ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ
Open in Telegram
ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።
Show more613
Subscribers
+124 hours
-17 days
-1030 days
Posts Archive
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤
❤ እንኳን #ለዘመነ_ክረምት_ሦስተኛ_ሳምንት_ዕለት እሑድ (ሰንበት) እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #የዚህ_ሳምንት_መዝሙር፦ ሃሌ ሉያ በ፯ "ንጉሥ ውእቱ #ክርስቶስ_ንጉሥ_ውእቱ_ክርስቶስ መሐሪ ውእቱ ይሁብ ዘርአ ለዘራኢ፤ (ን)፣ ያሠርቅ እክለ ለሲሳይ ያነሥኦ እድ ለነዳይ፤ (ን) ዘየኀይድዎ ሥልጣነኖ ዘይኤዝዝ ትፍሥሕተ ለጻድቃኒሁ፤ (ን)፣ ወሠርዐ ሰንበት ለሰብእ ዕረፍት ገባሬ ሕይወት #ያርኁ_ክረምተ_በበዓመት ንጉሥ ውእቱ ክርስቶስ፣ ንጉሥ ውእቱ ክርስቶስ። ትርጉም፦ ከዓለም በፊት #ክርስቶስ_ንጉሥ_ነው፣ #ክርስቶስ_ይቅር_ባይ መሐሪ ነው፣ ለዘሪ ዘርን ይሰጣል፤ የተዘራውን ዘር ለምግብ እንዲኾን ፍሬያማ ያደርገዋል፣ ደሀውን ከድህነቱ ያነሣዋል ባለጠጋ ያደርገዋል። (አዝ) ሥልጣኑን የማይቀሙት፤ ለጻድቃን ደስታን የሚያዝ የሚሰጥ፤ እርሱ የሕይወት መገኛ በመሆኑ የፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ ያርፉ ዘንድ ሰንበትን ለዕረፍት ሠራ፤ #ክረምትን_በየዓመቱ የሚያመጣ #ክርስቶስ_ንጉሥ_ነው_ክርስቶስ_ንጉሥ ነው። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በድጓው_ላይ።
✝ ✝ ✝
❤ #የዚህ_ሳምንት_የዕለቱ_ምስባክ፦ "ዘያበቊል ሣዕረ ለእንስሳ። ወሐምልማለ ለቅኔ እጓለ እመሕያው። ከመ ያውፅእ እክለ እምድር"። መዝ 103፥15-16። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ቆሮ 9፥1-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 3፥15-ፍ.ም፣ የሐዋ ሥራ 27፥21-33። የሚበበውወንጌል ማቴ 5፥43-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ኤጲፋንዮስ። መልካም ዕለተ ሰንበትና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤
❤ #ሐምሌ ፲፪ (12) ቀን።
❤ እንኳን ለከበረ መልአክ ለመላእክት አለቃ #ለቅዱስ_ሚካኤል_የፋርስ_ንጉሥ ወደ ሆነ ወደ ሰናክሬም ሠራዊት እግዚአብሔር ለላከበት ቀን #ንጉሥ_ሕዝቅያስን ረድቶ በአንድ ሌሊት ከሰናክሬም ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ አርበኞች ለገደለበት ለወራዊ መታሰቢያ በዓልና ስርያቆስ ከሚባል አገር ለሆነ #ለአባ_ሖር ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡት፦ #የአባ_ሖር_ማኅበር_ከመቶ_ሰባት_ወንዶችና_ከሃያ_ሴቶች_ሰማዕታት ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን፡፡
✝ ✝ ✝
❤ በዚች ቀን የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ #የቅዱስ_ሚካኤል_የበዓሉ መታሰቢያ ነው። በዚች ቀን የፋርስ ንጉሥ ወደ ሆነ ወደ ሰናክሬም ሠራዊት እግዚአብሔር ላከው ከሰናክሬም ሠራዊት ከሰናክሬም ሠራዊትም መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ አርበኞች ገደለ።
❤ ይህም እንዲህ ነው ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን በከበባት ጊዜ ሕዝቅያስንና ፈጣሪው እግዚአብሔርን እየዘለፈ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞችን ላከ እንዲህም አለ "እግዚአብሔር ያድናችኋል እያለ ሕዝቅያስ አያስታችሁ ከእጄ የሚያድናችሁ ማን ነው"።
❤ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ እጅግ አዘነ ወገኖቹንና አገሩ ኢየሩሳሌምንም ያድን ዘንድ ማቅ ለብሶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። እግዚአብሔርም ልመናውን ተቀበሎ ወደ ፋርስ ንጉሥ ወደ ሰናክሬም ሠራዊት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ላከለት። ድንቅ ሥራንም ሠርቶ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ሰዎች ሁሉ አዳናቸው።
❤ ስለዚህም የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል መታሰቢያ በዚች ቀን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን ረድኤቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ሖር፦ ይህም አባት ስርያቆስ ከሚባል አገሩ ነው። አባቱም አንጠረኛ ነበር አንዲት እኅቱም ነበረችው። ጎልማሳም በሆነ ጊዜ ሰማዕት ይሆን ዘንድ ወደ አገረ ፈርማ ሔደ በመኰንኑም ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኰንኑ ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው ከሥቃዩም ድኖ ተነሣ። መኰንኑም በእጁ ላይ ጌታችን ያደረገውን ይህን ተአምር አይቶ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋራ አመነ። በሌላ መኰንን እጅም ከሚስቱና ከልጆቹ ጋራ በሰማዕትነት ሞተ።
❤ ቅዱስ አባ ሖርን ግን ወደ እንዴናው ላከው በዚያም በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ አሠቃዩት በመንኰራኵሮችም አበራዩት ዘቅዝቀውም ሰቅለው በእሳት በአጋሉት የብረት በትር ደበደቡት። መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ የሰማዕትነትን አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 12 ስንክሳር።
✝️ ✝️ ✝️
❤ "#ሰላም_ለሖር_በኀበ_እግዚኡ_ዘተመዝገነ። አመ ጽዕለተ ተወክፈ ወበትረ ኀፂን ርሱነ። ወሶበ እምኔሁ ነጸረ ዕበየ ተአምር ዘኮነ። ምስለ ብእሲቱ ወደቂቁ ከዊኖ ፍልጣነ። በእደዊሁ መኰንን አምነ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_12።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦"ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዓውዶሙ። ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ። ጠዐሙ ወታምእሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር"። መዝ 33፥7-8። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 24፥30-36።
❤ ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሒዶ ከቅዱሳን መካናት ተባረከ በዚያም በቅድስት ትንሣኤ በተሰየመች ቤተ ክርስቲያን በጳጳሱ በአባ ሚካኤል እጅ ቅስና ተሾመ። ከዚያም ወደ ምስር አገር ተመልሶ በማዕልቃ ባለች በእመቤታችን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትን እየጻፈ ተቀመጠ።
❤ በዚያም ወራት ሊቀ ጳጳሳቱ አባ ቄርሎስ ዐረፈ። የወንጌላዊው የቅዱስ ማርቆስ መንበርም ያለ ሊቀ ጳጳሳት ነበር። ስለዚህም ኤጲስቆጶሳት የአገር ሽማግሌዎችና ሕዝቡ ሁሉ ተሰበስበው ይሾሙት ዘንድ በአንድ ምክር ተስማሙ ሰይጣን ግን ክፉዎች ሰዎችን አነሣሥቶ ተቃወሙት። ሹመቱንም አልፈቀዱም። ነገር ግን መንሳዊ አባት የነበረውን የከሊል ልጅ አባ አትናቴዎስን ሾሙት። እርሱም መንጋውን በበጎ አጠባበቅ ጠበቀ።
❤ እርሱም በዐረፈ ጊዜ ኤጲስቆሳትና የሕዝቡ አለቆች ዳግመኛ ተሰበሰቡና በእጃቸው ጽፈው አባ ገብርኤል እንዲሾም ፈቀዱ ሁለተኛም በሕቡም መካከል ሁከት ተነሳ ከሌሎችም ጋር እጣ ያጣጥሉት ዘንድ ተስማሙ ስሞቻቸውንም ጽፈው በመንበሩ ላይ አኖሩ በላዩም እየጸለዩና እየቀደሱ ሦስት ቀኖች ሰነበቱ። ከዚህም በኋላ ታናሽ ብላቴና አምጥተው በውስጡ የአባ ዮሐንስ ስም ያለበትን ክርታስ አወጣላቸው። ያም አባ ዮሐንስ ተሾመ ይህ አባ ገብርኤል ግን ለማዕልቃ ቤተ ክርስቲያን ተከራካሪ አድርገው ሾሙት።
❤ በዚያም ወራትም በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ላይ ችግር ሁኖ ነበር። ይህ አባ ገብርኤልም ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ሒዶ በጾምና በጸሎት በሥግደትም በቀንና በሌሊት ሲጋደል ኖረ። ከቅዱሳን መነኰሳት ብዙዎች መልካም ራእይን አዩለት ከእርሷቸው በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ልብስን እንደሚአለብሱት ብዙዎች ከአሕዛብ የተመለሱ ክርስቲያኖችም እንደሚያጅቡት ያየ አለ። ደግሞም ይሾምባት ዘንድ ወደ አስቄጥስ ወደ አባ መቃርስ ገዳም ሲሔድ ያየለት አለ። ቁጥር የሌላቸውንም መክፈቻዎችን ሲቀበል ያዩ አሉ።
❤ ከገዳሙም ሊወርድ ብዙ ጊዜ ይሻ ነበር ነገር ግን አልተቻለውም። ከዚህ በኋላ አባ እንጦንስ በራእይ ተገልጦ እንዲህ አለው "ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ከዚህ ገዳም ትወርድ ዘንድ እኔ አልፈቅድም ጊዜው ሳይደርስ አትውረድ" አለው።
❤ ከሦስት ዓመት በኋላም አንዱ አረጋዊ የከበረ መልአክ እንግዲህስ አባ ገብርኤልን ወስደው በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጵጵስና ይሾሙታል እያለ እንደሚያነጋግረው ራእይ አየ። በዚያችም ቀን የሀገረ እንጣፊ መኰንን መጣ ከእርሱም ጋር ብዙዎች መሳፍንቶች ነበሩ። አባ ገብርኤልን አምጥተው በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጵጵስና ይሾሙት ዘንድ የሚያዝዝ የንጉሥ ደብዳቤም ከእርሱ ጋር ነበረ።
❤ ከዚህም በኋላ ያለ ፈቃዱ ወስደው በወንጌላዊው በቅዱስ ማርቆስ ወንበር ላይ ሊቀ ጵጵስናን ሾሙት። ቀን እርሱ ለኢየሩሳሌም አንድ ጳጳስና ሌሎችንም ኤጲስቆጶሳት ቀሳውስትንና ዲያቆናትንም ሾመ። ከዚህም በኋላ ሦስት ጊዜ ሜሮን አከበረ ባረከ እንደዚህም አድርጎ አንድ ዓመት ከአንድ ወር ኖረ። በዚያን ጊዜም አባ እንጦንስ ተገልጦ እንዲህ አለው "እነሆ ዕረፍትህ ቀርቦአል ከዐሥራ ስምንት ወሮች በኋላ ወደ እግዚአብሔር ትሔዳለህ የዘላለም ሕይወትንም ትወርሳለህ"።
❤ ከዚህም በኋላ በክርስቲያን ወገኖች ላይ ታላቅ መከራ ሆነ። ይህም አባት ወገኖቹን ያድን ዘንድ ወደ ጌታችን ለመነ ክብር ይግባውና ጌታችንም ልመናውን ተቀብሎ ሕዝቡን ይቅር አለ።
❤ ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱ ከመንበረ ሢመቱ ወጥቶ በምስር አገር ዓመት ሙሉ ተሠወረ። ከአንድ ምእመን በቀር ማንም አላወቀበትም በቀንና በሌሊት በገድል ከመቀጥቀጡ የተነሣም መልኩ ተለወጠ ሥጋውም ደረቀ።
❤ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር እርሱን ለሚፈራው ለአንድ ምእመን ሥራውን ገለጠ። እርሱም ከዚያ ቦታ አውጥቶ በሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን አስቀመጠው በጸሎትና በቅዳሴ እያገለገለ ኖረ። ድኆችንም ይጐበኛቸው ነበር። የሚሹትንም ይሰጣቸው ነበር። ወደ ርሱ የሚመጡትንም ሕዝቦች ያስተምራቸውና ያጽናናቸው ነበር።
❤ በአንዲት ዕለትም ሊቀ ጳጳሳት አባ አትናቴዎስ በግልጽ ታየው እንዲህም አለው "ስለዚህ ፈጽሞ አትዘን ከዚህ ብዙ ድካምና መከራ እግዚአብሔር ያሳርፍሃልና አነሆ ምድራዊ ኑሮህን የሚፈጽም ደዌ በአንተ ላይ ይመጣል ነገር ግን ደስ ይበልህ ታላቅ የሆነ የእግዚአብሔርን ጸጋ ተቀብለሃልና። የዘላለም ሕይወትንና የማያልቅ ተድላ ደስታንም ትወርሳለህና" አለው።
❤ በዚያን ጊዜም በሚያስጨንቅ ደዌ ታሞ እየተጨነቀ ኖረ። ስለ ነፍሱም መውጣትና በእግዚአብሔር ፊት ስለ መቆሙ ይፈራና ይደነግጥ ነበር የእመቤታችን ማርያም ሥዕልም በዚያ ነበረ። ወደርሷም አዘውትሮ ይማልድ ነበረ በዚያን ጊዜም ክብር ይግባውና ራሱ እግዚአብሔር በብሩህ ገጽ "ተገለጠለት መንግሥተ ሰማያትን አግኝተሃልና ደስ ይበልህ እንጂ አትፍራ እስከ ሦስት ቀንም ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ትወጣለህ" በማለት አረጋጋው። ይህንንም ብሎ ከእርሱ ተሠወረ በሦስተኛውም ቀን ሐምሌ 11 ቀን በሰላም አረፈ። በቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያንም በታላቅ ክብር ተቀበረ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ገብርኤል በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 11 ስንክሳር።
