ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ
Відкрити в Telegram
ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።
Показати більше611
Підписники
-124 години
-17 днів
-1030 днів
Архів дописів
❤ አባታችንም የኢትዮጵያን ሰዎች ኃጢአታቸውን በግልጽ በተመለከቱ ጊዜ ተወርውረው ወደ ባሕሩ በመግባት ተዘቅዝቀው መጸለይ ጀመሩ፡፡ "ከባሕር እንዳልወጣ፣ በእግሬም እንዳልቆም በሕያው ስምህ ምያለሁ" ብለው አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ቆዩ፡፡በ40ኛ ቀናቸው የታዘዘ መልአክ መጥቶ "ስምህን የጠራ መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ ብሎሃ" አላቸው፡፡ አባታችንም መልአኩን "መላ ኢትዮጵያን ካልማረ ከዚህ ባሕር አልወጣም" አሉት፡፡ መልአኩም ከእሳቸው ተለይቶ ከሄደ በኋላ አባታችን በዚያ ባሕር ውስጥ መቶ ዓመት ተዘቅዝቀው ሲጸልዩ ኖሩ፡፡
❤ አባታችንም በባሕሩ ውስጥ ተዘቅዝቀው መቶ ዓመት ሲጸልዩ ከኖሩ በኋላ ደማቸው ፈሶ አለቀና ውኃው ደም መሰለ፡፡ ሥጋቸውም አልቆ አጥንቶቻው እንደበረዶ ሆኑ፡፡ ሰባት ሺህ እልፍ ሦስት መቶ የሚሆኑ አጋንንትም ከአራቱም አቅጣጫ እየመጡ ሰውነታቸውን በፍላፃዎቻቸው ይወጓቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ወደ አባታችን መጥቶ ከባሕሩ ዳር በመቆም "ወዳጄ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! መላ ኢትዮጵያን ምሬልሃለሁና ተነሥ ከባሕሩ ውጣ" አላቸው፡፡ አባታችንም አጥንታቸው እንደመርፌ ቀዳዳ ተበሳስቶ ፈጽመው ደክመው ነበርና ጌታችን በክቡራን እጆቹ ሁለንተናቸውን ቢዳስሳቸው እንደቀድሞው ደህና ሆኑ፡፡ጌታችንም ከባረካቸው በኋላ ወደ ምድረ ከብድ እንዲሄዱ ነገራቸው፡፡
❤ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምድረ ከብድ እንደደረሱ እንደ ዓምድ ተተክለው ሰባት ዓመት ቆመው ጸለዩ፡፡በዚህም ጊዜ ሰይጣን በቁራ ተመስሎ መጥቶ ሁለት ዐይኖቻቸውን አንቁሮ አጠፋቸው ነገር ግን አባታችን ጸሎታቸውን ሳያቋርጡ ሁለት ሳምንት በጸሎት ቆዩ፡፡ ከ2 ሳምንት በኋላ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል መጥተው በዐይኖቻቸው ላይ እፍ ብለው ብርሃናቸውን ከመለሱላቸው በኋላ አባታችንን "ከሰማይ ፍጹም ኃይል ይሰጥሃልና ጠላቶችህን ትበቀል ዘንድ ወደ ዝቋላ ሂድ" ብለዋቸው ዐረጉ፡፡
❤ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም እንደታዘዙት ወደ ዝቋላ እየሄዱ ሳለ በመንገድ ላይ ከዛፍ ሥር ያረፉ ሦስት ሽማግሌዎችን አገኙ፡፡ አባታችንም ባዩአቸው ጊዜ ለመሰወር ቢያስቡም ሽማግሌዎቹ ግን ይመጡ ዘንድ ጠሯቸውና "በእግዚአብሔር ዙፋን ተማጽነናል ሦስታችንንም በጀርባህ አዝለህ አንድ አንድ ምዕራፍ ሸኘን" አሏቸው፡፡ አባታችንም ሽማግሌዎቹን በቀረቧቸው ሰዓት ሽበት የከበባቸው የደከሙ ሽማግሌዎች ሆነው አገኟቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን አንደኛውን ሽማግሌ አዝለው ከአንድ ምዕራፍ አደረሷቸው፡፡ ያም ሽማግሌ "ከዚህ አሳርፈኝ፣ አንተ ደክመሃል የማትበላ የማትጠጣ ነህና" አሏቸው፡፡አባታችንም "አባ የት ያውቁኛል?" አሏቸው፡፡ሽማግሌውም "አሁን ደግሞ ሄደህ ጓደኞቼን አምጣልኝ" አሏቸው፡፡ አባታችንም የቀሩት ሁለቱ ሽማግሌዎች ካሉበት ደርሰው ሁለቱንም በየተራ እያዘሉ የመጀመሪያውን ካደረሱበት ቦታ አደረሷቸው፡፡ከዚህም በኋላ እነዚያን ሽማግሌዎች "አባቶቼ ሆይ! ከየት ነው የመጣችሁት?" አሏቸው፡፡ ሦስቱም ሰዎች ተነሥተው ቆሙና ለአባታችን በአንድነት በሦስትነት ተገለጡላቸው፡፡ አንድ ሲሆኑ ሦስት ሦስት ሲሆኑ አንድ ሆኑ፡፡ ሥሉስ ቅዱስ ለአብርሃም በመምሬ አድባር ሥር በአንድነት በሦስትነት እንደተገለጡለት ሁሉ አሁንም ለአባታችን ለገብረ መንፈስ ቅዱስ በአንድነት በሦስትነት ተገለጡላቸው፡፡ በጀርባቸውም አዘሏቸው፡፡ የእግዚአብሔርንም ክብር ስላዩ አባታችን ፊታቸው እንደፀሐይ አበራ፡፡ ቅዱሳን መላእክት ወርደው እንደሻሽ ተነጥፈው ሲያመሰግኑ ሰማይና ምድር ተነዋውጠው ተራሮች ኮረብቶች ዓለቶች ተሰነጣጠቁ፡፡ በዚያችም ሰዓት ታላቅ ፍርሃት ሆነ፡፡ አባታችንም ዙሪያቸውን በከበባቸው በምሥጢራት ጎርፍ ተውጠው ተንቀጥቅጠው በግንባራቸው ወደቁና እንደ በድን ሆኑ፡፡በራእይ ውስጥም ሆነው እነዚያ ሽማግሌዎች አባታችንን እስከ ሰባተኛው ሰማይ እንዳደረሷቸው ተመለከቱ፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ሐዋርያትን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስን እንደቀሰቀሳቸው አባታችንንም ቀሰቀሳቸውና "ወደ ዝቋላ ውረድ መቶ ዓመት ሙሉ አጥንትህን ሥጋህን እየነደፉ የተዋጉህን አጋንንት ታጠፋቸው ዘንድ፡፡ እነሆ እኔ እንደወሰድኩህ ባለማወቃቸው በትዕቢት ላይ ናቸውና "በባሕር ውስጥ አለ" ይሉሃል፡፡ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ይረዱሃል፤ መባርቅትም በፊት በኋላ ይከተሉሃል" አላቸው፡፡
ያንጊዜም አባታችን በመብረቅ ላይ ሆነው እነዚያ አጋንንት ወዳሉበት ወረዱ፡፡ አጋንንቱንም ደመናት ከበቡአቸው፣ መላእክትም በእሳት ሰይፍ መተሩአቸው፣ በመብረቅ አጨዷቸው፤ አመድ ሆነው በነፋስ በተኗቸው፡፡ የእነዚያም አጋንንት ቁጥራቸው ሰባ ሺህ እልፍ ከአንድ ሺህ ነበር፡፡ ሁሉም በአንድ ጊዜ አልቀዋልና ከእነርሱ ሸሽቶ ያመለጠም አልነበረም፡፡ ሰባቱ ሊቃነ መላእክትም ወደ ሰማይ ዐረጉ፡፡ አባታችንም አንበሶችና ነብሮች፣ ድብና ዘንዶ ወዳሉበት ምድረ ከብድ ተመለሱ፡፡
