ሰዋስው ☘☘☘☘
Open in Telegram
በሰዋስወ ብርሀን ቅዱስ ዻውሎስ ገዳም እና ለተለያዩ ቤተክርስቲያን ለክብረ በአላት ማውጫ ። በተጨማሪም-ዋዜማ ሥርዓተ ማኅሌት - መዝሙራት ስንክሳር - የየእለቱን ምስባክ ቅኔያት ጥያቄዎች እንዲሁም የወቅታዊ ነገር መወያያ በተጨማሪም @eotcww ብለው ይቀላቀሉን ለወዳጅ ዘመድዎ share#Share#Share# ያድርጉ።
Show more1 161
Subscribers
No data24 hours
No data7 days
No data30 days
Posts Archive
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤
+ + +
❤ "ሰላም ለሰሎሞን ንጉሥ ምሉአ ጥበብ ከመ ማየ ተከዚ ዘሰፍሐ አዕፁቀ ጥበቢሁ እስከ ባሕር ወእስከ አፍላግ ሠርጸ ቃሉ፤ ዘሐለየ በእንተ መርዓዊ ወመርዓት ለመንፈሳዊ ስብሳበ ወለሰብአ ከብካብ፤ ለእለ የኀሥሥዋ ለጥበብ ውእቱ መክብብ"። ትርጉም፦ እንደ ተከዚ ውሃ ጥበብን የተመላ፤ የጥበቡ ቅርንጫፎች እስከ ባሕር ዳርቻ፤ የቃሉ ቡቃያም እስከ ወንዞች ድረስ ለሰፋ፤ ለመንፈሳዊ ጋብቻ ለሰዎችም ሰርግ አምሳል ሊኾን ስለ ሙሽራውና ሙሽሪት ያመሰገነ፤ ጥበብንም ለሚሽዋት (ለሚፈልጓት) መምህራቸው ለኾነ ለንጉሥ ሰሎሞን ሰላምታ ይገባል። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።
https://t.me/Eotcw
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤
❤ ሰኔ ፳፫ (23) ቀን።
❤ እንኳን ለኢትዮጵያዊው ጻድቅ ለታላቁ አባት አራዊትና እንስሳት እንደሰው በድምፅ ያነጋግሯቸውና ይታዘዙላቸው ለነበረው፤ ይጠብቋቸው የነበሩትን በጐችና ፍየሎችን በነብርና በተኩላ ያስጠብቁ ለነበሩት ለአቡነ ተጠምቀ መድኅን ለዕረፍታቸው በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
+ + +
❤ አቡነ ተጠምቀ መድኀን፦ በጐጃም ከሚታወቁ ታላላቅ ቅዱሳን ውስጥ እንዱና ዋነኛው ናቸው። እርሳቸውም እንደነ አቡነ አብራንዮስ ላሉ ቅዱሳን ገዳማቸውን እንዲመሠርቱ ያደረጉ ታላቅ አባት ናቸው" አቡነ አብራንዮስ በነፋስ ሠረገላ እየሔዱ ሲታዩ እንዲሁም ሌሎች ተኣምራትን ሲያደርጉ ይኽንንም ድንቅ ሥራቸውን ሰዎች ቢያውቁባቸው ውዳሴ ከንቱን ንቀው ወደ አቡነ ተጠምቀ መድኅን ዘንድ ሔደው በዚያ በታላቅ ተጋድሎ ከኖሩ በኋላ አቡነ ተጠምቀ መድኀን "በአንተ ምክንያት ብዙ ነፍሳት ይድናሉ ክፍልህ በዚያ ነው" በማለት ዛሬ ላይ ኤርትራ ውስጥ ወደሚገኘው ደብረ ጥሉል ልከዋቸዋል። እርሳቸውም ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል እየመሯቸው መጥተው አስደናቂውን እንዳ ኣቦና ደብረ ጥሉል ገዳምን መሥርተዋል።
❤ አቡነ ተጠምቀ መድኅን በጻድቁ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት የነበሩ ሲሆን የታላቁ የጉሐንቻ አንድነት ገዳም መሥራች ናቸው። በ17ኛው መ/ክ/ዘ የነበሩት አቡነ ተጠምቀ መድኅን በርካታ ገዳማትን መሥርተዋል። ከእነዚኸም ውስጥ፡- አውሽካን ኢየሱስ ገዳም፣ ካጋና ኤዎስጣቴዎስ ገዳም፣ ወገዳ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም እና ሌሎችንም በርካታ ገዳማትን ጻድቁ እንዳቋቋሙ ከጎሐንቻ ቅድስት ማርያም ገዳም የተገኘ ጽሑፍ ይገልጻል። እነዚኸም ገዳማት አሁን ላይ የት እንዳሉ ማወቅ አልተቻለም፣ ምናልባትም በእነ ግራኝ አህመድ የጠፉ ይሆናሉ።
❤ ሌላኛዋ በአቡነ ተጠምቀ መድኅን የተመሠረተችው ሐረጽ ማርያም ገዳም ናት። ይኸችም ገዳም የምትገኘው በአዊ ዞን ሀገረ ስብከት መተከል ውስጥ በጓንጓ ወረዳ ውስጥ ነው። ሌላው የጻድቁ ገዳም ቻግኒ የሚገኘው የስጋዲ ቅዱስ ሚካኤል አቡነ ተጠምቀ መድኅን አንድነት ገዳም ነው። ይኸም የጻድቁ ገዳም በርካታ መነኰሳት የሚገኙበት ታላቅ የአንድነት ገዳም ሲሆን በተለያዩ የልማት ሥራዎች ይታወቃል። አቡነ ተጠምቀ መድኀን አባታቸው ወልደ ክርስቶስ እናታቸው ወለተ ማርያም የተባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች ሲሆኑ ጻድቁ የተወለዱት ታኅሣሥ 2 ቀን ነው። በጥምቀት ሀብተ ውልድና የተቀበሉት ደግሞ ጌታችን በተጠመቀበት ዕለት ጥር 11 ቀን ስለሆነ "ተጠምቀ መድኅን" ተብለው መጠራታቸውም ከዚህ ከክርስትና ቀናቸው በመነሣት ነው።
