2 383
订阅者
+424 小时
-67 天
-2230 天
帖子存档
2 383
"ዛሬ ግቢ በቃ! ይኸው ብር አይደለ?" ከኪሴ አምስት መቶ ብር አውጥቼ ሰጠሁዋት... ተቀብላኝ ወደ ደረቴ በትናው "ብላው... አሁን ስራዬን ልስራበት ተወኝ።" ብላ መለሰችው።
"እሺ ዛሬ ከእኔ ጋ ነሽ..." ብዬ ተኮሳተርኩ
"ትችላለህ....ለማኝ አይደለሁም...ገባህ!::"
ከመሽታ ቤቱ ወጣች። ሂሳብ ከፍዬ ተከተልኳት:: "ትንሽ በእግር እንሂድ?" አልኳት። መጠጥ ስለጠጣች ውስጧ ስካር አለ:: "ሰውዬ....በርዶኛል" አለች። ኮቴን አውልቄ አለበስኳት...ዝም አለች።ኮቴን ካለበስኳት በኃላ ብርዱ ውስጤ ድረስ ተሰማኝ። እሷ እንዴት እንደቻለችው ፈጣሪ ይወቀው። ቃል ሳናወጣ መጓዝ ጀመርን።
###
የአዲስ ዓመት በዓል ዋዜማ ምሽት ላይ ነበር ከጓደኞቼ ጋ እንዝናና ብለን ወጥተን አይቻት ፍቅር የያዘኝ...ሴተኛ አዳሪ ናት።ደስ አይልም አይደል?...የፍቅር ነገር ሆነና አዙሮ ምን ላይ እንደጣለኝ እኔም አልገባኝም....እሷንም ምን የህይወት ድጥ ወስዶ እዚህ ጋ እንደዘፈቃት ባላውቅም ልጅነቷና ውበቷን ማንም ሰው የሚስማማበት ነው:: ያኔ አብረን አሳለፍንና ምንም ሳይፈጠር ብር ሰጥቻት ብቻ ተለያየን። ተምራለች፣ በወሬያችን መሀል ጣል የምታደርጋቸው ሀሳቦች እንደገረሙኝ ነበር የተለየሁዋት....ሳምንት ሙሉ ከሀሳቤ ልትጠፋ አልቻለችም። ስልኳን ተቀብዬ ስለነበር በሳምንቱ ደወልኩላት...ራሴን ካስታወስኳት በኃላ አወቀችኝ።
"እንገናኝ..." አልኳት
"ያው ቢሮዬ መጥተህ አግኘኛ..." ብላ ሳቀች። መራር ቀልድ ሆነብኝ ሳቋን እስክትጨርስ ጠበቅኳት..."ሄሎ ምነው ዝም አልክ?" አለች
"እ....ሌላ ቦታ ብንገናኝ....ቅር ካላለሽ"
"ክፈል እንጂ ....ምን ቅር ይለኛል..." አለች... ተቀጣጥረን ስልኩን ዘጋሁ። ወደቀጠርኳት ካፌ ስትመጣ ድጋሚ ሳያት ልቤ ደነገጠ አወራን ከፈልኳት ሄደች:: ማታ ደወልኩላት ከስልኳ ጀርባ ሙዚቃ ይሰማል ትንሽ አውርተን ስልኩን ዘጋሁት...ቀናሁ...ማን እየነካት ይሆን የሚለው እንቅልፍ ነሳኝ:: አድሬ ዋልኩና በንጋታው ያለችበት ሄድኩ:: እየተፈጠረብኝ ያለውን ነገር ነገርኳትና እየወደድኳት እንደሆነ ገለፅኩላት... ከት ብላ ሳቀች:: "ወንዶች ስትባሉ ግን..." ብላ አሁንም መንከትከቷን ቀጠለች::
