👉 የሙሐረም ወርና ሙስሊሞች
የሙሐረም ወር ከሂጅሪያ ወሮች የመጀመሪያውና አላህ ለይቶ ካላቃቸው አራቱ ወራቶች አንዱ ነው ። ይህ ወር የሂጅሪያ ወር መጀመሪያ ቢሆንም ሙስሊሞች የዘመን መለወጫ ብለው በዚህ ወር መግቢያ ላይ የተለየ የሚሰሩት ነገር የለም ።
ይልቁንም ሙስሊሞቸው ህይወታቸው የሰከንዶች ሽርፍራፊ ጥርቅም መሆኑንና እየአንዳንዱ ሽርፍራፊ በተቀነሰ ቁጥር ከእድሜያቸው እየተቀነሰና ወደ ቀብር እየተጠጉ መሆናቸውን ነው የሚያውቁት ። በመሆኑም በየትኛውም ዘመን ፣ አመት ፣ ወር ፣ ሳምንት ፣ ሳአት ፣ ደቂቃና ሰከንድ ለሚቀጥለው ዐለም መዘጋጀት እንዳለባቸው ያውቃሉ ።
ከዚህ ዝግጅታቸው አንዱ ምንዳና ቱሩፋት አለባቸው በተባሉ ቦታና ጊዜያቶች የታዘዙትን መልካም ስራዎች መስራት ነው ። በመሆኑም በሙሐረም ወር ውስጥ የታዘዙ የአምልኮ አይነቶችን ይፈፅማሉ ምንዳውንም ከጌታቸው ይጠብቃሉ ።
የሙሐረም ወር ከአራቱ የተከበሩ ወራቶች ለመሆኑ በመልእክተኛው ሐዲስ የተረጋገጠ ሲሆን ከ12ቱ አራቱ የተከበሩ መሆናቸው ደግሞ አላህ በተከበረው ቃሉ በተውባ ምእራፍ 36ው አንቀፅ እንዲ ብሎ ይነግረናል : –
« إِنَّ عِدَّةَ الشُّهُورِ عِندَ اللَّهِ اثْنَا عَشَرَ شَهْرًا فِي كِتَابِ اللَّهِ يَوْمَ خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ مِنْهَا أَرْبَعَةٌ حُرُمٌ ۚ ذَٰلِكَ الدِّينُ الْقَيِّمُ ۚ فَلَا تَظْلِمُوا فِيهِنَّ أَنفُسَكُمْ ۚ وَقَاتِلُوا الْمُشْرِكِينَ كَافَّةً كَمَا يُقَاتِلُونَكُمْ كَافَّةً ۚ وَاعْلَمُوا أَنَّ اللَّهَ مَعَ الْمُتَّقِينَ »
" የወሮች ቁጥር አላህ ዘንድ በአላህ መጽሐፍ ውስጥ ሰማያትንና ምድርን በፈጠረበት ቀን ዐሥራ ሁለት ወር ነው ፡፡ ከእነሱ አራቱ የተከበሩ ናቸው ፡፡ ይህ ቀጥተኛው ሃይማኖት ነው ፡፡ በእነርሱ ውስጥም ነፍሶቻችሁን አትበድሉ ፡፡ አጋሪዎችንም በአንድ ላይ ኾነው እንደሚዋጉዋችሁ በአንድ ላይ ኾናችሁ ተጋደሉዋቸው ፡፡ አላህም ከሚፈሩት ጋር መኾኑን ዕወቁ ፡፡"
የአላህ መልእክተኛ – ሶለላሁ ዓለይሂ ወሰለም – የተከበሩት ወራት የተኞቹ እንደሆኑ በሚከተለው በሐዲሳቸው ነገረውናል : –
عن أَبي بَكْرَةَ رضي الله عنه عَنْ النَّبِيِّ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ أنه قَالَ :
" إنَّ الزَّمَانَ قَدْ اسْتَدَارَ كَهَيْئَتِهِ يَوْمَ خَلَقَ اللَّهُ السَّمَوَاتِ وَالأَرْضَ السَّنَةُ اثْنَا عَشَرَ شَهْرًا مِنْهَا أَرْبَعَةٌ حُرُمٌ ثَلاثٌ مُتَوَالِيَاتٌ ذُو الْقَعْدَةِ وَذُو الْحِجَّةِ وَالْمُحَرَّمُ وَرَجَبُ مُضَرَ الَّذِي بَيْنَ جُمَادَى وَشَعْبَانَ "
متفق عليه
አቡ በክረተ የተባለ ሶሐብይ እንዳወራው የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል ይላል : –
