uz
Feedback

Firibgarlarga uchmang! Telemetrio bunday kanallarni topadi va belgilaydi 👉 Belgini ko‘rmoqchi bo‘lsangiz, obuna bo‘ling 👈

ጲንኤል

ጲንኤል

Kanalga Telegram’da o‘tish

ጲንኤል ...አንዳንድ ጦርነቶች በውስጣችን ይካሄዳሉ። ይህ ቻናል እነዚያ ጦርነቶች በቃላት የሚገለጹበት፣ ሰው ከራሱ ጋር የሚገናኝበት፣ ሀሳብ፣ ትዝታ እና ውስጣዊ ግጭቶች የሚጻፉበት ገጽ። ✍️ እስራኤል ሰይፉ

Ko'proq ko'rsatish
Mamlakat belgilanmaganToif belgilanmagan
194
Obunachilar
Ma'lumot yo'q24 soatlar
-17 kun
-430 kun
Postlar arxiv
ዝምታ.... ወደኛ ሳይደርሱ ረጅም ጊዜ እንዲያልፍ ወደማይፈቅዱ ነገሮች ለመሄድ ነጻ የሚያደርግ መንገድ ነው። በዕለት ተዕለት ህይወታችን ብዙ ነገሮች ሀሳቦች ድምፆች እና ግፊቶች ያለማቋረጥ ይወተውቱናል። እነዚህ ነገሮች ብዙ ጊዜ እውነተኛ ማንነታችንን የሚሸፍኑ ጉልበታችንን የሚበሉ እና ወደ ውስጣዊ ሰላማችን እንዳንደርስ የሚያግዱን ናቸው። ዝምታ  ከዚህ ውጫዊና ረብ የለሽ ግርግር የምንወጣበት መሸሸጊያ ነው። ዝምታን ስንመርጥ እኛን ወደ እውነተኛው መዳረሻችን ሊያቀርቡን የሚችሉትን የህይወት እሴቶች ከመረባረብ እና ጊዜ ከመሻማት እናድናቸዋለን። ብዙ ጊዜ በጊዜያዊ ነገሮች ስንጠመድ ለአእምሮአችን ለነፍሳችን እና ለህይወት አላማችን አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ለምሳሌ፦ ጸሎት ራስን መመርመር አልያም እውነትን መፈለግ ሊሆን ይችላል ... ወደ እኛ እንዳይደርሱ እንቅፋት እንፈጥራለን። ዝምታ ይህንን ጊዜያዊ ግርግር በማቆም አስፈላጊ የሆኑትና የዘገዩብን ነገሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ህይወታችን እንዲመጡ በር ይከፍታል። በዝምታ ውስጥ ስንሆን አስፈላጊው ነገር ወደ እኛ ለመምጣት መንገድ ያገኛል ምክንያቱም እኛ የምናስቀድመው ድምፅ በሌለበት የህይወት ጥሪ በቀጥታ ልባችን ላይ ይደርሳልና በዝምታ ውስጥ ስትሆን ማንም አይፈርድብህም ምንም ነገር አትጠብቅም ለማንም ነገር ማብራሪያ አትሰጥም። ይህ ሙሉ ነጻነት ነው። በዚህ የነጻነት ሁኔታ ውስጥ ነው እንግዲህ እውነተኛው ማንነትህ ከፈጣሪህ ጋር የሚገናኘው። https://t.me/Oct13wed

ሰዎችን መቅረብ ብዙም ደስ አይለኝም። ምክንያቱም ሰው በቀረብከው እና ባወቀህ ልክ ይንቅሃል። ለዚህም ብዙ አጋጣሚዎች አሉኝ። That's why አሁን እዚህ ቴሌግራም ላይ ብዙ ሰዎች ጋ ከተራ የላይክ ወይም የኮሜንት ኢንጌጅመንት ውጭ በኢንቦክስ ማላወራው። ብዙ ሰው “በጣም ኩራተኛ ነህ!”፤ “ለምን አትደውልም?” ምናምን ይለኛል። ግን ከመቀራረብ በኋላ የሚመጣው disrespect እና መናናቅ ስለሚደብረኝ ነው። ከሩቅ ትወዱት የነበረን ሰው ስትቀርቡት መጥላት ተፈጥሯዊ ቢሆንም ባለበት Status እና በሌሎች ነገሮች መናቅ፣ ማዋረድና ክብርን መንፈግ ግን ድንቁርና ነው። be kind, be positive and be supportive.🙌 Show አታድርጉ። እንቁልልጭ ለማለት አትኑሩ። ሁሉንም ሰው እንደምትበልጡና ሁሌም ተጎሳቁሎ እንደሚኖር አታስቡ። ትንሽ ብትሆን እውቀት አለን[በተማርነው] ተስፋ አለን[በእግዚአብሔር] ገንዘብ ሳይዝ የሞተ የለም!! ሁሉም ሰው ያለፈበት የራሱ ቀራኒዮ አለው። ቁምነገሩ የነበሩበትን ማስታወስ ነው። በተረፈ በጊዜያችን እናንፀባርቃለን!!✌️ እኛ ግን እንላለን፤🗣ህይወት [ይቀጥላል]!!

ባልደራሱ.... ....ማንነበር ባለ ቁጥር ካሁን ካሁን ስሙን ጠራው እያልኩ ስሳቀቅ ለማስቀየስ እከሌ እላለሁ... ''ደህና ነው እሱ? እንዴት ነው?...'' እያለ ስለሱ ትንሽ እናወራና ሲጨርስ መልሶ ደግሞ... "እንትናስ በናትህ ስሙ ጠፋብኝ እኮ..'' ብሎ እንዳነሳለት ይጠብቃል። ...ስልኩን ገና ሳገኝ ምንም ምቾት ያልተሰማኝ ለዚህ እንደነበር የገባኝ ዘግይቶ ነው።  ስልኩ ሲላክልኝ ወዲያው ከመደወል ይልቅ  ለቦስ  ነበር የሰጠሁት። እሱ እንዲደውል... ቀድሞ ከደወለ እኔ አልጠየቅማ... አላረዳም። ለቦስ እንዲደውልለት ስልኩን ከላኩኝ በኋላም አላረፍኩም። ማወቅ ፈልጌ ከስር ከስር እጎተጉታለው እእ ደወልክለት...? ምን አለህ በናትህ? ስራ ላይ ነው ወይንስ? '' አዎን ደውዬለታለሁ። ፈታ ያለ ልጅ ሆኖ የለ እንዴ? ያስቅሀል ደውልለት... እንዴት ግን ሳትደዋወሉ እስካሁን?" ይጠይቃል። ስልኩን የላኩለት እኔው ሆኜ እንዴት እስካሁን እንዳልደወልኩለት በገረመው ድምጸት። ''...እንጃ ብቻ ዛሬ ነገ እደውላለሁ እያልኩ ዘነጋሁት። ብቻ እደውላለሁ እስቲ....የኔን መርሳት ታውቀው የለ?..." አልኩት። ሁሌም ለምን እንዳልደወልኩ ስጠየቅ... መርሳትን እንደ አመክንዮ የማቀርበውን ለመጠቀም እየሞከርኩ። "ኧረ ደውልለት ደስ ይላል አነጋገሩ። በየመሀሉ ደሞ ''መልካም ነው'' የምትል መልካም አነጋገር ጣል ያደርግባታል። ብቻ ፈታ ነው ደውልለት..'' "እሺ እደውልልለትና እነግርሃለሁ...'' ብዬው አሁንም ሳልደውልለት ቀናት አለፉ... ከተደዋወልን ድፍን ስምንት አመት ሞልቶታል። ስልኩን ለማግኘትም በተቻለኝ አቅም ሁሉ ሞክሬ ማግኘት አልቻልኩም። እንደውም ከአራት አመት በፊት ፌስቡክ ላይ ስፈልገው ከሳምንት በፊት እንደወጣ ፌስቡኩ ሲነግረኝ ተመልሶ ሲገባ ስልኬን እንዲያገኘውና እንዲደውልልኝ በinbox አስቀምጬለት ነበር። ከዛን ቀን በኋላ ተመልሶ አልገባም እንጂ.... ፎቶውን አግኝቼ ታድያ በራሴው አካውንት ለጠፍኩት። በInboxም በcommentም ተጠየቅኩኝ። '' የት አግኝተኸው ነው?''  ይላል አብዛኛው ሰው። በሰአቱ ሆሳዕና ስለነበርኩ በአካል እንዳገኘሁት በማሰብ። አብዛኞቻችን የምንፈልገውን ነገር እንደሆነ አድርገን እንቀበለዋለን። እውነታው ግን ያ አይደለም። የምንፈልገው ቢሆን ኖሮማ ስንት ያልፈለግናቸው ነገሮችን ከመሆን በታደግናቸው..... ...ከስንት ክረምት መሄድ እና ከስንት በጋ መሰዋት በኋላ ስልኩ በቴሌክራም መልዕክት ድንገት ሲደርሰኝ ግን ምንም አላላልኩም። መደወል ብፈልግም ልደውል  አልቻልኩም። ከደወልኩለት ስለ ማነግሮት ማንሳቱ እንደማይቀር አውቃለሁ። ምን ልለው ነው ታድያ...?  ወንድሜ ሞቷል?... እንዴት ነው ለወንድም ወንድሜ ሞቷል ተብሎ የሚነገረው?... የለም የለም አልደውልም። ግን ደግሞ እሱን ለማግኘት እኮ በጣም ስጥር ነበር። ስምንት አመት አልፏል ድምጹን ከሰማሁት... አሁንም ያ የድሮውን ድምጽ መስማት እችላለሁ። ስልኩን መጫን ብቻ ነው የሚጠበቅብኝ... እንዲህ እየተወዛገብኩ ቆይቼ ነበር ልደውልለት የቆረጥኩት... እስካሁንማ ቦስም ደውሎለታል... ሌሎችም ደግሞ ደውለውለት ስለሚሆን እነሱ ይነግሩታል ስለዚህ እኔ አላነሳውም ያንን ጉዳይ። ብዬ እንደሰማ እርግጠኝነት እየተሰማኝ ደወልኩለት። ሁለቴ ጠርቶ በሶስተኛው አነሳው። ''... ጠንጠኖ እንዴት ነህ?... ''  አልኩኝ ልክ ምሳ አብሮ በልቶ ለራት ግብዣ እንደሚደዋወል... (ጠንጠኖ ነበር የምንለው ድሮ.. ምን ማለት እንደሆነ ግን አላውቅም) ''ሀሎ..'' አለ የማያውቀው ስልክ ስለሆነ ረጋ ብሎ... ድምጹ ፍጹም ተቀይሯል። ለካ አንተዋወቅም። ቀስ አልኩኝ እኔም... ከስምንት አመት በኋላም ቢሆን እንደ አዲስ ነው የምንተዋወቀው ለካ። የኋላ ታሪካችን እንደ እንደ አንድ ዛፍ ስር አንድ ቢሆንም ለካ የተለያዩ ቅርንጫፎች ነን። ትዝታ ነው ግንዳችን። አንድ የሚያደርገን። እንጂማ... እኔ ያለሁ በሌላ ጫፍ እሱ ደግሞ ሌላኛው.... ''እስራኤል ነኝ...'' ብዬ ረጋ ባለ አወራር ማውራት ጀመርን ብዙ ትዝታዎችን አነሳን... ብዙ ብዙ አወጋን። በየመሀሉ እነ እገሌ እያልን እያነሳን እናወራለን። ማንነበር ባለ ቁጥር ካሁን ካሁን ስሙን ጠራው እያልኩ ስሳቀቅ ለማስቀየስ እከሌ እላለሁ... ''ደህና ነው እሱ? እንዴት ነው?...'' እያለ ስለሱ ትንሽ እናወራና ሲጨርስ መልሶ ደግሞ... "እንትናስ በናትህ ስሙ ጠፋብኝ እኮ..'' ብሎ እንዳነሳለት ይጠብቃል። ማንነግሮትን ሊል እንደፈለገ ቢገባኝም ሌላ ሰው አነሳለትና ስለሌላ ሰው እያወራን እንቆያለን። እንዲህ እንዲህ እያልን ስለማነግሮት ሳናነሳ ካርዴ አለቀ.... ስልኩን ደረቴ ላይ አድርጌ.... '' ይህ ጭንቀት እንዴት ይሆን የሚገለጸው? ሰው እንዴት ብል ነው የሚረዳኝ?.... ግዴታ ማስረዳት አለብኝ እንዴ?!. ሆ!.."  ብዬ ቀና ስል ''..ምነው?..." አለኝ ጓደኛዬ... ዘፈን ከፍቶ ቁጭ ብሎ ነበር። ''...የከፈትከው ዘፈን..'' ብዬው ወጣሁ... ቴዲ አፍሮ ግን እንዴት ቻለበት?... እየወጣሁም ዜማው ይከተለኛል። ባ..ልደራ...ሱ....... አልተገ..ራም...ወይ ፈረ..ሱ.... ምን ብዬ ልንገራት ምን ብዬ ልንገራት ምን ብዬ...  ምን ብዬ.... ምን  ብዬዬዬዬዬዬዬዬዬ..... https://t.me/Oct13wed

