ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ
Відкрити в Telegram
ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።
Показати більше611
Підписники
Немає даних24 години
-17 днів
-930 днів
Архів дописів
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ነሐሴ ፳፮ (26) ቀን።
❤ እንኳን #ለኢትዮጲያውያኑ_ጻድቃን ለአባታችን #ለአቡነ_ሀብተ_ማርያምና ታላቁ ገዳም ሐይቅ እስጢፋኖስ ላቀኑ #ለአቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ ለጽንሰታቸው ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል በዓል በሰላም አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #አቡነ_ሀብተ_ማርያም_ጽንሰት፦ " የኢትዮጵያ ንጉሥ እስክንድር በነገሠ በሺህ አራት መቶ ሰማንያ ስድስት ዓመተ ምሕረት ቅዱስ ፍሬ ብሩክ የሚባል አንድ ሰው በዚያች ሀገር ውስጥ ነበር፤ ይኸውም ከከበሩም ሰዎች ተለይቶ ብዙ ገንዘብ ያለው ባለ ጸጋ ነበር። በሕጋዊው ጋብቻ ስሟ ቅድስት ዮስቴና የምትባል ሴት አገባ፤ ይኽችውም ሴት በደግ ሥራ ሁሉ የተሸለመች ያጌጠች ነበረች።
❤ ብዙ ደግቷንና ትሩፋቷን ኋላ እንነግራችኋለን፤ ነገር ግን አስቀድመን በዚህ ዓለም ከሕጋዊ ባሏ ጋር በንጽሕ ጋብቻ እግዚአብሔር በመፍራት ምጽዋትን በመስጠት የውሃትንና ትሕትናን ገንዘብ አድርጋ በትግሥት በበጎ ሥነ ምግባር ሁሉ ጸንታ እንደኖረች እነግራችኋለን።
❤ እንዲህ ባለ ሥራ ሳለች መንፈሳዊ ሐሳብ እንዲህ ሲል ተነሳባት፤ "ለአንቺ በዚህ ዓለም መኖር ምን ይረባሻል የሚል መጣባት፤ ዛሬ የሚያልፍ የሚጠፋ ነውና፤ ጌትነቱ የሚመሰገንበት ለዘለዓለም የሚኖር የማያልፍ ሌላ ዓለም ይገለጣልና"፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል "ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ቢነዳ በነፍሱ ከተጎዳ ምን ይጠቅመዋል ምን ይረባዋል" እንዳለ።
❤ "ለአንቺ ግን በሰማይ ጸንቶ መኖርና ሁለተኛዋን ሀገር መያዝ ይሻላል" የሚል ሐሳብ መጣባት፤ ይህን ካሰበች በኋላ ፈጥና ተነሥታ በሌሊት ከቤቷ ወጥታ፤ በሀገሯ አንጻር ትይዩ ወደ ሆነው በረሃ ሄደች፣ በውስጡ ከሰው ወገን የማይኖርበት ቦታ መካከሉ ምድረ በዳ ወደ ሆነው በረሃ ደረሰች። ከጅቦች፣ ከነብሮች፣ ከዓሣሞች፣ ከጦጦችና ከዝንጆሮች በስተቀር ምንም ምን የማይኖርበት በረሃ ነበር።
❤ በዚያችም ቦታ ደጃፏ ያልተዘጋች ትንሽ ዋሻ አገኘች ምንም ምንም ሳትናገር ከዋሻው ውስጥ ገባች። በዋሻው ውስጥ ቁሞ በትጋት መዝሙረ ዳዊትን በአንክሮ በተደሞ የሚደግም ክቡር ባሕታዊን አየች፤ ባየችውም ጊዜ ደነገጠች። እርሱም ሴቲቱን ባያት ጊዜ ፍርሃት መንቀጥቀጥ በላዩ ላይ ወረደበት፣ በመስቀል ምልክትን አማተበ። ይህም ቅዱስ ባሕታዊ ፊቱን በአማተበና ስመ እግዚአብሔርንም በጠራ ጊዜ እንዳልሸሸች ስለአየ ይህች ሴት ክርስቲያን መሆኗን አወቀ።
❤ መጀመሪያ ስትገባ የጋኔን ምትሐት መስላው ነበርና፤ ሰው መሆኗን ባወቀና በተረዳ ጊዜ ተቆጣት። "አንቺ ዘማዊት ሴት ምንኵስናየን ታፈርሽ ዘንድ ከየት መጣሽ" አላት። "ወይም ደግሞ ሰይጣን በልብሽ ገብቷልን"። "ጌታዬ እኔስ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ነኝ እንጅ አንተ እንደምትለኝ ዘማዊት አይደለሁም" አለችው። "ነገር ግን ቤቴን ንብረቴን ያለኝን ትቼ መጥቻለሁ፣ በዓለም ውስጥ ያለውን ሁሉ ንቄ እመንን ዘንድ እወዳለሁና ስለዚህም ወደዚህ ምድር በዳ መጣሁ። በዚህም ገዳም ወይም በረሃ ሰው እንዳለ አላውቅሁም ነበር፤ ሰውን የሚባሉ አራዊት ብቻ የሚኖሩበት ይመስለኝ ነበር" አለችው።
❤ ይህም ባሕታዊ በትሕትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ይህን የሚያስደንቅ መልካም መልስ በመለሰችለት ጊዜ። አንድ ሰዓት ያኽል ካሰበ በኋላ "በፍቅር አንድነት ወደ ቤትሽ ተመለሽ" ብሎ በሰላም ተናገራት። እርሷም "ወደዚህ ቦታ ዳግመኛ አልመጣም እንጅ ካንተ ዘንድ ተለይቼ እሄዳለሁ። ነገር ግን ወደ ቤቴ ተመልሼ አልሄድም። ከገዳማት በአንድ ቦታ መንኵሼ መኖር እወዳለሁ እንጅ" አለችው። ጌታ "በወንጌል እርፍን በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚያርስ የለም" እንዳለ ወደ ዓለም አልመለስም" አለችው።
❤ ያም ባሕታዊ "ምንኵስናስ የለሽም አልታዘዘልሽም፤ ነገር ግን በሰላም ወደ ቤትሽ ወደ ሕጋዊ ባልሽ ተመለሽ። የተፈቀደልሽንስ እነግርሻለሁ ከሕጋዊ ባለቤትሽ ወንድ ልጅን ትወልጃለሽ እርሱም ለዓለም ሁሉ የሚጠቅም ይሆናል። የገድሉና የትሩፋቱ ዜና እስከ ዓለም ዳርቻ ይደርሳል፤ በሕይወተ ሥጋ ሳለ በፈጣሪው በእግዚአብሔር ፈቃድ የብዙዎቹን ሰዎች ነፍሳት ከሲኦል ያወጣል። እንደ መላእክትም ክንፈ ጸጋ ተሰጥቶታል። በሰው አካል በሥጋ ሁኖ ሳለ በተመሥጦ ወደ ሰማይ ወጥቶ የሥላሴን የአንድነትን የሦስትነት ምሥጢር ያያል"።
❤ ቅድስት ዮስቴናም ከአረጋዊ ባሕታዊ ይህን ነገር ሰምታ አደነቀች፤ "የፈጣሪየ ፈቃድ ከሆነ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ" አለች፤ ይህን ብላ ተመልሳ ወደ አገሯ ወደ ቤቷ ገባች፤ ቤተሰቦቿም መውጣቷንም መግባቷንም ምንም አላወቁባትም፤ ከዚያም በነሐሴ 26 ቀን ጸነሰች። ከዘጠኝ ወራትም ከቆየች በኋላ፤ መልኩ እንደ በረዶ ነጭ እንደ ጽጌ ረዳም ብሩህ ቀይ የሆነ መልከ መልካም ልጅ ወለደች ሁለተናውም ጨረቃ የጉለቱ ምልዓት 15 ሌሊት ሁኖ በብሩህ ብርሃን በምልዓት በሚያድርበት ጊዜ እንደሚያበራው መልካም ብርሃን ገጹ ብሩህ የሆነ ልጅ ወለደች፤ ይህ ሕፃን በግንቦት ወር በ 26 በተወለደ ጊዜ በአባቱና በእናቱ ቤት ታላቅ ደስታን ሆነ፤ ሜሉን ገቹን አርደው ዘመዶቻቸውን ጎረቤቶቻቸውን አማቾቻቸውን ምርዓቶቻቸውን ጠርተው ለበዓሉ እንደሚገባ መብሉንና መጠጡን ሰጥተው በሚገባ አጠገቡዋቸው፤ ...ካህኑም ተቀብሎ አጠመቀው ከአጠመቀውም በኋላ ለነፍሱ ዋስ (ለክርስትና አባቱ) አሳልፎ ሰጠው ስሙንም ሀብተ ማርያም ብሎ ሰየመው። ከአባታችን ከአቡነ ሀብተ ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ ገድለ አቡነ ሀብተ ማርያም።
✝ ✝ ✝
❤ #አቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ፦ አገራቸው ጎንደር ክፍለ ሀገር ስማዳ ወረዳ ሲና ዳኅና በሚባል ቦታ ነሐሴ 26 ቀን ተፀንሰው ግንቦት 26 ቀን 1210 ዓ.ም ከአባታቸው ከቅዱስ ዘክርስቶስና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ክብራ ተወለዱ፡፡ የተወለዱትም በቅዱስ ነአኲቶ ለአብ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡
❤ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የቆብ አባት ሲሆኑ ታላቁን ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገዳም የቆረቆሩ ደገኛ አባት ናቸው፡፡ ዕድሜያቸው 30 ዓመት እስከሚደርስ ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ትምህርተ ሃይማኖትንና ግብረ ገብን ሲማሩ ከቆዩ በኋላ በ1240 ዓ.ም ይህንን ዓለም በመተው ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገቡ፡፡ በደብረ ዳሞ ገዳም መነኰሳቱን እየረዱ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያጠኑ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየገለበጡ ለሰባት ዓመታት ከቆዩ በኋላ የደብረ ዳሞ 3ኛ አበ ምኔት ከሆኑት ከአባ ዮሐኒ እጅ ምንኲስናን በ1247 ዓ.ም ተቀበሉ፡፡
❤ አንድ ቀን ሌሊት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደርሳቸው መጥቶ "የስምህ መክበርያ ወደሆነው ሐይቅ ወደ ተባለው ሥፍራሂድ" አላቸው፡፡ አባታችንም "ቦታውን እንዴት ዐውቀዋለሁ?" በማለት መልአኩን ቢጠይቁት "ተነሥ! ጉዞህን ጀምር ቦታውን እኔ አሳይሃለሁ" አላቸው፡፡ አባ ኢየሱስ ሞዐ በመልአኩ እንደታዘዙት ከበዓታቸው ተነሥተው ተከተሉት፡፡ የብዙ ወራት መንገድ የሆነውን ጐዳናም በስድስት ሰዓት አደረሳቸው፡፡ በዚያን ወቅት ከሐይቅ ገዳም በስተ ሰሜን ወደነበረው የቅዱሳን ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ደረሱ፡፡ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ከመግባታቸው በፊት ለ 6 ወራት ያህል በቅዱሳን በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል፡፡ ያገለግሉበት በነበረው ቤተ
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ነሐሴ ፳፭ (25) ቀን።
❤ እንኳን #ለአባ_እንጦንስ_ደቀ_መዝሙር_ለሆነ ታላላቅ ተአምራቶችን ላደረገ ለታላቁ አባት #ለአባ_ቢጻርዮን_ለዕረፍት_በዓል፣ #ለቅዱስ_እንድርያኖስና_ሃያ_አራቱ_ባልንጀሮቹ ሰማዕታት ለዕረፍታቸው በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከኤልያኖስ_ከእኅቱ_አውዶክስያ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅዱስ_እንድርያኖስና_ሃያ_አራቱ_ባልንጀሮቹ ሰማዕታት፦ ይህም እንድርያኖስ ከመክስምያኖስ መኳንንቶች አንዱ ነበር እርሱም የጐልማሶች አለቃ ነበረ። ለጣዖት መስገድን እምቤ ስለአሉ ንጉሡ ምእምናንን ሲአሠቃያቸው ቅዱስ እንድርያኖስ የሰማዕታትን የልባቸውን ቆራጥነትና በመከራቸው ላይ መታገሣቸውን ተመልክቶ አደነቀ።
❤ እንዲህም አላቸው "ይህን ያህል ስትታገሡ ምን ታገኛላችሁ?" ቅዱሳን ሰማዕታትም "የሚጠብቀንን ተሰፋ ለመናገር አንደበታችን አይችልም" አሉት ስለ ዓለም ድኅነትም ክርስቶስ መከራ እንደ ተቀበለ ከብሉይና ከሐዲስ መጽሐፍ ነገሩት። እንድርያኖስም በሰማ ጊዜ ጽሕፈትን ወደ ሚያውቁ ብልሆች ሰዎች ሔደና "እኔ ከዛሬ ጀምሮ ክርስቲያን ነኝ ስሜን ከገድለኞቹ ጋራ ጻፉ" አላቸው።
❤ ለንጉሥ መክስምያኖስም እንዲህ እንዳለ በነገሩት ጊዜ ጠርቶ "እንድርያኖስ ሆይ አበድክን" አለው እንድርያኖስም "ከቀድሞው እብደቴ ተመለስኩ እንጂ እኔ አላበድኩም" ብሎ መለሰለት። ንጉሡም ሰምቶ ወደ ወህኒ ቤት ከንጹሐን ሰማዕታት ጋራ እንዲጨምሩት አዘዘ። ከአገልጋዮቹም አንዱ ሒዶ ለሚስቱ እንጣልያ ነገራት በሰማችም ጊዜ ደስ እያላት ወደ ወህኒ ቤት ሔደች ሃያ አራቱ ቅዱሳን ሰማዕታት የታሠሩበትን ማሠሪያቸውን ሳመች በሥቃዩ እንዲታገሥ የባሏን ልብ ያጽናኑ ዘንድ ለመነቻቸው። እርሱንም እንዲህ አለችው "ላህይህ ደምግባትህም ርስትህም ጥሪትህም አያስትህ ሁሉም ከንቱ ነውና ነገር ግን በእርሱ ዘንድ የማያልፍ መንግሥትን ትወርስ ዘንድ የክብር ንጉሥ ክርስቶስን ተከተለው" ይህንንም ብላ ወደቤቷ ገባች።
❤ ከዚህም በኃላ እንድርያኖስ ለፍርድ እንደ ሚአቀርቡት በአወቀ ጊዜ ሊሰናበታት ወደ ሚስቱ ሔደ መምጣቱንም ሰምታ የሸሸ መሰላት ደጇንም ዘግታ በውስጥ ሁና እንዲህ እያለች ዘለፈችው "ትላንት ሰማዕት ተብለኽ ዛሬ ክርስቶስን ካድከውን" እንድርያኖስም ሰምቶ የሃይማኖቷን ጽናት አደነቀ እንዲህም አላት "እኅቴ ሆይ እንድሰናበትሽ ክፈችልኝ" አላት። በሰማችም ጊዜ ከፈተችለት ከዚህም በኋላ ሁሉን እያነጋገራት እስከ እሥር ቤት ወሰዳት እንጣልያም ከዚያ በደረሰች ጊዜ የታሠሩትን ቅዱሳን ተሳለመቻቸው ቅስላቸውንም አጠበች።
❤ ከዚህም በኃላ ንጉሡ ቅዱሳኑን ከእሥር ቤት እንደአመጧቸው አዘዘ በመጡም ጊዜ ከሥቃይ ብዛት የተነሣ እንደደከሙ አያቸው። እንድርያኖስንም በፊቱ አቁሞ ለአማልክት ሠዋ አለው ቅዱሱም እርሱንና የረከሱ አማልክቶቹን ረገመ ንጉሡም የሆድ ዕቃው እስኪፈስስ ሆዱን እንዲደበድቡት አዘዘ በዚያን ጊዜም የእንድርያኖስ ዕድሜው ሃያ ስምንት ዓመት ነበር።
❤ ከዚህም በኃላ እንድርያኖስን ከባልንጀሮቹ ሰማዕታት ጋራ ወደ እሥር ቤት መለሱት እንጣልያም መጥታ የቅዱሳንን ደማቸውን ጠራረገችላቸው። እሊህ ቅዱሳንም እንድርያኖስን እንዲህ ብለው ተሳለሙት "እንድርያኖስ ሆይ ስምህ ተሳለሙት በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎአልና ደስ ይበልህ"።
❤ ንጉሡም መስፍ አምጥተው የቅዱሳኑን ሁሉ ጭናቸውን በድጅኖ ይሰብሩ ዘንድ አዘዘ እንጣልያም የእንድርያኖስን እጆቹንና እግሮቹን በመስፍ ላይ ለማኖር ቀደመች ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ እስከ ሰጠ ድረስ የእንድርያኖስን ዐጥንቶቹን ወታደሮች ቀጠቀጡ የቅዱሳኑንም ሁሉ ጭናቸውን ሰብረው ወደ እሳት ወረወሯቸው እሳቱ ግን ከቶ አልነካቸውም። ምእመናንም መጥተው በጭልታ ወደ ሌላ ቦታ ወሰዱአቸው የመከራውም ወራት እስቲያልፍ ሠወሩአቸው። እንጣልያም የእንድርያኖስን የእጁን ቁራጭ ወስዳ በትርአሷ ውስጥ አኖረችው።
❤ ከዚህም በኋላ የሀገሩ ገዥ እንጣልያን ሊአገባት ወደደ በአወቀችም ጊዜ የባሏን የእጅ ቁራጭ ይዛ በመርከብ ሸሸች የቅዱሳኑ ሥጋ ወዳለበትም ደርሶ ወደ እነርሱ ይቀበሏት ዘንድ ለመነች ጌታችንም ልመናዋን ተቀብሎ አሳረፋት ከእነርሱም ጋራ ተቀበረች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ እንድርያኖስና በሃያ አራቱ ባልንጀሮቹ ሰማዕታት አማላጅነት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ቢጻርዮን፦ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ምእመናን ነበሩ። በአደገም ጊዜ የምንኵስና ልብስን ለብሶ እግዚአብሔርን ሊአገለግል ወደደ ዓለምንም ንቆ ወደ አባ እንጦንስ ሔደ ለእርሱም ደቀ መዝሙር ሆኖ ብዙ ዘመናት አገለገለው።
❤ ከዚህም በኋላ ወደ አባ መቃርስ ሒዶ ቅዱሳን አረጋውያን መነኰሳትንም አገለገላቸው። በአስቄጥስም ገዳም ይዘዋወር ነበር በቤት ውስጥም አያድርም ነበር። ምንጣፍና ልብስ እስኪአጣ ድረስ ምንም ምን ጥሪት አልነበረውም መነኰሳቱም የማቅ ጨርቅ ይሰጡት ነበር። ወገቡንም ታጥቆ በመነኰሳቱ መንደር ይዞር ነበር በቤቶቻቸውም ደጃፍ እያለቀሰ ይቀመጥ ነበር።