❤ አባታችንም ወደ ምድረ ከብድ ከተመለሱ በኋላ መንፈስ ቅዱስ የጠራቸው ሦስት ቅዱሳን ሁሉም በየአንበሶቻቸው ላይ ተቀምጠው ወደ ምድረ ከብድ መጡ፡፡ እነዚህም ቅዱሳን የዋልድባው አቡነ ሳሙኤል፣ የአዘሎው አቡነ አንበስ እና ከላዕላይ ግብፅ ተነሥቶ የመጣው አቡነ ብንያም ናቸው፡፡ ነገር ግን አባታችን እነዚህን ቅዱሳን ስለተሰወሯቸው ቅዱሳኑ እስከ ሰባት ቀን ድረስ በምህላ ሰነበቱ፡፡ የአባታችን የሚያስፈሩ አንበሶች ወጥተው የቅዱሳኑን አንበሶቻቸውን ገድለው ደማቸውን አፍስሰው ሥጋቸውን በሉ፡፡ ሦስቱም ቅዱሳን በዚህ ፈጽመው ደንግጠው ሳለ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ 60 ነብሮችንና 60 አንበሶችን አስከትለው ተገለጡላቸውና "ሰላም ለእናንተ ይሁን የእግዚአብሔር ቅዱሳኑ አትፍሩ" አሏቸው፡፡ ቅዱሳኑም "አባታችን ሆይ! ጸሎትህ ቅድስት እንደሆነች ባወቅን ጊዜ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንባረክ ዘንድ ወደ አንተ መጣን፡፡ ነገር ግን ባላገኘንህ ጊዜ እስከ ሰባት ቀን አለቀስን" አሏቸው፡፡ ዳግመኛም "የእርስዎም አንበሶች መጥተው አንበሶቻችንን በሉብን" አሏቸው፡፡ አባታችንም አንበሶቻውን "እስከ ዕለተ ሞቴ ድረስ በእግሬ ከረገጥኩት ምድር በቀር እግዚአብሔር ያላዘዛችሁን ለምን በላችሁ? አሁንም የበላችሁትን ትፉ" አሏቸው፡፡ እነዚያም አንበሶች አፋቸውን ከፈቱና የበሉትን የአንበሶቹን ሥጋቸውን አጥንታቸውን ከደም ጋር ተፉ፤ በሆዳቸውም የቀረ የለም፡፡ አባታችንም ወዲያው ወደ ምሥራቅ ዞረው እግዚአብሔር ካመሰገኑ በኋላ "አቤቱ አልዓዛርን ከሞት ያስነሣኸው አንተ ነህና አሁንም እነዚህን አናብስት ከሞት አስነሣቸው፤ ለባሮችህም የድካማቸውን ማረፊያ ይሆኑላቸው ዘንድ የሰጠሃቸውን አትከልክላቸው… " እያሉ ጸለዩ፡፡ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ብለው ጸሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ የአንበሶቹን ሥጋቸውን በመስቀል ምልክት ባርከ "በጌታዬ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ተነሡ"አሏቸው፡፡ አንበሶቹም እንደ ዐይን ጥቅሻ ፈጥነው ተነሡና እንደቀድሞው ሆኑ፡፡ ለአባታችንም እጅ ነሥተውና ሰግደው የእግሩን ትቢያ ላሱ፡፡ አባታችንም ወደ ጌቶቻቸው መለሳቸው፡፡
❤ እነዚህም ሦስቱ ቅዱሳን በአባታችን ላይ አድሮ ድንቅ ነገርን የሚሠራ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ የዋልድባው አቡነ ሳሙኤልም አባታችንን "አባት ሆይ በዚህች ቀን ድንቅ ሥራን አየን፣ አርአያህ የእግዚአብሔርን መልአክ አርአያ ይመስላል፣ ቅድስናህ ፍጹም ነው፣ የጸሎትህ ኃይል ሙታንን ያስነሣል፣ የተበሉ አንበሶችን ከአንበሶች ሆድ አወጣህ" አሏቸው፡፡ቅዱሳኑም ሥራቸውን እያደነቁ በልተው ጠጥተው ጠገቡ፡፡ በማግሥቱም አባታችን ቅዱሳኑን "በሰላም ሂዱ" ብለው መርቀው ሸኟቸውና የእግዚአብሔር ሥራ እያደነቁ
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። ❤
❤ #መጋቢት ፭ (5) ቀን።
❤ እንኳን #ተአምራታቸውና_ትሩፋታቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት ለበዛ የእግዚአብሔር ማደርያ ተጋዳይ ለሆኑ #በዝቋላ_ተራራ_ባለው_ባሕር_ውስጥ_100 ዓመታት ተዘቅዝቀው #ለኢትዮጵያ_ሰዎች ምሕረትን ለለመኑት #ለታላቁ_አባት_ለአቡነ_ገብረ_መንፈስ_ቅዱስ ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #አቡነ_ገብረ_መንፈስ_ቅዱስ፦ ትውልድ አገራቸው ደቡባዊ ግብፅ ከቆላው ልዩ ስሙ ከንሒሳ አካባቢ ነው፡፡አባታቸው ስም ቅዱስ ስምዖን እናታቸው ስም ቅድስት አቅሌስያ ይባላሉ፡፡ ወላጆቻቸው በእግዚአብሔር ፊት ደጋጎች የነበሩ ቢሆኑም አቅሌስያ መካን ሆና ልጅ በማጣቷ እያለቀሰች 30 ዘመን ኖራለች፡፡
❤ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ እናታቸው ቅድስት አቅሌስያ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ሥዕል ካለበት ፊት ለፊት በመቆም እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣት ዘንድ አልቅሳ ስትለምን ያንጊዜ ከሥዕሉ ቃል ወጥቶ "ክቡሩ ከሰማይ ከምድር ከፍ ከፍ የሚል፣ ከሚካኤል ከገብርኤል ጋር በክብር የሚተካከል ክህነቱ እንደ መልከጼዴቅ ንጽሕናው እንደ እንደ ነቢይ ኤልያስ፣ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ የሆነ በክብር ከነቢያትና ከሐዋርያት ጋር የሚተካከል ልጅ ትወልጃለሽ" አሏት። ይኸውም ለአንቺ ብቻ አይደለም ለዓለሙ ሁሉ ነው እንጂ። ያን ጊዜ ከሦስቱ አንዱ ተነሥቶ በእጁ ባርኮ በሰላም ወደ ቤትሽ ግቢ አሏት"። እርሷም ደስ እያላት ወደ ቤቷ ገባች፡፡
❤ ቅድስት አቅሌስያም በመጋቢት 29 ቀን ፀንሳ በታኅሣሥ 29 ቀን ደም ግባቱ እጅግ የሚያምር ወንድ ልጅ እንደወለደች መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሰው አምሳል መጥቶ "የዚህ ልጅሽ ስሙ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ይሁን" አላት፡፡ ወዲያውም ሕፃኑ ተነሥቶ ከእናቱ ጭን ወርዶ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ሦስት ጊዜ ሰገደ፡፡ ዳግመኛም "ከጨለማ ወደ ብርሃን ለአወጣኸኝ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን" አለ፡፡
❤ ከ3 ዓመት በኋላም እግዚአብሔር መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን እንዲህ ብሎ አዘዘው፡- "ሕፃኑን ከእናቱ ክንድ ተቀበል፣ ብዙ ገዳማውያን ወዳሉበት ገዳም ውሰድና ከበራቸው አስቀምጠው፣ አበ ምኔቱንም ዘመደ ብርሃንን ከበር አንሥተህ ካንተ ዘንድ አኑረው ስለ ልብሱ ስለ ምግቡ አታስብ ሕፃኑ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነውና ምግቡም መንፈሳዊ ነው ይኸውም ከእግዚአብሔር የሚወጣ ቃል ነው፣ ሰው በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ዕወቅ በለው" በማለት አዘዘው፡፡ብርሃናዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም እንደታዘዘው ከሰማይ ወርዶ ሕፃኑን ከእናቱ ክንድ ወስዶ በክንፎቹ አቅፎ ስሞ እስከ ሰባቱ ሰማይ አውጥቶ በሥሉቅ ቅዱስ ፊት አቅርቦት አስባረከው፡፡ እግዚአብሔርም መልአኩን "ወደ እናቴ ወደ ማርያም ውሰደውና ትባርከው" አለውና ወስዶት እመቤታችንም ባረከችው፡፡ ዳግመኛም ከአዳም ጀምሮ ኄሮድስ በግፍ እስካስፈጃቸው ሕፃናት ያሉት ሁሉም ቅዱሳን ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ ደናግልና መነኰሳት ሁሉም እንዲባርኩት አደረገው መልሶ ከእግዚአብሔር ፊት አቆመው፡፡ መድኅን ጌታም ሕፃን ገብረ መንፈስ ቅዱስን "በመንግሥቴ ከእኔ ጋር ትነግሣለህና ደስ ይበልህ፣ በርታ የሚደርስብህን ሁሉ ታገሥ ብዙ ነፍሳት በአንተ ምክንያት ይድናሉ፣ ሰላሜ ከአንተ ጋር ይሆናል" አለው፡፡ ከዚህም በኋላ መልአኩ አባ ዘመደ ብርሃን ወዳለበት ገዳም አወረደውና ሕፃኑን ከበር ላይ አስቀምጦ እርሱ ወደ ውስጥ ገብቶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉን ነገረው፡፡
