uz
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

Kanalga Telegram’da o‘tish

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

Ko'proq ko'rsatish
611
Obunachilar
Ma'lumot yo'q24 soatlar
-17 kun
-930 kun
Postlar arxiv
🌼 "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼               🌼 #መስከረም ፲፯ (17) ቀን። 🌼 እንኳን #ለጌታችን_ለኢየሱስ_ክርስቶስ ለተሰቀለበት #ለከበረ_ለመስቀሉ_በዓል (ቁፍሮ ለተጀመረበት)፣ ለከበረች ለሮማዊት #ለቅድስት_ታኦግስጣ_ለዕረፍቷ_በዓልና ለእስክንድር ዐሥራ አራተኛ ሊቀ ጳጳሳት ለቅዱስ አባት #ለአባ_ዲዮናስዮስ_ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከቅዱሳን_ሊቢባ፣ #ከኪርያኖስ፣ #ከዮስጢና፣ #ከቴክሴልጥስ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                            ✝ ✝ ✝ 🌼 #የዕለቱ_ምልጣን_ግእዝ_ዜማ፦ ሃሌ ሉያ "#ሞገሰ_መስቀሉ የኀሉ ምስሌነ ለኢየሱስ ክርስቶስ እስመ ውእቱ ሰላምክሙ ዘረሰዮሙ አሐዱ ለክልዔሆሙ ወነሰተ አረፍተ ማእከል እንተ ጽልእ"። ትርጉም፦ ቅድመ ዓለም የነበረ ዛሬም ያለ ወደ ፊትም ዓለምን አሳልፎ የሚኖር የጌታችን የመስቀሉ ሞገስ ከሁላችን ጋር ይኑር፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላማችሁ ነውና፤ ሁለታቸውን አንድ ያደረገ የጸብን ግድግዳ አፈረሰ። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በድጓው_ላይ።                                                          ✝ ✝ ✝ 🌼 #መስከረም_ዐሥራ_ሰባት በዚች ቀን ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ_የተሰቀለበት #ለከበረ_መስቀል_በዓሉ ነው። ይህም የጻድቁ ንጉሥ የቈስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ከተሠወረበት የገለጠችው ነው። 🌼 የጎልጎታን ኮረብታ በአስጠረገች ጊዜ የከበረ መስቀልን አገኘችው ታላቅ ኮረብታም የሆነበት ምክንያት እንዲህ ነው። ብዙዎች ድንቆች ተአምራት ክብር ይግባውና ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቃብሩና ከመስቀሉ የሚገለጡ ሁነው ሙታን ይነሡ ነበርና የጎበጡና በሽተኞች ሁሉ ይፈወሱ ነበር። 🌼 ስለዚህም አይሁድ ተቆጡ እንዲህም ሥርዓትን ሠርተው አዘዙ በይሁዳ አገር ሁሉና በኢየሩሳሌም ቤቱን የሚጠርግ ሁሉ ወይም አፈር ወይም ጉድፍ የሚጠርግ በናዝሬቱ ኢየሱስ መቃብር ላይ ይጥል ዘንድ እንዲህም እያደረጉ ዕሌኒ ንግሥት እስከ መጣች ድረስ ከሦስት መቶ ዓመት በላይ ኖሩ። እርሷም በመጣች ጊዜ ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብርን እስከ አሳዩዋት ድረስ አይሁድን ይዛ አሠቃየቻቸው ያንን ኮረብታም እስከ ጠረጉ ድረስ አስገደደቻቸው የከበረ መስቀሉም ከተቀበረበት ተገልጦ ወጣ። 🌼 ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንም ተሠራች በዚች ቀንም አከበሩዋት ለመስቀሉም በዓልን መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን አከበሩለት። የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም ከሀገሮቻቸው በመምጣት ክብር ይግባውና ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤውን በዓል እንደሚያከብሩ ለመስቀልም ታላቅ በዓልን የሚያክብሩ ሆኑ። 🌼 ክርስቲያኖችም በጎዳና እየተጓዙ ሳሉ ስሙ ይስሐቅ የሚባል አንድ ሳምራዊ ሰው ከእርሳቸው ጋር ነበር ከእርሱም ጋር ብዙዎች ሳምራውያን ነበሩ ይህ ይስሐቅም የክርስቲያን ወገኖችን "ለምን በከንቱ ትደክማላችሁ ለዕንጨትስ ልትሰግዱ እንዴት ትሔዳላችሁ" እያለ ይሣለቅባቸው ነበር። ከክርስቲያን ወገኖችም ስሙ አውዶኪስ የሚባል አንድ ቄስ አለ ሕዝቡም በጎዳና ሲጓዙ የሚጠጡት ውኃ አላገኙም ነበርና ተጠሙ። 🌼 ወደ አንድ ጉድጓድም ሔዱ በውስጡም መሪር የሆነና የገማ ውኃ አገኙ እጅግም በውኃ ጥማት ተሠቃዩ። ይስሐቅም እጅግ ይሣለቅባቸው ጀመረ "የቀናች ሃይማኖት ካለቻችሁ ይህ የገማና የመረረ ውኃ ተለውጦ እስቲ ጣፋጭ ይሁን ይላቸው ነበር"። ቀሲስ አውዶኪስም በሰማ ጊዜ መንፈሳዊ ቅናትን ቀንቶ ከዚያ ሳምራዊ ይስሐቅ ጋር ተከራከረ ያ ሳምራዊም "በመስቀል ስም የተአምራት ኃይልን ከአየሁ እኔ በክርስቶስ አምናለሁ" አለ። ያን ጊዜም ቀሲስ አውዶኪስ በዚያ በገማ ውኃ ላይ ጸለየ ውኃውም ወዲያውኑ ጣፋጭ ሆነ ከእርሱም ሕዝቡ ሁሉ እንስሶቻቸውም ጠጡ። 🌼 ሳምራዊ ይስሐቅ ግን በተጠማ ጊዜ በረዋት ከያዘው ውኃ ሊጠጣ ፈለገ ግን ገምቶ ተልቶ አገኘውና መሪር ለቅሶን አለቀሰ። ወደ ከበረ ቄስ አውዶኪስም መጥቶ ከእግሩ በታች ሰገደ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አመነ በከበረ ቄስ በአውዶኪስ ጸሎት ጣፋጭ ከሆነው ከዚያ ውኃም ጠጣ። በዚያም ውኃ ውስጥ ታላቅ ኃይል የሚሠራ ሆነ እርሱ ለአማንያን የሚጣፍጥ ሲሆን ለከሀዲያንና ለአረማውያን የሚመር ሆነ በውስጡም የብርሃን መስቀል ታየ በአጠገቡም ውብ የሆነች ያማረች ቤተ ክርስቲያንን ሠሩ። 🌼 ሳምራዊ ይስሐቅም ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ በደረሰ ጊዜ ወደ ኤጴስቆጶሱ ሒዶ ከቤተሰቡ ጋር የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ። የከበረ መስቀልም ዳግመኛ የተገለጠበት መጋቢት ዐሥር ቀን ነው ዜናውንም በዚሁ ቀን ጽፈናል። 🌼 ምእመናንም በታላቁ ጾም መካከል በዓሉን ማክበር ስለአልተቻላቸው በዓሉን ቤተ ክርስቲያኑ በከበረችበት ቀን አደረጉ ይህም መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን ነው በዚህም ቀን አስቀድሞ ከከበረ መቃብር በንግሥት ዕሌኒ እጅ የተገለጠበት ነው። በመስቀሉ ላዳነን ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን ክብር ምስጋና ገንዘቡ ነውና ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ 🌼 #ሮማዊቷ_ቅድስት_ታኦግንስጣ፦ ይቺም ቅድስት በደጋጎች ነገሥታት በአኖሬዎስና በአርቃዴዎስ ዘመን የነበረች ናት። በዚያም ወራት የህንድ ንጉሥ መልእክተኞች እጅ መንሻ ይዘው ወደ ንጉሥ አኖሬዎስ መጡ በሚመለሱም ጊዜ ይችን ድንግል ታኦግንስጣን አገኟት የምታነበውም መጽሐፍ በእጅዋ ውስጥ ነበር ወደ አገራቸውም ነጥቀው ወሰዷት ለህንድ ንጉሥም ሚስቶቹንና ቤተሰቦቹን የምትጠብቅ ሆነች። 🌼 በአንዲት ዕለትም የንጉሡ ልጅ አስጨናቂ በሆነ ደዌ ታመመ የከበረች ታኦግንስጣም ወስዳ በብብቷ ታቅፋ በመስቀል ምልክት አማተበችበት በዚያንም ጊዜ ዳነ ከእርሷም ስለ ተደረገው ተአምር የዚች የከበረች ድንግል ታኦግንስጣ ዜናዋ በሀገሩ ሁሉ ተሰማ ከዚያችም ቀን ወዲህ በእነርሱ ዘንድ እንደ እመቤት እንጂ እንደ አገልጋይ አልሆነችም። 🌼 ከዚህም በኋላ የህንድ ንጉሥ ወደ ጦርነት በሔደ ጊዜ ጉም ጭጋግ ዐውሎ ነፋስና ጨለማ በላዩ መጣ ንጉሡ ግን የከበረች ታኦግንስጣ ስታማትብ ስለአየ በመስቀል ምልክት ማማተብን ያውቅ ነበርና ያን ጊዜ በጭጋጉ በጉሙ በጨለማውና በጥቅሉ ነፋስ ላይ በመስቀል ምልክት አማተበ። ወዲያውኑ ፀሐይ ወጣ ታላቅ ጸጥታም ሆነ ጠላቶቹንም በዚሁ የመስቀል ምልክት ድል አደረጋቸው እጅግም ደስ አለው። 🌼 ንጉሡም ከጦርነት በተመለሰ ጊዜ ለከበረች ታኦግንስጣ። ከእግርዋ በታች ሰገደ እርሱንና ቤተሰቦቹን ሁሉ የሀገሩንም ሰዎች የከበረች የክርስትና ጥምቀትን ታጠምቀው ዘንድ ለመናት ቅድስት ታኦግንስጣም እንዲህ አለችው "ይህን አደርግ ዘንድ ለእኔ አይገባኝም የሚያጠምቃችሁን ካህን ይልክላችሁ ዘንድ ወደ ንጉሥ አኖሬዎስ ላኩ"። ያን ጊዜም ከወገኖቹ ጋር የሚያጠምቀውን ካህን እንዲልክለት የህንድ ንጉሥ ወደ ንጉሥ አኖሬዎስ መልእክተኞችን ላከ ንጉሥ አኖሬዎስም ልመናውን ተቀብሎ የሚያጠምቃቸውን ቄስ ላከ ቄሱም አጠመቃቸው መሥዋዕትንም ቀድሶ ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው እግዚአብሔርንም የምትወድ የከበረች ድንግል ታኦግንስጣ እጅግ ደስ አላት ያንንም ቄስ መንፈሳዊ ሰላምታ ሰጠችውና ከእርሱ ቡራኬ ተቀበለች እርሱም ከእርሷ በረከትን ተቀበለ።

