ጲንኤል
Kanalga Telegram’da o‘tish
ጲንኤል ...አንዳንድ ጦርነቶች በውስጣችን ይካሄዳሉ። ይህ ቻናል እነዚያ ጦርነቶች በቃላት የሚገለጹበት፣ ሰው ከራሱ ጋር የሚገናኝበት፣ ሀሳብ፣ ትዝታ እና ውስጣዊ ግጭቶች የሚጻፉበት ገጽ። ✍️ እስራኤል ሰይፉ
Ko'proq ko'rsatishMamlakat belgilanmaganToif belgilanmagan
194
Obunachilar
+124 soatlar
+17 kun
-230 kun
Postlar arxiv
194
አይ ፍኖት!
✍️እስራኤል ሰይፉ
https://t.me/Oct13wed
....የያዝኩትን ጂን እያጣጣምኩ
''ተቀበል..." አልኩ ጮክ ብዬ።
ገርሞት አየኝና ተቀበለኝ
''ታፈጫለሽ አሉ ደሞ አይን እንዳለው!"
"ድገመው "
"ብታዪም ባታዪም ዛሬስ ቆርጫለሁ"
... ሰው ሁሉ ግራ ገብቶት ያየኛል።
የኔ ግራ መጋባት እንደባሰ ማን በነገራቸው።
...ፍቅረኛዬ ነች ነበረች ማለቴ ነች ው...ይ ነበረች በቃ😭
.......ሁሌ ሰፈሯ ስመጣ ልክ ወደ ቤታችው መታጠፊያ መንገድ ጋር ስደርስ...
አ..ቤ...ት የሚሰማኝ ሰላም!
የመንገዱ አቀጣጠን ለሷ ብቻ ተብሎ የተሰራ ነው የሚመስለኝ። ግራ ቀኙን በዛፍ ታጅቦ የፈጠረው ድባብ "በዚህ መንገድ የሚያልፍ ሁሉ መቼም ቢሆን ጸሀይ አይበርታበት" የሚል ቃልኪዳን ከላይ የተሰጠው ይመስላል።
እርግጠኛ ነኝ በረሀ ሚሄድ እንኳን ይህን መንገድ ካስታወሰ ጸሀዩ ምንም ነው። ምንም።
ሁሌ እኔን ማግኘት ከፈለገች እዚህች መንገድ ላይ ነው ምትቀጥረኝ።
''እስራ ዛሬ ፍኖትጋ አንሄድም?'' ትለኛለች ስናፍቃት።
ፍኖት ማለት ይህችው መንገድ መሆኗ ነው እንግዲህ።
እኔው ነኝ ያስለመድኳት።
መንገዱ ልዩ መሆኑን አስረድቻት ስም እናውጣላት ተባብለን ስም መረጣ ስትጀምር
" ለምን በራስሽ ስም አንጠራውም?" አልኳት።
ባይዋጥላትም እሺ ነበር ያለችኝ።
የማይለመድ የለ መቼስ ይሄው ለምዳው ፍኖት ጋር እንሂድ ትለኝ ጀምራለች።
ራሷውጋ።
...ዛሬ ታድያ እዛው መንገድ ላይ ቆሜ ፍኖትን እያየሁ ፍኖትን ስጠብቅ ሳትመጣ ቀረች።
እሷው ነበር የቀጠረችኝ ግን አልመጣችም።
ብጠብቅ አትመጣም።
ስልኳም አይሰራም።
ግራ እንደገባኝ ሲመሻሽ ወደቤቴ ሄድኩኝ።
.. ከዚያን ጊዜ በኋላም አንድም ቀን ስለሷ ባልሰማም ሁሌም ግን መንገዱ ጋር ሄጄ ፍኖትን ፈልጌ እመለሳለሁ።
በነጋ ቁጥር ትዝ የሚለኝ የመጨረሻ ቃሏ ነው።
"ፍኖት ጋር አንሄድም?'' የሚለው።
ይህ ትዝ እያለኝ ሁሌ መንገዱ ጋር እሄድና እሷን ሳጣት በንዴት ከመንገዱ ፊትለፊት ያለው ግሮሰሪ እገባለሁ።
ገና ከመቀመጤ በንዴት እያጨበጨብኩ
"ማነሽ አስተናጋጅ አንድ ጂን አምጬልኝ...'' እላለሁ
ልክ ጂኑ እንደመጣ ልጠጣ እጄን ስልክ የፍኖት ቃል ትዝ ይለኛል።
"እስራ መቼም ቢሆን እያየሁህ እንደሆነ እንድታስብ እፈልጋለሁ..." ያለችኝን ቃል።
'' ምን ማለት ነው ደሞ ይህ?'' ስላት እንዲህ ብላ ጉርድ ፎቶዋን ሰጠችኝ።
''ድሮ አባቴ ሊሞት ሲል የመጨረሻ ቃሉ ይህ ነበር። ''ልጄ መቼም ቢሆን እያየሁሽ እንደሆነ አስቢ '' ብሎኝ ጉርድ ፎቶውን ነበር የሰጠኝ። ይኸው ከዛን ቀን ጀምሮ ምንም ነገር ላደርግ ስል አባቴ እንደሚያየኝ አስታውሼ በጥንቃቄ ነው ማደርገው"
ግራ ቢገባኝም ፎቶዋን ተቀብዬ ኪሴ ውስጥ ነበር የከተትኩት።
ጂኑን እንዳነሳሁ መልሼ ቁጭ አደረኩትና ኪሴን ደባበስኩ።
ፎቶዋን አውጥቼ ትንሽ ካመነታሁ በኋላ።
'' አይ እያየችኝማ አልጠጣም'' ብዬ የሰውን ጨዋታ ማድመጥ ጀመርኩ።
ሬስቶራንቷ ከውጭ እንደምትታየው አይደለችም። ውስጧ ብዙ ባህላዊ ነገሮች ይስተዋሉባታል።
በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፈችውም በባህላዊ ቅርጿ ነው።
መሻሽቶ ስለነበር አዝማሪዎች መሰንቆ ይዘው ቤቷን ማማሟቅ ጀምረዋል።
ተቀበል ይላል አንዱ።
ይቀበላል...
"እኔን ያስገረመኝ ከሁሉ ነገርሽ.."
"ድገመው..."
"... አለሁ ብለሽ መጥተሽ እሰው ኪስ መግባትሽ!.. "
https://t.me/Oct13wed
ይጨበጨባል... ይሳቃል... ይፈሸካል
ብቻ ሁሉም በግጥም ብሶቱን ሀዘኑን ደስታውን እርሙን ያወጣል።
አገጣጠማቸው ደግሞ ድንገት ሳይሆን ብሶታቸውን ለማውጣት በመጠጥ አልሳካ ሲላቸው በግጥም ለማውጣት አቅደው የሚሞክሩ ነው የሚመስሉት።
የእነሱን ጨዋታ ሰምቼ መለስ እልና ያልጠጣኋትን ጂን ከፍዬባት ቤቴ እገባለሁ።
ይህ ድርጊቴ ታድያ ልምድ ሆኖ ቀረ።
በነጋ ቁጥር የፍኖት የመጨረሻ ቃል ትዝ ይለኛል፣ መንገዷ ጋር ሄጄ ፍኖትን እጠብቃለሁ፣
... ሳጣት ተናድጄ ወደዛች መከረኛ ግሮሰሪ፣
አዝና ቃሏ ትዝ እያለኝ ፎቶዋን አይቼ ሳልጠጣ ወደ ቤቴ።
እንዲህ እንዲህ እያለ አመታት አለፉ።
ሰው እንዴት እድሜውን በሙሉ ከምንንም ነገር ተቆጥቦ ይኖራል? ብቻ ግን ይመቻት! ዛሬ ቆረጥኩ እንጂ....
....መና የምትባል የተከራየሁበት ቤት ልጅ አለች።
ሁሌ ያለ ስራ ወጥቼ ስገባ እያየች ታዝንልኝ ስለነበር እራት ታመጣልኛለች።
የምታመጣልኝ ምግብ ግን ጣዕሙ እሷ የሰራችው አይመስልም።
ቆንጆ ሴቶች የፊት ብቻ ሳይሆን የእጅ ሙያም እንደሚኖራቸው መና ምስክር ነች።
ስራዬ ፍኖት ጋር እንደሆነ ስለማታውቅ ስራ ፍለጋ ውዬ የምገባ ነው የሚመስላት። ለዛም ይሆናል የምታዝንልኝ።
ሰሞኑን ግን ብዙ ጊዜ እንደምታፈቅረኝ ልትነግረኝ ስትል አስተውላለሁ። ፍኖት እንደምታየኝ ስለማውቅ ምንም ብያት አላውቅም።
እራት አምጥታልኝ እኔው ጋር ቆይታ ልክ ልትሄድ ስትል ብዙ ጊዜ እንዲህ ነው የምትለኝ።
"እስራ... ግን የሆነ ነገር ልነግርህ ነበር... አይደብርህማ?"
''ምንድነው ንገሪኝ ለምን ይደብረኛል?''
'' አይ.. ማለቴ....እ..እ...እወ...እ እ.. ተወው በቃ ቻው ደና እደር ነገ እነግርሃለሁ ''
ሁሌ እንዲህ ብትለኝም እኔ ግን እንዳልገባው ዝም ነው የምላት። ፍኖትስ...?
