ሰዋስው ☘☘☘☘
Open in Telegram
በሰዋስወ ብርሀን ቅዱስ ዻውሎስ ገዳም እና ለተለያዩ ቤተክርስቲያን ለክብረ በአላት ማውጫ ። በተጨማሪም-ዋዜማ ሥርዓተ ማኅሌት - መዝሙራት ስንክሳር - የየእለቱን ምስባክ ቅኔያት ጥያቄዎች እንዲሁም የወቅታዊ ነገር መወያያ በተጨማሪም @eotcww ብለው ይቀላቀሉን ለወዳጅ ዘመድዎ share#Share#Share# ያድርጉ።
Show more1 161
Subscribers
No data24 hours
No data7 days
No data30 days
Posts Archive
1 161
❤ ያን ጊዜም ተነሥቶ ወደዚያ ገዳም ሒዶ መነኰሳቱን ይረግማቸው ጀመረ። አበምኔቱም ሰምቶ ወጣና "መነኰሳቱን ለምን ትረግማቸዋለህ እግዚአብሔርን አትፈራውምን" አለው እርሱም በልጁ ላይ የሆነውን ነገረው አንዲህም አለው "አባ እንባመሪና የሚሉት ወጣት መነኰሴ የልጄን ድንግልና ስለደፈረ ነው" አለው። አበ ምኔቱም በሰማ ጊዜ እውነት መሰለውና እጅግ አዘነ ሰውየውንም እንዲህ ብሎ ለመነው "በአንድ ሰው በደል ንጹሐን የሆኑ መነኰሳትን በሕዝባውያን ፊት አታዋርዳቸው ይህንንም ነገር ሠውር"።
❤ ከዚህም በኋላ ቅድስት እንባመሪናን ጠርቶ ይገሥጻትና ይረግማት ጀመረ እርሷም ስለምን እንደሚረግማት አላወቀችም ነበር በአወቀችም ጊዜ ከእግሩ በታች ወደቃ "እኔ ወጣት ነኝና በደሌን ይቅር በለኝ" ብላ ለመነችው እርሱም አጅግ ተቆጥቶ ከገዳሙ አባረራት እርሷም ከገዳም ውጭ ሁና እየተጋደለች ኖረች።
❤ ያቺም ልጅ በወለደች ጊዜ የልጅቷ አባት ሕፃኑን አምጥቶ ለቅድስት እንባመሪና ሰጣት እርሷም እግዚአብሔርን እያመሰገነች ተቀበለችው በላሞችና በበጎች ጠባቂዎች ዘንድ ለሕፃኑ ወተትን እየለመነች መዞርን ጀመረች እንደዚህም አድርጋ ሕፃኑን አሳደገችው። ከሦስት ዓመትም በኋላ መነኰሳቱ ተሰብስበው አባ ምኔቱን ለመኑት አባ እንባመሪናን ይቅርታ አድርጎለት ወደ ገዳሙ ይመልሰው ዘንድ እርሱም ልመናቸውን ተቀብሎ ከመነኰሳቱ ጋራ ቀላቀላት ይኸውም ከባድ ቀኖና ከሰጣት በኋላ ነው።
❤ ከዚህም በኋላ ጭንቅ የሆኑ ሥራዎችን ትሠራ ጀመረች የመነኰሳቱንም ቤቶች ጠርጋ ተሸክማ ወስዳ ከገዳሙ ውጭ ትጥለዋለች ውኃንም ቀድታ ታጠጣቸዋለች ምግባቸውንም ታዘጋጃለች። ያም ሕፃን አደገ የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ተምሮ መነኰሰ።
❤ አርባ ዓመትም ሲፈጸም ሦስት ቀኖች ያህል ታማ በሰላም አረፈች ደወልንም ደውለው መነኰሳቱ ሁሉ ተሰበሰቡ ሊገንዙም ገብተው ልብሶቿን በገለጡ ጊዜ እርሷ ሴት እንደ ሆነች አግኝተዋት ደነገጡ መሪር እንባንም አለቀሱ አበ ምኔቱም በመጣም ጊዜ ያለ በደሏ ከባድ ንስሐ ቀኖና ስለ ሰጣትና በእርሷ ላይ ስለ አደረገው ተግሣጽ መሪር ዕንባን አለቀሰ።
❤ ከዚህም በኋላ መልእክተኞችን ልኮ የዚያችን የሐሰተኛ ልጅ አባቷን አስመጥቶ እንባመሪና ሴት እንደሆነች ነገረው ። ከዚህም በኋላ በድኗን ተሸክመው ይቅር ይበለን የሚል ቃል ከበድኗ እስከ ሰሙ ድረስ "አቤቱ ክርስቶስ ማረን" እያሉ ጸለዩ ከዚያም በኋላ በዝማሬና በማኅሌት ከብዙ ልቅሶ ጋር ገነዟት ከሥጋዋም ተባርከው ቀበሩዋት።
❤ እነሆ እግዚአብሔር ክፉ ሰይጣንን አዝዞት ያቺን ሐሰተኛ ሴት ልጅና ድንግልናዋን የደፈረውን ጉልማሳ ያዘው እያጓተተም አሠቃይቶ ይቀጣቸው ጀመረ ወደ ቅድስት እንባመሪና መቃብር ሔደው ኃጢአታቸውን በሕዝቡ ሁሉ ፊት እስከሚአምኑ እጅግ አሠቃያቸው። ከመቃብርዋም ቁጥር የሌላቸው ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት እንባ መሪና በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
+ + +
❤ ሰማዕቱ ቅዱስ ለውረንዮስ፦ በንጉሥ ዳስዮስ ቄሣር ዘመን ሰማዕትነት የተቀበለ ነው። ይህም ቅዱስ በሃይማኖት የጸና ነው የክብር ባለቤት ስለ ሆነ ስለ ክርስቶስ ሃይማኖት ሊቀ ዲቁና ተሹሞ የሊቀ ጵጵስናውን ገንዘብ ይጠብቅ ነበር።
❤ ንጉሥ ስለርሱ ሰምቶ አምጥተው ከወህኒ ቤት እንዲአስገቡት አዘዘ በአስገቡትም ጊዜ በዚያ ዕውር ሰውን አገኘና "አይኖችህ ይገለጡ ዘንድ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ አምነህ በስሙ ትጠመቃለህን?" አለው ዕውሩም "አዎን ጌታዬ" አለ። ያን ጊዜም በውኃው ላይ ጸልዮ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቀው ያን ጊዜም አይኖቹ ተገለጠ። እንዲህም ብሎ ጮኸ "በአገልጋዩ ለውረንዮስ ጸሎት ዐይኖቼን የገለጠ የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይክበር ይመስገን" ብሎ ጮኸ። ይህንንም ድንቅ አይተው ብዙዎች አመኑ።
❤ ንጉሡም በሰማ ጊዜ የከበረ ለውረንዮስን ወደርሱ ያቀርቡት ዘንድ አዘዘ በአቀረቡትም ጊዜ ለአማልክት እንዲሰዋ አግባባው እምቢ ባለውም ጊዜ ጥርሶቹን በደንጊያ ሰበሩ ልብሶቹንም ገፈው በብረት ዐልጋ ላይ አስተኝተው ሥጋው እስከሚቀልጥ ከበታቹ እሳትን አነደዱ።
❤ እርሱም ነፍሱን እስከአሳለፈ ድረስ ወደ ፈጣሪው ይጸልይ ነበር። መላእክትም ሃሌ ሉያ እያሉ ተቀብለው ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አስገቡት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ ቅዱስ ለውረንዮስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘለላለሙ አሜን፡፡ ምንጭ፦ የነሐሴ 15 ስንክሳር።
+ + +
❤ ሰላም ለክርስጢና ዘአጥመቃ እግዚአብሔር። ወተሀበያ መልአኩ ሚካኤል ክቡር። ለዛቲ ቅድስት ወንጽሕት እምነውር። እምነ ሥጋሃ ቅሡፍ ዘውኅዘ መዐር። ያማዕርር ጉርዔየ እሜጌጋይ መሪር"። ትርጉም፦ የከበረ መልአኩ ሚካኤል ዋስ የኾናት እግዚአብሔር ወልድ ያጠመቃት ለኾነች ለክስጢና ሰላምታ ይገባል፤ ከነውር ከነቀፋ ንጹሕት የኾነች ከዚኽች ቅድስት ከተገረፈ ሰውነቷ የፈሰሰው መዐር መሪር ከኾነ በደል ጉሮሮዬን ያጣፍጥ።
+ + +
❤ "ሰላም ለመሪና ወሬዛ በአምሳሉ፡፡ እንተ መከረት ኀበ ደብረ አኀው ተሀሉ። እንዘ ትትናገር ይእቲ ሶበ ይሰምዕዋ ኵሉ። ይትዋሥኡ ወይትባሀሉ ድቁቅ ቃሉ። እምተፀምዶቱ ብዙኅ ወፍድፋድ ገድሉ"። ትርጉም፦ በጎልማሳ አምሳል በወንዶች ደብር ትኖር ዘንድ የወደደች ለኾነች ለመሪና ሰላምታ ይገባል፤ ርሷ ስትናገር ኹሉ በሚሰሟት ጊዜ ከብዙ አገልግሎቱና ከጽኑ ገድሉ የተነሣ፤ ቃሉ ደቃቅ (ታናናሽ) ነው ይወያዩና ይነጋገሩ ነበር። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የነሐሴ15።
❤ በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።
https://t.me/Eotcw
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ ነሐሴ ፲፭ (15) ቀን።
❤ እንኳን አምላክን ስለወለደችን እመቤታችን ድንግል ማርያም ሥጋዋን ለመግነዝ ሐዋርያት ለተሰበሰቡበት ቀንና ጌታችን ከከበሩ ቅዱሳን መላእክቶቹ ጋር መጥቶ ላጠመቃት፣ ቅዱስ ሚካኤል በእሳጉጠት ቅዱስ ሥጋውን ክብር ደሙን ላቀበላትና ዋስ ለሆናት በተአምራቷም ሠላሳ ሺህ ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ላሳመነችው ለመኰንን ርባኖስ ልጅ ለታላቋ ሰማዕት ለቅድስት ክርስጢ ለዕረፍት በዓል፣ ሴት ሆና እንደ ወንድ መስላ ከወንዶች ገዳም ገብታ ገድሏን ለፈጸመች ታላቅ እናት ለቅድስት (ከአባ) እንባመሪና ለዕረፍት በዓልና በንጉሥ ዳንዮስ ቄሣር ዘመን በሰማዕትነት ለተቀበለ ለቅዱስ ለውረንዮስ ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪም በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከሠላሳ ሺህ ዐሥራ ሁለት ከቅድስት ክርስጢና ማኅበረ ሰማዕታት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
+ + +
❤ በዚህች ቀን አምላክን ስለወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ሥጋዋን ስለመገነዝ የሐዋርያት ስብሰባ ሆነ። ጸሎቷና በረከቷ የሐዋርያትም በረከታቸው ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
+ + +
❤ "ሰላም ለክርስጢና ድንግል ዘአጥመቃ ወልደ ልዑል በእደዊሁ ክቡር፤ ወተሀበያ ሚካኤል"። ትርጉም፦ ሚካኤል ዋስ የኾናት፤ በከበረ እጁ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ያጠመቃት ለኾነች ለድንግል ክርስጢና ሰላምታ ይገባል። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።
+ + +
❤ የመኰንን ርባኖስ ልጅ ታላቋ ሰማዕት ቅድስት ክርስጢና፦አባቷ ጣዖታትን የሚያመልክ ነው። እርሷም አባቷ እንደ አስተማራት ታጥናቸው ነበር። በአንዲት ዕለትም አስባ ተመራመረች በልቧም እግዚአብሔርን መፍራት አደረ ተነሥታም ፊቷን ወደ ምሥራቅ መልሳ ቆመች የምትጓዝበትንም የሕይወት መንገድ ይመራት ዘንድ ጸለየች መንፈስ ቅዱስም አንድነቱንና ሦስትነቱን ገለጠላት።
❤ አባቷም በመጣ ጊዜ "ልጄ እንዴት አለሽ" አላት "በክብር ባለቤት በክርስቶስ ሕይወት አለሁ" አለችው። አባቷም ሰምቶ ደነገጠ "ልብሽን ምን ለወጠው" አላት እርሷም "ከሰማይ አምላክ ተማረኩ" አለችው። ከዚህም በኋላ አባቷ እያዘነ ሔደ። እርሷም ተነሥታ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች ያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ እንዲህ አላት "በርቺ ከሦስት መኳንንት ትሠቃዪ ዘንድ አለሽ" አዳኝ በሆነ በጌታችን ክርስቶስ መስቀልም አማተመች ሰማያዊ ኅብስትንም ሰጣት።
