en
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

Open in Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

Show more
611
Subscribers
No data24 hours
+17 days
-1030 days
Posts Archive
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #መጋቢት ፲፪ (12 ) ቀን። ❤ እንኳን #ለሊቀ_መላእክት_ለቅዱስ_ሚካኤል ወደ #ፈላስፋው_በለዓም ለተላከበት ወራዊ መታሰቢያ በዓልና ለከበረና ለተመሰገነ ለእስክንድርያ ዐሥራ ሁለተኛ ሊቀ ጳጳሳት #ለአባ_ድሜጥሮስ ለልደቱና ድንግልናውን ለገለተለጠበት ቀን መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ ከፍልስጥዔም አገር ከሆነ #ከቅዱስ_መላዚ በሰማዕትነት ከዐረፈ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                              ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #ቅዱስ_ሚካኤል_ወደ_በለዓም_መላክ፦ በለዓምን እስራኤልንም ይረግማቸው ዘንድ ባላቅ በጠራው  ጊዜ። በጐዳናም በፊቱ ቅዱስ ሚካኤል ቆሞ ስለተገለጠ አስደንግጠው አህያው በሰው አንደበት እስተናገረች ድረስ። መርገሙንም ወደ በረከት መለሰው። በቅዱስ ሚካኤል በአማላጅነቱ ለዘላለሙ ይጠብቀን አሜን።                                             ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #ቅዱስ_ድሜጥሮስ፦ ድንግልናው የመገለጡ ምክንያት እንዲህ ነው ከእርሱ በፊት ሊቀ ጳጳሳት ለነበረው ለቅዱስ ዮልያኖስ መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገልጦለት "አንተ ወደ ክብር ባለቤት ወደ ክርስቶስ ትሔዳለህ የወይን ዘለላ ይዞ ነገ ወደ አንተ የሚገባ ሰው ከአንተ በኋላ ሊቀ ጳጳስ ሊሆን የሚገባው እርሱ ነው" አለው። ❤ ማግስት በሆነ ጊዜም የከበረና የተመሰገነ  ድሜጥሮስ የወይን ዘለላ ይዞ ወደ ከበረ ዮልያኖስ ዘንድ ገባ ቅዱስ ዮልያኖስም ያዘው "ከእኔ በኋላ ሊቀ ጳጳሳታችሁ እንሆ" ብሎ ለሕዝብ አስረከባቸው ስለእርሱም የእግዚአብሔር መልአክ እንደተገለጠለት ነገራቸው። ❤ አባ ዮልያኖስም በዐረፈ ጊዜ በወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ወንበር ላይ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት በወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ወንበር ከእርሱ በቀር ሚስት ኑራው የተሾመ የለም። ❤ ሰይጣንም በሰዎች ልቡና አደረ። በእርሱ ላይም በመናገር የሚያሙት ሆኑ። ስለዚህም ነገር ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለቅዱስ ድሜጥሮስ ተገልጦ እንዲህ አለው "ከሕዝቡ የሚያሙህ አሉና ከልባቸው ጥርጥርን ልታርቅ ይገባሃል። ከሚስትህም ጋር ያለውን የገድልህን ምሥጢር ልትገልጥላቸው ይገባሃል አንተ ራስህን አድነህ በአንተ ምክንያት ሌሎች ይጠፉ ዘንድ አይገባህም ቸር  ከሆንክስ ወገኖችህን ለማዳን ትጋ" አለው። ❤ ማግስት በሆነ ጊዜም ይህም መጋቢት ዐሥራ ሁለት ቀን ነው የቁርባንን ቅዳሴ ቀደሰ። ሕዝቡንም እንዲጠብቁ እንጂ ከቤተ ክርስቲያን እንዳይወጡ አዘዛቸው። ደግሞ እሳትን እንዲያነዱ አዘዛቸው ወደ ሴቶች መቆሚያም ልኮ ሚስቱን አስመጣት ከሥራው የተነሣ ሕዝቡ ያደንቁ ነበር ምን ሊሠራ እንደፈለገ ሕዝቡ አላወቁምና። ❤ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ድሜጥሮስ ተነሥቶ ተንቀሳቀሰ ከእሳቱ መካከል ገብቶ በመቆም በእሳቱ እየነደደ በውስጡ ጸለየ ከእሳቱም ፍም በእጁ ዘግኖ በልብሰ ተክህኖው ላይ አኖረ በእሳቱ ውስጥም ቁሞ ለረጅም ጊዜ ጸለየ በልብሰ ተክህኖው ውስጥ ያለ እሳቱንም አይቀጣጠልም። ከዚህም በኋላ ሚስቱን ጠርቶ ያንን እሳት በመጐናጸፊዋ ውስጥ  ጨመረ ረጅም ጸሎትም ጸለየ  ከልብሶቻቸው ምንም ምን አላቃጠለም። ሕዝቡም አድንቀው እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ❤ ሕዝቡም ይህን ሥራ በምን ምክንያት እንደሠራ ያስረዳቸው ዘንድ የከበረ ቅዱስ ድሜጥሮስን ለመኑት። እርሱም ከሚስቱ ጋራ ያለውን ገድሉን ገለጠላቸው "ያለውዴታው እርሷም ጋብቻ ሳትሻ እንዳጋቡት እንዲህም አለ እነሆ በአንድነት እኛ አርባ ስምንት ዓመት ስንኖር በጋብቻ ሥርዓት ከተገናኘንበት ጊዜ ጀምሮ በአንድ አልጋ አንድ ልብስን እንተኛለን ግን ወንዶች ሴቶችን በግብር እንደሚአውቋቸው ሴት እንደሆነች አላውቃትም። በዚህ ሁሉ ዘመን በየሌሊቱ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ እየወረደ በክንፎቹ ይሸፍነናል። ይህንንም በዚህ ሁሉ ዘመን ከሰው ወገን ለማንም ከቶ አልገለጥኩም። ልገልጠውም ከቶ አልሻምና ግን እናንተ ከበደል ትድኑ ዘንድ እርሱ እግዚአብሔር አዘዘኝ እንጂ" አላቸው። ❤ ከአዩትና ከሰሙት የተነሣ ሕዝቡ እጅግ አደነቁ እግዚአብሔር አመሰገኑት እርሱን ስለማማታቸው የበደሉትን በደል ይቅር ይላቸው ዘንድ እያለቀሱ ቅዱስ ድሜጥሮስን ለመኑት። እርሱም ስሕተቻቸውን ይቅር ብሎ "በጎ ሥራን ከሚጠላ ከሰይጣን እንጂ ከእናንተ አይደለምና አትዘኑ" አላቸው። ❤ ከዚህም በኋላ ባረካቸው ወደ ቤታቸውም ይገቡ ዘንድ በሰላም በፍቅር አሰናበታቸው ከሊቀ ጳጳሳቱ ከቅዱስ ድሜጥሮስ ከአዩት ተአምራት የተነሣ እግዚአብሔር እያመሰገኑ ወደ ቤታቸው ገቡ። ከቅዱስ ድሜጥሮስ በጸሎቱ የምትገኝ በረከት ከእኛ ጋር ለዘላለም ትኑር። ምንጭ፦ የመጋቢት12 ስንክሳር።                              ✝️ ✝️ ✝️ ❤ "#ሰላም_ለድሜጥሮስ እንተ በእዴሁ ተጽሕፋ። ሐሳበ አዝማን ዘድኅር ወእለ ኀለፋ። አርአየ ዮም ኃይለ ድንጋሌሁ በሥምረተ አምላክ አልፋ። ዐቊሮ እሳት በኵፋሩ ወለብእሲቱ በዓጽፋ። ለእለ ናፈቁ ሕዝብ ከመ ይኩን ተስፋ"።                            ✝️ ✝️ ✝️ ❤ "#ሰላም_ለከ_ሰማዕት_መላዚ። ዘምድረ ፍልስጥዔም ወልደ አግአዚ። ምሕረተ ነድያን እለቡ እንዘ ኢይሴዚ። ከመ ታምክረኒ ነዓ ናዛዚ። ቅድመ ይዳደቀኒ ሊተ እደ ሞት አኀዚ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመጋቢ_12።                          ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "አእይንትየሰ ኀበ መሃይምናን ምድር። ከመ አንብሮሙ ምስሌየ። ዘየሐውር በፍኖት ንጹሕ ውእቱ ይትለአከኒ። መዝ 100፥6-7። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥1-17።                          ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ_ምሰባክ፦" ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዓውዶሙ። ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ። ጠዐሙ ወታምእሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር"። መዝ33፥7-8። የሚነበበው ወንጌል ማቴ18፥10-21።  የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 7፥1-8፣ 2ኛ ጴጥ 2፥9-ፍ.ም እና የሐዋ 27፥1-11። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ሚካኤል ወራዊ በዓልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።                  