ዶክተር ምትኩ ....ከሰዓት በኋላ ያለው የክፍል ድባብ በፀጥታ ተሞልቷል። የተማሪዎቹ ትኩረት ሁሉ በክፍሉ መሃል ወደሚገኙት ሰው ላይ አርፏል። ዶክተር ምትኩ—በዘመናት የማስተማር ልምድ የለሰለሰና ጥልቅ መረጋጋት የሚሰማበት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፣ የነጭ ጠመኔውን አቧራ ከእጃቸው ላይ እያረገፉ ወደ ተማሪዎቻቸው ዞሩ። መነፅራቸውን በጣታቸው ቀና አደረጉና ሁላችንንም በተራ በዓይናቸው ቃኙን። ያች የሁልጊዜዋ፣ የዕውቀት መጋረጃ የምትከፍት ፈገግታቸው ፊታቸው ላይ በራች። "ስማችሁኛል አይደል?" አሉ። ድምፃቸው የክፍሉን ፀጥታ ሰብሮ ወደ ውስጥ ሲዘልቅ። "ብዙ ጊዜ እኛ ትልልቅ ሰዎች፣ መምህራንና ወላጆች ህፃናትን እንደ ሸክላ ጭቃ እንጭናቸዋለን። እንደፈለግን አድርገን ልንቀርፃቸው እንሞክራለን። ግን ትልቁ ስህተታችን የሚጀምረው እዚህ ጋ ነው።" ጠመኔውን በእርጋታ ጠረጴዛው ላይ አስቀመጡና እጆቻቸውን አጣመሩ። የንግግራቸው ክብደት ክፍሉን አየር በአንዴ ቀየረው። "ህፃን ልጅ ማለት ገና ያልተጻፈበት ነጭ ወረቀት  ነው የሚሉትን የድሮ ሰዎች ታውቋቸዋላችሁ። እኔ ግን ዛሬ የምላችሁ ሌላ ነው። ህፃናት እንዲሁ ባዶ ነጭ ወረቀት ብቻ አይደሉም፤ እነሱ ገና ከጅምሩ የራሳቸው የተፈጥሮ ቀለምና ስውር ስዕል ይዘው የመጡ ድንቅ መጽሐፍት ናቸው! የእኛ ስራ በእነሱ ላይ የፈለግነውን የራሳችንን ታሪክ መፃፍ ሳይሆን፣ በውስጣቸው ተደብቆ ያለውን ያንን መልካም ማንነት ፈልፍሎ ማውጣትና ማለምለም ብቻ ነው።" ዶክተር ምትኩ በጥያቄ አስተያየት ወደ እኔ ጠጋ አሉ። "ለመሆኑ... አንድ ህፃን ልጅ ወለል ላይ ተቀምጦ ሲጫወት ምን ይታይሃል?" እኔም ደንገጥ ብዬ ፣ "ጨዋታና... መረበሽ?" ሲል መለስኩኝ። ዶክተር ምትኩ እራሳቸውን እየነቀነቁ ሳቁ። በክፍሉ ውስጥ የነበረው ውጥረት በሳቃቸው ቀነሱት ። "አይደለም! ጨዋታ ለህፃን ልጅ ተራ መረበሽ ሳይሆን ትልቁ ሳይንሳዊ ላቦራቶሪው ነው። አሻንጉሊት ሲሰብር ጥፊና ጩኸት ሳይሆን የሚያስፈልገው፣ 'ለመሆኑ ይህ ነገር ለምን ተሰበረ? ውስጥስ ምን አለው?' ብሎ ለመመርመር ያለውን የሳይንቲስትነት ስሜት ማድነቅ ነው።" ወደ ጥቁር ሰሌዳው ተመልሰው ዞሩና በትልቁ አንድ ቃል  ጻፉ። "አንድ ህፃን በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት የሚያገኘው ፍቅር፣ ትኩረትና ደህንነት፣ ለዘላለም የሚኖርበትን የስነ-ልቦና ህንፃ መሰረት ይጥላል። መሰረቱ ካልጠነከረ፣ ወደፊት የምንገነባው ፎቅ ምንም ያህል ቢዋብና ቢረዝም... መውደቁ መቼም ቢሆን አይቀሬ ነው።" በመጨረሻም ዶክተር ምትኩ መነፅራቸውን አውርደው ጠረጴዛው ላይ አስቀመጡት። ንግግራቸውን ሁላችንም ልብ ውስጥ በሚቀርጽ ከባድ መደምደሚያ እንዲህ ሲሉ ቋጩት፡ "ስለዚህ፣ ነገ ወላጅ ወይም በዚህ ሙያ ላይ የምትሰማሩ ባለሙያ ስትሆኑ ህፃናትን ዝም ብላችሁ አትገስጿቸው፤ በደንብ ስሟቸው። እነሱ የሚናገሩት በቃላት ብቻ አይደለም። በለቅሶአቸው፣ በሳቃቸው... እንዲያውም አንዳንዴ በዝምታቸው ጭምር ትልቅ መልእክት ያስተላልፋሉ። የልጅነት ስነ-ልቦናን ማወቅ ማለት፣ የሰውን ልጅ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በበጎ መንገድ መቅረፅ ማለት ነው። እኔም ታዳያ የሳችውን ንግግር ና ትምህርት ከማርና ከወተት በላይ አጣጥሜው ክረምቱን ............ይቀጥላል Andualem (yosab) https://t.me/andupsychology

