uz
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

Kanalga Telegram’da o‘tish

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

Ko'proq ko'rsatish
613
Obunachilar
+124 soatlar
-17 kun
-1030 kun
Postlar arxiv
ልኑር አትበል። ❤ ስለዚህም እስራኤል ወደግብጽ አገር ከቤተሰቡ ሁሉና ከጓዙ ከገንዘቡ ጋር ወርዶ በዚያ የሚኖር ሆነ ። ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ ልጆቹን ጠርቶ እየአንዳንዳቸውን መረቃቸው ትንቢትንም ተናገረላቸው የዮሴፍንም ልጆች ኤፍሬምንና ምናሴን እጆቹን አመሳቅሎ ባረካቸው መረቃቸውም። ከዚህም በኋላ በመቶ ሠላሳ ሰባት ዕድሜው በሰላም በፍቅር ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን በቅዱስ ያዕቆብ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 28 ስንክሳር።                            ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ዘሠርዓ ለአብርሃም። ወመሐለ ለይስሐቅ። ወአቀመ ስምዐ ለያዕቆብ"። መዝ 104፥9። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 1፥1-18።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "አንሣእኩ አዕይንትየ መንገለ አድባር። እምአይቴ ይምጻእ ረድኤትየ። ረድኤትየሰ እምኀበ እግዚአብሔር"። መዝ 120፥1-2። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 4፥1-23፣ ያዕ 2፥20-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 7፥1-9። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 22፥23-34። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ የእመቤታች ማርያም ነው። መልካም የአርእስተ አበው የቅዱሳን የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።                  @Teamihokidusan

❤ ይስሐቅም ልጁን "ልጄ ሆይ ፈጥነህ ያገኘህ ይህ ምንድነው" አለው እርሱም "ፈጣሪህ እግዚአብሔር በፊቴ የሰጠኝ ነው" አለው። ይስሐቅም "ልጄ ቅረበኝ ልዳስስህ አንተ ኤሳው እንደሆንክ ወይም እንዳልሆንክ" አለው በቀረበም ጊዜ ዳሠሰውም "ቃልህ የያዕቆብ እጆችህ ግን የኤሳው ናቸው" አለው "ልጄ አድነህ ያመጣህልኝን በልቼ ነፍሴ ትመርቅህ ዘንድ አምጣልኝ" አለው አቅርቦለት በላ ወይንም አመጣለት ጠጣ። ❤ ይስሐቅም "ልጄ ቅረበኝና ሳመኝ" አለው ቀርቦም ሳመው የልብሱን ሽታ አሸተተው "እነሆ የልጄ ልብስ ሽታው እግዚአብሔር እንደባረከው እንደዱር አበባ ሽታ ነው" አለ። እንዲህም ብሎ መረቀው "ከሰማይ ጠል ከምድር ስብ ይስጥህ ሥንዴህን ወይንህንና ዘይትህን ያብዛልህ አሕዛብም ይገዙልህ አለቆችም ይስገዱልህ ለወንድሞችህም ጌታ ሁን የአባትህም ልጆች ይስገዱልህ። የሚረግምህም የተረገመ ይሁን" ይህም በእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ። ❤ ይህም አባት ይስሐቅ ወደ መቶ ሰማንያ ዘመን ደረሰ አባታችን ይስሐቅም እንዲህ ብሎ ተናገረ "ከዚህም በኋላ መልአክ ወደ ሰማይ ወሰደኝ አባቴ አብርሃምን አየሁትና ሰገድሁለት እርሱም ሳመኝ ንጹሕን ሁሉ ስለ አባቴ ተሰበሰቡና ወደ ውስጠኛው የአብ መጋረጃ ከበውኝ ከእኔ ጋራ ሔዱ እኔም ወድቄ ከአባቴ ጋራ ሰገድኩ። የሚያመሰግኑ መላእክት ሁሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብሎ የሚመሰገን አሸናፊ እግዘአአብሔር ምስጋናው በሰማይና በምድር የመላ ነው እያሉ ጮኹ። ❤ አባቴ አብርሃምን "እኔ በቦታዬ ልዩ ነኝ ሰው ሁሉ ልጁን በወዳጄ ይስሐቅ ስም ቢሰይም በቤቱ ውስጥ በረከቴ ለዘላለም ይኖራል የቡሩክ ወገን የሆንክ አንተ ቡሩክ አብርሃም ሆይ መምጣትህ መልካም ነው። አሁንም በወዳጄ በልጅህ ይስሐቅ ስም የሚለምን ሁሉ በረከቴ በቤቱ ውስጥ ለዘላለም እንዲኖር ቃል ኪዳኔን አጸናለታለሁ" አለው። "ትሩፋቱን ቅንነቱን ገድሉን የሚጽፍ ካለ ወይም በስሙ የተራበ የሚያጠግብ በመታሰቡያው ቀን የተራቆተ የሚያለብስ እኔ የማያልፈውን መንግሥት እሰጠዋለሁ"። ❤ አብርሃምም እንዲህ አለ "አቤቱ ዓለሙን ሁሉ የያዝክ አብ ሆይ ቃል ኪዳኑን ገድሉን ይጽፍ ዘንድ ካልተቻለው ቸርነትህ ትገናኘው አንተ ቸር መሐሪ ነህና አንጀራ የሌለው ችግረኛ ቢሆንም"። ጌታም እንዲህ ብሎ መለሰለት "በወዳጄ በይስሐቅ በመታሰቢያው ዕለት ከሌሊት ጀምሮ በጸሎት ይትጋ አይተኛ እኔም መንግሥቴን ከሚወርሱ ጋራ ከበረከቴ እሰጠዋለሁ"። ❤ አባቴ አብርሃምም ሁለተኛ እንዲህ አለ "በሽተኛ ድውይ ከሆነ ቸርነትህ ታግኘው" ጌታም እንዲህ አለ "ጥቂት ዕጣን ያግባ ዕጣንን ካላገኘ የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ፈልጎ በልጅህ በወዳጄ በይስሐቅ መታሰቢያ ቀን ያንብበው። ማንበብም የማያውቅ ከሆነ ወደሚያነቡለት ሒዶ እሷን አስነብቦ ይስማ። ከእነዚህም ይህን ማድረግ ካልቻለ ወደ ቤቱ ገብቶ ደጁን ይዝጋ እየጸለየ መቶ ስግደቶችን ይስገድ እኔም የሰማይ የመንግሥት ልጅ አደረገዋለሁ። ለቁርባን የሚሆነውንና መብራትን ያገባ እኔ ያልኩትን ሁሉ የሚያደርግ እርሱ የመንግሥተ ሰማያትን ርስት ይቀበላል። ቃል ኪዳኑንና ገድሉን ትሩፋቱን ለመጻፍ ልቡን ያበረታውን እኔ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፋለሁ በሺው ዓመት ምሳ ላይም ይገኛል"። ❤ እግዚአብሔርም ይህን ብዙ ነገርን በተናገረ ጊዜ ያዕቆብ አይቶ በመደንገጥ ነፍሱ ተመሠጠች ይስሐቅም ያዕቆብን አንሥቶ "ልጄ ሆይ ዝም በል አትደንግጥ ብሎ ጠቀሰው ከዚህም በኃላ ሳመውና በሰላም አረፈ። ከኤሞር ልጆች በገዛው እናቱ ሣራ በተቀበረችበት በአብርሃም መቃብር ተቀበረ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ይስሐቅ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                                                 ✝ ✝ ✝ ❤ #እስራኤል_ብሎ_እግዚአብሔር_ስም ያወጣለትን #የአባቶች_አለቃ_የሆነ_ቅዱስ_ያዕቆብ፦ ይህም ቅዱስ በበጎ ሥራ ሁሉ በመራራት በቅንነት በትሕትና በለጋስነት የአባቶቹን የአብርሃምንና የይስሐቅን መንገድ የተከተለ ሆነ። ❤ ወንዱሙ ኤሳውም ብኵርናውን በምስር ንፍሮ ደግሞ በረከቱን ስለወሰደበት አብዝቶ ስለጠላው ሊገድለው ይፈልግ ነበር ስለዚህም አባቱ ይስሐቅና እናቱ ርብቃ ያዕቆብን ወደ ርብቃ ወንድም ወደ ላባ ሰደዱት። እየተጓዘም ሳለ በአደረበት በረሀ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ መሰላል የእግዚአብሔርም መላእክት በውስጡ ሲወርዱ ሲወጡ በሕልሙ አየ እንዲህም አለ "ይህ የሰማይ ደጅ ነው ከዚህም የእግዚአብሔር ቤት ይሠራል"። ❤ በሶርያ ምድር ወደሚኖር ወደእናቱ ወንድም ወደ ላባ በደረሰ ጊዜ ሁለቱን ልጆቹን ልያንና ራሔልን አጋባው በዚያም የላባን በጎች እየጠበቀ ሃያ አንድ ዓመት ያህል ኖረ። ላባም "የምሰጥህ ምንድን ነው" አለው ያዕቆብም "ምንም የምትሰጠኝ የለም አሁን ወደፊት የምነግርህን ነገር ካደረግህልኝ ዳግመኛ በጎችህን ፈጽሜ እጠብቃለሁ። አሁን በጎችህ በፊት ይለፉና ከበጎችህ ሁሉ ጠጉራቸው ነጫጭ የሆኑትንና መልካቸው ዝንጉርጉር የሆነውንም ስለዋጋዬ ለይልኝ" አለው። ዓይነቱ ዝንጉርጉር ያልሆነውና መልኩ ነጭ ያልሆነው ሁሉ ግን ላንተ ይሁን አለው። ላባም "እንዳልክ ይሁን" አለ ። ❤ በዚያችም ቀን ነጩንም ቀዩንም ዝንጉርጉሩንም መልኩ ዳንግሌ የሆነውንም የፍየሉንም አውራ ለይቶ ለልጆቹ ሰጠ። በእነርሱና በያዕቆብ መካከል ሦስት ቀን የሚያስኬድ ጎዳና ርቀው ሔዱ ያዕቆብ ግን የቀሩትን የላባን በጎች ይጠብቅ ነበር። ያዕቆብም የልምጭ በትርንና ታላቅ የሎሚ በትርን ወስዶ ቅረፍቱን ልጦ ጣለው ያዕቆብ የላጣቸው በትሮች ነጫጭሁነው ታዩ። እነዚያንም በትሮች በጎች ከሚጠጡበት ገንዳ ላይ ጣላቸው በጎች ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ እነዚያ በትሮች በፊታቸው ሁነው ይታዩ ዘንድ። መጥተውም በጠጡ ጊዜ እነዚያን በትሮች አስመስለው ፀንሰው ነጩንና ሐመደ ክቦውን ዝንጉርጉሩን ወለዱ ። ❤ ያዕቆብም አውራ አውራዎቹን በጎች ለየ አውራ አውራውን ከለየ በኋላ እንስት እንስቶቹን በጎች ለይቶ ዝንጉርጉር ሐመደ ክቦና ነጭ በሆኑ አውራዎች ፊት አቆማቸው የራሱንም በጎች ለያቸው እንጂ ከላባ በጎች ጋራ አልቀላቀላቸውም ። ❤ ያዕቆብም እጅግ ፈጽሞ ባለጸጋ ሆነ ሴቶችንም ወንዶችንም አገልጋዩችን ገዛ ብዙ ከብት ላሞችን በጎችን ግመሎችንና አህዮችን ገዛ። ያዕቆብም ወደአገሩ በተመለሰ ጊዜ እስከ ንጋት ድረስ አንድ ሰው ሲታገለው አደረ ከእርሱም ጋራ ሲታገል እንዳልቻለው ባየ ጊዜ እርም የሚሆንበት ሹልዳውን ያዘው "ጎህ ቀድዷልና ልቀቀኝ" አለው "ካልመረቅከኝ አልለቅህም" አለው። "ስምህ ማን ይባላል" ቢለው "ስሜ ያዕቆብ ነው" አለው እንግዲህ "ስምህ ያዕቆብ አይባል እስራኤል ይባል እንጂ አለው ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋራ መታገልን ችለሃልና"። ❤ ከዚህም በኋላ ስለ ልጁ ዮሴፍ ብዙ ኀዘን አገኘው ወንድሞቹ ወደ ግብጽ ሸጠውታልና በጠየቃቸውም ጊዜ "ክፉ አውሬ በልቶታል" አሉት ከልቅሶውም ብዛት የተነሣ ዐይኖቹ ታወሩ። ❤ ከዚህም በኋላ ታላቅ ረሀብ ሆነ በግብጽ አገር እህል የሚሸጥ መሆኑን ያዕቆብ ሰማ ሥንዴ ይሸምቱ ዘንድ ልጆቹን ላካቸውና ወደ ዮሴፍ ደረሱ ንጉሥ ሆኖም አግኘተውት ሰገዱለት ወንድማቸው እንደሆነም አላወቁትም እርሱ ግን አውቋቸዋል ሥንዴውንም ሰጥቶ አስናበታቸው ሁለተኛም በተመለሱ ጊዜ ራሱን ገለጠላቸውና "ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትፍሩ እመግባችሁ ዘንድ በፊታችሁ እግዚአብሔር ለሕይወት ልኮኛልና" አላቸው። "አሁንም ፈጥናችሁ ሒዱና ለአባቴ ንገሩት ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል በሉት ለግብጽ አገር ሁሉ እግዚአብሔር ጌታ አድርጎኛል ፈጥነህ ና በዚያ

