es
Feedback

¡No caigas en manos de tramposos! Telemetrio encuentra y marca estos canales 👉 Si quieres ver la etiqueta, suscríbete

SABBATH SCHOOL (ሰንበት ትምህርት)

SABBATH SCHOOL (ሰንበት ትምህርት)

Ir al canal en Telegram

@TekalignSorato +251913070430 Daily Spiritual & Religious Education. Live Q&A Sessions & Daily Training. YouTube Content & Livestreams!

Mostrar más
9 663
Suscriptores
+1924 horas
+267 días
+11430 días
Archivo de publicaciones
እሑድ ጥቅምት 29 Nov 8 በእግዚአብሔር መልክተኛ ላይ ቁጣ በእግዚአብሔር የተመረጠው መሪ፣ ሙሴ፣ ድብልቅ ህዝብን በምድረ በዳ ወደ ተስፋዋ ምድር መምራት የሚያስከትለውን ደስታና ሀዘን ያውቅ ነበር። ዘሁልቅ 14:4-11ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር ምንድር ነው? ሕዝቡ በሙሴና በአሮን ላይ ለምን ተበሳጩ? Save Notes ጥቅሶቹ በጥንቃቄ ሲነበቡ የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ላይ የተቈጡት እርሱን ስላላመኑት ነው። የእግዚአብሔር የመጨራሻ የበላይነት ሰብአዊ ወኪሎች የሆኑት ሙሴና አሮን ለህዝቡ ቁጣ በቀላሉ ተዳረጉ። ማንኛውም ሰው አካላዊና አእምሮአዊ ጥበቃ(ደህንነት) ማግኘት ዋና አላማው ነው። እነዚህን ደህንነቶቻችንን አደጋ ላይ የሚጥል የሚመስል ነገር ሲያጋጥመን እንበሳጫለን። እንዲያውም አንዳንዴ ራሳችንን እንስታለን። ዘሁልቅ 13:26-30ን ያንብቡ። እስራኤላውያን እንዲህ የፈሩት ለምንድን ነበር? ካሌብ ምን አይነት የማደፋፈሪያ ቃል አካፈላቸው? Save Notes እስራኤላውያን የተስፋውን ምድር ለመውረስ በሚያደርጉት ሙከራ የሚገጥሟቸውን ችግሮች ቢፈሩ አይፈረድባቸውም። ነገር ግን ሰዎች ልባቸውን ለአለማመን ሲሰጡ ከሰይጣን ቁጥጥር ስር ይውላሉ። ሰይጣን ለምን ያህል ርቀት እንደሚመራቸው አያውቁም (አበውና ነቢያት ገፅ 389)። በዚህ ቅጽበት ሙሴ ለመወጣት ወደ አለመቻል የተቃረበ የመሪነት ችግር አጋጠመው። የህዝቡ ፍርሃት በሙሴና በአሮን ላይ ወደ መቆጣትና በእግዚአብሔር ላይ ወደ ማመፅ ተለወጠ። ህዝቡ እግዚአብሔር የመረጠውን ነቢይና መሪ በሌላ መሪዎች ለመተካት ሲሞክሩ (ዘዳግም 34:10-12፣ ዘሁልቅ 14:41) እያሱና ካሌብ ልብሳቸውን ቀደው ቢፈሩም በእግዚአብሔር እንዲያምኑ ተማፀኑ። ህ”እግዚአብሔርስ ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚህች ምድር ያገባናል እርስዋንም ይሰጠናል። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጥላቸው ከላያቸው ተገፍፎአል፥ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው ብለው ተናገሩአቸው” (ዘሁልቅ 14:8፣9)። ነገሮች ሲመቻቹ እግዚአብሔርን ማመን ቀላል ነው። አይደል? መከራ ሲመጣስ? እግዚአብሔርን ማመን የማይመችና የሚያስቸግር ሲሆንስ? ታዲያ ያኔ ምን ያደርጋሉ? @SabbathSchool @TekalignSorato

ጥቅምት 28 - ኅዳር 4 7ኛ ትምህርት Nov 7 - 13 አሁን ይህን ስሙ። ሰንበት ከሰዓት በኋላ ለዚህ ሳምንት ጥናት እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ። ዘሁልቅ 13:26-30፣ ኤርምያስ 36:20- 26፣ 2ኛ ዜና መጻሕፍት 36:15፣16፣ ማቴዎስ 23:30-35፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 10:6-12። የመታሰቢያ ጥቅስ፡“ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፥ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ” (1ኛ ቆሮንቶስ 10:11)። ዛሬ አንዳንድ ሰዎች የራሳችን “እውነት--የራሳቸውን ልምምዶች፣ የራሳቸውን ሀሳቦች፣ የራሳቸውን ፍላጎቶች፣ የራሳቸውን ወሰኖች፣ የራሳቸውን እምነቶች ምንም ቢሆኑ እንዲናገሩ ይደፋፈራሉ። እያንዳንዱ “እውነት” ዋጋ ጸለው የሚል አስተሳሰብ ቢኖርም ፈቃድ ሊሰጠው አይገባም። እነዚሀ ስር የሰደዱ “እውነቶች” ክእውነት፣ ከኢየሱስ ክርስቶስና ከተጻፈው ቃሉ ጋር ሲጋጩ ምን ይሆናል አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊውን እውነት ተቀብለው ከስህተታቸው ይታረማሉ። ሌሎች ደግሞ ከሀሰት ጋር ይጣበቃሉ። አንዳንዶች እውነቱን ሲቀበሉ ፀባያቸውን ይቀይራሉ። ሌሎች ደግሞ ያምፃሉ። የሰው ታሪክ እንደዚህ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ሊሰሙ የማይፈልጉትን መልእክት እንዲያስተላልፉ ይታዘዛሉ። ስለዚህ ብዙዎቹ ተነቅፈዋል፣ ተኮንነዋል፣ የሞት ዛቻም ደርሶባቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶች ተገድለዋል (ዕብራውያን 11:32-38)። ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ መለኮታዊ የሆነው ትንቢታዊ ምሪት አማራጭ የሌለው ስለነበር የእግዚአብሔር ነቢያት የሚያስከፍላቸው ግላዊ ዋጋ ምንም ቢሆን መልእክታቸውን በታማኝነት አስተላልፈዋል። @SabbathSchool @TekalignSorato

የዛሬ የሰንበት ትምህርት Live ፕሮግራም አለመኖሩን ከይቅርታ ጋር እናሳውቃለን ። @SabbathSchool @TekalignSorato