ዛሬ ታድያ እዛ ግሮሰሪ አንዱ ሰካራም ለአዝማሪው የተናገረው ቅኔ ፍኖትን እንድረሳ መልዕክት ነው የመሰለኝ።
ይህ ሁኔታዪን ፍኖት አስተውላ የላከችው አይነት ነገር።
''እስራ ተነስ እንጂ ረፈደ እኮ! '' እሚል ድምጽ ስሰማ ብንን ብዬ ነበር የነቃሁት። መና ነበረች።
ማታ ራት ካመጣችልኝ በኋላ ስለ ፍኖት እዛው መንገዱ ጋር ወስጄ ፍኖት እየሰማች ስለፍኖት ለመና ልነግራት እና ፎቶውን እዛው መንገድ ላይ ልጥለው አስቤ
''ነገ የምንሄድበት ቦታ ስላለ ጠዋት ቀስቅሽኝ'' ብያት ስለነበር አልነጋልሽ ብሏት ገና በሶስት ሰአት ነበር የቀሰቀሰችኝ።
ያው እስከ 5 ሰአት እተኛ ስለነበር 3 ሰአት ማለት ለኔ አልነጋም።
'እንዴት' ነው ያማረብሽ?'' አልኳት
ፈገግ ብቻ እንጂ ምንም አላለች።
አቤት ፈገግታ የጠዋት ጸሀይ ታስረሳ የለ እንዴ? ሆሆሆ
ልነግራት ያሰብኩትን እንዴት ብዬ እንደምጀምር እያሰላሰልኩ ወደ ፍኖት መንገድ ይዣት ሄድኩ። ደስ እንዳላት ሁኔታዋ ሁሉ ያስትስውቃል። በእርግጥ እሷን ደስ ስላላት እኔም ደስ ብሎኛል።
ከስንት ጊዜ በኋላ ነው ግን እንዲህ ደስ ያለኝ?
እንጃ ምን አልባት ከፍኖት ጋር?
ብቻ እንዲህ እንዲያ ሳስብ ተያይዘን ፍኖት ጋር ስንደርስ የማየውን ላምን አልቻልኩም።
ምን እየተካሄደ ነው ቆይ?
እንዴት ያንን የመሰለ ድባብ መንገድ ዛፉ ይቆረጣል?
ፍኖታችንን...
ማለቴ ፍኖቴን እኮ ነው እየቆረጡ ያሉት!
ግራ እየተጋባሁ ቆራጮቹን ለምን እንደሚቆርጡት ስጠይቅ ጭራሽ ግራ አጋቢ ነው መልሳቸው።
''ልብ ይሰውራል እኮ አታውቅም እንዴ?" አለኝ
''ማለት?''
ዛፎቹ ላይ የሚኖር መንፈስ አለ። ለወንዶች እንደ ሴት ለሴቶች ደግሞ እንደወንድ እየተመሰለ ቀርቦ ልብ ከወሰደ በኋላ ይሰወራል። እዚህ የምታየው ሰው በሙሉ ልቡ እንደተወሰደ የገባው ሰው ነው ልቡን ለማስመለስ..."
የተዘበራረቀ ስሜት ነው የተሰማኝ። ፍኖት ነች ሰዋሪዋ?
ፍኖት የምትባል ልጅ የለችም ማለት ነው?
ትዝ ሲለኝ ፎቶዋን ሰጥታኛለች ለካ...
እጄን ቶሎ ኪሴ ከትቼ ስወጣ የፎቶውን ወረቀት አለ...
https://t.me/Oct13wed
194
ሥላሴ ያዩናል!
✍️እስራኤል ሰይፉ (ቦኤዝ)
የስላሴን ስዕል ሳይ የልጅነት ጊዜዬ ነው ትዝ የሚለኝ።
...አባ ገሪማ የሚባሉ የሥላሴን ዝክር የሚዘክሩ አባት አሉኝ። የሥላሴ ቀን እሳቸው ቤት ለመግባት ታድያ ሽምግልና እንደመስፈርት ይቆጠር ይመስል ልጅ ሆኜ እሳቸው ቤት መግባቴን ልክ ስላሴ ቤት እንደመግባት ነበር የሚሰማኝ። ዝክር ቤቱ ውስጥ ሥላሴ መኖራቸውን ሁሌም ቢሆን እርግጠኛ ነበርኩ። ለዛም ይሆናል ሌላ ጊዜ እንደ ቤቴ የማየውን ቤት የዝክሩ ቀን ለመግባት የምፈራው።
...የአብርሃሙ ሥላሴ የሚባሉትም አብርሐም በስተ እርጅናው ለሥላሴ ዝክር ስለዘከረ እንደሆነ ነበር የሚሰማኝ።
ከአብርሃም በኋላ ሁሉም ሰው ሲያረጅ የሥላሴን ዝክር የሚዘክር ይመስለኝ ነበር። አባ ገሪማ ጋር ስሄድ ሁሌ የማስበው እኔም ስሸመግል እንዴት አድርጌ እንደምዘክር መቼ መዘከር እንደምጀምር ፣ እናም ማን እንደሚያሳውቀኝ...
አንድ ቀን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን የሥላሴን ስዕል አይቼ ከወትሮው ያላስተዋልኩት ነገር ያለ መሰለኝ። ሥላሴ እኔን ብቻ ትኩር ብለው ያዩኛል።
ፈራሁ።
ቦታ ስቀይርም ወደእኔ ዞረዋል...
ምን አድርጌ ይሆን?...
ትንሽ ፈራሁ።
የሸመገለ ሰው ካልዘከረ እንደዛ ስለሚታይ ላለመታየት ነው ማለት ነው የሚዘክረው።
እኔ ደግሞ አልሸመገልኩ ለምንድነው እንደዚህ የሚያዩኝ??
ከፊትለፊት ዘወር አልኩኝና ወደ ውጪ ወጥቼ በበሩ ተከለልኩ።
አጮልቄ ሳይ አሁንም እያዪኝ ነው።
በቃ ዛሬ ጉዴ ነው እያልኩ ወደ ቤቴ ሄድኩኝ።
በነጋታው ለቅዳሴ ስመጣ ይረሱታል ብዬ እንደማያዩኝ ነበር ሀሳቤ።
ግን ጭራሽ የባሰ መስሎ ተሰማኝ።
በቃ ምክንያቱን ሰው ልጠይቅ ይገባል አልኩና አንድ በእድሜው ወደ አርባዎቹ የሚጠጋ ሰው ጋር ጠጋ ብዬ ጠየቅሁት።
''ለምንድነው ግን ሥላሴ እንዲህ የሚያዩኝ?''
መለሰ
''ስለሚጠብቁን ነው። እናም ደግሞ የምናደርጋትን እያንዳንዷን ነገር ስለሚያዩ ሰው የለም ብለን ብንሰራ እንኳ እንዲህ ነው!"
''አንተንም ያዩሃል እንዴ? ''
''አዎን ሁላችንንም ነው የሚያዩን"
"አሁን ግን እኔን ብቻ እኮ ነው የሚያዩኝ" ስል
''እኔንም እያዩኝ ነው ና እስቲ እዚህ ጋር" ብሎ ወደላይ ከፍ ሲያደርገኝ እውነትም ለካ እያዩት ነው!
እኔን ብቻ ስላላዩኝ ደስ አለኝ። ለካ ሁላችንንም ነው የሚያዩት!
ከዛን ቀን በኋላ ብቻዬን ስሆን እንኳን እንደሚያዩኝ ትዝ እያለኝ አልፈራም።
ይጠብቁኛላ።
ስተኛም እንደሚያዩኝ እያሰብኩ ደስ ይለኝ ጀምሯል።
አሁን አድጌም ሲገባኝ ጥበቃቸው ሁሌም እንዳለ ነው። ያኔ ስዕሉን አይቼ ስደበቅ የማልታይ መስሎኝ እኮ ነው። ፕፕፕ
ተደብቄ ሞቻለሁ።
አላየኋቸውም ማለት እነሱ አያዩኝም ማለት አይደለም። አለመታየትም ደግሞ አይቻልም።
አባ ጋር ሥላሴ ሲዘከር እየፈራሁ እቀር የነበርኩት ልጅ ጭራሽ ቀኑ እስኪደርስ ከመጓጓቴ የተነሳ ሌላ ቀንም ቢዘክሩ ተመኘሁ።
https://t.me/Oct13wed
194
🌛የጨረቃ ስሜት...3🌜
✍️እስራኤል ሰይፉ
...አንድ ቀን ታድያ ከረጅም መተቃቀፍ በኋላ በቃ ተባብለን ጉንጯን ልስማት ዘወር ስል... እሷም ጉንጬን ልትስም አስባ ስትዞር ለጉንጭ የላክነው ከንፈር ሄዶ መንገድ ቀረ...
ውስጤ ቢደነግጥም ድንገት እንደተጋጨ መንገደኛ ምንም እንዳልተፈጠረ ቻው ተባብለን ተለያየን።
... ወደ ቤቷ ገብታ መልዕክት ላከች። በነገራችን ላይ ሁሌም ቢሆን ስልክ መልዕክት መላላክ የማይቀር ነገር ነበር... አንድ ቤት ውስጥ ሆነን በስልክ መልዕክት ብቻ ያወራንባቸውም ጊዜያት አሉ።
የዚያን ቀን ታድያ ስለ ክስተቱ ስናወራ አምሽተን አደርን።
መተቃቀፋችንን እሷም ቢሆን ትወደው የነበር ይመስለኛል። እንደውም አንዴ ''የማትረሽው ቀን የቱን ነው?" ስላት
"...እኛ ቤት ሰው አልነበረም አሞኝ ጠርቼህ አቅፈህ አስተኝተኸኝ እዛው እንዳቀፍከኝ የተኛህ ቀን አይረሳኝም" እንዳለችኝ አስታውሳለሁ።
...እቅፏ ግን ሱሴ ነበር ለኔ። እያወራችኝ እንኳ መጨረሻ ላይ እንደማቅፋት አስቤ ፈገግ ስል ይታወቀኝ ነበር።
"ምነው ሳቅህሳ..." ስትለኝ
"አይ!... ወዲህ ነው'' ብዬ አብረን ፈገግ እንልና ወደ ወሬው እንቀጥላለን...