🌼 ጦብያም "አባቴ ሆይ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ" አለ ከዚህም በኋላ አሽከር ሊፈልግ ሔደ ቅዱስ ሩፋኤልንም አሽከር በሚሆን ሰው አምሳል አገኘው እርሱም ከጦብያ ጋር መጣ "ስሙንም አዛሪያ ነኝ" አለ ጦቢትም ላካቸው። ሲሔዱም በመሸ ጊዜ ወደ ጤግሮስ ወንዝ ደረሱ ጦብያም ገላውን ይታጠብ ዘንድ ወረደ። ታላቅ ዓሣም ሊውጠው ተወረወረ ሩፋኤልም ጦብያን "ዓሣውን ያዘው አትፍራው እረደውና ጉበቱን፣ ልቡንና፣ ሐሞቱን ያዝ" አለው እርሱም እንዳዘዘው አደረገ። 🌼 ጦብያም ሩፋኤልን "አንተ ወንድሜ አዛርያ ይህ የዓሣ ሐሞት ጉበቱና ልቡ ምን ይደረጋል" አለው። አዛርያ የተባለ መልአክም እንዲህ ብሎ መለሰለት "ጋኔን ያደረበት ሰው ወንድ ወይም ሴት ጉበቱንና ልቡን ከደቀቀ ዕጣን ጋራ ያጤሱለት እንደሆነ ጋኔን ይሸሻል ሐሞቱም ዐይኖቹ የታወሩ ሰውን ቢኩሉት ይድናል"። ሁለተኛም የራጉኤልን ልጅ ሣራን ያገባት ዘንድ ተናገረው እግዚአብሔርም ይጠብቀዋልና እንዳይፈራ አጽናናው። ወደራጉኤል ቤትም በደረሱ ጊዜ ሣራ ተቀብላ ደስ አሰኘቻቸው። 🌼 ከዚህም በኋላ ጦቢያ ሣራን ወደዳት። እርሷንም ይሰጠው ዘንድ አባቷን ጠየቀው አባቷም ለሰባት ባሎች አጋብቷት ሰባቱም እንደሞቱ ነገረው ጦብያም "የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን" አለ። ወደ ጫጉላ ቤትም በአገቧቸው ጊዜ ሩፋኤል የነገረውን ቃል አስታወሰ የዓሣውንም ጉበትና ልብ ከደቀቀ ዕጣን ጋር አጤሰ ያን ጊዜ አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን ሸሸ መልአክ ሩፋኤልም ይዞ ለዘላለሙ አሠረው። 🌼 ጦቢያም ሚስቱን ሣራን ይዞ ደስ ብሎት ወደ አባቱ ቤት ተመለሰ አባትና እናቱም በደስታ ተቀበሉት የአባቱንም ዐይኖች በኳለ ጊዜ እንደ ጭጋግ ሁኖ ከዐይኖቹ ተገፈፈ ዐይኑን አሸ ወዲያውኑ ድኖ ልጁን አየ። ከዚህም በኋላ የከበረ መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ራሱን ገለጠላቸው ብዙ ነገርንም ነግሮአቸው ወደ ሰማይ ዐረገ። 🌼 ከዚህም በኋላ ከወገኖቹ ጋር ተድላ ደስታን አደረገ ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ መከራ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ "እርሱ በኃጢአታችን ይገርፈናል ደግሞ እርሱ ይቅር ይለናል" ሁለተኛም "መከራህን የሚያስቡ የተመሰገኑ ናቸው። እነርሱ ክብርህን በአዩ ጊዜ በአንተ ደስ ይላቸዋልና" አለ። 🌼 ዳግመኛም ስለ ኢየሩሳሌም መታነፅ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ "ኢየሩሳሌም ሰንፔር መረግድ በሚባል በከበረ ዕንቁ ትሠራለች ድልድልዋ፣ ቅጽርዋ፣ አደባባይዋ፣ ደጆቿም በከበረ ዕንቊ በጠራም ወርቅ ይሠራሉ አደባባይዋም ቢረሌ፣ አትራኮስ፣ ሶፎር በሚባል ዕንቁ ይሠራልና በመንገድዋ ሁሉ ሁሉም እግዚአብሔርን አስቀድሞ የነበረ ወደፊትም የሚኖር እያሉ ያመሰግኑታል ደግሞም ከዓለማት ሁሉ ጽዮንን ከፍ ከፍ ያደረጋት እግዚአብሔር ይመስገን ይላሉ"። 🌼 ሁለተኛም የእስራኤል ምርኮኞች ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመለሱ ትንቢት ተናገረ ሁለተኛም ደግሞ ዮናስ ከነነዌ እንዲወጣ ልጁን ጦብያን አዘዘው። ዳግመኛም ልጁን እንዲህ አለው "ልጄ ሆይ ምጽዋት እንደምታድንና እንደምታጸድቅ ተመልከት" ይህን ተናግሮ በዐልጋው ላይ ሳለ በመቶ ኀምሳ ስምንት ዘመኑ ዐረፈ በክብርም ቀበሩት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ጦቢት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የመስከረም 16 ስንክሳር።                               ✝ ✝ ✝ 🌼 "#ሰላም_ለጦቢት_መፍቀሬ_ምጽዋት ዘተብህለ። እስመ ይገብር ምጽዋተ ወብዙኅ ሣህለ። እንዘ ምስለ ሕዝቡ ይሄሉ ሀገረ ነነዌ ማዕከለ። እምከመ ረከበ በእሴ ቅቱለ። እንበ ይቅብሮ አይጥዕም እክለ"። #ሊቁ_አርከ ሥሉስ (አርኬ) የመስከረም 16።                          ✝ ✝ ✝ 🌼 #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ያበድሮን እግዚአብሔር ለአናቅጸ ጽዮን። እምኵሉ ተዓይኒሁ ለያዕቆብ። ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር"። መዝ 86፥2-3 ወይም መዝ 50፥18-19። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥13-17 ወይም ዮሐ 9፥1-12።                           ✝ ✝ ✝ 🌼 #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦"እቤ አዐቅብ አፋየ ከመ ኢይስሐት በልሳንየ። ወአንበርኩ ዐቃቤ ለአፉየ። ሶበ ይትቃወሙኒ ኀጥአን ቅድሜየ"። መዝ 38፥1-2 ወይም መዝ 50፥18-19። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 3፥10-18፣ ያዕ 1፥19-ፍ.ም እና  የሐዋ ሥራ 15፥13-21። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 9፥1-12 ወይም 10፥22-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእ መልካም የደመራ በዓል ሁላችንም ይሁንልን።

🌼 "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼            🌼 #መስከረም ፲፮ (16) ቀን። 🌼 እንኳን #ከጌታችን_ከኢየሱስ_ክርስቶስ መቃብር ላይ #ቤተክርስቲያን_ለታነፀችበትና_ለተቀደሰችበት በዓል፣ በኢየሩሳሌም አገር ንግሥት ዕሌኒ የገለጠቻቸው የከበሩ ቦታዎች ሁሉ ለተሠሩበትና ለከበሩበት በዓል (ለደመራ በዓል)ና በፋርስ ንጉሥ አሜኔሶር እጅ ተማርኮ ወደ ነነዌ አገር ለተወሰደ ከንፍታሌም ነገድ ለሆነ ለገባኤል ልጅ ለቅዱስ ጦቢት ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከቅዱሳን ከወርቅላ፣ ከስምዖን፣ ከመርቄኖስ፣ ከሐሊ፣ ከሮቂኖስ፣ ከሉክያኖስ፣ ከአርዝማኖስ፣ ከጴጥሮስ፣ ከሐና ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                           ✝ ✝ ✝ 🌼 #የዕለቱ_አንገርጋሪ፦ ሃሌ ሉያ "ዝኒ ኮነ በፈቃደ እግዚአብሔር ዝንቱ ኵሉ ኮነ ወአንቲኒ ታቦት እምኀበ መጻእኪ ወኀበኒ ተሐውሪ መድኃኒተ ኩኒ ታቦት ሕጉ ለንጉሥ ዐቢይ"። ትርጉም፦ የንጉሥ የሕጉ ታቦት መድኃኒትን ሁኚ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ሆነ፤ አንቺ ታቦት ከወዴት መጣሽ ወዴትስ ትሄጃለሽ።                                                    ✝ ✝ ✝ 🌼 በዚች ቀን #ከጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ_መቃብር ላይ #ቤተ_ክርስቲያን_የታነፀችበትና_የተቀደሰችበት ነው። ደግሞ በኢየሩሳሌም አገር ንግሥት ዕሌኒ የገለጠቻቸው የከበሩ ቦታዎች ሁሉ የተሠሩበትና የከበሩበት ሆነ። 🌼 ይህም እንዲህ ነው ልጇ ቈስጠንጢኖስ በነገሠ በሃያ ዓመት ቅዱሳን የሆኑ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶችን በኒቅያ ከተማ ከሰበሰበ በኋላ ቅድስት እናቱ ዕሌኒ እንዲህ አለችው "ልጄ ሆይ እኔ ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም በመሔድ የክብር ንጉሥ የሆነ የክርስቶስን ዕፀ መስቀል ፈልጌ አወጣ ዘንድ ለእግዚአብሔር ስዕለትን ተስያለሁ"። 🌼 ቈስጠንጢኖስም ሰምቶ በዚህ ነገር ደስ አለው ከብዙ ሠራዊትም ጋር ብዙ ገንዘብ ሰጥቶ ላካት የከበሩ የግምጃ ልብሶችንም ሰጣት እርሷም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰች ጊዜ ከከበሩ ቦታዎች ተባረከች። ከዚህም በኋላ ስለ ከበረና አዳኝ ስለ ሆነ ዕፀ መስቀል መረመረች በታላቅ ድካምና ችግር አገኘችውና ታላቅ ክብርን አከበረችው በታላቅ ምስጋናም አመሰገነችው። 🌼 ከዚህም በኋላ በጎልጎታ በቤተ ልሔምም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ዋሻ ደግሞ በጽርሐ ጽዮን የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ በተቀበረበት በጌቴሴማኒ በደብረ ዘይትም በከበሩ ቦታዎች ሁሉ የቤተ መቅደስ መሠዊያ እንዲሠሩ አዘዘች። ዳግመኛም በዕንቁ በወርቅና በብር እንዲአስጌጧቸው አዘዘች። 🌼 በኢየሩሳሌምም ስሙ መቃርስ የሚባል ኤጲስቆጶስ አለ። እርሱም ንግሥት ዕሌኒን እንዲህ ብሎ መከራት "ይህን እንዲህ አትሥሪ ከጥቂት ዘመናት በኋላ በዚህ አገር ሊነግሡ አሕዛብ ይመጣሉ። ሁሉን ይማርካሉ ቦታዎችንም ያፈርሳሉ ወርቁን፣ ብሩን፣ ዕንቁውን ይወስዳሉና ነገር ግን ጠንካራ የሆነ የማይናወጽና የማይፈርስ ጥሩ ሕንፃ ልታሠሪ ይገባል ከዚህ የሚተርፈውንም ለድኆችና ለችግረኞች ስጪአቸው" አላት። እርሷም የአባ መቃርስን ምክሩን ተቀብላ መኳንንቱ ሁሉ ለአባ መቃርስ በመታዘዝ በከበሩ ቦታዎች ሁሉ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲአንፁ አዘዘቻቸው። 🌼 ከዚህም በኋላ ንግሥት ዕሌኒ ወደ ልጅዋ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በተመለሰች ጊዜ በኢየሩሳሌም ያደረገችውን ሁሉ ነገረችው ሰምቶ እጅግ ደስ አለው እንደገና ሌላ ብዙ ገንዘብና ሕንፃውን ተቆጣጥረው የሚያሠሩ ሹሞችን ላከ ለሚገነቡና ለሕንፃው ሥራ ለሚአገለግሉ ሁሉ ደመወዛቸውን ሳያጓድሉ ሁል ጊዜ ወደ ማታ እንዲሰጧቸው ንጉሡ አዘዘ። ስለ ደመወዛቸው እንዳይጮኹና እንዳያዝኑ እግዚአብሔርም ስለ ጩኸታቸው በእርሱ ላይ እንዳይቆጣ ይፈራልና። 🌼 ጻድቅ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስም በነገሠ በ፴ ዓመቱ የከበሩ ቦታዎች ሕንፃቸው በተፈጸመ ጊዜ ንዋየ ቅዱሳትን ዋጋቸው ብዙ ድንቅ የሆነ የከበሩ የግምጃ ልብሶችንም ላከ። ደግሞም ወደ ቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ኤጲስቆጶሳቶቹን በመያዝ እንዲዘጋጅ እንዲሁም ወደ አንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳትና ወደ እስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ አትናቴዎስ ኤጲስቆጶሳቶቹን በመያዝ ሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ኢየሩሳሌም ተሰብስበው በከበሩ ቦታዎች ውስጥ የተሠሩትን ወይም የታነፁትን አብያተ ክርስቲያናት እንዲያከብሩ። 🌼 ንጉሡም እንዳዘዘ ሁሉም ተሰበሰቡ እስከ መስከረም ወር ዐሥራ ስድስት ቀን ኑረው በዚች ቀን ሁሉንም አብያተ ክርስቲያናት መሠዊያቸውንም አከበሩአቸው የቁርባን ቅዳሴንም ቀድሰው ለምእመናን ሥጋውንና ደሙን አቀበሉ በዚችም ቀን ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታን ሆነ። 🌼 የከበረ መስቀልንም በመሸከም በነዚያ በከበሩ ቦታዎች ዞሩ በውስጣቸውም ለእግዚአብሔር ሰገዱ አመሰገኑትም መስቀሉንም አከበሩት ወደ ሀገሮቻቸውም በሰላም በፍቅር ተመልሰው ገቡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በስቀሉ ኃይልም ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ 🌼 #ቅዱስ_ጦቢት፦ ይህም ጻድቅ በፋርስ ንጉሥ አሜኔሶር እጅ ተማርኮ ወደ ነነዌ አገር የተወሰደ ከንፍታሌም ነገድ የገባኤል ልጅ ነው፤ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ዕውነትና ቅን በሆነ ሕግ ጸንቶ የሚኖር ነው ከወገኖቹም ጋር ከመማረኩ በፊት ለችግረኞች ብዙ ምጽዋትን ይሰጥ ነበር ብዙ ጊዜም የበጎቹን ጠጉርና ከእህሉ ዐሥራቱን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ይወጣ ነበር ከገንዘቡም ከሦስት አንዱን ለድኆች የሚሰጥ ነው። 🌼 በዚያን ጊዜ ሕዝቡ ሁሉም ክደው በዓልና ደማሊ ለሚባሉ ጣዖታት ይሠው ነበር። ወገኖቹም ወደ ነነዌ በተማረኩ ጊዜ ሁሉም የአሕዛብን እህል በሉ እርሱ ግን ሰውነቱን ይጠብቅ ነበር የአሕዛብን መብል እንዳይበላ እግዚአብሔርን ያስበው ነበርና። 🌼 በአንዲት ዕለትም በአደባባይ የወደቀ በድን አግኝተው ነገሩት ወዲያውኑ እህል ሳይቀምስ ተነሥቶ ሔደ ፀሐይም እስከሚገባ ወደ አንድ ቤት ውስጥ አስገብቶ አኖረው ፀሐይ ሲገባም ቆፍሮ ቀበረው በዚያች ሌሊትም እንደ ኃጢአተኛ ሁኖ በእድሞ ሥር ተኝቶ አደረ። በእድሞውም ላይ ወፎች መኖራቸውን ስለ አላወቀ ፊቱን ገልጦ ሳለ ኩሳቸውን ከዐይኖቹ ላይ ጣሉበት ዓይኖቹም ተቃጠሉ ከእሳቸውም ጢስ ወጣ ታወሩም ባለመድኃኒትም ሊያድነው አልቻለም። 🌼 በዚያንም ጊዜ ጦቢት ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ለመነ "አቤቱ በቸርነትህ አስበኝ ወደ ችግረኛነቴም ተመልከት ለመማረክና ለመዘረፍ በአደረግኸን በእኔና በአባቶቼ ኃጢአት ተበቅለህ አታጥፋኝ። አሁንም በፊትህ ደስ የሚያሰኝህን ነገር አድርግ ከመኖር ሞት ይሻለኛልና በሞት እሰናበት ዘንድ አፈርም እሆን ዘንድ ነፍሴን የሚቀበል መልአክን እዘዝ"። 🌼 በዚያችም ዕለት የራጉኤል ልጅ ሣራን በጭኗ ያደረ ክፉ አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን ለሰባት ባሎች አጋብተዋት ወደርሷ ሲገቡ ሁሉንም ስለገደላቸው ስለዚህ የአባቷ አገልጋዮች ያሽሟጥጧት ነበርና ከሽሙጣቸው ያድናት ዘንድ እያለቀሰች ወደ እግዚአብሔር ትለምን ነበር ጸሎቷና የጦቢት ጸሎትም በልዑል እግዚአብሔር በጌትነቱ ልዕልና ፊት ተሰማ። 🌼 ጦቢትም በገባኤል ዘንድ አደራ ያስጠበቀውን የብሩን ነገር አሰበ ልጁ ጦብያንም ጠርቶ "ሳልሞት በገባኤል ዘንድ አደራ ያስጠበቅሁትን ብር ትቀበል ዘንድ ከአንተ ጋራ የሚሔድ በደመወዝ የሚቀጠር አሽከር ፈልግ" አለው።