❤ ከዚህም በኋላ ተነሥታ ጣዖታቱ ወደ አሉበት ቤት ገብታ ቀጠቀጠቻቸው። አባቷም አይቶ እጅግ ተቆጣ ልጁንም ይገርፏት ዘንድ አዘዘ ከሥጋዋም ስለ ደም ፈንታ ማር ወጣ። ሁለተኛም በብረት ዐልጋ ላይ አስተኝተው ከበታችዋ እሳትን እንዲያነዱ አዘዘ እርሷን የነካት የለም ግን ከአረማውያን ብዙዎችን አቃጠለ።
❤ ዳግመኛም በታንኳ አድርገው ወደ ባሕር ይጥሏት ዘንድ አዘዘ በጸለየችንም ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመላእክት ጋራ መጥቶ ራሱ አጠመቃት ቅዱስ ሚካኤልም በእሳት ጉጠት የክብር ባለቤት የሆነ የክርስቶስን ሥጋና ደም አቀበላት ከጣዖታት እድፍም አነጻት በዚያችም ሌሊት አባቷ ርባኖስ ሞተ ። ስሙ ድዮስ የሚባል ሌላ መኰንን መጣ ቅድስት ክርስጢናን አምጥተው ራቁቷን ሰቅለው ከበታችዋ እሳትን እንዲያነዱ አዘዘ። ሴቶችም ራቁትነቷን አይተው መኰንኑን ረገሙት እነርሱም በሰይፍ አስቆረጣቸው እርሷን ግን ምንም ምን አልነካትም ሕዝቡም ይህን ተአምር አይተው የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሠላሳ ሺህ ዐሥራ ሁለት ሰዎች አምነው በሰማዐትነት ሞቱ
ከሀዲው መኰንን ድዮስም በድንገት ሞተ።
❤ ሦስተኛም መኰንን መጣ የከበረች ክርስጢናንም ይዞ ለአማልክት ትሠዋ ዘንድ አባበለት እርሷም እንዲህ አለችው። "አንተና አማልክቶችህ ለዘላለም ወደማ ይጠፋ የገሀነም እሳት ትወርዳላችሁ"። እጅግም ተቆጥቶ ወደ እሳት ማንደጃ ውስጥ እንዲጨምርዋት አዘዘ ምንም የነካት የለም። ዳግመኛም ለአራዊት ይጥሏት ዘንድ አዘዘ እነርሱም የእግርዋን ትቢያ ላሱ እባቦችንም የሚያጠምደውን ነከሱትና ወዲያውኑ ሞተ።
❤ ሁለተኛም ምላሷንና ጡቶቿን ቆረጡ የምላሷንም ቁራጭ አንሥታ ከመኰንኑ ዐይኖች ላይ ጣለችውና ዐይኖቹን አሳወረችው። ቁጣውንም ተመልቶ ለእባቦች እንዲጥሏት አዘዘ አንዲቷም እባብ ልቧን ነደፈቻት አንዲቱ ደግሞ ጐኗን እንዲህም የምስክርነቷን ተጋድሎ ፈጸመች ነፍሷንም አሳልፋ የድል አክሊልን ተቀዳጀች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በታላቋ ሰማዕት በቅድስት ክርስጢና በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
+ + +
❤ ሰላም ለእንባምሪና ንጹሕ በድንግልና ከመ ብእሲ ተመሲላ ዘፈጸመት ገድላ"። ትርጉም፦ በወንድ ተመስላ ገድሏን የፈጸመች በድንግልናዋ ንጽሕት ለነበረች ለእንባምሪና ሰላምታ ይገባል። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።
+ + +
❤ ቅድስት (አባ) እንባ መሪና፦ የዚችም ቅድስት የእናቷ ስም ማርያም ይባላል ሕፃንም ሁና ሳለች እናቷ ሞተች አባቷም አድጋ አካለ መጠን እስከምታደርስ መልካም ትምህርትን እያስተማረ አሳደጋት። አባቷም እሷን አጋብቶ እርሱ ወደ አንድ ገዳም ሒዶ ይመነኲስ ዘንድ ወደደ ። እርሷም አባቷን "ያንተን ነፍስ አድነህ የኔን ነፍስ ታጠፋለህን" አለችው። እርሱም "ስለ አንቺ እንዴት አደርጋለሁ ከገዳም ውስጥ ሴትን አይቀበሉምና" አላት እርሷም እንዲህ አለችው "አባቴ ሆይ የሴቶችን ልብስ ከላዬ አስወግደህ የወንዶችን ልብስ አልብሰኝና ከአንተ ጋራ ውሰደኝ"።
❤ የልቧንም ጽናት አይቶ የወንድ ልብስ አልብሶ ከእርሱ ጋር ወሰዳት የቀድሞ ስሟ መሪና ነበር እርሱ ግን ስሟን ለውጦ እንባመሪና ብሎ ጠራት ገንዘቡንም ሁሉ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች በተነ ልጁንም በወንድ ስም እየጠራ ከእርሱ ጋራ ወስዳት ወደ አንድ የመነኰሳት ገዳምም ደርሰው በዚያ እየተጋደሉ ኖሩ።
❤ ከዚህም በኋላ አባቷ ታመመ ለሞትም በቀረበ ጊዜ አበ ምኔቱን ጠርቶ እርሷን ልጁን አደራ ሰጠው ስለ ገዳም አገልግሎት ከገዳም እንዳትወጣ ከዚያም በኋላ አረፈና ቀበሩት። የከበረች እንባመሪናም ከአባቷ ተለይታ ብቻዋን ቀረች በጾም በጸሎት በስግደት ከቀድሞዋ ዕጥፍ አድርጋ ተጋድሎ ጀመረች።
❤ ከዚህም በኋላ የገዳሙ መነኰሳት "ይህ ወጣት መነኰስ ከእኛ ጋራ ለገዳሙ አገልግሎት ለምን አይወጣም" ብለው ተቃወሟት እንዲህም አበምኔቱን በአሰጨነቁት ጊዜ ከእርሳቸው ጋራ ሰደዳት። ለመነኰሳቱ ቀልብ የሚሆነውን የገዳሙን እህል የሚሰበስብ አንድ ሰው አለ መነኰሳቱም በሚወጡ ጊዜ ከእርሱ ዘንድ አድረው እህላቸውን ይጭናሉ የእንግዳ መቀበያ ቤትም አለው በዚያ ያድራሉ።