...የመጨረሻ የተቃቀፍንበትን ቀን ደግሞ ትናንት እንደሆነ ሁሉ መቼም ትዝ ይለኛል።
...የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ተፈታኞች ስለነበርን የሰፈሩ ተፈታኞች በሙሉ አንድ ላይ ነበር የምናጠናው። መስቲ ቤት ውስጥ።
ለሊት 5 ሰአት አካባቢ መብራት ሲጠፋ ሁሉም ወደ ቤት ብሎ ሄዶ እኔና መስቲ ቀረን።
እንቅልፋችን ስላልመጣ መብራቱ ከመጣ እንጠብቀው ተባብለን ወሬ ጀመርን... እያወራን ሳይታወቀን ለሊቱ ተጋምሶ 7 ሰአት አልፏል።
... ልሂድ ብዬ እዛው ፍራሽ ላይ እንደተቀመጥን አቀፍኳት።
(...ፍራሹ ለጥናት እንዲመች ይመስለኛል መሬት ወርዶ ነበር...)
እሷም አታወራም እኔም አላወራ... ብቻ ተቃቅፈን ዝም....
ከረጅ...ም መተቃቀፍ በኋላ ድክም ብሎኝ እጄ ሲንቀጠቀጥ ይታወቀኛል... መተው ግን አልፈለኩም...
እንዲሁ ቢነጋ ደስ ባለኝ... ግን መሄዴ ግድ ነውና ተነሳሁ።
...እስከበሩ ሸኝታኝ ቻው ልትል አቀፈችኝና "...ከዛሬ በኋላ ግን ታቅፈኛለች ብለህ እንዳታስብ..." አለችኝ በሹክሹክታ...
...ያኔ ድምጿና ፊቷ ላይ ምንም ግልጽ ያልሆነልኝን ነገር ባነብም አሁን ላይ ሲገባኝ ግን...
...ብቻ ሸኝታኝ ስወጣ ግን ምታወራው የምሯን ሳይሆን ልክ ጨረቃን ስፈልግ ባላገኛት እንኳን በመጣች ጊዜም ቢሆን እንደማያት እንደሚሰማኝ አይነት ነበር የተሰማኝ።
...በዚህ ሁኔታ 12 ተፈትነን እኔም ወደዚህ መጥቼ ስራ ጀመርኩ እሷም ውጤት መጥቶላት ጊቢ ገባች...
ባይገርምህ ኤርሚ... ያኔ ላይ እሷ እንዳለችኝውም ከዛን ቀን በኋላ ተቃቅፈን አናውቅም።
በርግጥ እንደዛኔው ባይሆንም አሁን ላይ እንደ ግርዶሽ ከስንት አንዴም ቢሆን በቴሌግራም እናወራለን..."
...ኤርሚ ማመን አልቻለም... አፉን ከፍቶ እንደሰማኝ ነበር የቀረው።
ሻዩ መኖሩን እንኳ ረስቶት... መጨረሻ ላይ ሲያየው ውሀ ሆኖ ነበር።
.....ሰዓቱ ስለመሸ የተከራየሁት ጊቢ እንዳይዘጋ በመጣደፍ ሒሳቡን ከፈልኩና
"...ዛሬማ ጀመርክልኝ እንጂ አልጨረስንም... ነገ በሰፊው እንቀጥላለን.. "
ብሎኝ ተሰናብቼው ወጣሁ።
...ይቀጥላል 👇👇👇👇👇
https://t.me/Oct13wed
194
🌛#የጨረቃ ስሜት 2...🌜
✍️እስራእል ሰይፉ
ሌላ ምን መፍትሔ አለ?...
ፍቅር'ን ትቶ ከመሸሽ...
ወንድምነትን ትቶ ከመሸሽ...
አኩርፎ መሸሽ ግን መፍትሔ እንደማይሆን የገባኝ ዘግይቶ ነው።
ሳያኮርፉ መራቅ ይቻል ነበር አልነበር እንዴ? ይህ ነበር እኮ መፍትሔው። አልገባኝም እንጂ ማኩረፍ ለካ በጣም መቅረብ ነው!
የሚቀርብህ ሰው ካልሆነ አያኮርፍህም። ምንም ነገር ቢያይብህ ያራሱ ጉዳይ ብሎ ይተውህ ይሆናል እንጂ!
ካኮረፈህማ በዚያ ዙርያ መነጋገርህ አይቀርም ያኔ ችግሩ ይፈታል። እርስ በዕርስ ያለህም ግንኙነት የበለጠ ይጠነክራል። ታድያ እኔ ይህ መች ገብቶኝ። ጭራሽ በማታውቀው ጉዳይ አኩርፌ ምን ማብራርያ ነው መስጠት የምችለው...?
...አንድ ቀን ማታ ውጪ ጨረቃ ላይ ቁጭ ብዬ (ጨረቃን ማየት ያስደድተኛል። ጨረቃ ለሚወዳት ሁሉ ስሜቷን ሳታጋራ ትቀራለች? እንደተወደደች እያወቀች 14 ቀን መጥፋት ምን ይሉታል? ወይንስ ስፈልጋችሁ እንጂ ስትፈልጉኝ አልገኝም ነው?...) ጨረቃን ሳይ መስቲ መጣችና ደብተር ሰጥታኝ ምንም ሳትለኝ ሄደች።
ምን እንደሚሆን እያሰብኩ ደብተሩን ስገልጥ ወደ መሀል ላይ በቀይ እስክሪብቶ አንድ ገጽ የሚሆን ጽሁፍ ተጽፎበታል።
ሙሉ ጽሁፉን አንብቤ ስጨርስ የምለው ጠፍቶኝ መልስ ትሰጠኝ ይመስል ጨረቃ ላይ አፍጥጬ ቀረሁ።
መልዕክቱ አንድ ቦታ ላይ እንዲህ ነበር...
...እስሩ ግን ለምን እንዲህ እንደሆንክ ምንም ሊገባኝ አልቻለም። ማርያምን እኔ እኮ ከእናቴ ልጅ ለይቼ አላይህም ነበር..."
መጨረሻ ላይ ደግሞ ''...እኔ የዳኒ ምትክ ትሆናለህ ብዬ ሳስብ አንተ ግን...
ብቻ የሰው ነገር ግን ይገርማል...
መልስህን እጠብቃለሁ..." ብሎ ይጨርሳል።
ከጨረቃ መልስ ሳጣ ንዴቴ የታወቀኝ እንባዬ ጠብ ሲል ነበር።
'...ወንድሜ ሁነኝ አለችኝ...' ያለው ዘፋኝ ግን እንዲህ ብላው ይሆን እንዴ?..
...ከጨረቃ ጋር ብዙ ስመክር ቆይቼ ነበር አንድ ሀሳብ መጣልኝ። ቆይቶ ሲገባኝ ለካ ጨረቃ ''እኔን እንደወደድከኝ እሷንም ወደሀልና እኔን እንዳታገኝ ሁሉ እሷንም ስለማታገኝ ቢያንስ ወንድምነትህን አትንፈጋት" ብላኝ ነበር!
''...ለምን ሪሰርች ነበር አልላትም?..'' አልኩኝ ለራሴ
"ሞኝ ነህ እንዴ? ምን አይነት ቀልድ ነው? ፊልም መሰለህ እንዴ ቆይ ምን አስበህ ነው...?" ይለኛል ሌላኛው ሀሳቤ
"..አዎ ቢያንስ እንኳ እሷም ሌላ ነገር እያሰበች አትጎዳም ላንተም ማለፊያ ምክንያት ይሆንሀል" አለኝ አንደኛው ሀሳቤ።
በቃ ወሰንኩ... ሳስበው አኩርፌ እንዲሁ ብቀጥል ምንም የማገኘው ጥቅም የለም.. ወይ ፍቅሬ አልቀረ ወይ ወንድም አልሆንኳት... ዝም ብሎ መባከን ነው። ይህ ደግሞ ጥሩ እድል ነው.. በቃ ሪሰርች እንደነበር በጽሁፍ አሳማኝ አድርጎ መጻፍ ነው... ካመነችኝ እሰየሁ ካላመነችኝም ቢያንስ እኔ ጋር ምክንያት እንደሌለ ትረዳ። በእርግጠኝነት ደግሞ ታምነኛለች።
...ተነስቼ ወደ ቤት ገባሁና ጽሁፉን ማርቀቅ ጀመርኩ...
በጽሁፍ ምንም ይቻላል ለካ! መልሼ የጻፍኩትን ሳነበው ውሸት እንደሆነ ለራሴም ተጠራጠርኩት።
...ሰው ለኔ ያለውን ስሜት ማወቅ ስለፈለኩ እና ከዚህ በፊት ሌላ ሰው ላይም እንደሞከርኩት አድርጌ ረዘም ያለ ጽሁፍ ጽፌ አሁን ሪሰርቹን
እንደጨረስኩ... እሚገልጽ ባለ ሁለት ገጽ ጽሁፍ በሰማያዊ እስክሪብቶ ጽፌ መለስኩኝ።
በሚገርም ሁኔታ አመነችኝ። (ከልቧ ይሁን አይሁን እሷው ትወቅ። የሰውን ልብ ማወቅ ከባድ ነውና) በጣም እንደደነቃትም እንደገረማትም ነገረችኝ...
