ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ
Open in Telegram
ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።
Show more608
Subscribers
-124 hours
-47 days
-1230 days
Posts Archive
🌹 "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌹
🌹 #ጥቅምት ፳፭ (25) ቀን።
🌹 እንኳን #ለኢትዮጵያ_ጻድቅ_ለአቡነ_ተክለ_ሃይማኖት_ለአጎት_ልጅ ለታላቁ አባት ከበሬ ጋር ተጠምደው ሰማዕትነትን ለተቀበሉት #ለአቡነ_ሕፃን_ሞዐ_ቃል_ኪዳን_ለተቀበሉባት ለመታሰቢያ በዓላቸው እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
🌹 #አቡነ_ሕፃን_ሞዐ፡- በአባታቸው አርከሌድስ እናታቸው ትቤ ጽዮን ይባላሉ፡፡ የተወለዱት ጥር 25 ነው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ እና ከእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር የሥጋ ዝምድና አላቸው፡፡ ይኸውም አባታቸው አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ወንድማማቾቸ ናቸው፡፡ አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ሌሎች ሌሎች አራት ወንድሞች አሏቸው፡፡
🌹 እነርሱም እንድርያስ፣ ዘርዐ አብርሃም፣ ቀሲስ ዮናስ እና ቀሲስ ዮሐንስ ናቸው፡፡ አርከሌድስ ሕፃን ሞዐን ይወልዳል፣ ጸጋ ዘአብ ተክለ ሃይማኖትን ይወልዳል፣ እንድርያስ ሳሙኤል ዘወገግን፣ዘርዐ አብርሃም ታላቁ አኖሬዎዮስን፣ ቀሲስ ዮናስ ገላውዲዮስንና የፈጠጋሩን ማትያስን፣ እና ቀሲስ ዮሐንስ ዜና ማርቆስን ይወልዳሉ፡፡ እነዚህ የከበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን በእናታቸውም ወገን ቢሆን እንዲሁ በዝምድና የተቆራኙ ናቸው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ በሌላኛው ስማቸው ሕፃን ዘደብረ በግዕ ተብለውም ይጠራሉ፡፡ ይኸውም የደብረ በግዕን ገዳም የመሠረቱት እርሳቸው ስለሆኑ ነው፡፡
🌹 ከአራባ ሰባቱ የአገራችን ቀደምት ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ በመንዝና በተጉለት የሚገኙ ታላላቅ ገዳማትን አብዛኞቹን የመሠረቷቸው አቡነ ሕፃን ሞዐ ናቸው፡፡ ጻድቁ በክፉዎች ወሬና ሴራ ምክንያት ከበሬ ጋር ተጠምደው ሰማዕትነት የተቀበሉ አባት ናቸው፡፡ ከበሬ ጋር ሲታረሱ ውለው በእጅጉ ከደከማቸ በኋላ በኃይል የተነፈሱባት ምድሪቱ ዛሬም ድረስ ልክ እንደሰው የሚሞቅ ትንፋሽ ታወጣለች፡፡ ያም በጻድቁ እስትንፋስ አምሳል ከመሬት ውስጥ የሚወጣው እስትንፋስ ለአስም በሽታ መድኃኒት ሆኖ ብዙዎችን እየፈወ ነው፡፡ ገዳማቸው ከደብረ ብርሃን ከተማ በእግር የሁለት ሰዓት መንገድ ርቀት ይገኛል፡፡ ይኸውም ከወንይዬ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አጠገብ ነው፡፡ ጻድቁ ጥር 25 ቀን ልደታቸው፣ ጥቅምት 25 ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ዕለት ሲሆን ሐምሌ 25 ደግሞ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ምንጭ፦ ከገድላት አንደበት።
ጥቅምት ፳፫ /23/በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ኀምሳ ሁለተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ አረፈ። ይህም አባት ከመኑፍ አገር ከታላላቆች ተወላጆች ወገን ነው ወላጆቹም ብዙ ገንዘብ ያላቸው ነበሩ ታናሽም ሁኖ ሳለ አባትና እናቱ ትተውት ሲሞቱ ድኃ አደግ ሆነ አንድ እግዚአብሔርንም የሚወድ ሰው አሳደገው። አድጎ በጐለመሰም ጊዜ የወላጆቹን ገንዘብ ሁሉንም ወስዶ ለድኆችና ለምስኪኖች መጸወተ ከዚህም በኋላ ወደ አስቄጥስ ገዳም ወጥቶ ከአንድ ጻድቅ ሽማግሌ ሰው አባት ዘንድ መነኰሰ በበጎ ገድል ሁሉ እየተጋደለ ኖረ። ይህም ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሴፍ መናፍቃንን የሚገሥጻቸው ሆነ ሕዝቡንም ከአባቶቻቸው፤ በተቀበሏት በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ አስተማራቸው ከቅዱሳት መጻሕፍትም ለእነርሱም ሥውር የሆነውን ተርጕሞ ያስረዳቸዋል ያስገነዝባቸዋልም በትምህርቱና በጸሎቱም እንዲህ ጠበቃቸው ጌታችንም በእጆቹ ብዙዎች ተአምራትን አደረገ ያማረች ገድሉንም ፈጽሞ እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላም በፍቅር አረፈ። መላ የሕይወቱም ዘመን ሰባ ስምንት ነው ከምንኵስና በፊት ሃያ ዓመት በምንኵስና ተጋድሎ ሠላሳ ዘጠኝ ዓመት በሊቀ ጵጵስና ሹመት ዓሥራ ዘጠኝ ዓመት ኖረ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ:- መጽሐፈ ስንክሳር
#ጥቅምት_22
#ቅዱስ_ሉቃስ_ወንጌላዊ
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ ሁለት በዚህች ቀን ብልህ ጥበበኛ የሆነ ቅዱስ ወንጌላዊ ሉቃስ በሰማዕትነት አረፈ።
በሀገረ አንጾኪያ ከአሕዛብ ወገን የተለወደው አይሁዳዊው ሉቃስ ከሰባ ሁለቱ አርድእት የተቆጠረ ባለ መድኃኒትና ወንጌልን የጻፈ ቅዱስ ሐዋርያ ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በወንጌል ትርጓሜያቸው ስሙ ‹ዓቃቤ ሥራይ› ወይም ‹ባለ መድኃኒት› የሚል ትርጉም በውስጡ የያዘ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በላቲን ቋንቋ ‹ሉካስ› ማለት ‹ብርሃናማ፣ ብርሃን የያዘ› ማለት ነው፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር ደግሞ ብልህና ጥበበኛ በማለት ይገልጸዋል፡፡
ቅዱስ ሉቃስ የሚመሰለው በገጸ ላህም ነው፡፡ ‹‹ፍሪዳ አምጡና እረዱ፤ ከእርሱ ጋር እየበላን ደስ ይበለን›› እያለ ምሳሌውን ይጽፋልና፡፡ (ሉቃ.፲፭፥፳፫) በጤግሮስም ወንዝ ይመሰላል፤ ጤግሮስ ፈለገ መዓር ወይም የመዓር ወንዝ ነው፤ ርስትነቱም ጸዊረ ነገር (ምሥጢር መሸከም) የሚቻላቸው ሰዎች ርስት ነው፡፡
ቅዱስ ሉቃስ በአቴና ሀገር በእስክንድሪያ ሕክምናን አጥንቷል፤ የሥነ ሥዕልም ችሎታ ነበረው፤ ይህን የሥዕል ችሎታውንም በወንጌሉና በሐዋርያት ሥራ መጻሕፍቱ ላይ በሥዕላዊ መልክ ገልጾታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደሚናገረው እመቤታችን #ቅድስት_ድንግል_ማርያም ልጇን አቅፋ (ምስለ ፍቁር ወልዳ) ለመጀመርያ ጊዜ የሣለው እርሱ ነው፡፡ ሥዕሎቹም በኢትዮጵያ በተድባባ ማርያም፣ በደብረ ዘመዶ፣ በዋሸራና በጀብላ ይገኛሉ፡፡ ተመሳሳዩም በስፔን ቅድስት #ማርያም ካቴድራል እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በሰዓታት ምስጋናው ‹‹ከወንጌላውያን አንዱ የሆነው ጠቢቡ ሉቃስ ለሣላት ሥዕልሽ ሰላምታ ይገባል›› በማለት አመስግኗል፡፡