❤ የማያውቀውም ወደርሱ በደረሰ ጊዜ "አባቴ ሆይ ምን ያስለቅስሃል" ይለው ነበር። እርሱም "ንብረቴን ስለዘረፉኝ እንዳልሞት ሸሸሁ ከወገኔም ክብር ተለይቼ በጉስቁልና ወደቅሁ" ይለው ነበር። የቃሉንም ምልክት የማያውቅ የጠፋውን ገንዘብህን እግዚአብሔር ይመልስልህ ብሎ ካለው ይሰጠው ነበር። እርሱም ተቀብሎ ይሔድና ለሌለው ይሰጥ ነበር። የቃሉን ምልክት የሚያውቅ ግን በፈቃደ ነፍስ የሚሠሩ ትሩፋትን ሰይጣን ከሰዎች የማረካቸው መሆኑን ልብ ብሎ ያስተውል ነበር። አባቶችም ጭንቅ የነበረ ተጋድሎውን ስለርሱ ይናገሩ ነበር። እርሱ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ከቶ ሳይተኛ ቁሞ ኖሮአልና ።
❤ በምንኵስናውም ወራት ብዙ ጊዜ በየአርባ ቀን ጾመ እነሆ እንዲህ እየተጋደለ ድንቆችንም እያደረገ ኀምሳ ሰባት ዓመታት ኖረ። ቅዱሳን አባ ዱላስና አባ ዮሐንስም ከተአምራቱ ተናገሩ እነርሱ ከርሱ ጋር ወደ ኤርትራ ባሕር ዳርቻ ሔዱ። እጅግም በተጠሙ ጊዜ እንደተጠሙ አውቆ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ መራራውንም ውኃ ጣፋጭ አድርጎላቸው ጠጥተዋል።
✝ በሁለተኛም ጊዜ ወደ ፈሳሽ ውኃ ደርሶ መሸጋገሪያ አጣ ወደ ጌታችንም ጸለየ ያን ጊዜም እንደ የብስ በባሕሩ ላይ ሔደ። በአንዲት ቀንም የከበሩ አባቶች በጸሎታቸው ያድኑት ዘንድ ጋኔን ያደረበትን ሰው ወደ አስቄጥስ ገዳም ሰዎች አመጡ አባቶችም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ እርሱ ከከንቱ ውዳሴ ስለሚሸሽ ብንነግረው ይህን ጋኔን የያዘውን አያድነውም ።
❤ አባ ቢጻርዮን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለጸሎት ወደሚቆምበት ቦታ ያንን ጋኔን ያደረበትን ሰው አስተኙት። አባ ቢጻርዮንም በገባ ጊዜ ያን ጋኔን ያደረበትን ሰው ተኝቶ አገኘውና ቀሰቀሰው እጁንም ይዞ "ተነሥ" አለው ያን ጊዜም ድኖ ተነሣ አእምሮውም ተመለሰ። ያዩትም እጅግ አደነቁ ለሚፈሩት ስለሚሰጠው ጸጋውም እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
❤ የዚህም ቅዱስ ተአምራቶቹ ከነገርናችሁ የበዙ ናቸው እግዚአብሔርንም አገልገሎ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ቢጻርዮን ጸሎት ይማረን። በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 25 ስንክሳር።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ነሐሴ ፳፬ (24) ቀን።
❤ እንኳን #የኢትዮጽያ_ብርሃን_ለተባሉት ለታላቁ አባት ለከበረ ሐዲስ ሐዋርያ ለትሩፋትም መምህር ለሆነ #ለአቡነ_ተክለ_ሃይማኖት_በዓለ_ለዕረፍትና ለታላቁ አባት ለክርስቶስ ምስክር ለሐዋርያው ለመርዓስ አገር ኤጲስ ቆጶስ ለተጋዳይ #ለቅዱስ_አባት_ቶማስ በዓለ ለዐረፍት በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከአብርሃም_ከይስሐቅና_ከያዕቆብ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ነሐሴ ፳፬ (24) ቀን።
❤ እንኳን #ለታላቋ_የሰላምና_የምሕረት (የይቅርታ) እናት ለሆነችው ሰይጣንን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ለሞከረችው ለእናታችን #ለቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ_በዓለ_ዕረፍት፣ ለታላቁ ሰማዕት #ለአቡነ_ጊዮርጊስ_ዘግሽ ለበዓላቸው መታሰቢያቸው በሰላም አደረሰን።
+6
ብፁዕነታቸው !
" ሰው እንደ እናት እቅፍ የሚያምነው መሬት ሲከዳው ምንኛ ያሳዝናል፤ በደጉ ገበሬ ላይ በደረሰው ድንገተኛ አደጋ አዝኛለሁ " - ብፁዕ አቡነ ገሪማ
➡️ " ከሁሉ ነገር ስብዕና ይቀድማል !! "
በጌዴኦ ዞን የተከሰተውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከትሎ የጌዴኦ፣ ኮሬና ቡርጂ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ገሪማ በረጴ ወረዳ ጫራቃ ቀበሌ ድረስ ተገኝተው በመሬት ናዳ ምክንያት የሚወዷቸውን የተነጠቁና በሀዘን የተሰበሩ ቤተሰቦችን አፅናንተዋል፤ አስክሬን ፍለጋውንም ከሕዝቡ ጋር አብረዉ አግዘዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ብፁዕ አቡነ ገሪማን ከስፍራዉ ሲመለሱ ያነጋገራቸው ሲሆን " ሰው እንደ እናት እቅፍ የሚያምነዉ መሬት ሲከዳው ምንኛ ያሳዝናል፤ በደጉ ገበሬ ላይ በደረሰው ድንገተኛ አደጋ አዝኛለሁ " ሲሉ ገልፀዋል።
" የሞቱት ሰዎች ናቸው ስብዕና ደግሞ ከሁሉ ይቀድማል" ያሉት ብፁዕነታቸው " የሞቱት እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠራቸዉ ክቡራን የሰዉ ልጆች ስለሆኑ ብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከየየመምሪያ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ወደ ቦታዉ በማቅናት ሕዝቡን አፅናንተናል ፀሎትም አድርገናል " ብለዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ያነጋገርናቸው የአከባቢው ነዋሪዎች ብፁዕነታቸው ቦታው ድረስ መገኘታቸውና ሕዝቡን ማፅናናታቸው እንዲሁም ከሕዝቡ ጋር እየቆፈሩ አስክሬን መፈለጋቸው ትልቅ መፅናናት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
በጌዴኦ ዞን ረጴ ወረዳ ጫራቃ ተብሎ በሚጠራዉ አከባቢ ተከስቶ ለ9 ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ከሆነው የመሬት መንሸራተት አደጋ በተጨማሪ በዚሁ ዕለት በዞኑ ቡሌ ወረዳ አጋምሳ ተብሎ በሚጠራዉ አከባቢ ሌላ አደጋ ተከስቶ 17 ሰዎች እስካሁን አለመገኘታቸው ተገልጿል።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ነሐሴ ፳፫ (23) ቀን።
❤ እንኳን #በእስክድርያ (በግብጽ) በልዮናውያን ምክንያት በሰማዕትነት ለዐረፋ ለክርስቲያን #ለወንዶች_ለሴቶች_ለሕፃናት_ለሠላሳ_ሺህ_ሰዎችና ለዕረፍታቸው በዓልና #ለቅዱስ_ድምያኖስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #በዚች_ቀን_በእስክንድርያ_አገር_ከክርስቲያን #ወንድሞቻችን_ሠላሳ_ሺህ_ሰዎች_በሰማዕትነት ሞቱ። ይህም እንዲህ ነው ንጉሥ መርትያኖስ አባታችን ዲዮስቆሮስን ወደ ደሴተ ጋግራ በአጋዘው ጊዜ ብዙ ዘመናት በእስክንድርያ አገር ሁከትና ብጥብጥ ሆነ።
❤ መርትያኖስም በሞተ ጊዜ በርሱ ፈንታ ልዮን ነገሠ እርሱም አብሩታርዮስ የተባለውን መለካዊ ከሮማውያን ወገን ለእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ሾመ ይህም መለካዊ በኬልቄዶን ጉባዔ የሚያምን ነው ስለዚህም ከጥቂት ግብዞች ሰዎች በቀር የእስክንድርያ ሰዎች አልተቀበሉትም። ያልተቀበሉትም ሰዎች አስቀድሞ አባታችን ዲዮስቆሮስ ከሾማቸው ቀሳውስት ሥጋውንና ደሙን የሚቀበሉ ሆኑ። ከዚህም በኋላ በቃሉ ለሚያምኑ ባልንጀሮቹ ጉባኤ አደረገላቸውና የክርስቶስ መለኮቱ ከትስብእቱ ተቀላቀለ የሚል አውጣኪን አወገዘው ።
