en
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

Open in Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

Show more
611
Subscribers
No data24 hours
+17 days
-1030 days
Posts Archive
❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #የካቲት ፲፱ (19) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ በአባ ጰንጠሌዎን እጅ ምንኵስና ለተቀበሉ ለታላቁ አባት #ለአቡነ_አባለ_ክርስቶስ ለልደታቸው በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ስለ_አቡነ_አባለ_ክርስቶስ_ልደት፦ በመንፈስ ቅዱስ የተወለደው ይኸ ጻድቅ አባለ ክርስቶስ የአባቱ ስም አቃርዮስ ሲባል ትውልዱ ከላይኛው ግብጽ ነው፤ የእናቱ ስም ታውክልያ የምትባል ሲሆን ትውልዷ ከሰሜን ኢትዮጵያ በጌ ምድር ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ነው። ከየሀገራቸው ግብጽና ኢትዮጵያ የመጡ እነዚያም ሰዎች ቡሩካን ናቸው። በኢትዮጵያ የነገሥታት ከተማ በኾነችው በአኵሱም ተገናኙ። ጊዜውም በ910 ዓ.ም ነበር። በዚኸም ዘመን አባቱና እናቱ በአኵሱም ሀገር ሳሉ ይኽ ልጅ ተጸነሰ። ❤ ይኸ አባለ ክርስቶስ የተባለ ሕፃን ከእናቱ ከታውክልያ ማኅፀንና ከአባቱ ከአቃርዮስ አብራክ የእግዚአብሔር ፀባዖት ስሞች በሰውነቱ መሐል በዕብራይስጥ ቋንቋ ዲካባ፣ ማርትያስ፣ ክስብኤል ተብሎ ተጽፎበት የካቲት ዐሥራ ዘጠኝ ቀን በመላእክት አለቃ በቅዱስ ገብርኤል በወርኀዊ በዓሉ ዕለት በአኵሱም ከተማ ተወለደ። ❤ አባቱ አቃርዮስና እናቱ ታውክልያ ይኸን ኅቡዕ የመለኮት ስም በልጃቸው ሰውነት ላይ ተጽፎ በአገኙ ጊዜ ትርጒሙ ምን ይሆን እያሉ ፈጽመው አደነቁ። የሕፃን አባለ ክርስቶስ አባትና እናት በሰውነቱ ላይ ያለውን ምልክቱንና ጽሕፈቱን በገበዘ አኵሱም በቤታቸው ውስጥ እያዩ ሳለ የእግዚአብሔር አዶናይ የስሞችን ነገር ምልክቱና ትርጓሜው ምን ይሆን እየተባባሉ ሳለ ያን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በድንገት መጣ። ❤ ይኸ የኀይል መልአክ ቅዱስ ሚካኤልም በአቃርዮስና በታውክልያ ፊት ቆመ። ያን ጊዜም "ክቡራን የእግዚአብሔርባሮች ጻድቃን ሆይ! ሰላም ለእናንተ ይሁን" አላቸው። "እኔ በዚኽ 'አባለ ክርስቶስ' ተብሎ ታላቅ ስምን በሚሠየም ሕፃን በሰውነቱ ላይ የተጻፈውን የእግዚአብሔር ታዖስ የስሞቹን የጽሕፈቱን ነገር እተረጒምላችሁ ዘንድ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ እናንተ መጣሁ፤ ይኸ ጠላትን የሚያስገዛና አጋንንትን የሚያሳድድ ነውና" አላቸው። "ይኸ ሕፃን አባለ ክርስቶስም ከአደገ በኋላ መጀመሪያ በገበዘ አኵሱም ይኖራል። ዳግመኛም የእናቱ የትውልድ ሀገር በጌ ምድር ውስጥ እግዚአብሔርን የምትፈራ የብፅዕትና የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ማደሪያ ወደሆነችው እና እማሙዝ ተብላ ወደተጠራችው ከእናንተ ጋር ይሔዳል። በዚያም በእናቱ ሀገር ዐሥራ አምስት ዓመት ትኖራላችሁ"። ❤ "ከዚያም በኋላ የነገሥታት ከተማ የሙሴ ጽላት ማደሪያ ወደሆነች ወደ ገበዘ አኵሱም ትመለሳላችሁ። በዚኸ በገበዘ አኵሱም ውስጥም ዐሥራ ሰባት ዓመታትን ትኖራላችሁ። ዛሬም በዚኸች በመጋቢት ኻያ ስምንት ቀን ፈጥናቹ አጥምቁት" አላቸው። አባቱ አቃርዮስና እናቱ ታውክልያ ከድልነዓድ በፊትና ከላሊበላውያን ነገሥታት ከዛጔ ነገሥታት በፊት የነበረው ንጉሠ ጽዮን በነገሠ በኻያኛው ዓመት ወደ ገበዘ አኵሱም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሔዱ። ያን ጊዜ ጳጳሱ አባታችን ሉቃስ ያጠምቀው ዘንድ ቀረበ። ❤ በሕፃን አባለ ክርስቶስ በሰውነቱ ላይ ያለውን የትርጓሜው ነገር ተገልጦ ያልታወቀ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈውን በአየ ጊዜ ደነገጠ፤ ወደቀም፤ ታወከም፤ እንደ ሰከረም ሆነ። ነገር ግን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ፈጥኖ መጥቶ አነሣውና ከድንጋጤው አነቃው። ከድንጋጤውም ካነቃው በኋላ "አንተ የጳጳሳት አለቃ አባ ሉቃስ ይኸን ድንቅ በአየህ ጊዜ ፈጥነህ አጥምቀው" አለው። "ስሙንም አባለ ክርስቶስ" ብለህ አውጣለት፤ ትርጓሜውም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እንደ ቅዱስ ፋኑኤል አጋንንትን የሚያባርር፤ እንደ ጌታው እንደ ክርስቶስ መድኀኔ ዓለም ሕሙማንን የሚያድናቸው፤ በአጋንንት የተያዙትን፤ አጋንንት የሚጥሉዋቸውንና ሕሙማንን የሚፈውሳቸው፣ አጋንንትንም የሚያባርራቸው ነው"። ❤ "ይኸም ሕፃን አባለ ክርስቶስ ከተጠመቀና ከአደገ በኋላ በሕይወት ዘመናቸው እግዚአብሔርን ደስ ለአሰኙት ለማኅበረ ዴጔ ጻድቃን አባቶች አቅራብያ በሆነች ናዕዴር በምትባል በተባረከችና በተቀደሰች ሀገር ይኖራል"። "የደብሩም ስም አልሓትያ ትባላለች። ወደ ደብሩ በሚገባበት ጊዜም አንደበታቸው ድዳ የሆኑ ሰዎችና የእግዚአብሔር ወዳጅ የአምላክ ባሪያ እንደሆነ እንደ ሙሴ አንደበታቸው የተዘጋ በእርስዋ ያገኛል። ወደ ደብሩ በሚገባበት ጊዜም እነዚያ የተባረኩ ሕዝቦች የአንደበታቸው ድዳነት ማሰሪያ ይፈታል። ደብሩም ደብረ አልሓትያ ተብላ ትጠራለች። ❤ "ዛሬም ፈጥነህ አጥምቀው፤ ስሙንም 'አባለ ክርስቶስ' ብለህ አውጣለት" አለው። ይኸም አባት ጳጳሱ አባታችን ሉቃስ በዚያን ጊዜ መጋቢት ኻያ ስምንት ቀን በገበዘ አኵሱም አጠመቀው፣ ቅዱስ ቍርባንም አቈረበው። የተቀደሰች የልደቱ በረከት በኹላችን ሕዝበ ክርስቲያን ላይትሁን ለዘለዓለሙ አሜን። ከአባታችን ከአቡነ አባለ ክርስቶስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ ገድለ አባለ ክርስቶስ።                  

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #የካቲት ፲፱ (19) ቀን። ❤ እንኳን #ለተጋዳይ_መነኰስ ለሆኑት በዝሙት ላለመውደቅና ገሃነመ እሳትን በማሰብ እግራቸውን የሚነድ እሳት ውስጥ በመጨመር ዘማዊቷንም ሴት ለንስሓና ለጽድቅ ላበቋት ለታላቁ አባት #ለአባ_መርትያኖስ_ሥጋቸው_ከአቴና_አገር_ወደ_አንጾኪያ_ለፈለሰበት_በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                         ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #አባ_መርትያኖስ፦ እርሱም ሽንግላ በኃጢአት ልትጥለው በወደደች ጊዜ ከአመንዝራ ሴት ከተፈተነ በኋላ እርሱ ግን መንኵሳ በገድል እስከ ተጸመደች ድረስ ስቦ ወደ ንስሓ መልሷታል። ከዚህም በኋላ መኖሪያውን ትቶላት ከአገር ወደ አገር የሚዞር ሆነ ከአቴና አገርም ደርሶ በዚያ ጥቂት ቀን ኖረ ጥቂትም ታመመና በሰላም አረፈ ዜናው በግንቦት ሃያ አንድ ቀን እንደተጻፈ። ❤ የከበረ ቴዎድሮስም ለአንጾኪያ አገር በከሀዲው የፋርስ ንጉሥ ዘመን ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ይህ አባት የካህናት አለቆችንና ምእመናንን ልኮ ሥጋውን ከአቴና አፍልሰው ወደ አንጾኪያ ከተማ አመጡት በምስጋናም እየዘመሩ አክብረው ተቀበሉት ሊቀ ጳጳሳቱም ተሳለመው በሣጥንም አድርጐ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖረው። በዚችም ዕለት የካቲት19 በዓልን አደረገለት። ለእግዚአብሔር ምስና ይሁን እኛንም በአባ መርትያኖስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት19 ስንክሳር።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ "#ሰላም_ለፍልሰተ_ሥጋከ ኀበ አንጾኪያ እምአቴና። #በእደ_ቴዎድሮስ አብ ዘሥርግው በጵጵስና። #መርትያኖስ_ተወከፍ ዘመሥዋዕተ ቃል ጼና። በከናፍረ ልብ ወበአፈ ኅቡእ ሕሊና። ሶበ ለሥጋከ እኤምኅ ሣፁና"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲ_19።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "እስመ ብከ እምድኅን እምንሱት። ወበአምላኪየ እትዐደዋ ለዕረፍት። ለአምላኪየሰ ንጹሕ ፍኖቱ"። መዝ 17፥19-20።  የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 7፥22-ፍ.ም፣ ያዕ 4፥1-11 እና የሐዋ ሥራ 16፥16-22። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 13፥10-18። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም በዐልና የጾም ወራት። ለሁላችንም ይሁንልን።                 