❤ አቤሜሌክም ሺህ ምዝምዝ ብርን ሴቶች አገልጋዮችን ወንዶች አገልጋዮችን ላሞችና በጎችንም አምጥቶ ለአብርሃም ሰጠው ሚስቱ ሣራንም መለሰለት። አብርሃምም ወደ እግዚአብሔር ለመነ እግዚአብሔርም አቤሜሌክን ፈወሰው ሚስቱንም ባሮቹንና ቤተ ሰቦቹንም ልጆቹንም ሁሉም ወለዱ ስለ አብርሃም ሚስት ስለሣራ እግዚአብሔር ማሕፀንን ሁሉ በአፍአ በውስጥ ዘግቶ ነበርና። ❤ ከዚህም በኋላ በጎ ተጋድሎውን ፈጽሞ እግዚአብሔርንም አገልገሎ በመቶ ሰባ አምስት ዕድሜው ወደ ወደደው እግዚአብሔር ሔደ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን አብርሃም ጸሎት ይማረን በረከቱም ከኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                                                         ✝ ✝ ✝ ❤ #የቅዱስ_አብርሃም_ልጅ_ቅዱስ_ይስሐቅ፦ ይህ ጻድቅ ይስሐቅም በልዑል አምላክ ብሥራት ተወለደ። ይህንንም ንጹሕ ይስሐቅን እግዚአብሔር ለልጁ ክርስቶስ ምሳሌው አደረገው። አብርሃምን እንዲህ ብሎታልና "የምትወደው ልጅህ ይስሐቅን ከአንተ ጋራ ውሰደውና ወደላይኛው ተራራ ሒድ እኔ ወደ እምነግርህ ወደ አንዱ ተራራ ላይ አውጥተህ በዚያ ሠዋው"። ❤ አብርሃምም በጥዋት ተነሥቶ አህያውን ጫነ ልጁ ይስሐቅንና ሁለቱ ብላቴኖቹንም ወሰደ ለመሥዋዕትም ዕንጨትን ፈልጦ አሸክሞ ሔደ። በሦስተኛም ቀን እግዚአብሔር ወዳለው ወደዚያ ቦታ ደረሰ አብርሃምም በዐይኑ ቃኘ ቦታውንም ከሩቅ አየ። አብርሃምም ብላቴኖቹን "እናንተ አህያውን ይዛችሁ ከዚህ ቆዮ እኔና ልጄ ግን ወደ ተራራ እንሔዳለን ሰግደንም ወደእናንተ እንመለሳለን" አላቸው። አብርሃምም መሥዋዕት የሚቃጠልበትን ዕንጨት አምጥቶ ለልጁ ለይስሐቅ አሸከመው እሱም ወቅለምቱንና እሳቱን በጁ ያዘ ሁለቱም በአንድነት ሔዱ። ❤ ይስሐቅም አባቱ አብርሃምን "አባ" አለው እርሱም "ልጄ ምነው" አለው "እነሆ እሳትና እንጨት አለ መሥዋዕት የሚሆነው በጉ ወዴት ነው" አለው አብርሃምም "መሥዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል" አለው። አብረውም ሔደው እግዚአብሔር ወዳለው ወደዚያ ቦታ ደረሱ አብርሃምም በዚያ መሠዊያን ሠራ ዕንጨቱን ደረደረ ልጁ ይስሐቅንም አሥሮ ጠልፎ በመሠዊያው በዕንጨቱ ላይ በልቡ አስተኛው። አብርሃምም ልጁን ያርደው ዘንድ እጁን ዘርግቶ ወቅለምቱን አነሣ። ❤ እግዚአብሔርም "አብርሃምን አብርሃም አብርሃም" ብሎ ጠራው እርሱም "አቤት" አለ "በልጅህ ላይ እጅህን አትዘርጋ ምንም ምን አታድርግበት አንተ እግዚአብሔርን እንደምትፈራው አሁን አወቅሁ ለምትወደው ለልጅህ አልራራህለትምና" አለው። አብርሃምም በተመለከተ ጊዜ ቀንድና ቀንዱ በዕፀ ሳቤቅ የተያዘ አንድ በግ አየ አብርሃምም ሔደና ወስዶ በልጁ በይስሐቅ ፈንታ ሠዋው። ይህም ንጹህ ይስሐቅ ጎልማሳ ሲሆን አባቱ ሊሠዋው በአቀረበው ጊዜ እግዚአብሔር በበግ እስከ አዳነው ድረስ ለአባቱ በመገዛት ለመታረድ አንገቱን ዘርግቶ ሰጠ። እርሱም በአባቱ በአብርሃም ሕሊና ፍጽም መሥዋዕት ሆነ። ❤ ከዚህም በኋላ ይስሐቅን መቸገርና ስደት አግኝቶታል በአባቱ በአብርሃም ዘመን ከሆነው ሌላ በሀገር ረኃብ ሁኖ ነበርና የፍልስጥዔም ንጉሥ አቤሜሌክ ወዳለበት። ወደ ጌራራ ይስሐቅ ሔዶ በዚያ ተቀመጠ። የአገር ሰዎችም ይስሐቅን የሚስቱን የርብቃን ነገር ጠየቁት እርሱም እኅቴ ናት አላቸው ስለ ሚስቱ ስለ ርብቃ የዚያች አገር ሰዎች እንዳይገድሉት ሚስቴ ናት ብሎ መናገርን ፈርቷልና መልከ መልካም ነበረችና። በዚያም ብዙ ዘመን ኖሩ አቤሜሌክም በመስኮት በተመለከተ ጊዜ ይስሐቅን ከርብቃ ጋር ሲጫወት አየው። ❤ አቤሜሌክም ይስሐቅን ጠርቶ "እኅቴ ናት አልከኝ እንጂ እነሆ ሚስትህ ናት" አለው ይስሐቅም "በርሷ ምክንያት ይገድሉኛል ብዬ ነው" አለው። አቤሜሌክም "ይህ ያደረግኽብኝ ነገር ምንድን ነው ከዘመዶቼ የሚሆን አንድ ሰው ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ጥቂት ቀርቶት ነበር ባለማወቅም ኃጢአትን ልታመጣብኝ" ነበር። ❤ ንጉሡም "የዚህን ሰው ሚስቱን የነካ ሁሉ ፍርዱ ይሙት በቃ ነው ብሎ ሕዝቡን አዘዛቸው"። ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ መቶ ዕጽፍም ሆነለት እግዚአብሔርም ባረከው ከፍ ከፍም አለ እጅግም ገነነ ወንድ ባርያን ሴት ባርያን ላምን በግን አብዝቶ ገዛ የፍልስጥኤም ሰዎችም ቀኑበት። በአባቱም ዘመን የአብርሃም ብላቴኖች የቆፈሩአቸውን ጉድጓዶች የፍልስጥኤም ሰዎች ደፈኑዋቸው አፈርንም መሏቸው። አቤሜሌክም "ይስሐቅን ፈጽመህ በርትተህብናልና ከእኛ ተለይተህ ሒድ" አለው። ❤ ይስሐቅም ከዚያ ተነሥቶ በጌራራ ሸለቆ ሰፍሮ በዚያ ተቀመጠ። ይስሐቅም ያባቱ አገልጋዮች የቆፈሩዋቸውን አባቱ አብርሃምም ከሞተ በኋላ የፍልስጥኤም ሰዎች የደፈኗቸውን የውኃ ጉድጓዶች እንደገና ቆፈራቸው አብርሃም እንደጠራቸው ጠራቸው። የይስሐቅም አገልጋዮች በጌራራ ቆላ ጒድጓድ ቆፍረው የሚጣፍጥ የውኃ ምንጭ አገኙ የይስሐቅ እረኞችና የጌራራ እረኞች ይህ ውኃ የኛ ነው የኛ ነው በማለት ተጣሉ ያችንም የውኃ ጉድጓድ የዓመፅ ጉድጓድ ብሎ ጠራት ዐምፀውበታልና። ❤ ይስሐቅም ከዚያ ተጎዞ ሒዶ በዚያ ሌላ ጒድጓድ ቆፈረ በርሷም ምክንያት ተጣሉት ስሟንም "ጠብ" ብሎ ጠራት። ከዚያም ተጎዞ ሒዶ ሌላ ጒድጓድን ቆፈረ በርሱም ምክንያት ግን አልተጣሉትም ስሙንም "ሰፊ" አለው "ዛሬ እግዚአብሔር አሰፋልን በምድርም አበዛን" ሲል። ❤ ከዚህም በኋላ ሁለት ልጆችን ኤሳውንና ያዕቆብን ወለደ። ይስሐቅም ኤሳውን ጽኑዕ ኃይለኛ ስለሆነ ይወደዋል። ይስሐቅም አርጅቶ ዐይኖቹ ፈዘው የማያይ ከሆነ በኋላ እንዲህ ሆነ ታላቁ ልጁ ኤሳውን ጠርቶ "እነሆ አረጀሁ የምሞትበትንም ቀን አላውቅም ማዳኛ መሣሪያህን የፍላፃ መንደፊያህን ይዘህ ወደ በረሃ ውጣ። ሳልሞት ነፍሴ እንድትመርቅህ እበላ ዘንድ እንደምወደው አድርገህ አምጣልኝ" አለው። ❤ ርብቃም ልጁ ኤሳውን እንዲህ ሲለው ይስሐቅን ሰማችው ኤሳውም ወደ አደን ሔደ። ርብቃም ታናሹ ልጇ ያዕቆብን እንዲህ አለችው "እነሆ አባትህ ወንድምህን ኤሳውን ሳልሞት በእግዚአብሔር ፊት እንድመርቅህ ከአደንከው አዘጋጅተህ የምበላውን አምጣልኝ ሲለው ሰምቼዋለሁ። አሁንም ልጄ ሆይ በማዝህ ነገር እሽ በለኝ ወደ በጎቻችንም ሒደህ ያማሩ ሁለት ጠቦቶችን አምጣልኝና አባትህ እንደሚወደው ታዘጋጃቸው ዘንድ ሳይሞት በልቶ እንዲመርቅህ ወስደህ ለአባትህ እንድትሰጠው" አለችው። ❤ ያዕቆብም እናቱ ርብቃን እንዲህ አላት "እነሆ ወንድሜ ኤሳው ጠጒራም ነው እኔ ግን ጠጒራም አይደለሁም ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝ በፊቱ እንደምዘብትበት እሆናለሁና ምርቃን ያይደለ በላዬ መርገምን አመጣለሁ"። እናቱም "ልጄ ሆይ መርገምህ በእኔ ይሁን ቃሌን ብቻ ስማኝ ሒድና የምልህን አምጣልኝ" አለችው ሒዶም ለእናቱ አመጣላትና አባቱ እንደሚወደው አድርጋ መብሉን አዘጋጀች። ❤ ርብቃም ከርሷ ዘንድ የነበረ ያማረውን የታላቅ ልጅዋ የኤሳውን ልብስ አምጥታ ለታናሽ ልጅዋ ለያዕቆብ አለበሰችው ያንንም የሁለቱን ጠቦቶች ለምድ በትከሻውና በአንገቱ ላይ አደረገች ያንን ያዘጋጀችውን እንጀራና ጣፋጭ መብልን ለያዕቆብ በእጁ ሰጠችው። ወደ አባቱ ገብቶ "አባቴ ሆይ" አለው አባቱም "እነሆኝ ልጄ ሆይ አንተ ማነህ" አለው ያዕቆብም "እኔ የበኵር ልጅህ ኤሳው ነኝ ያልከኝን አዘጋጅቻለሁ ተነሥና ተቀመጥ ከአደንኩልህም ብላና ነፍስህ ትመርቀኝ ዘንድ" አለው።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ነሐሴ ፳፰ (28) ቀን። ❤ እንኳን #ለአርእስተ_አበው ለቅዱሳን #ለአብርሃም_ለይስሐቅ_ለያዕቆብ_ለዕረፍታቸው ዓመታዊ መታሰብያ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን  ከሚታሰቡ፦ በሰማዕትነት ከዐረፉ #ከአባ_በርሳቦ_ከደቀ_መዛሙርቶቹ_ከሆኑ_ከዐሥራ_ሁለት #መነኰሳት ጋር ደግሞ ከፋርስ ንጉሥ ከፈረሶች ባርደራሱ ጋርና #ስድስት_ሺህ_ከሆኑ_ከኤስድሮስ ማኅበር እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                                                 ✝ ✝ ✝ ❤ #አበ_ብዙሃን_ቅዱስ_አብርሃም፦ የእሊህንም አባቶች ትሩፋታቸውንና ጽድቃቸውን ከሰው መናገር የሚችል ማነው። ከሁሉ ነገር አስቀድሞ እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ እንዲህ አለው "ከአገርህ ወጥተህ ከዘመድህ ከአባትህ ወገን ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሒድ። ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ ስምህንም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ የተባረክህም ትሆናለህ። የሚአከብሩህንም አከብራቸዋለሁ የሚረግሙህንም እረግማቸዋለሁ የዚህ ዓለም አሕዛብም ሁሉ በአንተ ይከብራሉ"። አብርሃምም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሔደ የወንድሙን ልጅ ሎጥንና ሚስቱ ሣራንም ከርሱ ጋር ወሰደ። ❤ አብርሃምም ከካራን በወጣ ጊዜ ዕድሜው ሰባ አምስት ዘመናት ሁኖት ነበር በካራንም ያጠራቀሙትን ገንዘባቸውን ሁሉ ይዘው ወደከንዓን ምድር ደረሱ ። አብርሃምም ያቺን አገር ረጅም ዕንጨት እስከ አለበት እስከ ሴኬም ድረስ ዞራት የከነዓን ሰዎች ግን የዚያን ጊዜ በዚያች አገር ነበሩ ። ❤ እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተገልጦለት "ይችን አገር ለልጆችህ እሰጣታለሁ" አለው አብርሃምም በዚያ ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አዘጋጀ ። ከዚያም ወደ ምሥራቅ ወደ ቤቴል ሔደ በቤተልም በጋይ በኩል በስተምዕራብ ድንኳኑን ተከለና በዚያ ተቀመጠ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ ። ❤ አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ሔደ በዚያም ሊኖር ወደ አዜብ ተጓዘ። ባገርም ራብ በጸና ጊዜ አብርሃም በዚያ ሊኖር ወደ ግብጽ ወረደ በአገሩ ራብ ጸንቷልና ። አብርሃምም ወደ ግብጽ ይገባ ዘንድ በቀረበ ጊዜ እንዲህ ሆነ አብርሃም ሚስቱን ሣራን እንዲህ አላት "አንቺ መልከ መልካም ሴት እንደሆንሽ አውቃለሁ የግብጽም ሰዎች ካዩሽ ሚስቱ ናት ብለው ይገድሉኛል አንቺንም በሕይወት ያኖሩሻል። እንግዲህ ስለ አንቺ ይራሩልኝ ዘንድ በአንቺ ዘመንም ነፍሴ ትድን ዘንድ እኔ እኅቱ ነኝ በያአቸው"። አብርሃም ወደ ግብጽ በደረሰ ጊዜ እንዲህ ሆነ የግብጽ ሰዎች ሚስቱን እጅግ መልከ መልካም እንደሆነች አዩዋት የፈርዖን ወሰዷት ወደ ቤቱም አገቧት ። ❤ ስለርሷም ለአብርሃም በጎ ነገርን አደረጉለት ሴቶች አገልጋዮችንና ወንዶች አገልጋዮችን ላሞችንና በጎችን በቅሎዎችንና ግመሎችን አህዮችንም አገኘ ። እግዚአብሔርም በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት ፈርዖንንና ቤተሰቡንም ጽኑ ሥቃይን አሠቃያቸው። ፈርዖንም አብርሃምን ጠርቶ "በእኔ ያደረግከው ይህ ነገር ምንድን ነው ሚስትህ መሆኗን ያልነገርከኝ ለምንስ እኅቴ ናት አልከኝ ሚስት ልትሆነኝ ወስጃት ነበር አሁንም ሚስትህ ያቻት ይዘሃት ሒድ" አለው። ፈርዖንም አብርሃምንና ሚስቱን ሣራን ከጓዛቸው ሁሉ ጋር እንዲሸኙአቸው ብላቴኖቹን አዘዘ። ❤ ከዚህም በኃላ ለአብርሃም ዘጠና ዘጠኝ ዓመት በሆነው ጊዜ እግዚአብሔር ለአብርሃም ተገለጠለት እንዲህም አለው "በፊትህ የሔድኩ ፈጣሪህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ በፊቴ በጎ ነገርን አድርግ ንጹሕም ሁን። በእኔና በአንተ መካከል ኪዳኔን አጸናለሁ ፈጽሜም አበዛሃለሁ ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። እንግዲህም ስምህ አብራም አይባልም አብርሃም እንጂ እጅግም አበዛሃለሁ አሕዛብ ነገሥታትም ከአንተ እንዲወለዱ አደርጋለሁ"። ❤ አብርሃም በቀትር ጊዜ በድንኳን ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በወይራ ዛፍ አጠገብ ተገለጠለት። ዐይኖቹንም አቅንቶ በተመለከተ ጊዜ እነሆ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቁመው ነበር አይቶም ከድንኳኑ በር ሊቀበላቸው ሮጠ በምድር ላይም ሰገደ እንዲህም አለው "አቤቱ በፊትህ ባልሟልነትን አግኝቼ ከሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ውኃ አምጥተን እግራችሁን እንጠባችሁ ከጥላው ዕረፉ። እንጀራም እናምጣላችሁና ብሎ ከዚህም በኋላ ወደ አሰባችሁት ትሔዳላችሁ" "እንዳልክ እንዲሁ አድርግ" አሉት ። አብርሃምም ወደ ሚስቱ ወደ ሣራ ሩጦ ወደ ድንኳን ገብቶ እንዲህ አላት "ቶሎ በዪ ሦስቱን መሥፈሪያ ዱቄት አቡክተሽ አንድ ዳቦ ጋግሪ"። ❤ አብርሃምም ሁለተኛ ላሞች ወዳሉበት ሮጠ አንድ የሰባ ወይፈን ወሰደና ለብላቴናው ሰጠው እርሱም ፈጥኖ አዘጋጀው። ማርና እርጎ ያዘጋጀውንም ሥጋ አምጥቶ አቀረበላቸውና በሉ እርሱ ግን ቁሞ ያሳልፍላቸው ነበር። እርሱም "ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት" አለው። "እነሆ በድንኳን ውስጥ አለች" አለው "በተመለስኩ ጊዜ የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ወዳንተ እመጣለሁ ሣራም ወንድ ልጅን ታገኛለች" አለው ሣራም በድንኳኑ ደጃፍ በስተኋላው ቁማ ሳለች ይህን ሰማች። አብርሃምና ሣራ ግን ፈጽመው አርጅተው ዘመናቸው አልፎ ነበር ሣራንም የሴቶች ልማድ ትቷት ነበር። ❤ ሣራም ለብቻዋ ሳቀች በልቧ እንዲህ ብላለችና "እስከ ዛሬ ገና ነኝን ጌታዬም አርጅቷል"። እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው "ሣራን ለብቻዋ ምን አሳቃት እስከ ዛሬ ገና ነኝን በእውነትስ እወልዳለሁን ጌታዬም አርጅቷል እኔም እነሆ አርጅቻለሁ ብላ በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን በቀጠርኩህ ዓመት ወደአንተ በተመለስኩ ጊዜ ሣራ በሰባተኛ ወርዋ ልጅን ታገኛለች"። ❤ የዚህም አባት ተጋድሎው ትሩፋቱ ርኅራኄው ጽድቁም ብዙ ነው ሁል ጊዜ እንግዳ ካላገኘ በቀር በማዕዱ አብሮት ካልተቀመጠ አይበላም ነበር ስለዚህም ልዩ ሦስቱ አካላት በማዕዱ እንዲቀመጡ የተገባው ሆነ። አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ አዜብ ምድር ሔደ በሱሬና በቃዴስ መካከልም ኖረ በጌራራም ተቀመጠ ። ❤ አብርሃምም ሚስቱ ሣራን "እኅቴ ናት" አላቸው አቤሜሌክም ልኮ ሣራን ወሰዳት። በዚያችም ሌሊት አቤሜሌክ ተኝቶ ሳለ እግዚአብሔር ወደ አቤሜሌክ ገባ በሕልም እንዲህ አለው "እሷ የጎልማሳ ሚስት ናትና ስለዚች ስለወሰድካት ሴት እነሆ አንተ ትሞታለህ"። አቤሜሌክ ግን አልነካትም ነበር አቤሜሌክም እንዲህ አለ "በውኑ ያላወቀ ሰውን ታጠፋለህን እሱ እኅቴ ናት አለኝ እሷም ወንድሜ ነው አለችኝ ይህንንም ሥራ በንጹህ ልቤ በንጹሕ እጄ አደረግሁት"። ❤ እግዚአብሔርም በሕልም እንዲህ አለው "እኔም በየዋህነትህ እንዳደረግከው አውቄአለሁና ራራሁልህ ኃጢአትም እንዳትሠራ ጠበቅሁህ ስለዚህም እንድትቀርባት አልተውኩህም። አሁንም ለዚያ ሰው ሚስቱን መልስለት ነቢይ ነውና ስለ አንተ ይፀልይልህ አንተም ትድናለህ ባትመልስለት ግን አንተ ሞትን እንድትሞት ያንተ የሆነው ሁሉ እንዲጠፋ ዕወቅ"። አቤሜሌክም አብርሃምን ጠርቶ "ይህ በእኔና በመንግሥቴ ላይ ያደረግከው ምንድር ነው ማንም የማይሠራው ታላቅ ኃጢአት ነው ይህንንስ ያደረግህ ምን አይተህ ነው" አለው ። ❤ አብርሃምም እንዲህ አለ "ምናልባት በዚህ ቦታ እግዚአብሔርን መፍራት የለምና ስለሚስቴ ይገድሉኛል ብዬ ነው። ዳግመኛም በእውነት ከእናቴ ያይደለች ከአባቴ ወገን የሆነች እኅቴ ናት ሚስትም ሆነችኝ እግዚአብሔርም ከአባቴ ቤት ባወጣኝ ጊዜ ይህንን በጎ ሥራ አድርጊልኝ በገባንበትም ቦታ ሁሉ ወንድሜ ነው በዬ አልኋት"።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ነሐሴ ፳፯ (27) ቀን። ❤ እንኳን #ከሰባቱ_ሊቃነ_መላእክት_አራተኛ ለሆነው ለመላእክት አለቃ #ለቅዱስ_ሱርያል ለበዓሉ መታሰቢያ፣ ለአባቶቻችን #ለዐሥራ_ሁለቱ_ለቅዱስ_ያዕቆብ_ልጆች ለመታሰቢያቸው በዓል፣ በሊቀ ካህናት ኤሊ ዘመን #ለነቢዩ_ቅዱስ_ሳሙኤል_ለመጠራቱ ለመታሰቢያው በዓልና ሰብሲር ከሚባል አገር ለሆነ #ለቅዱስ_ብንያሚንና_ለእኅቱ_ለቅዱስ_አውዶክስያ ሰማዕትነ ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። በጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከእሰክድርያው_ቅዱስ_ፊቅጦርና #ከእናቱ_ሣራ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የነገደ_ሥልጣናት_አለቃ_ቅዱስ_ሱርያል፦ ያላቸው ከኤረር መኻከል በኹለተኛዋ በራማ ውስጥ ከሚኖሩት፡፡ ከ፴ው ነገድ ውስጥ ሲኾኑ፤ ስለነዚኽ ነገደ መላዕክት ሊቁ ኤጲፋንዮስ በአክሲማሮስ ላይ ሲገልጽ "ወለሣልስ ጾታ ዐሠርቱ ስሞሙ ሥልጣናት ወሊቆሙ ሱርያል መልአክ ወአንበሮሙ በሣልስ ሰማይ እሉ እሙንቱ እለ ይጸውሩ አብዋቀ ብርሃን ወያደምፁ ለመላእክት በጊዜ ቅዳሴሁ ወስባሔሁ ለእግዚአብሔር ለዘክሮቱ ይደሉ ሰጊድ" ይላል ለስም አጠራሩ ስግደት ይግባውና ልዑል እግዚአብሔር ሦስተኛ ዐሥሩን ነገድ ሥልጣናት ሲላቸው አለቃቸው መልአኩ ሱርያል ይባላል፤ እነዚኽም የብርሃን ነጋሪት የሚይዙ ሲኾኑ መላእክትን በስባሔ ሲያነቁ ሲያተጉ የሚኖሩ እነዚኽ መላእክት ሲኾኑ፤ በራማ በሦስተኘው ከተማ አስፍሯቸዋል። ምንጭ፦ ዶክተር ሮዳስ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ተአምኆ ቅዱሳን በተረጎመበት ላይ።                                                       ✝ ✝ ✝ ❤ በዚችም ቀን ዳግመኛ አባቶቻችን #ዐሥራ_ሁለቱን_የያዕቆብን_ልጆች_ያስቧቸዋል። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።                                                ✝ ✝ ✝ ❤ በዚችም ቀን #በሊቀ_ካህናት_ኤሊ_ዘመን #ነቢይ_ቅዱስ_ሳሙኤል ለመጠራቱ መታሰቢያ ሆነ። ይህንንም ነቢይ ተኝቶ ሳለ እግዚአብሔር ጠራው በኤሊም ፈንታ ነቢይና ካህን አድርጎ ለእስራኤል ልጆች ሾመው። የነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ሰማዕታት_ቅዱስ_ብንያሚንና_እህቱ #ቅድስት_አውዶከስያ፦ የእነዚህም ቅዱሳን ወላጆቻቸው እንግዳና መጻተኛን የሚወዱ ደጎች ክርስቲያኖች ናቸው ደግሞ ለክርስቲያኖች በሚገባ በበጎ ሥራ ሁሉ የተጠመዱ ቅድስና ያላቸው ናቸው። እሊህንም ቅዱሳን በወለዱዋቸውና በአሳደጓቸው ጊዜ ክርስቲያናዊት ትምህርትን አስተማሩአቸው። ❤ ከዚህም በኋላ ወደዚያች አገር ከሀዲ መኰንን መጣ ቅዱስ ብንያሚንም በሰማ ጊዜ የክብር ባለቤት ስለሆነ ክርስቶስ ደሙን ያፈስ ዘንድ ወደደ። በመኰንኑም ፊት ቁሞ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ ጽኑ የሆነ ሥቃይንም አሠቃይቶ ከዚያ በኋላ አሠረው። ወላጆቹና እኅቱ በሰሙ ጊዜ ወደርሱ መጡ አለቀሱ እጅግም አዘኑ እርሱም "የዚህ ዓለም ኑሮ እንደ ጥላ ፈጥኖ ያልፋል የወዲያኛው ኑሮ ግን ፍጻሜ የለውም" እያለ ያጽናናቸው ጀመረ። ❤ እኅቱ አውዶክስያም ይህን መልካም ትምህርቱን ከወንድሟ ሰምታ "ወንድሜ ሆይ ካንተ እንዳልለይ እግዚአብሔር ሕያው ነው አንተ የምትሞተውንም ሞት እኔም ከአንተ ጋራ እሞታለሁ" አለችው። ይህንንም ብላ ወደ መኰንኑ ሒዳ በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመኰንኑ ፊት ታመነች መኰንኑም ያሠቃያት ጀመረ። ከዚህ በኋላም ያለ መብልና ያለ መጠጥ በጨለማ ቤት ሃያ ቀን ከወንድሟ ጋር አሥረው እንዲያኖሩዋት አዘዘ። ❤ ከዚህም በኋላ ከዚያ አውጥቶ ከባድ የሆኑ ደንጊያዎችን  በአንገታቸው አንጠልጥሎ ከጥልቅ ባሕር ጣላቸው የእግዚአብሔር መልአክም ወርዶ ከአንገታቸው ደንጊያዎቹን ፈታላቸው እነርሱም ከወደብ እስቲደርሱ በባሕሩ ላይ ዋኝተው ብጥራ ከምትባል ቦታ ደረሱ አንዲት ብላቴና ድንግልም አግኝታቸው ስባ አወጣቻቸው። ❤ ያን ጊዜም ወደ መኰንኑ ሔደው እርሱንና የረከሱ አማልክቶቹን ረገሙ ብዙ ቀኖችም ጭንቅ የሆነ ሥቃይን አሠቃያቸው። ሥቃያቸውም በአደከመው ጊዜ ራሳቸውን በሰይፍ እንዲቆርጧቸው አዘዘና ቆረጡአቸው። የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕታት ቅዱስ ብንያሚንና በእህቱ ቅድስት አውዶከስያ በጸሎታቸው ይማረን። በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 27 ስንክሳር።                            ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለከ_ብንያሚን_ሰማዕት። ምቱረ ክሣድ በመጥባሕት። ወእለእኅትከ #ሰላም_አውዶክስያ ኅሪት። እንዘ ትብል ሰሚዓ ዘትቤ ከመ ጽላሎት ንብረት። በትምህርትከ አጥባዕካ ለሞት"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የነሐሴ_27።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወሳሙኤልኒ ምስለ እለ ይጼውዑ ስሙ። ይጼውዕዎ ለእግዚአብሔር ውእቱኒ ይሰጠዎሙ። ወይትናገሮሙ በዐምደ ደመና"። መዝ 98፥6-7። የሚነበቡት መልዕታት ዕብ 5፥1-10፣ 1ኛ ጴጥ 3፥14-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 3፥17-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 12፥26-31። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ቅዳሴ ነው። መልካም የመልአኩ የቅዱስ ሱርያል በዓልና የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ የልደት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።

