መብራት ይዟቸው ቆመው የነበሩ 10 ተሽከርካሪዎችን እና የመብራት ፖል ገጭቷል። በአደጋው በትራንስፖርት ተሽከርካሪ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ የ44 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አንዲት እናት ሞተዋል። በአንድ ሌላ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ላይ ከባድ የአካል ጉዳት እንዲሁም በ11 ሰዎች ላይ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል።
2. ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ ደግሞ ጀሞ ሦስት አካባቢ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2A-43228 አ/አ ፒክአፕ ተሽከርካሪ ይዞ ከጀሞ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ጀሞ ሶስት ሲጓዝ የነበረ አሽከርካሪ ከቀኝ ወደ ግራ ሲሻገር በነበረ ግለሰብ ላይ የሞት አደጋ አድርሷል።
3. በዕለቱ ከምሽቱ 4፡30 አካባቢ ደግሞ ሀጫሉ መንገድ አካባቢ የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 3-52305 አ/አ ሀዩንዳይ ተሽከርካሪን በመያዝ ወደ ጋርመንት እያሽከረከረ የነበረ ግለሰብ ከመንገድ ጠርዝ ጋር በመጋጨት የአሽከርካሪው ህይወት አልፏል።
በክ/ከተማው በተለያዩ አካባቢዎች በአንድ ቀን ብቻ በደረሱ አደጋዎች የሦስት ሰዎች ህይወት አልፏል። አሽከርካሪዎች እና እግረኞች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ፖሊስ መልዕክት አስተላልፏል።
ጥቅምት 8 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
#USA
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙትን ጥቃቶች ከተገንጣይ ቡድኖች እንቅስቃሴ እና ከሽብር ተግባራት ጋር አያይዘውታል።
ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር እየተዋጉ የሚገኙትን ኃይሎች "ተገንጣይ ቡድን" (separatist) በማለት የገለፁ ሲሆን፣ በሀገሪቱ ውስጥ ጥቃት የሚፈጽሙ ተገንጣይ ቡድኖች በመኖራቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ለነዚህ ጥቃቶች ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ዋና ከተማን አዲስ አበባን ዒላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት መፈፀሙን በመጠቆምም ድርጊቱን #ከሽብርተኝነት ጋር አያይዘውታል።
" ማንም ቢሆን ሽብርተኝነትን፣...በዋና ከተማቸው ላይ የተፈጸመውን የድሮን ጥቃቶች ጨምሮ የሚደግፍ የለም " ሲሉ የሽብር ተግባሩን አውግዘዋል።
አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት ከእነዚህ " ተገንጣይና የሽብር ተግባር ከሚፈጽሙ ኃይሎች " የሚሰነዘርበትን ፈተና በሚገባ እንደምትረዳ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አረጋግጠዋል።
በተገንጣይ ቡድኖች እንቅስቃሴ እና በተወሰዱት ምላሾች ምክንያት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ድንበሮች አቅራቢያ የጦር ኃይሎች ክምችት መጨመሩን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ሁለቱም ሀገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ድንበር ማስጠጋታቸው ሌሎች ጎረቤት ሀገራትን ጭምር የሚያካትት ሰፊ ቀጠናዊ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል በሚል ስጋታቸውን አመልክተዋል።
አሜሪካ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ጥላቸው የነበሩ አነስተኛ የጦር መሣሪያ ማዕቀቦችን ያነሳችው ከሁለቱም ወገኖች ጋር በመነጋገር የሰላም አስከባሪነት እና የአደራዳሪነት ሚናዋን ለመወጣት እንደሆነና ይህም ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌለው አስረድተዋል።
አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ላለፉት ዓመታት የጠበቀ ግንኙነት ያልነበራት ቢሆንም፣ ባለፉት ጥቂት ወራት ከተለመደው የተሻለ የሐሳብ ልውውጥ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማድረግ መቻሉን የገለጹት በአንጻሩ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር እጅግ የጠበቀና ጠንካራ ግንኙነት እንዳላት ተናግረዋል።
ሩቢዮ፣ በዚህ ሳምንት በግላቸው ከኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተው ሀገራቸው ኢትዮጵያ ከተገጣይ ኃይሎች የሚገጥማትን ፈተና በአግባቡ እንደምትረዳ ጠቁመዋል።
ነገር ግን መንግሥት ለተገንጣይ ቡድኖች ጥቃት የሚሰጠው ምላሽ ጥበብ የተሞላበት እና ሚዛናዊ ሊሆን እንደሚገባው፤ እምርጃው ሌሎች ሀገራትን ጭምር አሳትፎ ወደ አውዳሚ እና የሰፋ ጦርነት እንዳያመራ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል።
" ዓለም በአሁኑ ሰዓት ሌላ ተጨማሪ ጦርነት አይፈልግም " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ጥቅምት 8 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
+1
" ተደራጅተው ቤት ተከራይተው፣ በተለያየ ሰው ስም የወጣ የባንክ አካውንትና ሲም ካርድ በመጠቀም ነበር ሲያጭበረብሩ የነበረው " - ፖሊስ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በ658 ዜጎች ላይ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ በሞባይል ባንኪንግ ማጭበርበር የፈፀሙ 37 ተጠርጣሪዎችን ፦
🚙 ከ9 ተሽከርካሪዎች፣
📱 114 ስልኮች፣
👍478 ሲም ካርዶች ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጿል።
ተጠርጣሪዎቹ በቡድን በመደራጀት የባንክ የቴክኒክ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኛ በመምሰል ፦
📞 " ሽልማት ደርሶዎታል "
📞 " ሞባይል ባንኪንግ ሲስተም ልናዘምንልዎት ነው "