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #መጋቢት ፲፪ (12 ) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ "በዓለም ነግሦ መኖር አልፈልግም" ብለው ለመነኑ፤ #ለንጉሡ_ዐፄ_ዳዊት_ልጅና_ለዐፄ_ዘርዓያዕቆብ_ወንድሜ_ለሆኑት፤ በመስቀላቸው በመባረክ በሐምሌ ወር የዠማን ወንዝ አቁመው ለተሻገሩ ለታላቅ አባት #አቡነ_ተስፋ_ጽዮን_ዘሸዋ ለዕረፍቸው በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ተስፋ_ጽዮን፦ የተባሉት ጻድቅ አገራቸው ሸዋ ሲሆን የንጉሡ የዐፄ ዳዊት ልጅና የዐፄ ዘርያቆብ ወንድሜ ናቸው። ስንክሳሩ መናኔ መንግሥት ወብእስት በማለት ይጠራቸዋል። "በዓለም ነግሦ መኖር አልፈልግም" በማለት የዓለምን ጣዕም ንቀው በመተው ገዳም ገብተዋል። በታላቅ ተጋድሎ እየኖሩ አጠቃላይ የመርሐ ቤቴ ገዳማትን ሲመሩና ሲያስተዳድሩ ነበር። ❤ ጻድቁ በመስቀላቸው በመባረክ በሐምሌ ወር የዠማን ወንዝ አቁመው የተሻገሩ ታላቅ አባት ናቸው። ብዙ ሙታንን በማስነሣትና ታላላቅ ተአምራትን በማድረግ ነው ወንጌልን ሲሰብኩ የነበረው። በተለያየ አገር የሚኖሩ ቢሆኑም ከወለቃው አቡነ ዘአማሩኤል ጋር በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እየተገናኙ ስለ ገዳማት ይወያዩ ነበር። ጻድቁ በትግራይ ትልቅ ገዳም ያላቸው ሲሆን በደብረ በግዕና በዜና ማርቆስ ገዳም ደግሞ ቅዱስ ገድላቸው ይገኛል። ጻድቁ ከብዙ ተጋድሎ በኋላ ጌታችን ተገልጦላቸው ታላቅ ቃልኪዳን ከሰጣቸው በኋላ መጋቢት12 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል። ከአባታች አቡነ ተስፋ ጽዮን ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦መዝገበ ቅዱሳን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #መጋቢት ፲፩ (11) ቀን። ❤ እንኳን #ለቅዱስ_ቴዎቄጤኖስ፣ ለብፅዕት #ቅድስት_እስክንድራ በንጉሥ መክስምኖስ ዘመን ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓልና #ለተጋዳይ_ለሆኑ_ለኤጲስቆጶስ በመኰንኑ ልጅ መቃብር ላይ ጸሎት አድርገው ልጁን ከሞት ላስነሱና ሕዝቡን አሳምነው ላጠመቁ #ለአባ_ባስሊዖስ ሰማዕትነት ለተቀበሉት ለዕረፍታቸው በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከቅዱሳን_ከአውሳብዮስ_ከኤፍሬም_ከአርቃድዩና ከሰማዕቱ ኤልያስ ከመታሰቢያቸው ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                      ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_ቴዎቄጤኖስ፦ ይህ ቅዱስ አስቀድሞ ወታደር ነበር። ትጥቁን በንጉሡ ፊት ጥሎ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ታመነ ከርሱም  ጋር ብፅዕት እስክንድራ አለች። ❤ ንጉሡም ሰምቶ ተቆጣ ልብሱን አስወልቀው የሴቶች ልብስ አልብሰው ከሚፈትሉ ሴቶች ጋር እንዲጨምሩት ከዚያም የጋለ የብረት መንኰራኵር በላዩ አድርገው ዘቅዝቀው ቊልቊል እንዲሰቅሉት አዘዘ። ሁለተኛም እንዲህ ብሎ አዘዘ "የፈላ ቅጥራን የተመላ ወጭት አምጥታችሁ ወደ ጆሮው እስቲደርስ በራሱ ላይ ድፉበት ደግሞ ከተሰቀለበት አውርደው ከእሥረኛዋ እስክንድራ ጋር በፊቱ እንዲያቆሙት" አዘዘ። ከዚህም በኋላ ምላሱን እንዲቆርጡ አዘዘ በእሊህ ቅዱሳን በአንገቶቻቸው የሚካበዱተጋድሎአቸውንና ድንጊያዎችን አሥረው በኤፍራጥስ ወንዝ ውስጥ እንዲጥሉአቸው አዘዘ። በዚያም  ምስክርነታቸውን መጋቢት11 ፈጸሙ ሥጋቸውንም ምእመናን አግኝተው በሥውር ቦታ ቀበሩት። የቅዱስ ቴዎቄጤኖስ በረከታቸው ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ባስሊዖስ፦ ይህንንም ቅዱስ የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት አባ አርሞን ከሌሎች ኤጲስቆጶሳት  ጋር ሾመው። በታወቀና በተወሰኑ ቦታ ላይ አይደለም። በእምነት በሌላቸው በአረማውያን አገር ይሰብክ ዘንድ ላከው እንጂ። ❤ ይህም ቅዱስ ወደ ከሀድያን አገር ገብቶ የከበረ ወንጌልን ሰበከ። እነርሱም እየደበደቡ በአገራቸው ሁሉ አዞሩት። ደግሞ ወደ ሠርዑና አገርሮች ገብቶ የከበረ የወንጌል ትምህርትን አስተማረ። እኩሌቶቹ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ። ያላመኑት እኩሌቶቹ ከሀዲያን አስደዱት ከከተማው ውጭ ወጥቶ በዋሻ ውስጥ ተቀመጠ። የዚያች አገር ስዎች እግዚአብሔር ወደ ማወቅ ይመለሱ ዘንድ በአንድ ልጁም ያምኑ ዘንድ ስለዚያች አገር ሰዎች አዘወትሮ እግዚአብሔር ማለደ። ❤ በዚያንም ሰሞን ለእርሱ ለአባቱ አንድ ብቻውን የሆነ የመኰንኑ ልጅ ሞተ። አባቱም ታላቅ ኀዘንን አዘነ መኰንኑ አባቱም በሕልምሙ ልጁን አየው። እርሱም በፊቱ ቁሞ "አባቴ ሆይ እንሆ እኔ በታላቅ ጨለማ ውስጥ ነኝና ወደ ክርሰቶስ ስለ እኔ  ይጸልይ ዘንድ ኤጲስቆጶሱ አባ ባስሊዖስን ጠርተህ ለምነው ሲለው ነበር"። ከእንቅልፋም በነቃ ጊዜ ደንግጦ ተነሣ ከእርሱም ጋር የአገር ታላላቆችን ይዞ ወደ ቅዱስ ባስሊዖስ በዓት ሔዶ። ከእርሱ ጋራም ወደ ከተማ ገብቶ ስለ ልጁ እንዲጸልይ ለመነው። እርሱም ልመናውን ተቀብሎ። ወደ ከተማ ገባ በመኰንኑ ልጁ መቃብር ላይም ጸለየ ያንጊዜም የመኰንኑ ልጅ ድኖ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ተነሣ መኰንኑ ሕዝቡም ሁሉ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ። ከአገርም ሰዎች ብዙዎች አምነው የክርስትና ጥምቀትን በቅዱስ ባስሊዖስ እጅ ተጠመቁ በዚያቺም አገር ታላቅ የክርስቲያኖች ጉባኤ ሆነ። ❤ ክፉዎች ሰዎችም ባስሊዖስን ቀንተውበት በጠላትነት ተነሡበት በክርስቶስ ከማያምኑ ጋር ተሰባስበው ወደ ሸንጓቸውም አደረሱት ይህን ቅዱስ  ታላቅ ግርፋትን ገረፉት ነፍሱንም በጌታችን እጅ እስከሰጠ ድረስ እያሠቃዩ በዚያች አገር አዋሉት። የቅዱስ ባስሊዖስ በረከቱም ከእኛ ጋር ለዘላሙ ይሁን አሜን። ምንጭ፦ የመጋቢት11 ስንክሳር።                                                  ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለቴዎቄጤኖስ_ዘአድኀኖ°አምተኃጒሎ። ተመትሮ ልሳኑ ኢክህለ ለነቢበ ቃሉ ያብጥሎ። ለእስክንድራ ብፅዕት እንተ ተሳተፈት ገድሎ። ዕብንኒ ዘመኰንን ሰቀሎ። ከመ ልጥረ ፀምር ለክሣዱ ቀሎ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመጋቢት_10።                                                  ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ፍታሕ ሊተ እግዚኦ እስመ አንሰ በየዋሃትየ (በየውሃትየ) አሐውር። ወተወከልኩ በእግዚአብሔር ከመ ኢይድክም። ፍትነኒ እግዚኦ ወአመክረኒ"። መዝ 25፥1-2። የሚነበቡት መልዕክታት ቲቶ 1፥1-6፣ ያዕ 214-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 27፥22-27። የሚነበበው ወንጌል ማቴ18፥1-12። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ባስልዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የአቡነ አሌፍ የዕረፍት በዓልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤          ❤ #መጋቢት ፲፩ (11) ቀን። ❤ እንኳን #ከተስዓቱ_ቅዱስ ለአንዱ ኤርትራ ጠረፍ አካባቢ የሚገኘው ደብረ ብኅዛን (አኅሰአ) ለመሰረቱት #ለአቡነ_አሌፍ_ለዕረፍታቸው_በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                                                     ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_አሌፍ፦ ጻድቁ ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮዽያ ቢሆንም ሃገረ ሙላዳቸው የጥንቱ የሮም ግዛት የሆነችው ታናሽ እስያ ናት። አባ አሌፍ ከዘጠኙ (ተስዓቱ) ቅዱሳን አንዱ ናቸው። ዘጠኙ ቅዱሳን ተወልደው ያደጉት ምንም በአንድ የሮም ግዛት ሥር ቢሆንም መነሻ ቦታቸው ግን የተለያየ ነው። ❤ ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው መንፈስ ቅዱስ በኪነ ጥበቡ ነው። በምክንያት ደረጃ እንግለጸው ከተባለ ደግሞ የአንድነታቸው ምሥጢር:- 1.የቀናች ሃይማኖታቸው ተዋሕዶ። 2.ዓላማ (የእግዚአብሔር መንግስት) እና 3.ገዳማዊ ሕይወት ነው። ❤ አባ አሌፍን ጨምሮ ሁሉም ቅዱሳን ዘራቸው ከቤተ መንግስት ነው። እነርሱ ግን ምድራዊውን ክብር ንቀው ሰማያዊውን ክብር ገንዘብ ማድረግን መርጠዋል። አስቀድመው ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጠኑት አበው በተለያየ ጊዜ እየመነኑ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ በርሃዎች ወርደዋል። ❤ በምናኔ ቅድሚያውን አባ ዸንጠሌዎንና አቡነ አረጋዊ ይይዛሉ። ዘመኑ የተዋሕዶ አማኞች የሚሰደዱበት 5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነበርና እምነትን ላለመለወጥ ዘጠኙ ቅዱሳን ስደትን መረጡ። ❤ በወቅቱ ደግሞ ለስደት መጠለያ የምትሆንና ከኢትዮዽያ የተሻለች ሃገር አልነበረችም። ስለዚህም በ470ዎቹ ዓ.ም አልዓሜዳ በኢትዮዽያ ነግሦ ሳለ ቅዱሳኑ በአረጋዊ መሪነት መጡ። ❤ ንጉሡም ሲጀመር የእግዚአብሔር እንግዳ ስለሆኑ ሲቀጥል ደግሞ ቅድስናቸውን ተመልክቶ መልካም አቀባበልን አደረገላቸው። ማረፊያ ትሆናቸውም ዘንድ አክሱም ውስጥ አንዲት ቦታን ወስኖ ሰጣቸው። ይህች ቦታ ቤተ ቀጢን ትባላለች። አባ አሌፍና 8ቱ ቅዱሳን ወደ ሃገራችን እንደ ገቡ የመጀመሪያ ሥራቸው ቋንቋን መማር ነበር። ❤ ልሳነ ግእዝን በወጉ ተምረው እዛው አክሱም አካባቢ ሥራቸውን አንድ አሉ። በወቅቱ በአቡነ ሰላማ: በአብርሃ ወአጽብሐና በአቡነ ሙሴ ቀዳማዊ የተቀጣጠለው ክርስትና በተወሰነ መንገድ ተቀዛቅዞ ነበርና እነ አባ አሌፍ እንደ ገና አቀጣጠሉት። ❤ ሕዝቡን በራሱ ልሳን ለክርስትና ይነቃቃ ዘንድ ሰበኩት። የካደውን እየመለሱ፤ የቀዘቀዘውን እያሟሟቁ ለዓመታት ወንጌልን ሰበኩ። ቀጣዩ ሥራቸው ደግሞ መጻሕፍትን መተርጐም ሆነ:: ❤ ከሃገራቸው ያመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ተከፋፍለው ወደ ግዕዝ ልሳን ተረጐሟቸው። በዚህም ለሃገራችን ትልቁን ውለታ ዋሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን እነ አባ አሌፍ የሚመገቡትም ሆነ የሚጸልዩት በማሕበር ነበር። በመካከላቸውም ፍጹም ፍቅር ነበር። ጸጋ እግዚአብሔር አልተለያቸውም:: ❤ የነ አባ አሌፍ ቀጣዩ ተግባራቸው ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትን ማስፋፋት ሆነ። ይህንን ለማድረግ ግን የግድ መለያየት አስፈለጋቸው። እያንዳንዱም መንፈስ ቅዱስ ወደ መራው ቦታ ሔደ። *ዸንጠሌዎን በጾማዕት:: *ገሪማ በመደራ:: *ሊቃኖስ በቆናጽል:: *አረጋዊ በዳሞ:: *ጽሕማ በጸድያ:: *ሌሎችም በሌላ ቦታ ገዳማትን መሠረቱ። *አባ ይምዓታ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምርጫቸው ገርዓልታ (እዛው ትግራይ) ሆነ። ❤ አባ አሌፍ የተወለዱት አውሎግሶንና አትናስያ ከተባሉ ደጋግ ወላጆች ቂሳርያ ውስጥ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው። ጻድቁ በሕጻንነታቸው ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ገብተው ከዓመታት ተጋድሎ በሁዋላ ከ8ቱ ጉዋደኞቻቸው ጋር ወደ ኢትዮዽያ የመጡ ሲሆን ከተስዓቱ /9ኙ/ ቅዱሳን አንዱ ናቸው። ❤ በዐፄ አልዓሜዳ ዘመን አክሱም አካባቢ (ቤተ ቀጢን) የሃገራችንን ቋንቋ አጥንተው ቅዱሳት መጻሕፍትን ተርጉመዋል። ለሕዝቡም የወንጌልን የምሥራች ሠብከዋል። ❤ ከዚያም ገዳም መሥርተው፤ 500 መነኰሳትን ሰብስበው ለ70 ዓመታት በቅድስና ኑረዋል። ለዘጠኙ ቅዱሳን ሁሉ ስም ያወጡት የዘመኑ ሰዎች ቀድመው ወደ አክሱም ስለ ገቡ ጻድቁን "አሌፍ" ብለዋቸዋል። በዕብራይስጥኛ "አንደኛ" ማለት ነው። ጻድቁ ከፈጣሪያቸው የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብለው በዚሕች ቀን አርፈዋል። ከአባታችን ከአቡነ አሌፍ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ ዝክረ ቅዱሳን ዘተዋሕዶ ከዲያቆን ዮርዳኖስ መጽሐፍ።