ቅዱስ ሉቃስ #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ከመረጠው በኋላ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር በመሆን አገልግሏል፡፡ ቀድሞ ዓቃቤ ሥራይ ዘሥጋ (ሥጋዊ ሐኪም) ቢሆንም በኋላ ግን ዓቃቤ ሥራይ ዘነፍስ (መንፈሳዊ ሐኪም) እንደሆነ ሊቃውንቱ ይናገራሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እርሱ ሲመሰክር ‹‹የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል›› በማለት ገልጦታል፡፡ (ቆላ.፬፥፲፬) ቅዱስ ሉቃስ ተንሣኢ (ፈጣን) እየተባለም የሚጠራው ለስብከተ ወንጌል ስለሚፋጠን ነበር፤ በወንጌሉም አጻጻፍ ላይ ስለ ሕመማቸውና ድኅነት ስለሚያገኙበት ሁኔታ ገልጦ ጽፏል፤ ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑት ታሪኮች የደጉ ሳሚራዊና ደም ይፈሳት ስለነበረችው ሴት ናቸው፡፡ (ሉቃ.፲፥፴‐፴፭፤፰፥፵፫) ሐዋርያው መበሥር ወይም ብሥራት ነጋሪ እየተባለም ይጠራል፤ ይህም ብሥራተ መልአክን ጽፏልና ነው፡፡ (ሉቃ.፩፥፩)
የቅዱስ ሉቃስ ወንጌል የተጻፈው በሀገር አኪይያ (ሮም) በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ነው፤ የሉቃስ ወንጌል ‹የአሕዛብ ወንጌል›፣ ‹ሰባኬ መንፈስ ቅዱስ›፣ ‹ሰባኬ ጸሎት›፣ ወንጌለ አንስት ተብሎም ይጠራል፡፡
፩. ‹የአሕዛብ ወንጌል› እየተባለ የሚጠራው ወንጌሉ የተጻፈው ለአሕዛብ በመሆኑ ነው፡፡
፪. ሰባኬ #መንፈስ_ቅዱስ የሚባለው ስለ #መንፈስ_ቅዱስ ደጋግሞ ስለሚናገር ነው፡፡
፫. ሰባኬ ጸሎት የተባለው ከሌሎች ወንጌላት የበለጠ ደጋግሞ የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን እና እመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያምን ጸሎት ጽፏልና ነው፡፡
፬. ወንጌለ አንስት የሚባለው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያም፣ ስለ ቅድስት ኤልሳቤጥ፣ ስለ ማርያም እንተ እፍረት፣ ስለ ናይን እና ወዘተ በስፋት ስለሚናገር ነው፡፡
ወንጌሉን ከመጻፉ አስቀድሞም ቅዱስ ሉቃስ የቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር እንደነበረ ትርጓሜ ወንጌል ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በአንጾኪያ ሀገር ቅዱስ ጳውሎስን ካገኘው በኋላም ሊቀ ሐዋርያው ሰማዕት እስከሆነበት ድረስ አገልግሎታል፡፡ ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ጋርም በነበረበት ጊዜም መቄዶንያ የምትባል ሀገር ከፍሎ እንዲስተምር እንደሰጠው በወንጌል ትርጓሜ ተገልዿል፡፡ ቅዱስ ሉቃስም በዚያ ሀገር ከ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ መፀነስ ጀምሮ፣ መዋዕለ ስብከቱን፣ የሠራውን ትሩፋትና ገቢረ ተአምሩን በሙሉ ለአሕዛቡ በነገራቸው ጊዜ ከኃጢያት ወደ ጽድቅ፣ ከአምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮ #እግዚአብሔር ተመለሰው በማመን የክርስትና ጥምቀት ተጠምቀዋል፡፡ ለስብከት በሚጓዝበትም ወቅት ትምህርት ባልተዳረሰባቸው ስፍራ ሲያስተምር አንድ ታዖፊላ የተባለ የእስክንድርያ መኮንን ስብከቱን አድምጦ በማመን ‹ዜና ሐዋርያትን› (ገድለ ሐዋርያትን) እንዲጽፍለት በጠየቀው መሠረት ጽፎለታል፡፡ በዚህም ቅዱስ ሉቃስ የጻፋቸው መጻሕፍት ከወንጌሉና ከሐዋርያት ሥራ ጋር ሦስት ናቸው፡፡
ቅዱስ ሉቃስ የሕይወት ታሪኩ እንደሚገለጸው በድንግልና የኖረ ሐዋርያ ነው፤ ሐዋርያዊ አገልግሎቱንም የፈጸመው በአብዛኛው በግሪክ ነበር፡፡ ሐዋርያቱ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ካረፉ በኋላም በሮም ሀገር ማስተምር ቀጠለ፤ በቀናች ሃይማኖትም ይጸኑ ዘንድ ለምእመናን መልእክትን ይጽፍ ነበር፤ ስለዚህም ጣዖት አምላኪዎች ከአይሁድ ጋር በመስማማት በአንድ ምክር ሆነው በንጉሥ ኔሮን ፊት በመቆም ስለ ሐዋርያው ሉቃስ እንዲህ ብለው ተናገሩ፤ ‹‹ይህ ሉቃስ በሥራይ ብዙ ሰዎችን ወደ ትምህርቱ አስገባቸው፡፡›› ንጉሥ ኔሮንም ወደ ፍርድ ዐደባባይ ሉቃስን እንዲያቀርቡት ባዘዘ ጊዜ ሐዋርያው ሉቃስ ዕረፍቱ እንደ ደረሰ በ #መንፈስ_ቅዱስ ዐውቆ ወደ ባሕር ዳርቻ ሄደ፡፡ በዚያም ዓሣ የሚያጠምድ አንድ ሽማግሌ ሰው አግኝቶ መጻሕፍቱንና ደብዳቤዎችን እንደሰጠውና ‹‹ወደ #እግዚአብሔር መንገድ መርተው ያደርሱሀልና እነዚህን መጻሕፍት ጠብቃቸው›› በማለት እንደገነገረው መጽሐፈ ስንክሳር ይጠቅሳል፡፡
ከዚህም በኋላ በንጉሥ ኔሮን ፊትም ቀርቦ በቆመ ጊዜ ንጉሡ ‹‹በሥራይህ ሕዝቡን የምታስት እስከ መቼ ነው?›› ብሎ ጠየቀው፤ ቅዱስ ሉቃስም ‹‹እኔ ለሕያው #እግዚአብሔር ልጅ ለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሐዋርያ ነኝ እንጂ ሥራየኛ አይደለሁም›› ብሎ መለሰለት፡፡ ንጉሥ ኔሮንም ሁለተኛ እንዲህ አለው፤ ‹‹እየጻፈች ሰዎችን የምታስት ይህች እጅህን እኔ እቆርጣታለሁ፤›› ይህንንም ብሎ የቀኝ እጁን እንዲቆርጡት አዘዘ፡፡ በቆረጡትም ጊዜ ‹‹ንጉሥ ሆይ እኛ የዚህን ዓለም ሞት እንደማንፈራ ዕወቅ፤ ነገር ግን የ #ጌታዬና የፈጣሪዬን ኃይሉን ታውቅ ዘንድ አሳይሃለሁ፤›› ይህንንም ብሎ የተቆረጠች የቀኝ እጁን በግራ እጁ አንሥቶ ከተቆረጠችበት ቦታዋ ላይ አገናኝቶ እንደ ቀድሞዋ ደኅነኛ አደረጋት፤ ከዚህም በኋላ ለያት፤ በዚያም የነበሩ አደነቁ፤ የሠራዊቱም አለቃና ሚስቱ ብዙዎችም ሰዎች ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ፤ ቁጥራቸውም ዐራት መቶ ሰባ ሰባት ነፍስ ሆነ፡፡ ንጉሡም ከቅዱስ ሉቃስ ጋር ራሶቻቸውን እንዲቆርጡ በማዘዙ ቆረጡአቸው፤ የምስክርነት አክሊልም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ያረፈው በ፹፬ ዓመቱ ነው፡፡
ከዚህም በኋላ ሥጋውን በማቅ አይበት ውስጥ አድርገው ወደ ባሕር ጣሉት፡፡ በ #እግዚአብሔር ፈቃድ ወደ አንድ ደሴት ደረሰ ምእመናንም አግኝተው ወስደው ገነዙት፤ በአማረ ቦታም አኖሩት፡፡
#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ አማላጅነት፣ ተረዳኢነትና በረከት አይለየን፤ አሜን!
(ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥቅምት_22)
🌹 አባ ማርቆስም ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥ ስለሚላኩ ሰዎች ከመኳንንቱ ከኤጲስ ቆጶሳቱና ከሀገር ታላላቆች ሽማግሌዎች ጋር ተማክሮ እሊህን ብሩሀን ከዋክብት የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስን የምስር ኤጲስቆጶስ አባ ሳዊሮስን በእውቀታቸው በአስተዋይነታቸውና በቅድስናቸው መረጡአቸው ወደ ኢትዮጵያ ንጉሥም ይሔዱ ዘንድ ግድ አሏቸው።
🌹 እነርሱም ታዛዦች ሁነው ወደ ኢትዮጵያ መጡ የኢትዮጵያ ንጉሥም መምጣታቸውን በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው እሊህንም ቅዱሳን አባቶች ይቀበሏቸው ዘንድ አሽከሮቹን በቅሎዎችን አስይዞ ላከ በመጡም ጊዜ በታላቅ ደስታ ሰላምታ አቀረበላቸው ከእርሳቸውም ቡራኬን ተቀበለ ታላቅ ክብርንም አከበራቸው ። እነርሱም የሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስን ደብዳቤ ሰጡት እርሱም ተቀብሎ አንብቦ ለሊቀ ጳጳሳቱ ቃል ታዛዥ መሆኑን ገለጠላቸው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶቻችን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጥቅምት 21 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
🌹 "#ሰላም_ለኪ_ገነተ_ሚዓ_ወሰሊክ። ዘኢያይበሰኪ ነፋሰ መርቄ ወደደክ። እማእሠረ ጌጋይ ፍትሐኒ #ወላዲተ_ክርስቶስ_አምላክ። እምነ ሙቃሔ ጽኑዕ ወእማእሠር ድሩክ። ከመ ፈታሕኪዮ ዮም ለማትያስ ላእክ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የጥቅምት_21።
✝ ✝ ✝
🌹 #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት። ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ"። መዝ44፥9-10 ወይም 104፥14-15። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥39-57 ወይም ዮሐ 11፥38-46።
✝ ✝ ✝
🌹 #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ወገሠፀ ነገሥተ በእንቲአሆሙ። ወኢትግሥሡ መሲሐንየ። ወኢታሕስሙ ዲበ ነቢያትየ"። መዝ 104፥14-15። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 10፥9-17፣ 2ኛ ዮሐ 1፥5-8 እና የሐዋ ሥራ 2፥14-22። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ11፥38-46። የሚቀደሰው፡ቅዳሴ፡የቅዱስ፡ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ወይም የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የመታሰቢያ በዓል፤ የነቢዩ የቅዱስ ኢዩኤል የዕረፍት በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
🌹 "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌹
🌹 #ጥቅምት ፳፩ (21) ቀን።
🌹 እንኳን #ለእመቤታችን_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም ተአምራት አድርጋ #ሐዋርያው_ቅዱስ_ማትያስን ከእስራት ቤት ላአዳነችበት በዓል፣ ለነቢዩ #ቅዱስ_ኢዩኤል ለዕረፍት በዓል፣ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ላስነሣው #ለቅዱስ_አልዓዛር_ሥጋው_ከቆጵሮስ_አገር ወደ #ቊስጥንጥንያ_ለፈለሰበት፣ እግዚአብሔር በሚወድ #የንጉሥ_ሰይፈ_አርዕድ_ደግሞ_ቈስጠንጢኖስ ለሚባል ልጁ በሆነ #በንጉሣችን_በዳዊት ዘመን ለዐረፈው ለከበረች አገር #ኢየሩሳሌም_ሊቀ_ጳጳሳት ለሆነ ለቅዱስ አባት #ለአባ_ዮሐንስ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚችን ቀን ከምትታሰበው፦ አምላክ ከወለደች #ከእመቤታች_ከቅድስት_ድንግል_ማርያም ከወራዊ በዓሏ መታሰቢ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
🌹 #እመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም ተአምራት አድርጋ ደቀ #መዝሙር_ቅዱስ_ማትያስን ከእሥራት ቤት እንዳዳነች፦ የከበሩ ቅዱሳን ወንጌልን በዓለም ዞረው ይሰብኩ ዘንድ ዕጣ ሲጣጣሉ ለቅዱስ ማትያስ ዕጣ የደረሰው ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች አገር ነበር፡፡ ይህችም ሀገር እስኩቴስ የተባለች ሩሲያ እንደሆነች የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
🌹 ማትያስም እነዚህ ሰውን የሚበሉ ሰዎች አገራቸው እንደደረሰ ዐይኑን አውልቀው አሠሩት፡፡ ምግባቸውም የመጻተኛ ሰው ሥጋ ነው፡፡ በልማዳቸው መሠረት መጻተኛን ሰው ገና እንደያዙት ዐይኖቹን ዐውልቀው በእሥር ቤት ያኖሩታል፡፡ እስከ 30 ቀንም ድረስ ሳር እያበሉ ያስቀምጡትና በ30ኛው ቀን አውጥተው አርደው ይበሉታል፡፡
🌹 ሐዋርያው ማትያስንም በልማዳቸው መሠረት ዐይኖቹን አውልቀው አሠሩት፡፡ ሐዋርያውም በእሥር ቤት ሆኖ በዚያ ላይ ዐይኖቹን ታውሮ ሳለ በጭንቅ ወደ ጌታችንና ወደ እመቤታችን ይለምን ነበር፡፡ ነገር ግን እመብርሃንና ልጇ መድኃኔዓለም 30ኛው ቀን ሳይፈጸም ሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስን ወደ እርሱ ላኩለት፡፡ ማትያስም ዐይኑን ፈወሱለትና ማየት ቻለ፡፡
🌹 ሐዋርያውቅዱስ እንድርያስም በተዘጋው በር በተአምራት ገብቶ አሥርቤቱ ውስጥ ያሉ እሥረኞችን በስውር አውጥቶ ከከተማው ውጭ ካስቀመጣቸው በኋላ ሁለቱ ሐዋርያት ተመልሰው ሰውን ለሚበሉት ሰዎች ተገለጡላቸው፡፡ እነርሱም ይዘው በአንገታቸው ገመድ አግብተው ለሦስት ቀን በሀገራቸው ጎዳናዎች ላይ ሁሉ ጎተቱዋቸው፡፡ ሁለቱም ሐዋርያት በጸሎታቸው ከእሥር ቤቱ ምሰሶ ሥር ውኃ አፈለቁና ውኃው ሀገራቸውን ሁሉ እስኪያጥለቀልቅና ሰዎቹንም እስከ አንገታቸው ድረስ እስከሚደርስ ሞላ፡፡ ሁሉም በተጨነቁ ጊዜ ሁለቱ ሐዋርያት በፊታቸው ተገለጡና "በጌታችን እመኑ ትድናላችሁ" በማለት ወንጌልን ሰብከውላቸው አሳመኗቸው፡፡ ምሥጢራትንም ሁሉ ገለጡላቸው፡፡
🌹 ደግሞም የአራዊት ጠባይን ከሰዎቹ ያርቅላቸው ዘንድ ወደ ጌታችንና ወደ ተወደደች እናቱ ከጸለዩ በኋላ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው፡፡ ያ የአውሬነት ጠባያቸውም ጠፍቶላቸው የዋህ፣ ቅንና ሩኅሩኆቸ ሆኑ፡፡ ሐዋርያትም ሃይማኖትን እያስተማሯቸው 30 ቀን አብረዋቸው ከተቀመጡ በኋላ አገልጋይ ኤጲስ ቆጶሳትን፣ ካህናትንና ዲያቆናትን ሾመውላቸው ወደ ሌላ ሀገር ሄዱ፡፡ ለሐዋርያት ሞገሳቸው ጣዕመ ስብከታቸው የኾነች ክብርት እመቤታችን ለእኛም ትለመነን!።
✝ ✝ ✝
🌹 #ነቢይ_ቅዱስ_ኢዩኤል፦ ይህም የእስራኤልን ልጆች የሚያስተምርና የሚገሥጻቸው ነበር ስለ ክርስቶስም በኢየሩሳሌም መኖርና ማስተማር ትንቢት ተናገረ። ደግሞም ስለ መከራው በሐዋርያትና በሰባ ሁለቱ አርድእት በሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ላይ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ እንዲህ ሲል ተናገረ። "ከዚህ በኋላ በሥጋዊ በደማዊ ሰው ሁሉ ከመንፈሴ አሳድርበታለሁ ሴቶች ልጆቻችሁና ወንዶች ልጆቻችሁ ትንቢትን ይናገራሉ አለቆቻችሁ ሕልምን ያልማሉ ጎልማሶቻችሁም ራእይን ያያሉ"።