በአዋጅ ነጋሪ ቃልም ይሰበሰባሉ፡፡ ይህቺ ሀገር ትልቅ ናትና እስከ ዓርብም ያስተምራቸዋል፡፡ በዚያን ጊዜ ሰይጣን ቀና፡፡ አባ ሐዊም እንደልማዱ በዕለተ ዓርብ ወደ ሰማይ በሄደ ጊዜ ያ ሰይጣን በመቀመጫው ተቀምጦ በእርሱ በሐዊ ተመስሎ በቀዳሚት ሰንበት ቀንም ተገልጦ "ፈጣሪያችን የሚወዳትን ነገር እነግራችሁ ዘንድ ሁላችሁም ተሰብሰቡ" አለ፡፡ ሁላቸውም ተሰበሰቡ፡፡ "አባት ሆይ! ያለ ልማድህ ዛሬ ለምን መጣህና ጠራኸን?" አሉት፡፡ ያ ጠላት ዲያብሎስም "ጌታዬ ለሕዝቦቼ የዚያችን በቤትህ አንፃር ያለችውን እንጨት ቅጠል በጥርሳቸው ይጨምሩ ዘንድ፣ በአፋቸውም ያጤሱ ዘንድ ዛሬ ካልነገርሃቸው ወዳጄ አይደለህም አለኝ" አላቸው፡፡ ይህችንም እንጨት ባያት ጊዜ እንዲህ አደረገ፣ ሔዋንን በእንጨት እንዳሳታት አሳታቸው፡፡ ዛሬ እንደሚያደርጉትም የጥንባሆ ዕቃን አደረጉ፡፡ ቅጠሏንም አምጥተው ቀጥቅጠው በእሳት አጢሰው ትንሹም ትልቁም፣ የከበረውም የጎሰቆለውም ሁላቸውም ጠጡ፡፡ ❤ ሐዊም በሰማይ ሳለ በጸጋ አውቆ አዘነ፣ ነገር ግን ስለ ሰንበታት ክብር ብሎ አደረ፡፡ ሰኞ በነግህም ሐዊ መጣ፣ ሰይጣንም እንደ ጢስ በኖ ጠፋ፡፡ እርሱም ሰዎቹን ሰብስቦ "ይህን ማን አስተማራችሁ?" አላቸው፡፡ "አንተ ነህ" አሉት፡፡ "ሰይጣን ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፣ ከዛሬ ጀምሮ ተው" አላቸው፡፡ "ትናንት ጠጡ፣ ዛሬ ተው" ይለናል ብለው እምቢ አሉት፡፡ እርሱም አወገዛቸው፡፡ "በእርሻው የዘራት፣ በአፉም የጠጣት፣ በእጁም የያዛት የተረገመ ይሁን" አላቸው፡፡ ጋኔኑም በቅሉ ውስጥ ሆኖ ይነጋገራል፣ በውጭ ያሉትንም አጋንንት ይጠራቸዋል፡፡ በዚህን ሰዓት የተውም አሉ፣ እምቢም ያሉ አሉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ያቺ እንጨት ተረገመች፡፡ ሰውም በጠጣት ጊዜ የአምስት ቀፎ ሙሉ ንቦችን የሚያህሉ አጋንንት ይመጣሉ፡፡ በሁለቱ ዓይኖቹ ውስጥ፣ በሁለቱ አፍንጫዎቹም፣ በሁለቱ ጆሮዎቹም፣ በአፉም፣ በታች በሰገራ መውጫም በእነዚህ ሁሉ እንደ ቀፎ ንብ ይገባሉ፣ ይወጣሉ፡፡ ትምክህትን፣ ትዕቢትን፣ መግደልን፣ ሥርቆትንም፣ ክፉውንም ሁሉ ይመሉታል፡፡ ወሶበ ይሰትያ ብእሲ ይመጽኡ አጋንንት ዘየአክሉ መጠነ ፭ቱ ቀፈዋት ዘመልኡ አንህብት ወይበውኡ ውስቴቱ፡፡ በ፪ አዕይንቲሁ፣ ወበ፪ አዕናፊሁ፣ ወበ፪ አዕዛኒሁ ወበመንፈሱ ዘታህት በአፉሁ በዝንቱ ኵሉ ከመ ንህብ ዘቀፎ ይበውኡ ወይወጽኡ፡፡ ወይመልእዎ ትምክህተ፣ ወትዕቢተ፣ ቀትለ፣ ወሠሪቀ ወኵሎ ዕከያተ እንዲል መጽሐፍ፡፡ ❤ አባታችን ዘርዓ ቡሩክም ይህን ሰምቶ እጆቹን በትከሻው አመሳቅሎ አለቀሰ፣ በሥዕሉም አለ፣ በዚያን ጊዜ ወደ ዓለም ወጣ፡፡ ይህችን የተረገመች እንጨት እንዲህ ብሎ አወገዛት፡- "በአፉ የጠጣት፣ በእጁም የያዛት፣ የዘራት፣ የሸጣት፣ የገዛትም የጥምቀት ልጅ አይደለም፤ በሥጋው አይጠቀምም፣ ነፍሱም ወደ ሲዖል ትወርዳለች፡፡ ልጄ የሆነ ግን መድኃኔዓለምንና ኪዳነ ምሕረትን ያክብር፡፡ ጥንባሆንም አይጠጣ› አለ፡፡ የዚህ ጻዲቅ በረከቱ ያልታዘዝንውን ከመብላት ይጠብቀን አሜን" በማለት ተአምረ መድኃኔዓለም ወገድለ መባዓ ጽዮን ነገረ ጥንባሆን በሰፊው ዘግቦታል፡፡ በሌላም በኩል ትንባሆን በተመለከተ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ የሰጣቸው ቃልኪዳን በራሳቸው በዘርዐ ቡሩክ ገድል ላይ የተጻፈውን ወደፊት እናያለን፡፡ እንዲሁም ይህችን የተረገመች ዕፅ የሚጠቀሙባት ሁሉ የሰይጣን ማደሪያዎች እንደሚሆኑና ክፉውንም ሁሉ እንደሚያሠሩት በሌላም ቦታ በአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ገድል ላይ በሰፊው ተጽፏል፡፡ ከአባታች ከአቡነ ዘርዐ ቡሩክ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸውም ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።

❤ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ሳይጠመቁ ለሚሞቱ አሕዛብም ጭምር ትልቅ ቃልኪዳን የተሰጣቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ይኸውም በቅዱስ ገድላቸው ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል- "በሥራው ሁሉ ፍጹም የሆነና ገድሉ ያማረ ቅዱስ አባታችንን በአድማስ ራስ ቆሞ ምሥራቁንና ምዕራቡን፣ ሰሜኑንና ደቡቡን እንዲባርክ በአፉ እስትንፋስም የምሕረት እስትንፋስን እፍ እንዲል እስትንፋሱንም ከአድማስ እስከ አድማስ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይደርስ ዘንድ እግዚአብሔር አዘዘው፡፡ በእግዚአብሔር በቅዱስ ስሙ ያልተጠመቁ አሕዛብ በእስትንፋሱ ምክንያትና የምሕረት እስትንፋስን እፍ እንዲል እስትንፋሱንም ከአድማስ እስከ አድማስ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይደርስ ዘንድ እግዚአብሔር አዘዘው፡፡ በእግዚአብሔር በቅዱስ ስሙ ያልተጠመቁ አሕዛብ በእስትንፋሱ ምክንያት ልጅነት አግኝተው እንዲከብሩ በቃል ኪዳኑ ተማፅነው ሳይጠመቁ በሚሞቱበት ጊዜ "ይህ ከእኔ የተቀበልከው ቃልኪዳን ከጎኔና ከሰውነቴ እንደፈሰሰው ደሜ ይሁንላቸው" በማለት ለዓለም መድኃኒት አድርጎ ቃልኪዳን ሰጠው፡፡ ❤ ዳግመኛም በቅዱስ አባታችን ዘርዐ ቡሩክ ስም ከእግዚአብሔር ምሕረትን ለምነው በሚሞቱበት ጊዜ በውኃና በመንፈስ ቅዱስ እንደተጠመቁ ይሁንላቸው ብሎ ነገረው፡፡ በከበረና በገናና ስሙ የተጠመቁ ሕዝቡም በኃጢአታቸው በወደቁ ጊዜ በሥራቸውም በረከሱ ጊዜ በጻድቁ ጸሎት ቢማጸኑ በቃልኪዳኑ ቢያምኑ ይህ እስትንፋሱ የኃጢአት ማስተሠርያ ይሁናቸው ብሎታል፡፡ ጻድቁ አባታችንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በሰማ ጊዜ ከዚያ በፊት ለሌሎች ያልተሰጠ ቃልኪዳን ተቀብሎ በአድማስ ላይ ቆመ፡፡ በዚያም ቆሞ መንፈሳዊ እስትንፋሱን በምድር ላይ እፍ አለ፡፡ ያም የሕይወት እስትንፋስ በአራቱ ማዕዘን ደርሶ በኃጢአታቸው መከራ የተቀበሉ ለበደላቸውም የተገዙ ሰዎች በፈጣሪያቸው ስም እንዲከብሩ ዓለሙን ሁሉ ባረከ" ይላል ቅዱስ ገድላቸው፡፡ ይህም የሚያሳያየው መድኃኔዓለም ክርስቶስ የሰውን ልጆች ምን ያህል እንደወደዳቸውና በትንሽ ምክንያት የመዳንን መንገድ ያዘጋጀላቸው መሆኑን ነው፡፡ ❤ ሌላው አቡነ ዘርዐ ቡሩክ እሳቸው በባረኳት ምድርና በልጆቻቸው ላይ ችግርና ርኀብ እንደማይደርስባቸው ቃልኪዳን የተሰጣቸው ድንቅ አባት ናቸው፡፡ ይኸውም በቅርቡ እንኳን በ1977ቱ የርሃብ ዘመን በግልጽ ስለታየ ታሪክ ይመሰክረዋል፡፡ በዚህ ወቅት ከወሎና ከሌሎችም ቦታዎች በርሃብ ተሰዶ ጎጃም ለመጣው የሀገራችን ሕዝብ የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ በረከት ከበቂ በላይ ነበር፡፡ ❤ ጻድቁ በጎጃም ባሕር ዳር አካባቢ ሁለት ቤተ ክርስቲያን አላቸው፡፡ የዓባይ ምንጭ መነሻ የሆነው ፈለገ ግዮን ግሽ ዓባይ ከባሕር ዳር ከተማ 174 ኪ.ሜ የሚርቅ ሲሆን ከባሕር ዳር ቲሊሊ፣ ከቲሊሊ ሠከላ በመሳፈር በቦታው ላይ ለብዙ ዘመን ቆመው በመጸለይ ታላቅ ቃልኪዳን የተቀበሉበትን እጅግ ተአምረኛና ፈዋሽ የሆነውን ጸበላቸውን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቦታው መጽሐፋቸውን ለዓባይ ወንዝ አደራ የሰጡበት ነው፡፡ ❤ ሌላኛው ቤተ ክርስቲያናቸው ከባሕር ዳር የሁለት ሰዓት የመኪና መንገድ ርቀት ላይ በምትገኘውና አዴት በምትባለው ቦታ የሚገኘው ነው፡፡ የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ መካነ መቃብራቸውና ከሰማይ የወረደላቸው መስቀል እዚህ ይገኛሉ፡፡ ቦታውን የረገጠ ሁሉ ከመካነ መቃብራቸው ላይ እምነት ይወስዳል፣ በመስቀሉም ይባረካል፡፡ ነገር ግን ጻድቁ በቃል ኪዳናቸው መሠረት በዚህ መስቀላቸው የተባረከ ሁሉ ዲቁናን፣ ክህነትን መቀበል ስለሚችል ሴቶች አይባረኩበትም፡፡ መካነ መቃብራቸው ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከመቅደሱ ውጭ የሚገኝ ሲሆን ከመቃነ መቃብራቸው ላይ ያለው አፈር ሁልጊዜ እየፈላ መጠኑ ይጨምራል፡፡ ይህን የእምነቱን አፈር ቢዝቁት አያልቅም፣ ባዶ እንኳን ቢደረግ በተአምራት ሞልቶ ይገኛል፡፡ ለብዙ ሕመምተኞች ፍጹም ፈውስ የሆነው ይህ እምነት አጠቃላይ ሁኔታው ለዕይታ አመቺ ስለሆነ ይህንን ማንኛውም ሰው ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ማየትና እምነቱን ወስደው መጠቀም ይችላሉ፡፡ ❤ ጻድቁ አባታችን በ482 ዓመታቸው በዚህች ዕለት ጥር 13 ቀን በታላቅ ክብር ያረፉበት በዓላቸው በድምቀት ይከበራል፡፡ በዕረፍታቸው ዕለት ከቤተ ክርስቲያኑ አደባባይ ላይ አትሮንስ ወጥቶ ገድላቸው ይነበባል፡፡ ገድላቸው ሲነበብም ከአትሮንሱ ሥር ሰባት ጠርሙሶችና አንድ ማሰሮ ይቀመጥና በጠርሙሶቹ ውስጥ አንድ አንድ ስኒ ውኃ ይደረግባቸዋል፡፡ የአባታችን ቅዱስ ገድላቸው ሲነበብ ውኃው ይፈላል፣ ገድሉ ተነቦ እንዳለቀ ጠርሙሶቹና ማሰሮው በተአምራት ተሞልተው ይገኛሉ፡፡ ❤ ጌታችን ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ ትንባሆን ስለሚጠጡ ሰዎች ታላቅ ምሥጢርን እንደነገራቸው በቅዱስ ገድላቸው ላይ ተጽፏል፡፡ ቅዱስ አባታችን በየቀኑ ለሰባት ሰዓት ያህል በሲኦል ውስጥ ቆመው በመጸለይ ብዙ ነፍሳትን ከእሳት ያወጡ ነበር፡፡ አንድ ቀን ብዙ ነፍሳትን ካወጡ በኋላ አንዲት ነፍስ ግን ከሲኦል ግደግዳ ጋር እንደ ሰም ተጣብቃ እምቢ አለቻቸው፡፡ አባታችንም ያቺን ነፍስ አወጣለሁ ሲሉ ቆመው ይጸልዩበት የነበረው የሲኦል እሳት አሁን ያችን ነፍስ አወጣላሁ ባሉ ሰዓት ግን አቃጠላቸው፡፡ እሳቸውም ያችን ነፍስ እዚያው ሲኦል ጥለው በመውጣት ጌታችንን "የዚያች ነፍስ ኃጢአቷ ምንድን ነው?" አሉት፡፡ የዚህን ጊዜ ነው ጌታችን ትንባሆን ስለሚጠጡ ሰዎች ታላቅ ምሥጢርን የነገራቸው፡፡ ይኸውም አባ ሐዊ የሚባሉ ጻድቅ ያስተላለፉትን ውግዘትና ግዝት የጸና እንደሆነ ነው ጌታችን ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ የነገራቸው፡፡ ❤ ዝርዝር ታሪኩም በድርሳነ መድኃዓለም ላይ እንዲህ ተጽፎ ይገኛል፡- ትንባሆ የሚጠጡ ሰዎች ለምን ለማቆም እንደሚቸገሩና መጨረሻቸውም ምን እንደሆነ፡- "ይቅርታውና ምሕረቱ ከሁላችን የጥምቀት ልጆች ጋር ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኔዓለም ያደረገው ተአምር ይህ ነው፡- አባታችን ዘርዓ ቡሩክ መድኃኔዓለምን እንደወደደውና በየወሩ በሃያ ሰባት ቀን በዓሉን እንደሚያከብር በአሥራ ስድስት ቀንም ኪዳነ ምሕረትን እንደሚያከብር እነሆ እንነግራችኋለን፡፡ ባለሟልነትን ባገኘ ጊዜና መድኃኔዓለም የእሳት ፈረስንና የመስቀል ምልክት ያለበት የወርቅ በትርን በሰጠው ጊዜ "ወደ ሲዖል ሂድና መሸከም የምትችለውን ያህል ነፍሳትን አውጣ› አለው፡፡ ሄዶም ወደ ሲዖል ገባ፣ ነፍስ በነፍስ ላይ እንደ ንብ እየተጨናነቁ በሰውነቱ ላይ ታዘሉ፡፡ ነፍሳትንም ይዞ ሲወጣ አንድ ኃጢአተኛ ‹ዘርዓ ቡሩክ ብቻዬን ቀረሁ፣ አውጣኝ" አለው፡፡ ዘርዓ ቡሩክም ወደ እርሱ ተመልሶ ሳበው፡፡ ሰም ከፈትል ጋራ እንደሚጣበቅ ከሲዖል ጥልቅ ጋራ ተጣብቆ እምቢ አለው፡፡ የእሳቱ ነበልባልም ዘርዓ ቡሩክን አቃጠለው፣ እርሱም ተወው፡፡ ክብር ይግባውና እነዚያን ነፍሳት ይዞ ወደ ጌታው ወደ መድኃኔዓለም ሄደ፡፡ ❤ ሄዶም "ጌታዬ ሆይ! አንዲት ነፍስ ስሜን እየጠራች ቀርታለች ማርልኝ" አለው፡፡ መድኃኔዓለምም "ዘርዓ ቡሩክ ሆይ! በእኔ ዘንድ ባለሟልነትን ብታገኝ ትንባሆ የሚጠጣውን ማርልኝ ትለኛለህን?" አለው፡፡ እርሱም "ጌታዬ ሆይ! ይህቺ እንጨት በምን ትከፋለች?