📞 " የባንክ ሂሳብዎን ከፋይዳ መታወቂያዎ ጋር ለማስተሳሰር ነው " በሚል ስልክ በመደወል የይለፍ ቃል፣ OTP ፣ PIN ወይም ሌሎች ሚስጥራዊ መረጃዎችን በመጠየቅ እና የተለያዩ ማጭበርበሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም ሲያጭበረብሩ እንደነበር ፖሊስ አሳውቋል።
በቡድን የተደራጁት ተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤት በመከራየት፣ በተለያዩ ሰዎች ስም የወጣ በርካታ የባንክ አካውንትና ሲም ካርዶችን ከግለሰቦች ላይ በመግዛት እና በመከራየት የወንጀል ተግባሩን ይፈፅሙ እንደነበር ፖሊስ በምርመራ እንደደረሰበት አሳውቋል።
በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በአጭበርባሪዎቹ ጉዳት የደረሰበት ማንኛውም ሰው በEFPApp፣ በ991፣ በSPS እንዲሁም በአካል በወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ቢሮ በመቅረብ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።
ባንኮች በግል ስልክ ደውለው አገልግሎት እንደማይሰጡ ያሳሰበው ፖሊስ፣ ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገር ሲያጋጥመው በ991፣ በEFPApp ወይም በአካል ጥቆማ እንዲሰጥ መልዕክት አስተላልፏል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ጥቅምት 7 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
🇫🇷
በፈረንሳይ የኑሮ ውድነት መጨመርን ፣ የነዳጅ ዋጋ መናርን እና የመንግስት አገልግሎቶች ማሽቆልቆልን በመቃወም የተካሄደው ሰልፍ ወደ ከባድ ሁከት ተቀየረ።
በፓሪስና በርካታ የሀገሪቱ ከተሞች በተቀሰቀሰው አደገኛ ሁከት ሰልፈኞች ተሽከርካሪዎችን እና ህንፃዎችን በእሳት አቃጥለዋል።
ከ500 ሺህ በላይ የሚቆጠሩ ዜጎች በተሳተፉበት በዚህ ተቃውሞ በርካታ ዓለም አቀፍ ብራንድ የሆኑ መደብሮች እና ተቋማት መዘረፋቸው የተዘገበ ሲሆን፤ በተለይም በሊሞዥ ከተማ የሚገኝ ከ140 ዓመት በላይ የቆየ ታሪካዊ ህንፃ ሙሉ በሙሉ በእሳት መጋየቱ ታውቋል።
ለተከሰተው ሁከት፣ ዝርፊያ እና ውድመት ምላሽ የሰጡት የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፤ " ፈረንሳይ ውስጥ ለሁከት ቦታ የለም " ብለዋል። አያይዘው ንብረቶችን ያወደሙ፣ የንግድ ተቋማትን የዘረፉ አካላት ሁሉ ተለይተው በህግ እንደሚቀጡ አሳውቀዋል።
ቪድዮ ፦ ከማኅበራዊ ሚዲያ
ጥቅምት 7 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
+1
#Mekelle 📍
የመቐለን ሰላምና ጸጥታ ማስጠበቅ ፣ ሰብዓዊ ድጋፍና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን መስጠት ቀዳሚ የሥራ አቅጣጫዎቻቸው እንደሆነ በትግራይ ባለአደራ አስተዳደር የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሆነው የተሾሙት ሽሻይ አማረ (ዶ/ር) አሳውቀዋል።
ከንቲባ ሽሻይ (ዶ/ር) ይህንን ያሳወቁት በይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰራጩት መልዕክት ነው።
በመቐለ የኮሪደር ልማት ለመገንባት በፌዴራል መንግሥት ቃል መገባቱንም ከንቲባው አሳውቀዋል።
"በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከቤተመንግሥት ሳንወጣ ቃል የተገባልንን ኮሪደር እንሰራለን ፤ መቐለንም እናስውባለን " በማለት የኮሪደር ልማቱን ለማስፈጸም ቃል ገብተዋል።
" በመላው ትግራያችንም እንደ መቐለ ከተማ የምናበረክተውን እናበረክታለን " ብለዋል።
ከንቲባው በሽግግር ወቅት የመቐለን ሕዝብ ለማገልገል በፌዴራል መንግሥት የተሰጣቸው አደራ ለእሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የመቐለ ለውጥ ፈላጊዎች የተሰጠ አደራ መሆኑን ገልጸዋል።
" አብረን አደራችንን እንደምንወጣ እምነቴ ነው " ብለዋል።
ሽሻይ አማረ (ዶ/ር) በትግራይ ጦርነት ወቅት ወደ በረሃ ከወረዱ የህወሓት አመራሮች መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ በኋላም ለአጭር ጊዜ የትግራይ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።
ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በህወሓት አመራሮች መካከል በተፈጠረው ክፍፍል ፣ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራውን የለውጥ ኃይል ከደገፉ አመራሮች መካከል ይጠቀሳሉ።
በመጋቢት 2017 ዓ.ም. በትግራይ የፖለቲካ ብልሽት ምክንያት የአቶ ጌታቸው ረዳ አስተዳደር ከክልሉ ወደ አዲስ አበባ ከተባረረ በኋላ ፣ ሽሻይ አማረ (ዶ/ር) የትግራይ ስምረት ፓርቲን ከመሠረቱ አመራሮች መካከል አንዱ ሆነዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መቐለ
ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
ድሬዳዋ አስተዳደር በምግብ፣ መድኃኒትና ጤና አገልግሎቶች ላይ አዲስ የክፍያ ተመን መመሪያ አወጣ።
የድሬዳዋ ጤና ቢሮ " ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል " ያለውን ወቅታዊ ወጪ ታሳቢ ያደረገ አዲስ የአገልግሎት ክፍያ ተመን መመሪያ (መመሪያ ቁጥር 20/2019) አዘጋጅቶ ይፋ አድርጓል።
መመሪያው በምግብ ፣ በመድኃኒት ፣ በጤና ተቋማት ፣ ጤና ነክ አገልግሎቶች እና በጤና ባለሙያዎች ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ተፈጻሚ ይሆናል።
ክፍያውን በጥሬ ገንዘብ ፣ በባንክ ፣ በዴቢት ክሬዲት ካርድ ወይም በዲጂታል /ኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴዎች መፈጸም እንደሚቻል ተገልጿል
ዋና ዋና የክፍያ ተመኖች
1. የጤና ተቋማትና መድኃኒት ቤት የብቃት ማረጋገጫ
• አጠቃላይ ሆስፒታል ፦ ለአዲስ ፈቃድ 2,500 ብር | ለእድሳት 1,250 ብር
• የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና ፋርማሲ ፦ ለአዲስ ፈቃድ 2,000 ብር | ለእድሳት 1,000 ብር
• መካከለኛ ክሊኒክ ፦ ለአዲስ ፈቃድ 1,500 ብር | ለእድሳት 750 ብር