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #መጋቢት ፲ (10) ቀን። ❤ እንኳን #ለክብር_ባለቤት_ለጌታችን_ለአምላካችን_ለመድኃኒታችን_ለኢየሱስ_ክርሰቶስ_ለመስቀሉ_በንግሥት_ዕሌኒ አማካኝነት ተቆፋሮ ለተገኘበት፣ በድጋሚ በፋርሶች ከኢየሩሳሌም ተወስዶ እንደገና #በሮሜው_ንጉሥ_ሕርቃል ለተገኘበት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                                                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የቅዱስ_መስቀሉ_መገኘት_ታሪክ፦ የዚህም የከበረ ዕፀ መስቀል መገለጡና መገኘቱ ሁለት ጊዜ ሁኖአል። መጀመርሪያ የጻድቁ ንጉሥ የቈስጠንጢኖስ እናት በሆነች በንግሥት ዕሌኒ እጅ ነው። እርሷ ለእግዚአብሔር ተስላ ነበርና ልጅዋ ቈስጠንጢኖስ ወደ ክርሰቲያን ሃይማኖት ቢገባ ወደ ኢየሩሳሌም ሒዳ መስቀሉን እስከ አገኘችው ድረስ ልትፈልገው በኢየሩሳሌምም ያሉ ቅዱሳን መካናትንና አብያተ ክርስያናትን ልታንፃቸው ነው። ❤ ከዚህ በኋላ ልጅዋ አምኖ የክርስትና ጥምቀትን በተጠመቀ ጊዜ ዕሌኒ ቅድስት ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች ከእስዋ ጋራም ብዙ ሠራዊት ነበር ደርሳም ስለ ከበረ መስቀል መረመረች ቦታውንም የሚአስረዳት አላገኘችም የአይሁድ ወገን የሆነ ሽማግሌ ሰው አሥራ በረኃብና በጥማት አስጨነቀችው። በተጨነቀም ጊዜ ለንግሥት ዕለኒ የጎልጎታን ኮረብታ አስጠርጊ ብሎ ነገራት እርሷም ይጠርጉ ዘንድ አይሁድን አዘዘቻቸው። ቤቱን የሚጠርግ ሰው ሁሉ ጥራጊውን በውስጡ የከበረ መስቀል በአለበት በጌታችን መቃብር ላይ እንዲጥል አይሁድ አስቀድመው አዝዘው ነበርና ንግሥት ዕሌኒ እስከ ደረሰችበት ጊዜ ከሁለት መቶ ዓመት በላይ ጥራጊያቸውን ሲጥሉበት ኖሩ ኮረብታም ሆነ። ❤ አይሁድም በጠረጉ ጊዜ ሦስት መስቀሎች ተገለጡ የክቡር ባለቤት ክርሰቶስ የተሰቀለበት የትኛው እንደሆነ አላወቁም። የሞተ ሰውም አግኝተው አመጡ። አንዱንም መስቀል አምጥተው በሞተው ሰው ላይ አኖሩት አልተነሣም ደግሞ ሌላውን መስቀል አምጥተው በሙቱ ላይ አኖሩ አሁንም አልተነሣም ከዚህም በኋላ ሦስተኛውን መስቀል አምጥተው በሙቱ ላይ አደረጉት ያንጊዜ የሞተው ሰው ተነሣ ዕሌኒም የክርስቶስ መስቀል እንደሆነ አውቃ ሰገደችለት የክርስያንም ወገኖች ሁሉ ሰገዱለት። ለልጅዋ የላከችው ይህ መስቀል ነው የሚል መጽሐፍ ይገኛል የቀረው ግን ግንዱ በውስጡ ተተክሎበት የነበረው ከእርሱም እኩሌታውን ከቅንዋቱ ጋር ወደ ልጅዋ የላከችው ነው። ❤ ከዚህም በኋላ ሥርዓታቸውና የሕንፃቸው ነገር በመስከረም ወር በዐሥራ ሰባት ተጽፎ የሚገኝ አብያተ ክርስያናትንና የከበሩ ቦታዎችን አነፀች።                                ✝ ✝ ✝ ❤ #ሁለተኛው_በሮሜ_ንጉሥ_በሕርቃል_ዘመን የሆነው ሲሆን የፋርስ ሰዎች በግብጽ አገር ሳሉ ወደ አገራቸው ሊመለሱ ወደዱ። ከሹማምንቶቻቸው አንዱ የጦር መኰንን ተነጥሎ ወደ ኢየሩሳሌም አልፎ ደረሰ ወደ ከበረ መስቀል ቤተ ክርስቲያንም ገባ። መስቀሉም በላዩ በተተከለበት ግንድ ፊት ታላቅ ብርሃን ሲበራ አይቶ ሊያነሣው እጁን ዘረጋ። እሳትም ወጥታ እጁን አቃጠለችው። ❤ ከክርስቲያን በቀር ማንም ሊነካው እንማይችል የመስቀልን የክብሩን ነገር ሰዎች ነገሩት። ሁለት ዲያቆናትንም ይዞ የከበረ መስቀልን እንዲሸከሙ አዘዛቸው። ከኢየሩሳሌምም ብዙ ሰዎችን ማርኮ ወደ አገሩ ተመለሰ። ❤ የፋርስ ሰዎች ኢየሩሳሌምን እንዳጠፏት ብዙዎች ሰዎችንም እንደማረኩና የከበረ የክርስቶስንም መስቀሉን እንደ ወሰዱ የሮም ንጉሥ ሕርቃል በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ። ስለርሱም እንዲጾሙ ምእመናንን አዝዞ ወደ ፋርስ ዘምቶ ወጋቸው ብዙዎችንም ገደላቸው የከበረ ዕፀ መስቀልንም እየፈለገ በአገራቸው ሁሉ ዞረ ግን አላገኘውም። ❤ ያ ዲያቆናቱንና መስቀሉን የወሰደ መኰንን ከቦታዎች በቤቱ አንጻር ባለ በአንድ ቦታ ላይ ወስዷቸው ጥልቅ ጉድጓድ እንዲቆፍሩ አዝዞ በዚያ የከበረ መስቀልን አስቀበረ እነዚያንም ዲያቆናት ገደላቸው። ነገር ግን ያ መኰንን የማረካት የካህናት ወገን የሆነች በእርሱ ቤት የምትኖር አንዲት ብላቴና ነበረች። እርሷ የከበረ መስቀልን ሲያስቀብርና ሁለቱን ዲያቆናት ሲገድላቸው በቤቱ ውስጥ ሁና በመስኮት ትመለከት ነበር ወደ ንጉሥ ሕርቃልም ሒዳ መኰንኑ ያደረገውን ሁሉ ነገረችው። ይህንም ንጉሥ ሰምቶ እጅግ ደስ አለው ያቺ ብላቴናም መራችው ከእርሱም ጋር ብዙ ሠራዊት ሁኖ ኤጲስቆጶሳትና ካህናትም ነበሩ። ወደ ቦታውም እስከምታደርሳቸው ያቺን ልጅ ተከተሏት ቆፍረውም የከበረ ዕፀ መስቀልን አገኙ ከዐዘቅቱም አወጡት ንጉሡና ሠራዊቱም ሰገዱለት። በልብስ መንግሥቱም አጐናጸፈው ታላቅ ክብርንም አከበረው እጅግም ደስ አለው ከሠራዊቱ ጋር። ❤ የዚህም መስቀል ሁለተኛ የተገለጠበትና የተገኘበት በዚች ቀን በመጋቢት ዐሥር ነው። ከዚህ በኋላ ንጉሡ የከበረ ዕፀ መስቀልን ተሸክሞ ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ ወሰደው። የመድኃኒታችን የመስቀሉ በረከት ከሁላችን የክርስቲያን ወገንኖች ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የመጋቢት 10 ስንክሳር።                                                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ። ወየሐውር እምኃይል ውስተ ኃይል። ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን"። መዝ 83፥6-7። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥1-17።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ። ከመ ያምሥጡ እምገጸ ቅስት። ወይድኀኑ ፍቁራኒከ"። መዝ 59፥4-5። የሚነበቡት መልዕክታት ገላ 6፥1-ፍ.ም፣ ያዕ 4፥1-11 እና የሐዋ ሥራ 24፥1-13። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 16፥24-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዳሴ ነው። መልካም የመስቀለ ኢየሱስ በዓልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤                ❤ #መጋቢት ፲ (10) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያ_ጻድቅ ታላቁን ዲማ ጊዮርጊስን ለመሠረቱ #አቡነ_ተከስተ_ብርሃን_ዘደብረ_ድማኅ ለዕረፍታቸው በዓል መታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ተከስተ_ብርሃን፦ ትውልድ ቦታቸው መንዝ ከሚባለው አገር ነው። ይህች መንዝ የምትባለው አገር የምትገኘው በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ በተለየች በደብረ ብርሃን አውራጃ ውስጥ ነው። መንዝ ማለትም ነዝሀ ከሚለው ከግእዝ ቃል የተገኘ ነው። መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል እግዚአብሔር በሰጠው (በፈቀደለት) ስልጣን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም በሰጠው ተስፋ በተወለደ በ33 ዓመት ከ3 ወር ወንጌልን አስተምሮ ለድኅነተ ዓለም መጋቢት 27 ቀን በዕለተ አርብ በተሰቀለ ጊዜ የፈሰሰ ደሙን በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ በብርሃን መነሳንስ ዓለምን ሲረጭ አስቀድሞ ይችን መንዝ የምትባልን አገር ከሁሉ አስቀድሞ ስለረጫት ደመ መለኮቱን እንደ አውድማ ስለለቀለቀው በዚህ ምክንያት መንዝ ተብላለች። ❤ በዚች ቦታ ብዙ ቅዱሳን ተፀንሰው ተወልደውባታል። ከነዚህም ቅዱሳን በአካባቢውና በዚች ቦታ የተወለዱ እነ ቅዱስ ፊልጶስ፣ እነ ቅዱስ አኖሬዎስ፣ እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ እነ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ እርሷ የመሰሉ ብዙዎች ቅዱሳን ተፀንሰው ተወልደው አድገውበታል። ይህች ቦታም የተባረከች የተቀደሰች መሆኗ ቅዱስ አባታች ተፀንሰው እዲወለዱ አድርጋለች። ❤ እኚህ አባታችን አቡነ ተከስተ ብርሃን የመጀመርያ ስማቸው አባ በኪሞስ ይባላል። እኚህ አባ በኪሞስ ከመንዝ መንኖ ደብረ ሊባኖስ ሲረዱ ቆይቶ ወደ ጎጃም ክፍለ ሀገር በ12ኛው ክፍለ ዘመን በአምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት እንደ መጡ ገድላቸው ይናገራል። መጥተውም የተቀመጡበት ቦታ ቢቸና አውራጃ ድማ ጊዮርጊስ ነው። ከዚያም አባታቸው አቡነ ፊልጶስ ወደ ትግራይ ሲሰደዱ እሳቸውም ተሰደው ብዙ ጊዜ ከቆዩ በኋላ መምህራቸው አቡነ ፊልጶስ "ወደጎጃም ክፍለ አገር ሂደህ አስተምር" አሉት። ❤ ከዚያ ተነስተው በግሸና አድርገው የዐባይ ባሕር ተከፍሎላቸው ወደ ጎጃም ክፍለ አገር ተሻግረው አስተምረው በአንድ ቀን ዘጠኝ ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ (9999) ምዕመናንን ሲያጠምቁ አምደ ብርሃን ተተክሎ እያበራ ከዚያች ቦታ ስለታየ በኪሞስ ይባል የነበረ ስማቸው ተከስተ ብርሃን ተባሉ። ወንዚቱም እሳት ዙሪያዋን ስለከበባት ነድ ሐጸረ ተብላ ዛሬም ነድ አጥራ እየተባለች ትጠራለች። ከዚህ ተነስተው ወደ ቢቸና አውራጃ እነማይ ወረዳ ውስጥ አንድ ጫካ አገኘ። ከዚያም የያዙትን ታቦት በአንድ ዋሻ አኑረው። ስሟንም ዲማ ማርያም አሏት። ❤ ከዚህ በኋላ ተነስተው ገድ ወንዝ ላይ የነበረችቱን ብዙ ሕዝቦች ይሰግዱላት ያመልኳት የነበረችቱን ሙላድን ከዚያ አባረው ሰኔ 21 ቀን አገው ምድር እንጁባራ ላይ አድርሰዋት ተመልሰው ሲመጡ ዐባይን ተሻግረው ጉታ ሲደርሱ ከዚህ ናዳ ማርያም ገዳም ዐርፈው እንደሄዱ ገድላቸው ይናገራል። ከዚያ ተነስተውም ወደ ዲማ ሂደዋል። ከዚያም ድማ ማርያም የምትባል ተክለዋል። ድማ ማለት በኦሮምኛ ቋንቋ ቀይቱ ማርያም ማለት ነው። ❤ ከዚያም የወንዶችና የሴቶች ገዳም አቋቁመው ብዙ ጊዜ ከቆዩ በኋላ መጋቢት 9 ቀን ታመው ብዙ ቃል ኪዳን ተቀብለው ስምህን የጠራ፣ በዓልህን ያከበረ፣ ዝክር የዘከረ እስከ 22 ኛው ትውልድ እምርልህለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ከሰጣቸው በኋላ መጋቢት 10 ቀን ዐርፈዋል። በዚያው ባቋቋሙት በድማ ማርያም ተቀብረዋል። ከአባታች አቡነ ተከስተ ብሃርሃን እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን! ምንጭ፦ ከገድለ አቡነ ተከስተ ብርሃን መቅድም።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤                           ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_አንገርጋሪ_ግእዝ_ዜማ፦ ሃሌ ሉያ "#ወአንቲኒ_ቀራንዮ_መካነ_ጎልጎታ እስመ በኀቤኪ ተቀብረ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ህየ ህየ ህየ ንሰግድ ኲልነ #ኀበ_ቆመ_እግረ_እግዚእነ ኀበ ተረግዘ ገቦሁ #ዮም_በዓለ_መስቀሉ"። ትርጉም፦ #የጎልጎታ_ቦታ #አንቺ_ቀራንዮ_ባንቺ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተቀብሯልና፤ በዚያም #የጌታችን_እግር_ወደቆመበት፤ ጎኑ ወደ ተወጋበት ኹላችን እንሰግዳለን፤ #ዛሬ_የመስቀሉ_በዓል_ነው።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ__እግ_ነግ_ዓራራይ_ዜማ፦ "ይሰማዕ ሰማይ ወጽታምእ ምድር ወይትፌሥሑ #ተዓይነ_መላእክት_እስመ_ተረክበ_ዮም_ዕፀ_መስቀል_በዕደ_ዕሌኒ_ንግሥት"። ትርጉም፦ ሰማይ ይስማ ምድር ታድምጥ #የመላእክት_ከተሞች_ይደሰቱ፤ #ዛሬ_ዕፀ_መስቀል_በንግሥት_ዕሌኒ_አማካኝነት_ተገኝቷልና። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_ በድጓው_ላይ።             

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። ❤           ❤ #መጋቢት ፱ (9) ቀን። ❤ እንኳን #ለከበረ_ተጋዳይ_ለሆነ_ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገልጦ በጌታችን ማመን ላስተማለው በሐዋርያት እጅ ለተጠመቀ፤ ወላጆቹን በሚያደርገው ተዓምራት ላሳመነ፤ የጣዖት አምልኮን ላጠፋና ሰይጣንን ድል ላደረገ #ለጽኑ_አባት_ለአባ_ኩትን ለዕረፍት በዓል፣ ለከበሩ #ቅዱሳን_ለእድርያኖስና_ለሚስቱ፣ #አውሳብዮስና_አርማ_ሌሎች_አርባ_ሰዎችም ሰማዕትነት ለተቀበሉት ለዕረፍታቸው በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከአባ_ኖብ ጋር በሰማዕትነት ከዐረፉ #ከሁለት_ሺህ_ሰዎች ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                             ✝ ✝  ✝ ❤ #አባ_ኩትን፦ እርሱም በሶርያ አገር ስሟ በንጣንዮስ ከምትባል ቦታ የሚኖር ነው። አባቶቹም ከዋክብትን ያመልኩ ነበር የአባቱ ስም ንስጣር የእናቱም ስምp iቴዎድራ ይባላል። በአደገ ጊዜም ወላጆቹ ሊያጋቡት ፈለጉ እርሱ ግን አልወደደም ግድ ብለው ያለ ውዴታው ሚስትን አጋቡት ሊገናኛትም አልፈለገም ስለ ሥጋ ድካም ወይም ስለ ጽድቅ ሳይሆን የሥጋ ፍትወትን ስለሚጠላት ነው እንጂ። ደናግልም እንደሆኑ ሁለቱ ሁሉ ከሚስቱ ጋር በአንድነት ኖረ። ❤ "አምላክ ሆይ ወደ ዕውቀትህ ምራኝ" በማለት ጸሎትና ምልጃን ያዘወትር ነበር። ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለቆርኔሌዎስ እንደተገለጠ ተገለጦ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን አስተማረው ከሐዋርያትም ወደ አንዱ ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን እንዲጠመቅ አዘዘው። የሐዋርያት የስብከታቸው ወራት ነበርና ሒዶ ተጠመቀ የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ሁሉ ሕጉን ሥርዓቱንም ሁሉ ተማረ መለኮታዊ ምስጢርንም ተቀበለ። በየቀኑ ሁሉ የሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት ይሰማ ነበር። የጽድቅን ሥራ መሥራትና ንጽሕና፣ ለበጎ ሥራ መጠመድ ትጋት፣ ቅንነት፣ የዋህነት፣ ጾም፣ ጸሎትና ሰጊድ በላዩ ተጨመረ። በእነዚህ ሁሉ የሚተጋ ሆነ እግዚአብሔርም አስደናቂ ተአምራቶችን እንዲያደርግ በርኵሳን አጋንንት ሥልጣንን ሰጠው። ❤ በሚያደርገው ተአምራትም ወላጆቹን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ማመን ስቦ አስገባቸው ደግሞ ሚስቱንና ወላጆቿን አሰገባቸው። ከከሀድያን አንዱ ለሰይጣን ሊሠዋ ወደ ጣዖቱ ቤት በገባ ጊዜ ቅዱስ ኩትን አውቆ በሰይጣን ላይ ጮኸ እርሱ ሰይጣን እንጂ አምላክ እንዳልሆነ በሰው ፊት ያምን ዘንድ አዘዘው። ሰይጣንም እንዳዘዘው ራሱን ገለጠ በዚያ የነበሩ ሁሉም "የቅዱሰ ኩትን አምላክ አንድ እርሱ ብቻ ነው" እያሉ ጮኹ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቁ። ❤ ከዚህ በኋላ ከቀላውዴዎስ ቄሣር የተላከ መኰንን  የቅዱስ ኩትንን ዜናውን በሰማ ጊዜ ወታደር ልኮ አስቀረበው ስለ ሥራውም ጠየቀው እርሱም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ መኰንኑም ጽኑ ግርፋት ገርፈው እንዲሥሩት አዘዘ ይህንንም አደረጉበት። ❤ የአገር ሰዎችም ቅዱስ ኩትንን አሠቃይተው እንዳሠሩት በሰሙ ጊዜ ሁሉም ወደርሱ ተራወጡ መኰንኑንም ሊገሉት ወደዱ መኰንኑም ሸሸ። ቅዱስ ኩትንንም ከማሠሪያው ፈትተው ከደሙም አጥበው ተሸክመው ወደቤቱ ወሰዱት ከዚህም በኋላ ብዙ ዘመናት ኑሮ የወደደው እግዚአብሔርን አገልግሎ ደስ አሰኝቶ በፍቅር አንድነት መጋቢት 9 ቀን ዐረፈ። ❤ ከዕረፍቱም በኋላ ቤቱን ቤተ ክርስቲያን አድርገው ሥጋውን በውስጥዋ አኖሩ ጌታችንም ከሥጋው ብዙዎች ታላላቅ ተአምራቶችን አሳየ። አባ ኩትን በረከቱም ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ትሁን አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የከበሩ_ቅዱሳን_እድርያኖስና_ሚስቱ፣ #አውሳብዮስና_አርማ_ሌሎች_አርባ_ሰዎችም_ሰማዕትነት፦ እሊህንም ምርጦች ለረከሰ ከወርቅና ከብር ለተሠራ ጣዖት ማምለክን እምቢ ስላሉ የክብር ባለቤት ለሆነ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለስሙ ዐላውያን ጽኑ የሆነ ሥቃይን አሠቃዩአቸው። ❤ ከዚህም በኋላ ራሶቻቸውን መጋቢት 9 ቀን በሰይፍ ቆረጡ የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ። በረከታቸው ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን። ምንጭ፦የመጋቢት 9 ስንክሳር።                            ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለኩትን_በእደ_ሐዋርያት_ዘተጠምቀ። እመልአከ ሰማይ ትምርተ ከመ ተጠየቀ። ሶበ አገበርዎ እንተ ሕሊናሁ ኢጽሕቀ። በፍትወተ ሥጋ ኢተሞዐ ወበሥምረቱ ኢወድቀ። ምስለ ብእሲቱ ሰኪቦ ዘአኮ ርኁቀ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመጋቢት_9።                         ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ፈሪሃ እግዚአብሔር እምሀርክሙ። መኑ ውእቱ ብእሲ ዘይፈቅድ ሐይወ። ወያፈቅር ይርአይ መዋዕለ ሠናያት"። መዝ 33፥11-12። የሚነበቡት መልዕክታት ገላ 1፥1-11፣ ያዕ 2፥1-14 እና የሐዋ ሥራ 4፥13-19። የሚነበበው ወንጌል ማር 1፥23-29። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ቄርሎስ ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ወራትና በዓል። በሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። ❤           ❤ #መጋቢት ፰ (8) ቀን። ❤ እንኳን ብዙዎች ሰማዕታትን አሠቃይቶ ይገድል ለነበረው ለእንዴናው ገዥ #ለቅዱስ_አርያኖስ በሰማዕታቱ ጸሎት አምኖ እርሱም ራሱ በንጉሡ በዲዮቅልጥያኖስ ፊት የጌታችን አምላክነት መስክሮ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓልና ለእስክንድርያ ዐሥራ አንደኛ ሊቀ ጳጳስ ለቅዱስ አባት #ለአባ_ዮልዮስ ለዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                                   ✝ ✝ ✝ ❤ #መኰንን_ቅዱስ_አርያኖስ፦ ይህም እንዲህ ነው የከበሩ ፊልሞንና አብላንዮስ በእርሱ እጅ በሰማዕትነት ከሞቱ በኋላ እርሱም በሥቃይ ውስጥ ሳለ ከአማንያን አንዱ ከቅዱሳን ከደማቸው ወስደህ ዓይንህን ብትቀባ በዳንክ ነበር አለው። ያን ጊዜም ከደማቸው ወስዶ ዐይኑን ቀባ ወዲያው ድኖ ፈጥኖ አየ። ❤ ከዚህም በኋላ በቅዱሳን ላይ በአደረገው ክፉ ሥራ ሁሉ በድንቁርናውም ምሕረት የሌለው ሥቃይ ስለ አሠቃያቸው ታላቅ ጸጸት ተጸጽቶ አዘነ ተነሥቶም ጣዖታትን ሰበረ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አምኖ ምእመናንን ማሠቃየቱንም ተወ። ❤  ዲዮቅልጥያኖስም ወሬውን በሰማ ጊዜ ጭፍሮቹን ልኮ ወደርሱ አስመጣው "በምን ምክንያት አማልክትን ማምለክ እንደ ተወ" ጠየቀው። እርሱም "በቅዱሳን ሰማዕታት እጅ እግዚአብሔር የሚሠራቸውን አስደናቂዎች ተአምራት ሊነግረው ጀመረ ሕዋሳታቸውን እንዴት እንደ ሚቆራጡአቸው በየአይነቱ በሆነ ሥቃይም ሲያሠቃዩዋቸው ያለምንም ጉዳት ጤነኞች ሁነው ተመልሰ እንደሚነሡ" ነገረው። ዲዮቅልጥያኖስም የተአምራትን ነገር ስለ ነገረው ተቆጣ ጽኑ የሆነ ሥቃይንም እንዲያሠቃዩት አዘዘ። ሁለተኛም ከጉድጓድ እንዲጨምሩትና እስኪሞትም የጉድጓዱን አፍ እንዲዘጉ አዘዘ እንዲሁም አደረጉ። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልአኩን ልኮ ከጉድጓዱ አውጥቶ በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ መኝታ ላይ አቆመው። ንጉሡም በነቃ ጊዜ አይቶ ደነገጠ፣ ፈራ "ማንህ አንተ" አለው።