ከዚህ ጽሁፍ በኋላ ሁሉ ነገራችን አንድ ሆነ።
አባባ "...ማውራት አትፈልግማ?.." ብለው ሙድ ቢይዙብኝ እኔ መች ደንቆኝ?
'ደንቆሮ የሰማ እለት ያብዳል' አሉ እውነት እኮ ነው።
አልሰማትም ብዪ የቆየሁት ልጅ ይሄው ዛሬ ብሰማ አበድኩ።
ሙሉ ነገሬ እሷ ጋር ነው
ሲደብረኝ... ደስ ሲለኝ... ሲከፋኝ... በቃ ምን ስሆን እሷ ጋር እንደማልሆን እንጃ! ማንም ምንም ቢል ዴንታ የለኝም።
እሷም ታድያ ዳኒ ተሻሽሎ የቀረበ ይመስል ብሳ ቁጭ አለች።
ምንም ነገር አትደብቀኝም።
ስለ ፍቅረኛዋ በየ ቀኑ ታወራልኛለች።
ምን ያህል እንደተጎዳች ስለማይገባኝ ምንም አልልም ዝም ብዬ ብቻ እሰማታለሁ። አንዳንዴ ሰዎች ለካ ዝም ብሎ የሚሰማቸው ሰው ይፈልጋሉ! ምንም አለማውራቴ ይበልጥ የተስማማት ይመስለኛል (...አንዳንዴ ዝም እንዳልል ብትጠይቀኝም..)
እኔ የማላወራት ለራሴ ስል ነው። ካወራሁ ችግር ነዋ። የራሴን ቁስል መንካቴ ነው። ቁስሌን ካየች ደግሞ በሷ ቁስል ላይ የኔ ተጨምሮ ሌላ ችግር ነው። ስለዚህ ምንም አላወራም።
ለሷ ግን ሙሉ ጆሮ ሆንኳት... ምንም ትበል ምንም ዝም ብዪ እሰማታለሁ... ለረጅም ጊዜ አውርታ ቅልል ሲላት ግን ይታወቀኛል። ይህን ነገር እየወደድኩት መጣሁ...
ቅር ያላትን... ደስ ያላትን... አፍቅራው ስላላፈቀራት ልጅ ሁሉ ስታወራኝ ዝምምም ብሎ ሰምቶ ውስጧን ማቅለል።
ዛሬ ላይ ሳስበው ለካ ለሷ ትልቅ ነገር ነበር ይሄም!..
..ልክ ውሀ በሌለበት ቦታ ቆይቶ መጥቶ ቀዝቃዛ ውሀ እንደመጠጣት...
አውርታ ስትጨርስ እፎፎፎይ ስትል ይታወቀኛል። ቅዝቅዝ....
እኔም ታድያ ከሷ ጋር በመሆኔ ምቾት ስለሚሰማኝ አልደበረኝም።
አውርታ ስትጨርስ ሌሊቱ ተጋምሶ ስለሚሆን ወደ ቤቷ ሸኝቻት ልክ ቤቷ ጋር ልንደርስ ስንል ካለች አቮካዶ ስር እንቆምና ለረጅም ሰዓት ተቃቅፈን እንቆማለን።
... ሳቅፋት በጣም ደስ ይለኛል። ሁሌም ነበር "ምን አለ እንዳቀፍኳት ቢነጋ!...'' የምለው.. አይሆንም እንጂ...
ዛሬም ድረስ የሚገርመኝ የተቃቀፍንበትን ሰአት ሳስብ... ሰው እንዴት ከአንድ ለሊት በኋላ መልሶ ሊገናኝ ለመሰናበት በሚል ሰበብ ከሰላሳ ደቂቃ ባልተናነሰ ተቃቅፎ መንገድ ላይ ይቆማል?..
ያኔ ላይ ሳስብ እኔ የሷን ስሜት ጠብቄ ያን ያህል ሰዓት ስታወራ ስላደመጥኳት ብላ ለኔ ስሜት ስትል ያን ያህል ደቂቃ ቆማ ምታቅፈኝ ይመስለኝ ነበር...
ቆይቼ ግን ሌላ ነገር ማሰብ ጀመርኩ... ምን አልባት እንደ ፍቅረኛዋ እያሰበችኝ ቢሆንስ..? ማለትም ትንሽ ካቀፈችኝ በኋላ ያፈቀረችው ሰው
ትዝ እያላት... ''ምን አለ ያፈቀርኩት ሰው እቅፍ ውስጥ ብሆንስ...?" እያለችዛው አእምሮዋ እሱን እንደሆንኩ አድርጋ እንድትስለኝ አድርጓት..!?
...ስታቅፈኝ ተያይዘን ሌላ አለም ውስጥ እንደምንገባ ግን አውቃለሁ። እኔ በራሴ አለም ውስጥ ጭልጥ ብዬ... ስመለስ ሳላውቀው ደቂቃዎች እንደሚያልፉ ሁሉ እሷም ደግሞ
''...ቆይ ለምን? ... በምወደው ሰው እንዲህ ለምን አልታቀፍኩም?..."
እያለች ስለ ፍቅረኛዋ እቅፋት ደስታ ስታስብ እንዲሁ ተቃቅፈን የምንቆይ አይነት ነገር?.... ብቻ አላውቅም...
...ይቀጥላል👇👇👇👇👇
https://t.me/Oct13wed
194
🌛የጨረቃ ስሜት...🌜
✍️እስራኤል ሰይፉ
''...እስራ ግን ስለኔ ይሄን ሁሉ ነገር ነግሬህ አንተ ግን ፍቅር ይዞህ እንደማያውቅ ነው ዛሬም ምትለኝ?..."
አለኝ ኤርሚ አንድ ቀን ካፌ ቁጭ ብለን ሻዩን ፉት እያለ።
ሁሌ ሲደብረኝ እሱ የሚሰራበት ሱቅ እሄድና እስኪዘጋ ድረስ እዛው ቆይቼ ስራ ሲጨርስ ተያይዘን ወደዚህች ካፌ ነን።
ብረታ ብረት መሸጫ ነው የሚሰራው።
.. ሁሌም አስራ ሁለት ሰአት ስራ ስለሚጨርስ እስካለሁ ድረስ አብረን ነው የምናመሸው።
ዛሬ ታድያ እንደተለመደው እኔ ቡናዪን ይዤ እሱ ሻዩን ፉት እያለ ነው የምናወራበት ርዕስ ለመፍጠር የጠየቀኝ።
ፍቅር ይዞኝ እንደሚያውቅ ለማንም አውርቼ ባላውቅም ዛሬ ግን ልነግረው አስቤአለሁ።
እስከዛሬ ለሰው ያላወራሁትም ምን አልባት ስላላመንኩበት ይሆናል። ሰው ስለ አንድ ጉዳቱ መናገር አልፈለገም ማለት ያ ቁስል ጨርሶ አልሻረለትም አልያም ደግሞ ያፍርበታል ማለት ነው።
እኔም ምን አልባት አፍሬበት አልያም አልሻረልኝ ስለነበረው ታሪኬ ላወራው ያሰብኩት እዚህችው ካፌ ነበር።
''...እስራ ግን ስለኔ ይሄን ሁሉ ነገር ነግሬህ አንተ ግን ፍቅር ይዞህ እንደማያውቅ ነው ዛሬም ምትለኝ?..."
አለኝ ኤርሚ ካፌ ቁጭ ብለን ሻዩን ፉት እያለ።
''... ኤርሚ ምን እንደምልህ አላውቅም። ግን ትንሽ ቆየት ያለ ታሪክ አለኝ ሳልዋሽህ..." አልኩት በማፈር ስሜት
"የምርህን ነው?...'' አለኝ እንደ መደንገጥም እንደ መገረምም እያለ። ፊቱ ላይ እንዴት እስከዛሬ ደበቀኝ የሚል አይነት ጥያቄ ይነበባል።
''...አዎ ኤርሚ። እስከዛሬም የደበቅሁህ..." ብዪ ምክንያት ልደረድር ሲቃጣኝ
''ተው ተው ምክንያቱን ሌላ ቀን እዚሁ እናወራበታለን። አሁን ወደ ታሪኩ... "
ብሎኝ ሻዩን ቁጭ አደረገና መቀመጫውን እያመቻቸ ልክ አይጥ እንዳየ ድመት ታሪኬ ላይ ሊከመር አድፍጦ ቁጭ አለ።
ከነገርኩት በኋላ ይህን የመሰለ ታሪክ ደብቄው ምን ሊለኝ እንደሚችል እያሰብኩ ታሪኬን ጀመርኩ...