❤ በዚያችም ዕለት ከጐረቤቱ አንድ ጐልማሳ ሰው መጥቶ በዚህ ሰው ቤት አድሮ የልጅን ድንግልና አጠፋ። እንድህም አላት "አባትሽ ማን ደፈረሽ ብሎ የጠየቀሽ እንደሆነ አባ እንባመሪና የሚሉት ወጣት መነኰሴ ደፈረኝ በይው"። በፀነሰችም ጊዜ አባቷ አወቀ "ማነው የደፈረሽ" ብሎ ጠየቃት እርሷም እንዲህ ብላ መለሰችለት "አባ እንባመሪና የሚሉት ወጣት መነኵሴ ደፈረኝ"።
1 161
ነሐሴ ፲፬
#ምንባባት
፩ቆሮ ም፩÷፲-፲፪
ያዕ ም፩÷፲፪
ሐዋ ም፲÷፴-፵፬
#ምስባክ
መዝ ፵፫ ቊ፬-፭
ዘአዘዝከ መድኃኒት ለያዕቆብ ።
ብከ ንወግዖሙ ለኲሎሙ ፀርነ።
ወበስምከ ነኃሥሮሙ ለእለ ቆሙ ላዕሌነ።
#ትርጉም
አምላኬና ንጉሤ አንተ ነህ፣
ለያዕቆብ መድኃኒትን ያዘዝህ።
በአንተ በጠላቶቻችን ሁሉ እንወጋቸዋለን
በስምህም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋለን።
#ወንጌል
ማቴ ም፲፯÷፲፬-፳፬
#ቅዳሴ
ዘእግዝእትነ አው ዘዮሐንስ አፈወርቅ
https://t.me/Eotcw
1 161
🌹ደብረ-ታቦር /ቡሄ/ 🌿💖
🌿💖 ቡሄ ፣ ጅራፍ ማስጮ ፣ ችቦ ማብራትና ሙልሙል ዳቦ ሐይማኖታዊ ምስጢራቸው ምንድነው⁉
‼በቤተክርስቲያናችን ስርዓት ነሐሴ ውስጥ እጅግ በርካታ በዓላት ይከበራሉ፡ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በጾመ ማርያም/
ፍልሰታ/ መገባደጃ ላይ የምናከብረው ከጌታችንንና ከአምላካችን ከመድሐኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኝ አበይት በዓላት መካከል አንዱ የሆነው {#የደብረ_ታቦር }በዓል ትልቁና ዋነኛው ነው፡፡
ደብረ-ታቦር ጌታችን ያዕቆብ ዮሐንስንና ጴጥሮስን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ካወጣቸው በኃላ በዛ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበትና ሙሴና ኤልያስን ጠርቶ የህያዋንና የሙታን
አምላክነቱን ያሳየበት ዕለት ነው ።ታዲያ ይህን እለትበሀገራችንና ቤተ-ክርስቲያናችን በቀላሉ አክብራው የምታልፍ በዓል አይደለም፡፡ ይልቁንም የተለያዩ ሥርዓቶችን በመፈፀም አስባው አክብራው ታልፋለች፡፡ ስለዚህም ዛሬ የበዓሉ ዋዜማ ላይ እንገኛለንና እንደ እግዚአብሔር አምላካችን መልካም ፈቃድ በበዓሉ ላይ ትርጉማቸውን
አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ለበርካታ ጊዜያት የምንፈፅማቸውን ትውፊታዊ የሃይማኖት ሥርዓቶች ምስጢራቸው ምን እንደሆነ
እናያለን፡፡ ከስሙ ለመጀመር ያህል የደብረ-ታቦር በዓል በሀገራችን ቡሄ እየተባለ ነው የሚጠራው ቡሄ ምን ማለት ነው?
🌿💖 ቡሄ 🌿💖
,
ቡሄ ማለት ብራ፣ ብርሃን፣ ደማቅ ማለት ነው፡፡ ከስሙ ትርጉም እንደምንረዳው ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል
ስለሆነ ብራ፣ ብርሃን ደማቅ የሚል ፍቺ ያለው ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
አንድም ቡሄ ማለት በዓሉ የሚውልበት ወቅት የክረምት ጨለማ አልፎ የብርሃን ወቅት የሚመጣበት ሰማይም ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት
የሚለወጥበት የመሸጋገሪያ ወቀት ስለሆነ ብራ ተብሏል፡፡
"ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት እንዲሉ"
አንድም ቡሄ…..ቡኮ "/ሊጥ" ማለት ነው፡፡ በዚህ በዓል ቡኮ ተቦክቶ ዳቦ/ሙልሙል/ ተጋግሮ የሚታደልበት በዓል ስለሆነ
ይህ ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
እስኪ የሙልሙል ዳቦን ነገር ካነሳን እርሱስ ሃይማኖታዊ ትርጉም ይኖረው እንደሆነ የታሪኩንም አመጣጥ በዛው እንመልከት
🌿💖 ሙልሙል ዳቦ 🌿💖
,
ሙልሙል ዳቦ አመጣጡ ጌታችን ብርሃናዊ መለኮቱን በገለጠበት በዚህ ዕለት በደብረ-ታቦር አካባቢ የነበሩ ህፃናት እረኞች ቀኑ የመሸ ስላልመሰላቸው /ጌታችን በብርሃን
አካባቢውን ሞልቶት ስለነበረ/ በዛው ሆነው ከብትና በጎቻቸውን እየጠበቁ ሲቆዩባቸው የሰዓቱን መግፋት የተመለከቱ ወላጆች
በችቦ ብርሃን ተጠቅመው ለልጆቻቸው የሚቀመስ ሙልሙል ዳቦ ይዘው ወዳሉበት መምጣታቸውን ያሳያልና ታሪኩን እየዘከርን
በዓሉን እናከብራለን፡፡
አንድም እንደ ሐዋርያት የምስራች ሊነግሩን ወንጌል ሊሰብኩልን ነው። ታዳጊዎች በየደጃፋችን መጥተው "ቢሄ በሉ" ሲሉን ይበሉት ዘንድ ሙልሙል ይሰጣቸዋል። ይህም መጽሐፋዊ ነው ጌታችን ደቀ
መዛሙርቱን በደረሳችሁበት ሁሉ ሰላምታን ስጡ /ማቴ 10፣12/ብሏልና ሕፃናቱም የሐዋርያት ምሳሌ ስለሆኑ የጌታን በዓል ሊያበስሩ ሲመጡ ዳቦ መስጠት ልማዳዊ ብቻ ሳይሆን መጽሐፋዊ ነው ማለት ነው። መዝሙራቸው ደግሞ ሐዋርያት የምስራች ወንጌል ይዘው የመምጣታቸው ምሳሌ ነው፡፡ ሐዋሪያት በገቡበት ሀገር ሁሉ