2. የጤና ባለሙያዎች ምዝገባና ፈቃድ
• ሁለተኛ ዲግሪ፣ ስፔሻላይዜሽንና ዶክትሬት፦ ለአዲስ ፈቃድ 500 ብር | ለእድሳት 250 ብር
• የመጀመሪያ ዲግሪ፦ ለአዲስ ፈቃድ 400 ብር | ለእድሳት 200 ብር
• ዲፕሎማ፦ ለአዲስ ፈቃድ 200 ብር | ለእድሳት 100 ብር
3. የምግብና መጠጥ ተቋማት
• ባለኮከብ ሆቴሎች እና የምግብ አምራቾች ፦ ለአዲስ ፈቃድ 3,000 ብር | ለእድሳት 1,500 ብር
• መደበኛ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች እና ሱፐር ማርኬቶች ፦ ለአዲስ ፈቃድ 2,000 ብር | ለእድሳት 1,000 ብር
• አነስተኛ የምግብና ካፌ ተቋማት ፦ ለአዲስ ፈቃድ ከ1,000 እስከ 1,500 ብር
4. የውበትና አገልግሎት ተቋማት
• ከፍተኛ የውበት ሳሎኖች ፣ ማሳጅ፣ ስፓ እና ሳውና ባዝ ፦ ለአዲስ ፈቃድ 2,000 ብር | ለእድሳት 1,000 ብር
5. የተወገዱ ምርቶች ማረጋገጫ ሰርተፊኬት
• አገልግሎት የማይሰጡ መድኃኒቶችና ኮስሞቲክስ ፦ ከ1–100 ኪ.ግ (1,000 ብር) | ከ100–1000 ኪ.ግ (2,000 ብር)
• የተወገደ ምግብ ፦ ከ1 ቶን በታች (500 ብር) | ከ1–10 ቶን (1,500 ብር) | ከ100 ቶን በላይ (እስከ 6,000 ብር)
(ተጨማሪ የክፍያ ተመኖችን ከላይ በተያያዘው ፋይል ይመልከቱ)
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
+5
🌶️
" ...ማህበረሰቡ ምርቶችን ሲገዛ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ወይ ? ጥራቱ ምን ያህል ነው ? ከየት ነው የምገዛው ? የት ነው ንጹህ ምርት ያለው ? ብሎ በደንብ ማየት አለበት " - ጽ/ቤቱ
በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ከፍተኛ አፍላቶክሲን (ካንሰር ጭምር ሊያመጣ የሚችል ፈንገስ ወይም ሻጋታ የሚያመርተው ንጥረነገር ነው፡፡ መርዝ ማለት ይቻላል) መጠን የተገኘበት 69 ኩንታል የተበላሸ በርበሬ መወገዱን የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የኮልፌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።
ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ውሏል።
የተበላሸ የበርበሬ ምርት ስለመኖሩ መረጃው የተገኘው ከማኅበረሰቡ በመጣ ጥቆማ መሆኑን እና መጋዘኑ ተሰብሮ በርበሬው እንዳይወሰድ በፖሊስ የ24 ሰዓት ጥበቃ ሲደረግበት እንደነበር የጽ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙኒራ ነጋሽ ተናግረዋል።
" የተወሰደው የበርበሬ ናሙና የላቦራቶሪ ምርመራ ሲደረግበት የአፍላቶክሲን መጠኑ እጅግ ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል " ብለዋል።
በርበሬ ሲሻግት በራሱ የተለያዩ ችግሮችን ያመጣል ያሉት ሥራ አስኪያጇ፤ በአንድ የበርበሬ ምርት ላይ ሊኖር የሚገባው ትክክለኛ የአፍላቶክሲን መጠን 10 መሆኑንና ከዚህ በትንሹ እንኳ ከጨመረ ምርቱ ጤነኛ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
ይህ ምርት በሰው ልጅ ጤና ላይ ከፍተኛ እክል የሚያስከትል በመሆኑም ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት 69 ኩንታል ምርት በትናንት በስቲያ እንዲወገድ ተደርጓል ብለዋል።
የተበላሸውን በርበሬ ወደ ማኅበረሰቡ ሊያሰራጭ የነበረው ግለሰብ ከባለሥልጣኑ የብቃት ማረጋገጫ ያልወሰደ ፤ የምርቱ ጥራትና ደኅንነት ያልተረጋገጠ በዓይን ሲታይም የበርበሬነት ባህሪ የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።
" እርምጃው የተወሰደው በግብረ-ኃይል ነው፣ ምርቱ የጤና ጠንቅ መሆኑን የሚገልጽ ማብራሪያ ለፖሊስ ተጽፎ ግለሰቡ ፍርድ ቤት ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ የሕግ ሂደቱ እየተከናወነ ይገኛል " ሲሉ አብራርተዋል።
አክለውም፣ ተጠርጣሪው ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ የተበላሸ በርበሬ ወደ ማኅበረሰቡ አሰራጭቶ እንደሆነ አሁን ላይ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፣ ጉዳዩ እንደሚጣራ ገልጸዋል።
" ለማኅበረሰቡ የጤና ችግር የሚሆኑ ምርቶች ላይ ርኅራኄ የለንም፤ እርምጃ መውሰዳችንንም አናቆምም፣ ሕገ-ወጥ ምርቶች መመረታቸው እስኪቆም ድረስ ቁጥጥሩ ይቀጥላል " ብለዋል።
" ማህበረሰቡ ምርቶችን ሲገዛ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ወይ ? ጥራቱ ምን ያህል ነው? ከየት ነው የምገዛው ? የት ነው ንጹህ ምርት ያለው? ብሎ በደንብ ማየት አለበት። በተደበቁ ሰፈሮች እና በየጉራንጉሩ ተደብቀው ከሚሸጡ ለጤና ጠንቅ ከሆኑ ምርቶች ማህበረሰቡ እራሱን መጠበቅ አለበት " ሲሉ አሳስበዋል።
በበርበሬ ምርቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም ምርቶች ላይም እንደዚህ አይነት ነገሮች ስትመለከቱ በነጻ ስልክ መስመር 8864 ላይ በነጻ እየደወላችሁ ጥቆማ ስጡን ብለዋል።
" የጤና ችግር የሚያስከትሉ ሁሉንም ምርቶችን ለመቆጣጠር 24 ሰዓት ዝግጁ ነን ፣ ከጎናችን ቁሙ፣ ምርቶችንም ስትገዙ ጥንቃቄ አድርጉ " ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ
ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiooia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
+1
#Tigray
በእነ ሌ/ጄነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ የሚመራው እና በትግራይ ክልል የሽግግር ሂደቶችን ለማመቻቸት ሲንቀሳቀስ የነበረው "የትግራይ ሰላም እና ለውጥ ምክር ቤት" ከአሁን በኋላ "በተቋቋመበት አደረጃጀት" እንደማይቀጥል አስታወቀ።
ምክር ቤቱ የማይቀጥለው፣ ፌደራል መንግሥት በክልሉ ቀጣይ የሽግግር ተግባራትን የማከናወን ተግባርን "ራሱ ሊይዘው በመወሰኑ" እንደሆነ ገልጿል።
ምክር ቤቱ፣ አሁን በትግራይ ክልል የሚታየው " ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ድል " እንዲገኝ የበኩሉን መወጣቱን አመልክቷል።
