en
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

Open in Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

Show more
609
Subscribers
-124 hours
-37 days
-1130 days
Posts Archive
❤ ቅድስት እናታችን ጸበለ ማርያም ከነቢያት፣ ከሐዋርያትና ከሰማዕታት ዕድል የተሰጣት እናት ናት፡፡ እንደነቢያት የሚመጣውን ሁሉ እንዳለፈ አድርጋ ትናገራለች፡፡ ዳግመኛም የትምህርታቸውን ፍለጋ ስለተከተለችና ለሕጋቸው ስለተገዛች ከሐዋርያት ጋር ዕድል ተሰጣት፡፡ ሦስተኛ ግድ ሳይሏት በፈቃዷ ስለተቀበለቻቸው ግርፋቶቿና ስላገኛት መከራ የሰማዕታት ዕድል ተሰጣት፡፡ ከደናግል መነኰሳትም ዕድል ተሰጣት መነኵሲትም ድንግልም ናትና፡፡ ቅድስት እናታችን ጸበለ ማርያም መልካም የሆነውን ተጋድሎዋን ከፈጸመችና ጌታችን ታላቅ ቃልኪዳን ከገባላት በኋላ በሰላም ዐርፋለች፡፡ እንደ ንግሥት ዕሌኒም የሞቷን መስቀል ተሸክማ ተጠብቆላት ወዳለ ተስፋዋ በክብር ሄደች፡፡ ዕረፍቷ መስከረም 18 ነው፡፡ ጥር 18 የልደቷ ዓመታዊ በዓሏ ነው። ገዳሟ የሚገኘው ጃማ ወረዳ ልዩ ስሙ አህያ ፈጅ ከሚባለው አካባቢ ነው። ከእናታችን ቅድስት እናታችን ጸበለ ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን፣ በጸሎቷ ይማረን!። ምንጭ፦ ገድለ ቅድስት ጸበለ ማርያም፣ ደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት የንህበት ቅድስት ጸበለ ማርያም ቤ/ክ ያሳተመው።

❤ ቅድስት ጸበለ ማርያም ለአቅመ ሔዋን ስትደርስ ወላጆቿ በጋብቻ ሕግ እንድትወሰን ፈለጉ፡፡ ነገር ግን ቅድስት ጸበለ ማርያም "ቅዱስ ጳውሎስ ለእግዚአብሔር አጭቶኛልና ፈጣሪዬን በድንግልና ለማገልገል ተስያለሁ" በማለት ተቃወመቻቸው፡፡ ወደ አንድ ደገኛ ባሕታዊም ዘንድ ሄዳ በጸሎቱ ከዚህ ነገር እንዲያድናት ተማጸነችው፡፡ እርሱም ፈቃደ እግዚአብሔርን በጸሎት ከጠየቀላት በኋላ ማድረግ የሚገባትንና ወደፊት የሚገጥማትን ሁሉ ነገራት፡፡ እርሷም ለዕጣን እንዲሆን ጌጧን ሁሉ አውጥታ ሸጠችና "መሥዋዕቴን አሳርግልኝ" ብላ ለባሕታዊው ሰጠችው፡፡ እርሱም ከጸለየላት በኋላ የጸሎቱን ምላሽ ነገራት፡፡ ❤ ወላጆቿም ያለፈቃዷ በሕግ ቢያጋቧትም ቅድስት ጸበለ ማርያም ግን በሌሊት ማንም ሳያያት ከጫጉላ ቤት ወጥታ ሄዳ በልዳው ፀሐይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ወደተሠራች ቤተ ክርስቲያን ሔዳ እያለቀሰች ጸሎት አደረገች፡፡ እመቤታችንም ከቅዱሳን ሚካኤል ወገብርኤል እንዲሁም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተገለጠችላትና እንዲጠብቋት ነገረቻቸው፡፡ ቤተሰቦቿም እንዳያዝኑባት ፈርታ ተመልሳ ወደ ባሏ ዘንድ ብትገባም ባሏ በግብር እንዳያውቃት መላእክቱ ይጠብቋት ነበር፡፡ ባሏንም ሰውነቷ እንደእሳት ያቃጥለው ነበር፡፡ እርሱም አእምሮውን ከሳተ ከ3 ቀን በኋላ ሲነቃ የደረሰበትን ለቤተዘመዶቹ ባስረዳቸው ጊዜ "ከገዳም የመጣች ከሆነች ለእኛ ልትሆን አይገባም" አሉና አስጊጠውና ሸልመው መልሰው ወደ ቤተሰቦቿ ላኳት፡፡ አባቷም ዳግመኛ ወደባሏ እንድትመለስ በማስገደድ ብዙ አሰቃቂ ግርፋት ቢገርፋትም በተአምራት ምንም እንዳላገኛት ሆነች፡፡ ❤ ከዚኽም በኋላ ወጥታ ወደ ምድረ በዳ ሄደች፡፡ ወደ ገዳምም ሄዳ ዋሻ ውስጥ ገብታ ስትጸልይ አድራ አረፍ ስትል ነብር መጥቶ የእግሯን ትቢያ ይልሳት ነበር፡፡ ከዚያም ወጥታ ንህበት ወደሚባል ሀገር መጥታ ቶማስ ከሚባል መነኵሴ ጋር በታላቅ ተጋድሎ ኖረች፡፡ ቆማ ስትጸልይ እንባዋ መሬቱን ያርስ ነበር ነገር ግን ሰው እንዳያውቅባት አፈር በላዩ ትጨምርበታለች፡፡ በአንድ ዕለትም በቤተ ክርስቲያን ቆማ ስትጸልይ በሁለቱ ማዕዘን የተቀበሩ ምውታን ሲጮኹ ሰማቻቸው፣ እነርሱ ግን በሲኦል ነበሩ፡፡ ጩኸታቸውንም በሰማች ጊዜ በእንባዋ ላይ እንባን በጸሎቷም ላይ ጸሎትን ጨምራ ስለእነርሱ ለመነች፡፡ ስለእነርሱም ሱባኤ ያዘች፡፡ በባሕርይው ቸርና ይቅርባይ የሆነ ልዑል እግዚአብሔርም ጸሎቷን ሰምቶ እነዚያን ነፍሳት ማረላት፡፡ ❤ ቅድስት ጸበለ ማርያም በምግባርና በትሩፋት በጾም በጸሎት ጸንታ ከኖረች በኋላ የምንኩስና ቀንበርን ትሸከም (በመንናኔ ትኖር) ዘንድ በብሕትውና ወደሚኖረው ታላቁ አባት ወደ አቡነ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ ዘንድ ሄደች፡፡ እርሱም ማኅሌተ ጽጌን ከአባ ጽጌ ድንግል ጋር የደረሰው ነው፡፡ ✝ አቡነ ገብረ ማርያምም ካስተማራትና በኋላ አመነኰሳትና ስሟን "ጸበለ ማርያም" ብሎ ሰየማት፡፡ ከዚኽም በኋላ ተጋድሎዋን እጅግ በማብዛት ትኅርምትን ገንዘብ አደረገች፡፡ ከዕንጨት ፍሬዎች ውጭ የማትመገብ ሆነች፡፡ በተቀደሰችው የጌታችን 40 ጾም ወራት ግን ከሰንበት በቀር እርሱንም ፈጽሞ አትቀምስም፣ እስከ ፋሲካም ድረስ ከበዓቷ ስለማትወጣ ማንም አያያትም ነበር፡፡ ❤ ከመነኰሰችም ጊዜ ጀምሮ በጎኗ ተኝታ አታውቅም፡፡ ባመማት ጊዜም ተቀምጣ ታንቀላፋ ነበር፡፡ በውርጭ ቅዝቃዜ መከራን እየተቀበለች በባሕር ውስጥም ቆማ እየጸለየች ታድራለች፡፡ በስግደቷም በቀን እስከ 8 እልፍ ትሰግድ ነበር፡፡ ከወንድሟ ቶማስም የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ተማረች፡፡ የዮሐንስን ወንጌልና የራእዩን መጽሐፍ ዘወትር በማንበብ ትጸልያለች፡፡ የእመቤታችን በዓል በሆነ ጊዜ አርጋኖን ውዳሴዋን በቀን ሦስት ጊዜ ታነባለች፣ አንቀጸ ብርሃንንም በየሰባቱ ጊዜ ትጸልያለች፡፡ የዳዊትንም መዝሙር በፈጸመች ጊዜ የጌታችንን መከራ ግርፋት እያሰበች ራሷን ሺህ ጊዜ ትገርፋለች፡፡ ዳግመኛም አገዛዛቸው መልካም ይሆን ዘንድ ስለ ጳጳሱና ስለ ንጉሡ አንድ አንድ ሺህ ጊዜ፣ ስለ መነኰሳትም ሺህ ጊዜ፣ ስለኃጥአንም ሺህ ጊዜ ራሷን ትገርፋለች፡፡ ዳግመኛም ነጭ ዕጣን በእጇ ይዛ ሰባት ቀን እስኪሆን ድረስ ዕንባዋን ታፈስበታለች፣ ያም ነጭ ዕጣን ከዕንባዋ ብዛት የተነሣ ጥቁር ይሆናል፡፡ በዓል በሚሆንበት በሰባተኛው ቀን አስቀድማ ዐውቃ በመሠዊያ ያሳርገው ዘንድ ያን ዕጣን ለቄሱ ትሰጠዋለች፡፡ እግዚአብሔርም እንደሱራፌል የጽናሕ መዐዛና እንደኪሩቤል ዕጣን ሽታ አድርጎ ከቄሱ እጅ ሲቀበል በግልጽ ታያለች፡፡ ❤ ቅድስት እናታችን እሾህ ያለው የብረት ዛንዠር በወገቧ ትታጠቃለች፡፡ በወገቧና በጭኖቿ ያሰረችው ርጥብ የላም ቁርበት ከአጥንቶቿ ጋር ይጣበቃል፡፡ በደረቀም ጊዜ ሥጋዋ እየተቆራረጠ ይወድቃል፣ በምድርም ውስጥ ትቀብረዋለች፡፡ አምስት ጊዜም እንደዚህ እያደረገች ራሷን ጎዳች፣ ከዳነም መልሳ ታቆስለዋለች፡፡ በዚህም ጊዜ ጌታችን ተገለጠላትና "ወዳጄ ጸበለ ማርያም ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን" አላት፡፡ ዳግመኛም "በእንዲህ ያለ የቁስል መከራ መሠቃየት ይበቃሻል" ካላት በኋላ ተሰወረ፡፡ እርሷ ግን ሰባት ጊዜ እስኪሆናት ድረስ ይህንን አደረገች፡፡ በዚህም ጊዜ ሥጋዋ እጅግ ታመመ፡፡ ሥጋዋ እንደ ድንጋይ ደርቆ ቢቀር የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ እንደተላለፈች ዐውቃ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ተወች፡፡ ❤ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ቅድስት ጸበለ ማርያም እየጸለየች ሳለ የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቆሰለ ችግረኛ ደሃ ሰው ተመስሎ ለቅድስት ጸበለ ማርያም ተገልጦ ወደ እርሷ በመምጣት ቁራሽ እንጀራ ለመናት፡፡ እርሷም ፈጥና ይዛ መጥታ ሰጠችው። እንጀራውንም ተቀብሎ ሲያበቃ "በመንገድ ብዛት ደክሜአለሁና በጀርባሽ አዝለሽ ትሸኚኝ ዘንድ እወዳለሁ" አላት፡፡ እርሷም ለድሆች አዛኝ ናትና አዝላው የድንጋይ መወርወሪያ ያህል እንደወሰደችው ቁስሉ ይድን ጀመር፡፡ ወዲያውም ቁስሉ ድኖ ምንም እንዳላገኘው ፍጹም ደህነኛ ሰው ሆነ፡፡ ያንጊዜም ፊቱ እንደፀሐይ አበራ፣ ሁለንተናውም ተለወጠ፡፡ የክብር ባለቤት ጌታችን ከጀርባዋ ወርዶ በፊት ለፊቷ ቆመና "የከበርሽ አገልጋዬ ጸበለ ማርያም ሆይ! ምን እንዳድርግልሽ ትወጃለሽ?" አላት፡፡ እርሷም ከድንጋጤዋ የተነሣ እንደበድን ሆና መሬት ላይ ወደቀች፡፡ ጌታችንም አበረታትና እጇን ይዞ አነሣትና "የልብሽን መሻት ለምኚኝ" አላት፡፡ እርሷም "አምላኬ ሆይ ! በፊትህስ ሞገስ ካገኘሁ በሲኦል ያሉ ነፍሳትን ይቅር በላቸው" አለችው፡፡ በዚኽም ምክንያት በጌታችን ቸርነትና በእርሷም አማላጅነት ብዙ ነፍሳት ከሲኦል ወጡ፡፡ ጌታችንም ሰላምታ ሰጥቷት በክብር ዐረገ፡፡ ❤ ዳግመኛም ጌታችን ለቅድስት ጸበለ ማርያም ሦስት በትሮችን ሰጥቷት በእነርሱ እየተመረኮዘች እስከሲኦል ድረስ ትሄድና ነፍሳትን ታወጣና ታስምር እንደነበር ራሷ ተናገረች፡፡ ዳግመኛም ስትናገር "ሰማያውያን ብዙ ስሞች አወጡልኝ፣ "የወይን ፍሬ" እያሉ ይጠሩኛል፣ "የበረከት ፍሬ" የሚሉኝም አሉ፣ "የገነት ፍሬም" ይሉኛል" አለች፡፡ ዳግመኛም ከልዑል ዘንድ ብዙ ጸጋዎች እንደተሰጣት በሕይወት ሳለች ለአንደ ደገኛ ቄስ ነገረችው፡፡ ❤ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አምላክን በድንግልና የወለደች ክብርት እመቤታችን ለቅድስት ጸበለ ማርያም ተገለጠችላትና "ስሜን የተሸከምሽ ጸበለ ማርያም ሆይ! ሰላም ለአንቺ ይሁን" አለቻት፡፡ እመቤታችንም ብዙ ምሥጢርን ከነገረቻት በኋላ ጡቶቿንም አጠባቻትና በጸጋ የከበረች አደረገቻት፡፡ በስሟም ብዙ ተአምራትን የምታደርግ ሆነች፡፡

ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta): ❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤              ❤ #ጥር ፲፰ (18) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊቷ_ጻድቅ ጌታችን በደሃ ሰው ተመስሎ ተገልጦ ቁራሽ እንጀራ ለለመናትን በኋላም በጀርባዋ አዝላ ለሸኘችው፤ በጎኗ ተኝታ ለማታውቅ፤ በጌታችን 40 ጾም ወራት ከሰንበት በቀር ምንም የማትቀምስ፤ ነብሮች የእግሯን ትቢያ ይልሱላት ለነበረች #ለታላቋ_እናትን_ለቅድስት_ጸበለ_ማርያም ለልደቷ በዓል፣ #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ ኤርትራ ጠረፍ መረብ ወንዝ አካባቢ የሚገኘው ሩሑብ ገዳም ለተመሠረተ #ከአቡነ_ሐራ_ድንግል ጋር ተመሳሳይ ታሪክ ላላቸው ፣ ልክ እንደ አቡነ ሐራ ድንግል በቃላቸው ገዝተው ነብርንና ሚዳቋን ላስማሙ ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ለአቡነ_ቴዎድሮስ_ዘአዳይቦ ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ቴዎድሮስ_ዘአዳይቦ፦ አባታቸው ፈያት ገብረ ክርስቶስ እናታቸው መክብበ ድንግል ይባላሉ። ነገር ግን አቡነ ቴዎድሮስን ወላጆቻቸው በሕገ እግዚአብሔር በሥርዓተ ጋብቻ ጸንተው ኖረው የወለዷቸው አይደሉም። ❤ መክበብ ድንግል ዕንጨት እየለቀመች ሳለ ፈያት ገብረ ክርስቶስ በዚያ ሲያልፍ አግኝቷት በግብር አወቋትና ፀነሰች። ሰሎሜ የምትባለው ደገኛ ሴትም ይኽንን በመንፈስ ቅዱስ መነጽርነት አይታ መክብበ ድንግል እንደፀነሰች ተመለከተች በወቅቱ የነበሩትና ታሪካቸውን ቀደም ብለን ያየናቸው ታላላቆቹ ቅዱሳን አቡነ አዎስጣቴዎስና ልጃቸው አቡነ አብሳዲም ይኽን የመክበብ ድንግልን መደፈርና መፀነስ ዐውቀው አቡነ አምስጣቴዎስ "አረከሳት" ሲል አቡነ አብሳዲ ደግሞ "ቀደሳት ቀደሳት እንጂ አላረከሳትም"... በማለት ከመክብበ ድንግል የሚወለዱት ጻድቁ አቡነ ቴዎድሮስ መሆናቸውን ተናገሩ። መክብበ ድንግልም የብርሃን ዓምድ አዝላ ታየቻቸው። ❤ ከዚኽም በኋላ አቡነ ቴዎድሮስ በኤርትራ ልዩ ስሙ ዓዲ ተምሾ በሚባል ቦታ ተወለዱ። እርሳቸውም የእናታቸውን የመክብበ ድንግል ጡት ሳይጠቡ አደጉ ነገር ግን እንደ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሚዳቋ እያጠባቻቸው እንዳደጉ ገድላቸው ይናግራል። ✝ አባታችንም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተምረው ካደጉ በኋላ በቅዱስ ወንጌል "ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?" ማቴ 19፡26 ማር 8፡36። ተብሎ የተጻፈውን የወንጌል ቃል አስበው የነፍሳቸውን ድኅነት በመሻት መንነው ከሰው ተነጥለው ወደሚኖሩበት በረሓ ገቡ። በዚያም ከዓለም ተለይተው በታላቅ ተጋድሎ ኖረው የምንኵስናን ሥራ ሁሉ ፈጽሙ በአቡነ አብሳዲ እጅ መነኰሱ። አቡነ ቴዎድሮስ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጥናት ምሥጢራትን ካወቁና በአቡነ አብሳዲ እጅ ከመነኰሱ በኋላ በጽኑ ተጋድሎ ኖረዋል። ❤ ከዚኸም በኋላ አቡነ ቴዎድሮስ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እያደጉ ሔደው ከብቃት ደረጃ ላይ ሲደርሱ አቡነ አብሳዲ የአቡነ ቴዎድሮስን ማረፊያ በመንፈስ ቅዱስ ተረድተው "አንተ በመንፈስ አባቴ ነህ አሁን ግን እግዚአብሔር ካዘጋጀልህ የተጋድሎ ቦታህና ማረፊያ ወደሆነችው ርሒብ ሒድ" አሏቸው። ይኸችም ርሑም የተባለች የአቡነ ቴዎድሮስ ገዳም ዙሪያዋ እሳት መሀሏ ገነት የሆነች ለምለም ቦታ ናት አባታችንም ወደዚህች በአታቸው ሔደው እንዲያገለግሉ አቡነ አብሳዲ ላኳቸው፡ ❤ ቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስም የአቡነ አብሳዲን ቃል ተቀብለው ወደ ተነገራቸው ቦታ ርሑብ) ሔደው በዚያም በታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ መኖር ጀመሩ። ርሑ ማለት ሰፊ ቦታ እንደማለት ነው። ገዳማቸውንም ገድመው በርካታ መናንያንን አፍርተዋል። እርሳቸውም በተሰጣቸው መንፈሳዊ ጸጋ ለገዳሙ መነኰሳት መቊነን ያመጡ የነበረው ከሩቅ ቦታ በደመና ተጭነው እየተመላለሱ ነበር፣ በወቅቱ የነበሩ መነኰሳትም ይህን አይተው እጅግ ይገረሙና ለቅዱሳን ጸጋ የሚስጠውን ልዑል እግዚአብሔርን ያመሰግኑ እንደነበር ገድላቸው ይናገራል፡፡ ❤ ከዚኽም በኋላ ቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ በመንፈሳዊ ተጋድሏችው ጸንተው እስከ መጨረሻ ድረስ እግዚአብሔርን አገልግለው የዕረፍታቸው ጊዜ ሲደርስ ጌታችን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ተገለጠላቸውና ከዚህ ዓለም ድካም ወደ ዘለዓለማዊ ዕረፍት ሊወስዳቸው እንደመጣ ነገሯቸው ታላቅ ቃልኪዳን ገባላቸው። የተጋድሏቸውን ዋጋ አስቦ በቸርነቱ "ስለ ፍጹም ድንግልናህ ዓለምንና በውስጧ ያለውን ነገር ስለናቅህ ስለ ምንኵስናህ" በማለት አክሊላትን አቀዳጃቸው ዳግመኛም ገዳማቸውን የተሳለመ እና የገዳማቸው ጽላሎት ያረፈበትን እስከ 12 ትውልድ ድረስ እንደሚምርላቸው ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል። ❤ የቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስን ገድላቸውን በእምነት የሰማ፣ የተሳለመ እንዲሁም መጽሐፈ ገድላቸውን አዝሎ የተማጸነ ሁሉ ልጅ እንደሚያገኝ የታወቀ ነው አሁንም ድረስ በርካታ መውለድ ያልቻሉ እናቶች ገድላቸውን እያዘሉ ልጅ ይወልዳሉ። እንዲሁም ገዳሙ ውስጥ በምትገኘውና የጻድቁ የእጃቸው ምርኩዝ በነበረችው በመቋሚያቸው እጣቢ እጅግ በርካታ ምእመናን ከተለያዩ ደዌያትና ሕማማት ተፈውሰዋል። ከመካነ መቃብራቸውም ላይ የፈለቀው ጠበል እጅግ ፈዋሽ ነው። ገዳማቸው የሚገኘው ኤርትራ ጠረፍ መረብ ወንዝ አካባቢ ሲሆን ከኣዲ ነብሪ ኢድ ወደ ዓዲ ክልተ በመኪና ከተጓዙ በኋላ ከዚያ የአራት ሰዓት የእግር መንገድ ርቀት ላይ ነው። ❤ በቱርኮችና በዐረቦች ታግዞ የእነርሱንም ሠራዊት አስከትሎ 15 ዓመት ሙሉ የሀገራችንን ሊቃውንት ሲያሳርድ ገዳማትን ሲያቃጥል የኖረው የሰይጣን መልእክተኛ ግራኝ አህመድ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ሔዶ በወርቅ በዕንቍ ተጊጠው የተሠሩ እጅግ በርካታ ገዳማትንና አብያተ ክርስቲያናትን ሲያቃጥል በተለየ ተኣምር ግን ሊያቃጥላቸው ካልቻላቸው ገዳማት ውስጥ አንዱ ይኸ የአቡነ ቴዎድሮስ ገዳም ነው። ግራኝም ማቀጣጠያ እየጨመረ እሳቱን ለኮሶ ገዳሙን ለማቃጠል ብዙ ቢደክምም ይኽንን ገዳም ግን ለማቃጠል አልችል ብሎ ትቶት እንደሔደ ገድላቸው ይናገራል። ❤ የአቡነ ቴዎድሮስ በዓለ ዕረፍታቸው ጥር 18 ሲሆን መስከረም 18 ቀንም ከአባታችን ኤዎስጣቴዎስ በዓል ጋር ክብረ በዓላቸው በገዳሙ በድምቀት ይከበራል። ከዕለታትም በአንደኛው ቀን በገዳማቸው ውስጥ የጻድቁን በዓል ለማክበር ከተሰበሰቡት አገልጋዮች ውስጥ አንድ መነኵሴ ደክሟቸው በቅዳሴ ሰዓት ተኝተው ሳለ ጻድቁ አቡነ ቴዎድሮስ በአካል ተገልጠው በመቋሚያቸው ቀስቅስው"አንተ ደካማ ክብረ በዓሌ በሚከበርበት ቀን ለምን ትተኛለህ ?"ብለው ከዕንቅልፋቸው እንደ ቀስቀሷቸው የገዳሞ አባቶች ይናገራሉ ። ከአቡነ ቴዎድሮስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን። ምንጭ በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን መጽሐፍ የተወስደ።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅድስት_ጸበለ_ማርያም፦ ትውልዷ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ቀሐ አካባቢ ነው፡፡ ወላጆቿ አባቷ እንድርያስና እናቷ መስቀል ክብራ ፈሪሃ እግዚአብሔርንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እያስተማሩ በሃይማኖት በምግባር ኮትኮተው አሳደጓት፡፡ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ተከስተ ብርሃን የተባለ ደገኛ ባሕታዊ ወደ አባቷ ቤት መጥቶ ባደረበት መንፈስ ቅዱስ ኀይል የቅድስት ጸበለ ማርያምን ጸጋ አወቀ፡፡ ለወላጆቿም "ይኽቺ ልጅ ወደፊት ነፍሳት የሚድኑባት የከበረች ትሆናለች" ብሎ በእርሷ ላይ ትንቢት ተናገረ፡፡

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ  አሜን"። ❤           ❤ #ጥር  ፲፰ (18) ቀን። ❤ እንኳን #ለፀሓየ_ልዳ_ለኮከበ_ፋርስ ለሰማዕታት አለቃ #ለቅዱስ_ጊዮርጊስ (ለዝርወተ ዐፅሙ) ዐፅሙ ተቃጠጥሎ ተደቁሶ በይድራስ ተራራ በነፋስ ከተበተነ በኋላ ከሞት ለተነሳበት ዓመታዊ መታሰቢያ በዓልና በገድል ለተጸመደ ለከበረ አባት #ለቅዱስ_ኤፍሬም_ሶርያዊ_መምህሩ ቁጥሩ ከሠለስቱ ምዕት ለሆነ ለአገረ ንጺቢን ኤጲስቆጶስ #ለአባ_ያዕቆብ_ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚህ ቀን ከሚታሰቡ፦ ከአራት ቀኖች በኋላ ጌታች ከመቃብር ያነሳ  #ከአልዓዛር_እኅቶች_ከቅድስት_ማርያምና #ከቅድስት_ማርታ_ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                       ✝ ✝ ✝ ❤ #የቅዱስ_ጊዮርጊስ_ዝርወተ_አፅሙ፦ በዚች ቀን ሰባ ነገሥታት ማሰቃየት በሰለቻቸው ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ መጭመቂያ ሆኖ ከተሠራ የስቃይ መሣሪያ ላይ አውጥተው ሰውነቱን እንዲሰነጥቁት ንጉሥ ዱድያኖስ አዘዘ፡፡ አንጀቱ ሁሉ ወጥቶ ከምድር ላይ እስኪዘረግፉት ድረስ እንዲህ አደረጉበት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከስቃይ ብዛት የተነሳ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች ሥጋውንም በሙሉ በእሳት አቃጠሉት አመድም ሆነ፡፡ ❤ ከሐዲው ንጉሥ ዱዲያኖስ የተቃጠለውን የሥጋውን አመድ አፍሰው በቀፎ አድርገው ይድራስ ወደሚባል ተራራ ወስደው ምዕመናን ራሩን አመዱን እንኳን እንዳያገኙት በነፋስ እንዲዘሩት አዘዘ፡፡ ደብረ ይድራስ ማለት ምድረ በዳ ማለት ነው፡፡ ወታደሮቹም የሥጋውን አመድ በተራራ ላይ ነስንሰው የተመለሱበት፣ የሥጋው አመድ ያረፈበት ዕፅዋት ሁሉ ጊዮርጊስ ጊዮርጊስ ያሉበት፣ ጌታችን ከመላእክት ጋር ተገልጦ አራቱን የምድር ነፋሳትንም የቅዱስ ጊዮርጊስ የሥጋውን ትቢያ እንዲሰበስብ አዞ። "የኔ ሆይ! የመረጥኩህ ወዳጄ ጊዮርጊስ ከሞት ተነሥ አትፍራ፤ እኔ አዝዤሀለሁና" ሲል ኀያሉን ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ጠራው። ያን ጊዜ ልዑል ንዑድ ጊዮርጊስም ከጫጉላ ቤት እንደሚወጣ ሙሽራ ምንም ሕማም ሳይኖርበት ተነሣ። ❤ መድኃኒታችንም ባረከው። "አትፍራ፤ ይኸንን ከሀዲ ንጉሥም እስክታሳፍረው ድረስ እኔ አጸናሀለሁ። ከእንዲህስ ወዲህ አምላኩ ከእጃችን ሊያአድነው አይችሉም እንዳይሉ እነዚህን ከሐድያን ነገሥታትና የረከሱ ጣዖታቸውን ታሳፍራቸው ዘንድ ተነሣና ወደ አገር ውጣ፤ ሰላሜ ለዘለዓለም ከአንተ ጋር ይሁን" አለው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ተናግሮ ሳመው። በፍጹም ምስጋናም ወደ ሰማይ ዐረገ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጌታች ይህንንም ቃል ኪዳን የተቀበለበት ቀን ነው፡፡ ምንጭ፦ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ።                                                     ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ያዕቆብ_ዘንጽቢን፦ ይህም ቅዱስ ተወልዶ ያደገው በንጽቢን ከተማ ነው እርሱ ግን ሶርያዊ ነው ከታናሽነቱም የምንኵስና ልብስ መልበስን መረጠ ከጠጕር የተሠራ ማቅንም ለበሰ በጾም በጸሎት ተወስኖ በቀን በሌሊት በበጋ በሐሩር በክረምት ቊር የሚጋደል ሆነ ያንንም ማቅ ከቶ ከሥጋው ላይ አያወጣውም ነበር ምግቡም ቅጠላቅጠል ነው የሚጠጣውም የዝናብ ውኃ ብቻ ነው ስለዚህ ሥጋው ብሩህ ሆነ ነፍሱም እጅግ በራች። ❤ እግዚአብሔርም ሀብተ ትንቢት ድንቆች ተአምራቶችንም የመሥራት ጸጋን ሰጠው ለሰዎችም ከመሆኑ በፊት የሚሆነውን ይነግራቸውና እንዲሁም ይሆናል። ተአምራቱም እጅግ ብዙ ነው በአንዲትም ቀን ሴቶች በውኃ ምንጭ ላይ ያለማፈር ሲጫወቱና ሲሣለቁ አያቸው የውኃውንም ምንጭ አደረቀ የራሳቸውንም ጠጒር ነጭ ሽበትን አደረገ በተጸጸቱና የውኃውን ምንጭ እንዲመልስላቸው እየሰገዱ በለመኑት ጊዜ የውኃቸውን ምንጭ መለሰላቸው እንዳይታበዩም ይገሠጹ ዘንድ የራሳቸውን ጠጒር ነጭ እንደሆነ ተወው። ❤ በአንዲት ዕለትም በጐዳና አልፎ ሲሔድ አንዱን ሰው አስተኝተው ሰዎችን አገኛቸው መገነዣ ልብስም ይሰጣቸው ዘንድ ቅዱሱን ለመኑት እርሱ ግን በጸሎቱ ሰውዬውን ምውት አደረገው ሰዎችም ወደርሱ በተሰበሰቡ ጊዜ ሙቶ አገኙት ተጸጽተውም ሁለተኛ ያድንላቸው ዘንድ ለመኑት አዳነላቸውም። ትሩፋቱና ደግነቱም በተሰማ ጊዜ መርጠው በአገረ ንጽቢን ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾሙት የክብር ባለቤት የክርስቶስን መንጋዎች ከአርዮሳውያ ተኵላዎች በበጎ አጠባበቅ ጠበቀ። ❤ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስም የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱን የከበሩ አባቶች በኒቅያ ከተማ በሰበሰባቸው ጊዜ ይህ አባት አብሮ አለ ከእርሳቸውም ጋር አርዮስን አውግዞ ከክርስቲያን አንድነት ለየው የቤተ ክርስቲያንንም ሥርዓትና በሁሉ ምእመናን ዘንድ የታወቀች የሃይማኖት ጸሎትን ሠራ። ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በደረሰ ጊዜ የሞተውን ሰው በጉባኤው ውስጥ አስነሥቷል። ❤ የፋርስ ንጉሥም መጥቶ አገረ ንጽቢንን በከበባት ጊዜ ይህ ቅዱስ ያዕቆብ የጭጋግ ደመና በሠራዊቱ ላይ አመጣ ትንኞችም ፈረሶቻቸውንና ጐበዛዝቶችን ነደፏቸው ፈረሶችም ማሠሪያቸውን ቆርጠው ፈረጠጡ የፋርስ ንጉሥም አይቶ ታላቅ ፍርሀትን ፈራ ተነሥቶም ሽሽቶ ወደኋላው ተመለሰ። ነፍሱን የመንጋዎቹንም ነፍስ ጽድልት ብርህት አድርጎ ገድሉንም በፈጸመ ጊዜ ጥር18 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ያዕቆብ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጥር 18 ስንክሳር።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "እስመ ኀልቀ ከመ ጢስ መዋዕልየ። ወነቅጻ(ጸ) ከመ ሣዕር አዕፅምትየ። ተቀሠፍኩ ወየብሰ ከመ ሣዕር ልብየ"። መዝ 101፥3-4። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 11፥19-33።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወእምኵሉ ያድኅኖሙ እግዚአብሔር። እግዚአብሔር የዐቅዐብ ኵሎ አዕፅምቲሆሙ። ወኢይትቀጠቀጥ አሐዱ እምውስቴቶሙ"። መዝ 33፥19-20። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 8፥35-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 3፥1-7 እና የሐዋ ሥራ 17፥30-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥42-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ወይም የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ጊዮርጊስ ዝርወተ ዐፅም በዓል፣ የቅዱስ ባኮስ (አቤላክ) የስዋሬ በዓል፣ የቅድስት ጸበለ ማርያም የልደት በዓልና የአቡነ ቴዎድሮስ ዘአዳይቦ የዕረፍት ። ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ ከዚህም በኋላ ከማምጠቂያው ውስጥ ጨምረው መገዙአቸውና አመድ እስከሆኑ ከቅባትና ከጨው ጋር በብረት ምጣድ ውስጥ ቆሉአቸው ጌታችንም አስነሥቶ አዳናቸው። ወደ መኰንኑም በገቡ ጊዜ እንዲህ አላቸው "በእውነት ከሙታን ተለይታችሁ የተነሣችሁ ከሆነ ይህ ጫማዬ በእግሬ ወጥቶ እንደ ቀድሞው ሕያው እንዲሆን አድርጉ ሕፃን ቂርቆስም በጸለየ ጊዜ ያ ጫማ ታላቅ በሬ ሆነ ከአንገቱም ፍየል ወጣ። በዚያንም ሰዓት ለዐሥራ አንድ ሽህ አራት ሰዎች በሬውንና ፍየሉን አርደው ምሳ እንዲአደርጉላቸው መኰንኑ አዘዘ እንዲህም አለ ይህ "በቅቷቸው ከጠገቡ ከዚህም ሌላ ምግብ ካልፈለጉ የተሠራው ሁሉ ዕውነተኛ ነዋሪ ነው"። ❤ ከዚህም በኋላ አርደው ምሳ አደረጉላቸውና ከፍየሉ ሥጋ ስድስት እንቅብ ከበሬው ሥጋ አራት እንቅብ አተረፉ መኰንኑም የተረፈውን ሥጋ አይቶ ወደ ባሕር እንዲጥሉት አዘዘ። መኰንኑም ቢያፍር የሕፃኑን ምላስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ጌታችንም ምላሱን መለሰለት ዳግመኛም በታላቅ ጋን ውኃ አፍልተው ሕፃን ቂርቆስንና እናቱን ኢየሉጣን ይጨምሩአቸው ዘንድ አዘዘ እናቱም አይታ ፈራች። ልጅዋም ወደ እግዚአብሔር በጸለየላት ጊዜ አምላካዊ ኃይልን አሳደረባትና ከልጅዋ ጋር ወደ ጋኑ ገባች። እንደ ውርጭም ቀዝቃዛ ሆነ ደግሞም በውስጡ መንኲራኵር ወዳለበት የብረት ምጣድ እንዲጨምሩአቸውና ሥጋቸው እስከሚቦጫጨቅ እንዲስቡአቸው አዘዘ የእግዚአብሔርም መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም በሕይወት አወጣቸው። ❤ መኰንኑም እነርሱን ማሸነፍ በተሳነው ጊዜ ቸብቸቧቸውን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ በዚያን ጊዜ ለስም አጠራሩ ስግደት የሚገባው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወረደ ሕፃን ቅዱስ ቂርቆስንም "የምትሻውን ለምነኝ" አለው። ሕፃኑም "ሥጋዬ በምድር አይቀበር ስሜን ለሚጠራ መታሰቢያዬን ለሚያደርግ ቤተ ክርስቲያኔን ለሚሠራ የተጋድሎዬን መጽሐፍ ለሚጽፍና ለሚያጽፍ ወይም ለሚያነበው ለቤተ ክርስቲያኔ መባ ለሚያገባ በውስጧም ለሚጸልይ ለሁሉም ፍላጎታቸውን ስጣቸው ኃጢአታቸውንም ይቅር በል ስሜም በሚጠራበት በዚያች ቦታ የከብት ዕልቂት አይምጣ በሰውም ላይ አባር ቸነፈር በእህልም ላይ ድርቅ የውኃም ማነስ አይሁን"። ❤ መድኃኒታችንም "የለመንከኝ ሁሉ አስጥሃለሁ አንተም በቀኜ ትኖራለህ ሥጋህንም ኤልያስ በዐረገበት ሠረገላ ውስጥ አኖራለሁ" አለው ሕፃን ቂርቆስ በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ ብሎት ጌታችንን አመሰገነው። ከዚህም በኋላ በሌሊቱ እኩሌታም ከእናቱ ጋር አንገቱን ተቆረጠ መድኃኒታችንም በማይጠፋ አክሊል ጋረደው ነፍሶቻቸውንም በታላቅ ክብር ከእርሱ ጋር አሳረገ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ቂርቂቆስና በእናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #ነቢዩ_ቅዱስ_አብድዩ፦ ይህም ነቢይ የሐናንያ ልጅ ነው በንጉሥ ኢዮሳፍጥም ዘመን ትንቢት ተናገረ እግዚአብሔርም ስለ ትንሣኤና ስለ ፍርድ ቀን በቃሉ ነገረው። ሁለተኛም ከእስራኤል ልጆች የሚሆነውን ከአሕዛብም ለቀሩት አጸናቸው አብዝቶ መከራቸውም ገሠጻቸውም። ❤ ይህም ንጉሥ አካዝያስ ይጠሩት ዘንድ ወደ ኤልያስ ከላከቸው ሦስተኛ መስፍን ነው ከእርሱ አስቀድመው የመጡ እነዚያን ሁለት መስፍኖች በኤልያስ ቃል አሳት ከሰማይ ወርዳ ከእነርሳቸው ጋር ካሉ ወታደሮች ጋር በላቻቸው። ይህ ግን ወደ ኤልያስ በመጣ ጊዜ በፊቱ ተንበርክኮ ሰግዶ ተገዛለት እንዲህም አለው "የእግዚአብሔር ሰው ተገዛሁልህ የእሊህ የባሮችህ ሰውነትና የኔ ሰውነት በፊትህ ትክበር" በእግዚአብሔር ነቢይ ላይ ፈጽሞ አልታበየምና ነቢዩ ኤልያስም ራራለት ወርዶም ከርሱ ጋር ወደ ንጉሡ ሔደ። ❤ ይህም አብድዩ ከምድራዊ ንጉሥ አገልግሎት የኤልያስ አገልግሎት እንደምትበልጥ የኤልያስ አገልግሎት ለሰማያዊ ንጉሥ አገልግሎት ታደርሳለችና ይህን በልቡ ዐወቀ ስለዚህ ምድራውያን ነገሥታትን ማገልገል ትቶ ነቢዩ ኤልያስን ተከትሎ አገለገለው በላዩም ከእግዚአብሔር ሀብተ ትንቢት አደረበትና ትንቢትን የሚናገር ሆነ የትንቢቱም ወራት ሃያ ዓመት ነው ከጌታችን ሥጋዌ በፊት በዘጠኝ መቶ ዓመት በሰላም በፍቅር አንድነትም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ነቢያት ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጥር 15 ስንክሳር።                                                                                  ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወሥጋሆሙኒ ለጻድቃኒከ ለአራዊተ ገዳም። ወከዐዉ ደሞሙ ከመ ማይ ዐውዳ ለኢየሩሳሌም። ወኃጥኡ ዘይቀብሮሙ። መዝ 78፥2-3።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "አኅለፍከነ ማእከለ እሳት ወማይ። ወአውጻእከነ ውስተ ዕረፍት። እበውእ ቤተከ ምስለ መባእየ"። መዝ 65፥12-13። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 12፥1-11፣ 1ኛ ጴጥ 4፥11-15 እና የሐዋ ሥራ 16፥14-19። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 18፥1-12። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ቂርቆስ የዕረፍት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።

ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta): ❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤               ❤ #ጥር ፲፭ (15) ቀን። ❤ እንኳን #ለከበረ_ሕፃን በሦስት ዓመቱ ተጋድሎውን ለፈጸመ #ለቅዱስ_ቂርቆስ_ለዕረፍቱ ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል፣ #ለቅዱስ_ቂርቆስ_ማኅበር_ለዐሥራ_አንድ_ሽህ_አራት_ሰዎች_ሰማዕትነት ለተበቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓልና ለሐናንያ ልጅ ለዕውተኛ ነቢይ #ለቅዱስ_አብድዩ ለዕረፍት በዓል። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ በሶርያ አገር ያሉ የክርስቲያን ወገኖች #ለቅዱስ_ጎርጎርዮስ የዕረፍቱን መታሰቢያ በዓል ከመያከብሩት፣ #ከጴጥሮስ_ከሶፍያ_ከአድምራና_ከይስሐቅ ከዕረፍታቸው መታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                                                         ✝ ✝ ✝ ❤# ሕፃኑ_ቅዱስ_ቂርቆስ፦ በዚያንም ወራት የክብር ባለቤት የሆነ ክርስቶስን በሚያምኑ የክርስቲያን ወገኖች ላይ ታላቅ መከራና ስደት ሆነ። ስሟ ኢየሉጣ የሚባል አንዲት ሴት ነበረች እርሷም ከታናሽነቷ ጀምራ ደግ ናት ስደትም እንደሆነ በሰማች ጊዜ መኰንኑን ከመፍራት የተነሣ ሕፃኗን ይዛ ከሮሜ ከተማ ተሰዳ የኪልቅያ አውራጃ ከሆነ ከጠርሴስ ደርሳ ከዚያም በአገሮች ውስጥ እየተዘዋወረች ተቀመጠች። ወደዚያች አገርም ያ ከእርሱ የሸሸችው መኰንን እለእስክድሮስ መጣ ጭፍሮቹም ክርስቲያኖችን ፈለጓቸው። ይቺንም ቅድስት ኢየሉጣን አግኝተው ያዝዋትና ወደ መኰንኑ አደረሷት የክርስቲያን ወገንም እንደሆነች ነገሩት። ❤ መኰንኑም "ሴትዮ ተናገሪ ከወዴት ሕዝብ ወገን ነሽ ነገድሽ ምንድን ነው አገርሽስ ወዴት ነው" አላት። የከበረች ኢየሉጣም እንዲህ ብላ መለሰችለት "የአንጌቤን ሰው ለሆንኩ ለእኔ ወገኖቼ ኤሳውሮሳውያን ናቸው እኔም በአንተ ምክንያት ሸሽቼ ነበር እነሆ ዛሬ ግን በእጅህ ውስጥ ነኝ" አለችው። መኰንኑም "በእጄ ውስጥ እንደተገኘሽ ታውቂያለሽን" አላት "አሁንም የሚሻልሽን ምረጪ ስምሽንም ተናገሪ እኔንም እሺ በይኝና ለአማልክት ሠዊ" የከበረች ኢየሉጣም አለችው "ለረከሱ አማልክት እኔ አልሠዋም" አለችው መኰንኑም "ስምሽን ስጪ ተናገሪ" አላት እርሷም "የኔ ስም ክርስቲያን መባል ነው" አለችው። መኰንኑም "ይህስ ስንፍና ነው የሚጠቅምሽ አይደለም እንዳትሞቺ ስምሽን ስጪ ተናገሪ" አላት። የከበረች ኢየሉጣም "የኔ ስም ክርስቲያን መባል እንደሆነ ነገርኩህ ሞት የሚሽረው በሰዎች ዘንድ የምጠራበትን ከፈለግህ ስሜ ኢየሉጣ ነው" ብላ መለሰችለት። መኰንኑም "ጽኑ የሆኑ ሥቃዮችን በላይሽ ሳያመጡ ተነሥተሽ መሥዋዕትን ለአማልክት አቅርቢ" አላት። የከበረች ኢየሉጣም "ዕውነት ነገርን ለመሥራት የምትሻ ከሆነ ዕድሜው ሦስት ዓመት የሆነ ሕፃን ልጅ ይፈልጉ ዘንድ ወደ አገሩ መንደር ላክ ወዳንተም ያምጡትና የምንገዛለትንና የምናመልከውን እርሱ ይነገረን" አለችው። ❤ ያን ጊዜም የሦስት ዓመት ልጅ ይፈልጉ ዘንድ መኰንኑ ወታደሮችን ላከ የአገር ሰዎችም ልጆቻቸውን ሠውረዋልና አላገኙም ከዚያም ከከተማው ቅጽር ውጭ በፀሐይ መውጫ ወዳለው በረሀ በኩል ወጡ የቅድስት ኢየሉጣንም ልጅ አገኙት ይህ ሕፃን "የስንት ዓመት ልጅ ነው" ብለው ስለርሱ ጠየቁ ሰዎችም "ይህ ሕፃን የሦስት ዓመት ሲሆን የክርስቲያናዊት መበለት ልጅ ነው" አሏቸው። ያንንም ሕፃን ይዘው ወደ መኰንኑ ወሰዱት መኰንኑም መልኩ የሚያምርና ደም ግባት ያለው እንደሆነ በአየ ጊዜ "ደስ የምትል ደስተኛ ሕፃን ሰላምታ ይገባሃል" አለው። ሕፃኑም "እኔን ደስተኛ ማለትህ መልካም ተናገርክ ላንተ ግን ደስታ የለህም እግዚአብሔር ለዝንጉዎች ደስታ የላቸውም ብሏልና ብሎ መለሰለት መኰንኑም ሕፃኑን "ሳልጠይቅህ ይህን ያህል ትመልስልኛለህን" አለው። ሕፃኑም "ገና ከዚህ የሚበዛ ነገርን እመልስልሃለሁ" አለው። ❤ መኰንኑም "ስምኽ ማነው” ብሎ በጠየቀው ጊዜ "ከንጹሕ ዐዘቅትና ከማይለወጥ ከማይጠፋ ውኃ የተገኘ ሕፃን ስሜ ክርስቲያን መባል ነው" ብሎ መለሰለት። መኰንኑም "ዳግመኛ እንዳትሞት ስምህን ንገረኝ" አለው የከበረ ሕፃንም "ስሜ ክርስቲያን መባል እንደሆነ ነገርኩህ ሞክሼ ስም የምትሻ ከሆነ እናቴ የሰየመችኝ ቂርቆስ ነው" በማለት መለሰለት፡፡ መኰንኑም ሕፃን ቂርቆስን "እሺ በለኝና እሾምሃለሁ በብዙ ወርቅና ብርም አከብርሃለሁ" አለው። ሕፃኑም "የሰይጣ መልእክተኛ ለዕውነትም ጠላቷ የሆንክ ከእኔ ራቅ" አለው። መኰንኑም ሰምቶ ተቆጣ ደሙ እንደ ውኃ እስከሚፈስ ቆዳውን እንዲጨምቁትና እንዲግፉት አዘዘ። የከበረች ኢየሉጣሜ የልጅዋን ትዕግሥት በአየች ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነችው። ❤ ከዚህም በኋላ መኰንኑ "ጨውና ሰናፍጭ አምጡ አለ። የሁለቱንም አፍንጮቻቸውን ከፍተው ያንን ጨውና ሰናፍጭ እንዲጨምሩባቸው አዘዘ ያን ጊዜ ሕፃኑ "ትእዛዝህ ለጒረሮዬ ጣፋጭ ሆነ ከማርና ከስኳርም ለአፌ ጣመኝ" ብሎ ጮኸ። ሁለተኛም መኰንኑ እንዲህ ብሎ አዘዘ የረዘሙና የተሳሉ በእሳትም እንደ ፍም የጋሉ ዐሥራ አራት የብረት ችንካሮች አምጡ ሰባቱን በእናቱ አካላት ውስጥ ጨምሩ በሕፃኑም ሁለት ጆሮዎቹ ሁለት በዐይኖቹ ሁለት በአፉና በአፍንጫው አንድ በልቡ ጨምሩ እንዲህ ሲጨመርበት ጆሮዎቹ እንዲአሩ ዐይኖቹም ይጠፋ ዘንድ አንደበቱም ይቃጠል ዘንድ ወደ ልቡም ጽኑ ሕማም ገብቶ እርሱ ከዚህ ዓለም በሞት እንዲለይ ለእናቱም እንዲሁ አድርጉ ችንካሮችም በቅዱሳኑ በሥጋቸው ሁሉ ተጨመሩ። የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ትእዛዝ የብረቶቹ ግለት ጠፍቶ እንደ በረዶ ቀዘቀዘ ጤነኞችም ሆኑ መኰንኑም "ወደ ወህኒ ወስዳችሁ በዚያ አሥራችሁ ዝጉባቸው" አለ። ❤ ከዚህም በኋላ መኰንኑ "የሥቃይ መሣሪያን ይሠራ ዘንድ እንዳዝዘው ብረትን የሚያቀልጥ ሰው አምጡልኝ" አለ። በአመጡለትም ጊዜ ሰይጣን ወደ መኰንኑ ልብ ገብቶ አንደበቱን ዘጋውና መናገር ተሳነው ሕፃኑ ፈጥኖ አክሊልን ለመቀበል እንደሚተጋ ሰይጣን ስለ አወቀ ስለዚህ ዘጋው። ❤ ከዚህም በኋላ ሕፃኑ ሠራተኛውን ጠርቶ "እኔንና እናቴን የሚያሠቃዩ በትን የሥቃይ መሣሪያ መሥራት ትችላለህ ይህ መኰንን ግን ምንም የሚያውቀው ነገር የለም" አለው። ሠራተኛውም እንደምትሻው በል ንገረኝ እምታዝዘኝ እኔ መሥራት እችላለሁ" አለው። ሕፃኑም ቅዱስ ቂርቆስ እያዘዘው...። ብረት ሠሪውም ሰምቶ እጅግ አደነቀ የሚረዱትንም ከአገር ውስጥ መቶ ሠራተኞችን ሰብስቦ መሥራት ጀምረ በአርባ ቀንም ጨረሰ። ❤ ከዚህም በኋላ መኰንኑ እለእሰሰክድሮስ ቂርቆስንና እናቱን ወደ አደባባይ ያመጡአቸው ዘንድ አዘዘ ያን ጊዜ አንደበቱ ተፈትቶ ነበርና እንዲህ አለ "ሕፃኑንና እናቱን ከቆዳቸው ጋር ራሳቸውን ላጩአቸውና በላያቸው የእሳት ፍሞችን ጨምሩ እርር ብለው እንዲቃጠሉ ዳግመኛም አራት ችንካሮችን ከትከሻዎቹ እስከ ተረከዙ ድረስ እንዲተክሉበት አዘዘ የእግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ ሥቃዩን ከርሱ አራቀ። ዳግመኛም ከጥዋት እስከ ማታ ከሥቃይ መሣሪያዎች ውስጥ ጨምረው አዋሏቸው ግን ማሠቃየት ተሳናቸው።

ጥር ፲፬ /14/ በዚች ዕለት የከበረች ምህራኤል በሰማዕትነት አረፈች። የዚችም ቅድስት ወላጆቿ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ክርስቲያኖች ናቸው አባቷም ዮሐንስ የሚባል ቄስነው እናቷም ኢላርያ የምትባል ደ
ጥር ፲፬ /14/ በዚች ዕለት የከበረች ምህራኤል በሰማዕትነት አረፈች። የዚችም ቅድስት ወላጆቿ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ክርስቲያኖች ናቸው አባቷም ዮሐንስ የሚባል ቄስነው እናቷም ኢላርያ የምትባል ደግ ናት ለብዙ ዘመንም ልጅ አልነበራቸውም ነበር ከጊዜ በኋላም እግዚአብሔር የተቀደሰች ልጅ ተሰጠቻቸው ስሟንም ምህራኤል አሏት። በ12 አመቷም ድንቆች ተአምራቶችን መሥራት ጀመረች። ከዚህም በኋላ ከሀዲ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ በተነሣ ጊዜ ወደ ባሕር ዳርቻ ወጣች መርከብም አግኝታ በላዩ ተሳፈረች ለሰማዕትነት ከሚሔዱት ጋር በመሔድ ወደ እንጽና ከተማ በደረሰች ጊዜ ስሙ ፍልፍልያኖስ በሚባል መኰንን ፊት ቆመች በአያትም ጊዜ ስለታናሽነቷ ራርቶላት ሊተዋት ወደደ። ሊተዋትም እንደወደደ ዐውቃ እርሱንና የረከሱ አማልክቶቹን በድፍረት ረገመች። ስለዚህም መኰንኑ ተቆጥቶ ጽኑዕ የሆነ ሥቃይን አሠቃያት ከቀናች ሃይማኖቷ ሸንግሎ ይመልሳት ዘንድ በተሳነው ጊዜ ጊንጦችን እፉኝቶችንና እባቦችን ሰብስበው በዳውላ ውስጥ እንዲጨምሩአቸው እርሷንም ከእርሳቸው ጋር በዳውላ ውስጥ እንዲጨምሩ አጥማጆችን አዘዛቸው እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። ያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጸላትና ከጌታችን ዘንድ የተሰጣትን ቃል ኪዳን አስረከባት ከዚህም በኋላ ነፍሷን አሳለፈች የምስክርነት አክሊልንም ተቀበለች ከዳውላውም ውስጥ አውጥተው በዚያች ቦታ ቀበሩዋት። ከዚህም በኋላ አባቷና እናቷ በሰሙ ጊዜ ሥጋዋ ወዳለበት ከብዙ ሕዝብ ጋር መጡ ከዚያም ሥጋዋን አፈለሱና ወሰዱአት በታላቅ ክብርም ገንዘው በአማረች ሣጥን ውስጥ አኖሩዋት በሥውር ቦታም ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠሩላት ከእርሷም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ፦መጽሐፈ ስንክሳር

ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ በሚዲያና ዕቅበተ ዕምነት ክፍል የምስል ማህደር ለዛሬ በጥቂት ተጋበዙልን ለዓመቱ በሰላም ያድርሰን።
+5
ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ በሚዲያና ዕቅበተ ዕምነት ክፍል የምስል ማህደር ለዛሬ በጥቂት ተጋበዙልን ለዓመቱ በሰላም ያድርሰን።