❤ አቡነ ተጠምቀ መድኅን አስተዳደጋቸው እንደማንኛውም የገጠር ልጅ እረኛ ሆነው ያደጉት። እርሳቸው ግን ከልጅነታቸው ጀምረው መንፈሳዊ ትምህርት ለመማር ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሣ ያግዷቸው (ይጠብቋቸው) የነበሩትን በጐችና ፍየሎችን በነብርና በተኩላ አስጠብቀውና አደራ ሰጥተው ወደ አባቶች ዘንድ በመሔድ ከመነኰሳት እግር ሥር ተቀምጠው ዳዊት ደግመው ወንጌል ተምረው ማታ ይመለሳሉ። ተምረው ጨርሰው ሲመለሱም በጐቹና ፍየሎች ከነብርና ከተኩላ ከአራዊት ጋር ሲቦርቁ ያገኟቸዋል።
❤ አባታቸውም ሳያውቁባቸው ከእረኝነታቸው እንደተመለሱ ሆነው ማታ ወደቤታቸው ይመለሳሉ። ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አንድ ባሕታዊ አባታቸውን ወልደ ክርስቶስን አግኝቶ "ልጅህን ስጠኝ ላስተምረው" ሲላቸው አባታቸውም "በጎቹንና ፍየሎቹን ማን ይጠብቃቸዋል?" በማለት እምቢ አሉ። አባታቸውም ተጠምቀ መድኅንን ዳዊት አንግበው ስላዩዋቸው ይኸንን ሁኔታ ለማረጋገጥ ልጃቸው እያገዱ በእረኝነት ከሚውሉበት ቦታ ቢሔዱ በሚያስገርም ሁኔታ በጎቹና ፍየሎቹ ከነብርና ከተኩላ ጋር ሲጫወቱ ሲቦርቁ ተመለከቱ። ሲመሽም አውራዎቹ እንስሶቹን ሲሸኟቸው አዩ" ማታም ልጃቸውን ተጠምቀ መድኅንን "ልጄ የት ዋልህ?" ብለው ሲጠቋቸው "ከብት ሳግድ ዋልሁ" ሲሉ አባታቸውም "ልጄ ሆይ! ነገሩን ተረድቼዋለሁ፣ ከዛሬ ጀምሮ እረኛ አትሆንም፣ ከባሕታውያን ዘንድ ሔደህ ተማር" ብለው ወደ ገዳም ላኳቸው።
❤ ከዚህም በኋላ አቡነ ተጠምቀ መድኅን መንፈሳዊ ትምህርት እየተማሩ የአባቶችን መንገድ እየተከተሉ በተጋድሎ መኖር ጀመሩ። ገና ከሕፃንነታቸው ጀምረው ቁርስና ምሳቸውን ለነዳያን በመስጠት እርሳቸው ግን ሲጾሙ ውለው በቀን እንድ ጊዜ ብቻ ይቀምሱ ነበር። ተጋድሏቸውንም ለማጽናት ወደ ታላቋ መርጡል ማርያም በመሔድ በ23 ዓመታቸው አባ ዝክረ ማርያም በሚባለ አባት እጅ መነኰሱ። ከመነኰሱም በኋላ ከሚለብሱት የፍየል ቆዳ ሥር ሰውነታቸውን በሰንሰለት አሥረው ከመኖራቸውም በላይ ቅዳሜና እሑድ ከሚቀምሱት ዳቤ በቀር እህል አይቀምሱም ነበር። ስግደታቸውም በቀን አንድ ሺህ እንደነበር ገድላቸው ይናገራል።
❤ ጻድቁ ከተሰጣቸው ጸጋ የተነሣ አራዊትና እንስሳት እንደሰው በድምፅ ያነጋግሯቸውና ይታዘዙላቸው ነበር። እንደ ረድእ ሆኖ የሚታዘዛቸው ጸዋሬ መስቀል የሚባል አንድ አህያ ነበራቸው፤ እርሱም መልእክት በማድረስና በመቀበል አባታችንን ያገለግላቸው ነበር፣ አምጣ ያሉትን ያመጣል፣ ውሰድ ያሉትን ይወስዳል። እርሳቸውም ከጐጃም እስከ ሱዳን ጠረፍ ድረስ ወንጌልን ሰብከው በርካታ ከሃዲያንን አስተምረው በማጥመቅ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከጌታችን ቃልኪዳን ተቀብለው በጻድቁ ዮሐንስ ዘመን በ1670 ዓም በክብር ዐርፈዋል።
❤ አቡነ ተጠምቀ መድኀን ያረፉት ሰኔ 23 ሲሆን በዓለ ዕረፍታቸው ዐፅማቸው በክብር ተቀምጦ ባለበት በጋሾላ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድነት ገዳም ውስጥ በታላቅ ድምቀት ይከበራል። ያረፉትም ለአገልግሎት ወደ ጋሾላ ቅዱስ ጊዮርጊስ የእናቶች ገዳም በሔዱበት ወቅት ስለነበር ዛሬም የከበረ ዐፅማቸውም በዚያው ይገኛል። ከአቡነ ተጠምቀ መድኅን እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን፣ በጸሎታቸው ይማረን። ምንጭ፦ በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን መጽሐፍ።
https://t.me/Eotcw
1 161
❤ በአለፉም ጊዜ የደናግል ገዳማት ካሉበት ደረሱ ደናግሎም ወጥተው ተቀበሏቸው ቊጥራቸው ሰባት መቶ ነበር ከእነርሱ ጋራም እስከሚሰበሰቡ በቅዱሳን ፊት ይዘምሩ ነበር። ወደ ንጉሡ ከተማም በደረሱ ጊዜ ወደ ንጉሡ ከመግባታቸው በፊት በውኃ ያጥቧቸውና አዳዲስ ልብሶችን ያለብሷቸው ጀመሩ እንዲሁም ለሁሉ አደረጉ ቅዱስ አባ ኖብ ግን አልታጠበም ልብሱንም አልለወጠም።