✝️ ✝️ ✝️
❤ "#ሰላም_ለኢሳይያስ_ቀሲስ። ወግኍሥ ባሕታዊ ዘደብረ መቃርስ። ከመ አአምኀከ ዘልፈ በመሥዋዕተ ስብሐት ሐዲስ። አጒይይ እከይየ መንፈስ ቅዱስ። እስመ ለኃጥእ ተብህለ መሥዋዕቱ ርኵስ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_11።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ተፈሥሑ ጻድቃን በእግዚአብሔር። ወለራትዓን ይደልዎሙ ክቡር። ግነዩ ለእግዚአብሔር በመሰንቆ"። መዝ 32፥1-2። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ጢሞ 2፥1-9፣ 1ኛ ጴጥ 4፥12-17፣ የሐዋ ሥራ 14፥20-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ6፥20-27። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤
❤ #ሐምሌ ፲፩ (11) ቀን።
❤ እንኳን #ለመርባስ ከሚባል አገር ሰዎች ለሆኑ #ለቅዱሳን_ዮሐንስና_ለአባቱ_ወንድም_ልጅ_ለስምዖን ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓልና #ለእስክንድርያ_ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰባ ስምንተኛ ለሆነው #ሊቀ ጳጳሳት_ለቅዱስ_ለአባ_ገብርኤል ለዕረፍቱ በዓል በሰላሞ አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ በአስቄጥስ ገዳም ከነበረው ከቅዱስ አባት ኢሳይያስና እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅዱሳን_ዮሐንስና_የአባቱ_የወንድም_ልጅ_ስምዖን፦ የዚህም ቅዱስ ዮሐንስ እናቱ መካን ነበረች አባቱም ልጅን ይሰጠው ዘንድ ክብር ይግባውና እግዚአብሔርን ይለምነው ነበር ከዚህም በኋላ ልጁን በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር አገልጋይ ሊአደርገው ተሳለ።
❤ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስም እግዚአብሔር ልጅን እንደሚሰጠው በራእይ ተገልጦ ነገረው። ይህን ቅዱስም በወለደው ጊዜ ዮሐንስ ብሎ ጠራው በመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስም ስም ቤተ ክርስቲያን ሠራ።
❤ ከዚህም በኋላ አድጎ ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ አባቱ የበጎች እረኛ አደረገው ምሳውንም ለእረኞችና ለመንገደኞች ሁል ጊዜ ይሰጥ ነበር እርሱ ግን እስከ ምሽት ይጾም ነበር። አባቱም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ስለዚህ ሊአረጋግጥ ወደ እርሱ ሔደ አባቱንም በአየው ጊዜ ዮሐንስ ፈርቶ ሊሸሽ ወደደ። አባቱም "የዛሬ ምሳህን አሳየኝ" አለው ብላቴናውም "ታይ ዘንድ ግባ" አለው ወደ መጠለያውም በገባ ጊዜ አገልግሉን ትኩስ እንጀራን ተመልቶ አገኘው እጅግም አደነቀ ከልጃቸው የሆነውንም ለሚስቱ ነገራት።
❤ ከዚያችም ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር ጸጋ እንደ አደረችበት አወቁ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲማር አደረጉት እንጂ በጎችን የሚጠብቅ እረኛ እንዲሆን አልተዉትም።
❤ ከዚህም በኋላ አባቱ ሊአጋባው ወደደ። እርሱ ግን ይህን አልወደደም። ዐሥራ ስምንት ዓመት በሆነውም ጊዜ ቅስና ተሾመ የአባቱ የወንድም ልጅ የሆነ ስምዖንም በጎቹን ትቶ መጥቶ የእርሱ ደቀ መዝሙር ሆነ። እርሱም ስለ ተአምራቱ የተናገረ ነው። እግዚአብሔር በእጆቹ ላይ ድንቆችንና ተአምራቶችን ገልጧልና። ደዌ ያለባቸውንም ሁሉ ያመጡአቸው ነበር እርሱም በዘይቱ ላይ ይጸልይና ይቀባቸው ነበር ወዲያውኑም ከደዌያቸው ይድኑ ነበር። እርሱም ወደርሱ የሚመጡትን ከኃጢአት ይርቁ ዘንድ ያስተምራቸው ነበር። ይመክራቸውና ይገሥጻቸውም ነበር። ከተአምራቱም አንዱ ይህ ነው በአንዲት መበለት የተሸከመችውን ገብስ ቀምቶ ለፈረሱ አበላት ያችም መበለት በዚህ ቅዱስ ዘንድ ከሰሰችው ቅዱስ ዮሐንስም ረገመው ያን ጊዜም ፈረሱ ሞተች።
❤ ዳግመኛም የንጉሥ የጭፍራ አለቃ ግብር ሊሰበስብ መጣ አንድ ዐይኑ የታወረች አንድ አገልጋይም ነበረው። ከእርሱም ተባርኮ ወዲያውኑም የታወረች ዐይኑ ተገለጠች በእርስዋም ደኅና አድርጎ አየ። ይህም ቅዱስ የሰዎችን ሥራቸውን በግልጽ ያይ ነበር ስለ ኃጢአታቸውም ንስሓ ይገቡ ዘንድ ይገሥጻቸው ነበር።
❤ ዜናው በንጉሥ ማርያኖስ ዘንድ ተሰማ ለእርሱም አንዲት ሴት ልጅ ብቻ ነበረችው ወደ ሆድዋም ከይሲ ገብቶ ለሞት ተቃረበች ከዚህም በኋላ ያድኗት ዘንድ ገንዘቡን ለባለ መድኃኒቶች ሰጠ ነገር ግን አልተቻላቸውም። ከዚህም በኋላ የጭፍራ አለቃው የባሪያውን ዐይን እንደ አዳነ የቅዱስ ዮሐንስ ዜና ነገረው ንጉሡም ጭፍራ ልኮ ወደርሱ ሊአስመጣው ወደደ ቅዱስ ዮሐንስም በመንፈስ ዐወቀ እርሱ ግን የመንገዱን ድካምና ባሕሩን ይፈራ ነበር ያን ጊዜም ደመና መጥታ ነጠቀችው ሰርመላስ ከሚባል አገርም ወደ አንጾኪያ ከተማ አደረሰችው። ንጉሡም ዐልጋ ላይ አቆመችው ንጉሡም ደነገጠ ቅዱስ ዮሐንስም "ወደዚህ ወዳንተ ልታስመጣኝ የተመኘኸው ምስኪን ሰው እኔ ነኝ" ብሎ ነገረው። "አሁንም ልጅህን አምጣት" አለው ልጁንም አመጣ። በላይዋም በጸለየ ጊዜ ከይሲው ሳያሳምማት ከሆድዋ ወጣ። ንጉሡም ከቤተ መንግሥቱ ሰዎች ሁሉ ጋር ከእርሱ ተባረኩ። እጅግም አደነቁ ለሚፈሩት ይህን ጸጋ የሚሰጥ የተመሰገነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ።
❤ እጅ መንሻውንም ብዙ ገንዘብ አቀረበለት እርሱ ግን ምንም አልወሰደም። ንጉሡም በእርሱ ዘንድ ሊያኖረው ወደደ ቅዱሱ ግን አልወደደም ንጉሡም እንዳይሔድበት ቀሚሱን ያዘ ያንጊዜም ንጉሡ ቀሚሱን እንደያዘ ደመና ነጥቆ ወሰደው ቀሚሱም ተቆርጦ በንጉሥ እጅ ላይ ቀረ ቅዱስ ዮሐንስም በዚያች ሰዓት ወደ አገሩ ደረሰ።
❤ ንጉሡም ቤተ ክርስቲያ ሠርቶ የቀሚሱን ቊራጭ በውስጧ አኖረ ቤተ ክርስቲያኒቱም እስከ ዛሬ ድረስ የፊቃር ቤተ ክርስቲያን ተባለች። የቊርባን ቅዳሴ በሚቀደስ ጊዜም ሥጋውንና ደሙን መቀበል የሚገባቸውንና የማይገባቸውን ጻድቃንና ኃጥአንን ያያቸዋል።
❤ ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ የጣዖትን አምልኮ በአቆ ጊዜ ለአባቱ ወንድም ልጅ ለስምዖንም ይህን አስረድቶት ወደ እስክንድርያ ከተማ ሔዱ በመኰንኑ ፊትም ቁመው ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ ጽኑዕ የሆነ ሥቃይም አሠቃያቸው ከዚህም በኋላ ራሶቻቸውን ሐምሌ 11 ቀን በሰይፍ አስቈረጣቸው የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ ከሥጋቸውም ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ ለበሽተኞችም ታላቅ ፈውስ ተገኘ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ዮሐንስና ስምዖን በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ትድረስን ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ገብርኤል፦ ይህም አባት ለእስክንድርያ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰባ ስምንተኛ ነው። የዚህም ቅዱስ ወላጆች እግዚአብሔር ሕግ የጸኑ ደጋጎች ፈቃዱንና ትእዛዙንም የሚፈጽሙ ነበሩ። ይህንንም ቅዱስ በወለዱት ጊዜ በፈሪሀ እግዚአብሔር አሳደጉት።
❤ በአንዲት ዕለትም ቅዱሳን መነኰሳት ወደርሱ መጡ ከውስጣቸውም መልካም ገድል ያለው አንድ አረጋዊ ነበረ። እርሱም ብዙዎች ኤጲስቆጶሳት ሕፃኑን ከበው እጃቸውን እንደሚጭኑበት እንደሚባርኩትና ይሁን ይሁን ይገባዋል እንደሚሉ ራእይን አየ።
❤ ሽማግሌውም ይህን ራእይ በአየ ጊዜ ሕፃኑ ታላቅ እንደሚሆን አሰበ ለአባቱም "ይህን ሕፃን አስተምረው ለብዙዎች ሕዝቦች አለቃ ይሆን ዘንድ አለውና" አለው። አባቱም ሰምቶ እግዚአብሔርን አመሰገነው "ከዚህ ሕፃን ምን ይደረግ ይሆን" አለ።
❤ ሕፃኑ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ፈቃድ አባቱ ዐረፈ። ብህና በሚባል አገርም በገድሉ የተደነቀ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ብሉያትንና ሐዲሳትንም የሚያውቅ የእናቱ ወንድም ስሙ ጴጥሮስ የሚባል ጴጲስቆጶስ ነበረ ሕፃኑንም ወስዶ አስተማረው ከተሰጠውም ጸጋና ዕውቀቱ የተነሣ ያዩት ሁሉ ያደንቁ ነበር ዲቁናም ተሾመ።
❤ ዐሥራ ሁለት ዓመትም በሆነው ጊዜ የምንኵስናን ልብስ ሊለብስ ወደደ ይህንም ኃላፊውን ዓለም ናቀ ኢጴጲስቆጶሱ አባ ጴጥሮስም በገድል ተጸምዶ ለሚኖር ለቀሲስ አባ ጴጥሮስ ሰጠው እርሱም በጥቂት ቀኖች የምንኵስናን ገድል አስተማረው ከእርሱም ብዙ ትሩፋቶች ታዩ።
❤ ከዚህም በኋላ መምህሩ ቀሲስ አባ ጴጥሮስ በአረፈ ጊዜ ከዚያ ተነሥቶ ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ሔደ በዚያም በጾምና በጸሎት በስግደት በመትጋት እየተጋደለጨ ያለ ማቋረጥ ብዙ ዘመናት ኖረ።
❤ ከዚህም በኋላ ወደ አስቄጥስ ገዳም ወደ አባ መቃርስ ደብር ሔደ። ደብረ ማርስ ባለች በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን አበምኔት አደረጉት። ሕንፃዋንም አደሰ።
ሁሉ መጽናኛ ይሆን ዘንድ ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉና ወደ ገዳማትም ላክሁ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛን በአባ ኪሮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ሚሳኤል፦ ይህም አባት አባ ኪሮስ የቀበረው የንጉሥ ልጅ ድኃ የነበረ ነው። ዜናውም እንዲህ ነው። አባ ኪሮስ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ሳት ገዳም ሔደ። ከዚያም ደርሶ ቤተ ክርስቲያኒቱን ተሳለማት በዚያም አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ሥዕል አየ። ከዐይኖቹም ዕንባ እያፈሰሰ "እመቤቴ ሆይ አስቢኝ" አላት ሥዕሊቱም "ኪሮስ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው ከዚህም አትለፍ የአባትህን ዐፅም ትጠብቅ ዘንድ ወደ ማደሪያህ ተመለስ እንጂ" አለችው። አባ ኪሮስም ይህን ሰምቶ ከሥዕሏ ፊት ሰባት መቶ ሰግደትን ሰገደ። በዕብራይስጥም ቋንቋ "እንግዳ ነህና በቃህ በምሕረት መዝገብም ተመዝግቦልሃል" የሚለውን ቃል ሰማ።
❤ ከዚያም በአለፈ ጊዜ መነኰሳቱ መልኩ የተዋበ ሁለመናውም ያማረ እንደሆነ ተመለከቱ። እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ "ይህ መነኵሴ ከመንግሥት ከተማ ከግብጽ አገር የመጣ ነው ሰውነቱ በጾምና በጸሎት አልጠወለገምና"። እጅግም ነቀፉት አልተቀበሉትም።ነገር ግን ወደ ሌላ ወደሚንቁት ቦታ ሰደዱት።
❤ በዚያም መስፈርስ በሚባል ሕማም ለብዙ ጊዜ የታመመና በምድር ላይ የተጣለ ድኃ ሰውን አገኘ። በራስጌውም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን በግርጌው ቅዱስ ገብርኤልን በቀኙም ቅዱስ ሩፋኤልን በግራውም ቅዱስ ሰዳካኤልን አየ። እነርሱም በክንፋቸው ጋርደውት ነበር ከሰውም ያለርሱ ያያቸው አልነበረም። "በገዳዩች ፊት ሞትን የማይፈራ ጐበዝ እንዴት ነህ" ብለው ሰላምታ ሰጡት። አባ ኪሮስም አደነቀ "በልዕልና ነዋሪዎች ሆይ ከዚህ ለምን ተቀመጣችሁ" አላቸው "ይህንን ድኃ እንድንጠብቀው ከእግዚአብሔር ታዘናል" አሉት አባ ኪሮስም "እስከ መቼ ነው" አላቸው። "ከዚህ ድካም እስከሚአሳርፈው ድረስ ነው" አሉት።
❤ ከዚህም በኋላ ወደ ታመመው ደኃ ተመልሶ "በዚህ ቦታ ከኖርህ ምን ያህል ዘመን ነው" አለው በሽተኛውም "ሠላሳ አምስት ዓመት ነው" አለው ሁለተኛም "ከታመምክ ስንት ዓመት ነው" አለው "ሃያ ዓመት ነው" ብሎ መለሰ። "አበ ምኔቱና የገዳሙ መነኰሳት ይጐበኙሃልን" ብሎ ጠየቀው በሽተኛውም "አባቴ ሆይ የለም አይጐበኙኝም ፊታቸውን ከአየሁ ዓሥራ አምስት ዓመት ይሆናል" ብሎ መለሰ።
❤ አባ ኪሮስም "ና ንገረኝ አባትህ ማነው እናትህስ ማናት" አለው በሽተኛውም እንዲህ ብሎ መለሰ "አባቴ የኬልቄዶን ንጉሥ እናቴም የራሕራሕ ንጉሥ ልጅ ናት። አባቴ ኪሮስ ሆይ እውነት እልሃለሁ በአባቴ ቤት ያሉ ሰዎች ወርቁንና ብሩን ቀጭኑንም ልብስ በእግሮቻቸው ይረግጡአቸዋል"። አባ ኪሮስም "ወደዚች ገዳም ማን አደረሰህ" አለው ድውዩም "እንዳንተ ያሉ ሁለት ሰዎች ወደ አባቴ ቤት መጥተው በዚያ አደሩ። እኩለ ሌሊትም ሲሆን ፊቱ ብሩህ የሆነ ሰውም ወደኔ መጣ "ሚሳኤል ብሎ ጠርቶ ሲነጋ ተነሥተህ ከእነዚህ ቅዱሳን ጋራ ሒድ" አለኝ በእንዲህ ያለ ሥራ ወጥቼ ወደዚህ ቦታ ደረስሁ ምንም በጎ ሥራ ሳልሠራም እንደ እነርሱ ሆንሁ"።