ዓርብ ጥቅምት 27 Nov 6 የኤለን ጂ ዋይት ጽሑፎች የኤለን ጂ ዋይት የኑሮ ተሞክሮና ጽሑፎች በዚህ ሳምንት ካጠናናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክተኞች የኑሮ ተሞክሮና ጽሑፍ ይመሳሰላል። እርስዋም የተገለጠላትን እንድትጽፍ መለኮታዊ ተልዕኮ ተቀብላለች። ኤለን ጂ ዋይት በ 1909 ዓም እንዲህ ስትል ፃፍች፦ “ለሕይወቴ ያሰጋ ከባድ አደጋ ደርሶብኝ ስለነበረ የጤና ችግር ስለነበረብኝ ልጽፍ አልቻልኩም ነበር። ነገር ግን አንድ ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ አልጋዬ አጠገብ ሆኖ እንዲህ አለኝ፦ ´የሰጠሁሽን ነገሮች መጻፍ አለብሽ።´ እኔም መጻፍ አልችልም አልኩት። ነገር ግን እንደገና ´የሰጠሁሽን መጻፍ አለብሽ አለኝ´። መሞከር አለብኝ ብዬ መጻፍ ጀመርኩ። ከዚያም ቃላቱን ለመጻፍ እንደማይቸግረኝ ተገነዘብኩ።” (The General confer- ence Bulletin, may 31, 1909)። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሁሉ ኤለን ጂ ዋይትም ረዳት ፀሐፊዎችን ተጠቅማለች። ፀሐፊዎቿ አርታኢዎች እንዲሰሩ የሚጠበቅባቸውን ነገር--የራሳቸውን ሀሳብ ሳይጨምሩ መልእክተኞቹ ሀሳባቸውን በግልጽ እንዲገልጹ በማገዝ አልሰሩም። ድብቅ ደራሲዎች (ghost writers) ወይም ተባባሪ ደራሲዎች አልነበሩም። ስራቸው በቃልም ሆነ በጽሑፍ ኤለን ጂ ዋይት የሰጠቻቸውን መጻፍ ነበር። ኤለን ጂ ዋይት መልእክቷን ለማስተላለፍ በበለጠ እንዲረዳት ክሌሎች የሰነ- ጽሑፍ ምንጮች አንዳንድ ነገሮችን ጠቅሳለች ወስዳለችም። እሷ የተጠቀመቻቸውን መጻሕፍት አንባቢዎች እንዲያነቡ ማደፋፈሯ ለማታለል ላለመሞከሯ ማስረጃ ይሆናል። ነገር ግን በእነዚያ ደራሲያን ቋንቋ መልዕክቱን በግልጽ ለማስተላለፍ ጠቃሚ ነገሮችን አገኘች። ስለ መሳሳትና ስለ መቃረንስ? “መሳሳትን በተመለከተ አልሳሳትም አላልኩም። የማይሳሳት እግዚአብሔር ብቻ ነው” ብላለች። (ምርጥ መልክቶች 1ኛ መጽሃፍ ገፅ 37) አንዳንዴ በጽሑፎቿ ውስጥ ለማስተዋል የሚያስቸግሩና ከሌሎች ጋር ለማጣጣም የሚያስቸግሩ አባባሎች ሊገኙ ይችላሉ። የኤለን ጂ ዋይት ሰብአዊነት በመለኮታዊ ጥሪዋ አልተሰረዘም። ኤለን ጂ ዋይት እንደ ሁላችንም ታድጋለች ብስለትንም ታገኛለች። ዕድገቷና ብስለቷ በጽሑፎቿ ተንፀባርቋል። አስቀድሞ እንደተገለጸው፣ ግን ቢደገም የተገባ ስለሆን፣ እሷ የጻፈችው ቃል ሁሉ ከእግዚአብሔር የመጣ ነው ብለው የሚያምኑትን አርማለች። “አንዳንድ ጊዜ ተራ ነገሮች መነገር ያለባቸው ጊዜያቶች አሉ፣ ተራ ሀሳቦች አእምሮን መያዝ ያለባቸው ጊዜያቶች አሉ፣ ተራ ደብዳቤዎች መፃፍ ያለባቸው ጊዜያቶች አሉ፣ ከአንዱ ሰራተኛ ወደ ሌሎች ሰራተኞች መተላለፍ ያለበት ተራ መረጃ መሰጠት አለበት። እነዚህን የመሰሉት ቃላትና መረጃዎች በእግዚአብሔር መንፈስ አነሳሽነት የተሰጡ አይደሉም።” (ምርጥ መልእክቶች 3ኛ መፃፍ ገፅ 58) @TekalignSorato @TekalignSorato

ሐሙስ ጥቅምት 26 Nov 5 መለኮታዊ መልዕክትና ሰብአዊ ጉድለቶች ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር መዝገብ በ2ኛ ቆሮንቶስ 4:7 ላይ ምን ይላል? Save Notes ጳውሎስ የእግዚአብሔር ኃይል ከሰብአዊ ድክመት ጋር ያለውን ንጽጽር ለማሳየት የእግዚአብሔር መዝገብ “በሸክላ ዕቃ ውስጥ” እንድተቀመጠ በመጥቀስ ይጽፋል። የእግዚአብሔር መልእክተኞች በግል ህይወታቸው እንዳይሳሳቱ ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ ሀይል እንዳልተጠበቁ ሁሉ (ለምሳሌ ሙሴ፣ ኤልያስ፣ ዮናስና ጴጥሮስ) ጽሑፎቻችውም ከሰብአዊ መረዳትና ግንኙት ጉድለቶች የጸዱ አልነበሩም። “በክርስቶስ የታየው መለኮታዊና ሰብአዊ ህብረት በመጽሐፍ ቅዱስም አለ። የተገለጡት እውነቶች ሁሉ “በእግዚአብሔር አነሳሽነት” የተሰጡ ናቸው። ነገር ግን የሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት በሰዎች ቃላት የቀረቡ ናቸው።”(Testimonies to the church vol. 5 p. 747) ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 4:7 እንደጻፈው የእግዚአብሔር መልክተኞች እውነቱን እንዲያስተላልፉ ሲጠሩ ሰብአዊነታቸው አልተሰረዘም። በተጨማሪም ዛሬ ለእኛ ለማስተዋል የሚያስቸግሩ አነጋገሮችና አጻጻፎች እንዳይነገሩና እንዳይፃፉ አልከለከላቸውም። ቢሆንም በእነዚህ ለማስተዋል አስቸጋሪ በሚመስሉ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ሃሳቦች የምንሰናከልባቸው በጠባብ አስተሳሰብ ስናያቸው ብቻ ነው። አማኞች ክርስቲያኖች እንደመሆናችን በተገለጠልን ብርሃን እየተመራን ያልተገለጠልንን ደግሞ ለእግዚአብሔር መተው አለብን። አንዳንድ ልዩነቶች ሰዎች በኋላ ሲገለብጡ የፈጸሟቸው ቀላል ስህተቶች ሊሆኑ ወይም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የጻፉ ጸሐፊዎች ከተደገፉአቸው ምንጮች የተነሳ የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ አይነት አስቸጋሪ ክፍሎች ሲያጋጥሙን የፀሐፊዎችን ሀሳብ በተሳሳተ መንገድ ወስደን እንዳይሆን ተጨማሪ ሀሳብ ማድረግ ያስፈልገን እንደሆነ ራሳችንን መጠየቅ አለብን። ስህተት ለሚመስሉ ሃሳቦች ወይም ልዩነቶች ሁሉ መፍትሄ ባናገኝላቸውም እየተሰጠ ካለው ዋና መልዕክት በፍጹም የማይጣጣሙ አይደሉም። የእግዚአብሔር መልክተኞች ጉድለት ቢኖርባቸውም በተገለጡላቸው መለኮታዊ እውነቶች ሙሉ በሙሉ ልንተማመን እንችላለን። መልክቱን ለማቀበል ኃጢአት ያልሰሩን መላዕክት በመምረጥ ፋንታ ጉድለት ያላቸውን ሰብአዊ ፍጡራን የመረጠው ለምን ይመስልዎታል? @SabbathSchool @TekalignSorato

ረቡዕ ጥቅምት 25 Nov 4 የስነ-ጽሑፍ ምንጮች “ሰባኪውም ጠቢብ ስለ ሆነ ለሕዝቡ እውቀትን አስተማረ፤ እርሱም ብዙ ምሳሌዎችን መረመረና ፈላለገ አስማማም። ሰባኪው ያማረውን በቅንም የተጻፈውን እውነተኛውን ቃል መርምሮ ለማግኘት ፈለገ” (መክ 12:9፣10)። ይህ ምንባብ የሚያሳየው ሰለሞን የዘገባቸውን ምሳሌዎች ሁሉንም እራሱ እንዳላመነጨ ነው። በእግዚአብሔር ምሪት ብዙ አባባሎችን “ፈለገ” እና “ያማሩ ቃላትን”ፈለገ። እንዲያውም በምሳሌ 31 ላይ የምትገኘውና ብዙ ጊዜ የምትጠቀሰው የመልካሟ ሴት ታሪክ የሰለሞን ሳይሆን የአንድ የማይታወቅ ንጉስ እናት ንግግር ነው (ምሳሌ 31:1)። በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የግብጻዊያን ስነጽሑፍ ተጽዕኖ እንዳለበት መረጃ ያመለክታል። በተመሳሳይ ሁኔታም በመንፈስ ቅዱስ ተነስተው የፃፉ የብሉይ ኪዳን ታሪክ ዘጋቢዎች የእግዚአብሔርን ህዝብ ታሪክ በታማኝነት ለመተረክ የታሪክ ቅርሶችንና ሌሎች ምንጮችን እንደ ማጣቀሻ መጠቀማቸውን ነግረወናል። 1ኛ ነገ 11:41፣ ሉቃ 1:1-4 እና ይሁዳ 14፣15ን ያንብቡ።። በመንፈስ ቅዱስ የተነሳሱ ፀሐፊዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆኑ ምንጮችን መጠቀማቸውን እነዚህ ጥቅሶች እንዴት ያሳዩናል? Save Notes መጽሐፋቸውን ለመፃፍ ታሪካዊ ዘገባዎችን ከተጠቀሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መካከል ዕዝራና ነህምያ ይገኛሉ። ዕዝራ እየሩሳሌምንና ፋርስን በሚመለከት ንጉሳዊ ደብዳቤዎችንና አዋጆችን ይጠቀማል (ዕዝራ 4:7ን ይመልከቱ)። ነህምያ ደግሞ ያገኛቸውን የትውልድ መዝገቦች በታሪክ ውስጥ ያካትታል (ነህ 7:5- 72ን ይመልከቱ)። የዚህ ዓይነት አሰራር በአዲስ ኪዳንም ይገኛል። “የሉቃስ ልምምድ የሚያሳየው የመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ከአእምሮ አስተሳሰብ ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ ነው። በዚሀ ቦታ በመንፈስ ቅዱስ የተነሳሳ ፀሐፊ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ስለ ክርስቶስ ሕይወት በቃልና በጽሑፍ አስቀድሞ ያለውን ታሪክ አቀነባብሮ በጽሑፍ ለማቅረብ ተግቶ አጠና።” (Bible commentary vol.5 page 669)። ይሁዳ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተካተተውን የአይሁዶች ስራ የሆነውን አንደኛ የሄኖክ መጽሐፍ 1:9ን ይጠቅሳል። ጳውሎስ ስማቸውን ሳይጠቅስ ከግሪክ ፈላስፋዎችም ተውሷል (የሐዋ 17:28 ና ቲቶ 1:12ን ይመለከቱ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አብዛኛውን ጊዜ መልዕክታቸውን በሕልምና በራዕይ ቢቀበሉም መንፈስ ቅዱስ ከሌላ ምንጮች መረጃ እንዲመርጡ አነሳስቷቸዋል። ይህን መገንዘባችን ለእኛ እንዴት ይጠቅመናል? @SabbathSchool @TekalignSorato

ማክሰኞ ጥቅምት 24 Nov 3 የፅሁፍ ረዳቶች ኤርምያስ 36:17ና 18 እና ሮሜ 16:22ን ያንብቡ። የመጽሐፍ ቅዱስ ፀሐፊዎች የፅሁፍ ረዳቶች ስለ መጠቀማቸው እነዚህ ጥቅሶች ምን ይነግሩናል? Save Notes ምናልባት ኤርምያስ መልዕክቱን ራሱ ሊጽፈው ይችል ነበር። ነገር ግን ትንቢቶቹን በጥንቃቄ ጽፎ ለህዝቡ መሪዎች እንዲያቀርብ የሚተማመንበትን ፀሐፊውን ተጠቀመ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መለኮታዊ መልዕክቱን ለሌሎች ለማስተላለፍ የጽሑፍ ረዳትን አገልግሎቶች የተጠቀሙ ነቢያት ምሳሌ ኤርምያስ ብቻ አልነበረም። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ ምንም እንኳን ጤርጥዮስ “ይህን መልዕክት ጻፍሁት” (ሮሜ 16:22) ቢልም ከሮሜ መጽሐፍ ጅምር ጀምሮ ጳውሎስ የተናገረውን መጻፉ ግልጽ ነው። ጤርጥዮስ የጳውሎስ ፀሐፊ ነበር። ጳውሎስ የተናገረውን በጽሑፍ አሰፈረ። ይህ ለጳውሎስ ያልተለመደ ነገር አልነበረም። ደብዳቤው በሙሉ እውነተኛ መሆኑን ለማረጋገጥ በቆላስያስና በተሰሎንቄ ደብዳቤዎች መደምደሚያ ላይ “በገዛ እጄ” ሲል ደብዳቤዎቹን ይደመደማል (ቆላ 4:18፣ 2ኛ ተሰ 3:17)። ይህ የሚያመለክተው ደብዳቤዎቹን በጽሑፍ የሚያሰፍርለት ሌላ ሰው እንደነበር ነው። ደብዳቤው በትክክል እርሱን ስለመወከሉ ወይም በፍጹም ከእርሱ ላለመሆኑ ይህ እውነታ ጥርጣሬ ሊያነሳ ስለሚችል ስለ መልእክቱ ትክክለኛነት ምንም ጥርጣሬ እንዳይኖር ጳውሎስ በመጨረሻ ላይ የራሱን የእጅ ጽሑፍ አስቀመጠ። ብዙ ምሁራን የጳውሎስ ደብዳቤዎች የተለያየ አጻጻፍ ስልት ያላቸው፣ የተለያዩ ረዳቶች እንዲፅፉለት ስላደረገ ነው ይላሉ። ስለ ጴጥሮስ 2 ደብዳቤዎችም የዚሁ ዓይነት ጥርጣሬ አለ። “የ1ኛ ጴጥሮስና የ2ኛ ጴጥሮስ የአጻጻፍ ስልት የተለያየ ቢሆንም በግሪክ ቋንቋ ለጻፈው መልዕክቱ ረዳት ተጠቅሞ ይሆናል። የግሪክን ቋንቋ በሚገባ የሚያውቅ ጳውሎስ ጸሐፊዎችን ከተጠቀመ የአረማይክ ቋንቋ ተናጋሪ የነበረው ጴጥሮስ ጸሐፊዎችን መጠቀሙ አመክንዮአዊ ሲሆን ፀሐፊዎቹ በግሪክ በተጻፉ ደብዳቤዎቹ የቃላት አጠቃቀም ላይ ተጽዕኖ አሳድረው ሊኖራቸው ይችላል (SDA Bible commentary ጥራዝ 5 ገፅ 186)። ይህ የሚያመለክተው የእግዚአብሔር መልክተኞች ለማስተላለፍ ለሚፈልጉት ሀሳብና ትርጉም ታማኝ ሆነው ሳለ በቃላት አመራረጥና በአረፍተ ነገር አሰካክ ላይ የረዳቶቹ አፃፃፍ ስልቶች ተጽዕኖ አላቸው ማለት ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ የመራው ሀሳቦቹን እንጂ በመንፈስ ምሪት የተሰጡ ሀሳቦችን ለመግለጽ ስራ ላይ የዋሉትን ቃላት አይደለም። @SabbathSchool @TekalignSorato

