የቡራዩ ደ/ሰላም መድኃኔዓለም ካቴድራል ፍኖተ ሰላም ሰንበት ት/ቤት
الذهاب إلى القناة على Telegram
ይህ ገፅ የቡራዩ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ካቴድራል ፍኖተ ሰላም ሰንበት ትምህርት ቤት መልዕክቶችን ዘመኑ በሚፈቅደው መንገድ እንዲተላለፍበት በህዝብ ግንኙነት ክፍል የሚመራ ይፋዊ ገጽ ነው። 📞+251944247165 ሀሳብ አስተያየት ካሎት @finoteselam27PR በinbox አድራሻችን ያድረሱን።
إظهار المزيد1 638
المشتركون
+324 ساعات
لا توجد بيانات7 أيام
-530 أيام
أرشيف المشاركات
#ፍኖት_ከሰሞኑ_በረከት
ሰኔ 12 የቅዱስ_ሚካኤል ዓመታዊ በዓል!
እንኳን ለመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለእናታችን ቅድስት አፎሚያ አመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ። ሰኔ 12 ቅዱስ ሚካኤል እናታችን ቅድስት አፎሚያን ከጠላት ዲያብሎስ እጅ ያዳነበት ፣ እናታችን ቅድስት አፎሚያ እረፍቷ ነው ።እግዚአብሔር ከቅዱሱ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ፣ ከእናታችን ቅድስት አፎሚያ በረከት ተካፋይ ያድርገን ።
👉 በወርኃ ሠኔ መታሰቢያ ከሚደረግላቸው ቅዱሳን መካከል እግዚአብሔርን የሚፈራ የአስተራኒቆስ ሚስት የሆነች የቅድስት አፎምያን ታሪክ በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡
ቅድስት አፎምያ በትዳር በነበረችባቸው ዘመናት እግዚአብሔርን ከሚወድ ባለቤቷ ጋር እግዚአብሔርን ስታገለግለው የኖረች ሴት ነበረች፡፡ በየወሩ በ29 ቀን የጌታችንን የልደቱን፣ ወር በገባ በ21 የእመቤታችንንና ወር በገባ በ12 የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያደረጉ ነዳያንን ይጎበኙ እንደነበር ታሪካቸው ይነግረናል፡፡
ባለቤቷ አስተራኒቆስ ከዚህ ዓለም የሚያርፍበት ጊዜ እንደደረሰ ባወቀ ጊዜ ይሰጡት የነበረውን ምጽዋት እና የሦስቱን በዓላት መታሰቢያ ማድረግ እንዳታስታጉል ከአደራ ጋር አዘዛት፡፡ እሷም የመልአኩን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ያሥልላት ዘንድ ባለቤቷን ጠይቃ አሠርቶ ሰጣት፡፡ በከበረ ቦታም አኖረችው፡፡
ባሏ ካረፈ በኋላ ያዘዛትን መንፈሳዊ ሥራ ከወትሮው አስበልጣ መሥራት ቀጠለች፡፡ የሰው ልጆች ጠላት የሆነው ሰይጣንም በመልካም አገልግሎት ስትበረታ ባያት ጊዜ ዝም ብሎ ሊተዋት አልወደደም፡፡ በመጀመሪያ ባል ሳታገባ ማገልገሏን ትታ፣ ሌላ ባል አግብታ፣ ልጅ ወልዳ እንድትኖር በብዙ ማባበል ጠየቃት፡፡ ባሏ መንግሥተ ሰማያትን ስለወረሰ ምንም ምጽዋት እንደማይሻ አስመስሎ ነገራት፡፡
ቅድስት አፎምያ ግን ዳግመኛ ትዳር ላለመመሥረት ቃል ኪዳን እንደገባች ርግብንና ዖፈ መንጢጥን አብነት አድርጋ፤ እነሱ እንኳ በሕይወት ዘመናቸው ከአንድ ባል ውጪ ሌላ ባል እንደማያውቁ በመጥቀስ አሳቡን እንደማትቀበለው ገለጸችለት፡፡ ሰይጣንም አስመሳይ መሆኑ አላዋጣ ሲለው ማንነቱን ቀይሮ ሊያንቃት ቢሞክር የእግዚአብሔርንና የቅዱስ ሚካኤልን ስም ጠርታ አባረረችው፡፡ እሱም ተመልሶ መጥቶ እንደሚያጠፋት ዝቶባት እንደአቧራ በኖ፤ እንደ ጢስም ተኖ ጠፋ፡፡
በሠኔ ፲፪ ቀን የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያዘጋጀች ሳለች ሰይጣን ብርሃናዊ መልአክ መስሎ መጣ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ገልጾ የመጀመሪያውን የመሰለ ከንቱ ምክሩን አሰማምሮ አቀረበላት፡፡ አሳቡንም የእግዚአብሔር ፈቃድና አሳብ እንደሆነ አድርጎ ለማሳመን ሞከረ፡፡ ሰይጣን አስቀድሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በገዳመ ቆሮንቶስ መጻሕፍትን እየጠቀሰ እንደተፈታተነው ሁሉ ቅድስት አፎምያንም ለማሳመንም አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን፣ ዳዊትን የመሳሰሉ ደጋግ አባቶችን ታሪክ እየጠቀሰ ወደ ትዳር እንድትገባ ደጋግሞ ወተወታት፡፡
ቅድስት አፎምያም በእግዚአብሔር ኃይል ጸንታ በቅዱስ ሚካኤልም ተራዳኢነት ታምና “የእግዚአብሔር መልአክ ከሆንክ መንፈሳዊ ማረጋገጫህ የሆነው የመስቀል ምልክት የታለ?” በማለት በምድራዊ ንጉሥና በጭፍራው መካከል የሚኖርን የጋራ መግባቢያ መንገድ ዋቢ አድርጋ ጠየቀችው፡፡
ለጊዜው “በኛ በመላእክት ዘንድ እንዲህ አይደለም” ብሎ ሊሸነግላትና አቋሟን ሊያስቀይራት ሞከረ፡፡ ከቤቷ ያለ የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ላይ ያለውን ምልክት አብራርታ የእሱ ግን ከዛ ጋር አንድነት እንደሌለው አረጋገጠችበት፡፡ ከቤቷ ላለው ለቅዱስ ሚካኤል ሥዕል እጅ እንዲነሣ ጠየቀችው፡፡ በዚህ ጊዜ መልኩ ወደ ትክክለኛ ማንነቱ ተለወጠና ጨለማ ለብሶ እየዛተ አነቃት፡፡ ቅድስት አፎምያም የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልን “ድረስልኝ” እያለች በጠራችው ጊዜ መልአኩም ፈጥኖ በመድረስ ከሰይጣን እጅ አዳናት፡፡
የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ለሰይጣኑ ተገቢውን ቅጣት ሰጥቶ ቅድስት አፎምያን ባረካት፡፡ የዕረፍት ቀኗ በዚህ ቀን መሆኑን ነግሮ ቤቷን እንድታዘጋጅ አዘዛት፡፡ የበዓሉን ዝግጅት አከናውና ሥጋ ወደሙን ተቀብላ ኤጲስ ቆጶሱንና ካህናቱን እንደየመዓርጋቸው ጠርታ በቤቷ አክብራ ተቀበለቻቸው፡፡ ለነዳያንና ለጾም አዳሪዎች በኤጲስ ቆጶሱና በካህናቱ እጅ ገንዘቧን መጽውታ መንገዷን አሳመረች፡፡ ስለ ኃጢአቷ እንዲጸልዩላት ተማፅና በፊታቸው ተንበርክካ ጸለየች፡፡ ባሏ ያሠራላትን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል አቅፋ ስማ ከተማጸነች በኋላ ሠኔ ፲፪ ቀን በሰላም ዐረፈች፡፡
ይህች የታመነች ቅድስት አፎምያ በሰላም እስክታርፍ ጊዜ ድረስ የተጓዘችበትን መንፈሳዊ ጎዳና አስተውለን ይሆን? አስቀድማ ከባሏ ጋር አንድ ሆና በታማኝነት ፈጣሪዋን አገለገለችው፡፡ በኋላም የባሏን ኑዛዜ አክብራ ምንም እንኳን ኃጢአት ባይሆንባትም በሁለተኛ ትዳር ራስዋን ማጠላለፍ አልፈለገችም፡፡ በጎ ሥራ አብልጣ በመሥራት እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ተፋጠነች እንጂ፡፡
ሰይጣን ልጅ አለመውለዷን ተጠቅሞ ያቀረበላትን የጋብቻ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ “መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ መናፍስት ከእግዚአብሔር እንደሆኑ መርምሩ” ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት የታዘዘውን መመሪያ ተጠቅማ ሰይጣንን በተወክሎ እግዚአብሔር ተቃውማ አሸነፈችው፡፡ የቅዱስ ሚካኤልን ርዳታ ያገኘችውና በሰላም ዐርፋ ወዳገለገለችው እግዚአብሔር በክብር የሔደችው በጽናት ተጋድላ ነው፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በጸሎቷ ይማረን፤ የቅዱስ ሚካኤል የረድኤቱ ኃይል ሁላችንንም ይጠብቀን፣ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
_
ፍኖተ ሰላም ሚዲያ
"ምን አልባት እግዚአብሔር ፈተናዎቻችንን ያበዛብን በጣም እንድንጠራው ፈልጎ ይሆን?