አስተምረው አጥምቀው የፀጋ ልጅነትን አሰጥተው እንደሚቆዩ ሁሉ ልጆቹም ዘምረው አመስግነው መርቀው ውለዱ ክበዱ የመንግስተ ሰማያት ወራሾች ያድርጋችሁ ብለው አመስገነው ይሄዳሉና ህፃናቱ በሐዋሪያት ይመሰላሉ፡፡ ሌላው ሕፃናትና እረኞችን ስናነሳ ጅራፋቸውንም
ማንሳታችን አይቀሬ ነው፡፡ በሀገራችንም ከበዓሉ ቀን መድረስ አንስቶ ለበርካታ ቀናት በተለያዩ አካባቢዎች ጅራፍ ይጮሃል ይሄም በዚህ ታላቅ በዓል ሌላው ምሳሌያዊ ምስጢር ነው።
🌿💖 የጅራፍ ማጮህ ምሳሌነት 🌿💖
,
በደብረ ታቦር በዓል በትውፊታዊ መልኩ የሚታየው ምስጢር በእየሩሳሌም ስለሚሆነው የጌታችን የሞቱ ምሳሌ ነው፡፡ በዚህ በዓል ጅራፍ መገመዱ እና ማጮሁ ሁለት አይነት ምሳሌ አለው፡፡የመጀመሪያው ጌታችን በዕለተ አርብ የደረሰበትን ግርፋትና
ሕማም እናስብበታለን፣ ሁለተኛው ደግሞ ድምፁን ስንሰማ የባህሪ አባቱን የአብን የምስክርነት ቃልና በግርማው ሲገለጥ
የተሰማውን ነጎድጓድ ያስታውሰናል፡፡ የጅራፍን ትውፊታዊ ውርስ መጽሐፋዊ ትምህርቱንና ምስጢሩን ከትውልድ ጠብቆ
ለማስተላለፍ ከመኖሪያ ቤት ርቆና በሜዳ በተራራማ አካባቢ ብናረገው ጠቃሚ ነው፡፡ አሁን አሁን ግን ጅራፍን በርችት መቀየሩ
የሚያመጣውም የምስጢር ተፋልሶ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡
የደብረ ታቦር በዓል በዚህ አይነት ምሳሌያት እየተከበረ ሰንብቶ መጠናቀቂያ የሚሆነው በሌላ ምሳሌያዊ ምስጢር ችቦ በማብራት ነው።
💖 ችቦ ማብራት 💖
,
በዚህ በዓል ምዕመናን በቤተ ክርስቲያንና በየቤታቸው ችቦ ለኩሰው የማብራታቸው ምስጢር ስለሁለት ነገር ነው። የመጀመሪያው ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ተራራ ላይ የገለጠውን ብርሃናዊ መለኮት ለማሳየት የሚያመለክት ሲሆን ያንን በዘመናችን ለመግለጥ የበዓሉ ዋዜማ ማታ ችቦ አብርተን አምላካችንን እናመሰግናለን፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በተራራው ላይ የነበሩትን እረኞች ፍለጋ የወጡ ቤተሰቦቻቸው መሽቶ ስለነበር ይታያቸው ዘንድ እሳት ለኩሰው መብራት የመያዛቸውን ታሪክ ለመዘከር ነው።
በአጠቃላይ እንግዲህ በዓለ ደብረ ታቦር ከእነዚህ ምስጢር ካላቸው ትምህርቶችና ትርጓሜያት ጋር ይከበራል። እንግዲህ ይህ ታላቅ በዓል ከነሥርዓቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ በቅብብል እንደመጣልን እኛም ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ሳይለቅ ማስተላለፍ
ይጠበቅብናል፡፡ የዚህ ነገር ባለ ድርሻ አካላት ደግሞ ወጣቶችና ወላጆች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቡሄ ጨዋታ የሚሰሙ ግጦሞች ስድብ ፌዝና ሳቅ ያዘሉ ሆነው ይታያሉ። ተጫዋቾቹም ከሰጡን እንመርቃለን ካልሰጡን እንራገማለን አይነት መልዕክት
ያስተላልፋሉ።የሚብሰው አሳባቢ ነገሩ ደግሞ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ወደ ገንዘብ ማግኛ መቀየሩ ነው፡፡ ስለሆነም ይህን
ነገር በተለይ የነገ የሀገር ተረካቢና የቤተክርስቲያን ተተኪ የሆንን ወጣቶች ማስተካከል ይኖርብል፡፡ወላጆችም ሕፃናት በየደጃፋችን ላይ በዓሉን ሊያበስሩ ሲመጡ አስደንግጦ ከማባረር በሚገባው መልኩ አስተምረን መርቀን ማስተናገድ ይጠበቅብናል ባህሉም እንዳይተው የበኩላችንን አደረግን ማለት ነው።
💖❤️💛💚💓❤️💖💖💖👏
ወስብሓት ለእግዚአብሔር
ወወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክብር አሜን።።።።
መልካም በአል!!!!
1 161
መወድስ
*+
ይብል ጴጥሮስ ፈራሐ ልቡና
ኢየአምን ሰብአ ዘእንበለ አምላክ በተጋንዮ
እንዘ የአምኖ ለወልድ ለቢሰ ሥጋሁ ሐልዮ
ወልደ ማርያም ለጴጥሮስ
ዲበ ታቦር ምስለ አኃዊሁ ውስተ ነድ ወደዮ
ወሰብአ ተመሢሎ
አምጣነ ባሕርዮ ወለጠ እምድኅረ ለጴጥሮስ አስተርአዮ
ሶበ መጽአሂ ወልደ ድንግል በዘየዐቢ ተርእዮ
አርሞንኤም ተፈሢሓ ታስቆቁ ቀራንዮ
እንዘ ያለብሳ ለታቦር ብርሃነ መለኮት አጥርዮ
ማእከለ ጽልመት እስመ ገደፋ ለቀራንዮ ዘታዐብዮ
1 161
መወድስ
ቅኔ ባይኖር በምን እንገልጠው ነበር ?
🤔🤔🤔
ኢይትሐተት ሰብእ በዜና አፉሁ
ወልቡናሁ ዕሙቅ ኢይትረከብ ለኲልነ
እስመ ድኅረ በአፍ ይሴብሕ እንዘ ይነብር ምስሌነ
ስብሐተ አፉሁ ተወኪፈነ
በቅጽበት አመ ተሌለይኖ ያማስን ስመነ
ወአመ ተዋነይነ ተዋንዮ
እንዘ በስኑ ይስሕቅ በልቡናሁ ይረግመነ
ሰብእሂ እኩየ ልብ ዘኢያፈቅር ክብረነ
እንዘ ይጸልአነ ከመሐማ ከመ ይሁዳ ይስእመነ
ወከመ ክርስቶስ ጻድቅ እንተ አፍቀረ ኪያነ
እንዘ በፍቅረ ልብ ናጠርዮ በፍቅረ ብሩር ይሠይጠነ
1 161
🥖 ደብረ ታቦር 🥖
ክፍል ሁለት
✝ለምን ሦስቱን ሐዋርያት ብቻ ይዞ ወጣ?