❤ አባ ዘመደ ብርሃንም ሕፃኑን አስገብቶ በእንክብካቤ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሁሉ እያስተማረ አሳደገው፡፡ ሕፃኑም ትምህርቱን በጨረሰ ጊዜ ዲቁና ተቀብሎ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ጸጋንና ሞገስን የተመላ ሆነ፡፡ ፍጹም የእግዚአብሔር ጸጋ አድሮበታልና ሥራው ሁሉ በዕውቀት የተመላና የተቃና ሆነ፡፡ አባ ዘመድ ብርሃንም በሕፃኑ ላይ ያደረበትን ጸጋ እያየ እጅግ ደስ ይለው ስለነበር እንደ ቅዱስ እንጦንስ አስኬማን ሰጠው፡፡ ከዚህም በኋላ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቅስናን ተቀበሉና በጾም በጸሎት ተጠምደው በታላቅ ተጋድሎ መኖር ጀመሩ፡፡ እንደ ሐዋርያትም የተአምራትና የፈውስ ሀብት ተሰጣቸውና ድውያንን የሚፈውሱ፣ ሙታንን የሚያነሡ፣ አጋንንትን የሚያወጡ ሆኑ፡፡
❤ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ዳግመኛ ተገልጦላቸው ወደ ሰማይ አሳረጋቸውና ከእግዚአብሔር ፊት አቆማቸው፡፡ ያን ጊዜም ጌታችን ክቡራን የሆኑ እጆቹን ዘርግቶ ከባረካቸው በኋላ "በጸሎትህ ከሲኦል የምታወጣቸው ብዙ ነፍሳት አሉ፤ ድውያንንም ትፈውሳለህ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ከሰው ተለይተህ ወደ ጫካ ገብተህ ከአንበሶችና ከነብሮች ጋር ኑር" አላቸው ቁጥራቸውም ስልሳ ነብርና ስልሳ አንበሶች፡፡አባታችንም ጌታችንን "የሰጠኸኝ እነዚህ አንበሶችና ነብሮች ምን ይመገባሉ?" አሉት፡፡ ጌታችንም "የረገጥከውን መሬት ይልሳሉ በዚያም ይጠግባሉ፡፡ ወደ እኔም እስክትመጣ ድረስ ይኸው ምግብ ይሆናቸዋል" አላቸው፡፡ ቅዱሳን መላእክትም ይህንን በሰሙ ጊዜ ደስ አላቸው፡፡ ጌታችንም መልአኩን ወደ ቀደመ ቦታቸው ይመልሳቸው ዘንድ አዘዘው፡፡ ከዚህ በኋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከራሳቸው እስከ እግራቸው ድረስ ጠጉር በቀለላቸው፡፡ የጠጉራቸውም ርዝመቱ አንድ ክንድ ከስንዝር ነው፡፡ አባታችንም በታላቅ ተጋድሎ ሲኖሩ በጸጋ ላይ ጸጋ ተጨመረላቸው፡፡ከዕለታት በአንድ ቀን የፈወሳቸው ሕሙማን ብዛታቸው እልፍ ሆነ፡፡ የሀገሩ ሰዎችም ሥራቸውን ስላወቁባቸው አዘኑ፡፡ "ውዳሴ ከንቱ እንዳይሆንብኝ ተነሥቼ ሰው ወደማያውቀኝ አገር እሄዳለሁ" ብለው ተነሥተው ሄዱ፡፡ሕዝቡም አባታችን እንደተሰወሩ ባወቁ ጊዜ በሀዘን አለቀሱ፡፡
❤ ከዚህም በኋላ አባታችን ወደ ጫካ ገብተው ብቻቸውን የበጋውን ሐሩር የክረምቱን ቁር ታግሰው ምንም ልብስ ሳይለብሱ ራቁታቸውን ሆነው በተጋድሎ ኖሩ፡፡ ከጽኑው ተጋድሎአቸውና ከጫካው ቅዝቃዜ የተነሣ ሰውነታቸው አልቆ ከአጥንታቸው ጋር ተጣበቀ፡፡ ፍራፍሬም ሆነ ምንም ነገር አይመገቡም ውኃም ፈጽሞ አይጠጡም ነበር፡፡ አባታችን በምድረ በዳ እንደሰው ሳይሆን እንደመላእክት ኖሩ፡፡ ቅዱሳን መልእክትም ዘወትር ይጎበኟቸው ነበር፤ ስለምግባቸውም ሰማያዊ ኅብስት አምጥተው ይሰጧቸዋል ነገር ግን አባታችን ያንን ኅብስት አይመገቡትም ይልቁንም ጽዋውን ባሸቱት ጊዜ እንዲሁ ይጠግባሉ ይረካሉ፡፡
❤ ዕድአቸው 300 ዓመት በሆነ ጊዜ ጌታችን "ወደ ኢትዮጵያ ሂድ በዚያም ከደይን የምታወጣቸው ነፍሳት አሉ" አላቸው፡፡ አባታችንም "አምላኬ ሆይ ወደዚያች አገር ማን ያደርሰኛል?" አሉት፡፡ እግዚአብሔርም "እኔ በሥልጣኔ አደርስሃለሁ" ካላቸው በኋላ ከእርሳቸው ተሰወረ፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን ስድሳ አንበሶችና ስድሳ ነብሮች እየተከተሏቸው ወደ አገራችን ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ብርሃናዊው መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ከእነዚሁ ተከታዮቻቸው ጋር በነፋስ ሠረገላ ጭኖ ምድረ ከብድ አደረሳቸው፡፡ ዳግመኛም "ደብር ቅዱስ" ወደሚባለው ወደ ዝቋላ ወሰዳቸው፡፡ አባታችንም በውኃው ዳር ቆመው ምሥራቁን፣ ምዕራቡን፣ ሰሜኑን፣ ደቡቡን በመለከቱ ጊዜ የኢትዮጵያ ሰዎች ኃጢአታቸው በፊታቸው የተገለጠ ሆነ፡፡ ሰው የገዛ ፊቱን በመሥታወት እንደሚያይ የኃጥአንም ሥራቸው በአባታችን ፊት እንዲሁ የተገለጠ ነውና፡፡
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #መጋቢት ፬ (4) ቀን።
❤ እንኳን #ስለ_ፋሲካ_በዓል የአይሁድ ተሳታፊዎች ስለ ሚባሉ ክፉዎች ሰዎች #በአምር_ደሴት_የዐሥራ_ስምንት_ኤጲስቆጶሳት አንድነት ስብሰባ ለተደረገበትና ለከበረና ለተመሰገነ ከጵንፍልያ አውራጃ ብርግያ በትምባል ከተማ ለሆነ ለመኰንን #ለቅዱስ_ሐኑልዮስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #የአሞር_ደሴት_የአንድነት_ስብሰባ፦ እነሱ የከበረ የፋሲካን በዓል በኔሳን ወር ማለት በሚያዝያ ዐሥራ አራት ቀን ከአይሁድ ጋር ያከብሩ ነበርና። ሰኞ ቢሆን ማክሰኞም ቢሆን ወይም ረቡዕ ወይም ሐሙስ ወይም በዓርብ ቀን ወይም በቅዳሜ ሰንበት ከአይሁድ ጋር ያከብሩ ነበርና የደሴታቸውም ኤጲስቆጶስ አወገዛቸው ግን አልተመለሱም።