በአፋችን ብቻ ሳይሆን ከልባችን በጣም እንድንቀርበው ፈልጎ ቢሆንስ.….. እግራችንንና አፋችንን ብቻ ሳይሆን ልባችንንም ወደ እግዚአብሔር እናቅርብ…!
እግዚአብሔርን ጠርቶና ቀርቦ ያፈረ የለምና!
እግዚአብሔርን ይዘን በትዕግስት ከጠበቅን እሩቁም ቅርብ ትልቁም እንደ ትንሽ ይሆናልና” መልካሙን ፍሬ ለማግኘት ሁሌም በትዕግስት እንጠብቅ፡፡"
#የመረጃ_ሰዓት
በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው የተመራ የቤተክርስቲያናችን ልዑክ አርሲ-አቦምሳ ወረዳ ተገኝቶ ምዕመናንን አጽናና ጊዜያዊ እርዳታም አበረከተ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በአርሲ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች የተከሰተውን ችግር ተከትሎ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው የሚመራ የቤተክርስቲያናችን ልዑክ በሥፍራው በመገኘት ተጎጂዎችን እንዲያጽናና ጊዜያዊ ርዳታም እንዲያደርግ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ዛሬ ማለዳ ወደ አርሲ ዞን አቦምሳ ወረዳ በመጓዝ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች አጽናንቷል፤ ጊዜያዊ እርዳታም አበርክቷል።
በአቦምሳ ወረዳ የትንሣኤ ብርሃን ደብረ ገነት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በመገኘት ተጎጂ ኦርቶዶክሳዊያንን ያጽናኑት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ቅድስት ቤተክርስቲያን በኦርቶዶክሳዊያን ልጆቿ ላይ በደረሰው ጉዳት እጅግ በጣም ማዘኗን ገልጸው እግዚአብሔር አምላክ ለሞቱት ወገኖቻችን መንግስተሰማያትን እንዲያወርስልን፣ለቤተሰቦቻቸው መጽናናት እንዲያድልልን የዘወትር ጸሎታችን ነው።በርቱ፣ጠንክሩ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን ብለዋል።
አያይዘውም ቋሚ ሲኖዶስ በአካል ተገኝቶ እናንተን ለማጽናናትና ጊዜያዊ ድጋፍ ለማድረግ በመካከላችሁ ተገኝተናል ያሉት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታትና የተቃጠለውን ቤተክርስቲያን ለመሥራት የሚያስቼል አቢይ ኮሚቴ በጠቅላይ ቤተክህነት ተሰይሞ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ቅድስት ቤተክርስቲያን በተከሰተው ችግር ጥልቅ ኃዘን የተሰማት መሆኑን ገልጸው ምዕመናን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፣በፈተና ሁሉ እንዲታገሱ አደራ ካሉ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ኃዘንተኞችን እንዲያጽናና ከዳግም ኃዘን እንዲሰውርልን ዘወትር እንጸልያለን በማለት ቃለ ምዕዳንና ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ለተፈናቀሉ ወገኖች የተዘጋጀውን ርዳታ ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ አስረክበዋል።በዚሁ ጊዜ የአቦምሳ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች ብፁዓን አባቶችን እንኳን ደህና መጣችሁልን በማለት በሀገሩ ባህል መሰረት የሰንጋ ስጦታ ካበረከቱ በኋላ የደረሰውን ጉዳት በመኮነን ሕዝቡ በስምምነት፣በአንድነትና በመቻል የኖረና ወደፊትም የሚኖር ሕዝበብ መሆኑን ጠቅሰው የተፈጠረውን ችግር ሃይማኖታዊ መልክ ለማስያዝ የሚደረገው ጥረት ተገቢነት የሌለው ነው ብለዋል።ለብፁዓን አባቶች የተበረከተው የሰንጋ ስጦታም ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲደርስ ተደርጎ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።
ምንጭ:- የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
_
ፍኖተ ሰላም ሚዲያ
ቋሚ ሲኖዶስ በምሥራቅ አርሲ የተጎዱ ወገኖችን የሚያጽናኑ በፁዓን አባቶችን መደበ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ተገኝተው ጉዳት የደረሰባቸውን ኦርቶዶክሳዊያን የሚያጽናኑ ብፁዓን አባቶችን መደበ።
የቋሚ ሲኖዶስ አባላት በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት በአሰኮ፣ በሺርካ፣ በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች በኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በዛሬው ዕለት ባካሔደው መደበኛ ስብሰባው በችግሩ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እንዲደረግ፣ በብፁዓን አባቶች የሚመራ የቤተ ክርስቲያናችን ልዑካን ቡድን ችግሩ ወደ ተፈጠረበት ቦታ በመሄድ ተጎጂዎችን እንዲጎበኝ፣ እንዲያጽናና እና አስፈላጊውን ጊዜያዊ ድጋፍ አንዲያደርግ ወስኗል።
ቋሚ ሲኖዶስ በጠቅላይ ቤተክህነት በኩል በሚቋቋም ኮሚቴ አስተባባሪነትም በተፈጠረው ችግር ምከንያት የመቃጠል አደጋ የደረሰበት ጥንታዊው የጠላታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን እንዲያሰራ፣ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በቋሚነት ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ፣ በሀገረ ስብከቱ ዳግመኛ መሰል ችግሮች እንዳይፈጠርሩ ጥናት አካሒዶ ከመፍትሔ ሐሳብ ጭምር የሚያቀርብ ዐቢይ ኮሚቴ ተሰይሞ በአስቸኳይ ወደ ሥራ እንዲገባ ወስኗል።
ምንጭ:- EOTC
_
ፍኖተ_ሰላም_ሚዲያ
#የመረጃ_ሰዓት
በአርሲ ሀገረ ስብከት በኦርቶዶክሳውያን ላይ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሰላም ሚኒስቴርና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተደረገ !
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት አንዳንድ ወረዳዎች በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት በኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ሕልፈተ ሕይወትና የቤተ ክርስቲያን መቃጠልን በማስመልከት የተሰማትን ጥልቅ ኀዘን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አማካኝነት ከገለጸች በኋላ ቋሚ ሲኖዶስ በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቅ ውይይት በማድረግ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተመራ ከፍተኛ የቤተክርስቲያናችን የልዑካን ቡድን ከሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ ፣ ከሚኒስትር ዲኤታው ከዶ/ር ኸይረዲን ተዘራና ከሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስና ብፁዕ አቡነ ዲዮስሮስ በምሥራቅ አርሲ በአሰኮ፣ በሺርካ፣ በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች በኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ላይ በደረሰው የሕይወት ጉዳት እና በጥንታዊው ቤተ ክርስቲያን መቃጠል እጅግ ማዘናቸውን ገልጸው መንግሥት የችግሩን ምንጭ አጣርቶ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልግና በአካባቢውም አስተማማኝ ሰላምን እንዲያሰፍን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
አያይዘውም በአሁኑ ወቅት በችግሩ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበትና መልሰው የሚቋቋሙበት ሥራ እንዲሠራ፣ ወንጀሉን የፈጸሙ ሰዎችም ለፍርድ ቀርበው
ቅጣታቸውን እንዲያገኙ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የምሥራቅ አርሲና የጅግጅጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሀገረ ስብከታቸው የተከሰተውን ችግር በማስመልከት ዝርዝር መረጃዎችን በቊጥራዊ ማስረጃዎች አስደግፈው አቅርበዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው
በተፈጠረው ችግር እጅግ በጣም ማዘናቸውን ገልጸው በመንግሥት በኩል በአስቸኳይ አጣሪ ቡድን ተቋቁም ወደ ስፍራው ተልኳል ካሉ በኋላ የአጣሪ ቡድኑን ሪፖርት መሠረት በማድረግም አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ብፁዓን አባቶቻችን በኦሮሚያ ፕ/ት ጽ/ቤት ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ከብልጽግና ፓርቲ ድ/ ቤት አመራሮች ጋር ዝርዝር ውይይት አድርገዋል። በውይይቱ ወቅት የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንደገለጹት የክልሉ መንግሥት በሥፍራው የተከሰተውን ችግር ለመቆጣጠርና ሊከሰት ይችል የነበረውን ተጨማሪ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉን፣ በአሁኑ ወቅትም ወደ ሥፍራው አጣሪ ቡድን መላኩንና የማጣራት ውጤቱን ተከትሎም አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ቤተክርስቲያኗ ምዕመናንን ለማጽናናትና ድጋፍ ለማድረግ በምታደርገው ጥረት ሁሉ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደረግላት ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ እና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ፣ወደ ቀያቸው ለመመለስ እንዲሁም የተቃጠለውን ቤተ ክርስቲያን መልሶ ለመገንባት እና በአካባቢው ዳግመኛ መሰል ችግር እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚያስችል ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚያከናውኑ ከልዑካን ቡድኑ ጋር ባደረጉት የማጠቃለያ ውይይት ገልጸዋል።
ምንጭ:- ኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
_
ፍኖተ ሰላም ሚዲያ
متاح الآن! بحث تيليغرام 2025 — أهم رؤى العام 