❤ ወደ ንጉሡም በገቡ ጊዜ ከእነርሱ ቡራኬ ተቀበለ ቁስላቸውንም ሳመ እጅግም አከበራቸው ብዙ ገንዘብም ሰጣቸው እነርሱ ግን ለቤተ ክርስቲያን ከሚሆን ንዋየ ቅዱሳት በቀር ምንም ምን አልተቀበሉም ከዚህም በኋላ ሰላምታ ሰጥቶ ወደየአገራቸው በሰላም አሰናበታቸው። አባ ኖብም ወደ ቦታው ተመልሶ ዐረፈና ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔደ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ኖብ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ 23 ስንክሳር ።
+ + +
❤ የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ "እግዚኦ ኵነኔከ ሀቦ ለንጉሥ። ወጽድቀከኒ ለወልደ ንጉሥ። ከመ ይኰንኖሙ ለሕዝብከ በጽድቅ"። መዝ 71፥1-2። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 12፥38-42።
+ + +
❤ የዕለቱ የቅዳሴ ምስባክ፦ "በጽሑ መላእክት ወቦሙ መዘምራን። ማዕከለ ደናግል ዘባጥያተ ከበሮ። በማኅበር ባርክዎ ለእግዚአብሔር"። መዝ 67፥25-26። የሚነበበው መልዕክታት ሮሜ 13፥1-11፣ 1ኛ ጴጥ 2፥13-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 7፥44-54። የሚነበበው ወንጌል ማቴ11፥12-30 ወይም ማቴ12፥38-43። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች ማርያም ወይም የወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።
https://t.me/Eotcw
1 161
አገኘሁ በነጋም ጊዜ አየሁት እነሆ የወለድሁት ልጄ አይደለም" አለች።
❤ ያቺ ሁለተኛዋ ሴትም "አይደለም ይህ ደኅነኛው የኔ ልጅ ነው እንጂ ያንቺ ልጅ አይደለም ያንቺስ የሞተው ነው" አለች። በንጉሡም ፊት እንዲህ ተባባሉ። ንጉሡም "ሰይፍን አምጡ ደኅኛውንም ልጅ ከሁለት ቆርጣችሁ እኵሌታውን ለዚች እኵሌታውን ለዚያች ስጡ" አለ። ስለ ልጅዋ ማሕፀኗ ታውኳልና ልጅዋ ደኅና የሆነ ያቺ ሴት መልሳ ንጉሡን "ጌታዬ አይደለም መግደልስ አትግደሉት ደኅነኛውን ልጅ ለሷ ሰጧት" አለችው ያቺ ሴት ግን "አካፍሉን እንጂ ለእኔም ለእርሷም አይሁን" አለች። ንጉሡም መግደልስ አትግደሉት እሱን ለእሷ ስጧት ላለችው ለዚች ሴት ደኅነኛውን ሕፃን ስጧት እርስዋ እናቱ ናትና" አለ። እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ የፈረደውን ይህን ፍርድ ሰምተው ቅን ፍርድን ይፈርድ ዘንድ የእግዚአብሔር ጥበቡ በሱ ላይ እንዳለ አይተዋልና በንጉሡ ፊት ፈሩ።
❤ ከዚህም በኋላ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ከወጡ አራት መቶ ሰማንያ አራት ዘመን በሆነ ጊዜ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሊያንፅ ጀመረ። በዐሥራ አንደኛውም ዘመነ መንግሥቱ ወሩ ባዕድ በሚባል በስምንተኛው ወር ቤቱንና ሥርዓቱን ሁሉ ፈጸመ በሰባት ዓመትም ውስጥ ሠራው የራሱንም ቤት በዐሥራ ሦስት ዓመት ሠርቶ ጨረሰ።
❤ ከዚህ በኋላ ሰሎሞን የእግዚአብሔር ቤትና የራሱን ቤት በሃያ ዘመን ሠርቶ በጨረሰ ጊዜ የእግዚአብሔርን ታቦተ ሕግ ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ያመጣቴ ዘንድ ያን ጊዜ የእስራኤልን ሽማግሌዎችና የነገድ አለቆች የአባቶቻቸውንም ቤት አለቆች ሁሉ በኢየሩሳሌም በሰበባቸው። የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን በሰባተኛው ወር በጥቅምት ተሰበሰቡ። የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ ካህናቱም ታቦትዋንና የምስክሩን ድንኳን በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ያለ ንዋየ ቅዱሳቱንም ሁሉ ተሸከመ። ንጉሡና እስራኤል ሁሉ በታቦትዋ ፊት ሥፍር ቊጥር የልላቸው በጎችና ላሞችን ይሠዉ ነበር። ካህናቱም ታቦቷን ከኪሩቤል ክንፎች በታች በቤቱ ውስጥ ወዳለው ወደ ቅድስት ቅዱሳን ቦታዋ አገቧት። ኪሩቤል በታቦትዋ ቦታ ላይ ክንፋቸውን ጋርደዋልና ኪሩቤልም በስተላይ በኩል በቅድስተ ቅዱሳን ላይ ታቦትዋን ጋርደዋት ነበር። ከቅድስተ ቅዱሳንም ጋራ የተያያዙ ነበር። ቅዱሳን ኪሩቤል ከፍ ብለው ከቅድስተ ቅዱሳኑ አንጻር ላይ ሁነው ያያሉ በውጭ ግን አይታይም ነበር። ከግብጽ አገር በወጡ ጊዜ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ጋራ ቃል ኪዳን ከገባባቸው ሙሴም በዚያ በኮሬብ ከአኖራቸው ከሁለቱ ጽላቶች በቀር በታቦቱ ውስጥ ሌላ አልነበረም።