🌼 "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼            🌼 #መስከረም ፲፭ (15) ቀን። 🌼 እንኳን #ለዲያቆናት_አለቃ_ለቀዳሜ_ሰማዕት #ለቅዱስ_እስጢፋኖስ_ለሥጋው_ፍልሰት ለመታሰብያ በዓል፣ ጠራው ከሚባል አገር ለሆኑ እግራቸው በውኃው ሳይርስ በእግራቸው በባሕር ላይ ሲራመዱ ለነበሩት ለከበረ #ለጻድቁ_ለአባ_ጴጥሮስ በዓለ እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                                                             ✝ ✝ ✝ 🌼 #የዲያቆናት_አለቃ_ቀዳሜ_ሰማዕት #ቅዱስ_እስጢፋኖስ_የሥጋው_ፍልሰት፦ ይህም እንዲህ ነው ከዐረፈበት ጊዜ ብዙ ዓመቶች ከአለፉ በኋላ ሦስት መቶ ዓመት ያህል ከዚያም የሚበዛ ጻድቁ ቈስጠንጢኖስ ሲነግሥ የቀናች ሃይማኖትም ተገልጣ የሕያው እግዚአብሔር አምልኮት በሁሉ ሲዘረጋ ያን ጊዜ የቅዱስ እስጢፉኖስ ሥጋ በአለበት አቅራቢያ የገማልያል ቦታ በትምባል በኢየሩሳሌም በአንዲት ቦታ አንድ ሰው ይኖር ነበር። የዚያም ሰው ስም ሉክያኖስ ነው ተጋዳይ የሆነ እስጢፋኖስም ብዙ ጊዜ በሕልም ተገለጠለት እንዲህም ብሎ አስረዳዉ "እኔ እስጢፋኖስ ነኝ ሥጋዬ በዚህ ቦታ ተቀብሮ" አለ። 🌼 ያም ሉክያኖስ የሚባል ሰው የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ወደ ሆነው መጥቶ በራእይ ያየውን ይህን ነገር ነገረው ኤጲስቆጶሱም ሰምቶ እጅግ ደስ አለው ያን ጊዜም ሁለት ኤጲስቆጶሳትን፣ ካህናትንና፣ የቤተ ክርስቲያንን ሰዎች ሁሉ ከእርሱ ጋራ ይዞ ተነሣ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋ በውስጡ ወዳለበት ወደዚያ ቦታ ደርሰው ሊቆፍሩ ጀመሩ ታላቅ ንውጽውጽታም ሆነ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋ በውስጡ ያለበት ሣጥን ተገለጠ ከእርሱ እጅግ በጎ የሆነው የሽቱ መዓዛ ሸተተ። "በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስገና ሆነ በምድርም ሰላም ለሰው ነፃነቱ ይሰጠው ዘንድ በጎ ፍቃድ" እያሉ ሲያመሰግኑ የመላእክትን ቃሎች ሰሙ። እንዲህም መላልሰው ሦስት ጊዜ አመሰገኑ ኤጲስቆጶሳቱና ካህናቱም የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ በያዘ ሣጥን ፊት ለጌታ ሰገዱ ከዚያም በኋላ ወደ ጽርሐ ጽዮን እስኪያደርሱት ብዙ መብራቶችን አብርተው በመያዝ በማኀሌት ምስጋና እየዘመሩ ተሸከሙት። 🌼 ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ በኢየሩሳሌም ነዋሪ የሆነ የቊስጥንጥንያ ተወላጅ ስሙ እለእስክንድሮስ የሚባል ሰው ነበር ለቅዱስ እስጢፋኖስም ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንን ሠርቶለት ሥጋውን አፍልሰው ወደርሷ ወስደው አኖሩት ከአምስት ዓመት በኋላም እለእስክንድሮስ ዐረፈ ሚስቱም በቅዱስ እስጢፋኖስ አስከሬን ጕን ቀበረችው። ከሌሎች አምስት ዓመቶችም በኋላ የእለእስክንድሮስ ሚስት የቧላን አስከሬን ወደ ቊስጥንጥንያ አገር ይዛ ልትሔድ አሰበች ባሏንም ወደ ቀበረችው እርሱ ባሏ ወደ ሠራት ቤተ ክርስቲያን ሔደች የባሏ ሥጋ ሣጥን ግን የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ በያዘ ሣጥን አምሳል ነበር በእግዚአብሔር ፈቃድ የቅዱስ እስጢፋኖስን ሣጥን ወስዳ እስከ አስቃላን ከተማ ተሸከመችው ከዚያም ወደ ቊስጥንጥንያ ልትጓዝ በመርከብ ተሳፈረች። 🌼 በመርከብ ስትጓዝ ከሣጥኑ ጣዕም ያለው ምስጋናን የምትሰማ ሆነች እጅግም አድንቃ ያን ሣጥን ልታየው ተነሣች በውስጥ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋ ያለበት ሣጥን እንደሆነ ተረዳች ይህም የሆነው ክብር ይግባውና በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነም አወቀች ወደ ኢየሩሳሌም ትመለስ ዘንድ አልተቻላትም ይህንንም ታላቅ ጸጋ ስለሰጣት ልዑል እግዚአብሔርን አመሰገነች። 🌼 ወደ ቍስጥንጥንያ አገርም በደረሰች ጊዜ ያቺ ሴት ወደ ንጉሡ ሒዳ የቅዱስ እስጢፋኖስን ዜና ከእርሱ የሆኑትን ተአምራት ወደ ቍስጥንጥንያ አገር ወደብም እንደ ደረሰ ነገረችው ሰምቶም እጅግ ደስ አለው ንጉሡም ከሊቀ ጳጳሳቱና ከካህናቱ ከብዙ ሕዝቦችም ጋር ወጣ ከወደቡም በክብር አንሥተው ወደ መንግሥት አዳራሽ እስከ አስገቡት ድረስ በፍጹም ደስታ እየዘመሩና እያመሰገኑ ተሸክመውት ተጓዙ። 🌼 ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከእርሱ ተአምራትን ገለጠ በሠረገላ ሥጋውን ጭነው በሁለት በቅሎዎች በሚስቡት ጊዜ ቍስጣንጢንዮስ ከሚሉት ቦታም ሲደርሱ የቅዱስ እስጢፋኖስንም ሥጋ በዚያ እንዲያኖሩ ስለ ፈቀደ የሚስቡት በቅሎዎች ቆሙ። አልተንቀሳቀሱም በቅሎዎችንም ይመቷቸው ጀመሩ "የቅዱስ እስጡፋኖስን ሥጋ በዚህ ሊያኖሩ" ይገባል የሚል ቃል ከአንዱ በቅሎ ሰሙ ይህንንም ያዩና የሰሙ ሁሉም አደነቁ። 🌼 እግዚአብሔርንም አመሰገኑት የበለዓምንም አህያ ያናገራት እርሱ እነዚህን የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ የተሸከሙትን በቅሎዎች ያናገራቸው እርሱ እንደሆነ አወቁ። ንጉሡም በዚያ መልካም የሆነች ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ይህን የከበረና ንጹሕ የሆነ ዕንቈ ባሕርይ በውስጧ እንዲያኖሩ አዘዘ። ይኸውም ለተመሰገነና ለተባረከ ሐዋርያ የዲያቆናት አለቃና የሰማዕታት መጀመሪያ ለሆነ እስጢፋኖስ ሥጋው ነው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ 🌼 #አቡነ_ጴጥሮስ_ዘሃገረ_ጠራው፦ ይህም ቅዱስ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተሰጠ የስእለት ልጅ ነው። በአደገም ጊዜ ለታላቅ ተጋድሎ ክልቡ በቆራጥነት ተነሣ በቀንና በሌሊትም በጾም በጸሎት ተወስኖ ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን የሚያገለግል ሆነ። ሰው የሚመገበውንም ምንም አይመገብም በዱር ያገኘውን ጥቂት ሣርን ይመገባል እንጂ። ደገኛው ምግቡ ግን ክብር ይግባውና የጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ስም ማመስገን ነው። በዚህም ምግባቸው የእግዚአብሔር ምስጋና የሆነ መላእክትን መሰላቸው። 🌼 አሎን በሚባል የወንዝ ውኃ ላይም ይመላለስ ዘንድ ተገባው እግሮቹም አይርሱም ሥጋ እንደ ሌለው መንፈስ እስከ ሚሆን በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ከችግር ብዛትና ከሚለብሰው የብረት ልብስ ክብደት የተነሣ ሥጋው እጅግ ደርቆ የረቀቀም ሁኖ ነበርና በእንዲህ ያለ ተጋድሎም እግዚአብሔርን ከአገለገለው በኋላ ወደርሱ ሔደ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ጴጥሮስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የመስከረም 15 ስንክሳር።                                ✝ ✝ ✝ 🌼 "#ሰላም_እብል_ለጴጥሮስ_ብሕትወ። ኮከበ ጠራው። ወውስተ ዓለም ኅሩም እምበሊዐ ኅብስት ወጼው። እስከ አስተርአየ በአምሳለ ምትሐት ሕስው። ተሴስዮ ሣዕር አብደረ በበድው"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመስከረም_15።                             ✝ ✝ ✝ 🌼 #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወጾሩ ዘርዖሙ። ወሶበ የአትዉ ወጽኡ እንዘ ይትፌሥሑ። ወፆሩ ከላስቲሆሙ። መዝ 125፥6 ወይም መዝ 64፥4። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 4፥39-45 ወይም ሉቃ 10፥30-38።                            ✝ ✝ ✝ 🌼 #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ብፁዕ ዘኀረይኮ ወዘተወከፍኮ። ወዘአኅደርኮ ውስተ አዕፃዲከ። ጸገብነ እግዚኦ እምበረከተ ቤትከ"። መዝ 64፥4-5። የሚነበቡት መልዕክታት የሚነበበው 2ኛ ቆሮ 3፥12-16፣ 2ኛ ጴጥ 2፥15-ፍ.ም፣ የሐዋ ሥራ 7፥55-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 10፥30-38። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ነው። መልካም የቅዱስ እስጢፋኖስ የሥጋው ፍልሰት በዓል ለሁላችን ይሁንልን።

መለኮት ዮሐንስ ይሁንልህ" አላቸውና በቅዱሳን እጆቹ ዳስሷቸው ቢስማቸው ነፍሳቸው ከሥጋቸው መስከረም 15 ቀን ተለይታለች፡፡ ከአባታችን ከአቡነ ገብረ ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸውም ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ።