ግንቦት 2018 ዓ.ም. የተመሠረተው ይህ ምክር ቤት ከህወሓት የተለዩ እና የተቃረኑ ፖለቲከኞች እንዲሁም የትግራይ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የያዘ ነበር።
የምክር ቤቱ አባል ከሆኑት ስምንት ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩት ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ (ስምረት) ነው።
ከህወሓት በተለዩ አመራሮች የተመሠረተው ሌላኛው ፓርቲ ወለዶ ትግራይ እንዲሁም አረና ትግራይ ለዴሞክራሲ እና ሉዓላዊነት (አረና) እና ትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲዎችም ይጠቀሳሉ።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ " ከአስር በላይ የሲቪል ማኅበራት፣ የሚዲያ አካላት እና የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተደራዳሪ ግለሰቦችም " የምክር ቤቱ አባል ነበሩ።
በምክር ቤቱ ሥር የተቋቋሙ ኮሚቴዎችን የሚመሩት ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ናቸው።
ይህ ሰላም እና ለውጥ ምክር ቤት እስካሁን ሲንቀሳቀስበት በነበረው አደረጃጀት እንደማይቀጥል ያሳወቀው፣ የፌደራል መንግሥት ዛሬ አርብ ጥቅምት 6/2019 ዓ.ም. ትግራይ ክልልን ለሚቀጥሉት 6 ወራት የሚመራ ባለአደራ አስተዳደር ማቋቋሙን ካስታወቀ ከሰዓታት በኋላ ነው።
Via BBC Amharic
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
+1
" በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተጣርቶ ውጤቱ ለጥቅምት 13/2019 ዓ/ም እንዲቀርብ ተቀጥሯል " - ጠበቃ አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ
" የይቅርታ ሰነድ ላይ አንፈርምም " በሚል በእስር ላይ ከቆዩት እስረኞች መካከል አቶ ዮሐንስ ቧያሌው እና ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በተለምዶ "ታንከር" በሚባለው "የቅጣት ቤት" እንዲገቡ ተደረጉ መባሉ ይታወሳል።
የቅጣት ቦታ "ውሃ እና መብራት የሌለው" መሆኑን የታሳሪ ቤተሰብ እና ጠበቃቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸው ነበር።
ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ወደ ማረሚያ ቤቱ ሄደው ባደረኩት ምልከታ አቶ ዮሐንስ ጋዜጠኛ ዳዊት "ታንከር" በሚባለው ቦታ እንዲገቡ መደረጋቸውን እንዳረጋገጡ፣ ለፍርድ ቤት አቤቱታ አስገብተው ለዛሬ ተቀጥሮ መሰጠቱን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ገልጸው ነበር።
በዛሬው ቀጠሮ ምን ተባለ ?
ጠበቃ ሰለሞን፥ ፍርድ ቤት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ኮማንደር ጣሰው ለዛሬ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ መስጠቱን ትናንት ገልጸውልን የነበረ ሲሆን፣ በትዕዛዙ መሰረት ኃላፊው መቅረባቸውን ዛሬ ነግረውናል።
እነ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው ያሉበት ቦታ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያጋልጥና የማይመች መሆኑን ቢገልጹም፣ የማረሚያ ቤት ኃላፊው " እንደተባለው ቦታው አስቸጋሪ አይደለም " በሚል መከራከራቸውን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
በዚህም፣ " አቶ ዮሐንስ 'ቦታው መንቀሳቀሻ የለውም ጠባብ ነው። የፀሐይ ብርሃን የለውም፤ ፀሐይ ባለማግኘቴ እጄን አሞኛል' " እንዳሉ፣ " ኮማንደር ጣሰው ደግሞ ቦታው 'የተወሰነ ፀሐይ አለው፤ አነስተኛም ቢሆን መንቀሳቀሻ አለው' " ማለታቸውን አስረድተዋል።
በመሆኑም፣ " 'ቦታው የቅጣት ቦታ ነው ወይስ አይደለም ? መብራት አለው ወይስ የለውም ? ጠባብ ነው ወይስ አይደለም ? መንቀሳቀሻ አለው ወይስ የለውም ? ' የሚሉት ጉዳዮች አጨቃጫቂ ስለሆኑ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተጣርቶ ውጤቱ ለጥቅምት 13/2019 ዓ/ም እንዲቀርብ ተቀጥሯል" ሲሉ አቶ ሰለሞን ነግረውናል።
በተያያዘ፣ በእነ አቶ ዮሐንስ መዝገብ ስር ባሉት ተከሳሾች ዛሬ የብይን ቀጠሮ እንደነበር አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
ከ52 ተከሳሾች መካከል 36ቱ በሌሉበት፣ 16ቱ በችሎት ተገኝተው ሲከታተሉ እንደነበር፣ ከ16ቱ 12ቱ ቅድመ ሁኔታ ላይ ፈርመው እንደወጡ፣ 'አንፈርምም' ብለው ለቀሩት አራት ተከሳሾች ፍርድ ቤት በክስ መገባችሁ "ተከላከሉ" ብሎ ዛሬ ብይን መስጠቱን አስረድተዋል።
በክስ መዝገባቸው ተከላከሉ የሚል ብይን የተሰጠባቸው ተከሳሾች፦
- ጋዜጠኛ አባይ ዘውዱ፣
- አቶ ዮሐንስ ቧያሌው፣
- አቶ ደሳለኝ እጅጉ፣
- ዶ/ር ዘሪሁን ባህሪው ናቸው።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
ቪድዮ፦ የቴስላ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢሎን ማስክ በቴክሳስ በሚገኘ የስፔስ ኤክስ የሙከራ ማዕከል " በአየር ላይ መብረር ይችላል " ያሉትን አዲስ የኤሌክትሪክ መኪና ይፋ አደረጉ።
በሮኬት አይነት አስወንጫፊዎች የታገዘው 'ቴስላ ሮድስተር' የተሰኘው ይህ የሁለት ሰው የስፖርት መኪና በኤሌክትሪክ መኪና ኩባንያው ቴስላ እና በስፔስ ኤክስ የሮኬት ቴክኖሎጂ ትብብር የተሰራ መሆኑን ኤሎን መስክ ገልጸዋል።
ይህ ድንቅ መኪና በሰዓት ከ0 እስከ 97 ኪ/ሜ ያለውን ፍጥነት ከ1 ሰከንድ ባነሰ ጊዜ (በ0.8 ሰከንድ) ውስጥ መጓዝ ይችላል።
የላቀ የአየር ግፊት እና የታመቀ አየር ማስወጫ ቴክኖሎጂን በመጠቀም፦
- ቁልቁል ተደፍቶ/የላይኛውን አካሉን ወደታች ዘቅዝቆ የመጓዝ፣
- ከከፍታ ላይ ዘሎ አየር ላይ የመቆየት፣
- ከመሬት ላይ ተነስቶ አየር ላይ የመንሳፈፍ፣
- አየር ላይ የመሽከርከር፣ የመገለባበጥ እንዲሁም አቅጣጫውን መቀየር የሚያስችል ችሎታዎች አሉት ተብሏል።
በሙከራው ወቅት ሊከሰት የሚችል የአደጋ ስጋት ለመቀነስ እና የሰዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ሙከራው ሙሉ በሙሉ ሰው አልባ (ያለ አሽከርካሪ) ነው የተከናወነው።