❤ ከዚህ በኋላ ካህናቱ ከቤተ መቅደስ በወጡ ጊዜ ቤተ መቅደሱን ሁሉ ብርሃን መላው። የእግዚአብሔር ብርሃን በማደሪያው ቤተ መቅደስ መልቷልና ከብርሃኑ መገለጥ የተነሣ ካህናቱ ሥራቸውን መሥራትና ከፊቱ መቆም ተሳናቸው። ያን ጊዜ ሰሎሞን "እግዚአብሔር በደመና ውስጥ እኖራለሁ ብሏል"። "እኔም ለዘላለም የምትኖርበት ማደሪያ ቤተ መቅደስን በእውነት ሠራሁልህ" አለ።
❤ ንጉሡም በፊቱን መልሶ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቃቸው ወደ እግዚአብሔርም ረዥም ጸሎትን ጸለየ። ሰሎሞንም ይህን ሁሉ ልመና ወደ እግዚአብሔር ለምኖ በጨረሰ ጊዜ በጉልበቱ ተንበርክኮ ከሰገደበት እጆቹንም ከዘረጋበት ከመሠዊያው ፊት ተነሣ። ቆሞም "የእስራኤልን ማኅበር እንደተናገረው ሁሉ ለወገኖቹ ለእስራኤል ዕረፍትን የሰጣቸው እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን" ብሎ በታላቅ ቃል መረቃቸው።
❤ ከዚህ በኋላ ንጉሡና የእስራኤል ልጆች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕትን ሠዉ። ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ስለ ሰላም መሥዋዕት የሠዋቸው ሃያ ሁለት ሽህ ላሞችና አንድ መቶ ሃያ ሽህ በጎች ናቸው ንጉሡ ሰሎሞንና እስራኤል ልጆች ሁሉ ያንጊዜ ለእግዚአብሔር ማደሪያ ለቤተ መቅደስ ቅዳሴ ቤት አደረጉ።
❤ ቀድሞ በገባዖን እንደታየው ዳግመኛ እግዚአብሔር ለሰሎሞን ታየው "በፊቴ የለመንኸኝ ልመናህንና ጸሎትህን ሰማሁ። እንደ ልመናህም ሁሉ አደረግሁልህ ስሜ በዚያ ለዘላለሙ ጸንቶ ይኖር ዘንድ የሠራኸውንም ቤተ መቅደስ አከበርሁት ልቡናዬም ዓይኖቼን በመኑ ሁሉ በዚያ ጸንተው ይኖራሉ" አለው።
❤ ሰሎሞንም አርባ ዘመን ነገሠ ከመንገሡም በፊት ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ መላ ዕድሜውም ሃምሳ ሁለት ዓመት ነበር በሰላም ዐረፈ። ይህም ጥበብ የተሰጠው ንጉሥ ሰሎሞን ጥቅም ያላቸው ብዙዎች መጻሕፍትን ደርሶአል። እሊህም ትንቢትና ትምህርት ያለባቸው ምሳሌዎችንና መኃልዮች ናቸው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
+ + +
❤ አባ ኖብ፦ ይህም ቅዱስ መነኰስ በላይኛው ግብጽ ከሚገኙ ገዳማት በአንዱ ገዳም ውስጥ የሚጋደል ጽሙድ ነበር። ዲዮቅልጥያኖስም ብዙዎች ሰማዕታትን ሊአሠቃይና ደማቸውን ሊያፈስስ በጀመረ ጊዜ በአንዲት ቀን ሰማንያ ሰማዕታትን አቅርቦ ደማቸውን አፈፈሰሰ።
❤ በዚያን ጊዜ አባ ኖብን አስታወሱት የእንዴናው ገዥ ወደሆነው ወደ አርያኖስ አቀረቡት። እርሱም "ለአማልክት ዕጠን ሠዋ ይህንንም የምንኵስና ልብስ ከላይህ አውጥተህ ጣል" አለው። አባ ኖብም "ይህ ሥራ ከቶ ከእኔ ዘንድ አይደረግም የክብር ባለቤት ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስንም አልተውም የረከሱ ጣዖታትንም አላመልክም" አለ። መኰንኑም በየራሱ በሆነ ሥቃይ እጅግ አሠቃየው ያም አባ ኖብ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ኃይል ታግሦ ተቀበለ።
❤ ከዚህም በኋላ ወደ አምስቱ አህጉር ሰደደው በዚያም በጒድጒድ ውስጥ ጣሉት በውስጡም ጌታችን ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ አጥፍቶ ደግ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስን እስከሾመው ድረስ ሰባት ዓመት ኖረ።