አገልግሎት ከአቡነ ጽጌ ድንግል ጋር ፈጽመው ኅዳር 8 ቀን ወደ ደብራቸው ደብረ ሐንታ ይመለሳሉ፡፡ 🌼 በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ አቡነ ጽጌ ድንግል ከገዳማቸው ከደብረ ብሥራት ተነሥተው ወደ ደብረ ሐንታ ሄደው እንዲሁ እንደ አቡነ ገብረ ማርያም 40ውን ቀን አግልግሎ ይመለሳል፡፡ እነዚህ ሁለት ቅዱሳን እንደዚህ እያደረጉ በየተራ አንደኛው ወደ ሌላኛው ገዳም እየሄዱ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ በፍጹም ፍቅርና በትሕትና አብረው ሲያገለግሉ ኖረዋል። ይኸውም በራሳቸው በአቡነ ገብረ ማርያም ገድል ላይ እና በአቡነ ዜና ማርቆስ ገድል ገጽ 72-73 ላይ በሰፊው ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ 🌼 የሁለቱ ድርሰታቸው የሆነው "ማኅሌተ ጽጌ" ድርሰት የእመቤታችንንና የልጇን የጌታችንን ሥጋዊ ስደት የሚገልጽ ሲሆን በጨማሪም ስደት የማይገባው አምላካችን ወደ አህጉራችን አፍሪካ ተሰዶ የሠራቸውን ድንቅ ድንቅ ተአምራትና  የእመቤታችንን ንጽሕናዋን ቅድስናዋን አማላጅነቷን የሚያስረዳ ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡ 🌼 አቡነ ገብረ ማርያም አዲስ አፍልሰው በሠሯት ቤተ ክርስያን ውስጥ ልጆቻቸው ተሰበሰቡና "አባታችን ሆይ የት እናድራለን? ማረፊያን ያዘጋጅልን ዘንድ እግዚብሔርን ለምነው" አሉት፡፡ አባታችንም "ይህ ሥራ ለእኔ አይቻለኝምና እናንተ ለምኑት" አላቸው፡፡ እነርሱም "አባታችን ሆይ አትበትነን" ብለው ግድ አሉት፡፡ ልጆቹም ግድ ባሉት ጊዜ አባታችን ተነሥቶ ጸለየ፡፡ ስለዚህም ነገር ሲናገር አባታችን እንዲህ አለ፡- "ከዚህ ነገር አስቀድሞ በቊርባን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣና ይባርከኝ ነበር፣ እናቱ ድንግል ማርያምም ትባርከኝ ነበር፡፡ ስለዚህ ነገር ግን ጌታችን ተቆጣ፣ እምቢ አለኝ፡፡ ከእኔም ፊቱን መለሰ፡፡ እኔም ብዙ አለቀስኹ የእጁን ቡራኬ አጥቻለሁና፡፡ እናቱ ድንግል ማርያምም ፈጽሜ ሳለቅስ ባየችኝ ጊዜ "ወዳጄ ገብረ ማርያም ሆይ ለምን ታለቅሳለህ?" አለችኝ፡፡ እኔም እመቤቴ ሆይ ጌታዬና አምላኬ ፊቱን ከእኔ መልሷልና ስለዚህ አለቅሳለሁ አልኳት"፡፡ እመቤታችን ማርያምም የተወደደ ልጇን "ልጄ ሆይ ወዳጅህ ገብረ ማርያምን በምን ሥራ አሳዘነህ?" አለችው፡፡ ጌታችንም ለድንግል እናቱ "እርሱ አሳዝኖኛል፣ የዮሴፍ ልጅ ያዕቆብ "ይህን ዓለም የሚወድ የእግዚአብሔር ጠላት ይሆናል" (ያዕ 4፡4) እንዳለ ከእኔ ፍቅር ይልቅ የዓለምን ፍቅር ወዷልና" አላት"፡፡ 🌼 እናቱ እመቤታችንም የተወደደ ልጇን "ልጄ ሆይ ወዳጅህ ገብረ ማርያምን አታሳዝነው ይቅር በለው ባጠባሁህ ጡቶቼ አምልሃለሁ" አለችው፡፡ ጌታችንም ይህን ጊዜ ቅድስት እናቱን "የላይኛውን ወይም የታችኛውን ይወድ እንደሆነ ጠይቂው" አላት፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም ከዚያ ቆሞ ነበርና ወደ ለእኔ "የላይኛው ያለህ መንግሥተ ሰማያትን ነው፣ የታችኛው ያለህ ይህች ዓለም ናት" አለኝ፡፡ እኔም ያንጊዜ ይህችን ዓለም አልፈልጋትም ነገር ግን ማረፊያ እንዲሰጠን በጸሎቴ የጠየቁት ልጆቼ ከሞቴ በኋላ ተስፋ እንዳይቆርጡ እንዳይበተኑም ብዬ ነው አለኩት፡፡ ጌታችንም "ገብረ ማርያም ሆይ ለምን ይህንን ታስባለህ? ለልጆችህ እኔ አስብላቸዋለሁና፡፡ ወዳጄ ዳዊት "የጻድቃን ልጆች ይባረካሉ፣ ክብርና ባለጠግነት በቤቱ ነው፣ ጽድቁም ለዘለዓለም ይኖራል" (መዝ 111፡33) ብሎ እንደተናገረ እኔ ለፍጥረት ወገን ሁሉ አስባለሁ" አለኝ፡፡ ይህንንም ብሎኝ ሰላሙን ሰጥቶኝ ወደ ሰማያት ዐረገ"፡፡   🌼 አቡነ ገብረ ማርያም ያደረጓቸው ተአምራት ተነግረው የሚያልቁ አይደሉም፡፡ በብቸኝነት ሳለ በአንዲት አገር የሚኖር ልጁ የሞተበት ሰው የልጁን አስክሬን ወደ አባታችን አምጥቶ በፊታቸው አስቀመጠውና "አባታችን ሆይ ልጄ እንደሞተ ተስፋዬ ሁሉ ጠፍቷልና አሁን ብትወድ ከሞት አንሣው ባትወድ ግን እዚሁ ቅበረው" እያለ አለቀሰባቸው፡፡ አባታችንም የሰውየውን ሁኔታውን አይተው ፈጽመው አለቀሱ፡፡ ልቡናቸውም ታወከባቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ይጸልዩ ዘንድ ተነሡና "…በተቀበረ በ4ኛው ቀን አልዓዘርን ያስነሣኸው አሁንም ይህን ሕፃን አስነሣው…" ብለው ከጸለዩ በኋላ የልጁን እጅ ይዘው "በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ተነሥ" ብለው እፍ አሉበት፡፡ ያንጊዜም ሕፃኑ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ አፈፍ ብሎ ተነሣ፡፡ ለአባቱም "ልጅህን ውሰድ ፈጣሪዬ አስነሣልህ" ብለው ሰጡት፡፡ ሰውዬውም ከአግራቸው ሥር ሰግዶ የእግራቸውን ትቢያና ሰውነታቸውን ሁሉ ሳመው፡፡ ልጁንም ይዞ ፈጽሞ ደስ እያለው ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ 🌼 በአንዲት ሀገርም አንድ ልጅ ብቻ ያላት አንዲት ሴት ነበረች፡፡ ልጁም ወደ አባታችን እየመጣ "አመንኵሱኝ" እያለ ሁልጊዜ ይጠቃቸው ነበር፡፡ አንድ ቀንም እንዲሁ መጣና "አባት ሆይ ካላመነኰሱኝ ወደሌላ ሰው ዘንድ ሄጄ እመነኵሳለሁ" አላቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አባታችን ፈቃደ እግዚአብሔርን ጠይቀው የፍላጎቱን ፈጸሙለትና አመነኰሱት፡፡ ወላጅ እናቱም መጥታ ልጇ የምንኵስናን ልብስ እንደለበሰ ባየች ጊዜ እያለቀሰች ሄደችና ራሷን ወደ ገደል ውስጥ ጨመረች፣ ሞችም፡፡ ሰዎችም ተሰብስበው አለቀሱላትና አስክሬኗን ተሸከመው ይቀብሯት ዘንድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወሰዷት፡፡ ሰዎችም ወደ አባታችን መጥተው "ሴትዮዋ ከመቀበሯ በፊት መጥተው ይዩዋት" አሏቸው፡፡ አባታችንም "ወደ አስክሬኗ አልመለከትም" አሉ፡፡ እነርሱም በእግዚአብሔር ስም ባማሏቸው ጊዜ አባታችን አስክሬኗ ወዳለበት መጡና አዩዋት፡፡ በማግሥቱም ከገነዟት በኋላ አባታችን ከመዝገበ ጸበላቸው በአፏና በጆሮዎቿ ጸበልን ጨመሩባት፡፡ በፊቷም "እፍ" አሉባትና "በጌታዬ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ተነሺ" አሏት፡፡ ያንጊዜም አፈፍ ብላ ከሞት ተነሣች፡፡ አባታችን ከሞት ያስነሷቸው ሰዎች እንዲሁ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ 🌼 ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ሆዱን የታመመ አንድ ሰው ነበር፡፡ እርሱም ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ አቡነ ገብረ ማርያም በመምጣት ጉዳዩን ሳይነግራቸው አንድ ቀን ቆየ፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን የመጣበትን ጉዳዩን በጠየቁት ጊዜ "አባት ሆይ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ታመምኩ፣ እህል አልበላም ውኃም አልጠጣም" አላቸው፡፡ አባታችንም ሆዱን ይዘው በእጃቸው አሻሹትና ምራቃቸውን ቀቡት፡፡ በዚህም ጊዜ በሆዱ ውስጥ ልዩ ልዩ ዓይነት ድንፆች ተሰሙ፡፡ በውሻ ድንፅ አምሳል፣ በድመት ድንፅ አምሳል፣ በዝንጀሮ ድንፅ አምሳልና በቁራዎቸ ድንፅ አምሳል ጮኸ፡፡ አባታችንም ልጁን "ልጄ ሆይ እግዚብሔር አድኖሃልና ወደ ቤትህ ተመለስ" አሉት፡፡ ልጁም "አባቴ ሆይ ተመልሼ ወደቤቴ አንገባም እስከ ዕለቴ ሞቴ ድረስ አልመለስም ከአንተም አልለይም" አላቸው፡፡ አባታችንም "በዚህ መኖር ክፍልህ አይደለምና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለፈወሰህ ወደ ቤትህ ተመለስ" አሉት፡፡ በደስታም ወደ ቤቱ ሄደና በሌላ ጊዜ ከብዙ ሰዎች ጋር መጥቶ አባታችን  ያደረጉለትን ተአምር ለሕዝቡ ሁሉ መሰከረ፡፡ 🌼 አቡነ ገብረ ማርያም በእንዲህ ዓይነት አገልግሎት በተአምራታቸው ድውያንን እየፈወሱ ሙታንን እያስነሡ በወንጌል ቃል የነፍስን ቁስል እየፈወሱ የጌታችንንም መከራውን እያሰቡ ራሳቸውን ከመከራው ተሳታፊ በመሆን ብዙ ከደከሙ በኋላ በሥጋ ሞት ከማረፋቸው በፊት ቅዱሳን መላእክት ነጥቀው ገነትንና ሲኦልን አሳይተዋቸዋል፡፡ ጌታችንም በመጨረሻ ተገልጦላቸው "ወዳጄ ገብረ ማርያም ሆይ ከፍጹም ድካምና መታከት ከኃዘንም ታርፍ ዘንድ ወደ ፍጹም ደስታና ወደ ዘላለማዊ ዕረፍት ወደ እኔ ና" አላቸው፡፡ እርሳቸውም "ጌታዬ ሆይ ምን ዋጋ ትሰጠኛለህ?" ቢሉት ጌታችም ብዙ አስደናቂ ቃልኪዳኖችን ሰጣቸው፡፡ "እንደፈጠርኩህ አግኝቼሃለሁና ክብርህ እንደ መጥምቀ

🌼 "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼          🌼 #መስከረም ፲፭ (15) ቀን። 🌼 እንኳን #ለኢትዮያዊው_ጻድቅ_ማኅሌተ_ጽጌ #ከአባ_ጽጌ_ድንግል ጋር በአንድነት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን ለደረሱት ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ገብረ_ማርያም_ዘደብረ_ሐንታ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ 🌼 #አቡነ_ገብረ_ማርያም_ዘደብረ_ሐንታ፦ ጻድቁ  ሃይማኖታቸው ከቀና፣ ትሩፋት ተጋድሎአቸው ከሰመረ ደጋግ ወላጆቻቸው ከአባታቸው ኒቆዲሞስ እናታቸው አመተ ማርያም በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት ኅዳር 24 ቀን ተወለዱ፡፡ ዕደሜአቸው ለትምህርት ሲደር እነዚህ ደጋግ ወላጆቻቸው ፈሪሃ እግዚአብሔርንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እያስተማሩ አሳደጓቸው፡፡ 🌼 አባታችን በልጅነታቸው የወላጆቻቸውን ላሞች እየጠበቁ ሳለ ከዕለታት አንድ ቀን ጌታችን በወጣት አምሳል ተገለጠላቸውና "ወዳጄ ገብረ ማርያም ሆይ ለምን እንስሳትን ትጠብቃለህ ደቀ መዝሙሬ ጴጥሮስን ዓሣ ማጥመድን ትተህ ተከተለኝ እንዳልኹት በእንስሳት ፈንታ ሰውን ትጠብቅ ዘንድ …" አላቸው፡፡ አባታችንም ይህንን በልቡናቸው ሲያወጡ ሲያወርዱ ለ2ኛ ጊዜ ጌታችን በሚያስፈራ ግርማ በእርሻ መካከል ተገለጠላቸው፡፡ ስለዚህም ነገር አባታችን ሲናገሩ "ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወጣት አምሳል ሁለት ሰዎች ከእኔ ጋር ሳሉ በእርሻ መካከል ወደ እኔ መጣ፤ እነዚያም ከእኔ ጋር የነበሩት ሁለት ሰዎች ባዩት ጊዜ እጅግ ደንግጠው ከግርማው የተነሣ ወዲያና ወዲህ ወደቁ፡፡ በኋላም ተነሥተው ያዩትን መሰከሩ፡፡ ዳግመኛም በሦስተኛ መምጣት ጌታችን እንዲህ አለኝ፡-  "ለምን ዘገየህ አብርሃምን ለአባቱ ርስት ለይቼ ያወጣሁት እኔ እንደሆንኹ አላወቅህምን? አለኝ"፡፡ 🌼 ከዚህም በኋላ አባታችን "እናት አባቱን ያልተወ ሊያገለግለኝ አይችልም" (ማቴ 10፥37) የሚለውን የጌታችንን አምላካዊ ቃል ሰምተው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ወጥተው በመሄድ ቀበት በምትባል ቦታ በዓት ሠርተው በጾም በጸሎት እየታደሉ መኖር ጀመሩ፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር ያገለግላቸው ዘንድ አንዱን ነብር አዘዘላቸው፡፡ ሰዎችም ከአባታችን በረከትን ለመቀበል ወደ እርሳቸው ይመጡ ነበርና ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አንድ ምእመን ወደ አባታችን በመጣ ጊዜ አባታችንን የሚያገለግላቸው ነብር ሰውየውን ዘሎ ያዘው፡፡ ሰውየውም "አባታችን አድኑኝ" እያለ ሲጮኽ አቡነ ገብረ ማርያም ከበዓታቸው ወጥተው ነብሩን በመስቀላቸው ቢባርኩት ኃይሉ ደክሞና ለቃላቸው ታዝዞ ሰውየውን ለቀቀው፡፡ አባታችንም ያንን ወጣት ያየውን ነገር ለማንም እንዳይነግር አዘዙት፡፡ አቡነ ገብረ ማርያም እንደ ሊቀ ነቢያት 40 ቀንና 40 ሌሊት እህል ሳይበሉ ውኃ ሳይጠጡ እየጾሙ ወንጌላትን ያነቡ ነበር፡፡ ከመጾማቸውም ብዛት ሰውነታቸው ፍጹም በደከመና አንደበታቸውም መናገር በሳናቸው ሰዓት የብርሃን እናቱ እመቤታችን ተገልጻላቸው "ወዳጄ ገብረ ማርያም ሆይ ይህን ያህል ገድል የምትጋደል ሰውነትህንስ የምትታስጨንቃት ለምንድነው?" በማለት አጸናቻቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ረሀብና ጥሙ ጠፋላቸው፡፡ 🌼 በአንደኛውም ቀን ከሰማይ እንዲህ የሚል ቃል ወደ አባታችን መጣ፡- "ገብረ ማርያም ሆይ በተክለ ሃይማኖት ወንበር ከተሾመ ከመርሐ ክርስቶስ እጅ የመላእክትን አስኬማ ትቀበል ዘንድ ወደ እርሱ ሂድ" አላቸው፡፡ አባታችንም ወደ ደብረ ሊባኖስ ከመሄዳቸው በፊት አቡነ መርሐ ክርስቶስ በደብረ ሊባኖስ ሆኖ ይህን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ዐውቆ ለደቀ መዛሙርቱ "እነሆ ከፀሐይ ይበልጥ የሚያበሩ ሦስት ከዋክብት ቅዱሳን ይመጣሉ" አላቸው፡፡ አቡነ መርሐ ክርስቶስም እንደተናገረው እነ አቡነ ገብረ ማርያም ደብረ ሊባኖስ ደረሱ፡፡ አቡነ መርሐ ክርስቶስም የምንኵስናን ልብስ አለበሳቸው፡፡ 🌼 አቡነ ገብረ ማርያም ከመነኰሱ በኋላ ወደ በዓታቸው ተመልሰው ከበፊቱ ይልቅ በጾም በጸሎት ሲተጉ ጌታቸን አሁንም ተገለጠላቸውና "በጾም በጸሎት ብቻ ተወስነህ አትቀመጥ ሂድና ወንጌልን አስተምር፣ ድውያንን ፈውስ፣ ሙታንን አንሣ…" ብሎ ነገራቸው፡፡ ዳግመኛም በከበረ እስትንፋሱ እፍ አለባቸውና "መንፈስ ቅዱስን ተቀበል፤ ይቅር ያልካቸው ኃጢአታቸው ይቀርላቸዋል፣ ይቅር ያላልካቸው ኃጢአታቸው አይቀርላቸውም፡፡ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ በምድር ያሰርከው በሰማያት የታሰረ ነው፤ በምድርም የፈታኸው በሰማያት የተፈታ ይሁን" አላቸው፡፡ ጌታችን ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት "ካህናት በሊቃነ ጳጳሳት አፍ ይሾማሉ አንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ አፍ ተሾምህ" እንዳላቸውና እንደሾማቸው ሁሉ አሁንም አባታችን አቡነ ገብረ ማርያምን እንዲሁ ብሎ ራሱ ሾማቸው፡፡ 🌼 አባታችንም እንደታዘዙት ልዩ ልዩ ተአምራትን እያደረጉ ድውያንን እየፈወሱ ሙታንን እያስነሡ ወንጌልን ዞረው አስተማሩ፡፡ ቂሐ ወደምትባል ምድር ገብተው ጎሽ ወደምትባለው ሀገርም ደርሰው ጣዖታትን የሚያመልኩትን የሀገሪቱን ሰዎች አገኟቸው፡፡ ሰዎቹም የሚያመልኩትን ትልቅ ዘንዶ በመስቀሉ ባርኮ ከገደለው በኋላ በውስጧ ወንጌልን እያስተማረ ድውያንን እየፈወሰ ሲቆይ ሰዎቹም አባታችንን "ቅዳሴ ቀድስልን" አሉት፡፡ አባታችንም ስለዚህ ነገር ጌታችንን በጸሎት በጠየቁት ሰዓት "ሳትናዘዛቸውና ሳታጠምቃቸው አትቀድስላቸው" የሚል ቃል ከሰማይ ወደ አባታችን መጣ፡፡ ያንጊዜም ሰዎቹን ሁሉ ሰብስቦ በአብ በወልደ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸውና ቅዳሴ ቀድሶ አቆረባቸው፡፡ 🌼 እመቤታችን ልጇን ይዛ ወደ ግብጽ ከዚያም ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ስትሰደድ በእግሯ እየሄደች በሞረት ዋሻ በአቡነ ዜና ማርቆስ ቦታ ግራርያ ከሚባል ቦታ ተቀምጣ እንደነበር የሐምሌው ድርሳነ ቅዱስ ዑራኤል ይናገራል፡፡ በኋላም ተጭነው ከእነ ልጇ በዚህ በአቡነ ገብረ ማርያም ገዳም በሆነ ቦታ ስታልፍ ጌታችን ለቅድስት እናቱ "ይህች ቦታ ሐንታ ትባላለች፣ በኋለኛው ዘመን በስምሽ የሚጠራ የእኔ ወዳጅና ታዛዥ የሆነ የታላቅ ጻድቅ ቦታ ትሆናለች" ብሎ ስለነገራት በኋላም ትንቢቱ ደርሶ ጻድቁ ገዳማቸውን በዚሁ ቦታ ስለገደሙት ገዳሙ "አማን ደብረ ሐንታ" ይባላል፡፡ ጻድቁ በመንዝና በመርሐ ቤቴ ከ1245-1268 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከ19 በላይ የተላያዩ አብያተ ክርስቲያናትን ተክለዋል፡፡ ጾም ጸሎተኛ ባሕታዊ ከመሆናቸው በተጨማሪ የወንጌል ገበሬ፣ ጻድቅና ደራሲም ናቸው፡፡ 🌼 አቡነ ገብረ ማርያም በጣም ከሚታወቁበት ድርሰታቸው አንዱ የማኅሌተ ጽጌን ድርሰት ከታላቁ ሊቅ ከአባ ጽጌ ድንግል ጋር እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው እመቤታችንንና ፈጣሪ ልጇን በጎ መዓዛ ባላቸው አበባዎችና ፍሬዎች እየመሰለ የሚያመሰግነውን ድርሰቱን በመዝሙረ ዳዊት መጠን 150 አድገው ደርሰዋል፡፡ አቡነ ገብረ ማርያምና አቡነ ጽጌ ድንግል ማኅሌተ ጽጌን በጥምረት ሊደርሱት የቻሉት አቡነ ገብረ ማርያም በወሎ ክፍለ ሀገር በወረኢሉ አውራጃ ልዩ ስሙ ደብረ ሐንታ በሚባለው ገዳም የሕግ መምሕር ሆነው በተሾሙበት ወቅት ነው፡፡ እነዚህም ሁለት ቅዱሳን የዘመነ ጽጌ የማኅሌት አገልግሎትን ሳይለያዩ በሰላምና በፍቅር በአንድነት አግልግለዋል፡፡ ይኸውም የሆነው እንዲህ ነው፡- አንድ ዓመት አቡነ ገብረ ማርያም የክረምት መውጫና የዘመነ ጽጌ ዋዜማ በሆነው መስከረም 25 ቀን ከደብረ ሐንታ መጥቶ ደብረ ብሥራት አቡነ ጽጌ ድንግል ገዳም ገብተው ከመስከረም 25 ቀን እስከ ኅዳር 5 ቀን ያለውን የዘመነ ጽጌ የ40 ቀን

🌼 አቡነ ያሳይ በ13ኛው መ.ክ.ዘመን በአባታቸው የዘመነ ንግሥና መጨረሻ ወደ አርባ ምንጭ ሄደው ከዚያው ሱባኤ ገብተው ፈጣሪያቸውንነ ቢማጸኑ እግዚአብሔርም ከዚያው አካባቢ የሚኖር አንድ ባሕታዊን የመድኃነዓለምን ጽላት እንዲወጣላቸው አዘዘላቸው፡፡ እርሳቸውም ጽላቱን ተቀብለው በጎጃም በኩል አድርገው ወደ ጣና ተመልሰው በዘጌ አከባቢ ሲደረሱ ከጣና ባሕር ዳር ቆመው በየብስ ያለውን ርቀትና በባሕሩ ያለውን ቅርበት አይተው አሁንም ወደ ፈጣሪያቸው በጸሎት ተማጸኑ፡፡ በዚህም ጊዜ ጌታችን ተገልጦላቸው "ወዳጄ ያሳይ ሆይ አትጨነቅ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፣ ከጎንህ ያለውን ድንጋይ በባሕሩ ላይ ጫነው፤ ድንጋዩም ለልጅ ልጅ እኔ ዓለምን ለማሳለፍ እስከምመጣበት ሰዓት ድረስ መታሰቢያ ትሁንህ" አላቸውና ተሰወረ፡፡ አቡነ ያሳይም የመድኃኔዓለምን ጽላት ይዘው በድንጋዩ ላይ እንደተቀመጡ ድንጋዩ እንደታንኳ በባሕሩ ላይ ተንሳፈፈ፡፡ ባሕሩም ከማዕበሉ ብዛት የተነሣ ይታወክ ነበር፡፡ አባታችንም ያለ ምንም ቀዘፋ ልብሳቸውም ውኃ ሳይነካው ቁጭ እንዳሉ ማን እንደአባ ወደ ተባለው ቦታቸው ደረሱ፡፡ 🌼 ከዚህም በኋላ አቡነ ያሳይ ገዳማቸውን ገድመው ወንድሞቻቸውን ሰብስበው በተጋድሎ በመኖር ብዙ ቅዱሳንን አፍርተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የጌታችንን እግር ያጠቡት አቡነ አብሳዲ፣ እንደ ነቢዩ ኤልያስ ዝናብንና ነፋስን የከለከሉት አቡነ ያዕቆብ፣ እሬትን እንደ ማር ያጣፈጡት አቡነ ገብረ ኢየሱስ፣ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጸጋንና ሞገስን የተሞሉት አቡነ ዳንኤል፣ እንደ ንጉሥ ሰሎሞን ጥበብን የተሞሉት አቡነ ፊቅጦርና ሌሎችም ብዙዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በወቅቱም ብዙ የበቁ ቅዱሳን በአካባቢው ነበሩ፡፡ በአጽፋቸውና በእግራቸው በባሕሩ ላይ የሚሄዱ ነበሩ፣ በጸጋ ክንፍ ተሰጥቷቸውም የሚበሩ ነበሩ፡፡ የአቡነ ያሳይ ተአምራቶቻቸው ተነግረው አያልቁም፡፡ በወቅቱ የነበሩት ቅዱሳን ልጆቻቸው "ከቅዱሳን ማን እንደ አባ ያሳይ በከባድ ድንጋይ ላይ ተጭኖ በባሕር ላይ የተጓዘ አለና.." ብለው ይገረሙባቸው ነበር፡፡ ቦታቸውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ "ማን እንደ አባ" ተባለ፡፡ ይህም የአቡነ ያሳይ ገዳም በሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት በደንቢያ ወረዳ በጎርጎራ ጣና ሐይቅ አካባቢ ይገኛል፡፡ 🌼 በጣና ደሴት ላይ ከሚገኙት ታሪካዊ ቦታዎች ውስጥ አንዱ "አትማረኝ ዋሻ" ነው፡፡ ይህም ዋሻ ታሪኩ ከአቡነ ያሳይ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ታሪኩም እንዲህ ነው፦ አትማረኝ ዋሻ በጣና ሐይቅ ደሴቶች መካከል ከሚገኙ ገዳማት መካከል ከማን እንደ አቡነ ያሳይ መድኀኔዓለም አንድነት ገዳም በስተ ምዕራብ አቅጣጫ የጣና ሐይቅን ጉዞ ከገታው አንድ ተራራ ሥር የሚገኝ ዋሻ ነው፡፡ ይህ ዋሻ ለብዙ ዘመናት አንድ ታላቅ አባት የጸሎት በዓት አድርገውት "አትማረኝ" እያሉ የጸለዩበት ቦታ ነው፡፡ አቡነ ያሳይ ወደ ጣና ደሴት ከአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ እና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ጋር በመሆን በጸሎት ይተጉ እንደነበር ገድላቸው ይናገራል፡፡ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸውም ጸጋ በጣና ሐይቅ ላይ እንደ ጀልባ የሚጓዙበት አንድ ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይ በጣና ደሴት ላይ ለአገልግሎት በመፋጠን ላይ እያሉ ዛሬ አትማረኝ ዋሻ ተብሎ ወደሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ አንድ አባት ዋሻው ውስጥ "አትማረኝ፣ አትማረኝ፣ አትማረኝ" እያሉ ሲጸልዩ ያገኟቸዋል፡፡ አቡነ ያሳይም በሰውዬው ጸሎት በመገረም ቀርበዋቸው "አባቴ ምን ዓይነት ጸሎት ነው የሚጸልዩት?" አሏቸው፡፡ ያም አባት "አባቴ እንደ እርስዎ ያሉ አባት መጥተው "አትማረኝ" እያልክ ጸልይ ብሎኝ ነው" በማለት መለሱላቸው፡፡ አቡነ ያሳይም "እንዲህ ዓይነት ምክር የሚመክር ጠላት ዲያብሎስ ነው፡፡ ከዛሬ ጀምረው "ማረኝ" እያሉ ይጸልዩ በማለት አቡነ ዘበሰማያትን አሰተምረዋቸው ይሄዳሉ፡፡ "አትማረኝ" እያሉ ይጸልዩ የነበሩት አባትም "ማረኝ" እያሉ መጸለያቸውን ቢቀጥሉም ብዙ መግፋት ሳይችሉ ቀሩና ጸሎቱ ይጠፋባቸዋል፡፡ ወደ ሐይቁ ሲመለከቱም አቡነ ያሳይ ድንጋዩን እንደጀልባ ተጠቅመው እየሄዱ ነው፡፡ ጸሎቱን ያስጠኗቸው አቡነ ያሳይ ርቀው ሳይሄዱባቸው ያ አባት በውኃ ላይ በእግራቸው እየተራመዱ በመከተል ይደርሱባቸዋል፡፡ ከኋላቸውም ሆነው "አባታችን ያስጠኑኝ ጸሎት ጠፋብኝ፤ እባክዎን እንደገና ያስተምሩኝ" አሏቸው፡፡ አቡነ ያሳይም ሐይቁን በእግራቸው እረግጠው እስኪሄዱ ድረስ ጽድቃቸው የተገለጠውን የእኚህን አባት መብቃት ተመልከተው "አባቴ እግዚአብሔር የልብ ነውና የሚመለከተው እንዳስለመዱት ይጸልዩ የእርስዎ ይበልጣል" ብለዋቸው ሔዱ፡፡ በዚህም ምክንያት ቦታው "አትማረኝ ዋሻ" ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ከአባታችን ከአቡነ ያሳይ ዘመዳባ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ።                                                     ✝ ✝ ✝ 🌼 #አቡነ_ጴጥሮስ_ቀዳማዊ፡- ትውልድ አገራቸው ሸዋ ቡልጋ ልዩ ስሙ ደብረ ጽላልሽ ነው፡፡ ጻድቁ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ለ48 ዓመታት የቅዱስ ገላውዲዮስን ቤተ ክርስቲያን ሲያጥኑ ኖረዋል፡፡ ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አቡነ ሊቃኖስ እጆቻቸው እያበሩ ለገዳሙ መብራትነት ይጠቀሙባቸው እንደነበረው ሁሉ የአቡነ ጴጥሮስ ቀዳማዊም እጆቻቸው እንደፋና እያበራ ለጣና ሐይቅ ገዳማት በመብራትነት ያገለግል ነበር፡፡ ጻድቁ ለ31 ዓመታት ከመላእክት ጋር እየተነጋገሩ የኖሩ ሲሆን መናም ከሰማይ እያወረዱ መነኰሳቱን ይመግቡ ነበር፡፡ድውያንን በመፈወስ፣ ሙታንን በማንሣት ብዙ አስተደናቂ ተአምራት እያደረጉ ወንጌልን በሀገራችን ዞረው በማስተማር እግዚብሔርን ሲያገለግሉ ኖረው መስከረም 14 ቀን በሰላም ዐርፈው ቅድስት ነፍሳቸውን ቅዱሳን መላእክት በክብር ተቀብለዋታል። ከአባታችን ከአቡነ ጴጥሮስ ቀዳማዊ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን!።  ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳንና የመስከረም 14 ስንክሳር።