ሰኞ ጥቅምት 23 Nov 2 የስነ-ጽሑፍ አይነቶችና የአፃፃፍ ስልቶች መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ የተነሳሱ የእግዚአብሔር መልክተኞች የተጠቀሙአቸውን የተለያዩ የኣአጻጻፍ ስልቶችን ይይዛል። አንዳንዶቹ ማስታወሻ ይመስላሉ (ዘሁ 33:1-49ን ይመልከቱ)። በሌላ በኩል ደግሞ የዳንኤል፣ የዘካሪያስ እና የዮሐንስ መጻሕፍት ደግሞ ትንቢታዊ ጽሑፎችን፣ ታላላቅ ምስሎችን፣ ዓለም አቀፋዊ ሃሳቦችን እና የሰማይ ፍጡራንን መግለጫዎችን ይይዛሉ። ኢሳያስ 13:1ን ያንብቡ። ኢሳያስ ያስተላለፈውን መልእክት መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ላይ እንዴት ያቀርበዋል? Save Notes ነቢያት የሚያዩአቸው ራእዮች አንዳንድ ጊዜ “ቃል ኪዳን” ይባላሉ። ይህም ማለት ከእግዚአብሔር የመጣ መልዕክት ማለት ነው። አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በተደጋጋሚ የተጻፉ ቅኔዎች አድርገው ያቀርቧቸዋል። ለምሳሌ: “በዚያ ቀን ሰው ወደ ፈጣሪው ይመለከታል፣ አይኖቹም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ” (ኢሳ 17:7)። ከዚህ ላይ “ፈጣሪ” እና “ቅዱስ” ተመሳሳይ ናቸው። አንዱ ሌላውን ያብራራል። በተጨማሪም ነቢያት እንደ ምሳሌ (ምስል) እና ቃለ አጋኖ (ማጋነን) የመሳሰሉ የተለመዱ የአጻጻፍ ስልቶችን ስልቶችን ተጠቅመዋል። መልእክቶቹን አስተውለን ከስራ ላይ ማዋል እንድንችል እነዚህን የመሳሰሉትን ያፃፃፍ ስልቶችን ማዋቅ ይጠቅመናል። ሌላ በብዛት ከስራ ላይ ውሎ የምናየው የአፃፃፍ ስልት ደግሞ “የክስ ቃል ኪዳን” የተባለውን የአፃፃፍ ስልት ነው። ለምሳሌ በኤርምያስ 2:4-9 ላይ ኤርምያስ ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ስለጣሱ ህጋዊ ክስ ያቀርብባቸዋል። የፍርድ ቤት ምስል በመጠቀም እግዚአብሔር እንደ አቃቤ ህግ ሆኖ ሕዝቡን ለምን እንደቀጣቸው ምክንያቶቹን በግልጽ ዝርዝሮ ያቀርባል። በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢታዊ መጻሕፍትን፣ ታሪክን፣ መዝሙሮችንና ምሳሌዎችን ያካትታል። ኤርምያስ መልዕክቱንበመጽሐፍ መልክ እንዲያቀርብ ሲጠየቅ (ኤር 36:2) በአንጻሩ ደግሞ አብዛኛው የአዲስ ኪዳን ክፍል ለግለሰቦችና ለህብረተሰቦች የተፃፉን ደብዳቤዎች ያካትታል። ቢሆንም አንድ አይነት የአፃፃፍ ስልት ከሌላው አያንስም ወይም አይበልጥም። በመንፈስ ቅዱስ ተነሳስቶ መጻፉን በግልጽ ስለሚናገሩ የጳውሎስ ደብዳቤዎች የጥንት ነቢያት ከጻፏቸው መጻሕፍት ጋር እኩል ክብደት አላቸው (1ኛ ቆሮ 7:10፣12:40)። አንዳንድ ምሁራን የመጽሐፍ ቅዱስን መለኮታዊ ክፍል በሚበድል አይነት የሰብአዊውን ክፍል አጉልተው ይናገራሉ። ይህ አቀራረብ መንፈሳዊ ጉዳት የሚያደርሰው እንዴት ነው? (ለምንድነው?) @SabbathSchool @TekalignSorato

እሑድ ጥቅምት 22 Nov 1 ለመፃፍ መጠራት እግዚአብሔር መልእክቱን ለሰዎች ለማስተላለፍ የተጠቀመበት ቀደምት ዘዴ እንደሚሰማ ድምጽ ወይም ሕልም፣ ወይም መላእክት ያለ ቀጥተኛ ንግግርን በመጠቀም ነበር። ቃሉ በጽሑፍ መዘገብ የተጀመረው ለመጀመሪያ ጊዜ በሙሴ ዘመን ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ጽሑፍ የተወሳው መቼ ነበር? ዘፀ 17:14ን ያንብቡ። Save Notes ቃሉን ዘግበው ለህዝቡ እንዲያስቀምጡ እግዚአብሔር መልእክተኞቹን እንዳዘዛቸው በብሉይ ኪዳን ውስጥ በብዙ ቦታዎች እናገኛለን። ለሙሴ እንደተነገረው ለኤርምያስም ተነግሮት ነበር። “አንድ የመጽሐፍ ክርታስ ውሰድ፥ ለአንተም ከተናገርሁበት ቀን ከኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተናገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት” (ኤርምያስ 36:2)። ትንቢቶቹን ለምን መጻፍ እንዳለበትም ተነግሮት ነበር። “ምናልባት የይሁዳ ቤት፦ እኔ አደርግባቸዋለሁ ያልሁትንና ያሰብሁትን ክፉ ነገር ሁሉ ይሰሙ ይሆናል፥ ከክፋ መንገዳቸው ይመለሱ ዘንድ እኔም በደላቸውንና ኃጢአታቸውን ይቅር እል ዘንድ” (ኤርምያስ 36:3)። ትንቢቶቹ የተሰጡት የሰዎችን የወደፊቱን ለማወቅ ያላቸውን ጉጉት ለማርካት ሳይሆን ለመዳናቸው ነበር። የእግዚአብሔር መልክተኞች የፃፉት በተለያዩ ሁኔታዎች እያሉ ነበር። ሙሴ የመጀመሪያዎቹን አምስቱን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የጻፈው በምድረ በዳ ሳለ ነው። ዳዊት ብዙዎቹን መዝሙሮቹን የፃፈው ሳኦል እያሳደደው ሳለ ነው (መዝ 52፣54፣57፣59ን ይመልከቱ)። ዳንኤል ራዕዮቹን የፃፈው በባቢሎን እና በሜዶ-ፋርስ ቤተ መንግስታት በሚያገለግልበት ጊዜ ነበር። በአንጻሩ ደግሞ ጳውሎስ የኤፌሶንን፣ የፊሊጵስዩስን፣ የቆላስያስንና የፊሊሞናን ደብዳቤዎች የፃፈው እስር ቤት ውስጥ ሆኖ ነበር። ዮሐንስ ደግሞ ራእዩን የጻፈው በጳጥሞስ ደሴት ተግዞ ሳለ ነበር። የእግዚአብሔር መልክተኞች መልዕክቱን ለመጻፍ በመንፈስ ቅዱስ ከተመሩ ያሉበት ሁኔታ ልዩነት አያመጣም። የሚያስገርመው ነገር ደግሞ ኢየሱስ ያስተማራቸው እነዚያ የከበሩ እውነቶች ሁሉ የተጻፉት እግዚአብሔር በተማመነባቸው እና በመረጣቸው ሰዎች ነበር። ይህ የሚያሳየን እነዚህ መለኮታዊ መልዕክቶች በጥንቃቄ መዘገባቸው ምን ያህል አስተማማኝ መሆኑን ነው። አንድ ሰው የመጀመሪያዎቹ (original) ጽሑፎች ሰለሌሉን መጽሐፍ ቅዱስን ማመን አንችልም ቢል ምን ይመልሱለታል? በነገራችን ላይ ይህ አይነት ጥያቄ ደካማ ጥያቄ የሆነው ለምንድር ነው? @SabbathSchool @TekalignSorato

