ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ
Відкрити в Telegram
ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።
Показати більше611
Підписники
Немає даних24 години
-17 днів
-930 днів
Архів дописів
❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ጳጒሜን ፭ (5) ቀን።
❤ እንኳን #ከዐሥራ_ሁለቱ_ደቂቀ_ነቢያት አንዱ ለሆነው ለታላቁ ነቢይ #ለቅዱስ_አሞጽ_ለዕረፍት በዓልና እናትና አባቱ የተውለትን ንብረት በመተው ከዓለም ለወጣ (ወደ ገዳም ለገባ) ከልብስ ተራቁቶ ለሚኖር በጸሎቱ ታላቁን አስፈሪ ዘንዶ ለማዳ እንስሳ ላደረገ ለታላቁ አባት ለብርቱ ልጅ #አባ_በርሱማ ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በፍቅር አደረሰን፡፡ በተጨማሪ በዚች ቀንከሚታሰቡ፦ ከንጽሕ ከድግል አባት ከምስር አገር ኤጲስቆጶስ #ከአባ_ያዕቆብ_ዕረፍትና ከታላቁ አባት #ከአባ_መግደር_ዕረፍት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ይደርብን።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰአሉ_ለነ_ነቢያት ስኩራነ መንፈስ ምሉኣን ሞገስ አቅርንተ ሥሉስ ቅዱስ"። ትርጉም፦ የሥላሴ ነጋሪቶች (ዐዋጅ ነጋሪዎች) የምትኾኑ ክብርን የተመላችኊ በመንፈስ ቅዱስ የተቃኛችኊ ነቢያት ለምኑልን ለእኛ አማልዱን። #ሊቁ_አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ_በሰዓታቱ_ላይ።
✝ ✝ ✝
❤ #ነቢዩ_ቅዱስ_አሞጽ፦ ይህም ዕውነተኛ ነቢይ በእስራኤል ነገሥታት በኢዮአስና በኦዝያ ዘመን አስተማረ የእስራኤልንም ልጆች የእስራኤልንና የይሁዳንም ነገሥታት ይገሥጻቸው ነበር።
❤ ስለ ክብር ባለቤት ስለ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ስለመቀበሉ በዚያችም ቀን ስለ ፀሐይ መጨለም ከዚያም በኋላ እስራኤልን ስለሚደርስባቸው መከራ ኀዘን ልቅሶ ረድኤትም እንደሚአጡ የእግዚአብሔርንም ቃል መስማትን ከማጣት የተነሣ እንደሚራቡና እንደ ሚጠሙ። በሀገሩ ሁሉ በአሕዛብም መካከል እንደሚበተኑ አሕዛብም እንደ አጃ ሸክሽከው እንደሚአጓልቧቸው ትንቢትን ተናገረ ትንቢቱም በላያቸው ተፈጸመ።
❤ ስለኃጢአታቸውና ስለ ክፉ ሥራቸው ስለ ዘለፋቸው እነርሱ እንደ ገደሉት ተናገረ። የትንቢቱም ዘመን ከጌታችን ሥጋዌ በፊት በስምንት መቶ ዓመት ነው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቅ ነቢይ በቅዱስ አሞጽ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_በርሱማ፦ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ በምስር አገር እጅግ ባለጸጎች ነበሩ እነርሱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ መጻተኞችንም በፍቅር የሚቀበሏቸው በእግዚአብሔርም በሕጉ ሁሉ ጸንተው የሚኖሩ ናቸው።
❤ ይህን ቡሩክ በርሱማን በወለዱት ጊዜ በፈሪሀ እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትንም ሁሉ በማስተማር አሳደጉት። ከዚህም በኋላ ወላጆቹ አረፉ የእናቱም ወንድም ወላጆቹ የተውለትን ገንዘብ ሁሉንም ወሰደ አባ በርሱማም አባትና እናቱ የተውለትን ገንዘብ የእናቱ ወንድም እንደ ወሰደ አይቶ የዓለምን ኃላፊነት አሰበ። እንዲህም አለ "መድኃኒታችን "ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ይጣላት ስለእኔም ሰውነቱን የጣላት ያገኛታል" ብሏል"። "ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን በሰጠ ነበር። የሰው ልጅ በአባቱ ጌትነት ከመላእክቶቹ ጋር ይመጣ ዘንድ አለውና ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ይከፍለዋል"።
❤ ይህንንም ብሎ ከዓለም ወጣ በበጋ ቃጠሎ፣ በክረምት ቅዝቃዜ ልብስ ሳይለብስ በአምስት ኮረብታዎች ላይ ኖረ። ወገቡንም በማቅ መታጠቂያ ይታጠቃል በልቡም እንዲህ ይላል "በርሱማ ሆይ በሚያስፈራ ዕውነተኛ ፈራጅ ፊት ትቆም ዘንድ አለህ እኮን"። ሁልጊዜም በጾም በጸሎት በስግደት በቀንና በሌሊት ይተጋ ነበር። በሚመገቡም ጊዜ በውኃ የራሰ ደረቅ ቂጣ ይመገባል ቆዳውም ከአጥንቱ ጋር ተጣበቀ።
❤ ከዚያም ቦታ ሊሸሽ ወደደ ከንቱ የሆነ የሰውን ምስጋና ፈርቷልና በምስር ወዳለት የቅዱስ መርቆሬዎስ ቤተ ክርስቲያን ደረሰ በዚያም በጾም በጸሎት በስጊድ እየተጋደለ ሃያ አምስት ዓመት ኖረ። በዚያችም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በዋሻ ውስጥ ታላቅ ዘንዶ አለ ዘንዶውንም ከመፍራት የተነሣ ሰው መብራትን ማብራት የማይችል ነው። እግዚአብሔርም የዚህን ቅዱስ የአባ በርሱማን ደግነቱን ሊገልጥና በእጆቹም ድንቆች ተአምራትን ለማድረግ በወደደ ጊዜ አባ በርሱማ ወደዚያች ዋሻ ገባ ወደ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ጸለየ "የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እባቡን ጊንጡን እንረግጥ ዘንድ በጠላት ኃይል ላይ ሁሉ ሥልጣንን የሰጠኸን አንተ ነህ። አሁንም በዚች ዋሻ ውስጥ በሚኖር ከይሲ ላይ ታሠለጥነኝ ዘንድ እለምንሃለሁ ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ"።
❤ ከዚህም በኋላ ራሱን በመስቀል ምልክት አማተበ እንዲህም እያለ ዘመረ "በተኲላና በእባብ ላይ ትጫማለህ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ"። ከዚህም በኋላ ያንን ዘንዶ በእጁ ይዞ እንዲህ አለው "ከእንግዲህ ገራም ሁን ታጠፋ ዘንድ ሥልጣን አይኑርህ ኃይልም ቢሆን በማንም ላይ ከሰው ወገን በአንዱ ላይ ክፉ ሥራ አታደርግ የሚሉህን ሰምተህ የምትታዘዝ ሁን እንጂ" በዚያን ጊዜም አንበሶች ለነቢዩ ዳንኤል እንደተገዙ ያ ዘንዶ ከአባ በርሱማ እግሮች በታች ተገዢ ሆነ።
❤ ከዚህም በኋላ አባ በርሱማ በመራብ በመጠማት ተጋድሎውን ጨመረ በየሁለት ቀን፣ በየሦስት ቀን፣ በየሰባት ቀን እያከፈለ ብርሃን በላዩ እስቲወጣ ያለ ማቋረጥ የሚጾም ሆነ። ለጸሎት በሚቆም ጊዜ ከይሲው ከርሱ ይርቃል በሚቀመጥም ጊዜ ሲጠራው ወደርሱ ይመጣል።
❤ በዚችም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የውኃ ጒድጓድ አለች ወደርሷ በመውረድ ሁል ጊዜ ከማታ እስከ ንጋት ከውስጧ ገብቶ ያድራል በክረምትም በበጋም እንደዚህ ያደርጋል መላዋን ሌሊትም በውስጥዋ እየጸለየ ያድራል። የሚመገበውም የደረቀና የሻገተ ቂጣ ሲሆን የሚጠጣውም የከረፋ ውኃ ነው።
❤ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን አዘውትሮ ያነባል ይልቁንም የዳዊትን መዝሙር አባቶችም ሥጋቸውን ለማድከም ያደረጓቸውን ትኀርምቶች በማንበብ ስለዚህ ትኀርምትን ንጽሕናን ወደደ ለሰዎችም እንዲህ እያለ ጠቃሚ ሥራዎችን ያስተምራል "ያለ ልብ ንጽሕና በቀር አንዱ እንኳን የእግዚአብሔር መንግሥት ማየት አይችልም ኃጢአት ሁሉ ከንስሓ በኋላ ይሠረያልና"። ለክርስቲያን ወገኖችም እንዲህ ያስተምራቸዋል ከእግዚአብሔርም ተአምራት የማድረግ ሀብት ተሰጠው ከገድሉም ለሰው የገለጥነው ጥቂቱን ነው።
❤ የዚህም አባት አርአያው የሚያምር መልኩም በብርሃን ያሸበረቀ ገጽታው ደስ የሚል ነው። ጥሪት በማጣቱም ደስ ይልዋልና። ከዓለማዊ ልብስ የተራቆተ ዓለምን ከማግኘትም የራቀ ነው። ቀድሞ ከቤቱ ከወጣ ጀምሮ የቀይ ግምጃ ጨርቅ በማገልደም ሥጋውን ይሸፍናል በክረምትም በበጋም የቀን ሐሩርን የሌሊት ቊርን ይታገሣል በጐኑና በምድር መካከል ምንጣፍ አላደረገም ወደ ሕይወት አገር ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት የሚያደርስ ተጋድሎን እንደዚህ ተጋደለ።
❤ ከክፉዎች ሰዎችና ከክፉዎች አጋንንት ብዙ ጊዜ ኀዘን ፈተና አግኝቶታል ከዚህም ሁሉ ጋር በዚህ ጭንቅ በሆነ ሥራ የረዳው እግዘሐአብሔርን ፈጽሞ ያመሰግነዋል። ይህንን በጎ የገድል ጒዞ በተጓዘ ጊዜ ሰዎት ዜናውን ሰሙ ሽማግሎችም ጐልማሶችም ከእነርሱ በጽነት የተሰነካከለ ወይም ከጠላት ሰይጣን ፈተና ያገኘው ወይም የመንፈስ ደዌ ያገኘው ሁሉ መሪና አጽናኝ ይሆናቸው ዘንድ ተመኝተውት ፈለጉት ከእርሱ ፈውስ ያገኙ ዘንድ መጡ።
+2
ቅዱስነታቸው ምን አሉ ?