፣ ከሁሉ ኃጢአትስ በምን ትበልጣለች?" አለው፡፡ ወይቤሎ መድኅን ኢሰማዕከኑ ግብራ ለዛቲ ዕፅ ዘከመ ዘርዓ ሰይጣን ውስተ ገራህተ ዓለም፡፡ መድኃኔዓለምም "የዚህችን እንጨት ሥራ በዓለም እርሻ ሰይጣን እንደዘራት አልሰማህምን?" አለው፡፡ እነሆም እንነግራችኋለን፣ ስሙ ሐዊ የሚባል የፈጣሪውንም ሕግ የሚጠብቅ አንድ መምህር ነበረ፡፡ በዓርብ ቀንም ወደ ሰማይ ይሔዳል፤ በቀዳሚት ሰንበትና በእሑድ ከፈጣሪው ጋር ይነጋገራል፡፡ በሰኞ ቀንም ወደ ቦታው ይመለሳል፡፡ ለሀገር ሰዎችም በጉባኤ ይነግራቸዋል፣

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ነሐሴ ፳፯ (27) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ ሲዖል ውስጥ ገብተው ይጸልዩ ለነበሩት ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ዘርዐ_ብሩክ_ለልደታቸው_በዓል እግዚአብሔር አምላክ ሰላም አደረሰን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ዘርዐ_ቡሩክ፦ ከመወለዳቸው አስቀድሞ ትንቢት ተነግሮላቸው ነበር፡፡ አባታቸው ደመ ክርስቶስ ዐይነ ሥውር የነበረ ሲሆን አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በተወለዱ ጊዜ ግን የአባታቸውን ዐይን አብርተውለታል፡፡ አባታችን ዘርዐ ቡሩክ ገና በሰባት ዓመታቸው ነው ረቡዕና ዓርብ መጾም የጀመሩት፡፡ በዚሁ በሰባት ዓመታቸውም "ይህን ዓለም ክፋቱን እንዳላይ ዐይኖቼን አሳውርልኝ" በማለት ዐይናቸውን እንዲያጠፋላቸው አምላካቸውን ለምነው እንደፈቃዳቸው ዐይነ ሥውር ሆነዋል፡፡ ነገር ግን ከሰባት ዓመት በኋላ በ12 ዓመታቸው ጌታችን "ለዓለም የምታበራ ብርሃን አደርግሃለሁና ዐይንህም ይብራ" በማለት ዐይነ ብርሃናቸውን መልሶላቸው እንዲያዩ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ዕድሜያቸው (በ12 ዓመታቸው) ሰባቱንም አጽዋማት ይጾሙ ነበር፡፡ ❤ ከዚህም በኋላ ጌታችን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ሁሉ ገለጠላቸው፡፡ መጻሕፍተ ብሉያትን፣ መጻሕፍተ ሐዲሳትን፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትን፣ መጻሕፍተ መነኮሳትን፣ አዋልድ መጻሕፍትን ሁሉ ገልጦላቸዋል፡፡ ከሟርት መጻሕፍት በቀር ያስቀረባቸው ነገር አልነበረም፤ የቅዱስ ያሬድንም ዜማ እንዲሁ ገለጠላቸው፡፡ ❤ ጻድቁ ከሁሉ ቅዱሳን በበለጠ ሁኔታ ዐሥራ ሁለት ክንፍ የተሰጣቸው ሲሆን በ12 ክንፎቻቸውም የሰማይን ደጆች ሁሉ ገሃነመ እሳትንም አልፈው በመሄድ ቀጥታ በሥሉስ ቅዱስ ዙፋን ፊት ይቆሙ እንደነበር ቅዱስ ገድላቸው ይናገራል፡፡ እጅግ በሚደንቅና ከአእምሮ በላይ በሆነ ሁኔታ አባታችን ለሰባት ቀናት በየቀኑ ለሰባት ሰዓት ያህል በሲኦል ውስጥ ቆመው ይጸልዩ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ቅዱሳን በምልጃቸው ነፍሳትን ከሲኦል ሲያወጡ ነው የምናውቀው እንጂ እንደ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በሲኦል ውስጥ ገብቶ ጸሎት የጸለየ ጻድቅ እስካሁን እኔ አላጋጠመኝም፡፡ ❤ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ እንደ አባታችን ተክለሃይማኖት ለጸሎት በመቆም ብዛት አንድ እግራቸው እስኪሰበር ድረስ በብዙ መከራ ተጋድለዋል፡፡ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋር መንበሩን ያጥኑ ዘንድ ከፈጣሪአቸው ታዘው አጥነዋል፡፡ ጌታችን ለአቡነ ዘርዐ ቡሩክ ፍጥረታትን ከመፍጠር በቀር ያልሰጣቸው ሥልጣን የለም፡፡ "እግዚአብሔር ብፁዕና ቅዱስ ለሚሆን አባታችን ዘርዐ ቡሩክ "እኔ ከሥልጣኔ ሥልጣንን፣ ከክብሬም ክብርን፣ ከጥበቤም ጥበብን፣ ከተአምራቴም ተአምራትን፣ ከስጦታዬም ስጦታን፣ ከትዕግስቴም ትዕግስትን፣ ከፍቅሬም ፍቅርን፣ ከትሕትናዬም ትሕትናን፣ ከባለሟልነቴም ባለሟልነትን ሰጥቼሃለሁና ሁሉ ከሥልጣንህ በታች ሆኖ ይታዘዝልህ" የሚል እጅግ ድንቅ ቃልኪዳን ነው የሰጣቸው፡፡ ልዩ ልዩ ሀብታትን ሁሉ ሰጣቸው፡፡ "ለሥላሴ ከሚገባ ከስግደትና በቃልና በሥልጣን ፍጥረታትን ለመፍጠር በቀር ምንም ያልሰጠሁህ የለም" ብሎ ጌታችን በማይታበል ቃሉ እንደነገራቸውና ቃል እንደገባላቸው በቅዱስ ገድላቸው ላይ ተጽፏል፡፡ (የአባታችን ገድላቸው ከመጥፋቱ የተነሣ በአሁኑ ሰዓት አንዳንድ ነጋዴዎች አንዱን ፍሬ ከ3 ሺህ ብር በላይ እየሸጡት ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ቲሊሊ የሚገኘው ገዳማቸው በድጋሚ አሳትሞታል፡፡ ❤ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ በወቅቱ በነበረው ገዥ ፊት በሐሰት ተከሰው ለ5 ዓመታት ያህል በእስርና በእንግልት ሲኖሩ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ምግብ የሚባል አይቀምሱም ነበርና ከእስር ሲፈቱ አምስት ዓመት ሙሉ ሲሰጣቸው ያጠራቅሙት የነበረው ምግብ ትኩስ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ያሳሰራቸውንም ንጉሥ ገና ሕፃን ሳለ እናቱ ልታስባርከው ወደ አባታችን ዘንድ ወስዳው ነበር፡፡ አቡነ ዘርዐ ቡሩክም ሕፃኑን ከባረኩት በኋላ ለእናቱ "ይህ ልጅሽ ወደፊት ይነግሣል በንግሥናው ዘመንም እኔን ያስርና ያንገላታኛል" ብለው ይህ እንደሚሆን አስቀድመው ትንቢት ተናግረው ነበር፡፡ እንዳሉትም ልጁ አድጎ ሲነግሥ ጭፍሮቹ "ንጉሥ ሆይ አንተን የማይወድ ለቃልህም የማይታዘዝ አንድ መነኩሴ አለ" በማለት ምንም እንኳን ንጉሡ ባያውቃቸውም በሐሰት ነገር ስለከሰሱለት በግዞት እንዲኖሩና እንዲታሰሩ አድርጓቸዋል፡፡ ጻድቁ በግዞት ሲወሰዱ "እነዚህን መጻሕፍቶቼን ለሰዎች አደራ ብሰጣቸው ይክዱኛል፣ ቤተ ክርስቲያን ባስቀምጣቸው ይጠፉብኛል" በማለት ሰባት መጽሐፎቻቸውን ለግዮን (ለዓባይ) ወንዝ አደራ የሰጡ ሲሆን ከ5 ዓመት በኋላ ከእስር ተፈተው ሲመለሱ በወንዙ አጠገብ እንደደረሱ ጸሎት ካደረጉ በኋላ "ግዮን ሆይ በእግዚአብሔር ፊት በአደራ የሰጠሁሽን መጽሐፎቼን ግሺ (ትፊ)" ብለው እጃቸውን ወደ ወንዙ ሰደው መጽሐፎቻቸው ሳይረጥቡና ሳይበሰብሱ ከወንዙ ውስጥ አውጥተዋቸል፡፡ እንዲያውም አቧራውን ከመጻሕፍቶቻቸው ላይ እፍ ብለው አራግፈውታል፡፡ ❤ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጠቀሰው የጠለቀው ምሳር እየተንሳፈፈ ወደ ኤልሳዕ እንደመጣ ሁሉ አሁንም እንዲሁ የቅዱስ አባታችን መጽሐፎች አብሯቸው ከነበረውና ዘሩባቤል ከሚባለው ደቀ መዝሙራቸው ጋር ወዳሉበት ተንሳፈው ሊመጡ ችለዋል፡፡ መጽሐፎቻቸውንም አብሯቸው ለነበረው ደቀ መዝሙራቸው ካሳዩት በኋላ እንዲይዛቸው ሰጥተውታል፡፡ ❤ የግዮን ወንዝ "ግሺ ዓባይ" ወይም "ዓባይ" እየተባለ መጠራት የጀመረው አቡነ ዘርዐ ቡሩክ "ግዮን ሆይ በእግዚአብሔር ፊት በአደራ የሰጠሁሽን መጽሐፎቼን ግሺ (ትፊ)" ብለው እጃቸውን ወደ ወንዙ ሰደው መጽሐፎቻቸው ሳይረጥቡና ሳይበሰብሱ ከወንዙ ውስጥ ካወጡበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ አባታችን በቦታው ላይ 30 ዓመት ሙሉ ቆመው ጸልየው ቦታውን የባረኩት ሲሆን ጌታችንም በቦታው ላይ ትልቅ ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ "ብፁዕ አባታችን ለግዮን ወንዝ መጽሐፎቹን በአደራ ሰጥተው በኋላም ከደቀ መዝሙራቸው ከዘሩባቤል ጋር መጽሐፎቹን ከግዮን ምንጭ ውስጥ ከተቀበለ በኋላ "በግዮን ውኃ ውስጥ ሳይረጥቡ በደረቅ መጽሐፎቼን የጠበቀ እግዚአብሔር ይመስገን" ብሎ ፈጣሪውን አመሰገነ፡፡ "ያንጊዜም በውስጥሽ ታላቅ ድኅነት ይደረግብሽ፣ ሕመምተኞች ሁሉ ይዳኑብሽ፣ መካኖች ይውለዱብሽ" ብሎ ግዮንን በቃሉ መረቃት፣ በእጁም ባረካት፡፡ ብፁዕ አባታችንም በዚህች ቦታ ላይ ፈውስ፣ ረድኤት፣ በረከት ይደረግብሽ ብሎ ብዙ ዘመን ቆሞ ጸለየ፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ "ይህ በረከት፣ ረድኤት፣ ሀብት፣ ፈውስ እንደወደድህ እስከዘለዓለሙ በዚህ ቦታ ይሁንልህ" አለው" ተብሎ ነው በቅዱስ ገድላቸው ላይ የተጻፈው፡፡ ❤ ጻድቁ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ ሌላው የሚታወቁበት "ብሄሞትና ሌዋታን" የተባሉ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሁለት ዘንዶዎችን ጥርሳቸውን ቆጥረው ምላሳቸው ሲጣበቅ የዓለም ፍጻሜ እንደሚሆን አስቀድመው ያወቁ ድንቅ ነቢይ የሆኑ አባት በመሆናቸው ነው፡፡ እነዚህም እጅግ ግዙፍ የሆኑ ሁለት እንስሳት ሴትና ወንድ ሆነው ምድርን እንደመቀነት ከበው የያዙ ናቸው፡፡ ዝርዝር ታሪካቸው በመጽሐፈ አክሲማሮስ (ሥነ ፍጥረትን በሚያስረዳው መጽሐፍ) ላይ በስፋት ተጠቅሰዋል፡፡