❤ ቈስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ የታሠሩትን ሁሉ ፈትተው ወደርሱ እንዲአበርቧቸው ከእርሳቸው እንዲባረክ ወደ አገሮች ሁሉ ደብዳቤዎችን ላከ። ለመልእተኞችም እንዲህ አላቸው "ሁሉንም ወደእኔ ማድረስ ካልተቻላችሁ እጆቻቸውን በራሴ ላይ ጭነው ይባርኩኝ ዘንድ ክብር ያላቸውን ታላላቆችንና መምህራኑን አምጡአቸው"። ከእነርሱም ውስጥ የታወቁ አህናህ ከተባለ አገር አባ ዘካርያስ ከፍዩም መክሲሞስ ከአገረ ድኂን አጋብዮስ ከአገረ በላኦስ አባ ኖብ ናቸው የንጉሥ መልእክተኞችም በየአገሮች ሁሉ እየዞሩ የታሠሩ ቅዱሳንን ከእሥር ያወጡአቸው ነበር እነርሱም ደስ ይላቸው ነበር የተመሰገነ እግዚአብሔርንም ያመሰግኑት ነበር ይዘምሩለትም ነበር።
❤ የንጉሥ መልእክተኛም አባ ኖብን ከአምስቱ አገሮች ፈልጎ የአገሩ አንጻር ወደ ሆነች ወደ አገር በሰላ ወሰደው። በዚያም የብረት ልብስ ለብሶ ተቀምጦ ነበር የንጉሡ መልእክተኛም አገኘውና ከእርሱ ጋራ ወሰደው ወደ እንዴናውም እስከ ደረሱ በመርከብ ተሳፈሩ ክርስቲያኖችም ተሰበሰቡ ከውጣቸውም አራት ኤጲስቆጶሳት ነበሩ አባ ኖብንም ያለ ውዴታው ቅስና ሾሙትና የቊርባን ቅዳሴን ቀደሰ። በቅዳሴውም ፍጻሜ "ቅዱሳት ለቅዱሳን" ብሎ ጮኸ ይህም ማለት ንጹሕና ቅዱስ የሆነ ሥጋው ከደሙ ይቀበል ማለት ነው በዚያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በመሠዊያው ላይ ተቀምጦ ንስሐ የገቡትን ኃጢአታቸውን ይቅ ሲላቸው አየው ሥጋውንና ደሙንም ከአስቀበላቸው በኋላ ወደ ንጉሡ ለመሔድ ተዘጋጁ ቊጥራቸውም ሰባ ሁለት ነበር ሠላሳ ሰባት ሠረገላም አዘጋጅተውላቸው እየአንዳንዳቸው በሠረገላው ተቀምጡ።
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤
❤ ሰኔ ፳፫ (23) ቀን።
❤ እንኳን ለንጉሥ ለቅዱስ ዳዊት ልጅ ለጥበበኛው ንጉሥ ለቅዱስ ሰሎሞን ለዕረፍቱ መታሰቢያ ቀን በዓል፣ በክብር ባለቤት በኢሱስ ክርስቶስ ለታመነ ለአባ ኖብ ለዕረፍት መታሰቢያ በዓልና ለሊቀ ሰማዕታት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለወራዊ በዓል መታሰቢያ በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከቅዱሳን ሰማዕታት ከመርቆሬዎስ፣ ከቶማስና ፊልጶስ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከት ያሳትፈን።
+ + +
❤ የልበ አምላክ የቅዱስ ዳዊት ልጅ ንጉሥ ሰሎሞን፦ የዚህ የሰሎሞንም እናት ስም ቤርሳቤህ ነው ዳዊትም ሕግ ተላልፎ ከእርሷ ጋራ ስለ መበደሉ ባሏንም ስለ ማስገደሉ ጌታ በገሠጸው ጊዜ ንስሓ ገብቶ መሪር ልቅሶን አለቀሰ ጌታም ንጹሕ ስለሆነ ንስሓው ይቅር አለው። ከዚህም በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ እርሷን አገባትና ሰሎሞንን ወለደው ንጉሥ ዳዊትም ከእርሱ በኋላ ልጅዋ ሰሎሞን እንዲነግሥና በዙፋኑ ላይ እንዲቀመጥ ቃል ገባለት።
❤ እንዲህም ሆነ ሰሎሞን ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ አዶንያስ እነግሣለሁ ብሎ ተነሣ ምክሩም ሁሉ ከሶርህያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ አብያታር ጋር ሆነ። እርሱም አዶንያስን ተከትለው ሰደዱት። አዶንያስም በሮጌል ምድር ምንጭ አጠገብ ባለ በኤልቲ ዘዘኤልቲ ላይ ፍየሎችን በጎችንና ላሞችን አርዶ የንጉሥ አሽከሮች የሆኑ የይሁዳ አርበኞችን ሁሉና የንጉሡን ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ ጠራ።
❤ ከዚህም በኋላ አዶንያስ ይህን እንዳደረገ ለቤርሳቤህ በነገሩዋት ጊዜ ወደ ንጉሥ አዳራሽ ውስጥ ገብታ ለንጉሡ ሰገደች ንጉሥ ዳዊትም "ምን ሆነሽ" አላት። "ጌታዬ ንጉሥ ሆይ ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል በዙፋኔም ላይ ይቀመጣል ብለህ ለእኔ ለባርያህ በፈጣሪህ በእግዚአብሔር ስም አንተ ማልክልኝ እነሆ ዛሬ አዶንያስ ነገሠ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ አንተ ግን አላወቅህም" አለችው። ከንጉሥም ጋራ ገና ስትነጋገር ነቢዩ ናታን መጣ ለንጉሡም "ናታን መጣ" ብለው ነገሩት። ወደ ንጉሡም ገባ በምድር ላይም በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደ። ነቢዩ ናታንም "ከእኔ ቀጥሎ አዶንያስ ይንገሥ በዙፋኔም ላይ ይቀመጥ ያልክ አንተ ነህን ዛሬ ወርዶ በጎችንና ብዙ ፍየሎችን አርዶ የሠራዊቱ አለቆችንና የንጉሥ አሽከሮችን ሁሉ ካህኑ አብያታርንም ጠርቷልና በፊቱም ይበላሉ ይጠጣሉ አንዶንያስ ሽህ ዓመት ያንግሥህ ይሉታል" አለው።