❤ አባ ኪሮስም "እኔ አጽናናሃለሁና ወንድሜ ሆይ ስማ ስሙ በብኑዳ የሚባል አንድ እጅግ ድኃ የሆነ በበረሃ የሚኖር መነኵሴ ነበረ። የበጎ ሥራ ጠላት ሰይጣን ወደርሱ መጥቶ አሳተው እግዚአብሔርም ሥጋውን ለአንበሳና ለሰማይ ወፎች ሰጠ እርሱም በወገን የከበረ ከሮም ንገሥ በታች የሚገዛ የኬፋዝ ንጉሥ ልጅ ነበረ"። ሁለተኛም እነግርሃለሁ "የሮሜ ንጉሥ ልጅ የሆነ አንድ ድኃ ነበረ። እርሱም ከበትር ብቻ በቀር ከአባቱ ቤት ምንም ሳይዝ በቀስታ ወጣ ያንንም ሰው እኔ እጅግ አውቀዋለሁ። ከገዳም ወደ ገዳም ከተራራም ወደ ተራራ ይዞር ነበር ሞቱንም አላስተዋልኩም ሕይወቱንም አላወቅሁም"።
❤ ዳግመኛም "አንድ የንጉሥ ልጅ ድኃ ነበረ። እርሱም በሰንበታት እነጂ በሌላ ቀን ምንም ሳይቀምስ ማቅ ለብሶ በቀንና በሌሊት ለጸሎት ይተጋ ነበር። በእንዲህ ያለ ሥራም ኑሮ አረፈ የብርሃን መላእክትም ነፍሱን ወስደው በመንግሥተ ሰማያት አኖሯት። አሁንም ወንድሜ የምነግርህን ስማ። የፈጣሪህ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አታድንቅ የወደደውን ይገሥጻልና" ያም በሽተኛ ድኃ መነኰስ "እውነት ነው ለእኔ ይገባኛል ስለ ኃጢአቴም ይህን ተቀበልሁ" ብሎ መለሰ። ይህንንም ብሎ ዝም አለ።
❤ በዚያች ሰዓትም ያን በሽተኛ በሞት ያሰናብተው ዘንድ አባ ኪሮስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በድንገት መጣ። እልፍ አእላፋት መላእክትም በዙሪያው ሆነው ከእርሱ ጋር ነበሩ ለጻድቃን ሞገሳቸውና ንጉሣቸው የሆነ አምላካችንን እናመስግነው ለችግረኞችም ተስፋ የሆነ አምላካችንን እናመስግነው እያሉ ይዘምሩ ነበር። በዚህ ዓለም በገድል የደከሙ በእርሱ ደስ ይላቸዋል።
❤ አባ ኪሮስም በአየ ጊዜ በምድር ላይ ሰግዶ "ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ ወደዚህ ምን አመጣህ" አለ ጌታችንም "ስለ ጠራኸኝ መጣሁ" አለው። አባ ኪሮስም "ይህ ሰው ፃዕር በዝቶበታልና ያርፍ ዘንድ አሰናብተው" አለው። ጌታችንም "ምን ያህል እንደምወድህ የመላእክት ሠራዊት ያዩና ያውቁ ዘንድ ይቺን የገነት ተክል አበባ ከእጄ ወስደህ በዚህ በሽተኛ በፊቱ ላይ ጣል" አለው። አባ ኪሮስም ያንን የገነት ተክል አበባ ከጌታችን እጅ ተቀብሎ በበሽተኛው ፊት ላይ አኖረ ያን ጊዜም ነፍሱ ያለ ፃዕር በፍጥነት ወጣች መድኃኒታችንም ተቀብሎ ሳማት ከእርሱም ጋር በብርሃን ሠረገላ ውስጥ አስቀመጣት አውጥቶም በሰማያዊ ክብር አኖራት።
❤ አባ ኪሮስም እያደነቀ አለቀሰ ከዚህም በኋላ ወደ አበምኔቱ ሔዶ "እነሆ ያ ድኃ ስለ አረፈ መቃብር ቆፍረው ይቀበሩት ዘንድ ከመነኰሳቱ እዘዝ" አለው አበ ምኔቱም "ምን ግዴታ አለብኝ" አለው አባ ኪሮስም ትኩር ብሎ ተመለከተውና "ይህ የሰይጣን ሥራ እንጂ የሰው ሥራ አይደለም" አለው። ሰለ አስጨነቀውም ሰባት መነኰሳትን አዘዘለት እነርሱም ማዕጠንታቸውን ይዘው ተነሡ አባ ኪሮስም "የሚአጥኑት አሉና የረከሱ ማዕጠንቶቻችሁን አስወግዱ። በቦታቸውም ተዉአቸው ነገር ግን ቅበሩት" ብሎ አማላቸው።
❤ ያን ጊዜም አራቱ የመላእክት አለቆች ሥጋውን በከርቤና በሚዓ አጠኑ መዓዛውም ያንን በዓት "መላው እነዚህ መነኰሳትም የሚያሸተን ምንድነው ይህመነኰስ ሥራይን ያውቅ ይሆን" ተባባሉ። ከዚህም በኋላ ሥጋውን ወስደው በዚያው ገዳም በእንግዳ መቃብር ቀበሩት ከመቃብሩም ጥሩ ውኃ ፈልቆ ለበሽተኞች ፈውስ ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛን በአባ ሚሳኤል በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 8 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለሚሳኤል ሶበ አዕረፈ እምተጽዕሮ። እደ ኪሮስ ድኅረ ቀበሮ። ለእለ መነንዎ ቅድመ ወኢሐወጹ ማኅደሮ። ያቅልል ለክሙ ይቤሎሙ ለጌጋይክሙ ፆሮ። እስመ በግፍዕክሙ ቦእኩ ለክርስቶስ ሀገሮ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_8።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤
❤ #ሐምሌ_፰ (8) ቀን።
❤ እንኳን #ጌታችን_በአረጀ_መነኲሴ አምሳል ለተገለጸላቸ በጀርባቸው ላዘሉት የሚነድ መለኮት በከንፈራቸው ለሳሙ ለአባታችን #ለአቡነ_ኪሮስ ለዓመታዊ ለዕረፍታቸው በዓላቸው፣ አባ ኪሮስ ለቀበረው ለንጉሥ ልጅ ድኃ ለነበረው #ለአባ_ሚሳኤል ለዕረፍት መታሰቢያ በዓልእግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #አቡነ_ኪሮስ፦ ይህም ቅዱስ የታላቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ወንድሙ ነበር በከተማ ውስጥ የሚሠራውን ዐመፅ በአየ ጊዜ ገንዘቡን ሁሉ ትቶ ከሀገሩ ወጣ። ጌታቸንም መርቶ ወደዚች ምዕራባዊት በረሀ አደረሰው በውስጧም ብዙ ዘመናት ብቻውን ኖረ ከሰው ማንም አላየውም በዚህ ሁሉ ዘመን የዱር አራዊትም ቢሆኑ።
❤ በአስቄጥስም ገዳም ስሙ አባ ባውማ የሚባል አንድ ቄስ ነበረ እርሱም የንጉሥ ዘይኑን ልጅ ቅድስት ኢላርያን ሥጋዋን የገነዘ ነው። እርሱም እንዲህ አለ በቤተ ክርስቲያን ወስጥ እያለሁ "አባ ባውማ ሆይ ተነሥ ወደ በረሀው ውስጥ ገብተህ ወደ ፀሐይ መግቢያ ሒድ ከቅዱሳን ሁሉ አብዝቶ ፈቃዴን የፈጸመውን የአንድ ገዳማዊ ሥጋ ትገንዝ ዘንድ የሚለኝን ቃል ከሰማይ ሰማሁ"። ያን ጊዜም ደስ ብሎኝ ተነሣሁ በበረሀውም ውስጥ ሦስት ቀን ተጉዤ ከአንድ ገዳማዊ በዓት ደርሼ ደጁን አንኳኳሁ አንድ ሽማግሌ ገዳማዊም ከፈተልኝና እርስ በርሳችን ሰላምታ ተለዋወጥን "በዚች በረሀ ሌላ ገዳማዊ አለን?" ብዬ ጠየቅሁት "አዎን" አለኝ። ሁለተኛም "ስምህ ማነው አባቴ ሆይ በዚችስ በረሀ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ኖርክ አልሁት" "ስሜ ስምዖን ነው በዚች በረሀ የኖርኩትም ሰባ ዓመታት ነው" አለኝ።
❤ ከእርሱ ዘንድም ወጥቼ ሦስት ቀን ተጓዝኩ ሁለተኛም ስሙ ባሞን የሚባል ገዳማዊ አገኘሁ ሰላምታም ሰጠሁትና "በዚች በረሀ ሌላ ገዳማዊ አለን?" አልሁት "አዎን አለ" አለኝ። አራት ቀንም ተጓዝኩ ወደ አባ ኪሮስ በዓት ደረስኩ "ቅዱስ አባት ሆይ ባርከኝ" እያልኩ ደጁን አንኳኳሁ "አባ ባውማ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው" ብሎ ከውስጥ ተናገረኝ። "እግዚአብሔር ያከበረህ ሰው በሰላም በፍቅር ወደእኔ ግባ" አለኝ ያን ጊዜ ገብቼ ከእርሱ ተባረክሁ በፊቱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ክብር አየሁ የራሱ ጠጉርና ጽሕሙ እንደ በረድ የነጣ ነበር።
❤ ከዚህም በኋላ ተቀመጥሁ በብብቻውም አቀፈኝ እንዲህም አለኝ "እነሆ ይችን ሰዓት እየጠበቅኋት በዚች በዓት ሃምሳ ሰባት ዓመት ኖርኩ" ይህንንም ሲል ጥቂት ታመመና ተኛ እየደነገጠ ያቺን ሌሊት አደረ ሲነጋም በበዓቱ ውስጥ ታላቅ ብርሃን በራ ብርሃናዊ ሰውም ገባ በእጁም የብርሃን መስቀል አለ በአባ ኪሮስ አጠገብም ተቀምጦ ሳመዉ ባረከውም አጽናናው ሰላምን ፍቅርን አንድነትን አደረገለት ከእርሱም ተሠወረ እኔም ፈራሁ "እንዲህ የሚበራ ይህን ክብር የተጐናጸፈ ይህ ማነው" አልሁት።
❤ እርሱም "ልጄ ሆይ ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ልማዱ ስለ ሆነ ሁልጊዜ ይመጣል ያጽናናኛልም" አለኝ። "በቀዳሚት ሰንበት ዕለትም ዘጠኝ ሰዓት በሆነ ጊዜ እስከ ሰማይ የሚደርስ ታላቅ ጩኸትን ሰማሁ ከጩኸታቸውም ኃይል የተነሣ ምድር ተናወጸች። እኔም "ይህ የምሰማው ጩኸት ምንድነው ብዬ ጠየቅሁት እርሱም ልጄ ሆይ ይህ በሲኦል የሚኖሩ የኃጥአን ጩኸት ነው ስለ ቅድስት ትንሣኤው የእሑድ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ እግዚአብሔር ያሳርፋቸዋልና ስለዚህም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል" አለኝ"። በዚችም ዕለት ሐምሌ ሰባት ቀን ቅዱስ አባ ኪሮስ ጩኾ አለቀሰ ዛሬ "በግብጽ አገር ታላቅ ምሰሶ ወደቀ ይኸውም የገዳማውያን አለቃ ቅዱስ አባ ሲኖዳ ነው" አለ።
❤ ከዚህም በኋላ ከደዌው ጽናት የተነሣ እሑድ ሌሊት እጅግ ደነገጠ በበዓቱም ውስጥ እነሆ ታላቅ ብርሃን በራ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ገብቶ በአባ ኪሮስ ራስ አጠገብ ተቀመጠ። አባ ኪሮስም መድኃኒታችንን "ጌታዬ ሆይ ይህን ሰው ባርከው" አለው መድኃኒታችንም "የመረጥሁህ አባ ባውማ ሆይ ጽና አትፍራም ሰላሜ በረከቴም ከአንተ ጋራ ይኑር። አሁንም ታማኝ አገልጋዬ የሆነ የዚህን የቅዱስ ኪሮስን ያየኸውንና የሰማኸውን ወደፊትም ዳግመኛ የምታየውንና የምትሰማውን ገድሉን ጻፍ" አለኝ።
❤ ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን አባ ኪሮስን እንዲህ አለው "እነሆ አንተ ትሞታለህና አትዘን ሞትህ ሞት አይደለም የዘላለም ሕይወት ነው እንጂ። የገድልህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውን የሚሰማውንም ሁሉ በምድርም መታሰቢያህን የሚያደርገውን ሁሉ በደብረ ጽዮን በሚደረገው የሽህ ዓመት በዓል ምሳ ከእኔ ጋር ይቀመጥ ዘንድ አደርገዋለሁ ከቅዱሳኖቼም ጋራ እቆጥረዋለሁ። የኃጢአቱንም መጽሐፍ ቀድጄ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ። ለመሥዋዕት የሚገባውንም ዕጣኑንና ወይኑን መብራቱንም መባ አድርጎ ለሚሰጥም በስምህም ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋትን ለሚያደርግ ዓይን ያላየውን ጆሮም ያልሰማውን በሰው ልቡናም ያልታሰበውን በጎ ዋጋ እኔ እጥፍ ድርብ አድርጌ እሰጠዋለሁ። በበኵር ቤተ ክርስቲያንም ሥጋዬንና ደሜን አቀብላቸዋለሁ በዚህም ዓለም ቤታቸውን እባርካለሁ። ልጆቻቸውን አሳድጋለሁ ከበጎ ነገር ሁሉ ምንም ምን አያጡም። አሁንም ከዚህ ዓለም ድካም ወደ ዕረፍት የዘላለም ተድላ ደስታ ወዳለበት ወደ ብርሃን ቦታ እወስድህ ዘንድ ጊዜው ደረሰ" መድኃኒታችንም ይህን ሲናገር እነሆ ነቢዩና ዘማሪው ዳዊት መጣ መሰንቆውም ከእርሱ ጋራ ነበረች። "ይቺ ዕለት በእርሷ ፈጽሞ ሐሤት እናደርግ ዘንድ እግዚአብሔር የሠራት ናት" እያለ አመሰገነባት።
❤ መድኃኒታችንም አባ ኪሮስን "እነሆ ዘማሪው ዳዊት መጥቷልና ይዘምርልህ ዘንድ የምትሻውን ንገር" አለው። ዳዊትም ቅዱስ አባ ኪሮስን "በየትኛው አውታር እንድዘምርልህ ትሻለህ ደግሞስ በየትኛው ዜማ በየትኛው ስልት በመጀመሪያው ነውን ወይስ በሁለተኛው ወይስ በሦስተኛው" አለው። ቅዱስ አባ "ኪሮስም በዐሥሩም አውታር በየስልታቸውና በየዜማቸው ልሰማ እሻለሁ" አለ። ያን ጊዜ ዳዊት መሰንቆውን አዘጋጅቶ "የጻድቅ ሞቱ በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው" አለ ዳግመኛም "ጐለመስሁ አረጀሁም የሚወድቅ ጻድቅን አላየሁም" አለ። ዳዊትም ድምፁን አሣምሮ ዘመረ መሰንቆውንም በስልት መታት። ያን ጊዜም የቅዱስ አባ ኪሮስ ነፍሱ ወጣች ኃኒታችንም ተቀብሎ ሳማት ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤልም ሰጣት።
❤ እኔ አባ ባውማም የቅዱስ አባ ኪሮስን ሥጋውን ቀበርኩ ከበዓቱም በወጣሁ ጊዜ በረሀው በሰማይ ሠራዊት ተመልቶ አየሁ መድኃኒታችንም የቅዱስ አባ ኪሮስ ሥጋው ባለበት በዓት ላይ መስቀሉን አኑሮ ዘጋት። ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን ለኔ ሰላምታ ሰጥቶኝ መላእክትና የመላእክት አለቆች በፊቱ እያመሰገኑና እየዘመሩ በታላቅ ክብር ዐረገ። የቅዱስ አባ ኪሮስን ነፍስ ከመድኃኒታችን ጋራ እንደዚህ አሳረጓት። እርሷም በተሰጣት ክብር ደስ እያላት ዐረገች።
❤ እኔም አባ ባውማ በዚያ ቦታ ብቻዬን ቀረሁ ተመልሼም ወደ አባ አሞን በዓት ደረስሁ። ከዚያም የሦስት ቀን መንገድ ተጉዤ ወደ አባ ስምዖን በዓት ደረስሁ። ከዚያም ሦስት ቀን ተጉዤ ወደ ቦታዬ ወደ አስቄጥስ ገዳም ደረስሁ። ለመነኰሳቱም ሁሉ ያየሁትንና የሰማሁትን ሁሉ የቅዱስ አባ ኪሮስን ገድሉን ስለ አባ ሲኖዳም ዕረፍት ትንቢት እንደ ተናገረ ነገርኋቸው። መነኰሳቱም ሰምተው እጅግ አደነቁ የተመሰገነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት። እኔ አባ ባውማም የቅዱስ አባ ኪሮስን ገድሉን ጽፌ ለሚያነበውና ለሚሰማው
❤ ከዚህ በኋላ ወደ እስክንድርያ ከተማ ላከው ክብር ይግባውና ጌታችንም ተገልጾለት አጽናናው ከዚህም በኋላ በወህኒ ቤት ጨመሩት በዚያም ተአምራትን አደረገ። ጋኔን ያደረባት የአቅፋሃስ ሀገር ሰው የዮልያኖስ እኅት ነበረች ቅዱስ ቢማም ያንን ጋኔን ከእርሷ ላይ አወጣውና አሳደደው ዜናውም በሀገሩ ውስጥ በተሰማ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ብዙዎች አመኑ።