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #የካቲት ፲፰ (18) ቀን። ❤ እንኳን #ከሰባ_ሁለቱ_አርድእት ለአንዱ ለጌታችን ወንድም ለተባለ #ለሐዋርያው_ለቅዱስ_ያዕቆብ ለዓመታዊ ለመታሰቢያ በዓሉና ለታማኝ ለከበረ አባት ለአንጾክያ አገር ሊቀ ጳጳስ ከአርዮሳውያን ብዙ ስደትና እንግልት ለደረሰበት #ለአባ_መላልዮስ ለዕረፍቱ  መታሰቢያ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን፡፡                                                          ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ወልደ_ዮሴፍ፦ ይኸውም ቅዱስ የጌታችን ወንድም የተባለውና የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ የነበረው ነው፡፡ እርሱም የጠራቢው የዮሴፍ፡ልጅ ሲሆን ከአራቱ ልጆቹ ትንሹ መጨሻው ነው፡፡የቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ እናቱ በልጅነቱ ስለሞተችበትና የብርሃን እናቱ የሆነች ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን ዮሴፍ አረጋዊ በ83 ዓመቱ ጠባቂ ይሆናት ዘንድ ወደቤቱ ሲወስዳት ድንግል ማርያም ቅዱስ ያዕቆብን የሙት ልጅ ሆኖ አግኝታው ከተወደደ ልጇ ከጌታች ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብራ ተንከባክባ አሳድጋዋለች፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ያዕቆብ ድንግልና ንጹሕ ሆኖ ከጌታችን ጋር እየተጫወተ አብሮ አድጓል፡፡ ❤ ከጌታችን ዕርገት በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ አድርገው ሾመውታል፡፡ ብዙዎችንም አስተምሮ ወደ ቀናች ሃይማኖት መልሷቸዋል፡፡ ሕዝቡም የታመሙትን ድውያንን ሁሉ እያመጡለት ይፈውሳቸው ነበር፡፡ ከኢየሩሳሌምም ውጭ እየሄደ ያላመኑትንም አስተምሮ እያጠመቀ ቤተ ክርስቲያን ይሠራላቸው ነበር፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ በጾም በጸሎት ሆኖ በመቆም ብዛት እግሮቹ አብጠው ነበር፡፡ ❤ አንድ ቀን አይሁድ ተሰብስበው መጥተው ጌታችን የማን ልጅ እንደሆነ ይነግራቸው ዘንድ ወደ ቅዱስ ያዕቆብ መጡ፡፡እነርሱም ወደ ቅዱስ ያዕቆብ የመጡት ጌታችን የዮሴፍ ልጅ እንደሆነና የእርሱም የሥጋ ወንድም እንደሆነ እንደሚነግራቸው አስበው ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ያዕቆብ ከፍ ካለው ከሦስተኛው መደብ ላይ ወጥቶ ጌታችን የራሱ የያዕቆብና የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ መሆኑን መሰከረባቸው፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ፍጹም አምላክ መሆኑን፣ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና ከአብም ጋር፡ ትክክል እንደሆነ መሰከረባቸው፡፡ ይህንንም በሰሙ ጊዜ አይሁድ እጅግ ተናደው በጽኑ ግርፋት ካሠቃዩት በኋላ ራሱን ቀጥቅጠው ስለገደሉት ሰማዕትነቱን፡ ሐምሌ 18 ቀን በድል ፈጽሟል፡፡ ከሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ረድኤት በረከትን ያሳትፈን። በጸሎቱ ይማረን!። ምንጭ፦ ገድለ ሐዋርያትና መዝገበ ቅዱሳን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_መላልዮስ፦ ይህም ቅዱስ አዋቂና አስተዋይ ነበረ ነው፡፡ በታናሹ ቈስጠንጢኖስም ዘመነ መንግሥት በአንጾኪያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ፡፡ ከተሾመም እስከ ሠላሳ ቀን ኖረ፡፡ ከዚያም በኋላ አርዮሳውያንን አወገዛቸው። በአንጾኪያ ካለች ቤተ ክርስቲያንም፡ አሳደዳቸው። ንጉሡም በሰማ ጊዜ ከመንበረ ሢመቱ ሊቀ ጳጳሱን አሳደደው እርሱ አርዮሳዊ ነውና። ❤ የአንጾኪያ አገር ታላላቆችና ኤጲስጶሳት ካህናቱም ተሰብስበው ስለ ሊቀ ጳጳሳቱን ይመልስላቸው ዘንድ የልመና ደብዳቤ፡ ጽፈው ለንጉሡ ላኩ፡፡ ንጉሡም ልመናቸውን ተቀብሎ መለሰላቸው፡፡ ይህም አባት በተመለሰ ጊዜ አርዮሳውያንን ወደ ማውገዙ ተመለሰ በቃላቸው የሚያምኑትንም ስሕተታቸውንና ስድባቸውን ግልጽ እያደረገ ወልድ ከአብ ባሕርይ እንደ ተወለደ በመለኮቱም ትክክል እንደሆነ በሁሉ የሚሰብክ የሚያስተምር ሆነ። ዳግመኛ አርዮሳውያን ተነሡ የንጉሡን ልብ ወደእርሳቸው እስከ መለሱ ድረስ ይህን አባት እየወነጀሉ ወደ ንጉሥ ጻፉ ዳግመኛም ልኮ ከፊተኛው ወደሚርቅ አገር አሳደደው። ወደ ተሰደደበት አገር በደረሰ ጊዜ መልእክቶቹን ጽፎ በመላክ ከወገኖቹ ጋር እንደ ሆነ ከእርሳቸውም ሥውር የሆነውን የመጻሕፍትን ቃል ይተረጒምላቸው ነበር፡፡ በአንጾኪያ ላሉ መንጋዎቹም ይደርሳቸውል አዋቂዎች የሆኑ ኤጲስቆጶሳትንና ቀሳውስትን ልዩ በሆነች ሦስትነት ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ አባቶቻችን ያስተማሩዋት የቀናች ሃይማኖትን እንዲህም እያደረገ እስከ ዐረፈበት ቀን ድረስ በተሰደደበት ብዙ ዘመናት ኖረ። ❤ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም አመስግኖታል፡፡ የምስጋና ድርሰቶችንም ደረሰለት፡፡ ስለቀናች ሃይማኖትም ብዙ መከራ ስለደረሰበት ክብሩ ግርማው ከከበሩ ሐዋርያት ክብር እንደማይጎድል ተናገረ፡፡ የአባ መላልዮስ ዕረፍቱ የካቲት18 ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱ ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የካቲት 18 ስንክሳር።                              ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለመላልዮስ_ዘእሙን_ነገሩ። አርዮሳውያን ሕዝብ እለ አውጽእዎ እማኅደሩ። #አፈ_ወርቅ_ዮሐንስ_በከመ_ወደሶ በዕለተ ተዝካሩ። እንበይነ ስደቱ ወእንበይነ ብዙኅ ኅሣሩ። እምሐዋርያት ይቤ ኢየሐጽጽ ክብሩ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_18።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ይዘግቡ ወኢየአምሩ ለዘይስተጋብዑ። ወይእዜኒ መኑ ተስፋየ አኮኑ እግዚአብሔር። ወትግሥትየኒ እምኀቤከ ውእቱ"። መዝ 38፥6-7። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 6፥19-22።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ። ውስተ ኵሉ ምድር ወጽአ ነገሮሙ። ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ"። መዝ 18፥3-4። የሚነበቡት መልዕክታት ገላ 1፥15-ፍ.ም፣ ያዕ 1፥1-12 እና የሐዋ ሥራ 21፥17-27። የሚነበበው ወንጌል ማቴ13፥53-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም የቅዱስ ያዕቆብ የዕረፍት  በዓልና የጾም ወራት። በሁላችንም ይሁንልን።                

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #የካቲት ፲፯ (17) ቀን። ❤ እንኳን #የእግዚአብሔር_ሰው ለሆነ #ለየዋህ_ለትሑቱ_ለነቢያት_አለቃ_ለቅዱስ_ሙሴ ለዕረፍቱ መታሰቢያ ለበዓል፣ ከላይኛው ግብጽ ከአክሚም መንደር ለሆነ ስለ #እግዚአብሔር_አብ_አባትነት_ስለ_ወልድ_ልጅነት መስክሮ በእስላሞች መኰንን እጅ ሰማዕትነት ለተቀበለ #ለታላቁ_ጻድቅ_ወሰማዕት_ለመነኰስ_አባ_ሚናስ ለዕረፍቱ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ሊቀ_ነቢያት_ቅዱስ_ሙሴ፦ ይህ ነቢይ ነፍሱን ስለእርሳቸው አሳልፎ እስከ መስጠት ደርሶ ከእግዚአብሔር ወገኖች ጋር የደከመ ነው እርሱም በግብጽ አገር በኤርትራ ባሕርም ድንቆች ተአምራትን ያደረገ ነው። ይህም ስለ ፈርዖን ትእዛዝ ወላጆቹ በግብጽ ወንዝ ውስጥ በጣሉት ጊዜ አውጥታ ላሳደገችው ለፈርዖን ልጅ ለተርሙት ልጅዋ መባልን አልወደደም። እርሱ ፈርዖን የዕብራውያንን ወንዶች ልጆች ይገድሏቸው ዘንድ አዝዞ ነበርና። በአገኘችውም ጊዜ ለርሷ ልጅ ሊሆናት ወስዳ በመልካም አስተዳደግ አሳደገችው። ❤ አርባ ዓመትም በሆነው ጊዜ አንዱን ዕብራዊ የግብጽ ሰው የሆነ ሲያጠቃው አየ ለዕብራዊው ተበቅሎ ግብጻዊውን ገደለው። በማግሥቱ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አያቸው ሊያስታርቃቸውና በመካከላቸው ሰላምን ሊአደርግ ወደደ። አንዱ ዐመፀኛም "ትላንት ግብጻዊውን እንደገደልከው ልትገድለኝ ትሻለህን" አለው። ስለዚህም ነገር ሙሴ ፈርቶ ወደ ምድያም አገር ሸሸ በዚያም ሚስት አግብተሸ ሁለት ልጆችን ወለደ በዚያም አርባ ዓመት ኖረ በጳጦስ ቊጥቋጦ ውስጥ እግዚአብሔር ተናገው። ወደ ግብጽ አገርም ሒዶ የእስራኤልን ልጆች ከዚያ እንዲያወጣቸው አዘዘው። ❤ ከዚህም በኋላ ሕዝቡን ከግብጽ አገር አወጣቸው የኤርትራንም ባሕር ከፍሎ በውስጡ አሳለፋቸው የባሕሩንም ውኃ በጠላቶቻቸው በፈርንና በሠራዊቱ ላይ ገልብጦ አሠጠማቸው። ከዚህም በኋላ በምድረ በዳ ውስጥ አርባ ዓመት ሙሉ መና አወረደላቸው ውኃንም ከአለት አፈለቀላቸው ይህን ሁሉ በጎ ሥራ በዚህ በደግ ነቢይ ሙሴ እጅ እግዚአብሔር አደረገላቸው እነርሱ ግን ይዘልፉት ነበር ብዙ ጊዜም በድንጊያ ሊወግሩት ሽተው ነበር። እርሱ ግን በእነርሱ ላይ ልቡን አስፍቶ በመታገሥ ስርሳቸው ወደ እግዚአብሔር ይማልዳል። እነርሱንም አብዝቶ ከመውደዱ የተነሣ እግዚአብሔርን "አቤቱ የዚህን ሕዝብ በደሉን ይቅር ካላክ ከሕይወት መጽሐፍህ ሰርሰዘኝ" አለው። ❤ ሰው ከወዳጁ ጋር እንደሚነጋገር አምስት መቶ ሰብዓ ቃላትን ከእግዚአብሔር ጋር እንደተነጋገረ መጽሐፍ ምስክር ሆነ። የእስራኤል ልጆችም በሚያዩት ጊዜ እንዳይሞቱ ፊቱን እስከ መሸፈን ድረስ በእግዚአብሔር በጌትነቱ ብርሃን ፊቱ በራ። ❤ መቶ ሃያ ዓመት የሆነ ዕድሜውም በተፈጸመለት ጊዜ ለአገልጋዩ ለነዌ ልጅ ለኢያሱ ሕዝቡን እርሱ እንዲጠብቃቸው በእጁ ውስጥ እንዲአስረክበው እግዚአብሔር ሙሴን ለኢያሱ አስረክብ ብሎ አዘዘው። ሙሴም ኢያሱን ጠርቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አዘዘው ሕጉንም እንዲጠብቅ ሕዝብንም ለኢያሱ በእጁ አስረከባቸው ወደ ምድረ ርስት እርሱ እንደ ሚአስገባቸው አረጋገጠላቸው። ❤ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው በምስክር ድንኳን ውስጥ የሚሠራውን ሁሉ ሠርቶ ከአዘጋጀ በኋላ በናባው ተራራ ውስጥ ዐረፈ በዚያም በመላእክት እጅ በሥውር ተቀበረ። የእስራኤል ልጆች ወስደው እንዳያመልኩት እግዚአብሔር የሙሴን ሥጋ ሠወረ። በእስራኤል ልጆች ውስጥ እንደ ሙሴ ያለ ደግ የዋህ ቅን የሆነ ነቢይ እንደማይነሣ መጽሐፍ ምስክር ሆነ። ❤ ሰይጣንም የሙሴን ሥጋ ለእስራኤል ሊገልጠው በወደደ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ በጻፈው መጽሐፍ እንደመሰከረ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ገሠጸው ከዚህም ሥራ ከለከለው። የእስራኤል ልጆች አርባ ቀን አለቀሱለት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሊቀ ነቢያት በቅዱስ ሙሴ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የመስከረም 8 ስንክሳር።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #መነኰስ_አባ_ሚናስ፦ የዚህም ቅዱስ፡ ወላጆቹ ምድርን የሚያርሱ ክርስቲያን ገበሬዎች ናቸው። እርሱም ይህን ዓለም ንቆ ትቶ በአገረ አክሚም በሚገኝ በአንድ ገዳም መነኰሰ ለመብልና ለመጠጥ ሳይገዛ በየሁለት ቀን እየጾመ ብዙ ቀኖችን ኖረ ከዚያም ወጥቶ ወደ እስሙናይን አገር ሒዶ በአንድ ገዳም ውስጥ እያገለገለና እየተጋደለ ከገዳሙ ደጃፍ ሳይወጣ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖረ። ❤ እስላሞችም በግብጽ አገር በነገሡ ጊዜ ለእግዚአብሔር ከርሱ ጋር ለዘላለሙ ህልው የሆነ የባሕርዩ የተወለደ ልጅ የሚሠርፅ መንፈስ ቅዱስም የለውም እንደሚሉ ሰማ ስለዚህም ነገር እጅግ አዘነ። ከአበ ምኔቱም ቡራኬ ተቀበለ ወደ እስሙናይን ከተማ ወጥቶ ሔደ የእስላሞች ሠራዊት አለቃ በሆነ በመኰንኑ ፊት ቁሞ እንዲህ አለው "እናንተ ለእግዚአብሔር ከባሕርዩ የተወለደ ልጅ እንደ ሌለው አድርጋችሁ የምትናገሩ እውነት ነውን?" መኰንኑም "አዎን ልጅ አለው ማለትን ከእግዚአብሔር እናርቃለን" አለ። አባ ሚናስም "ያለ ልጅ ልታምኑ አይገባም እርሱም ያለ ዘር ያለ ሩካቤ የሆነ ነው ከባሕርዩ ተወለደ እንጂ" አለው። መኰንኑም "ልጅ አለው ማለት በሕጋችን ክህደት ነው" አለ። አባ፡ሚናስም እንዲህ አለው "መኰንን ሆይ እወቅ የከበረ ወንጌል በወልድ ያመነ የዘላለም ሕይወት አለው በእግዚአብሔር ልጅ በወልድ ያላመነ ሕይወትን አያይም የእግዚአብሔር ቊጣ በላዩ ይወርዳል እንጂ ብሏልና"። ስለዚህም መኰንኑ እጅግ ተቆጣ ራሱንም በሰይፍ እንዲቆርጡ ሥጋውንም በየቊርጥራጭ ቆራርጠው ከባሕር እንዲጥሉት አዘዘ ምእመናንም ሥጋውን ወስደው በበጎ አገናነዝ ገንዘው ቀበሩት መታሰቢያውንም አደረጉ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት17 ስንክሳር።                             ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_እብል_ለሚናስ_ፍጹም። ዘሀገረ አክሚም። ሶበ ይብል አምላክ ወልደ ማርያም ተንባላት በበግማድ ገመድዎ ዮም። ወወረውዎ ውስተ ባሕር መሥጥም"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_17።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "አርአየ ፍናዊሁ ለሙሴ። ወለደቂቀ እስራኤል ሥምረቶ። መሐሪ ወመስተሣህል እግዚአብሔር"። መዝ 102፥7-8። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 11፥23-29፣ ይሁ 1፥7-11 የሐዋ ሥራ 7፥20-44። የሚነበበው ወንጌል  ሉቃ 20፥37-41። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ሙሴ የዕረፍት በዓልና የጾም ወራት ለሁላችንም ይሁንልን።                

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #የካቲት ፲፮ (16) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ለጻድቁ_ንጉሥ #ለቅዱስ_ላሊበላ_ታላቅ_ወንድም ለሆነው #ለቅዱስ_ገብረ_ማርያም ለዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል፣ ጌታችንን ልጅን በሞት እዲወስድለት የለመነው #ለጻድቁ_ንጉሥ_ለቅዱስ_ነዓኩቶ_ለአብ_ለልጁ ለዕረፍት በዓልና ለኢትዮጽያዊው ጻድቅ #ለአቡነ_መልከ_ጼዴቅ_ዘሚዳ ለልደታቸው መታሰቢያ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #ጻድቁ_ንጉሥ_አፄ_ገብረ_ማርያም፦ የላስታ ገሥታት የዘር ሐረጋቸው ከንጉሥ ሰሎሞን ዘር ሲያያዝ የመጣ ነው፡፡ ከ10ኛው እስከ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (920-1253 ዓ.ም ገደማ) በላስታ ቡግና ምድር የነገሡ የላስታ ቡግና ተወላጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ቅዱሳን ነገሥታት የንግሥናቸው መጠሪያ "የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት "ወይም" የላስታ መንግሥት" በመባል ይታወቃል፡፡ ከላስታ(ከዛጉዌ)ነገሥታት መካከል ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ገብረ ማርያም፣ ቅዱስ ላሊበላና ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ እነዚህ አራቱ ነገሥታት እንደ መልከጼዴቅ(ዘፍ14፥18) ክህነትን ከንግሥና፣ ቅድስናን ከንጽሕና ጋር አንድ አድርገው በመያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅድስናና፡ በንጽሕና አገልግለው አልፈዋል፡፡ ❤ ጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ገብረማርያም በሌላኛው ስማቸው ሐርቤይ እየተባሉ የሚጠሩ ሲሆን የቅዱስ ላሊበላ ታላቅ ወንድም ናቸው፡፡ ታላቁን ጻድቅ ንጉሥ ቅዱስ ነዓኵቶ ለአብን ወልደዋል፡፡ አባታቸው ዣን ስዩም 40ዓመት ከነገሡ በኋላ በ76ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ልጃቸው ገብረ ማርያም ንግሥናውን ተቀብለዋል፡፡ ከእርሳቸው ቀጥሎ ታናሽ ወንድማቸው ቅዱስ ላሊበላ ተወልዶ እንደሚነግስ በትንቢት ተነግሮ፡ ነበር፡፡ ይህን ጊዜ ከላሊበላ ጋር በአባት እንጂ በእናት ይለያዩ ነበርና የበጎ ነገር ጠላት የሆነ ክፉ ሰይጣን የእኅታቸው ክፉ ምክር ተጠቅሞ በወንድማቸው በላሊበላ ላይ በቅናት ክፉ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል፡፡ስለ ንግሥናቸው ሲሉ ምንም እንኳን በወንድማቸው ላይ ክፉ አስበው የነበረና በእኅታቸውም ክፉ ምክር መርዝ የሰጡት ቢሆንም በኋላ በክፉ ሀሳባቸው እጅግ ተፀፅተው "አምላኬንም ወንድሜንም አሳዘንኩ" በማለት ወንድማቸውን ይቅርታ በመጠየቅ ላሊበላን አንግሠውት እርሳቸው መንኵሰው ገዳም ገብተዋል፡፡ ❤ ቅዱስ ላሊበላ ካለበት አክሱም ድረስ ሄደው በዕንባና በልቅሶ ይቅርታ ጠይቀው ወደ አገራቸው ሮሐ ከተማ ይዘውት በመምጣት መንግሥታቸውን አስረክበውት ነው የመነኑት፡፡ በምንኵስናም ሆነው በታላቅ ተጋድሎ በጾም በጸሎት በመትጋት እግዚአብሔርን እያገለገሉ እያለ ጌታችን ተገልጦላቸው "ክብሩ እንደ መላእክት የሆነ ታላቅ ልጅ ትወልዳለህና ወደቤትህ ተመለስ" ብሎ ከነገራቸው በኋላ ወደቤታቸው ተመልሰው ቅዱስ ነአኵቶ ለአብን ወልደዋል፡፡ ❤ ንጉሥ ቅዱስ ገብረ ማርያም በዘመናቸው ከነበሩት ከእስክንድሪያ ሊቀ ጳጳሳት ከአባ ዳንኤል ጋር መልእክት በመላላክ "ከሀገሬ ሊቃውንት መነኰሳት የሕዝቡን ቋንቋ የሚሰሙና የሚያስተምሩ ጳጳስ ይሹሙልን" በማለት ለእስክንድሪያ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ምንም እንኳን የእስክንድሪያ ሲኖዶስ በወቅቱ ኢትዮጵያ፡ የራሷንልጆች እንድትሾም ስላልፈለጉና በወቅቱ ፈቃደ እግዚአብሔርም ስላልነበረ የቅዱስ ገብረ ማርያምን ጥያቄ ንግሥት ዘውዲቱና ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ድጋሚ በመጠየቅ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ቢያደርጉትም መሠረቱን ግን የጣሉት ዐፄ ገብረ ማርያም ናቸው በዘመናቸው ብዙ አብያተ ክርስቲያናትንም ያሠሩ ሲሆን ጊዜ ዕረፍታቸው ሲደርስ ጌታችን ተገልጦላቸው "የእኔን መከራ እያሰብክ ከዓይንህ ዕንባ ሳያቋርጥ በጾም በጸሎት ተወስነህ ስላገለገልኸኝ በአንተ ስም ለተራበ ያበላውን፣ ለተጠማ ያጠጣውን፣ ለታረዘ ያለበሰውን ምሬልሃለሁ" በማለት ትልቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸው በካቲት 16 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡ ጻድቁን ንጉሥ ዐፄ ገብረ ማርያምን ሚያዝያ10 ቀን የሚነበበው ስንክሳር በሰፊው ይጠቅሳቸዋል፡፡ ከጻድቁ ከአቡነ ገብረ ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን! ።                                ✝ ✝ ✝ ❤ #ጻድቁ_ንጉሥ_ነአኵቶ_ለአብም፦ እጅግ ጻድቅ ንጉሥ ሲሆን ያሳደገው ቅዱስ ላሊበላ ነው። ከላሊበላ ቀጥሎ በመንገሥ 40ዓመት በቅድስና አገልግሏል። "ነአኵቶ ለአብም" ብሎ ስሙን ያወጣለት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው። ዕድሜው ከፍ ሲል ጌታችን ለላሊበላተገልጦለት ሚስት እንዲያጭለት ነግሮት ሚስት የታጨለት ቢሆንም እርሱ ግን እግዚአብሔርን በድንግልና ማገልገል ይፈልግ ነበር ሚስት ካገባም በኋላ ከሚስቱ ጋር ተማክሮ ሁለቱም ድንግልናቸውን ጠብቀው 25ዓመት ሙሉ በትዳር ውስጥ አብረው እየኖሩ ነገር ግን በድንግልና ሆነው ኖረዋል። እንዲህ አይነቱ ቅድስና በምን ዓይነት ቃል ይገለጻል በእውነት!?ከዚያም በኋላ መልአክ ተገልጦ ነአኵቶ ለአብን "በሕግ በንጽሕና የተጋባችሁት ልጅ ልትወልዱ ነው እንጂ ዝም ብላችሁ ልትኖሩ አይደለም" ብሏቸው እነርሱም ፈቃደ እግዚአብሔር ከሆነ ብለው አንድ ቀን ብቻ በግብር ተዋወቁና ልጅ ወለዱ። ልጁም እጅግ የሚያምርና የሚያሳሳ ቢሆንም፡ ንጉሡ ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ የወደፊቱን ያውቅ ነበርና ሱባኤ ገብቶ "በእኔ እግር ተተክቶ ሲነግሥ ፍርድ አጣሞ አንተንም ሰውንም ከሚበድል ይህን ልጄን ቅሰፍልኝና ሄሮድስ ካስፈጃቸው ሕፃናት ጋር ደምርልኝ" በማለት፡ ወደ፡እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ እንደ ጸሎቱም ጌታችን የካቲት 16 ቀን ልጁን በሰላም አሳርፎለት ሄሮድስ ካስፈጃቸው ሕፃናት ጋር ደምሮለታል፡፡ ከጻድቁ ንጉሥ ነአኵቶ ለአብ ልጅ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_መልከ_ጼድቅ_ዘሚዳ፦ አባቶቻችንና ወንድሞቻችን እነሆ እነግራችኋለን አባታችን መልከ ጼድቅ አገር ጐጃም ኤናይ በምትባል ቦታ በየካቲት ዐሥራ ስድስት ቀን ተወለደ። ይህ ቅዱስ አባት በተወለደ ጊዜም በአባትና እናቱ ቤት ታላቅ ደስታ ሆነ እግዚአብሔር ለብዙዎች አባት አድርጎ መርጦታልና። ይህም ጻድቅ ከከበሩና ነገሥታት ከሆኑት ወገን ተወለደ ልደቱም እንዲህ ነበር ንጉሥ ዓምደ ጽዮን፣ ምስርነዓዳን ወለደ ምስርነዓዳን በዝራምበሳን ወለደ፣ በዝራምበሳም ፍሬጽዮንን ወለደ፣ ቅዱስ ፍሬጽዮንም መልከጼድቅን ወለደ የእናቱም ስም ቅድስት ዓመተ ማርያም ነው። ከአቡነ መልከ ጼድቅ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። ምንጭ፦ገድለ አቡነ መልከ ጼድቅ የሰኞ።                 

❤ ከዚህም በኋላ ይቺ ቅድስት ኤልሳቤጥ መጥምቁ ዮሐንስን ፀንሳ ወለጀችው ከሰዎችም የሚደርስባት ሽሙጥ ተወግዶ እጅ ደስ አላት። ሕፃኑም በማሕፀኗ እያለ እመቤታችን ድንግል ማርያም ሰላምታ በሰጠቻት ጊዜ እንዲ ብላ ጮኸች "ከሴቶች ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ የማሕፀንሽም ፍሬ ቡሩክ ነው። የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ እነሆ እንዴት ነሽ ስትይኝ የሰላምታሽን ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ልጁ በማሕፀኔ ውስጥ በደስታ ዘለለ (ሰገደ)"። ❤ ከዚህም በኋላ ጌታችንን አየችው በአምላክነቱም አመነች የሚያምኑበትም በመዳናቸው ደስ አላት ዕድሜዋንም በፈጸመች ጊዜ በበረሀ ውስጥ ሳለች የካቲት16 ቀን በሰላም ዐረፈች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ኤልሳቤጥ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት 16 ስንክሳር።                             ✝️ ✝️ ✝️ ❤ "ሰላም ለኪ መጽሐፈ ሕግ ወኪዳን። አምሳለ ጽሌ ዘዕብን። ለእለ ጸውዑ ስምኪ ውስተ ገጸ ኵሉ መካን። ርኅርኅተ ልብ ለኃጥአን ርኅርኅተ ልብ ለግፉዐዓን። ርኅርኅተ ልብ ለኵሉ ማርያም አማን"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የየካቲት 16።                                                     ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ዘያነብራ ለመካን ውስተ ቤቱ። ወያስተፌሥሓ ለእመ ውሉድ። ዘያነብራ ለመካን ውስተ ቤቱ። መዝ 112፥9። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ1፥5-18።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "እስመ ትቤ ለዓለም አሐንጽ ምሕረተ። በሰማይ ፀንዐ ጽድቅከ። ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ"። መዝ 88፥2-3። የሚነበቡት መልዕክታት ገላ 4፥1-12፣ 2ኛ ዮሐ 1-8 እና የሐዋ ሥራ 1፥13-15። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥39-57። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ቃል ኪዳን የተቀበለች (የኪዳነ ምሕረት) በዓል፣ የቅድስት ኤልሳቤጥ የዕረፍት በዓልና የጾም ወራት። ለሁላችንም ይሁንልን።                

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #የካቲት ፲፮ (16) ቀን። ❤ እንኳን #አምላክን_ለወለደች_ለእናታችን_ለእመቤታች_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም ከተወደደ ልጅዋ #ከጌታችና_ከመድኃኒታች_ከኢየሱስ_ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳንን ለተቀበለችበት (#ለኪዳነ_ምሕረት) ዓመታዊ በዓልና ለመጥምቀ መለኮት #ለቅዱስ_ዮሐንስ_እናት ለከበረች #ለቅድስት_ኤልሣቤጥ ለዕረፍቷ መታሰቢያ በዓል  በሰላም አደረሰን።                                                   ✝ ✝ ✝ ❤ በዚች ዕለት የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም #አምላክን_ለወለደች_ለእመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም በዓልን ያደርጋሉ። በዚች ዕለት መታቢያውን ለሚያደርግ ስሟን ለሚጣራ ለድኆችና ለችግረኞች እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ከተወደደ ልጅዋ ከጌታችና ከመድኃኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳንን ተቀብላለችና። ❤ ይህችም የከበረች እመቤታች ልጅዋ ንጹሕ ሥጋዋን ተዋሕዶ ከብቻዋ ኃጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ ፈጽሞ ስለእኛ መዳን ወዶ ያደረገውን መከራ ተቀብሎ ሙቶ ተነሥቶ ከዐረገና በአባቱ ዕሪና ከተቀመጠ በኋላ እርሷን እናቱን ማርያምን በደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ዘንድ ትቷት ነበር እነሆ ልጅሽ እርሱንም እነሆዋት እናትህ ብሎ አደራ እንዳስጠበቀው። ከዚያንም ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ማርያም ትጸልይ ዘንድ ያለ ማቋረጥ ወደ ልጅዋ መቃብር ሁል ጊዜ ስትሔድ ኖረች ይኸውም ጎልጎታ ነው። አይሁድም በአዩዋት ጊዜ ቊጣንና ቅናትን ተመልተው በደንጊያ ሊወግሩዋት ወደዱ እግዚአብሔርም ከዓይናቸው ሠወራት ከዚህም በኋላ ዳግመኛ መጥታ በዚያ እንዳትጸልይ ተማክረው ከመቃብሩ ዘንድ ጠባቂዎችን አኖሩ እርሷ ግን በየዕለት መሔድን አላቋረጠችም ጠባቆችም አያይዋትም የልጅዋ የጌትነቱ መጋረጃ ሠውርዋታልና መላእክትም መጥተው ያገለግሏታል ጌታችንም ዘወትር፡ ይጐበኛታል የምትሻውንም፡ ይፈጽምላት ነበር። ❤ ከዚህም በኋላ መላእክት ወደ ሰማያት አሳረጓትና የጻድቃንን ማደሪያዎች አሳዩዋት አብርሃም፣ ይስሐቅና፣ ያዕቆብም ወዳሉበት አደረሱዋት ከአዳም ጀምሮ እስከዚያ ዕለት በአካለ ነፍስ ያሉ አባቶች ሁሉ "አንቺን ከሥጋችን ሥጋን ከዐፅማችን ዐፅምን ለፈጠረልን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የአምላክ ልጅ ከአንቺ ሰው በመሆኑ በአንቺ ድኅነትን አግኝተናልና ከጥፋትም የሕይወት ወደብ ሁነሽናልና" እያሉ ሰገዱላት። ከዚያም ወደ ተወደደ ልጅዋ የእሳት መጋረጃ ወደተተከለበት ወደ ጌትነቱ ዙፋን አደረሱዋት ጌታችንም እጅዋን ይዞ ወደ ውስጠኛው መጋረጃ አስገብቶ ከጌትነቱ ዙፋን ላይ አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጣት ያዘጋጀላትንም ዐይን ያላየው ጆሮ ያልሰማውን በሰው ልቦና ያልታሰበው ተድላ ደስታን ሁሉ ነገራት። ከጌትነቱ ዙፋንም በታች የእስራኤል ንጉሥ አባቷ ዳዊትን የነቢያትና የመላእክት ማኅበር እንደግድግዳ ከበውት በመሰንቆ ሲያመሰግን አየችው እንዲህም ይላል "ልጄ ስሚ ጆሮሽም አድምጪ ወገንሽን የአባትሽንም ወገን ርሺ ንጉሥ ደም ግባትሽን ወዷልና እርሱም ጌታሽ ነውና። ❤ ዳግመኛም የሥቃይን ቦታ ያሳዩዋት ዘንድ መላእክት ከዚያ ወሰዱዋት ለሰይጣንና ለሠራዊቱ በእርሱ ጐዳና ለሚጓዙ ሁሉ ወደተዘጋጀ ወደጨለማው ዳርቻ አደረሷት። እመቤታችን ማርያምም "ወዮልኝ ወደዚህ እንዳይመጡ ለሰው ልጆች ማን በነገራቸው" አለች መልአኩም "እመቤቴ ቡርክት ማርያም ሆይ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ይኖራልና ለአንቺም ከአንቺ በኋላም በቃል ኪዳንሽ ለሚታመኑ አትፍሪ" አላት ከዚህም በኋላ ወደ ቦታዋ መለሷት። ❤ ከዚያንም ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ድንግል ማርያም ስለ ኃጥአን እጅግ እያዘነች ኖረች እንደ ዛሬዪቱም የካቲት ዐሥራ ስድስት ቀን በጎልጎታ ቦታ ቁማ ወደ ልጅዋ እንዲህ ብላ ለመነች። "ልጄ ሆይ በእግዚአብሔር አባትህ በክርስቶስ ስምህ፤ ከአንተ ጋርም ህልው በሆነ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ አማፅንሃለሁ፤ ዓለም ሁሉ ሊሸከምህ የማይችል ሲሆን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በተሸከመችህ ማኅፀኔ አማፅንሃለሁ፤ ልጄ ሆይ ያለ ሕማም ያለ ድካም ከእኔ በመውጣትህ በመወለድህ በአሳደጉህ ጡቶቼ ከአንተ ጋር በተመላለሱ እግቼ አማፅንሃለሁ። በውስጡ በተኛህበት በረት፤ በተጠቀለልክበት ጨርቅ አማፅንሃለሁ፤ የምወድህ ልጄ ሆይ በልቡናዬ ያለውን ሁሉ ትፈጽም ዘንድ የልመናዬን ቃል ሰምተህ ወደእኔ ትመጣ ዘንድ ወዳንተ ፈጽሜ እማልድሃለሁ"። ❤ የብርሃን እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም እዲህ ብላ በጸለየች ጊዜ እንሆ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወረደ ከእርሱም ጋር አእላፋት መላእክት አሉ በዙሪያውም ሁነው ያመሰግኑታል። እርሱም "እናቴ ማርያም ሆይ ምን ላድርግልሽ" አላት እመቤታችንም ለተወዳጅ ልጅዋ እንዲህ ብላ መለሰችለት "ልጄ ወዳጄ ሆይ ጌታዬና ፈጣሪዬ አለኝታዬና መጠጊያዬ በእናቴ ማኅፀንም ሳለሁ በአንተ ጸናሁ አንተም ጠበቅኸኝ ሁልጊዜም ስም አጠራሬ አንተ ነህ። አሁንም ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ ቃሌንም አድምጥ እኔ እናትህ እኔ አገልጋይህ የምለምንህ ይህ ነው መታሰቢያዬን ለሚያደርጉ በስሜ አብያተ ክርስቲያን ለሚሠሩ ወይም የተራቆተውን ለሚያለብሱ የተራበውን ለሚያጠግቡ የተጠማውን ለሚያጠጡ የታመመውን ለሚጐበኙ ያዘነውን ለሚያረጋጉ፣ የተከዘዌንም ደስ ለሚያሰኙ ወይም ምስጋናዬን ለሚጽፉ፣ ልጆቹንም በስሜ ለሚሰይም፣ በበዓሌም ቀን በማኅሌት ለሚያመሰግን አቤቱ ዐይን ያላየው ጆሮ ያልሰማውን በሰውም ልቡና ያልታሰበውን በጎ ዋጋ ስጣቸው በአማላጅነቴም የሚታመን፡ ሁሉ ከሲኦል ነጻ አድርገው ከአንተ ጋር የደረሰብኜን ረኃብና ጥማቱን መከራውን ሁሉ አስብ አለችው"። ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ "እንደልሽው ይሁንልሽ የሰጠሁሽም ቃል ኪዳን እንዳይታበል በራሴ ማልኩሌሽ" አላት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን ድንግል ማርያም በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላላለሙ አሜን።                                                                                    ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅድስት_ኤልሳቤጥ፦ ይህች ቅድስት ከኢየሩሳሌም የሆነች የእናቱዋ ስም ቅድስት ሶፍያ ነው። እርሷም ከሌዊ ነገድ ከአሮን ወገን ለሆነ ለማጣት ልጅ ናት በዝምድና አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የእናቷ እኅት ልጅ ናት። ማጣት ሦስት ልጆችን ወለዷልና የታላቂቱም ስም ማርያም ነው እርሷም ወደ ግብጽ በተሰደደች ጊዜ እመቤታችንን ያገለገለች ሰሎሜን ወለቻት፣ ሁለተኛዋም ሶፍያ ናት እርሷም የዚች ቅድስት ኤልሳቤጥ እናቷ ናት፣ የታናሺቱም ስም ሐና ነው። እርሷም የከበረች ድንግል እመቤታችንን ማርያምን ወለጀቻት። ሰሎሜ ኤልሳቤጥ እመቤታችን ማርያም የእኅትማማች ልጆች ናቸው። ❤ ይችንም ቅድስት ኤልሳቤጥ ካህኑ ዘካርያስ አገባት የከበረ ወንጌልም ስለርሳቸው፡ ተናግሯልና እነርሱ ሁለቱም ያለ ነውር ያለ ነቀፋ በእግዚአብሔር ሕግ ጸንተው የሚኖሩ ዕውነተኞች ደጎች ሆኑ። ኤልሳቤጥም መካን ስለሆነች ወደ እግዚአብሔር የሚለምኑና የሚሚማልዱ ሆኑ አርጅተውም የመውለጃቸው ዘመን በአለፈ ጊዜ እግዚአብሔር መልአኩን ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ዘካርያስ ልኮ ጸሎታቸው ልመናቸው እንደ ተሰማ ስለ ዮሐንስ መወለድና ከእርሱ ስሚሆነው አስረዳው።

ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ዐቢይ ጾምን አገልግሎትን አስመልክተው ለገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች መመሪያ አስተላለፉ። ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ
+5
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ዐቢይ ጾምን አገልግሎትን አስመልክተው ለገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች መመሪያ አስተላለፉ። ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ዐቢይ ጾምን አስመልክተው ለገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች መመሪያ አስተላለፉ። በትናትናው ዕለት በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ በተከናወነው መርሐ ግብር ብፁዕነታቸው ጾሙ በረከት የምናገኝበት ታላቅ ሕይወት ጾም በመሆኑ የቤተ መቅደሱና የዐውደ ምሕረቱ አገልግሎት  ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ በመልኩ በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል አሳስበዋውል። በተለይም ቅዳሴ ሰዓት እንዲሁም የቅዱስ ወንጌል አገልግሎት በተመለከተ በትጋትና በጥንቃቄ እንዲከናወን አዳራ ብለዋል። በመርሐ ግብሩ ላይ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የሀገረ ስብከቱ ዋና ክፍል ሐላፊዎች፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ሌሎች የአገልግሎት መሪዎች ተገኝተዋል።

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤ ❤ እንኳን #ለዐቢይ_ጾም_ሁለተኛ_ሳምንት_ለቅድስት እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዚህ_ሳምንት_የቅድስት_መዝሙር፦  ሃሌ ሉያ ፭ "#ግነዩ_ለእግዚአብሔር_ወጸውዑ_ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ ሀቡ ስብሐተ ለስሙ #አክብሩ_ሰንበተ ተገበሩ ድድቀ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት ኀበ ፃፄ ኢያማስኖ ወኢይረክቦ ሰራቂ #ድልዋኒክሙ_ንበሩ ዘበላዕሉ ሀልዩ ኀበ ሀሎ #ክርስቶስ። ትርጉም፦ #ለእግዚአብሔር_ተገዙ ስሙንም ጥሩ ሥራውንም ለአሕዛብ ንገሯቸው፤ ለስሙም ምስጋናን ስጡ (አቅርቡ) #ሰንበትን_አክብሩ፤ እውነትንም አድርጉ፤ ብል የማያበላሸው ሌባም የማያገኘው በሰማያት ያለ መዝገብን ለእናንተ ሰብስቡ፤ #ተዘጋጅታችሁም_ተቀመጡ፤ #ክርስቶስ_ወዳለበት ወደ ላይ አስቡ። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በጾመ_ድጓ ላይ።                      ✝ ✝ ✝                     ❤ ቅድስት፦ ❤ የዐቢይየዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሣምንት ቅድስት ይባላል።  የተቀደሰች፣ የተባረከች፣ ንጽሕት ማለት ነው። ❤ ለምን ቅድስት ተባለ?፦ "ጾምን ቀድሱ ጉባኤውን አውጁ  ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤተ ሰብስቡ"፡፡ ት.