❤ አብሩታርዮስም ይህን ማድረጉ የእስክንድርያን ሰዎች ሸንግሎ ወደ ከፋች እምነቱ ሊስባቸው ወዶ ነው እንጂ ስለዚህ ነገር አባ ዲዮስቆሮስ አውጣኪን አስቀድሞ አውግዞታል። የአባታችን የዲዮስቆሮስ ሃይማኖት እንደ ባስልዮስና ጎርጎርዮስ እንደ ቅዱስ ቄርሎስ ቃል ከሥጋ ጋር ከተዋሐደ በኋላ አንድ አካል፣ አንድ ባሕርይ ብለው እንደሚያምኑ የሚያምን ነውና።
❤ ከጉባኤውም በኋላ የሰበሰባቸው የአብሩታርዮስ ተባባሪዎቹ ወደየቦታቸው ተመለሱ። እርሱም ራሱ አብሩታርዮስ በቤቱ ውስጥ ተገድሎ ተገኘ ለባልንጀሮቹም የአባታችን ዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት ወይም የአውጣኪ ባልንጀሮች ወይም ሌቦች ገንዘቡን ለመውሰድ የገደሉት መሰላቸው ይህም እውነት ይመስላል።
❤ የአብሩታርዮስም ባልንጀሮች ወደ ንጉሥ እንዲህ ብለው መልእክትን ላኩ "እነሆ የዲዮስቆሮስ ወገኖች የንጉሥን ትእዛዝ በማቃለል ደፍረው የሾምከውን ሊቀ ጳጳሳት ገደሉት። በዚያንም ጊዜ ወንድሞቻችን የእስክንድርያ ሰዎች በላያቸው ጢሞቴዎስን ሊቀ ጵጵስና ሾሙት"። እሊህ መናፍቃንም ከዚህ በኋላ ሁለተኛ እንዲህ ብለው ወደ ንጉሥ መልእክትን ላኩ። "እነሆ አብሩታርዮስን የገደሉት ሰዎች አሁንም ያለ ንጉሥ ፈቃድ ደፍረው ሊቀ ጳጳሳት ሾሙ"።
❤ ንጉሡም በሰማ ጊዜ ከሁለቱ መልእክቶች የተነሣ እጅግ ተቆጣ። ሰይጣንም በልቡ አድሮ ጭፍሮቹን ልኮ ሃይማኖታቸው ከቀና ወንድሞቻችን ክርስቲያኖች ታላላቆችና ታናናሾች ሠላሳ ሺህ ሰዎች ተገደሉ ጢሞቴዎስንም ወደ ደሴተ ጋግራ አጋዘው በዚያም ሰባት ዓመት ኖረ።
❤ ከአባታችን ዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት አንዱ የገደለውስ ቢሆን ስለ አንድ ሰው ፈንታ ሠላሳ ሺህ ሰው መግደል ይገባልን ስለዚህ ከሰይጣን ሥራ እንደሆነ ይታወቃል።
❤ ከዚህ ከከፋ ዕልቂት በኋላም ወንድሞቻችን የሆኑ የዲዮስቆሮስ ደቀ መዛሙርት አብሩታርዮስን እንዳልገደሉት ንጉሡ ተረዳ እጅግም አዘነ ጢሞቴዎስንም ከተሰደደበት መልሶ በመንበረ ሢመቱ አኖረው ታላቅ ክብርንም አከበረው። መንጋውንም እያበረታ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በ 30 ሺህ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #ሰማዕቱ_ቅዱስ_ድምያኖስ፦ ይህንንም ቅዱስ የአንጾኪያ አገር መኰንን ይዞ ብዙ አሠቃየው፡፡
በኋላ ቅዱስ ድምያኖስ በእምነቱ መጽናቱን ሲያውቅና ማሠቃየትም በሰለቸው ጊዜ አንገቱን በሰይፍ ቆረጠውና ሰማዕትነት ፍጻሜው ሆነ፡፡ የክብር አክሊንም ተቀዳጀ፡፡ የቅዱስ ድምያኖስ በረከቱ ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 23 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለክሙ_በቃለ_ብዙኅ_ብፅዓን። #ሠለስቱ_እልፍ_ምእመናን። ዘተቀተልክሙ በእደ አርዮሳውያን። ኦ አብያዝ ጽዱላን ስን። ደዩ ውስተ ሥጋየ እምቅብዕክሙ ርጢን። ማኅቶቱ ኢይጥፋእ ዘተብህለ ዐይን"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የነሐሴ_23።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወለእመኒ ፈለሱ አድባር ውስተ ልበ ባሕር። ደምፁ ወተሐምጉ ማያቲሆሙ። ወአድለቅለቁ አድባር እምኃይሉ"። መዝ 45፥2-3። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 13፥1-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 5፥6-12 እና የሐዋ ሥራ 12፥18-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 21፥18-23። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን ማርያም ወይም የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችን ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ነሐሴ ፳፪ (22) ቀን።
❤ እንኳን #ከዐሥራ_ሁለቱ_ደቂቀ_ነቢያት አንዱ ለሆነው ለታላቁ ለሞራት ልጅ ለነቢዩ #ለቅዱስ_ሚክያስ ለዕረፍት በዐል እግዚአብሔር አምላክና በሰላም አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #የሞራት_ልጅታላቁ_ነቢይ_ቅዱስ_ሚክያስ፦ ይህም ነቢይ በይሁዳ ነገሥታት በኢዮአታም፣ በአካአዝና በሕዝቅያስ ዘመን ትንቢት በመናገር አስተማረ።
❤ ስለጌታችን መውረድም እንዲህ አለ። "እነሆ እግዚአብሔር ከልዑል መንበሩ ወደዚህ ዓለም ይወርዳል"።
❤ ሁለተኛም ስለ ልደቱ እንዲህ ብሎ ተናገረ "የኤፍራታ ዕጣ የምትሆኚ አንቺ ቤተ ልሔም የእስራኤል ነገሥታት ከነገሡባቸው አገሮች አታንሺም ወገኖቹን የሚጠብቃቸው የእስራኤል ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና"።
❤ ስለ ምኵራብ መቅረት፤ ስለ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ሁሉ መታነፅ ትንቢት ተናግሮአል። ዳግመኛም ስለ ሕገ ወንጌል መሠራት "ከጽዮን የእግዚአብሔር ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣል" አለ። የትንቢቱም ወራት ሲፈጸም ወደ በጎ ሽምግልና ደርሶ ወደ ወደደው እግዚአብሔር ሔደ።
❤ የትንቢቱ ዘመን ከጌታችን መምጣት በፊት በስምንት መቶ ዓመት ነው። ማርታ በምትባልም ቦታ ተቀበረ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የነቢዩ የቅዱስ ሚክያስ በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 22 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለሚክያስ_ነባቢተ_ትንቢት_ልሳኑ። ዘይከውን በበዘመኑ። እንዘ ይብል ከመዝ ኂሩተ አምላክ ይዜኑ። መኑ ከማከ እግዚኦ አምሳለ አማልክት ዘኮኑ። አበሳ ርስቱ ዘይትነሐይ መኑ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የነሐሴ_22።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወገሠፀ ነገሥተ በእንቲአሆሙ። ወኢትግሥሡ መሲሐንየ። ወኢታሕስሙ ዲበ ነቢያትየ"። መዝ 104፥14-15። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 11፥25-ፍ.ም፣ 2ኛ ጴጥ 1፥19-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 7፥51-54። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 2፥1-7። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን ማርያም ወይም የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የነቢዩ የቅዱስ ሚክያስ የዕረፍትበዓል።