🌼 "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼            🌼 #መስከረም ፲፬ (14) ቀን። 🌼 እንኳን #ለኢትዮጽያውያኑ_ጻድቃን #ከሰባቱ_ከዋክብት_ለአንዱ ለቀዳማዊው ንጉሥ #ለዓምደ_ጽዮን_ልጅ ለነበሩና ድንጋዩን እንደ ጀልባ ተጠቅመው የጣናን ሐይቅ ለተሻገሩት ለታላቁ አባት #አቡነ_ያሳይ_ዘማንዳባ እና እጆቻቸው እንደፋና እያበሩ #ለጣና_ሐይቅ_ገዳማት_በመብራትነት_ያገለግሉ ለነበሩት #ለፃህና (ጣና) መምህራን ለሆኑ አባቶች ዐሥራ አንደኛ ለሆነ #ለቅዱስ_አባት_ለአቡነ_ጴጥሮስ ቀዳማዊ ለዕረፍታቸው በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                            ✝ ✝ ✝ 🌼 #አቡነ_ያሳይ_ዘማንዳባ፡- አቡነ ያሳይ "ሰባቱ ከዋክብት" ከሚባሉት የሀገራችን ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ እነዚህም "ሰባቱ ከዋክብት" የተባሉት አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አቡነ ያሳይ ዘማንዳባ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘቆየፃ፣ አቡነ ሳሙኤል ዘጣሬጣ፣ አቡነ ታዴዎስ ዘባልታርዋ፣ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤ እና አቡነ ዮሐንስ ዘጉራንቄ ናቸው፡፡ እነዚህን የመላእክትን ሕይወት በምድር የኖሩ ታላላቅ የሀገራችንን ቅዱሳን በአንድ ጊዜ አስተምረውና አመንኲሰው ለጽድቅ ያበቋቸው አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ናቸው፡፡ "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን" የተባሉት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ የኢትዮጵያ ብርሃኗ በሆኑት በአቡነ ተክለ ሃይማኖት እጅ ከመነኰሱ በኋላ አቡነ መድኃኒነ እግዚእም በተራቸው ያስተማሯቸውና ያመነኰሷቸው መነኰሳት ቁጥራቸው በውል አይታወቅም፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ለአቡነ መድኃኒነ እግዚእ "ስፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብት ቅዱሳንን" በመንፈስ ቅዱስ እንደሚወልዱ ትንቢት ተናግረውላቸው ነበር፡፡ የተንቤኑን አቡነ ዐቢየ እግዚእን፣ የዞዝ አምባውን አቡነ አብሳዲን ጨምሮ አባታችን መድኃኒነ እግዚእ ብርሃን ሆነው በጣም ብዙ ቅዱሳንን ያመነኰሱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን" የተባሉት፡፡ 🌼 አቡነ መድኃኒነ እነዚህንም ሰባቱን ቅዱሳን በአንድ ጊዜ ሲያመነኲሷቸው በዚያው ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ገዳሙን በብርሃን አጥለቅልቆት ታይቷል፡፡ ከሰማይም የምስክርነት ድምፅ ተሰምቷል፡፡ በዚህም ምክንያት አንድ ላይ የመነኰሱት እነዚህ ሰባቱ ቅዱሳን "ሰባቱ ከዋክብት" እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ እነዚህም ሰባቱ ከዋክብት የጣናን ባሕር በእግራቸው ጠቅጥቀው ተሻግረው ብዙዎቹን ደሴቱ ላይ ያሉ አስደናቂ የጣና ገዳማትን የመሠረቱት ናቸው፡፡ ከእነርሱም ውስጥ ባሕሩን በእግራቸውም እየረገጡ ጠቅጥቀው የተሻገሩ አሉ፤ በሌላም ቦታ በየብስ የተሰማሩትም ቢሆኑ መጻሕፍቶቻቸውን በአንበሳ ጭነው የተጓዙ አሉ፤ ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይን እንደጀልባ ተጠቅመው በእርሱ ላይ ሆነው ወደ ደሴት የገቡ አሉ፡፡ አንዱ ዛሬ በዓላታቸውን የምናከብራለቸው አቡነ ያሳይ ናቸው፡፡ ቅዱስ ዳዊት "እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው" መዝ 67፥35 ብሎ እንደተናገረ ጻድቁ አቡነ ያሳይ ከእግዚአብሔር በተሰጣቸውም ጸጋ ጣና ሐይቅን የሚያቋርጡት በአንድ ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ድንጋዩን እንደ ጀልባ ተጠቅመው ነበር፡፡ ያ ድንጋይ ዛሬም ድረስ በገዳማቸው ውስጥ በክብር ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ጻድቁ ከአቡነ ሳሙኤል ጋር አብረው ወደዚህ ቦታ መጡ፡፡ ከዚያም የቦታው አቀማመጥ የብስ መሬትና ደሴት መሆኑን አይተው "እግዚአብሔር ፈቅዶ ይችን ደሴት የጸሎት ቦታችን አድርጎ ቢሰጠን በጸሎት እንጠይቀው" ተባብለው ሁሉቱም ቅዱሳን ሱባኤ ገቡ፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችንም ለአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ በገሃድ ተልጦላቸው "ወዳጄ ሳሙኤል ሆይ ይህ ቦታ የአንተ አይደለም የወንድምህ የያሳይ ቦታ ነው፡፡ እኔ ወዳዘጋጀሁልህ ቦታ ወደ ዋሊ ሂድ" ብሎ የዋልድባን ምድር አሳያቸው፡፡ አቡነ ሳሙኤልም የጌታችንን ትእዛዝ ተቀብለው ወንድማቸውን አቡነ ያሳይን ተሰናብተው ወደ ዋልድባ ሄደው ገዳማቸውን አቅንተው ተጋድሎቸአውን በዚያ ፈጸሙ፡፡ 🌼 ጌታችን ዳግመኛም ለአቡነ ያሳይ ተገለጠላቸውና "ወዳጄ ያሳይ ሆይ የአባትህን መንግሥትና የዓለሙን ክብር ከምኞቱ ጋር ለእኔ ብለህ ስለተውክ ይህንኑ ቦታ በዚህ ዓለም ሳለህ ለአንተ፣ ወደ ዘላለማዊ መንግሥቴ ከወሰድኩህ በኋላም ለልጆችህ ምንዳህ አድርጌ ሰጥቼሃለሁ፤ ምሕረቴንም በቦታህ አዘንባለሁ ቸርነቴም አይለያትም፣ ብዙ የመንፈስ ልጆችንም ታፈራለህ፤ ቦታህም እኔ ለፍርድ እስክመጣ ድረስ ትኖራለች" በማለት ቃልኪዳኑን አቆመላቸውና ተሰወራቸው፡፡ "ምንዳህ" ማለት ደመወዝ ማለት ነውና በዚህም "ማንዳባ" ማለት "የአቡነ ያሳይ ምንዳ-ደመወዝ" ማለት ነው ሲሉ አባቶች ገዳሙን "ማንዳባ-ምን እንደ አባ" ብለው ሰየሙት፡፡                            ✝ ✝ ✝ 🌼 #አቡነ_ያሳይ፦ የትውልድ ሀገራቸው ሸዋ ተጉለት ነው፡፡ አባታቸው ንጉሡ ዓምደ ጽዮን ቀዳማዊ ነው፡፡ ይኸውም ከ1296-1326 ዓ.ም የነበረው ነው፡፡ አቡነ ያሳይ በልጅነታቸው በንጉሡ አባታቸው ቤት ሲኖሩ የገዳማ መነኮሳት ለመንፈሳዊ ሥራ ወደ ንጉሡ ዘንድ እየመጡ ደጅ ሲጠኑ ያዩአቸዋል፡፡ በዚህም ጊዜ አባታችን ገና በልጅነታቸው የመነኰሳቱን እግር ያጥቡ ስለነበር በዚሁ አጋጣሚ መነኰሳቱን ስለምንኲስና ሕይወት ይጠይቋቸው ነበር፡፡ መነኰሳቱም ሕይወታቸውን ያስረዷቸዋል፡፡ አቡነ ያሳይም ብሉያትንና ሐዲሳትን ከልጅነታቸው ጀምሮ የተማሩ ስለነበር የአባቶችን ትምህርትና የወንጌልን ቃል በማገናዘብ የፈጣሪያቸው ፍቅር በልቡናቸው እንደ እሳት ነደደ፡፡ ይልቁንም "ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል" የሚለውን የጌታችንን ቃል አሰቡ፡፡ ማቴ 16፥26፡፡ ከዚህም በኋላ የንጉሡ አባታቸውን የአልጋ ወራሽነት ማለትም የንጉሥነትን ክብር ፈጽመው በመናቅ "እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር እራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ" ማቴ 16፥27 ያለውን የጌታችንን ቃል አስበው ንጉሣውያን ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ለምነና ወጡ፡፡ 🌼 ለምነና እንደወጡም ከሸዋ ተነሥተው ወደ ትግራይ ክፍለ ሀገር በአክሱም አቅራቢያ ከሚገኘው ገዳም ደብረ በንኰል ከሚባለው ከአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ደረሱ፡፡ አቡነ መድኃኒነ እግዚእም አቡነ ያሳይ የእግዚአብሔር ጸጋ ያደረባቸው ሰው መሆናቸውንና ወደ እርሳቸውም እየመጡ መሆኑን በመንፈስ ዐውቀውት ስለነበር በደስታ ተቀበሏቸውና በረድእነት ከወንድሞቻቸው ጋር ጨመሯቸው፡፡ አቡነ ያሳይም የገዳም መነኰሳትን በማገልገል በመንፈሳዊ ተጋድሎ ብዙ ደከሙ፡፡ በደብረ በንኰል ገዳምም ብዙ አስገራሚ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ወደ መካነ ገድላቸው በጣና አካባቢ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ "ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን" የተባሉ አቡነ መድኃኒነ እግዚእም ቀደም ብለን የጠራናቸውን "ሰባቱን ከዋክብት" ምግባር ሃይማኖታቸውን፣ ተጋድሎ ትሩፋታቸውንና ገቢረ ተአምራታቸውን አይተው ፈቃደ እግዚአብሔርን ጠይቀው በአንድ ቢያመነኲሷቸው በዚያው ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ገዳሙን በብርሃን አጥለቅልቆት ታይቷል፡፡ ከሰማይም የምስክርነት ድምፅ ተሰምቷል፡፡ ከዚህም በኋላ ከሰባቱ ቅዱሳን ውስጥ ሦስቱ ቅዱሳን አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣ አቡነ ያሳይ እና አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ሆነው ከደብረ በንኰል ገዳም አባታቸውን አቡነ መድኃኒነ እግዚእን ተሰናብተው ወደ ጣና ደሴት መጥተዋል፡፡

