ግጥም ሲጥም - Gitem Sitem
Kanalga Telegram’da o‘tish
የዘመናችንን ቀለም ያሳያሉ ያልናቸውን የዚህ ትውልድ የስነ ግጥም ውጤቶችን እንጋራ - እናጋራ። ለማካፈል የፈለጋችሁትን በGitem_Sitem ፣ gitemsitem@gmail.com የጸሃፊ ስም እና ርዕስ አክላችሁ ላኩልን። We are all about sharing this generation's poetry. Please email us your pieces gitemsitem@gmail.com
Ko'proq ko'rsatish1 720
Obunachilar
-124 soatlar
-47 kunlar
-1430 kunlar
Postlar arxiv
ልወዳት እየጣርኩ ነው
ቁንጅናዋን አይኔ አክብዶት ከልቤ ጋር ከመከረ
ከጉያዋ የፈለቀ እሳት ውስጤን ካኮማተረ
አቅሜን የያዘችው ቢመስላት እንዳሻት የምትዘውረው
በቀና ልብ ተንደርድሬ ልወዳት እየጣርኩ ነው
ከፍታ ቢሰማው ቀልቧ የወጣ መስሎት ከማማ
ወስኜ ነበር ልረሳት ክብሬን እንዳላስቀማ
ዛሬ 'ምማትር ዞሬ ገጿን እማይ አጮልቄ
ልመራት እንጂ ደፍሬ አይደለም ብርሃን ናፍቄ
እዩልኝ ሰዎች ልብ አርጉ
ድብቅ መናፍስት ካሉበት በዐይኖቿ ሲበረግጉ
ከጠረኗ እጣን ወጥቶ ንቦች ሲውረገረጉ
ከአናብርት ቆዳ አብልጠው አዳኞች እሷን ሲወጉ
ልብ አርጉ ሰዎች እዩልኝ
የወፏ ዜማ ቢያቅታት ንፋስ ስታዜምብኝ
ከአሳ ቀድሞ 'ሚበላሽ ፀዳሏን ስትበትንብኝ
ከረግረግ ጨፌ በጥሼ በጣቷ 'ምታሾፍብኝ
እዩልኝ ልብ አርጉ ሰዎች
በየደፍ በአፀድ በጥጉ ስሜን ቆልላዋለች
ደሞም በውበት ሰክራ ምኑምኔ ትላለች
የልቧን መንፈቅ ከልላ በቀሪው ትጫወታለች
ቁማር መሰላት መዋደድ
የሆነ ስሜት አስይዞ የሆነ ስሜት ደብቆ
ያልሆነ ንዴት መናደድ
ይልቅስ አቅሜን እንዳሻት ቢመስላት የምትዘውረው
እኔስ በቀና ልቤ ልወዳት እየጣርኩ ነው
ሰይፈ ተማም 2010
በጾሙ
ልቤ ጠረጠረ ነገር ነገር አለኝ
ከተኩሎቹ መሃል ፍየል ቢጤ ባገኝ
ስጋዋም ወተቷ መድሃኒት ነው አሉ
ዘምዘም እጠጣለሁ ሲያሻኝ ከጠበሉ
ወይ እታከማለሁ ደሞ በዶክተሩ
ልቤ እንዲጠራልኝ እንዲቀለኝ ቂሙ
እላለሁ ተኩሎቹም አብይን በጾሙ
አብይን በጾሙ አብይን በጾሙ
ሰይፈ ተማም 2010
ከመሬት ነኝ
መሬት አይደል መነሻዬ
መሬት ያጣሁ መሬት ሁኜ
መነሳትን ተጠይፌ
የወደቅኩኝ ተንሳፍፌ
እኔም ራሴ መሬት
ለመብቀያ ያበቀለኝ
ከመሬት ነኝ?
ከምሬት ነኝ?
ከምር የት ነኝ?