ለሁላችን ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ነሐሴ ፳፩ (21) ቀን።
❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊ_ጻድቅ ኤርትራ አገር የሚነኘው #ደብረ_ጥሉል_ገዳምን_ለመሰረቱ በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የነበረውን የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት ላለማየት ሳይወለዱ በእናታቸው ማኅፀን 7 ዓመት ከ6 ወር ለቆዩት #ለታላቁ_አባት_አቡነ_አብራኒዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓላቸው በሰላም አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #አቡነ_አብራኒዮስ፦ አባታቸው ወልደ ክርስቶስ እናታቸው ወለተ ትንሣኤ የሚባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የተወለዱት በ1624 ዓ.ም ምሥራቅ ጎጃም አካባቢ ልዩ ስሙ እነብሴ ይሁን እንጂ ተጋድሏቸውን ያደረጉትና ገዳማቸውን የገደሙት በዛሬዋ ኤርትራ ውስጥ ነው፡፡ ገዳሙ ኤርትራ ውስጥ ዞባ ድባርዋ ደቂ ድግና በተባለ አካባቢ ይገኛል፡፡ የገደሙት ጻድቁ በ1705 ዓ.ም ነው፡፡
❤ አቡነ አብራኒዮስ የተፀነሱት በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አብሳሪነት ነው፡፡ ነገር ግን ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ጻድቁ በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የነበረውን የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት ላለማየት ሳይወለዱ በእግዚአብሔር ፈቃድ በእናታቸው ማኅፀን 7 ዓመት ከ6 ወር ተቀምጠዋል፡፡ በዚህም ወቅት እሳት ልትጭር ከጎረቤቷ የመጣች አንዲት ሴት የአቡነ አብራኒዮስ እናት "የማትወልጂው ምን ሆነሽ ነው?" ብላ ስትናገር ጻድቁ በእናታቸው ማኅፀን ሆነው "…ለምን ክፉ ትናገሪያለሽ?" ብለው መልስ ሰጥተዋታል፡፡ ይህም ቅዱሳን ልክ እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ገና በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ እንደሚመረጡ አንድ ማሳያ ነው፡፡
❤ በርካታ ምእመናንን በሰማዕትነት ከገደሉ በኋላ በመጨረሻም ዐፄ ሱስንዮስ በመቅሰፍት ተመተው ሊሞቱ ሲሉ "ሃይማኖት ይመለስ፣ ፋሲል ይንገሥ" ብለው የቤተ ክርስቲያን ሰላም መልሰው ንስሓ ገብተው ሞቱ፡፡ አቡነ አብራኒዮስም ይህ የቤተ ክክርስቲያን የመከራ ዘመን ሲያልፍና ሃይማኖት ሲመለስ ተወለዱ፡፡ ገና በ5 ዓመታቸው ከጥንቆላ መጻሕፍት በቀር ሁሉንም የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትንና ምሥጢራትን ሁሉ ተምረው ዐወቁ፡፡ በ12 ዓመታቸው መነኰሱ፡፡ ዲቁና ሲሾሙም ጳጳሱ "ገና ሕፃን ነው፣ አሁን አልሾመውም" ሲሉ የሰማይ መላእክት "ይባዋል" ብለው መስክረውላቸዋል፡፡
❤ በልጅነታቸውም መነኰሳቱ ወደ ጫካ ሔደው ዕንጨት እንዲሰብሩ ሲያዟቸው ጌታችን ግን ለአቡነ አብራኒዮስ ኃይል ሰጥቷቸው በነፋስ ሠረገላ እየሔዱ የ6 ሰዓቱን የእግር መንገድ እሳቸው ግን ዕንጨቱን ሰብረው በቶሎ ይመለሱ ነበር፡፡ ይህም ሲታወቅባቸው ውዳሴ ከንቱን ንቀው ከዚያ ገዳም ወጥተው ወደ አቡነ ተጠምቀ መድኅን ዘንድ ሔዱ፡፡ በዚያም በታላቅ ተጋድሎ ከኖሩ በኋላ አቡነ ተጠምቀ መድኅን "በአንተ ምክንያት ብዙ ነፍሳት ይድናሉ፣ ክፍልህ በዚያ ነው" ብለው አሁን ገዳማቸውን ወደገደሙበት ቦታ (ኤርትራ) ላኳቸው፤ ሲመጡም ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል እየመሯቸው እንደመጡ ገድላቸው ይናገራል፡፡ ጻድቁ ወደዚህ ገዳም ሲመጡ በፊት ይቀመጡባት የነበረችው ትልቅ ድንጋይ በተኣምር ከመሬት 7 ክንድ ከፍ ብላ አብራቸው መጥታለች፡፡ ድንጋይዋ ዛሬም ድረስ በገዳማቸው በክብር ስለተቀመጠች ምእመናን እየዳሰሷት ይባረኩባታል፣ መካኖች ይወልዱባታል፣ ሕሙማን ይፈወሱባታል፡፡
❤ አቡነ አብራኒዮስ በቅዳሴ ጊዜ ጌታችንን በዕለተ ዐርብ እንደተሰቀለ ሆኖ ይመለከቱት ስለነበር በኀዘን በተመስጦ ሆነው ይቆዩም ስለነበር ሕዝቡም "በቅዳሴ ሰዓት ይተኛል" እያሉ ያሟቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ጻድቁ ወደ አካለ ጉዛይ በመሔድ በዘንዶ ላይ አድሮ ይመለክ የነበረውን ሰይጣን በጸሎታቸው አጥፍተው ዘንዶውን ገድለው ሕዝቡንም አስተምረው በንስሓ መልሰው አጥምቀዋቸዋል፡፡ ወደ ታላቁ ገዳም ደብረ ቢዘንም ሲሔዱ 6400 አጋንንትን አግኝተው በጸሎታቸው አጥፍተዋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አቡነ አብራኒዮስ "ሰዳዴ አጋንንት-አጋንንት አባራሪ" ተብለዋል፡፡
❤ አቡነ አብራኒዮስ ወደ ሌላ ቦታ ሔደው ሰለዳዋ የምትባል ቦታ ላይ ሆነው ሳለ አንድ ሰው ወደ ገዳማቸው ገብቶ አንዲትን ዛፍ ሲቆርጥ በመንፈስ ቅዱስ መነጽርነት አዩት፡፡ ቆራጩም ሰው "ተው አትቁረጥ" የሚል የአባታችንን ድምፅ ሰማ፣ በአካል የሉም ብሎ እምቢ አለ፣ ነገር ግን በመቅሠፍት ተመቶ ወዲያው ሞተ፡፡ በአንድ ዕለትም ልጃገረዶች እየዘፈኑ ሲሔዱ ብዙ አጋንንት በዘፈናቸው ተደስተው አብረዋቸው ሲጨፍሩ አባታችን በመንፈስ ተመልክተው ለልጃገረዶቹ ዘፈን የአጋንንት መሆኑን እንዳስተማሯቸው ገድላቸው ይናገራል፡፡
❤ ለአቡነ አብራኒዮስ ለዕፍታቸው ሲደርስ ክብርት እመቤታችን ተገልጻ "ቤተ ክርስቲያን በስሜ አንጽልኝ" አለቻቸው፡፡ እርሳቸውም ውብ አድርገው በእመቤታችን ስም አነጹ ነገር ግን ፍጻሜውን ሳያዩ በዕለተ ቀኗ ነሐሴ 21 ቀን ዐረፉ፡፡ በዕረፍታቸውም ወቅት ጌታችን ተገልጦ ታላቅ ቃልኪዳን ሲሰጣቸው "...ዋስ እፈልጋለሁ፣ ዋስ ስጠኝ" አሉት፡፡ ጌታችንም "ሐዋርያት፣ ሰማዕታት፣ ከአንተ በፊት የነበሩ ጻድቃን ያልጠየቁኝን አንተ እንዴት ጠየከኝ?" አላቸው፡፡ እርሳቸውም "አምላኬ ሆይ! አንተ መሐሪና በጽድቅ ፈራጅ ቃልህም የማይለወጥ እንደሆንክ አውቃለሁ" አሉት፡፡ ጌታችም ፍግግ ብሎ "ይሁን የምትሻውን አላሳጣህም" በማለት ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ የሆነች ክብርት እመቤታችንንና ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ዋስ አድርጎ ቃል ኪዳን ከገባላቸው በኋላ ነሐሴ 21 ቀን 1713 ዓ.ም በሰላም ዐረፉ። ከታላቁ ጻድቅ ከአባታች አቡነ አብራኒዮስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን፣ በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ ከገድላት አንደበት።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ነሐሴ ፳ (20) ቀን።