ሙሉ ደቂቃ ቁጭ ብዬ ኳስ ያየሁበትን ቀን እምብዛም አላስታውስም። ነገር ግን በተለይ ሃይስኩል እያለሁ በአጋጣሚ ሳልፍ አልያም ደግሞ መሄጃ ከሌለኝ ሻይ እየጠጣሁ ሀይላይት አይ እንደነበር ግን በደምብ ትዝ ይለኛል። ልጅ እያለሁ በራሱ ታላላቆቼ ብስራት ኤፍ ኤም ከፍተው ሲሰሙ ግን እማልክደው የልጅነት ሀቅ ነው። መሰለ መንግስቱ ያወጣው ዘፈን ዛሬም ጆሮዬ ላይ አለ። ''እግርኳስን በሬድዮ ተመልከቱ። መሰ...............ለ መንግስቱ!..'' የሚል ድምጽ.... በዚህ መሃል ግን አርሰናል ከሌሎች ክለቦች በተሻለ ለእኔ ጎልቶ እንዲታይ የሆነበትን ምክንያት ግን እነሆ.... ልጅ እያለሁ ከማልረሳቸው ኵነቶች አንዱ በታላላቅ ወንድሞቼ የሚደረገው የአርሰናል እና ማንችስተር ጨዋታ ነው። ምን DSTV ገብቼ የእውነተኛውን አርሰናል እና ማንችስተር ጨዋታ ባላይም፣ እውነተኞቹን ተጫዋቾች በመልክ ባላውቃቸውም (በስም ሲጠሩ ስለምሰማ) አርሰናል ልቤ እንዲገባ ግን የግድ DSTV መግባት አልተጠበቀብኝም ነበር። ...ሁሌም ቅዳሜ ቅዳሜ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ውስጥ ጨዋታ አይጠፋም ነበር። ብዙውን ሳምንት ጨዋታው የሚደረገው በአርሰናል እና በማንችስተር ሲሆን (አንዳንዴ ቆላ እና ደጋ፣ ድፍን ምስር ክፍት ምስር....እየተባለ ቢከፈልም አብዛኛው እና ምቹው ግን የአርሰናልና ማንችስተር ክፍፍል ነበር) ... አሸናፊው ቡድን ታድያ ሳምንቱ የሱ ነው። ቀጣይ ሳምንት መጥቶ ተሸናፊው ቡድን መልሶ አሸንፎ ድሉን እስካላስመለሰ ድረስ ሳምንቷን ተሸማቆ ነው የሚጨርሰው። ሁሌም የምበሳጭበት ግን አንድ ነገር ነበር። ትንሹ ስለነበርኩ ለትዕዛዝ ተመችቼ ይሁን አልያም ፊትለፊት ተገኝቼ ባላውቅም ተጫዋቾቹ በሙሉ በተራ ተራ ውሀ እንዳመጣላቸው የሚልኩኝ ነገር... ...እንዳያመልጠኝ እልና እየፈጠንኩ ሄጄ በያዝኳት ማንቆርቆርያ የምትመስል የፕላስቲክ ጆግ (ትልቱ እኔን ይበልጣል😀) ውሀዬን ይዤ ልክ ሜዳ ስደርስ የላከኝ ልጅ ኳሷን ይዟል እየተጫወተ... ሌሎች ተጫዋቾች ይቀሙኝና ይጠጡታል... አልከለክል መቼስ ኩርኩሙስ🤛 የላከኝ ልጅ ሲመጣ ውሀው አልቋል። '' ለምን አባክ ሰጠሀቸው?...'' ይለኝና መልሶ ይልከኛል... ...እንዲህ ውሀ እያመላለስኩ የጓጓሁለትን ኳስ ሳላየው ያልቃል.. ሳምንቱን ደግሞ እቅድ አወጣለሁ። "...ሜዳው አጠገብ ያለው ትልቁ ዛፍ ጫፍ ላይ እወጣለሁ መቼስ ከዛ አያስወርዱኝም እንደውም በደምብ ይታየኛል ወደታች..'' ብዬ አቅድና ልክ ሳምንቱ ሲመጣ እወጣለሁ ዛፍ ላይ። ልክ ኳሱ ተጀምሮ ትንሽ እንዳየሁ አንዱ ተጫዋች ይጣራል "...እስራኤል አይቼሀለሁ ና ውረድ...'' እየተነጫነጭኩ እወርዳለሁ። ''..ኤጭ ምንድነው? ሌሎቹ ልጆች አያመጡም እንዴ? ወይስ እኔ ማመጣው ውሀ ይጣፍጣቸዋል?...'' ንጭንጭ እያልኩ ወደ ስራ.. ሙሉ ኳስ የማየው ከስንት አንዴ ነው እንደ እድል። ሰአት ያዝ ከተባልኩ...   ጥቁሯን እጅ ላይ የምትታሰረዋን ሰአይ ይሰጡኝና ኳስ ሲወጣ ሰአት እያቆምኩ...(ከሜዳው ጀርባ ያሽቆለቆለ ስለሆነ ኳሷ ሩቅ ሄዳ እስክትመጣ ይቆያል)  ኳሷ ስትመለስ ደግሞ እንዳስቀጥል። እሱም ደግሞ ኳሱን ሙሉ ደቂቃ እንዳይ ጥሩ እድል ቢሆንም ግንሌላ ጣጣ አለው። እየመራ ያለ ቡድን ሁሌም ማሸነፍ ይፈልጋል ስለዚህ ደቂቃው አላልቅ ሲለው እኔ ላይ ሲጮህ... እየተመራ ያለ ቡድን ደግሞ ኳሷ የእጅ እንኳን ስትሆን እንዳቆምለት ይጨቃጨቃል። ሌላው ጣጣ ደግሞ ድንገት እመሰጥና ኳሱ ሲወጣ ያቆምኩት ደቂቃ ኳሷ ስትመለስ አላስጀምረውም። ልክ ሁለተኛ ፎሪ ሲወጣ ሰአቱን ለማቆም ሳየው ለካ ቅድም እንዳቆምኩት ነው.... ...ያዩብኝ ይመስል ድንግጥ እልና ኳሱ ውጪ እንዳለ ማስቆጠር እጀምራለሁ... አንዳንዴ ደግሞ አጫውት የተባልኩት ደቂቃ ሳላውቀው አልቆ ሌላ አጫውት የተባልኩትን ግማሽ የሚያህል ደቂቃ... ሰአት መያዜን ሳላውቀው ረስቼ እያጫወትኩ በመሀል አንዱ የደከመው ''  ኧረ ዳኛ ምንድነው ሰአት..'' ሲል ድንግጥ እልና ''የባከነ አምስት ደቂቃ ጨምሬአለሁ..'' ብዬ እጮሀለሁ። ሰአት መያዙ ግን ለኔ አሪፍ መበቀያ መንገድ ሆኖልኝ ነበር። ሁሌ ውሀ አምጣ ብሎ የሚልከኝ የአርሰናል ተጫዋች ይሆንና ውሀውን ሳመጣው በግድ የሚወስድብኝ ካልሰጠሁትም የሚኮረኩሙኝ የማንችስተር ተጫዋች ነበር። (አጋጣሚ ይሁን ታስቦበት ግን አላውቅም) ...ውሀ እንዳመጣ የላከኝ ቢያናድደኝም ያመጣሁትን ውሀ ሳይልከኝ ኮርኩሞ ከወሰደ በኋላ መልሶ እንዳመጣ የሚያደርገኝ የማንችስተር ተጫዋችን መበቀያዬ ታድያ ሰአት ነው። ሌላው የማንችስተር ተጫዋቾች የሚያናድዱኝ ጉልበት ይጠቀማሉ። ኳስ ካለፈ እግር አይለፍ አይነት ነገር። ... ሁለቱም ቡድን ላይ የተሻለ ብቃት ያላቸው ልጆች ቢኖሩም አርሰናል ላይ ያሉት በብቃት በልጠው ጉልበት እንደሌላቸው (ከማንችስተር የበለጠ) ሳይ ለአርሰናል እንዳደላ የሚያደርገኝ  ምክንያት ነበር። ... አርሰናል ሲመራ ኳሷ ብትወጣ እንኳን ሰአቱ አይቆምም። ማንችስተር ሲመራ ግን የግድ አርሰናል እስኪያገባ እጠብቃለሁ። ማግባት ካቃታቸውና ተስፋ ካልቆረጡ በቀር ያልታወቀ ጭማሪ ግድ ነው። ...በዚህ መልኩ የእንግሊዙን አርሰናል ሳላይ የኛው አርሰናል ግን በትንሹ ልቤ ገብቶ ነበር። አድጌ ታድያ "ማናቸው እንዲህ በልጅነት ያስጨነቁኝ ክለቦች?" ብዬ ሳያቸው ምንም ለውጥ አላየሁባቸውም። ልክ በስልካችን ላይ ከምናስጭናቸው አኒሜሽን ጌሞች ሊለዩልኝ አልቻሉም። ውሃ አልቀዳላቸው፣ሰአት አልይዝላቸው...ወይ ኳስ አላቀብላቸው ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ዝም ብሎ ማየት... ኳስ ገብተው ባይጫወቱም የጫወታው አንዱ አካል መሆን ግን ደስ የሚል ጣዕም ያለው ይመስለኛል። እንግሊዝ ተኪዶ አንድ አካል አይኮን ነገር... ብቻ እንደኔዎቹ ማንችስተርና አርሰናሎች አልጥም አለኝ ጨዋታቸው። ከዛን ጊዜ በኋላ አርሰናል እና ማንችስተር ሲባል የልጅነቴ ይናፍቀኛል። አላገኘው መቼስ። አርሰናል ከ22 አመት በኋላ ዋንጫ በላ ሲሉኝ ታድያ ደስ አለኝ። ልክ በልጅነቴ ውሀ ያመጣሁላቸው እና  ሰአት የጨመርኩላቸው አርሰናሎች እኔ በሌለሁበት ዋንጫ የበሉ አይነት ነገር ነው ደስታው። አሸናፊነት የትናንት የጽናት ውጤት ነው። በውጣ ውረድ፣ በሽንፈትና በድል ውስጥ አብሮ የቆየ ሰው ውጤት።  አርሰናል ሻምፒዮን ሲሆን፣ እኔም ሻምፒዮን ነኝ። ይህ ዋንጫ የክለቡ ብቻ ሳይሆን፣ እኔን ጨምሮ በክለቡ ላይ እምነት ላሳዩ ደጋፊዎች ሁሉ የተበረከተ በልጅነት ያመላለስኩት ውሀ ውጤት ነው። ዛሬ የምደሰተው በዋንጫው ብቻ አይደለም፤ የልጅነቴ አርሰናል ደጋፊዎች እንደዛ ሲጫወቱ እና ሲለፉ አርሰናል ያልሰጣቸውን ዋንጫ ዛሬ እንደሰጣቸው ሳስብ ነው የምደሰት። ይህ ደስታ የዘመናት ጥያቄያቸው መልስ ነው። አርቴታ አርሰናል ሲጫወት ያላገኘውን ዋንጫ እልህ ይዞት አሰልጣኝ ሆኖ ተመልሶም ዋንጫውን ለማሳካት 7 አመት ፈጅቶበታል። ልቤን የነካው ደግሞ እንዲያ እየለፋ የሊቨርፑል ይሁን የሲቲ ደጋፊዎች ሚዜ አድርገው የሰሩበት ምስልን ሲያሳዩኝ ነበር ዘንድሮ ሙሽራ ሆኖ ስላሳያቸው ደስ ብሎኛል። ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ቃል አትናገር ማለት ይሄኔ ነው። ለማንኛውም የልጅነቴ አርሰናሎች እነ ራያችን እንኳን ደስ አላችሁ! ዛሬም የእናንተ ደጋፊ ነኝ!🏆🏆🏆🏆 አብረን ሆነን ባነብላችሁ ደስ ይለኝ ነበር ግን አብረን ስላልሆንን እናንተው አንብቡት። የእናንተው አርሰናለር እስራኤል ሰይፉ (ቦዔዝ) https://t.me/Oct13wed

