ሰዋስው ☘☘☘☘
Open in Telegram
በሰዋስወ ብርሀን ቅዱስ ዻውሎስ ገዳም እና ለተለያዩ ቤተክርስቲያን ለክብረ በአላት ማውጫ ። በተጨማሪም-ዋዜማ ሥርዓተ ማኅሌት - መዝሙራት ስንክሳር - የየእለቱን ምስባክ ቅኔያት ጥያቄዎች እንዲሁም የወቅታዊ ነገር መወያያ በተጨማሪም @eotcww ብለው ይቀላቀሉን ለወዳጅ ዘመድዎ share#Share#Share# ያድርጉ።
Show more1 161
Subscribers
No data24 hours
No data7 days
No data30 days
Posts Archive
1 161
19/12/2012 ዓ.ም (፲፱/፲፪/፳፻፲፪ ዓ.ም)
🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯
በእለቱ በነግህ የሚባል ምስባክ
🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯
ወትቀውም ንግሥት በየማንከ።
በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት።
ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ እዝነኪ፡፡ መዝ. 44፥9
🕯 ትርጉም
በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና።
ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።
ልጄ ሆይ ስሚ፤ እዪ፤ ጆሮሽንም አዘንብዪ፡፡
🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯🕯
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
+ + +
❤ "ሰላም ለአልዓዛር ወፊንሐስ ካህናት በዐይት እለ ቅቡዓን በቅብዐ ዕረፍት"። ትርጉም፦ በጣፈጠ ቅብዐ ክህነት ለተቀቡ ለታላላቆች ካህናት አልዓዛርና ፊንሐስ ሰላምታ ይገባል። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።
❤ በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።
https://t.me/Eotcw
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ ነሐሴ ፲፱ (19) ቀን።
❤ እንኳን ለአልዓዛር ልጅ ለካህኑ ለፊንሐስ ለዕረፍት በዓል መታሰቢያ፣ ለታላቁ አባት ለአባ መቃርስ ሳስዊር ከሚባል አገር ወደ አስቄጥስ ገዳም ሥጋው ለፈለሰት በዓል፣ ለአበ ብዙኀን ለአባታችን አብርሃም ጣዖታቱን ለሰበረበትና አምላኩን በሥነ ፍጥረት ተመራምሮ ላገኘበት ቀንና ለእመቤታችን ለትንሣኤዋና ለዕርገቷ አራተኛ ቀን መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። (ስለ ካህኑ ፊንሐስ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ኦ.ዘኊ 25፥1-17 ይገኛል)።
+ + +
❤ የታላቁ አባት የአባ መቃርስ የሥጋ ፍልሰት፦ ይህም ሳስዊር ከሚባል አገር ወደ አስቄጥስ ገዳም የሥጋው ፍልሰት ሆነ።
❤ ከዕረፍቱ በኋላ ከሀገሩ ከሳስዊር ሰዎች መጥተው ሥጋውን ሰርቀው ወደ ሀገራቸው ወሰዱት ቤተ ክርስቲያንም ሠርተውለት ሥጋውን በዚያ አኖሩት እስላሞች እስከ ነገሡበት ዘመንም በዚያ ኖረ።
❤ ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ ቦታ አፍልሰውት በዚያም ቤተ ክርስቲያን ሠሩለት። ለአባ መቃርስ ገዳም አበ ምኔት ሁኖ አባ ዮሐንስ እስከ ተሾመበት ዘመን ኖረ። ሊቀ ጳጳሳቱም የከበረች ጾመ አርብዓን ሊጾም ወደ አባ መቃርስ ገዳም በወጣ ጊዜ ፈጽሞ አለቀሰ እንዲህም ብሎ ጸለየ። "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የከበረ የአባ መቃርስ ሥጋ በዚህ ገዳም በመካከላችን ይሆን ዘንድ እንድትረዳኝ እመኛለሁ"።
❤ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ አባ ሚካኤል ሔደ ከእርሱ ጋራም ስለ ገዳሙ አገልግሎት አረጋውያን መነኰሳት አሉ ልቦናቸውም በመንፈሳዊ ሁከት ተነሣሥቶ ያመጡት ዘንድ የአባ መቃርስ ሥጋ ወደ አለበት ቦታ ደረሱ። የአገር ሰዎችም በአዩአቸው ጊዜ በትሮቻቸውንና ሰይፎቻቸውን በመያዝ ከመኰንናቸው ጋራ ተሰብስበው ከለከሏቸው። በዚያቺም ሌሊት በልባቸው ፈጽሞ እያዘኑ አደሩ። አባ መቃርስም በዚያች ሌሊት ለመኰንኑ በራእይ ተገለጠለትና "ከልጆቼ ጋራ መሔድን ለምን ትከለክለኛለህ እንግዲህስ ተወኝ ከእሳቸው ጋራ ወደ ቦታዬ ልሒድ" አለው።
❤ ያ መኰንንም በጥዋት ተነሣ እየፈራና እየተንቀጠቀጠ የከበሩ አረጋውያን መነኰሳትን ጠርቶ የከበረ የአባ መቃርስን ሥጋ ሰጣቸው። እነርሱም ደስ ብሏቸው ተቀበሉት በመርከብም ተሳፍረው ተርኑጥ ወደሚባል አገር ደረሱ ከእርሳቸውም ጋራ የሚሸኙአቸው ከየአገሩ የመጡ ብዙ ሕዝቦች ነበሩ። በዚያችም ሌሊት በዚያ አደሩ ጸሎትንም አደረጉ ቀድሰውም ለሕዝቡ ሥጋውንና ደሙን አቀበሉ።
❤ ከዚህም በኋላ ተሸክመው ወደ ገዳም ተጓዙ ሲጓዙም ከበረሀው እኵሌታ ደርሰው ከድካማቸው ጥቂት ሊአርፉ ወደዱ። አባ ሚካኤልም "የከበረ የአባታችን የአባ መቃርስን ሥጋ የምናሳርፍበትን እግዚአብሔር እስከ ገለጠልን ድረስ እንደማናርፍ ሕያው እግዚአብሔርን" ብሎ ማለ።
❤ ከዚህም በኋላ የከበረ የአባ መቃርስን ሥጋ የተሸከመ ገመል ወደ አንድ ቦታ ደርሶ በዚያ በረክ አለ። የከበረ የአባ መቃርስ ሥጋ ያለበትንም ሣጥን ይጥል ዘንድ በራሱ ወዲያና ወዲህ ይዞር ጀመረ። አረጋውያን መነኰሳትም እግዚአብሔር የፈቀደው ያ ቦታ እንደሆነ አወቁ እጅግም አደነቁ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ያም ቦታ እስከ ዛሬ የታወቀ ነው።