"...ምን ብዬ እንደምትጀምርልህ አላውቅም..." አልኩ ከየት እንደምጀምር ጭንቅ ብሎኝ።
''...ገና ከጅምሩ ነው ምፈልገው..." አለኝ። እስኪሰማ ከመቸኮሉ የተነሳ ይቅበጠበጣል።
"...እሺ ታሪኩ የሆነው አስረኛ ክፍል እያለሁ ነው።
... እስከ ስምንተኛ ክፍል መማሬን እንጂ እንዴት እንደተማርኩ ምንም የማስታውሰው ነገር የለም። ዝም ብሎ መነዳት ነገር በለው።
ዘጠነኛ ክፍል ስገባ ሙሉ ክፍሉ ለኔ አዲስ ነበር። የማውቀው ምንም ሰው የለም። ከጓደኞቼ ጋርም ተማሪው ብዙ ስለነበር በ section ተለያይተናል።
...የማይለመድ የለ እንግዲህ ክፍሉን ለምጄው ከጊዜ በኋላ ደስ የሚሉ ክላስሜቶችን አግኝቼ ደስ እያለኝ መማር ጀምሬአለሁ። ማሾፍ ልበለው እንጂ ምን መማር..." ተሳሳቅን ሁለታችንም።
( ኤርሚ ትምህርት ጎበዝ እንደነበርኩ ነው እሚያውቀው)
"...ታስታውስ እንደሆነ ኤርሚ... ትምህርት ቤቱ ከሰፈራችን እሩቅ ስለሆነ ምሳ ቋጥረን ነበር የምንሄደው።
ከሰፈራችን አንድ ትምህርት ቤት የምንማር ብዙ ልጆች ብንኖርም ሁሌ ግን ከዳኒ ጋር ነው የምንሄደው።
እንደምታውቀው ዳኒ አንባቢ ነው። ከሱ ጋር ስለገጠምኩ ይመስለኛል እንደሱ ለመሆን የምሞክረው።
እሱ ብዙ መጽሀፍ የማግኘት እድሉ ስለነበረው ብዙ ሰዎች ይዋሱት ነበር። ታድያ መስቲን የማስታውሳት መጽሐፍ ስትዋስ ነው።
... በርግጥ እስከ ስምንት የተማርነው አንድ ክፍል ውስጥ ነበር። እስከ ስምንት መማሬን እንጂ አብረውኝ የተማሩትን እንኳ የማስታውሰው ጥቂቶቹን ነው። መስታወት ከሌሎቹ በተሻለ ከዳኒ ጋር ትግባባ ነበር።
...ሰፈራችን መግቢያው አካባቢ ሰብሰብ ያሉ የጽድ ዛፎች አሉ። ከስሩ (የደበረው እንዲቀመጥ ነው መሰለኝ) እንደ መቀመጫ ነገር ተሰርቶለታል።
ከትምህርት ስንመለስ ብዙውን ቀን እዚህ ዛፍ ስር ተቀምጠው የምናገኛቸው አባባ የሚባሉ ሸምገል ያሉ ሰው ናቸው።( ሁሌ እዚህ የሚቀመጡት ስለሚደብራቸው ይመስለኝ ነበር)
ሰፈራችን ላይ ለሁላችንም በልጅነታችን ተረት ይነግሩን የነበሩ አባት። አባባ ነው የምንላቸው። (በነገራችን ላይ ስማቸውን እስካሁን አላውቀውም)
... ማታ ማታ ደግሞ ዳኒ ከመስታወት ጋር እዚህ ዛፍ ስር ቁጭ ብለው ነው የሚያመሹት።
ታድያ የሰፈሩ ሰው በሙሉ መስቲን የዳኒ ፍቅረኛ እንደሆነች ነው የሚያወራው። እኔ በግሌ ግን ዳኒን ስለምቀርበው መስቲ ፍቅረኛው እንዳልሆነች አውቃለሁ። (ስለሚነግረኝ )
የሚወራውን ነገር ታድያ ሁለቱም ያውቃሉ ግን ግድም አይሰጣቸውም።
...ዳኒ እና እኔ ከትምህርት ቤት ስንመለስ አንዳንዴ ስለ መስቲም ያወራኝ ነበር..
ስላፈቀረችው ልጅ እና ስለቤተቦቿም ትንሽ ትንሽ ነገር ያወራኝ ነበር።
ኧረ እንደውም አሁን ባላስታውሰውም ሌላ ስምም አውጥቶላታል...
...በቀጣዩ አመት አስራ አንደኛ ክፍል እንደጀመርን ያኔ ለምን እንደሆነ ባላውቅም መስቲን እንዲሁ አኮረፍኳት። (ምን አልባት ዳኒ ወደ ዩኒቨርስቲ ስለሄደ እኔን እንደ ዳኒ ይሆንልኛል ብላ ታስባለች ብዬ ፈርቼ ይሆናል... ብሆንላት ግን ምንድነው ችግሩ?... አሁን ሲገባኝ ዳኒን እንደ ወንድሟ ታየው ስለ ነበር...?!)
... መስቲን መንገድ ላይ ሳገኛት ራሱ አቀርቅሬ ማለፍ ጀምሬአለሁ።
ልትጠራኝ ስትሞክርም ባልሰማ እሄዳለሁ። ምንም ያስቀየመችኝ ነገር እንደሌለ ስታስበው ግራ ገብቷታል።
በግሏ ልታወራኝ ስላልቻለች በሰው ሞከረች። በአባባ።
የተረት አባታችን ስለነበሩ ሁላችንም የሰፈሩ ልጆች ለሳቸው ልዩ ቦታ አለን። ቤታቸውም ለልጆች ሁሌም ክፍት ነው።
ለምን እንደሆነ በማይገባኝ ምክንያት እስካሁን አላገቡም።
ይህን ሁሉ ዘመን ብቻቸውን ነው የሚኖሩት።
''...እስራኤል ይህች ልጅ ምን አድርጋህ ነው ግን ያኮረፍካት?"
አሉኝ አንድ ቀን ሁሌ የሚቀመጡባት ጽድ ስር ሰላም ልላቸው በሄድኩበት።
"...ተዉኝ አባባ ስለሷ ምንም ነገር ማውራት አልፈልግም።"
አልኳቸው በደፈናው። በርግጥ ምንም ምክንያት ስለሌለኝ እንደዛ ብላቸውም እንዳኮረፍኳት አባባ ማወቃቸውም ግን ደስ አላለኝም ነበር።
"... አፈቀርካት እንዴ..?" አሉኝና ፈገግ አሉ።
''...እርስዎ ይቀልዱ!" ብዬ ተነስቼ ወደ ቤት ሄድኩ።
ደንግጫለሁ በጣም! እንዴት እንዲህ ሊሉ ቻሉ...? ያኔ ቢገርመኝም በሌላ ጊዜ እንዴት እንዲህ እንዳሉ ስጠይቃቸው...
''...እሷ እንዳኮረፍካት ስትነግረኝ ስሜቷ ላይ የተረዳሁትን ነው ያልኩህ" ነበር ያሉኝ።..."
...ኤርሚ ተመስጧል... ስልኩ ሲጠራ እንኳ silent አድርጎት ነው የሚሰማኝ። ምንም ነገር እንዳያቋርጠው የፈለገ ይመስላል።
አቤት ጉጉት...
"...በመስቲ ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሴን የጠየቅሁት ቤት እንደገባሁ ነበር።
''...እውነት ግን ስላፈቀርኳት ነው እንዴ ያኮረፍኳት?" ብዬ ራሴን ስጠይቅ እንዲህ ነበር ያገኘሁት መልስ።
...አዎ አፍቅሬ ነው ግን ደግሞ የማይሆን ፍቅር። ዘመድ እንደሆንን እያወቁ ማፍቀር ምን ይሉታል?
ምንስ ነው የሚባለው? ማንስ ነው የሚቀበለኝ?... እሷንስ ምንድንነው የምላት? አፍቅሬሻለሁ..? እሷስ ምን ትላለች?.. ወንድሜ አፈቀረኝ?...
...ለራሴም ግራ የሚሆኑብኝ ብዙ ጥያቄዎች ስላሉ እነሱን የመለስኩ መስሎኝ ነበር ማኩረፌ።
በወንድምነቴ ብቀርባት ደግሞ አልችልማ። ፍቅሬስ? እሷ እንደወንድም ቁጭ ብላ ስታወራኝ እኔ ፍቅሬን ረስቼ እንደ ወንድም አስባለሁ? አልመሰለኝም።
እንደ መፍትሔ ያስቀመጥኩት መራቅን ነበር.... መሸሽ...
...ይቀጥላል👇👇👇👇👇
https://t.me/Oct13wed
194
"እስራ አታስብ እግዚአብሔር ይረዳናል የሚያስፈልገንን የሚያውቅ እርሱ እንጂ እኛ በጣም ያስፈልገናል ያልነው ነገር ግን የማይጠቅመን ሊሆን ይችላል። እኔም አካሄድ ማረም ያለብኝ ይመስለኛል ምን አልባት እማርበትም ይሆናል ለማንኛውም በጸሎት አስበኝ..."
'' ግድ ነው አካሄድ አስተካክል። እንዳገባች አስበህ ለመርሳት ሞክር ፈጣሪም ይረዳሀል አይዞን ወንድሜ። ለማንኛውም ደህና እደር።"
ብዬ ካወራሁት በዃላ ለምን እሷን አላወራትም ብዬ በቀጣዩ ቀን እሷን ማውራት ጀመርኩኝ።
ደህንነቷን ጠይቄ ዋናውን ላወራ ዳር ዳር ስል ራሷ አነሳችልኝ
"...ላገባ ነው ብሮ"
"የት? መቼ... "
"መች እንደሚሆን አልወሰንኩም ግን ሽምግልና ተልኳል.."
" የየት ሀገር ልጅ ነው?"
"እዚሁ እኛጋር ነው አንድ ሰፈር ነን።"
"ለአቤል ነግረሽዋል እንዴ?..''