ኢሎን ማስክ እንደገለጹት ተሽከርካሪው በ2028 ወደ ምርት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
የዘርፉ ባለሙያዎች የሮኬትና መኪናን ቴክኖሎጂ አዋህዶ ረጅም ርቀት የማንሳፈፍ / የመብረር አቅሙን በተግባር ማረጋገጥ ከፍተኛ የቴክኒክ ፈተና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ሲኤንኤን
ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
#Tigray
የትግራይ የሰላም ኃይል (TPF)ን የሚመሩት ብ/ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር በየነ (ወዲ አንጥሩ) ዛሬ በተቋቋመው የስድስት ወር የትግራይ ባለአደራ አስተዳደር የጸጥታና ሰላም ዋና አስፈጻሚ ተደርገው ተሹመዋል።
ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
+1
የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ተመሰረተ።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ም/ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና በዐዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 14/2/ለ/ መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ባስተላለፈው ውሳኔ እና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰጠው ሥልጣን መሠረት የኢፌዴሪ መንግሥት የትግራይ ክልልን የሚያጸና ውሳኔ ወስኗል።
ዛሬ የፌዴራል መንግሥት ባወጣው መግለጫ ፤ " በትግራይ ክልል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ለመፍታት የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት በሕወሓት ዕንቅፋትነት የተነሣ ሳይሳካ ቀርቷል " ብሏል።
" ሰላምን ያልፈለገው የሕወሐት አመራር ለአራተኛ ጊዜ የጀመረው አውዳሚ ጦርነት ለአራተኛ ጊዜ በሕወሓት ሽንፈት ተጠናቋል " ያለው የፌዴራል መንግሥት ፥ " የትግራይ ሕዝብ የራቀውን ሰላም እንዲጎናጸፍ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱ እንዲረጋገጥ፣ እንዲሁም ላለፉት በርካታ ዓመታት ያላገኛቸውን የልማት ትሩፋቶች ለማጣጣም እንዲችል ከግጭት አዙሪት መውጣት አለበት " ሲል ገልጿል።
" ለዚህ ደግሞ በፌዴሬሽኑ ውስጥ የሚገባውን ቦታ አግኝቶ ሰላሙን ማስከበር፣ ትኩረቱን በልማት ላይ ማድረግና ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ጸንቶ መኖር አለበት " ብሏል።
እነዚህን ሁኔታዎች ባጠረ ጊዜ ለማመቻቸት እንዲቻል የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሠረት መመስረቱን ይፋ አድርጓል።
ይህ የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር ለሚቀጥሉት ስድስት (6) ወራት ትግራይን የሚያስተዳድር ይሆናል።
የባለአደራ አስተዳደሩ ዋና ተግባራት ምን ምን ናቸው ?
1. በትግራይ ክልል ውስጥ ተፈጥሮ ያለውን የሰላምና የመረጋጋት ችግር በፍጥነት በመፍታት የተረጋጋ ሁኔታን መፍጠር፣
2. የፈረሱ የመንግሥት መዋቅሮችን መልሶ በመዘርጋት ሕዝቡ የመደበኛ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር፤
3. በጦርነት ምክንያት የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን በመጠገንና ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ በሀገር ደረጃ የሚታዩ የልማት ትሩፋቶች ትግራይ ውስጥም መስፋፋት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤
4. የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደየቀያቸው መመለስ፤
5. በክልሉ ውስጥ ተቋርጠው የነበሩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ ማድረግ፤
6. እንዲሁም የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ተፈጥሮ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ነጻና ግልጽ ምርጫ ተከናውኖ ትግራይ የፌዴሬሽኑ መደበኛ አካል የምትሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤
7. ከፌዴራል የመከላከያ፣ የፖሊስና የደኅንነት ተቋማት እንዲሁም ከትግራይ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ከክልል እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ውስጥ የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በማስረከብ ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱና ተሐድሶ እንዲያደርጉ ሁኔታውን ማመቻቸት፣ የክልሉን የጸጥታ መዋቅር እንደ አዲስ የማዋቀር ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡
8. ሰላም እንዲጸና ፣ የሕዝቡ ሥነ ልቡና እንዲስተካከልና ወደ ልማትና የመልሶ ግንባታ ሥራ ለመግባት የሚያስችለው ዝግጁነት እንዲኖረው ማድረግ፤
9. የሚዲያ ሥራዎችን የማስተባበር፤ በየደረጃው የሚደረጉ የሕዝብ መድረኮችን የማዘጋጀት፤
10. ለቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊና አካታች እንዲሆን የሚያስችሉ ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነት አለበት፡፡
የባለአደራ አስተዳደሩ በሚያከናውናቸው ሁሉም ተግባራት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት፣ የትግራይ ሕዝብን መሠረታዊ ጥቅሞች መሠረት ማድረግ አለበት ተብሏል።
በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስከሚቋቋም ድረስ የክልሉን የዕለት ተዕለት አገልግሎቶች ከማቅረብና ለቀጣይ ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎችን ከመፍጠር በዘለለ ረዘም ያለ ስትራቴጂያዊ አንድምታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ እንደማይንቀሳቀስ ተገልጿል።
