en
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

Open in Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

Show more
610
Subscribers
No data24 hours
-37 days
-1130 days
Posts Archive
❤ ሌሊት ሲሆንም ይገድሉት ዘንድ እስከሚሰበሰቡ ድረስ ወደ እስር ቤት አስገቡት፡፡ መንፈቀ ሌሊት ሲሆንም በሮች ተዘግተው ጠባቂዎችም ተኝተው ሳሉ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ የእግዚአብሔር መልአክም "የግብጽን አገራት ሁሉ የምታረጋጋ የእግዚአብሔር አገልጋይ ማርቆስ ሆይ ስምህ በሰማይ ባለ የሕይወት መጽሐፍ ተጽፏል ከሐዋርያት ቁጥርም ተቆጥሮአል፤ መታሰቢያህም አይረሳም፤ በምድርም ስፍር ቁጥር የሌላትን ሥልጣን፣ ጸጋ ኃይል እነሆ ሰጥቶሃልና፤ ነፍስህ በሰማይ ይሆናል ሥጋህም በመሬት አይጠፋም" አለው፡፡ ❤ ቅዱስ ማርቆስም ይህን ምሳሌ በተመለከተ ጊዜ እጆቹን ወደ ሰማይ አነሣ "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከፊትህ አልጣልኸኝም፣ ከቅዱሳን ማኀበርም ደምረኸኛልና አመሰግንሃለሁ፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እለምንሃለሁ ነፍሴን በሰማይ ተቀበላት፤ ከፊትህም አትተወኝ" አለ፡፡ ይህን በተናገረ ጊዜ ጌታችን አዳኝ ከሆነው ከሕማሙ በፊት በመቃብርም ከመጨመሩ አስቀድሞ በሐዋርያት መካከል እንደነበረ ሆኖ ታየው፡፡ "የመረጥሁህ ማርቆስ ሆየ ሰላሜ ከአንተ ጋር ይሁን፤ በወንጌል አስተማርሁህ፤ እነሆመ መከራን ከመቀበሌ አስቀድሞ ከጓደኞችህ ከሐዋርያት ጋር አንደሆንሁት በአርአያ ተገለጥኩልህ፤ ከእነርሱ ምንም ጉድለት እንዳይኖርብህ" አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከጸጋህ ታላቅነት የተነሣ አመሰግንሃለሁ፤ በሥጋህ አንደነበርህ ሁነህ አንዳይህ የተገባኝ አድርገኸኛልና” አለው "ስለተቀደሰው ስምህ መከራን እቀበል ዘንድ ትዕግሥትን አድለኸኛልና" ጌታችንም ሰላምን ሰጠውና በታላቅ ምስጋና ወደ ሰማይ አረገ ፡፡ ሲነገም የአገሩ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ከእስር ቤትም አወጡት በሰንሰለትም አሰሩት፤ ዳግመኛም በላሞች ቦታ እንደፍየል እንጐትተው እያሉ በከተማው ጐተቱት፡፡ ❤ ብፁዕ ማርቆስም ምስጋናን አቀረበ በሰማይ ተገለጠ፡፡ በየአገሩ ከጎተቱት በኋላም ደሙ በየመንገዱና በየአደባባይዋ ሞላ "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ነፍሴን በእጅህ ሰጠሁ" አለ፡፡ ይህን ከተናገረ በኋላም ሚያዝያ 30 ቀን ዐረፈ፡፡ ሁሉም አረማውያን ቅዱስ ማርቆስ አንዳረፈ በተመለከቱ ጊዜም ሥጋውን በእሳት ያቃጥሉት ዘንድ አውበካልዮን በምትባል ቦታ ጽኑ እሳትን አነደዱ፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድም ጨለማና ቀዝቃዛ ነፋስ ሆነ፤ ፀሐይም ብርሃኑን ሰወረ፡፡ በዚች ዕለትም እስከ ምሽት ድረስ መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ዝናምና ብርድም ሆነ፤ ከአገሩ ሰዎች ከሽማግሌዎች ብዙዎች ወደቁ ከእነርሱም ብዙዎቹ ሞቱ ያን ጊዜ ፈሩ ሂደወም ከአገሩ ሰዎች የቅዱሱን ሥጋ አኖሩት፤ የተዘባበቱበትም አሉ “ ታላቁ አምላክ ሆይ የዚህን ሰው ነፍስ ተቀበላት በዚች ዕለት የልደቱ ዕለት ናትና” አሉ፡፡ ምዕመናን ወንዶች ደረሱና የቅዱሱን ሥጋ ከእሳቱ ወሰዱት ጸሎት ወደሚጸለይበት ቦተም አደረሱት በእርሱ ላይም ተሳሉ፣ ምስጋናንም አቀረቡ እንደ ሥርዓታቸውም እንደ አገሩ ሰዎች ገነዙት በቆፈሩለት መቃብርም ቀበሩት፡፡ መታሰቢያውንም በደስታ፣ በምሥጋና አብዝተው አደረጉ፣ አበዙ በአገሩ መሠረታዊ ቦታም አስቀመጡት፡፡ ❤ የሰማዕታት መጀመሪያ በግብጽ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰ የወንጌላዊው የቅዱስ ማርቆስ ዕረፍቱ በሚያዝያ ወር መጨረሻ በ30 ሠላሳኛው ቀን ዕለቱመ ሰኞ ጠዋት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ በተገለጸ 68 ዓ.ም ወደ ሰማይ ባረገ በ35 ዓ.ም በታላቋ አገር በእስክንድርያ ሆነ ፡፡ ከሐዋርያውና ከወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን፡፡ በጸሎቱ ይማረን!፡፡ ምንጭ፦ ገድለ ሐዋርያት ፤ የሚያዝያ 30 ስንክሳር ፤ ክብረ ቅዱስ ማርቆስ ከሚለው መጽሐፍ።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር። እግዚኦ አነ ገብረከ። ገብረከ ወልደ ዓመትከ"። መዝ 115፥6-7። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 10፥1-12።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ። ወየሐውር እምኃይል ውስተ ኃይል። ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን"። መዝ 83፥6-7። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ጢሞ 4፥1-20፣ 1ኛ 5፥12-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 15፥36-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 10፥1-19። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱሳን ሐዋርያት ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ማርቆስ የዕረፍት በዓልና የትንሣኤ ሰሞን ለሁላችንም ይሁንልን።                                                                

❤ ቅዱስ ማርቆስ በኢየሩሳሌም የእናቱ የማርያም ቤት የደቀ መዛሙርቱ መገናኛና መሰባሰቢያ ስለነበር ደቀመዛሙርቱን የበለጠ እንዲያውቃቸውና እንዲቀርባቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማድረጉም በላየ በተለይም ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር ባለው የጠበቀ ዝምድናና ቀረቤታ ለቅዱስ ጴጥሮስ የሃይማኖት ልጅ በመሆንና ለአገለግሎቱም ፍጹም መንፈሳዊና እውነተኛ የክርስቶስ ምስክር ለመሆን በቅቷል፡፡ ቅዱስ ማርቆስ በልጅነቱ በኢየሩሳሌም ለመኖር በመታደሉ በዚያም ዘመን ይሰጥ የነበረውን ትምህርት የማግኘት ዕድል ገጥሞት ነበርና የዕብራይስጥ፣ የላቲንና የግሪክ ቋንቋዎችን ያውቅ ነበር፡፡ ❤ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌልን መስበክ የጀመረው ገና በወጣትነቱ ነበር በመጀመሪያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብሮ ያስተምር ነበር፡፡ በግብረ ሐዋርያት አንደተገለጸው ቅዱስ ማርቆስ ከቅድስ ጳውሎስና ከቅድስ በርናባስ ጋር ይሰበክ ነበር፡፡ ከዚያም በፊት ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ አስተምሮአል፡፡ ❤ ቅዱስ ማርቆስ ንጹሕና ድንግል መሆኑን መልካምነቱንና ትምህርቱን ተመልክቶ ቅዱስ ጴጥሮስ ለግብጽና ለአካባቢዋ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አድርጎ ሾመው፡፡ በግብጽ አገሮች በሎኒያ፣ በመርቅያ፣ በጣውንቄ፣ በበርቃ ለመጀመሪያ አስተማረ እርሱ ነው፡፡ ወንጌልን አስተማራቸው፡፡ አዳኝ በሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንንም አስተማራቸው፡፡ ሁሉም የዚያች አገር ሰዎች ልቡናቸው የደነደነ ነበሩ በርኵሰት ሁሉ የተሞሉ አማልክትንም ያመልኩ ነበር፡፡ ሰይጣንን በማምለክም ይኖሩ ነበር፡፡ በየቦታው በየመንገዱም ሁሉ ምኩራቦችን የአማልክትን ቤት ይሠሩ ነበር፡፡ መድኃኒትን፣ ዝሙትንም ያደርጉ ሕጻናትን ይገድሉ በደማቸው መድኃኒትን ያደርጉ ነበር፡፡ ❤ ቅዱስ ማርቆስም ወደ ሐዋርያት በሄደ ጊዜ አስቀድሞ በርቃ ደረሰ፡፡ ዘመዶቹ ከእነርሱ ወገን ናቸውና፡፡ እግዚአብሔርን ቃልም አስተማራቸው በመካከላቸው ብዙ ተአምራትን አደረገ፤ በሽተኞችን ፈወሳቸው ለምጻሞችንም አነጻቸው፤ በእርሱ ላይ በአደረው ጸጋም አጋንንትን አስወጣ፤ ብዙዎችም በትምህርቱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ አምላኮቻቸውንም (ጣዖቶቻቸውንም) ሰባበሩ፤ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምም አጠመቃቸው፡፡ ❤ በዚያ ቦታም ወደ እስክንድርያ ይሄድ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ተገለጠለት፡፡ በዚያም መልካም ተዘራባት ይኸውም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ወንጌላዊው ብፁዕ ቅዱስ ማርቆስም ለጦርነት እንደተዘጋጀ ጎልማሳ ሆነ ወንድሞቹንም ሰላም አላቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ቦታ ቅዱስ ወንጌልን አስተምር ዘንድ ወደ እስክንድርያ እንድሄድ አዝዞኛል" አላቸው፡፡ እነርሱም ሸኙት በመርከብም ተሳፍሮ ወደ እስክንድርያ ሄደ በደረሰ ጊዜም ወደ ከተማው በር ገባ የጫማው ማሠሪያም ተቆረጠ "በቅንነትም መንገድ ፈጠነች" አለ በዚያም ከከተማው መግቢያ ጫማ ሰፊ ነበር፡፡ ቅዱስ ማርቆስም እንዲሰፋለት ለርሱ ሰጠው ሲሰፋም ጣቱን ወግቶ ሰነጠቀው ከእርሱም ደም ፈሰሰ በዩናኒም ቋንቋ "ኢታስታያስ"  አለ ትርጓሜው አንድ እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም "ስሙን የምትጠራው አውቀኸው ነውን" አለው "እንጠራዋለን እንጂ አናውቀውም" አለ፡፡ ቅዱስ ማርቆስ በጣቶቹ ላይ መራቅ ጨመረና አፈር ወሰደ ያን ጫማ ሰፊ ቀባው "በሕያው አግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ስም አጅህ ትፈወስ" አለው፡፡ ስለዚህም ተፈወሰች ጫማ ሰፊውም በሥልጣኑ በቃሉ ያደረገውን ድንቅ ተአምር በተመለከተ ጊዜ  "የቸሩ አምላክ አገልጋይ ሆይ እለምንሃለሁ ዛሬ ውጣና በቤቴ ዕረፍ በአንድነትም እንመገብ መልካም ነገርን አድርገህልኛልና" አለው፡፡ ❤ ብፁዕ ቅዱስ ማርቆስም ተደሰተ፡፡ "እግዚአብሔር ሰማያዊት የምትሆን ሕይወት ኀብስትን ይስጥህም" አለው፡፡ ጫማ ሰፊውም ሐዋርያውም እየተደሰተ ወደ ቤቱ አስገባው፡፡ ሐዋርያውም እየተደሰተ ወደ ቤቱ ገባለት። "የእግዚአብሔር በረከት በዚህ ቤት ይኑር" አለ፡፡ ወንድሞች በአንድነት ጸለዩ ከጸሎት በኋላም ተቀመጡና ደስ እያላቸው ተመገቡ፡፡ ጫማ ሰፊውም ቅዱስ ማርቆስን  "አባት ሆይ እለምንሃለሁ ይህንን የምትለው እንዴት ነው፤ ይህ ስምስ ምንድን ነው ይህ እንደዚህ የሚቻለው ነው" አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም "እኔ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ነኝ" አለው፡፡ ጫማ ሰፊውም "እኔ ላየው እሻለሁ" አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም "እኔ አሳይሃለሁ" አለው፡፡ ቅዱስ ማርቆስም የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዳዊት ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ ነው እያለ የወንጌሉን መጀመሪያ አስተማረው፡፡ በትንቢት ስለ እርሱ የተናገሩትንም ከመጻሕፍት ተናገረ፡፡ ጫማ ሰፊውም "እኔ የምትለውን ይህን መጽሐፍ እለምንሃለሁ ከረጅም ዘመን ጀምሮ የግብጻውያን ልጆች እንደማይማሩበት አልሰማህምን" አለው ቅዱስ ማርቆስ እንዲህ በማለት የእግዚአብሔርን ነገር ይነግረው ዘንድ አስቀደመ  "የዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ዘንድ ናት" አለው ጫማ ሰፊውም የቅዱስን ነገር በሰማ ጊዜ በእግዚአብሔር አመነ ለእርሱም አመለከተው ከእርሱም ኃይላትን ተአምራትን አየ እርሱ ቤተሰቡ፣ ከአገሩ ሰዎችም ብዙዎቹ ተጠመቁ፡፡ የጫማ ሰፊው ስምም አንያኖስ ይባላል፡፡ ያን ጊዜም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ምዕመናን በዙ፡፡ የአገሩ ሰዎች በሰሙ ጊዜም "ይህ የገሊላ ሰው ከዚህ አገር ደርሷል፤ የአማልክትን እጅ መንሻ ለውጧል፤ እንዳይመለኩ ከልክሏል" አሉ ሊገሉትም ፈለጉት ይጥሉት ዘንድም በእርሱ ላይ ፍለጋን አበዙ ብፁዕ ማርቆስ ይህን በተረዳ ጊዜ አስተማራቸውና አንኖስንም ኤጲስ ቆጾስነት ሾመላቸው ሦስት ካህናትንም ሾመላቸው ስማቸውም ወልዮስ፣ መሪደስና በሪሞስ ይባላል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮም ሰባት ዲያቆናትን አንድ ላይ አሥራ አንድ ሰዎችን ሾመላቸው፡፡ ❤ ቅዱስ ማርቆስም ወደ ብርቃ ወጣ ለዓመታትም በእርሷ ተቀመጠ፡፡ በሁሉም አገራት ኤጲስቆጶሳትን፣ ካህናትን ሾሞላቸው ወደ እስክንድርያም ተመለሰ፡፡ በእግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ጸጋና ማመን በዛባት የላም ቦታ በሚባለው በባሕሩ ዳር ካለው ቦታም ቤተ ክርስቲያን ሠሩ ከዚያ ቦታ ከዓለቱ ሥርም ታላቅ ድንጋይ ቁራጭ ነበር፡፡ ጻድቁም ስለ ምዕመናን መልካም ሃይማኖት እግዚአብሔርን አመሰገነ ብዙ ዘመን በቆየ ጊዜም ክርስቲያኖች በዙ አማልክትንም ተዘባበቱባቸው፤ አረማውያንንም ናቋቸው፡፡ አረማውያንም ቅዱስ ማርቆስ እንደሆነ ወደ አገራቸው እንደ ደረሰ ተረዱ፡፡ ከሰሙት ተአምራት ብዛት የተነሳ ልቡናቸው በቁጣ ተሞላ እርሱ ሕመምተኞችን ይፈውስ፣ ለምጻሞችንም ያነጻ፣ ደንቆሮዎችንም እንዲሰሙ፣ እውራንንም እንዲያዩ ያደርጋል መልካም ተስፋንም ያስተምራቸው ነበር ይይዙት ዘንድም ፈለጉት፤ በየቤታቸውም ጥርሳቸውን ያፋጩ ነበር፤ በአማልክቱ ምኵራብም "እኛ ለዚህ ጠንቋይ ተሸነፍን" እያሉ ጮኹ፡፡ ምዕመናን የሚያከብሩት ዕለት ሰንበት የተባረከው የፋሲካ በዓልም በሰንበት ቀን ሆነ፤ ይህም ዕለት ሚያዝያ 17 ቀን ነው፡፡ ❤ በዚያች ዕለትም በእነርሱ ዘንድ የሰራቢስ የልደቱ ቀን ነበር፡፡ ያማረች ዕለትን አገኙ ሰላዮችን ላኩና ያዙት፡፡ እርሱን የቅዳሴ ጸሎት ሳይፈጽምም በሰንሰለት አሠሩት በላሞች ቦታ እንጐትተው እያሉም እንደ አውራ ፍየል በየመንገዱ ጐተቱት፡፡ ቅዱስ ማርቆስም በጐተቱት ጊዜ አግዚአብሔርን አመሰገነው፡፡  "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በተቀደሰው ስምህ መከራን እንድቀበለ አዘጋጅተኸኛልና አመሰግንሃለሁ” አለ፡፡ ሥጋውም በየመሬቱ ተቆራረጠ ደሙም በየዐለቱ ፈሰሰ፡፡

ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta): ❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ  ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤         ❤ #ሚያዝያ ፴ (30) ቀን። ❤ እንኳን #ለሐዋርያው_ለወንጌላዊው ለእስክንድርያ ሊቃነ ጳጳሳት አለቃ (መጀመርያ) ከሰባ ሁለቱ አርድእት ለአንዱ ለሆነው #ለቅዱስ_ማርቆስ_ዘአንበሳ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                                                         ✝ ✝ ✝ ❤ #ሐዋርያው_ወንጌላዊው_ቅዱስ_ማርቆስ_ዘአንበሳ፦ የቅዱስ ማርቆስ ወላጆች ስም የአባቱ ስም ቅዱስ አርሰጡጳውሎስ ሲሆን የእናቱ ስም ቅድስት ማርያም ይባላል፡፡ አባቱ ባለፀጋና ያላገባ ነበር የአባቱ ስም ስምዖን ይባል ነበር፡፡ ስምዖንም አርስጡጳውሎስን እንዲያገባ ይገፋፋው ነበር፡፡ አንድ ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በቤቷ እንግዶችን የምትቀበልና የምታስተናግድ ማርያም የተባለችውን የወንጌላዊ የቅዱስ ማርቆስ እናት አገኘ ፡፡ እሱም እሷም ሳያስቡት ባዩት ሕልምና በመፈክረ ሕልም (በሕልም ፈቺዎች) በተነገራቸው መሠረት ተገናኝተው የትዳር ሕይወትን መሠረቱ፡፡ ❤ አርስጡጳውሎስ ከከበረውና በባለጸግነቱ ከታወቀው ከአባቱ ካገኘው ሀብት ለነዳያን የሚመጸውት፣ ዐሥራት በኩራት የሚያወጣና ወደ እግዚአብሔርም ዘወትር የሚጸልይ ደግ አባት ነበር፡፡ እሱም የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስ ዘመድ የአክስት ልጅ እንደሆነና ቅዱስ ጳውሎስም በመልአክቱ የጠቀሰው እሱን እንደሆነ አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ "አብሮ ከእኔ ጋር የታሰረ አርስጥሮኮስ የበርናባስም የወንድሙ ልጅ ማርቆስ ኢዮስጦስም የተባለ ኢያሱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል" ቈላስይስ 4፥10 ነገር ግን አንዳንድ የግሪክ፣ የላቲን፣ የግእዝና የኮኘት ትርጉሞች "የበርናባስ የወንድሙ ልጅ" የሚለውን ሐረግ አይጠቅሱም ይህም ምንአልባት አንዳንድ የግሪክ ቃላት ከአንድ በላይ ትርጉም ስላላቸው ይሆናል፡፡ ❤ የቅዱስ ማርቆስ እናት ማርያም ተብለው ከተጠሩት ብዙ ቅዱሳት አንስት መካከል አንዷ ናት፡፡ ቤቷ በኢየሩሳሌም እንደነበረና ምዕመናንም በቤቷ በጸሎት ይሰበሰቡ እንደነበር በሐዋ 12-12-17 በሰፊው ተገልጾአል፡፡ ይህም በጥንት ወይም በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ካሉት መንፈሳውያኑ ሴቶች (ቅዱሳት አንስት) ከፈተኛ ቦታ ያላት እንደነበር ያመለክታል። በዚያን ጊዜ የነበሩ ምዕመናን በአንድነት በክርስቶስ ስም ይሰባሰቡ ስለነበር ክርስቲያን የሚለውን ስም ያገኙትም በዚሁ ወቅት ነበር፡፡ "በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፤ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርቱም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ"፡፡ ሐዋ 11-26 ❤ የቅዱስ ማርቆስ እናት የማርያም ቤት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለጸሎት የሚሰበሰቡበት ነበር፡፡ በማርቆስ እናት በማርያም ቤት በጽርሐ ጽዮን ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ እንደተገለጸላቸውና መንፈስ ቅዱስን እንደላከላቸው በቅዳሴ ዲዮስቆሮስ እንዲህ ተጽፏል "አመ ሣልስት ዕለት ተንሥአ እሙታን ወቦአ ኀበ ሀለው አርዳኢሁ ጉቡአን ወአስተርእዮሙ በጽርሐ ጽዮን … ወበ  ፶ ዕለት ፈነወሎሙ መንፈሰ ቅዱስ ከመ ዘእሳት ወተናገሩ በነገረ ኩሉ በሐውርት … በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ የተሰበሰቡ ደቀ መዛሙርት ባሉበት ገባ በጽርሐ ጽዮንም ታያቸው …በ50ኛው ቀንም በእሳት አምሳል መንፈስ ቅዱስን ሰደደላቸው በአገሩ ቋንቋ ሁሉ ተናገሩ" ❤ በኢየሩሳሌም ውስጥ የማርያም ቤት የሐዋርያት መገናኛና መሰባሰቢያ ነበር፡፡ ስለዚህም የማርቆስ እናት የማርያም ቤት የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ኀብረት መለያ ሆኖ ይታወቃል፡፡ ❤ ቅዱስ ማርቆስ የተወለደው በአባቱ ወገን ከነገደ ይሁዳ ሲሆን የተወለደበት ቦታ ከአምስቱ የምዕራብ ከተሞች አንዷ በሆነችው በሊቢያ በሲርኔ ይኸውም አብራይሮሎስ በተባለች ትንሽ መንደር ተወለደ፡፡ ትውልዱ ዕብራዊ ቤተሰቦቹም ይኖሩበት የነበረው በሰሜን አፍሪካ በጥንታዊቱ ፔንዲፓሊስ ሲሪኒካ (ቀሪና) በተባለችው በዛሬው ሊቢያ ምዕራባዊ ጠረፍ በተቆረቆረችው ደማቅ ከተማ ስለነበር ቅዱስ ማርቆስ አፍሪካዊ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ሉሌ መላኩ ቤተክርስቲያንህን እወቅ። ❤ ቅዱስ ማርቆስ ሰኔ 3 ቀን በዕለተ ረቡዕ ተጸንሶ መጋቢት 3 ቀን በዕለተ ዐርብ ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት ተወለደ፡፡ ❤ የቅዱስ ማርቆስ የስሙ ትርጓሜ ማርቆስ ማለት ንህብ ማለት ነው ንብ ከሁሉ እንዲቀስም አስቀድሞ ከክርስቶስ በኋላም ከሐዋርያት ተምሮአልና፡፡ አንድም አንበሳ ማለት ነው አንበሳ ለላሕም ጌታው እንደሆነ እንዲሰብረው እርሱም አምልኮተ ላሕምን ከግብጽ አጥፍቷልና፡፡ አንድም ካህን ልዑክ ማለት ነው፡፡ ብሥራተ ማሪ ማርቆስ ይላል የተደራረበ ቀለም ነው፡፡ ሁሉም ካህን ማለት ነው፡፡ እመልአክተ ሲኖዲቆስ ባለ ጊዜ መልእክትም ሲኖዲቆስም ክታብ ማለት እንደሆነ ….።  ❤ የቅዱስ ማርቆስ ሁለተኛ ስሙ ዮሐንስ ይባላል። "ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለ ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ" ሐዋ12፥12 ❤ የቅዱስ ማርቆስ ተክለ ቁመናና መልክ እንዲሁም አለባበሱን እንዲህ በማለት ተጠቅሷል፡፡ "የግብጽና የኢትዮጵያ ኮከብ ብፁዕና ቅዱስ ማርቆስ መልኩ ቀይ ቅንድቦቹም ከበድ ያሉ ዓይኖቹም እንደሰማያዊ ኀብር የጠሩ ቁመቱ ረጅም ከአንገቱም ስር ስርጉድ የሆነ እንደ ነቢዩ ኤልሳዕ ራሰ በራህ የሆነ ቀሚስ (ልባልባውም) በወገቡ የሆነ የግብጽና የኢትዮጵያ አባት የቅዱስ ማርቆስ ምልክቱ ይኸ ነበር፡፡ ❤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዊ በሚሰብክበት ጊዜ ቅዱስ ማርቆስ ወጣት ነበር፡፡ ልቦናው የቀና እንደሆነም አውቆ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የመጀመሪያ አድርጐ መረጠው ከዚህ በኋላ የክርስቶስ ደቀመዝሙር ሆኖ ጌታ ወንጌልን ሲያስተምር፤ ተአምራት ሲያደርግ ያስተውል ነበር ፡፡ በምሴተ ሐሙስ በአይሁድ ሲያዝና መከራን ሲቀበል ቅዱስ ማርቆስ በኢየሩሳሌም መንገድ ላየ ሆኖ በርቀት ድርጊቱን ይከታተለ ነበር፡፡ በወንጌሉም እንዲህ ተብሎ የተጻፈው ስለ አርሱ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ "ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጐበዝ ይከተለው ነበር ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ"፡፡ ማር14-51-52 ❤ ቅዱስ ማርቆስ በቤቱ መጻፊያ ይዞ የጌታን ተአምራት ይጽፍ ነበር፡፡ የግሞ ሊናሮስ የሚባል አገልጋዩን ጌታን እንዲከተልና የሚያደርገውንም ተአምራት እንዲጽፍ ያደርግ ነበር ፡፡ "ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዓለ ፋሲካን ሲያከብር ተከተሉት" የተባለውም ቅዱስ ማርቆስን እንደሆነ እንዲህ ተጽፍል፤  "ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እነዲህም አላቸው ወደ ከተማ ሂዱ ማድጋ ውሃ የተሸከመ ሰውም ያገኛችኋል ተከተሉት የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ መምህሩ፣ ከደቀመዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው ይላል በሉት፡፡ እርሱም በደርብ ላይ ያለውነ የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፣ በዚህም አሰናዱልን፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ ፋሲካም አሰናዱ” ማር 14፥13-15፤ ሉቃ 22፥10-12።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤         ❤ #ሚያዝያ ፳፱ (29) ቀን። ❤ እንኳን #ከሰባ_ሁለቱ_አርድእት ለአንዱ መራራ የሆኑ ውኃዎችን ለውጦ ጣፋጮች ላደረጋቸው፤ የደረቁ ዕንጨቶችንም ላለመለመና በደዌ የተጨነቁ ብዙ በሽተኞችንም ላዳነ #ለሐዋርያ_ለቅዱስ_አርስጦስ ዕረፍት በዓልና ለንጹሕ ደግ ቅን ለሆነ ለኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ #ለአባ_አካክዮስ ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡት፦ ከክብር ባለቤት #ከጌታችን_ከኢየሱስ_ክርስቶስ_ከልደቱ (በዓለ ወልድ) ከወራዊ መታሰቢያ በዓል፣ #ከአባ_ገምሶና ከእርሱ ጋራ ከሆኑ ከብዙ ሰማዕታት ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_አርስጦስ፦ ይህም ቅዱስ ከሐዋርያት ጋራ በጽርሐ ጽዮን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ከተቀበለ በኋላ ከአገሩ ሁሉ ቋንቋ ተናገረ። ሐዋርያትንም እያገለገለ ከእሳቸው ጋራ ሲሰብክ ብዙ ጊዜ መከራ ተቀበለ። ❤ ከዚህም በኋላ ሐዋርያት መርጠው ለኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ሾሙት። በዚችም አገልግሎት ጥቂት ቆይቶ ብስጥስ በሚባል አገር ላይ ሁለተኛ ኤጲስቆሰነት ሾሙት። በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም በውስጥዋ አስተምሮ አንድነትንና ሦስትነትን በማሳወቅ የሰዎቿን ልቡና ብሩህ አደረገ። የጣዖታትንም ቤቶች አፍርሶ አብያተ ክርስቲያንን ሠራ በክብር ባለቤት በጌታችንም ስም አጸናቸው። ❤ ታላላቅ አስደናቂ ተአምራትን በማድረግ መራራ የሆኑ ውኃዎችን ለውጦ ጣፋጮች አደረጋቸው፣ የደረቁ ዕንጨቶችንም እንዲያለመለመልሙና እንዲአፈሩ አደረጋቸው፣ በደዌ የተጨነቁ ብዙ በሽተኞችንም አዳነ ወደ በጎ እርጅና ደርሶ እግዚአብሔር አገልግሎ ሚያዝያ29 በሰላም ዐረፈ። እንሆ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልክቱ አስታውሶታል። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ሐዋርያ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_አካክዮስ፦ ይህ አባት ንጹሕ ደግ ቅን የሆነ የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ነው። ይህንንም ቅዱስ ከሀድያን ብዙ ቀኖች አሠቃዩት እግዚአብሔር በእጆቹ ብዙ ተአምራትን አደረገ ከዚህም በኋላ ሚያዝያ29 በፍቅር አንድነት ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዠላለሙ ትኑር አሜን። ምንጭ፦ የሚያዝያ 29 ስንክሳር።                         ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ዕብል_አርስጦስሃ_ፍጹም። ኤጲስቆጶስና በእደ ሐዋርያት ተሠይመ። ለሀገረ ብናጥስ ሕዝብ እንዘ ያርኢ መድምመ። ገብረ በጸሎቱ ይቡስ ዕፅ ልምሉመ። ወምረረ ማይ ረሰየ ጥዑመ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሚያዝያ_29።                        ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ። ውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ። ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ"። መዝ 18፥3-4። የሚነበቡት መልዕክታት ቈላ 4፥10-14፣ 1ኛ ዮሐ 4፥918 እና የሐዋ ሥራ 13፥4-16። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 10፥1-12።  የሚቀደሰው ቅዳሴ የ­ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓልና የበዓለ ሃምሳ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።

በግራር ደብረዓባይ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን አካባቢ የምትገኙ ፣ መኖርያችሁን 📍በአለምባንክ ፣ 📍በአየርጤና ፣ 📍በካራ፣ 📍በቤቴል ያደረጋችሁ:: በቅርብም በሩቅም ያላችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦ
በግራር ደብረዓባይ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን አካባቢ የምትገኙ ፣ መኖርያችሁን 📍በአለምባንክ ፣ 📍በአየርጤና ፣ 📍በካራ፣ 📍በቤቴል ያደረጋችሁ:: በቅርብም በሩቅም ያላችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች ተጋብዛችኋል:: ወጣቶች፣ በአቅራቢያ የምትገኙ በሰንበት ት/ቤት ያደጋችሁ፣ በመንፈሳዊ ማኅበራት ያደጋችሁ፣ የጽዋ ማኅበራትም ጭምር፣ ጥሪው ሁሉንም ኦርቶዶክሳዊ ይመለከታልና አዳርሱ:: Forward

❤ "በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #ሚያዝያ ፳፰ (28) ቀን። ❤ እንኳን በኮራሳት ተራራ በገድል ተጠምዶ ለሚኖር በሐሰት ሰው ገድለሃል ብለውት የሞተውን ሰው አስነስቶ ላስመሰከረ #ለቅዱስ_አባት_ለአባ_ሜልዮስና መቅሱር ለሚባል አገር ለሆነ #ለቅዱስ_ብስጣውሮስ ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡት፦ #ከዋሲሊኮስና ከብዙ ሰማዕታት ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_ሜልዮስ፦ ይህም አባት ኮራሳት በሚባል አገር በተራራ ባሉ ዋሻዎች ከሁለት አርድእቱ ጋራ ይኖር ነበር። የኮራሳት ንጉሥ ሁለት ልጆቹ ወደዚያ ወጡ ከእርሳቸውም ጋራ አገልጋዮች አሉ አራዊትን አጥምደው በፍላፃዎች ይገሉ ዘንድ መረባቸውን ተክለው አርባ ምዕራፍ ያህል ሔዱ። መረቡን በጠቀለሉት ጊዜ ይህን ቅዱስ አባት ማቅ ለብሶ ጠጉሩም የረዘመ ሁኖ አገኙት። ❤ የንጉሥ ልጆችም በአዩት ጊዜ ፈሩ አንተ ሰው ነህን ወይም መንፈስ ብለው ጠየቁት እርሱም "በዚህ ተራራ ውስጥ የምኖር ለሕያው እግዚአብሔር ልጅ ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የምሰግድ ሰው ነኝ" ብሎ መለሰላቸው። እነርሱም "ከእሳትና ከፀሐይ በቀር አምላክ የለም እንዳንገድልህ ሠዋላቸው" አሉት። እርሱም "እሳትና ፀሐይ የተፈጠሩ ናቸው እናንተም ተሳስታችኋል ፍጥረቶችን በፈጠረ በእውነተኛ አምላክ ታምኑ ዘንድ እኔ እለምናችኋለሁ" ብሎ መለሰላቸው። በዚያን ጊዜ ይህን አባት ሁለቱን አርድእትም ይዘው ጽኑ ሥቃይ አሠቃዩአቸው በዚህ ወር በዐሥራ ሦስት የሁለቱን አርድእት ራሳቸውን ቆረጡአቸው የሰማዕትነት አክሊል ተቀበሉ። ❤ አረጋዊ ቅዱስ ሜልዮስን ግን ዐሥራ አምስት ቀን ያህል ሲአሠቃዩት ኖሩ ከዚህ በኋላ በመካከላቸው አቆሙት አንዱ በፊት አንዱ በኋላ ሁነው በፍላፃ ይነድፉት ጀመር። እርሱም "በእናንተ ላይ ክፉ ያልሠራውን ለመግደል ሁለታችሁ ስለተስማማችሁ እንዲሁ እንደሥራችሁ በፍላፃችሁ ነገ ትሞታላችሁ" አላቸው። ሰምተውም አልፈሩም ነፍሱን እስከሚአሳልፍና ምስክርም ሆኖ የሰማዕትነት አክሊል እስከሚቀበል ነደፉት እንጂ። በማግሥቱም እንደልማቸው ለአደን ወጡ የዱር አህያም አገኙ ተከትለውም ቀስታቸውን አስፈነጠሩ እግዚአብሔር ፍላፃቸውን ወደልባቸው መለሰ ቅዱስ ሜልዮስም እንደተናገረባቸው ሞቱ። ❤ በዚህ ቅዱስም እጅ ጌታችን ተአምራትን ገለጠ በአንዲት ዕለትም አልፎ ሲሔድ በመንገድ ላይ የሞተ ሰው አገኘ የአገር ሰዎች ግን አንዱን መነኰስ አንተ ነህ የገደልከው ብለው ያዙት። ቅዱስ ሜልዮስም ጸለየ "የሞተውም በውኑ የገደለህ ይህ መነኵሴ ነውን?" አለው ያን ጊዜ የሞተው ተነሥቶ "እርሱስ አልገደለኝም ነገር ግን ብዙ ገንዘቤን ከአንድ ቄስ ዘንድ አደራ አስጠበቅሁ ስለዚህ ገደለኝ ከዚህም ጣለኝ" አለ ደግሞ እንዲህ ብሎ ለመነው "ዕገሌ ወደሚባል ወደዚያ ቄስ ሒደህ ገንዘቤን ከርሱ ተቀብለህ ለልጆቼ ስጥ" አለው። ቅዱስ ሜልዮስም "እስከ ትንሣኤ ቀን በሰላም ዐርፈህ ተኛ እኔ ገንዘብ አከፋፋይ ዳኛ አይደለሁም" አለው ያንጊዜም ተኛ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ በቅዱስ ሜልዮስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_ብስጣውሮስ፦ የዚህም ቅዱስ አባቱ ጻድቅ ሰው ነው እናቱን ግን ሰይጣን አስቷት ወደ እስልምና ገባች እርሱም ፈሪሀ እግዚአብሔርን እየተማረ እስከሚጐለምስ አደገ አካለ መጠንም አድርሶ ሚስት አገባ ከርሷም ልጆችን ወለደ። ❤ ብዙ ዘመናትም በአለፉ ጊዜ አንገተ ደንዳና በቀለኛ ሰው በእርሱ ላይ ተነሥቶበት ወደ እስላሞች መኳንንት ሒዶ ሰው ወደ እኛ ሕግ ቢገባ ልጆቹም ሃይማኖቱን ይከተላሉ ይህ ብስጣውሮስ ግን ከሕጋችን የተለየ ነው ብሎ ነገር ሠራበት። የእስላሞች ዳኞችም በሰሙ ጊዜ መልክተኞች ልከው ወደርሳቸው ወደ ሸንጎ አቀረቡት ስለ ሃይማኖቱም ጠየቁት ክርስቲያን እንደሆነ ያለ ፍርሀት ክርስቲያን ነኝ ብሎ ታመነ። ዳኛው ግን ይሸነግረው ዘንድ በፍቅር ይናገረው ጀመር ከከበረችና ከቀናች ሃይማኖቱ ይመለሰው ዘንድ ብዙ ስጦታዎችን እንደሚሰጠው ቃል ገባለት ቅዱሱ ግን ከቶ አልተመለሰም ወደ ስጦታውም ከቶ ልቡ አላዘነበለም። ❤ ከዚህ በኋላ ወደ ግዞት ቤት ወስደው በእግረሙቅ እንዲአሥሩት በአንገቱም የተበሳ ታላቅ ግንድ አሥረው በግንባሩ ደፍተው በኵስ ላይ እንዲጥሉት መኰንኑ አዘዘ። እንዲሁም አደረጉበት እስከ ሦስት ቀን በእሥር ቤትም ሳለ ፀዐዳ ርግብ መጥቶ ጋረደው ስለዚህም የእሥር ቤቱ ጠባቂ ምስክር ሆነ። ❤ ከዚህም በኋላ ዳኞች ወደ ሸንጎ አስቀርበው "ከእንዲህ አንታገሥህም ወደ ሃይማኖታችን ከምትገባና ወይም በእሳት ከምናቃጥልህ ምረጥ" አሉት። እርሱም እኔ ከእናንተ ጋራ ለዘላለሙ ዕድል ፈንታ የለኝምና የወደዳችሁን አድርጉ" ብሎ መለሰላቸው። በዚያን ጊዜም እጅግ ተቆጡ ያለ ርኅራኄ ይደበድቡት ዘንድ አዘዙ ያገር ሰዎችም በጫማቸው መቱት አንዲት ሴትም መጥታ በጫማዋ መታችው ወዲያውኑ እጆቿ ደረቁ። ከዚህም በኋላ ባለ ሰይፍ ከመኰንኑ ታዝዞ ወጣ ሰይፉንም መዝዞ ሳያቋርጥ መላልሶ አንገቱን መታው። ምቱም ወደ ጐን ሒዶ ጀሮውን ቆረጠው አመታቱ ክፉ ስለ ሆነ ከሥሮቿ ብዙ ደም ፈሰሰ። ከዚህም ደግሞ ተዉት እምነታቸው ሊአስገቡት እምቢ በአላቸውም ጊዜ ሁለተኛ ሰይፉን መዝዞ ሰያፊው የከበረች አንገቱን ሚያዝያ28 ቆረጠው በመንግሥተ ሰማያትም የምስክርነት አክሊልን ተቀበለ። ሥጋውንም ከእሳት ጨመሩ ግን አልተቃጠለም። ዘመዶቹም መጥተው በድኑን ወደአገሩ ወሰዱ። በቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ ጐን ቀበሩት። የክብር ባለቤት ጌታችንም ብዙ ድንቆች ተአምራትን ከሥጋው ገለጠ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ በከበረ ሰማዕት ጸሎት ለዘለዓለሙ ይቅር ይበለን አሜን። ምንጭ፦ የሚያዝያ 28 ስንክሳር።                           ✝ ✝ ✝   ❤ "#ሰላም_ዕብል_ለሚልዮስ_ጻድቅ። እምፍትወተ ሥጋ ርኁቅ። እንዘ ይነድፍዎ ሎቱ በአሕፃሆሙ ውሱቅ። እፎ ኢያኅዘኖሙ ለነዐውተ አርዌ ደቂቅ። ሥእርተ ርእሱ ነዊኀ ወልብሱ ዘሠቅ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሚያዝያ_28።                         ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ዕቀበኒ እምሥገርት እንተ ኀብኡ ሊተ። ወእማዕቀፎሙ ለገብርተ ዓመፃ። ለይደቁ ውስተ መሥገርቶሙ ኃጥአን"። መዝ 140፥9-10። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 4፥1-14፣ ያዕ 2፥19-ፍ.ም፣ የሐዋ ሥራ 7፥1-9። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 12፥8-17። የሚቀደሰው ቅዳሴ የ­ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወይም የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የበዓለ ሃምሳ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።   

"ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ፤ እግዚአብሔር በመካከልዋ ነው አትናወጥም" መዝ ፵፮፥፭ ሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳ
+5
"ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ፤ እግዚአብሔር በመካከልዋ ነው አትናወጥም" መዝ ፵፮፥፭ ሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና በብፁዓን አባቶች ተባርከው  አገልግሎት የጀምሩት የመድኃኔ ዓለም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ። ① የካራ አሎ ደብረ ቀርሜሌዎስ መድኃኔዓለምና ጻድቁ አቡነ ገሪማ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ② የቃሊቲ በርታ ደብረ መንክራት መድኃኔዓለም  ቤተ ክርስቲያን  ③ በሸገር ከተማ ሀገር ስብከት የቀርሳ ደብረ ሰላም መድኃኔለም ቤተ ክርስቲያን ④ የአሶሳ እንዚ መካነ ገነት መድኃኔዓለም  ካቴዴራል ⑤ አምቦ ደብረ መንክራት ቤተ ሰይዳ መድኃኔዓለም እና በዓታ ማርያም ካቴድራል ⑥ በደቡብ  ወሎ ዞን  በወገልጤና ከተማ ደብረ ሰላም  መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን

"ሁለቱም አንድ አካል ይኾናሉ ፤ ይህ ነገር ጥልቅ ፤ ረቂቅ ምሥጢር ነው ፤ እኔም ለክርስቶስና ለቤተክርስቲያን ምሳሌ አድርጌ እናገረዋለሁ፡፡" ሃይማኖተ አበው ዘስምዓት ✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨ ሚያዚያ
+4
"ሁለቱም አንድ አካል ይኾናሉ ፤ ይህ ነገር ጥልቅ ፤ ረቂቅ ምሥጢር ነው ፤ እኔም ለክርስቶስና ለቤተክርስቲያን ምሳሌ አድርጌ እናገረዋለሁ፡፡" ሃይማኖተ አበው ዘስምዓት ✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨ ሚያዚያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በግራር ደብረ አባይ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን  ከወንድማችን ብርሃኑ ሀይሌ ( ሀይለ ማርያም ) ጋር  የጋብቻ ሥነ ሥርዓትሽን የፈጸምሺው የሰንበት ት/ቤታችን አገልጋይ ቤተልሔም ጌትነት ( ወለተ ሥላሴ ) እንኳን ደስ ያለሽ እንኳን ደስ ያላችሁ ። የአብርሃምንና የሣራን ፤ የይሰሐቅንና የርብቃን ጋብቻ የባረከ አምላክ አንድነታችሁን  ይባርክ እመብርሃን በአማላጅነቷ አትለያችሁ ፤ ቅዱስ ሚካኤል ከፊት ይምራችሁ ከኋላ ይከተላችሁ እያለች ፍኖተ ብርሃን  ሰ/ት/ቤት መልካም የትዳር ሕይወት ትመኝላችኃለች። " ጋብቻ ንጹሕ ነው የወንድና የሴት አንድ መሆንንም እግዚአብሔር አክብሮታል "                           መጽሐፈ ዲድስቅልያ

"ሁለቱም አንድ አካል ይኾናሉ ፤ ይህ ነገር ጥልቅ ፤ ረቂቅ ምሥጢር ነው ፤ እኔም ለክርስቶስና ለቤተክርስቲያን ምሳሌ አድርጌ እናገረዋለሁ፡፡" ሃይማኖተ አበው ዘስምዓት ✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨ ሚያዚያ
+9
"ሁለቱም አንድ አካል ይኾናሉ ፤ ይህ ነገር ጥልቅ ፤ ረቂቅ ምሥጢር ነው ፤ እኔም ለክርስቶስና ለቤተክርስቲያን ምሳሌ አድርጌ እናገረዋለሁ፡፡" ሃይማኖተ አበው ዘስምዓት ✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨ ሚያዚያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በግራር ደብረ አባይ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን  ከእህታችን ፌቨን ( ወለተ ተክለሃይማኖት ) ጋር  የጋብቻ ሥነ ሥርዓትህን  የፈጸምከው የሰንበት ት/ቤታችን አገልጋይ ድንቅነህ ሲሳይ ( ሀብተ ማርያም ) እንኳን ደስ ያለህ እንኳን ደስ ያላችሁ ። የአብርሃምንና የሣራን ፤ የይሰሐቅንና የርብቃን ጋብቻ የባረከ አምላክ አንድነታችሁን  ይባርክ እመብርሃን በአማላጅነቷ አትለያችሁ ፤ ቅዱስ ሚካኤል ከፊት ይምራችሁ ከኋላ ይከተላችሁ እያለች ፍኖተ ብርሃን  ሰ/ት/ቤት መልካም የትዳር ሕይወት ትመኝላችኃለች። " ጋብቻ ንጹሕ ነው የወንድና የሴት አንድ መሆንንም እግዚአብሔር አክብሮታል "                           መጽሐፈ ዲድስቅልያ

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ሚያዝያ ፳፯ (27) ቀን። ❤ እንኳን #ለምካየ_ኅዙናን_መድኃኔዓለም_ለዓመታዊ በዓል (በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ፋሽሽት ጣልያን 1928 በድጋሚ ኢትዮጵያን ወሮ 1933 ድጋሚ ተሸንፎ ለወጣበት፤ #ለ84 (ለሰማንያ አራተኛው ዓመት ለርበኞች ቀን መታሰቢያ) ፣ በአባቱ ትዕዛዝ ሰማዕታት ለተቀበለ #ለታላቁ_ሰማዕት_ለቅዱስ_ፊቅጦር ለዕረፍትና በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡት፦ #ከቅዱስ_ፊቅጦር እናት #ከቅድስት_ማርታ፣ #ከቅዱሳን_ሲኖዳና_እስጢፋስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                             ✝ ✝ ✝      ❤ #ሰማዕቱ_ቅዱስ_ፊቅጦር፦ ለዚህ ቅዱስ የአባቱ ስም ኅርማኖስ ነው እርሱም ለዲዮቅልጥያኖስ የአማካሪዎቹና የሠራዊቱ አለቃ ነው ስለ አምልኮ ጣዖት ሥራ ምክሩና ንግግሩ ሁሉ ከእርሱ ጋራ ነበር የእናቱም ስም ማርታ ይባላል በክርስትናዋ የጸናች ብፅዕት ናት። ❤ ቅዱስ ፊቅጦርም በአደገ ጊዜ አባቱ ወደ ንጉሥ አቀረበው ንጉሡም በመንግሥቱ ውስጥ ሦስተኛ ማዕርግ አድርጎ ሾመው በዚያን ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበረ። እርሱም የዚህን ዓለም ክብር