"ምነው?..ሰው ነኝ አንቺም ሰው አይደለሽ እንዴ...? ይሄ እኮ ሊፈጠር የሚችል ነገር ነው።
"አትቀልድ ባክህ...ለእንደዚህ መጃጃል ከሆነ የፈለከኝ አጠገቤ እንዳደርስ... ለወር ያህል ነው የእናንተ አበድኩልሽ፣ ሞትኩልሽ...በል ቻው" ወደተጠቃቀሰችው አንድ ደንበኛ ጋር ሄደች::ሂሳብ ከፍዬ ወጣሁ ውስጤ ሲጨስ ይታወቀኛል ' ፍቅር ነው?፣ ቅናት ነው?፣ወይስ እሷ ያሰበችው አይነት ጊዜያዊ ስሜት?' ቤቴ ገባሁ። በንጋታው ደወልኩላት "ምንድነው?" አለችኝና ስልኩን በጆሮዬ ዘጋችው። 'እውነትም ምንድነው?' ጠየቅኩት ራሴን ለማንም ተሰምቶኝ የማያውቀው ስሜት እንዴት ለእሷ ሲሆን ተሰማኝ?...አፍቅሬያታለሁ::' ባለችበት ቦታ መመላለስ አበዛሁ... እንኳን እሷ በዙሪያዋ ያሉት እሷን መሰል ሴቶች አወቁኝ..."መጣልሽ" ይሏታል:: ከሌለችም "ትመጣለች ጠብቃት" ይሉኛል:: ከቀን ቀን ፍላጎቴ ለእሷ ብቻ መሆኑን ስላወቁ አንዷም ሴት ወደ እኔ አትጠጋም:: እንግዲህ የምጠብቃት ከሌላ ወንድ ጋ ተኝታ እስክትመለስ ነው:: ዕንባ እየተናነቀኝ እጠብቃታለሁ። አንድ ቀን ስትመለስ ፊቷ አለቀስኩ...ሳቀች፣ ስለሳቀች አኮረፍኳት ሳምንት ካለችበት ቦታ ራቅኩኝ። 'አጠገቧ ብደርስ ውሻ ነኝ።' ያልኩት ልጅ በሳምንቱ ናፈቀችኝና ሄድኩ.... "ከእኔ ምን ጎድሎብሽ ነው?" ብዬ ጠየኳት።
"በወንዶች ምን ያልጎደለብኝ አለ?...ትዕግስት ካለህ ጠብቀኝ።" አለች ፊቷን አኮሳትራ...ግራ መጋባቴን ስታይ መልሳ ሳቀች። ታገስኩኝ...
###
አንድ የዝናብ ጠብታ ግንባሬ ላይ አረፈችና አባነነችኝ። ምን ይህል ዝም ተባብለን በእግር እንደሄድን እንጃ...ሰማዩ ዳመና እንዳዘለ በጭለማ ውስጥም ያስታውቃል...
"አትጫወቺም...ዝም አልሽ?"
"ልመንህ..?" አለችኝ። ዞር ብዬ አየሁዋት:: ዓይኗ ዕንባ አቅርሯል::
"ማለት..?" አልኩኝ
" ሰልችቶኛል ይሄንን መንገድ ወደኃላ ባልመለስበት ደስ ይለኛል... ግን ደግሞ አንተ እስከመቼ እንደምትቀበለኝ አላውቅም... ነገ ፍቅርህ ሲበርድ በዛሬው ማንነቴ መልሰህ ልትለካኝ ትችላለህ። ገባህ?.... ታድያ ልመንህ?"