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሀይማኖት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምርቃትን አስመልክቶ የደስታ መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዚህም መልዕክታቸው " የዛሬዋን ቀን በመናፈቅ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ ለዚህ ሥራ በማዋጣት ታሪክ በመልካም የሚያስታውሰውን ዋጋ የከፈላችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ልጆቻችንን እንኳን ደስ አላችሁ " ብለዋል።
" የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ወደቀጣይ የልማት ሥራ የሚያሸጋግር እንዲሆን፤ ከምንም በላይ ሰላም በምድራችን ላይ እንዲስፍን ሕዝባችንም እግዚአብሔር የሰጠው በነፃነት የመኖር መብት ተከብሮለት የልማቱን በረከት መሳተፍ እንዲችል ሁሉም ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በትኩረት ሊሠሩ ይገባል " ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን በእግዚአብሔር ስም አስተላልፈዋል።
❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ጳጒሜን ፬ (4) ቀን።
❤ እንኳን ለታላቁ ለተጋዳይ አባት #ለአባ_ባይሞንና ለሮሜ ሊቀ ጳጳሳት አርዮሳውያንን በመቃወም በማውገዝ ብዙ ለደከመ ሃይማኖትን ለጠበቀ ላጸና ለታላቅ አባት #ለአባ_ሊባርዮስ_ለዕረፍታቸው_በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታቡ፦ #ከአባ_ባይሞን_ከስድስቱ_ወንዱሞቹ_መነኰሳት ስማቸው #ከዮሐንስ_ከኢዮብ_ከዮሴፍ_ከላስልዮስ፣ #ከያዕቆብና_አብርሃም ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ባይሞን፦ ይህም ቅዱስ ከምስር ሀገር ነው ስማቸው ዮሐንስ፣ ኢዮብ፣ ዮሴፍ፣ ላስልዮስ፣ ያዕቆብ፣ አብርሃም የሚባል ስድስት ወንድሞች አሉት ሁሉም መነኰሳት ሁነዋል። ከእሳቸውም ዮሐንስ ይልቃል ነገር ግን በእውቀትና በጥበብ ባይሞን ይበልጣል። ሁሉም ተስማምተው ከዓለም ወጡ ከሰውም ሩቅ በሆነ ቦታ የሚኖሩ ሆኑ የክብር ባለቤት የሆነ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ቀንበር ተሸክመው ከዘመድም ተለይተው በጠባብ መንገድ ተጓዙ።
❤ እናታቸውም ልታያቸው ወዳ ወደ በዓታቸውም ደርሳ በውጭ ቆመች ወደርሷም መጥተው እንድታያቸው ላከችባቸው እነርሱም ወደርሷ እንዲህ ሲሉ ላኩ "በዚህ በኃላፊው ዓለም ልታይን ከወደድሽ በወዲያኛው ልታይን አትችይም" እርሷም አስተዋለች አልመለሰችላቸውም መንገዷን ተጓዘች።
❤ ይህም አባት ባይሞን በአስቄጥስ ገዳም ለሽማግሌዎችም ለጐልማሶችም አረጋጊ ወደብ ሆነ። ከጠላት ሰይጣን ፈተና የሃይማኖት ጥርጥር ወይም ደዌ ያገኘው ሁሉ ወደርሱ ይመጣል ወዲያውኑ ያረጋጋዋል ከደዌውም ይፈውሰዋል። ይህም አባት በምንኲስና ሕግ ስለ መጋደል ስለ አምልኮም ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ። በትምህርቱም እንዲህ አለ "የተሰነካከለ ወንድምን ብታይ ስለርሱ ተስፋ አትቁረጥ ልቡን አንቃለት እንጂ ከወደቀበትም እንዲነሣ አጽናንተህ ሸክሙን አቃልለት። አፍህ የተናገረውን ይሠራ ዘንድ ልብህን አስተምረው" አለ።
❤ አንድ ወንድም እንዲህ አለው "ሥራው መልካም የሆነ ወንድም ያየሁ እንደሆነ ደስ ይለኛል ወደቤቴም አስገብቼ ባለኝ ነገር ደስ አሰኘዋለሁ። ግን ሥራው ብልሹ የሆነ ወንድም ያየሁ እንደሆነ አልፈቅደውም ወደ ቤቴም አላስገባውም"። አባ ባይሞንም እንዲህ ብሎ መለሰለት "ሥራው በጎ ለሆነው እንዳረግኸው ለዚህም ሥራው ብልሹ ለሆነው ዕጥፍ አድርገህ በመሥራት ደስ አሰኘው ለታመመ መድኃኒት ያደርጉለት ዘንድ ይገባልና"።
❤ ከዚህም በኋላ ለዚያ ከርሱ ጋር ለሚነጋገር ወንድም እንዲህ ብሎ ነገረው "በመነኰሳት ገዳም ስሙ ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ በኃጢአትም ወድቆ "አቤቱ ይቅር በለኝ" እያለ የሚጮህና የሚያለቅስ ሆነ። ከሰማይም እንዲህ የሚል ቃል መጣ "አንተ ወንድምህን በመከራው ጊዜ ቸለል ያልከው ባትሆን እኔ ባልጣልኩህም ነበር"።
❤ ይህ አባት ደግሞ እንዲህ አለ "እኛ የወንድማችን በደል ብንሰውር እግዚአብሔርም በደላችንን ይሠውርልናል"። ይህም አባት ዕድሜውን በተጋድሎና በትሩፋት ሥራ ከፈጸመ በኋላ ወደ መልካም ዕርግና ደርሶ እግዚአብሔርን አገልግሎ ጳጒሜን 4 ቀን በሰላም አረፈ።
✝ ✝ ✝
❤ #የሮሜ_ሊቀ_ጳጳሳት_አባ_ሊባርዮስ፦ ይህም አባት አርዮሳዊ በሆነ በሁለተኛው ቈስጠንጢኖስ ዘመን ተሾመ። የቈስጠንጢኖስም ወንድሙ ቊንስጣ በሮሜ ነግሦ ነበር።
❤ ሐዋርያዊ አትናቴዎስንና ጳውሎስን ከመንበረ ሢመታቸው በአሳደዳቸው ጊዜ እነርሱም ወደዚህ አባት ሊባርዮስ መጡ። ይረዳቸውም ዘንድ ለመኑት እርሱም ተቀበላቸው ከደብዳቤ ጋርም ወደ ንጉሥ ቊንስጣ ላካቸው ንጉሡም ደብዳቤያቸውን ተቀብሎ በጎ ነገር እንዲያደርግላቸው ወደ መንበረ ሢመታቸውም እንዲመልሳቸው ወደ ወንድሙ ቈስጠንጢኖስ ደብዳቤ ጻፈላቸው። እርሱም የወንድሙን ደብዳቤ በአነበበ ጊዜ አትናቴዎስን ወደ መንበረ ሢመቱ እስክንድርያ፣ ጳውሎስንም ወደ መንበረ ሢመቱ ቊስጥንጥንያ መለሳቸው።
❤ ከዚህም በኋላ ቊንስጣ ንጉሥ በዓመፀኞች በተገደለ ጊዜ ቈስጠንጢኖስ ወደዚህ አባት ሊባርዮስ መልእክት ላከ ሐዋርያዊ አትናቴዎስን ያሳድደው ዘንድ የአርዮስንም ወገን እንዲቀበላቸው ብዙ ቃል ኪዳናትንም ገባለት እርሱ ግን አልተቀበለውም በምክሩም ከእርሱ አልተስማማም። ስለዚህም ይህን አባት ሊባርዮስን ሩቅ አገር አጋዘው።
❤ ከዚህም በኋላ ወንዱሙ ቊንስጣን የገደለውን ጭፍራ ልኮ ገደለው። ከዚህም በኋላ ቈስጠንጢኖስ ወደ ሮሜ ከተማ ሔደ ስለዚህ አባት ሊባርዮስም የገዳማትና የአድባራት ሊቃውንት ካህናቱም ሁሉ ወደ መንበረ ሢመቱ ይመልሰው ዘንድ ንጉሡን ለመኑት እርሱም ምልጃቸውን ተቀብሎ ወደ መንበረ ሢመቱ መለሰው።
❤ ይህ አባት ወደ መንበሩ በተመለሰ ጊዜ በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ ሁልጊዜ መንጋዎቹን ማስተማር ጀመረ ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትንም ደረሰ የአርዮስ ወገኖችንም እየተቃረናቸው ኖረ ያወግዛቸውና ያሳድዳቸውም ነበር። ከስደት ከተመለሰ በኋላ በሰባት ዓመት በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ሊባርዮስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጳጒሜን 4 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ዕብል_በልሳንየ_መዋቲ። ፯ተ አኃወ ኅዱራነ በአት አሐቲ። ሶበ ፈቀደት እሞሙ ትርእዮሙ ይቤልዋ ላቲ። ኢትክሊ ትርአዪነ በዓለም ሰማይ እንታክቲ። ለእመ በዝየ ርኢክነ አንቲ"። #ሊቁ አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የጳጉሜን_4።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ክላእ ልሳንከ እምእኩይ። ወከናፍሪከኒ ከመ ኢይንብባ ጒኅሉተ። ተገኃሥ እምእኩይ ወግበረ ሠናየ"። መዝ 33፥13-14። የሚነበቡት መልክዕታት 2ኛ ጢሞ 2፥11-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 5፥1-6 እና የሐዋ ሥራ 15፥19-25። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 18፥23-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም፣ የጸሎትና የምሕላ ጊዜና በዓል ለሁላችን ይሁንልን።