"አው ካንተ ጋር እያወራሁ ደውዬለት ነበር ይህን ያህል ነገር እሱጋ እንዳለ አላውቅም አልተረዳሁትም ነበር...አልደወለልህም?..."
"ለምን ነገርሽው?እኔው ቀስ ብዬ እነግረው ነበር እኮ...
እሱስ እንደዛ እየሆነ አልተረዳሁትም ማለት አይከብድም? እኔ የጠየኩሽ እኮ እንድትነግሪው አልነበረም ወይንስ ልትጎጂው ነው ሐሳብሽ?... "
''እንዴት እጎዳዋለሁ እኔ? ሲጀምር ሀሳቡን አልተረዳሁትም። የሚቀልድ ነው የመሰለኝ። እኔ አሁን ትልቅ ፀፀት ውስጥ ነኝ ምክንያቱም ልጅነቴ ነው እሱን እንድጎዳው ያደረገኝ"
ብዙ አወራን ከሷ ጋር ግን ምንም የሚፈይድ ወሬ አልነበረም። አንድ የፈየደው ነገር እኔ ልነግረው የተጨነኩትን ነገር እሷ እንደቀልድ እንድትነግረው ማድረጉ ነበር።
በነጋታው ስደውልለት ያለኝ ይህን ነበር
''እስራ የምር ልትፈትነኝ ነው እየመሰለኝ ያለው። ውሸት ነው በለኝ አንተ።
ይህን ከምሰማ አስቀድሞ በወሰደኝ..."
ምን ያህል እንደተጎዳ ድምጹ ያስታውቃል። ምን ብዬ እንደማጽናናው ግራ ሆነብኝ። ምንስ ተብሎ ነው የሚጽናናው?? ምንስ ተብሎ ነው የሚረጋጋው? ምን አለ በአካል አብሬው እንኳ በነበርኩ...
...የአቤል ፍቅር ታድያ ሁሌም ጽሁፉን ሳይ እንድጨምር ያደርገኛል።
#ፍቅር እንደ አቤል
https://t.me/Oct13wed
ተፈጸመ ዝንቱ ፍቅረ አቤል
✍️እስራኤል ሰይፉ
194
...የቀጠለ
.....መጀመርያ ቃለአብ ስለ አቤል ፍንጭ ሊነግረኝ ያለበትን ቀን በተለየ ሁኔታ አስታውሰዋለሁ።
በወረቀት ላይ የክፍሉን አቀማመጥ ስሎ አቤል እና ሰላም የሚቀመጡበትን ወንበር በመክበብ ነበር ወረቀቱን የሰጠኝ።
የክፍሉን ወንበር አቀማመጥ ከመሳል በስተቀር ምንም አይነት ጽሁፍ እንዳልነበረው አስታውሳለሁ። ለዛም ይሆናል በተለየ ሁኔታ እንደ ትዝታ ላስቀረው የቻልኩት።
...ሁላችንም ውስጥ ለሰው ለማስረዳት መናገር የምንፈራው/የምናፍረው ወይ ሌላ ሰው እንዳይሰማ አልያም በተለያየ ምክንያት ቃል ላማናወጣባቸው ግን ደግሞ ሰዎች እንዲረዱን የምንፈልጋቸው ነገሮች አሉ።
እነዛ ሰዎች አልረዳ ካሉን ደግሞ ቁጥርን በቃላት በመሰየም ሊሆን ይችላል.. ስዕል በመሳል..አልያም የራሳችንን ኮድ በመጠቀም... ብቻ የራሳችን የሆነ የማስረጃ መንገድ እንጠቀማለን።
ቃለአብ ታድያ ለመጀመርያ ጊዜ ስለሚነግረኝ ሼም ይዞት ይሁን አልያም ሌላ ምክንያት... ወረቀቱን በመክበብ ያለ ምንም ቃላት የገለጸልኝ መንገድ ቶሎ ስለገባኝ ይመስለኛል እንዳልረሳው ሆኖ ትቀርጾብኛል...
...#አቤል ስላለበት ሁኔታ ለኔ አለመንገሩ መጋረጃ አለመፈለግ ይመስለኛል።
ከመንገሩ በፊት እኔ ባይገባኝም ሰዎች ግን የሱ ሁኔታ እየገባቸው ስለ እሱ ትምህርት መቀነስ፣ ስለ ሰላም የቀደመ ህይወት ስለመሳሰሉት... ማውራት ጀምረው ነበር። የሆዱን በሆዱ ይዞ ለማንም ስለማይናገር ውስጡ የያዘው ነገር ውጤቱ ለሌሎች መታየት ጀምሮ ነበር።
... ሁላችንም የሆነች ነገር ስትሰማን የግድ ለአንድ ሰው ካልተነፈስናት እያደር ትመርዘንና ውጤቷን በአካላችን አልያም በዙርያችን (በትምህርታችን... በምንሰራው ስራ...) ትኩረት እንድናጣ አድርጋ ለሰዎች ታጋልጠናለች።
ውስጣችን መቅደሳችን ነው። ይህን መቅደስ የራሳችን ሰዎች እንዲገልጡ እስካላደረግን ድረስ የእኛ ያልሆኑ አካላት እንደፈለጉት አድርገው በፈለጉት አቅጣጫ ለማንም ይገልጡብናል።
የራሳችን ሰው ብናጣ እንኳን የግድ መዘጋት ስለሌለበት ''ቀና ቢታጣ ይመለመላል ጎ*ጣ'' እንዲሉ አንዳንዶች እብደስስ መጋረጃ ሸፈኑልን ስንል ሸፍነው ቢያሳዩም የተሻለ ልንመርጥ ግድ ይለናል።
ታድያ መጋረጃ ከመጋረጃ ይለያያል። ስስ አለ ወፍራምም አለ።
'የመቅደሳችን መጋረጃ ገላጭ ማን ነው?' የሚለውን መወሰን የራሳችን ፋንታ ነው።
...አቤልም እንዲሁ ነበር ሲጋለጥ የነበረው። ባልወፍርም የመቅደሱ መጋረጃ እሆንለት ዘንድ ቅርቡ እኔ ነበርኩ።
ሲከፋው ይደውልልልኛል ለኔ ሲያወራኝ ትንሽ ቀለል ይለዋል። ፈጣሪ ይመስገን እንደድሮው ባይሆንም ወደ ንባቡ ተመልሷል። ይወራ የነበረውም ቀንሶ የነበር ይመስለኛል።
አይደርስ የለ አስራ ሁለተኛ ክፍል ፈተናን ተፈተንን።
...ውጤት እንደወጣ ቀድሜ ያየሁት የሰላምን ነበር። ውጤቷ ከ 50% በላይ ቢሆንም በጊዜው ማለፊያ ይዘገይ ስለነበር ማለፍ አለማለፋችንን ለማወቅ የግድ ማለፊያ እንድንጠብቅ የሚያደርግ ውጤት ነበር የመጣው። አቤል ግን ማለፉን ከወዲሁ እርግጠኛ ነበር...
...ማለፊያ ሲነገር ታድያ እሱ ቢያልፍም እሷ ግን 3 ነጥብ አንሷት ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ስለሷ ልነግረውም ላወራውም አልፈለኩም።
... አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ስለ ህመማቸው ምንም ማድረግ የማንችል ከሆነ መጠየቁ ቁስላቸውን መነካካት ስለሚሆን እስኪሽር ድረስ ባንጠይቃቸው ይሻላል።ቁስላቸው የሻረ ቀን ታድያ ስለቁስላቸው ጊዜ ራሳቸው ይነግሩናል።
...አቤል ዩኒቨርስቲ ሄዶ ትምህርት እስኪጀምር ድረስ በዚህ ጉዳይ አላወራንም።
ጊቢ ከገባ በኋሏ አንድ ቀን እንዲህ አለኝ...
''እስራ.. ለምን አንተ ልታስረዳት አትሞክርም ግን?..
ማለት እኔ ሳወራት ስለዛ ጉዳይ ማውራት አትፈልግም መሰል 'አሁን ላይ ስለ እንደዚህ አይነት ነገር ማሰብ አልፈልግም ዝግጁ ስሆን እናወራለን...' ትለኛለች። በሌላ ጉዳይ ከሆነ ግን ከ አንድ እስከ ሁለት ሰአት ድረስ በስልክ ታወራኛለች ምንም ሊገባኝ አልቻለም...''
መሀል መግባቴ ልክ ነው ብዬ ባላስብም የግድ ከሆነ ግን መግባት እንዳለብኝ ስለተሰማኝ በራሴ በኩል ላስረዳት እንደምሞክር ነገርኩት።
እሱ እንዳለው ታድያ በስልክ ሳወራት ስለዛ ጉዳይ ማውራት እንደማትፈልግ ያሳብቅ ነበር። ስለሱ ሳነሳ በዛም በዚህ አድርጋ ስለሌላ ጉዳይ እንድናወራ ታደርግና ምንም ስለጉዳዩ ሳላወራት ስልኩ ይዘጋል።
በስልክ እማይሆን ነገር መስሎ ስለተሰማኝ ለምን በቴሌግራም
አይሆንም ብዬ በቴሌግራም ሳወራት ስለሱ የማውቅ አልመሰላትም መሰል ያን ልታወራኝ አልሻተችም።
ለአቤልም አይሆንም ብዬ ነግሬው እንዲሁ እያለ ጊዜው ቀጠለ።
አንድ ቀን ታድያ ከሰላም ጓደኛ ቤቲ ጋር በ ቴሌግራም እያወራን ከሰላም ጋር ይደዋወሉ እንደሆነ ስጠይቃት የነገረችኝን ለማመን ትንሽ ቸግሮኝ ነበር።
''የዘንድሮው መስቀል እኮ ሽምግልናዋ ነበር አልነገረችህም እንዴ?''