አየችኝ....አየሁዋት ዕንባዋ ፈሰሰ ከጉንጯ ጠረግኩት....እጇ ላይ ሸክም መስሎ የታየኝን ቦርሳዋን ተቀበልኳትና.…. ዝም አልኩ። መልሼ ዞር ብዬ ሳያት መሬት መሬቱን እያየች እየተራመደች ነው። ይሄ ህይወት እንደማይገባት የአየሁዋት ቀን ነበር የተረዳሁት...መራራ እውነት እንደ ፊልም እያየሁ ጠብቄያታለሁ...ታገስ ያለችኝ ቀን ትዕግስቱን እንዲሰጠኝ ፈጣሪን ለምኛለሁ... እንደበደለችኝ ውስጤ በተሰማኝ ቁጥር ልክ ይቅርታ አድርጌላታለሁ...ነገ ክፉ ጎረቤት ስሟን ቢያጠለሽብኝ ምን ይህል ከለላ ልሆናት እንደምችል በምናቤ ስንቴ ተመልክቻለሁ...የእመቤት ኑሮ እንደማኖራት ለራሴ ቃል ገብቻለሁ... ካየሁዋቸው ንፁህ ከተባሉ ሴቶች በላይ አፈቅራታለሁ።
"እኔ በህይወት እስካለሁ ይሄን መንገድ ወደኃላ አትመለሺበትም...።" ቀና ብላ አየችኝ...ከሆዷ ፈንቅሎ የወጣ ዕንባ በዓይኖቿ ፈሰሰ... ወደጎኔ አስጠግቼ አቀፍኳት... ወደፊት መጓዛችንን ቀጠልን...ወደቤቴ ላገባት።
Abrham F. Yekedas
@HAKiKA1
2 383
እያንደረደረን ልክ እንደ ቁልቁለት
እንዲህ እንደዋዛ ዓመት መስሎ ዕለት
የጣልነውን ሳንለይ የያዝነውን ሳናይ
"እንኳን አደረሰን፣ አዲስ ዓመት ሰናይ"
ብለን ተሸናግለን፥
አ
ለ
ን!
Abrham F. Yekedas
@HAKiKA1
2 383
Repost from N/a
2 383
ጓደኛዬ ከሀብታሞች መለስ ከደሀዎች ቀለስ የምትል ከወሽመጧ ጠበብ ብላ ሶስት በሰውነታቸው ጠጪውን የሚያጣብቡ ጋርዶች ባሉበት መሸታ ቤት ውስጥ ሁለት ቢራ ጋብዞ እንዲህ ሲል አበረታታኝ።
"ይኸውልህ አብሬ አንተ እምቅ አቅም አለህ...እምቅ አቅም...ቲክ ቶክ ክፈት"!
ወድያው እኔም ተወጣጥሬ ከፈትኩ ከፍቼም አልቀረሁ ፎቶዬን በዘፈን አቀናብሬ ለጠፍኩ...። ይሄ እስኪሆን ስድስተኛ ቢራ ላይ ነበርኩ።
አንድ ሰው ነው ቪዲዮውን ያየው... እሱም እንዲህ አለና ኮመተ "ሄዋንን ያሳታትን እባብ በትንሳኤው ቀን አየሁ የአለም መጨረሻ ደረሰ" ወሽመጤ ሰባት ቦታ ተከፈለ። ሞቅታዬ ሁሉ ጠፋ። ሞቅታ ነበረ ስካር?....ብቻ መካሪ ጓደኛዬን ካቀረቀርኩበት ስልኬ ቀና ብዬ ፈለኩት። ከአንዷ ጋር ይደንሳል። እሷ ትስቃለች... እሱ በርሃ ላይ ጊንጥ ያስደነበራት ግመል ይመስል በሀይል እየተቀነጣጠሰ ይውረገረጋል። በሳቀች ቁጥር ያበረታታችው እየመሰለው መውረግረጉንና መቀነጣጠሱን በአምስት እጥፍ ያህል ከፍ አደረገው። መቼም ወንድ የሴት ጥርስ አይከፈትለት...የገነት በር ተከፍቶ በደስታ እየዘለልክ ግባ ተብሎ የሚዘል ይመስል ሰው ሁሉ እንዳበደ ይመለከተው ጀመር። 'ይሄ ጊንጥ... እኔን እምቅ ችሎታ አለህ ብሎ ጉድ ይስራኝ። እኔማ ተውም አልለው ይዋረዳት።ምን አገባኝ' ብዬ በውስጤ ዝም ብዬ ማየት ጀመርኩ። ቆየት ብሎ የቤቱ ጋርድ መጣና "ብራዘር...ጀለስህን አረጋጋው የዳንስ ወለሉን እኮ ብቻውን አጨናነቀው።" ብሎ በደረቱ አጨናንቆኝ ሄደ። ለሀጣን የመጣ ለፃድቃን ይተርፋል ነውና ነገሩ
"አንተ ወረታው... አንተ ወረታው ...ወረታው...ወሬ...ና ቁጭ በል" ብዬ ከልጅቷ አላቀኩት። በስካር አንደበቱ "እሙዬ...የኔ እናት..ሌላ ግዜም እምቅ ችሎታዬን አሳይሻለሁ...ተመችቻታለሁ እኮ" እያለ ስልኳን ተቀብሎ ተቀመጠ። እንደተቀመጠ ስልኬን አዙሬ "እምቅ ችሎታ አለህ ብለህ የሰራኸኝን አየኸው?" አልኩት ቆጣ ብዬ
" ፐ...." አለኝ
"ፐ!....ምንድነው ፐ?" አልኩት
"አብርዬ የምር ደስ ብሎኛል።አካውንትህ ሊተኮስ ነው" አለ ጮክ ብሎ... የተኩስ ነገር ያሳሰባቸውና... አካውንት ሲባል ገንዘብ የሚያባንናቸው ገልመጥ ገልመጥ አድርገው ወደ ወንበራችን ተመለከቱ። ጋርዱ ድጋሚ ጠጋ አለኝና " ጀለስህን አረጋጋው....ፖለቲካ ማውራት አይቻልም።" ብሎ ሁለተኛ አስጠነቀቀኝና ዞር አለ።
"ወረታው ድምፅ ቀንስ.... " አልኩት
"ለምን ብዬ በሀገሬ....አንተም በአንድ ጡንቻ ራስ እባብ መባልን..."
