Debtera Media
Kanalga Telegram’da o‘tish
ደብተራ ሚዲያ የእውነት ድምጽ! ሰብስክራይብ በማድረግ ቤተሰብ ይሁኑ!👇 በዩቲዩብ 👉 https://bit.ly/3bMfT8D በፌስቡክ 👉 fb.me/DebteraMedia በቴሌግራም 👉 t.me/DebteraMedia ማንኛውንም ሃሳብ አስተያየት ሆነ መረጃ በ t.me/DebteraMedia_Bot ማድረስ ትችላላችሁ።
Ko'proq ko'rsatish3 552
Obunachilar
-824 soatlar
-187 kun
-5730 kun
Postlar arxiv
3 552
[ † ጥቅምት ፮ [ 6 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሐዋርያዊ
፪. አባ ዸንጠሌዎን ዘጾማዕት
፫. ቅዱስ ዕንባቆም ነቢይ [ዕን. ከ፩ - ፫ ያንብቡ]
፬. ቅድስት ሐና ነቢይት [የሳሙኤል እናት - ፩ሳሙ. ከ፩ - ፪ን ያንብቡ]
፭. ቅዱሳን ኡሲፎርና ኡርያኖስ [ሰማዕታት]
፮. አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ኢትዮዽያዊ [ፍልሠቱ]
፯. ቅዱስ ሄኖስ ነቢይ
[ † ወርሐዊ በዓላት ]
፩. ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
፪. አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
፫. አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
፬. ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
፭. ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
፮. ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
፯. ቅድስት ሰሎሜ
፰. አባ አርከ ሥሉስ
፱. አባ ጽጌ ድንግል
፲. ቅድስት አርሴማ ድንግል
" ምንም እንኩዋ በለስም ባታፈራ: በወይን ሐረግም ፍሬ ባይገኝ: የወይራ ሥራ ቢጐድል: እርሾችም መብልን ባይሰጡ: በጐች ከበረቱ ቢጠፉ: ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ: እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል:: በመድኃኒቴ አምላክ ሐሴት አደርጋለሁ::" [ዕን.፫፥፲፯]
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
3 552
🕊
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞
❖ ጥቅምት ፮ [ 6 ] ❖
[ 🕊 ✞ እንኩዋን ለቅዱስ "ዲዮናስዮስ ሐዋርያዊ" ወአባ "ዸንጠሌዎን" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ 🕊 ]
† 🕊 ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሐዋርያዊ ሊቅ 🕊 †
በዘመነ ሐዋርያት ከነበሩና አስደናቂ ታሪክ ከነበራቸው ቅዱሳን አንዱ ይህ አባት ነው:: ቅዱስ ዲዮናስዮስ በትውልዱ አረሚ [ ግሪካዊ ] የሆነ ፈላስፋ: ከነ አሪስቶትል ሲያያዝ የመጣውን ፍልስፍና ጨርሶ በማጥናቱ ርዕሰ ሊቃውንት [የፈላስፎች አለቃ] የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር::
በግሪክ አቴና [ATHENS] ለነበሩ ፈላስፎችም ሁሉ የበላይ ሲሆን በአርዮስፋጐስ [ሐዋ.፲፯] ታላቁ ሰው እርሱ ነበር:: ይህ ሁሉ ሲሆን ግን እድሜው ገና ወጣት ነበር:: ቅዱስ ዲዮናስዮስ ፈላስፋ ስለ ሆነ ቅሉ ይመራመር ነበር::
ይልቁኑ ስለ እውነተኛው አምላክ ያስብ ነበር:: በግሪክ ምድር ከሚመለኩ ፪፻፶ አማልክት መካከል ቁም ነገር አልተገኘምና:: ነገር ግን አንድ ቀን ዓለም በተፈጠረች በ፭ሺህ ፭፻፴፬ [5,534] ዓመት: መጋቢት ፳፯ ቀን: በዕለተ ዓርብ: ፮ ሰዓት ላይ ምድር ተናወጠች:: ፀሐይ ጨለመች: ጨረቃ ደም ሆነች: ከዋክብትም ረገፉ::