''ሳትነግሪኝ አገባሽ እንዴ?.."
"ኧረ የሰላምን ነው ያልኩህ እንዴት አልነገረችህም አታወሩም እንዴ?..." አለችኝ።
"ኧረ እናወራለን የምርሽን ነዋ ግን?"
"አው የምሬን ነው ጠይቃት ከፈለክ።"
እንዴት ልመን?... እኔስ ልሁን እሺ ምን ብዬ ነው ለአቤል የምነግረው?.. ምንስ ተብሎ ይነገራል?
በቴሌግራም ታድያ ቀጥታ ከምነግረው ብዬ እንደዚህ ቢገጥምህ ምን የምትሆን ይመስልሀል... የሚል የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲያደርግ ላወራው አሰብኩኝ።
...አንድ ቀን ታድያ ደብሮኛል ብሎ ሊያወራኝ ሲጀምር በዚሁ አጋጣሚ ብዪ ወሬውን ጀመርን።
"ዛሬ ምን እንደሆነ አላውቅም ዝም ብሎ ደብሮኛል እስቲ ምከረኝ.." አለኝ አንዳንዴ መነቃቃት ሲፈልግ እንደ ቡና የኔን ወሬ መስማት ይፈልጋል።
"ምንድን የሚደብርህ ትምህርት ነው ወይስ?"
"አላውቅም ማርያምን ሰሞኑን እየደበረኝ ነው ምን እንደሆነ ግን አላውቅም"
"ምንድን ዝም ብሎ መደበር? ወይስ እንዳዲስ ሊጀማምርህ ነው?
ከሰላም ጋር ታወራላችሁ እንዴ?"
"ሰሞኑን ፎቶዋን ቴሌግራም ላይ 'ስቶሪይ' አድርጋ ስንቀለቀል አስተያየት እሰጣለሁ ብዬ በሌላ ተረጎመችው። ድብርቱ ግን ከዛ ጋር የሚገናኝ አይመስለኝም።''
"ከዛ በፊት መች ነበር ያወራችሁት?.."
"የልደቴ ቀን ይመስለኛል..."
''ጊቢ ግን ምንም ሴት ልትቀርብ አልሞከርክም?" አልኩት ዳር ዳር ስል።
''መቻል አቃተተኝ ማርያምን እስሩ ከልቤ ነው
ትቻታለሁ እልና ከዛ ደግሞ ትናፍቀኛለች... ብቻ ይከብዳል።"
"እሱማ ይከብዳል ይገባኛል ግን አቤል ከአሁን በኋላ የምር እንዲቆርጥልህ ነው የምፈልገው። በቃ ሌላ ሴትም እንዳለች ለልብህ አሳምነው። ሴት ቅረብ የምልህም ምን አልባት ሰላምን ብታስረሳህ ብዬ ነው። ከቻልክ እንደውም በጭራሽ አታውራት። ትምህርትህ ላይ ትኩረት አድርግ። ቴሌግራም ስትገባም ሌሎች ሰዎችን እያወራህ ለማሳለፍ ሞክር። ይከብዳል ይገባኛል ግን ግድ ነው።''
"እሺ እስራ ብቻ እግዚአብሔር ይርዳን እንደዛ ለማድረግ እሞክራለሁ..."
''ቆይ ግን ሰላም አግብታለች ወይ ደግሞ ወልዳለች ቢባል ምን ልትሆን ነው ፍቅርህ የሚጠፋ ይመስልሀል ወይንስ...? አስበው እስኪ..."
"ባይቀንስም ተስፋ እቆርጣለሁ
'...የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን' በሚለው እጽናናለሁ "
"ትምህርትህ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ያለስ ይመስልሃል?
ካሁኑ ማሰብ አይከፋም ብዬ ነው የምጠይቅህ... ምን አልባት በመንፈስ እንድትዘጋጅ ይረዳህም ይሆናል"
194
ሱሴከጓዶቼ ጋር ስለ ሱስ እያወራን በመሀል አንድ ነገር አሳሰበኝ እና በሀሳብ ትቻቸው ሄድኩኝ። በርግጥ እየተነጋገርን የነበረው ስለ ሱስ አስከፊነት ነበር። አንደኛው ጓድ ታድያ ሱስ እንደነበረበት እና ድሮ ከኖረበት ኑሮ እየመዘዘ ይነግረናል። ይቅም እንደነበር ያጨስ እንደ ነበር መጠጡም እንዳልቀረው...ሁሉም የሚያወራው ስለመቃም፣ ስለማጨስ አልያም ስለመጠጥ ሱስ ነው። አብዛኛው ሰው የተጎዳው ግን በዚህ ሱስ አይመስለኝም። .... እሚቃም እሚጠጣ እና እሚጨስ ብቻ እየመሰለው ስንቱ ገደል ገብቷል? መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉም ሰው ሱስ አለበት። ...አንድ ነገር ሱስ ሆኗል ለመባል የግድ መበላት አልያም ደግሞ መጠጣት ወይ ደግሞ የሚጨስ ነገር መሆን የለበትም። ማንኛውም የምናደርገው ነገር፣ የምንናገረው ንግግር፣ የምንሰራውን ሰራ፣ አይተነው ነገሩ የሚጎዳ እስከሆነና ልንቆጣጠረው/ልናቆመው የማንችልበት ሆኔታ ላይ ከደረሰ ያ ነገር ሱስ ሆኗል። መጠጥና መብሉን ትተን ስንቶቻችን የወሬ ሱሳችንን መቆጣጠር አቅቶን ያንንም ያንንም አሉባልታ ስንቃርም የስንቱን አይፈርስም የተባለለት ጓደኝነት፣ የስንቱን መተማመን ሸርሽረን ይሆን?.. ምን ያህሎቻችን ነን እግሮቻችንን ማዘዝ ተስኖን ሁለተኛ አልሄድም ካልንበት ቦታ ራሳችንን ያገኘን?... በእጃችን ከእንግዲህ ንክች አላደርጋትም ያልናትን ነገር አቅፈን የሙጥኝ ያልንስ?.. .በተደጋጋሚ ቤቲንግ እሚቆምር ጓደኛዬን ቤቲንግ ሱስ እንደሆነበት እና ወደ ከፋ ችግር ሊያመራበት እንደሚችል ስመክረው የመለሰልኝ መልስ አስገርሞኛል። '' እስራ እኔ ግን እኮ ብር ከሌለኝ አልቆምርም'' ነበር ያለኝ። ብር ሳይኖረው ሊቆምር እንደማይችል ግን ረስቶታል። አብዛኞቻችን ትልቁ ችግራችን ራሳችንን ሱስ እንደሌለብን እንሸውደዋለን። ሱስ በልጅነቱ ለራሳችን አይታወቀንም። ከሱስ ለመውጣት የመጀመሪያው እርምጃ ታድያ ሱስ እንዳለብን ራሳችንን ማሳመን ነው። ይህን ሳናሳምን ከሱስ ለመውጣት የምንንቀሳቀሳቸው እርምጃዎች ሁሉ ምን አልባት ልፋታችን በጊዜ ሂደት ሱስ እንዳለብን ያሳምነናል ካላልን በቀር ከንቱ ልፋት ነው። ዘወር ብለን ራሳችንን እንመልከት እስኪ... ✍️እስራኤል ሰይፉ https://t.me/Oct13wed
194
ወይ #ፍቅር✍️እስራኤል ሰይፉ "#ደግ እንደ አብርሃም፤ #ታዛዥ እንደ ይስሐቅ፤ #የዋህ እንደ ዮሴፍ፤ #ቅን እንደ ሙሴ፤ #ትዕግሥት እንደ እዮብ፤ #ምስጋና እንደ ዳዊት፤ #ጥበብ እንደ ሰለሞን፤ #እምነት እንደ ዳንኤል፤ #ትህትና እንዴ ጴጥሮስ፣ #ሰባኪ እንደ ጳውሎስ..." ...የሚል ጽሁፍ የተጻፈበትን የመድኃኔዓለምን ስዕል ሳይ ጸሐፊዎቹ አንድ ነገር የረሱ ይመሰለኝና እኔ ይህን እጨምራለሁ... ...#ፍቅር እንደ አቤል ...ሀይስኩል እንደገባን ትምህርት ቤቱ ከበፊቱ ርቀት ስለነበረው ምሳ ቋጥሮ መሄድ የግድ ነበር። ትምህርት ቤቱ ለአካባቢው ብቸኛ እንደመሆኑ ደግሞ የተማሪው ብዛት ደግሞ ከበፊቱ በርከት ይል ነበር። አብረን ከምንመጣ ጓዶች ጋር ክፍል ስለተለያየን የክፍል ጓደኛ ማፍራት ቢኖርም ለኔ ግን ሙሉ ክፍሉ ጓደኞቼ ናቸው ብል ማጋነን ይመስላል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው ከአቤል ጋር የልብ ጓዶች የሆንነው። በርግጥ አቤል ብዬው አላውቅም ኤቢ ነው የምለው። '' ለአለም የከበደ ስም ይዘህ ለቁልምጫ አትመችም'' ይለኛል እስራኤል ማለት ሳይመቸው ሲቀር። እንደምንም አቆላመጥኩ ብሎ ታድያ ''እስራ'' ነው የሚለኝ። እስራ ሲለኝ... ያስቀራቸው ፊደላት የአምላክ ስም መሆናቸውን አስተውሎ ''አይገባህም'' ያለኝ ይመስለኛል። ... ቤቱ ሩቅ ስለሆነ ትምህርት ቤቱ አካባቢ ተከራይቶ ነው የሚኖረው። በትምህርቱም ታድያ እሳቱ ይሉት እንደነበር ሰምቻለሁ። ማትስ ራስ ምታት ሲሆንብኝ አይቶ ባልድንም መድሐኒት ሊሆነኝ ሲሞክር ነበር ''እሳቱ'' መባሉ ለምን እንደሆነ የገባኝ... ... ትምህርት ቤት ሁሌ በ እረፍት ሰአት ውሀ ለመጠጣት ወደ ትምህርት ቤቱ ታንከር አብረን ነበር የምንሄደው። ...