"...ኧረ ወረታው በማርያም ዝምበል" ብዬ ተማፀንኩት
"አብርዬ ሙት....እደግመዋለሁ ...በአንድ ጡንቻ ራስ ኮመንት እባብ መባል ከብረት የጠነከረ አለት ሊያደርግህ ይገባል እንጂ አያስደንብርህ። አብርሽ አለት ነህ....የምር አለት ነህ" ብሎ ጠረጴዛውን በኃይል ደቃው
ጋርዱን ሸረፍ አድርጌ እያየሁት " ወረታው....አዎ አለት ነኝ በቃ....ስለ እምቅ ችሎታችንም ውጪ እንመክርበታለን...ጠጣ ዝም ብለህ.." ጋርዱ ትዕግስቱን እንደጨረሰ ያስታውቃል
" ምክክር .... ወይ ምክክር.... ይሄሄሄ አሁን እራሱ ምክክር ብለው ሊመካከሩ የገቡት ሁላ ስድስቱ ይሄኔ እየተጣሉ ነው። ምንም ምክክር አያስፈልግም...እንደ ሀገር" ጋርዱ መጣና "ኑ እስቲ ውጪ እናውራ" አለ
"ወንድሜ እዚህ ብናወራስ..." አልኩት
ወረታው ከእኔም ከጋርዱም አፍ ቀድሞ "ምንድነው ኧ ፀብ ነው?...እንደ አለት የጠነከርን መሆናችንን አላወቀ። ና ውጣለት..…የወንዱ ልጅ" ብሎ ቀድሞ ወጣ። እኔም ተከተልኩ።
እንግዲህ ይሄን ፅሁፍ ስከትብ 'አለቶቹ' እኔና ወረታው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በአንድ ክፍል ጎን ለጎን ተኝተን መሆኑ እንዳይረሳ።
Abrham F. Yekedas
@HAKiKA1
2 383
እንዴት እንደዚህ አይነት መዘፈቅ ውስጥ እንደገባሁ አላውቅም። ተገናኝተን እንደተለያየን 'ከዚህ በኃላ ይሄን ነገር አቆማለሁ' እያልኩ ለራሴ መሀላ እንደደረደርኩ ነው።ሳገኘው ግን ሁሉም ነገር በእኔ ብሶ ቁጭ ይላል። ማህሌት እንዲህ
አይነት ሁኔታ ውስጥ ትገባለች ብሎ ማን ያስባል? እንኳን ሌላ ሰው እኔም አላስበውም ነበር። የጠሉት ይወርሳል ሆነና መገኘት ያልፈለኩበት ላይ ተገኘሁ።
አብረን ተኝተን እያለ ስልኩ ጮኸ እያቀበልኩት ጥሪውን ስመለከት "ሚስቴ" ይላል። ማቀበሌን ትቼ ቀዩን ተጭኜ ዘጋሁት።
"ያምሻል እንዴ..." ብሎ በቁጣ ስልኩን ከእጄ ወሰደው። እንደተናደደ "ሳታውቂ የገባሽበት አታስመስይ..." እያለ ድጋሚ ለሚስቱ ሊደውል ስልኩን መነካካት ጀመረ። ቃል ሳላወጣ ተነስቼ መታጠቢያ ቤት ገባሁ። ሻወሩን እስከመጨረሻው ከፍቼ ውሀ ውስጥ ተንሰቅስቄ አለቀስኩ። ያቺ ሀይማኖተኛዋ፣ ትጉዋ፣ በራሷ የምትተማመነዋ፣ ከአቋሟ ዝንፍ የማትለዋ፣ ለክብሯ የማትደራደረዋ ማህሌት በየት ቅያስ አምልጣኝ ዛሬ እዚህ ጋ እንዴት እንደቆምኩ አላውቅም። ሰውነቴን ተጠየፍኩት።