በዚህ የተደናገጡ የአቴና [ATHENS] ነዋሪዎችና ፈላስፎች ወደ ዲዮናስዮስ ተሰብስበው "መምሕራችን የተፈጠረውን ነገር መርምረህ አስረዳን" አሉት::
ዲዮናስዮስም ባለው ጥበብ ባሕሩን: የብሱን: ፀሐይ: ጨረቃን: ከዋክብትን መረመራቸው:: "ወረከቦሙ ኅዱዓነ" እንዲል በቀደመ ቦታቸው አገኛቸው:: ግራ ቢገባው እንቅልፍ ከዐይኑ ተከለከለ::
ከዚያም ወደ ቤተ መዛግብቱ ገብቶ መጻሕፍትን ሲያገላብጥ "አርስጣላባ" የሚባል ግዙፍ መጽሐፍ አግኝቶ ቢገልጠው "እልመክኑን" የሚል ጽሑፍ አገኘ:: ወደ ውጪ ወጥቶ በሕዝቡና ጠቢባኑ ፊት ልብሱን ቀድዶ አለቀሰ::
እነርሱም ደንግጠው "ምነው መምሕራችን? ምን ሆንህ?" ቢሉት "የማይታየው አምላክ ቢወርድ በምቀኝነት ገደሉት የሚል ጽሑፍ አገኘሁ" አላቸው:: "እልመክኑን" ማለት "የማይታይ አምላክ" ማለት ነውና:: "ዘኢያስተርኢ ኅቡዕ እስመ አስተርአየ ለነ: እሳት በላኢ አምላክነ" እንዲል::
ከዚህ በሁዋላ ደቀ መዛሙርቱን [ተማሮቹን] ጠርቶ [ኡሲፎስና ኡርያኖስ ይባላሉ] "እልመክኑን" የሚለውን ስም "ከቤተ ጣዖቱ በር ላይ ለጥፉት" ብሏቸው ለጠፉት:: በእንዲህ ያለ መንገድ ፲፬ ዓመታት አልፈው ቅዱስ ዻውሎስ ወንጌልን እየሰበከ አቴና ደረሰ:: ዘመኑም በ፵፰ ዓ/ም ነበር::
ወደ ከተማዋ ሲገባ በጣዖት ቤቱ በር ላይ የተለጠፈውን ጽሑፍ ተመለከተና ያስተምራቸው ያዘ:: ትምሕርቱን የሰሙ ጠቢባኑና ሕዝቡ ሐዋርያውን ይዘው ወደ ዲዮናስዮስ ፊት አቀረቡት:: "ምንድን ነው በደሉ?" ቢላቸው "አዲስ አምላክን ሲያስተምር አግኝተነዋል" አሉት::
ቅዱስ ዻውሎስም "እኔ አዲስ አምላክን የምሰብክላችሁ አይደለሁም:: ይልቁኑ ከቀድሞም የፈጠራችሁ: ቀጥሎም የሞተላችሁ: እናንተም "እልመክኑን" ብላችሁ ሳታውቁት ታመልኩት የነበረውን ጌታ እንጂ:: እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው አላቸው::
ዲዮናስዮስም ቅዱስ ዻውሎስን "ለዚህ ምን ምልክት አለህ?" ቢለው "የዛሬ ፲፬ ዓመት: መጋቢት ፳፯ ቀን: በዕለተ ዓርብ ፮ ሰዓት ላይ ታላላቅ ተአምራት የተደረጉ አይደለምን! እነዚህ ሁሉ የተደረጉት በስቅለቱ ጊዜ ነው" ሲል መለሰለት::
ዲዮናስዮስም ፈጥኖ በክርስቶስ አመነ:: የአካባቢው ጠቢባንና ሕዝቡም አምነው ከመሪያቸው ጋር ተጠመቁ:: ቅዱስ ዻውሎስም ቅዱስ ዲዮናስዮስን አስተምሮ የአቴና የመጀመሪያው ዻዻስ አደረገው:: ቅዱሱም ክርስቲያኖችን ያበዛ: መንጋውንም ያጸና ዘንድ ብዙ ተጋ::
በተለይ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩ ታዋቂ ደራስያን አንዱ ሆነ:: በርካታ ድርሰቶችንም በመንፈስ ቅዱስ ደረሰ:: ዛሬ ድረስ እንኩዋ ሃይማኖተ አበው ውስጥ የሚገኘው ድርሰቱ [ዘዲዮናስዮስ] ጣዕሙ ልዩ ነው:: ቅዱሱ ለብዙ ዘመናት ለወንጌል አገልግሎት ተግቶ: በዚህች ቀን የአካባቢው አገረ ገዥ አንገቱን አስቆርጦት ሰማዕት ሆኗል::
የሚገርመው ግን ሲገድሉት በቦታው ሰው ስላልነበረ ቅዱሱ ተነስቶ: ተቆርጣ የወደቀች ራሱን አነሳት:: በጐኑ አቅፎም ደቀ መዛሙርቱ እስካሉበት ሒዶ በፊታቸው ዘንበል አለ:: ምዕመናንም እያለቀሱና እየዘመሩ ከአርድእቱ ኡሲፎስና ኡርያኖስ ጋር ቀብረውታል:: እነርሱም አብረውት ተሰይፈዋልና::
† 🕊 አባ ዸንጠሌዎን ዘጾማዕት 🕊 †
ታላቁ ጻድቅ: ሰባኬ ወንጌልና ገዳማዊ አባ ዸንጠሌዎን የተስዓቱ [ዘጠኙ] ቅዱሳን መሪ [አባት] ናቸው:: ጻድቁ ሃገረ ሙላዳቸው ሮም ቢሆንም ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮዽያ ነው::
ወላጆቻቸው በሮም ቤተ መንግስት የቀኝ መንበር ያላቸው ክቡራን ቢሆኑም ልጃቸውን ይማር ብለው ወደ ገዳም ከተቷቸው:: በገዳም ትምሕርቱን ከጠነቀቁ በሁዋላ በዚያው ጠፍተው ወደ ግብጽ ወረዱ:: በዚያም መነኮሱ::