ቁንጥር አፈር ዘግኖ በእጁ ካበጃጀኝ
ቁንጽል አንቀጽ ጠቅሶ በእጁ 'ሚያስፈጀኝ
መሆኔ አይደለም ወይ ከመሬትም መሬት
ሲረማመዱብኝ እንቁዬን ደብቄ በቀን እኩለ ሌት
ሲዘንብ እምቦካ የቋጠርኩኝ አለት
ሲያርሱ 'ምበረበር
ሲበትኑ 'ምዘር
የማያዳብረኝ የሰጡኝ ምርጥ ዘር
አለቴን ገድዬ 'ማረገው አፈር
ጨረቃን ጋርጄ ፀሃይ የምሰፍር
ፀሃይ በዛ ብዬ ደሞ ምንጨረጨር
ህዋ ላይ ተጥዬ የማርፍበት የናፈቀኝ
አዎ መሬት ያጣሁ መሬት ነኝ
ቀማሽ ምላስ ሰጥቶ ጣ'ም 'ሚያስቆጥረኝ
ጣፋጭ ስኳር ነስቶ በጨዉ ሲያስመርረኝ
መሆኔ አይደለም ወይ ከምሬትም ምሬት
ወዳጄ ስሞታ ወዳጄ ጣ'ም ሃሞት
የማያጣኝ ከቤት
የማያጣኝ ከሬት
ብሶት የወለደው ብሶ ያንገሸገሸኝ
ጣ'ም ያጣሁ ምሬት ነኝ
አገር ማለት መሬት
አገር ማለት ምሬት
አገር ማለት እኔ
ተምታቶብኝ ድንገት
መሬት ምሬት ምርየት
መሬቱ ሰው አለው
አለው የሰው ኩሩ
'ራሱን እማይነጥል
ከዱሩ ከአፈሩ
ሲጠብቃት ኖሮ
ከሷው ነው አዳሩ
ይኸም ሰው ጨፍግጓል
መረሮታል ጠአሙ
መጣፈጥ ጠፍቶታል
መልኩም ሆነ ስሙ
ለአንድ ቡሃቃ ሊጥ
20 ሺ እያሰሙ
ከምር ወደየት ነው
ከየት ወየት መንገድ
(ከሰከሩም እንኳን)
አይቶ ገምቶ ነው
ኋላ መንገዳገድ
ወይ የሚያቅፉ መስሎ
ትከሻ መላመድ
ወይ እራስን መብላት
ከመሬት መዋደድ
የምን ቆሞ መሄድ
የምን ሄዶ መቆም
በራስ ቤት መታሰር
ቂም ይዞ እንደመፆም
ለመዋደድ ነቅቶ
በፍቅር ነው መሾም
እንዳሹት ከምታሽ
እንደ ደማከሴ
የት እንዳለሁ ሳላውቅ
አድር ይሆን ፈውሼ?
ያለት ስንጣሪ
ከምድር የቀረፀኝ
ቅምሻ ፍርፋሪ
ኮምጥጦ አገረሸኝ
አይኔን አስጨፈነኝ
ኸረ ከምር የት ነኝ?
ታውሮ ሚመራው
መንገዴን ነጠቀኝ
እኔጠፋሁ ልበል
ካለሁስ ወዴት ነኝ
አገር ማለት መሬት
አገር ማለት ምሬት
አገር ማለት እኔ
ተምታቶብኝ ድንገት
... ሆኜ ካለሁበት
ሰይፈ ተማም 2010
ለመስራት
ለመጨረስስ አልሰራም ለመስራት ልጨርስ እንጂ
ተጨርሶ ሲመረቅ እንደሚታደስ መንገድ
ስካሩ ጠፋ ሲባል መልሶ 'ሚንገዳገድ
እንኳን ተሻለህ ሲሉት እንደሚያቃስት ህመመኛ
ለመጨረስስ አንስራ ለመስራት እንጨርስ እኛ
ሰይፈ ተማም 2010
ሁለት አለሜ
መጀመሪያ ሳይሽ ልቤ ምቱ ጠፋው
ግጥሜ ተበላሸ
ቀለሙ እየሸሸ
መጀመሪያ ሳውቅሽ ሰው አለኝ የሚለው
ቃልሽ ልቤን ወጋ
እንዴት ካንቺ ላውጋ
ክንፍ ያለኝ ይመስልጊዜን መራመጃ
ነገን ካንቺ ከረምኩ የዛሬዬን እንጃ
ጸዳልሽን አየሁ ከጎኔ ሲበራ
የቆዘመ ገጼን በሙቀት ሲጣራ
ደሞም ደስስ እያለ መልሶ ሲያስፈራ
እኔና አንቺ ብቻ ካለንበት ቦታ
ከቦን ያለም ሃዘን ከቦን ያለም ሆታ
ቅጽበታት ደምረን ስናረገው አፍታ
ዱካክ እንዳጠረው እንቅልፍ አልባ ጊዜ
ባንኖ መታ ልቤ ባንቺው ስልት አባዜ
ሁለት አለም ኖረኝ
አንደኛው የንቃት ሌላው የትካዜ
ሰይፈ ተማም 2010
ሁለት አለሜ
መጀመሪያ ሳይሽ ልቤ ምቱ ጠፋው
ግጥሜ ተበላሸ
ቀለሙ እየሸሸ
መጀመሪያ ሳውቅሽ ሰው አለኝ የሚለው
ቃልሽ ልቤን ወጋ
እንዴት ካንቺ ላውጋ
ክንፍ ያለኝ ይመስልጊዜን መራመጃ
ነገን ካንቺ ከረምኩ የዛሬዬን እንጃ
ጸዳልሽን አየሁ ከጎኔ ሲበራ
የቆዘመ ገጼን በሙቀት ሲጣራ
ደሞም ደስስ እያለ መልሶ ሲያስፈራ
እኔና አንቺ ብቻ ካለንበት ቦታ
ከቦን ያለም ሃዘን ከቦን ያለም ሆታ
ቅጽበታት ደምረን ስናረገው አፍታ
ዱካክ እንዳጠረው እንቅልፍ አልባ ጊዜ
ባንኖ መታ ልቤ ባንቺው ስልት አባዜ
ሁለት አለም ኖረኝ
አንደኛው የንቃት ሌላው የትካዜ
ሰይፈ ተማም 2010
ግዝት
አድምጡኝ እንጂ አትስሙኝ
በክፋት ጥላቻ በህይወት ገላችሁ
ከነመፈጠሬም በቁሜ ረስታችሁ
የአፈሬን ሳጥን በቅርቡ አይታችሁ
እንዳታለቅሱልኝ ...