" ዘመን አላህ ሰማይና ምድር ሲፈጥር ወደ ነበረበት ተመልሷል ። ( የሐጅ ወር አላህ በዙል ሒጃ አድርጎታል ። መሀይማኖች የቀየሩት ውድቅ ሆኖ ወደዛው ተመልሷልና ይህን ያዙ ) ። አመት አስራ ሁለት ወር ነው ። ከእነሱ ውስጥ አራቱ የተከበሩ ናቸው ። ሶስቱ ተከታታዮች ናቸው ። ዙል ቀዕዳ ፣ ዙል ሒጃ ፣ ሙሐረም , ረጀብ ደግሞ በጁማደ ሳኒና በሻዕባን መካከል ነው ። "
ከእነዚህ ከአራቱ ደግሞ ሙሐረም ይበልጥ የተከበረ ወር መሆኑን ሲነግሩን የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ይላሉ : –
عن أبي ذر رضي الله عنه قال :
سألت النبي – صلى الله عليه وسلم – : أي الليل خير وأي الأشهر أفضل؟ فقال :
" خير الليل جوفه وأفضل الأشهر شهر الله الذي تدعونه المحرم "
አቡ ዘር የተባለ ሶሐብይ – ረዲየላሁ ዐንሁ – የአላህ መልእክተኛን የትኛው ለይል ይበልጣል ? የትኛውስ ወር በላጭ ነው ብዬ ጠየቋቸው ። እሳቸውም እንዲ አሉ : –
" ከለሊቱ ውስጥ በላጩ ድቅድቁ ( ከመካከለኛው በኋላ) ያለው ነው ። ከወሮች ደግሞ እናንተ ሙሐረም ብላችሁ የምትጠሩት ነው ። "
በዚህ ወር ውስጥ ተወዳጅ የሆው መልካም ስራ ደግሞ ፆም ነው ። ይህንንም መልእክተኛው እንዲህ በማለት ይነግሩናል : –
عن أبي هريرة أن النبي صلى الله عليه وسلم قال :
" أفضل الصيام بعد شهر رمضان شهر الله الذي تدعونه المحرم وأفضل الصلاة بعد الفريضة قيام الليل " .
رواه مسلم
አቡ ሁረይራ ባወሩትና ኢማሙ ሙስሊም በዘገቡት ሐዲስ ነብዩ እንዲህ ብለዋል : –
" ከፆሞች ሁሉ በላጩ ከረመዳን ወር በኋላ ሙሐረም ብላችሁ የምትጠሩት ወር ( መፆም ነው) ከሶላት ሁሉ በላጩ ከፈርድ ሶላት በኋላ የለይል ሶላት ነው ። "
የአላህ መልእክተኛ በሙሐረም ወር መፆም ( የቻሉትን ማለት ነው) ከረመዳን ወር ፆም ቀጥሎ የተወደደ መሆኑን እየነገሩን ነው ። በመሆኑም አንድ ሰው በሙሐረም ወር ውስጥ የቻለውን ያክል ቢፆም በጣም ተወዳጅ ነው ። እዚህ ጋር መታወቅ ያለበት ከረመዳን ውጪ ወሩን ሙሉ መፆም እንደማይቻል ነው ።
በዚህ በሙሐረም ወር የዐስረኛውን ቀን መፆም ያለፈውን አመት ወንጀል የሚያስምር መሆኑን መልእክተኛው በሚቀጥለው ሐዲሳቸው ነግረውናል ።
عن أبي قَتادة رضي الله تعالى عنه ، عن الرّسول - صلّى الله عليه وسلّم - قال :
"
صوم عاشوراء يكفِّر السّنة الماضية "
رواه النسائي
አቡ ቀታዳ የተባለ ሶሐብይ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል ይላል : –
" የዓሹራእ ቀንን መፆም ያለፈው አመት ወንጀል ያስምራል ። "
ከእነዚህ መረጃዎች በመነሳት ሙስሊሞች በሙሐረም ወር ከፆም የበለጠ የተወደደ ስራ አለመኖሩን ያውቃሉ ። በቻሉት አቅም በፆም ወደ አላህ ይቃረባሉ ከዚህ ውጪ አላስፈላጊ አመለካከትና እምነት ከኢስላም አንፃር ቦታ የለውም ።
አላህ ከተጠቃሚዮች ያድረገን ።
https://t.me/bahruteka