እድሜአቸው እየገፋ ሲሔድ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ፰ቱን ቅዱሳን ሰብስበው: በአቡነ አረጋዊ [ዘሚካኤል] መሪነት ወደ ሃገራችን መጡ:: በ፬፻፸ [470] ዎቹ አካባቢ የነበረው ንጉሥ አልዓሜዳም በክብር ተቀብሎ አክሱም ውስጥ "ቤተ - ቀጢን" የሚባል ቦታን ሰጣቸው::
ዘጠኙ ቅዱሳን በአንድነት: ቀን ቀን ወንጌልን ሲያስተምሩ ውለው ሌሊት ሲጸልዩና መጻሕፍትን ሲተረጉሙ ያድሩ ነበር:: ነገር ግን ለየብቻቸው መኖራቸውን መንፈስ ቅዱስ ስለ ወደደ ሁሉም በየራሳቸው ገዳማትን መሠረቱ::
አባ ዸንጠሌዎንም ከአክሱም ከተማ በላይ ከደብረ ቆናጽል ጐን ወደ ሚገኝና 'ጾማዕት' ወደ ሚባል ረዥም ተራራ ወጡ:: ቦታው ዛሬ "እንዳባ ዸንጠሌዎን" ይባላል:: በዚያም አስቀድመው ለወንጌል አገልግሎት እየተጉ ድውያንን ፈወሱ::
ሙታንን አስነሱ: አጋንንትን አሳደዱ:: ብዙ ተአምራትንም አደረጉ:: እንዲያውም አንድ ቀን ወይራውን በጧት ተክለው: በሠርክ ትልቅ ዛፍ ሆነላቸው:: ከዚያ ዘንጥፈው እሳቱን በቀሚሳቸው ላይ አፍመው ማዕጠንት አሳርገዋል::
የሚገርመው ያ ዛፍ ዛሬም ድረስ ለምስክርነት ቁሟል:: እኛም ሳይገባን ሔደን በዓይናችን አይተነዋል:: አምላከ ቅዱሳን ግሩም ነው !!! በመጨረሻ ዘመናቸው ግን ጻድቁ ፭ ክንድ ርዝመት ባላት ጾማዕት [በዓት] ውስጥ ገብተው ቆሙ:: ለ፵፭ ዓመታት ሳይቀመጡና ሳይተኙ በእንባ ቢጸልዩ ቅንድባቸው ተላጠ:: አካላቸውም በአጥንቱ ብቻ ቀረ::
በ፮ኛው ክ/ዘመንም በዚህች ዕለት የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም መጥቶ "ወዳጄ! ስምህን የጠራ: መታሰቢያህን በእምነት ያደረገውንም ሁሉ እምርልሃለሁ" አላቸው:: ያን ጊዜ አጥንቶቻቸው ተወዛወዙና ነፍሳቸው በክብር ዐረገች:: ከዚህ አስቀድሞም ንጉሡን አፄ ካሌብን አባት ሆነው ያመነኮሱት እርሳቸው ናቸው::
አምላከ አበው የወጡ ወገኖቻችንን ሁሉ በሰላም ይመልስልን:: ከክብረ ቅዱሳንም አይለየን::
🕊
3 552
🕊
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞
❖ ጥቅምት ፭ [ 5 ] ❖
[ ✞ እንኩዋን ለጻድቁ "አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ" እና "ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ ]
† 🕊 አቡነ ገብረ ሕይወት 🕊 †
ጻድቁ የተወለዱት ግብፅ [ንሒሳ አካባቢ] ሲሆን አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ:: አባታችን ገብረ ሕይወት የጻድቃን አለቃ: የቅዱሳን የበላይ: ተጋድሎአቸውና ድንቅ ተአምራቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ቅዱስ ሰው ናቸው::
የጻድቁን ክብር መናገር የሚችል ምን አነደበት ይኖራል? እንደ ምንስ ባለ ብራና ይጻፋል? ዜናቸውንስ ለመስማት የታደለ እንደ ምን ዓይነት ሰው ይሆን?
አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለ፭፻፷፪ [562] ዓመታት በዚህች ዓለም ሲኖሩ እህል ያልቀመሱ [ምግባቸው ምስጋና ነውና]: ልብስ ያልለበሱ [ጠጉር አካላቸውን ይሸፍን ነበርና]: ሐዋርያዊ ሆነው ከግብፅ እስከ ኢትዮዽያ ብዙ ነፍሳትን ያዳኑ አባት: ሃገራችንን አስምረው: አስራት እንድትሆናቸውም ተቀብለው ምድረ ከብድ አካባቢ አርፈዋል::
ጻድቁ ገብረ መንፈስ ቅዱስም: ገብረ ሕይወትም ይባላሉ:: በ፭፻፷፪ [562] ዓመታት ሕይወታቸው እንደ ሐዋርያት ከምድረ ግብጽ እስከ ኢትዮዽያ ወንጌልን ሰብከዋል:: በዚህም በሚሊየን [አእላፍ] ለሚቆጠሩ ነፍሳት የድኅነት ምክንያት ሆነዋል::
ጻድቁ እንደ ሰማዕታትም ከከሃዲ ሰዎች ብዙ መከራን ተቀብለዋል:: እንደ ባሕታውያን ለብዙ መቶ ዓመታት ሰው ሳያዩ ቆይተዋል:: ለየት የሚለው ግን የጽድቅ ሕይወታቸው ነው:: ከእልፍ አዕላፍ አጋንንት ጋር ተዋግተው ድል ማድረግ ችለዋልና::