❤ ወደ ገዳሙም በቀረቡ ጊዜ መነኰሳቱ ሁሉም ወጡ ወንጌልና መስቀሎችን ይዘው መብራቶችን እያበሩ እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን እስከ አስገቡት ድረስ በታላቅ ክብር በራሳቸው ተሸክመው ወሰዱት። እግዚአብሔርም በዚያች ሌሊት ተአምራትን አደረገ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ መቃርስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ይድረሰን ለዘላለሙ አሜን።
+ + +
❤ አበ ብዙሃን(የብዙዎች አባት) ቅዱስ አብርሃም፦ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የአብርሃም አባቱ ታራ ጣዖትን ይጠርብና ይሸጥ ነበር። ሽጦ ገንዘብ የሚያመጣለት ደግሞ ልጁ አብርሃም ነበር። በዚያ ወራት አብርሃም እውነተኛውን አምላክ ፍለጋ ገብቶ ነበር። አንድ ቀን ጣዖቱን ሊሸጥ ወደ ገበያ እየሔደ የተሸከመውን እንጨት ይመራመረው ገባ። "አሁን ይሔ ምኑ ነው አምላክ!" እያለም ያደንቅ ገባ። መንገድ ላይም ደክሞት ካረፈበት "ለምን አልጠይቀውም" በሚል አናገረው።
❤ "እርቦኛል አብላኝ" አለው። መልስ የለም። "እሺ አጠጣኝ" አለው። አሁንም ያው ነው። "ባይሆን እሺ አጫውተኝ" አለው። ጣዖቱ ተራ እንጨት ነውና መልሱ ዝምታ ነበር። ከዚያ ተነስቶ ወደ ገበያው ሲደርስ "ዐይን እያለው የማያይ፤ ጀሮ እያለው የማይሰማ አምላክ የሚገዛ" እያለ ይጮህ ጀመር።
❤ ይህን ሲሰሙ አንዳንዶቹ "የታራ ልጅ አብዶ" ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ "እሱ ያቀለለውን ማን ይገዛዋል" ብለውት ሔደዋል። ከገበያ ሲመለስም ጣዖቱን ተመልክቶ አብርሃም እንዲህ አለ። "አንተ ቀድሞውን በዕለተ ሠሉስ የተፈጠርክ ዕፅ ነህ" ብሎ ሰባበረው።
❤ ወደ ቤቱ ሲመለስም ሁሉንም ጣዖታት ሠባበራቸው። ይህ የተደረገው ከ 2,000 ዓመታት በፊት በዚህች ቀን ነው። የመንግስተ ሰማያት አበጋዝ የእግዚአብሔር ወዳጅ አባታችን አብርሃም በመጨረሻው በውሃ፣ በነፋስ፣ በእሳትና በፀሐይ ተመራምሮ ፈጣሪውን አግኝቷል። ምንጭ፦ ከዲያቆን ዮርዳኖስ አበባ።
+ + +
❤ የዕለቱ ምስባክ፦ "በእግዚአብሔር እሴብሕ ቃልየ። በእግዚአብሔር ይከብር ዘነበብኩ። ወበእግዚአብሔር ተወከልኩ ኢይፈርህ ምንተ ይሬስየኒ ሰብእ"። መዝ 55፥10-11 ወይም መዝ 44፥9-10። የሚነበቡ መልዕክታት ሮሜ 1፥8-15፣ 1ኛ ጴጥ 3፥8-15 እና የሐዋ ሥራ 16፥35-ፍ.ም። የሚበበው ወንጌል ማቴ 27፥50-57 ወይም ሉቃ 1፥39፥57። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ወይም የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የእመቤታችን የትንሣኤዋና የዕርገቷ በዓል ሰሞን። ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።
https://t.me/Eotcw
1 161
«ማንም፦ እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።"
1ኛ ዮሐ. 4 ፥ 20-21
የሰው ልጅ የተፈጠረበት አራቱ ባሕርያተ ሥጋ ምሳሌነታቸው እንደምንድን ነው ቢሉ፦
# እሳት ፡- በእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት ይመሰላል። ለምን ቢሉ እሳት ፈቃድ ፈጻሚ ነው አንድ ቦታ ላይ ብንጭረው ሃገርን ሊያወድም ይችላል እግዚአብሔርም ሁሉን ማድረግ የሚችል ምንም ማይሳነው አምላክ መሆኑን።
# ውሃ ፡- በእግዚአብሔር ርህራሄ ይመሰላል። ውሃ እድፍን እንደሚያጠራ በኃጥያታችን ተጸጽተን ንስሐ ብንገባ ይቅር ሊለን፣ ከኃጢአታችን ሊያነጻን የታመነ መሆኑን።
# ንፋስ፡- በእግዚአብሔር ፈራጅነት ይመሰላል። ንፋስ ገለባውን ከስንዴ እንደሚለይ እግዚአብሔርም በዳግም ምጽዓት ጊዜ ኃጥኡን ከጻድቁ በእውነተኛው ፍርዱ የሚለይ መሆኑን።
# መሬት (# አፈር):- በእግዚአብሔር ታጋሽነት ይመሰላል። መሬት ጥቁር፣ ቀይ፣ ወፍራም፣ ቀጭን ፣ ኃጥእ፣ ጻድቅ ሳትል ሁሉንም ችላ ትኖራለች ፈጣሪም እንዲሁ በማንነታችን ሳይለየን የሚታገሰን መሆኑን።ነው እግዚአብሔር ለንስሐ ያብቃን ቃሉን ሰምተን 30-60-100 እንድናፍራ ያድርገን
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ ነሐሴ ፲፰ (18) ቀን።
❤ እንኳን ለእስክንድርያ ዐሥራ ዘጠነኛ ሊቃነ ጳጳሳት በኒቅያ ጉባኤ በ325 ዓ.ም ከሀዲው (መናፍቁን) አርዮስ ከአትናቴዎስ ጋር በመሆን ተከራክሮ ላወገዘው ለታላቁ አባት ለአባ እለእስክድሮስ ለመታሰቢያው በዓሉና ለእመቤታችን ለትንሣኤዋና ለዕርገቷ ሦስተኛ ቀን መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪም በዚች ቀንከሚታሰበው፦ ከዲያቆን እንድራኒቆስ ከመታሰቢያው በዓሉ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
+ + +
❤ "ሰላም ለእለእስክንድሮስ ዘደለዎ ጵጵስና ስርግው በቅድስና"። ትርጉም፦ ጵጵስና የተገባው ለኾነ በቅድስና ላጌጠ (ለተሸለመ) ለእለእስክንድሮስ ሰላምታ ይገባል። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።
+ + +
❤ አባ እለእስክንድሮስ፦ እርሱም ቊጥሩ ከአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ነው። ይህም አባት ከአርዮስ ወገኖች ብዙ ችግር ደርሶበታል እርሱ ከወገኖቹ ጋር ሁኖ አርዮስን አውግዞ ከቤተክርስቲያን አሳዶት ነበርና።