ተግባሩን ከፌዴራል መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ እና መመሪያ መሠረት እንደሚያከናውን ተመላክቷል።
የባለአደራ አስተዳደሩ ዋና አስፈጻሚዎች ፦
1. አቶ አሰፋ አብርሃ ሐጎስ - የአስተዳደር እና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈጻሚ
2. ዶክተር ቴዎድሮስ አረጋይ ወ/ሥላሴ - የኢኮኖሚ እና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ
3. ብ/ጄ ገብረእግዚአብሔር በየነ ኃይሉ - የጸጥታና ሰላም ዋና አስፈጻሚ
4. አቶ ረዳኢ ኃለፎም ወ/ሥላሴ - የፖለቲካ እና ሕዝብ አደረጃጀት ዋና አስፈጻሚ
5. ዶክተር ሽሻይ አማረ - የመቐለ ከተማ ከንቲባ ሆነው ተሹመዋል።
ተሾሚዎች ለሚያከናውኗቸው ሁሉም አይነት እንቅስቃሴዎች የፌዴራል መንግሥቱ መመሪያ፣ አቅጣጫ፣ ድጋፍና ክትትል ይደረግላቸዋል ተብሏል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ጥር 6 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
+1
🕯 በወጣት ዮርዳኖስ አምበሉ ግድያ ወንጀል በተጠረጠረው ኢዮብ እንዳለ ላይ ምርመራ መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አሳውቋል።
በሰዓቱ ዮርዳኖስን ወደ ሆስፒታል ያልወሰዷት እና ተከሳሹ ቢላዋ ይዞ ሲገባ ያልፈተሹ 4 ጥበቃዎች ታስረዋል።
በግቢው የነበሩ 36 ሌሎች ሰዎችም ታስረዋል።
ልጃቸውን ለማሸሽ የሞከሩ የተከሳሽ ወላጅ አባት ታስረው በዋስ ወጥተዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ምን አለ ?
ፖሊስ፣ በወጣት ዮርዳኖስ ግድያ የተጠረጠረው ተጠርጣሪ ኢዮብ እንዳለ እንደሚባልና የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመው መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ/ም በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሠባት ልዩ ቦታው ብሔራዊ ቤተ መፃህፍትና ቤተ መዛግብት (ወመዘክር ) ቅጥር ግቢ ውስጥ ከምሽቱ 2፡10 ሠዓት አካባቢ መሆኑን ገልጿል።
በግድያ ወንጀል የተከሰሰው ኢዮብ እንዳለ ለፖሊስ በሰጠው ቃል፣ ከሟች ዮርዳኖስ አምበሉ ጋር " ከአንድ ዓመት በላይ ትውውቅ አለን ፤ በፍቅር ግንኙነትም ቆይተናል " ብሏል።
" ከጊዜ ወደ ጊዜ የባህሪዋ መለዋወጥና በስልክ የምናደርገውን የድምፅ ድውውሎሽ ወደ ፅሁፍ መልዕክት በመቀየሯ በሌላ ሰው እንድጠረጥራት አድርጎኛል " ሲልም ገልጿል።
" (መስከረም 26) ሌላም ጊዜ ወደምንሄድበት ብሔራዊ ቤተ መፃህፍትና ቤተ መዛግብት (ወመዘክር) ለመገናኘት ከቀኑ 10፡00 ሠዓት አካባቢ ቄራ አካባቢ ተቀጣጥረን ነበር " ብሏል።
" ቄራ አካባቢ በቀጠሮአችን ሰዓት ስላረፈደች የሽንኩርት መክተፊያ ቢላዋ በመግዛት ደብቄ ይዤ ጠበቅኳት ስትመጣም የራይድ ከፍላ ወደ ወመዘክር ሄድን " ሲል ገልጿል።
" ከዚህ ቀደም ወደ ምንቀመጥበት ቦታ ሄደን አረፍ ብለን ስናወራ ነበር። በመሀላችን በንግግር ያለ መግባባት በመፈጠሩ እና በሌላ ሰው ጥቃት ልታደርስብኝ ትችላለች በሚል ጥርጣሬ ለወንጀሉ ድርጊት በገዛሁት ቢላዋ አራት ቦታ ወግቻታለሁ " ሲል ለፖሊስ ቃሉን ሰጥቷል።
እንደ ፖሊስ መረጃ፣ ተከሳሹ ወንጀሉን ከፈፀመ በኋላ ስልኩን በማጥፋት ከግቢው በማምለጥ ወደ ሀዋሳ ጉዞ ለማድረግ ሞጆ ላይ ቆይቶ፤ ኋላም ስልኩን በመክፈት ወደ አዲስ አበባ ቃሊቲ አካባቢ ተመልሷል።
ፖሊስ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) ጋር በመሆን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ክትትል አድርጎ ከተደበቀበት አካባቢ 48 ሠዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
ሟች በወቅቱ አደጋው እንደደረሰባት በግቢው ውስጥ የሚገኙት አራት የጥበቃ ባለሙያዎች በአካባቢው ወደሚገኘው ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መውሰድ ሲገባቸው ይህን ኃላፊነት ያልተወጡ በመሆኑና ግለሰቡም ወደ ግቢው ሲገባ ፍተሻ ባለማድረጋቸው ምክንያት ሁሉም ታስረዋል።
በወቅቱ በግቢው ውስጥ የነበሩ ሌሎችም 36 ሰዎችም ታስረው ምርመራ እየተጣራ ይገኛል።
የተከሳሽ ወላጅ አባት አቶ እንዳለ ልጃቸውን ለማሸሽ ባደረጉት ሙከራ ተይዘው ምርመራ ሲጣራባቸው ቆይቶ በፍ/ቤት ዋስ መለቀቃቸውን ፖሊስ አሳውቋል።
ወንጀል በሚፈፀምበት ወቅት እያዩ አለማስቆም ፣ ወንጀል የተፈፀመበትንና አደጋ የደረሰበትን ግለሰብ የህክምና እርዳታ እንዲያገኝ አለማድረግ ወይም አለመርዳት የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚያስከትል ህብረተሰቡ ተገዝቦ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አሳስቧል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ጥቅምት 5 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
+1
🇪🇺 አኔት ዌበር ለEU PSC በኢትዮጵያ እና በሰፊው የቀጠናው ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ገለፃ ሰጡ።
የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባህር ቀጠና ልዩ መልእክተኛ አኔት ዌበር በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት ፦
- ከኢትዮጵያ መንግሥት፣
- ከአፍሪካ ህብረት፣
- ከተለያዩ አጋሮች ጋር በሰላም ማስከበር መንገድ ዙሪያ ጠቃሚ ውይይት ማድረጋቸውን እና ህብረቱ የቀጣናውን ሰላም መደገፉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በዚሁ የኢትዮጵያ ጉብኝት ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ከልዩ መልእክተኛዋ እና በኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ጋር ተወያይተዋል።
አቶ ጌታቸው በአስመራ (ኤርትራ) ያለው አገዛዝ እና ስፖንሰሮቹ ቀጠናውን ለማወክ እያደረጉ ያለውን አደገኛ እንቅስቃሴ አጉልተው በማሳየት፣ በጊዜው እርምጃ አለመውሰድ ስለሚያስከትለው አስከፊ መዘዝ ማስረዳታቸውን ገልጸዋል። ሁለቱም ወገኖች ውጥረቱ እንዳይባባስ በቅንጅት ለመስራት ተስማምተዋል።