የንሒሳው ኮከብ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለኢትዮዽያ ልዩ ፍቅር አላቸው:: ስለ ሃገሪቱና ሕዝቧ ፍቅር ሲሉ ለ፻ [100] ዓመታት በደብረ ዝቁዋላ መከራን ተቀብለዋል:: ምሕረትን ሲለምኑ ሥጋቸው አልቆ በአጥንታቸው ቁመው ነበርና ሃገራችን አሥራት ሆና ተሰጠቻቸው::
ስለዚህም ነው በሃገሪቱ ውስጥ ከ፳፻ [2,000] በላይ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳማትና አድባራት ዛሬም ድረስ ያሉት:: በ፰ [8] ኛው ክ/ዘመን አካባቢ የተወለዱት አባታችን ያረፉት በ፲፬ [14] ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ ነው:: ፍጥረታትን ሁሉ አዘው መጋቢት ፭ [5] ቀን ሲያርፉ ግሩማን መላእክት ገንዘው አካላቸውን ሠውረዋል::
ሥላሴን የተሸከመ አካላቸው በጐልጐታ ተቀብሯል የሚሉም አሉ::
"ሰላም ለመቃብሪከ ዘኢተከሥተ ለባዕድ:
ከመ መቃብሩ ለሙሴ ወልደ ዮካብድ:
ዜና መቃብሪከሰ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸማድ:
ቦ ዘይቤ በኢየሩሳሌም አጸድ:
ወቦ ዘይቤ ኀለወ በከብድ::" እንዲል::
የጻድቁ በዓል ጥቅምት ፭ [ 5 ] ቀን የሚከበረው ብዙ ጊዜ መጋቢት ፭ [ 5 ] ዐቢይ ጾም ውስጥ ስለሚውል ተውላጥ [ቅያሪ] ሆኖ ነው::
† 🕊 ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ 🕊 †
ይህ ቅዱስ አባት ስም አጠራሩ የከበረ: ሽምግልናውም ያማረ ነው:: ብዙዎቻችን የምናውቀው በበዓለ መስቀል ስሙ ተደጋግሞ ሲጠራ ነው:: ግን ይህ ታላቅ ሰው ለቅድስት እሌኒ መካነ መስቀሉን አሳያት ከሚል አረፍተ ነገር የዘለለ ታሪኩ ሲነገርለት ብዙ ጊዜ አንሰማምና እስኪ በዕለተ ዕረፍቱ ስለ ቅዱሱ ጥቂት እንበል::
ቅዱስ ኪራኮስ የተወለደው በ፫ [3] ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን እናቱ ቅድስት ሐና ትባላለች:: በእጅጉ የተባረከች ሴት ናት:: ምንም በነገዳቸው አይሁድ ቢሆኑም የዘመኑ የአይሁድ ክፋት አልገዛቸውም:: የተባረከች እናቱ ታሪክ እያስጠናች ከማሳደጉዋ ባለፈ አስቀድማ ኦሪቱን: ነቢያቱን እንዲያውቅ አደረገች::
አስከትላም ሕገ ክርስትናን እንዲረዳ አደረገችው:: የታሪክና የመጻሕፍት ምሑሩ ቅዱስ ኪራኮስ ከእናቱ ጋር ሆኖ እግዚአብሔርን እያገለገለ: ክርስቶስን እያመለከ ቆየ:: በዚህ ጊዜ ግን እድሜው እየገፋ ነበር::
ሠለስቱ ምዕት [፫፻፲፰ [318] ቱ ሊቃውንት] ጉባኤያቸውን ከፈጸሙ በሁዋላ ቅድስት እሌኒም መስቀሉን ፍለጋ ስትወጣ ትልቁ ፈተናዋ የተቀበረበትን ቦታ ማወቅ አለመቻሏ ነበር:: እንዲያውም አማራጭ ስታጣ በአካባቢው የነበሩ አይሁድን ምሥጢር እንዲያወጡ ቀጥታቸው ነበር:: በሁዋላ ግን ኪራኮስ ስለሚባል ደግ ታሪክ አዋቂ ሰው ሰምታ ተገናኙ::
ቅዱስ ኪራኮስም አባቶቹ አይሁድ ናቸውና አካባቢውን ያውቀው ነበር:: ችግሩ ቆሻሻው ተራራ በመሆኑ ከ፫ [3] ቱ የትኛው እንደ ሆነ አለመታወቁ ነበር:: ቅዱሱ ግን ለዚህም መፍትሔ ነበረውና "ደመራ ደምረሽ: በእሳት አቃጥለሽ: እጣን ጨምሪበትና ይገለጥልሻል" አላት::
ቅድስት እሌኒም የተባለችውን በትክክል ፈጽማ የመድኅን ክርስቶስን ቅዱስ ዕጸ መስቀል አገኘች:: ቅድስት እሌኒ ወደ ሃገሯ ከተመለሰች በሁዋላም ቅዱስ ኪራኮስ በኢየሩሳሌም አካባቢ ዻዻስ ሆኖ ተሾመ::
አረጋዊው ቅዱስ የሚገርም እረኛ ነውና የባዘኑትን ሲፈልግ: በቤቱ ያሉትንም ሲያጸና ብዙ ደከመ:: በቅርቡ ያሉትን በአፉ: የራቁትን ደግሞ በጦማር [በመልእክት] አስተማረ:: በወቅቱ በአካባቢው ኤልያኖስ የሚሉት ከሃዲ ንጉሥ ነበርና በቅዱስ ኪራኮስ ላይ ተቆጣ::
ወደ እርሱ አስጠርቶ በአደባባይ: ቅዱስ ቃሉን ይጽፍበት የነበረው ቀኝ እጁን አስቆረጠው:: ቅዱስ ኪራኮስ ግን እጁ መሬት ላይ ወድቃ: ደሙ እየተንጠፈጠፈ ተናገረ :- "አንተ ልብ የሌለህ ንጉሥ! እጄን ቆርጠህ ከክርስቶስ ፍቅር ልትለየኝ አትችልም" አለው::