ጥቅምት 21 - 27 6ኛ ትምህርት Oct 31 - Nov 6 ትንቢታዊ ጽሑፎች ሰንበት ከሰዓት በኋላ ለዚህ ሳምንት ጥናት እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ፦ዘፀ 17:14፣ ኢሳ 13:1፣ ኤር 36:17ና 18፣ ሮሜ 16:22፣ ሉቃ 1:1-4፣ ይሁዳ 14ና 15፣ 2ኛ ቆሮ 4:7። የመታሰቢያ ጥቅስ፡“በመጽናናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፏልና” (ሮሜ 15:4)። እግዚአብሔር ራሱ የደረሰውን መዝሙር መዘመርን መማር የሚፈልጉት እንዴት ነው? በዘዳግም 32 ላይ የሚገኘው ግጥም በእግዚአብሔር ምሪት በሙሴ የተጻፈ ነው (ዘዳ 31:19-32።) ስለ ትንቢታዊ መጻሕፍት ስናስብ መዝሙሮች ወደ አይምሮአችን አይመጡም። ጝጥሞቹ ቀጥታ ቃል በቃል በእግዚአብሔር የተነገሩ ባይሆኑም መዝሙረ ዳዊት በአብዛኛው በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፈ መዝሙር ነው። ነቢያት የእግዚአብሔርን መልዕክት የሚያስተላልፉባቸውን 3 መንገዶች መጽሐፍ ቅዱስ ዘግቧል፦ (1) በቃል (2) በጽሑፍ (3) በምልክት ወይም በትይንት። በዚህ ሳምንት በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በሚገኙት ጽሑፎች ላይ እናተኩራለን። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል፣ በመልእክተኞቹ በተገለጹ ቃላት አማካይነት፣ የነቢያቱን ስብከቶችና ንግግሮች በማካተት መዝግቦታል። በትንቢታዊ ጽሑፎች ውስጥ ስላሉ የተለያዩ የአጻጻፍ ዘይቤዎች ዓይነቶች አስቡ፦ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያክል ትረካ፣ ታሪክ፣ ግጥም (ቅኔ)፣ ሰቆቃና ደብዳቤዎች ይገኙበታል። የተመረጡ ወንዶችና ሴቶች ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የተቀበሏቸውን መልዕክቶች በራሳቸው ቋንቋ ዘገቧቸው። በዚህ ሳምንት ጽሑፎቻቸውን ስንመለከት በረዳት ፀሐፊዎች መገልገላቸውንና አንዳንድ ለማስተዋል ቀላል ያልሆኑ ጽሑፎች ሲገጥሙን ማሰብ ሰላለብን ነገሮች እንመለከታለን። @SabbathSchool @TekalignSorato

ዓርብ ጥቅምት 20 Oct 30 ኤለን ጂ ዋይት ስለ ራዕይና በመንፈስ ቅዱስ ስለ መነሳሳት 7ኛ ቀን አድቬንቲስቶች ኤለን ጂ ዋይት መለኮታዊ መነሳሳት ተቀብላለች ብለው ያምናሉ። ጽሑፎቿ፣ ኑሮዋና አገልግሎቶቿ የእውነተኛ ነቢይን መስፈርት ያሟላሉ። የመንፈስ ቅዱስ መነሳሳቷ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት ካገኙት ጋር አንድ ቢሆንም ጽሑፏን ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አታወዳድርም። እንዲያውም በአንጻሩ ኤለን ጂ ዋይት መጽሐፍ ቅዱስን ሁል ጊዜ ከፍ ከፍ ታደርጋለች። ታዲያ እግዚአብሔር ትንቢታዊ ራዕይ እንዴት እንደሰጣትና ሂደቱንስ እንዴት ታየዋለች? በአንደኛ ደረጃ፣ ኤለን ጂ ዋይት መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም ኃይል ያለውና የማይሳሳት የእግዚአብሔር መገለጥ መሆኑን ታምናለች። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን እውነትና እግዚአብሔር ለወደቀው የሰው ዘር ያለውን የመዳን እቅድ ይገልጣል። በዚያ ሂደት አሁን እንደምንማረው ያን መልዕክት ለማስተላለፍ ነቢያቱን ይጠቀማል። በሁለተኛ ደረጃ፣ የመነሳሳት ሂደት በመለኮታዊና በሰብአዊ ፍጡራን መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመለከት ነው። እግዚአብሔር መልዕክቱን ሲሰጥ ነቢይ ደግሞ መለኮታዊ መልእከቱን የራሱን ወይም የራሷን ቃል በመጠቀም ለሰዎች ያስተላልፋል ወይም ታስተላልፋለች። ኤለን ጂ ዋይት እንዲህ ብላለች፦ “በመንፈስ ቅዱስ የተነሳሱት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ቃላት ሳይሆን የጻፍዋቸው ሰዎች ናቸው። መንፈስ ቅዱስ የሰራው፣ ሰው በፃፋቸው ቃላት ላይ ሳይሆን በፀሐፊው ላይ ነው። መንፈስ ቅዱስ በፀሐፊው ውስጥ አድሮ ባስተሳሰቡ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። መለኮታዊ ሀሳብና ፈቃድ ከሰብአዊ ሀሳብና ፍቃድ ጋር ተዋህዶ የሰው ንግግር የእግዚአብሔር ቃል ሆነ” (ምርጥ መልዕክቶች 1ኛ መጽሐፍ ገጽ 21)። ራዕዮችንና ትንቢታዊ ህልሞችን በሚመለከት ኤለን ጂ ዋይት “የሀሳብ በመንፈስ ቅዱስ መነሳሳትን” የመለኮታዊ መገለጥና ሰብአዊ የኑሮ ተሞክሮ ውህደት እንደሆነ ተረድታለች። እንዲህ ብላለች፦”መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ቋንቋ ከተገለጹ እግዚአብሔር ከሰጣቸው እውነቶቹ ጋር የሰብአዊውንና መለኮታዊውን ጥምረት ያቀርባል።” (ምርጥ መልዕክቶች 1ኛ መጽሃፍ ገፅ 25)። መልእክተኛው መልዕክቱን እንዲያስተውል ለማድረግ እግዚአብሔር የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሟል። እነዚህም ስዕላዊ አቀራረብን እና ቃላትንና የነቢዩን ህዋሳት በሙሉ የያዙ ሀሳቦችን ያካትታሉ። የኤለን ጂ ዋይት ልምምድም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ልምምድ ጋር ይመሳሰላል። በሦስተኛ ደረጃ፣ ኤለን ጂ ዋይት ሰብዓዊ ልምምዶቿና ግንኙነቶቿ በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ የተነሳሱ (የተገፋፉ) አለመሆናቸውን አስገነዘባለች። “ተራ ንግግሮች መነገር፣ በአእምሮ ውስጥ ተራ ሀሳቦች መመላለስ፣ እና ተራ ደብዳቤዎች በሰራተኞች መካከል ተጽፈው ተራ መልዕክቶችን ማካፈል ያለባቸው ጊዜያቶች አሉ። የዚህ ዓይነት ቃላትና የዚህ አይነት መረጃ በእግዚአብሔር መንፈስ ልዩ መነሳሳት የተሰጡ አይደሉም” ብላለች (ምርጥ መልዕክቶች 1ኛ መጽሃፍ ገጽ 39)። የእሷን ጽሑፎች ስናነብና ከጽሑፎቿና ልምምዶቿ ጋር ግንኙነት ስንፈጥር፣ በተለይም ደብዳቤዎቿንና ማስታወሾቿዋን ስናነብ ይህን ልዩነት መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ኤለን ጂ ዋይት ስለ ራእይና በመንፈስ ቅዱስ ስለ መነሳሳት ያላትን ማስተዋል ማወቅ፣ ምክሯን ስናነብ ጽንፍ ከመያዝ በመከላከል ምክሮቿን በጥንቃቄና በመረዳት እንድናነብ ይረዳናል። @SabbathSchool @TekalignSorato