🌹 ሁለተኛም እንዲህ አለ "ያን ጊዜ ከተራራው ማር ከኮረብታውም ወተት ይፈሳል በቤተ እግዚአብሔር አጠገብ ካሉ ከይሁዳ አገሮች ሁሉ ምንጩ ከላይ ወደታች ይፈሳል"።
🌹 ሙታን በሚነሡ ጊዜ ስለሚሆነው የፍርድ ሰዓት እንዲህ አለ "ፀሐይና ጨረቃ ይጨልማሉ የከዋክብትም ብርሃናቸው ይጠፋል"። የትንቢቱንም ወራት አድርሶ እግዚአብሔርንም አገልግሎ ጥቅምት 21 በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በነቢዩ ቅዱስ ኢዩኤል ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
🌹 #ቅዱስ_አልዓዛር_ሥጋ_ከቆጵሮስ_አገር_ወደ #ቊስጥንጥንያ_መፍለስ፦ ከክርስቲያን ነገሥታትም አንዱ ሥጋው በቆጵሮስ እንዳለ በሰማ ጊዜ ከቆጵሮስ ደሴት ወደ ቊስጥንጥንያ አፈለሰው። ሊአፈልሱትም በወደዱ ጊዜ በከበረ የደንጊያ ሣጥን ውስጥ ሁኖ በምድር ውስጥ ተቀብሮ አገኙት በላዩም እንዲህ የሚል ጽሑፍ ነበረ "ይህ በመቃብር ውስጥ አራት ቀን ከኖረ በኋላ ከሙታን ለይቶ ላስነሣው ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጁ የሆነ የቅዱስ አልዓዛር ሥጋ ነው"።
🌹 ይህንንም በአዩ ጊዜ ደስ ተሰኙበት ተሸክመውም ወደ ቊስጥንጥንያ አገር ወሰዱት ካህናቱም ሁሉ ወጥተው በታላቅ ክብር በመዘመርና በማመስገን ተቀበሉት በአማረ ቦታም አኖሩት በዚችም ቀን በዓልን አደረጉለት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አልዓዛር ጸሎት ይማረን።
✝ ✝ ✝
🌹 #ኢየሩሳሌም_ሊቀ_አገር_ጳጳሳት_አባ_ዮሐንስ፦ ይህም አባት ያረፈው እግዚአብሔርን በሚወድ የንጉሥ ሰይፈ አርዕድ ደግሞ ቈስጠንጢኖስ ለሚባል ልጁ በሆነ በንጉሣችን በዳዊት ዘመን ነው።
✝ ይህም ቅዱስ ከምስር አገር ታላላቆች እግዚአብሔርን የሚፈሩ የክርስቲያኖች አባቶች ልጅ ነው። የዲቁና መዓረግንም ለመሾም እስከ ተገባው ድረስ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያስተማሩ በበጎ አስተዳደግ አሳደጉት። ከዚህም በኋላ በዲቁናው ሹመት አገልግሎቱን በአሳመረ ጊዜ የቅስና መዓረግ የሚገባው ሁኖ ቅስና ተሾመ።
🌹 በጾም በጸሎት እግዚአብሔርንም በመፍራት የተጠመደ ሁኖ ድኆችንና ችግረኞችን የሚወዳቸው የሚረዳቸው ሆነ ያን ጊዜ የሐዋርያት የሆነች የጵጵስና ሹመት የምትገባው ሁና በከበረች አገር በኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ፈቃድ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ ሕዝቡንም በፈሪሀ እግዚአብሔርና በትሕትና የሚያስተምራቸው ሆነ።
🌹 እነርሱም ስለ ቅድስናው እጅግ የሚወዱት ሆኑ መልኩና የአንደበቱ አገላለጥ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ያማረ ነበር። በሹመቱም ጥቂት ዘመናት ከኖረ በኋላ ከመንበረ ሢመቱ እስከ አራቀው ድረስ በላዩ ሰይጣን ምክንያትን አመጣ።
🌹 ይህም እንዲህ ነው በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በአባ ማርቆስ ዘመን በግዛቱ ውስጥ ያሉ እስላሞች ስለ ዐመፁበት የኢትዮጵያ ንጉሥ ፈጅቷቸው ነበርና ስለዚህ በግዛቱ ውስጥ በሚኖሩ እስላሞች ላይ ክፉ እንዳያደርግ ለኢትዮጵያ ንጉሥ መልእክት እንዲልክ ሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስን የምስር ንጉሥ አዘዘው።
ጥቅምት ፳ /20/ዳግመኛም በዚህች ቀን የስሙ ትርጓሜ ጠባቂና አዳኝ የሆነ የታላቅ ነቢይ የኤልሳዕ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። እርሱም አሜሁላ ከሚባል አገር ከይሳኮር ነገድ ነው ብዙ ትንቢትን ተናግሮአል ብዙ ተአምራትንም አድርጓል። የኢያሪኮም ሰዎች ኤልሳዕን "ጌታችን እንደምታያት የዚች አገር ኑሮዋ ያማረ የተወደደ ነው የአገሩ ውኃ ግን ክፉ ነው ሴቶች ሲጠጡት ይመክናሉ አሉት" ኤልሳዕም ጨው ጨምራችሁ አዲስ ሸክላ አምጡልኝ አላቸው እነርሱም አመጡለት ። ኤልሳዕም ወደ ውኃው ምንጭ ሒዶ ያንን ጨው በውስጡ ጨመረውና እግዚአብሔር እንዲህ አለ "እርሱን ከመጠጣት የተነሣ የሚሞት እንዳይኖር የሚመክንም እንዳይኖር ይህን ውኃ ለውጥኩት" አለ አላቸው። ከዚያችም ቀን በኋላ ኤልሳዕ እንደተናገረ እስከ አሁን ድረስ ያ ውኃ ተለወጠ። የዚህ የነቢይ ኤልሳዕ ተአምራቱ ብዙ ነው የሶርያውን ሰው ንዕማንን ከለምጹ ያነጻው እርሱ ነው ሁለት ሙታንን አንዱን በሕይወት ሳለ ሌላውንም ከሞተ በኋላ አስነሥቷል። በኋላም የትንቢቱን ወራት ፈጽሞ በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር
✞ ስንክሳር ጥቅምት 19 ✞
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞
✞✞✞ ጥቅምት 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞✞✞
+" ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ንጉሥ "+
✞✞✞ የሰው ልጅ 'ንጉሥ' ተብሎ 'ቅዱስ' መባል ግን ምን ይደንቅ?! ይህ ታላቅ ኢትዮዽያዊ መሪ ንጉሥ ሲሆን: እንደ ደናግል ድንግል: እንደ ባሕታውያን ገዳማዊ: እንደ ቀስውስት ካህን: እንደ ሐዋርያት ሰባኪ ሆኖ መገኘቱ ይደንቃል::
+የሚያሳዝነው ይህንን እንቁ ንጉሣችን ብዙ ኢትዮዽያውያን መዘንጋታችን ብቻ ነው:: የላስታ አካባቢ እጅግ የታደለችና የተቀደሰች ናት:: እንደ ሌሎቹ የሃገራችን ክፍሎች ሁሉ እሷም መካነ ቅዱሳን ናትና::
+ቅዱስ ይምርሐ የዘር ሐረጉ ከዛግዌ ነገሥታት ሥር ሲሆን አባቱ ግርማ ስዩም ይባላል:: ይኸውም በመጀመሪያው ሺህ ዓመት (Millenium) መጠናቀቂያ ላይ ነግሶ የነበረ ነው:: ዣን ስዩም
(የላሊበላ አባት): ጠጠውድም (ንጉሡ) እና ግርማ ስዩም ወንድማማቾች ናቸው::
+ቅዱሱ ሲወለድ አባቱ በሕይወት አልነበረም:: እናቱና የወቅቱ አባቶች "ይምርሐነ ክርስቶስ-ክርስቶስ ይምራን" አሉት:: ገና ከሕጻንነቱ መንፈስ ቅዱስ አድሮበታልና ረቡዕና ዓርብ ቀን እስከ 9 ሰዓት ድረስ የእናቱን ጡት አይቀምስም ነበር:: እናቱ ግን ባለመረዳት ትጨነቅ ነበር::
+የወቅቱ ንጉሥ ጠጠውድም "ከእኔ ቀጥሎ የሚነግሠውን ባወኩት" እያለ ሲመኝ በሕልሙ "ሕጻኑ ይምርሐ ነው" የሚል በማየቱ ሕጻኑን አስመጣው:: ከደም ግባቱ የተነሳም ቅንዓት አድሮበት አማካሪዎቹን "ምን ላድርገው?" አላቸው::
+እነርሱም "ብትገድለው እግዚአብሔር በደሙ ይጠይቅሃል:: ግን እንዳይወርስብህ ከፈለክ እረኛ አድርገው" አሉት:: (የዋሃን! ቅዱስ ዳዊት ከእረኝነት መጠራቱን ዘንግተውታል) ከ7 ቀናት በኋላ ግን መጥተው "ንጉሥ ሆይ! ፈጣሪ ካለ የሚቀር ነገር የለምና በቃ ዝም ብለህ ግደለው" አሉት::
+በዚያች ሰዓት ቅዱስ ሩፋኤል ከሰማይ ወርዶ እናቱን "ይምርሐን ስጭኝ" አላት:: እናት ናትና ጨነቃት:: መልአኩ ግን እንደሚጠብቀው ቃል ገብቶላት ከላስታ ነጥቆ ኢየሩሳሌም አደረሰው::
+ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስም ለዓመታት ተምሮ ዲቁናን ተቀበለ:: በኢየሩሳሌም አካባቢም በጾምና በጸሎት ተወስኖ ፈጣሪውን እያገለገለና ወንጌልን እየሰበከ የወጣትነት እድሜውን ገፋ::
+አንድ ቀን ግን መድኃኒታችን ተገልጦ "ወዳጄ ይምርሐ! ሚስት አግብተሀ: ቅስና ተቀብለህ አገልግለኝ" አለው:: ቅዱሱ ይህንን ሲሰማ አዝኖ "ጌታየ! የእኔስ ፈቃዴ በድንግልና አገለግልህ ዘንድ ነው" አለው:: ጌታችንም "ግዴለህም! ሁሉም አይቀርብህም" ብሎ አንዲት ሕዝባ የምትባል ደግ እሥራኤላዊት ጠቆመው::
+ቅዱስ ይምርሐም ቅድስት ሕዝባን በተክሊል አግብቶ: ቅስናን ተቀበለ:: ግሩም የሚያሰኘው ግን 2ቱ ቅዱሳን ከ40 ዓመታት በላይ በትዳርም: በድንግልናም መኖራቸው ነው:: "ለሚያምን ሁሉ ይቻላል" ይል የለ ቅዱስ መጽሐፍ!