🌿🌿🌿🌿  የዕለቱን ወንጌል እናንብብ! 🌿🌿🌿🌿          ዕለተ ረቡዕ! ነሐሴ 27 ቀን 2018 ዓ.ም          የዮሐንስ ወንጌል ም 12 ቁ 26 - 31 —————————————————————————— ²⁶ የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፥ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል። ²⁷ አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ። ²⁸ አባት ሆይ፥ ስምህን አክብረው። ስለዚህም፦ አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ። ²⁹ በዚያ ቆመው የነበሩትም ሕዝብ በሰሙ ጊዜ፦ ነጐድጓድ ነው አሉ፤ ሌሎች፦ መልአክ ተናገረው አሉ። ³⁰ ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ ይህ ድምፅ ስለ እናንተ መጥቶአል እጂ ስለ እኔ አይደለም። 🔴ይህን ግሩፕ ✨pin ✨እንዲሁም✨ unmute ✨ ማድረጎን አይርሱ ❗️❗️❗️ ✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨ √ የዩቲዩብ ገጻችንን https://youtube.com/@FinoteBirhanzkidistarsema?feature=shared √ ፌስቡክ ገጻች https://www.facebook.com/finotebirhanzekidistarsema √ የቴሌግራም ገጻችንን https://t.me @Z_FINOTE_BIRHAN √ የኢንስታግራም ገጻችን https://www.instagram.com/ FINOTE BIRHAN Z KIDIST ARSEMA √ የቲክ ቶክ ገጻችንን tiktok.com/@finotebirhanzkidstarsema ✨✨ፎሎ በማድረግ ቤተሰብ ይሁኑ ✨✨ ✨✨✨✨ሰናይ ዕለት✨✨✨

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ነሐሴ ፳፮ (26) ቀን። ❤ እንኳን #ለአብርሃም_ሚስት ለተመሰገነች ለእናታችን #ለቅድስት_ሣራ ለበዓሏ ለመታሰቢያዋ ቀንና ለከበሩ #ለአባ_ሞይስስና ከእኅቱ #ቅድስት_ሣራ ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ ከዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ በከሀዲው ሉልያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ከዐረፉ #ከመነኰሳት_አጋቦስና_ቴክላ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከት፡ያሳትፈን።                                               ✝ ✝ ✝ ❤ #በዚህች_ቀን_ለቅዱስ_አብርሃም ሚስት ለተመሰገነች #ቅድስት_ሣራ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶች አዘዙ። ❤ ይቺንም ክብርተ ማሕፀን የሆነች ጡቶቿም የተባረኩ ክብርት ሣራን የጌራራ ንጉሥ አቤሜሌክ ባል እንዳላት ሳያውቅ በወሰዳት ጊዜ እንዳይቀርባት እግዚአብሔር ገሠጸው በደዌም ቀሠፈው ባሏ አብርሃምም በጸለየለት ጊዜ ከደዌው ተፈወሰ ከዚህም በኋላ ከብዙ ገንዘብ ጋራ ወደ ባሏ መለሳት። ❤ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር በሦስትነቱ  ተገልጦ ወደ ቤቷ እንግድነት በመጣ ጊዜ ለአብርሃምም የይስሐቅን መወለድ በነገረው ጊዜ ሣራም በድንኳኑ ውስጥ ሳቀች እንዲህ ስትል "እስከ ዛሬ ገና ነኝን ጌታዬም አርጅቷል"። እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው "ሣራን ለብቻዋ ምን አሳቃት እስከ ዛሬ ገና ነኝን ጌታዬም አርጅቷል እኔም አሁን አርጅቻለሁ ብላ በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን"። ❤ ከዚህም በኋላ ሣራ ፀንሳ እግዚአብሔር ባለው ወራት በርጅናዋ ለአብርሃም ወንድ ልጅን ወለደች። ይስሐቅም በአደገ ጊዜ ልጅዋ ይስሐቅን ከእስማኤል ጋራ ሲጫወት አየችው። አብርሃምንም ሣራ እንዲህ አለችው "ይቺን ባሪያ ከነልጅዋ አባራት የባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋራ አይወርስምና"። ይህም ነገር ለአብርሃም ስለ ልጁ እስማኤል እጅግ ጭንቅ ሆነበት። ❤ እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው "የዚህ ልጅ የዚችም ባሪያ ነገር በፊትህ ጭንቅ አይሁንብህ የምትልህን ሁሉ ሣራን ስማት ከይስሐቅ ዘር ይተካልሃልና"። ❤ ይህም ነገር ታላቅ ምሥጢር አለው የተመሰገነ ጳውሎስ ቅድስት ሣራን የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ አድርጓታልና። ከዚህም በኋላ በበጎ እርጅና በአረፈች ጊዜ ከኬጢያዊ ኤሞር ልጆች በገዛው ቦታ ቀበራት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበረች እናታችን ቅድስት ሣራ በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #ሰማዕታት_አባ_ሞይስስና_እህቱ_ቅድስት_ሣራ፦ የእሊህም ቅዱሳን ወላጆቻቸው ደጎች እጅግም ባለጸጎች ናቸው። የከበረ ሞይስስ ወላጆቹ ከዐረፉ በኋላ እኅቱ ሣራን ሊአጋባትና ወላጆቹ የተዉትን ገንዘብም ሊሰጣት እርሱም ወደ ገዳም ሒዶ ሊመነኵስ አሰበ። ይህን አሳቡንም በነገራት ጊዜ እንዲህ ብላ መለሰችለት "እኔን ልታጋባኝ ከወደድክ አስቀድሞ አንተ አግባ" እርሱም እንዲህ አላት "እኔ ብዙ ኃጢአት ሠርቻለሁ ስለዚህ ኃጢአቴን ለመደምሰስ እመነኵስ ዘንድ እሻለሁ ማግባት አይቻለኝም የነፍሴን መዳኛ አስባለሁ እንጂ"። ❤ ሁለተኛም እንዲህ ብላ መለሰችለት "አንተ ነፍስህን ስታድን እኔን በዓለም ወጥመድ ውስጥ እንዴት ትጥለኛለህ"። እርሱም እንዲህ አላት "ምንኵስና ከፈለግሽ ስለ ራስሽ የምታውቂ አንቺ ነሽ እኔም የወደድሺውን አደርግልሻለሁ"። እንዲህም አለችው "ለነፍስህ የምታደርገውን ለኔም እንዲሁ አድርግ እኛ ሁለታችን ከአንድ ባሕርይ ከአንድ አባት ከአንዲት እናት የተገኘን ነንና" የልቧንም ቆራጥነት አይቶ ወዲያውኑ ከእርሷ ጋራ ተነሣ ገንዘባቸውንም ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በተኑ። ❤ ከዚህም በኋላ እኅቱ ሣራን ወሰዳት ከእስክንድርያ ከተማ ውጭ ወዳለ የደናግል ገዳም ውስጥ አስገባት እርሱም ከወንዶች ገዳም ገብቶ በዚያ ተጋድሎን ተጋደለ። እንዲሁ እኅቱም ጽኑዕ በሆነ ገድል ተጠምዳ እየተጋደለች ሁለቱም ሳይገናኙ ዐሥር ዓመት ኖሩ። ❤ በሊቀ ጳጳሳት አባ ድሜጥሮስ የሹመት ዘመን ሳዊርያኖስ የሚባል ከሀዲ ተነሥቶ የክርስቲያንን ወገኖች ማሠቃየት ጀመረ። ከመነኰሳት ገዳማትም ብዙዎች በሰማዕትነት ሞቱ። አባ ሞይስስም ተነሣ ሊሰናበታትም ወደ እኅቱ ሣራ ላከ በሰማዕትነት መሞት እንደሚሻም ነገራት። ሣራ እኅቱም በሰማች ጊዜ ወዲያውኑ ተነሣች ሒዳ በሰማዕትነት ትሞት ዘንድ እንድታሰናብታት እመ ምኔቷን ለመነቻት እመ ምኔቷም ጸለየለችላት ሰላምታም ሰጥታ አሰናበተቻት እርሷም ደናግሉን ሁሉ ተሰናበተቻቸው። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ ወንድሟ ሔደች በጐዳናም አገኘችውና እርስ በርሳቸው ሰላም ተባባሉ ወደ እስክንድርያ ከተማም ገብተው በመኰንኑ ፊት ቁመው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ መኰንኑም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ከዚህም በኋላ ራሳቸውን በሰይፍ አስቆረጠ። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ሰማዕታት_መነኰሳት_አጋቦስና_ቴክላ፦ እሊህም ቅዱሳን በከሀዲው ሉልያኖስ ዘመን መከራ በመቀበል ተጋደሉ። ከመኳንንቶቹም አንዱ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው። ሥቃያቸውም በአሰለቸው ጊዜ ለአንበሶች ጣላቸውና ገድላቸውን ፈጽመው የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ። የመነኰሳት አባ አጋቦስና እህቱ ቅድስት ቴክላ በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                          + + + ❤ "#ሰላም_ለክሙ_ሣራ_ወሞይሰስ። ወለቴክላ ሰላም ወአጋቦስ። ዘኀበርክሙ መዊተ በእንተ ክርስቶስ። እትሜነይ በደምክሙ ነጺሐ እምርኵስ። ወበብዕልክሙ እብዓል ጽኑስ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የነሐሴ_26።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ብፁዕ አንተ ወሠናይ ለከ። ብእሲትከ ከመ ወይን ሥሙር ውስተ ጽርሐ ቤትከ። ወውሉድከ ከመ ተክለ ዘይት ሐዲስ ዓውደ ማዕድከ"። መዝ 127፥2-3። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 11፥8-17፣ 1 ጴጥ 3፥1-10 እና 16፥1-16። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥27­-33። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የአቡነ ሀብተ ማርያምና የአቡነ ኢየሱስ ሞዐ የፅንሰት በዓልና የቅስት ሣራ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

ክርስቲያን ቀን ቀን ሕዝቡን ሲያስተምሩ በመዋል ሲመሽ ወደ ሐይቁ በመግባት ሲጸልዩ ያድሩ ነበር፡፡ በሐይቅ እስጢፋኖስና በዙርያው ለነበሩ አበው ማታ ማታ አንድ ብርሃን ወደ ሐይቁ ሲገባ ጠዋት ጠዋትም ሲወጣ ይታያቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን በገዳሙ አባቶች ልመናና በልዑል እግዚአብሔር ትዕዛዝ ወደ ሐይቅ ገዳም ገብተው አበምኔት ሆኑ፡፡ ❤ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከደሴ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ሲሆን የመሠረቱት ካልዕ ሰላማ የተባሉ ግብፃዊ ጻድቅ ናቸው፡፡ ሐይቅን አባ ሰላማ ካልዕና ዐፄ ድል ነአድ በ862 ዓ.