❤ እንኳን #ሦስት_መቶ_ሰባ_ሁለት_ዘመናት አንቀላፋተው #በንጉሥ_በቴዎዶስዮስ_ዘመን ተነስተው ትንሣኤ ሙታን ለሰበኩ በከሀዲው ንጉሥ ዳኬዎስ ዘመን ለነበሩ ከኤፌሶን ሀገር ለሆኑ #ለሰባቱ_ደቂቅ_ለዕረፍት_በዐላቸውና #ለእመቤታችን_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም #ለትንሣኤዋና_ለዕርገቷ_አምስተኛ_ቀን መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከምትታሰበው፦ #ከቅድስት_ሄዛዊ ከመታሰቢያዋ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅዱሳን_ሰባቱ_ደቂቅ፦ እሊህም ስማቸው መክሲሞስ፣ ታሙኪሮስ፣ መርዳዲሞስ፣ ዮሐንስ፣ ቆስጠንጢኖስ፣ ዝሚና ዲዮናስዮ ናቸው። ንጉሥ ዳኬዎስ ጭፍሮች ውስጥ በመዛግብቱ ላይ የሾማቸው ነበሩ። አምልኮ ጣዖትንም በአወጀ ጊዜ ጣዖትን በማምለክ ሥራ አልተሳተፉም። እሊህንም ቅዱሳን በንጉሥ ዘንድ ወነጀሏቸው ይዞም አሠራቸው።
❤ ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ ቦታ ለመሔድ በፈለገ ጊዜ እስከ ሚመለስ ድረስ ፈትቶ ለቀቃቸው ምናልባት ከምክራቸው ቢመለሱ ብሎ በልቡ አስቦ። ከዚህም በኋላ እሊህ ቅዱሳን ለረከሱ ጣዖታት እንዳይሰግዱ የጭፍራነት ሥራቸውን ትተው በተራራ ውስጥ ወደአለ ዋሻ ሒደው በዚያ ተሠወሩ። የዋሻውን አፍ ዘጉ ከእሳቸውም ጋራ በንጉሥ ዳኬዎስ ስም የተቀረጸ ብር ነበር። ከእርሳቸውም አንዱም አንዱ በየተራቸው ወጥቶ ምግባቸውን ገዝቶ ወደእሳቸው ይመለስ ነበር። ዳኬዎስም ከሔደበት እንደተመለሰ በሰሙ ጊዜ የዋሻውን ደጃፍ ዘግተው ተኙ።
❤ የእሊህንም ቦታቸውን የሚያውቅ አማኒ የሆነ ከጭፍሮች ውስጥ አንድ ሰው ነበረ ወደ ከተማ ሲወጡ ያገኛቸው ዘንድ ጠበቃቸው ባልመጡም ጊዜ ተነሥቶ ወደ ዋሻቸው ሔደ። ዋሻዋንም ከውስጥ እንደ ዘጓት ሁና አገኛት እነርሱም በረሀብ የሞቱ መሰለው ታላቅም የደንጊያ ሠሌዳ አምጥቶ ከእሳቸው የሆነውን ገድላቸውን ጽፎ በቀዳዳ ወደ ዋሻው ውስጥ አስገባው። እሊህም ቅዱሳን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዘመናት አንቀላፉ ዳኬዎስም ሙቶ እስከ ቴዎዶስዮስ ብዙ ነገሥታት ነገሡ።
❤ በዚህም ምእመን ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘመን ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዎች ተነሥተው ብዙዎች ተከተሏቸው። በዚያንም ጊዜ እሊህን ቅዱሳን ሰባቱን ደቂቅ እግዚአብሔር አነቃቸው ትንሣኤ ሙታን መኖሩን ግልጽ ያደርግ ዘንድ።
❤ ከዚህም በኋላ ከእርሳቸው አንዱ ምግባቸውን ሊገዛ የከሀዲ ዳኪዎስንም ወሬ ይሰማ ዘንድ ብር ይዞ ወጣ ወደ ከተማም በገባ ጊዜ የከተማዋ ሁኔታ ተለወጠበት። በከተማውም በር መስቀሎችን አየ በየቅጽሮቿም የክብር ባለቤት የሆነ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ስሙን ያለ መፍራት ሲጠሩ ሰማ አንዱንም ሰው"ይች አገር ኤፌሶን አይደለችምን?" ብሎ ጠየቀ እርሱም "አዎን ናት" አለው። ያንንም ብር አውጥቶ ለባለ ሱቁ ሰጠው ምግባቸውን ይሸጥለት ዘንድ ባለ ሱቁም ያን ብር ተመለከተው የንጉሥ ዳኬዎስም ስም ተቀርጾበት አገኘውና ያንን ሰው ይዞ "በአንተ ዘንድ የተሸሸገ መዝገብ አለ ይህ ምልክት ከአንተ ተገኝቷልና" አለው።
❤ እንዲህም ሲጣሉ ወደእርሳቸው ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ እንዲህም ብለው ጠየቁት "አንተ ከወዴት ነህ?" "ከዚች አገር ነኝ" አላቸው። "ማንን ታውቃለህ" አሉት እርሱም "ዕገሌንና ዕገሌን" አላቸው ከዘመን ብዛት የተነሣ የጠራቸውን ሰዎች የሚያውቃቸው የለም። ስለዚህም በእርሱ ላይ ተቆጥተው ወደ ዳኞችና ወደ ኤጲስቆጶስ አባ ቴዎድሮስ ወደ ንጉሥ ቴዎዶስዮስም አቀረቡት። ንጉሡና ኤጲስቆጶሱም "ከአንተ የሆነውን እውነቱን ንገረን ከወዴት አገር ነህ" አሉት። እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው "እኛ ሰባታችን የከሀዲ ንጉሥ ዳኬዎስ ጭፍሮች ነን እርሱም ወጥቶ ወደ ሌላ አገር በሔደ ጊዜ ከአንዷ ዋሻ ውስጥ ገብተን የዋሻዋን በር ዘግተን ተኛን"። እነሆ ስንነቃ የምንመገበውን ምግብ እገዛ ዘንድ ላኩኝ።
❤ ንጉሡና ኤጲስቆጶሱ በሰሙ ጊዜ ተነሥተው ወደዚያ ዋሻ ከእርሱ ጋራ ሔዱ ከእርሳቸውም ጋራ ብዙ ሕዝቦች አሉ ቅዱሳኑንም ተቀምጠው አገኙአቸው። የዘመኑም ቁጥር በውስጡ የተጻፈበትን በከሀዲው ንጉሥ በዳኬዎስ ዘመን የሆነውን ሠሌዳውን ወድቆ አገኙት ዘመኑም ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት እንደሆነ ታወቀ። ንጉሡና ኤጲስቆጶሱ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር አደነቁ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉትም ይህን ድንቅ ሥራ አይተው ትንሣኤ ሙታን እንዳለ አመኑ። እሊህ ሰባቱ ደቂቅንም በጠየቋቸው ጊዜ ከእርሳቸው የሆነውን ሁሉ ነገሩአቸው።
❤ ከዚህም በኋላ ተመልሰው ተኙ። ነፍሳቸውንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጡ። ንጉሥም የወርቅ ሣጥን ሠራላቸው በሐር ልብሶችም ገንዘው በመልካም ቦታ አኖሩዋቸው። ከሥጋቸውም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የእሊህም የሰባቱ ደቂቅ ቅዱሳን በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ዕብል_ሰብዓተ_ዕደው። እለ ኮኑ ቅድመ ዘበሃይማኖት ስንዕወ። አዝማነ ዕልወት ይኅልፋ እለ አጽምዑ ብጽወ። ማዕዖ በዓቶሙ በሥምረተ አምላክ ተርኅወ። ነቂሖሙ ህየ ይግበሩ ፍናው"። #ሊቁ_አርከ ሥሉስ (አርኬ) የነሐሴ20።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ነጽረኒ ወስምዐኒ እግዚኦ አምላኪየ። አብርሆን ለአዕይንትየ ከመ ኢይኑማ ለመዊት። ወከመ ኢይበሉኒ ጸላእትየ ሞዕናሁ"። መዝ 12፥3 ወይም መዝ 44፥9-10። የሚነበቡ መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 15፥31-51፣ ያዕ 4፥11-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 23፥22-ፍ.ም። የሚበበው ወንጌል ማቴ 22፥23-34 ወይም ሉቃ 1፥39፥57። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የእመቤታችን የትንሣኤዋና የዕርገቷ በዓል ሰሞን። ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ነሐሴ ፲፱ (19) ቀን።
❤ እንኳን #ለአልዓዛር_ልጅ_ለካህኑ_ለፊንሐስ ለዕረፍት በዓል መታሰቢያ፣ ለታላቁ አባት #ለአባ_መቃርስ ሳስዊር ከሚባል አገር ወደ አስቄጥስ ገዳም #ሥጋው_ለፈለሰት_በዐል፣ ለአበ ብዙኀን ለአባታችን #ለቅዱስ_አብርሃም ጣዖታቱን ለሰበረበትና አምላኩን በሥነ ፍጥረት ተመራምሮ ላገኘበት ቀንና ለእመቤታችን ለትንሣኤዋና #ለዕርገቷ_አራተኛ_ቀን መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። (ስለ ካህኑ ፊንሐስ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ኦ.ዘኊ 25፥1-17 ይገኛል)።