ሐሙስ ጥቅምት 19 Oct 29 ትይንት፣ ምልክቶች፣ ምሳሌዎች መጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩና የዳበሩ የቃላት ስዕሎችና ምሳሌዎች አሉት። ለምሳሌ በብሉይ ኪዳን የሚገኘው የአበው የመሰዊያዎች የመስዋእት ስነ ስርዓት፣ የሙሴ የመገናኛው ድንኳን፣ የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ፣ እነዚህ ሁሉ የክርስቶስን በመስቀል ላይ ያደረገውን የቤዛነት መስዋዕትና በሰማይ የሚያካሄደውን ይክህነት አገልግሎት የሚያሳዩ ስዕላዊ ቃላት ናቸው (ዕብ 8:1-6)። በዳንኤል ትንቢቶች ውስጥ የዓለም መንግስታትና ሃይላት በታላቁ ምስል በተለያዩ ክፍሎች (ዳንኤል 2:31-35)፣ በተለያዩ እንስሳትና ቀንዶች (ዳንኤል 7 እና 8) እና በሁለት ነገስታት (ዳንኤል 11) ተገልጸዋል። በራዕይ ዮሐንስም ተመሳሳይ ምስሎች፣ ለምሳሌ በምዕራፍ 13 በተገለጹት ሁለት አራዊት(አውሬዎች) ቀርበዋል።። ኢየሱስ ራሱ ሲያስተምር እራሱን በህይወት እንጀራ (ዮሐ 6:35፣41-58)፣ የዓለም ብርሃን (ዮሐ 8:12፣9:5) እና እውነተኛ የወይን ግንድ (ዮሐ 15:1-8) መስሏል። በዘሪው ምሳሌና (ማቴ 13:1-9፣18-23) በሌላም ብዙ ምሳሌዎች (ማቴ 13:24-52፣ ወዘተ) ኢየሱስ የመንግስቱን ተፈጥሮ እና አስተዳደግ በምሳሌዎች አስረድቷል። ሕዝቅኤል 4:1-8ን ያንብቡ። እግዚአብሔር በቃሉ ከመናገሩም በላይ አንዳንድ መልእክቶቹን በትይንት (drama) ያቀረበው ለምን ይመስሎታል? Save Notes በሕዝቅኤል 4:1-8 ላይ እግዚአብሔር ነብዩን ትንሽ የኢየሩሳሌም ምስል ሰርቶ መጀመሪያ የእስራኤልን ቤት በመወከል በምስሉ ላይ ለ390 ቀናት በግራ ጎኑ እንዲጋደምባት፣ ከዚያም የይሁዳን ቤት በመወከል በቀኝ ጎኑ ለ40 ቀናት እንዲጋደምባት ባዘዘው ክፍል ግልጽ የሆነ ትይንታዊ አቀራረብ ይታያል። ሌላው ምሳሌያዊ ትይንት ደግሞ እስራኤል በመንፈሳዊ ሁኔታ ለእግዚአብሔር ታማኝ አለመሆኗን ለማሳየትን ሆሴዕን ጎሜር የተባለችውን ገላሞታ እንዲያገባ ያዘዘበት ክስተት ው (ሆሴዕ 1:2-9)። የሕዝቅኤልና የሆሴዕ ትይንታዊ ልምምዶች ዛሬ ስናያቸው ያስደነግጣሉ። አላማውም ያው ነበር። ለእኛ ብቻ ሳይሆን በዘመኑ ለነበሩ ሰዎችም አስደንጋጭ እንዲሆኑ የታቀዱ ትይንቶች ነበሩ። እነዚህ ነቢያት ያሰሟቸውን ማስጠንቀቂያዎች ሕዝቡ በግልጽ ችላ ሲላቸው (2ኛ ዜና 36:15-21ን ይመልከቱ)። የመጨረሻው መለኮታዊ ምህረት ድርጊት ሕዝቡን ወደ እውነተኛ ንስሐ ለመምራት መልዕክቱን በእንዲህ አይነት ትይንታዊ መንገድ ማቅረብ ነበር። የዚህ ዓይነት አቀራረብ እግዚአብሔር የገለፀላቸውን ማስጠንቀቂያዎች ምን ያህል ከልብ ሊቀበሉ እንደሚገባቸው ሊያስረዷቸው ይገባ ነበር። ዛሬስ እኛ ከሎዶቂያዊነታችን እንድንነቃ ምን አይነት ትይንታዊ መልዕክት የሚያስፈልገን ይመስልዎታል? (ራዕይ 3:14-18ን ይመልከቱ) @SabbathSchool @TekalignSorato

ረቡዕ ጥቅምት 18 Oct 28 የጽሑፍ መልዕክቶች አንዳንድ የታወቁ ንግግሮች በሰዎች ህይወት ላይ ጥልቅ ተጽዕኖ ከማሳደራቸው አልፎ ታሪክንም ቀይረዋል። እነዚህ ንግግሮች ባይዘገቡ ኖሮ እነዚህ ንግግሮች ከጊዜ ጋር ይረሱ ነበረ ወይም ይዘበራረቁ ነበር። ስለዚህ ጽሑፍ በቃል የተነገረውን ቋሚ አድርጎት ይኖራል። መልእክቱም በዘመናት ሁሉ ተላላፊ ይሆናል። እስራኤላውያን ግብጽን እንደለቀቁና አማሌቃውያንን እንዳሸነፉ ብዙም ሳይቆይ እግዚአብሔር ሙሴን “ይህን ለመታሰቢያ በመጽሐፍ ጻፈው” አለው (ዘፀ 17:14)። የመጀመሪያ 5ቱን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትና መዝሙር 90ን ከጻፈው ሙሴ ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ 66 መጻሕፍትን የሚያካትተውን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ መንፈስ ቅዱስ ነቢያትን መራቸው። ዘፀ 17:14፣ዮሐ 20:30፣31፣1ኛ ቆሮ 10:11 እና ራዕ 1:19ን ያንብቡ። እግዚአብሔር የሰጣቸውን መልዕክቶች እንዲጽፉ ነብያቱን ከጠየቀበት ምክንያቶች መካከል ጥቂቶቹ ምንድን ናቸው? Save Notes የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የጸሐፊዎቹን የስነ ጽሑፍ ዘዴና ችሎታ ያሳያሉ። ቢሆንም በሚመጣው ሳምንት ጥናት እንደምንወያየው ይህ የፀሐፊዎቹ የግል የአፃፃፍ ዘዴና ችሎታ የመልእክቶቹን በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍቶ የመጻፋቸውን ደረጃ በምንም አይነት አይቀንሰውም። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከሌሎቹ ይልቅ ዛሬ ለህይወታችን በበለጠ ወቅታዊ ናቸው። ይህም ቢሆን የአንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሌላው ይልቅ በመንፈስ የተፃፈ አያደርገውም። አንዳንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በመጀመሪያ በቃል ያስተላለፉትን መልዕክት በኋላ ራሳቸው ጽፈውታል፣ ወይም በሌላ በሚያምኑት ሰው አጽፈውታል። ሙሴ ሊሞት ሲቀርብ ለእስራኤላውያን የተናገረውን የመጨረሻውን ንግግር በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ ዘግቦታል። አራቱ ወንጌሎች ኢየሱስ በዚህ ምድር በነበረ ጊዜ ከሰበካቸው ስብከቶች ብዙዎቹን መዝግበው ይዘዋል። ነገር ግን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ያልተሰጡ ምንጮችን (የሐዋ 17:18፣ 1ኛ ቆሮ 15:53፣ ቲቶ 1:12) እና የሰይጣንን ቃላት ሳይቀር የጠቀሱበት ጊዜ አለ (ዘፍ 3:1-5፣ማቴ 4:1-11)። ማስታወስ ያለብን ነገር ቢኖር ነቢያት የሌሎች ሰዎችን ምኞትና ስሜት እንደዘገቡ ሁሉ የራሳቸውን ሰብአዊ ስሜትም መዘገባቸውን ነው።(ዳን 8:27፣ ራዕይ 22:8፣9ን ይመልከቱ)። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ልንከተላቸው የሚገቡንን መልካም ምሳሌዎች ሲዘረዝር ልናስወግዳቸው የሚገቡ መጥፎ ምሳሌዎችንም ያካትታል (1ኛ ቆሮ 10:1-11)። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ መገንዘብ ያለብን ፍፁም በሆነ ቋንቋ ባይጻፍም የዘመናትን ፈተና የሚያልፍ የማይወድቅ መልዕክት መያዙን ነው። @SabbathSchool @TekalignSorato