❤ በታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ዘመን በኒቅያ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶች ሊቃውንት አርዮስን በጉባኤ አውግዘው ከቤተ ክርስቲያን ለይተው በአሳደዱት ጊዜ ወደ ንጉሡ ቈስጠንጢኖስ ጓደኞቹን ይዞ ገብቶ በእለእስክንድሮስና በአትናቴዎስ ላይ ነገር ሠራ ሁለተኛም እለእስክንድሮስ ከካህናቱ ጋር ይቀበለው ዘንድ እንዲያዝለት ንጉሡን ለመነው።
❤ ንጉሡም ልመናውን ተቀብሎ መልእክተኞችን ልኮ አባት እለእስክንድሮስን አስመጥቶ እንዲህ አለው "አትናቴዎስ ትእዛዛችንን በመተላለፍ አርዮስን አልቀበልም ብሏል፤ እኛም አንተን እንዳከበርንህ አንተ ታውቃለህ አሁንም ትእዛዛችንን አትተላለፍ አርዮስንም ከውግዘቱ ፈትተህ ልባችንን ደስ አሰኝ" አለው ። ቅዱስ እለእስክንድሮስም ለንጉሥ እንዲህ ብሎ መለሰለት "አርዮስን እኮን ቤተክርስቲያን አልተቀበለችውም። ልዩ ሦስትነትን አያመልክምና" ንጉሡም "አይደለም እርሱ በሥሉስ ቅዱስ ያምናል እንጂ" አለው ቅዱስ እለእስክንድሮስም "ወልድ በመለኮቱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ትክክል እንደሆነ የሚያምን ከሆነ በእጁ ይጻፍ" ብሎ መለሰለት።
❤ ንጉሥም አርዮስን አስቀርቦ "ትክክለኛ ሃይማኖትህን ጻፍ" አለው አርዮስም በልቡ ሳያምን "ወልድ ከአብ ጋራ በመለኮቱ ትክክል ነው" ብሎ ጻፈ በሐሰትም የከበረ ወንጌልን ይዞ ማለ። ንጉሡም ቅዱስ እለእስክንድሮስን "አሁን በአርዮስ ላይ ምክንያት አልቀረህም ትክክለኛ ሃይማኖቱን ጽፎአልና በከበረ ወንጌልም ምሎአልና" አለው ።
❤ አባ እለእስክንድሮስም ንጉሡን እንዲህ አለው "በአባትህ በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እጅ የተጻፈ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ አባቶች በእጆቻቸው የጻፉትን እርሱንና ወገኖቹን ከቤተ ክርስቲያን እንዳሳደዷቸው የአርዮስን ክህደቱንና ውግዘቱን አትናቴዎስ አንብቦታል። ነገር ግን አንድ ሱባዔ በእኔ ላይ ታገሥ በዚህ ሱባዔ በአርዮስ ላይ አንዳች ነገር ካልደረሰ ይህ ካልሆነ ሃይማኖቱ መሐላውም እውነት ነው እኔም ተቀብዬ ከካህናቱ ጋር እቀላቅለዋለሁ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም ከእሳቸው ጋራ አንድ ይሆናል"።
❤ ንጉሡም አባት እለእስክንድሮስን እንዲህ አለው "እወቅ እኔ ስምንቱን ቀኖች እታገሥሃለሁ አርዮስን ካልተቀበልከው በአንተ ላይ የፈለግሁትን አደርጋለሁ።" ከዚህም በኋላ ከንጉሡ ዘንድ ወጥቶ ወደ ማደሪያው ሔደ ቤተክርስቲያንን ከአርዮስ መርዝ ያድናት ዘንድ በዚያ ሱባዔ እየጾመና እየጸለየ ወደ እግዚአብሔር ሲለምን ሰነበተ።
❤ ከዚያም ሱባዔ በኋላ አርዮስ መልካም ልብስን ለበሰ ወደ ቤተክርስቲያንም ገብቶ በመሠዊያው ፊት ከካህናቱ ጋራ ተቀመጠ። ከዚህም በኋላ አባ እለእስክንድሮስ እያዘነና እየተከዘ ገባ ከኀዘኑም ብዛት የተነሣ የሚሠራውን አላወቀም የቅዳሴውንም ሥርዓት ሊጀምር ቆመ። ያን ጊዜ የአርዮስ ሆዱ ተበጠበጠና "ወጥቼ ልመለስ" አለ ይህንንም ብሎ ወደ መጸዳጃ ቦታ ወጣ። ሊጸዳዳም በተቀመጠ ጊዜ አንጀቱና የሆድ ዕቃው ሁሉ ወጣ በዚያውም ላይ ሞተ። በዘገየም ጊዜ ሊፈልጉት ወጡ በመጸዳጃውም ቦታ ሬሳውን ወድቆ አገኙት። ለዚህም ለአባት እለእስክንድሮስ ነገሩት እርሱም አደነቀ የከበረች ቤተክርስቲያኑን ያልጣላት ምስጉን የሆነ ክርስቶስንም አመሰገነው።
❤ ንጉሡም በሰማ ጊዜ አደነቀ ከሀዲ አርዮስም በሐሰት እንደማለና በሽንገላ እንደጻፈ አወቀ። የዚህንም አባት የእለእስክንድሮስን ቅድስናውን ዕውነተኛነቱ ሃይማኖቱም የቀናች መሆኗን የአርዮስንም ሐሰተኛነቱንና ከሀዲነቱን ተረዳ።
❤ አንድ የሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስንም አመሰገነው መለኮታቸውም አንድ እንደሆነ ታመነ። ይህም አባት በበጎ ሥራ ጸንቶ ኖረ ለምለም ወደ ሆነ እርግናም ደርሶ ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔደ የሕይወት አክሊልንም አገኘ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ እለስክንድሮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 18 ስንክሳር።
+ + +
❤ "ሰላም ለከ እለእስክንድሮስ ሥዩም። በዕብረሬት ዘወረደ ኃይለ አርያም። ለአርዮስ ውቁይ በሰይፈ መርገም። እስከ ኢተርፈ ሎቱ እንበለ አነዳ ወዐፅም። ንዋየ ውስጡ ተክዕወ ከመ ዐፍዕ ዘላህም"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የነሐሴ 18።
+ + +
❤ የዕለቱ ምስባክ፦ "አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር። ወኢትትኃጎሉ እምፍኖተ ጽድቅ። ሶበ ነደት ፍጡነ መዓቱ"። መዝ 2፥12፣ መዝ 108፥18-19 ወይም መዝ 44፥9-10። የሚነበቡ መልዕክታት ፊሊ 3፥1-6፣ 1ኛ ዮሐ 2፥1-20 እና የሐዋ ሥራ 20፥28-31። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 15፥6-21። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ወይም የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የእመቤታችን የትንሣኤዋና የዕርገቷ በዓል ሰሞን ለሁላችን ይሁንልን።