1⃣ጌታ "እሞታለሁ፤ እሰቀላለሁ" ባለው ጊዜ ጴጥሮስ "ልትሞት አይገባም፤ ይህ ላንተ አይገባም" ብሎ ተቃውሞት ነበርና በአብ ቃል "እርሱ ያላችሁን ስሙት፤ ይህ ለአንተ አይገባም አትበሉት፤ አትቃወሙት" ለማለት፡፡
2⃣ ጌታ "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" ብሎ ደቀመዛሙርቱን በጠየቃቸው ጊዜ ጴጥሮስ "አንተ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ" ብሎት ነበርና አሁንም አብ "አዎ ልክ ነህ! እመለክበት ዘንድ ለተዋሕዶ የመረጥኩት የምወደው ልጄ ይህ ነው" ብሎ ለማረጋገጥ፡፡
3⃣ ለፍቅሩ ስለሚሳሱ ነው፡፡ ይህም በዕብራይስጡ ኬፋ ፤ በግሪኩ ጴጥሮስ ፤ በግዕዙ ኰኲሕ (ዐለት) የተባለው የዮና ልጅ ስምዖን ጌታችን "እሞታለሁ" እያለ ሲናገር "እሞታለሁ" ማለቱ አስቀድመን እንደተናገርን "ለጌታ ካለው ፍጹም ፍቅር የተነሣ ነው" ይላል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡፡
ዮሐንስም በወንጌል "የጌታ ወዳጅ" ተብሎ ተጽፏል፡፡ ያዕቆብ ደግሞ ጌታን በእጅጉ እንደሚወደው በኋላ ታውቋል፡፡ ይኸውም "እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ?" ማቴ ፳፥፳ ሲባሉ "አዎ" ብሎ መመለሱና በዚህም በሄሮድስ ዘአግሪጳ ሰማዕት ሆኖ መሞቱ ምስክር ነው፡፡
4⃣በይሁዳ ምክንያት ነው፡፡ "ኃጥእ ሰው የእግዚአብሔርን ክብር እንዳያይ ያርቁታል" እንዲል ኢሳ ፳፮፥፲፫ እርሱን ጥሎ አሥራ አንዱን ወደ ተራራ ይዞ ቢወጣ ከምሥጢር ቢለየኝ በሞቱ ገባሁበት እንዳይል፡፡ ያም ባይሆን ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ለምን ይከለከላሉ ቢሉ አልተከለከሉም በርእሰ ደብር (በተራራው አናት) ለሦስቱ ደቀ መዛሙርት የተገለጸው ምስጢር በእግረ ደብር (በተራራው ግርጌ) ለነበሩት ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ተገልጦላቸዋል፡፡
ይህም በደብረሲና ለሰባው ሊቃናት የተገለጠ ምሥጢር በከተማ ለነበሩት ለኤልዳድና ሙዳድ እንደተገለጠ ማለት ነው ዘኁ፲፩፥፳፮
✝ኤልያስና ሙሴን ለምን አመጣቸው?
1⃣ በአንድ ወቅት ሙሴ እግዚአብሔርን "በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘቴ እውነት ከሆነስ ፊት ለፊት ተገልጸህልኝ ልይህና በአንተ ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘቴን ልወቀው" ሲል ጠይቆት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም "ጀርባዬን ታያለህ ፊቴን ግን አታይም" ብሎት ነበር ዘጸ ፴፫፥፲፫-፳፫ የዚህ ኃይለ ቃል ትርጓሜና ሐተታ በደብረ ታቦር ተፈጽሟል፡፡
እንዲህ ማለቱ "አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ሰው ሆኜ ሥጋ ለብሼ ኋላ በደብረ ታቦር እስክገለጽልህ ድረስ አንተ በመቃብር ተወስነህ ትኖራለህ" ማለቱ ነበርና፡፡ ይህን ማለቱ እንደሆነ የታወቀው ግን በደብረ ታቦር ሙሴን ከብሔረ ሙታን አምጥቶ ባቆመው ጊዜ ነበር፡፡
2⃣ ልዑል እግዚአብሔር ነቢዩ ኤልያስን፡- "አንተ በኋለኛው ዘመን ምስክር ትሆነኛለህ" ብሎት ነበር፡፡ ይኸውም ኃይለ ቃል ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ "የእኔን የኤልያስን ጌታ ማን ኤልያስ ነው ይልሃል? እግዚአ ኤልያስ፤ አምላከ ኤልያስ ይበሉህ እንጂ" ሲል በደብረ ታቦር ተፈጸመ፡፡ ታያለህ የተባለው ሙሴም አየ፣ ትመሰክራለህ የተባለው ኤልያስም መሰከረ፡፡
3⃣ በፊልጶስ ቂሳርያ ጌታ ሐዋርያትን "ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል?" ብሎ በጠየቃቸው ጥያቄ ሲመልሱ "ሙሴ ነው ይሉሃል ፤ እንዲሁም የኃይል ሥራህን ተመልክተው ኤልያስ ነው ይሉሃል" ብለው ነበርና ሙሴን ከመቃብር ፤ ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ እግዚአ ሙሴ ፤ አምላከ ሙሴ ፤ እግዚአ ኤልያስ ፤ አምላከ ኤልያስ መሆኑን ለማስመስከር፡፡
4⃣ አይሁድ ፈሪሳውያን ጌታን እንደ ሕግ ተላላፊና የእግዚአብሔርን ክብር ለራሱ የሚወስድ አድርገው ያስቡት ስለነበረ ዮሐ፱፥፲፮ ፣ ፲፥፴፫ ሕግን የሰጣቸው ሙሴንና ለሕገ እግዚአብሔር ቀናተኛ የነበረው ኤልያስን አምጥቶ ሕግ አፍራሽ አለመሆኑን የእግዚአብሔር ተቃዋሚም አለመሆኑን ለማስረገጥ፡፡
5⃣ ጌታችን በሙታንና በሕያዋን ላይ ሥልጣን ያለው እንደሆነ ይታወቅ ዘንድ ሞተው ከተቀበሩት ሙሴን ከብሔረ ሕያዋንም ደግሞ አልያስን አምጥቶ ሲነጋገር ታየ፡፡
6⃣ የሐዋርያቱን የወደፊት አገልግሎት ሲነግራቸው፡፡ ይኸውም ሙሴ እና ኤልያስ ለሕዝበ እስራኤል በጣም ታማኝ እንደነበሩ ሁሉ እነርሱም ለሚያገለግሉት ሕዝብ ታማኝ እረኞች እንዲሆኑ፡፡ ሆኖም ግን አገልግሎታቸው ከሙሴና ከኤልያስ ይልቅ ጠንከር እንደሚልም አሳይቶአቸዋል፡፡ ምክንያቱም ውጊያቸው እንደ ሙሴ ከፎርዖን እንደ ኤልያስም ከአክዓብ ጋር ሳይሆን ከክፋት መናፍስት ጋር ነውና፡፡
6⃣ ጽድቃቸው ከእነዚህ ከሙሴና ከኤልያስ የበለጠ ሊሆን እንደሚገባ ለማሳየት ማቴ፭፥፳ ምክንያቱም ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ቢመራ ምድረ ፍልሥጥኤምን ለማውረስ ነው፡፡ እነዚህ ግን ሕዝቡን መርተው የሚያስገቡት መንግሥተ ሰማያትን ነው፡፡ ኤልያስ ሰማያትን ቢለጉምም ከጊዜአዊ ዝናም ነው፡፡ እነዚህ ግን ለዘለዓለም መንግሥተ ሰማያትንም የመለጎም ሥልጣን አላቸውና፡፡
ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ "ጌታ ሆይ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው" ሲል ተደምጧል፡፡ ይህም የተለያየ ትርጉም አለው፡፡ ቃል በቃል (Literaly) ስናየው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታ ሆይ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው ማለቱ "አንተ እያበላኸን እየፈወስከን፣ ሙሴ እነዚህ መከራ ያደርሱቡኛል ይገድሉኛል ያልካቸውን ጸሐፍትና ፈሪሳውያን እንዳይመጡ በደመና እየጋረደ፣ ቢመጡም አልያስ እሳት እያዘነመ እያባረራቸው በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው" ማለቱ ሲሆን ምሥጢራዊው መልእክቱ ግን.....
ክፍል ሦስት ይቀጥላል በዲ/ን የአብስራ ጌታሁን
https://t.me/Eotcw
1 161
🥖 ደብረ ታቦር 🥖
በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ክፍል አንድ
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊሊጶስ ቂሳርያ ለደቀመዛሙርቱ "ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?" ብሎ ጠይቋቸው ነበር፡፡ እነርሱም "አንዳንዶች ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ቅዱስ ነውና ኤርሚያስ ነው ይሉሀል፤ አንዳንዶቹ ድንቅ የሆነ ልደትህንና የምታጠምቀውን አዲስ ጥምቀት አይተው መጥምቁ ዮሐንስ ነው ይሉሀል፤ ሌሎች ደግሞ ለአባቶችህ ቤት ያለህን ቅናት አይተው ኤልያስ ነው ይሉሃል" እያሉ መልሰውለት ነበር፡፡
ጌታችንም መልሶ፡- "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" ብሎ ጠየቃቸው፡፡ የሐዋርያት አፈጉባዔ የሚሆን ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም "አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ነህ" ብሎ መልሷል፡፡ ጌታም "የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ በሰማይ ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም (ምድራዊ መምህር) ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ" ብሎታል፡፡
ከዚህ በኋላ ጌታችን በኢየሩሳሌም ሊቃነ ካህናት፣ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ስለሚያደርሱበት መከራ ስለሚሞተው ሞት ይነግራቸው ጀመር፡፡ ሰይጣንም አስቀድሞ በቀዳሚት ሔዋን እንዳደረገው አሁንም በስምዖን ጴጥሮስ አንደበት ወዳጅ መስሎ "አይሆንም አይደረግም" በማለት መከራከር ጀመረ፡፡
ጌታችን ግን ጴጥሮስን አድርጎ ሰይጣንን ይገሥፀጸው ጀመር፡- "ጴጥሮስ ሆይ! የእኔ አመመጣጥ ለምን እንደሆነ አታስተውልምን? የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ! በቤተ ልሔም ተወልጄ ከሴቶች ለሚወለዱ ሕፃናት ሁሉ ደስታ እንደሆንኩላቸው አሁንም የእኔን እዚያ መውረድ እየተጠባበቁ የሚገኙትን ቅዱሳን ወደ ገነት እመልስ ዘንድ ወደ ሲዖል መሄድ አለብኝ፡፡ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን ይህን ሊያዩ ይመኛሉና፤ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ይናፍቃልና፡፡ ስለዚህ አያቸው ዘንድ መውረድ አለብኝ፤ እጎበኛቸው ዘንድ ልሞት ልሰቀል ይገባኛል፡፡ በእውነት ሰይጣን ካልሆነ በቀር የእኔን መሰቀል የሚቃወም የነፍሳትንም ነፃ መውጣት የማይናፍቅ ማን ነው? አንተ ጴጥሮስ! ይህን ሁሉ የምትለኝ ሰይጣን በአንተ ተመስሎ አንድም አንተው ራስህ ለእኔ ካለህ ፍቅር የተነሣ መሆኑን ብረዳም ጀሮህ ትንቢተ ነቢያትን ባይሰማ ይልቁንም ዓሣ ማጥመድን ብቻ ስለሚያውቅ ነውና ወግድ" አለው፡፡
ይህም በሆነ በሰባተኛው ቀን ሦስቱን ደቀ መዛሙርት ማለትም ጴጥሮስ፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ወጣ፡፡ ክርስቶስ ባይሞት እንዴት ያለ ክብር እንደሚቀርባቸው ያሳያቸው ዘንድ ምስክርም እንዲሆኑ እነዚህን ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ይዞ ወጣ፡፡ በዚያም እንደ ዮርዳኖሱ መድኃኔዓለም ክብረ መንግሥቱን፣ ብርሃነ መለኮቱን ገልጠላቸው፡ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን ቤተ ክርስቲያናችን የምታከብረው ከዘጠኙ ዐበይት የጌታ በዓላት አንዱ የሆነው በዓለ ደብረታቦር የዚህ ታሪክ መታሰቢያ ነው ፡፡
በዚህ ዕለት ሕፃናት ጅራፋቸውን ገምደው እያስጮኹ ይጨፍራሉ፡፡ ይኸውም ጅራፍ ሲጮህ እንደሚያስደነግጥ ሁሉ ከጌታ ጋር የነበሩት ሦስቱ ደቀ መዛሙርትም አብ በደመና ሆኖ ሲናገር መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን የሚያስታውስ ነው፡፡
ታቦር ተራራ ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ ደቡብ በኵል 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፣ ከናዝሬት ከተማ በስተምሥራቅ፣ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ተራራው ከባሕር ወለል በላይ 572 ከፍታ አለው፡፡ ብዙ ሰዎች ከላይ ወደታች ሲታይ ታቦር ተራራ ቅርጹ የተገለበጠ የሻይ ስኒ ይመስላል ይላሉ ፡፡
✝ምሥጢረ መንግሥቱን ለምን በታቦር ተራራ ገለጸው?