❤ ስለዚህም ወደ ሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ወደ ድምትራጥዮስ ወደ አንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ ሰራባሞን ወደ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ ድሜጥሮስ ወደ ኢየሩሳሌሙ ኤጲስቆጶስ ወደ ሲማኮስ መልእክትን ላከ። የእነዚህንም ሰዎች ስሕተታቸውን ነገራቸው። አራቱም ሊቃነ ጳጳሳት ከእርሱ እየአንዳንዳቸው የከበረ የፋሲካ በዓልን በእሑድ ቀን ካልሆነ በቀር ከአይሁድ በዓልም በኋላ ካልሆነ በቀር አታድርጉ የሚል መልእክትን ላኩ። ይህንም ትእዛዝ የሚተላለፈውን ከምዕመናን እንዲለይ አወገዘ።
❤ በዚህም ጉባኤ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳት ተሰበሰቡ። እነዚያንም ሕግ ለዋጮች አቅርበው የሊቀነ ጳጳሳቱን መልእክቶቻቸውን በፊታቸው አነበቡ ከእነርሱም በከፋች ምክራቸው የተመለሱ አሉ። በስሕተቻቸውም ጸንተው የቀሩ አሉ። ረግመውና አውግዘውም ከምዕመናን ለዩአቸው።
❤ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያትም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣባት ዕለት ፋሲካን ያለ እሑድ ቀን የሚያከብር እርሱ በበዓላቸው ከአይሁድ ጋር ተሳታፊ ነውና ከምዕመናን ይለይ ብለው እንዳዘዙ እንዲሁ የፋሲካ በዓል በዕለተ እሑድ እንዲከበርና ሕጉም ጸንቶና ተወስኖ እንዲኖር ተሠራ። እግዚአብሔር ከሰይጣን ስሕተት ይጠብቀን። በተጋድሎአቸውና በትሩፋታቸው ደስ ባሰኙት በቅዱሳን ጸሎትም ከወጥመዶቹና ከሽንገላውም ያድነን ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅዱስ_ሐኑልዮስ፦ ይህንንም ቅዱስ ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ መውደዱና እርሱንም ስለ ማምለኩ ከዲዮቅልጥያኖስ ተልኮ የመጣ ብርይንኮስ መኰንን ያዘው። በመኰንኑም ፊት በቆመ ጊዜ ምስጋና ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት ከፍ ከፍ ባለ ቃላት አብራርቶ ገለጠ። ብዙ ምስጋናዎችንም ለእግዚአብሔር አቀረበ የረከሱ ጣዖታትንም ረገማቸው።
❤ መኰንኑም በዕንጨት መስቀል ላይ ይሰቅሉት ዘንድ አዘዘ ስለ ከበረ ስሙም ምስክር ይሆን ዘንድ ስለ አደለው ምስጋና ይግባውና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰገነው። ከዚያም ምስጋና ይግባውና በእግዚአብሔር እጅ ነፍሱን መጋቢት4 ሰጠ። የቅዱስ ሐኑልዮስ ጸሎቱና በረከቱ ከሁላችን ጋር ለዘላለም ይኑር አሜን። ምንጭ፦ የመጋቢት 4 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለክሙ_አሐተኔ_ጉቡአን። ኤጲስቆጶሳት ዐሥር ዘተውሳክክሙ ሳምን። አመ ፲ ወ ፬ ለወርኃ ኔሳን። በፋሲካ ኦሪት ኢይግበሩ ፋሲካ ወንጌል ብርሃን። ከመ ትምትርዎሙ ለዕልዋን በበሊሕ ልሳን። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመጋቢት_4።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ጸላእኩ ማኅበረ እኩያን። ወኢይነብር ምስለ ጽልሕዋን። ወአሐፅብ በንጹሕ እደውየ"። መዝ 25፥5-6። የሚነበቡት መልዕክታት ፊሊ 3፥1-ፍ.ም፣ 2ኛ ዮሐ 1፥1-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 20፥1-7። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 22፥1-24። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #መጋቢት ፬ (4) ቀን።
❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊቷ_ጻድቅ በዝዋይ ደብረ ጽዮን ሐይቅ ውስጥ ገብታ ለአምስት ዓመት ለጸለየች ለታላቋ እናት #ለቅድስት_ሐይመተ_ሥላሴ ለዕረፍቷ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅድስት_ሐይመተ_ሥላሴ፦ የትውልድ ሀገሯ ጎጃም ደብረ ጽላሎ ነው፡፡ ብዙ እናቶች በጣና ደሴት ውስጥ እየገቡ እንደጸለዩ ሁሉ እሷም ወደ ዝዋይ ሄዳ በዝዋይ ደብረ ጽዮን ሐይቅ ውስጥ ገብታ አምስት ዓመት ከባሕሩ ላይ የጸለየች ቅድስት እናት ናት፡፡ በታዘዘ መልአክ መሪነት ከሐይቁ ውስጥ ከወጣች በኋላ በገዳሙ ውስጥ ዐሥራ ዘጠኝ ዓመት ቆማ ጸልያለች፡፡
❤ በመልአኩ መሪነት ወደ ቡልጋ ሄዳ በዚያም ዐሥራ አምስት ዓመት በታላቅ ተጋድሎ ኖራለች፡፡ ሰውነቷም እጅግ ከስቶ ሥጋዋ አልቆ ይታይ ነበር፡፡ በመጨረሻም መልአኩ ተገልጦ ጊዜ ዕረፍቷን ከነገራት በኋላ ወዲያው መጋቢት 4 ቀን በሰላም ስታርፍ ሦስት አክሊላት ወርደውላታል፡፡ ቅድስት ሐይመተ ሥላሴን ስንክሳሩም "የጽድቅ ኮከብ" እያለ ይጠቅሳታል፡፡ ቅዱስ ገድሏ በደብረ በግዕ ይገኛል፡፡ ከእናታችን ቅድስት ሐይመተ ሥላሴን እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #መጋቢት ፫ (3) ቀን።
❤ እንኳን #ለእስክንድርያ_ሃምሳ_ስምንተኛ ሊቀ ጳጳሳት #ለብፁዕ_ወቅዱስ_ለአባ_ቆዝሞስ ለዕረፍት በዓልና ከፎንዮስ አገር ለሆነ #ለአባ_በርፎንዮስ ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ቆዝሞስ፦ ይህም እውነተኛና ንጹሕ፣ የዋህ ርኅራኄው የባዛ የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍትና ትርጓሜያቸውን የሚያውቅ ነበር። እግዚአብሔር በወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ መንበር ላይ ለሊቀ ጵጵስና ሹመት መረጠው የግብጽ ንጉሥ መቅትር በነገሠ በዐሥራ ስምንት ዓመት ሊቀ ጳጳሳት ሁኖ ተሾመ።
❤ በተሾመም ጊዜ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንጋዎች በፈሪሃ እግዚአብሔር በጥበብ ጠበቃቸው። ለእርሱ ከሚገባው ከግብሩ ገንዘብ የሚተርፈውን ለጦም አዳሪዎች ይሰጣቸው ነበር ደግሞም ለቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ማሠሪያ ያወጣ ነበር።
