ru
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

Открыть в Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

Больше
611
Подписчики
-124 часа
-17 дней
-1030 дней
Архив постов
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቤተልሔም ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጡ። ​ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት
+2
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቤተልሔም ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አስቀመጡ። ​ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በ13ኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸው በጥንታዊውና ታሪካዊው የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ደረጃውን የጠበቀ የቤተልሔም ግንባታ ለማከናወን  የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #የካቲት ፳፬ (24) ቀን። ❤ እንኳን #ለከበረ_አባት ለንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ወታደር አለቃ ለነበረው ብዙ ተአምራትን ላደረገ፤ ብዙ ሰዎችን ያጠፋውን ታላቅ ከይሲ በጸሎቱ ለገደለው #ለኤጲስቆጶስ_ቅዱስ_አጋቢጦስ ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከከበሩ በጋዛ ሰማዕት ከሆኑ #ከጢሞቴዎስ፣ ከቆጵሮስ ከአገረ #ከሚናስ ከመታሰቢያቸው ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #ኤጲስቆጶስ_ቅዱስ_አጋቢጦስ፦ ይህም አባት በከሀድያን ነገሥታት በዲዮቅልጥያኖስና በመክስምያኖስ ዘመን ነበር። ወላጆቹም ደጎች ምእመናን ነበሩ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተምረውት ዲቁና ተሾመ። ከዚያም በኋላ እናትና አባቱን ትቶ ወደ አንድ ገዳም ሔደ የሸመገሉ መነኰሳትን አገለገለ። ከእርሳቸውም በጎ አምልኮትን አገለገለ። ከእርሳቸው በጎ አምልኮትን ተማረ አረጋውያኑንም እያገለገለ በገድል ተጠመደ ያለ ማቋረጥም በጾም በጸሎትና በስግደት ይተጋል ከጥዋትም እስከ ምሽት በመጾም የሽንብራ አሠር የሚመገብ ሆነ። ከእንቅልፍም ጋር ሊታገል በወደደ ጊዜ ከሽምብራ አሠር ጋር አመድ እየተመገበ ሰማንያ ቀን ኖረ ከዚህም ተጋድሎ ውስጥ እያለ ኃይሉ ግን ይጨመርለት ነበር። ለአረጋውያንም አገልግሎቱን አላስታጐለም ሲጠራቸው ጌቶቼ ይላቸዋል የጽድቅንና የትሩፋትን ሥራ ሁሉ ፈጸመ። ❤ እግዚአብሔርም የሚያስደንቁ ብዙዎች የሆኑ ታላላቅ ተአምራቶችን በእጆቹ ገለጠ። ከእርሳቸውም አንዲቷን ብላቴና አዳናት እርሷም እንደ ዕንጨት የደረቀች እስከምትሆን ብዙ ዘመን ጭንቅ በሆነ ደዌ ታማ የኖረች ናት። ዳግመኛም ብዙ ሰዎችን ያጠፋውን ታላቅ ከይሲ በጸሎቱ ገደለው። ከሰውና ከእንስሳም፡አስጨናቂ የሆኑ በሽታዎችን አስወገደ። የተጋድሎውና፡የኃይሉ ጽናት ወሬው በተሰማ ጊዜ ስሙ ሉክያኖስ፡የሚባል መኰንን ወደርሱ ልኮ አስመጥቶ ያለ ውዴታው በግድ የጭፍራ አለቃ አድርጎ ሾመው እርሱ ግን ተጋድሎውን አልተወም ጾምንም ጸሎትንም የትሩፋትን ሥራ የሚጨምር ሆነ እንጂ የቀደመ ሥራውን አልተወም በጥቂት ቀኖችም ዲዮቅልጥያኖስ መክስምያኖስን እግዚአብሔር አጠፋቸው አምላክን የሚወድ ጻድቅ ሰው ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ነገሠ ይህም ቅዱስ ከጭፍራ ውስጥ ይወጣ ዘንድ ምክንያት የሚሻ ሆነ። ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እጅግ የሚወደው መልከ መልካም የሆነ ወጣት ብላቴና ነበር ክፉ ጋጌንም ተጫነበት በቀንም በሌሊትም ታላቅ ሥቃይን የሚያሠቃየው ሆነ ቅዱስ አጋቢጦስንም ከሚያውቁት ውስጥ አንድ ሰው በአየው ጊዜ "የወታደር አለቃ አጋቢጦስ ቢመጣ በአዳነህ ነበር" አለው የታመመውም "እርሱ በንጉሥ ጭፍራ ሥርዓት ውስጥ ያለ፡፡ በውኑ ይህን ሥራ መሥራት ይችላልን" አለ ሰውዬውም ገድሉንና ሥራውን ሁሉ አስረዳው። ጋጌን ያደረበትም "በእውነት ሊያድነኝ ዘንድ የወታደር አለቃ አጋቢጦስን ፈጥናችሁ አምጡልኝ" አለ። ንጉሥም ይህን በአወቀ ጊዜ ቅዱስ አጋቢጦስን እንዲአመጡት አዘዘ በመጣ ጊዜም በወጣቱ ላይ ጸለየ በከበረ መስቀልም አማተበው በዚያንም ጊዜ በእግዚአብሔር ኃይል ዳነ ንጉሡም በዚህ ደስ ብሎት ቅዱስ አጋቢጦስን አከበረው "ምን እንዳደርግልህ ትሻለህ?" አለው እርሱም ንጉሡን "ከወታደርነት ውስጥ አሰናብተኝ" አለውና አሰናበተው አስቀድሞ ወደ ነበረባትም ቦታው ተመለሰ ብዙ ዘመናትም እጅግ እየተጋደለ ኖረ። ❤ ከዚህም በኋላ የዚያች አገር ኤጲስቆጶስ ይዞ ቅስና ሾመው ይህም ኤጲስቆጶስ በሞተ ጊዜ ቅዱስ አጋቢጦስን ይሾምላቸው ዘንድ ሕዝቡ ሊቀ ጳጳሳቱን ለመኑት እርሱም ሾመላቸው መልካም ተናጋሪዎች የሆኑትን የክርስቶስን መንጋዎች በበጎ አጠባበቅ ጠበቃቸው። እግዚአብሔርም የትንቢትን ጸጋ የተሠወረውንም የማወቅ ድንቆች ተአምራቶችንም የማድረግ ሀብትን ሰጠው። በሥውር ኃጢአትን ሆነ የሚሠሩትን ኃጢአተኞች የሚገሥጻቸው ሆነ በንስሐም እስኪመለሱ ከመቅደስ ያርቃቸዋል። ❤ ዳግመኛም በገድሉ መጽሐፍ ተጽፎ የተገኘ የታላቅ ወንዝ ወራጅ ውኃን በመስቀሉ አቁሞ ወደ ሌላ መንገድ መለሰው የዕውር ዐይኖችንም ገለጠ ለምጻሞችንም አነጻ ብዙዎች በሽተኞችንም አዳነ። ያማረና መልካም የሆነ ተጋድሎውንና አገልግሎቱን ፈጽሞ በዚህች ዕለት የካቲት24 ዐረፈ፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ አጋቢጦስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት24 ስንክሳር።                             ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለማትያስ_ቆጵሮስ_ወሬዘ። #ጢሞቴዎስ_ዓዲ ዘብሔረ ጋዛ። ትኩላን ዕፀው ለማየ ሃይማኖት ኀበ ሙሐዛ። ይደዩ ውስተ አንፍየ እምፍሬሆሙ መዓዛ። ለጺዓተ ጊጋይ ሕሱም ዘያለስሕ ሕምዛ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_24።                         ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወበትእዛዝከ ይቀውም ዕለት። እስመ ኵሎ ቀነይከ። ሶበ አኮ ሕገከ ተመሐርየ ውእቱ"። መዝ 118፥51-52። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 13፥1-11፣ 1ኛ ጴጥ 2፥16-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 19፥11-21። የሚነበበው ወንጌል ማር 1፥23-29። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም በዓልና የጾም ወራት። ለሁላችንም ይሁንልን።                    