ም ነው የቆረቆሩት። ገዳሙን ካቀኑት በኋላ "የማንን ታቦት እናስገባ?" ብለው ሲያስቡ ቶራ የምትባል እንስሳ ጭነት ተጭና ከመካከላቸው ተገኘች፤ ጭነቱን አውርደው ቢያዩት በሐር ጨርቅ የተጠቀለለ የቅዱስ እስጢፋኖስንና የቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለት ታቦት አገኙ፡፡ በላዩም ላይ "ይህንን ታቦት በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የተሰወሩ ቅዱሳን ከእግዚአብሔር ታዘው የላኩት ነው" የሚል ጽሑፍ አገኙ፡፡ ይህ ከሆነ ከ 400 ዘመን በኋላ ነው አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ወደዚህ ቦታ የመጡት፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ለ52 ዓመት ቀን ቀን መንፈሳዊ ሥራቸውን እየሠሩ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ቆመው ሲጸልዩ ያድራሉ፡፡ ❤ አባ ኢየሱስ ሞዐ በሐይቅ እስጢፋኖስ በአበ ምኔትነት በቆዩባቸው 45 ዓመታት ከየገዳማቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመገልበጥና በማሰባሰብ የመጀመርያው ዘመናዊ የቤተ ክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ በዚሁ ገዳም ውስጥ የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ቋሚ ትምህርት ቤት በማቋቋም 800 መነኰሳትን በትምህርተ ሃይማኖት አሠልጥነው በንቡረ ዕድነት ማዕረግ ሾመው በመላ ሀገራችን እንዲሠማሩ አድርገዋቸዋል፡፡ ከእነዚህም ተማሪዎቻቸው መካከል አቡነ ተክለ ሃይማኖት (ደብረ ሊባኖስ)፣ አቡነ ኂሩተ አምላክ (ጣና ሐይቅ ዳጋ እስጢፋኖስ)፣ አቡነ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ቦረና)፣ አባ በጸሎተ ሚካኤል (ቦረና)፣ አቡነ ገብረ እንድርያስ (ቦረና)፣ አቡነ ሕዝቅያስ (ቦረና)፣ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ዳውንት)፣ አቡነ አሮን (መቄት)፣ አቡነ ተክለ ኢየሱስ ሞዐ (ሐይቅ)፣ አቡነ አላኒቆስ (ትግራይ)፣ አቡነ በግዑ (ሐይቅ)፣ አቡነ ሠረቀ ብርሃን (ሐይቅ)፣ አቡነ ብስጣውሮስ (ሐይቅ)፣ አቡነ ዮሴፍ (ላስታ) ዋና ዋናዎቹና በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ጻደቁን ንጉሥ ዐፄ ይኩኖ አምላክንም በትምህርተ ሃይማኖት አንጸውና ኮትኩተው ያሳደጉት ጻድቁ አባታችን ናቸው፡፡ ❤ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ መጥተው በሐይቁ ዳር ቆመው ሳለ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ በእግሩ በውኃው ላይ እየሄደ እያሳያቸው ተከትለውት እንዲሄዱ ነገራቸው። አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ሐይቁን በእግራቸው ጠቅጥቀው ተራምደው ተሻግረው አቡነ ኢየሱስ ሞዐን አገኟቸው፡፡ እርሳቸውም አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ እርሳቸው እየመጡ እንደሆነ በመንፈስ ዐውቀው ነበርና ሲያገኟቸው በጣም ተደስተው ከተቀበሏቸው በኋላ አመነኵሰዋቸዋል፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ እጅግ በጣም ብዙ መነኰሳትን አፍርተዋል፡፡ የመጀመሪያው መነኩሴ አባ እንጦንስ ነው፡፡ እንጦንስ መቃርስን፣ መቃርስ ጳኵሚስን፣ ጳኵሚስ ቴዎድሮስን፣ አቡነ አረጋዊንና 8ቱን ቅዱሳን አመነኰሱ፡፡ አቡነ አረጋዊም ወደ ኢትዮጵያ በ460 ዓ.ም መጥተው ክርስቶስ ቤዛን፣ አባ ክርስቶስ ቤዛም መስቀለ ሞዐን፣ መስቀለ ሞዐም አባ ዮሐኒን፣ አባ ዮሐኒም አባ ኢየሱስ ሞዐን፣ አባ ኢየሱም ሞዐም አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አመነኰሱ፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ምን ያህል ቀደምትና ባለ ታሪክ አባት እንደሆኑ ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ ❤ በዮዲት ጉዲት እጅጉን ተጐድታ የነበረችው አገራችን ዳግም የወንጌሉ ብርሃን እንዲበራባት ሊቃውንት፣ እንዳይታጡባት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳይቆነጻጸሉ፣ መነኰሳት አባቶች ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ወርደው ገዳማትን እንዲያስፋፉ ያደረጉት አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለአገራችን ትልቅ ባለውለታ ናቸው፡፡ በተለይም በሐይቅ እስጢፋኖስ ያፈሯቸውን 800 ሊቃውንት መነኰሳት በመላዋ ኢትዮጵያ በመሰማራታቸው ዛሬ የምናያቸውን አብዛኛዎቹን ገዳማትና ቅዱሳት መጻሕፍት አቆይተውልናል፡፡ አባታችን ለ45 ዓመታት ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምን በአበ ምኔትነት እያስተዳደሩ ከቆዩ በኋላ ኅዳር 26 ቀን 1292 ዓ.ም በዕለተ እሑድ ዐርፈዋል፡፡ ከአባታች ከአቡነ ኢየሱስ ሞዐ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ነሐሴ ፳፮ (26) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጲያውያኑ_ጻድቃን ለአባታችን #ለአቡነ_ሀብተ_ማርያምና ታላቁ ገዳም ሐይቅ እስጢፋኖስ ላቀኑ #ለአቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ ለጽንሰታቸው ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል በዓል በሰላም አደረሰን።                                                        ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ሀብተ_ማርያም_ጽንሰት፦ " የኢትዮጵያ ንጉሥ እስክንድር በነገሠ በሺህ አራት መቶ ሰማንያ ስድስት ዓመተ ምሕረት ቅዱስ ፍሬ ብሩክ የሚባል አንድ ሰው በዚያች ሀገር ውስጥ ነበር፤ ይኸውም ከከበሩም ሰዎች ተለይቶ ብዙ ገንዘብ ያለው ባለ ጸጋ ነበር። በሕጋዊው ጋብቻ ስሟ ቅድስት ዮስቴና የምትባል ሴት አገባ፤ ይኽችውም ሴት በደግ ሥራ ሁሉ የተሸለመች ያጌጠች ነበረች። ❤ ብዙ ደግቷንና ትሩፋቷን ኋላ እንነግራችኋለን፤ ነገር ግን አስቀድመን በዚህ ዓለም ከሕጋዊ ባሏ ጋር በንጽሕ ጋብቻ እግዚአብሔር በመፍራት ምጽዋትን በመስጠት የውሃትንና ትሕትናን ገንዘብ አድርጋ በትግሥት በበጎ ሥነ ምግባር ሁሉ ጸንታ እንደኖረች እነግራችኋለን። ❤ እንዲህ ባለ ሥራ ሳለች መንፈሳዊ ሐሳብ እንዲህ ሲል ተነሳባት፤ "ለአንቺ በዚህ ዓለም መኖር ምን ይረባሻል የሚል መጣባት፤ ዛሬ የሚያልፍ የሚጠፋ ነውና፤ ጌትነቱ የሚመሰገንበት ለዘለዓለም የሚኖር የማያልፍ ሌላ ዓለም ይገለጣልና"፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል "ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ቢነዳ በነፍሱ ከተጎዳ ምን ይጠቅመዋል ምን ይረባዋል" እንዳለ። ❤ "ለአንቺ ግን በሰማይ ጸንቶ መኖርና ሁለተኛዋን ሀገር መያዝ ይሻላል" የሚል ሐሳብ መጣባት፤ ይህን ካሰበች በኋላ ፈጥና ተነሥታ በሌሊት ከቤቷ ወጥታ፤ በሀገሯ አንጻር ትይዩ ወደ ሆነው በረሃ ሄደች፣ በውስጡ ከሰው ወገን የማይኖርበት ቦታ መካከሉ ምድረ በዳ ወደ ሆነው በረሃ ደረሰች። ከጅቦች፣ ከነብሮች፣ ከዓሣሞች፣ ከጦጦችና ከዝንጆሮች በስተቀር ምንም ምን የማይኖርበት በረሃ ነበር። ❤ በዚያችም ቦታ ደጃፏ ያልተዘጋች ትንሽ ዋሻ አገኘች ምንም ምንም ሳትናገር ከዋሻው ውስጥ ገባች። በዋሻው ውስጥ ቁሞ በትጋት መዝሙረ ዳዊትን በአንክሮ በተደሞ የሚደግም ክቡር ባሕታዊን አየች፤ ባየችውም ጊዜ ደነገጠች። እርሱም ሴቲቱን ባያት ጊዜ ፍርሃት መንቀጥቀጥ በላዩ ላይ ወረደበት፣ በመስቀል ምልክትን አማተበ። ይህም ቅዱስ ባሕታዊ ፊቱን በአማተበና ስመ እግዚአብሔርንም በጠራ ጊዜ እንዳልሸሸች ስለአየ ይህች ሴት ክርስቲያን መሆኗን አወቀ። ❤ መጀመሪያ ስትገባ የጋኔን ምትሐት መስላው ነበርና፤ ሰው መሆኗን ባወቀና በተረዳ ጊዜ ተቆጣት። "አንቺ ዘማዊት ሴት ምንኵስናየን ታፈርሽ ዘንድ ከየት መጣሽ" አላት። "ወይም ደግሞ ሰይጣን በልብሽ ገብቷልን"። "ጌታዬ እኔስ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ነኝ እንጅ አንተ እንደምትለኝ ዘማዊት አይደለሁም" አለችው። "ነገር ግን ቤቴን ንብረቴን ያለኝን ትቼ መጥቻለሁ፣ በዓለም ውስጥ ያለውን ሁሉ ንቄ እመንን ዘንድ እወዳለሁና ስለዚህም ወደዚህ ምድር በዳ መጣሁ። በዚህም ገዳም ወይም በረሃ ሰው እንዳለ አላውቅሁም ነበር፤ ሰውን የሚባሉ አራዊት ብቻ የሚኖሩበት ይመስለኝ ነበር" አለችው። ❤ ይህም ባሕታዊ በትሕትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ይህን የሚያስደንቅ መልካም መልስ በመለሰችለት ጊዜ። አንድ ሰዓት ያኽል ካሰበ በኋላ "በፍቅር አንድነት ወደ ቤትሽ ተመለሽ" ብሎ በሰላም ተናገራት። እርሷም "ወደዚህ ቦታ ዳግመኛ አልመጣም እንጅ ካንተ ዘንድ ተለይቼ እሄዳለሁ። ነገር ግን ወደ ቤቴ ተመልሼ አልሄድም። ከገዳማት በአንድ ቦታ መንኵሼ መኖር እወዳለሁ እንጅ" አለችው። ጌታ "በወንጌል እርፍን በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚያርስ የለም" እንዳለ ወደ ዓለም አልመለስም" አለችው። ❤ ያም ባሕታዊ "ምንኵስናስ የለሽም አልታዘዘልሽም፤ ነገር ግን በሰላም ወደ ቤትሽ ወደ ሕጋዊ ባልሽ ተመለሽ። የተፈቀደልሽንስ እነግርሻለሁ ከሕጋዊ ባለቤትሽ ወንድ ልጅን ትወልጃለሽ እርሱም ለዓለም ሁሉ የሚጠቅም ይሆናል። የገድሉና የትሩፋቱ ዜና እስከ ዓለም ዳርቻ ይደርሳል፤ በሕይወተ ሥጋ ሳለ በፈጣሪው በእግዚአብሔር ፈቃድ የብዙዎቹን ሰዎች ነፍሳት ከሲኦል ያወጣል። እንደ መላእክትም ክንፈ ጸጋ ተሰጥቶታል። በሰው አካል በሥጋ ሁኖ ሳለ በተመሥጦ ወደ ሰማይ ወጥቶ የሥላሴን የአንድነትን የሦስትነት ምሥጢር ያያል"። ❤ ቅድስት ዮስቴናም ከአረጋዊ ባሕታዊ ይህን ነገር ሰምታ አደነቀች፤ "የፈጣሪየ ፈቃድ ከሆነ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ" አለች፤ ይህን ብላ ተመልሳ ወደ አገሯ ወደ ቤቷ ገባች፤ ቤተሰቦቿም መውጣቷንም መግባቷንም ምንም አላወቁባትም፤ ከዚያም በነሐሴ 26 ቀን ጸነሰች። ከዘጠኝ ወራትም ከቆየች በኋላ፤ መልኩ እንደ በረዶ ነጭ እንደ ጽጌ ረዳም ብሩህ ቀይ የሆነ መልከ መልካም ልጅ ወለደች ሁለተናውም ጨረቃ የጉለቱ ምልዓት 15 ሌሊት ሁኖ በብሩህ ብርሃን በምልዓት በሚያድርበት ጊዜ እንደሚያበራው መልካም ብርሃን ገጹ ብሩህ የሆነ ልጅ ወለደች፤ ይህ ሕፃን በግንቦት ወር በ 26 በተወለደ ጊዜ በአባቱና በእናቱ ቤት ታላቅ ደስታን ሆነ፤ ሜሉን ገቹን አርደው ዘመዶቻቸውን ጎረቤቶቻቸውን አማቾቻቸውን ምርዓቶቻቸውን ጠርተው ለበዓሉ እንደሚገባ መብሉንና መጠጡን ሰጥተው በሚገባ አጠገቡዋቸው፤ ...ካህኑም ተቀብሎ አጠመቀው ከአጠመቀውም በኋላ ለነፍሱ ዋስ (ለክርስትና አባቱ) አሳልፎ ሰጠው ስሙንም ሀብተ ማርያም ብሎ ሰየመው። ከአባታችን ከአቡነ ሀብተ ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ ገድለ አቡነ ሀብተ ማርያም።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ፦ አገራቸው ጎንደር ክፍለ ሀገር ስማዳ ወረዳ ሲና ዳኅና በሚባል ቦታ ነሐሴ 26 ቀን ተፀንሰው ግንቦት 26 ቀን 1210 ዓ.