❤ ዳዊትም መልሶ "ቤርሳቤህን ጥርዋት" አለና ጠሩዋት ገብታም በንጉሡ ፊት ቆመች። "በእግዚአብሔር ፊት እንደማልኩልሽ አሁንም በዚች ቀን እንደዚሁ እንዳደርግ ሰውነቴን ከመከራዬ ሁሉ ያዳናት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሕያው ነው" ብሎ ማለ። በቤርሳቤህም አንገቷን ደፍታ በግምባርዋ በመሬት ወድቃ ለንጉሡ ሰገደች "ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም ኑር" አለች።
❤ ንጉሥ ዳዊትም "የዮዳሄ ልጅ ብንያስና ካህኑ ሳዶቅን ነቢዩ ናታንንም ግራዝማቹንና ቀኝ አዝማቹን ጥሩልኝ" አለ። ንጉሡም ከእናንተ ጋራ የጌታችሁ አሽከሮችን ይዛችሁ ልጄ ሰሎሞንን በበቅሎዬ ላይ አስቀምጣችሁ ወደ ግዮን አውርዱት"። በዚያም ነቢዩ ናታንና ካህኑ ሳዶቅ "ቀብታችሁ በእስራኤል ላይ አንግሡት" አላቸው። ቀንደ መለከት ንፉ "ሰሎሞን ሺህ ዓመት ያንግሥህ በሉ። ተከትላችሁም ውጡ ገብቶም በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ እርሱም ስለ እኔ ፈንታ ይንገሥ በሁሉቱ ነገድና በዐሥሩ ነገድ ይነግሥ ዘንድ እኔ አዝዣለሁ"።
❤ ካህኑ ሳዶቅም ከድንኳን ቀርነ ቅብዑን ወስዶ ሰሎሞንን ቀባው ቀንደ መለከትንም ነፉ ሕዝቡም ሁሉ ተከትለውት ወጡ ከበሮም መቱ ታላቅ ደስታም አደረጉ ከድምፃቸውም የተነሣ ምድሪቱ ተናወጸች።
❤ ሰሎሞንም በመንግሥት ዙፋኑ ተቀመጠ። የንጉሡም አሽከሮች ጌታቸው ንጉሡ ዳዊትን ሊአመሰግኑ ገቡ። "እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ይልቅ መልካም ያደርገው ዙፋኑንም ከዙፋንህ ይልቅ የበለጠ ያድርገው" አሉት። ንጉሡም በዐልጋው ሁኖ ሰገደ። እንዲህም አለ "ዐይኖቼ ሲያዩ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጥ ልጅን ለኔ ለባሪያው ዛሬ የሰጠ የእስራኤል ፈጣሪ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን" አለ።
❤ ዳዊትም የሚሞትበት ወራት በደረሰ ጊዜ ልጁ ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው። "እኔ ሰው ሁሉ በሚሔድበት በሞት ጎዳና እሔዳለሁ አንተ ግን ጽና ብልህ ሰውም ሁን። በሕጉ ጸንተህ ትኖር ዘንድ የፈጣሪህ የእግዚአብሔርን ትእዛዝን ጠብቅ እኔ እንዳዘዝሁህ እንዴት እንደምታደርግ ታውቅ ዘንድ በመሴ ሕግ የተጻፈውን ትእዛዙንና ሕጉን ፍርዱንም ጠብቅ ልጆችህ ሕጌን ቢጠብቁ በፊቴም በፍጹም ልቡናቸው በፍጹም ሰውነታቸው በዕውነት ጸንተው ቢኖሩ ከእስራኤል ዙፋን ላይ ሰው አይጠፋብህም ብሎ እግዚአብሔር ለእኔ የነገረኝ ቃሉን ያጸና ዘንድ ጠብቅ" ብሎ አዘዘው። ዳግመኛም ከኢዮአብና በሳሚ ወልደ ጌራ ላይ በቀል እንዲአደርግ አዘዘው እነርሱ እጅግ የከፋና ብዙ ክፋት የሠሩ ነበሩና።
❤ ከዳዊት ዕረፍትም በኋላ ሰሎሞን ከዚያ መሥዋዕትን ይሠዋ ዘንድ ተነሥቶ ወደ ገባዖን ሔደ ገባዖን ፈጽማ ትሰፋ ነበርና ሰሎሞንም በገባዖን በዚያው መሠዊያ ውስጥ ሽህ መሥዋዕትን ሠዋ።
❤ እግዚአብሔርም ለሰሎሞን በሌሊት በሕልም ተገለጠለት "ለአንተ እሰጥህ ዘንድ በልብህ ያሰበውን ልመናን ለምን" አለው። ሰሎሞንም "በቅንነትና በእውነት በንጹሕ ልቡናም ከአንተ ጋራ በፊትህ ጸንቶ እንደኖረ ከአባቴ ከዳዊት ጋራ ታላቅ ቸርነትን አድርገሃል በዚችም ቀን ልጁን በዙፋኑ ላይ ታስቀምጠው ዘንድ ይህን ታላቁን ቸርነት አጽንተህለታል" አለው። "አሁንም አቤቱ አንተ ፈጣሪዬ ስለ አባቴ ስለ ዳዊት ፈንታ እኔን ባሪያህን አነገሥኸኝ እኔም መግቢያዬንና መውጫዬን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ። እኔ ባሪያህ ግን የማይቈጠር ብዙ ሕዝብ በሆነ በመረጥከው ወገንህ መፍረድ የሚችል የለምና ሰምቶ ለወገኖችህ በእውነት ፍርድን ይፈርድ ዘንድ ከክፉ ነገርም ለይቶ በጎውን ነገር ያውቅ ዘንድ ለባሪያህ ዕውቀትን ስጠው"። ሰሎሞን ይህንን ነገር ለምኖታልና ይህ ነገር እግዚአብሔርን በፊቱ ደስ አሰኘው።