ኢዩ 1፥14 ብሎ በነቢዩ ኢዮኤል አፍ የተናገረ ቅዱስ እግዚአብሔር የጾማት ጾም ስለሆነች (የጌታችን ጾም ከቅድስት ጀምሮ በመሆኑ) ቅድስት ትባላለች። ❤ እንዲሁም የዲያብሎስን ፈተና ድል ለመንሳት በቅድስት ከተማ በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ጫፍ የቆመባት ዕለት በመሆኗ ማቴ 4፥5 ዮሐ 10፥22-23 ሰው ሁሉ ጾምን ጾሞ እንደ ፈጣሪው ፈተናን ድል ነሥቶ ቅድስና እና ክብርን ያገኛልና ቅድስት ተብላለች። ❤ ቅድስት ዕለተ ሰንበት፦ "እግዚአብሔር ሰባተኛይቱን ቀን ባረካት ቀደሳት" ዘፍ 2÷3፣ ዘጸ 20፥8 ሰዎች ፍጥረት ያልተፈጠረባት ዕለት ብለው እንዳይንቋት እንዳያቃልሏት ዕረፍተ ሥጋ ዕረፈተ ነፍስ የተገኘባት ዕለት ስለሆነች ቀደሳት አለ፡፡ ቅዱስ ያሬድም "ሰንበትየ ቅድስትየ ዕንተ አዕረፍኩ እምኩሉ ግብርየ ይቤ እግዚኣብሔር " ብሉአል። በዚህ እሁድ (ሳምንት ) ቀደሳት፣ አከበራት፣ ከፍ ከፍ አደረጋት :- የተባለች ሰንበትን የምትታሰብበት የሰንበትንም ቅድስና የሚመለከቱ መዝሙሮች የሚቀርብበት ሳምንት በመሆኑ ቅድስት ተብሏል። ምንጭ፦ ከአምኃ ሥላሴ ፔጅ የተወሰደ።                                                         ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ። አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ። ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ"። መዝ 95፥5-6። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛተሰሎ 4፥1-13፣ 1ኛ ጴጥ.1÷13-ፍም እና የሐዋ ሥራ 10፥17-30። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 6፥16-25። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ኤጲፋንዮስ ቅዳሴ ነው። ዕለት ሰንበት (ቅድስት)ና የጾም ወራት። ለሁላችንም ይሁንልን።                 

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #የካቲት ፲፭ (15) ቀን። ❤ እንኳን #ከዐሥራ_ሁለቱ_ደቂቀ_ነቢያት ለአንዱ ለታላቁ ለእውነተኛው ነቢይ #ለቅዱስ_ዘካርያስ ለዕረፍት በዓል፣ በገድል ተጠምዶ ለኖረ የገዳማውያን አባቶችን ገድል ለመጻፍ ብዙ ለደከመ (በበረሀ ውስጥ በመግባቱ ከርኃብ የተነሣ ሥቃይ ደርሶበታል ያለምግብ ሦስት ቀን ከቆየ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦለት ሰውነቱን ሁሉ አፉንም ለሠሠው ያለ ምግብም ዐሥራ ሰባት ቀን ለኖረ) ስለእነርሱም ብዙ ምሥጢራትን ላወቀ #ለአባ_በፍኑትዮስ ለዕረፍት በዓልና ስብስጥያ በምትባል አገር የሰማዕታት #አርባ_ሐራ_ሰማይ_ቤተ_ክርስቲያናቸው_ለከበረችበት እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #ነቢዩ_ቅዱስ_ዘካርያስ፦ እርሱም ከሌዊ ነገድ ነው የአባቱም ስም በራክዩ ነው በገለዓድም ወለደው በባቢሎን ምርኮ ጊዜ ተማረከ ከዚያ ሳለም በላዩ የወረደለትን መለኮታዊ ትንቢትን ተናገረ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ አንደበት ጠቃሚዎች የሆኑ ብዙ ቃሎችን ተናገረ። ለኢዮሴዴቅም እንዲህ ብሎ ትንቢትን ተናገረ "በኢየሩሳሌም እግዚአብሔር ን ካህን ሁኖ የሚያገለግል ልጅ ትወልዳለህ" ከሚጠትም በኋላ እንደቃሉ ሆነ። ለሰላትያልም ትንቢት ተናገረለት ባረከውም "ወንድ ልጅ ትወልዳለህ ስሙንም ዘሩባቤል ትለዋልህ እርሱም በኢየሩሳሌም መቅደስን ይሠራል" አለው ዳግመኛም ለፋርስ ንጉሥ ተናገረ የድል ምልክትንም ገለጠለት። ❤ ጌታችን በውርጫዪቱና በታላቂቱ አህያ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ስለ መምጣቱ ተናገረ። ይሁዳም መድኃኒታችንን ክርስቶስን አሳልፎ በመስጠቱ ስለ ተቀበለው ሠላሳ ብር ትንቢት ተናገረ። መድኃኒታችንም በሚሰቀልበት ዐርብ ሌሊት ስለ ሐዋርያት መበተን ተናገረ። በቀትር ጊዜም ስለ ፀሓይ መጨለም ተናገረ። ስለ እስራኤል ልጆች ኀዘንም እንዲህ አለ "ያን ጊዜ የወጉትን ያዩት ዘንድ አላቸው ወደ ኀዘንም ይመለሳሉ እንደ ሚወዱትም ያለቅሱለታል ሰው ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን ጽኑ ኀዘንን ያዝናሉ"። የትንቢቱም ወራት በተፈጸመ ጊዜ የካቲት15 በሰላም ዐረፈ በነቢያት መቃብርም ተቀበረ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በነቢዩ በቅዱስ ዘካርያስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱ ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_በፍኑትዮስ፦ ይህም አባት ከታናሽነቱ መንኵሶ በጾምና በጸሎት በስግደትም እየተጋ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ። ያማረ ምንኵስናውን ሥራ ፈጸመ ጊዜ መነኰሳት ከሚኖሩበት ገዳማት ርቆ ወደሚገኝ። በርሀ ውስጥ ይገባ ዘንድ የከበሩ ገዳማውያንንም ይጐበኛቸው ዘንድ ለሚያነቧት ጥቅም ትሆን ዘንድ ገድላቸውንም እንዲጽፍ ልዑል እግዚአብሔር አዘዘው። በዚያንም ጊዜ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ራሱን ዘንበል አድርጎ ወደ ውስጠኛው በርሀ ገባ በመንደር ውስጥ እንደ ሚዞር ሰው በዱር መካከል ዞረ። ከገዳማውያንም ብዙዎችን አገኛቸውና ዜናቸውን ተረድቶ ገድላቸውን ጻፈ ከውስጣቸውም የከበሩ ገዳምውያን ጢሞቴዎስና አቡናፍር አሉ። ❤ ይህንንም አባት በፍኑትዮስ ወደ ውስጠኛው በርሀ በመግባቱ ከርኃብ የተነሣ ሥቃይ ደርሶበታል ያለምግብ ሦስት ቀን አድሮአል። ከዚያም በኋላ ተርቦ ለሞት ተቃረበ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ሰውነቱን ሁሉ አፉንም ዳሠሠው ያለ ምግብም ዐሥራ ሰባት ቀን ኖረ። ❤ ዳግመኛም ከቶ ሰው ሳያዩ ስድሳና ሰባ ዓመት ከዚያም የሚበዛ የሚያስደንቅ የገዳማውያንን ኑሮአቸውን ተናገረ ወደ ውስጠኛው በረሀ በሚገቡ ጊዜ እርሱን ስለሚወጓቸው ከርኵሳን መናፍስትና ከሚያስፈሩ አራዊት ስለሚደርስባቸውም ፈተና ተናገረ ከዚህም በኋላ በትዕግሥታቸው የሚገዙላቸው ይሆናሉ አራዊትም እንደ ባሮች ያገለግሏቸዋል ቅዱስ ቊርባንንም እንዴት እንደሚቀበሉ ደግሞ ተናገረ በዕለተ ሰንበት የመድኃኒታችንን ክርስቶስን ሥጋና ደም መላእክት አምጥተው ያቀብሏቸዋልና ከገነትም ፍራፍሬዎችን ይሰጧቸዋል። ለዚህም አባት ስለ እሊህ ድንቆች ሥራዎች አይቶ ምስክር ሊሆን የተገባው ሆነ ከዚያም በኋላ የካቲት15 በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ በፍኑትዮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #ስብስጥያ_በምትባል_አገር_የሰማዕታት #አርባ_ሐራ_ሰማይ_ቤተ_ክርስቲያናቸው_ተከበረች፦ ይህች ቤተ ክርስቲያን በስማቸው አስቀድማ ተሠራች ታላቁ አባት ባስልዮስም አከበራት ስለርሳቸውም ድርሳናትን ደረሰ የካቲት15 በዚችም ዕለት በዓልን አደረገላቸው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የካቲት 15 ስንክሳር።                               ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለዘካርያስ_ዘኮነ_ልዑለ_ቃል። በወራኀ ከሲል። ለቤተ ክርስቲያን ቅድስት ዘሐዋርያት መድብል። አምሳለ ተቅዋም ዘመኃቲዊሃ ጽዱል። ማዕከለ ክልኤ አዕፅቅ ርኢክዋ ይብል"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_15።                 

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #የካቲት ፲፬ (14) ቀን። ❤ እንኳን #ለታላቁ_አባት ሃይማኖታቸው ለቀና ምዕመናን መምህራቸው ለሆነ ለአንጾክያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ለከበረ አባት #ለአባ_ሳዊሮስ ለዕረፍቱ በዓል፣ ለእስክንድርያ ለኃምሳኛ ሊቀ ጳጳስ በጸሎቱ አንድ ሙት ላስነሳ ለከበረ አባት #ለአባ_ያዕቆብና ሰባ አምስተኛ ሊቀ ጳጳሳት ለከበረ አባት #ለአባ_ቄርሎስ ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከቅዱሳን_ከዳርዮስ፣ #ከጳውሎስ_ከአኩደራስና_ከሊድና ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                                               ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ሳዊሮስ_ዘአንጾኪያ፦ የዚህ ቅዱስ ዘመዶቹ ከሮሜ አገር ናቸው አባቱም ስሙ ሳዊሮስ የሚባል ኤጲስቆጶስ ነው። እርሱም ስለ ንስጥሮስ በኤፌሶን ከተማ ጉባኤ በሆነ ጊዜ ከሁለት መቶ አባቶች ኤጲስቆጶሳት ጋር መጣ በዚያም እንዲህ የሚለውን ራእይ አየ "ከአንተ የሚወለድ ልጅህ ስሙም እንደ ስምህ ሳዊሮስ ተብሎ የሚጠራ እርሱ ለቀናች ሃይማኖትን" ያጸናታል። ❤ ይህም ኤጲስቆጶስ በዐረፈ  ጊዜ ልጁን ሳዊሮስ ብለው ጠሩት ከቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆነውን ጥበብን ሁሉ ተማረ። ከመምህሩም ወጥቶ ወደ አንድ ቦታ ሲጓዝ በዋሻ ራሱን እሥረኛ አድርጎ የሚኖር ጻድቅ ሰው ተገናኘው በእርሱም ደስ ብሎት "የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሃይማኖታቸው ለቀና ምዕመናን