❤ ከዚህም በኋላ ደግሞ አውሳብዮስን ወደ ግብጽ አገር ወስደው በዚያ ይገድሉት ዘንድ ህርማኖስ ንጉሡን መከረው "እርሱ በዚች አገር ከኖረ ያገር ሰዎችን በላይህ ያስነሣብሃልና ያሰብከው ምንም ምን መሥራት አትችልም" አለው። ንጉሡም ቅዱስ አውሳብዮስን ጽኑዕ ሥቃይን ያሠቃዩት ዘንድ ወደ ግብጽ አገር ወደ ቅፍጥ ገዥ ሉልያኖስ ዘንድ እንዲወስዱት ጻፈ ወደ መኰንን ሉልያኖስም በደረሰ ጊዜ በመንኰራኵር ሕዋሳቱን በመቈራረጥ በግርፋት አሠቃዩት። ዳግመኛም በብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት ጌታችንም መልአኩን ልኮ ከመከራው ሁሉ አዳነው አጽናንቶም አረጋግቶ ያለ ጉዳት አስነሣው። ነፍሱንም ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት ወሰዳት የጻድቃንና የሰማዕታትንም መኖሪያ አየ ለርሱና ለአባቱ ለዘመዶቹም ያዘጋጀላቸውን ቦታዎች አይቶ ነፍሱ እጅግ ደስ አላት። ከዚያም በኋላ ወደ እሳት ማንደጃ ውስጥ ይጨምሩት ዘንድ መኰንኑ አዘዘ ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ወርዶ እሳቱን እንደ ጠል አቀዝቅዞ ያለ ጥፍት የከበረ አውሳብዮስን አወጣው። መኳንንቱም እንዲህ ብለው መከሩት "መኰንን ሆይ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ እዘዝ ከእርሱም ትግል ታርፋለህ" እርሱም የአውሳብዮስን የከበረች ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና የካቲት23 ቀን ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አውሳቢዮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የካቲት23 ስንክሳር።                               ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለከ_ወልደ_ፋሲለደስ_ሊቀ_ሖራ። ወቢጸ ብፁዕ መርቆራ። አውሳብዮስ ሰማዕት ትቤዝወኒ እምከራ። አርኢ ሊተ ለአምላክ መሐሪ ለአባልከ ምታራ። አመ ለነፍስየ ይትነበብ እኩይ ምግባራ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_23።                

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #የካቲት ፳፫ (23) ቀን። ❤ እንኳን #ለሐዋርያውና_ለሰማዕቱ_ለቅዱስ_ፖሊካርፐስ ለዕረፍቱ በዓል፣ ለክቡር #ለቅዱስ_ፋሲለደስ ልጅ ለከበረ #ለቅዱስ_አውሳብዮስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ ከምስራቃዊ #ቅዱስ_ቴዎድሮስ አገልጋይ #ከቅዱስ_አውስግንዮስ ከምስክርነቱ መታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #ሐዋርያውና_ሰማዕቱ_ቅዱስ_ፖሊካርፐስ፦ ይኽም ቅዱስ ሐዋርያና ሰማዕት የሆነው ፖሊካርፐስ ከ70 ዓ.ም እስከ 156 ዓ.ም የነበረ ሲሆን ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በራእዩ ከመሰከረላቸው ከ7ቱ አብያተ ክርስቲያናት የአንዱ ይኸውም የሰርምኔስ ዻዻስ የነበረ ነው፡፡ ይኽም ቅዱስ ከሐዋርያው ከቅዱስ ዮሐንስ ቃል በቃል የተማረና ደቀ መዝሙሩ የነበረ ነው፡፡ አቡነ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ የቅዱስ ፖሊካርፐስ ባልንጀራው ነበር፡፡ ቅዱስ ፖሊካርፐስ ከ46 ዓመታት በላይ በፍጹም ትጋት ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎ አረማውያን በ86 ዓመቱ በአደባባይ በእሳት አቃጥለው በሰማዕትነት አርፏል፡፡ ❤ የቅዱስ ፖሊካርፐስ የሰማዕትነቱ ዜና የተገኘው የራሱ የሆነችው የሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን ሰማዕትነቱን በአካል በተከታተሉ ወንድሞች አማካኝነት ጽፋ ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ከበተነችው መልእክት ነው። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የሰማዕታት የሰማዕትነታቸው ሁኔታ፣ ሳይፈሩ ሰውነታቸውን ለሰይፍ ለስለት እንዴት እንደሰጡ፣ ስለ ክርስቶስ ለመመስከር እንዴት ይጨክኑ እንደነበር በሙሉ ዜና ገድላቸው እየተጻፈ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ይሰራጭነበር። እንደ አግናጥዮስ ሁሉ በሮም ፖሊካርፐስ ሰማዕት በሆነበት ጊዜም በሰምርኔስ ከተማ የሕዝብ በዓል ተደርጎ ነበር:: እንደልማዳቸው በዓሉ በሚከበርበት በእስታድየማቸው የአራዊት ትርኢት ነበር። አሬኒከስ የተባለ አንድ ክርስቲያንም "የአሕዛብ ጣዖታትን ካላመለክህ ለአራዊት እንሰጥሃለን" ብለውት አሻፈረኝ ብሎ በመፅናቱ በዚያ በአራዊት ተበልቶ ሰማዕት ሆነ። በዚህ ጊዜም ሕዝቡ "ክርስቲያኖች እንዲህ እንዲፀኑ የሚያስተምራቸው ዋነኛው ፖሊካርፐስ ነው እርሱ ተይዞ ይምጣ" እያሉ ጮሁ። ❤ ቅዱስ ፖሊካርፐስ የሞት ፍርድ ሲፈረድበት ፀንቶ በከተማዋ ቢቆይም ምእመናን እንዲሸሽ እያለቀሱ ስለለመኑት ባጠገብ ወዳለች መንደር ሸሸ። በዚያ ሳለ ሰማዕት እንደሚሆን በራእይ ተረድቶ እንደሚሞት ለወንድሞችና እህቶች ነገራቸው። ወዲያው በጥቆማ ተይዞ ወደ ሰምርኔስ ከተማ እያንገላቱ ወስደው ሕዝብ በተሰበሰበበት በበዓሉ አደባባይ አቆሙት። እርሱም ክርስቶስ በሕዝብ አደባባይ ቆሞ የተቀበለውን መከራ እያሰበ የመከራው ተካፋይ ስላደረገው በፍጹም ደስታ መከራውን ይቀበል ነበር። በሕዝቡ ፊት አቁሞ የሚያናዝዘው ሹም ክርስቶስን እንዲክድ ብዙ ማግባቢያዎችንና ማስፈራሪያዎችን ቢያቀርብለትም ያለፍርሃት ፀንቶ ክርስቲያንነቱን ስለመሰከረ በእሳት እንዲቃጠል ተፈረደበት። ወታደሮቹ እሳቱ ውስጥ ከገባ በኋላ የሚያመልጠን መስሏቸው ለማጠር ሲዘጋጁ አይቶ "ወደ እሳቱ እንድገባ ያበረታኝ ጌታዬ በእሳቱ ውስጥም ፀንቼ እንድቆይ ያስችለኛል" አላቸው። ❤ ወታደሮቹ እጅና እግሩን አስረው ወደ እሳቱ ሲያቀርቡት አይኑን ወደ ሰማይ አቅንቶ እንዲህ በማለት የመጨረሻ ጸሎት አደረገ፦ "አቤቱ ልዑል እግዚአብሔር የተወደደው ልጅህ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ሆይ በልጅህ አንተን እንድናውቅ ሆነናል። የመላእክትና የኀይላት እንዲሁም የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ አንተ ነህ፤ ፍጥረታትም ሁሉ የሚኖሩት ባንተ ነው በመንፈስ። ቅዱስ አጋዥነት ለዘላለማዊ ሕይወት ትንሣኤ ያለፍርሃት ከክርስቶስ መከራ ተካፋይ ከሆኑት ከሰማዕታት ወገን እንድቆጠር ስላደረግኸኝ እና በዚህች ቀንና ሰዓት በሚገባ ስላስተማርኸኝ አመሰግንሃለሁ። እንደ እነርሱ ዛሬ በፊትህ ተቀብያለሁና እንደ መልካምና የተወደደ መሥዋዕት አድርገህ ተቀበልልኝ። አንተ አስቀድመህ እንዳሳየኸኝ እና እንዳዘጋጀኸኝ አንተ እውነተኛና ታማኝ አምላክ ነህና ስለሁሉ ነገር አመሰግንሃለሁ፣ አከብርሃለሁ፣ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ። ከሰማያዊው ዘላለማዊ ሊቀ ካህናት ከተወደደው ልጅህ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብርና ምስጋና ለአንተ ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን!።" ❤ የጸሎቱ ይዘት ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን ከምታስተምረው ምሥጢረ ሥላሴ ጋር አንድ አይነት ሲሆን ይህንኑም የመሰለ ጸሎት አላት። በዚህም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጥንታዊና ከምንጮቹ ከሐዋርያት የተረከበችው ለመሆኑ ታላቅ ማስረጃ ነው። ቅዱሱ ጸሎቱን ሲጨርስ በእሳቱ ውስጥ ወረወሩት። በቅዱሳኑ ላይ አድሮ ተአምር የሚሠራ እግዚአብሔር ለምእመናን መጽናኛ የሚሆን ድንቅ ተአምርን አደረገ። እሳቱ የቅዱሱን ሰውነት ዙሪያውን እንደግድግዳ ከቦ የማያቃጥለው ሆነ። ሕዝቡም እሳቱ እንዳላቃጠለው ባዩ ጊዜ "በጦር ተወግቶ ይሙት" እያሉ ጮሁ፤ ወታደሮቹም በጦር ወጉትና በዚህ ሰማዕትነቱን ፈጸመ። ክርስቲያኖች እንዳያመልኩት በሚል የከበረ ሥጋውን አቃጠሉ፤ በዚህ ጊዜ ደስ የሚያሰኝ የእጣንና የሽቶ መአዛ ሸተተ። ክርስቲያኖችም ተረፈ አፅሙን በክብር ወሰደው ቀበሩት ቤተ ክርስቲያንም በስሙ ሠሩለት። ከቅዱስ ፖሊካርፐስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከት ያሳትፈን በጸሎቱ ይማረን!።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የቅዱስ_ፋሲለደስ_ልጅ_ቅዱስ_አውሳብዮስ፦ ይህም የከበረ ፋሲለደስ ለአንጾኪያ መንግሥት የሠራዊት አለቃ ነው። ለመንግሥት ልጅችም አባታቸው ነው እርሱም ከፋርስ ሰዎች ጋር ጦርነት ውስጥ እያለ ዲዮቅልጥያኖስ የክብር ባለቤት ጌታችንን ክርስቶስን ክዶ ጣዖትን እንዳመለከ ሰማ። እጅግ አዝኖ ወደ ልጁ ወደ አውሳብዮስ ልኮ ይህን ነገረው የከበሩ የቤተ መንግሥት ሰዎች ዘመዶቹን ዳግመኛ ጠራቸው እነርሱም የንጉሥ ልጅ ዮስጦስ፣ አባዲር፣ ገላውዴዎስና ቴዎድሮስ ከእርሳቸውም ጋር ያሉትን ጠርቶ ስለ ከሀዲው ንጉሥ ነገራቸው። ሁሉም እጅግ አዘኑ ዳግመኛም እንዲህ አላቸው "እኔ ደሜን አፈሳለሁ" ሁሉም በዚህ በጎ ምክር ተስማምተው እርስ በርሳቸው ተማማሉ። ጠላቶቻቸውንም ድል አድርገው ወደ አገራቸው በተመለሱ ጊዜ ንጉሡ ከሠራዊቱ ጋር ወጥቶ በደስታ ተቀበሏቸው። ❤ ከዚህም በኋላ የቅዱስ ፊቅጦር አባት ህርማኖስ ለቅዱሳኑ ጣዖትን እንዲአቀርብላቸውና እንዲሰግዱለት ንጉሡን መከረው ንጉሡም ህርማኖስ እንደ መከረው አደረገ። በዚያንም ጊዜ ቅዱሳንን ጠርቶ እንዲህ አላቸው "እኔ እጅግ እንደምወዳችሁ እናንተ ታውቃላችሁ አሁንም ለአጵሎን ሰግዳችሁ ልቤን ደስ ታሰኙ ዘንድ ከእናንተ እሻለሁ"። ቅዱሳንም ሰምተው እጅግ ተቆጡ አውሳብዮስም ንጉሡን ሊገድለው ሰይፋን መዘዘ ንጉሡም ሸሽቶ ተሸሸገ ከንጉሥም ባለሟሎች ብዙዎችን ሥራዊቱንም ጭምር ገደለ የከበረ ፋሲለደስም ባይከለክላቸው ከንጉሥ ቤት ምንም ሰው ባልቀራቸው ነበር።

❤ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ከአደዋ ጦርነት ከተመለሱ በኋላ በአዲስ አበባ በምትበል ከተማው መካከል በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ቤተክርስቲያን አሠራ። ስሟንም ገነተ ጽጌ ብለው ሰየሟት። ቅዱስ ጊዮርጊስ በጦርነት ቦታ ሁሉ ይረዳው ነበርና። ልመና ክብሩ በኛ ለዘላለሙ በዕውነት ይደረግል። በረከቱ ከእኛ ጋር ትሁን እኛንም በቅዱስ ጊዮርጊስ አማላጅነት ይማረን ለዘለዓለሙ አሜን!!! ምንጭ፦ ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተአምር ዐሥራ ሰባት።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወይርአዩ አሕዛብ በቅድመ አዐይንቲነ። በቀለ ደሞሙ ለአግብርቲከ ዘተክዕወ። ይባዕ ቅድሜከ ገዐሮሙ ለሙቁሓን"። መዝ 78፥10-11። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 26፥46-55።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር። ነገሥተ ምድር ሰብሕዎ ለእግዚአብሔር። ወዘምሩ ለአምላክነ"። መዝ 67፥31-32 ወይም መዝ 79፥6። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ቆሮ 4፥7-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 4፥12-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 9፥23-32። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 17፥1-7። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም ዓድዋ በዓልና የጾም ወራት። ለሁላችንም ይሁንልን።                 