photo content
+2

Repost from N/a
📢 OFFICIAL ANNOUNCEMENT The Ethiopian Psychology Students Association (EPSA) proudly announces that Emphatic Bloom Psycholog
📢 OFFICIAL ANNOUNCEMENT The Ethiopian Psychology Students Association (EPSA) proudly announces that Emphatic Bloom Psychology Club from Dilla University is officially the SECOND university psychology club to partner with EPSA. 🎉🤝 Through this partnership, Emphatic Bloom members will gain access to special trainings, professional opportunities, national collaborations, and EPSA student support programs. In addition, Emphatic Bloom activities, events, and announcements will now be officially featured on the EPSA Website, News & Events section, Student Portal, and EPSA communication channels.

ዘጠኛ ክፍል አብሯችሁ የተማረና ትምህርቱን ከዘጠኝ ያቋረጠ ሰው ሁልጊዜ እናንተም ዘጠነኛ ክፍል ነው የምትመስሉት። አንተ ስትቆም ዓለም አልቆመም ብትሉት አይሰማችሁም። ​ብዙ ሰዎች ትዝታቸውን እንደ ፎቶግራፍ ነው የሚያዩት። ላእናንተ ያላቸው ግንዛቤ ዘጠነኛ ክፍል ላይ "ክሪስታላይዝ" ሆኖ ቀርቷል። ያ ምስል አሮጌና ያለፈበት የታሪክ ማህደር ሲሆን፣ ለእነሱ ግን አሁንም ትኩስና ብቸኛው መረጃቸው ነው። ያንተን እድገት ለውጥ መቀበል ማለት ለእነሱ የራሳቸውን የጊዜ ጉዞ እና "ባለህበት ሂድ" እውነት መጋፈጥ ስለሚሆንባቸው፣ ይተናነቃቸዋል። በለመዱት የድሮ ማንነትህ መቆየትን ይመርጣሉ። "በቃ ዘጠነኛ ክፍል ነን" ይሉሃል "ነን" ። ይሄ ነገር ደብሯችሁ ራቅ ስትሉ ኮራች ፣ ኮራ አናውቀውም እንዴ? Time Crystallization ይሉታል። (አሌክስ አብርሃም)

በአንድ ዝናብ ሁለት ጠብታ.... ✍️እስራኤል ሰይፉ (ቦዔዝ) ...የዛሬው ደግሞ ይለያል። ጥላ ሲያረጅ እንዲህ ነው እንዴ? ኧረ ያረጀ ጥላ ያለው ፈልጉልኝ። ምን አይነት ስሜት እየተሰማኝ እንደሆነ አላውቅም። ብቻ ቀና እያልኩ ይህን ስሜት እንድጋራው ያደረገችኝን ልጅ ማመስገኔን ግን አላቆምም። ....ከሆነ ጊዜ ጀምሮ ሁሌም ዝናብ ሲዘንብ ወጥቼ እቆማለሁ። ጥላ ይዤ ነው ግን። ለምን አትሉኝም? እንጃ ብቻ ከሷ ስላየሁት? አላውቅም.... እንዲህ ነበር አጀማመሬ.... ... ልክ ዝናብ ሲዘንብ መኝታ ክፍሌ መስኮቱን ገርበብ አድርጌ ከፍቼ ሁሌም ጥላ ይዛ በዝናብ የምትቆመዋን ቆንጅዬ ጎረቤታችንን ነው ማየው። ምን አልባት ስለምጠብቃትም ሊሆን ይችላል ብቻ ግን አላውቅም። ሰማዩ ዳምኖ ሲያጉረመርም ሳሎን ከቤተሰቦቼ ጋር በምንም ጉዳይ እያወራን ቢሆን እንኳ ቶሎ ወደ መኝታ ክፍሌ ነኝ። የሚጠብቀኝ ውበት ስላለ። ወላጆቼም ታድያ ይህን ጸባዬን ለምደውታል... ለምን እንድሆነ ባያውቁም። ....ልክ መኝታ ቤቴ እንደገባሁ ዝናቡ በደምብ እስኪዘንብ እቁነጠነጣለሁ። እንደውም አንዳንዴ አጉረምርሞ ሳይዘንብ ሲመለስ ብስጭት ነው የምለው። ምን አለ ባያጓጓኝ። ልክ ሳምንት ተርቦ ለቆየ ሰው ምግብ ከቀረበለት በኋላ በስህተት እንደቀረበለትና የሱ እንዳልሆነ ሲነገረው የሚሰማው አይነት ነበር ስሜቱ። ....ሊዘንብ ሲጀምር ታድያ እያንዳንዱን ጠብታ አንድ በአንድ ነው የምቆጥረው። ጣርያው ቅርብ ስለሆነ መሰል ቆርቆሮው ላይ የሚወርዱትን እያንዳንዳቸውን ጠብታዎች እንድቆጥር ምቹ ሆኖልኛል። አብዝሀኛውን ጊዜ ከ ሀያ ጠብታ አያልፍም በደምብ እስኪዘንብ። መዝነብ ከጀመረ በኋላ የሚንጠባጠበው ደግሞ አንድ ነው። አንድ። ታድያ ልክ በደንብ መዝነብ ሲጀምር እንደለመደችው ጥላዋን ይዛ በመስኮቴ በኩል ትይዩ በሆነው መንገድ ዳር ጠብ ትላለች። ያኔ ለኔ የዝናቡ ጠብታ አንድ ይሆናል። እስካሁን ጠብ ያለውን ሀያ ጠብታ ብቻውን የሚያስንቅ አንድ ጠብታ። ጎዳናው ጭርርርር ያለ ነው። ማንም አያልፍበት.... አልፎ አልፎ ከሚሰሙ የተሽከርካሪ ድምጾች በስተቀር። ዳሯን ይዛ ቆማ ከሩቅ ስትታይ ከዝናቡ እና ከጥላዋ ጋር ተደምሮ አንዳች ስሜት ይፈጥራል። የዝናቡ ጠብታ ከላይ ጥላዋ ላይ እያረፈ ሲፈናጠር ጉም ይመስል ጭጋግ ይፈጥራል። ያልተፈናጠረው ጠብታ ደግሞ እንባ ይመስል ቁልቁል በጥላዋ ይወርዳል። አይኗን ጨፍና ቆማ ሁሌም ሳያት አስባለሁ። ለምን ይሆን በዝናብ የምትቆም? ያውም ጥላ ይዛ... በዝናብ የሄደ ጓደኛ አላት እንዴ? በዝናብ ሚመለስ? ወይንስ ፈልጋው ነው?... አንድ ቀን ታድያ ብጠብቅ ብጠብቅ የለችም። ዝናቡም ሀያዎቹን አልፎ ወደ ዶፉ ገብቷል። ግራ ገባኝ። የት ሄዳ ይሆን ያልለመደባትን? አስሬ እቁነጠነጣለሁ። መብረቁ ደግሞ ያለወትሮው እየደጋገመ ይወርዳል። ዛሬ ተሰምቶኝ ይሁን አልያም ለመቅረቷ መርዶ ነጋሪ ሆኖ ተከስቶ አላውቅም። መኝታ ቤቴ ውስጥ ብቻዬን ማውራት ጀመርኩ። አንዴ መነሳት... አንዴ መቀመጥ... አንዴ መስኮቱን መክፈት... ራሴንም በየመሀሉ እጠይቃለው። ''...ቆይ ምን አገባኝ? አታውቀኝ አላውቃት። ለምን በዛው አትቀርም። ለምን በዝናብ ትቆማለች እያልኩ አልነበር? ይሄው ቀረች። በቃ!...'' ''የለም የለም! ምንም ሳትሆን በሰላም እንኳ አትቀርም። ደህንነቷን ደግሞ ማረጋገጥ አልችል ነገር... ቤታቸው ማንም ሲገባም ሆነ ሲወጣ አይቼ አላውቅም። ምን ላድርግ...'' ''...ቆይ ግን ወደድኳት እንዴ? መላመድ መዋደድን ያመጣል እንዲሉት ሆኖ ይሆን እንዴ? አይ እንደዛ ደግሞ አይደለም እሷ መች ታውቀኝና ነው ምንላመደው....'' እንዲህ እየተወዛገብኩ ዘወር ስል ድሮ እህቴ ትጠቀምበት የነበረው አሮጌ ጥላ አልጋ ስር ወድቆ ጫፉ ታየኝ። ምንም ሳላመነታ ብድግ አድርጌው ወደ ውጪ ወጥቼ አበራሁት። ... ልክ እሷ ትቆምበት የነበረው ቦታ ላይ ስደርስ ግራ ፊቴን ወደእኛ ቤት አዙሬ ልክ እሷ ትቆም እንደነበረው ቆምኩኝ። የመኝታ ቤቴ መስኮት ትቼው እንደመጣሁት ገርበብ እንዳለ ነው። ዝናብ በመስኮት እንደሚገባ የገባኝ ዝናብ ላይ ቆሜ ሳየው ነው። ብዙ ጊዜ መኝታ ቤቴ ውስጥ ውሀ የተደፋ እየመሰለኝ ብወለውልም አንድም ቀን ግን በመስኮት የሚገባው ወጨፍ እንደሆነ ግን ልብ ብዬው አላውቅም። ትኩረቴ አልነበረማ.... ...ዝናቡ ላይ ጥላ ይዤ ቆሜ አይኔን ጨፈንኩት። ምን አይነት ስሜት እየተሰማኝ እንደሆነ አላውቅም። ብቻ እንደጨፈንኩ ቀና እያልኩ ይህን ስሜት እንድጋራው ያደረገችኝን ልጅ ማመስገኔን ግን አላቆምም። ዝናቡ ጥላዬ ላይ ሲያርፍ የሚሰማኝ.... ሿሿሿሿሿሿ...የሚል ድምጽ... (ጥላ ሲያረጅ እንዲህ ነው እንዴ? ኧረ ያረጀ ጥላ ያለው ፈልጉልኝ) መብረቅ ብልጭ እያለ የሚያሰማው የጎረምሳ ሰማይ ድምጽ.... ቀዝቀዝ ያለ ነፋስ የለበስኩትን ሸሚዝ እያውለበለበ ራሴኑ ሲመታኝ የፈጠረው ድምጽ... እያንዳንዱ ቅጽበት የሚፈጥረው ደስታ ሊሰማ እንጂ ሊገለጽ አላለውም። ... አይኔን ስገልጥ እንዴት ልመን?!... ልጅቷ ጥላ ሳትይዝ ፈገግ ብላ ፊቴ ቆማለች። የተሰማት ደስታ ፊቷ ላይ ይነበባል። እናቱን ያየ ህጻን ልጅ አይነት ፊት... ''ምን ሆነሻል..?'' ብዬ ብደነግጥም አስጠለልኳት። ባዶ እግሯን ነች... ትንፋሿ ልክ ሲጋራ እንደሚያጨስ አይነት ሰው ቡንንን ይላል... ሰውነቷም ልክ ጸሀይ የመታው አስፓልት ላይ ሲዘንብ እንዲተነው ትናኝ ልብሷን አልፎ ይታያል። የዝናቡን እዥ ከፊቷ ላይ እየጠረገች ተጠለለችና ጥምጥም አለችብኝ። ... ምንም ሊገባኝ አልቻለም። በዝናብ ትጠብቀው የነበረው ሰው መስያት ይሆን እንዴ?... ግራ እንደገባኝ ዝም ብዬ አቀፍኳት እኔም። ይህ እድል አይገኝ መቼስ.. ተሳስታም ቢሆን እንኳን ተሳሳተች እስከዛሬ በመስኮት ከማይ ምንአለ ቀድሜ በመጣሁ.... ይላል ልቤ። ''...ስጠብቅህ ነበር.. ተስፋ ስቆርጥ መጣህ..'' አለች በተቆራረጠ ድምጽ። እያለቀሰች እንደነበር ገመትኩ። ዝናብ እየዘነበ ስለነበር እርግጠኛ ግን አልሆንኩም። በዝናብ የሚያለቅስ ሰው ግን እንዴት እድለኛ ነው... እየሳቀ ማልቀስ የታደለ። ቀጠለች ማውራቷን... ''... ሁሌ ጠዋት ከቤት ስትወጣ አይህ ነበር። እንዴት ላገኝህ እንደምችል ግን የሁሌም ጭንቀት ሆነብኝ። አማራጭ ሳወጣ ሳወርድ ታድያ አንድ ሀሳብ መጣልኝ። መዋደድ የመላመድ ውጤት አይደል? እኔ ሁሌ ጠዋት ጠዋት እንደማይህ ሁሉ አንተም በተመሳሳይ እኔን ልታየኝ የምትችልበትን መንገድ መፈለግ.... ከዛ በመስኮትህ ትይዩ በዝናብ ሰአት መቆም መልመጃ አንድ ይሁን ብዬ አሰብኩ። ታድያ ተደጋጋሚ ቀን ዝናብ ሲዘንብ ትዝ ትለኝና ጥላ ይዤ እወጣለሁ። ስወጣ በጣም ይዘንብ የነበረው ዝናብ ጥላ ይዤ አንተ መስኮት ፊትለፊት ስቆም ግን ያሁሉ የዝናብ ጠብታ ባንተ አንድ ጠብታ ይጠቃለልና አንተ ትሆናለህ ዝናቤ...'' ብላ ዝም አለች። ዝናቡ አሁንም ይዘንባል... መብረቁ ግን ከመርዶ ወደ ቡረቃ ተቀይሯል። ሿሿሿሿ የሚለው የጥላው ድምጽ ዝም ባይልም ለኛ ግን ሁለት ጠብታ ያህል ነበር። ... አንድ እኔ.... አንድ እሷ። https://t.me/Oct13wed