🌼 "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼         🌼 #መስከረም ፲፬ (14) ቀን። 🌼 እንኳን #ለሃምሳ_ዓመታት_በዓምድ_ላይ ቆሞ ሲጸልይ ለኖረው #ለአቡነ_አጋቶን_ዘአምድ ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከቀሲስ ዴግና ዕረፍት፣ #ከሰማዕት_ቅዱስ_መቃራ፣ #ከቅዱሳን_በርተሎሜዎስ_ከአውዳራና_ከናሶን ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                          ✝ ✝ ✝ 🌼 #አባ_አጋቶን_ዘዓምድ፦ ይህም ቅዱስ ለግብጽ አገር ደቡብ ከሆነ ተንሳ ከሚባል መንደር የሆነ ነው ወላጆቹም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ለድኆችና ለችግረኞች መመጽወትን የሚወዱ ደጎችና ቸሮች ነበሩ። የአባቱም ስም መጥራ የእናቱም ማርያ ነው የምንኲስና ልብስን ይለብስ ዘንድ የሚተጋና በልቡም ሁል ጊዜ የሚያስብና የሚታወክ ሆነ። 🌼 ዕድሜውም ሠላሳ አምስት ዓመት በሆነው ጊዜ ቅስና ተሾመ ከዚህ ዓለምም የሚወጣበትን መንገድ ይጠርግለት ዘንድ ወደ ገዳም ሒዶ በዚያ እንዲመነኲስ እግዚአብሔርን እየለመነው የከበረች ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል የተጠመደ ሆነ። 🌼 ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት ሰጥቶት ከሀገሩ ወጣ መርዩጥ ወደሚባልም አገር ገባ ከዚያም ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ በመነኰስ አምሳል ከእርሱ ጋር በመጓዝ ወደ ቅዱስ አባ መቃርስ ገዳም እስከ አደረሰው ድረስ እየመራው ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ። ለከበሩ አረጋውያንም ለአባ አብርሃምና ለአባ ገዐርጊ ደቀ መዝሙር ሁኖ ከእሳቸው ጋር ሦስት ዓመት ያህል ኖረ። 🌼 ከዚህም በኋላ በአባ ዮሐንስ ቤተ መቅደስ ፊት አቆሙት በምንኵስናው ልብስና በአስኪማው ላይ ሦስት ቀኖች ያህል ጸልየው አለበሱት ከዚያችም ቀን ወዲህ ተጋድሎውንና የእግዚአብሔርን አገልግሎት እጥፍ ድርብ አደረገ። ተጋድሎውም ሁል ጊዜ በቀንና በሌሊት በመጾም፣ በመጸለይ የሥጋው ቆዳ ከዐጥንቱ እስቲጣበቅ ያለ ምንጣፍም በምድር ላይ በመተኛት ሆነ። ሁል ጊዜም የአባ ስምዖን ዘዓምድን ገድል ያነብ ነበረ መንፈሳዊ ቅናትንም ቀንቶ ራሱን በገድል እሥረኛ ሊያደርግ በልቡ አስቦ ለከበሩ አባቶች አማከራቸው እነርሱም ይህ ሀሳብ መልካም ነው አሉት በላዩም ጸለዩ ከእርሳቸውም በረከትን ተቀብሎ ከገዳም ወጣ ለዓለም ቅርብ ወደ ሆነ ስካ ወደሚባል አገር ሒዶ በአንዲት ትንሽ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀመጠ ምእመናንም ዓምድ ሠሩለት። በዚያ ላይም ወጥቶ እየተጋደለና እያገለገለ ሃምሳ ዓመት ያህል ቆመ። 🌼 በዘመኑም ሰይጣን ያደረበት ሰው ተገለጠ ብዙ ወገኖችንም አሳታቸው እርሱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚቀመጥ ሁኖ ትምህርቱን የሚሰሙ ሕዝቦች የዕንጨት ቅርንጫፎችን በመያዝ በዙሪያው ይቀመጣሉ አባ አጋቶንም ልኮ ወደርሱ አስመጣው በላዩም ጸለየና በሰውዬው ላይ አድሮ ለሰዎች በመናገር የሚያስተውን ሰይጣን ከእርሱ አስወጣው። 🌼 እንዲሁም ሰማዕት ሚናስ ያነጋግረኛል የምትል ሴት ተነሥታ በቅዱስ ሚናስ ስም የውኃ ጒድጓድ እንዲቆፍሩ በጠበሉ ውኃ ተጠምቀው ከደዌያቸው እንዲፈወሱ የአገርዋን ሰዎች አዘዘቻቸው ያቺንም ሴት ወደርሱ አስመጥቶ በላይዋ ጸለየ ርኵስ መንፈስንም ከእርሷ አስወጣው የዚያችንም የአገርዋን ሰዎች አዘዘቻቸው ያችንም ሴት አዘዛቸው። 🌼 ዳግመኛም ሌላ ሰው ተነሣ እርሱም ጋኔን ይዞ ያሳበዳቸውን ሰበሰባቸው ሲደበድባቸውም ለጥቂት ጊዜ ጋኔኑን ያስተዋቸዋል ብዙዎችም ጋኔን የያዛቸው ወደርሱ ተሰበሰቡ ቅዱስ አባ አጋቶንም ወደርሱ እንዲመጣ ወደ ሰውዬው ላከ ሰውዬውም ትእዛዙን ሰምቶ አልመጣም የስሕተት ሥራውንም አልተወም። የዚያችም አገር ገዥ ሲያልፍ የሰበሰባቸው እብዶች ሰደቡት ረገሙትም ስለዚህ ያን ሰው መኰንኑ ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየውና በሥቃዩ ውስጥ ሞተ። ሌላው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድ ቄስ ነበረ እርሱም ከአንዲት ሴት ጋር በዝሙት ወደቀ የአካሉም እኩሌታ በደዌ ተበላሸ ተሸክመውም ወደ አባ አጋቶን አደረሱት እርሱም ጸልዮለት በእግዚአብሔር ስም አዳነው ያንንም ቄስ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ እንዲጠነቀቅና በክህነቱም እንዳያገለግል አዘዘው። ይህም ቅዱስ አባ አጋቶን ብዙ ተአምራትን አደረገ ብዙዎች በሽተኞችንም አዳናቸው። 🌼 ከዚህም በኋላ በመላእክት አምሳል በመልካም ዝማሬ በመዘመር እያመሰገኑት ሰይጣናት ተገለጡለት እርሱ ግን የክብር ባለቤት ክርስቶስ በሰጠው ጸጋ ሽንገላቸውን አውቆ አዳኝ በሆነ በመስቀል ምልክት አማተበባቸው ፈጥነውም ከፊቱ ተበተኑ። 🌼 ክብር ይግባውና እግዚአብሔርም ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው በወደደ ጊዜ ጥቂት ታሞ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ አስረከበ። ከዚህም በፊት ሕዝቡ ወደርሱ ይሰበሰቡና የእግዚአብሔርን መንገድ ያስተምራቸውና በጸሎቱም ከበሽታቸው ይፈውሳቸው ስለነበር አሁን በዐረፈበት ላይ በአገኙት ጊዜ መሪር ልቅሶን አለቀሱ እነርሱ የሚያጽናናቸውን አባታቸውን በማጣት ከእርሱ ከቅዱስ አባት በመለየት የሙት ልጆች ሁነዋልና። 🌼 መላው የሕይወቱ ዘመንም መቶ ዓመት ሆነ ከርሱም ሠላሳ አምስቱን በዓለም ውስጥ ኖረ። ዐሥራ አምስቱን ዓመት በገዳም ኖረ ኃምሳውን በዓምድ ላይ ቁሞ ኖረ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ አጋቶን ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የመስከረም 14 ስንክሳር።                           ✝ ✝ ✝ 🌼 "#ሰላም_ለአጋቶን_አክሊለ_ወሞገሳ። ሀገረ ተንሳ። በብዙኅ ጻሕቅ ለመግሥተ ሰማይ እንዘ የኃሥሣ። ፃመወ ዓመታተ እሥራ ወሠላሳ። ወበላዕለ ዓምድ አዝማናተ፡ኃምሳ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመስከረም_14።                             ✝ ✝ ✝ 🌼 #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ። ከመ ያምሥጡ እምገጸ ቅስት። ወይድኀኑ ፍቁራኒከ"። መዝ 59፥4-5። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 14፥34-ፍ.ም፣ 1ኛ ዮሐ 2፥18-21 እና የሐዋ ሥራ 5፥11-17። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 14፥22-36። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ነው። መልካም የአቡነ ያሳይና የአቡነ ጴጥሮስ የዕረፍት በዓል ለሁላችን ይሁንልን።

                           ✝️ ✝️ ✝️ 🌼 #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ብፁዓን እለ ተኀድገሎሙ ኃጢአቶሙ። ወእለ ኢሐሰበ ሎሙ ኵሎ ጌጋዮሙ። ብፁዕ ብእሲ ዘኢኈለቈ ሎቱ እግዚአብሔር ኃጢአቶ"። መዝ 31፥1-2። የሚነበቡት መልዕክታት 1ቆሮ 7፥12-18፣ ያዕ 5፥14-17 እና የሐዋ ሥራ 19፥17-21። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 11፥5-14። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ባስልዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።          