ናቀ ሥጋ አይባላም ወይን አይጠጣም ዘወትርም ይጾማል ጸሎትንም ባለማቋረጥ በቀንና በሌሊት ይጸልያል። በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም የታሠሩትን ይጐበኛቸዋል ለድኆችና ለምስኪኖችም ይመጸውታል። ❤ የቅዱስ ቆዝሞስና ድምያኖስ እናት ቅድስት ቴዎዳዳን በገደሉዋት ጊዜ ንጉሡም ስለ መፍራት ሊቀብራት ማንም አልደፈረም። ይህ ቅዱስ ፊቅጦርም መጥቶ ሥጋዋን ወሰደ ከንጉሥ ስለሚመጣው ቅጣት ሳይፈራ ቀበራት። ጣዖት ስለ ማምለኩ አባቱን ዘወትር የሚገሥጸውና ብዙ ጊዜም የሚመክረው ሆነ አባቱም ወደ ንጉሥ ከሰሰው እንጂ አልሰማውም። ተከሶም ወደ ንጉሥ በአቀረቡት ጊዜ "አማልክት ያልሆኑ ርኲሳን ጣዖታትን ለሚያመልክ ሰነፍ ዝንጉ ልብ የለሽ ለሆነ ንጉሥ አላገለግልም። ከዛሬ ጀምሮ ለሕያው ንጉሥ ክርስቶስ እገዛለሁ የሰጠኸኝንም ገንዘብህን ንሣ" ብሎ በፊቱ ትጥቁን ፈትቶ ጣለለት። ❤ አባቱ ኅርማኖስም ወደ እስክንድርያ እንዲልከውና በኄርሜኔዎስ መኰንን ዘንድ በዚያ ፊቅጦር እንዲቀጣ ንጉሡን መከረው። በዚያን ጊዜም ከአደባባይ አወጡት እናቱም በብዙ ልቅሶ ልትሸኘው መጣች። እርሱም ሲመግባቸው ስለ ነበረ የታሠሩ ምዕመናን ስለ ድኆችና ምስኪኖች ስለ ሙት ልጆችና ስለ ባልቴቶች የሚሹትን በመስጠት እንድትጐበኛቸው አዘዛት ከዚያም አፉን ለጉመው ወሰዱት። ❤ በእስክንድርያ አገር ወደ መኰንኑ ኄርሜኔዎስ ዘንድ በደረሰ ጊዜ ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ ሰማያት አውጥቶ ስለ ክብራቸው ለመናገር የሚያስጨንቁ የብርሃን ማደሪያዎችን አሳይቶ ወደ መኖሪያው መለሰው። መኰንኑም በእሳት በአፈሉት በዝፍት፣ በዲን ደግሞ አሠቃየው ከዚያም በብረት አልጋ ላይ አስተኝተው ከበታቹ እሳትን አነደዱ። ደግመው ከውሽባ ማንደጃ ውስጥ ጨመሩት በየአይነቱ በሆነ ሥቃይም አሠቃዩት የክብር ባለቤት ጌታችንም ያጸናውና ከሥቃዩ ያስታግሠው መልአኩንም ልኮ ከቊስሉ ይፈውሰው ነበር። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ እንዴናው ከተማ ላከው በዚያም ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት ምላሱን ቆረጡ። በእሳት ያጋሉዋቸውን ችንካሮች በጐኖቹ ውስጥ ጨመሩ እግዚአብሔር ግን አጽንቶ አስታግሦ ያለ ጉዳት በደኅና ያነሣዋል። ከዚህም በኋላ በዚያ በረኃብ እንዲሞት ከዱር ባለ ግምብ ውስጥ አሠሩት። እርሱ ግን መጥረብ የሚያውቅ ስለሆነ ላይዳዎችን በመጥረብና በመሸጥ በየጥቂቱ እየተመገበ የቀረውን ለድኆች እየሰጠ ኖረ። አንድ መኰንንም መጥቶ በዚያ ግምብ አቅራቢያ አደረ ስለ ቅዱስ ፊቅጦርም እርሱ የንጉሥ የሠራዊት አለቃ የሆነ የኅርማኖስ ልጅ እንደሆነ ነገሩት። መኰንኑም ወደርሱ አቅርቦ ብዙ ሸነገለው ባልሰማውም ጊዜ ያሠቃዩት ዘንድ አዘዘ ጅማቶቹን መዘዙ አፋን መቱት ቊልቊል ሰቀሉት በእጆቹ ላይ ከባድ ደንጊያ አንጠልጠሉ። ከዚያም ከሚነድ እሳት ውስጥ ጨመሩት ሙጫ፣ አደሮ፣ ማርና ዘይትን አፍልተው በላዩ ደፉበት በማበራያም አበራዩት አፉንም በአሞትና በእሬት አመረሩት ዐይኖቹንም አወለቁት ደግመውም ዘቅዝቀው ሰቀሉት። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾለት አጸናው አረጋጋው። ሥሮቹንም ሕዋሳቶቹን በቦታቸው መለሰለትና አዳነው። ❤ አንዲት ዓሥራ አምስት ዓመት የሆናት ብላቴና ነበረች ቅዱስ ፊቅጦርን ሲአሠቃዩት በቤቷ መስኮት ታየው ነበር። መላእክትም በእጆቻቸው አክሊሎችን ይዘው እነርሱም በቅዱስ ፊቅጦር ራስ ላይ ሲያኖሩአቸው አይታ እንዴት እንዳየች ለአሕዛብ ነገረቻቸው እጅግም አደነቁ ከእርሳቸውም ብዙዎች በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት ዐረፉ። ያቺም ብላቴና በጌታችን አመነች መኰንኑም ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። የሕይወት አክሊልንም ተቀበለች ሁለተኛም የአመኑትን ሁሉ ራሳቸውን እንዲቆርጡአቸው አዘዘ የሕይወትንም አክሊል ተቀበሉ። ❤ ከዚህም በኋላ የከበረች የቅዱስ ፊቅጦርን ራስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ተጋድሎውንም ሚያዝያ27 ፈጽሞ የሕይወትና የድል አክሊል ተቀበለ። ምዕመናን ሰዎችም ሥጋውን ወስደው በከበሩ ልብሶች በድርብ በፍታ ገነዙት። እናቱ ማርታም ከአንጾኪያ እስክትመጣ በንጹሕ ቦታ አኖሩት በመጣችም ጊዜ ከዚያ ወሰደችው። ውብ ቤተ ክርስቲያንም ሠርታ ሥጋውን በውስጥዋ አኖረች ከእርሱም ታላላቅ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የቅዱስ ፊቅጦር በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን። ምንጭ፦ የሚያዝያ 27 ስንክሳር።                            ✝ ✝ ✝  ❤ "#ሰላም_ለፊቅጦር_ተአምራቲሁ_ዘአርአየ። ድኅረ በሰይፍ ተወቅየ። ልብሱ ዘወርቅ አመ ተኀድገ በዝየ። ያሠርጉ ጣዖታቲሁ ሶበ ልበ ንጉሥ ሐለየ። ኀበ ህላዌሁ ተመሥጠ ሰማየ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሚያዝያ_27።                          ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ውእተ ጊዜ እቤ ነየ መጻእኩ። ውስተ ርእሰ መጽሐፍ ተጽሕፈ በእንቲአየ። ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ"። መዝ 39፥7-8። የሚነበበው ወንጌል ማር 10፥1-12።                          ✝️ ✝️ ✝️ ❤ የዕለቱ የቅዳሴ ምስባክ፦ "ወበእግዚአብሔር ተወአልኩ ኢይፈርህ ምንተ ይሬስየኒ ዘሥጋ። ወኵሎ አሚረ ያስቈርሩኒ ዘነበብኩ። ወላዕሌየ ይመክሩ ኵሎ እኩየ"። መዝ 55፥4-5። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ቆሮ 8፥4-10፣ 1ኛ ጴጥ 2፥21-ፍ.ም፣ የሐዋ ሥራ 5፥29-34። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 10፥16-24። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወይም የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጎድ ቅዳሴ ነው። መልካም የምካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም በዓልና የበዓለ ሃምሳ ጊዜ ለሁላችን ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤         ❤ #ሚያዝያ ፳፮ (26) ቀን። ❤ እንኳን በአባቱ እጅ በመጥረብያ አንገቱን ተመቶ ሰማዕትነት ለተቀበለ፤ አባቱን ከዐረፈ በኋላ ለፈወሰው #ለጠራቢ_ልጅ_ለቅዱስ_ዮሐንስ ለዕረፍት ለዕረፍቱ በዓልና #ለሱሴ_ልጅ_ለቅዱስ_ሱስንዮስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡት፦ #ከቅዱሳን_ስብስጥራስ_ከአባ_ሠርጋና፣ #ከይድራስ ከምስክርነታቸው መታሰቢያና #ከቅዱስ_ሱስንዮስ ጋራ ሰማዕትነት ከተቀበሉ #ከአንድ_ሺህ_አንድ_መቶ_ዘጠኝ_ሰማዕታት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                     ✝ ✝ ✝  ❤ #ቅዱስ_ዮሐንስ፦ ይህም ቅዱስ ከነነዌ አገር ነው አባቱ ጣዖትን የሚጠርብና የሚያመልክ ነው። እናቱ ግን ክርስቲያናዊት ናት ልጅ በአጣችም ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ለመነች ጌታም ልመናዋን ተቀብሎ ይህን የተባረከ ልጅ ሰጣት ስሙንም በሥውር ዮሐንስ ብላ ጠራችው። ስምንት ዓመትም በሆነው ጊዜ የጠረበውን ጣዖት እየሸጠለት አባቱን ያገለግል ነበር። ❤ በአንዲት ዕለትም ጣዖቱን ሊሸጥ ሲሔድ የእግዚአብሔር መልአክ ተገናኘውና "ጣዖት የሰይጣን ማደሪያ እንደሆነ ነገረው ጣዖቱንም ከእጁ እንዲጥለው አዘዘው በክብር ባለቤት በክርስቶስ ማመን አስተማረው" ወደ አባቱም በተመለሰም ጊዜ "ሰማይና ምድርን በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ ከፈጠረ ከክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም እኔ ለሰው እጅ ሥራ አልሰግድም" አለው። አባቱም ሰምቶ በእሥር ቤት