✝ ✝ ✝
❤ #ለእግዚአብሔር_ልጅ_ምሳሌው_የሆነ #ካህኑ_ቅዱስ_መልከጼዴቅ፦ መልከጼዴቅም ዐሥራ አምስት ዓመት በሆነው ጊዜ ከአዳም ሥጋ ጋር እንዲልከውና በምድር መካከል እንዲያኖረው እግዚአብሔር ኖኅን አዘዘው እርሷም ቀራንዮ ናት። የዓለም መድኃኒት ክርስቶስም መጥቶ በዚያ እንደሚሠዋ አዳምንም ከልጆቹ ሁሉ ጋር እንደሚያድነው አመለከተው።
❤ ከዚህም በኋላ በአባቱ በኖኅ ትእዛዝ ሤም መልከጼዴቅን በሥውር ወሰደው የእግዚብሔርም መልአክ እየመራቸው ሔደው ወደ ቀራንዮ ተራራም አደረሳቸው መልከጼዴቅም ክህነትን ተሾመ። ዐሥራ ሁለት ደንጊያዎችንም ወስዶ መሠዊያ ሠራ ከሰማይ የወረደለትንም ኅብስትና ወይን መሠዊያ በሠራቸው ደንጊያዎች ላይ መሥዋዕትን አሳረገ።
❤ ምግቡንም መላእክት ያመጡለታል ልብሱም ዳባ ነው በአባታችን አዳም ሥጋ ዘንድ ሲያገለግል ኖረ። አብርሃምም ከጦርነት ነገሥታትን ድል አድርጎ በተመለሰ ጊዜ ኅብስትንና ወይንን አቀረበለት አብርሃምም ከገንዘቡ ሁሉ ከዐሥር አንድ ሰጠው እርሱ ካህንም ንጉሥም ሁኖ ተሹሟልና። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በካህኑ ቅዱስ መልከጼዴቅ በአማላጅነቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅዱስ_ሰራጵዮን፦ ይህም ቅዱስ ሰንዱን ከሚባል አገር ነው። ከታናሽነቱ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ትርጓሜያቸውንም ተማረ የዚህንም ዓለም ገንዘብ ሁሉ ትቶ ወደ አረሚ አገር ሔደ ራሱንም በሃያ ብር ሸጦ ማገልገል ጀመረ የሽያጩንም ዋጋ ጠበቀው። እንጀራ ሳይበላ ውኃ ሳይጠጣ ከስሕተታቸው ይመልሳቸው ዘንድ ሁል ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር።
❤ ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት በሆነ በክርስቶስ አሳመናቸው ሕግንና ሥርዓትንም ሁሉ አስተማራቸው ከዚህም በኋላ ስለርሳቸው ራሱን ባሪያ አድርጎ እንደሸጠ እንጂ እርሱ ባሪያ እንዳልሆነ ነገራቸው ሽያጩንም ለድኆች እንዲሰጡት ሰጣቸው።
❤ ከዚህም በኋላ መንካያውያን ወደሚባሉ ሕዝቦች ሒዶ ለነርሱም ራሱን ሸጠ የክብር ባለቤት ወደሆነ ክርስቶስ እምነት እስከመለሳቸው ድረስ ተገዛላቸው። ከዚህም በኋላ ደግሞ ወደ ሮሜ አገር ሒዶ በሰላም እስከ አረፈ ድረስ በጾምና በጸሎት እየተጋደለ ኖረ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጳጒሜን 3 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "መሐለ እግዚአብሔር ወኢይኔስሕ። አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከጼዴቅ። እግዚአብሔር በየማንከ"። መዝ109፥4-5። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 17፥20-31።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "እግዚአብሔር ገሃደይ መጽእ። ወአምላክነሂ ኢያረምም። እሳት ይነድድ ቅድሜሁ"። መዝ 49፥2-3። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 7፥1-7፣ ይሁ 1፥11-17 እና የሐዋ ሥራ 5፥16-26። የሚነበው ወንጌል ማቴ 25፥3146። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ነው። መልካም የመልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል በዓል ለሁላችን ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ጳጒሜን ፫ (3) ቀን።
❤ እንኳን #ለሊቀ_መላእክት_ለቅዱስ_ሩፋኤል ለተሾመበት፣ #ቅዱስ_ጦቢትን_ዐይኑን_ለአበራለትና ልጁ #ቅዱስ_ጦብያን_ለረዳበት፣ የራጉኤልን ልጅ #ሣራን_ተቆራኝቷት_የነበረው_አስማንድዮስ_ጋኔን ላወጣላት በዓል (ታሪክ በጽሐፈ ጦብት ላይ ያንብቡ)ና #ለሊቀ_ካህን_ለኢየሱስ_ክርስቶስ ምሳሌ ለሆነ #ለካህኑ_ቅዱስ_መልከፄዴቅ ለመታሰቢያ በዓሉ በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ ሰንዱን ከሚባል አገር #ከቅዱስ_ሰራጵዮን ዕረፍት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #ሊቀ_መላእክት_ቅዱስ_ሩፋኤል፦ እርሱም ከመላእክት አለቆች ሦስተኛ የሆነ ነው። ደግሞም ከእስክንድርያ ውጭ በደሴት የታነፀች ቤተ ክርስቲያኑ በከበረ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን በውስጧ ተአምር የተገለጸባት የከበረችበት ነው።
❤ ይህም እንዲህ ነው ሀብታም ሴት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ መጥታ ሳለ ከእርሷ ጋርም ብዙ ሰው ነበረ። ከባሏም የወረሰችው ብዙ ገንዘብ አላት በሊቀ ጳጳሳቱ ቤት አንጻር ያለውን ኮረብታ አስቆፈረችው በጥቅምት ወር ዐሥራ ስምንት ቀን እንደጻፍን የወርቅ መዝገብ ተገለጠ። በዚያም ወርቅ ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትን አነፀ ከእርሳቸውም አንዲቱ የመላእክት አለቃ በሆነ በከበረ መልአክ ሩፋኤል በስሙ የታነፀች ይህች ናት። ሥራዋንም በፈጸመ ጊዜ እንደዛሬው በዚች ቀን አከበራት።
❤ ብዙ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጸች ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና። የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው። ወደ ክብር ባለቤት እግዚአብሔርም በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮኹ ያን ጊዜ ይህ የከበረ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በጦሩ ወግቶ እንዲህ አለው "እግዚአብሔር አዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጽ ጸጥ ብለህ ቁም"። አንበሪውም ጸጥ ብሎ ቆመ አልታወከም በውስጧም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆነ።
❤ ይቺም ቤተ ክርስቲያን እስላሞች እስከተነሡበት ዘመን ኖረች ከዚህም በኋላ ሁለተኛ ያ አንበሪ ተናወጸ ደሴቲቱም በላይዋ ከሚኖሩ ብዙ ሕዝብ ጋራ ሠጠመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የመልአክ ቅዱስ ሩፋኤል በረከቱ ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #ዳግመኛም_የቊስጥንጥንያ_ሊቀ_ጳጳሳት #አባ_ዮሐንስ_ጻድቅ_ለሆነ_ንጉሥ_አኖሬዎስ_ተናገረው፦ እንዲህም አለው "ንጉሥ ሆይ እኛ ወዳንተ ልንመጣ በመርከብ እንደተሳፈርን ዕወቅ በጒዞ ላይ ሳለንም በቀዳሚት ሰንበት ቀን በደሴት ውስጥ ታናሽ ቤተ ክርስቲያን አየን ወደ ወደቡም ደርሰን በዕለተ እሑድ ሥጋውን ደሙን እንቀበል ዘንድ ወደርሷ ሔድን።