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #የካቲት ፳፫ (23) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያ°ገበዝ (ጠባቂ) ለአድዋው አርበኛ፣ ለፍጡነ ረድኤት፣ ለገባሬ ተአምር #ሊቀ_ሰማዕታት_ለቅዱስ_ጊዮርጊስ_በ1888ዓ.ም በአድዋ ጦርነት ንጉሠ ነገሥትን ምኒልክና ሠራዊቱ ለረዳበት፤ ኢትዮጵያ በሮማውያንን (ጣልያንን) ድል ለተቀዳጀችበት ለ130 (ለአንድ መቶ ሠላሳኛው) ለዓድዋ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                                                             ✝ ✝ ✝ ❤ ልመናው ጸሎቱ በረከቱ አማላጅነቱ በዕውነት በመላው ሕዝበ ክርስቲያን ይደረግልንና #ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ያደረገው_ተአምር_ይህ_ነው፦ በዚያን ወራት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ከአንድ ሺህ ስምንት መቶ ሃምሳ አራት ዓመት በኋላ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በነገሡ በሃያ ስድስት ዓመት የምኒልክ የጦር አለቃ ገበየሁ ድል ከአደረጋቸው በኋላ እንደገና ምኒልክም ወግተው ኢትዮጵያን በቅኝ አገዛዝ ሊገዙ የሮም ሰዎች መጡ። ❤ ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ (ዓፄ) ምኒልክ መስከረም፯ ቀን ፲፰፻፹፰ (1888 ዓ.ም ) ላይ "እግዚአብሔር በቸርነቱ እስከ አሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም እስከ አሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለ እኔ ሞት አላዝንም፡፡ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፡፡እንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት፤ እግዚአብሔር የወሰነልንን የባህር በር አልፎ መጥቷልና እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስከ አሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው፤ ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም አንተም እስከ አሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ስለዚህ ስንቅህን በአህያ አመልህን በጉያህ ይዘህ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፤ ለሚስትህ፤ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን በኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም፡፡ ማርያምን! በዚህ አማላጅ የለኝም"፡፡ ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ" ብለው አዋጅ አስነገሩ፡፡ ዳግኛም በፈረሶታቸው መጣብር ላይ በጦራቸው አንደበት ላይ የመስቀል ምልክት እንዲያደርጉ ጭፍሮችን አዘዛቸው መስቀል ጠላትን ድል አድራጊ እንደሆነ አስቀድሞ ያውቅ ነበርና። ❤ አዋጁን ካስነገሩ በኋላ ከዚያም ተነሥቶ ወደ ትግራይ ክፍለ አገር ዘመቱና ከትግራይ አውራጃ አንዷ የምትሆን አድዋ የምትባል አገር ደረሱ፡፡ የሣህለ ማርያም (ዳግማዊ ምኒልክ) ሚስት ወለተ ሚካኤል (እቴጌ ጣይቱም) በንጉሡ ትዕዛዝ ታቦተ ጊዮርጊስን አስይዘው ከሊቀ ጳጳሱ ከአባ ማቴዎስ እንዲሁም ከቀሳውስቱና ከመነኰሳቱ ጭምር ከንጉሡ ጋር ወደ ጦርነቱ ተጓዘች፡፡ በዚያም ጊዜ የአክሱም ጽዮን መነኰሳትና ካህናት የእመቤታችንን ሥዕል ይዘው ወደ ንጉሡ ወደ ምኒልክ መጥተው ከሊቀ ጳጳሱ ከነአቡነ ማቴዎስ ጋር ተቀላቀሉ ከዚያም ሌሊቱን ሙሉ ጸሎት ምሕላ ሲያደርሱ አደሩ። ❤ ቅዳሜ ማታ ለእሑድ አጥቢያ የካቲት ሃያ ሁለት ቀን ነው ንጉሡ ሣህለ ማርያም (ምኒልክ) የጦር ልብሱን ለብሰው ከሠራዊቱ ጋር ወደ ጦር ግንባር ሄደ፡፡ ከዚያም ከሮማውያን የጠላት ጦር ጋር ተገናኝቶ ከሌሊቱ ዐሥራ አንድ ሰዓት ጦርነቱን ጀመረ፡፡ የንጉሡ የሣህለ ማርያም (የምኒልክ) ሚስት ወለተ ሚካኤል (እቴጌ ጣይቱም) ሌሊት በታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስና በእመቤታችን ሥዕል ፊት በጸሎትና በስግደት እያደረች ሲነጋ ወደጦርነቱ ቦታ በመሄድ እጅግ ለሚያስደንቅ የአነጋገሯ ኃይል ቃል በጦርነቱ መካከል እየተገኘች ለንጉሡ ወታደሮች የሞራልና የብርታት ድጋፍ ትሰጣቸው ነበር። በእውነትም ለተመለከታት ሁሉ እንደ ኃይለኛ ተጋዳይ አርበኛ ትመስል ነበር እንጂ የሴቶች የተፈጥሮ ባሕርይ በእርሷ ላይ አይታይባትም ነበር። የንጉሡም ወታደሮች የንግሥቲቱን የጀግንነት አነጋገር በሰሙ ጊዜ በእሳት ላይ እንደተጣደ የብረት ምጣድ ልባቸው ጋለ ይልቁንም ላም እንዳየ አንበሳና የፍየል መንጋ እንዳየ ነብር እየተወረወሩ በጦርነቱ መካከል በመግባት የጠላትን ጦር በሰይፍ ይጨፈጭፋት ነበር። መጽሐፍ ሹመትን ሽልማትን ያየ አርበኛ ከጦርነት ከሰልፍ ወደኋላ አያፈገፍግም ብሎ ተናግሯልና። በዚያም ጊዜ ንጉሡ ሣህለ ማርያም (ምኒልክ) በጦርነቱ መካከል ሳለ ሊቀ ጳጳሱ አባ ማቴዎስ እንዲሁም የአክሱም መነኰሳትና ሌሎቹ ካህናት በሙሉ ታቦተ ጊዮርጊስንና ሥዕለ ማርያምን ይዘው ከንጉሡ በስተኋላ በደጀንነት ቆመው ጸሎተ ምህላ ያደርሱ ነበር። ንግሥቲቱ ወለተ ሚካኤል (እቴጌ ጣይቱም) በጸሎት ጊዜ በመዓልትም በሌሊትም ከእነርሱ አትለይም ነበር። የጽዮን አገልጋዮችም በእግዚአብሔር የሕጉ ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር። ❤ በዚህም ዕለት ይኸውም የካቲት ሃያ ሦስት ቀን በሮማውያንና በኢትዮጵያውያን መካከል ከፍተኛ ጦርነት ሆነ በዚህም ጊዜ በሰማይ ታላቅ ተአምር ተደረገ። ማለትም የቀስተ ደመና ምልክት ታየ ከዚያም ከቀስተ ደመናው ውስጥ መልኩ አረንጓዴ የመሰለ ጢስ ይወጣ ነበር፡፡ ከዚህም ጢስ ውስጥ እንደ ክረምት ነጐድጓድ ያለ ድምጽ ተሰማ፡፡ ከዚህም የነጐድጓድ ድምጽ የተነሳ በሮማውያን ወታደሮች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤና ሽብር ሆነ ለመዋጋት አልቻሉም፡፡ ይልቁኑ ኃያሉ ገባሬ ተአምር ማር ቅዱስ ጊዮርጊስ በአምባ ላይ ፈረሱ ተቀምጦ ከነፋስ ሩጫ ይልቅ እየተፋጠነ በአየር ላይ በተገለጸ ጊዜ በግንባራቸው ፍግም እያሉ ወደቁ፡፡ "የኢትዮጵያ ህዝብ አምላካቸው ሊረዳቸው መጣ እንግዲህ ማን ያድኅነናል" አሉ ምድርም ጠበበቻቸው በዚህን ጊዜ የኢትዮጵያ ሠራዊት የሮምን የጦር ሠራዊት ፈጁዋቸው የተረፉትንም ማረኳቸው ፈጽመውም እስኪያጠፏቸው ድረስ በሮማውያን ላይ በእግዚአብሔር ሥልጣን የኢትዮጵያውያን እጅ እየበረታ ሄደ፡፡ ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሣህለ ማርያም (ምኒልክ) በእግዚአብሔር ኃይልና በተአምራት አድራጊው በቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳይነት የሮማውያንን የጦር ሠራዊት ድል አድርገው የድል አክሊል ተቀዳጅተው ተመለሱ፡፡ ❤ ስለዚህም በዳዊት የምስጋና ቃል የድል ዘውድ ያቀዳጀኝን እግዚአብሔር "ባለ ዘመኔ ሁሉ አመሰግነዋለሁ ለፈጣሪዬ እዘምራለሁ" አለ ሕዝቡም ሁሉ "በክብር ከፍ ከፍ ያለ እግዚአብሔርን በፍጹም ምስጋና እናመስግነውለን የሮማውያንን ኃይል ቀጥቅጦ አጥፍቷልና ሠረገሎቻቸውንም ሠባብሯልና ሠራዊቱንም ሁሉ በምድር ላይ በትኗልና" እያሉ አመሰገኑ። በፈጣሪው በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል በጦርነቱ መካከል የረዳውን ቅዱስ ጊዮርጊስንም በፍጹም ማድነቅ አደነቁ። የሮማም የጦር ሠራዊት በኢትዮጵያውያን ፊት ተዋረዱ ዳግመኛም በኢትዮጵያ ላይ ራሳቸውን ከፍ ከፍ አላደረጉም። በምኒልክም ዘመነ መንግሥት ኢትዮጽያ ከጦርነት ለዓርባ ዓመት ያህል አረፈች።