❤ በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።
https://t.me/Eotcw
1 161
እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ ፍቺ በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ! በየትም ዓለም የምትኖሩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ሰላምታችን ይድረሳችሁ፡፡
የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር የኖረችው ስልሳ አራት ዓመት ነው፡፡ እነዚህ ዓመታት ሲተነተኑ ሦስት ዓመት በወላጆቿ ሐናና ኢያቄም ቤት፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፣ ሠላሣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከልጇ ከወዳጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አሥራ አምስት ዓመት ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ጋር ነው፡፡
ያረፈችውም ጥር 21 ቀን በ50 ዓ.ም ነው፡፡ ባረፈችበት ወቅት ቅዱሳን ሐዋርያት ክቡር ሥጋዋን ለማሳረፍ ወደ ጌቴ ሴማኒ ሲሔዱ አይሁድ "ቀድሞ ልጇ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፤ በአርባኛውም ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ተመልሶም ይህን ዓለምን ለማሳለፍ ይመጣል እያሉ በማስተማር ሕዝባችንን ወስደውብናል፡፡ አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷም እንደ ልጇ ተነሳች እያሉ በማስተማር ሊያውኩን አይደለምን? ኑ! ተሰብስበን በእሳት እናቃጥላት" ብለው ክፉ ምክር ተማከሩ፡፡
ከመካከላቸውም ብርቱ ሰው የሆነው #ታውፋንያ የተባለ ቅድስት ሥጋዋን ከሐዋርያት ነጥቆ ለማስቀረት ክቡር ሥጋዋ ያለበትን የአልጋ ሸንኮር ሲይዝ በመልአከ እግዚአብሔር እጁ ተቆርጣ ከአልጋው ላይ ተንጠልጥላ ቀረች፤ ከዚህ የጥፋቱ ሥራው ተምሮ እመቤታችንን በመለመኑ እመቤታችን የተቆረጠች እጁን መልሳለታለች፡፡
ከዚህ በኋላ መልአከ እግዚአብሔር የእመቤታችንን የተቀደሰ ሥጋዋን ጌታችን ይወደው የነበረ ተብሎ የተነገረለት ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ይዞ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም የሆነውን ሁሉ ለወንድሞቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ነገራቸው፡፡ እነሱም የእመቤታችን ሥጋ በክብር ለማሳረፍ ካላቸው ጉጉት የተነሣ ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ ሱባኤ ገቡ፡፡
ከሁለተኛ ሱባኤ ቆይታቸው በኋላ በአሥራ አራተኛ ቀናቸው ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ ሥጋ ሰጣቸው፡፡ ሐዋርያትም በዝማሬና በታላቅ ምስጋና በጌቴ ሴማኔ ቀበሯት፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት› › ተብሎ ትንቢት የተናገረውን ሲተረጉሙት ‹‹ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ሆይ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት የምታሳርፈው የመቅደስህ ታቦት የሆነችውን ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ›› ብለው ያመሰጥሩታል፡፡ /መዝ. 131፥8/፡፡
የእመቤታችንን ቅድስት ሥጋዋን ሐዋርያት ሲቀብሯት በሀገረ ስብከቱ ሕንድ የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ ሲመለስ እመቤታችን ስታርግ ያገኛታል ለምልክት እንዲሆነው ሰበኗን (የመግነዟን ጨርቅ) ተቀብሏት ይለያያሉ፡፡ ለወንድሞቹ ሐዋርያት ያየውን ይነግራቸዋል፡፡
ለበረከት የሰጠችውንም ሰበን ያካፍላቸዋል፤ ሐዋርያት ‹ ‹ዕርገቷን እንዴት እሱ ብቻ ተመልክቶ ለምን እኛ ይቀርብናል› › ብለው በዓመቱ ነሐሴ አንድ ቀን ሱባኤ ገቡ፡፡ ነሐሴ 16 ቀን የልባቸው መሻት ተፈጸመላቸው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቀ (ረዳት) ቄስ፣ ቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ (ዋና ዲያቆን) አድርጎ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው፡፡
በትኅትና የያዙት ሱባኤም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርገቷን ለማየት አበቃቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን መሠረት አድርጋ ከነሐሴ 1-16 ጾመ ፍልሰታ በማለት ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ አድርገን እንድንጠቀምበት ሥርዐት ሠራችልን፡፡
በነቢያና በሐዋርያት መሠረት ላይ የታነጽን ኦርቶዶክሳውያን የተዋሕዶ ልጆች በየዓመቱ ይህን ጾም በሱባኤ በማሳለፍ ከእመቤታችን ጸጋና በረከት ተሳታፊዎች እንሆናለን፤ ሆነናልም፡፡ የዓመት ሰዎች ይበለን፡፡
ከእመቤታችን ረድኤት በረከት ተቋዳሾች ያድርገን፡፡
አሜን!