በዚህ የተበሳጨ ንጉሡ እሳት አስነድዶ: አልጋውን አግሎ ቅዱሱን ጠበሰው:: ኪራኮስ ግን በእሳቱ ላይ ሳለ ወደ እሥራኤል ፈጣሪ በእብራይስጥኛ ጸለየ:: በማግስቱ እናቱን ቅድስት ሐናን አምጥተው የነደደ እሳት ውስጥ ጣሏት::
ለ፫ [3] ሰዓት ያህል በእሳት ውስጥ ስትጸልይ ቆይታ በጦር ወግተው ገደሏት:: ቅዱስ ኪራኮስንም ለአራዊት ሰጡት:: አራዊቱ ሰገዱለት:: በሌሎች ዓይነት ስቃዮችም ፈተኑት: ግን እንቢ አላቸው:: በመጨረሻው በዚህ ቀን ገድለውት የክብርን አክሊል ተቀዳጅቷል::
አምላከ ቅዱሳን በእነርሱ ላይ የበዛች ፍቅሩን ለእኛም ያድለን:: ፍሬ ትሩፋት: ፍሬ ክብር እንድናፈራም ይርዳን:: ክብራቸውንም አያጉድልብን::
🕊
[ † ጥቅምት ፭ [ 5 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ
፪. ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ [ዻዻስ ወሰማዕት]
፫. ቅድስት ሐና ሰማዕት [እናቱ]
፬. ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ [ከ፲፪ቱ ሐዋርያት]
፭. አባ ዻውሎስ ሰማዕት [አርዮሳውያን አንቀው የገደሉት አባት]
[ † ወርሐዊ በዓላት ]
፩. ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
፪. ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
፫. ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
፬. ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
፭. ቅድስት አውጋንያ [ሰማዕትና ጻድቅ]
" ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት: እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ:: በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና:: " [ገላ.፮፥፲፬] (6:14)
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
3 552
🌺 ♱ 🌺
🕊 የማይሰለች ተጋዳይ ፤ የክብር ኮከብ ! 🕊
🌸 ♱ 🌸
❝ እንግዲህ ከሰው ተለይቶ ወደ ጫካ ገባ ፤ በዚያም ኖረ። በበጋው ፡ ሓሩር ፡ በክረምቱ ፡ ቍር ፡ እየተሠቃየ ፡ ኖረ። በሰውነቱ ላይ ፡ ልብስን ፡ አልለበሰም ፡ ዕራቁቱን ፡ ነበረ እንጂ ራቁቱን ፡ በብርድ ፡ ላይ ፡ ቆሞ ፡ ይጸልይ ነበር ፤ ወገቡንም ፡ በማቅ ፤ በሠንሰለት ታጥቆ ነበር። ከዚያ ፡ ጫካ ፡ ቅዝቃዜ ፡ የተነሣም ፡ ሰውነቱ ፡ አልቆ አጥንቱ ፡ ደርቆ ፡ ነበር።
ሰውነቱንም በእግዚአብሔር ፊት ዕራቁትሽን ትቆሚአለሽና እወቂ ፥ ጽኚ በርቺ ጨክኚ ይላት ነበር ፤ እንደዚህ ባለ ሥራ በጾምና ፡ በጸሎት ፡ በስግደትና ፡ በብዙ ፡ ትጋት ቀንም ሌሊትም ጽሙድ ሆኖ ኖረ።
ያለ ዕረፍት ብዙ ጸሎትን ይጸልይ ፡ ብዙ ስግደት ይሰግድ ነበር። ሥጋው እስኪደርቅ ቍርበቱም ከአጥንቱ እስኪጣበቅ ድረስ ከእንጨት ፍሬና ሥራ ሥር ወይም ከአትክልት ወይም ገዳማውያን ከሚመገቡት ከሌሎች ፍሬያት ምንም ምን የሚመገበው አልነበረውም። ለሥጋውም ምንም ምን ምክንያት አልሰጠም። ❞ [ ገድለ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ]
🌸 ♱ 🌸
የጻድቁ በዓል ጥቅምት ፭ [ 5 ] ቀን የሚከበረው ብዙ ጊዜ መጋቢት ፭ [ 5 ] ዐቢይ ጾም ውስጥ ስለሚውል ተውላጥ [ቅያሪ] ሆኖ ነው::
🌸 🌸
†††
✟ 𝐎𝐑𝐓𝐇𝐎𝐃𝐎𝐗Y ✟
🕊 💖 🕊
3 552
🌸 🌸
[ 🕊 ✞ እንኩዋን ለጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ 🕊 ]
🕊 💖 🕊
[ የክብር ኮከብ ፤ የገዳም መብራት ]