❤ መኰንኑም በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይም አሠቃየው በመንኰራኵርም የእጆቹንና የእግሮቹን ጥፍሮች አወለቁ በእሳትበአጋሉት በብረት ሰንሰለትም አሥረው ጐተቱት። በውሽባ ቤት ማንደጃ ውስጥም ጣሉት ከዚህም ጌታችን አዳነው። ከዚህም በኋላ በአንገቱ ታላቅ ደንጊያ አንጠልጥለው በባሕር ውስጥ ጣሉት አሁንም ጌታችን አዳነው። ሁለተኛም ከእሳት ጨመሩት። ከዚህም ጌታችን አዳነው በእሳቱም መካከል እየጸለየ ቆመ።
❤ መኰንኑም ማሠቃየቱን በሰለቸ ጊዜ ወደ ላይኛው ግብጽ ሰደደው በዚያም ያሠቃዩት ጀመሩ ዘቅዝቀውም ሰቀሉት ከዚህም በኋላ በብረት ምጣድ ውስጥ ጨምረዉ በላዩ እሳትን አነደዱበት ጌታችንም ተገለጠለትና ከእሳቱ አዳነው። ከዚህም በኋላ ጌታችን ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ገድሉን ለሚጽፍ በስሙም ምጽዋት ለሚያደርግ ሁሉ የዘለላም ሕይወትን ያድለው ዘንድ ቃል ኪዳንን ሰጠው።
❤ መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንደ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማይ ተቀበለ። የአቅፋሃስ ከተማ ሹም የሆነ የዮልዮስ ባሮችም ሥጋውን አንሥተው ወደ ሀገሩ ወሰዱት እስከ ስደቱ ዘመን ፍጻሜ ድረስም በመልካም ቦታ አኖሩት። ከዚህም በኋላ መልካም የሆነች ቤተ ክርስቲያንንና ገዳምን ሠሩለት ሥጋውንም በውስጧ አኖሩ ከእርሱም ታላላቅ ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ በሽተኞችም ሁሉ ይፈወሱ ነበርና። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ በአባ ቢማ ጸሎት ይማረን በረከቱ ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 8 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ዮም አመ ሰማዕክሙ ቃሎ። ኢታጽንዑ ልበክሙ። ከመ አመ አምረርው በገዳም"። መዝ 94፥8-9። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 9፥8-16።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር። እግዚኦ አነ ገብርከ። ገብርከ ወልደ አመትከ"። መዝ 115፥15-16። የሚነበቡት መልዕክታት ኤፌ 6፥10-19፣ 1ኛ ጴጥ 3፥10-15 እና የሐዋ ሥራ 26፥12-19። የሚነበበው ወንጌል ማር4፥1-24። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የአባቶቻች የአባ ኪሮስና አባ ብሶይ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ የበርበር ሰዎችም ወደ አስቄጥስ ገዳም በመጡ ጊዜ ወደ እንዴናው ገዳም ሔዶ በዚያ ተቀመጠ ከዚህም በኋላ ሐምሌ 8 ዐረፈ። የመከራውም ወራት ጸጥ ባለ ጊዜ የቅዱስ አባ ብሶይን ሥጋ ከቅዱስ አባ ቡላ ሥጋ ጋር በአንድነት ወደ አስቄጥስ ገዳም አመጡ። ከሥጋውም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ ዘመኑ አምሳ ሰባት ነበር። በአስቄጥስም ገዳም እየተጋደለ ሀያ ሰባት ዓመት ኖረ። በእንዴናው ገዳም ዐሥር ዓመት ኖረ ከመመንኰሱም በፊት በዓለም ውስጥ ሃያ ዓመት ተቀመጠ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ብሶይ በጸሎቱ ይማረን በረከቱ ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅዱሳን_አቤሮንና_አቶም፦ እነዚህ ከእስክንድርያ ከተማና ከገምኑዲ የሆኑ ናቸው። የእሊህም ቅዱሳን ወላጆቻቸው እግዚአብሔርን የሚፈሩ ምእመናን ነበሩ። ብዙ ምጽዋትንም ይሰጡ ነበር። የአባታቸውም ስም ዮሐንስ የእናታቸው ማርያም ነበር። አባታቸው በአረፈ ጊዜ የአቤሮን ዕድሜ ሠላሳ የአቶምም ዕድሜ ሃያ ሰባት ዓመት ነበረ። በቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም የተፀመዱ ነበሩ የሚራሩም ነበሩ መጻተኞችንም በፍቅር ይቀበሏቸው ነበር በትሩፋት ሁሉና በበጎ ሥራ ፍጹማን ነበሩ።
❤ ፈርማ በሚባል አገር ብዙ ሰዎች በሰማዕትነት በሞቱ ጊዜ እሊህ ቅዱሳን ገንዘባቸውን ይዘው ለንግድ ወደ ፈርማ ሔዱ። የንጉሥ ጭፍሮችንም አገኟቸው ከእርሳቸውም ጋራ የሰማዕቱ የቅዱስ አንያኖስ ሥጋ ነበረ ለጭፍሮችም ብዙ ገንዘብ ሰጥተው ከጭፍሮች እጅ ወደ ቤታቸው ወሰዱት ከከበረ ደንጊያ በተሠራ ሣጥን ውስጥም አኖሩት በፊቱም ሁል ጊዜ የሚበራ መብራትን አኖሩ። ከሥጋውም ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ። በዚያን ጊዜም እሊህ ቅዱሳን ስለዚህ ስለ ኃላፊው ዓለም ፍጻሜና በመንግሥተ ሰማያት ስላለው ዘለዓለማዊ የተድላ ደስታ ኑሮ አሰቡ። ከዚህም በኋላ ተስማምተው ወደ እስክንድርያ ከተማ ሔዱ በመኰንኑም ፊት ቁመው ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ መኰንኑም ከእሳት እንዲጨምሩአቸውና ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ ደማቸው እስኪፈስ ድረስ እንዲገርፉአቸው አዘዘ።
❤ ዳግመኛም ስለታምና ረጃጅም በሆኑ ችንካሮች ሥጋቸውን ቸንክረው ከታች እሳትን አነደዱባቸው ጌታችንም መልአኩን ልኮ ከእሳቱ አዳናቸው። እንደገናም በታላቅ ዛፍ ላይ ዘቅዝቀው ይሰቅሏቸው ዘንድ አዘዘ። ከአፍንጫቸውና ከአፋቸው ብዙ ደም ወረደ ጌታችን ፈጣሪያችንም ከመላእክቱ ጋራ ወርዶ አዳናቸው መኰንኑም በፊቱ በቆሙ ጊዜ ከጽናታቸው የተነሣ እጅግ አደነቀ።
❤ ከዚህም በኋላ ወደ ሀገረ ፈርማ ላካቸው መኰንኑም "ለአማልክት ዕጣን አጢሱ" አላቸው እምቢ በአሉትም ጊዜ ከኮምጣጤና ከሙጫ ጋራ ጨው ደባልቆ አፍልቶ በአፋቸውና በአፍንጫቸው ጨመረ እነርሱም ይህን ሁሉ ሥቃይ ታገሡ። ከዚህም በኋላ በብረት አልጋ ላይ አስተኝተው ከታች እሳትን አነደዱባቸው የእጆቻቸውንና የእግሮቻቸውንም ጥፍሮች አወለቁ በብረት በትሮችም አጽንተው መቷቸው። በዚያን ጊዜም የመኰንኑ ሚስት ሞተች እርሱም ደንግጦ ይቅር እንዲሉት ሚስቱንም እንዲአስነሡለት ቅዱሳኑን ለመናቸው። እነርሱም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመኑት ያን ጊዜም ተነሣች መኰንኑም ከሕዝቡ ሁሉ ጋራ በጌታችን አመነ ቅዱሳኑንም ወደ ሀገራቸው ይሔዱ ዘንድ ለቀቃቸው። ወደ ሀገራቸው ወደ ገምኑዲም በደረሱ ጊዜ የቀረ ገንዘባቸውን ለድኆችና ለችግረኞች ሰጡ የቅዱስ አንያኖስንም ሥጋ ስሙ ሰረባሞን ለሚባል አንድ ጻድቅ ሰው አደራ አስጠበቁት እንደቀድሞውም በፊቱ መብራትን እንዲአበራ አዘዙት።
❤ ከዚህም በኋላ በርሙን ወደሚባል አገር ሔደው በመኰንኑ ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ። መኰንኑም እንዲገርፉአቸውና እንዲጐትቱአቸው አዘዘ ደማቸውም እንደ ውኃ ፈሰሰ ደንቆሮና ዲዳ የሆነች ሴትም መጥታ ከቅዱሳኑ ደም ወስዳ አፏንና ጆሮዎቿን ልቧንም ቀባች ወዲያውኑም ድና ተናገረች ሰማችም። መኰንኑ ግን አሠራቸው ከዚህም በኋላ እነርሱን ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጡአቸው። ሐምሌ 8 ቀን የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበሉ። በዚያም ከገምኑዲ አገር ሰረባሞንና ሌሎች ሰዎችም ነበሩ በበፍታና በከበሩ ልብሶች ገነዙአቸው መዓዛው ጣፋጭ በሆነ ሽቱም ቀቡአቸው ወደ አገራቸው ወደ ገምኑዲም ወሰዱአቸው።
❤ ከገምኑዲም ከተማ ውጭ በደረሱ ጊዜ ሥጋቸው የተጫነበትን ሠረገላ የሚስቡ እንስሶች ቆሙ። "ሥጋችን በውስጡ ይኖር ዘንድ እግዚአብሔር የመረጠው ቦታ ይህ ነው" የሚል ቃልን ከሰማይ ሰሙ በዚያም አኖሩአቸው። ከዚህም በኋላ ቤተ ክርስቲያን ሠሩላቸው ሥጋቸውንም ከቅዱስ አንያኖስ ሥጋ ጋር በውስጥዋ አኖሩ በገምኑዲ አገርም ድንቆችንና ተአምራቶችን እያሳዩ እስከ ዛሬ ድረስ አሉ።
❤ ለእኒህ ቅዱሳንም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስማቸውን ለሚጠራ መታሰቢያቸውንም እንደችሎታው ለሚያደርግ ኃጢአቱ ይሠረይለታል ሥቃይንም ከቶ አያይም ብሎ መከራ በሚቀበሉበት ጊዜ ቃል ኪዳን ሰጣቸው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት አቤሮንና አቶም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸው ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_በላኒ፦ ይህም ከግብጽ ደቡብ አካ በሚባል አውራጃ ባራ በምትባል መንደር ይኖር የነበረ ነው። ይህም ቅዱስ ቄስ ነበር። የምእመናንን መከራቸውን የሰማዕታትንም መገደላቸውን በሰማ ጊዜ ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጥቶ ወደ እንዴናው ከተማ ሔደ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በመኰንኑ ፊት ታመነ መኰንኑም ጽኑ የሆነ ሥቃይን ብዙ ቀን አሠቃየው ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀዳጀ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ በላኒ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ቢማ፦ ይህም አባት በግብጽ ከብህንሳ ከተማ ነው ይህም ሰው ባለጸጋና በጎ የሚሠራ ድኆችንም የሚወድ በሀገርም ላይ የተሾመ ነበር። በአንዲት ዕለትም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በራእይ ፊቱ ከፀሐይ ብርሃን እጅግ እየበራ አየው እንዲህም አለው "ሰላም ለአንተ ይሁን ወደ መኰንኑም ሒደህ በስሜ ታመን። እኔ የክብር አክሊልን አዘጋጅቼልሃለሁና"። ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ተነሥቶ ገንዘቡን ለድኆችና ለችግረኞች ሰጠ። ከዚህም በኋላ ጸሎት አድርጎ ከቤቱ ወጣ ሉቅያኖስ ወደሚባል መኰንንም ሒዶ በፊቱ ቁሞ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ።
❤ መኰንኑም በአየው ጊዜ ሹም እንደሆነ አውቆ ከእርሱ ንዋየ ቅድሳትን ፈለገ ዳግመኛም ለአማልክት እንዲሠዋ ፈለገ ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት "ስለ ንዋየ ቅድሳት ከእኔ ልትሻ አይገባህም የረከሱ አማልክትንም ስለማምለክ ትእዛዝህን አልሰማም እኔ ሰማይንና ምድርን በውስጣቸው ያለውን ሁሉ የፈጠረ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አመልከዋለሁና"። መኰንኑም ይህን በሰማ ጊዜ ተቆጥቶ ምላሱን ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ጌታችንም እንደ ቀድሞው ምላሱን መለሰለት። ከዚህ በኋላ በማበራያ ውስጥ አበራዩት በብረት ዐልጋ ላይም ቸንክረው በበታቹ እሳትን አነደዱ እግዚአብሔርም አዳነው ያለ ጉዳትም አስነሣው።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤
❤ #ሐምሌ_፰ (8) ቀን።
❤ እንኳን #ለዓለም_ሁሉ_ኮከብ ለሆነኑ #የጌታችን_እግር_ላጠቡ ለቅዱስ አባት #ለአባ_ብሶይ_ለዕረፍት_በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን በስክሳሩ ከሚታሰቡ፦ #ከግብጽ_ደቡብ አካ በሚባል አውራጃ ባራ በምትባል መንደር ይኖር ከነበረው ከቅዱስ ሰማዕት #ከአባ_በላኒ_ዕረፍት፣ በሰማዕትነት ከዐረፋ ከእስክድርያ ከተማና ከገምኑዲ ከሆኑ #ከቅዱሳን_አቤሮንና_አቶም፣ በሰማዕትነት ከዕረፈው ከላይኛው ግብጽ ከብህንሳ ከተማ ከሆነ #ከአባ_ቢማና ቁጥራቻው #ዐሥራ_አምስት ከሚሆኑ #ከአባ_ኖብ_ጋር_በሰማዕትነት_ከዐረፋ ከመታሰቢያቸው ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ብሶይ፦ ይህም አባት በጎ ስም አጠራር ያለው የአባ መቃርስ ገዳምና የዓለም ሁሉ ኮከብ የሆነው ታላቅ አባት ነው። ይህም ቅዱስ ከግብጽ አገር ስሟ ሰነስ ከምትባል አገር ነበር ሰባት ወንድሞችም ነበሩት እናቱም የእግዚአብሔር መልአክ እግዚአብሔር ያገለግለኝ ዘንድ ከሰባቱ ልጆችሽ አንዱን ስጪኝ ብሎሻል እያለ እንደሚያነጋግራት ራዕይን አየች። እርሷም "ጌታዬ ሆይ የወደድከውን ውሰድ ሁሉም ገንዘቦቹ ናቸውና" አለችው። መልአኩም እጁን ዘርግቶ የብሶይን ራስ ይዞ "ለእግዚአብሔር መልካም ሥራ የሚሠራ ይህ ልጅ ነው" አለ። ይህ ብሶይ የከሳና ሥጋው የኮሰሰ ነበርና እናቱ ለዚያ መልአክ "ጌታዬ ሆይ እግዚአብሔርን የሚያገለግል ከእነዚህ አንዱን ጠንካራውን ውሰድ" አለችው። መልአኩም "እግዚአብሔር የመረጠው ይህ ነው" አላት። ከዚህም በኋላ ከእርሷ ተሠወረ።