+ቅዱሳኑ ወዲያው ለአገልግሎት ወደ ግብጽ ወረዱ:: በዚያ ለጥቂት ዓመታት እንደቆዩ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ወደ ኢትይዽያ መመለስ ፈለገ:: አንድ ቀን ሕዝቡ ተሰብስበው ጸሎተ ኪዳንን ሲመራ "እግዚአብሔር አብ ወሐቤ ብርሃን-ብርሃንን የምትሰጥ እግዚአብሔር አብ" ከሚል ሲደርስ ወደ ሰማይጮኸ::
+ከሰማይም "አቤት ልጄ ሆይ!" የሚል መልስ መጣለት:: ይምርሐም "ምነው ጌታየ በሰው ሃገር ረሳኸኝ?" ቢለው "አልረሳውህም:: ይልቁኑ ሊገድልህ የሚፈልግህ ንጉሥ ሙቷልና ሒደህ ንገሥ" ሲል አዘዘው::
+ቅዱሱም ሚስቱን ሕዝባን ይዞ ላስታ ሲደርስ ሕዝቡ በዕልልታ ተቀብሎ ወዲያው አነገሠው:: በዚያም ለ15 ዓመታት ቅዱስ ሩፋኤል እየተራዳው: ሕብስትና ጽዋዕ ከሰማይ እየወረደለት ቀድሷል:: ሃገሪቱንም መርቷል::
+አንድ ቀን ግን ክፉ መካሪዎች "ተጨማሪ ሚስት አግባ" ቢሉት ተቆጣቸው:: በኋላ ደግሞ 'ለምን ተቆጣሁ' ብሎ አዘነ:: ስለዚህም ሃሳቡ ሰማያዊው ስጦታ ቀረበት::
+እያለቀሰ ጌታን ቢማጸን ጌታችን "ስላሰብከው ክፉ ሃሳብ (ለምን ተቆጣሁ ማለቱ ወደ ምክራቸው ማዘንበሉን ያሳይነበርና) ይቅር ብየሃለሁ:: ነገር ግን እኔ ወደ ማሳይህ ቦታ ካልሔድክ 2ኛ አይወርድልህም" አለው::
+ቅዱሱ ለጊዜው ትንሽ ቢከራከርም "እሺ" ብሎ በቅዱስ ሩፋኤል መሪነት ዛሬ ወደ ምናውቀው አካባቢው ሔደ:: በዚያም አራዊትን በጸሎቱ አድክሞ: መሠሪዎችን አስተምሮ: ሕዝቡንም አሳምኖ አጠመቃቸው::
+ጌታም "ከኢየሩሳሌም በደመና እየጫንክ በዚህ ባሕር ላይ ቤቴን ሥራልኝ" አለው:: ቅዱስ ይምርሐም መስከረም 13 ቀን (በበዓለ ባስልዮስ) ጀምሮ ሰኔ 20 (በበዓለ ሕንጸታ) ፈጸመና ታቦተ ገብርኤልን ሰኔ 21 ቀን ቀደሰው::
+ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ ግን በዚያ ቦታ እየቀደሰ ለ25 ዓመታት ሃገሪቱን አስተዳደረ:: አንድ ጊዜ ቅዱስ ሩፋኤል ለንጉሡ ከሰማይ ሕብስትና ጽዋዕ ሲያወርድለት 1 ባሕታዊ አይቶ "ለምን?" ብሎ ተቆጣ:: መልአኩ ግን የንጉሡን ክብር ነግሮ "እየዞርክ ስበክ" ብሎታል::
+በዚያ ባሕታዊ ስብከትም ከመላው ዓለም ብዙ ሺህ ሰወች መጥተው ቅዱስ ይምርሐን "ቀድሰህ አቁርበን?" ብለውለምነውታል:: ቅዱሱም ሲያቆርባቸው በመምሸቱ ጸሐይን አቁሟታል::
+ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ እንዲህ ባለ ጣዕመ ሕይወት ኑሮ: ለ40 ዓመታት ሃገራችንን አስተዳድሮ ጥቅምት 19 ቀን ዐርፎ በዚያው ሥፍራ ተቀብሯል:: ጌታችንም "መታሰቢያህን ያደረገውን: ደጅህን የረገጠውን እምርልሃለሁ" ብሎታል::
✞✞✞ አምላከ ይምርሐ ደጉን መሪ: አምላከ ዮሐንስ ቸሩን አስተማሪ ያምጣልን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
++"+ አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል::በማዳንህ እጅግ ሐሴትን ያደርጋል:: የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው::የከንፈሩንም ልመና አልከለከልኸውም:: በበጐ በረከት ደርሰህለታልና::ከከበረ ዕንቁ የሆነ ዘውድን በራሱላይ አኖርህ:: ሕይወትን ለመነህ ሰጠኸውም::ለረጅም ዘመን ለዘለዓለሙ:: በማዳንህ ክብሩ ታላቅ ነው:: +"+ (መዝ. 20:1-5)
† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
ጥቅምት ፲፰ /18/በዚህች ቀን የከበረ ቅዱስ ሮማኖስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ የክርስቲያን ወገኖችን መኰንኑ እንዳሳደዳቸው በሰማ ጊዜ ከቀሳውስትና ከዲያቆናት ጋር የክርስቲያን ወገኖችን ሁሉ በአንድነት ሰበሰባቸው ስለ ክርስቶስ ሃይማኖትም መክሮ አጸናቸው። አስቅልጵያኖስም ይህን ሰምቶ እንዲአመጡት አዘዘ በፊቱም በቆመ ጊዜ በወገን የከበርክ ሮማኖስ አንተ ነህን? አለው ቅዱሱም የወገን ክብር ምን ይጠቅመኛል ክብሬ ግን ክርስቶስ ነው ብሎ መለሰለት። መኰንኑም ሰምቶ እንዲሰቅሉትና ጉንጮቹን ይሰነጣጥቁ ዘንድ አዘዘ። በዚያንም ጊዜ ሮማኖስ መኰንኑን እንዲህ አለው "እነሆ ስንፍናህን እዘልፍ ዘንድ ፈጣሪዬ አፌን ከፈተ፤እውነት ነገርን ብታውቅ ለእግዚአብሔር እንሰግድ ዘንድ ይገባ እንደሆነ ወይም ለአማልክት እንዲነግረን ሕፃን ልጅ እንዲአመጡ እዘዝ" መኰንኑም ታናሽ ሕፃንን እንዲአመጡ አዘዘ መኰንኑም ሕፃኑን ስግደት ለማን እንዲገባ ዕውነቱን ንገረን አለው። ሕፃኑም በአንዲት ቃል ዓለሙን ሁሉ ለፈጠረ ለሕያው እግዚአብሔር ስግደትና አምልኮ እንዲገባ አታውቅምን አለው። በዚያንም ጊዜ የቅዱስ ሮማኖስንም ምላሱን ከግንዱ እንዲቆርጡ መኰንኑ አዘዘ። ያን ጊዜ መኰንኑን ይዘልፍ ዘንድ ለአባ ሮማኖስ ረቂቅ አንደበት ተሰጠው ሲዘልፈውም መኰንኑ ሰምቶ ምላሱ እንዳልተቆረጠ ተጠራጠረ፤ ወታደሩንም ጠርቶ ምላሱን ያልቆረጥክ ለምንድን ነው አለው ወታደሩም የምላሱን ቁራጭ ያመጡ ዘንድ እዘዝ አለው አምጥተውለትም አየ መኰንኑም ወደ ወህኒ ቤት አስገብተው በዚያ አንቀው እንዲገድሉት አዘዘ የምስክርነት አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ። የቅዱሳን በረከታቸው ይደርብን! ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር
ጥቅምት ፲፮ /16/
በዚች ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ዘጠነኛ የሆነ፤ ቅዱስ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ያቃቱ አረፈ።
ከርሱ በፊት የነበረ አባ ብንያሚን በአረፈ ጊዜ ይህን አባት መርጠው በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት በዘመኑም ብዙ ችግር ደርሶበታል ስሙ ቴዎዶስዮስ የሚባል አንድ መለካዊ ሰው ነበረ እርሱም ወደ ደማስቆ ንጉሥ ወደ ዘይድ ሒዶ ብዙ እጅ መንሻ ሰጥቶ ለእስክንድርያ አገረ ገዥ ሁኖ ተሾመ ። ይህንንም አባት አባ ያቃቱን ያስጨንቀው ጀመረ በየዓመቱ ግብር ሰባት ሺህ የወርቅ ዲናር ከእርሱ እስከተቀበለ ድረስ እግዚአብሔርም እስከ አጠፋው ድረስ ይህን አባት እንዲህ አሠቃየው ።
በአንዲት ሌሊትም ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለዚህ አባት ተገለጸለት ፍዩም በሚባል አገር በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግል ዮሐንስ የሚባል ጻድቅ ሰው መነኰስ እንዳለ ነገረው ። ሕዝብን በማስተማርና በመምከርም ይረዳው ዘንድ መልእክተኞችን ልኮ እንዲአስመጣውም አዘዘው ሁለተኛም ከእርሱ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት እንደሚሆን ገለጠለት ።
በዚያንም ጊዜ መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጣው ሥራውንም ሁሉ አስረከበው ይህንንም አባት ከብዙ ድካም የሚያሳርፈው ሆነ በሹመቱ ወንበር ዐሥራ ዘጠኝ ዓመት ኑሮ ከዚህም በኋላ በሰላም አረፈ ።
የቅዱሳን በረከታቸው ይደርብን አሜን !
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር
🌹 "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌹
🌹 #ጥቅምት ፲፭ (15) ቀን።
🌹 እንኳን #ለዐሥራ_ሁለቱ_ቅዱሳን_ሐዋርያት ዓለም በእጣ ለተካፈሉበት ለመታሰቢያ ቀን፣ ለቅዱስ ጳውሎስ ረድ #ለቅዱስ_ሲላስና_ለኒቆድምያ አገር ለሆነ ለሰማዕቱ ለቅዱስ ቢላሞን ለዕረፍታቸው መታሰቢያ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከቢላሞን_ማኅበር_ከሆኑ_ከመቶ_ሃምሣ_ስምንት ሰማዕታት ከመታሰቢያቸው፣ #ከሰላትዮን_ከአጥራኪስ #ከአርሞቅስ_ከአድማንያ_ከአርሚስ_ከቅድስት ጾመታ፣ #ከአባት_ኢሳይያስና_ከሐዋርያትም ከዕፍታቸው መታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
🌹 #ከኒቆምድያ_አገር_የሆኑ_ቅዱስ_ቢላሞን፦ የዚህም ቅዱስ አባቱ ጣዖት አምላኪ ነው እናቱ ግን ክርስቲያን ናት ጥበብንም አስተማሩት ከዚህም በኋላ ስሙ አርማላስ ከሚባል ቄስ ጋር ተገናኘ። እርሱም ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የቀናች ሃይማኖት አስተማረው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቀው ታላቅ የሆኑ ድንቆች ታምራትን የማድረግ ሀብትን እግዚአብሔር እስከ ሰጠው ድረስ በጾም በጸሎት ታላቅ ገድልን ተጋደለ።
🌹 በአንዲት ቀንም ለዓይኖቹ መድኃኒትን እንዲአደርግለት አንድ ዕውር ሰው ወደርሱ መጣ ቅዱስ ቢላሞንም "በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም" እያለ በዕውሩ ዐይኖች ላይ የመስቀልን ምልክት አደረገ ያን ጊዜ ዐይኖቹ ድነው አየባቸው ጤነኛም ሆነ። ንጉሥም ዐይኖቹ የተገለጡለትን የዚያን ዕውር ዜና በሰማ ጊዜ ወደርሱ አስቀረበውና "ዐይኖችህን ማን አዳነህ?" ብሎ ጠየቀው እርሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት "ቅዱስ ቢላሞን ፈወሰኝ እርሱ እጁን በዐይኖቼ ላይ አድርጎ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እያለ በመስቀል ምልክት አማተበብኝ ያን ጊዜ አየሁ" ይህንንም ብሎ"እኔ ክርስቲያን ነኝ" እያለ በንጉሡ ፊት በግልጽ ጮኸ። ንጉሡም ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጡት የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
🌹 ከዚህም በኋላ ወታደር ልኮ ቅዱስ ቢላሞንን አስቀረበው ስለ ሃይማኖቱም በጠየቀው ጊዜ እርሱም "ክርስቲያን ነኝ" ብሎ በፊቱ ታመነ ንጉሡም ብዙ ሽንገላን በመሸንገል አባበለው። ብዙ ቃል ኪዳንም ገባለት ባልሰማውም ጊዜ በእርሱ ላይ ተቆጥቶ ድምፁን ከፍ አድርጎ "ካልሰማኸኝ እኔ ጽኑ ሥቃይን አሠቃይሃለሁ" አለው። ቅዱስ ቢላሞንም "እኔ ከሥቃይህ የተነሣ ፈርቼ ሃይማኖቴን ለውጬ ፈጣሪዬን አልክድም" አለው።
🌹 ከዚያችም ቀን ጀምሮ በብዙ አይነት ሥቃይ በብዙ ቀኖች ውስጥ ማሠቃየትን ጀመረ። በግርፋት በስቃላትም በባሕር ስጥመትም ወደ እሳት በመወርወርም የሚያሠቃይበት ጊዜ አለ።
በዚህም ሥቃይ ውስጥ ሳለ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጠመቀው ቄስ በአርሜላዎስ አምሳል ተገልጾለት እንዲህ የሚል የደስታ ቃል አሰማው። "የመረጥኩህ ቢላሞን ሆይ ደስ ይበልህ እኔ ሰማያዊ መንግሥትን አዘጋጅቼልሃለሁና"።
🌹 የንጉሡ ጭፍሮችም ይህን የደስታ ቃል ሰሙ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አምነው እነርሱ በሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የአመኑ መሆናቸውን በንጉሡ ፊት ገለጡ በዚያንም ጊዜ ራሳቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ ንጉሡ አዘዘ። ቅዱስ ቢላሞንንም እንዲቆርጡት አዘዘ ከእሊህ ጭፍሮች ጋርም እንዲህ ገድሉን ፈጸመ ቁጥራቸውም መቶ ኀምሣ ስምንት ነው የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ቢላሞን ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጥቅምት 15 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
🌹 "#ሰላም_እብል_ለርክበተ ዐፅምክሙ ወርቅ። #አዝቂር_ወኪርያቅ። #ወሰላም_ለሲላስ ረድአ ማዕነቅ። ዘጸለለ በጌጋይ እምነጽሮታ ለጽድቅ። ዐይነ ሐሊናየ ፈውሱ በምራቅ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የጥቅምት_15።
✝ ✝ ✝
🌹 #የዕለቱ_ምስባክ፦ "እነግሮሙ ስመከ ለአኀውየ። ወበማዕከለ ማኅበር እሴብሐከ። እለ ትፈርህዎ ለእግዚአብሔር ሰብሕዎ"። መዝ 21፥22-23። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 8፥31-35፣ ይሁ 1፥17-22 እና የሐዋ ሥራ 15፥22-30። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 18፥12-21። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ነው። መልካም በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችን ይሁንልን።
ጥቅምት ፲፬ /14/በዚህች ቀን ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ የሆነ ቅዱስ ሐዋርያ ፊልጶስ አረፈ። ከመድኃኔታችንም ዕርገት በኋላ ሐዋርያት ከሾሟቸው ከሰባቱ ዲያቆናት ውስጥ የተቆጠረ ነው። እርሱም ወደ ሰማርያ ወርዶ አስተማረ ብዙዎችንም አሳምኖ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው። ከዚህም በኋላ ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ ይሔድ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ፊልጶስን አዘዘው በሔደም ጊዜ ለኢትዮጵያ ንግሥት ለህንደኬ በጅሮንዷ የሆነ ጃንደረባውን አገኘው እርሱም እንደ በግ ሊታረድ መጣ የሚለውን የነቢይ ኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። ፊልጶስም ጃንደረባውን የምታነበውን ታስታውለዋለህን አለው። ጃንደረባውም ያስተማረኝ ሳይኖር እንዴት አውቃለሁ አለ። ፊልጶስም ስለ ጌታችን ስለ መከራው ለዓለሙ ሁሉ ድኅነት ስለሆነው ሞቱ እንደተነገረ ተረጐመለት። ጃንደረባውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አመነ ያን ጊዜም በፊልጶስ እጅ ከወንዝ ውኃ ውስጥ ተጠመቀ ከውኃውም በወጡ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ፊልጶስን ነጥቆ ወሰደው ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም። ሐዋርያው ፊልጶስም እግዚአብሔርን አገልግሎ በዚህች ዕለት ፈጽሞ በሰላም አረፈ። የቅዱሳን በረከታቸው ይደርብን አሜን ! ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር
🌹 ከዚህም በኋላ ሥጋውን በታላቋ በሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን አኖሩ ከሥጋውም ብዙ ድንቆች ተአምራት ተደረጉ ዕውሮች አይተዋልና ሐንካሶችም ቀንተው ይሔዳሉና ደንቆሮዎችም ይሰማሉና ለምጻሞችም ይነጻሉና አጋንንት ያደሩባቸውም ይወጡላቸዋልና ሁሉም ካለባቸው ደዌ ይድናሉና። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሙሴ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጥቅምት 14 ስንክሳር።
አመሰግንሃለሁ"። የአባቱ አገልጋዮችም ብዙ ወራት በሁሉ አገሮች ሲዞሩ ኑረው ወደ አውፊምያኖስ ጌታቸው ተመለሱ። የእግዚአብሔር ሰው ቅዱስ ሙሴም ከሰንበት ቀኖች በቀር እህልን የማይቀምስ እስቲሆን ድረስ ተጋድሎውን በመጨመር በየሁለትና በየሦስት ቀኖች የሚጾም ሆነ።