photo content

የሰሞኑ ጀምበር ደግሞ እንዴት ነው ግን? ልክ ድግስ ጠርቶ ሳይዘጋጁ ቀኑ እንደደረሰባቸው ሰዎች አይነት እኮ ነው አቸኳኮሏ.... ልክ ለሊቱን ምትሰራው ስራ ኖሮ ሳታስበው ነግቶባት ሰአቱን በጉጉት ትጠ
+1
የሰሞኑ ጀምበር ደግሞ እንዴት ነው ግን? ልክ ድግስ ጠርቶ ሳይዘጋጁ ቀኑ እንደደረሰባቸው ሰዎች አይነት እኮ ነው አቸኳኮሏ.... ልክ ለሊቱን ምትሰራው ስራ ኖሮ ሳታስበው ነግቶባት ሰአቱን በጉጉት ትጠብቅ የነበር አይነት ነገር..ሲመስለኝ ግን በቀን ውሎዋ ያየችውን የሰው ጥድፊያ ልትተገብር ልምምድም ጀምራለች። አይመስላችሁም?. ውበቷ ራሱ እንደበፊቱ አይደለም። የሰሞኑ ለሊት ለመኳኳል አልበቃ አላት እንዴ? ወይንስ ሌላ ስራ ጀመረች? ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ አይነት ፊት ነው የሚመስል ፊቷ.... ነው ወይንስ ለኔ ብቻ ነው?

ይታይሽ ሚራዡ ✍️እስራኤል ሰይፉ ፍቅርሽ ውስጤ እንዳለ ባልጠረጠርኩበት ጭራሹን ሳይገባኝ ማናት በምልበት ልክ እንደወላፈን ተሰማኝ ሙቀቱ ጊዜው ደርሶ መሰል ይኸው ነበር ወቅቱ በጠራራ ጸሀይ እንደሚንቀለቀል ሜዳ ታየብኝ ሚራዡ ወጥቶ ከልብ ጓዳ አልደብቀው ነገር ወጥቶብኛል አንዴ እዤም አልደረቀ በቦታው ባይሆንም አንዴ ሆኗል መቼስ እንግዲህ አለቀ ቃሉን ባላወጣም አሳብቋል ሚራዡ ሙቀት የፈጠረው መሰከረ እዡ ምን አለፋኝ ታድያ ለምን ቃላት ላክል እኔ እንደምወድሽ ምላሴ ሳይናገር ተግባራቱ ቀድሟል እናም ስሚው እዡን ይታይሽ ሚራዡ ዋናው ቃሉ ሳይሆን ተግባር ነው ፈራጁ። https://t.me/Oct13wed

"ወደ ገነት የገባው የመጀመሪያው ሰው ወንበዴ ነበር፤ ወደ ሲኦል የገባው የመጀመሪያ ሰው የጌታ ሐዋርያ ነበር!" ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።

የሚወዱትን እና የራስ የሆነን ነገር መግለጽ በጣም ይከብዳል። ነገር ግን ዝም ማለት ደግሞ ካለመውደድ እኩል ነው ሊያስብል ይችላልና የእናቶች ቀን እንደመሆኑ ስለ ትንሽ ማለት ግድ ይላል... ...እናት ማለት በምድር ላይ የፈጣሪ የቸርነቱ መገለጫና የፍቅር ትርጉም ሆና የተሰጠች የሕይወት መጀመሪያ ናት። ገና በጨለማው ማኅፀን ውስጥ ሳለን በደሟ ደም ሰጥታ በሥጋዋ ሥጋ አበጅታ የገዛ ትንፋሿን አካፍላ ለዚህ ብርሃን ዓለም ያበቃችን ድንቅ ፍጥረት ነች። እናትነት ሰፊ ባሕር ነው የማይጎድል የማይደርቅና የማይለወጥ... ... በዓለም ላይ ሁሉም ነገር ሲለወጥ ጓደኝነት ሲሻክር፣ የሰው ፍቅር እንደ ፀሐይ ጥላ ሲያጥርና ሲረዝም የእናት ፍቅር ግን ሁልጊዜ እንደ እኩለ ቀን ፀሐይ ደምቆ የሚኖር ነው። እናት ለልጇ ስትል ራሷን የምትረሳ፣ ለልጇ መኖር ስትል የራሷን ሕይወት የምትሰጥ፣ ለልጇ ስኬት ስትል ሺህ መከራዎችን በአኮቴት የምትቀበል ታላቅ መጽሐፍ ናት። የእናትነት ክብር የሚጀምረው ከእግር ጫማ ስር ነው እንዲሉ.... በዚያ በቆሸሸና በደከመ እግሯ ስር ግን ዓለምን የሚያክስ ገነት አለ። እርሷ ዝም ብትል መልኳ ይናገራል። በቤት ውስጥ የምታበራው ሻማ የእርሷ የድካም ውጤት ነው... በማዕድ ዙሪያ የምንሰበሰበው የእርሷ ፍቅር ማግኔት ሆኖ ስለሳበን ነው። እናት ማለት የሕመም ማስታገሻ፣ የጭንቀት ማራገፊያና የደስታ ምንጭ ነች። ... ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው ዛሬ ለደረሰበት ማንነት ጀርባውን አዝላ፣ እንባውን አብሳና ራሷን ገድላ ያሳደገች እናት አለችና። በዚህ ታላቅ ቀን እናቶችን ስናስብ በስጦታና በቃላት ብቻ ሳይሆን፣ እርሷ ላፈሰሰችው እንባ ሳቅ በመሆን፣ እርሷ ለደከመችው ድካም እረፍት በመሆንና እርሷ ላሳየችን ፍቅር መታዘዝን በመመለስ ነው። እናትነት በሰውኛ ቃላት ተተርጉሞ የሚያልቅ አይደለም የግድ ግን ይህንን ካልን ዘንዳ ማለፊያ ይሆነናል። የፈጣሪ ጥበቃና በረከት ከእናቶቻችን ጋር ይሁን፤ ክብርና ምስጋና ለእናትነት ይሁን😍😍😍🎂🎂🎂 (ስለ እናቴ መጻፍ ስላቃተኝ(ቀን ስለሌላት) ነው ስለ እናት የጻፍኩት)