❤ መልካም ተጋድሎውንም በአየ ጊዜ ሰይጣን ያለ ኀዘን አልተወውም ነገር ግን የሚያዝንበትን ምክንያት በላዩ አመጣ። ይኸውም እንዲህ ነው ጴጥሮስ የሚባል ጳጳስ ለኢትዮጵያ አገር ሹሞ ነበር አባ ጴጥሮስም ወደ ኢትዮጵያ በደረሰ ጊዜ ጥቂት ዘመን በሰላም ኖረ። ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሥ ታመመ አባ ጴጥሮስንም ጠርቶ ሁለቱን ልጆቹን አቀረበ ዘውዱንም ከራሱ ላይ አንስቶ ለአባ ጴጥሮስ ሰጠው "እንሆ እኔ ወደ ክብር ባለቤት ወደ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ እሔዳለሁ እንሆም ሁለቱ ልጆቼ በፊትህ ናቸው አንተም ከሁለቱ አንዱን ከእኔ በኋላ አንግሥ" አለው። ንጉሡም ካረፈ በኋላ ጳጳሱ መንኳንንቱና የጦር ሥራዊቱ አለቆችና የመንግሥት ሠራዊት አለቆች ተማከሩ እርስ በርሳቸውም ለመንግሥት የሚሻል የሚያንሰው ነው ተባባሉ። ጳጳሱ አባ ጴጥሮስ ታናሹን የንጉሥ ልጅ ቀብቶ አነገሠው በኢትዮጵያ መንግሥት ዙፋን ላይም አስቀመጠው ጥቂት ዘመንም በሰላም ኖረ።
❤ በዚያም ወራት ከሶርያ አገር በሆኑ በሁለት መነኰሳት ልብ ሰይጣን አደረ ከአባ እንጦንስ ገዳም እስከ ሚደርሱ ከቦታ ወደቦታ ይዞሩ ነበር። በዚያም በአባ እንጦንስ ገዳም ጥቂት ቀኖች ተቀመጡ ስለ ሥራቸውም ክፋት አባረሩአቸው። ከዚያም በኋላ አንዱ ጳጳስ ሁለተኛውም ረዳት ሊሆን እርስ በርሳቸው ተስማሙ። ተነሥተውም ወደ ኢትዮጵያ ደረሱ። የሐሰት ጽሑፍንም ጻፉ ያ ጽሑፋቸውም እነርሱ ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ከአባ ቆዝሞስ ዘንድ ተሹመው እንደ መጡ የሚገልጥ ነበር። በዚያ ጽሑፍም "እኛ ያልሾምነውና ወደ እናንተ ያልላክነው ራሱን ጳጳስ ያደረገ ስሙ ጴጥሮስ የተባለ ሰው ወደ እናንተ እንደመጣ ሰምተናል እርሱ ሐሰተኛ ነው እንጂ እውነተኛ አይደለም። ይህን ጽሑፍ ይዞ የሚመጣው ግን ስሙ ሚናስ የሚባል ጳጳስ በእውነት እኛ የሾምነውና ወደ እናንተ የላክነው እውነተኛ ነው" አሉ። ሁለተኛም እንዲህ ብለው ጻፋ "ጳጳሱ ጴጥሮስ ታላቁን ትቶ ታናሹን የንጉሥ ልጅ አነገሠው ይህም የማይገባ ነው ዐመፅ ነውና"።
❤ እሊህም ክፋዎችና ሐሰተኞች ሁለቱ መነኰሳት ሚናስና ፊቅጦር የሐሰት ጽሑፋቸውን ሳይጽፉ ወደ ጳጳሱ ጴጥሮስ ደርሰው ወርቅ ይሰጣቸው ዘንድ ፈለጉ እርሱም ምንም አልሰጣቸውም። ይህንንም የከፋና የረከሰ ሥራ ሰይጣን አስተማራቸው። የሐሰት ደብዳቤም ጽፈው ወደ ታላቁ የንጉሥ ልጅ ወሰዱ እርሱም ከጥቂት ሰዎች ጋር ለብቻው ይኖር ነበር እነዚያንም የሐሰት ደብዳቤዎች አነበቡለት እጅግም ደስ አለው።
❤ ከዚህም በኋላ ብዙ ሠራዊት ሰብስቦ እሊያን የሐሰት ደብዳቤዎች በፊታቸው አነበበላቸው ከንጉሡ ወንድሙ ጋራም ጦርነት ገጥሞ ድል አደረገው፤ ወንድሙንም አሠረው የመንግሥቱንም ሥልጣን ያዘ እንዲሁም ጳጳሱን ጴጥሮስን አሠረው በሩቅ አገርም አጋዘው ያንንም ሐሰተኛ ሚናስን በጳጳሱ በጴጥሮስ ፈንታ አስቀመጠው።
❤ ከጥቂት ቀንም በኋላ ሐሰተኞች ፊቅጦርና ሚናስ እርስ በርሳቸው ተጣሉ ፊቅጦርም በመንበረ ጵጵስና ያለውን ገንዘብ ሁሉ ሰርቆ ወደ ግብጽ አገር ሸሽቶ ሔደ። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ካደው። ከመንበረ ጵጵስናው የሰረቀውንም ገንዘብ ሁሉ እግዚአብሔር የማይወደውን ሥራ በመሥራት አጠፋው።
❤ ሊቀ ጳጳሳት ቆዝሞስም ሐሰተኛ ሚናስ ያደረገውን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ ደብዳቤም በመጻፍ አውግዞ ለየው። የኢትዮጵያ ንጉሥ ሰምቶ እጅግ አዘነ ሐሰተኛው ሚናስንም ይዞ ገደለው። ጳጳሱ ጴጥሮስንም ከተሰደደበት ይመልሱት ዘንድ መልክተኞችን ላከ ግን ሙቶ አገኙት።
❤ ይህም ነገር በሊቀ ጳጳሳት በቆዝሞስ ዘንድ ተሰማ ሁለተኛም ጳጳስ አልሾመላቸውም ከእርሱም በኋላ የነበሩ ሊቃነ ጳጳሳት አባ መቃርስ፣ አባ ታውፋንዮስ፣ አባ ሚናስና አባ አብርሃም በእነዚህ ዘመን ከ911 ዓ.ም እስከ 995 ዓ.ም ድረስ ለሰማንያ አራት ዓመታት ያህል ለኢትዮጵያ ሰዎች ጳጳስ ተሹሞ አልተላከላቸውም።
❤ የኢትዮጵያ ንጉሥ ግን የጳጳሱ የጴጥሮስ ረዳት የነበረውን ወስዶ በመምህርህ ፈንታ ጳጳስ ሁነህ ተቀመጥ አለው። እርሱም እኔ ጳጳስ ልሆን አይገባኝም የሐዋርያትንም ሥርዓት ተላልፌ ይህን ሥራ አይቻለኝም ግን ልቀቀኝና ወደ ግብጽ ልሒድ ጳጳስ እንዲሾምላችሁም ሊቀ ጳጳሱን እለምነዋለሁ ከዚህም በኋላ ወደ እናንተ እመለሳለሁ እያለ ንጉሡን ማለደው። ንጉሡም ወደ ግብጽ እንዲሔድ አላሰናበተውም ያለ ውዴታው ወስዶ የጵጵስናውን ልብስ አለበሰው እንጂ። የጵጵስናውንም ሥራ እንዲሠራ አደረገው።
❤ አባ ቆዝሞስም እጅግ ሸመገለ የሹመቱም ዘመን ደኅንነትንና ሰላምን የተመላ ነበር በወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ወንበርም ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖረ በሰላምም መጋቢት 3 ቀን ዐረፈ። እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛን በአባ ቆዝሞስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የመጋቢት 3 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለከ_በርፎንዮስ_አብ። ምሉዐ ጥበብ። ከመ ማኅቶት ዘአስተርአይከ ለሀገረ ፍንዮስ ሕዝብ። ለመርዓ ስምከ ኀበ ይትገበር ከብካብ። ረስየኒ እትረከብ በልብስ ሕፁብ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመጋቢት_3።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወባሕቱ መከሩ ይሥዐሩ ክብርየ። ወሮፅኩ በጽምእየ። በአፉሆሙ ይድኅሩ ወበልቦሙ ይረግሙ"። መዝ 61፥4። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ተሰ 1፥3-ፍ.ም፣ 2ኛ 2ኛ ጴጥ 3፥14-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 4፥13-27። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 12፥25-38። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ወራትና በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
“መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ”
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ አምላክ አሜን !!