🌹 ከዚህም በኋላ እመቤታችን የከበረች ድንግል ማርያም ከዚያች ቤተ ክርስቲያን ካህናት ውስጥ ለአንድ ደግ ጻድቅ ቄስ ተገልጻ እንዲህ አለቸው "በጥዋት ወደ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ውጣ ከምሰሶ አጠገብ ብቻውን ቁሞ የሚጸልይ ሰው ታገኛለህ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ወደ ቤተ ክርስቲያን ግባ በለው በውጭ አትተወው ጾሙ ጸሎቱ በእግዚአብሔር ፊት መዓዛው ጣፋጭ እንደሆነ ዕጣን ተቀባይነትን አግኝቷልና"። ሲነጋም ያ ቄስ ወደ ቅዱስ ሙሴ ሒዶ "የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ወደ ቤተ ክርስቲያን ግባ" አለው ሙሴም "አባቴ ሆይ በከበረ ቦታ ላይ መቆም የማይገባኝ ኃጢአተኛ ነኝና ተወኝ" አለው ቄሱም "ወደ ቤተ መቅደስ አስገባህ ዘንድ ከቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም ወዳንተ ተልኬአለሁ" ብሎ መለሰለት ወደ ቤተ መቅደስም ያስገባው ዘንድ እንዳዘዘችው ነገረው ከዚህም በኋላ አስገባው።
🌹 ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ ወደ ሀገረ ጠርሴስ ይሔድ ዘንድ አስቦ እርሷም የሐዋርያው ጳውሎስ አገር ናት እንዲህም አለ "እስከ ዕለተ ሞቴ በውስጥዋ እኖራለሁ ሥጋው ምንም በሮሜ አገር የሚኖር ቢሆንም የትውልድ አገሩ ናትና በረከትን እቀበላለሁ" ብሎ ነው።
🌹 በሌሊትም ወጥቶ ወደ ባሕር ዳርቻ ሔደ ወደ ጠርሴስም ይሔድ ዘንድ በመርከብ ተጫነ በባሕር መካከልም ታላቅ ነፋስ ተነሣባቸው ባሕሩም ከነፋሱ ኃይል የተነሣ ታወከ ወደየትም እንደሚሔዱ አያውቁም ነበር ቀኑ ጨልሞባቸዋልና ስለ ነፍሳቸውም ድኅነት ወደ እግዚአብሔር ለመኑ በዚያንም ጊዜ ባሕሩ ጸጥ ብሎ ታላቅ ደስታ ሆነ ብርሃንም ታየ ወደ ሮሜ ሀገር ወደብም እንደ ደረሱ አወቁ።
🌹 ቅዱስ ሙሴም ተነሥቶ በመርከብ ውስጥ ያሉትን በሰላምታ ተሰናብቷቸው ጉዞውን ጀመረ በልቡም እንዲህ አለ "ይህ ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነ እንግዲህ እስከ ዕለተ ሞቴ ራሴን ለማንም እንዳልገልጥ ሕያው ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያውቀኝ የለምና በአባቴ ደጅ እኖራለሁ" ይህንንም ብሎ ወደ አባቱ ቤት ተጓዘ። በመንገድም ላይ አባቱን ተገናኘው ብዙ ሰውም ተከትሎት ነበር የእግዚአብሔር ሰው ሙሴም ቀረብ ብሎ አባቱ የተቀመጠበትን ፈረስ ልጓሙን ያዘ እንዲህም አለው "እግዚአብሔር የባረከህ ያከበረህ አንተ ደግ ሰው እግዚአብሔርም ኃጢአትህን ይቅር ይበልህ የልብህንም ልመና ይስጥህ እኔም መጻተኛ ድኃ ሰው እንደ ሆንኩ እወቅ ለመጻተኛነቴና ለችግረኛነቴ የምትራራ ሁነህ ከማዕድህ ፍርፋሪ ልትመግበኝ ከወደድህ መኖሪያዬን በቤትህ አንጻር በደጃፍህ አድርግልኝ ዋጋህንም የሚሰጥህ እግዚአብሔር ነውና"።በዚያንም ጊዜ አውፊምያኖስ የልጁ የሙሴን ስደት አስታውሶ በተቃጠለ ልብ አለቀሰ መኖሪያውንም በቤቱ ደጅ እንዲሠሩለት አዘዘለት። ሁለተኛም ከአገልጋዮቹ አንዱን በሚያሻው ነገር ሁሉ እንዲአገለግለው አዘዘው።
🌹 የእግዚአብሔር ሰው ሙሴም ያን የሚያገለግለውን "ወንድሜ ሆይ ከሰንበት ቀኖች በቀር መብልና መጠጥ እንዳታመጣልኝ እለምንሃለሁ ይኸውም ከቁርባን በኋላ ግማሽ እንጀራና የጽዋ ውኃ ብቻ ነው" አለው። በጾምና በጸሎትም እየተጋደለ በዚያ በአባቱ ደጅ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ።
🌹 ሰውን የሚወድ ቸር ጌታችን ኢየሱስ ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው ወዶ ተገለጠለት እንዲህም አለው "የመረጥሁህ አንተ ብፁዕ ነህ አንተ ፈቃዴን ፈጽመሃልና በዚህ ዓለም ከደስታ ኃዘንን ከብልጽግና ድኅነትን መርጠሃልና እኔም የማይጠፋ ብልጽግናን እሰጥሃለሁ ዳግመኛም ስምህን የሚጠራ መታሰቢያህንም ለሚያደርግ የተራበውን ለሚያጠግብ የተጠማውን ለሚያጠጣ የተራቈተውን ለሚያለብስ ገድልህንም ለሚጽፍ ወይም ለሚያጽፍ ስለ ስምህ በጎ ሥራ ሁሉ ለሚሠራ ቃል ኪዳንን ሰጠሁህ። በሰማያዊት መንግሥትም በጎ ዋጋን እሰጠዋለሁ ተጠራጣሪ ካልሆነ በዚህ ዓለምም እጠብቀዋለሁ ከበጎ ነገር ሁሉ ምንም አላሳጣውም። አሁንም ከአራት ቀን በኋላ እወስድሃለሁ ምርጦቼ ነቢያት ሐዋርያት ጻድቃን ሰማዕታት ከአሉበትም አኖርሃለሁ" ይህንንም ብሎ ከእርሱ ዘንድ ወደ ሰማይ በታላቅ ክብር ዐረገ።
🌹 ቅዱስ ሙሴም ከእግዚአብሔር ዘንድ ይህን ጸጋ በተሰጠ ጊዜ እጅግ ደስ አለው ያን የሚያገለግለውንም ወንድሜ ሆይ እንግዲህ "ስለ እኔ ከመድከም ታርፋለህና ወረቀትና ቀለም አምጣልኝ" አለው። ያ አገልጋይም ከአነጋገሩ የተነሣ አድንቆ ወረቀቱንና ቀለሙን አመጣለት የከበረ የእግዚአብሔር ሰው ሙሴም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ገድሉን ሁሉ ጻፈ በአራተኛውም ቀን ያቺን የጻፋትን መጽሐፍ በእጁ ጨበጣት በእሑድ ቀንም በሰላም ዐረፈ። መላእክት "ነቢያት ሐዋርያት ጻድቃን ሰማዕታት ለሚያገለግሉት የዘላለም ተድላ ደስታ ለሚሰጥ ለነበረና ለሚኖር ፈጣሪያችን ምስጋና ይሁን" እያሉ ነፍሱን ተቀበሏት። ሕዝቡም ሁሉ በቅዳሴ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሰብስበው እያሉ ከመሠዊያው በላይ "የጌታቸውን ሕጎቹንና ሥርዓቱን የሚያደርጉ ደጎች አገልጋዮች ባሮች የተመሰገኑ ናቸው እነርሱ ወደ ዘላለም ተድላ ደስታ ይገባሉና" የሚል ቃልን ሲጮህ ሰሙ ።
🌹 ሊቀ ጳጳሳቱና ኤጲስቆጶሳቱ ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ሕዝብም ሁሉ በሰሙ ጊዜ በላያቸው ታላቅ ፍርሀት ወደቀባቸው። የቅዳሴውም ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ይህን ምሥጢር ይገልጽላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በመጸለይ ማለዱ በዚያንም ጊዜ "የእግዚአብሔርን ሰው በአውፊምያኖስ ቤት ፈልጉት እነሆ እርሱ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጥቷልና" የሚል ቃልን ሰሙ። ሊቀ ጳጳሳቱም ይህን ነገር ሰምቶ አውፊምያኖስን ጠራውና "ይህ ታላቅ ጸጋ በቤትህ ውስጥ ሲኖር በሕይወቱ ሳለ እንድንጎበኘው በረከቱንም እንድንቀበል ለምን አልነገርከንም" አለው አውፊምያኖስም እንዲህ ብሎ መለሰ "ክቡር አባት ሆይ ቅድስናህ ይመስክር ይህን የሚመስል በቤቴ ውስጥ እንዳለ አላወቅሁም"።
🌹 በዚያንም ጊዜ ሊቀ ጳጳሳቱ ከሁሉ ካህናትና ሕዝብ ጋር ተነሥቶ ወደ አውፊምያኖስ ቤት ሔደ የከበረ የእግዚአብሔር ሰው ሙሴንም በዐረፈበት ቦታ አገኙት ክርታሱም በእጁ ውስጥ ነው ሊቀ ጳጳሳቱም ያቺን ክርታስ አንሥቶ "የእግዚአብሔር ሰው ሙሴ የአውፊምያኖስ ልጅ እናቱም አግልያስ" እስከሚለው ስሙ እስቲደርስ በሕዝቡ ሁሉ ፊት አነበባት። እናትና አባቱም በሰሙ ጊዜ ደነገጡ መራር ልቅሶንም አለቀሱ ቤተሰቦቻቸውም ሁሉ ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱ አጽናንቶ ጸጥ አደረጋቸው።
🌹 በዚያንም ጊዜ ሊቀ ጳጳሳቱ የሐር ልብስ አስመጥቶ በክብር ገነዘው ወደ ቤተ ክርስቲያንም ወስደው ከሥጋው እስከሚባረኩ በቤተ መቅደስ አኖሩት። ካህናቱና ሕዝቡ ሁሉ ከዚህም በኋላ ብዙ በሽተኞች ዕውሮች ሐንካሶች ደንቆሮዎች ዲዳዎች መጥተው ከሥጋው በተሳለሙ ጊዜ ሁሉም ከደዌያቸው ዳኑ በዚያችም ቀን ታላቅ ደስታ ሆነ። ሕዝቡም በበዙ ጊዜ የልጁን የሙሴን ሥጋ ከዐልጋው ላይ እንዳይጥሉት አውፊምያኖስ ፈራ ብዙ ገንዘብም አምጥተው ይበትኑ ዘንድ አገልጋዮቹን አዘዛቸው። ሥጋውን ትተው ወደ ተበተነው ገንዘብ ይሔዳሉ ብሎ አስቦ ነበር ግን ከቶ አንድ እንኳ ወደ ገንዘብ የሔደ የለም።
🌹 ለሠርጉም የታደሙት ሁሉ እንደተኙ በሌሊት ወጥቶ ሔደ ወደ ባሕርም ዳርቻ ደርሶ በመርከብ የሚጓዙ መንገደኞችን አገኘ የዓመት መንገድ ወደሚሆን አርማንያም እስከሚደርስ ከእነርሱ ጋር ተጓዘ። ነግቶ ወደ ሠርጉ አዳራሽ አባትና እናቱ በገቡ ጊዜ ሙሽራውን ልጃቸውን አላገኙትም ሙሽሪትንም "ልጃችን ወዴት አለ?" ብለው ጠየቋት እርሷም እንዲህ አለቻቸው። "በሌሊት ወደ እኔ ገባ መሐላን አማለኝ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ ራሴንም ስሞኝ ከእኔ ዘንድ ወጣ እኔም እያለቀስኩ ብቻዬን አደርኩ" ነገርዋንም ሰምተው ወድቀው በመጮህ ታላቅ ልቅሶን አለቀሱ ።