❤ በአደገም ጊዜ የምንኵስና ልብስ ሊለብስ ወደደ። ወደ አስቄጥስም ገዳም ሔደ በአባ ባይሞይ ዘንድም መነኰሰ እርሱም አባ ዮሐንስ ሐፂርን ያመነኰሰ ነው። ከዚህም በኋላ እጅግ ጽኑ የሆነ ተጋድሎን መጋደል ጀመረ ምንም ምን ሳይቀምስ አርባ ቀን እስከ መጨረሻው ሦስት ጊዜ ጾመ። በቀንና በሌሊት በጾምና በጸሎት እየተጋ ቅዱሳት መጻሕፍትን አዘውትሮ በማንበብ በመጻሕፍት ቃል ነፍሱን ያረካት ነበር። የእግዚአብሔርን ቃል እጅግ ይወድ ነበርና ከማር ከስኳርም እጅግ ይጥመው ነበርና በውኃ ዳርም እንዳለች ተክል ሆነ። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ያየው ዘንድ የተገባው ሆኖ ነበር ጌታችንም ብዙ ጊዜ ይገለጽለት ነበር። ከእርሱም ጋራ ይነጋገር ነበር። እርሱም እግሩን አጥቦ እጣቢውን ይጠጣው ነበር።
❤ በአንዲት ቀንም የመድኃኒታችንን እግሮቹን አጥቦ ግማሹን ጠጥቶ ግማሹን ለደቀ መዝሙሩ እንዲጠጣ ተወለት። ረድኡም በመጣ ጊዜ "ልጄ ሆይ ተነሥና በኵስኵስቱ ውስጥ ካለው ውኃ ጠጣ" አለው ረድኡም በልቡ "በመቅጃው ውስጥ ካለው ከጥሩው ውኃ ለምን አይሰጠኝም" አለ። ይህንም ብሎ ቸለል አለ። መምህሩ እንዳዘዘውም አልጠጣም ሁለተኛም "ልጄ ሆይ ተነሥና ከኵስኵስቱ ያለውን ያንን ውኃ ጠጣ" አለው። ግድ ጠጣ ባለውም ጊዜ ተነስቶ ወደኵስኵስቱ ሔደ። ነገር ግን ውኃ አላገኘም አባ ብሶይም የጌታችንን እግር እንዳጠበና ግማሹን ጠጥቶ ግማሹን እንዲጠጣ ለእርሱ እንደተወለት አስረዳው። በነገረውም ጊዜ እጅግ አዘነ ፍጹም ድንጋፄም ደነገጠ።
❤ አባ ብሶይም ረድኡን ራሱን እብድ አስመስሎ ወደሚኖር ወደ አንድ ጻድቅ ሰው ዘንድ ላከው እርሱም አረጋግቶ ወደ አባቱ ወደ አባ ብሶይ መለሰው። ድንጋጤውም ባልተወው ጊዜ ወደዚያ ጻድቅ ሰው ዳግመኛ ላከው በሔደም ጊዜ ሙቶ አገኘው አባ ብሶይም ለረድኡ "ይህን በትሬን በላዩ አኑርና ተነሥተህ እንድታነጋግረኝ አባቴ አዞሃል በለው" አለው ሔዶም የአባ ብሶይን በትር በዚያ ጻድቅ በድን ላይ አኖረ ወዲያውኑም ተነሥቶ "ስማ ለአባትህም ታዘዝ ታዛዥ ብትሆን ይህ ድንጋጤ ባላገኘህም ነበር" አለው ይህንንም ብሎ ተመልሶ ተኛ።
❤ በአንዲት ቀንም ከቅዱስ አባ ብሶይ ደቀ መዛሙርት አንዱ መጣ ወደ እርሱም ከመግባቱ በፊት ከሰው ጋራ ሲነጋገር ሰማው በገባ ጊዜም ከሰው ማንንም አላገኘም "አባቴ ሆይ ከአንተ ጋራ ሲነጋገር የነበረ ማን ነው?" ብሎ ጠየቀው አባ ብሶይም እንዲህ ብሎ መለሰለት "ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ወደኔ መጥቶ ይህ ታላቅ ክብር ለመነኰሳት እንዳላቸው አውቄ ቢሆን ኖሮ መንግሥቴን ትቼ መነኰስ በሆንኩ ነበር" አለኝ እኔም "ምን ጐደለብህ የጣዖትን አምልኮ አስወግደህ የቀናች ሃይማኖትን ሥልጣን አጽንተሃልና አልሁት"። እርሱም መልሶ እንዲህ አለኝ "እግዚአብሔር ይመስገን ክብርንስ እጅግ አብዝቶ ሰጥቶኛል ነገር ግን የመነኰሳትን ክብር ያህል አይሆንም እነርሱ በእሳት ክንፎች እየበረሩ ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ሲገቡ አይቻቸዋለሁና" አለኝ። እኔም እንዲህ አልሁት "የእግዚአብሔር ፍርድ በእውነት ትክክል ነው ለእናንተ ቤቶች፣ ሚስቶችና ልጆች፣ ሀብትና ለዓለም የተዘጋጀው ሁሉ አሉአችሁ በእነርሱም ትጽናናላችሁ። መነኰሳት ግን ከዚህ ከተድላ ዓለም የተለዩና በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ችግረኞች ናቸው ስለዚህም ይህን ታላቅ ክብር እግዚአብሔር ሰጣቸው" አልሁት።
❤ በአንዲት ዕለትም እግዚአብሔር አባ ብሶይን እንዲህ ብሎ ተናገረው "ይህን ገዳም እንደርግቦች ማደሪያ አደርገዋለሁ። በውስጡም መነኰሳትን እመላለሁ"። ቅዱስ አባ ብሶይም "ጌታዬ ፈጣሪዬ ሆይ የበዙ ከሆነ ምግባቸውን ከወዴት ያገኛሉ" አለው። ክብር ይግባውና ጌታችንም "እኔ አስብላቸዋለሁ ምንም ምን እንዲአጡ አልተዋቸውም" አለው።
❤ በአገረ እንዴናው ስለሚኖር ስለ አንድ ገዳማዊ ሽማግሌ ተነገረ በትምህርቱ አምነው ወደ ርሱ ብዙ ሕዝቦች ተሰበሰቡ እርሱ "መንፈስ ቅዱስ የለም" ብሎ ተሳስቶ ነበርና። ብዙዎችም ተከትለውት ነበርና ቅዱስ አባ ብሶይም ይህን ነገር ሰምቶ ስለዚያ ገዳማዊ እጅግ አዘነ መስሚያውንም ሦስት ጆሮዎች አድርጎ ወደ ገዳመ እንዴናው ሔደ ከዚያ ገዳማዊ ሽማግሌ ጋራ ተገናኘ ብዙ ሕዝቦችንም በእርሱ ዘንድ አገኛቸው ሁሉም ለቅዱስ አባ ብሶይ ሰላምታ ሰጡት። መስሚያ ስለአደረጋቸው ስለ ሦስቱ ጆሮዎችም ጠየቁት እንዲህም አላቸው። "ለእኔ ልዩ ሦስት አካላት አሉኝ ሥራዬ ሁሉ በእነርሱ አምሳል ነው" "በውኑ መንፈስ ቅዱስ አለን?" አሉት። ከብሉይና ከሐዲስ መጻሕፍትም ይተረጒምላቸው ጀመረ። ከሦስቱ አካላት አንዱ መንፈስ ቅዱስ እንደ ሆነ በመለኮትም አንድ እንደ ሆነ አብራራላቸው። ሁሉም ከስሕተት ተመልሰው ንስሓ ገቡ። ወደ ቀናች ሃይማኖትም ተመለሱ።
❤ ለአባ ብሶይም የዋህ ረድእ ነበረው የእጅ ሥራውንም ሊሸጥ በሔደ ጊዜ ከአሕዛብ ወገን አንድ ሰው አገኘ። ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የፅርፈት ቃልን እስከሚናገር ድረስ ከዕውነት መንገድ አሳሳተው። በተመለሰ ጊዜም በክርስትና ጥምቀት ያገኘው የልጅነት ክብር ከእርሱ እንደተለየው አባ ብሶይ ተመልክቶ "ልጄ ሆይ በአንተ ላይ የደረሰው ምንድነው?" አለው። እርሱም ያ ሽማግሌ እንዳሳተው ነገረው አባ ብሶይም ስለርሱ ሰባት ቀን ሲጸልይ ሰነበተ በፍጻሜውም በክርስትና ጥምቀት የተሰጠው የመንፈስ ቅዱስ ልጅነት በርግብ አምሳል በላዩ ወርዶ በውስጡ ሲያድር አየ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም አመሰገነው። ረድኡንም እንዲጠነቀቅና የቀናች ሃይማኖቱን እንዲያጸና ልዩ ከሆነ ሰውም ጋር ስለ ሃይማኖት እንዳይነጋገር አዘዘው።
❤ የአባ ጊዮርጊስ ሌላው ተማሪ የነበረው ዐፄ ይስሐቅ በ1399 ዓ.ም መንግሥቱን ሲይዝ አባ ጊዮርጊስን ከግዞት አውጥቶ ወደ ጋሥጫ መለሰው፡፡ በዚያ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ እድሜው 42 ዓመት ሲሆን በስደትና በጤንነት መታወክ የተነሣ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜውን በጾም፣ በጸሎትና በድርሰት ያውለው ነበር፡፡ አንድ ቀን ቴዎድሮስ የተባለ መስፍን፣ ዳግመኛም የጦሩ አዛዥ የሚሆን፣ አባ ጊዮርጊስን ስለ ርትዕት ሃይማኖት በጠየቀው ጊዜ አባ ጊዮርጊስም "ፍካሬ ሃይማኖት" የተባለውን መጽሐፍ ደርሶ ሰጠው፡፡ ንጉሡና የምሥጢር ሊቃውንት የሆኑ ካህናት ይህንን በተመለከቱና ባነበቡ ጊዜ "በእውነት ዮሐንስ አፈወርቅና አፈ በረከት የሆነው ቄርሎስ በዘመናችን ተነሥተዋል፡፡ ኢትዮጵያም ቍስጥንጥንያን መስላለች፣ ከእስክንድርያም በላይ ከፍ ከፍ ብላለች" ብለው አደነቁ፡፡
❤ ይህም ፍካሬ ሃይማኖት የተሰኘው ድንቅ ድርሰቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታምነውንና የምታወግዘውን በግልጽና በዝርዝር የጻፈበት መጽሐፍ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በፍካሬ ሃይማኖት ድርሰቱ ላይ የዘረዘራቸው የመናፍቃን ስሞችንና ክህደታቸውን ስንምለከት በዘመኑ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ስለ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያላቸውን ዕውቀት በግልጽ ያሳየናል፡፡ አባ ጊዮርጊስ መከራ ያልተለየው አባት በመሆኑ አሁንም በቤተ መንግሥት የነበሩ ሰዎች የእርሱን መከበርና መወደድ አይፈልጉትም ነበር፡፡ በተለይም "ፍካሬ ሃይማኖት" የተሰኘውን መጽሐፍ በመጻፉ በዚህም ዝናው የበለጠ ስለተነገረ እነርሱ በሁሉም ዘንድ መከበሩን አልወደዱትም ነበር፡፡ ስለዚህም ነገር ሠርተው ከዐፄ ይስሐቅ ጋር አሁንም አጣሉት፡፡
❤ ዐፄ ይስሐቅ አባ ጊዮርጊስን አሳስሮ ውኃ ወደማይገኝበት ዓለታማ ቦታ አጋዘው፡፡ በዚያም በመከራ ለብዙ ጊዜ ኖረ፡፡ በዚያ እያለ ዘወትር በጸሎት አብዝቶ ይተጋ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ዐፄ ይስሐቅ ወደ ልቡናው እንዲመለስ አደረገ፡፡ ንጉሡ በአባ ጊዮርጊስ ላይ የፈጸመው ነገር ሁሉ ስለፀፀተው አገልጋዮቹን ጠርቶ አባ ጊዮርጊስን እንዲያመጡት አዘዘ፡፡ ነገር ግን እነዚያ ተንኮል ሠሪዎች የአባ ጊዮርጊስ መምጣት ተንኮላቸውን ስለሚያጋልጠው "አባ ጊዮርጊስ ሞቷል" ብለው አስወሩ፡፡ ይህንን ሲሰማ ዐፄ ይስሐቅ ፈጽሞ አዘነ፡፡
❤ አባ ጊዮርጊስም ሞቷል እየተባለ መወራቱን ከደቀ መዝሙሩ ስለ ሰማ በሕይወት የመኖሩን ዜና ጽፎ ለዐፄ ይስሐቅ እንዲያደርስለት መልእክቱን በአውሎ ንፋስ አሳስሮ ላከለት፡፡ አውሎ ንፋሱ ለአባ ጊዮርጊስ በመታዘዝ ደብዳቤውን ተሸክሞ በመሄድ ዐፄ ይስሐቅ በድንኳን ተቀምጦ በነበረ ጊዜ ጉልበቱ ላይ አስቀመጠው፡፡ ንጉሡ ምትሐት የተሠራበት ስለመሰለው ደነገጠና መኳንንቱንና ሕዝቡን ሰብስቦ ጉዳዩን ገለጠ፡፡ ወዲያውም ነፋሱ ያመጣለትን መልእክት እሳት አስነድዶ ከዚያ ውስጥ ቢጥለው ሊቃጠል አልቻለም፡፡ ወደ ውኃም ቢጨምረው አልጠፋም፡፡ በዚህ ተደንቆ ወረቀቱን ከፍቶ አነበበው፡፡ ደብዳቤው ከአባ ጊዮርጊስ የተላከ መሆኑን ሲያውቅ ዐፄ ይስሐቅ ደነገጠ፡፡ እነዚያን መልእክተኞች ይዞ ወደ ወኅኒ ከጨመራቸው በኋላ አባ ጊዮርጊስን ከግዞት ያወጡት ዘንድ ላከ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲመጣ ንጉሡ በደስታ ተቀብሎ ማረኝ ብሎ ለመነው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ይቅር አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ደብዳቤውን በማን እጅ እንደ ላከው ጠየቀው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ደብዳቤውን በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ በነፋስ እንደ ላከው አስረዳው፡፡
❤ አባ ጊዮርጊስ ከግዞት ከተመለሰ በኋላ እመቤታችን ተገልጣለት መከራው ሁሉ እንደ ሐዋርያት መሆኑን ገለጠችለት፡፡ አእምሮውን ብሩህ፣ ልቡናውን ትጉኅ የሚያደርግ እጅግ ብዙ ምሥጢርም ነገረችው፡፡ ተሰናብታው ከሄደች በኋላ "እጅግ ብዙ መብራት አቅርቡ አምስት ፈጣን ጸሐፊዎችንም አምጡ" ብሎ አዘዘ፡፡ ከዚህም በኋላ እርሱ እየነገራቸው እነርሱ እየጻፉ እረፍት ሳያደርጉ ሦስት ቀን ሙሉ አጽፎ "መጽሐፈ ምሥጢር" የተሰኘውን መጽሐፍ ፈጸመ፡፡ አምስቱ ጸሐፍትም የየድርሻቸውን አጠናቅቀው በአንድ አደረጉት፡፡ አባ ጊዮርጊስም ይህን ተመልክቶ በእጅጉ አደነቀ፡፡ "እኔ የዚህን መጽሐፍ ቃል አልተናገርኩም፤ መንፈስ ቅዱስ በእኔ አፍ ተናገረ እንጂ" ሲል በወቅቱ መስክሯል፡፡ የመጽሐፉንም ስም "መጽሐፈ ምሥጢር" ብሎ የሰየመው ራሱ ነው፡፡ የጻፈው በ1409 ዓ.ም እድሜው 52 በደረሰ ጊዜ ሲሆን በወቅቱም የዚህ መጽሐፍ ቅጅ በነጋድያን እጅ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ሄዶ ነበር፡፡
✝ ዐፄ ይስሐቅ ለአባ ጊዮርጊስ "ምድረ ሰዎን" የተባለውን የጳጳሳት መቀመጫ የነበረውን ሀገር በርስትነት ሰጥቶት ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ በምድረ ሰዎን ንጉሥ ይስሐቅ ክረምቱን ያሳልፍበት በነበረው ቦታ ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠራ፡፡ በዚያም በማስተማርና በጾም በጸሎት ይተጋ ነበር፡፡ በጋሥጫ እያለ ዐፄ ይስሐቅ አስጠራው፡፡ በዚያ ጊዜ ንጉሡ የመናገሻ ማርያምን ቤተ ክርስቲያን አሠርቶ ስለነበር እንዲባርክለት ፈልጎ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን በዚያ ጊዜ ታሞ የተኛም ቢሆን ወደ ንጉሡ ተጓዘ፡፡ እዚያ ሲደርስ በጣም ተዳክሞ ነበር፡፡ ሥርዓቱን ለመፈጸምም አቅም አልነበረውም፡፡ ስለዚህም ንጉሥ ይስሐቅ በአልጋ ተሸክመውት እንዲዞሩና ቤተ ክርስቲያኗን እንዲባርካት አድርጓል፡፡ ቡራኬውን ከፈጸመ በኋላ ደቀ መዝሙሮቹን ሰብስቦ "ከሞትኩ አባቴ በጸሎተ ሚካኤል መከራ ወደ ተቀበለባትና እኔም ቤተ ክርስቲያን ወዳነፅኩባት ቦታ ወስዳችሁ ቅበሩኝ" ሲል አዘዛቸው፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ የመጨረሻ የስንብት ትምህርቱን አስተማራቸው፡፡ እነርሱም በአልጋ ተሸክመውት ወደ ጋሥጫ እያመሩ ሳለ በመንገድ ላይ ሐምሌ 7 ቀን 1417 ዓ.ም በ60 ዓመቱ ዐረፈ፡፡ ከአባታችን ከአባ ጊዮርጊስ እግዚአብሔር አምላክ ዘጋስጫ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቱ ይማረን!።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅድስት_እኅተ_ጴጥሮስ፦ ይቺም ጻድቅ አገሯ ጎንደር ነው። የቅድስት ወለተ ጴጥሮስ የቅርብ ጓደኛ የነበረች ሲሆን አብረው ከዐላዊያን ጋር በሰማዕትነት ሲጋደሉ ኖረዋል። በደብረ ዳሞ ተራራ ሥር ባለው የሴቶች ገዳም ተቀምጣ ዐላውያን ካቶሊኮችን