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤ ❤ እንኳን #ለዐቢይ_ጾም_ሦስተኛ_ሳምንት_ለምኵራብ እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የምኵራብ_መዝሙር፦ ሃሌ ሉያ ፭ "#ቦአ_ኢየሱስ_ምኵራበ_አይሁድ ወመሀረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እምሥዋዕት #አነ_ውእቱ_እግዚአ_ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት #እግዚእ_ውእቱ_ለሰንበት_ወልደ_እጓለ_እምሕያው ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ #ቤትየሰ_ቤተ_ጸሎት_ይሰመይ_ቦአ_ምኵራቦሙ ወገሠፆሙ ያርምሙ አንበሩ ምህሮቶ ሞገሰ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሳአ አፋሁ"። ትርጉም፦ #ኢየሱስ_ወደ_አይሁድ_ምኵራብ_ገባ ሃይማኖት ቃል አስተማረ ከመስዋዕት ምጽዋትን አላቸው፤ #የሰንበት_ጌታዎ_የምሕረት_አባትዋ_እኔ_ነኝ አላቸው፤ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታዋ ነውና የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ ቤቴ የጸሎት ቤት ነው (ይባላል)  ምኵራባቸው ገባ ዝም ይሉ ዘንድም ገሠጻቸው። ጽምጹና ቃሉን ሞገስ (መውደድ) የነገሩትን የአፉን ለዛ አደነቁ። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በጾመ_ድጓው_ላይ።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #ምኩራብ፦ የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሣምንት ምኩራብ ይባላል። ❤ ምኵራብ ፦ የአይሁድ መቅደስ ቤተ ጸሎት ታላቅ አዳራሽ ነበር። ❤ በዚህ ሣምንት ጌታ በመዋዕለ ስብከቱ፡ በምኩራብ ገብቶ ማስተማሩ ይነገራል ማቴ 4፥23፣ ማር 1÷21፣ ሉቃ 4÷15። ❤ ክርስቶስ ለማስተማር በገባ ጊዜ አይሁድ ቤተ ጸሎቱን እንደ ስያሜው ሳይሆን መሸጫና መለዋወጫ መገበያያ አድርገውት ስለአገኛቸው ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ መሸጫ መለዋወጫ አደረጋችሁት ብሎ ሰዎችንና እንስሳትን በጅራፍ እየገረፈ ገበታቸውን እየገለበጠ አባሮአቸዋል ስለዚህ ይህ ሳምንት ለታሪኩ መታሰቢያ ምኩራብ ተብሉአል ማቴ 21፥12-13፣ ማር 11፥15-18፣ ሉቃ 19÷45-47 ዮሐ 2÷14-16። ❤ ቅዱሳን ሐዋርያትም እንደ ጌታችን ለጸሎትና ለትምህርተ ወንጌል ወደ ምኩራብ ይወጡ ነበር፡፡ የሐዋ ሥራ 3፥1፣ የሐዋ ሥራ 13፥5፣ የሐዋ ሥራ14፥1፣ የሐዋ 17-1፣ የሐዋ.10-17፣ የሐዋ ሥራ 18-4፣ የሐዋ ሥራ 19፥8። 1. ምኩራብ ፦ ለአምልኮና ለትምህርት ለሕብረተሰቡም ጠቅሞአል። 2. ምኩራብ በአለቆች ይመራ ነበር ማር 5፥ 22፣ የሐዋ ሥራ 3÷14-15፣ የሐዋ18፥8። 3 በየሳምንቱ ሕዝቡ ሁሉ በምኩራብ ይሰበሰቡ ነበር፡፡ ሉቃ 4÷16፣ የሐዋ ሥራ 15 21፡፡ 4 ወንዶችና ሴቶች ለየብቻቸው ይቀመጡ ነበር። 5 የእግዚአብሔር ቃል ሲነበብ አንባቢው እንዲሰማ በተዘጋጀው ከፍተኛ ቦታ ይቆም ነበር። የክብር ወንበሮች ከዚህ ቦታ ፊት ለፊት ነበሩ ማቴ 23÷6፣ ሉቃ 4፥20። ምንጭ፦ ከአምኃ ሥላሴ ፌስቡክ ፔጅ የተወሰደ።                                                                                 ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "እስከ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ። ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ። ወቀጻዕክዋ ለጾም ለነፍስየ። መዝ 68፥9-10። የሚነበቡት መልዕክታት ቈላ 2፥16-ፍ.ም፣ ያዕ 2፥14-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 10፥1-9። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 2፥12-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም የጾም ወራትና ዕለተ ሰንበት (ምኵራብ) ለሁላችንም ይሁንልን።                    

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #የካቲት ፳፪ (22) ቀን። ❤ እንኳን የፋርስ ንጉሥ ልጅ በጸሎቱ ከነበረባት ጋኔን ለፈወሳት #ለኤጲስቆጶስ_ለአባ_ማሩና ለዕረፍቱ በዓል መታሰቢያና በከሀዲ በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን #በፋርስ_አገር_ለተገደሉ_ሰማዕታት ለሥጋቸው ለፈለሰበት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በዚች ቀን በተጨማሪ ከሚታሰቡ፦ ከከበረ #ከአባ_ቡላና_ከሦስት_መቶ_ሰማንያ ሰማዕታት ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ማሩና፦ ኤጲስቆጶስ ማሩናንም ስለ ድንቆች ተአምራቶቹ ስለ ትሩፋቱና ስለ ጽድቁ የአኖርዮስና የአርቃድዎስ አባት ታላቁ ቴዎዶስዮስ ንጉሥ ላከው ከእርሱም ጋር እጅ መንሻ በመካከላቸው ስለ አለው ፍቅር ተላከ። ወደ ሳቦር ወደ ፋርስ ንጉሥም በደረሰ ጊዜ ታላቅ ክብርንም አከበረው በቤተ መንግሥቱም እልፍኝ ውስጥ አኖረው። ❤ ይህ ቅዱስም የንጉሡ ልጅ ጋኔን አድሮበት እንደታመመች በሰማ ጊዜ የከበረ አባ ማሩና ብላቴናዪቱን ጠርቶ በፊቱ አቁሞ በላይዋ ጸለየ ጋኔኑም ከእርሷ ወጥቶ ዳነች ንጉሡም ልጁ እንደ ዳነች አይቶ እጅግ ደስ አለው የአባ ማሩናንም ፍቅርና አክብሮት ጨመረ። ከዚህም በኋላ አባ ማሩና በፋርስ አገር በሰማዕትነት ስለሞቱ የከበሩ ሰማዕታት ሥጋቸውን ስለ መሰብሰብ ከንጉሥ ዘንድ ፈለገ ንጉሡም የሰማዕታትን ሥጋቸውን ይሰብስቡ ዘንድ አዘዘ ያች ቤተ ክርስቲያንም በዚች ዕለት ከበረች። ዳግመኛም በታላቋ ከተማ ውስጥ በከበረ አባ ማሩና ስም ያማረች ቤተ ክርስቲያንን ሠሩ እርሷም ማረፊያ የተባለች ናት። ❤ ከዚህም በኋላ ይህ አባት ወደ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ተመልሶ በሮሜ አገር ሁለት ዓመት ተቀመጠ የእነዚያ ሰማዕታት ቤተ ክርስቲያን በከበረችበት በዚች በየካቲት22 ዕለት ዐረፈ ከቤተ ክርስቲያኒቱም ክብር ጋር በዓሉንና መታሰቢያውን የሚከብሩበት ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የአባ ማሩና በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት 22 ስንክሳር።                              ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለማሩና_ሠናየ_ተልእኮ_ቀሲስ። ወዓዲ ካዕበ ኤጲቆጶስ። ቤተ ሰማዕታት ሐኒፆ በአገረ ፋርስ። በዕለተ ቀደሳ #በስመ_ኢየሱስ_ክርስቶስ። ተጸውዐ ዮም ለመርዓ ሐዳስ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_22።                  

❤ በመነኰሱም ጊዜ በብዙ ተጋድሎ ተጠመዱ ይልቁንም አባ ዘካርያስ በዚያም ወራት አረጋውያን አባ አብርሃምና አባ ገዐርጊ ነበሩ ወደ እርሳቸው እየመጡ በሥራቸው ሁሉ ያረጋጉዋቸውና ያጸኑዋቸው ነበር። የአገረ ስሐ ኤጲስቆጶስም በዐረፈ ጊዜ ሕዝቡ አባ ዘካርያስን አሰቡት እርሱንም ይሾሙላቸው ዘንድ ስለ አባ ዘካርያስ እየለመኑ ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ የመልእክትን ደብዳቤ ጻፈ። ሊቀ ጳጳሳቱም ወደ አስቄጥስ ገዳም ልኮ አባ ዘካርያስን ወደ እርሱ አስመጣው በአገረ ስሐ ላይም ኤጲስቆጶስነት ሾመው ሊቀ ጳጳሳቱም እጁን በላዩ በጫነ ጊዜ የእግዚአብሔርን ኃይል አየ በላዩ ወርዷልና ፊቱም በብርሃን ተጋረደ። ❤ ወደ መንበረ ሢመቱም በደረሰ ጊዜ ሕዝቡ በታላቅ ደስታ ተቀበሉት በዕለተ ሆሣዕና የእስራኤል ሕዝብ መድኃኒታችንን እንደተቀበሉት።ከዚህም፡በኋላ፡በትምህርቱና በድርሰቶቹ ቤተ ክርስቲያን ብርሃን ሆነች ቃሉም እጅግ ጣዕም ያለው እርሱም የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ የተመላ ነው። በመንበረ ሢመቱም አርባ ዘመን ኖረ እግዚአብሔርንም አገልግሎ የካቲት21 በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን። ምንጭ፦ የካቲት21 ስንክሳር።                              ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለኪ_ለብርሃን_ሕይወት_መፆሩ። አምሳለ ተቅዋም ዘወርቅ ጠበብተ እስራኤል ዘገብሩ። #ማርያም_ክብርት_ለእግዚአብሔር በክብሩ። ረስዪ ትሕትና አእጋርየ ይሑሩ። ትዕቢትሰ ለአምላክ ፀሩ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_21።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት። ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ"። መዝ44፥8-9። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥46-57።                          ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ኪያከ ተወከሉ ወኢተኃፍሩ። አንሰ ዕፄ ወአኮ ሰብእ። ምኑን በኀበ ሰብእ ወትሑት በውስተ ሕዝብ"። መዝ 21፥5-6። የሚነበቡት መልዕክታት ፊል 1፥10-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 5፥5-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ  13፥1-7። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 22፥24-31። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ወራዊ፣ የቅዱስ አናሲሞስ የዕረፍት በዓልና የጾም ወራት። ለሁላችንም ይሁንልን።                   

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #የካቲት ፳፩ (21) ቀን። ❤ እንኳን አምላክን ለወለደች #ለእመቤታች_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም ለወራዊ በዓልዋ መታሰቢያ፣ ለከበረ ለሐዋርያው #ለቅዱስ_ጳውሎስ ደቀ መዝሙር ለሆነ #ለቅዱስ_አናሲሞስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል፣ ለእስክድርያ ኃምሳ ሰባተኛ ሊቀ ጳጳሳት #ለአባ_ገብርኤል ለዕረፍት በዓልና ለአገረ ስሐ ኤጲስቆጶስ ለከበረ አባት #ለአባ_ዘካርያስ ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከከበሩ #ከአባ_አካክዮስና ከኢትዮጵያ አገር ጳጳስ #ከአባ_ገብርኤል ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ በዚች ቀን አምላክን ለወለደች #ለእመቤታችን_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም የበዓልዋ መታሰቢያ ነው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በአማላጅነቷና በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_አናሲሞስ፦ ይህም ቅዱስ አስቀድሞ ከሮሜ ሰዎች ወገን የሚሆን ስሙ ፊልሞና ለሚባል ለሮሜ ሰው አገልጋይ ሆኖ ነበር ይህም ፊልሞና በሮሜ በአስተማረ ጊዜ በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት በጌታችን አመነ ይህ ፊልሞናም ከዚያ ከሮሜ አገር ወደ አስባንያ ሔደ። ይህንንም አገልጋዩን አናሲሞስን ከእርሱ ጋር ወሰደው ሰይጣን ግን አናሲሞስን አሳተው ልቡንም ለወጠውና የጌታውን ገንዘብ ሰረቀው ጌታውም እንደሚቆጣው አውቆ ሸሽቶ ወደ ሮሜ ተመልሶ ሔደና በዚያ ተቀመጠ። በእግዚአብሔርም ፈቃድ ወደ ከበረ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ሔደ ትምህርቱንም ሰምቶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ ለቅዱስ ጳውሎስም ደቀ መዝሙሩ ሆነ። ነገር ግን የጌታውን ገንዘብ በመስረቁ በአናሲሞስ ልብ ጽኑ ኀዘን አደረ ለሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የሠራውን ሁሉ ነገረው ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም "አትፍራ ልብህም አይዘን" አለው ወደ ጌታው ወደ ፊልሞናም መልክትን ጻፈለት ይቺም ስለ አናሲሞስ የጻፋት ከመልእክቶቹ አንዲቱ ናት። በመልክቱም እንዲህ አለው "እኔ በእሥራቴ ጊዜ ስለወለድኩት ልጄ እማልድሃለሁ ይኸውም አናሲሞስ ነው። የቀድሞው ሥራው አልጠቀመህም ነበር ዛሬ ግን ላንተም ለእኔም እጅግ የሚጠቅም ሁኗልና አሁንም ወዳንተ ልኬዋለሁና ልጄ እንደመሆንህ ተቀበለው። የበደለህ በደልም ቢኖር ወይም የሚከፍልህ ቢኖር በኔ ላይ አድርገው"። ❤ ይህ የከበረ አናሲሞስም ወደ ፊልሞና ወደ ጌታው በደረሰ ጊዜ በማመኑና በመጸጸቱ ደስ አለው ሐዋርያው እንዳዘዘውም አደረገለት እጅግም ወደደው ብዙ ገንዘብም ሰጠው እርሱ ግን ምንም ምን አልወሰደም" እኔ በክርስትና ባለጸጋ ሁኜአለሁ" አለ እንጂ። ከዚህም በኋላ ሸኙትና ወደ ሮሜ አገር ተመለሰ በሰማዕትነት እስከ ሚሞትበት ጊዜ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስን የሚያገለግለ ሆነ። ይህም ቅዱስ ካህን ሆኖ ተሾመ ሐዋርያትም በሥርዓት መጽሐፋቸው በአንቀጽ ሰባ ሰባት፣ ሰማንያ አንድ፣ በኅምሳ ሦስትና በኅምሳ ሰባት በምስጋና አስታውሰውታል "እንደ ታማኝ ካህን ነው" አሉ። ❤ ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የምስክርነት ዕረፍት በኋላ የንጉሥ ጭፍራ አለቃ ይህን ቅዱስ ይዞ ወደ አንዲት ደሴት ሰደደው የዚያችን ደሴት ሰዎች ሃይማኖትን እያስተማራቸው ኖረ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው። ከብዙ ቀኖችም በኋላ የንጉሥ የጭፍራ አለቃ ወደዚያች ደረሰ የከበረ አናሲሞስንም ሕያው ሁኖ የክቡር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት ለሰዎች ሲያስተምራቸው አገኘው ጽኑ ግርፋትምንም ገረፈው ጭኖቹን እንዲሰብሩ አዘዘ ምስክርነቱንም የካቲት21 ፈጸመ። የሰማዕትነት አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አናሲሞስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ትኑር  ለዘላለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የእስክንድርያ_ሊቀ_ጳጳስ_አባ_ገብርኤል፦ ይህም አባት በታናሽነቱ በአስቄጥስ ገዳም መነኰሰ በጾም በጸሎት በስግደት ተጠምዶ ኖረ በውስጡም ትሕትና ፍቅር ቅንነት አለው። በአንዲት  ዕለት ስሙ መክሲሞስ ወደ ሚባል አረጋዊ ቤት ገባ እርሱም "ልጄ ከሰው ለምን ትሸሻለህ አንተ ግን በወንዶችና በብዙ ሴቶች መካከል ትኖር ዘንድ አለህ"አለው። እርሱ ግን የሽማግሌውን የቃሉን ትርጓሜ አላስተዋለም ከጠላትም ወጥመድ ያድነው ዘንድ ሁል ጊዜ በማልቀስ እግዚአብሔርን የሚለምን ሆነ። ❤ ከእርሱም አስቀድሞ የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል በዐረፈ ጊዜ ይህን አባት ይዘው ያለ ውዴታው ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት አረጋዊ አባ መክሲሞስ ትንቢት እንደ ተናገረለት በተሾመ ጊዜ በአስቄጥስ ገዳም ተቀምጦ የቀድሞውን ተጋድሎውንና አገልግሎቱን ቸለል አላለም ስለ አብያተ ክርስቲያንም ጉዳይ ወደ እስክንድርያና ወደ ምስር ይሔድ ዘንድ ግድ በአሉት ጊዜ ይሔዳል ፈጥኖም ወደ አስቄጥስ ገዳም ይመለሳል። ❤ እርሱም በዕድሜው ጐልማሳ ስለሆነ እንስሳዊት ፍትወት ትነሣሣበት ነበር እርሱም ያጠፋት ዘንድ ለጾም ለጸሎት ለስግደትም መትጋትን ያበዛል ሊያበርዳትም ባልተቻለው ጊዜ ለአንድ አረጋዊ ተናዘዘለት እርሱም እንዲህ አለው "ይህች እንስሳዊት ፍትወት ከጾምና ከጸሎት ከስግደትም ጋር ያለ ትሕትና ሥራ አትጠፋም በበለጠ ግን ትሕትና መድኃኒትቷ ነውና"። ይህንንም በሰማ ጊዜ የጉድፍ መጐተቻ ከብረት ሠራ አጭር የሆነ የቆሸሸ ልብስ በመልበስ በሌሊት ተነሥቶ የመኰሳቱን መንደር እየዞረ ቆሻሻውን ጠርጎ ተሸክሞ ወስዶ ከራቀ ቦታ ይጥለዋል። ይህንንም ሥራ እየሠራ ሁለት ዓመት ያህል ኖረ እግዚአብሔርም ንጽሕናውንና የልቡን ትሑትነት ተመልክቶ የባሕርይ የሆነውን ፍትወት አራቀለት። ይህም አባት በገድል እንደተጠመደ ሁኖ መንጋዎቹ በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ እያስተማራቸውና እየገሠጻቸው እየመከራቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመት ኑሮ የካቲት21 በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ገብርኤል በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ዘካርያስ፦ ይህም አባት የጸሐፊዎች ወገን ነው አባቱ ግን ጸሐፊነቱን ትቶ ቅስና ተሾመ ስሙም ዮሐንስ ነው። ልጁ ዘካርያስም በአደገ ጊዜ ትምህቶችን ሁሉ ጽሕፈትንም የጽርእና የሮማውያንን ጥበብ የቤተ ክርስቲያንንም ሕግ ተማረ የንጉሥም የጭፍራ አለቃ ወሰደውና በንጉሡ ቤት ጸሐፊነት ሾመው። በጽሕፈቱም የአገረ ስሐ መኰንን የሆነው ስሙ አብጥልማዎስ የሚባል ወዳጅ ሆነው እርሱም ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደው ይመነኵሱ ዘንድ ተስማሙ። በዚያንም ጊዜ ከአስቄጥስ ገዳም ከአባ ዮሐንስ ደብር አንድ መነኰስ ወደነርሱ መጣ አብረውትም ይሔዱ ዘንድ ተስማሙ መኳንንቶችም ይህን በሰሙ ጊዜ መሔድን ከለከሉዋቸው። ከጥቂት ቀኖች በኋላ "ለእግዚአብሔር የተሰላችሁትን ስለት ለምን አትፈጽሙም" የሚላቸውን ራእይ አዩ በዚያንም ጊዜ በሥውር ወጡ እነርሱ ግን  መንገዱን አያውቁትም ነበር አንድ መነኰስም ተገለጠላቸውና ወደ አስቄጥስ ወደ አባ ዮሐንስ ገዳም መርቶ አደረሳቸው። መኳንንቱም መሔዳቸውን በሰሙ ጊዜ ከንጉሥ ዘንድ ደብዳቤ ተቀብለው በላክ ከገዳም ሊአሰወጡአቸው ተስማሙ የክቡር ባለቤት ጌታችንም ምክራቸውን በተነ።