ከዚህ ውይይት በኋላ ልዩ መልእክተኛዋ አኔት ዌበር የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው በቀጥታ ወደ ብራሰልስ ያቀኑ ሲሆን በዚያም ለአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የፖለቲካ እና የፀጥታ ኮሚቴ (PSC) በኢትዮጵያ እና በሰፊው የቀጠናው ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ጥቅምት 4 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
+1
ኬፊ በቱሉ ካፒ የሚያካሂደውን የወርቅ ማዕድን ፕሮጀክት በድጋሚ ጀመረ።
"ኬፊ ጎልድ ኤንድ ኮፐር" (KEFI) የተባለው የውጭ ማዕድን ኩባንያ በኦሮሚያ ክልል በሚገኘው የቱሉ ካፒ የወርቅ ፕሮጀክቱ ላይ አጋጥሞት በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት አቋርጦት የነበረውን ሥራ በድጋሚ መጀመሩን አስታወቀ።
ባለፈው ዓመት መጨረሻ የተከሰተውንና በ12 ዓመታት የፕሮጀክት ስራው የሰው ህይወት ያለፈበትና ጉዳት የደረሰበትን የደህንነት እንዲሁም የፀጥታ ችግር ክስተት "የገንጂ ሁነት" በማለት ጠርቶታል።
ኩባንያው ከአካባቢው ማህበረሰብ፣ ከፌደራልና ከኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት፣ ከጸጥታ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ችግሩ መፍታቱን ገልጿል።
ውይይቱ ፦
- የማህበረሰቡ ማህበራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች፣
- የሥራ ዕድል ፈጠራ፣
- የጸጥታና አጠቃላይ የደህንነት ጉዳዮች፣
- የሥራ ቦታ ደህንነት ... ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር ተብሏል።
ኩባንያው በፕሮጀክቱ ላይ ከሚሰሩ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችና ተቋራጮች በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በቂ የሥራ ልምድ ያላቸውን የአካባቢው/የሀገር ውስጥ ተቋራጮችን ቅድሚያ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
አሁን ላይ ሥራውን በደረጃ የሚጀመር ሲሆን፣ በመጀመሪያ መብራትና መንገድ የማመቻቸት፣ በመቀጠልም የአካባቢውን ተፈናቃዮች የመካስና የማሰፈር ሥራዎች ይከናወናሉ።
ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ምርት ሲገባ ለአካባቢው 1,000 ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።
#KEFI
ጥቅምት 4 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
+1
#Ethiopia
#USA
" ሁሉም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ከድንበር ተሻጋሪ ወረራዎች/ጥቃቶች መቆጠብ አለባቸው " - የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከኢትዮጵያ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በስልክ እንደተወያዩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት አሳውቋል።
መስሪያ ቤቱ፤ " የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል እየከረረ ስለመጣው ውጥረት መመክረዋል " ብሏል።
ሩብዮ ሁለቱም ወገኖች ሁኔታውን እንዲያረግቡት ጥሪ ማቀረባቸውን አመልክቷል።
" ለውስጥ እና ውጭ ውጥረቶች ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ በ2018ቱ የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት ማዕቀፍ መሠረት የሚደረግ ውይይት ብቻ ነው " ማለታቸውን መ/ቤቱ ገልጿል።
በተጨማሪም ሩቢዮ በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ሁሉም አገራት የጎረቤቶቻቸውን ሉአላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት ማክበር እንዳለባቸውና ከድንበር ተሻጋሪ ወረራዎች/ጥቃቶች መቆጠብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
" የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ተጨማሪ ግጭቶችን ማስተናገድ አይችልም " ሲሉ ሚኒስትሩ መግለጻቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ጥቅምት 4 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
+1
#Ethiopia
#USA
ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር በስልክ ተወያዩ።
ውይይቱ በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊ እና በባለብዙ ወገን የጋራ ትኩረትን በሚሹ ጉዳዮች ላይ እንደነበርና እጅግ ፍሬያማ እንደሆነ ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
" ያካሄድነው ውይይት በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን እድሜ ጠገብ ወዳጅነት ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊና ተግባራዊ አጋርነት ለማሳደግ በሁለቱም አገራት በኩል ያለውን ቁርጠኝነት ማረጋገጫ ነው " ብለዋል።
በውይይቱ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ በተመለከተ ማረጋገጫ መስጠቷን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንንም እንደሚያደንቁ ገልጸዋል።
" የሁለትዮሽ ትብብራችንን ለማጠናከር እንዲሁም በቀጣናዊና ባለብዙ ወገን መድረኮች ቅድሚያ በምንሰጣቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ አብረን ለመሥራት ያለንን ቁርጠኝነት አረጋግጣለሁ " ሲሉም አሳውቀዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ጥቅምት 4 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
+1