❤ ለዚያች ቤተ ክርስቲያንም በጐኗ ታናሽ ገዳም አገኘን በውስጧም ወንድሞች መነኰሳት አሉ በክብር ባለቤት ጌታችንም ፈቃድ ወደ ርሳቸው ደረስን። መነኰሳቱንም "በቀደሙ አባቶች ዘመን የተጻፈ አሮጌ መጽሐፍ በእናንተ ዘንድ እንዳለ እጽናናበት ዘንድ እርሱን ሰጡኝ" አልኳቸው።
❤ እንዲህም ብለው መለሱልኝ "እኛ ትርጓሜያቸውን የማናውቀው መጻሕፍቶች በዕቃ ቤት አሉ"። እኔም "አያቸው ዘንድ ወደዚህ አምጡልኝ" አልኳቸው። በአመጡአቸውም ጊዜ መረመርኳቸው ጌታችንም በደቀ መዛሙርቱ ፊት ያደረጋቸውን ኃይሎችና ድንቆች ተአምራቶችን ስለ ሰማይና ምድርም ጥንተ ተፈጥሮ አገኘሁ።
❤ ሁለተኛም ስመረምር ስለ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ሹመትና መዐርግ አባቶቻችን ንጹሐን ሐዋርያት የጻፉትን አገኘሁ ይኸውም ጌታችን በደብረ ዘይት ከእሳቸው ጋራ እያለ የመለኮቱን ምሥጢር በገለጠላቸው ጊዜ። ሐዋርያትም እንዲህ ብለው እንደለመኑት "ጌታችንና ፈጣሪያችን ሆይ የከበረ የሩፋኤልን ክብሩን ታስረዳን ዘንድ እንለምንሃለን በየትኛው ዕለት በየትኛው ወር ሾምከው"። ከባልንጀሮቹ የመላእክት አለቆችም ትክክል ነውን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ዘንድ በዓለም ውስጥ ስለርሱ እንድናስተምር እርሱም በመከራቸው ጊዜ ይረዳቸው ዘንድ በአማላጅነቱም በአንተ ዘንድ ይቅርታን ያገኙ ዘንድ።
❤ ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዘዘና ከሦስተኛው ሰማይ ሦስቱ የመላእክት አለቆች ሚካኤል፣ ገብርኤልና ሩፋኤል መጡ በታላቅ ደስታም ለክብር ባለቤት ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰገዱ። ጌታችንም ሩፋኤልን እንዲህ አለው "የክብርህን ገናናነት የባልንጀሮችህንም ልዕልናቸውን እንዲያውቁ ለሐዋርያት ንገራቸው"። ያን ጊዜም ለጌታችን ሰገደ ይነግራቸውም ዘንድ ጀመረ እንዲህም አላቸው "ደገኛው የመላእክት አለቃ ሚካኤል ለሁሉም መላእክት አለቃቸው ነው ስሙም ይቅር ባይ ይባላል"።
❤ "ሁለተኛም የመላእክት አለቃ ገብርኤል የስሙ ትርጓሜ አገልጋይም ጌታም የሆነ የዓለሙ ሁሉ እመቤት የሆነች አምላክን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያምን ያበሠራት ነው"። "የእኔም ስሜ ሩፋኤል ነው ይህም ደስ የሚያሰኝ ቸር መሐሪ ቅን የዋህ ማለት ነው እኔም ኃጢአተኞችን በእግዚአብሔር ዘንድ አልከሳቸውም ከኃጢአታቸው በንስሓ እስኪመለሱ ስለ ቅንነቴ በእነርሱ ላይ እታገሣለሁ እንጂ። በሃያ ሦስቱ የመላእክት ነገድ ሠራዊት ላይ እግዚአብሔር የሾመኝ እኔ ሩፋኤል ነኝ እግዚአብሔር አብን ይቅር ባይ ልጁን አጽናኝና አዳኝ የሆነ መንፈስ ቅዱስን እናመሰግነው ዘንድ።
❤ በደብረ ጽዮን በሚደረገው የሺህ ዓመት ተድላ ደስታ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክብር ጽዋን በሚሰጣቸው ጊዜ ለቅዱሳኖቹ በጎ ነገርን እንድሰጣቸው እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ። ደግሞም በዚች ቀን ከዕፀ ሕይወት ዐጽቅ ወስጄ ለተመረጡ ክርስቲያኖች በእጄ እንድሰጣቸው እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ። የሰማያት መዛግብትም ከእጄ በታች ተጠብቀው የሚኖሩ እኔ ሩፋኤል ነኝ። እኔም እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ እከፍታቸዋለሁ እዘጋቸዋለሁም።
❤ በምድር ሰው ለባልንጀራው ስለ ስሜ በጎ ነገር ቢያደርግ እኔ በመከራው በችግሩ ረዳዋለሁ ወይም የሹመቴን ነገር የሚጽፍ ወይም ከቅዱሳን ጋራ ስሜን የሚያስብ ወይም በስሜ ለቊርባን የሚሆነውን የሚሰጥ ወይም በበዓሌ ቀን ምጽዋትን የሚሰጥ ይኸውም እግዚአብሔር በሊቃነ መላእክት ክብር የሾመኝና ያከበረኝ ጳጕሚን ሦስት ቀን ነው። ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እስከማስገባው በብርሃን ሠረገላ እኔ እሸከመዋለሁ በምድር ላይ ከቶ እንደርሱ ያለ የማይገኝ መዐዛው እጅግ ጣፋጭ በሆነ ሽቱ ነፍሶቻቸው እርሱን በማሽተት ደስ እንዲላቸው አደርጋለሁ።
❤ ሐዋርያት ሆይ በእግዚአብሔር ፊት እስከምትቆሙ እጠብቃችሁ ዘንድ ከእኔ ርዳታን ሹ። የዚህ የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሩፋኤል ተአምራቶቹ ብዙ ናቸው ስለእኛ ይማልድ ዘንድ የበዓሉን መታሰቢያ ልናደርግ ይገባናል። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል አማላጅነት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ጳጒሜን ፪ (2) ቀን።
❤ እንኳን #ከሰባ_ሁለቱ_አርድእት አንዱ ለሆነው ሐዋርያው #ቅዱስ_ጳውሎስ_መልእክት_ለጻፈለት ለከበረ #ለሐዋርያው_ለቅዱስ_ቲቶ ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #ሐዋርያው_ቅዱስ_ቲቶ፦ የዚህም ቅዱስ ትውልዱ ቀርጤስ ከሚባል አገር ነው። እርሱም ለዮናናውያን ወገን ለሆነ ለአገረ ገዥው እኅት ልጅዋ ነው። ከታናሽነቱም የዮናናውያንን ትምህርትና ፍልስፍና ተምሮ እጅግ አዋቂ ሆነ በጠባዩም ቅን ሥራው ያማረ ለድኆችና ለችግረኞች መራራት የሚወድ ነው። ከሌሊቶችም በአንዲቱ "ቲቶ ሆይ ስለ ነፍስህ ድህነት ተጋደል ይህ ዓለም አይጠቅምህምና" የሚለውን በሕልሙ አየ። ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ደነገጠ ምን እንደሚሠራም አላወቀም።
❤ ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት በተሰማ ጊዜ ብዙዎች ሰዎችም ተአምራቱን እርስበርሳቸው ተነጋገሩ የአክራጥስ መኰንንም ሰምቶ አደነቀ ዕውነት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ወይም የሥራይ እንደሆነ ሊያውቅ ሽቶ የሚልከው ብልህ ሰው ፈለገ የእኅቱንም ልጅ ቲቶንን መረጠው ከእርሱ የሚሻል የለምና። ሲልከውም ታላቅና ጥልቅ የሆነ ምርመራ እንዲመረምር አዘዘው።
❤ ቲቶም ከይሁዳ ምድር በደረሰ ጊዜ የመድኃኒታችንን ድንቆች የሆኑ ተአምራቶቹን አየ ሕይወትነት ያላቸው ትምህርቶቹንም ሰማ። ከዮናናውያንም በትምህርታቸውና በሥራቸው መካከል ታላቅ የሆነ መራራቅን አግኝቶ የዮናናውያን ሃይማኖታቸው የቀናች እንዳልሆነች ለይቶ ዐወቀ።
❤ ከዚህም በኋላ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ አመነ፤ ደቀ መዝሙሩም ሁኖ ተከተለው። ወደ እናቱ ወንድም ወደ አገረ ገዥውም መልእክትን ላከ የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምረውና የሚሠራው ዕውነት እንደሆነ ነገረው።