ስትከራከርና እነርሱም ሲያሠቃዩአት የኖረች ደገኛ ሰማዕት እናት ናት። በደብረ ዳሞ፣ በማኅበረ ሥላሴ ገዳምና በደብረ ሞጊና ገዳም መነኰሳትን እየተራዳችና እያገለገለች ኖራለች። ጻድቋ እናታችን በቀን አንድ ሺህ አቡነ ዘበሰማያት ትጸልይና 1500 ትሰግድ የነበረች ሲሆን መላእክትም ዕለት ዕለት ያነጋግሯት ነበር። በሰማዕትነት ስታርፍም ክብሯን የመሰከሩላት ቅዱሳን መላእክት ናቸው። ከእናታች ከሰማዕቷ ከቅድስት እኅተ ጴጥሮስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቷም ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።
❤ የመጀመርያውን ድርሰቱን አርጋኖንን እመቤታችን አብዝታ ስለወደደችለት ዚማት በሚባለው ሀገር በነበረ ጊዜ "ከድርሰቶችህ ሁሉ እንደ አርጋኖን የምወደው የለም" ብላዋለች፡፡ ከዚህ በኋላ የደረሰው ድርሰት ውዳሴ መስቀል ይባላል፡፡ ቀጥሎም መጽሐፈ ስብሐት ዘመዓልት ወዘሌሊት የተባለውን ወይም እርሱ ራሱ መጽሐፈ ብርሃን ብሎ የሰየመውን መጽሐፍ አዘጋጅቷል፡፡ መጽሐፉም የእግዚአብሔርን የምስጋናውን መንገድ ያበራል፣ አብርቶ ያመለክታልና፣ ልዑላነ ብርሃን የሆኑትን የማኅበረ ቅዱሳንንና የትጉኃንን የምስጋናቸውን መንገድ ያመለክታልና፣ የእመቤታችንንም የምስጋናዋን ጣዕም ይገልጣልና መጽሐፉ "መጽሐፈ ብርሃን" ተባለ፡፡ በዘመኑ በነበረው ልማድ ካህናቱ ቍርባን በሚያቀብሉ ጊዜ ሕዝቡ ወደ ካህናቱ መጥተው ሲቀበሉ ንግሥቲቱ ግን ካለችበት ድረስ ካህናቱ ሄደው ነበር የሚያቆርቧት፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን "ይህ ቁርባን ንጉሠ ነገሥት ነውና ንግሥቲቱ ወደዚህ መጥታ ልትቀበል ይገባታል እንጂ እኛ መሄድ የለብንም" ሲል ተቃወመ፡፡ ይህ ነገር ንግሥቲቱንና አባ ጊዮርጊስን ስላጋጫቸው ዐፄ ዳዊት ችግሩን ለመፍታት አባ ጊዮርጊስን ወደ ሀገረ ዳሞት ንቡረ እድነት ሾሞ ላከው፡፡
❤ ከዚህ በኋላ አባ ጊዮርጊስ ዋናው ትኩረቱ በድርሰቱ ላይ በማድረግ ወደ ጳጳሱ ወደ አቡነ በርተሎሜዎስ ዘንድ በመሄድ የቅዳሴ ድርሰት ለመድረስ እንዲፈቀድለት ጠይቆ ሲፈቀድለት የቅዳሴ ድርሰት ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ነገረ ሃይማኖትን ጠንቅቆ የተረዳና የሚያስረዳ ስለነበር በዘመኑ የተነሡ የሃይማኖት ክርክሮች ሁሉ እርሱ ከሌለ አይሳኩም ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ በሸዋ በይፋት ራሳቸውን ቤተ እስራኤል እያሉ የሚጠሩ አይሁድ ነበሩ፡፡ ከአቡነ ዜና ማርቆስ ጀምሮ ብዙ መምህራን ወደነዚህ ሕዝቦች እየተሠማሩ ወንጌልን አስተምረዋል፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ክርስትና ለተመለሱት ቤተ እስራኤላውያን በእመቤታችን፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በአባ ኖብና በሰማዕቱ በጊጋር ስም አራት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተው ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ቤተ እስራኤላውያኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ክርስትና አልተመለሱም ነበር፡፡
❤ ከእነዚህ አይሁድ መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ፡፡ "ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደነርሱ ሃይማኖት እገባለሁ እኔ ከረታኋቸውም ወደኔ ሃይማኖት ይገባሉ" ሲል ነገሩን ጥብቅ አደረገው፡፡ ዐፄ ዳዊት ይህን ጉዳይ ሲሰማ በጣም ስለ ተናደደ ሊቃነ ካህናቱን፣ ንቡራነ እዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር፡፡ አይሁዳዊው በአንድ ወገን መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን ጀመሩ፡፡ የመጀመርያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አቀረበ፡- "እናንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉት ይሄ ክርስቶስ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፣ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ "አልዓዛርን የት ቀበራችሁት?" ብሎ እንደ ጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ስጡኝ፣ እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪቴ ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ?" ሲል የመከራከርያ ነጥቡን አቀረበ፡፡
❤ ሊቃውንቱም በዚህ ጊዜ ታሞ አልጋ ላይ የነበረውን አባ ጊዮርጊስን እንዲመጣላቸው ፈልገው "እንዲህ ያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ" ሲሉ ለዐፄ ዳዊት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደርጎ በአልጋ ላይ ሆኖ በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ ጉባኤተኞቹ የቀረበውን ጥያቄ በነገሩት ጊዜ አባ ጊዮርጊስ የሰጠውን መልስ እንዲህ የሚል ነው፡- "እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ፡፡ የምኩራብ መጻሕፍት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና፡፡ ምኩራብ ዘራች ቤተ ክርስቲያንም አጨደችው፤ ምኩራብ ፈተለችው ቤተ ክርስቲያን ለበሰችው፤ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ ወዴት ነህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? አብርሃምንስ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? ብሎ የጠየቀው ማነው? እስቲ መልስልኝ? ሰይጣንንስ ከወዴት መጣህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? እግዚአብሔር አብ አይደለምን?" እያሉ የጥያቄ ዓይነት ባሽጎደጎዱለት ጊዜ አይሁዳዊው መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡ መልስ በማጣቱም አፈረ፡፡ ንጉሡ፣ ሊቃውንቱና መኳንንቱም እጅግ ተደሰቱ፡፡
❤ አባ ጊዮርጊስ ሌላው ያጋጠመው ክርክር ቢቱ ከተባለው ሰው ጋር ያደረገው ክርክር ነበር፡፡ ቢቱ "በምጽዓት ጊዜ የሚመጣው ወልድ ብቻውን እንጂ አብና መንፈስ ቅዱስ አይመጡም" የሚል ኑፋቄ ማስተማር ጀምሮ ነበር፡፡ ቢቱ ከዚህ ኑፋቄው በተጨማሪ የጥንቆላ ሥራም ይሠራ ነበር፡፡ ቢቱ በጥንቆላ ሥራው የተነሣ በቤተ መንግሥቱ ተቀባይነት የነበረው ሰው ነበረ፡፡ ይህን መሰሉን ተግባር አጥብቆ የተዋጋው ዘርዐ ያዕቆብ እስኪመጣ ድረስ ነገሥታቱ ምንም ክርስቲያኖች ቢሆኑ በዚህ መሰሉ ስንኩል ሕፀፅ ይዋጡ ነበር፡፡ ቢቱና አባ ጊዮርጊስ ወደ ንጉሥ ዳዊት ቀርበው በጉዳዩ ላይ መነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጡ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ጳጳሱና ሊቃውንቱ ባሉበት እንዲነጋገሩ ስለወሰነ ጳጳሱ እንዲመጡ አዘዘ፡፡ በዚህ ጊዜ ተንኮለኛው ቢቱ ከአባ ጊዮርጊስ ጋር ከተከራከረ እንደሚሸነፍ ስላወቀ "ንጉሡ የአባቶቻችንን ሃይማኖት ክዷልና አትምጣ" የሚል ደብዳቤ በአባ ጊዮርጊስ ስም ጽፎ ጳጳሱን ሊጠሩ በሄዱት መልእክተኞች እጅ ላከ፡፡ ወድያውም ለዐፄ ዳዊት ይህንን ነገር አሳበቀ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ፈጣን መልእክተኞች ልኮ የፊተኞቹ መልእክተኞች እንዲመለሱ አደረገና ደብዳቤው ተነበበ፡፡ የቢቱ ተንኮል ያልገባው ንጉሥ ዳዊት ይህን ደብዳቤ ሲመለከት አባ ጊዮርጊስን በደም እስኪነከር ድረስ እንዲደበደብ አድርጎ ወደ እስር ቤት አስገባው፡፡
❤ ዐፄ ዳዊት እስኪሞትና ልጁ ቴዎድሮስ እስኪነግሥ ድረስም በዚያ ቆየ፡፡ ቢቱ ግን በመልአክ ተቀስፎ ሞተ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን በወኅኒ ቤት እያለ የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስ እየመጡ ያጽናኑት ነበር፡፡ "ውዳሴ ሐዋርያት" የተሰኘውንና ከሐምሌ 5 ጀምሮ በ12ቱም ወራት የሚመሰገኑበት የሐዋርያትን ምስጋና የያዘውን መጽሐፍ ያዘጋጀው በወኅኒ ቤት ሆኖ ጴጥሮስና ጳውሎስ ከጎበኙት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
❤ አንድ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ በእስር ላይ ሳሉ ንጉሡ ዐፄ ዳዊት መሞታቸው ተሰማ፡፡ ሰዎችም ወደ አባታችን መጥተው "ያሳሰረህ ንጉሥ ሞቷል" በማለት ነገሩት፡፡ ይህንንም ተቻኩለው የነገሩት ያሰረው ንጉሥ መሞቱን ሲሰማ ይደሰታል ብለው ነበር፡፡ ነገር ግን አባ ጊዮርጊስ በታላቅ ሀዘን ውስጥ ሆኖ የሰጣቸው መልስ "አይ ንጉሡ ባይሞት እኔም እንደታሰርኩ ብቀር ይሻል ነበር፡፡ ንጉሡ ዐፄ ዳዊትኮ እኔን ባይወደኝ የአምላክን እናት እመቤታችንን ይወዳት ነበር" አላቸው፡፡
❤ ዐፄ ቴዎድሮስ አባ ጊዮርጊስን ከወኅኒ ቤት አውጥቶት በጥንቱ ቦታ አስቀመጠው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን የቤተ መንግሥትን ነገር ለመሸሽ ስለ ፈለገ በጋሥጫ ከመቀመጥ ይልቅ ርቆ ጥንት ወደ ነበረበት ወደ ዳሞት በመሄድ ማስተማር ጀመረ፡፡ ወደ ዳሞት ሲሄድ እግረ መንገዱን ወደ ደብረ ሊባኖስ ገብቶ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን መቃብር ተሳልሟል፡፡ በዚያ ጊዜ የደብረ ሊባኖሱ አበ ምኔት እጨጌ ዮሐንስ ከማ ነበሩ፡፡ እርሳቸውም ሰባተኛው የደብረ ሊባኖስ እጨጌ ነበሩ፡፡ አባ ጊዮርጊስን በዕውቀቱ የሚቀኑበት፣ በችሎታው የሚመቀኙት ሰዎች ነገር ሠርተው ከንጉሥ ቴዎድሮስ ጋር ስላጣሉት እልም ካለ በረሃ እንዲጋዝ ተደረገ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ከግዞት የወጣው ዐፄ ቴዎድሮስ ሲሞት ነበር፡፡
ነውና አጋንንትን ያሳድዳል መላእክትንም ያቀርባል፡፡ እመቤታችንም ከእርሱ ተለይታ ካረገች በኋላ ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ የልቡ ዓይን ተከፈተለት፡፡ ኅሊናውም በመንፈስ ቅዱስ ክንፎች ተመሰጠ፡፡ ወደ አብም ደረሰ፤ በዚያም ኢየሱስን በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ጰራቅሊጦስንም በአንድ አኗኗር አገኘው፡፡
❤ ከዚህ በኋላ በሐይቅ እስጢፋኖስ የዜማ የቅኔና የመጻሕፍትን ትርጓሜ ትምህርቱን በሚገባ ተምሮ አጠናቀቀ፡፡ በዕውቀቱም ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ይደነቁበት ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ የያሬድን ዜማ ከአቡነ ሳሙኤል ተማረ፡፡ በዚያ ዘመን በዐፄ ዳዊት አማካይነት በሰሜን ኢትዮጵያ የያሬድ ድጓ ዋና ማዕከል በሆነው በደብረ ነጎድጓድ ተሾሞ ያስተምር ነበር፡፡ የማስተማር ሥራውን የጀመረው በዚያው በሐይቅ እስጢፋኖስ ነበር፡፡
❤ ከሐይቅ በኋላ በዚያ ዘመን ሸግላ በመባል ትጠራ ወደ ነበረችው ወደ ትውልድ ሀገሩ ወደ ጋሥጫ ተጓዘ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ወደ ሸግላ ሲመጣ አባቱ በጣም አርጅቶና መንኲሶ ነበር፡፡ ስለዚህም በአባቱ እግር ተተክቶ በቤተ መንግሥቱ ያለችውን ሥዕል ቤት እንዲያገለግል ወደዚያው አስገቡት፡፡ በቤተ መንግሥቱም የንጉሡን ልጆች ከማስተማሩም በላይ በቤተ መንግሥቱ ዙርያ ከነበሩት ሊቃውንት መካከል አባ ጊዮርጊስ አንዱ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ግብፃዊው ጳጳስ አቡነ በርተሎሜዎስ "ሥላሴን አንድ ገጽ" ብለው ያምናሉ ተብለው በተከሰሱ ጊዜ ነገሩን እንዲያጣሩ ከተመረጡት ከቄስ ዐፄ ተከሥተ ብርሃንና ከሐይቁ መምህር ከዐቃቤ ሰዓት ዮሴፍ ጋር አብሮ ተልኮ ነበር፡፡ እነዚህ ሦስት አበው ጳጳሱን ካነጋገሩ በኋላ ክሱ ውሸት መሆኑን በማረጋገጥ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የሚገልጠውን የጳጳሱን እምነት በጽሑፍ ይዘው መጡ፡፡