ማክሰኞ ጥቅምት 17 Oct 27 በቃል የተላለፉ መልዕክቶች 2ኛ ጴጥ 1:18-21ን ያንብቡ። በእግዚአብሔር ነቢያት በቃል ብቻ የተላለፉት መልዕክቶች በጽሑፍ እንደሰፈሩት መልዕክቶች ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተሰጡ ለመሆናቸው ምን ማረጋገጫ አለን? Save Notes እግዚአብሔር አዳምንና ሄዋንን ከመውደቃቸው በፊት (ዘፍ 2:16፣17) እና ከወደቁም በኋላ (ዘፍ 3:9-19) አነጋግሯቸዋል። በሁለቱም ጊዜያት ቃላቱን በትክክል አስተውለዋል። ድምጹ በሲና (ዘፀ 20:20)፣ እንዲሁም በኢየሱስ ጥምቀትና መለወጥ (ማቴ 3:17፤ ማቴ 17:5) በደንብ ተሰምቷል። ሰዎች ሲያነጋግሩን ንግግራቸውን በተሳሳተ መንገድ ልንተረጉመው እንችላለን። እግዚአብሔር በሚናገርበት ጊዜ ግን የመረጃ መዛባት ወይም ማታለል አይኖርም። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ለሙሴ እንደተናገረ እና ´እኔ እግዚአብሔር ነኝ´” እንዳል ያረጋግጣል (ዘፀ 6:2)። አያሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የእግዚአብሔርን ድምጽ እንደ ሰሙ ይናገራሉ። ለምሳሌ ኢሳያስ (ኢሳ 8:1፣11)፣ ሕዝቅኤል (ሕዝ 3:16፣ 6:11) እና ኤርምያስ (ኤር 1:4፣9:11) የእግዚአብሔርን ድምጽ ሰምተዋል። እነዚህን እና ሌሎች ተመሳሳይ ክስተቶችን ለመካድ መሞከር የነቢያቱን ሀቀኝነትና የመጽሐፍ ቅዱስን ተአመንነት ወደ መጠራጠር ያመራል። እግዚአብሔር ግልጽ በሆነ በሰው ቋንቋ የገለጠላቸውን መልዕክት ነቢያትም ግልጽ በሆነ በራሳቸው ቋንቋ ለአድማጮቻቸው አስተላልፈዋል። ለምሳሌ ኖህ እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይ እና “የጽድቅ ሰባኪ” ነበር (2ኛ ጴጥ 2:5)። ነገር ግን የትኛውንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አልጻፍም። ቢሆንም በወቅቱ ለነበረው ህዝብ መልዕክቱን በቃሉ አስተላለፈ። መልእክቱ እንደተፃፉት የነቢያት መልእክቶች ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ በመነሳሳት የተሰጠ ነበር። ናታንን፣ ኤልያስን፣መጥምቁ ዮሐንስንና ኤልሳዕን ጨምሮ ሌሎች አያሌ ነቢያትም የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍል አልጻፉም። ነገር ግን መልዕክታቸውን በቃል አስተላልፈዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱስ? ወንጌል ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት “ጎንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ፃፈ” ሲል ወንጌል ዘግቧል (ዮሐ 8:6)። ይህን ነበር ያደረገው። ኢየሱስ ሌላ ነገር መጻፉን የሚያሳይ ሌላ ምንም አይነት መረጃ የለም። ነገር ግን “እንደ ባለስልጣን ሆኖ (ማቴ 7:29) በቃሉ አስተምሯል፣ ሰብኳልም። ከአዳማጮቹ መካከል አንዳንዶች እንዲህ ሲሉ መስክረውለታል። “እንደዚህ ሰው ማንም ከቶ አልተናገረም” (ዮሐ 7:40፣46)። ኢየሱስ በዋነኝነት የእግዚአብሔርን መልዕክቶች በቃል አስተላላፊ ነበር። ቢሆንም ከመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንዱንም አለመጻፉ የመልዕክቱን ስልጣንና እውነት አይቀንስበትም። እግዚአብሔር መጽሐፍ ያልጻፉ ነቢያት እንዳሉት ማወቁ ምንኛ አስገራሚ ነገር ነው። ታዲያ እነዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጽህፈታቸው ያልተካተተ ነቢያት መልዕክት ክብደት ወይም ሀቀኝነት የሚኖረው ለምንድነው? @SabbathSchool @TekalignSorato

ዜና እረፍት ፓስተር ጥሩነህ ወ/ስላሴ (1920 – 2019) በአድቬንቲስት ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያሳረፉ ታላቅ የወንጌል አርበኛ ነበሩ። እኛ የSabbath School Telegram Channel አ
ዜና እረፍት ፓስተር ጥሩነህ ወ/ስላሴ (1920 – 2019) በአድቬንቲስት ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያሳረፉ ታላቅ የወንጌል አርበኛ ነበሩ። እኛ የSabbath School Telegram Channel አባላት ለመላው ቤተሰብ፣ ለወዳጅ ዘመዶች እና ለቤተክርስቲያን ምዕመናን ሁሉ መጽናናትን እንመኛለን።

ሰኞ ጥቅምት 16 Oct 26 በመንፈስ ቅዱስ የመነሳሳት ሂደት በዘመናት ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን ሌላም ጽሑፎችና መጻሕፍትም ተጽፈዋል። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን እንቀበላለን። ከሌላ መጽሃፍት በምን ይለያል? 2ኛ ጢሞ 3:15-17ን እና ያዕ 1:17ን ያንብቡ። እነዚህን ጥቅሶች ስናነብ የምናገኘው ዋና መልዕክት ምንድነው? Save Notes የ2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16ን ትርጉም በተመለከተ አንዳንድ ውይይቶች አሉ፣ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ትርጉሞች መጽሀፍ ቅዱስ በሙሉ ምንጩ መለኮታዊ በመሆኑ ላይ አጽንዖት ስለሚሰጡ የሚሰጡት መልዕክት ተመሳሳይ ነው (2ኛ ጴጥ 1:20-21)። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አብራሪ(ተንታኝ) እንዲህ የሚል መግለጫ አበርክቷል(ሰጥቷል)፦”ጳውሎስ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል ሲል ቃሉን በጠቅላላ ማለቱ ነው እንጂ እያንዳንዱ ምንባብ ማለቱ አይደለም።” G. W. Knight III, The Pastoral Epistles: A Commentary on the Greek Text (Grand Rapids, MI: Eerdmans, 1992), p. 445. ነገር ግን መነሻው መጽሐፍ ቅዱስ የሆነውን በመንፈስ ቅዱስ የመነሳሳት ሂደት የምናስተውለው እንዴት ነው? መገንዘብ ያለብን ትንቢታዊ መነሳሳት ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ መለኮታዊ መልዕክት የሚያስተላልፉበት ሂደት መሆኑን ነው። ያ እርዳታ መልእክቱን በመቀበል ብቻ የተወሰነ ሳይሆን መልዕክቱን ለተቀባዮቹ ግልጽ በሆነ መንገድ ማስተላለፍንም ያካተተል። የእግዚአብሔር መልዕክት በራእይ እና በህልም አማካይነት መጣ (ዘሁ 12:6፣ኢሳ 6:1፣8)። እግዚአብሔር የአይን ምስክሮችን (1ኛ ዮሐ 1:1-3)፣ በመንፈስ ምሪት የተደረገ ታሪካዊ ምርምርን (ሉቃ 1:1-3) እና በአዕምሮ ውስጥ የተፈጠሩ መለኮታዊ ተጽዕኖዎችንም ተጠቅሟል (2ኛ ጴጥ 1:21)። መንፈስ ቅዱስ የተጠቀመበት መንገድ ምንም ቢሆን ነቢያትና የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲዎች ሁሉ ለሌሎች ለማጋራት የተቀበሉት እውነተኛ መልዕክት እንጂ ግምታዊ መልዕክት አይደለም። ይህ ማለት ምንም እንኳን መልእክተኞቹ መልእክቶቹን ለመግለጽ የራሳቸውን ቃላት ቢጠቀሙም የእግዚአብሔር መልእክቶች በምንም መንገድ በመልእክተኞቹ መደፍጠጥ ወይም መዛባት የሌለባቸው ናቸው። ትንቢታዊ መልዕክቶችን ለመጀማሪያዎቹ አድማጮች የማስተላልፍ ተግባር በቃል (2ኛ ጴጥ 1:19-21)፣ በጽሑፍ (ዮሐ 20:30፣ 31)፣ ወይም በትይንት መልክ (በመግለጫ) ሊሆን ይችላል (ሕዝ 4:1-8)። መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት በመንፈስ ቅዱስ ምሪት እንደተጻፈ ወይም በመንፈስ ቅዱስ መነሳሳት በአጠቃላይ እንዴት እንደሚሰራ ብዙ ጥያቄዎች ሊኖሩ ቢችሉም፣ ደግሞ እንዴት እንደተጻፈም ሙሉ በሙሉ ባናስተውልም፣ መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ማመን እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድር ነው? @SabbathSchool @TekalignSorato