❤ ጌታችንም ከሰባ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ውስጥ የተቆጠረ አደረገው ከዕርገቱም በኋላ ከሐዋርያት ጋር የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀብሎ ከእሳቸው ጋር በሀገሮች ሁሉ ዙሮ አስተማረ። ጌታችንም ጳውሎስን ጠርቶ ሐዋርያው በአደረገው ጊዜ ያን ጊዜ ሐዋርያ ጳውሎስን ተከተለው በብዙ አገሮችም ወንጌልን ሰበከ።
የከበረ ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜ ከተማ ምስክር ሆኖ ከሞተ በኋላ ቅዱስ ቲቶ ወደ ሀገረ አክራጥስ ተመለሰ ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው በዙሪያቸው ላሉ አገሮችም እንዲሁ አደረገ።
❤ ከዚህም በኋላ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሞ ወደ ወደደው እግዚአብሔር ጳጒሜን 2 ቀን ሔደ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ቅዱስ ቲቶ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለከ_ቲቶ_መስተሳልም። ለእከ ጳውሎስ ዘኮንከ እንበለ ድካም። ከመ ገሠጸከ በቃል ወይቤለከ በሕልም። ተጋደል በእንተ ነፍስከ በገድለ ሃይማኖት ፍጹም። ኢይበቊዓከ ዝንቱ ኃላፊ ዓለም"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የጳጒሜን_2።
+3
❤ #ብፁዕ_ወቅዱስ_አቡነ_ማትያስ_ፓትርያርክ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ጨርሰው #ዛሬ_ጳጒሜን_1_ቀን 2017 ዓ.ም በሰላም አዲስ አበባ ገቡ።
❤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት #ሐምሌ_1_ቀን_2017 ዓ.ም ወደ አሜሪካ ያቀኑ ሲሆን በዛሬው ዕለት ማለት ጳጒሜን 1 ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።
❤ ቅዱስነታቸው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን ተከትሎ ክብረ አበውን አሠረ ሐዋርያትን መሠረት በማድረግ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጀምሮ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የእንኳን ደህና መጡ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
❤ የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን የአቡነ ማትያስ ቡራኬ አይለየን።
❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ እንኳን #ለጾመ_ዮዲት_ለጾመ፤ የኢትዮጵያ ንጉሥ #ዐፄ_ናኦድ_ስምንተኛው_ሺህ እንዳያዩት ለጾሙት (የፈቃድ ጾም) እግዚአብሔር አምላከ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ "ሰብአ ነነዌ #ጸዊሞሙ_ተማኅሊሎሙ ድኅኑ እሞቶሙ" ትርጉም፦ የነነዌ ሰዎች #ጾመውና_ምሕላ ይዘው ከሞት ዳኑ። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በጾመ_ድጓው_ላይ።
✝ ✝ ✝
❤ አምላከ ቅዱሳን ልዑል እግዚአብሔር ጾሙን፣ ጸሎቱንና ምሕላውን ተቀብሎ በአዲሱ ዓመት በዘመነ ቅዱስ ማርቆስ በአገራችን ኢትዮጵያዊ ያለውን የእርስ በእርስ ጦርነት አስወግዶ ሰላም፣ ፍቅርን፣ አድነትንና መተሳሰብን ይላክል፤ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን በቅዱስ ሲኖዶስ በአባቶችን ዘንድ ያለው መከፍፈል አስወግዶ አንድ ያድርግልን። መልካም የጾም፣ የጸሎትና የምሕላ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #የተባረከ_የጳጒሜን_ወር_ባተ።
❤ #ጳጒሜን ፩ (1) ቀን።
❤ እንኳን #ለወንጌላዊው_ለቅዱስ_ዮሐንስ ረድእ #ለሐዋርያውና_ለሰማዕቱ_ለከበረ_ቅዱስ_ዑቲኮስ ለዕረፍት በዓል፣ #ለአባ_ሖር_ወንድም ለሰማዕቱ #ለቀሲስ_ቅዱስ_አባ_ብሶይ_ለዕረፍት በዓል አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከከበሩ #ከአባ_ጳኩሚስና_ከአባ_ሰራብዮን ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #በዚች_ቀን_መጥምቀ_መለኮት_ቅዱስ_ዮሐንስ ሄሮድስን የወንድምህን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ማግባት የለብህም ብሎ ይገስጸው ስለነበር በሳምንቱ በልደቱ ቀን መስከረም 2 እስኪገለው በዛሬው ዕለት ወደ እስር ቤት ያስገባበት ነው።
✝ ✝ ✝
❤ #የሐዋርያው_የቅዱስ_ዮሐንስ_ረድእ_ቅዱስ_ዑቲኮስ፦ ይህም ቅዱስ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስን ሲያገለግለውና ሲታዘዘው ኖረ። ከዚያም ከሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ጋራ ሔደ እርሱም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲሰብክ አዘዘው በአረማውያንና በዮናናውያንም መካከል ሰበከ። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ወደማወቅ ብዙዎችን መለሳቸው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው።
❤ የጣዖታት ቤቶችን አፍርሶ አብያተ ክርስቲያናትን ሠራ። ከሀድያንም ብዙ መከራ ደረሰበት መታሠርና ብዙ ቀኖች ግርፋቶችን በመቀበል የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ እሥር ቤት ከምግብ ጋር መጥቶ ይመግበዋል።
❤ ከዚህም በኋላ ከእሳት ውስጥ ጣሉት እሳቱም ከቶ አልነካውም ሁለተኛም ለአንበሶች ጣሉት እነርሱም እንደ በጎች ሆኑለት።
❤ ከዚህም በኋላ ወደ ቊስጥንጥንያ አገር ሔደ ሲሔድም የእግዚአብሔር መልአክ ይመራውና ያጸናናው ነበር ተጋድሎውንም ፈጽሞ በበጎ ሽምግልና ጳጉሜን 1 ቀን ወደ እግዚአብሔር ሔደ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ቅዱስ ዑቱኮስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #የአባ_ሖር_ወንድም_ቀሲስ_ቅዱስ_ብሶይ፦ ይህም ቅዱስ ከአንጾኪያ አገር ክብር ካላቸው ወገኖች ውስጥ ነው ስለ ዕውቀቱና ስለ ሃይማኖቱ ጽናት ቅስና ተሾመ።
❤ ወንድሙ አባ ሖርና እናቱ ወደ ግብጽ አገር ሒደው በሰማዕትነት ከሞቱ በኋላ እርሱም ተነሥቶ ወደ እስክንድርያ ሥጋቸውን ያይ ዘንድ ሔደ። ገንዘቡን ሁሉ ለድኆች ሰጠ ከሦስት እንጀራና ከሚመረጐዛት ከአንዲት የሰኔል በትር በቀር ምንም አልያዘም ነበር።
❤ ወደ እስክንድርያ አገርም በደረሰ ጊዜ የዘመዶቹ በድን ወዳለበት ሰዎች መርተው አደረሱት የእናቱንና የወንድሙንም ሥጋ በአየ ጊዜ ከእርሳቸው ስለ መለየቱ መሪር ልቅሶን አለቀሰ።
❤ ከዚህም በኋላ ወደ መነኰንኑ ሒዶ በፊቱ ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ። ለመኰንኑም የአባ ሖር ወንድም እንደሆነ ነገሩት መኰንኑም ታላቅ የደንጊያ ምሰሶ በሆዱ ላይ እንዲአቆሙበት አዘዘ ይህንንም በአደረጉበት ጊዜ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጠ።