‹‹ወነአምር ከመ ለእመሂ ተነሥተ ቤተ ማኅደርነ ዘበምድር ዘውእቱ ሥጋ ብነ ሕንጻ በኀበ እግዚአብሔር በሰማያት ዘኢገብሮ እደሰብእ፡-
በምድር ያለው ማደሪያ ቤታችን ቢፈርስም በሰማይ በእግዚአብሔር ዘንድ የሰው እጅ ያልሠራው ዘለዓለማዊ ቤት እንዳለን እናውቃለን፡፡›› (2ቆሮ. 5፡1)በልዩ ልዩ ጊዜያት ዐረፍተ ዘመን የገታቸውን ወገኖች ልንሸኝ እንችላለን፤ የአንዳንድ ሰዎች ሞት ግን ከልብ ቶሎ የማይወጣ፤ ለዘመናትም በህሊና መዝገብ ላይ የሚቆይ ነው፡፡
በመሆኑም የሚከተሉት ሃይማኖት ወይም መርጠው ያልተወለዱበት አካባቢ እንደበደል ተቆጥሮባቸው ከየአቅጣጫው በሚሰነዘረው ጥቃት በሚገደሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች፣ ምእመናን በአጠቃላይ የሰው ልጆች ኀዘን ልባችን በትካዜ ውስጥ በገባበት በዚህ ወቅት በመንፈሳዊ ሕይወቱ እና በትጋቱ ለቤተ ክርስቲያን ተስፋ የነበረው፤ ለበርካታ ዓመታትም በገጠር፣ በከተማ፣ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ እየተዘዋወረ ወንጌለ መንግሥትን ሲያስተምር የቆየው የመንፈስ ቅዱስ ልጃችን መ/ር ዘለዓለም ወንድሙ ለመንፈሳዊ አገልግሎት በተጓዘባት ሰሜን አሜሪካ ባጋጠመው ሕመም ከዚህ ዓለም ድካም በሥጋ ማረፉን ስንሰማ ታላቅ ድንጋጤ ፈጥሮብናል፡፡
በእርግጥ መምህር ዘለዓለም ወንድሙ ስመ ጥምቀቱ ወልደ ሰማእት በሥጋ ከእኛ ቢለይም ያለዋጋ የተቀበለውን የእግዚአብሔር ቃል ለምእመናን በማስተማር አደራውን በሚገባ ተወጥቶአልና በሰማይ ወደሚጠብቀው ዘለዓለማዊ ስፍራ በክብር እንደሚገባ እናምናለን፡፡
የመልካም ሰዎች መጉደል ለሀገር በተለይም ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚያስጨንቅ ቢሆንም ሁሉን የሚችል አምላክ ተተኪዎችን እንዲያዘጋጅልን በመጸለይ፤ ለመንፈስ ቅዱስ ልጃችን ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶችና ምእመናን መጽናናትን እየተመኘን አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ የአገልጋዩ ወልደ ሰማዕትን ነፍስ በመንግሥቱ ያሳርፍልን፤
“እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ”
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኣሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጲያ
ፍቁረ እግዚእ ሚዲያ Fikure Egzi Media – FEM:
የብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ወላጅ እናት የእማሆይ አጸደ ማርያም ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ።
በሆሳዕና መንበረ ጵጵስና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በተፈፀመው በዚሁ የእማሆይ አጸደ ማርያም ሥርዓተ ቀብር ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሓፊን የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ጨምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል።
በተመሳሳይ የጠቅላይ ቤተክህነት የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ የሀድያ ስልጤ አህጉረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፤የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሥራ ኃላፊዎች ፤ ምእመናንና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዚሁ ጊዜ ትምህርተ ወንጌል የሰጡት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሸካ ቤንች ማጅ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲህ ባለ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፤ በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ታጅበው በደመቀና ባማረ መርሐ ግብር መሸኘት መታደል መሆኑን ጠቁመዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም "እናታችን አረፉ ነው የሚባሉት ሞቱ አይባልም ፤ ሞቱ የሚባሉት ሲሰርቁ ፣ ሲገሉ ፣ ሲያስለቅሱ የኖሩ ሰዎች ናቸው ሞቱ የሚባሉት ፤ በወዲያኛው ዓለም መልካም ነገር አይቆያቸውም እና ተድላ ደስታቸውን በከንቱው ዓለም ጨርሰውታል ፤ በወዲያኛው ዓለም የሚቆያቸው ነገር የለም" ብለዋል።
ከዚህ በመለስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀድያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙትን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን እና ሁሉንም አካላት አመስግነዋል።
በሆሳዕና መንበረ ጵጵስና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን መጋቢት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ሥርዓተ ቀብራቸው የተፈፀመላቸው የብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ወላጅ እናት እማሆይ አጸደ ማርያም ከአባታቸው ከአቶ መንገሻ ጋሻው በዛ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ እጥፍወርቅ ፈጅር ጥር 21 ቀን 1928 ዓ.ም ተወልደው ባደረባቸው ሕመም በተለያዩ ሆስፒታሎች በሕክምና ሲረዱ ቆይተው የካቲት 29 ቀን 2018 ዓ.ም በተወለዱ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን ታሪካቸው ያስረዳል።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #መጋቢት ፪ (2) ቀን።