ለወዳጅዎ ሼር ያድርጉ
https://t.me/Eotcw
1 161
" #ኢየሱስ ያድናል ??"
"ኢየሱስ ያድናል!!!" የሚለው ኃይለ ቃል የሰሞኑ መጨቃጨቅያ ርዕስ ነበረ፣ ብዙዎች ሐሳቡን ከማብራራት ይልቅ ስለሰዎች ማንነት በማውራት ተጠምውደውበታል፣ እንዳዶች ደግሞ እርስ በእርሳቸው በጥላቻ ሲናቆሩ ቆይተዋል። ጥቂቶች ደግሞ ከመካሰስ እና ከመብት ጋር ስላሉት ነገሮች አንስተዋል። አሁን ሁሉም ጋብ ስላሉ ሐሳቡ ላይ ማብራሪያ ያስፈልጋል ብዬ ይህቺን አጭር ፁሕፍ ፃፍኩ።
"ኢየሱስ ያድናል!!" በሚለው ኃይለ ቃል ማንም ክርስቲያን የሆነ ሰው ሁሉ የሚጠራጠር አይመስለኝም። ግን "የትኛው ኢየሱስ ያድናል ?" የሚለው ሊይአከራክር ይችላል። የቁራኑ ኢየሱስ ከሆነ ነቢይ ነው፣ ማዳን አይችልም ፣የታልሙዱ ኢየሱስም ከሆነ ፣ ዕሩቅ ብዕሲ ነው ፣እርሱም ቢሆን ማዳን አይችልም። የፈላስፎች ኢየሱስም ከሆነ ምናባዊ ነው ፣እርሱም ቢሆን በታሪክ ሳይኖር አይቀርም" ተብሎ እንአንዳድ ፈላስፎቹ የሚጠቀስ እንጂ አዳኝ ተብሎ አልተገለፀም ።
የመ"ና"ፍ"ቃ"ኑ ኢየሱስም ከሆነ አንዳድ ጊዜ ሰው አንዳድ ጊዜ አምላክ እያሉት ከባህርይው አውጥተውታል። እርሱም ቢሆን እናት ሰለሌለችው ያለቅሳል ፣አባቱ ከእርሱ ሰለሚበልጥ ይለምናል እስከአሁን ያለቅሳል እስከአሁን ይለምናል ። እንኳን እኛን ሊያድን እራሱን ማዳን አልተቻለውም ።
#ነገር ግን ከሰማይ የወረደው ወደ ሰማይ ያረገው የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እርሱ አዳኝ ነው ፣ያድናል። አምላክ ነው፣ ይመለካል ፣ጌታ ነው፣ይሰገድለታል፣ ይህ የኦርቶዶክስ ኢየሱስ ነው።
ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ ድንግል ማርያምን ያበሰራት "ኢየሱስ "ይሄ ነው። በማርያም አንፃር ለእኛም የኢየሱስን አዳኝነት የሰበከን ቅዱስ ገብርኤል ነው። በቅዱስ ገብርኤል እንደተገለፀው ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሸ ። እርሱም ሕዝቡን ከሀጢያታቸው ያድናቸዋል። ሲል ስብከቱን ሰምተነዋል። ይህ ቃል ለድንግል ማርያም ብስራት ሲባል ለእኛ ግን ስብከት ነው።
ኢየሱስ የሚለውን ስም "ኢየሱስ ያድናል" ብሎ የተረጎመልን ቅዱስ ገብርኤል ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ያድናል? ለሚለን "አዎ ኢየሱስ ያድናል!!" መልሳችን ነው። የኢየሱስን ደም አልፎ የእኛን ሀጢያት የሚቆጥር ማንም ሀይል የለም።
የኢየሱስን አዳኝነት ከቅዱሳን አማላጅነት ጋር ግን አደባልቆ ማምታታትም አያስፈልግም።
#የቅዱሳን አማላጅነት ለግብረ ሀጢያታችን የሚጠቀስ እንጂ ለአዳማዊ ሀጢያታችን መሰረዝ የሚነገር አይደለም፣ ከእኛ ላይ አዳማዊ ሀጢያታችንን በመስቀል ተሰቅሎ ያስወገደልን እና ያዳነን እንዲሁም ያነፃን እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።
ወደ ፊትም ከባህርይ አባቱ ጋር ከአብ ጋር ከባህርይ ህይወቱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሆኖ እንደ ስራችን የሚከፍለን ፈራጅ እርሱ ብቻ ነው። ቃል ኪዳን በሰጣቸው መሠረትም የቅዱሳን አማላጅነት ላይ ውሳኔ የሚሰጥ ፈራጅ እርሱ ነው።
#ሌላው ኢየሱስ ያድናል !!" ከሚለው ኃይለ ቃል ጋር በተያያዘ ኢየሱስ 'መንገድ ነኝ' ያለበትን እና 'በር' ነኝ ያለበትን የመፅሀፍ ቅዱስ ቃል ከአውድ ውጪ በመተርጎም አንዳድ ሰዎች ሲጨቃጨቁበት አስተውያለው።
በዮሐንስ ወንጌል መንገድ እና በር በሚል ፈሊጣዊ አነጋገር ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ አንደበት የተገለፀበት አውደ ቃል በጥሬ 'በር' ወይም 'መንገድ' ተብሎ የሚተረጎም አይደለም።
መንገድም ሆነ በር ማለት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ መግቢያ ያለ የመጽሐፍት ይዘት የምንአውቅበት መግለጫ ማለት ነው፣ ለዚህም ነው ኢየሱስ "እኔን ያየ አብን አየ'' ያለው ። ወይም ወንጌላዊ ዮሐንስ በወንጌሉ እንደፃፈልን ;-
"እግዚአብሔርን ያየው አንድ ሰው እንኳን የለም ፣ ነገር ግን በአባቱ እቅፍ ያለው አንድያ ልጁ ተረከልን። ሲል አብን የምንአይበት እና የምንአውቅበት "መንገድ" እና "በር" ኢየሱስ መሆኑን ተነገረ እንጂ አየሱሰ ማለትን በጥሬው አገላለጽ ወደ አብ የምንሄድበት 'መንገድ' ወይም ወደ አብ የምንገባበት 'በር' ነው ማለት አይደለም።
"መንገድነት" እና "በርነት "የእግዚአብሔርን ህልውና ከመግለፅና አንድነቱን ሦስትነቱን ከማወቅ ጋር የተጠቀሰ ፈሊጣዊ አነጋገር እንጂ ከኢየሱስ አዳኝነት ጋር ተያይዞ የተጠቀስ ቃል አይደለም።