እርሱም "እኔ የእዴናው ገዥ አርያኖስ ነኝ" ብሎ መለሰለት ንጉሡም ደንግጦ እየተንቀጠቀጠ  በማቅ ጠቅልለው ከባሕር እንዲያሰጥሙት አዘዘ። በባሕሩም ውስጥ ነፍሱን በጌታችን እጅ መጋቢት8 ሰጠ። ❤ እንዲህም ሆነ ቅዱስ አርያኖስ ዘመዶቹንና አገልጋዮቹን ሲሰናበታቸው እንዲህ ብሎ ነገራቸው "ለሥጋዬ እርሱ እንደሚያስብና ወደአገሬ ወደእንዴናው እንደሚመልሰው በሌሊት ራእይ እግዚአብሔር አስረድቶኛልና እንተም በእስክንድርያ ወደብ ሥጋዬን ጠብቁ" አላቸው። በአሰጠሙትም ጊዜ ጌታችን ዓሣ አንበሪን አዘዘ አንበሬውም ተሸክሞ ወስዶ በእስክንድርያ ወደብ አውጥቶ በየብስ ላይ አኖረው። አሽከሮቹ ከዚያ እየጠበቁት ነበር። ወደ አገሩ ወደ እንዴናው አድርሰው ከቅዱሳን ሰማዕታት ከፊልሞና ከአብላንዮስ ከሥጋቸው ጋር በአንድነት አኖሩት። የቅዱስ አርያኖስ በረከቱ ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ዮልዮስ፦ ይህም አባት አስቀድሞ በእስክንድርያ ቄስ ሆኖ ነበር። እርሱም በአለበት ዘመን በግብጽ አገር እንደርሱ ያለ የሌለ አዋቂ ብልህ የሆነ ምሁር ነበር። የክብር ባለቤት በሆነ በእግዚአብሔርም ፈቃድ በእስክንድርያ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ ብዙዎች ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ። ❤ የሹመቱም ዘመን በሰላም የሰፈነበት ነበር በቀናች ሃይማኖትም ይጸኑ ዘንድ ሕግና ሥርዓትንም ሁሉ እንዲጠብቁ ሕዝቡን ሁል ጊዜ ይመክራቸውና ያስተምራቸዋል። ❤ በወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ወንበር ዐሥር ዓመት ከኖረ በኋላ መጋቢት 8 በሰላም በፍቅር ዐረፈ። በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን። ምንጭ፦ የመጋቢት 8 ስንክሳር። ❤ "#ሰላም_ለአርያኖስ_አማልክቲሁ_ኀዲጎ። ዘተለወ ፍጹመ ለእግዚአብሔር ሕጎ። ዲዮቅልጥያኖስ ምዑክ ቢጸ አራዊት በዛውጎ። እምድኅረ  ደፈኖ አፈ ግብ መሪጎ። መልዕልተ ምስካቡ ንጹፍ ተረክበ ዐሪጎ"። #ሊቁ_አርከ ሥሉስ (አርኬ) #የመጋቢት_8።                

❤ የተባረከው ሐዋርያ ቅዱስ ማትያስም የአማልክቱን አዳራሾች ሁሉ ያፈርሱ ዘንድ በውስጥ ከሚደርጉት ክፉ ተግባር የተነሣ ከእርሱ ምንም እንዳይገናኙ ከባሕር ይጥሏቸው ዘንድም ይህን አዘዛቸው። ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ስምም ቤተ ክርስቲያን ሠራላቸው። በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምም አጠመቃቸው። የአገሩን ሰዎችም ወንዶችንም፣ ሴቶችንም፣ ሕፃናቱንም አንድ በሆነ በማይከፈል በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው። ❤ ከጥምቀት በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱን አከበረላቸው (ባረከላቸው)። በይቅርታና በሕይወት ትምህርትም ገሠጻቸው። የወንጌልን ሕግም አስተማራቸው፤ ከእርሱም ተለየ። ሁሉም በሰላም ሸኙት። እርሱ ትክክለኛውን ዕውቀትና ቅን የሆነች መንገድን አስተማሯቸዋልና። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የማመን ዕውቀትን በማስተማርም ከስህተት አድኗቸዋልና። ❤ ካስተማረና የምስራችን ከነገረ በኋላም መልካም እንቅልፍን ተኛ። ከይሁዳ አገሮች ፍዕላዎን በምትባል አገርም በጌታችን በአምላካችን በእግዚአብሔር ጸጋ መጋቢት ስምንት ቀን ዐረፈ። ምስጋናና ክብር ለእርሱ ይሁን ። ከሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎቱ ይማረን!። አሜን ምንጭ፦ ገድለ ሐዋርያትና የመጋቢት 8 ስንክሳር።                                                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ "#ሰላም_ለማትያስ_ዘተኀረየ_ወተፈቅረ። ህይንተ ይህዳ ይተኌለቊ ምስለ ሐዋርያት ኅቡረ። ከዊኖ #ማትያስ በላእለ እኩያን ኄረ። ሥጋ ወልደ አምላክ  ሴሰዮሙ ወደሞ ክብረ። ተውላጠ ሴሰይዎ ሎቱ ከመ ላሕም ሣዕረ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመጋቢት_8።                          ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "እግዚአብሔር ያበርህ ሊተ ያድኅነኒ ምንትኑ ያፈርሀኒ። እግዚአብሔር ምእመና ለሕይወትየ ምንትኑ ያደነግፀኒ። ሶበ ይቀርቡኒ እኩያን ይብልዑኒ ሥጋየ"። መዝ 26፥1-2። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 18፥35-ፍ.ሜ።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ። ውስተ ኵሉ ምድር ወጽአ ነገሮሙ። ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ"። መዝ 18፥3-4። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 2፥1-17 ይሁዳ 1፥17-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 1፥15-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 10፥1-16። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱሳን ሐዋርያት ቅዳሴ ነው። መልካም የሐዋርያው የቅዱስ ማትያስ የዕረፍት በዓልና የጾም ወራት። በሁላችንም ይሁንልን።                 

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #መጋቢት ፰ (8) ቀን። ❤ እንኳን #ከዐሥራ_ሁለቱ_ሐዋርያት ለአንዱ በአስቆርቱ ይሁዳ ፈንታ ለተሾመው #ለቅዱስ_ማትያስ_ለዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_ማትያስ፦ ይህ ሐዋርያ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሰማይና የምድር ንጉሥ በሚሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም ሰይጣንና ሠራዊቱ ያፍሩ ዘንድ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ እንዲህ ሆነ፤ ይሁዳ ግን ከፍጥረቱ ሁሉ ተለይቶ ምስኪንና ጐስቋላ ነበር። ጌታውን ክፋ ለሆኑ አይሁድ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ ሄደና ራሱን አጠፋ። ክብሩንም አጣ፤ ከሐዋርያት ዙፋንም ተጣለ። ስለእርሱም ማትያስን ሾመው። ቅዱስ ማትያስም ያስተምር ዘንድ ወደ ደማስቆ ወጣ። ዕጣም እንዲያስተምር ደርሶታልና። ቅዱስ ወንጌልንም አስተማራቸው። ❤ ይህም ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች አገር ወንጌልን ይሰብክላቸው ዘንድ በሔደ ጊዜ ወዲያውኑ ይዘው ዐይኖቹን አውልቀው አሠሩት ምግባቸው የመጻተኛ ሰው በድን