መምህራቸው የሆንክ ሳዊሮስ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው" አለው። ሳዊሮስም ከቶ ሳያውቀው በስሙ በጠራው ጊዜ የሚደረግለትንም ከመሆኑ አስቀድሞ በመናገሩ አደነቀ። ❤ ከዚህም በኋላ ሳዊሮስ ትሩፋት በመሥራት አደገ መልካም ስም አጠራሩና ዜናው ተሰማ በአባ ሮማኖስ ገዳም መንኵሶ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ በትሩፋትም ሥራ እጅግ የተጠመደ ሆነ የከበረ ወንጌል "በተራራ ላይ የተሠራች መንደር መሠወር አትችልም" እንዳለ ዜናው በሁሉ ዘንድ ተሰማ። የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳትም በዐረፈ ጊዜ አዋቂዎች ኤጲስቆጶሳት ይህን የከበረ ሳዊሮስን ይሾሙት ዘንድ ተስማምተው ያለ ውዴታው ወስደው በአንጾኪያ አገር ላይ ጵጵስና ሾሙት በሹመቱም እስከ ዓለም ዳርቻ ያለች ቤተ ክርስቲያን ብርሃን ሆነላት በአገሮች ሁሉ ወዳሉ መናፍቃን ከሀድያን ትምህርቱ በሚደርስ ጊዜ ሁለት አፍ እንዳለው ስለታም ሰይፍ ሥራቸውን ይበጥሳልና። ❤ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ አማኒ ንጉሥ ሙቶ በርሱ ፈንታ ስሙ ዮስጥያኖስ የሚባል መናፍቅ ነገሠ ንግሥቲቱ ሚስት ግን ሃይማኖቷ የቀና ነው ስማ ቴዎድራ ይባላል። ንጉሡም የኬልቄዶን ወደ ሆነች ወደረከሰች ሃይማኖቱ ይህን የከበረ አባት ያስገባው ዘንድ ያስፈራራው ነበር እርሱ ግን ፈርቶ አይትዘዝለትም ቊጣውንም የሚፈራ መስሎት በእርሱ ላይ አብዝቶ ተቆጣ ቊጣውንም ባልፈራ ጊዜ በሥው፡ ሊያስገድለው መከረ ንግሥቲቱም አውቃ ከንጉሡ ፊት ይሸሽ ዘንድ ሊቀ ጳጳሱን መከረችው እርሱም በሥውር ወጥቶ ገለል አለ። እግዚአብሔር የዚህን አባት ሞት አልፈቀደምና ስለ ምእመናንም ጥቅም ጠበቀው። በአንድ ተራ መነኵሴ አምሳል ሁኖ፡ በቦታዎችና በገዳማት የሚዘዋወርና ምእመናንን የሚያጠናክራቸው ሆነ ስካ በሚባል አገር ስሙ ዶርታኦስ ከሚባል ደግ ምእመን ባለ ጸጋ ሰው ዘንድ ተምጦ ሳለ ጌታችን በእጆቹ ብዙ ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ ስካ በተባለ አገር እስከ ዐረፈ ድረስ በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ ሁሉንም ያስተምራቸው ነበር ከዚህም በኋላ ወደ ዝጋግ ገዳም አፈለሱት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ሳዊሮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ቄርሎስ፦ ይህም አባት ፍዩም ከምትባል አገር ነው። በእርሷም ቅስና ተሹሞ ኖረ ከዚህም በኋላ ከዚያ፡ ለቆ ከምስር ከተማ ውጭ ወደ ሆነች የኢትዮጵያውያን የጒድጓድ ውኃ ወዳለበት ወደ ቅዱስ ፊቅጦር ገዳም ደረሰ በውስጡም ታላቅ ተጋድሎን እነተጋደለ ብዙ ዘመናትን ኖረ። ❤ የዕውቀቱና የቅድስናው ዜና በተሰማ ጊዜ ያለ ውዴታው ይዘው በእስክድርያ አገር ሊቀ ጵጵስና ሾሙት መንጋውንም በበጎ አጠባበቅ ጠበቀ በቊርባንና በጸሎት ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊሠሩት የሚገባቸውን ለካህናት ሦርዓትን ሠራ። በሹመቱም ሰባት ዓመት ከዘጠኝ ወር ከሃያ ሰባት ቀን ኑሮ የካቲት14 በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #አባ_ያዕቆብ፦ ይህም አባት እልመቱዝ ለተባለ የግብጽ ንጉሥ በነገሠ በ17 ዓመት ተሾመ እርሱም ለመኰንኑ ለወልደ ኀሮን ረሽድ ወንድም የሆነ ነው፡ በዚህም አባት ዘመን የአስቄጥስ ገዳማት ታድሰው መነኰሳቱ ወደሳቸው ተመለሱ። ❤ አፎን በሚባል አገር ስሙ መቃርስ የሚባል ሰው ነበር ወደዚህ አባት ወደ ያዕቆብ መጥቶ ወደቤቱ በመሔድ ቤቱን ይባርክለት ዘንድ ለመነው እርሱም አብሮት ሔደ ታሞ የነበረ ልጁም ሞተ ወደ አባ ያዕቆብ አቅርቦ እንዲህ ብሎ ለመነው "ከርሱ በቀር ልጅ የለኝምና አባቴ ሆይ ራራልኝ እርሱም እነሆ ሞተ ስርሱ፡ ወደ እግዚአብሔር ትማልድ ዘንድ እለምንሃለው" አለው። አባ ያዕቆብም "እንደ እምነትህ ይሁንልህ አትፍራ" አለው። ሕፃኑንም ከአባቱ ተቀብሎ ታቀፈውና በላዩ ጸለየ በመስቀል ምልክትም አማተበበት ስለርሱም ወደ እግዚአብሔር ለመነ ጌታችንም ልመናውን ተቀበለው የሕፃኑ ነፍስ ተመልሳ ዐይኖቹን ገለጠ ከሞትም ድኖ ተነሣ አባቱንም "ልጅህን ውሰድ የሞተ አይደለም ያንቀላፋ ሁን ነው እንጂ" አለው። የሕፃኑም አባት ይህን ድንቅ ሥራ በአየ ጊዜ እጅግ ፈራ የገንዘቡንም እኩሌታ ለምጽዋት ብሎ ሰጠው እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ልኮ ሃይማኖታቸው ለቀና ምእመናን ሁሉ ወደርሷ በመጡ ጊዜ መጠጊያ ይሆን ዘንድ ቤተ ክርስቲያንን ሠራበት። ❤ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ዲዮናስዮስም ወደ ምስር በመጣ ጊዜ ከአባ ያዕቆብ ጋር ተቀምጦ ወደ አገሩ ተመለሰ። ይህ አባት ያዕቆብ በሹመቱ ዐሥር ዓመት ከስምት ወር፡ ከሦስት ቀን ኑሮ የካቲት14 በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ያዕቆብ በጸሎቱ ይማረን በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት 14 ስንክሳር።                              ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለያዕቆብ_ለእግዚአብሔር_ቅዱሱ። ዘአድባረ ገዳም ኵሉ በመዋዕሊሁ ተሐደሱ። እስከ አቡሁ ገነየ ለብዕለ ጸጋሁ ወዕበየ ሞገሱ። በግሠተ እዱ ወበጽላሎታ ለእርሱ። ውስተ በድነ ሕፃን ገብአት ዘወጽአት መንፈሱ። #ሊቁ_አርከ¶ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_14።                                                          ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "አሕፃከ ስሑል ኃያል። አሕዛብ ይወድቁ ታሕቴከ። ውስተ ልቦሙ ለጸላዕተ ንጉሥ"። መዝ 44፥5። የሚነበቡት መልዕክታት ቲቶ 1፥7-12፣ 1ኛ ዮሐ 2፥20-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 20፥28-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 18፥15-23። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ቄርሎስ ቅዳሴ ነው። መልካም የአቡነ ሳዊሮስ የዕረፍት በዓልና የጾም ወራት። ለሁላችንም ይሁንልን።               

❤ እንዲህም ሆነ ከሕዝቡ ውስጥ አንድ ታናሽ ሕፃን እግዚአብሔር ዐይኖቹን ገልጦለት የቅዱሳን ሰማዕታትን ነፍሶቻቸውን መላእክት ወደ ሰማያት ሲያወጧቸው አይቶ "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ይቅር በለኝ" እያለ በከፍተኛ ቃል ጮኸ እናትና አባቱም መኰንኑ ሰምቶ ስርሱ እንዳያጠፋቸው አፋን የሚዘጉ ሆኑ እርሱ ግን እንዲህ እያለ መጮኹን አልተወም በላዩ እስከ ተኙበትና ነፍሱን እስከ አሳለፈ ድረስ ከሰማዕታትም ጋር የምስክርነት አክሊልን ተቀበለ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕታት በጸሎቱ ይማረን በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት13 ስንክሳር።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የእስክንድርያ_አገር_ሊቀ_ጳጳሳት_አባ_ጢሞቴዎስ፦ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳ ሁለተኛ ነው። ይህንንም አባት ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ መከራና ችግር ደርሶበታል ። እንዲህም ሆነ በዚያ ወራት የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሳዊሮስ ወደ ግብጽ አገር መጣ እርሱም ከዚህ አባት ጢሞቴዎስ ጋር ምእመናንን እያጽናና ከሀገር ወደ ሀገር ከገዳም ወደ ገዳም ከቦታ ወደ ቦታ የሚዘዋወር ሆነ። ❤ በዚህም አባት ጢሞቴዎስ ዘመን ከቊስጥንጥንያ የመጡ ክፉዎች ሰዎች በግብጽ አገር ተገለጡ እነርሱም የክርስቶስን ተዋሕዶ ምትሐት በሚያደርግ መከራውንና ትንሣኤውንም በሚክድ በረከሰ በአውጣኪ ትምህርት የሚያምኑ ናቸው ይህም አባት አውግዞ ከግብጽ አገር አሳደዳቸው። ❤ ዳግመኛም በዘመኑ ምእመን ንጉሥ አንስጣስዮስ አረፈና በርሱ ፈንታ ኬልቄዶናዊ መናፍቅ ዮስጣትያኖስ ነገሠ እርሱም በአባ ጢሞቴዎስ ፈንታ ሊናርዮስን ሊቀ ጵጵስና ሾመው ሃይማኖታቸው የቀና ምእመናንን ሁሉ በኬልቄዶን ግባኤ ወደተወሰነ ሃይማኖት ሊመልሳቸው ወዶ በቅስጥንጥኒያ ጉባኤ ሰብስቦ የአንጾኪያውን ሊቀ ጳጳሳት አባ ሳዊሮስን ከኤጲስቆጶሳቶቹ ጋር አስመጣው። ❤ በኬልቄዶን ጉባኤ በተወሰነች በተበላሸች ሃይማኖቱ ያምኑ ዘንድ አስገደዳቸው እነርሱ ግን አልተቀበሉትም ትእዛዙንም አልሰሙም ስለዚህም ሃይማኖታቸው በቀና ምእመናን ሁሉ ታላቅ መከራ አደረሰባቸው። ❤ ይህም አባት ጢሞቴዎስ በመንበረ ሢመቱ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኑሮ በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ  ጢሞቴዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን።                           ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_እብል_ጢሞቴዎስሃ_ሰባኬ። ወሊቀ ጳጳሳት ዝኬ። ዘበመዋዕሊሁ ተውህበ ለመሃይምናን ቡራኬ። ወውዕዩ በነደ ቃሉ ከመ አገዳ ሐመል ወመሎኬ። እለ ተአመኑ በትምህርቱ ለዕልው አውጣኬ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_13።                         ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦"አይቴኑ አሐውር እመንፈስ። ወአይቴ እጐይይ እምቅድመ ገጽከ። እመኒ ዐረጉ ውስተ ሰማይ ህየኒ አንተ"። መዝ 138፥7-8። የሚነበቡት መልክታት 2ኛ ቆሮ 12፥1-11፣ 1ኛ ጴጥ 1፥6-10 እና የሐዋ ሥራ 15፥22-36። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥27-33። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ፡ነው። መልካም በዓልና የጾም ወራት በሁላችንም ይሁንልን።