photo content
+1

ወንድም ዳኒ እንኳን ተወለድክ።🎂🎂🎂🎂 በጣም ደስ የሚሉ ብዙ ትዝታዎች ነበሩን። ዳቦ ከመጋገር ጀምሮ ''ለወደፊት ስናድግ ምልክት ይሁነን'' ብለን መቅደስ ውስጥ ምልክት እስከማስቀመጥ ድረስ...
+1
ወንድም ዳኒ እንኳን ተወለድክ።🎂🎂🎂🎂 በጣም ደስ የሚሉ ብዙ ትዝታዎች ነበሩን። ዳቦ ከመጋገር ጀምሮ ''ለወደፊት ስናድግ ምልክት ይሁነን'' ብለን መቅደስ ውስጥ ምልክት እስከማስቀመጥ ድረስ.... ... ቀሪ ዘመንህን አምላክ ይባርክልህ። የትዝታችን ነገር በጣም ሰፊ ስለሆነ ቀጣይ በዝርዝር እመጣበታለሁ እስከዛው ግን በዚሁ ላብቃ። የምታገለግላት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቀሪ ዘመንህን ሁሉ አትለይህ። መልካም ልደት ወንድሜ❤❤❤

ይህ አባባሌ ዛሬም ይገርመኛል። ምንም ስራ እሰራለሁ እልና እንዴት ስባል እመቤቴ ትሞላዋለች ነው መልሴ። ያኔ ሸክሜን አቅልላልኝ የለ? በእንተ ልደታ የማይቀል ሸክም የለምና ዛሬም የከበደንን ሸክም እናታችን ታቅልልልን! ለእናቷ ቅድስት ሐና እና ለአባቷ ቅዱስ ኢያቄም በስለት የተገኘች እመቤታችን ለእኛም በስለታችን ትገኝልን! https://t.me/Oct13wed

በእንተ ልደታ ለማርያም ...በልጅነቴ ልደታ ለማርያምን በምሁር ኢየሱስ ሳከብር የነበረበት ትዝታ እንደ ጅረት ሁሌም ስዞር ከጀርባዬ አለ። ልክ እንደተንጣለለ ባህር ዝርግት ብሎ አሁን ላይ እዚህ ሆኜ ሳየው መግባት የማልችልበት ግን ደግሞ ዳር ላይ የቆምኩ አይነት ነገር... እንዲህ ይታየኛል... ... ግንቦት አንድ ማለት ለምሁር ኢየሱስ ልክ እንደ ድልድይ ነው። ኦሪትን ጨርሶ ወደ ሐዲስ መግቢያ የመጀመሪያው ጫፍ። የመጀመሪያው መጀመርያ እንዲሉ የሐዲስ መጀመርያ መጀመርያ ነው ልደታ ለምሁር። በዚህ ቀን ታድያ የገዳሙ ቤተሰብ ተሰብስቦ ለመጀመርያዋ ሐዲስ ደማቅ አቀባበል የሚያደርግበት ልዩ እና አስደሳች የቤተሰብ ምሽት የሚያደርግበት ቀን ነው። በዚህ ቀን የሚኖረው መርሀ ግብር ሁሌም ተናፋቂ ነው። ትምህርቱ (ማለዳ ማለዳ አዲስ የሆነው ትምህርት ዛሬም ይናፍቀኛል) ግጥም፣ ቅኔ፣ ጥያቄና መልስ ምግቡ... እያንዳንዱ መርሐ ግብር እጅግ አስደሳች አዝናኝ እና አስተማሪ ነው። ...ትንሽ ለትዝታ ወደ አንዱ አመት እንመለስ እስኪ.... ....በአንደኛው ቀን ልክ እንደወትሮው የሰርክ ጸሎት መሐረነ አብ (በዓለ 50 ስለሆነ መሐረነ አብ ባይኖርም ጸሎት ግን አለ) በሰአቱ ሳይሆን ቀደም ብሎ 10:30 ላይ ተደወለ። የልጅ ነገር መቼስ የጨዋታ ሰአት ሲቀነስ አይወድም ቅር እያለኝ የቤተክርስቲያን ቀሚሴን ለብሼ ወደ ጸሎት ተነሳሁ... ...ልክ ቤተክርስቲያን መግቢያው ላይ ስደርስ መናኝ ሀይለ ገብርኤል ጠርቶኝ ዘወር ስል ''...ስለትህን አስገባህ?'' አለኝ እንዳላስገባሁ ቢያውቅም ላለማስደንገጥ። ''ሀይሌ እኔ 1 ሸክም እንጨት ነበር የተሳልኩት። ግን ግራ ገባኝ አንድ ሸክም እንጨት ስንት ነው?" አልኩት እየፈራሁ። ትናንትና ትላልቅ ልጆች የስለታቸውን እንጨት ሲያስገቡ ያየሁት እንጨት በጣም ትልቅ ሆኖ ስለታየኝ ከአቅሜ በላይ እንደተሳልኩ ገብቶኝ ልተወው አስቤ ነበር። ግን ደግሞ እንዳልተወው ስለት ካላስገባሁ እመቤቴ እንዳትረሳኝ ፈራሁ። በሁሉቱ ግጭት መሀል ሆኜ ወደ መተው ሳዘነብል ነው ሀይሌ የጠየቀኝ። ፍርሀቴን አየና ጥያቄዬ አስገርሞት የግርምት ፈገግታ ፈገገና " አሁን ሄደህ የቻልከውን ሸክም አምጣና ለእመቤቴ 'የቀረውን አንቺ ሙዪልኝ' በላት ትሞላልሀለች" አለኝ። እሺ ብዬ ቀሚሴን ቤተ ክርስቲያን ጊቢው በር ላይ ትቼ ወደ ጫካው ገባሁ። እነዛ ግርማውያን ጥንታዊ የዝግባ ዛፎች በሰውኛ የሚያወሩ ነው ሚመስሉት። ብዛታቸው ሌላ ታሪክ... ደግሞ ትልቀታቸው.. ጫካው ውስጥ እንዳለሁ ጸሎት ከመግባታችን በፊት የምናጠናውን የዕለቱን ምስባክ ከሩቅ ሲያጠኑ ይሰማኛል። ዘሩን ጨርሰው ዜማውን እያሉ ነው.. የብዙ ሰው ድምጽ ከጫካው ጋር መስተጋብር ፈጥሮ ሌላ አይነት ሰማያዊ ዜማን ፈጥሯል። መ...ሰ...ረታቲሀ... ው..ስተ አድባ...ር ቅዱሳን ያበድሮ....ን እግዚአብሔ...ር ለአ.....ናቅ...ጸጽ...ዮ....ን... እምኵሉ... ተዐይኒ...ሁ... ለ...ያዕ...ቆብ.... ...ጫካው እያስተጋባ ምስባኩን ድጋሚ ይልልኛል። ... ጸሎት አመለጠኝ በቃ? ብዬ ብዙም ሳልርቅ ልክ ዛፎቹ ተመካክረው ያስቀመጡልኝ ይመስል የወዳደቀ ወፋፍራም ሁለት የዝግባ ቅርንጫፍ አገኘሁ። ' እፎይ ለዚሁ ነበር የተጨነቅሁት?' እነሱን ይዤ ወደ ተግባር ቤት ስሄድ እማሆይ አርሴማ ለማታ ልደታ የሚሆን የዳቤ ቂጣ እየጋገሩ ነው። የትኩስ ዳቤው እንፋሎት ልክ እንደ እጣን ጢስ ወደላይ ሲያርግ ዛሬም ይታየኛል። ያለው መዓዛ ደግሞ አፍንጫ በተበደርኩ ያሰኛል። እንጨቱን ቁጭ አድርጌ... ''ይሄው እማሆይ ስለቴን አስገብቻለሁ" አልኳቸው አይኔን ከዳቤው ሳልነቅል ቀና ብለው በእናትነት ፈገግታ እያዩኝ "ኧይ የልጅ ነገር! ይህችው ናት አንድ ሸክም?" አሉኝ። ''ኧረ እማሆይ ይሞላል እኮ። እመቤቴ ትሞላልኛለች የቀረውን'' አልኩኝ በሙሉ ተስፋ። አይኔ ግን አሁንም ዳቤው ላይ እንዳለ ነው። ''አሜን እመቤቴ ትሙላልህ! እኔስ መች ዳቤው ይበቃል ብዬ አስቤ ነበር? ለልደቷ ስለሆነ ትሙላልኝ ብዬ ስጋግር ሞልታልኝ እንጂ... በል ሂድ ጸሎት እንዳይረፍድብህ..'' ብለው ከሚጋገሩት ዳቤ ቁራሽ ሰጡኝ.... አይቼ አልቀር መቼስ... ...ቤተ ክርስትያን ስደርስ ምስባክ አጥንተው ጨርሰው እየገቡ ነበር። የምወደው ምስባክ ስለሆነ ባላጠናውም ስለማውቀው አብሬ ገባሁ። ጸሎት ሲያልቅ ሰአቱ እንደሌላው ጊዜ አልመሸም ነበር። የዛሬውን ልደታ ስለቴን ስላስገባሁ ድግሱ በሙሉ በእኔ እንጨት ብቻ እንደተጋገረ ስለተሰማኝ መርሐ ግብሩ ሲጀመር ደስ እንዳለኝ አስታውሳለሁ። ... አባ ፍቅረ ስላሴ ናቸው በጸሎት የከፈቱት። ልክ በጸሎት ተከፍቶ ያለውን መርሀ ግብር አስተዋውቀው በመጨረሻም ለቀጣይ አመት ስለት ተስለን እንደምንጨርስ ነገሩን። ሶስት ነገሮች በጣም ስላጓጉኝ ከሌሎቹ በበለጠ እንዳይጠፋ ሆነው ውስጤ ቀርተዋል። አንደኛው ቅኔ ነው። የቅኔ ተማሪዎች ያለቻቸውን መወድስ ሸክፈው ይዘው ስለሚመጡ አቀራረባቸውም ያጓጓል። ልክ አንደኛውን ቤት ሲጨርሱ ድምጻቸው ከፍ ስለሚል ''ይበል ነው!'' እያልን እናጨበጭባለን። በጭብጨባ ስናሞቀው ዳር ሆኖ ላየ... ''ለኔ ያልገባኝ የተለየ ነገር ለነሱ ምን ያህል ቢገባቸው ነው?.." ብሎ ሳይገረም አይቀርም። እኛ ግን የግድ እስኪገባን አንጠብቅም። መቼስ አባቶች ይበል ነው ካሉ እኛ ባይገባንም ይበል ነው። ኧይ የልጅ ነገር... ሌላው ያጓጓኝ ደግሞ ምግቡ... ራሴው በተሳልኩት እንጨት የተጋገረው... በበርበሬ የታሸው ቂጣ ጣዕሙ ከስንት አንዴ የምበላው ምግብ ላይ የማገኘው እየመሰለኝ ተሸውጄበታለሁ። የትም ብሄድ ማንም ቢሰራው ያንን ጣዕም ከገዳም ውጪ የትም አይገኝም። የሚሰጠንን ከረሜላ አሳድሬ ትምህርት ቤት እወስደው ነበር። ክፍል መምህር እያስተማረ ከደበረን ከጓደኞቼ ጋር በዛች ከረሜላ እንነቃቃ ነበር። ያ ልምድ ሆኖ አድጌም አለቀቀኝ ዛሬም አልፎ አልፎ ኪሴ ውስጥ ከረሜላ አይጠፋም። ሶስተኛው የጓጓሁለት ደግሞ ለቀጣይ ስለት መሳል... ስለት ሲባል ሁሉም ደስ እያለው ይሳላል። ከማልረሳቸው ስለቶች አንዱ የጓደኛዬን ስለት ነው። ምን አስቦ እንደው ባላውቅም እንዲህ ነበር ያለው... ''...ለዛሬ አመት እመቤቴ የልቤን ሀሳብ ከሞላችልኝ 500 ሳንቲም..'' ደንግጬ አየሁት...የተሳሳተ መስሎኝ። ግን እርግጠኝነት ፊቱ ላይ ይታያል። ቆይቶ ግን ስጠይቀው ፈገግ ብሎ ''5 ብር እኮ ነው 500 ሳንቲም። ቲቸር ነች ያለችው'' አለ። በቀጣዮቹ ወራት ያገኛትን አምስትም አስርም ሳንቲም ለስለት ቀን እያለ ማጠራቀሙን ተያይዞት ነበር። መቆጠብ አልችልም ሲል የነበረው ልጅ ሲቆጥብ ሳይ ገርሞኛል። አይለመድ የለ መቼስ... ...ሌላውም ይሳላል። ሚንስትሪ ካሳለፈችኝ... ይላል አንዱ... ስሜን እመቤቴ ታውቀዋለች የዛሬ አመት ቅኔ ከተቀኘሁ ይህን አደርጋለሁ እሚልም አለ... እከሌን ከማረችልኝ ይሄን አመጣለሁ... ብቻ ብዙ አይነት ስለት ይሰማል። እኔም ታድያ እጄን ሳወጣ አባ ጠጋ አሉና ጠየቁኝ። ''... 3 ሸክም እንጨት...'' ስል በድፍረት ገርሟቸው ''...ምን ብዬ ልጻፈው? ምን እንዲደረግልህ?'' ሲሉ ''... እመቤቴ ትሞላዋለች'' አልኳቸው። እሺ ብለው ጻፉት። ስለቱ አልቆ ወደቤት ሄድን።