ስለሆነ ልማዳቸውም እንዲህ ነው። መጻተኛ ሰው ሲይዙ ዐይኖቹን አውልቀው በእሥር ቤት ያኖሩታል። የያዙበትንም ቀን ይጽፋሉ ሠላሳ ቀንም እስቲፈጸም ሣር ያበሉታል ከዚያ በኋላም አውጥተው አርደው ይበሉታል። ❤ ሐዋርያ ቅዱስ ማትያስም ታሥሮ ሳለ ሠላሳው ቀን ሳይፈጸም በጌታችን ትእዛዝ ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ ወደርሱ ደረሰ የአገሩ ሰዎች የሚሠሩትን ክፋ ሥራ አይቶ አደነቀ እጅግም አዘነ እሥረኞችንም ሁሉ አውጥቶ የአገር ሰዎች ወደማያገኙአቸው ቦታ አኖራቸው። እነርሱ ግን ሁለቱ ሐዋርያት ቅዱሳን እንድርያስና ማትያስ ተገለጡላቸው የአገሩም ሰዎች ያዙአቸው በአንገታቸውም ገመድ አስገብተው እስከ ሦስት ቀን በአገሩ ጥጋጥግ ጐተቷቸው ሐዋርያት ስለዚያች አገር ሰዎች ስለድኅነታቸው ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ ያንጊዜ ከወህኒ ቤቱ ምሰሶ ሥር ውኃን አፈለቁ ውኃውም ከፍ ከፍ ብሎ በአገር ውስጥ እስከሚአጥለቀልቅና ወደ ሰዎች አንገት እስከ ደረሰ አየበዛ ሔደ። በተጨነቁና የሕይወታቸውን ተስፋ በቆረጡ ጊዜ ወደ ሐዋርያት መጡ በፊታቸውም ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ አለቀሱ ሐዋርያትም በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመኑ እናንተም ትድናላችሁ አሉአቸው እሊያ ሁሉም በክብር ባለቤት በጌታችን አመኑ። ❤ ሐዋርያትም አሰተማሩአቸው ገሠጹአቸውም የአንድነትን የሦስትነትን የመድኃኒታችን ሰው የመሆኑን ምስጢር ገለጡላቸው ደግሞም ይህን የአራዊት ጠባይ ጌታችን ከእነርሱ ያርቅ ዘንድ ጸለዩላቸው ከዚህ በኋላ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው ያ የአውሬ ጠባይ ከእርሳቸው ርቆ ሰው የሚመገበውን የሚመገቡ የዋሆች ቅኖች ሆኑ። ኤጲስቆጶሳትን፣ ቀሳውስትና ዲያቆናትንም ሾሙላቸው በቀናች ሃይማኖትም እያጸኑዋቸውና እያስተማሩዋቸው ሠላሳ ቀኖች ያህል ከእርሳቸው ጋር ኖሩ ከዚህም ወጥተው ሔዱ። የአገር ሰዎች ግን በሌላ ጊዜ ወደ እነርሱ እንዲመለሱላቸው ሐዋርያትን ለመኑዋቸው። ❤ ከዚያም ሐዋርያው ቅዱስ ማትያስ ወደ ደማስቆ አገር በገባ ጊዜም "በኃጢአታቸው የወደቁትን እውነተኛ እግዚአብሔር የማያውቁትን ሰነፍ ሰዎች ሆይ አምላካችሁ ሌላ ሰው ሠራሽ ነው። ሰዎች ሁሉ እንደ እናንተ የወደቁ እንዲሆኑም ትሻላችሁ? በደማስቆ የምትኖሩ ሰዎች ሆይ ትምህርቴን ስሙ አማልክትን ማምለክም ተው። ስህተትን ክፋ መሥራትንም ከእናንተ አስወግዱ። ወደ ፈጣሪያችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ። ከእኔ ትምህርት የተነሣም ተመለሱ። እኔም ወደ እግዚአብሔር አቀርባችኋለሁ። እርሱ ለመንግሥቱ የተዘጋጃችሁ ያደርጋችኋል። የመላእክትን ሥርዓት አስተምራችሁ ዘንድም ወደ እኔ ተመለሱ። እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ሕያዋን ትሆኑ ዘንድም የሕይወት ኅብስት እንዲሰጣችሁ ወደ እኔ ተመለሱ። የሰው ሥራ የሆኑ አማልክትንም እንቢ በሏቸው። የእውነተኛው አምላክ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ትሆኑ ዘንድም ከሰይጣናዊ ምክንያት ራቁ። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰማይና የምድር ገዢ ነው፤ የወረደው፣ ያለወንድ ዘር በድንግል ማርያም ማኅፀን ያደረው የእግዚአብሔር ቃል ቀዳማዊ ነው፤ የአዳምን ዘር በክብሩ በገናናነቱ የማይታይ ሰይጣንን ከማምለክ ያድነው ዘንድም መከራን ተቀበለ፤ እንደ ሥጋዊ ልጅም በምድር አባት ያለው አይደለም፤ እርሱም ያለመለየት ከአባቱ ጋር አለ፤ እርሱ ሁሉንም በጥበቡ ያረጋጋል፤ ከመሬት አፈርን የወሰደና አዳምን ከአፈር የፈጠረውም እርሱ ነው፤ የመጀመርያው አባትም እርሱ ነው፤ ይህ አምላክም ፍጥረታት ሁሉ ነፍስ በእጁ ናት፤ እርሱ ይወዳቸዋል፣ መመለሳቸውም በቀናች ሃይማኖት በምታምር ሕሊና ነው፤ እርሱ አባቱና መንፈስ ቅዱስ አንድ ናቸው፤ሦስትም ናቸው፤ አንድ መለኮት አንድ ሥልጣን" አላቸው። ❤ በመጀመሪያ የማዝዛችሁም "ከርኵሰት ሁሉ ትርቁ ዘንድ ነው፤ እግዚአብሔር ንጽሕናችሁን እንዲመለከትና ሰማያዊትና መንፈሳዊት በሆነች በረከት እንዲባርካችሁ፣ በፍርድ ቀንም እንዲምራችሁ ከሴት ጋር አንድ መሆንን (መገናኘትን) አታብዙ" አላቸው። ❤ የአገሩ ሰዎችም ይህን ነገር ከእርሱ በሰሙ ጊዜ በምክንያቱና በክፉ ሥራው ሰይጣን በልባቸው አደረ። እርስ በእርሳቸውም "በእውነትም ይህ ሰው በአገሩ ከሚዞሩ ከዐሥራ ሁለቱ ጠንቋዮች ወገን ነው፤ ሴቶችን ከባሎቻቸው ይለያሉ ምን እንደምታደርጉት አስቡ" ተባባሉ። እነርሱም ተሰበሰቡ። ሐዋርያውንም ያዙትና አሰሩት። በብረት አልጋም አስቀመጡት። ሥጋው እስከ ሚሸት ድረስም በታቹ እሳት አነደዱበት እያንዳንዳቸውም ተመለከቱ። ቁመቱ ከአልጋው ዐሥራ አምስት ክንድ ሆኖ የእሳቱ ነበልባል ከፍ ባለ ጊዜም አደነቁ። ❤ በአደባባይ የቆሙና የተሰበሰቡ ሰዎችም "ይህ ሰው ጠንቋይ ቢሆን ኖሮ እነሆ በጠፋ ነበር" ተባባሉ። ከሦስት ቀን በኋላም ክፉ ተገባራቸው ይገለጣል። ሦስት ቀን ከሆነ በኋላም ቅዱስ ማትያስን ያስቀመጡበት የብረት አልጋ ካለበት ቦታ በደረሱ ጊዜ በእሳት ሳይቃጠል በሕይወትም አገኙት፤ ዓይኖቹም የተገለጡ ነበሩ፤ በጤናም አገኙት፤ ምንም ዓይነት ጥፋት አላገኘውም፤ በእርሱ ላይ ምንም ዓይነት የእሳት ሽታ አልነበረም፤ ልብሱም አልተቃጠለም። ❤ የአገሩየአገሩ ሰዎች ለተባለረከው ሐዋርያ የእግዚአብሔር ይህን ይቅርታ በተመለከቱ ጊዜ ከአገሩ ሰዎች ብዙዎቹ በእግዚአብሔር አመኑ። ይህ አምላካቸው ነውም አሉ። ሰባት ቀንም ስምንት ቀንም አለፈ። ቅዱሱ ግን በአልጋው ተኝቶ ነበር። የአገሩ ሰዎችም ሁሉ ይመለከቱት ነበር። በዚህም ከአገሩ ሰዎች ብዙዎች በትክክለኛዋ ሃይማኖት አመኑ። በተባረከው ሐዋርያ በቅዱስ ማትያስ ትምህርትም አመኑ። በትምህርቱ ያላመኑም ነበሩ። እሳቱም ሃያ አራት ቀን ይንቦገቦግ ነበር። ❤ ሐዋርያው ስሙን የሚጠራው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በቀንና በሌሊት ሁሉ ምንም እንዳይነካው ከክፉ ነገር ያድነው ነበር።በእርሱ ስም መከራን ተቀብሏልና። ከዚህ በኋላም ከእሳቱ አወጡት። ሥጋውም ሕያው(ጤነኛ) ነበር። ፊቱም እንደ ሕፃናት ፊት ነበር። ሁሉም ወደ እርሱ ይመለከቱ ነበር። እርሱ በእሳት ውስጥ አልነበረም። "ከራሱ ፀጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ ጤነኛ ነውና" አሉ። በዚያችን ሰዓትም የአገሩ ሰዎች ብዙዎች አመኑ። በአገሩ ያሉትም ሁሉ ጮኹ "በቅዱስ ስሙየሚያምኑበትን ሁሉ ከአዳናቸው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከቅዱስ ማትያስ አምላክ ከእግዚአብሔር በስተቀር በሰማይም በምድርም ሌላ አምላክ የለም" አሉ።