❤ ከዚህም በኋላ ደግሞ ሥጋውን ከወንድሙና ከእናቱ ሥጋ ደግሞ ቊጥራቸው ሰማንያ ስምንት ከሆነ ከሌሎች ሰማዕታት ሥጋ ጋር በአንድነት ያቃጥሉ ዘንድ መኰንኑ አዘዘ ወደ እሳት በጨመሩአቸውም ጊዜ ከቶ እሳቱ አልነካቸውም።
❤ ምዕመናን ሰዎችም መጥተው የከበሩ የአባ ሖርና የወንድሙ የአባ ብሶይን የእናታቸውንም ሥጋ ወሰዱ። አገርዋ ዲብቅያ የሚባል የቅድስት ዳሞንንም ሥጋ አገሩ በረሞን ከሚባል የቅዱስ ቢማኮስም ሥጋ ጡልያ ከሚባል አገር የመጣ የውርሱኑፋን ሥጋም አብስላሲ ወደሚባል አገር እስከሚያደርሷቸው በመርከብ ጫኗቸው። የስደቱ ወራት እስከሚፈጸም አክብረው ወስደው በመልካም ቦታ አኖሩዋቸው።
❤ ከዚህም በኋላ አብያተ ክርስቲያን ተሠርቶላቸው ሥጋቸውን በውስጣቸው አኖሩ ከእርሳቸውም ተአምራት ተገለጡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆኑ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጳጕሜን 1 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለዑቲኮስ_ዘተሰምየ_ሱታፎ። ለወንጌላዊ ዮሐንስ ለንጹሐ መላእክት ዘተዐጽፎ። መኰንን ዕልው አመ ውስተ እሳት ገደፎ። ካዕበኒ እምህየ ለአናብስት አኅለፎ። በአናብስት ስእኑ ይግሥሥዎ ወእሳት ይልክፎ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የጳጒሜን_1።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "እስመ ጽድቀ ወምጽዋተ ያበድር እግዚአብሔር። እግዚአብሔር ይሁብ ክብረ ወሞገሰ። እግዚአብሔር ኢያስተፄንሶሙ እምበረከቱ ለእለ የሐውሩ በየዋሃት"። መዝ 83፥11። የሚነበቡት መልዕክታት ፊል 1፥12-25፣ 1ኛ ዮሐ 5፥1-6 እና የሐዋ ሥራ 18፥21-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 14፥1-7። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችን ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ነሐሴ ፴ (30) ቀን።
❤ እንኳን #ከዐሥራ_ሁለቱ_ደቂቀ_ነቢያት አንዱ ለሆነው ለታላቁ ነቢይ #ለቅዱስ_ሚልክያስ_ለዕረፍት በዓል፣ #ጌታችን በባሕር ውስጥ በሊቀ ሐመር አምሳል ለሐዋርያው #ቅዱስ_እንድርያስ_ለተገለጠለትና ድንቅ ተአምር ላደረገበት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ ከሀገረ ፈርማ ኤጲስቆጶስ #ከአባ_ሙሴ_ዕረፍት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #ነቢዩ_ቅዱስ_ሚልክያስ፦ ይህም ነቢይ የእስራኤል ልጆች ከተሰደዱበት ከባቢሎን ሀገር በተመለሱ ጊዜ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፋቸው ገሥጿቸዋል።
❤ ሁለተኛም ነቋር ስለሆነ መሥዋዕት ስለ አሥራትና በኵራት ገሥጿቸዋል። በዚህ ነቢይ አንደበት እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሯልና "ርኅራኄ አድርጋችሁ ምጽዋትን መጽውቱ፣ ዐሥራቴንና በኵራቴንም አስገቡና እስቲ ፈትኑኝ እኔ ከሰማይ ዝናሙን ባላወርድላችሁ በረከትንም አስቲበቃችሁ ባልጨምርላችሁ የምድራችሁንም ፍሬ ነቀዝና መሰክ እንዳይበሉት እከለክላለሁ"።
❤ ዳግመኛም ከክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ አስቀድሞ መጥምቁ ዮሐንስ ስለ መምጣቱ ስለ ነቢዩ ኤልያስም ተናገረ። ደግሞ ስለ አይሁድ የሥርዓተ ክህነት ፍጻሜ ተናገረ በአሕዛብም አገር ውስጥ ለእግዚአብሔር የሚቀበላቸውን መሥዋዕት የሚያሳርጉ ዕውነተኞች ንጹሐን ካህናት እንዳሉ ገለጠላቸው።
❤ በበጎ ተጋድሎውም እግዚአብሔርን ከአገለገለ በኋላ ከዚህ ዓለም በመፍለስ በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በነቢዩ ቅዱስ ሚልክያስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ነሐሴ ፴ (30) ቀን።
❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊቷ_ጻድቅ ጌታችን በዕለተ አርብ የጠጣው መራራ ሐሞት በማሰብ #በቅል_ውስጥ_የሚገኘውን_መራራ_ፍሬ_ከኮሶ ጋር #በአንድነት_ደርጣ (አዋህዳ) ትመመገብ ለነበረች ለታላቋ እናት #ለቅድስት_ዜና_ማርያም_ለዕረፍቷ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #ጻድቋ_ቅድስት_ዜና_ማርያም፦ ከአባቷ ከቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ከእናቷ ከቅድስት አመተ ማርያም በ11 መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት በምድ ነጋሲ በጎጃም ምድር ግንቦት 30 ቀን የተወለደች ሲሆን ለአቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ በንፅህ ድንግልና በምድረ ሂንፍራንስ ጣራ ገዳም አካባቢ በሚገኘው በአቡነ እንድርያስ ዋሻ ለ25 ዓመት በጾም በፀሎት ምንም አይነት የላመ የጣፈጠ እህል ሳትቀምስ በቅል ውስጥ የሚገኘውን መራራ ፍሬ ከኮሶ ጋር በአንድነት ደርጣ (አዋህዳ) በመዘፍዘፍ ከ3 ቀን በኃላ በመመገብ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ አደባባይ ላይ የቀመሰውን መራራ ሐሞትን በማሰብ ሙሉ ሕይወቶን እየተመገበች ታላቅ ተጋድሎዋን ፈፅማለች፡፡ ከዚህ የተነሳ ሸክላ ማርያም ተብላ ትጠራ የነበረችው ቦታ ስያሜ ተቀይሮ ደሪጣ ዜና ማርያም ዋሻ ተብሎ እስከ አሁን ድረስ በስሞ እየተጠራ ይገኛል፡፡
❤ ከአቡነ እድርያስ ዋሻ በመቀጠል ከአዲስ አበባ ተነስተን ስንጓዝ አዲስ ዘመን ከተማ በስተቀኝ በኩል ተገንጥለን 15 ኪሜ ያክል የጥርጊያ መንገድ እንደተጓዝን በስሟ የተሰየመውን ደሪጣ ጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም ገዳም ላይ ቀሪ ሕይወቶን ምንም አይነት ዋሻ ባልነበረበት በከፍተኛ ተራራ ላይ እጅግ አስቸጋሪ ቀዝቃዛ አየር ባለበት ብርዱን፣ ፀሐዩን፣ ቁሩን፣ ረኃቡንና ጥሙን በመቋቋም ራቁቶን በመሆን መራራ ምግቦችን አዋህዳ በመመገብ በጾም በፀሎት በመትጋት አስቸጋሪ የሆነውን ተጋድሎዋን በመፈፀም በዚሁ በተቀደሰ ስፍራ ነሐሴ 30 ቀን በታላቅ ክብር አርፋለች፡፡
❤ በዚህም ወቅት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያምና ከእልፍ አላፋት ቅዱሳ መላዕክት ጋር እንዲሁም ከሐዋርያት ፣ ከሰማዕታት ፣ ከጻድቃን ፣ ከደናግል ጋር በመሆን ከሰማይ በመውረድ በታላቅ ክብር ዕረፍቷን አክብሮላታል ታላቅ ኪዳንም ገብቶላታል፡፡
❤ በዚሁ በተቀደሰ ስፍራ ላይ ወይንም በአሁኑ ሰዓት መቃብሯ በሚገኝበት ዋሻ ቤተመቅደስ አካባቢ በተጋድሎዋ ጊዜ ራቁቷን በሆነች ሰዓት መላ ገላዋን የሸፈነላት ፀጉር በእየ ዛፎቹ ላይ እስከ አሁን ድረስ አለ፡፡ ይህም የጸጉር አምሳያ ከገዳሙ በመውሰድ ብዙ ሰዎች በቤታቸው በመታጠን ከአስም እንዲሁም ከተለያዩ በሽታዎች እየተፈወሱና እየዳኑ ሲሆን ታላላቅ ታምራትን እያደረገ ይገኛል፡፡