በሀዋሳ ከተማ የ10 ዓመት ሕፃን አግቶ 400 ሺህ ብር ተቀብሎ ለተጨማሪ ገንዘብ ሲደራደር የነበረ አጋች በቁጥጥር ስር ዋለ።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ በዚሁ ጉዳይ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር መሳፍንት ሙልጌታን አነጋግሯል።
ም/ኮሚሽነር መሳፍንት እንደገለጹት፣ በሀዋሳ ከተማ ታቦር ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ ወላጅ አባት ልጃቸው ከሚጫወትበት ቦታ መጥፋቱን ለታቦር ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ያመላክታሉ።
ወላጅ አባት ለፖሊስ በሰጡት ተጨማሪ መረጃ አጋች ስልክ ደውሎ " ልጅህን በሕይወት ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ 700,000 (ሰባት መቶ ሺህ) ብር በላኩልህ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ አድርግ፤ ለፖሊስ ከገለፅክ ልጅህን አታየውም " ብሎ እንዳስፈራራቸው ገልጸዋል።
ለጊዜው ማግኘት የቻሉትን 400,000 (አራት መቶ ሺህ) ብር በአገብተው ቢጠባበቁም አጋች ልጁን ከመልቀቅ ይልቅ ብር እንዲጨምርለት እየተደራደረ ባለበት ወቅት ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ይዘው መምጣታቸውን አስረድተዋል።
አዛዡ እንዳሉት፣ የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከክ/ከተማው ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ባደረገው የክትትል ' ካሌብ ባሻና አስፋው ' የተባለን ተጠርጣሪ የተላከውን ገንዘብ ከባንክ ሳይቀበልና ሳይወጣ ሕፃኑም ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስበት እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር ውሏል።
" ታግቶ የነበረው የ10 ዓመት ታዳጊም በሰላም ወደ ወላጆቹ እንዲቀላቀል ተደርጓል " ያሉት ም/ኮሚሽነር መሳፍንት ሙሉጌታ " ወላጆችና የሕፃናት አሳዳጊዎች ልጆቻቸው የት እንደዋሉና ከማን ጋር እንደሚጫወቱ የቅርብ ክትትልና ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። እንዲህ አይነት የወንጀል ድርጊቶችም ሲያጋጥሙ ወዲያውኑ ለአቅራቢያው ፖሊስ ጣቢያ ጥቆማ መስጠት ይገባል " ሰሉም ለህብረተሰቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ
ጥቅምት 4 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
🇸🇦
ሳዑዲ ዓረቢያ በአንድ የሲሪላንካ ስደተኛ ሠራተኛ ላይ በፌስቡክ በተጻፈ አስተያየት ምክንያት አስተላልፋው የነበረውን የሞት ፍርድ እንዲሻር ማድረጓን የሲሪላንካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሩን ሄማቻንድራ ገለጹ።
ዕድሜው 27 ዓመት የሆነው አኖጃን ሲቫራሳ በፌስቡክ በጻፈው አስተያየት " እስልምናን እና ነቢዩ ሙሐመድን ተሳድቧል " በሚል በሚል የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ነበር።
ጉዳዩ በሲሪላንካ ከፍተኛ ድንጋጤን የፈጠረ ሲሆን፣ የምህረት ጥያቄ ለማቅረብም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
የሳዑዲ ዓረቢያ ጠቅላይ ፍርድቤት ውሳኔውን ትላንት መሰረዙን አሩን ሄማቻንድራ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አሳውቀዋል። የሁለቱን ሀገራት ባለሥልጣናት እና የሕግ ቡድኖችም አመስግነዋል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ በሶሻል ሚዲያ ላይ በነበረ ሃይማኖታዊ ክርክር ወቅት አንድ ግለሰበ በሂንዱ አማልክት ላይ የጸያፍ አስተያየት በመጻፉ፣ ሲቫራሳ በታሚል ቋንቋ ነቢዩ ሙሐመድን የሚሰድብ ምላሽ ሰጥቶ ነበር።
ሲቫራሳ ወዲያውኑ ጽሑፉን አጥፍቶ የይቅርታ ቪዲዮ ቢለጥፍም፣ የጽሑፉ ቅጂ (screenshot) ለአሰሪው እና ለሳዑዲ ባለሥልጣናት በመድረሱ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ነበር።
አሁን የሞት ቅጣቱ የተሰረዘለት ሲቫራሳ በእስር ላይ የሚቆይትበት ጊዜ ያልተነገረ ሲሆን ከባድ ቅጣት እንደማይቀርለት ተነግሯል።
https://t.me/tikvahethiopia/108508
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ጥቅምት 4 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
4 586
Repost from TIKVAH-ETHIOPIA
+1
" ይሄ ተቋም ነው (ሀገር መከላከያ ሰራዊት) የእኔንና የባልደረቦቼን ህይወት የታደገው " - ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ
ከእገታ አምልጠው ቤተሰባቸውን የተቀላቀሉት የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ " አውራምባ ታይምስ " ከተሰኘ የዩትዩብ ቻናል ጋር ቆይታ አድርገው ነበር።
በቆይታቸው ፖለቲኮ-ሚሊተሪ ያሏቸውን አካላት " ተው ፤ የምትሄዱበት አካሄድ ትግራይን ያጠፋል ብንላቸውም ሰሚ አላገኘንም " ሲሉ ገልጸዋል።
ነገር ግን ይኸው አልሰማ ባይ ቡድኑ ትግራይን ሳያጠፋ " በአጭር ጊዜ ወደሚሄድበት ሄዷል " ሲሉ ተናገረዋል።
እሳቸው እና ባልደረቦቻቸው ላይ ስለተወሰደው እርምጃ " ፖለቲካዊ አይደለም፣ ህጋዊ አይደለም ምንም ስም የለውም " ሲሉ ገልጸዋል።
እንዴት ከእገታው እንዳመለጡና እንደወጡ አሁን በዝርዝር መናገር እንደማይፈልጉ የተናገሩት ሌ/ጄነራል ታደሰ ነገር ግን በሂደቱ ህይወታቸውን ለመታደግ ለተሳተፉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
" ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ለትግራይ ሰላም ሰራዊት ምስጋና አቀርባለሁ " ያሉት ሌ/ጄነራል ታደሰ " በተለይም ግን መከላከያ ሰራዊትን አመሰግናለሁ " ብለዋል።
" መከላከያ ሰራዊት ትልቅ ውለታ ነው የዋለልኝ ፣ ያገለገልኩበት ተቋም ነው። በብዙ ኃላፊነት ያገለገልኩበት ተቋም ነው። ይሄ ተቋም ነው የእኔንና የባልደረቦቼን ህይወት የታደገው " ሲሉ ገልጸዋል።
በሂደቱ ለተሳተፉ የመከላከያ ኦፊሰሮች፣ ኃላፊዎች ምስጋና አቅርበዋል።
#አውራምባታይምስ
ጥቅምት 4 ቀን 2019 ዓ/ም
@tikvahethiopia