ኻላ እንዳላዝንባችሁ
አትክልት አይደለሁ እንባችሁ አይረባኝ
ከሞት አለምልሞ ህይወት አይዘራብኝ
እንዲያው ከንቱ ድካም እንዳይሆንባችሁ
መኖሬን ከድታችሁ ሞቴን ካመናችሁ
ያኔ... በበድኔ ዙሪያ እንዳላይ ከባችሁ
በቁሜ እያለሁ ይኸው ገዘትኳችሁ።
እንዳታለቅሱልኝ...!!!
ኖታ
እዬዬ
ከውዶቹ መሃል አንድ ሰው አነሰኝ
ሀዘን ሆዴ ገብቶ እያንሰፈሰፈኝ
ጠቆረብኝ ውስጤ ልቤም ጨላለመ
ያሸከምኩት ተስፋ በአፈር አከተመ
እዬዬ ለራሴ እዬዬ ለሃገሬ
ታናሼ ሲቀድመኝ እኔ ተገትሬ
እዬዬ ለቋሚ ውዱን ለሸኘ ሰው
ከተመረጠማ የአብስራ ድንቅ ነው
ሰይፈ
ውዴ
ዝምታሽ ቢጨንቀኝ ቴክስትሽ ቢርቀኝ
ስልኬ ያለልማዱ ብሬን ቢምርልኝ
አፌን አሞጥሙጬ ልነግርሽ ቆረጥኩኝ
እቱ የኔ አበባ....
ዝምታሽ ከባድ ነው ሆድን ያሸብራል
ቀልብንም አርቆ አንጀት ያላውሣል.....
ብዬ እንዳልልሽ.... ብዬ እንዳልልሽ
ቃላት አይገዙ በቂ ስንኝ የለኝ
እኔም ካንቺ የባስኩ ስንኞች የከዱኝ
ብቻ....
ጀማሪ መሆኔ እንዳይነቃብኝ
ኝ ኝ ኝ ..... እያልኩኝ
መግጠሙ ደብሮኝ
የሆዴን ሣልሸና ልተኛ ወሠንኩኝ።
(እባክሽ አደራ እንዳትስቂብኝ.ኝ ኝ ኝ..)
ኖታ
40 ልብ
አይ እታባ ...
እንዴት ቀለድሽ ባክሽ
ሆድ ሆዴን ቢበላው ይመጣል ማለትሽ
አልታይህ ቢለኝ የያኔው ተረትሽ
አልጨበጥ ቢለኝ የፊተኛው ተስፋሽ
ይኸው እታባዬ ...... ቧልተኛ ነሽ አልኩሽ
ቁጥር እንደው አያፍር .....
ደንደሱን አስፍቶ ደሞ እያጠበበ፤ ይከንፋል... ይበራል
ሺዘጠኙን በቅጡ ሳንኖር፤ ፪ሺ ሠፍቶ ያተራምሰናል
እሱ ምን አለበት..... እንዳባይ ይነጉዳል...
እኔ አለሁ እዚ በሀሳብ የምርድ
አርባዬን ቀርጥፌ አፋሽ የሆንኩ አመድ
እና እታባዬ.....
የታል ታድያ ያ ልብ የነገርሽኝ ቀድሞ
በ40 ዘመኔ የማገኘው ቆሞ... (አልያም ተጋድሞ)
ከብትንትን ኑሮ የሚገላግለኝ
ከ40 ልብ ህይወት የሚያሰናብተኝ
የታለ እታባ?? ... የታለ??...
🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼
በዚህ አመት ደግሞ ሌላ ውድድር አዘጋጅቼላችኋለሁ በማንኛውም ርዕስ ላይ የተጻፈ የራሳችሁ ግጥም ። format: ርዕስ ፣ ግጥም ፣ የጸሃፊ ስም መልካም ዕድል!!! ልብ በሉ ተሸላሚ የሚሆነው በብዙ ሰው የተወደደው ብቻ ሳይሆን የ 👎 ምልክት የተሰጠውም ጭምር ነው ። ለመላክ @seifetemam የሚለውን በመጠቀም በቀጥታ አድርሱኝ ። በድጋሚ መልካም በዓል!!!
🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼
Endi mavjud! Telegram Tadqiqoti 2025 — yilning asosiy insaytlari 