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ  አሜን"። ❤             ❤ #የካቲት ፳ (20) ቀን። ❤ እንኳን #መኰንን_አርያኖስን_ለሚያጫውተው ለበገና ደርዳሪው #ለቅዱስ_ፊልሞንና ለጓደኛው #ለአናጉንስጢስ_ለቅዱስ_አስቃሎን ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓልና ለእስክድርያ አገር ሃያ አንደኛ ሊቀ ጳጳስ #ከሐዋርያው_ቅዱስ_አትናቴዎስ በኋላ ለተሹመት #ለአባ_ጴጥሮስ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከማታሰቡ፦ ከከበሩ #ከቅዱሳን_ባስልዮስ_ከቴዎድሮስና #ከጢሞቴዎስ_በእስክድርያ አገር በሰማዕትነት ከዐረፉ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                        ✝ ✝ ✝ ❤ በገና ደርዳሪው #ቅዱስ_ፊልሞን ጓደኛው #ለአናጉንስጢስ_ለቅዱስ_አስቃሎን ፦ በአንዲትም ዕለት አርያኖስ አናጉንስጢስ አስቃሎንን ጠርቶ "ለአጵሎን ሠዋ" አለው አስቃሎንም ወደ ፊልሞን ሒዶ "በእኔ ፈንታ ብትሠዋ አራት የወርቅ ዲናር እስጥሃለሁ" አለው  ፊልሞንም "ልብስህን ስጠኝና ተሸፋፍኜ በአንተ ፈንታ እሠዋለሁ" አለው። በገባም ጊዜ አውቀውት "ምን ሆንክ" አሉት ፊልሞንም "በክርስቶስ የማን ክርስቲያን ነኝ"አላቸው። አርያኖስም "በሕይወት እንድትኖር ለአማልክት ሰዋ" አለው። "ፊልሞንም በክርስቶስ ስም ከመሞት በቀር ሕይወት የለም" አለው። አርያኖስም "ጥምቀትን ሳታገኝ ፈጥኜ እገድልሃለሁ ተስፋህን ታጣለህ" አለው። ፊልሞንም ሰምቶ የክርስትና ጥምቀትን ያድለው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ በዚያንም ጊዜ ከሰማይ ብሩህ ደመና መጥቶ አጠመቀው። አርያኖስም አፍሮ ቢመለስ ብሎ ሦስት ወታደሮች እንዲጸፋት አዘዘ ፊልሞንም "የእግዚአብሔር መላእክት ስለ እኔ ደስ ሲላቸው አያለሁና ከዚህ የከፋ ቢጻፋኝም አልፍርም" አለ። አርያኖስም ባላ ባለው ግንድ ላይ ሰቅለው በፍላፃዎች ይነድፉት ዘንድ አዘዘ ግን ምንም የነካው የለም ፍላፃውም እንዳልካው ለአርያኖስ ነገሩት ዳግመኛም እርሱ እንደ ቆመ ይነድፉት ዘንድ አዘዘ አንዲትም ፍላፃ ተመልሳ፡ የአርያኖስን ዐይን ነድፋ ዐሳወረችው በዚያን ጊዜ ከተሰቀለበት አውርደው ከአናጉንስጢስ አስቃሎን ጋር ራሱን እንዲቆርጡ አዘዘ ገድላቸውን፡ ፈጽመው የሰማዕትነት አክሊል የካቲት20 ተቀበሉ። ❤ መኰንኑም በፍላፃው ሕመም በተሠቃየ ጊዜ ከቅዱሳን ደም ወስዶ ከዐይኑ ውስጥ እንዲጨምር ሰዎች መከሩት ይህንንም ሲያደርግ ዳነ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም አመነ እሥረኞችንም ሁሉ ፈታቸው እርሱም መጋቢት ስምንት ቀን በዲዮቅልጥያኖስ እጅ በሰማዕትነት ዐረፈ። የሰማዕታትም በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን አሜን።                                                       ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ጴጥሮስ፦ የእስክድርያ ሃያ አንደኛ ሊቀ ጳጳስ ነው። ይህንንም ቅዱስ ከሐዋርያዊ አትናቴዎስ በኋላ በሹመቱ ወንበር በተቀበጠ ጊዜ ከንጉሥ ዳርዮስ ከከሀዲ አርዮስ ወገኖች ብዙ መከራ ደርሶበታል። ሊገሉትም በፈለጉ ጊዜ ሸሽቶ ሁለት ዓመት ያህል ተሠወረ አርዮሳውያንም ሉቅዮስ የተባለ ከሀዲውን ሰው በእርሱ ፈንታ በወንበሩ ላይ አስቀምጠው ሁለት ዓመት ኖረ። ከዚያም በኋላ ሃይማኖታቸው የቀና ምዕመናን ሁሉም ተነሥተው አርዮሳዊ ሉቅዮስን አሳደዱትና ይህን አባት ጴጥሮስን ወደ መንበረ ሢመቱ መለሱት አርዮሳውያንንም በመጣላት እያወገዛቸው እያሳደዳቸው ሰባት ዓመት ኖረ። ከዚህም በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም የካቲት20 ዐርፎ ወደ ዘላለም ዕረፍት ሔደ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ጴጥሮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት 20 ስንክሳር።                                                       ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_እብል_ለባስልዮስ_ብፁዕ። #ወቴዎድሮስ_ካዕለ#ወጢሞቴዎስ_ሣልስ ቅኑታነ ኃይል ወጽንዕ። ውስተ ቤተ መረዓ አምሳለ እሡራን ሰብእ። ዘተጸዋዕክሙ ኅቡረ ለስምዕ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_20።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦"ተገኃሥ እምእኩይ ወግበር ሠናይ። ኅሥሣ ለሰላም ወዴግና። እስመ አዕይንቲሁ ለእግዚአብሔር ኀበ ጻድቃኑ"። መዝ 33፥14-15። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ጢሞ 3፥1-13፣ 1ኛ ጴጥ 5፥1-11 እና የሐዋ ሥራ 9፥23-32።  የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥1-17። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም በዓልና የጾም ወራት። ለሁላችንም ይሁንልን።                  

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #የካቲት ፳ (20) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያውያን_ጻድቅ ውኃ ከዓለት ድንጋይ ላይ እያፈለቁ አሕዛብን ሁሉ እያስተማሩ ያጠምቁ ለነበረ፤ ኅብስትም ከሰማይ እየወረደላቸው ሕዝቡን ያቆርቡ ለነበረ ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ክፍለ_ማርያም_ዘድባጋ ከዚህ ዓለም እንደነ #ቅዱሳን_ሄኖክና_ኤልያስ ከሞት ለተሰወሩበት በዓልና #ለአባ_ገብረ_መርዓዊ_ዘአግዶ_ገዳም ለመታሰቢያ በዓላቸው እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ለአቡነ_ክፍለ_ማርያም_ዘድባጋ፦ ትውልዳቸው እንደርታ ሲሆን በ14 ዓመታቸው መንኵሰው፡ መንነው በቅተው ሲኖሩ በአንድ ወቅት ወደ አክሱም ሄዱና ወላጆቻቸው ካሉበት ደረሱ። ከቅዳሴ በኋላ መክፈልት ቆርሰው ሲያድሉ ወላጅ እናታቸው ከስተውና ጠቁረው ስላዩአቸው ለእናታቸው አዳልተው በብዙ ሰጧቸው። እናትየው ግን ጻድቁ የሰሩትን አያወቁም ነበር። ጻድቁ ከብቃታቸው የተነሳ መና ከሰማይ አየወረደላቸው ከዓለትም ላይ ውኃ እያፈለቁ ይጠጡ ነበር። አድሎ ስላደረጉ ግን በዚህ ድርጊታቸው እግዚአብሔር ተቆጥቷቸው የሰጣቸውን ይህን ጸጋውን ነሳቸው። አቡነ ክፍለ ማርያምም ይህን ባወቁ ጊዜ "ወዮልኝ ወዮታ አለብኝ" ብለው ከሰው ሳይገናኙ ዋሻ ገብተው ድፍን 11ዓመት በለቅሶና በዋይታ እግዚአብሔርን ለምነው ነው ይቅር ተብለው የቀደመ ጸጋቸውና ክብራቸው የተመለሰላቸው። ❤ ከዛ በኋላ ውኃ ከደረቅ ጭንጫ ላይ እያፈለቁ አሕዛብን ሁሉ እያስተማሩ ያጠምቁ ጀመር። ኅብስትም ከሰማይ እየወረደላቸው ሕዝቡን ያቆርቡ ጀመር። ጻድቁ በመጨረሻ በየካቲት 20 ቀን እንደነ ሄኖክና ኤልያስ ዐርገዋል እንጂ በምድር ሞት አልቀመሱም። ትልቅና አስደናቂ ገድላቸው በአክሱም ይገኛል። ከአቡነ ክፍለ ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።