❝ ብፁዕ አባታችን ከራሱ አብልጦ ባልንጀራውን ወደደ፤ ቆሞ ስለ ኃጥአን ይጸልያል፤ ለራሱ ምንም ሳያስብ ኖረ፤ ስለ ኃጥአን ነፍሳት ሁል ጊዜ በስግደት ብዛት ላቡን ሲያፈስ ኖረ፤ ከሲኦል ሜዳ የኃጥአንን ነፍሳት በረበረ፤ ለሥጋው አስፈላጊ ስለሆነው፤ የሚበላውን የሚጠጣውን የሚለብሰውን አይለምንም ነበር ፤ የዚህን ዓለም ገንዘብ አይፈልግም ነበር፤ ፈጣሪውን መሰለው ፣ ባልንጀራውን ይወዳል፤ ስለ ኃጥአንም ምሕረትን ይለምናል፡፡
የማይሰለች ተጋዳይ፤ የክብር ኮከብ፤ የገዳም መብራት ስም አጠራሩ እርግናው የተመሰገነ፤ ብፁዕ ቅዱስ ደግ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከግብጽ ደቡብ ከቆላው አገር ከንኂሳ ሀገር የተገኘ ገዳማዊ ነው፡፡ በግብጽ በረሃ ፫ መቶ ዓመት ኖረ፡፡
ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ወጥቶ በዝቋላ ገዳም እህል ሳይበላ ውኃ ሳይጠጣ፥ ልብስ ሳይለብስ ሁለት መቶ ስድሳ ሁለት ዓመት ዕራቁቱን ኖረ፤ ኑሮውም እንደ ሰው አልነበረም፤ በምድር ላይ እንደ መላእክት ሆኖ ኖረ እንጂ ተጋድሎውንም መጋቢት አምስት ቀን በዕለተ እሑድ ፈጸመ፡፡❞
🕊
እግዚአብሔር ስለ እውነተኛ ወዳጁ ስለ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ ብሎ ይማረን፡፡
🌸 🌸
†††
✟ 𝐎𝐑𝐓𝐇𝐎𝐃𝐎𝐗Y ✟
🕊 💖 🕊
3 552
🕊 † 🕊
[ ተዋሕዶ ፍጽምት የቅዱሳን ሃይማኖት ]
🍒▬▬▬▬▬ † ▬▬▬▬▬🍒
[ የቀናች ቤተ ክርስቲያን ! ]
💛 💛
❝ [ እንደ መናፍቃኑ ] አንድ ብቻ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ልንከፍለው ፤ ሁለት ልናደርገው አይገባም ፤ የሃይማኖት ትምህርት በሁሉ የቀናች ስትሆን በዚህ ምግባር ከአነጋገር በምንም በምን እውነተኛ አይገኝም።
ተዋሕዶ አካላትን በመለየት ብቻ እንደ ተደረገ የሚናገር ቢኖር ቃል እንደ ተዋሐደ መጽሐፍ አልተናገረም ፤ ቃል ሥጋን እንደሆነ እንደኛ ያለ ሥጋን ነፍስን እንደ ተዋሐደ ተነገረ እንጂ። ሥጋን ነሥቶ ሰው ሆነ ከድንግልም ተወለደ ፤ ከጌትነቱ ባሕርይም አልተለወጠም።
እርሱ ከእግዚአብሔር አብ ተወለደ ፤ ሰውም ቢሆን እንደ ቀደመ ባሕርዩ ጸንቶ ኖረ ፤ በእርሱ አምነን የቀናች የሃይማኖትን ትምህርት በየቦታው እናስተምራለን ፤ አባቶቻችንም እንዲህ ብለው አምነዋል ፤ ንጽሕት ድንግልንም እግዚአብሔርን የወለደች ናት ባሏት ጊዜ እንዲህ ተመክተው ተናገሩ። [ ዮሐ.፩፥፲፬ ። ፩ቆሮ.፩፥፴፩ ። ፪ቆሮ.፲፥፲፯ ]
የቃል የባሕርዩ መገኘት ከንጽሕት ድንግል አይደለም ፤ በንጹሕ ሥጋ ከእርሷ ተወለደ እንጂ ይኸውም ቃል ነው ፤ ቃል አንድ አካል በመሆን የተዋሐደው ሥጋም የምትናገር ነፍስ ያለችው ፍጹም ሥጋ ነው ፤ በሥጋ የተወለደው ልደቱም እንዲህ ነው።
ክርስቶስን በመውደድ ጸንቼ ዛሬ ይኸን ጻፍኩልህ ወንድሜም እንደ መሆንህ እማልድሀለሁ ፣ በክርስቶስ ፊት ንጹሐን ክቡራን በሚሆኑ በመላእክትም ፊት አዳኝብሃለሁ ፤ በዚህ ሃይማኖት ጸንተህ ትኖር ዘንድ ሌሎችንም ታስተምር ዘንድ ፤ እንዲህ የሆነ እንደሆነ የቀናች ቤተ ክርስቲያን ፍቅር ባለቤት ፍጹም አንድነት ሰላም ትሆናለች ፤ ስምምነት ያለው ልብ ከእግዚአብሔር አገልጋዮች ጋር ይኑር። ❞ [ቅዱስ ቄርሎስ]
🕊
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን።
🌸 🌸
†††
✟ 𝐎𝐑𝐓𝐇𝐎𝐃𝐎𝐗Y ✟
🕊 💖 🕊
3 552
🕊
[ † እንኩዋን ለቅዱሳን ነገሥታት "አብርሃ ወአጽብሃ" እና ለቅዱስ "ሐናንያ ሐዋርያ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ † ]
† 🕊 ቅዱሳን አብርሃ ወአጽብሃ 🕊 †
እነዚህ ነገሥታት ሞገሶቻችን: ብርሃኖቻችን ናቸውና ደስ እያለን እንወዳቸዋለን: እናከብራቸዋለን:: ሥላሴ ቢመርጧቸው ዛሬ ላለንበት ሕይወት መሠረቱን ጥለው አልፈዋልና::