በሴክረተሪ ተመርቄ በአንድ ድርጅት ስራ ስቀጠር የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ እሱ ነበር። "ኦ አንቺ ነሽ ፀሀፊያችን Welcome welcome...አሮን እባላለሁ" ብሎ ተዋወቀኝ.....ምኑም ደስ ይላል ቁመቱ፣ አለባበሱ፣ ሳቁ፣ ጨዋታ አዋቂነቱ... እንዲህ እያልኩ ብዘረዝርም አይበቃውም። የድርጅቶቹ ባለቤቶች እሱን በሚሰራበት ቦታ ላይ ለማስቀጠል ሲሽቆጠቆጡለት ሳይ ደግሞ ምን ያክል ቁልፍ ሰው እንደሆነ ለመረዳት ቀላል ነበር። በኃላ ስሰማ መኪና እራሱ በስጦታ አበርክተውለታል። በአጠቃላይ የታደለ ነው። ከስራ ወጥቼ መንገድ ላይ "ፀሀፊያችን ግቢ እንጂ..." ብሎ መኪናውን አቆመልኝ ገባሁ።
"ስምሽን አልነገርሽኝም ወይስ ፀሀፊያችን እያልኩ ልቀጥል?" ሳቀ...እየሳቅኩኝ "ማህሌት..." ብዬ እራሴን አስተዋወኩ
"ኧረ ባክሽ... የባለቤቴም ስም ማህሌት ነው። ግን ሚስቴ ቆንጆ ናት " ሳቀ። ምን ማለት እንዳለብኝ ግራ ገባኝና ዝም ስል "አንቺም ቆንጆ ነሽ ስቀልድ ነው" ደግሞ ሳቀ...እየተሽኮረመምኩ ሳቅኩ (በህይወቴ ለመጀመሪያ ግዜ ተሽኮረመምኩ).... የግራ እጅ ጣቱ ላይ ቀለበቱን ለማየት መሪው ከለለኝ። ሸኝቶኝ ከመኪናው ስወርድም ጣቱ በግልፅ ሊታየኝ አልቻለም "እስቲ እጅህን" አልለው ነገር... ጠዋት ቢሮ ስገባ የመጀመሪያ ስራዬ የሆነው ጣቱን ማየት ነበር። ጣቶቹ ዘለግ ብለው ያምራሉ። ያደረገው ቀለበት ጣቱ ላይ ይበልጥ ያምራል። ምንም ነገሩ ላይ ውበት አለ። ከቢሮው ወጣሁ 'ትዳር እንዳለው አወቅሽ አይደል? ምን ይፈጠር ነው የምትይው ፈጣጣ አትሁኚ ማህሌት' እራሴን ወቀስኩ
በሶስተኛ ወር ከንፈሩን ሳምኩት ቢሮ ውስጥ.... ከዛ ሁለታችንም ተፋፈርን። እኔ ስለገፋፋሁት ደሞ ይበልጥ አፈርኩ። በሌላኛው ቀን እሱ ሳመኝ። መሳሳም ኖርማል ሆነ። በ አምስተኛ ወር room ያዝን።ሁኔታችን የእብደት ይመስል ነበር። ደጋገምነው። ከሆነ በኃላ እሱም እኔም እንፀፀታለን ማቆም ግን አልቻልንም። ሁለት ዓመት ይሄ ነገር ቀጠለ ሚስቱን ይወዳታል። ከእሷ ሁለት ልጆች አሉት። እኔን እንዴት እንደሚመለከተኝ አላውቅም.….ብቻ...