❤ በዚህ ገዳም ከሌሎች ገዳማት ለየት የሚያደርገው ታሪክ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ በመውረድ ራሱ የባረከው ልዩ ታሪክ ያለው ጠበል የሚገኝ ሲሆን ይህም ጠበል በቦታው ላይ ሆኖ የተጠመቀ ፣ የጠጣ ፣ አልያም በአለበት ቦታ ሆኖ የተጠቀመ እስከ አሁን ድረስ መካን የሆኑ ሰዎች በፍጥነት ልጅ የሚያገኙ ከመሆናቸው ባሻገር ከማንኛውም ከተለያዩ በሽታዎች በመፈወስ ታላላቅ ታምራትን እየሰራ ይገኛል፡፡
❤ በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱስ ላሊበላ በጌታችን በአምላካችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ መሰረት ወደዚሁ ታላቅ ስፍራ በመምጣት የጻድቋ ማረፈያ መታሰቢያ ዋሻ ቤተ መቅደስ በመፈልፈል የሰራላት ሲሆን በመቀጠል አፄ ይስሐቅ በ14ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይህን ገዳም በስሟ በመገደም በዚሁ ዋሻ ውስጥም የጻድቋ የቅድስት ዜና ማርያም መቃብሯ እንዲሁም የመታሰቢያዋ ፅላት የሚገኝ ከመሆኑ አንጻር በአካባቢው ያሉት ሕዝበ ክርስትያን ከካህናት ጋር በመሆን ሥርዓተ አምልኮ በመፈፀም እየተገለገሉበት ይገኛሉ፡፡
❤ ይህ ዋሻም አስቀድሞ ሦስቱ ቅዱሳን ማለትም አቡነ እንድርያስ ዘጣራ ገዳም ፣አቡነ ተክለኃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ፣ ጻድቋ ቅድስት ዜናማርያም ዘደሪጣ ውስጥ ለውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት በፀጋ እግዚአብሔር ይገናኙበት የነበረ ሲሆን በአሁን ሰዓትም እግዚአብሔር የመረጣቸው ቅዱሳን ይመላለሱበታል፡፡
❤ ለጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም የተሰጠ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር አምላክ መርጦና ፈቅዶ በጻድቋ አማላጅነት ካለበት ስፍራ ተነስቶ የጻድቋ ደጃን የረገጠ ለ3 ግመል ጭነት ጤፍ ወይም የሦስት አህያ ጤፍ ያህል ነፍሳትን እምርልሻለሁ፤ ከሲዖልም እሳት ነፍሳትን አወጣልሻለሁ የሚል ቃል ኪዳን ለጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም ተሰቶታል። ከእናታችን ቅድስት ዜና ማርያም ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቷም ይማረን!። ምንጭ፦ ማኅበረ ቅድስት ዜማ ማርያም ካዘጋጁት በራሪ ወረቀት የተወረደ።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ነሐሴ ፳፯ (27) ቀን።
❤ እንኳን #ከሰባቱ_ሊቃነ_መላእክት_አራተኛ ለሆነው ለመላእክት አለቃ #ለቅዱስ_ሱርያል ለበዓሉ መታሰቢያ፣ ለአባቶቻችን #ለዐሥራ_ሁለቱ_ለቅዱስ_ያዕቆብ_ልጆች ለመታሰቢያቸው በዓል፣ በሊቀ ካህናት ኤሊ ዘመን #ለነቢዩ_ቅዱስ_ሳሙኤል_ለመጠራቱ ለመታሰቢያው በዓልና ሰብሲር ከሚባል አገር ለሆነ #ለቅዱስ_ብንያሚንና_ለእኅቱ_ለቅዱስ_አውዶክስያ ሰማዕትነ ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። በጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከእሰክድርያው_ቅዱስ_ፊቅጦርና #ከእናቱ_ሣራ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #የነገደ_ሥልጣናት_አለቃ_ቅዱስ_ሱርያል፦ ያላቸው ከኤረር መኻከል በኹለተኛዋ በራማ ውስጥ ከሚኖሩት፡፡ ከ፴ው ነገድ ውስጥ ሲኾኑ፤ ስለነዚኽ ነገደ መላዕክት ሊቁ ኤጲፋንዮስ በአክሲማሮስ ላይ ሲገልጽ "ወለሣልስ ጾታ ዐሠርቱ ስሞሙ ሥልጣናት ወሊቆሙ ሱርያል መልአክ ወአንበሮሙ በሣልስ ሰማይ እሉ እሙንቱ እለ ይጸውሩ አብዋቀ ብርሃን ወያደምፁ ለመላእክት በጊዜ ቅዳሴሁ ወስባሔሁ ለእግዚአብሔር ለዘክሮቱ ይደሉ ሰጊድ" ይላል ለስም አጠራሩ ስግደት ይግባውና ልዑል እግዚአብሔር ሦስተኛ ዐሥሩን ነገድ ሥልጣናት ሲላቸው አለቃቸው መልአኩ ሱርያል ይባላል፤ እነዚኽም የብርሃን ነጋሪት የሚይዙ ሲኾኑ መላእክትን በስባሔ ሲያነቁ ሲያተጉ የሚኖሩ እነዚኽ መላእክት ሲኾኑ፤ በራማ በሦስተኘው ከተማ አስፍሯቸዋል። ምንጭ፦ ዶክተር ሮዳስ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ተአምኆ ቅዱሳን በተረጎመበት ላይ።
✝ ✝ ✝
❤ በዚችም ቀን ዳግመኛ አባቶቻችን #ዐሥራ_ሁለቱን_የያዕቆብን_ልጆች_ያስቧቸዋል። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ በዚችም ቀን #በሊቀ_ካህናት_ኤሊ_ዘመን #ነቢይ_ቅዱስ_ሳሙኤል ለመጠራቱ መታሰቢያ ሆነ። ይህንንም ነቢይ ተኝቶ ሳለ እግዚአብሔር ጠራው በኤሊም ፈንታ ነቢይና ካህን አድርጎ ለእስራኤል ልጆች ሾመው። የነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #ሰማዕታት_ቅዱስ_ብንያሚንና_እህቱ #ቅድስት_አውዶከስያ፦ የእነዚህም ቅዱሳን ወላጆቻቸው እንግዳና መጻተኛን የሚወዱ ደጎች ክርስቲያኖች ናቸው ደግሞ ለክርስቲያኖች በሚገባ በበጎ ሥራ ሁሉ የተጠመዱ ቅድስና ያላቸው ናቸው። እሊህንም ቅዱሳን በወለዱዋቸውና በአሳደጓቸው ጊዜ ክርስቲያናዊት ትምህርትን አስተማሩአቸው።
❤ ከዚህም በኋላ ወደዚያች አገር ከሀዲ መኰንን መጣ ቅዱስ ብንያሚንም በሰማ ጊዜ የክብር ባለቤት ስለሆነ ክርስቶስ ደሙን ያፈስ ዘንድ ወደደ። በመኰንኑም ፊት ቁሞ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ ጽኑ የሆነ ሥቃይንም አሠቃይቶ ከዚያ በኋላ አሠረው። ወላጆቹና እኅቱ በሰሙ ጊዜ ወደርሱ መጡ አለቀሱ እጅግም አዘኑ እርሱም "የዚህ ዓለም ኑሮ እንደ ጥላ ፈጥኖ ያልፋል የወዲያኛው ኑሮ ግን ፍጻሜ የለውም" እያለ ያጽናናቸው ጀመረ።
❤ እኅቱ አውዶክስያም ይህን መልካም ትምህርቱን ከወንድሟ ሰምታ "ወንድሜ ሆይ ካንተ እንዳልለይ እግዚአብሔር ሕያው ነው አንተ የምትሞተውንም ሞት እኔም ከአንተ ጋራ እሞታለሁ" አለችው። ይህንንም ብላ ወደ መኰንኑ ሒዳ በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመኰንኑ ፊት ታመነች መኰንኑም ያሠቃያት ጀመረ። ከዚህ በኋላም ያለ መብልና ያለ መጠጥ በጨለማ ቤት ሃያ ቀን ከወንድሟ ጋር አሥረው እንዲያኖሩዋት አዘዘ።
❤ ከዚህም በኋላ ከዚያ አውጥቶ ከባድ የሆኑ ደንጊያዎችን በአንገታቸው አንጠልጥሎ ከጥልቅ ባሕር ጣላቸው የእግዚአብሔር መልአክም ወርዶ ከአንገታቸው ደንጊያዎቹን ፈታላቸው እነርሱም ከወደብ እስቲደርሱ በባሕሩ ላይ ዋኝተው ብጥራ ከምትባል ቦታ ደረሱ አንዲት ብላቴና ድንግልም አግኝታቸው ስባ አወጣቻቸው።