፪ቱ ቅዱሳን ነግሥታት መንትያዎች ሲሆኑ ወላጆቻቸው ንጉሥ ታዜር / አይዛና / ሠይፈ አርዕድ እና ንግሥት አሕየዋ / ሶፍያ ይባላል:: ንጉሡና ባለቤቱ ልጅ ቢያጡ ወደ እግዚአብሔር ለመኑ:: ፈጣሪም በቅዱስ ሚካኤል አብሳሪነት ፪ ዕንቁዎችን አስረከባቸው::
ንግስት አሕየዋ [ሶፍያም] መጋቢት ፳፱ ቀን በ፫፻፲፩ ዓ/ም ጸንሳ: ታሕሳስ ፳፱ ቀን በ፫፻፲፪ ዓ/ም ፪ቱን ቅዱሳን ወልዳቸዋለች:: "አምላክ ሽሙጥን አራቀልኝ" ስትልም "አዝጉዋጉ" ብላቸዋለች:: እነዚህ ፪ ፍሬዎች በልጅነታቸው ከወቅቱ ሊቀ ካህናት እንበረም ኦሪቱን ጠንቅቀው ተምረዋል::
ከእግዚአብሔር የተሰጡ ናቸውና በ፲፪ ዓመታቸው ወደ ቤተ መቅደስ ገብተዋል:: ትንሽ ቆይቶ ግን አባታቸው ታዜር በማረፉ ሕዝቡ ፪ቱን ቅዱሳን "ንገሡልን" አሏቸው:: እነርሱም "እኛ የፈጣሪ አገልጋዮች ነንና አንችልም" በማለታቸው ለተወሰነ ጊዜ እናታቸው አስተዳደረች::
ቆይቶ ግን ቅዱስ ሚካኤል ለሊቀ ካህናቱ እንበረም "የፈጣሪ ፈቃዱ ስለ ሆነ አትዘኑ:: ፪ታችሁም በአንድ ዙፋን ላይ ንገሡ: ታላቅ ጸጋ ለሃገሪቱ ይሆናል በላቸው" አለው::
ሊቀ ካህናቱም የታዘዘውን ተናግሮ: በ፲፱ ዓመታቸው: ፪ቱንም በአንድ ዙፋን ላይ "ነገሥተ ኢትዮዽያ" ሲል አስቀምጦ ቀባቸው:: ስማቸውን "ኢዛና" እና "ሳይዛና" አላቸው:: ቅዱሳኑ እንደ ነገሡ ቀዳሚ ሥራቸው የቀናችውን ሃይማኖት መፈለግ ሆነ::
በወቅቱ ፍሬምናጦስ [የሁዋላው አቡነ ሰላማ] በቤተ መንግስቱ ውስጥ የቅርብ አማካሪ ነበርና ጠርተው ተጨዋወቱት:: "አንተ ወንድማችን! ክርስቶስ ይወርዳል: ይወለዳል ተብሎ የተቆጠረው ሱባኤ እኮ አልፏል:: ምነው ቀረሳ? በርግጥ ምሥጢሩ ንገረን" አሉት::
እርሱም አትቶ: አመሥጥሮ: ከ፫፻ ዓመታት በፊት አምላክ ሰው መሆኑንና ዓለምን ማዳኑን አስተማራቸው:: "አጥምቀን?" ቢሉት "አልችልም" አላቸው:: እነርሱም ከብዙ ስጦታ ጋር ወደ ግብጽ ላኩት::
ቅዱስ አትናቴዎስም ፍሬምናጦስን "አቡነ ሰላማ" ብሎ ከብዙ መጻሕፍት ጋር ላከው:: በመጀመሪያ ኢዛናና ሳይዛና ተጠመቁ:: ስማቸውም "አብርሃ ወአጽብሃ" ተባለ:: ቀጥሎም ሠራዊቱና ሕዝቡ ተጠመቀ::
ሃገራችንም በእነዚህ ቅዱሳን አማካኝነት ከጨለማ ወደ ብርሃን መጣች:: የክርስትና ደሴት ሆነች:: ሃገረ እግዚአብሔርነቷንም አጸናች:: ቅዱሳኑ ከዚህ በሁዋላ በሞገስ ክርስትናን ያስፋፉ ዘንድ ደከሙ:: ከ፻፶፬ በላይ አብያተ ክርስቲያናትን ሲያንጹ አብዛኞቹ ፍልፍል ነበሩ::
በተለይ ግን በአክሱም ከተማ ላይ ያነጿትና ፲፪ ቤተ መቅደሶች የነበሯት የጽዮን ቤተ ክርስቲያን ልናያት ትናፍቀናለች:: ጌጧ: ብርሃኗ ውል ውል ይልብናል:: ይህቺው ቤተ ክርስቲያን በ፲ ኛው ክ/ዘመን ዮዲት ጉዲት በእሳት አውድማታለችና:: መሠረቱ ግን ዛሬም አለ::
ቅዱሳን አብርሃ ወአጽብሃ ግን ክርስትናን ለማስፋፋትና መንግስትን ለማጽናት ሲሉ ከአክሱም በተጨማሪ በሽዋም ዙፋንን ዘረጉ:: ለብዙ ዓመታትም አምላክ በፈቀደው መንገድ እስከ የመን ድረስ ገዙ:: ክርስትናንም አስፋፉ::
ቅዱስ አብርሃ በተወለደ በ፶፪ ዓመቱ: በ፫፻፷፬ ዓ/ም ጥቅምት ፬ ቀን ሲያርፍ ወንድሙ ለ፲፭ ዓመታት ብቻውን አስተዳድሯል:: በ፫፻፸፱ ዓ/ም ደግሞ በዚሁ በጥቅምት ፬ ቀን ቅዱስ አጽብሃም በተወለደ በ፷፯ ዓመቱ በክብር ዐርፏል::
ከሁለቱም መቃብር ላይ ለ፴ ቀናት የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ ታይቷል:: ጌታችንም በማይታበል ቃሉ "ስማችሁን የጠራውን: መታሰቢያችሁን ያደረገውንም እምርላቹሃለሁ" ሲል ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::
† 🕊 ቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ 🕊 †