❤ እንኳን #ለኒቅዮስ_ኤጲስቆጶስ ለአቅፋስ ከተማ ሹም ለሆነ ለዮልስዮ ስሙ አውካሪስጦስ የሚባል እጆቹና እግሮቹ ሽባ የሆነ ልጅ ለፈወሰው ለታላቁ አባት #ለአባ_መከራዊ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓልና ለሮሀ አገር ለሆነ የተሰወረውን ለሚያይ #ለቅዱስ_ጎርጎርዮስ ለዕረፍቱ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #ለአባ_መከራዊ፦ይህም አባት በግቡጽ ደብቡ ከምትገኝ ከእስሙናይ ከታላላቆቹቿ ወገን ነው። ለኒቅዮስ ከተማም ኤጲስቆጶስነት ተሾመ። የስደቱና የመከራ ወራት በሆነ ጊዜም ስሙ ዮፋንስ የሚባል መኰንን ወደዚያች አገር ከንጉሥ ተልኮ መጣ። የክርስቲያን ወገኖችንም ያሠቃይ ዘንድ ጀመረ። የዚህንም የቅዱስ ኤጲስቆጶስ አባ መከራዊን ዜና ሰምቶ ወደርሱ ያመጡት ዘንድ ወታደሮቹን ላከ እርሱም ወደ መኰንኑ ከመሔዱ በፊት ወደ ቅዱስ መሠዊያው ገባ እጆቹንም ዘርግቶ ጸለየ። ንዋየ ቅዱሳቱንና የመቅደሻውን ልብሶች በመቅደሱ ውስጥ አኖረ። ከዚያም በኋላ ቤተ ክርስቲያን ይጠብቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጽሞ ማለደ። በላያችሁ የጽዮን ልጅ ደጆች ሆይ ለእግዚአብሔር ቤት ማገልጊያ የሆነ ንዋየ ቅድሳቱን ጠብቁ እያለ ታላቅ ልቅሶ በማልቀስ ጮኸ።
❤ ከዚህም በኋላ ከንጉሥ መልክተኞች ጋራ ወጥቶ ሔደ። ወደ መኰንኑም ቀረበ። ስለ ስሙና ስለ አገሩ ስም ስለ ሥራውም ጠየቀው። የኒቅዮስ ከተማ ኤጲስቆጶስ እንደሆነም ባወቀ ጊዜ እንዲገርፉትና እንዲያጐሳቁሉት ብርና እርሳስም አቅልጠው በአፉ እንዲጨምሩ አዘዘ። እግዚአብሔር የሚያጸውና የሚያስታግሠው ሆነ። ያለ ጉዳትም በጤንነት መልሶ ያነሳው ነበር። ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ገዥ ወደ ኄርሜኔዎስ ሰደደው። እርሱም ቅዱስ አባ መከራዊን እንዲአሥሩት አዘዘ።
❤ እግዚአብሔር በእጆቹ ብዙዎች ድንቆች ተአምራትን አደረገ ከአተአምራቱም አንዱ ለአቅፋስ ከተማ ሹም ለሆነ ለዮልስዮ ስሙ አውካሪስጦስ የሚባል እጆቹና እግሮቹ ሽባ የሆነ ልጅ ነበረው አባ መከራዊም በላዩ ጸለየ። ከደዌውም አዳነው። ከዚህ በኋላ በዮልዮስ ቤት ቀድሶ ለአማንያን ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው። ስለ ሥጋውም እንዲአስብና ገድሉንም እንዲጽፍለት ከዮልዮስ ጋር ስምምነት አደረገ።
❤ መኰንኑ ኄርሜኔዎስ አባ መከራዊ ስለ አደረጋቸው አስደናቂ ተአምራት በሰማ ጊዜ በተለያየ ሥቃይ ያሠቃዩት ዘንድ አዘዘ። ሕዋሳቶቹ እስቲቆራረጡ በመኰራኵሮች ውስጥ አስገብተው አሠቃዩት። ለነጣቂዎች አንበሶችም ጣሉት በባሕርም አሠጠሙት በእሳት ምድጃ ውስጥም ጨመሩት። ቅዱስ አባ መከራዊ በሥቃዩ ሁሉ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል የሚታገሥና የሚጸና ሆነ። ጌታም ያለጉዳት መልሶ በጤንነት ያስነሣው ነበር።
❤ የእመቤታችን የድንግል ማርያም ቤተ ክርቲያን የምታገለግል አንዲት ድንግል እኅትም ነበረችው። ሁለት ወንድምችም ነበሩት የአንደኛው ስም ዮሐንስ የሁለተኛውም ይስሐቅ ይባላል በእሥርቤትም ሳለ ወደርሱ መጡ አንተ ስለ አባታችን ፈንታ አባት ሁነኸን ነበር፤ እነሆ የሙት ልጆች እንሆን ዘንድ ትተኸን ትሔዳለህ እያሉ በፊቱ አለቀሱ። እርሱም አጽናንቶ ወደ ቤቶቻቸው አሰናበታቸው።
❤ ዮልዮስም "የዚህን ሽማግሌ ሞት በጽሑፍ እዘዝ ከእርሱም ታርፋለህ"ብሎ መኰንኑን መከረው። ቃሉንም ተቀብሎ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊል ተቀዳጀ።
ዮልዮስም የቅዱስ አባ መከራዊን ሥጋ ወስዶ በከበሩ በወርቅ መስቀል አደረገ ወደ አገሩ ወደ ኒቅዮስም ከአገልጋዮቹ ጋራ ሰደደው። መልካም ነፋስም ሆኖላቸው መርከቢቱ ፈጥና ሔደች፤ በከተማውም በር አንጻር ደርሳ ቆመች። ቀዛፊዎችም ሊያንቀሳቅሱዋት ፈልገው ነበር ግን አልተቻላቸውም አብዝተው በደከሙም ጊዜ ሥጋዬ በውስጡ እንዲኖር እግዚአብሔር የፈቀደው ቦታ ይህ ነው የሚል ቃል ከበድኑ ወጣ። ይህንንም ለአገር ሰዎች ንገሩአቸው የሰሌን ዝንጣፊም እየያዙ ወደርሱ መጡ በአገራቸውም ውስጥ እርሱ በመረጣት ቦታ እስከ አኖሩት ድረስ በታላቅ ክብር ተሸክመው ወሰዱት።
❤ መላው የሕይወቱ ዘመን አንድ መቶ ሠላሳ አንድ ሆነ። መጻሕፍትን እስከተማረ ድረስ ስምንት ዓመት በዲቁና ሹመት ሃያ አራት ዓመት፤ ከዚያም ቅስና ተሹሞ በቅስና አገልግሎት ሠላሳ ዓመት ኖረ፤ ከዚያም በኋላ ኤጲስቆጶስ ሁኖ ተሾመ። በዚያም ስልሳ ዘጠኝ ዓመት ኑሮ መልካም ተጋድሎውን ፈጸመ። የሕይወትን አክሊልንም ከክብር ባለቤት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርሰቶስ ዘንድ ተቀበለ። ጸሎቱ በረከቱም ከእኛ ጋር ለዘላለም ይኑር አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #የሮሀ_አገር_የተሰወረውን_የሚያይ #ቅዱስ_ጎርጎርዮስ፦ ይህም ቅዱስ ሰው አስቀድሞ ዐመፀኛና ኃጥእ ነበር። ከዚህም በኋላ ተመልሶ መነኰሰ። የጻድቃንን ማደሪያና ብዙ ዋጋቸውን የኅጥአንንም ኵነኔና አየራሱ የሆኑ ሥቃያቸውን እግዚአብሔር እስከ አሳየው ድረስ ብዙ ተጋደለ እግዚአብሔር በጸሎቱ ይማረን አሜን። ምንጭ፦ የመጋቢት2 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለጎርጎርዮስ አመ ፃመወ ወተግሀ። መልዕልተ ደብር ዘሀገረ ሮሀ። መካነ ኃጥአን ብካየ ወመካነ ጻድቃን ፍሥሐ። ዘበበፆታሁ ነጺሮ ብዙኃ። ለእለ ውስተ ምድር ሰበከ ንስሐ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመጋቢት_2።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "አፉሁ ለጻድቅ ይትሜሐር ጥበበ። ወልሳኑ ይነብብ ጽድቀ። ወሕገ አምላኩ ውስተ ልቡ"። መዝ 36፥30-3። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 1፥8-18፣ 1ኛ ዮሐ 1፥1-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 8፥14-26። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥20-31። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ባስልዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ወራትና በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