✝ ✝ ✝
❤ #የታላቁ_አባት_የአባ_መቃርስ_የሥጋ_ፍልሰት፦ ይህም ሳስዊር ከሚባል አገር ወደ አስቄጥስ ገዳም የሥጋው ፍልሰት ሆነ።
❤ ከዕረፍቱ በኋላ ከሀገሩ ከሳስዊር ሰዎች መጥተው ሥጋውን ሰርቀው ወደ ሀገራቸው ወሰዱት ቤተ ክርስቲያንም ሠርተውለት ሥጋውን በዚያ አኖሩት እስላሞች እስከ ነገሡበት ዘመንም በዚያ ኖረ።
✝ ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ ቦታ አፍልሰውት በዚያም ቤተ ክርስቲያን ሠሩለት። ለአባ መቃርስ ገዳም አበ ምኔት ሁኖ አባ ዮሐንስ እስከ ተሾመበት ዘመን ኖረ። ሊቀ ጳጳሳቱም የከበረች ጾመ አርብዓን ሊጾም ወደ አባ መቃርስ ገዳም በወጣ ጊዜ ፈጽሞ አለቀሰ እንዲህም ብሎ ጸለየ። "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የከበረ የአባ መቃርስ ሥጋ በዚህ ገዳም በመካከላችን ይሆን ዘንድ እንድትረዳኝ እመኛለሁ"።
❤ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ አባ ሚካኤል ሔደ ከእርሱ ጋራም ስለ ገዳሙ አገልግሎት አረጋውያን መነኰሳት አሉ ልቦናቸውም በመንፈሳዊ ሁከት ተነሣሥቶ ያመጡት ዘንድ የአባ መቃርስ ሥጋ ወደ አለበት ቦታ ደረሱ። የአገር ሰዎችም በአዩአቸው ጊዜ በትሮቻቸውንና ሰይፎቻቸውን በመያዝ ከመኰንናቸው ጋራ ተሰብስበው ከለከሏቸው። በዚያቺም ሌሊት በልባቸው ፈጽሞ እያዘኑ አደሩ። አባ መቃርስም በዚያች ሌሊት ለመኰንኑ በራእይ ተገለጠለትና "ከልጆቼ ጋራ መሔድን ለምን ትከለክለኛለህ እንግዲህስ ተወኝ ከእሳቸው ጋራ ወደ ቦታዬ ልሒድ" አለው።
❤ ያ መኰንንም በጥዋት ተነሣ እየፈራና እየተንቀጠቀጠ የከበሩ አረጋውያን መነኰሳትን ጠርቶ የከበረ የአባ መቃርስን ሥጋ ሰጣቸው። እነርሱም ደስ ብሏቸው ተቀበሉት በመርከብም ተሳፍረው ተርኑጥ ወደሚባል አገር ደረሱ ከእርሳቸውም ጋራ የሚሸኙአቸው ከየአገሩ የመጡ ብዙ ሕዝቦች ነበሩ። በዚያችም ሌሊት በዚያ አደሩ ጸሎትንም አደረጉ ቀድሰውም ለሕዝቡ ሥጋውንና ደሙን አቀበሉ።
✝ ከዚህም በኋላ ተሸክመው ወደ ገዳም ተጓዙ ሲጓዙም ከበረሀው እኵሌታ ደርሰው ከድካማቸው ጥቂት ሊአርፉ ወደዱ። አባ ሚካኤልም "የከበረ የአባታችን የአባ መቃርስን ሥጋ የምናሳርፍበትን እግዚአብሔር እስከ ገለጠልን ድረስ እንደማናርፍ ሕያው እግዚአብሔርን" ብሎ ማለ።
❤ ከዚህም በኋላ የከበረ የአባ መቃርስን ሥጋ የተሸከመ ገመል ወደ አንድ ቦታ ደርሶ በዚያ በረክ አለ። የከበረ የአባ መቃርስ ሥጋ ያለበትንም ሣጥን ይጥል ዘንድ በራሱ ወዲያና ወዲህ ይዞር ጀመረ። አረጋውያን መነኰሳትም እግዚአብሔር የፈቀደው ያ ቦታ እንደሆነ አወቁ እጅግም አደነቁ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ያም ቦታ እስከ ዛሬ የታወቀ ነው።
❤ ወደ ገዳሙም በቀረቡ ጊዜ መነኰሳቱ ሁሉም ወጡ ወንጌልና መስቀሎችን ይዘው መብራቶችን እያበሩ እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን እስከ አስገቡት ድረስ በታላቅ ክብር በራሳቸው ተሸክመው ወሰዱት። እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት ተአምራትን አደረገ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ መቃርስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ይድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አበ_ብዙሃን(የብዙዎች አባት) #ቅዱስ_አብርሃም፦ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የአብርሃም አባቱ ታራ ጣዖትን ይጠርብና ይሸጥ ነበር። ሽጦ ገንዘብ የሚያመጣለት ደግሞ ልጁ አብርሃም ነበር። በዚያ ወራት አብርሃም እውነተኛውን አምላክ ፍለጋ ገብቶ ነበር። አንድ ቀን ጣዖቱን ሊሸጥ ወደ ገበያ እየሔደ የተሸከመውን እንጨት ይመራመረው ገባ። "አሁን ይሔ ምኑ ነው አምላክ!" እያለም ያደንቅ ገባ። መንገድ ላይም ደክሞት ካረፈበት "ለምን አልጠይቀውም" በሚል አናገረው።
❤ "እርቦኛል አብላኝ" አለው። መልስ የለም። "እሺ አጠጣኝ" አለው። አሁንም ያው ነው። "ባይሆን እሺ አጫውተኝ" አለው። ጣዖቱ ተራ እንጨት ነውና መልሱ ዝምታ ነበር። ከዚያ ተነስቶ ወደ ገበያው ሲደርስ "ዐይን እያለው የማያይ፤ ጀሮ እያለው የማይሰማ አምላክ የሚገዛ" እያለ ይጮህ ጀመር።
✝ ይህን ሲሰሙ አንዳንዶቹ "የታራ ልጅ አብዶ" ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ "እሱ ያቀለለውን ማን ይገዛዋል" ብለውት ሔደዋል። ከገበያ ሲመለስም ጣዖቱን ተመልክቶ አብርሃም እንዲህ አለ። "አንተ ቀድሞውን በዕለተ ሠሉስ የተፈጠርክ ዕፅ ነህ" ብሎ ሰባበረው።
❤ ወደ ቤቱ ሲመለስም ሁሉንም ጣዖታት ሠባበራቸው። ይህ የተደረገው ከ 2,000 ዓመታት በፊት በዚህች ቀን ነው። የመንግስተ ሰማያት አበጋዝ የእግዚአብሔር ወዳጅ አባታችን አብርሃም በመጨረሻው በውሃ፣ በነፋስ፣ በእሳትና በፀሐይ ተመራምሮ ፈጣሪውን አግኝቷል። ምንጭ፦ ከዲያቆን ዮርዳኖስ አበባ።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "በእግዚአብሔር እሴብሕ ቃል። በእግዚአብሔር ይከብር ዘነበብኩ። ወእግዚአብሔር ተወከልኩ ኢይፈርህ። መዝ 55፥10-11። የሚነበቡ መልክታት ሮሜ 1፥8-15፣ 1ኛ ጴጥ 3፥8-15 እና የሐዋ ሥራ 16፥35-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 27፥50-57። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ወይም የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የእመቤታችን የትንሣኤዋና የዕርገቷ በዓል ሰሞን። ለሁላችንም ይሁንልን።
ነሐሴ ፲፱ /19/በዚች ቀን ሳስዊር ከሚባል አገር ወደ አስቄጥስ ገዳም የታላቁ አባ መቃርስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ። ከዕረፍቱ በኋላ ከሀገሩ ከሳስዊር ሰዎች መጥተው ሥጋውን ሰርቀው ወደ ሀገራቸው ወሰዱት ቤተ ክርስቲያንም ሠርተውለት ሥጋውን በዚያ አኖሩት እስላሞች እስከ ነገሡበት ዘመንም በዚያ ኖረ ። ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ ቦታ አፍልሰውት በዚያም ቤተ ክርስቲያን ሠሩለት ። ለአባ መቃርስ ገዳም አበ ምኔት ሁኖ አባ ዮሐንስ እስከ ተሾመበት ዘመን ኖረ ። ሊቀ ጳጳሳቱም የከበረች ጾመ አርብዓን ሊጾም ወደ አባ መቃርስ ገዳም በወጣ ጊዜ ፈጽሞ አለቀሰ እንዲህም ብሎ ጸለየ ። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የከበረ የአባ መቃርስ ሥጋ በዚህ ገዳም በመካከላችን ይሆን ዘንድ እንድትረዳኝ እመኛለሁ። እግዚአብሔርም ይህን ጸሎቱን ሰምቶት የቅዱሱን ሥጋ እንዲያገኝ አስቻለው። ባገኘውም ጊዜ በየት እንደሚያኖረው ሲያስብ የአባ መቃርስን ሥጋ የተሸከመ ግመል ወደ አንድ ቦታ ደርሶ በዚያ በረክ አለ ። የከበረ የአባ መቃርስ ሥጋ ያለበትንም ሣጥን ይጥል ዘንድ በራሱ ወዲያና ወዲህ ይዞር ጀመረ ። አረጋውያን መነኰሳትም እግዚአብሔር የፈቀደው ያ ቦታ እንደሆነ አወቁ እጅግም አደነቁ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ያም ቦታ እስከ ዛሬ የታወቀ ነው ። ወደ ገዳሙም በቀረቡ ጊዜ መነኰሳቱ ሁሉም ወጡ ወንጌልና መስቀሎችን ይዘው መብራቶችን እያበሩ እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን እስከ አስገቡት ድረስ በታላቅ ክብር በራሳቸው ተሸክመው ወሰዱት። እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት ተአምራትን አደረገ ። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ:- መጽሐፈ ስንክሳር