መድኃኔዓለም ሌሎች ተራሮች እያሉ ክብሩን ለመግለጥ ስለምን ደብረ ታቦርን መረጠ ቢሉ
ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡
1⃣ ትንቢቱን ለመፈጸም
"ታቦርና አርሞንኤም በስምህ አምነው በተደረገላቸው ነገር ደስ ይላቸዋል፣ ስምህን ያመሰግናሉ፣ ለስምህም ምስጋና ያቀርባሉ" እንዲል መዝ፹፰፥፲፪
2⃣ ምሳሌውን ለመፈጸም
ይህ ተራራ ባርቅ ሲሳራን ድል አድርጎበታል መሳ፬፥፮
ታሪኩም እንዲህ ነው፡፡ "የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደገና ክፉ ሥራ ሠሩ፡፡ እግዚአብሔርም በአሶር በነገሠው በከነዓን ንጉሥ በኢያቡስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የሠራዊቱም አለቃ በአሕዛብ አሪሶት የተመረጠው ሲሣራ ነበር፡፡… ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩትና የእስራኤልንም ልጆች ሃያ ዓመት ያስጨንቃቸው ነበር" መሳ ፬፥፩-፫
ሁሌም ቢሆን የሰውን በደል ዐይቶ እንደወጣችሁ ግቡት፣ እንደገባችኋት ውጧት የማይልና "ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል" የተባለለት እግዚአብሔር ከዚህ ቀንበር የሚላቀቁበትን መላ ራሱ አመለከታቸው ፩ቆሮ ፲፥፲፫
እስራኤላውያን ወደ ፈጣሪያቸው በጮኹ ጊዜ የለፊዶት ሚስት የሆነችውንና እስራኤልን በነቢይነትና ዳኝነት ታገለግል የነበረችው ነቢይቱን ዲቦራን ተጠቅሞ የማሸነፊያ መላውን አመለከታቸው፡፡
ነቢይቱ ዲቦራ ትንቢት ከመናገር አልፋ የእስራኤልን ንጉሥ ባርቅ ከእኔ ጋር ወደ ጦርነቱ ውጪ ብሎ ባስጨነቃት ጊዜ በጦር አዝማችነትም ተሳተፈች፡፡
እግዚአብሔር በነቢይቱ በዲቦራ በኩል ለእስራኤል ንጉሥ "ሔደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጡ" ብሎ አዞት ነበርና ንጉሡ ዐሥር ሺሕ ብረት ለበስ ያልሆነ እግረኛ ሠራዊት ይዞ ደብረ ታቦርን ተማምኖ በተራራው ላይ መሸገ፤ ጦርነቱም ሳይጀመር አለቀ፡፡
ምክንያቱም "እግዚአብሔርም ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሁሉ ሠራዊቱንም ሁሉ ከባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት አስደነገጣቸው፡፡ ሲሣራም ከሰረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ" መሳ፬፥፲፭
እስራኤል በእግዚአብሔር አጋዥነት በታቦር ተራራ ላይ የሃያ ዓመት የግፍና የሰቀቀን አገዛዝ ቀንበራቸውን ከትከሻቸው አሽቀንጥረው በምትኩ የድል ካባን ደረቡ፡፡ "በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ የባዕድ ጭፍሮችንም አባረሩ" ተብሎም ጀግንነታቸው ተጻፈላቸው፡፡ የታቦር ተራራ ያኔ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ባለውለታቸው ነበር።
ዕብ ፲፩፥፴፪-፴፬
ጌታም በልበ ሐዋርያት ያለ ሰይጣንን ድል ያደርግበታልና ማለትም በልባቸው ጥርጥርን እና ፍቅረ ሢመትን (የሥልጣን ፍቅር) ያሳደረ ዲያብሎስን ድል ነስቶላቸዋል ፡፡ ከዚህም በመነሣት ነው "በዓለ ደብረታቦር የደቀመዛሙርት ተማሪዎች በዓል ነው" የሚባለው ፡፡
✝ለምን ሦስቱን ሐዋርያት ብቻ ይዞ ወጣ?
በ ዲ/ን የአብስራ ጌታሁን
@Eotcww ክፍል ሁለት ይቀጥላል
https://t.me/Eotcw
1 161
"ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ልብሱም አንጸባረቀ፤
አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ።
ኤልያስና ሙሴም ታዩአቸው፥ ከኢየሱስም ጋር ይነጋገሩ ነበር።
ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን። መምህር ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው።
እጅግ ስለ ፈሩ የሚለውን አያውቅም ነበር።
ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፥ ከደመናውም። የምወደው ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።
ድንገትም ዞረው ሲመለከቱ ከእነርሱ ጋር ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም።
ከተራራውም ሲወርዱ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይነግሩ አዘዛቸው።"
ማር ፱፥፪-፱
https://t.me/Eotcw
1 161
#ይቤሎ_ጴጥሮስ
ይቤሎ ጴጥሮስ ለኢየሱስ ንንበር ዝየ ሊቅ ንንበር ዝየ
አሐደ ለከ ወአሐደ ለሙሴ ወአሐደ ለኤልያስ ንግበር ማኅደረ
#ትርጉም
ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን። መምህር ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው።
ማር ፪፥፭
https://t.me/Eotcw
1 161
የዕለቱ የቅዳሴ ምስባክ፦ "ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ። ወይሴብሑ ለስምከ። መዝራዕትከ ምስለ ኃይል"። መዝ 88፥12-13። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 11፥23-30፣ 2 ጴጥ 1፥15-ፍ.ም እና የሐ ሥራ 7፥44-54። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 9፥28-38። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ወይም የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ነው። መልካም የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
1 161
የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ ደብር ርጉዕ ወደብር ጥሉል። ለምንት ይትነሥኡ አድባር ርጉአን። ደብር ዘሠምሮ እግዚአብሔር የኀድር ውስቴቱ። መዝ 67፥15-16። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 17፥1-14።