❤ እግዚአብሔርም "ይህንን ነገር ከእኔ ለምነሃልና ለአንተም ብዙ ዘመንንና ባለጸግነትን አለመንህምና ጠላቶችህንም አጥፋልኝ ብለህ አልለመንህምና ነገር ግን ፍርድ መስማትን ታውቅ ዘንድ ለምነሃልና እነሆ እንዳልህ አደረግሁልህ። እነሆ ከአንተ አስቀድሞ እንዳልነበረ ከአንተም በኋላ እንዳንተ ያለ እንዳይነሣ አድርጌ ብልህና አስዋይ ልቡናን ሰጠሁህ። ሰው በመንግሥቱ እንዳንተ እንዳልሆነ አድርጌ ያልለመንኽኝን ባለጠግነትንና ክብርንም በዘመንህ ሁሉ እሰጥሃለሁ" አለው። ሰሎሞንም ከእንቅልፋ በነቃ ጊዜ እውነተኛ ሕልም እንደ ሆነ ዐወቀ ተነሥቶም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደ በጽዮንም በእግዚአብሔር ታቦት ሕግ አንጻር ባለ በመሠዊያው ፊት ቆሞ የሰላም መሥዋዕትን አቀበረ ለሰዎቹና ለሱም ታላቅ ግብዣ አደረገ።
❤ በዚያን ጊዜም ሁለት አመንዝራ ሴቶች ወደ ንጉሡ መጥተው በፊቱ ቆሙ አንዲቱም ሴት "ጌታዬ ስማኝ እኔና ይህች ሴት በአንድ ቤት እንኖራለን በአንድ ቦታም ወለድን እኔ በወለድሁ በሦስተኛው ቀን ይህች ሴት ወለደች በአንድነትም እንኖራለን በዚያም ቤት ከሁለታችን በቀር ከኛ ጋራ ማንም አልነበረም። በላዩ ላይ ተጭናዋለችና የዚያች ሴት ልጅ በሌሊት ሞተ። በሌሊት እኩሌታም ተነሥታ ተኝቼ ሳለሁ ልጄን ከአጠገቤ ወስዳ በብብቷ አስተኛችው። የሞተውን ልጅዋንም በአጠገቤ አስተኛችው። ልጄን አጠባ ዘንድ በጧት በነቃሁ ጊዜም ያንን የሞተ ልጅ
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤
❤ እንኳን በታላቁ ገዳም በዋልድባ (ዋሊ) ገዳም ብቻ ለሚደረገው ሱባዔ (ህርመት) አደረሳችሁ ፥ አደረሰን።
+ + +
❤ ከሰኔ 21- ኅዳር 24፤ 4ት ሱባኤ (4x40 = 160 ቀናት) በኢትዮጵያ በብቸኝነት ጌታችን በመሠረተው በዚህ ታላቅ ገዳም በዋልድባ ብቻ ከሚደረጉ ሥርዐቶች መካከል አንዱና ከቀድሞ አባቶች ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣው መካከል፤ ከሰኔ ፳፩ እስከ ኅዳር ፳፬ ድረስ የወጣ ሳይገባ፥ የገባ ሳይወጣ (መርፌም ቢኾን ከሱባዔው በፊት ወደ ገዳሙ ካልገባ ሱባዔው እስኪያልቅ ጥቅም ላይ ሳይውል) ለ 160 ቀናት የሚደረግ ሱባዔ ነው፡፡
❤ የ160 ቀናት ሱባዔ (4ት ሱባኤ (4x40/)፤
ከሰኔ 16-21 በዋልድባ ገዳም ያሉ ምዕመናን ከገዳሙ ይወጣሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ ከገዳሙ ለተለያዩ ጉዳዮች ወጥተው የነበሩ አባቶች ወደ በዓታቸው ይሰባሰባሉ፤
❤ ከሰኔ 21- ነሐሴ 16 በበዓታቸው ሆነው ሱባኤውን ይጀምራሉ፤ ከነሐሴ 16 ጀምሮ አብዛኞቹ በዓታቸውን ለቅቀው በገዳሙ ውስጥ በሚገኙ ዋሻዎች፣ ፍርክታዎች፣ ገደላ ገደሎች፣ …. መንነው ሱባኤውን ይይዛሉ፡፡ እጅግ በጣም አስቸኳይ ጉዳይ ያጋጠማቸውና ለተልእኮ የሚፈለጉ አባቶችና አርድዕት አመ ሰዱሱ ለመስከረም (መስከረም 6፤ የአቡነ ሳሙኤል በዓለ ፍልሰት ላይ) አባቶች ፈቅደውና ጸሎት አድርገውላቸው መውጣት ይችላሉ፤
❤ ከ140 ቀናት በኋላ ከኅዳር ፮ - ፰ በዋልድባ አብረንታንትና በሥሩ ያሉ በሱባኤ የቆዩ አባቶች በማኅበር ደረጃ ወደ ማይለበጣ ይሰበሰባሉ፤ በኅዳር ፱ ተዝካረ አበው ይደረጋል፤ ተዝካረ አበው የሚደረገው በማይ ለበጣ ብቻ ነው፤ ግድፍት ምግብም እስከ ገና ጾም መግቢያ ኅዳር 14 ድረስ ይበላል፡፡ መልሰው ከኅዳር ፱ ጀምረው ደግሞ እስከ ኅዳር ፳፬ ወደ ሱባዔ ገብተው በ፳ወ፬ቱ ካህናተ ሰማይ ትልቁ ሱባዔ ያበቃል፤ ነገር ግን እህል መቅመስ የማይፈልጉ አባቶች ወደ ማይለበጣ ሳየመጡ ሱባኤያቸውን ኅዳር ፳፬ ይጨርሳሉ፤ የፈለገ በኅዳር 24 ወደ ማይለበጣ መጥቶ እህል ብቻ ይቀምሳል፤ ያልፈለገ ግን ከሱባዔ ወደ ሱባዔ በመሸጋገር አያይዞ የገናን ጾም እስከ ገና ጾሞ፤ የገና ወደ ማይለበጣ መጥቶ ይገድፋሉ፡፡
ከኅዳር ፳፬ ጀምሮ ወደ ገዳም መግባት መውጣት ይፈቀዳል፨