እ .. ረ .. ስ .. ቸ .. ዋ .. ለ .. ሁ ..!! ከእለታት በአንዱ ቀን አንዲት ምስኪን ሴት ወደ አንድ መንፈሳዊ አባት ዘንድ ቀርባ "እግዚአብሔር ሁሌም ያናግረኛል" ትላቸዋለች። በሴትየዋ ሁኔታ ግራ የተጋቡት እኚህ አባትም በሁኔታው ተበሳጭተው ጥለዋት ይሄዳሉ። ከዚያን ቀን በኋላ እቺ ሴት እየደጋገመች በመምጣት "እግዚአብሔር ማታ ማታ እየመጣ ያናግረኛል" ትላቸዋለች። በሴትየዋ ጭቅጭቅ የተሰላቹት እኚህ አባትም እንደለመደችው አንድ ቀን መጥታ ስታናግራቸው እንዲህ አሏት "እውነት አንቺን እለት እለት እየመጣ ፈጣሪ የሚያናግርሽ ከሆነ አምንሽ ዘንድ አንድ የቤት ስራ ልስጥሽ" አሏት ትኩር ብለው እየተመለከቷት! ሴትዮይቱም የሚሏትን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገባች! እኚህ አባትም ከዚች ሴት ጭቅጭቅ ይገላግለኛል ያሉትን ጥያቄ አቀረቡላት እንዲህ በማለት "እውነት አንቺን እግዚአብሔር የሚያናግርሽ ከሆነ እስቲ ዛሬ ማታ አንድ ጥያቄ ጠይቂልኝ" አሏት። ሴትየዋም በእርጋታ "ምን ልጠይቅልዎ አባቴ?" አለቻቸው። "ለረጅም አመት ልተወው ያልቻልኩት የዛሬ ወር ገደማ ግን ንስሐ ገብቼ የተውኩት አንድ ኃጢአት እሰራ ነበር። ያ በፊት እሰራው የነበረ አሁን ግን ንሰሐ ገብቼ የተውኩት ኃጢአት ምን እንደነበረ ጠይቀሽ ንገሪኝ። እሱን ከነገረሽ እውነትም ላንቺ እግዚአብሔር እንደሚናገር አምናለሁ" አሏት። ሴትዬይቱም ወደቤቷ ሄደች። ተመልሳ እንደማትመጣ ግን ገምተው ነበር አባ፤ በበነጋው ያቺ ሴት መጥታ አባን አስጠራቻቸው። አባም ሴትዮዬቱን ሲያዩ በጣም ተገርመው ወደሷ በመሄድ በፌዝ መልክ "እህሳ ልጄ እግዚአብሔርን ንስሐ ገብቼ ያቆምኩት ኃጢአት ምን እንደነበር ጠየቅሺው?" አሏት ሳቅ እያሉ ... "አዎን አባ" አለቻቸው ሴትየዋ አንገቷን እንዳቀረቀረች ... "እህሳ ምን አለሽ?" አሏት አባ በመጓጓት ... "እረስቸዋለሁ አለኝ" አለቻቸው .... እኚህ መንፈሳዊ አባት ባልገመቱት የእግዚአብሔር ምላሽ ልባቸው ተነክቶ ስቅስቅ ብለው እያለቀሱ ወደደረታቸው አስጠግተው አቀፏት! እ .. ረ .. ስ .. ቸ .. ዋ .. ለ .. ሁ ..!! የሰው ልጅ ሙሉ ይቅርታ የለውም። ዛሬ ምን ፍሪዳ አርዶ ቢታረቅህ፣ ምን በልቅሶ ታጅበህ እየተንፈራፈርክ ይቅር በለኝ ብትለው "ይቅር ብዬሃለሁ" ይልህና የሆነ ቀን ስታስቀይመው ይቅር ያለውን በደልህን እየቆጠረ ሲወቅስህ ይውላል! እግዚአብሔር ግን ይቅር ካለህ በቃ ረሳው! ፍቅር ነዋ! ስንቶቻችን እንሆን እግዚአብሔርን በእኛ መጠን መትረን ንስሐ በገባንበት ኃጢአት ዘወትር የምናለቅስ? ስንቶቻችን እንሆን እግዚአብሔር እንደኛ ቂመኛ መስሎን በፍቅር ሂፆጱ ያጠበውን ኃጢአታችንን እያስታወስን ዘወትር በፀፀት እሾህ ራሳችንን የምንገርፍ? ይቅርታ ከመለመን እኮ ይቅር ማለት ይከብዳል! ምሬሃለሁ ከማለት ማረኝ እያሉ እግር ስር መደፋት እንዴት በቀለለ! በህይወታችን የገፋንና ያቆሰለንን ሰው በደል ከመርሳት ሺህ ጊዜ ፍሪዳ እያረዱ "እንታረቅ" ማለቱ እጅግ ቀላል ነው'ኮ! ለዚያም ነው መሰል ኢየሱስ ክርስቶስ ፀሎት አስተምረን ባሉት ጊዜ "እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል አንተም ይቅር በለን" ብላችሁ ፀልዩ ያለን ... እግዚአብሔር የይቅርታን ልብ ይስጠን!