ም ከአባታቸው ከቅዱስ ዘክርስቶስና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ክብራ ተወለዱ፡፡ የተወለዱትም በቅዱስ ነአኲቶ ለአብ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ❤ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የቆብ አባት ሲሆኑ ታላቁን ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገዳም የቆረቆሩ ደገኛ አባት ናቸው፡፡ ዕድሜያቸው 30 ዓመት እስከሚደርስ ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ትምህርተ ሃይማኖትንና ግብረ ገብን ሲማሩ ከቆዩ በኋላ በ1240 ዓ.ም ይህንን ዓለም በመተው ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገቡ፡፡ በደብረ ዳሞ ገዳም መነኰሳቱን እየረዱ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያጠኑ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየገለበጡ ለሰባት ዓመታት ከቆዩ በኋላ የደብረ ዳሞ 3ኛ አበ ምኔት ከሆኑት ከአባ ዮሐኒ እጅ ምንኲስናን በ1247 ዓ.ም ተቀበሉ፡፡ ❤ አንድ ቀን ሌሊት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደርሳቸው መጥቶ "የስምህ መክበርያ ወደሆነው ሐይቅ ወደ ተባለው ሥፍራሂድ" አላቸው፡፡ አባታችንም "ቦታውን እንዴት ዐውቀዋለሁ?" በማለት መልአኩን ቢጠይቁት "ተነሥ! ጉዞህን ጀምር ቦታውን እኔ አሳይሃለሁ" አላቸው፡፡ አባ ኢየሱስ ሞዐ በመልአኩ እንደታዘዙት ከበዓታቸው ተነሥተው ተከተሉት፡፡ የብዙ ወራት መንገድ የሆነውን ጐዳናም በስድስት ሰዓት አደረሳቸው፡፡ በዚያን ወቅት ከሐይቅ ገዳም በስተ ሰሜን ወደነበረው የቅዱሳን ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ደረሱ፡፡ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ከመግባታቸው በፊት ለ 6 ወራት ያህል በቅዱሳን በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል፡፡ ያገለግሉበት በነበረው ቤተ

                          ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለቢጻርዮን_እምሐውዘ_ዓለም ዘተኅግሡ። እንዘ ኢያጠሪ ሎቱ መንጸፈ ወልብሰ። እምኀበ አምላክ አድምዐ ወተጸገወ ሞገሰ። በምድረ ምቅዋሙ ዘአስከቡ እስከ ድውየ ፈወሰ። እስከ ማየ ባሕር ኬደ ከመ ይከይድ የብሰ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የነሐሴ_25።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወይእዜኒ መኑ ተስፋየ አኮኑ እግዚአብሔር። ወትዕግሥትየኒ እምኀቤከ ውእቱ። ወእምኵሉ ኃጢአትየ አድኀንከኒ"። መዝ38፥7-8። የሚነበቡት መልዕክታት ኤፊ 6፥10-19፣ 1ኛ ጴጥ 3፥1-10 እና የሐዋ ሥራ 12፥12-20። የሚነበበው ወንጌል ማር 3፥7-13። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ባስልዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ነሐሴ ፳፭ (25) ቀን። ❤ እንኳን #ለአባ_እንጦንስ_ደቀ_መዝሙር_ለሆነ ታላላቅ ተአምራቶችን ላደረገ ለታላቁ አባት #ለአባ_ቢጻርዮን_ለዕረፍት_በዓል፣ #ለቅዱስ_እንድርያኖስና_ሃያ_አራቱ_ባልንጀሮቹ ሰማዕታት ለዕረፍታቸው በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከኤልያኖስ_ከእኅቱ_አውዶክስያ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_እንድርያኖስና_ሃያ_አራቱ_ባልንጀሮቹ ሰማዕታት፦ ይህም እንድርያኖስ ከመክስምያኖስ መኳንንቶች አንዱ ነበር እርሱም የጐልማሶች አለቃ ነበረ። ለጣዖት መስገድን እምቤ ስለአሉ ንጉሡ ምእምናንን ሲአሠቃያቸው ቅዱስ እንድርያኖስ የሰማዕታትን የልባቸውን ቆራጥነትና በመከራቸው ላይ መታገሣቸውን ተመልክቶ አደነቀ። ❤ እንዲህም አላቸው "ይህን ያህል ስትታገሡ ምን ታገኛላችሁ?" ቅዱሳን ሰማዕታትም "የሚጠብቀንን ተሰፋ ለመናገር አንደበታችን አይችልም" አሉት ስለ ዓለም ድኅነትም ክርስቶስ መከራ እንደ ተቀበለ ከብሉይና ከሐዲስ መጽሐፍ ነገሩት። እንድርያኖስም በሰማ ጊዜ ጽሕፈትን ወደ ሚያውቁ ብልሆች ሰዎች ሔደና "እኔ ከዛሬ ጀምሮ ክርስቲያን ነኝ ስሜን ከገድለኞቹ ጋራ ጻፉ" አላቸው። ❤ ለንጉሥ መክስምያኖስም እንዲህ እንዳለ በነገሩት ጊዜ ጠርቶ "እንድርያኖስ ሆይ አበድክን" አለው እንድርያኖስም "ከቀድሞው እብደቴ ተመለስኩ እንጂ እኔ አላበድኩም" ብሎ መለሰለት። ንጉሡም ሰምቶ ወደ ወህኒ ቤት ከንጹሐን ሰማዕታት ጋራ እንዲጨምሩት አዘዘ። ከአገልጋዮቹም አንዱ ሒዶ ለሚስቱ እንጣልያ ነገራት በሰማችም ጊዜ ደስ እያላት ወደ ወህኒ ቤት ሔደች ሃያ አራቱ ቅዱሳን ሰማዕታት የታሠሩበትን ማሠሪያቸውን ሳመች በሥቃዩ እንዲታገሥ የባሏን ልብ ያጽናኑ ዘንድ ለመነቻቸው። እርሱንም እንዲህ አለችው "ላህይህ ደምግባትህም ርስትህም ጥሪትህም አያስትህ ሁሉም ከንቱ ነውና ነገር ግን በእርሱ ዘንድ የማያልፍ መንግሥትን ትወርስ ዘንድ የክብር ንጉሥ ክርስቶስን ተከተለው" ይህንንም ብላ ወደቤቷ ገባች። ❤ ከዚህም በኃላ እንድርያኖስ ለፍርድ እንደ ሚአቀርቡት በአወቀ ጊዜ ሊሰናበታት ወደ ሚስቱ ሔደ መምጣቱንም ሰምታ የሸሸ መሰላት ደጇንም ዘግታ በውስጥ ሁና እንዲህ እያለች ዘለፈችው "ትላንት ሰማዕት ተብለኽ ዛሬ ክርስቶስን ካድከውን" እንድርያኖስም ሰምቶ የሃይማኖቷን ጽናት አደነቀ እንዲህም አላት "እኅቴ ሆይ እንድሰናበትሽ ክፈችልኝ" አላት። በሰማችም ጊዜ ከፈተችለት ከዚህም በኋላ ሁሉን እያነጋገራት እስከ እሥር ቤት ወሰዳት እንጣልያም ከዚያ በደረሰች ጊዜ የታሠሩትን ቅዱሳን ተሳለመቻቸው ቅስላቸውንም አጠበች። ❤ ከዚህም በኃላ ንጉሡ ቅዱሳኑን ከእሥር ቤት እንደአመጧቸው አዘዘ በመጡም ጊዜ ከሥቃይ ብዛት የተነሣ እንደደከሙ አያቸው። እንድርያኖስንም በፊቱ አቁሞ ለአማልክት ሠዋ አለው ቅዱሱም እርሱንና የረከሱ አማልክቶቹን ረገመ ንጉሡም የሆድ ዕቃው እስኪፈስስ ሆዱን እንዲደበድቡት አዘዘ በዚያን ጊዜም የእንድርያኖስ ዕድሜው ሃያ ስምንት ዓመት ነበር። ❤ ከዚህም በኃላ እንድርያኖስን ከባልንጀሮቹ ሰማዕታት ጋራ ወደ እሥር ቤት መለሱት እንጣልያም መጥታ የቅዱሳንን ደማቸውን ጠራረገችላቸው። እሊህ ቅዱሳንም እንድርያኖስን እንዲህ ብለው ተሳለሙት "እንድርያኖስ ሆይ ስምህ ተሳለሙት በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎአልና ደስ ይበልህ"። ❤ ንጉሡም መስፍ አምጥተው የቅዱሳኑን ሁሉ ጭናቸውን በድጅኖ ይሰብሩ ዘንድ አዘዘ እንጣልያም የእንድርያኖስን እጆቹንና እግሮቹን በመስፍ ላይ ለማኖር ቀደመች ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ እስከ ሰጠ ድረስ የእንድርያኖስን ዐጥንቶቹን ወታደሮች ቀጠቀጡ የቅዱሳኑንም ሁሉ ጭናቸውን ሰብረው ወደ እሳት ወረወሯቸው እሳቱ ግን ከቶ አልነካቸውም። ምእመናንም መጥተው በጭልታ ወደ ሌላ ቦታ ወሰዱአቸው የመከራውም ወራት እስቲያልፍ ሠወሩአቸው። እንጣልያም የእንድርያኖስን የእጁን ቁራጭ ወስዳ በትርአሷ ውስጥ አኖረችው። ❤ ከዚህም በኋላ የሀገሩ ገዥ እንጣልያን ሊአገባት ወደደ በአወቀችም ጊዜ የባሏን የእጅ ቁራጭ ይዛ በመርከብ ሸሸች የቅዱሳኑ ሥጋ ወዳለበትም ደርሶ ወደ እነርሱ ይቀበሏት ዘንድ ለመነች ጌታችንም ልመናዋን ተቀብሎ አሳረፋት ከእነርሱም ጋራ ተቀበረች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ እንድርያኖስና በሃያ አራቱ ባልንጀሮቹ ሰማዕታት አማላጅነት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ቢጻርዮን፦ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ምእመናን ነበሩ። በአደገም ጊዜ የምንኵስና ልብስን ለብሶ እግዚአብሔርን ሊአገለግል ወደደ ዓለምንም ንቆ ወደ አባ እንጦንስ ሔደ ለእርሱም ደቀ መዝሙር ሆኖ ብዙ ዘመናት አገለገለው። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ አባ መቃርስ ሒዶ ቅዱሳን አረጋውያን መነኰሳትንም አገለገላቸው። በአስቄጥስም ገዳም ይዘዋወር ነበር በቤት ውስጥም አያድርም ነበር። ምንጣፍና ልብስ እስኪአጣ ድረስ ምንም ምን ጥሪት አልነበረውም መነኰሳቱም የማቅ ጨርቅ ይሰጡት ነበር። ወገቡንም ታጥቆ በመነኰሳቱ መንደር ይዞር ነበር በቤቶቻቸውም ደጃፍ እያለቀሰ ይቀመጥ ነበር። ❤ የማያውቀውም ወደርሱ በደረሰ ጊዜ "አባቴ ሆይ ምን ያስለቅስሃል" ይለው ነበር። እርሱም "ንብረቴን ስለዘረፉኝ እንዳልሞት ሸሸሁ ከወገኔም ክብር ተለይቼ በጉስቁልና ወደቅሁ" ይለው ነበር። የቃሉንም ምልክት የማያውቅ የጠፋውን ገንዘብህን እግዚአብሔር ይመልስልህ ብሎ ካለው ይሰጠው ነበር። እርሱም ተቀብሎ ይሔድና ለሌለው ይሰጥ ነበር። የቃሉን ምልክት የሚያውቅ ግን በፈቃደ ነፍስ የሚሠሩ ትሩፋትን ሰይጣን ከሰዎች የማረካቸው መሆኑን ልብ ብሎ ያስተውል ነበር። አባቶችም ጭንቅ የነበረ ተጋድሎውን ስለርሱ ይናገሩ ነበር። እርሱ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ከቶ ሳይተኛ ቁሞ ኖሮአልና ። ❤ በምንኵስናውም ወራት ብዙ ጊዜ በየአርባ ቀን ጾመ እነሆ እንዲህ እየተጋደለ ድንቆችንም እያደረገ ኀምሳ ሰባት ዓመታት ኖረ። ቅዱሳን አባ ዱላስና አባ ዮሐንስም ከተአምራቱ ተናገሩ እነርሱ ከርሱ ጋር ወደ ኤርትራ ባሕር ዳርቻ ሔዱ። እጅግም በተጠሙ ጊዜ እንደተጠሙ አውቆ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ መራራውንም ውኃ ጣፋጭ አድርጎላቸው ጠጥተዋል። ✝ በሁለተኛም ጊዜ ወደ ፈሳሽ ውኃ ደርሶ መሸጋገሪያ አጣ ወደ ጌታችንም ጸለየ ያን ጊዜም እንደ የብስ በባሕሩ ላይ ሔደ። በአንዲት ቀንም የከበሩ አባቶች በጸሎታቸው ያድኑት ዘንድ ጋኔን ያደረበትን ሰው ወደ አስቄጥስ ገዳም ሰዎች አመጡ አባቶችም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ እርሱ ከከንቱ ውዳሴ ስለሚሸሽ ብንነግረው ይህን ጋኔን የያዘውን አያድነውም ። ❤ አባ ቢጻርዮን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለጸሎት ወደሚቆምበት ቦታ ያንን ጋኔን ያደረበትን ሰው አስተኙት። አባ ቢጻርዮንም በገባ ጊዜ ያን ጋኔን ያደረበትን ሰው ተኝቶ አገኘውና ቀሰቀሰው እጁንም ይዞ "ተነሥ" አለው ያን ጊዜም ድኖ ተነሣ አእምሮውም ተመለሰ። ያዩትም እጅግ አደነቁ ለሚፈሩት ስለሚሰጠው ጸጋውም እግዚአብሔርን አመሰገኑት። ❤ የዚህም ቅዱስ ተአምራቶቹ ከነገርናችሁ የበዙ ናቸው እግዚአብሔርንም አገልገሎ በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ቢጻርዮን ጸሎት ይማረን። በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 25 ስንክሳር።