❤ ያን ጊዜም ወደ መኰንኑ ሔደው እርሱንና የረከሱ አማልክቶቹን ረገሙ ብዙ ቀኖችም ጭንቅ የሆነ ሥቃይን አሠቃያቸው። ሥቃያቸውም በአደከመው ጊዜ ራሳቸውን በሰይፍ እንዲቆርጧቸው አዘዘና ቆረጡአቸው። የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕታት ቅዱስ ብንያሚንና በእህቱ ቅድስት አውዶከስያ በጸሎታቸው ይማረን። በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 27 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለከ_ብንያሚን_ሰማዕት። ምቱረ ክሣድ በመጥባሕት። ወእለእኅትከ #ሰላም_አውዶክስያ_ኅሪት። እንዘ ትብል ሰሚዓ ዘትቤ ከመ ጽላሎት ንብረት። በትምህርትከ አጥባዕካ ለሞት"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የነሐሴ_27።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወሳሙኤልኒ ምስለ እለ ይጼውዑ ስሙ። ይጼውዕዎ ለእግዚአብሔር ውእቱኒ ይሰጠዎሙ። ወይትናገሮሙ በዐምደ ደመና"። መዝ 98፥6-7። የሚነበቡት መልዕታት ዕብ 5፥1-10፣ 1ኛ ጴጥ 3፥14-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 3፥17-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 12፥26-31። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ቅዳሴ ነው። መልካም የመልአኩ የቅዱስ ሱርያል በዓልና የአቡነ ዘርዐ ቡሩክ የልደት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
ክርስቲያን ቀን ቀን ሕዝቡን ሲያስተምሩ በመዋል ሲመሽ ወደ ሐይቁ በመግባት ሲጸልዩ ያድሩ ነበር፡፡ በሐይቅ እስጢፋኖስና በዙርያው ለነበሩ አበው ማታ ማታ አንድ ብርሃን ወደ ሐይቁ ሲገባ ጠዋት ጠዋትም ሲወጣ ይታያቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን በገዳሙ አባቶች ልመናና በልዑል እግዚአብሔር ትዕዛዝ ወደ ሐይቅ ገዳም ገብተው አበምኔት ሆኑ፡፡
❤ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከደሴ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ሲሆን የመሠረቱት ካልዕ ሰላማ የተባሉ ግብፃዊ ጻድቅ ናቸው፡፡ ሐይቅን አባ ሰላማ ካልዕና ዐፄ ድል ነአድ በ862 ዓ.ም ነው የቆረቆሩት። ገዳሙን ካቀኑት በኋላ "የማንን ታቦት እናስገባ?" ብለው ሲያስቡ ቶራ የምትባል እንስሳ ጭነት ተጭና ከመካከላቸው ተገኘች፤ ጭነቱን አውርደው ቢያዩት በሐር ጨርቅ የተጠቀለለ የቅዱስ እስጢፋኖስንና የቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለት ታቦት አገኙ፡፡ በላዩም ላይ "ይህንን ታቦት በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የተሰወሩ ቅዱሳን ከእግዚአብሔር ታዘው የላኩት ነው" የሚል ጽሑፍ አገኙ፡፡ ይህ ከሆነ ከ 400 ዘመን በኋላ ነው አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ወደዚህ ቦታ የመጡት፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ለ52 ዓመት ቀን ቀን መንፈሳዊ ሥራቸውን እየሠሩ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ቆመው ሲጸልዩ ያድራሉ፡፡
❤ አባ ኢየሱስ ሞዐ በሐይቅ እስጢፋኖስ በአበ ምኔትነት በቆዩባቸው 45 ዓመታት ከየገዳማቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመገልበጥና በማሰባሰብ የመጀመርያው ዘመናዊ የቤተ ክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ በዚሁ ገዳም ውስጥ የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ቋሚ ትምህርት ቤት በማቋቋም 800 መነኰሳትን በትምህርተ ሃይማኖት አሠልጥነው በንቡረ ዕድነት ማዕረግ ሾመው በመላ ሀገራችን እንዲሠማሩ አድርገዋቸዋል፡፡ ከእነዚህም ተማሪዎቻቸው መካከል አቡነ ተክለ ሃይማኖት (ደብረ ሊባኖስ)፣ አቡነ ኂሩተ አምላክ (ጣና ሐይቅ ዳጋ እስጢፋኖስ)፣ አቡነ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ቦረና)፣ አባ በጸሎተ ሚካኤል (ቦረና)፣ አቡነ ገብረ እንድርያስ (ቦረና)፣ አቡነ ሕዝቅያስ (ቦረና)፣ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ዳውንት)፣ አቡነ አሮን (መቄት)፣ አቡነ ተክለ ኢየሱስ ሞዐ (ሐይቅ)፣ አቡነ አላኒቆስ (ትግራይ)፣ አቡነ በግዑ (ሐይቅ)፣ አቡነ ሠረቀ ብርሃን (ሐይቅ)፣ አቡነ ብስጣውሮስ (ሐይቅ)፣ አቡነ ዮሴፍ (ላስታ) ዋና ዋናዎቹና በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ጻደቁን ንጉሥ ዐፄ ይኩኖ አምላክንም በትምህርተ ሃይማኖት አንጸውና ኮትኩተው ያሳደጉት ጻድቁ አባታችን ናቸው፡፡
❤ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ መጥተው በሐይቁ ዳር ቆመው ሳለ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ በእግሩ በውኃው ላይ እየሄደ እያሳያቸው ተከትለውት እንዲሄዱ ነገራቸው። አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ሐይቁን በእግራቸው ጠቅጥቀው ተራምደው ተሻግረው አቡነ ኢየሱስ ሞዐን አገኟቸው፡፡ እርሳቸውም አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ እርሳቸው እየመጡ እንደሆነ በመንፈስ ዐውቀው ነበርና ሲያገኟቸው በጣም ተደስተው ከተቀበሏቸው በኋላ አመነኵሰዋቸዋል፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ እጅግ በጣም ብዙ መነኰሳትን አፍርተዋል፡፡ የመጀመሪያው መነኩሴ አባ እንጦንስ ነው፡፡ እንጦንስ መቃርስን፣ መቃርስ ጳኵሚስን፣ ጳኵሚስ ቴዎድሮስን፣ አቡነ አረጋዊንና 8ቱን ቅዱሳን አመነኰሱ፡፡ አቡነ አረጋዊም ወደ ኢትዮጵያ በ460 ዓ.ም መጥተው ክርስቶስ ቤዛን፣ አባ ክርስቶስ ቤዛም መስቀለ ሞዐን፣ መስቀለ ሞዐም አባ ዮሐኒን፣ አባ ዮሐኒም አባ ኢየሱስ ሞዐን፣ አባ ኢየሱም ሞዐም አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አመነኰሱ፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ምን ያህል ቀደምትና ባለ ታሪክ አባት እንደሆኑ ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡
❤ በዮዲት ጉዲት እጅጉን ተጐድታ የነበረችው አገራችን ዳግም የወንጌሉ ብርሃን እንዲበራባት ሊቃውንት፣ እንዳይታጡባት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳይቆነጻጸሉ፣ መነኰሳት አባቶች ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ወርደው ገዳማትን እንዲያስፋፉ ያደረጉት አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለአገራችን ትልቅ ባለውለታ ናቸው፡፡ በተለይም በሐይቅ እስጢፋኖስ ያፈሯቸውን 800 ሊቃውንት መነኰሳት በመላዋ ኢትዮጵያ በመሰማራታቸው ዛሬ የምናያቸውን አብዛኛዎቹን ገዳማትና ቅዱሳት መጻሕፍት አቆይተውልናል፡፡ አባታችን ለ45 ዓመታት ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምን በአበ ምኔትነት እያስተዳደሩ ከቆዩ በኋላ ኅዳር 26 ቀን 1292 ዓ.ም በዕለተ እሑድ ዐርፈዋል፡፡ ከአባታች ከአቡነ ኢየሱስ ሞዐ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ።