አንድ ቀን የተፈጠረው ነገር ታድያ አስገራሚ ታሪኩን ለማወቄ ድንገተኛ ምክንያት ነበር። እንደወትሮው በእረፍት ሰአት ውሀ ለመጠጣት ወደ ታንከሩ ሶስት ሆነን ነበር የሄድነው። ውሐው ጋር ስንደርስ ሁለት የክፍላችን ሴቶች ውሐ እየጠጡ ነበር። እኔ ታድያ ከሁሉም ሴቶች ጋር ስለምግባባ እቀልድ ነበር... ውሀ ለመጠጣት ጠጋ ስል ከሁለቱ የክፍላችን ሴቶች (ሰላም እና ቤቲ) ሰላም ፊቴን ውሀ ረጨችኝ። ያኔ ምንም ሳላስበው ስለነበር ደንግጫለሁ። ትንሽ ቆየት ብዬ በእፍኜ ውሀ ይዤ ስረጫት... እሷ አይታኝ ሽል ለማለት ዝቅ ስትል ለፊቷ የወረወርኩት ውሀ በጡቶቿ መሀል...(አንገቷን ግልጥ አድርጎ ለእዩኝ የሚጋብዙ የጡቶቿን መሀል ያልሸፈነ ቲሸርት ነበር የለበሰችው...) ያኔ ሮጥ ብላ ከታንከሩ ጀርባ ሄዳ አራግፋ ተመልሳ መጣች። እኔን ያስገረመኝ ልትክስ የሞከረችበት መንገድ ነበር። ፊቴን ታጥቤ ዘወር ስል ውሀ በእጇ ይዛ (ልክ እኔ እንዳደረኩት) ደረቴን ልታበሰብሰኝ ነበር የሞከረችው። .....ስንመለስ ታድያ በነገሩ እየሳቅን ወደ መማርያ ክፍላችን እንደገባን ቃለአብ ጠራኝና አብሬው ሽንት ቤት እንድሄድ ጠየቀች። እሺ ብዪው ከክፍል እንደወጣን... ''...እስራ አብረኸኝ እንድትመጣ የፈለግሁት የሆነ ነገር ልጠይቅህ ነው።''አለኝ። ''ምንድንነው እንዲህ እንደ ትልቅ ሰው... ዝም ብለህ አጠይቅም?'' አልኩ በቁም ነገር ሊያወራኝ የፈለገውን ነገር ቀለል አድርጎ እንዲነግረኝ በማሰብ። ''...እስራ አትቀልድ... ቅድም በእረፍት ሰአት ውሀ ስትራጩ የገረመኝ ነገር አለ'' ''..ምንድን የገረመህ?..'' አልኩኝ። ደግሞ ምን ሊለኝ ነው በሚል ስሜት። ''... ስለ አቤል የምታውቀው ነገር አለ እንዴ? የነገረህ ነገር ካለ ንገረኝ እስኪ...'' '' ኧረ እኔ ምንም ያወራኝም ነገር የለም ምንም የማውቀው ነገር የለም። ለምን በግልጽ አትናገርም?'' '' አቤል ሰላምን ይወዳታል ብዬ ነው አንተማ ታውቃለህ አውቀህ ካልሆነ በስተቀር..'' ''ኧረ እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለም። እንዴት እንዲህ ልትል ቻልክ?.." ''... ሰው ነው ያለኝ። እንዲያውም ስልኩ ሲጠራ እሷ ከሆነች ይደነግጣል አሉ። ቅድም ደግሞ እያየሁት ነበር። ከአንተ ጋር ውሀ ስትራጭ ፈዞ እያያችሁ ነበር። አላስተዋልክ ይሆናል እንጂ አንተ... እንደውም በቃ እንጠይቀው። ዛሬ አርብ ነው። ቅዳሜ እና እሁድ ሁለታችንም በየ ግል እንጠይቀውና ምን እንደሚለን ሰኞ እናወራለን።"... ተስማምተን ወደ ክፍል ገባን። ... እኔን ግን በጣም ሲገርመኝ ነበር። እንዴት እስካሁን ምንም ነገር ሳይነግረኝ...?? እኔስ ብሆን ይህ ሁሉ ሲሆን እስካሁን የት ነበርኩ?? እንዴትስ አልጠረጠርኩም? ውሀ ስራጭ እያየኝ ''እኔ ነበር መራጨት የነበረብኝ። ለምን እዚህ እቆማለሁ..?" ሲል ነበር? ወይስ ራሱን በኔ ቦታ ስሎ በሐሳቡ ሲንቦራጨቅ ነበር? አንዳንዴ ነገሮችን ባለማወቃችን መሆን የሌሉብን ቦታዎች እንገኛለን። ... ከትምህርት ቤት ወጥተን የምንለያይበት ቦታ እስከምንደርስ ሶስታችንም አብረን ነው የምንሄደው። መለያያችን ጋር ስንደርስ እነሱ የተምወሰነ መንገድ ስለሚያመሳስላቸው እኔን ቻው ብለው አብረው ሄዱ። ያኔ ታድያ ቃለአብ አቤልን ለብቻው ስላገኘው ሊጠይቀው እንደሚችል እኔ ደግሞ በስልክ ልጠይቀው እያሰብኩ ወደ ቤቴ ተጓዝኩ። ...በነጋታው ቅዳሜ በስልክ ስጠይቀው ያለውን ነገር በግልጽ ነገረኝ። "እንደውም እስካሁን ሳትጠረጥር መቅረትህ ይገርመኛል። ለ ቃለአብ ግን እንዳትነግረው። ብነግረውም ሙድ ይይዛል ብዬ ሲጠይቀኝ እንኳን ግልጹን አልነገርኩትም 'ብር ትወዳለች...' ነው ይስልኩት በደፈናው" ነበር ያለኝ። ሰኞ ትምህርት ቤት ቃለአብም አልጠየቀኝ እኔም እንደረሳ ሰው ምንም አላልኩ። አቤል ታድያ አንድ የሚተነፍስለት ሰው አገኘ መደበቂያው ሆንኩ። እስካሁን እንዴት እንደቆየ እና መች ፍቅር እንደጀመረው ሲያወራኝ እንዲህ ነበር ያለኝ ''...ባይገርምህ እስራ ምንም እንቅልፍ በአይኔ ሳይዞር እሷን ሳስብ ያደርኩበት ቀን አለ...'' ''ያደርኩበት ማለት ነጋ ሳትተኛ!?'' ገርሞኛል በጣም። ''አው ነጋ..'' እንዴት ይህ ሊሆን ይችላል?? ላምነው አቃተኝ። ፍቅር እንዲህ ነው እንዴ? ብዙዎች ያፈቀሩትን ሲያጡ እንቅልፍ እንኳ ብንተኛ ብለው ፍቅርን እንደ ምርቃና ቆጥረው ይሆን እንዴ መጠጥን እንደ መስበርያ ወይም ማጥፊያ የሚጠቀሙት?.... "...እንደምትወዳት ታውቃለች?'' ''ነግሬአታለሁ ግን... 'አሁን እንደዚህ አይነት ነገር የማስብበት ሰአት አይደለም'... ነው የምትለኝ...'' አለ። ...የምር ከልቤ አዘንኩኝ። ትምህርት የቀነሰው በሷ በሷ ምክንያት እንደሆነ ሳስብ አዘንኩኝ። ...ይህን ከነገረኝ ቀን ጀምሮ በተገናኘን ቁጥር እስከዛሬ የት ነበር እስክል ድረስ ስለሷ ነው የሚያወራኝ።ሰላሙን ነስታው ሰላምታችን ሆና አረፈችው። ከዛን ጊዜ በኋላ ሰላም የሚባሉ ሴቶች ሰላም ነሺዎች ይመስሉኛል። ሰላም ነስቶ ሰላምታ ከመሆን በላይ ምን ረብሻ አለ?... ...ከተለያየን በኋላ እንኳን ቀጣይ ሳገኘው እንደ ሰላምታ ሰላምን ባቀረብኩለት ብዬ እመኛለሁ። ከሁለት አንዱ ማቅረብ አልቻልኩም እንጂ... ...ፈተና ደረሰ። ይህ (Entrance) ፈተናን አልፈው አንድ ዩኒቨርሲቲ በደረሳቸው የሚለው የሁሌም ምኞቴ ነበር። ... እኔ ንባብ ላይ ያን ያህል ስላልነበርኩ ዝግጅት ባልጀምርም እሱ ግን ጀምሮ ነበር። እንዲጀምርም ያደረገው ምን አልባት ከሰላም ጋር አንድ ዩኒቨርሲቲ ይደርሰኛል የሚል ሀሳብ ይመስለኛል። . . .. ይቀጥላል... https://t.me/Oct13wed