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ ነሐሴ ፲፰ (18) ቀን።
❤ እንኳን #ለእስክንድርያ_ዐሥራ_ዘጠነኛ ሊቃነ ጳጳሳት በኒቅያ ጉባኤ #በ325 ዓ.ም አርዮስ #ከአባ_አትናቴዎስ ጋር በመሆን ተከራክሮ ላወገዘው ለታላቁ አባት #ለአባ_እለእስክድሮስ ለመታሰቢያው በዓሉና ለእመቤታችን ለትንሣኤዋና ለዕርገቷ ሦስተኛ ቀን መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪም በዚች ቀንከሚታሰበው፦ #ከዲያቆን_እንድራኒቆስ ከመታሰቢያው በዓሉ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝️ ✝️ ✝️
❤ "#ሰላም_ለእለእስክንድሮስ ዘደለዎ ጵጵስና ስርግው በቅድስና"። ትርጉም፦ ጵጵስና የተገባው ለኾነ በቅድስና ላጌጠ (ለተሸለመ) #ለአባ_እለእስክንድሮስ ሰላምታ ይገባል። #ሊቁ_አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ_በተአምኆ_ቅዱሳን_ላይ።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #አባ_እለእስክንድሮስ፦ እርሱም ቊጥሩ ከአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ነው። ይህም አባት ከአርዮስ ወገኖች ብዙ ችግር ደርሶበታል እርሱ ከወገኖቹ ጋር ሁኖ አርዮስን አውግዞ ከቤተክርስቲያን አሳዶት ነበርና።
❤ በታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ዘመን በኒቅያ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶች ሊቃውንት አርዮስን በጉባኤ አውግዘው ከቤተ ክርስቲያን ለይተው በአሳደዱት ጊዜ ወደ ንጉሡ ቈስጠንጢኖስ ጓደኞቹን ይዞ ገብቶ በእለእስክንድሮስና በአትናቴዎስ ላይ ነገር ሠራ ሁለተኛም እለእስክንድሮስ ከካህናቱ ጋር ይቀበለው ዘንድ እንዲያዝለት ንጉሡን ለመነው።
❤ ንጉሡም ልመናውን ተቀብሎ መልእክተኞችን ልኮ አባት እለእስክንድሮስን አስመጥቶ እንዲህ አለው "አትናቴዎስ ትእዛዛችንን በመተላለፍ አርዮስን አልቀበልም ብሏል፤ እኛም አንተን እንዳከበርንህ አንተ ታውቃለህ አሁንም ትእዛዛችንን አትተላለፍ አርዮስንም ከውግዘቱ ፈትተህ ልባችንን ደስ አሰኝ" አለው ። ቅዱስ እለእስክንድሮስም ለንጉሥ እንዲህ ብሎ መለሰለት "አርዮስን እኮን ቤተክርስቲያን አልተቀበለችውም። ልዩ ሦስትነትን አያመልክምና" ንጉሡም "አይደለም እርሱ በሥሉስ ቅዱስ ያምናል እንጂ" አለው ቅዱስ እለእስክንድሮስም "ወልድ በመለኮቱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ትክክል እንደሆነ የሚያምን ከሆነ በእጁ ይጻፍ" ብሎ መለሰለት።
❤ ንጉሥም አርዮስን አስቀርቦ "ትክክለኛ ሃይማኖትህን ጻፍ" አለው አርዮስም በልቡ ሳያምን "ወልድ ከአብ ጋራ በመለኮቱ ትክክል ነው" ብሎ ጻፈ በሐሰትም የከበረ ወንጌልን ይዞ ማለ። ንጉሡም ቅዱስ እለእስክንድሮስን "አሁን በአርዮስ ላይ ምክንያት አልቀረህም ትክክለኛ ሃይማኖቱን ጽፎአልና በከበረ ወንጌልም ምሎአልና" አለው ።
❤ አባ እለእስክንድሮስም ንጉሡን እንዲህ አለው "በአባትህ በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እጅ የተጻፈ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ አባቶች በእጆቻቸው የጻፉትን እርሱንና ወገኖቹን ከቤተ ክርስቲያን እንዳሳደዷቸው የአርዮስን ክህደቱንና ውግዘቱን አትናቴዎስ አንብቦታል። ነገር ግን አንድ ሱባዔ በእኔ ላይ ታገሥ በዚህ ሱባዔ በአርዮስ ላይ አንዳች ነገር ካልደረሰ ይህ ካልሆነ ሃይማኖቱ መሐላውም እውነት ነው እኔም ተቀብዬ ከካህናቱ ጋር እቀላቅለዋለሁ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም ከእሳቸው ጋራ አንድ ይሆናል"።
❤ ንጉሡም አባት እለእስክንድሮስን እንዲህ አለው "እወቅ እኔ ስምንቱን ቀኖች እታገሥሃለሁ አርዮስን ካልተቀበልከው በአንተ ላይ የፈለግሁትን አደርጋለሁ።" ከዚህም በኋላ ከንጉሡ ዘንድ ወጥቶ ወደ ማደሪያው ሔደ ቤተክርስቲያንን ከአርዮስ መርዝ ያድናት ዘንድ በዚያ ሱባዔ እየጾመና እየጸለየ ወደ እግዚአብሔር ሲለምን ሰነበተ።
❤ ከዚያም ሱባዔ በኋላ አርዮስ መልካም ልብስን ለበሰ ወደ ቤተክርስቲያንም ገብቶ በመሠዊያው ፊት ከካህናቱ ጋራ ተቀመጠ። ከዚህም በኋላ አባ እለእስክንድሮስ እያዘነና እየተከዘ ገባ ከኀዘኑም ብዛት የተነሣ የሚሠራውን አላወቀም የቅዳሴውንም ሥርዓት ሊጀምር ቆመ። ያን ጊዜ የአርዮስ ሆዱ ተበጠበጠና "ወጥቼ ልመለስ" አለ ይህንንም ብሎ ወደ መጸዳጃ ቦታ ወጣ። ሊጸዳዳም በተቀመጠ ጊዜ አንጀቱና የሆድ ዕቃው ሁሉ ወጣ በዚያውም ላይ ሞተ። በዘገየም ጊዜ ሊፈልጉት ወጡ በመጸዳጃውም ቦታ ሬሳውን ወድቆ አገኙት። ለዚህም ለአባት እለእስክንድሮስ ነገሩት እርሱም አደነቀ የከበረች ቤተክርስቲያኑን ያልጣላት ምስጉን የሆነ ክርስቶስንም አመሰገነው።
❤ ንጉሡም በሰማ ጊዜ አደነቀ ከሀዲ አርዮስም በሐሰት እንደማለና በሽንገላ እንደጻፈ አወቀ። የዚህንም አባት የእለእስክንድሮስን ቅድስናውን ዕውነተኛነቱ ሃይማኖቱም የቀናች መሆኗን የአርዮስንም ሐሰተኛነቱንና ከሀዲነቱን ተረዳ።
❤ አንድ የሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስንም አመሰገነው መለኮታቸውም አንድ እንደሆነ ታመነ። ይህም አባት በበጎ ሥራ ጸንቶ ኖረ ለምለም ወደ ሆነ እርግናም ደርሶ ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔደ የሕይወት አክሊልንም አገኘ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ እለስክንድሮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 18 ስንክሳር።
✝️ ✝️ ✝️
❤ "#ሰላም_ለከ_እለእስክንድሮስ ሥዩም። በዕብረሬት ዘወረደ ኃይለ አርያም። ለአርዮስ ውቁይ በሰይፈ መርገም። እስከ ኢተርፈ ሎቱ እንበለ አነዳ ወዐፅም። ንዋየ ውስጡ ተክዕወ ከመ ዐፍዕ ዘላህም"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የነሐሴ_18።