አሰረው እናቱም መጥታ በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም ደሙን ያፈስ ዘንድ አጸናችው። ❤ ከዚህም በኋላ በነገራቸው ሊሸነግሉት የአገር ሰዎች መጥተው "የአባትህ አምላኮች ለምን ተውክ" አሉት እርሱም "እኔ የሰው እጅ ለሰራቸው ጣዖቶች አልሰግድም እነርሱም የእርኵሳን አጋንንት ማደርያዎች ናቸውንና" አላቸው። አባቱም ይህንን በሰማ ጊዜ ምሳር አንስቶ አንገቱ ቆረጠው በድኑም አልወደቀም በደሙም እስከተጠመቀ ድረስ በእግሮቹ ቆመ እጅ። ❤ እናቱም በደሞ ተጠምቃ "አቤቱ የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የአቤል መስዋዕት በምድረ በዳ የተቀበልክ ይህንን መስዋዕት ከእኔ ተቀበል" አለች። በዚያ ጊዜ አባቱ ሰይጣን አደረበትና አበደ ሚስቱን ወደ ልጇ መቃብር ወስዳው ስለ እርሱ ጸለየች ቅዱስ ዮሐንስም በሌሊት ወደ እርሱ መጥቶ አባቱ በጦር ወጋው ሰይጣኑም ከእርሱ ወጣ ከዚህ በኋላ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመነና በስሙ ተጠመቀ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር አሜን።                            ✝ ✝ ✝  ❤ #ቅዱስ_ሱስንዮስ፦ ይህም ከሀዲው ከዲዮቅልጥያኖስ ወዳጁ ነበረ የእግዚአብሔር መልአክም ተገለጠለትና ሰማዕት እንደሚሆን ነገረው ይህም ነገር በልብ አደረ። ❤ከዚህም በኋላ አምልኮ ጣዖትን እንዲያስፋፋና እንዲያድሱ ከሹመት ደብዳቤ ጋራ ንጉሡ ወደ ኒቆድምያ ላከው ቅዱሱም አይቶ እጅግ አዘነ ወደ እርሱ አንድ ቄስ አምትቶ ክርስትናንን ተምሮ ተጠመቀ። ከዚህ በኋላ ወደ አንጾኪያ ተመለሰ ፍጥረቱ ልዩ የሆነ ልጅ ወልዳ እቱን አገኛት ከዚህ በፊት ሴት ልጅ ወልዳ ገድላ ደሙን ጠጥታለች ሰይጣን አድሮባታልና በወፍና ከይሲ አምሳልም ይገለጣል በአገር ውስጥም ልጅ በሚወለድ ጊዜ ወደርሱ ወርዳ በሥራይም ገድላ ደሙን ትጠጣለች። ❤ ቅዱስ ሱስንዮስም ይህን በአየ ጊዜ ጦሩን አንስቶ ከልጅዋ ጋራ እኅቱን ገደላት ልጅዋ የሰይጣን ልጅ ነውና ሁለተኛም ሥራየኞች ሲሆኑ ባሏንና የባሏን አባቱን ገደላቸው እነርሱ በሥራያቸው ሰውን እያሳመሙ ይድላሉና። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ ኒቆድምያ ተመለሰ ወደዚያ ወደ አጠመቀው ቄስ ደርሶ ያደረገውን ሁሉ ነገረው። ወደ አገሩ አንጾኪያም በተመለሰም ጊዜ ከእርሱ የሆነውን አባቱ ሱሲ አወቀ መገደሉንም ወዶ ከንጉሥ ዘንድ ነገር ሠራበት። ያንጊዜም ቅዱስ ሱስንዮስ ወደ ጣዖታት ቤት ሒዶ ወደ ሲዖል ይወልዱ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዘዘቸው ያን ጊዜም ምድር አፋን ከፍታ ዋጠቻቸው። አባቱ ዳግመኛ በንጉሡ ዘንድ ከሰሰው ታላቅ ሥቃይም ያሰቃዩት ዘንድ ንጉሥ አዘዘ በብረት ዘንጎችም ደበደቡት፣ በመንኰራኵር አበራዩት፣ በመዶሻም ቀጥቅጠው ሁለተኛ ደግሞ እህል በሚያበራዩበት መሳርያ አበራዩት፣ ከዚያም በከተማ ውስጥ ጎተቱት የክብር ባለቤት ጌታችንም ያጸናውና በስቃዩም ውስጥ ያስታግሰዋል ከቊስሉም የሚፈውሰውን መልአኩንም ልኮ ያለምንም ጉዳት አነሳው ብዙ ሰዎችም አይተው በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በእርሱ ምክንያት ሰማዕት ሆኑ። ንጉሡም ከማሠቃየት በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለ። በሥቃዩም ወራት በሰማዕትነት የሞቱት ቊጥራቸው አንድ ሺህ አንድ መቶ ዘጠኝ ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሚያዝያ 26 ስንክሳር።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤          ❤ #ሚያዝያ ፳፭ (25) ቀን። ❤ እንኳን በጡቶቿ ደም ልጆቿን ላጠመቀች #ለቅድስት_ሣራና_ከሁለት+ልጆቿ ጋራ ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍት በዓላቸው እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡት፦ #ከባሕታዊ_አባ_በብኑዳ፣ ከተጋዳዩ #ቅዱስ_ቴዎድሮስ_ከአባ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳሳት በፋርስ መከራን ከመቶ ሰማዕታትና #ከዶራም ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                            ✝ ✝ ✝  ❤ #ቅድስት_ሣራና_ሁለት_ልጆቿ፦ ይቺም ቅድስት ከአንጾኪያ አገር ናት እርስዋም ከዲዮቅልጥያኖስ መኳንንት ለአንዱ ስሙ ስቅራጥስ ለሚባል ሚስቱ ናት እርሱም በፊት ክርስቲያን ነበረ በኋላ ንጉሡን በመፍራት ካደ እርስዋ ግን በክርስትናዋ ጸንታ ኖረች። ባልዋ ስቅራጥስም "እኔ የክርስቲያንን ሃይማኖት እወዳለሁ የንጉሡን ሥቃይ ከመፍራት በቀር ክርስቶስን በልቤ አልካድኩትም" ይላት ነበር። እንደዚህም ስትኖር ሁለት ልጆችንም ወለደች በአንጾኪያም አገር የክርስትና ጥምቀትን ልታስጠምቃቸው አልተቻላትም። አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተዋልና ጠፍተዋልምና ሰውን ወዳድ ክርስቶስን ብዙ ስለመውደዷ ልጆቿን ታስጠምቃቸው ዘንድ ታላቅ ተጋድ አደረች ወደ እስክንድርያ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጴጥሮስ ልትሔድ ወዳ አሽከሮቿን አስከትላ ሁለቱን ልጆቿን ይዛ በመርከብ ተሳፈረች። ❤ የክብር ባለቤት ጌታችንም የሃይማኖቷን ልዕልና ለመጪው ትውልድ ሊገልጥ ወዶ ያቺ መርከብ ለመሥጠም እስከምትደርስ በባሕር መካከል ጥልቅ ነፋስን አስነሣ። ይቺ ቅድስትም ልጆቿ ሳይጠመቁ እንዳይሞቱ ፈራች ተነሥታም ጸለየች ከዚያም ምላጭ አንሥታ ጡቷን የቀኙን በጣች ከደሟም ወስዳ ፊታቸውን በመስቀል ምልክት ቀባች በደረታቸውና በጀርባቸውም ላይ እንዲሁ አደረገች በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስም ስም በባሕሩ ውስጥ አጠመቀቻቸው ያን ጊዜም ታላቅ ጸጥታ ሆነ። ❤ ወደ እስክንድርያ አገርም በደረሰች ጊዜ ከአገር ልጆች ጋራ ያጠምቃቸው ዘንድ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጴጥሮስ ልጆቿን አቀረበች በዚያን ጊዜም ከአገር ልጆች አጠመቀ። ወደልጆቿም ደርሶ ሊአጠምቃቸው ወሰዳቸው ያን ጊዜ ውኃው ረጋ እነርሱን ትቶ ከአገር ልጆች አጠመቀ ውኃውም ተፈትቶ ወረደ ደግሞ ሊአጠምቃቸው ወደ ልጆቿ ተመለሰ አሁንም እንደቀድሞው ውኃው ረጋ እንዲሁም ሦስት ጊዜ አደረገ ውኃውም ይረጋል አደነቀ። እናታቸውን አቅርቦ ጠየቃት እርሷም የሆነውን "በባሕር መካከል ዐውሎ ነፋስ እንደተነሣባት ጡቷን በጥታ ደሟን እንደ ቀባቻቸውና በባሕር ውስጥ እንዳጠመቀቻቸው ነገረችው ስለ አደረገችውም በድፍረት በፊቱ ሰግዳ ይቅር ይላት ዘንድ ለመነችው"። አባ ጴጥሮስም " ሴትዮ አትፍሪ ሃይማኖትሽ ፍጹም ነው አንቺ በባሕር ውስጥ በአጠመቅሻቸው ጊዜ በመለኮታዊት እጁ ያጠመቃቸው ባለቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና አይዞሽ" አላት። ማጥመቁን በፈጸመ ጊዜ ሥጋውን ደሙን አቀበላቸው። ❤ ይቺም ቅድስት ወደ አንጾኪያ ቤቷ ተመለሰች። ባሏም በአያት ጊዜ ይህን በማድረጓ ተቆጥቶ ወደ ንጉሡ ሒዶ ከሰሳት ያደረገችውንም ነገረው። ንጉሡም ወደርሱ ያቀርቧት ዘንድ አዘዘ ስትቀርብም ወደ "እስክንድርያ ለምን ሔድሽ ከክርስቲያን ወገኖች ጋራ ልታመነዝሪ ነውን" አላት። እርሷም እንዲህ ብላ መለሰችለት "ክርስቲያኖች አያመነዝሩም እንደናንተ የረከሰ ጣዖትን አያመልኩም ከእንግዲህ ደግሞ ከእኔ ቃልን አትሰማም የወደድከውን አድርግ" ሁለተኛም "በእስክንድርያ ካንቺ የሆነውን ንገሪኝ ብሎ ጠየቃት ምንም ምን አልመለሰችለትም። ❤ ንጉሥ ከዲዮቅልጥያኖስም እጆቿን የኋሊት አሥረው ሁለቱን ልጆቿን በሆድዋ ላይ አድርገው ሦስቱንም በእሳት ያቃጥሉአቸው ዘንድ አዘዘ። ፊቷንም ወደ ምሥራቅ መልሳ ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ጸለየች ከዚያም ከልጆቿ ጋራ ሚያዝያ25 አቃጠሉዋት የድልና የሕይወት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ለዘላለም ይማረን አሜን። ምንጭ፦ የሚያዝያ 25 ስንክሳር።                            ✝ ✝ ✝     ❤ "#ሰላም_ለሣራ_እምሥርወ_ክርስቲያን_ሙላዳ። ብእሲሃ ዕልው ሶበ ዐውደ ምኵናን ወሰዳ። እምሰሚዐ ቃሉ ርኵስ ሶበ ኢትሠጥወቶ ለአግሪጳዳ። አዘዘ ያውዕይዋ ለእቶነ እሳት በነዳ። አንቢሮሙ በከርሣ ፪ተ ውሉዳ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሚያዝያ_25።                        ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወአምላክነሂ መስተሣህል። የዐቅብ ሕፃናት እግዚአብሔር። ተመንደብኩሂ ወአያድኃነኒ"። መዝ 114፥5-6። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 10፥12-22፣ 1ኛ ዮሐ 4፥4-18፣ የሐዋ ሥራ 8፥1-13። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 18፥1-8። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወይም የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የበዓለ ሃምሳ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።

#EOTC ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር)፣ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ (ዶ/ር) እና ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ለመገኘት እንዲችሉ መንግሥት የሚጠ
+3
#EOTC ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር)፣ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ (ዶ/ር) እና ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ለመገኘት እንዲችሉ መንግሥት የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግ አሳወቀ። መንግሥት ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ ፥ " ከዚህ በፊት አንዳንድ ወገኖች በፈጠሩት ችግር የተነሣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ጉባኤ ለመሳተፍ ላልቻሉ ሦስት አባቶች ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን አሳውቃለሁ " ብሏል። በመግለጫው ፤ ሀገራዊ ተቋማት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን የላቀ ሚና   በመረዳት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት እንዲፈታ የመሪነቱን ሚና መጫወቱን አስታውሷል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሀገር ግንባታ የነበራትንና የሚኖራትን ሚና በመገንዘብ አስፈላጊውን ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱን በዚህ አቋሙም እንደሚቀጥል ገልጿል። " ይሄንን ያልተረዱ አንዳንድ አካላት ችግሮችን ፈጥረው የነበረ ቢሆንም እንኳን፣ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያንዋ እና ለምእመንዋ ሲል በሆደ ሰፊነት ለማለፍ ወስኗል " ብሏል። መግለጫው " አንዳንድ አካላት " ያላቸውን እና የፈጠሩትን ችግሮች በግልጽ ያላብራራ ቢሆንም ችግሩ እንዲፈታ ሲኖዶሱ ጥያቄ ማቅረቡንና ይህንንም ጥያቄ መቀበሉን ይፋ አድርጓል። " በሂደቱም ተቀራርቦ መነጋገር ከሁሉም የተሻለ የመፍትሔ መንገድ መሆኑ ታይቷል " ብሏል። ሲኖዶሱ መንግሥት ነገሩን በሆደ ሰፊነት እንዲመለከተው እንደጠየቀና በዚህም ሶስቱ ብፁአን አባቶች ወደ ሀገራቸው ገብተው በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ለመገኘት እንዲችሉ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግ አሳውቋል።

✝️ #ቋሚ_ሲኖዶስ_የብፁዕ_አቡነ_ገብርኤል ጉዳይ ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ብፁዕነታቸው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በተአቅቦ እንዲቆዩ ውሳኔ አሳለፈ! ✝️ ቋሚ ሲኖዶስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ከቤተክርስቲያናችን የነገረ ማርያም አስተምህሮ ውጪ በፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማኅበር አዳራሽ የሰጡትን ትምህርትና በማኅበሩ ሚዲያ የተላለፈበትን ሁኔታ በተመለከተ #በዛሬው_ሚያዚያ_22_ቀን_2017 ዓ.ም መደበኛ ጉባኤው በሰፊው ተወያይቶ ለመወሰን በያዘው ቀጠሮ መሰረት በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቅ ውይይት ካደረገ በኋላ የሚከተሉትን ውሳኔዎችን አስተላልፏል። 1. ፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማህበር በተለያዩ ጊዜያት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውጪ በሚዲያው ያስተላለፈው የስሕተት ትምህርት የቤተክርስቲያናችንን አባቶች፣ሊቃውንቱንና መላው ሕዝበ ክርስቲያኑን ያሳዘነ በመሆኑ በማህበራት ምዝገባ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያ በኩል ጊዜያዊ የእገዳ ደብዳቤ እንዲደርሰው እና በመምሪያው በኩል አስፈላጊው ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ ሆኖ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ መስጠት ይቻል ዘንድ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ እንዲቋቋም አድርጓል። በዚህም መሰረት ቋማ ሲኖዶስ ያቋቋማቸው አጣሪ ልዑካን አጠቃላይ የማህበሩን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እና በሚዲያው ያስተላለፋቸውን የስህተት ትምህርቶች በተመለከተ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና ከማህበራት ምዝገባ፣ ቁጥጥርና ክትትል መምሪያ ጋር በመነጋገር በሚገባ መርምርውና አጣርተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከውሳኔ ሐሳብ ጋር ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲያቀርቡ፣ 2. ብፁዕ አቡነ ገብርኤል “ማርያም ቤዛዊተ ዓለም” አትባልም በማለት ከቤተ ክርስቲያናችን የነገረ ማርያም አስተምህሮ ውጪ የሰጡት ሕጸጽ ያለበት ትምህርት በሊቃውንት ጉባኤ በኩል በሚገባ ተመርምሮና ተጣርቶ ከመፍትሔ ሐሳብ ጋር ለቋሚ ሲኖዶስ በአስቸኳይ እንዲቀርብ ብፁዕነታቸውም ጉዳዩ ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በተአቅቦ እንዲቆዩ፣ 3. ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እና ብፁዕ አቡነ በርናባስ የደቡብ ካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ያስተላለፏቸው የስሕተት ትምህርቶችና በሌሎችም መምህራን የተላለፉ ነቀፋ ያለባቸው ትምህርቶች ካሉ የሊቃውንት ጉባኤ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ አንጻር በሚገባ መርምሮና አጣርቶ ከመፍትሔ ሐሳብ ጭምር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲያቀርብ፣ 4. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኝ ብዙኃን ስርጭት ድርጅት ለፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማህበር ሚዲያ የአየር ሰዓት የሰጠበትን ዝርዝር ሁኔታና ከማኅበሩ ጋር በተያያዘ አየር ላይ ያዋላቸውን ትምህርቶች የሚያሳይ ሪፖርት እንዲያቀርብ ይደረግ በማለት ቋሚ ሲኖዶስ ወስኖ የዕለቱን ጉባኤ በቅዱስነታቸው ጸሎተ ቡራኬ አጠናቋል። መረጃው፦ የሕዝብ ግንኙነት ነው።