እሑድ ጥቅምት 15 Oct 25 ጠቅላላና ዝርዝር ራዕይ ዕብ 1፣1ና 2ን ያንብቡ። እግዚአብሔር ይህን ያህል ሊናገረን የፈለገው ለምንድነው? በኢየሱስ እና በነብያቱ በኩል ሊነግረን የፈለገው ነገር ምንድነው? Save Notes አለማትን ሁሉ የፈጠረው ፈጣሪ ምን ይለናል? ከእኛ ጋር ለመነጋገር የሚፈልገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በኀጢአት በተሞላ ዓለም የምንኖር የወደቅን ሰብአዊያን ስለሆንን እና ለመከራ፣ ለስቃየና ለሞት የተዳረግን ስለሆንን ነው። ከዚህ ለምን እንደተገኘን፣ ነገሮች በጣም የከፉ እንደሆኑ፣ ያ ሁሉ ሆኖም ለእኛ ባለው ፍቅር ተስፋ እንዳለን እንድናውቅ ይፈልጋል። በተፈጥሮ ሁሉ የሚታየው የእግዚአብሔር ጠቅላላ ራዕይ ወሰን የሌለውን ኃይሉንና ጥንቃቄውን በግልጽ ይናገራል። “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ የሰማይ ጠፈር የእጁን ስራ ያወራሉ” (መዝ 19:1)። ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲህ ይላል፦”የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ” (ሮሜ 1:20-21)። በአለማችን የሚታየውን ምስጢራዊ የመፈወስ ሂደት ስናይ የእግዚአብሔር ግሩም የአዳሽነት ኃይሉ ላይ ማጤን (ማሰላሰል) ያስፈልጋል። እውነቱን ለመናገር “የእግዚአብሔር የመፈወስ ኃይል በተፈጥሮ ሁሉ ላይ ይታያል። ዛፍ ሲቆረጥ፣ ሰው ሲቆስል ወይም አጥንቱ ሲሰበር ተፈጥሮ በተጎዳው ላይ እደሳዋን ትጀምራለች። ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት የፈውስ ወኪሎች በተጠንቀቅ ቆመዋል። ጉዳቱ ወዲያው ሲደርስ የፈውሱ ወኪሎች ስራቸውን ወዲያውኑ ይጀምራሉ።” (ኤለን ጂ ዋይት ኤዱኬሽን ገጽ 113)። ተፈጥሮኣዊ ዓለም ውብና ትምህርት አዘል ቢሆንም የእግዚአብሔርን ኃይል እና ፍቅር ከመግለጹ አንጻር የክፋትን መኖር ያመለክታል (ዘፍ 3:14-19፣ማቴ 13:24-30)። ይህ የተዘበራረቀ መልዕክት ግልጽ ሊሆን የሚችለው በእግዚአብሔር ልዩ መገለጥ ብርሃን--ስጋ በለበሰው በኢየሱስ ክርስቶስ እና ለእርሱ በሚመሰክረው በተጻፈው በእግዚአብሔር ቃል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃን ብቻ ነው (ዮሐንስ 5:39)። ቃሉ በዘመናት ሁሉ ለሚገኘው የሰው ዘር ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የተሰጠ የእግዚአብሔር መልዕክት ነው። ስለ ዓለም አፈጣጠርና ስለሚያሳዝን ውድቀቱ፣ ስለ እግዚአብሔር አስገራሚ የማዳን ዕቅድ እና ስለ ምድር በመጨረሻ መታደስ የምስራች ይነግረናል። መጽሃፍ ቅዱሳዊ መረጃዎች አንዳንዴ አጭርና ምርጥ ቢሆኑም ከእግዚአብሔር ስለመነጩ ምን ጊዜም የታመኑ ናቸው (2ኛ ጢሞ 3:16፣2ኛ ጴጥ 1:19-21)። ተፈጥሮ የፈጣሪን ኃይልና ፍቅር በግልጽ ቢያሳይም፣ አሁንም የተጻፈው ቃሉ በጥብቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ተፈጥሮ ብቻውን ሊነግረን የማይችለው ግን ቃሉ የሚነግረን ነገር ምንድር ነው? @SabbathSchool @TekalignSorato

ጥቅምት 14 - 20 5ኛ ትምህርት Oct 24 - 30 ራእይና በመንፈስ ቅዱስ መነሳሳት ሰንበት ከሰዓት በኋላ ለዚህ ሳምንት ጥናት እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ። ዕብ 1:1-2፣ 2ኛ ጢሞ 3:15-17፣ 2ኛ ጴጥ 1:18-21፣ዘፀ 17:14፣ ራዕ 1:19፣ ሕዝ 4:1-8 የመታሰቢያ ጥቅስ፡“ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥ እርሱም ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ” (ራዕይ 1:1፣ 2)። ሐዋርያው ዮሐንስ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል ለኢየሱስ ቅርብ ከሆኑት አንዱ ነበር (ሉቃ 8:15፣ማቴ 17:1፣ማቴ 26:36፣37)። ከክርስቶስ እርጋት በኋላ ዮሐንስ አገልግሎቱን በኢየሩሳሌም ቀጠለ። ከእየሩሳሌም ውድቀት በኋላ ግን (70 ዓም) ትንሹ እስያ በመባል በሚታወቀው የሮማ ክፍለ ግዛት ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት ለማስተዳደር ወደ ኤፌሶን ሄደ። በሮማ ንጉስ በድምጥሬስ ዘመነ መንግስት የክርስቲያኖች ስደት ጊዜ ዮሐንስ በአግኒያስ ባህር ወደ ምትገኘው ወደ ጳጥሞስ ደሴት ተጋዘ። በጳጥሞስ ደሴት ሳለ በዘመኑ ለነበሩ በትንሿ እስያ ለሚገኙት ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ሁሉ ለሚኖሩት ክርስቲያኖች የሚጠቅም የተለየ ትንቢታዊ መልዕክት ተቀበለ (ራዕ 1:2-3፣9-11)። ዮሐንስ የመልእክቱ አካል የሆነበት የትንቢታዊ መልእክቱ ሰንሰለት ይህን ይመስላል፦ ከእግዚአብሔር አብ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከዚያ ለመልአኩ፣ ከዚያ ለሐዋርያው ዮሐንስ፣ እና በመጨረሻም ለአንባቢያንና ለአድማጮች። እግዚአብሔር ለሰው ዘር ሁሉ መልዕክቱን ለማድረስ በራዕይና በመገፋፋት ነቢያትን የሚጠቀምበት ታዋቂ መንገዱ ይሄው ነው። የዚህ ሳምንት ትምህርት የራዕይና በመንፈስ ቅዱስ የመገፋፋትን ሂደት፣ እንዲሁም መልእክቱ በተለያዩ መንገዶች እንዴት ለሰው ዘር ሁሉ እንደሚደርስ እንመለከታለን። ይህን የምናደርገው በተለየ መንገድ በጽሑፍ፣ በቃልና ትይንታዊ በሆኑ መንገዶች መለኮታዊ መልእክት ለሰዎች በተላለፈበት መንገድ ላይ ትኩረት በማድረግ ነው።  @SabbathSchool @TekalignSorato