🌼 "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼           🌼 #መስከረም ፲፫ (13) ቀን። 🌼 እንኳን #ለታላቁና_ቅዱስ የሆነ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_ባስልዮስ አንድ ጎልማሳ አገርልጋይ የጌታውን ልጅ ስለወደዳት እርሷንም ከመውደዱ የተነሣ እርሷን ለማግባት ብሎ ወደ አንድ ከሀዲ ሥራየኛ ሔዶ እግዚአብሔር ክዶ በሰይጣን አምኖ በእጁ ፈርሞ ለሰይጣን ሰጠው ይህንን የጽሕፈት ደብዳቤ በእግዚአብሔር ኃይልና በጸሎቱ #ቅዱስ_ባስልዮስ በመደምሰስ ድንቅ ተአምር ላደረገበት ለመታሰቢያ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ ከከበረ ከባሕታዊ #ከአባ_ይስሐቅ ከመታሰቢያው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                         ✝️ ✝️ ✝️ 🌼 #የቂሣርያ_ሊቀ_ጳጳሳት_ቅዱስ_ባስልዮስ ያደረገው ተአምር፦ ይህም እንዲህ ነው አንድ ጐልማሳ አገልጋይ የጌታውን ልጅ ስለወደዳት ልቡ እርሷን ወዶ እንደ እሳት እስከ ነደደ ድረስ እርሷንም ከመውደዱ ብዛት የተነሣ ወደ አንድ ከሀዲ ሥራየኛ ሔደ። ሥራየኛውም የክህደት ደብዳቤ ጽፎ ሰጠው። ወደ አረሚ መቃብርም ሒዶ በመንፈቀ ሌሊት ደብዳቤዋን ይዞ ወደላይ እጁን አንሥቶ በዚያ እንዲቆም አዘዘው። 🌼 ይህም አገልጋይ ይህን ነገር ተቀብሎ ያ መሠርይ እንዳዘዘው አደረገ። በዚያንም ጊዜ ከሰይጣናት አንዱ መጥቶ ወደ አለቃቸው ወስዶ አደረሰው ያቺንም የክህደት ደብዳቤ ከእጁ ወሰደ። እንዲህም ብሎ ጠየቀው "ንጉሥህ ክርስቶስን ትክደዋለህን? ፈቃድህን ከፈጸምኩልህ በኋላ ወደእርሱ አትመለስምን?" ይህም ጐስቋላ ባሪያ "አዎን ጌታዬ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ" አለው። መስሐቲ ዲያብሎስም "ይህን ልታደርግ በእጅህ ደብዳቤ ጻፍልኝ" አለው። እርሱም በከበረ ደሙ የዋጀውን የክብር ባለቤት ክርስቶስን ክዶ በደብዳቤ ውስጥ የክህደቱን ቃል ጻፈለት። 🌼 በዚያንም ጊዜ ሰይጣን በጌታው ልጅ ልብ ውስጥ የፍትወት እሳትን አነደደ ይህንንም ባሪያ እጅግ ወደደችው ከእርሱም መታገሥ አልተቻላትም። ወደ አባቷ በመጮህ በግልጥ "ከዕገሌ ባሪያህ ጋር ካላጋባኸኝ አለዚያ ራሴን እገድላለሁ" ትለዋለች እንጂ መታገሥ አልተቻላትም። አባትና እናቷም ፈጽሞ አዘኑ በምንም በምን ሊያስታግሥዋት አልቻሉም። የዚያም አገልጋይ ፍቅሩ በየዕለቱ በልቧ ይጨመር ነበር እንጂ። ስለዚህም ራሷን እንዳትገድል አባቷ ፈራ ለዚያ ባሪያ ሰጠው። እርሱም የጌታውን ልጅ ተቀብሎ ወደቤቱ አስገባት። ከርሷ ጋር ያለውን ፍላጎቱንም ፈጸመ። ከእርሱም ጋር ረጅም ጊዜ ከኖረች በኋላ አባትና እናቷም ይቅር ብሎ ኀዘናቸውን ከላያቸው ያርቅላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ኀዘንንና ልቅሶን አብዝተው ነበር። 🌼 ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ ጩኸታቸውን ሰማ ልመናቸውንም ተቀብሎ ይህ የወደደችው አገልጋይ ጐልማሳ ክርስቲያን እንዳልሆነ አስገነዘባት ከእርሷ ጋር በነበረበት በዚህ በረጅም ዘመን አንዲት ቀን እንኳ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሔድ ሥጋውንና ደሙንም ሲቀበል ወይም አዳኝ በሆነ በመስቀል ምልክት ራሱን ሲአማትብ እርሷ አላየችውም። 🌼 ስለእምነቱም ጠየቀችው ግን አልገለጠላትም እርሷም እንዲህ አለችው "አንተ ክርስቲያን ከሆንክ ና በአንድነት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሒድና በፊቴ ቅዱስ ቊርባንን ተቀበል"። እንዲህም በአስገደደችው ጊዜ ስለርሷ ያደረገውን ሁሉ ወደ ሥራየኛ እንደሔደም በሰይጣንም አምኖ እምነቱንም በክርታስ ጽፎ ያንን ክርታስ ለሰይጣን እንደ ሰጠው ነገራት። 🌼 ይህንንም ነገር ከእርሱ በሰማች ጊዜ ደነገጠች መሪር ልቅሶንም አለቀሰች ራሷንም በማወዛወዝ እጅግ ተጸጽታ አዘነች። ያን ጊዜም ፈጥና ተነሣች የቤተ ክርስቲያን ምሰሶ ወደሆነው ወደ ሀገርዋ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ሔደች ከእግሩ በታችም ወድቃ ሰገደችለት በላይዋ የደረሰውን ሁሉ አስረዳችው ለሰው ልጆች ጠላት ከሆነ ከሠይጣን እጅ ፈጽሞ ያድናት ዘንድ ብዙ በማልቀስ ለመነችው። ቅዱስ ባስልዮስም ባሏ የሆነውን ባርያ ወደርሱ ልኮ አስመጣውና ጠየቀው እርሱም የሠራውን ሁሉ አስረዳው ቅዱስ ባስልዮስም "ተመልሰህ ክርስቲያን ልትሆን ከሰይጣንም እጅ ልትድን ትወዳለህን?" አለው ያም ባርያ "ጌታዬ ይሆንልኛልን?" አለ ይህ ቅዱስ አባትም "የፈጣሪህን ስም እየጠራህ ልብህን አጽና" አለው። 🌼 ከዚህም በኋላ ከእርሱ ዘንድ በአንድ ቦታ ዘጋበት በመስቀል ምልከትም አማተበበት እንዲጸልይም አዘዘው ራሱ ቅዱስ ባስልዮስም ስለርሱ ጸለየ። ከሦስት ቀኖች በኋላም ጎበኘው እንዲህም አለው "በእሊህ በሦስት ቀኖች የደረሰብህ ምንድን ነው" እርሱም በላዩ በመጮህ ሠይጣናት ሲያስፈራሩት ያንንም ደብዳቤ ሲአሳዩትና በእርሱ ላይ ሲቆጡ በመከራ ውስጥ እንደኖረ ነገረው ቅዱስ ባስልዮስም "ከእሳቸው ቁጣ የተነሣ አትፍራ እግዚአብሔር ይረዳሃልና አጽንቶም ይጠብቅሃል" አለው። 🌼 ከዚህም በኋላ ጥቂት እንጀራና ውኃ ሰጥቶ ወደ ቦታው መለሰው ቅዱስ ባስልዮስም ስለዚያ አገልጋይ ሒዶ ይጸልይ ጀመረ። ዳግመኛም ከሦስት ቀኖች በኋላ ጐበኘውና በእርሱ ላይ ምን እንደ ደረሰበት ጠየቀው ያ አገልጋይም "ጩኸታቸውን እሰማለሁ ግን አላያቸውም" ብሎ መለሰለት። እንጀራና ውኃም ሰጠውና መከረው ወደ ቦታውም መለሰውና ስለርሱ ሊጸልይ ቅዱስ ባስልዮስ ሔደ። እስከ አርባ ቀኖች ፍጻሜ ድረስ እንዲህ አደረገ። በአርባውም ቀን ፍጻሜ ከእርሱ ስለ ሆነው ጠየቀው ያ አገልጋይም እንዲህ አለው "ቅዱስ አባቴ ሆይ ስለ እኔ ሰይጣንን ስትጣላውና ድል አድርገህ ጥለህ ስትረግጠው በዛሬዋ ሌሊት አየሁ" አለው። 🌼 ቅዱስ ባስልዮስም ይህን ነገር ከእርሱ በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው የገዳማቱን መነኰሳትና ካህናቱንም ጠርቶ ስለዚያ ሰው ያቺን ሌሊት መላዋን እንዲጸልዩባት አዘዛቸ። በነጋ ጊዜም ያንን አገልጋይ ወደ ቤተክርስቲያን እንዲአመጡት የዚያችንም አገር ሕዝብ ሁሉንም ሰብስቦ እጆቻቸውን ወደ ሰማይ አንሥተው "አቤቱ ክርስቶስ ማረን ይቅር በለን" እያሉ ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ እንዲማልዱ አዘዛቸው እንዳዘዛቸውም አደረጉ። 🌼 እንዲህም እያሉ ሲማልዱ ያ ሰው ጽፎ ለሰይጣን የሰጠው የክህደት ደብዳቤ ከሰይጣን እጅ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ወደቀ ሁሉም ደስ ብሏቸው ምስጉን እግዚአብሔርን አመሰገኑት የከበረ አባት ባስልዮስም ባረካቸው ሥጋውንና ደሙንም አቀብሎ ወደ ቤቶቻቸው በሰላም በፍቅር አሰናበታቸው። እነርሱም ስለ ኃጢአታቸው ስርየትና ስለ ድኅነታቸው ፈጽሞ ደስ እያላቸው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይህንን ቅዱስ አባት ባስልዮስን እያከበሩ ወደ ቤታቸው ገቡ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ባስልዮስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የመስከረም 13 ስንክሳር።                            ✝️ ✝️ ✝️ 🌼 "#በዛቲ_ዕለት_እግዚአብሔር_ገብረ። በእደ #ባስልዮስ_መንክረ። በአፍቅሮ ወለት አሐቲ ኀበ መሠርይ ዘሖረ። እንዘ ይከሥት በቅድመ መጽሐፈ ክህደቱ ስውረ። እምእደ ሰይጣን አንገፈ ወፄወወ ገብረ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመስከረም_13።

🌼 "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼           🌼 #መስከረም ፲፪ (12) ቀን። 🌼 እንኳን #በኤፌሶን_አገር በ_431 ዓ.ም (ሦስተኛው ጉባኤ) ሁለት መቶ ኤጲስ ቆጶሳት  በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #በቅዱስ_አባ_ቄርሎስ ሊቀ መንበርነት ንስጥሮስ ለማውገዝ ለተሰበሰቡበት ቀን ለመታሰቢያ በዓል፣ #ለሊቀ_መላእክት_ለቅዱስ_ሚካኤል እግዚአብሔር ወደ አሞፅ ልጅ ወደ #ነቢዩ_ቅዱስ_ኢሳይያስ_ለንጉሡ_ሕዝቅያስ ከደዌው እንዳዳነው በዕድሜው ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እንደተጨመረለት ንገረው ብሎ ለተላከበት ለወራዊ መታሰብያ በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከሰማዕት #ቅዱስ_አፍላሆስ ከመታሰቢያውና ከሥጋው ፍልሰት፣ ከእስክድርያ አገር ከሆኑ ከባልንጀሮቹ ሰማዕታትም ከመታሰቢያቸው፣ #ከሰማዕታት_ከቅዱሳን_ከሉዩራስና_ባሌኒኮስ፣ #ከቅዱስ_ኢያቄምና_ከቅድስት_ሐናም ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                      ✝️ ✝️ ✝️ 🌼 በዚችም ቀን ደግሞ #በኤፌሶን_ከተማ #የቅዱሳን_የሁለት_መቶ_ኤጲስቆጶሳት_ስብሰባ ሆነ ይህም ለታላላቆች ጉባኤያት ሦስተኛ ነው። 🌼 ስብሰባቸውም የተደረገው የታላቁ ቴዎዶስዮስ ልጅ አርቃድዮስ የወለደው ታናሹ ቴዎዶስዮስ በነገሠ በሃያ ዓመት ነው። የስብሰባቸውም ምክንያት የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት በሆነ በንስጡር ነው። እርሱ ስቶ እንዲህ ብሏልና "እመቤታችን ድንግል ማርያም አምላክን በሥጋ አልወለደችውም እርሷ ዕሩቅ ሰውን ወልዳ ከዚህ በኋላ በውስጡ የእግዚአብሔር ልጅ አደረበት ከሥጋ ጋር በመዋሐድ አንድ አልሆነም በፈቃድ አደረበት እንጂ። ስለዚህም ክርስቶስ ሁለት ጠባይ ሁለት ባህርይ አሉት" የተረገመ የ*ከ*ሐ*ዲ ንስጡር የከፋች ሃይማኖቱ ይቺ ናት። 🌼 ስለ እርሱም የተሰበሰቡ እሊህ አባቶች ከእርሱ ጋር ተከራከሩ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው አምላክ እንደሆነ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ በአበሠራት ጊዜ ከተናገረው ቃል ምስክር አመጡ። እንዲህ የሚል "እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው ከአንቺ የሚወለደውም ጽኑዕ ከሀሊ ነው የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል"። ዳግመኛም "እነሆ ድንግል በድንግልና ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች" ብሎ በትንቢቱ ከተናገረው ከኢሳይያስ ቃል ሁለተኛም "ከእሴይ ዘር ይተካል ከእርሱም ለአሕዛብ ተስፋቸው ይሆናል"። 🌼 ዳግመኛም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ ገሠጸው መከረው ስለዚህም እንዲህ ሲል አስረዳው "ክብር ይግባውና የክርስቶስ የመለኮቱና የትስብእቱ ባሕርያት በመዋሐድ አንድ ከሆኑ በኋላ አይለያዩም አንድ ባሕርይ በመሆን ጸንተው ይኖራሉ እንዲህም አምነን ሰው የሆነ እግዚአብሔር ቃል አንዲት ባሕርይ ነው እንላለን"። 🌼 ከ*ሀ*ዲ ንስጥሮስ ግን ከክፉ ሐሳቡ አልተመለሰም ከሹመቱም ሽረው እንደሚአሳድዱትም ነገሩት። እርሱ ግን የጉባኤውን አንድነት አልሰማም ስለዚህም ከሹመቱ ሽረው ረግመው ከቤተ ክርስቲያን ለይተው አሳደዱት ወደ ላይኛውም ግብጽ ሒዶ በዚያ ምላሱ ተጎልጒሎ እንደ ውሻ እያለከለከ በክፉ አሟሟት ሞተ። 🌼 እሊህም ሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት አባቶች ሃይማኖትን አጸኑዋት በዚህም ጉባኤ ውስጥ እንዲህ ብለው ጻፉ "እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእርሷ ሰው የሆነውን የእግዚአብሔርን አካላዊ ቃል በሥጋ ወለደችው"። 🌼 ከዚህም በኋላ ሥርዓትን ሠርተው ሕግንም አግገው በእጆቻቸው ጽፈው ለምእመናን ሰጡ። እኛም የሕይወትንና የድኅነትን መንገድ ይመራን ዘንድ እግዚአብሔርን እንለምነው። ለእርሱም ክብር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።                           ✝️ ✝️ ✝️ 🌼 በዚች ቀን #የመላእክት_አለቃ_የቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። 🌼 በዚችም ቀን ክብር ይግባውና እግዚአብሔር ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢይ ኢሳይያስ ላከው ይቅርም ብሎት ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስ ሒዶ እግዚአብሔር ይቅር እንዳለውና ከደዌው እንዳዳነው በዕድሜውም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እንደ ጨመረለት ይነግረው ዘንድ አዘዘው። ንጉሱም ሚስት አግብቶ ምናሴን እስከወለደው ድረስ እንዲሁ ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን። ምንጭ፦ የመስከረም 12 ስንክሳር።                                                       ✝️ ✝️ ✝️ 🌼 "#ሰላም_ለምቅወምከ_ዘልዑል_ማዕረጋ። እምቅዋመ አእላፍ እንግልጋ። #ሚካኤል_መንፈስ ዘንበለ ሥጋ። ታድኅን ዘተመንደበ ለማዕበለ ባሕር እምጹጋ ወለእለ በበድው ትባልሕ በጸጋ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመስከረም_12።                        ✝️ ✝️ ✝️ 🌼 #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦"ሐለዩ ወነበቡ ከንቶ። ወነበቡ ዓመፃ ውስተ አርያም። ወአንበሩ ውስተ ሰማይ አፉሆሙ"። መዝ 72፥8-9። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 13፥424-44።                          ✝️ ✝️ ✝️ 🌼 #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዐውዶሙ። ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ። ጠዐሙ ወታእሙሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር"። መዝ 33፥7-8። የሚነበቡት መልዕክታት 1ቆሮ 5፥3-11፣ ይሁ 1፥9-20 እና የሐዋ ሥራ 20፥28-31። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 18፥15-19። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ የቅዱስ ቄርሎስ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ሚካኤል ወራዊ በዓልና የኤፌሶን ጉባኤ የተሰበሰቡ የ200 ኤጲስቆጶሳት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።