❤ በቤተ መንግሥቱ በነበረ ጊዜ የንጉሡን ልጆች ይስሐቅን፣ ቴዎድሮስን፣ እንድርያስን፣ ሀብተ ኢየሱስን፣ ሕዝቅያስን፣ ኢዮስያስን፣ ዘርዐ ያዕቆብንና ሴት ልጁን እሌኒን በምግባርና በሃይማኖት ቀርጿቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዘርዐ ያዕቆብ በድርሰቱ ሲመስለው ቴዎድሮስ ደግሞ በሕይወት መስሎታል፡፡ ዐፄ ዳዊት የአባ ጊዮርጊስን ሊቅነትና መልካም ሥነ ምግባር በሚገባ ስላወቀ በጋብቻ ሊዛመደው ወዶ ስለነበር ልጁን እንዲያገባ ዘወትር ይጠይቀው ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን በድንግልና ጸንቶ ለመኖር እንደሚፈልግ ከመግለጽ አልተቆጠበም፡፡ የዐፄ ዳዊት ጥያቄ ስለበዛበት ወደ አቡነ በርተሎሜዎስ ሄዶ ቅስናን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው መነኰሰ፡፡
✝ ከመነኰሰ በኋላ ወደ ሸግላ በመምጣት ለነገሥታትና በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ካህናት እንዲሁም በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ታላላቆች፣ ለንቡራነ እድና ለመኳንንት፣ ለመሳፍንትና በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ባለሟሎች ሁሉ መምህር ሆነ፡፡
❤ አባ ጊዮርጊስ በሸግላ በነበረ ጊዜ በወባ በሽታ ታምሞ ሊሞት ደርሶ ነበር፡፡ ታምሞ በነበረ ጊዜ አንድ ሌሊት የከበሩ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ተገልጠውለት "ከእኛ ጋር ትኖር ዘንድ ልንወስድህ መጣን" አሉት፡፡ እርሱም "የድርሰት ሥራዬን ሳልሠራና እግዚአብሔርንም አብዝቼ ሳላመሰግነው አሁን አትውሰዱኝ" ሲል ለመናቸው፡፡ እነርሱም ልመናውን ተቀብለውት ከሕመሙ ፈውሰውት ሄዱ፡፡ ለዚህም ነው ከበሽታው እንደ ተፈወሰ ወድያው የድርሰት ሥራውን የጀመረው፡፡ የመጀመርያ መጽሐፉን ጽፎ እንደ ጨረሰ ጠፍቶበት ነበር፡፡ በማግሥቱ በዚያው ላይ ሊጨምር በወደደ ጊዜ የተጻፈበት ጥራዝ ቀለሙ ጠፍቶ ነጭ ሆኖ አገኘው፡፡ ስለዚህም የተሰረቀ መስሎት ልቡ አዘነ፡፡ የተስተካከሉ ጥራዞችንም በቈጠረ ጊዜ ደኅና ሁነው አገኛቸው ሁለተኛም በድጋሚ ጻፈ፡፡ በማግሥቱም እንደ መጀመሪያው ነጭ ሁኖ አገኘው እስከ ሦስትና ዐራት ቀንም እየተደጋገመ እንዲሁ ሆነ፡፡
❤ ከዚህ በኋላ አባታችን ወደ እመቤታችን ይጸልይ ጀመረ፡፡ "ይህ የሆነ በኃጢአቴ ነውን? ወይስ አይደለም? ግለጭልኝ" አላት፡፡ አንድ ቀንም በሌሊት እኩሌታ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለጸሎት ሲሄድ እመቤታችን በድንገት በማይነገር ክብር ለጊዮርጊስ ተገለጠችለት፡፡ ከእርሷም ጋር የቅዱሳን ማኅበር ሁሉ ነበሩ፡፡ በእጇም ከፀሐይና ጨረቃ የበለጠ የሚያበራ መጽሐፍን ይዛ ነበር፡፡ ጊዮርጊስም ባየ ጊዜ ወደ መሬት ወደቀ፡፡ እንደ በድንም ሆነ፡፡ እመቤታችንም አነሣችውና "ሳትጠይቀኝ መጽሐፌን ትጽፍ ዘንድ ለምን ደፈርህ?" አለችው፡፡ "እኔ ወድጄህ ከእናትህስ ማኅፀን መርጬህ ለጴጥሮስ፣ ለጳውሎስና ለዮሐንስ አደራ ሰጥቼህ የለምን?" አለችው፡፡ አባ ጊዮርጊስም "እመቤቴ ሆይ ይቅር በይኝ፣ ደስ የሚያሰኝሽ መስሎኝ ይህን ባለማወቅ ሠርቼዋለሁና" አላት፡፡ እመቤታችንም "ወዳጄ ሆይ ይቅር ብየሃለሁ" አለችው፡፡ "ልትጽፈው የወደድኸው መጽሐፍም እነሆ በእጄ አለ፣ ከአሁን በኋላ የተወደደ ልጄ በአንደበትህ ሊገልጸው ወዷል፡፡ ነገር ግን ከአርያም ከሰማይ ኀይልን እስክትለብስ ድረስ አትቸኩል"፡፡ ይህንም ብላው ከእርሱ ተሰወረች፡፡ ያን ጊዜም ልቡ እንደ ፀሐይ በራ፣ የመለኮትም ባሕር በኅሊናው አበራ፡፡ በመንፈስ ቅዱስም መስተዋትነት የተሰወረውን ሁሉ አየ፡፡
❤ የመጀመርያው ድርሰቱ አርጋኖን የተሰኘውና በቅኔ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚያመሰግነው መጽሐፉ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በሚወድ በንጉሥ ዳዊት ዘመንም አርጋኖን መጽሐፍን ይደርስና ይጽፍ ጀመረ፡፡ በሦስትም ስሞች ጠራው እነዚህም አርጋኖና ውዳሴ፣ መሰንቆ መዝሙር፣ ዕንዚራ ስብሐት ናቸው፡፡ ስለ መጽሐፉም ጣፋጭነት ንጉሡ ዐፄ ዳዊት ድርሰቱን በጣም ከመውደዱ የተነሣ በወርቅ ቀለም አጻፈው፡፡ ወርቁን የሚያንጸባርቅበት ድንጋይ (ዕንቊ) ባጣ ጊዜ እመቤታችን ማርያም በሌሊት ራእይ ዘማት በሚባል አገር እንዳለ ለጊዮርጊስ ነገረችው ኅብሩንም አሳየችው፡፡ አባታችን ጊዮርጊስም ከደረስኳቸውና ከተናገርኋቸው ድርሳናት ሁሉ አርጋኖን ውዳሴ ይጣፍጣል ይበልጣል አለ፡፡
❤ እንደዚሁም በፈጣሪው ቸርነት በእመቤታችን ረድኤት ብዙ ድርሳናትንና የጸሎት መጻሕፍትን ደረሰ፡፡ የእሊህም ድርሳናት ስማቸውና ቁጥራቸው በሊቃውንት ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ እሊህም ውዳሴ መስቀል፣ መጽሐፈ ብርሃን፣ መጽሐፈ ሰዓታት የመዓልትና የሌሊት፣ መጻሕፍተ ቅዳሴያት ናቸው፡፡ ጸሎተ ፈትቶ (የፍታቴ ጸሎት) የሐዋርያት ማኅሌት፣ መልክአ ቊርባን፣ እንዚራ ስብሐት፣ አርጋኖን ውዳሴ፣ ፍካሬ ሃይማኖት፣ ውዳሴ ሐዋርያት፣ ኖኅተ ብርሃን ይኸውም ከመጽሐፈ አርጋኖን ጋር አብሮ የታተመው ነው፡፡ ፍካሬ ሃይማኖት፣ መጽሐፈ ምስጢር፣ ሕይወታ ለማርያም፣ ተአምኆ ቅዱሳን፣ ጸሎት ዘቤት ውስተቤት፣ ውዳሴ ስብሐት፣ ሰላምታ፣ ጸሎተ ማዕድ፣ ቅዳሴ እግዚእ ካልእ፣ መዝሙረ ድንግልና የመሳሰለው ነው፡፡ ቅዱስ ገድሉ እንደሚናገረው የአባ ጊዮርጊስ "ድርሳናት ስማቸውና ቁጥራቸው በሊቃውንት ዘንድ የታወቀ ነው" ብሎ ከጀመረ በኋላ በቁጥር የተወሰኑትን ድርሰቶቹን ብቻ ጠቅሶ መጨረሻ ላይ "… እና የመሳሰለው ነው" ብሎ ይደመድመዋል፡፡ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ደግሞ የአባ ጊዮርጊስ ድርሰቶች ከ12 ሺህ በላይ ቢሆኑም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እየሰጡ ያሉት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸውን በቅዱሳን ታሪክ መጽሐፋቸው ላይ ጠቅሰውታል፡፡ ሌሎች ሊቃውንት አባቶቻችንም የአባ ጊዮርጊስን ድርሰቶች ከግምት ባለፈ ሁኔታ በቁጥር ወስኖ ለማስቀመጥ አስቸጋሪ መሆኑን ይገልጣሉ፡፡ ይኸውም ወደፊት ራሱን የቻለ በቂና ብዙ ጥናት ማድረግ ሳያስፈልገን እንደማይቀር አመላካች ነው፡፡
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤
❤ #ሐምሌ ፯ (7) ቀን።
❤ እንኳን_ለታላቁ_ሊቅ_ለኢትዮጵያዊው_ቄርሎስ ለአባታችን #አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ_ለልደትና #ለዕረፍት_በዓል፣ #ለኢትዮጵያዊቷ_ጻድቅ #ለቅድስት_እኅተ_ጴጥሮስ_ለዕረፍቷ_በዓል በሰላም አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #ታላቁ_ሊቅ_ኢትዮጵያዊው_ቄርሎስ #አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ፦ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ዘትግራይ እናቱ አምኃ ጽዮን ዘወለቃ ይባላሉ፡፡ ስለሆነም ሀገሩ ትግራይና ወሎ ቦረና ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ በመባል የሚታወቀው ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በድርሰቱ ከቅዱስ ያሬድ ቀጥሎ ስሙ የሚነሣ ታላቅ መመኪያችን የሆነ ጻድቅ አባታችን ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ከመናኝ ጻድቅነቱ በተጨማሪ በመላእክትም ዘንድ የተመሰከረለት ታላቅ ፈላስፋና ደራሲም ነው፡፡ በድርሰቱ ላይ ስለ ሰማይ፣ ስለ መብረቅ፣ ስለ ደመና፣ ስለ ዝናብ አፈጣጠር፣ ስለ አራቱ ዓለማትና ስለ ሰባቱ ሰማያት… በእነዚህና በመሳሰሉት በመንፈሳዊው በሚገባና እጅግ በሚያስደንቅ መንገድ ተፈላስፎባቸዋል፡፡
❤ ጻድቁ ድርሰቶቹን እርሱ ካለበት ወደ ሌላ ቦታ ለመላክ ንፋስ ይታዘዝለት ነበር፡፡ ስለ ጾምና ስለ በዓላት የደረሰውን ድርሰቱን ለሸዋው ንጉሥ ደብዳቤ ጽፎ በነፋስ ጭኖ ልኮለታል፡፡ አስደናቂ ገደሙ ወሎ ቦረና ውስጥ ይገኛል፡፡ ጋስጫ በድሮ ስሟ ደብረ ባሕርይ ትባላለች፡፡ በአጠገቡም ራሱ አባ ጊዮርጊስ የፈለፈላቸው ብዙ ዋሻዎች አሉ፡፡ ከአባ ጽጌ ድንግል ጋር ለመገናኘት እንዲያመቻቸው ብለው የሠሩት ድልድይ "የእግዜር ድልድይ" ይባላል፡፡ በእግር 5 ሰዓት የሚያስኬድ መንገድ ነው፡፡ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም የአውሬ ሰጋጅና ባሕታዊ ያለበት አስደናቂ ገዳም ነው፡፡ በየዓመቱ የስቅለት ዕለት ቁመቱ 60 ክንድ የሆነ ዘንዶ ከመቅደሱ ወጥቶ ግብረ ሕመማት ከሚነበብበት ከአትሮንሱ ሥር ሆኖ ተጠምጥሞ እራሱን ቀና አድርጎ ሲሰግድ ውሎ ካህኑ ሲያሰናብት ማታ ተመልሶ ወደ መቅደሱ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ የተሰኘውን የዚህን ድንቅ አባታችንን ዜና ሕየወቱን በደንብ መመልከቱ ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡
❤ የተወለደው በ1357 ዓ.ም በወሎ ክፍለ ሀገር በቦረና ወረዳ ሰግላ በተሰኘች ቦታ ነው፡፡ የተወለደው በቅዱስ ዑራኤል አብሳሪነት ነው፡፡ ወላጆቹ አስቀድሞ ልጅ አልነበራቸውምና በስለት ነው ያገኙት፡፡ አባ ጊዮርጊስ በመጀመርያ እናቱ ፈሪሐ እግዚአብሔርን እያስተማረች በጥበብና በዕውቀት አሳደገችው፡፡ ቀጥሎም የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተማረው ከአባቱ ነበር፡፡ ሊቅ የነበረው አባቱ ካስተማረው በኋላ በ 1341 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ከመጡትና እስከ ዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ጳጳስ የነበሩት ከአቡነ ሰላማ መተርጕም ዘንድ ወስዶ ዲቁና አሹሞታል፡፡
❤ ዲቁና ከተቀበለ በኋላ ለትምህርት ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ወሰደው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት አልገባው ብሎ ለሰባት ዓመታት ተቀምጦ ነበር፡፡ አብረውት የሚማሩት ተማሪዎች "ይህ ትምህርት የማይገባው ስለ ምንድን ነው? በእርሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ?" ይሉት ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የሐይቁ መምህር የነበረው ዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ለአባቱ "ልጅህ ትምህርት አይገባውምና የቤተ መንግሥት ነገር አስተምረው" ብሎ መለሰው፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ግን "አንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ እዚያው ገዳሙን ያገልግል" ብሎ እንደ ገና ወደ ሐይቅ ላከው፡፡
❤ አባ ጊዮርጊስ ከቀለም ትምህርቱ ይልቅ በሥራ እየደከመ የገዳሙን አባቶች ይረዳ ጀመር፡፡ በገዳሙ እንጨት ይሰብር ውኃ ይቀዳ ይልቁንም ደግሞ አብዝቶ እህል በመፍጨት ያገለግል ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ እህል ይፈጭበት የነበረውን የድንጋይ ወፍጮና ንፍሮ ይቀቅልበት የነበረው የድንጋይ ትልቅ ማሰሮ አሁንም ድረስ በሐይቅ ገዳም በክብር ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን ትምህርቱን ለመረዳት የዘገየ ሆነ፣ የእግዚአብሔር ቃልም አልገባውም ነበር፡፡ ይህም ስለ ኃጢአቱ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ሥራና ጌትነቱ በእርሱ ላይ ይገለጥ ዘንድ ነው እንጂ፡፡ ጸጋ ያለመከራ አይሰጥምና ያለመፈተንም ማብዛት አይቻልም፡፡ ጌታችንን ዕውር ሆኖ ስለተወለደው ሕፃን ደቀ መዛሙርቱ በጠየቁት ጊዜ "ይህ ሕፃን ዕዉር ሆኖ የተወለደው በማን ኃጢአት ነው? በራሱ ነውን ወይስ በወላጆቹ?" አሉት፡፡ ጌታችንም "እርሱም አልበደለም፣ ወላጆቹም አልበደሉም፣ የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ ላይ ይገለጥ ዘንድ ነው እንጂ" አላቸው፡፡ ዮሐ 9፡1፡፡ ሐዋርያትም መንፈስ ቅዱስ እስኪወርድላቸው ድረስ በትንሽ ዕውቀት ነበሩ፡፡ "በመጻሕፍት ያለውን ገና ዐላወቁምና" ተብሎ እንደተጻፈ እንዲሁ አባ ጊዮርጊስም ዕውቀት ስለ ተሰወረውና ጓደኞቹ በትምህርት ሲቀድሙት ባየ ጊዜ እጅግ አዘነ፡፡ ስለዚህም በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መጮኽ ጀመረ፡፡