ፎጣ ጣል አድርጌ ከሻወር ወጣሁ ልብሱን ለባብሷል ሱፍ ያዘወትራል ተጠጋሁትና ባሏን ወደስራ እንደምትሸኝ ሚስት ከረቫቱን አስተካከልኩለት..…"ቢቀርብንስ" አለኝ። ለ መቶኛ ግዜ እንዲህ ሲለኝ
እኔም ለመቶኛ ጊዜ "ከዚህ በኃላ አይደገምም" አልኩት። ልብሴን ለባብሼ ቤት አድርሶኝ ወደቤቱ ሄደ።
በቀጣይ ቀን ቢሮ ተገናኘን...እንደተነፋፈቅን በዓይናችን አወራን... በድብቅ የምንገናኝበት ቦታ እንድንገናኝ በዓይናችን ተነጋገርን። ተገናኘን ድጋሚ ወደቅን...አበድን። ምን አይነት ሴጣን መሀላችን እንደገባ አላውቅም። ይሄ ሰይጣን ነው እንጂ ሰው እንዴት እንዲ ይሆናል?
#ሰይጣን:- "አልቀረብሽም....ምን አባሽ ላድርግሽ ስሜን እንዳትጠሪ። አሁንስ አልበዛም እንዴ... እዛው በፀበላችሁ...ሰበበኛ"
Abrham F. Yekedas
2 383
የቀሬናው ስምዖን ድንገት በመንገዱ
ከክፉ ቀን ግማሽ ከደግ ቀን በአንዱ
ሄዶ ተረማምዶ መንገዱን ሳይጨርስ
ተብሎ ተጎተተ "ና... ይሄን ሰው አግዝ"
አቅማምቶ ተጠጋ
ከአንድ ምስኪን ገላ ደም ከለዋወሰው
በአዳናቸው ሳይሆን
በሚገርፉት ብቻ በተከበበ ሰው
ግማደ መስቀሉን
እንደቻለው አቅም አብሮ ተሸክሞ
ከባለ ፍዳው ጋር
ገፍቶ ያንን ዳገት... ወጣ ቀራንዮ
ተመልከት
እንዲ ነው አንዳዴ የህይወት ጎዳና
የግድ ተጎትተህ
ድንገት ከመከራው ገፈት ትቀምስና
ካሰብከው ዘግየተክ
ከአለምከው አርፍደህ መድረሻህ ይርቃል
ለፅድቅ መታጨትን
አንተ አትረዳውም የእግዜር ልብ ግን ያውቃል።
እንግዲህ
ለባለ መንገዱ ለቀሬናው ስምዖን
በገጠመው ሲሳይ በስቃይ እንዲያ መሆን
ምን ይሆን ምላሹ ለዚህ ኩነት ምንዳ?
አምላኩን ለረዳ...
Abrham F. Yekedas
@HAKiKA1
2 383
2 383
እንዲ ነበር እንዴ? የእሷነቷ ፊደል
ውስጥ ሀሳቧ ሁሉ ያውቅ ነበር ወይ በደል
እንዲ ነበር እንዴ? ስቀምሰው የእሷ ጣ'ም
(... ገረመቺኝ በጣም)
ከሰቀልኳት ሰማይ አራሷን ፈጥፍጣ
ከውሸቷ ጭብጥ እውነት ተፈልቅቃ
እንዳላሰብን በፍቅር የነገን ጎዳና
እንዳላወጋነው ስንቱን ቀና ቀና
እንዳልታየን ሁሉ የተስፋችን ፋና
ዛሬ ሲሆን ባዶ ደርሶ ሲሆን ወና
ነገሯ ሲገባኝ.....
ከቅኔ ህብረቃል ሰም ወርቋ ሲረዳኝ
እኔና እሷ ብዬ ስንቱን እያሰብኩኝ
ልብ ልቧን ታይቶኝ
እጅግ ተደንቄ ታዝቤያት አበድኩኝ።
Abrham F. Yekedas
@HAKiKA1