ሐናንያ ቁጥሩ ከ፸፪ቱ አርድእት ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስማቸው ተመዝግቦ ከተቀመጠልን ከጥቂቶቹ ዋነኛው ነው:: ከነገደ እሥራኤል ተወልዶ: በሕገ ኦሪት አድጐ: ከወጣትነት ዕድሜው ትንሽ እልፍ ሲል ጌታችን ወንጌልን ማስተማር ጀምሯልና ጠራው:: እርሱም በበጐ ፈቃድ ተከትሎታልና ከ፸፪ቱ አርድእት ደመረው::
ለ፫ ዓመታት ከጌታ እግር ተምሮ: ከዕለተ ስቅለት በፊት ሀብተ ፈውስም ተሰጥቶት ነበር:: ምክንያቱም ቅዱስ ሉቃስ እንደ ጻፈልን ሰብዐው አርድእት "ጌታ ሆይ! አጋንንት በስምህ ተገዙልን" ማለታቸውን አስቀምጦልናል:: [ሉቃ.፲፥፲፯] ቅዱስ ሐናንያ በበዓለ ዕርገት ተባርኮ በ፶ኛው ቀንም መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ለስብከተ ወንጌል ወጥቷል::
በሚያስተምር ጊዜ የሶርያዋን ደማስቆን ማዕከል አድርጐ ነበር:: በሁዋላም አበው ሐዋርያት የዚህች ከተማ የመጀመሪያው ዻዻስ አድርገው ሹመውታል:: ጌታ ባረገ በ፰ኛው ዓመት ክርስቲያኖችን ያሰቃይ የነበረው ሳውል [የሁዋላው ቅዱስ ዻውሎስ] ወደ ደማስቆ የተጉዋዘው ክርስቲያኖችን በተለይም ቅዱስ ሐናንያን ለማሠር ነበር::
ለእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ ይሆን ዘንድ መብረቅ ዐይኑን አጠፋው:: ወዲያውም ጌታችን ሳውልን ወደ ሐናንያ እንዲሔድ ነው የነገረው:: ከ፫ ቀናት በሁዋላ ጌታችን ለሐናንያ ተገልጦ አነጋግሮታል:: ሳውል [ዻውሎስ] ወደ ሐናንያ የደረሰው በመሪ ነበር::
፪ቱ እንደተገናኙ ቅዱስ ሐናንያ ሳውልን አስተማረው: ፈወሰው: አጠመቀው: በጐ መንገድንም መራው:: በዚህ ምክንያት ቅዱሱ ሐዋርያ የቅዱስ ዻውሎስ የንስሃ አባቱ ይሰኛል:: [ሐዋ.፱፥፩-፲፱]
ከዚህ በሁዋላ ቅዱስ ሐናንያ ለብዙ ዓመታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወንጌልን አስተማረ መከራንም ተቀበለ:: በመጨረሻም በዚህ ቀን ክፉዎች ከብዙ ስቃይ በሁዋላ በድንጋይ ወግረው ገድለውታል::
አምላከ አብርሃ ወአጽብሃ "ድሃ ተበደለ: ፍርድ ተጉዋደለ" የሚል ዳኛ: ሃይማኖቱ የቀና መሪንም ያምጣልን:: የቅዱሳኑን ክብር በእኛ ላይ ያድርግልን::
🕊
[ † ጥቅምት ፬ [ 4 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]
፩. ቅዱሳን ነገሥት አብርሃ ወአጽብሃ
፪. ቅዱስ ሐናንያ ሐዋርያ [ከ፸፪ቱ አርድእት]
፫. ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
፬. ቅዱስ ባኮስ ሰማዕት
፭. ቅዱሳን ባባ እና ማማ
፮. ቅዱስ ዮሐንስ ሕጽው
[ † ወርኀዊ በዓላት ]
፩. ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ
፪. ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
፫. ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
፬. ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ [ሰማዕት]
" እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ: ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር: ልመናና ጸሎት: ምልጃም: ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ: ስለ ነገሥታትና መኩዋንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ:: ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው:: " [ጢሞ.፪፥፩-፬]
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †
[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ ]
† † †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖 🕊 💖