#የብፁዕ_አቡነ_ሕርያቆስ_ወላጅ_እናት_እማሆይ_አጸደ_ማርያም_ዐረፉ
መጋቢት ፩/፳፻፲፰ ዓ/ም
የብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ እና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ወላጅ እናት እማሆይ አጸደ ማርያም ከድካመ ሥጋ ዐረፉ።
በሀዲያ ሆሳዕና ከተማ ልጆችን ወልደው በክብር ያሳደጉ ከመሆናቸው በላይ "በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከብዙ ሚሊዮኖች ለአንድ የሚታደለው የሊቀ ጵጵስና ማዕረግ ያገኙትን ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስን ለቤተ ክርስቲያን ዐሥራት አድርገው ያበረከቱ ታላቅ እናት ናቸው።
ሥርዐተ ቀብራቸው በሀዲያ ሆሳዕና ከተማ በነገው ዕለት እንደሚፈጸም ተገልጿል። ኦ እግዚኦ አዕርፍ ነፍሰ አመትከ አጸደ ማርያም ሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያት ያውርስልን። በአብርሃም በይስሐቅ በያዕቆብ ዕቅፍ ያኑርልን። ለብፁዕ አባታችን እና ለቤተሰቦቻቸው እግዚአብሔር አምላክ መጽናናትን እንዲያድልልን የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ይመኛል።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #የተባረከ_የመጋቢት_ወር_ቀኑ_ዐሥራ_ሁለት ሲሆን ከሌሊቱ ሰዓት ጋር ትክክል ነው። ከዚህም በኋላ ይጨምራል።
❤ #መጋቢት ፩ (1) ቀን።
❤ እንኳን #ላሜህንም_ለወለደው ለኄኖክ ልጅ #ለማቱሳላ_ለዕረፍቱ መታሰቢ በዓል፣ ለኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ #ለአባ_በርኪሶስ_ለዕረፍቱ በዓልና #ለሰማዕቱ_ቅዱስ_እለእስክድሮስ_ለመታሰቢያ_በዓሉ እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከመታሰበው፦ #ከቅዱስ_መርቆሬዎስ ከመታሰቢያ በዓሉ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #የኄኖክ_ልጅ_ማቱሳላ፦ ዕድሜውም ዘጠኝ መቶ ስልሳ ዘጠኝ ዓመት ሆነ። በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ አባ በርኪሶስ፦ ይህም አባት ክርስቲያኖችን በሚወዳቸው በቄሣር እለእስክድሮስ ዘመን መንግሥት ተሹሞ ሳለ ሐዋርያት ሲጠብቋቸው እንደነበር በበጎ አጠባበቅ ሕዝቡን ጠበቃቸው። ከጥቂት ቀን በኋላ እለእስክድሮስ ሞተ ከእርሱም በኋላ ቄሣር መክስምያኖስ ነገሠ። ክርስቲያኖችንም በጽኑ መከራ አሠቃያቸው ከእርሳቸውም ብዙዎችን ገዳላቸው። አገሮቻቸውን ትተው የተሰደዱም አሉ። ይህም አባት ሸሽቶ ወደ ገዳም ገባ ሕዝቡም ፈልገው አጡት። ከዚህም በኋላ ስሙ ዲዮስ የተባለ ሌላ ኤጲስቆጶስ በላያቸው ሾሙ። እርሱም በጥቂት ቀን ዐረፈ። ከዚያህ በኋላ ስሙ አግርንዲኖስ የሚባል ሌላ ኤጲስቆጶስ ሾሙ። የስደቱም ወራት በአለፈ ጊዜ ይህ አባት በርኪሶስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ተመለሰ። አግርንዲኖስ የሚባል ሌላ ኤጲስቆጶስ ሹመው አገኛቸው። ወደርሳቸውም በደረሰ ጊዜ ሕዝቡ በመምጣቱ ደስ አላቸው አግርንዲኖስም ተልመሶ በመንበረ ጵጵስናው ላይ እንዲቀመጥ ለመነው በታላቅ ድካምም በወንበሩ ላይ አስቀመጡት። አግርንዲኖስም ዐረፈ።
❤ አባ በርኪሶስም እጅግ እስኪያረጅና እስኪደክም ድረስ ኖረ ወገኖቹንም ሌላ ኤጲስቆጶስ በላያቸው እንዲሾሙ ለመናቸው እነርሱም አይሆንም አሉ። በዚያም ወራት የቀጰዶቅያ ኤጲስቆጶስ ስሙ እለእስክድሮስ የሚባል አንድ ሰው ነበር። እርሱም በውስጥዋ ሊጸልይና ወዳገሩ ሊመለስ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። ሥራውንም በጨረሰ ጊዜ የበዓሉም ቀኖች በተፈጸሙ ጊዜ ወዳገሩ ሊመለስ ወደደ። በመድኃኒታችን ትንሣኤ በዓል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ መግቢያ ወደ ዕገሌ ደጃፍ ውጡ ወደ ደጃፋ መጀመሪያ የሚገባውን ያዙት፤ በጵጵስና ሥራም ይረዳው ዘንድ ከበርኪሶስ ጋር አድርጉት የሚል ቃል እንሆ ተሰማ። ወጥተውም ወደ ደጃፋ በደረሱ ጊዜ እለእስክድሮስን አገኙት ይረዳውም ዘንድ ያለ ፈቃዱ ከአባት በርኪሶስ ጋራ አደረጉት። እስከሚአርፍበትም ጊዜ አብሮት ኖረ።
መላ የሕይወቱ ዘመን አንድ መቶ ዐሥራ ሰባት ዓመት ሆነ ኤጲስቆጶስነት ሳይሾም ሰማንያ አንድ ዓመት ኖረ በሹመቱም ላይ ሠላሳ ስድስት ዓመታትን ኖረ። እግዚአብሔር አገልግሎ መጋቢት1 በሰላም አረፈ። ጸሎቱና በረከቱ ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ይኑር አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #ሰማዕቱ_ቅዱስ_እለእስክድሮስ፦ ይህም ቅዱስ ሰማዕት የሮሜ አገር ሰው ነው ለእርሱ ባለመታዙና ለረከሱ ጣዖቶቹ ባለመሠዋቱ ከሀዲው መክስምያኖስ ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው። እጅግ ከባድና ታላቅ የሆነ ደንጊያ በእጆቹና በእግሮቹ ላይ አሥሮ ሰቀለው። ብዙ ግርፋትንም ገረፈው ጐኖቹንም ቀደደ በፊቱም ላይ እሳት መብራት ጨመሩ። ሥቃዩንም ባልፈራ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕቲትን አክሊል ተቀዳጀ። የፈጣሪው በረከት ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ትኑር አሜን። ምንጭ፦ የመጋቢት1 ስንክሳር።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "አንተ ውእቱ ዘታገብእ ሊተ ርስትየ። አሕባለ ወረዉ ሊተ የአኀዙኒ። ወርስትየሰ እኁዝ ውእቱ ሊተ"። መዝ 15፥5-6። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ጢሞ 2፥1-17፣ ያዕ 1፥5፥15 እና የሐዋ ሥራ 15፥1-13። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 10፥17-26። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ወራትና በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