እስራኤል ሠይፋ ሰላም ቤተሰብ እንዴት ናችሁ? እንኳን ለዛሬዋ ድንቅ እለት በሰላም በፍቅር በጤና አደረሳችሁ። ..እግዚአብሔር ይመስገን እኔ ደህና ነኝ። ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን🙏 ...ስለ ገዳማችን ህንጻ በሚያዝያ ወር መመረቅ እና ስለ ፈጀው ጊዜ እያሰብኩ ድንገት ''ህንጻውን ማውራት ብችልና ስላሳለፈው ጊዜ ምን ሊለኝ ይችላል?" ብዬ  ህንጻው ሊያወራኝ የሚችለውን ነገር እንዲህ ከተብኩት እና አንብባችሁም የእናንተንም ግርምት ታዩ ዘንድ እንዲህ ላጋራችሁ ወሰንኩ።     ...እንዲህ ይል ይመስለኛል:- '' '...ሚያዝያ 24 እና 25 ትመረቃለህ' ይላሉ በራሳቸው ሐሳብ እየተመሩ። ለኔ ግን የምርቃቴ ቀን ብቻ እንደሆነ አይሰማኝም። መመረቅ አንድ ነው። ነገር ግን ይህች ቀን ማለት ለኔ ትልቅ ቀን ነች። ከብዙ ትግል በኋላ ራሴን የምችልበት፣ አያቴ ተቸግራ አሳድጋ አሁን ተራዋ ደርሶ እሷን መጦር የምጀምርበት ቀን። የባላደሮች ቀንም ነች። ባላደሮች አደራቸውን የተወጡባት የምስክር ቀን።  ታሪክሽን ተናገሪ ብባል እንዲህ እንድል ይሰማኛል... ብጹዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የምሁር አቡነ ዜና ማርቆስ ቤተክርስቲያን ህንጻ ግንባታ ላይ ሳለ አንድ ህልም ያያሉ...(አያቴ ስትነግረኝ)         ... አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት በልጅነቷ የምትወልዳትን አንድያ ልጇን ስትወልድ ልትሞት እንደምትችል አስባ ከሞተች በኋላም ልጇን አሳድጋ ለወግ ማዕረግ ታበቃላት ዘንድ እናቷን ስትለምን ሰምተው እሳቸውም እንደሚያግዟት እና ልጇን ከአያቷ ጎን በመሆን ተንከባክበው አሳድገው ለወግ ማዕረግ እንደሚያበቋት ለነፍሰጡሯ ሴት ቃል  ቢገቡም ነፍሰጡሯ ሴት በብጹዕነታቸው ቃል አላመነችም። አባ ዘኢየሱስን ጠርተው  ብጹዕነታቸው በማይኖሩበት ጊዜ አባ ዘኢየሱስ የልጅቷን ጉዳይ በተለየ መልክ ይዘው ቃሉን እንደሚያስፈጽሙላቸው ተናግረው ይተማመናሉ... ...ይህን ህልም አይተው ታድያ የነፍሰጡሯ እርሳቸውን ያለ አባ ዘኢየሱስ አለማመን እንቆቅልሽ ቢሆንባቸውም ፍቺውን ፈተው ወደ ስራ ለመግባት ጊዜም አልፈጁ። ... ህልሙ የታያቸው ስለእኔ መሆኑ ነው እንግዲህ። ...ከጊዜ በኋሏ መሰረት ድንጋይ ተጥሎ በልጅነት እድሜ ላይ የነበረችው ውቧ እናቴ የምመጣውን ልጇን አብራት ባለችው በእናቷ እና በብጹዕነታቸው እንዲሁም በአባ ዘኢየሱስ እጅ ጥላ ፈረሰች። ...ብጹዕነታቸውም የእናትን አደራ እንዴት መቀበል እንዳለባቸው ከሚገባው በላይ የሚችሉበት ብልህ ሰው ነበሩና እኔን እንደ ልጅ ተቀብለው ለወደፊት ትልቅ እንድሆን አድርገው ተንከባከቡኝ። ታድያ ብጹዕነታቸው እጅ ላይ ሳለሁ ምን ያህል ተመችቶኝ እንደነበር ለማወቅ አሁን ላይ ያለሁበትን ሁኔታ ከማየት ሌላ ምስክር አያሻም። ጥሩ ዘር ከተዘራ የሚያፈራውም ጥሩ ነውና። ...ታድያ ገና በእግር መቆም ስጀምር ብጹዕነታቸው በፅኑ ይታመማሉ። ገና ልጅ ስለነበርኩ የብጹዕነታቸው መታመም በእድገቴ ላይ ስለሚያመጣው ተጽዕኖ ምንም አልገባኝም ነበር። ...ታመሙ ከተባልኩ በኋላ ብጹዕነታቸውን አይቻቸው ባላውቅም አባ ዘኢየሱስ ጋር ስለነበርኩ ብዙም የምጎዳ አይመስለኝም ነበር። ...የብጹዕነታቸውን መምጣት በመጠባበቅ መንገድ ሳይ የምውልበት ጊዜ ብዙ ነበር። በተለይ አባ ዘኢየሱስንም ሳላይ ቀናት ካለፉ ብጹእነታቸው እየናፈቁኝ ምርር ብዬ ማልቀሴ ትዝ ይለኛል። ...ታድያ ብዙዎች እየመጡ እየጎበኙኝ ሳለ የሚያወሩት ነገር ሊዋጥልኝ አልቻለም። ''... ይሄኔ እኮ ተመርቆ ነበር...'' ይላል አንዳንዱ እየገባ። ብመረቅ ምን ለውጥ እዳለው ባይገባኝም አያቴ ለበአል ብዙ ሰው ስለሚያስቀድስባት ስትጨናነቅ ሳይ ግን ታሳዝነኝ ነበር። ሁል ጊዜ ደስተኛ እየሆነች የበዓል ቀን ብቻ ማረፍ ያምራታል። ያኔ ነው የኔ ምርቃት ትዝ የሚላት። ''አንተ ስትመረቅልኝ እንደ አያት ኮራ ብዪ ቁጭ ብዪ እምጎበኘው እኔ ነኝ.." ትለኛለች አንዳንዴ ተመስጦ ውስጥ ገብታ። እናም አንድ ቀን አያቴና አባ ዘኢየሱስ ስለምርቃት ሲያወሩ ስለኔ መሆኑ ገባኝና መስማት ጀመርኩ። '... ቢመረቅልኝ ደስ ይለኝ ነበር።' አለች አያቴ '...ምርቃቱማ እኔንም ያስደስተኛል። የአባቴን አደራ ከጫፍ ማድረስ ለኔ ምን ማለት እንደሆነ ባወቅሽ። ኧረ እንደውም አልባሳትንና የትምህርት ቁሳቁሶቿን የሚችሏት ዘመዶቿም ትመረቅ ዘንድ ቀኑን ሲጠይቁኝ ነበር። ነገር ግን እንዳትመረቅ እሚያደርጓት ቅድመ ሁኔታዎች ስላልተጠናቀቁልኝ እግዚአብሔር የፈቀደ ቀን ትመረቃለች..' አሉ አባ ዘኢየሱስ። ይህን ስሰማ በቅርቡ ልመረቅ እንደምችል እና ለአያቴም ስራ እንደማቀልላት እያሰብኩ ደስ ተሰኘሁ። ይበልጥ እንድጓጓ ያደረገኝ ደግሞ በኮሮና ሰዓት ሰዉ ይራራቅ ስለተባለና አያቴ ጠበብ ስለምትል ሰፋ ሰፋ ብለው ለመገልገል ስላሰቡ ለስቅለት ቀን እኔ ጋር ነበር ስግደቱ። ያኔ ታድያ የአያቴ ስራ ማቅለል ያልኩት ለካ ስራም አልነበር? ነው ያስባለኝ። የዕጣኑ ሽታው አይነገር። በዛ ላይ የተነበበልኝ የመጻህፍት አይነት፣ የበራልኝ ሻማና ጧፉ...ኧረ ምኑ ተገልጾ... ብቻ ምነው ባልጨረሱ ያስብላል። ምርቃቴ መራቁ የታወቀኝ ያኔ ነው። ሚያዝያ 24 እና 25 ይህን አገልግሎት ስጀምር አባ ዘኢየሱስ ቃላቸውን እንደሚፈጽሙ፣አያቴን እንደማሳርፍ እንዲሁም እኔን ስመረቅ ለማየት የጓጉትን በሙሉ እንደሚደሰቱ ሳስብ እንዴት የምርቃቴ ቀን ብቻ ይምሰለኝ?   ...አንድ ቅር ሲለኝ የሚኖረው ነገር ግን የብጹእነታቸው አለመምጣት። እንዲያ እየናፈቅኳቸው መንገድ መንገዱን ሳይ፣ ሲናፍቁኝ እያለቀስኩ  ኖሬ ሳላያቸው አድጌ ለምርቃት መብቃቴ ሁሌም ቅር ቢለኝም እርሳቸውን ተክተው የተገኙ 11 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በማየቴ እና ብፁዕ አቡነ ማርቆስ እኔን ከበው ስለሚገኙ እድሜ ጠገብ ዛፎቼ የተናገሩትን በመስማቴ እጅጉን በጣም መደሰቴን ልገልፅላችሁ እወዳለሁ። ... በዚሁ አጋጣሚ የምርቃቴን ቀን በጉጉት ትጠብቁ የነበራችሁ፣ የኔ ጉዳይ ሐሳብ ገብቷችሁ እንቅልፍ አጥታችሁ አብራችሁኝ ብዙ የተንከራተታችሁ፣ ውስጤ እየገባችሁ አይታችሁኝ መልካም ምኞት የተመኛችሁልኝ እንዲሁም በሀሳባችሁ፣ በገንዘባችሁ፣ በጉልበታችሁ ላገዛችሁኝ በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ አመሰግናለሁ!!! ''