❤ በአንዲት ዕለት የሶርያው ንጉሥ ሚስት ቅዱስ አውሳብዮስን አይታው እጅግ ወደደችው፡፡ ከባሮቿም ውስጥ ሁለቱን ልካ ካስመጣችው በኋላ በወርቅ አጊጣ በሐር በተነጠፈ አልጋ ላይ ሆና ጠበቀችው፡፡ከእርሷም ጋር እንዲተኛ ስትጠይቀው "እኔስ ሚስቴንም እንኳን በግብር ያላወኩ ነኝና ተይኝ ንጉሡ ባልሽ በቤት ባይኖር ሰውም ባያየን እግዚአብሔር ግን ያየናልና እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት እሠራለሁ? "በማለት ትቷት ሊወጣ ሲል ልብሱን ያዘችው፡፡ እርሱም ሮጦ በማምለጥ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ እርሷ ግን በመጮህ ባሮቿ ሲመጡላት" ክፉ ነገርን አድርጎብኝ ሄደ" ብላ በሐሰት ተናገረች፡፡ ጭፍሮቿም ቅዱስ አውሳብዮስን ከቤተ ክርስቲያን አውጥተው እየደበደቡ ወደ ንግሥቲቱ አመጡት፡፡ እጆቹንና እግሮቹንም አሥረው ከከተማ ውጭ በአራት ዕንጨቶች ላይ አሰቀለችው፡፡ ከባሮቿም ውስጥ አንዲቱ በንግሥቲቱ ተልካ ሄዳ አውሳብዮስን "ከተሰቀልክበት እንዲታወርድህ ለእመቤቴ ያለችህን እሺ በላት" አለችው፡፡ እርሱም "የአመንዝራን ቃል አልሰማም" አላት፡፡ ንግሥቲቱም እሺ እንዳላላት ስታውቅ አንገቱን በገመድ አሳንቃ 160 ፍላጻዎችን በሰውነቱ ውስጥ እንዲጭምሩበት አደረገች፡፡ጌታችንም ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን ልኮለት ፍላጻዎቹን ከሰውነቱ ውስጥ አወጡለትና ፍጹም ጤነኛ ሆነ፡፡ ንጉሡም ከሄደበት ሲመለስ ንግሥት ሚስቱን አውሳብዮስን ለስቅላትና ለሞት ያበቃችው በምን ምክንያት እንደሆነ ሲጠይቃት አንተ በሌለህበት ወደ መኝታ ቤቴ ገብቶ ሊናገሩት የማይገባ ነገር ጠየቀኝ በከለከልኩትም ጊዜ በሥራዩ አሳመመኝ" አለችው፡፡ንጉሡም ተቆጥቶ ቅዱስ አውሳብዮስን ከተሰቀለበት አስወርዶ ካስመጣው በኋላ ለምን ይህን እንዳደረገ ጠየቀው፡፡ አውሳብዮስም እውነቱን በነገረው ጊዜ ጭፍሮቹን ምስክር ይሆኑ ዘንድ ሲጠይቃቸው ንግሥቲቱ ስትጮህ ወደ ውስጥ ሲገቡ ያጋጠማቸውን መሰከሩ፡፡ ንጉሡም የሚስቱን ነገር አምኖ በመቀበል በንዴት የቅዱስ አውሳብዮስን ሰውነቱን በሰይፍ አስቆርጦ ሥጋውን እንደ ላም ሥጋ ቆራርጦ በምንቸት አድርጎ በእሳት እንዲበስል አደረገው፡፡ ነገር ግን አሁንም ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ከምቸቱ አውጥተው ከሞትም አድነው በማስነሣት ፍጹም ጤነኛ አደርገው አቆሙት፡፡ ❤ ከሞት ከተነሣም በኋላ በአገሩ ውስጥ ሲሄድ ሰዎች አይተውት ለንጉሡ ስለነገሩት ንጉሡ ድጋሚ ካስመጣው በኋላ አራት ዛንጅሮች በአካላቶቹ ውስጥ በማስገባት እጅና እግሩን አሳስሮ በእሳት ውስጥ ጨመረው፡፡ የከበሩ ሁለቱ ቅዱሳን መላእክት አሁንም መጥተው ፈወሱት፡፡ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤልም ነጥቆ ወደ ሰማይ አሳርጎት በዚያው በሰማይ 14ዓመት ኖረ፡፡ ከዚያም ወደ ምድር ተመልሶ መጥቶ ወንጌልን እያስተማረ 40 ዓመት ኖረ፡፡ በእርሱም ትምህርት 85ሺህ አረማውያን አምነው ተጠምቀዋል፡፡ ቅዱስ አውሳብዮስ በመጨረሻ ሰማዕትነቱንና ተጋድሎውን ፈጽሞ የካቲት13 ቀን በክብር ዐርፏል፡፡ጌታችንን፡ኢየሱስም ስሙ ለሚጠራ መታሰቢያውንም ለሚያደርግ እስከ ሰባት ትውልድ ሊምርለት ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አውሳብዮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_ሰርግዮስ፦ የዚህ ቅዱስ አባቱና እናቱ ደጎች ናቸው። የአባቱ ስም ቴዎድሮስ የእናቱም ስም ማርያም ነው። ዕድሜውም ሃያ ዓመት ሲሆነው በክብር ባለቤት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይሞት ዘንድ አሰበ ወደ መኰንኑ ቆጵርያኖስም ቀርቦ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመነ መኰንኑም ጽኑ ሥቃይን ያሠቃዩት ዘንድ ያሥሩትም ዘንድ አዘዘ ጌታችንም ነፍሱን ወደ ሰማይ አምጥቀው የቅዱሳን ሰማዕታትን መኖርያ ያሳዩዋት ዘንድ አዘዘ አይታም ተጽናናች ከሥቃይ ከሕማሙም ፈወሰው። ❤ ቀሲስ አባ መጹንና ሁለት ዲያቆናትም ተጋድሎውን ሰሙ ያን ጊዜም ተነሥተው ወደ አትሪብ አገር ገዥ ቀርበው በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ የጸና ግርፈትም ይገርፋቸው ዘንድ አዘዘ እንዲሁም አደረጉባቸው። ሕዝቡም ሁሉ በዙርያቸው ሁነው ይመለከቷቸው ነበር ስለ ቄሱና ከእርሱ ጋር ስላሉትም አዘኑ ቄሱ ግን ፊቱን ወጀርሳቸው መልሶ ገሠጻቸው አስተማራቸውም "በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ በቀናች ሃይማኖት እንዲህ ጽኑ" አላቸው ከዚህም በኋላ በውኋ ላይ ጸልዮ በላያቸው ረጨ በዚያንም ጊዜ በላያቸው ወርዶአልና የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀበለው በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ ራሶቻቸውንም በሰይፍ ቆረጧቸው የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ። ከዚያም በኋላ ቄሱን ከውሽባ ቤት ማንደጃ ውስጥ ይጨምሩት ዘንድ መኰንኑ አዘዘ እግዚአብሔርም ከእሳት አዳነው። ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ተገለጠለትና እርሱ ስለ ክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም ሦስት ጊዜ ምስክር እንደሚሆን አሰረዳው ከእሳት ማንደጃው ውስጥም አወጣው። መኰንኑም ወደ እስክድርያ አገር ላከው ተጋድሎውንና ምስክርነቱን በዚያ ፈጸመ የምስክርኘቱን አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ። ❤ ከዚያም በኋላ መኰንኑ ቆጵርያኖስ የከበረ ሰርግዮስን ያቀርቡት ዘንድ አዘዘ ታላቅ ሥቃይንም አሠቃየው የነሐስ መንኰራኵሮችንም አምጥተው ከውስጣቸው አስገብተው አበራዩት ሕዋሳቱም አራት ክፍል ሁኖ ሥጋው ሁሉ ተቆራረጠ ጌታችንም አድኖ ያለ ጉዳት በጤና አስነሣው። ዳግመኛም እንዲሰግድለት ጣዖትን አመጡ ቅዱሱ ግን ሲረግጠው ወድቆ ተቀጥቅጦ ደቀቀ መኰንን ቆጵርያኖስም አይቶ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመነ "አምላክ ቢሆን ራሱን ማዳን በቻለ ነበር" አለ። ❤ ከዚህም በኋላ የጭፍራ አለቃ ስሙ አውህዮስ የሚባል የከበረ ሰርግዮስን ፈልጎ ያዘው ቆዳውንም ገፈው በተቀላቀለ ኮምጣጤና ጨው ቊስሉን ያሹት ዘንድ አዘዘ ጌታችን ግን በሥቃዮች ላይ ያጸናውና ያበረታው፡ ነበር። እናቱና እኅቱም ሰምተው ወደርሱ መጡ በአዩትም ጊዜ በላዩ አለቀሱ ከኀዘንም ብዛት እኅቱ ነፍሷን አሳለፈች የከበረ ሰርግዮስም ስለ እኅቱ ወደ ጌታችን ጸለየ ከሞትም ድና በሕይወት ተነሣች። ያን ጊዜ የሰማዕታትን ገድል የሚጽፍ የአቅፋስ፡አገር ሰው የከበረ ዮልዮስ መጣ ገድሉንም ሁሉ ከእርሱ ተረዳ ለሥጋውም እንደሚያስብ ቃል ገባለት። ❤ ከዚህም በኋላ ደግሞ የከበረ ሰርግዮስን በመንኰራኵር ውስጥ ያሠቃዮት ዘንድ በጆሮዎቹ የእሳት መብራቶችን እንዲጨምሩ የእጆቹንና የእግሮቹን ጥፍሮች እንዲነቅሉ በአንገቱም ከባድ ደንጊያ አንጠልጥለው ከብረት ዐልጋ ላይ አስተኝተው ከበታቹ እሳትን እንዲያነዱ አውህዮስ አዘዘ እንዳዘዘውም አደረጉበት ጌታችን ኢየሱስ ያጸናውና ያለ ጥፋት በጤና ያስነሣው ነበር። የሠራዊት አለቃ አውህዮስም ማሠቃየቱን በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ፡አዘዘ የከበረ ሰርግዮስ ሰምቶ እጅግ ደስ አለው ወደ አባቱና ወደ እናቱ ወደ ወንድሞቹም ላከ ዘመዶቹ ሁሉም የእርሱ የሆኑ ሰዎችም መጡ በአፋም ልጓም ለጒመው ቸብቸቦውን ወደሚቆርጡበት ሲስቡት አገኙትና መኰንኑን የረከሱ ጣዖታቱንም ረገሙ መኰንኑም ከከበረ ሰርግዮስ ጋር ሁሉንም ቸብቸቧቸውን እንዲቆርጡ አዘዘ በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።