❤ ሁልጊዜም በሥዕለ ማርያም ሥር እየተንበረከከ ጥበብን እንዲሰጠው ወደ እግዚአብሔር አብዝቶ በመለመን እንባንም በማፍሰስ ይጸልይ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ እመቤታችን ተገለጠችለትና አረጋጋችው፡፡ ዳግመኛም እንደምትመጣ ቀን ቀጥራው ከእርሱ ተሰወረች፡፡ በሰጠችውም ቀጠሮ መሠረት በነሐሴ 21 ኛው ቀን እመቤታችን ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በቀኝና በግራ ሆነው ኪሩቤልንና ሱራፌልን አስከትላ ተገለጠችለትና "አይዞህ ዕውቀት የተሰወረብህ ትምህርት ስለማይገባህ ሳይሆን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እንዲገለጥ ነው" አለችው፡፡ "የመረጥሁህ የልጄ ወዳጅ ጊዮርጊስ ብላ በስሙ ጠራችው፡፡ ከዕውቀት ወንዝ የመጣና ከጥበብ ምንጭ የተገኘ ከመለኮት ባሕር የተቀዳ ይህን ንጹሕ ጽዋ ንሣ ጠጣ" በማለት ጽዋዓ ልቡናን አጠጣችው፡፡
❤ ይኸውም ጽዋዕ ልቦና በዮሴፍ ቤት በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት የጠጡት መንፈሳዊና ሰማያዊ መጠጥ ነው፤ በበዓለ ሃምሳ ከጠጡት ያልተለየ ነው፡፡ ይኸውም የሚናገር እሳት፣ የሚያድን እሳት፣ መለኮታዊ እሳት ነው፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን ያስጌጠበት የመጻሕፍትን ምስጢራት፣ የማኅሌትንና የድርሳናትን ቃል፣ ምስጋናዎችንም ሁሉ እመቤታችን ገለጠችለት፡፡
❤ እመቤታችን ማርያም ለብፁዕ ጊዮርጊስ ጽዋውን ካጠጣችው በኋላ ያን ጊዜ አምስት የምሥጢር ቃላትን አስተማረችው፡፡ የኅሊናን ዓይኖች ያበራሉና የልቡናንም ጆሮዎች ይከፍታሉና፡፡ ከዚህ በኋላ ከእርሱ ተሰወረች፤ ከማይተኙ ከትጉሃን መላእክትም ጋር ወደ ሰማይ ዐረገች፡፡ የአምስቱ የምሥጢር ቃላት ትርጉምም ዕውቀትን የተመሉ መንፈሳውያን አባቶቻችን እንደ ነገሩን ከእመቤታችን ማርያም እጅ በተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ትምህርት ሳይማር በአንድ ቀን የዳዊትን መዝሙር ማጥናት ነው፡፡ መዝሙረ ዳዊትን ግን ዕብራውያን በአምስቱ የስሜት ሕዋሳት ቁጥር ለአምስት ከፍለውታል፡፡ እነዚህም መስማት፣ ማየት፣ ማሽተት መቅመስና፣ መዳሰስ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል መጨረሻው 40ኛው መዝሙር ነው፤ የሁለተኛው ክፍል መጨረሻው 71ኛው መዝሙር ነው፡፡ ሦስተኛው ክፍል መጨረሻው 88ኛው መዝሙር ነው፤ አራተኛው ክፍል መጨረሻው 105ኛው መዝሙር ነው፡፡ አምስተኛው ክፍል መጨረሻው 150ኛው ነው፡፡ የእነዚህም ክፍላት መጨረሻ ለይኩን ለይኩን ባለ ጊዜ ይታወቃል፡፡ አባ ጊዮርጊስም የእነዚህን ምስጢር በልቡ ጠበቃቸው፡፡ አምስቱንም ቃላት በልቡ መዝገብነት ሰወራቸው፤ ሊገልጣቸው እግዚአብሔር አልፈቀደላትምና በተረዳ ነገር ግን መዝሙረ ዳዊት ነው፡፡ የገነትን ፍሬዎች ሁሉ የሰበሰበ መዝሙረ ዳዊት የገነት አምሳል
✝ ✝ ✝
❤ #የሮሜ_ከተማ_ሊቀ_ጳጳሳት_አቡነ_አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ፦ እርሱም ከቅዱስ ጴጥሮስ በኋላ በከሀዲው ንጉሥ በጠራብያኖስ ዘመን ሆነ። ይህም ንጉሥ ስለ አባት አግናጥዮስ የጣዖት አምልኮን እንደሚአቃልል ሕዝቡንም ሁሉ እንደሚያስተምር ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማመን እንደሚያስገባቸው በሰማ ጊዜ ወደ እርሱ አስቀርቦ "ለአማልክት መሥዋዕት አቅርብ" አለው ቅዱሱም "እኔ ለረከሱ ጣዖታት አልሠዋም" ብሎ መለሰለት።
❤ ንጉሡም ብዙ ቃል ኪዳኖችን በመግባት አባበለው በአልተቀበለውም ጊዜ ለአንበሳ ሰጠው ያን ጊዜም ቅዱስ አግናጥዮስ በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ ሕዝቡን አዘዛቸው። ከዚህም በኋላ አንዱ አንበሳ ቀርቦ አንገቱን ያዘው ያን ጊዜም ክብር ይግባውና በጌታችን እጅ ነፍሱን ሰጠ። ከዚህ በኋላ ያ አንበሳ ወደ ሥጋው አልቀረበም ምእመናንም መጥተው ሥጋውን ወሰዱ በመልካም ቦታም አኖሩት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአቡነ አግናጥዮስ በጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 7 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለአግናጥዮስ_ለመንበረ_ጴጥሮስ ዘወረሳ። እምነ መናብርት ኵሉ ዘተለዓለ ሞገሳ። ለመሥዋዕተ ጣዖት ምንንት እንዘ ያረኵሳ። በፍጻሜ ስምዑ ቀተሎ አንበሳ። ወእምድኅረዝ ኢቀርበ ለሥጋሁ ይግሥሣ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_7።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ሣህሉ ለእግዚአብሔር መልአ ምድረ። ወበቃለ እግዚአብሔር ፀንዐ ሰማያት። ወእምእስትንፋሰ አፋሁ ኵሉ ኃይሎሙ"። መዝ 32፥5-6። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 1፥1-6
✝️ ✝️ ✝️
❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ወኀሠሥኩ ገጸከ። ገጸ ዚአከ አኀሥሥ እግዚኦ። ወኢትሚጥ ገጸከ እምኔየ"። መዝ 26፥8-9። የሚነበበው መልዕክታት ሮሜ 9፥1-17፣ 1ኛ ዮሐ 4፥11-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 11፥11-19። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 8፥51-59። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የአጋእዝተ ዓለም የቅድስት ሥላሴ በዓል ለሁላችን ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤
❤ #ሐምሌ ፯ (7) ቀን።
❤ እንኳን #ለአጋእዝተ_ዓለም_ለቅድስት_ሥላሴ ወደ #አብርሃም_ቤት_ለገቡበት_የይስሐቅን_መወለድ_ለአበሰሩበት ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል፣ ለሮሜ ሊቀ ጳጳስ ለሐዋርያው #ለቅዱስ_አግናጥዮ_ምጥው_ለአንበሳ_ለዕረፍት_በዓልና ለባሕታውያን አለቃ ለሆነ ለመስተጋድል #አባ_ሲኖዳ_ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከአባ መቃቢስ፣ ከአግራጥም ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ በዚችም ቀን ልዩ የሆኑ ሦስቱ አካላት (#አጋዝእተ_ዓለም_ሥላሴ) በኦሪት መጽሐፍ እንደተጻፈ ወደ አብርሃም ቤት ገብ ያቀረበላቸውን ተመገቡ የይስሐቅንም ልደት አሠሰሩት ባረኩት አከበሩትም። ለእግዚአብሔር ይስጋና ይሁን በአባታችን በቅዱስ አብርሃም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ታሪኩን በመጽሐፍ ቅዱስ ዘፍ 18 ላይ ያንብቡ።
✝ ✝ ✝
❤ #የባሕታውያን_አለቃ_የሆነ_መስተጋድል_አባ_ሲኖዳ፦ ይህም ቅዱስ በግብጽና በአክሚም አውራጃ ስሟ ስንላል ከምትባል ሀገር ከላይኛው ግብጽ ነበር። ስለእርሱም የመላእክት አምሳል የሆነ አባ ሐርስዮስ ትንቢት ተናገረለት። እርሱም ስለ ገዳም አገልግሎት ከመነኰሳት ጋር ሲሔድ የዚህን የቅዱስ ሲኖዳን እናት ውኃ ለመቅዳት ወጥታ አገኛት። ወደርሷ ሒዶ ሦስት ጊዜ ራሷን ሳማትና እንዲህ አላት "ዜናው በዓለሙ ሁሉ የሚሰማ የስሙ መዓዛ ከሽቱ የሚጥም የሆነ የሆድሽን ፍሬ እግዚአብሔር ይባርክ"።
❤ እነዚያ መነኰሳትም በአዩት ጊዜ አድንቀው "አባታችን አንተ የሴት ፊት ማየት ከቶ አትሻም ነበር ዛሬ ግን ከሴት ጋራ ትነጋገራለህ" አሉት። "ልጆቼ ሆይ ሕያው እግዚአብሔርን የእግዚአብሔርን ምሕረት ተስፋ የሚያደርግ ዓለሙ ሁሉ የሚጣፍጥበት ከዚች ሴት የሚወጣ የጨው ቅንጣት አለ" አላቸው።
❤ አንድ በገድል የጸና ጻድቅ ሰው መነኰስ ነበረ እርሱም መልሶ አባ ሐርስዮስን እንዲህ አለው "እግዚአብሔር ሕያው ነው አንተ ራሷን ትስም ዘንድ ወደዚያች ሴት በቀረብክ ጊዜ በእጁ የእሳት ሰይፍ የያዘ የእግዚአብሔርን መልአክ በዙሪያዋ አየሁት። ራሷንም በሳምካት ጊዜ ክብር ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጁ ሆይ ሰላምታ ይገባሃል ሲልህ ደግሞም ከዚች ሴት የሚወለደው የተመረጡ ቅዱሳንን ሁሉ ልባቸውን ደስ ያሰኛል ወልደ እግዚአብሔርም ከርሱ ጋር ብዙ ጊዜ ይነጋገር ነበር ሲል ሰማሁት" አለ።
❤ በግንቦት ሰባት ቀን ይህ ቅዱስ አባ ሲኖዳ ተወለደ በአደገም ጊዜ አባቱ በጎች ስለነበሩት ለልጁ ለሲኖዳ እንዲጠብቃቸው ሰጠው ይህ ሲኖዳም ምሳውን ለእረኞች ሰጥቶ እስከ ማታ ድረስ ይጾም ነበር። በሌሊትም ከውኃ ዐዘቅት ውስጥ ወርዶ በዚያ ቁሞ እስቲነጋ ድረስ ሲጸልይ ያድር ነበር። በክረምትም ሆነ በቊር ሰዓት እንዲሁ ያደርግ ነበር። አባቱም የሲኖዳ እናት ወንድም ወደ ሆነው ወደ አባ አብጎል እጁን በላዩ ጭኖ ይባርከው ዘንድ ወሰደው። አባ አብጎልም በአየው ጊዜ የሕፃኑን እጅ አንሥቶ በራሱ ላይ አድርጎ "ሲኖዳ ሆይ ባርከኝ ለብዙ ሕዝብ ታላቅ አባት ትሆን ዘንድ የሚገባህ ሁነሃልና" አለው። አባቱም በአባ አብጎል ዘንድ ተወው።
❤ ከዕለታትም በአንዲቱ ቀን አባ አብጎል እንዲህ የሚል ቃል ከሰማይ ሰማ "እነሆ ሲኖዳ ለዓለሙ ሁሉ አርሲመትሪዳ የባሕታውያን አለቃ ሁኖ ተሾመ"። ይህም ሲኖዳ ለዓለሙ ሁሉ ብርሃን እስከሚሆን በበጎ አምልኮ ያለ ማቋረጥ በጾምና በጸሎት በስግደትና በመትጋት ታላቅ ተጋድሎ መጋደልን ጀመረ።
❤ ከዚህም በኋላ በአንዲት ቀን ለአባ አብጎል የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና የኤልያስን አስኬማ የሠለስቱ ደቂቅን ቆብና የመጥምቁ ዮሐንስን ቅናት አመጣለት። እንዲህም አለው "እንድትጸልይና የምንኵስና ልብስ ለሲኖዳ እንድታለብሰው እግዚአብሔር አዝዞሃል"። ያን ጊዜም አባ አብጎል ተነሥቶ ጸለየ የምንኵስና ልብስንም አለበሰው።
❤ ከዚህም በኋላ ተጋድሎውን አበዛ። ለመነኰሳት፣ ለመኳንንት፣ ለሕዝባውያንና ለሴቶች ለሰዎች ሁሉ መመሪያ የሚሆን ሥራትን ሠራ። በኤፌሶንም የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ጉባኤ ስለ ከሀዲው ንስጥሮስ በተደረገ ጊዜ ከማኅበሩ አባት ከሊቀ ጳጳሳት ቄርሎስ ጋራ ወደ ጉባኤው ሔደ ንስጥሮስም ከክህደቱ ባልተመለሰ ጊዜ አውግዘው ለይተው አሳደዱት።
❤ ከዚህ በኋላም ወደ ሀገራቸው በመመለሻቸው ጊዜ መርከበኞች ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋራ አትሳፈርም ብለው አባ ሲኖዳን ከለከሉት እርሱም ወደ እግዚአብሔር በጸሎት ማለደ። ወዲያውኑም ደመና መጥታ ተሸከመችውና አባ ቄርሎስ በመርከቡ ውስጥ እያለ በበላዩ በአንጻሩ አደረሰችው። "አባቴ ሆይ ሰላም ለአንተ ከአንተ ጋራ ላሉትም ይሁን" ብሎ ሰላምታ አቀረበ። በመርከብ ያሉት ሁሉም "ላንተም ሰላም ይሁን በጸሎትህም አትርሳን" አሉት። እጅግም አደነቁ ለሚፈሩት ይህን ያህል ጸጋ የሚሰጥ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።
❤ ወደ ገዳሙም ደርሶ ከልጆቹ መነኰሳት ጋራ የመንፈቀ ሌሊትን ጸሎት አደረገ። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ብዙ ጊዜ ወደርሱ እየመጣ ያነጋግረው ነበር። እርሱም የመድኃኒታችንን እግሩን ያጥበው ነበር እጣቢውንም ይጠጣ ነበር ጌታችንም ብዙ ምሥጢራትን ገለጠለት ትንቢቶችንም ተናገረ።
❤ ከዚህም በኋላ ፈጽሞ በአረጀ ጊዜ ሐምሌ ሰባት ቀን ተኛ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መጥቶ እያረጋጋው በእርሱ ዘንድ ተቀመጠ። ብፁዕ አባ ሲኖዳም ጌታችንን እንዲህ አለው "ጌታዬ ፈጣሪዬ ልዩ ሦስትነትህንና ጌትነትህን ስለሚነቅፉ ከሀድያን ወደ ጉባኤው እሔድ ዘንድ እንዲጠሩኝ ሊቀ ጳጳሳቱ ወደ እኔ ልኳልና እንደቀድሞው ታጸናኛለህን?"። ጌታችንም በጸጋና በጥዑም ቃል እንዲህ ብሎ መለሰለት "ወዳጄ ሲኖዳ ሆይ ሌላ ዕድሜ ትሻለህን?። እነሆ ዕድሜህ ሁሉ መቶ ሃያ ዓመት ከሁለት ወር ሁኖሃል ዕድሜህ ዘጠኝ ዓመት ሲሆን አስኬማን ለበስኽ ከዚያ በኋላ መቶ ዐሥራ አንድ ዓመት ከሁለት ወር ኖርኽ አሁንስ ድካምህ ይብቃህ" ይህንንም ብሎ ጌታችን በክብር ዐረገ።
❤ በዚያንም ጊዜም የቅዱሳን አንድነት ማኅበር ወደርሱ መጡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ዳግመኛ አየው ልጆቹንም ክብር ይግባውና "ለጌታዬ ለኢየሱስ ክርስቶስ እሰግድ ዘንድ አንሱኝ" አላቸው አንሥተውትም ሰገደለት። ከዚህም በኋላ ዳግመኛ እንዲህ አላቸው "ወደ እግዚአብሔር አደራ አስጠብቅኋችሁ ነፍሴም ከዚህ ከደካማው ሥጋዬ የምትለይበት ጊዜ ደርሷል እኔም ለአባታችሁ ለዊዳ እንድትታዘዙ አዝዛችኋለሁ ከእኔ በኋላ ጠባቂያችሁ እርሱ ነውና" አላቸው።
❤ ለልጆቹም ይህን በተናገረ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "የመረጥሁህ ሲኖዳ ሆይ ብፁዕ ነህ ቸርነቴም ይደረግልሃል በሕይወትህ ዘመን ሁሉ አንተ የምወደውን ሥራ ሠርተሃልና እንግዲህ ወደ ዘለዓለም ተድላ ታርፍ ዘንድ ወደእኔ ና" አለው። ያን ጊዜም ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛን በአባ ሲኖዳ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