#ባጭር ቃል "ኢየሱስ ያድናል!!" ስንል ፈራጅ ማለታችን ነው እንጂ አማላጅ ነው ማለታችን አይደለም። አማላጅነት የቅዱሳን ስራ ነው ፣አዳኝነት ግን የእግዚአብሔር ስራ ነው ፣ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ ከማርያም ቢወለድም እግዚአብሔርነቱን አልተቀማም ።
ሊቀ ጠበብት ዶ/ር ዘሪሁን ሙላቱ
https://t.me/Eotcw
1 161
#የሻደይ_በዓልና_ፍልሰታ
የሻደይ በዓል አጀማመርን በተመለክተ ከላይ
ከተቀመጡት ታሪኮች በተጨማሪ በአካባቢው
ሕዝብና በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ
ተደጋግሞ የሚነሣው ታሪክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ በዓል ነው፡እግዚአብሔር ለአዳምና ሔዋን ከአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመት በኋላ ወደዚህ ዓለም አንድያ ልጁን ልኮ ከኀጢአት እሥራት ነጻ እንደሚያወጣቸው በገባላው ቃል ኪዳን መሠረት አምላክ የተወለደባት እና ትንቢቱ የተፈጸመባት፣ ከገነት የተባረረው የሰው ልጅ ወደ ገነት እንዲመለስ ምክንያት የኾነችው፣ የሰው ልጆች መመኪያ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ዓለም ድካም ካረፈች በኋላ ሞትን ድል አድርጋ ከመቃብር ተነሥታ ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡
👉 #በፍልሰታ_ወቅት_በዓሉ
_መከበሩም
ለሻደይ ተጨዋቾች ተምሳሌትና የድንግልናቸው አርአያ የሚያደርጓት ድንግል ማርያም አካላዊ ሥጋዋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለሱን፤ እንደዚሁም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ምክንያት በማድረግ እንደኾነ የሚገልጹት የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል መምሪያ ሓላፊ መጋቤ ምሥጢር ገብረ ሕይወት ኪዳነ ማርያም ‹‹የሻደይ በዓል በልጃገረዶች ዘንድ ተወዳጅ የኾነው በሔዋን ምክንያት የተዘጋው ገነት በእመቤታችን አማካኝነት በመከፈቱ ነው። እመቤታችን መመኪያቸው ስለ ኾነች ልጃገረዶች በዓሉን በደስታ ያከብሩታል፤ ድንግልናቸውንም አደራ የሚሉት ለእርሷ ነው›› ሲሉ ይናገራሉ።
እመቤታችን በነሐሴ ፲፮ ቀን በቅዱሳን መላእክት ሽብሸባ፣ ዕልልታና ዝማሬ ታጅባ ከምድር ወደ ሰማይ ስታርግ ሐዋርያት በታላቅ ደስታ ይመለከቱ፣ ይደነቁም ነበር፡፡ ደናግልም ከቅዱሳን መላእክት ከተመለከቱት ሥርዓት በመነሣት ነጫጭ ልብሶችን ለብሰው፣ አምረውና አጊጠው፣ ረጃጅምና ለምለም ቅጠል በወገባቸው አሥረው እንደ መላእክቱ አክናፍ ወገባቸውን ከግራ ወደ ቀኝ እያመላለሱ፣እያዘዋወሩና እያሸበሸቡ፣ በአንደበታቸው እየዘመሩና በእጆቻቸው እያጨበጨቡ በአንድነት ተሰባሰባስበው በፍቅርና በሐሴት የወቅቱ መታሰቢያ የኾነውን የሻደይን በዓል ያከብራሉ ፡፡
እናቶችና እኅቶች በዐደባባይ ወጥተው የድንግል ማርያምን ትንሣኤና ዕርገት እንደ ነጻነታቸው ቀን በመቍጠር ከበሮ አዘጋጅተው ‹‹አሸንድዬ›› የተባለውን ቄጠማ በወገባቸው ታጥቀው ምስጋና በማቅረብ በዓሉን ይዘክራሉ፡፡ በአጠቃላይ የሻደይ ጨዋታ የፍልሰታ በዓል መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በምእመኑ ዘንድ ለበርካታ ዓመታት እየተከበረ የኖረ ሃይማኖታዊ በዓል ነው፡፡ ይህንን ሃይማኖታዊ መሠረትነት ያለውን ትውፊት የመጠበቅና የማስጠበቅ ሓላፊነት ከኹላችንም ይጠበቃል።
የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ተፅህፈ ፡ እም የአብስራ ጌታሁን
https://t.me/Eotcw
1 161
❤ መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በሠለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ አዘዘና ቆረጡት የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበለ። ከገምኑዲ ሀገር የሆኑ አብርሃምና ዮሐንስም ከእርሱ ጋራ ሰማዕታት ሆነው ሞቱ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ ቅዱስ ያዕቆብና በባልንጀሮቹ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 17 ስንክሳር።
+ + +
❤ "ሰላም ለእንጣዎስ ለሃይማኖቱ ዘአጽደላ። እምነ ኦርያሬስ ወስነ እብላ። ከመ ኢትትሀጐል ነፍሱ እግዚአብሔር ሶበ ተሣሃላ። በሐፀ እሳት ቀዲሙ አቊሰላ። ወጠለ ምሥዋዕ ካዕበ ውእቱ አጥለላ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የነሐሴ 17።