🌹 በዚያችም ጊዜ በሀገሮች ውስጥ ሁሉ ልጁን ገብረ ክርስቶስን ይፈልጉት ዘንድ ንጉሡ አምስት መቶ አገልጋዮቹን ላከ ለድኆችና ለምስኪኖችም ምጽዋት አድርገው የሚሰጥዋቸውን ብዙ ገንዘብን ሰጣቸው።
ገብረ ክርስቶስ ግን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም በአርማንም አገር በተሠራች በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ደጅ የሚኖር ሆነ። አባቱ የላካቸውም ሁለቱ አገልጋዮች ከዚያ ደርሰው ስለርሱ መረመሩ ግን ወሬውን ማግኘት ተሳናቸው ለድኆችም ምጽዋትን ሰጡ እርሱም ከድኆችም ጋር ምጽዋትን ተቀበለ።
🌹 በዚያም ዐሥራ አምስት ዓመት ከኖረ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለአንድ ቄስ ተገለጸችለት ቦታውንም አመልክታ እንዲህ አለችው። "የእግዚአብሔር ሰው ገብረ ክርስቶስን ይዘህ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስገባው ከውጭ አትተወው" ቄሱም እመቤታችን እዳዘዘችው አደረገ።
🌹 ከዚህም በኋላ የተመሰገነ ገብረ ክርስቶስ በሌሊት ተነሣ ከእመቤታችንም ሥዕል ፊት ቁም ጸለየ እንዲህም አላት "እመቤቴ ሆይ የተሠወረ ሥራዬን አንቺ ለምን ገለጥሽ አሁንም ወደሚሻለኝ ምሪኝ" ይህንንም ብሎ የእመቤታችንን ሥዕሏን ተሳልሞ በሌሊት ወጥቶ ወደ ባሕሩ ወደብ ደረሰ ወደሌላ ሀገርም ሊሔድ ወዶ በመርከብ ተሳፈረ። ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ከአባቱ አገር ደረሰ የአባቱና የእናቱም ባሮች እየናቁትና እየሰደቡት በአባቱ ደጅ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ። ሲገቡና ሲወጡም ሽታው እንዳያስጨንቀን "ይህን ምስኪን አስወግዱልን" ይላሉ ወጭትና ድስትም አጥበው በላዩ ይደፉበታል ውሾችም እንዲናከሱበትና እንዲበሉት የሥጋ ትርፍራፊ ይጥሉበታል ውሾች ግን ቁስሉን ይልሱለት ነበር እንደዚህም አብዝተው አሠቃዪት ።
🌹 ከዚህም በኋላ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ለመነ "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለአባቴና ለእናቴ ባሮች በደል እንዳይሆንባቸው ወዳንተ ውሰደኝ"። በዚያንም ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው። ከዚህም በኋላ ገድሉን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ጻፈ በእጁም ጨብጧት ጥቅምት 14 ቀን ዐረፈ።
🌹 በእሑድ ቀንም ሕዝቡ ሁሉና ካህናቱ ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋር በቅዳሴ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሳሉ "የእግዚአብሔርን ሰው በንጉሥ ቴዎዶስዮስ ቤት ፈልጉት" የሚል ቃል ከሰማይ ሰሙ በዚያን ጊዜ ሔደው በአረፈበት ቦታ አገኙት። በእጁም ውስጥ የተጨበጠ ክርታስን አዩ ሊወስዷትም ሽተው መውሰድ ተሳናቸው ።
✝ በአንድነትም በጸለዩ ጊዜ እጁ ተፈትታ ወስደው አነበቧት አባትና እናቱም ልጃቸው እንደሆነ አወቁ ታላቅ ጩኸትም ሆነ መሪር ልቅሶንም አለቀሱ አክብረውም ቀበሩት መቃብሩም በሽተኞችን ሁሉ በመፈወስ ድንቆች የሆኑ ብዙ ተአምራትን የሚያደርግ ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
🌹 #ከሮሜ_ሀገር_የሆነ_የከበረ_የእግዚአብሔር ሰው #ቅዱስ_ሙሴ፦ የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም አውፊምያኖስ የእናቱ አግልያስ ነው እነርሱም እግዚአብዘሔርን የሚፈሩ እጅግም ባለጸጎች ናቸው። አብዝተውም ይመጸውታሉ ሁልጊዜም ይጸልያሉ እስከ ዘጠኝ ሰዓትም ይጾማሉ ድኆችንና ችግረኞችንም ሳይይዙ አይበሉም።
🌹 ነገር ግን ልጆች የሏቸውም ነበር የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ የተባረከ ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔርን ይለምኑት ነበር ጌታችንም ልመናቸውን ተቀብሎ ይህን መልኩ እጅግ ያማረ የከበረና የተባረከ ልጅን ሰጣቸው በወለዱትም ጊዜ በርሱ ደስ ብሏቸው ለድኆችና ለምስኪኖች ታላቅ ምሳ አደረጉ ስሙንም ሙሴ ብለው ሰየሙት ትርጓሜውም የእግዚአብሔር ሰው ማለት ነው ስለእርሱ እግዚአብሔር ልመናቸውን ሰምቷልና።
🌹 ከዚህም በኋላ ሙሴን በመልካም አስተዳደግ አሳደጉት መንፈሳዊና ሥጋዊ ትምህርትን ጥበብን ሁሉ አስተማሩት። አድጎም በጎለመሰ ጊዜ አባቱ አውፊምያኖስ ሚስቱ አግልያስን "እነሆ ልጃችን ሙሴ አደገ ሚስትን ልናጋባውና በጋብቻውም ደስ ሊለን ለእኛ ይገባናል" አላት። የሙሴ እናት አግልያስም ሰምታ በዚህ ነገር ደስ አላት ከሮሜ አገር ታላላቆች ሰዎች ወገንም መልኳ እጅግ ያማረ አንዲት ብላቴና አጋቡት። ታላቅ ሠርግንም በማዘጋጀት ሸልመው አስጊጠው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጋብቻ ሥርዓት አክሊላትን አቀዳጇቸው። ከዚህ በኋላ ሥጋውንና ደሙንም ተቀብለው ወደሚሠረጉበት ቤት ገቡ።
🌹 ከዚህም በኋላ በማግሥቱ አውፊምያኖስ ሚዜውን ጠርቶ እንዲህ አለው ሙሽራው ወደ ሙሽሪቷ ገብቶ የጋብቻውን ሕግ እንዲፈጽም ንገረው ያ ሚዜውም በነገረው ጊዜ ወደ ሙሽራዪቷ ገባ ድንቅ የሆነ ውበቷንና ደም ግባቷን ተመለከተ በልቡም አስቦ እንዲህ አለ "ይህ ሁሉ ውበትና ደም ግባት አላፊ ጠፊ አይደለምን"። ይህንንም ብሎ ወደ ሰማያዊት መንግሥቱ የሚደርስበትን መንገድ እንዲመራው እግዚአብሔርን ለመነው። ሙሽራዪቱንም እንዲህ አላት "የተባረክሽ እኅቴ ሰላም ይሁንልሽ የእግዚአብሔርም ፍቅር አንድነት ከአንቺ ጋር ይኑር ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እስከምንገናኝ ደኅና ሁኚ"። ይህንንም በሚላት ጊዜ ልብሶቹን አውልቆ ሰጥቷት ከእርሷ ዘንድ ወጣ የተሞሸረበትንም ልብስ ለውጦ ከባሕር ዳርቻ እስከሚደርስ መንገዱን ተጓዘ። ልብሶቹንም ሁሉ ሽጦ ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋትን ሰጠ እርሱም ጨርቅ በመልበስ እንደ ድኃ ሁኖ ቁራሽ እንጀራ እየለመነ በየጥቂቱ እየተመገበ እስከ ሀገረ ሮሀ ድረስ ሔደ።
🌹 ከዚያም በደረሰ ጊዜ ወደቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ ለሮሀ ንጉሥ ለአቃርዮስ በስብከቱ ወራት የተላከለትን ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሥዕልና የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕል አግኝቶ ከሥዕሎቹ ተሳልሞ በረከትን ተቀበለ ወደ ልዑል እግዚአብሔርም ፈጽሞ እያመሰገነ ጸለየ። ወጥቶም ኑሮውን ከድኆችና ከምስኪኖች ጋር አደረገ።
🌹 ከዚህም በኋላ መጸለይና መጾምን ጀመረ እስከ ምሽትም ይጾማል በቀንና በሌሊትም ጸሎቱን አያቋርጥም ምጽዋትንም ከድኆች ጋር ተቀብሎ እርሱ መልሶ ለሌሎች ይሰጣል። በዚያቺም ዕለት በነጋ ጊዜ ወደ ሠርጉ አዳራሽ አባትና እናቱ ሲገቡ ሙሽራው ልጃቸው ሙሴ በጫጉላው ቤት እንደ ሌለ ሰሙ ደስታቸውም ወደ ኀዘን የሠርጉም ዘፈን ወደ ልቅሶ ወደ ዋይታ ተለወጠ።
🌹 ከዚህም በኋላ አውፊምያኖስ ባሮቹን ጠርቶ ብዙ ገንዘብን ሰጣቸው እንዲህም አላቸው "ልጄን እስከምታገኙት ድረስ ሁለት ሁለት እየሆናችሁ ወደ ሀገሩ ሁሉ ሒዱ ለድኆችና ለችግረኞች ምጽዋትን ስጡአቸው"። እነርሱም በሀገሩ ሁሉ ተበታተኑ። ከአባቱ አገልጋዮችም ሁለቱ አገኙት ግን አላወቁትም ምጽዋትንም ከድኆች ጋር ሰጡት ቅዱስ ሙሴም አውቋቸው እንዲህ ብሎ አመሰገነ "ጌታዬ ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ስለ አንተ ፍቅር ከአባቴ ባሮች እጅ ምጽዋትን እቀበል ዘንድ ለዚህ ታላቅ ክብር አድለህኛልና