❤ በእነዚህ 160 የሱባኤ ቀናት (ከሰኔ ፳፩ - ኅዳር ፳፬ ድረስ)፤ ማንኛውንም ነገር ወደ ገዳሙ የሚገቡ የቤተ ክርስቲያን መገለገያዎችም ጭምር አገልግሎት ላይ አይውሉም፤ በዕቃ ቤት እስከ ኅዳር 6 ይከርማሉ፤
በእነዚህ 160 ቀናት ከቀባሪ በስተቀር ወደ ገዳሙ ምዕመናን መግባትም አይችሉም፨
❤ የአበው ጸሎት ምሕረት ያውርድ፤
የአበው እንባ የነደደውን እሳት ያብርድ፤
የአበው አምላክ ኢትዮጵያን ይጠብቅ፡፡
❤ ከአርጋብ ጸዓድዒድ ቅዱሳን አበው አንድነት፥ ከአቡነ ሳሙኤል ረድኤት፥ ከሥላሴ ልጅነት፥ ከገዳመ ዋሊ በረከት ይክፈለን፥ ከቅድስቲቷ እምነት አያናውጸን። ምንጭ፦ አርከ ሥሉስ ፌስቡክ ገጽ የተወሰደ።
https://t.me/Eotcw
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤
❤ ሰኔ ፳፪ 22 ቀን።
❤ እንኳን ለመነኰሳት መጀመሪያቸው ለሆነ ለከበረ አባ እንጦንስ ረድእ ለነበረው ለየዋህ ለቅዱስ ጳውሎስና ለሊቀ መላእክት ለቅዱስ ዑራኤል ለወራዊ መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከከበሩ ቅዱሳን ከቆዝሞስና ከድምያኖስ ከእናታቸውና ከወንድሞቻቸው ከበዓላቸው መታሰቢያና ቤተ ክርስቲያናቸውም ከከበረችበት ተአምራታቸውም ከተገለጠበት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
+ + +
❤ የከበረ የአባ እንጦስ ረድእ የዋህ ቅዱስ ጳውሎስ፦ ይህም ጳውሎስ በረኸኛና እጅግ የዋህ ነበር ደም ግቧቷ ውብ ሥራዋ ግን ክፉ የሆነ ሚስት አገባ ከእርሱም ልጆችን ወለደች። በአንዲትም ቀን ከእርሻው በተመለሰ ጊዜ ከሎሌው ጋራ ስታመነዝር አገኛት በአያቸውም ጊዜ ሣቀ ያንን ሎሌውንም እንዲህ አለው "ከልጆቿ ከቤቷና ከንብረቷ ጋራ ውሰዳት እኔ ምንም አላዝንም እግዚአብሔርም ወደ ፈቀደልኝ እሔዳለሁ" አለው።
❤ ከዚህም በኋላ ወጥቶ ወደ አባ እንጦንስ ሒዶ የምንኵስና ልብስ ለበሰ የአባ እንጦንስንም ሥራ ተከተለ። በደዌያትና በሰይጣናት ላይ ጸጋና ኃይል እስከተሰጠው ድረስ በጾምና በጸሎት ተጋደለ።
❤ በአንዲት ዕለትም ጋኔን የያዘውን ሰው ያድነው ዘንድ ወደ አባ እንጦንስ አመጡ። አባ እንጦንስም ይፈውሰው ዘንድ ረድኡ ጳውሊን አዘዘው ጳውሊም ጋኔናሙን ሰው ወስዶ "አባቴ እንጦንስ ውጣ ይልሃል" አለው ሰይጣኑ ግን መውጣትን እምቢ አለ። እርሱንም እንጦንስንም ተሳደበ። ጳውሊም "ካልወጣህስ ለእንጦስ እነግረዋለሁ እንደሚቀጣህም ታያለህ" አለ። ይህንንም ብሎ በቀትር ጊዜ ወጥቶ ፀሐይ በአጋለው ደንጊያ ላይ ቁሞ "ይህ ጋኔን ያደረበት ሰው እስኪድን ድረስ ከዚህ አለት እንዳልወርድ እንዳልበላና እንዳልጠጣ ሕያው እግዚአብሔር" አለ። በዚያንም ጊዜ ጋኔኑ ጮኸ በታላቅ ዘንዶ አምሳልም ከሰውዬው ላይ ወጥቶ በኤርትራ ባሕር ውስጥ ገባ።
❤ ይህም የዋህ ጳውሊ የሰዎችን ሥራ ሁሉ እያየ ስለ ኃጥአን ያለቅስ ነበር ስለ እነርሱም ይማልድ ነበር። በመልካም እርጅናም ሰኔ 22 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ የዋህ በቅዱስ ጳውሎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ 22 ስንክሳር።
+ + +
❤ "ሰላም ዕብል ለጳውሎስ ሊሉይ። እምነ ብእሲት ዘማ ሠናይተ ላህይ። ቀዊሞ ወዓለ እንበለ ናህይ። በመልዕልተ ኰኵሕ እንተ አርሰኖ ፀሐይ። እስከ እምጋኔን ሐይወ ብእሲ ድውይ"። አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሰኔ 22።
+ + +
❤ የዕለቱ ምስባክ፦ "ወኢትቅናእ ላዕለ ዘይዴሎ በሕይወቱ። ወላዕለ ሰብእ ዘይገብር ዐመፃ። ኅድጋ ለመዓት ወግድፋ ለቊጥዓ"። መዝ 36፥7-8። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 5፥6-ፍ.ም፣ ያዕ 5፥14-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 13፥44-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥39-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ባስልዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።
https://t.me/Eotcw