+ + +
❤ የዕለቱ ምስባክ፦ "ገሥፆሰ ገሠፀኒ እግዚአብሔር። ወለሞትሰ ባሕቱ ኢመጠወኒ። አርኅው ሊተ አናቅጸ ጽድቅ"። መዝ 117፥18-19 ወይም መዝ 44፥9-10። የሚነበቡት መልዕክታት ፊሊጵስ 3፥6፣ 1ኛ ጴጥ 4፥12-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 9፥1-8። የሚበበው ወንጌል ዮሐ 15፥12-26 ወይም ሉቃ 1፥39፥57። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም የእመቤታ የትንሣኤ የዕርገት በዓል ሰሞን ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።
https://t.me/Eotcw
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ ነሐሴ ፲፯ (17) ቀን።
❤ እንኳን ለአሞራዊው ለቅዱስ እንጣዎስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓልና ከደቡብ ግብጽ አቡስ ከሚባል አውራጃ መኑፍ ከሚባል ታናሽ መንደር ለቅዱስ ያዕቆብ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን። በጨማሪም በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከቅዱስ እንጣዎስ ወንድሙ ከቅዱስ አክራጥስ ከዕረፍቱ ከዕረፍቱ መታሰቢያ፣ ከቅዱስ ያዕቀብ ጋር ሰማዕትነት ከተቀበሉ ከገምኑዲ ሀገር ከሆኑ ቅዱሳን አብርሃምና ዮሐንስምና ከቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ከእለእስክድሮስ ከዕረፍቱ መታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
+ + +
❤ አሞራዊ ሰማዕቱ ቅዱስ እንጣዎስ፦ ይህም ቅዱስ አስቀድሞ ክርስቶስን የካደ ነበር ገንዘብ ለማከማቸትም የሚተጋ ነበር። በአንዲትም ዕለት ወደ ደማስቆ ከተማ ሔደ የበዓላቸው ቀን ነበርና ሕዝቡ ተሰብስበው ሳሉ ወደ ምሥራቃዊው ቅዱስ ቴዎድሮስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገባ ገብቶም ዕቃዎችን ማቃጠል ጀመረ መስቀልንም ሰበረ።
❤ ከዚህም በኋላ በሰማይ ውስጥ የእሳት ፍላፃዎችን ይዘው ከሀዲዎችን ሲነድፏቸው አየ እርሱንም የቀኝ ጐኑን አንዲት ፍላፃ ነደፈችው። ያን ጊዜም ተጨንቆ ላቡ ተንጠፈጠፈ ከጥልቅ ልቡም እንዲህ ብሎ ጮኸ "የቅዱስ ቴዎድሮስ አምላክ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አመንኩብህ" ከእንግዲህ ዳግመኛ ሌላ አምላክ እንዳያመልክ በልቡናው ቃል ገባ።
❤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖችም በእርሱ ላይ የሆነውን አላወቁም ነገር ግን ጩኸቱንና የሚናገረውን ሰምተው አደነቁ እምነታቸውም ጠነከረ እጅግም ጸና። እንጣዎስም ኤልያስ ወደ ሚባል ጳጳስ ሒዶ በርሱ ላይ የሆነውን ሁሉ ነገረው የክርስትና ጥምቀትንም ያጠምቀው ዘንድ ለመነው። ጳጳሱም በውኃው ላይ በጸለየ ጊዜ የብርሃን ምሰሶ እንደ ቀስተ ደመና ሁኖ ሕዝቡ ሁሉ እያዩት ወረደ ቅዱስ እንጣዎስም ተጠመቀ። ከእርሱም ጋራ ከአይሁድና ከአረሚ ዐሥር ሽህ ሰባት መቶ ዘጠና ስምንት ያህል ሰዎች ተጠመቁ። ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋውንና ደሙን ተቀበሉ።
❤ ቅዱስ እንጣዎስም እንዲህ አለ "እነሆ ይህን እያደነቅሁ ሳለ በእንቅልፌ ሕልምን አየሁ። ብርሃንን የለበሰች ሴት እጄን ያዘችኝ ወስዳም ወደ ኢየሩሳሌም አደረሰችኝ ወደ መሠዊያውም አቀረበችኝ እኔም ቅዱስ ቊርባንን ለመቀበል ተዘጋጀሁ በመሠዊያውም ውስጥ ነጭ በግን አየሁ ካህኑም በዕርፈ መስቀል በሠዋው ጊዜ ደሙ ጽዋው ውስጥ ተጨመረ ከእርሱም የክርስቶስን ሥጋና ደም በተቀበልሁ ጊዜ ሥጋው ንጹሕ ኅብስት ደሙም ጥሩ ወይን ሆነ"።
❤ ከዚህም በኋላ በደማስቆ ጐዳና ሲጓዝ አስቀድሞ የሚያውቁት ያዙት ወደ ንጉሡም ወሰዱት ንጉሡም ክርስቶስን በማመን እንደጸና አይቶ ጥርሶቹ እስቲበተኑ አፉን በበሎታ እንዲመቱት አዘዘ አፉም ደምን ተመላ። ከዚህም በኋላ እህል ውኃን ሳይሰጡ በተበሳ ግንድ ውስጥ ሰባት ቀን ያህል አሠሩት ከዚያም አውጥተው ዲን፣ ሙጫ፣ ዝፍት ከስብ ጋራ ባፈሉበት እሳት ውስጥ ጨመሩት ከእርሱም የመልካም መዓዛ ሽታ ወጣ።
❤ ወታደሮችም ከእሳት ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ አገኙት። እሳቱም አልነካውም ወደ ንጉሥም ወሰዱት ንጉሡም "የሥራይን ኃይል መቼ ተማርክ" አለው ቅዱስ እንጣዎስም ንጉሡን እንዲህ አለው "ሥራይንስ አላውቅም ነገር ግን ክብር ይግባውና በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል አሳፍርሃለሁ"። ንጉሡም ቁጣን ተመልቶ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ።
❤ ከዚህም በኋላ ቅዱስ እንጣዎስ ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ ቆመ እጆቹንም ዘርግቶ ነፍሱን ወደ እግዚአብሔር አማፀነ ሲጸልይም ወደርሱ እንዲህ የሚል ቃል መጣ "ከእስጢፋኖስና ከጊዮርጊስ ጋራ ታርፍ ዘንድ አገልጋዬ በሰላም ና"። ጸሎቱንም በፈጸመ ጊዜ ራሱን ቆረጡት ምስክርነቱንም ፈጸመ ከሥጋውም ቁጥር የሌላቸው ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ እንጣዎስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
+ + +
❤ ቅዱስ ያዕቆብ፦ ይህም ቅዱስ ከደቡብ ግብጽ አቡስ ከሚባል አውራጃ መኑፍ ከሚባል ታናሽ መንደር ነው። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ክርስቲያኖች ነበሩ ከእርሱ መወለድም በፊት ሦስት ሴቶች ልጆችን ወልደው ነበር። ጥቂትም በአደጉ ጊዜ እንዲያስተምሩአቸውና በፈሪሀ እግዚአብሔር እንዲአሳድጓቸው በገዳም ለሚኖሩ ደናግል ሰጧቸው። የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍትንም ተማሩ።
❤ ወላጆቻቸውም ሊወስዷቸው በወደዱ ጊዜ እነርሱ ከደናግል ገዳም መውጣትን አልወደዱም። ነገር ግን ለድንግል ማርያምና ለልጅዋ ለክርስቶስ ሙሽሮች ይሆኑ ዘንድ መረጡ ወላጆቻቸውም ከእርሳቸው በመለየታቸው አዘኑ። መሐሪ ይቅር ባይ እግዚአብሔርም በዚህ ቅዱስ ያዕቆብ መወለድ አጽናናቸው። ሰባት ዓመትም በሆነው ጊዜ አባቱ ዐውሎ ወደ ሚባል አገር ጥበብን ይማር ዘንድ ላከው ትምህርትንም ተምሮ በትምህርት ሁሉ ፍጹም ሆነ።
❤ አባቱም ለገንዘቡና ለጥሪቱ ለእንስሶቹም ሁሉ ተቈጣጣሪ አደረገው በዚያም አንድ በሥውር ብዙ ትሩፋትን የሚሠራ የበጎች ጠባቂ ነበረ በክረምትም በበጋም ብዙ ጊዜ ወደ ውኃ ጒድጓድ እየወረደ መላዋን ሌሊት ሲጸልይ ያድር ነበር። ቅዱስ ያዕቆብም ሽማግሌው የበግ ጠባቂ በሚያደርገው አምሳል እያደረገ በዚህ ሥራ ብዙ ዘመን ኖረ።
❤ ከዚህም በኋላ ሰይጣን በክርስቲያን ወገኖች ላይ መከራን አስነሣ ብዙዎች ክርስቲያኖችም በሰማዕትነት ሞቱ። በዚያንም ጊዜ ቅዱስ ያዕቆብ በሰማዕትነት ይሞት ዘንድ ከዚያ ሽማግሌ ጋራ ተስማማ ቅዱስ ያዕቆብም ከሽማግሌው ጋራ ሒዶ ይመለስ ዘንድ አባቱን ፈቃድ ጠየቀ እርሱም "ሒድ" አለው።
❤ በሔዱም ጊዜ በላይኛው ግብጽ የንጉሥ ልጅ ቅዱስ ዮስጦስን መኰንኑ ሲአሠቃየው አገኙት ሽማግሌውም "ልጄ ሆይ ይህ የንጉሥ ልጅ መንግሥቱን ትቶ እውነተኛውን ንጉሥ ክርስቶስን እንደ ተከተለ ከሚስቱና ከልጆቹም እንደተለየ ተመልከት። እኛ ድኆች ስንሆን ለምን ችላ እንላለን ልጄ ሆይ እንግዲህ ተጽናና ከወላጆችህም በመለየትህ አትዘን" አለው።
❤ ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ ቀርበው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ የረከሱ አማልክቶቹንም ረገሙ ያን ጊዜም መኰንኑ አስቀድሞ ሽማግሌውን ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው ራሱንም በሰይፍ ፈጥኖ አስቆረጠው ምስክርነቱንም ፈጸመ።
❤ ቅዱስ ያዕቆብን ግን ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው ከገመድ በተሠራ ጅራፍ ገረፈው ድንጋይም በእሳት አግለው በሆዱ ላይ አኖሩ። ዐይኖቹንም አቅንቶ ክብር ይግባውና ወደ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ጸለየ "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከዚህ መከራ ርዳኝ አጽናኝም" ያን ጊዜም ያለ ምንም ጉዳት አስነሣው።
❤ ከዚህም በኋላ በማቅ ውስጥ አስጠቅልሎ በባሕር ውስጥ አስጣለው የእግዚአብሔርም መልአክ አውጥቶ ያለ ጉዳት በመኰንኑ ፊት አቆመው። መኰንኑንም አሳፈረው የረከሱ አማልክቶቹንም ረገመ።
❤ ከዚህም በኋላ ፈርማ ወደሚባል አገር ላከው በዚያም የፈርማ መኰንን ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው ምላሱን ቆረጠው፣ ዐይኖቹንና ቅንድቦቹንም አወጣ፣ በመንኰራኩርም ውሰጥ አኬዱት፣ በመጋዝም መገዙት፣ ሕዋሳቱ ሁሉም ተሠነጣጠቁ። ደሙም እንደ ውኃ ፈሰሰ የእግዚአብሔር መልአክ ሱርያል ወርዶ ቊስሎቹን አዳነለት።
