uk
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

Відкрити в Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

Показати більше
609
Підписники
-124 години
-37 днів
-1130 днів
Архів дописів
ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta): ❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #የካቲት ፳፩ (21) ቀን። ❤ እንኳን  አምላክን ለወለደች #ለእመቤታች_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም ለወራዊ በዓልዋ መታሰቢያ፣ ለከበረ ለሐዋርያው #ለቅዱስ_ጳውሎስ ደቀ መዝሙር ለሆነ #ለቅዱስ_አናሲሞስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል፣ ለእስክድርያ ኃምሳ ሰባተኛ ሊቀ ጳጳሳት #ለአባ_ገብርኤል ለዕረፍት በዓልና ለአገረ ስሐ ኤጲስቆጶስ ለከበረ አባት #ለአባ_ዘካርያስ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከከበሩ #ከአባ_አካክዮስና ከኢትዮጵያ አገር ጳጳስ #ከአባ_ገብርኤል ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ በዚች ቀን አምላክን ለወለደች #ለእመቤታችን_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም የበዓልዋ መታሰቢያ ነው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በአማላጅነቷና በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_አናሲሞስ፦ ይህም ቅዱስ አስቀድሞ ከሮሜ ሰዎች ወገን የሚሆን ስሙ ፊልሞና ለሚባል ለሮሜ ሰው አገልጋይ ሆኖ ነበር ይህም ፊልሞና በሮሜ በአስተማረ ጊዜ በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት በጌታችን አመነ ይህ ፊልሞናም ከዚያ ከሮሜ አገር ወደ አስባንያ ሔደ። ይህንንም አገልጋዩን አናሲሞስን ከእርሱ ጋር ወሰደው ሰይጣን ግን አናሲሞስን አሳተው ልቡንም ለወጠውና የጌታውን ገንዘብ ሰረቀው ጌታውም እንደሚቆጣው አውቆ ሸሽቶ ወደ ሮሜ ተመልሶ ሔደና በዚያ ተቀመጠ። በእግዚአብሔርም ፈቃድ ወደ ከበረ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ሔደ ትምህርቱንም ሰምቶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ ለቅዱስ ጳውሎስም ደቀ መዝሙሩ ሆነ። ነገር ግን የጌታውን ገንዘብ በመስረቁ በአናሲሞስ ልብ ጽኑ ኀዘን አደረ ለሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የሠራውን ሁሉ ነገረው ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም "አትፍራ ልብህም አይዘን" አለው ወደ ጌታው ወደ ፊልሞናም መልክትን ጻፈለት ይቺም ስለ አናሲሞስ የጻፋት ከመልእክቶቹ አንዲቱ ናት። በመልክቱም እንዲህ አለው "እኔ በእሥራቴ ጊዜ ስለወለድኩት ልጄ እማልድሃለሁ ይኸውም አናሲሞስ ነው። የቀድሞው ሥራው አልጠቀመህም ነበር ዛሬ ግን ላንተም ለእኔም እጅግ የሚጠቅም ሁኗልና አሁንም ወዳንተ ልኬዋለሁና ልጄ እንደመሆንህ ተቀበለው። የበደለህ በደልም ቢኖር ወይም የሚከፍልህ ቢኖር በኔ ላይ አድርገው"። ❤ ይህ የከበረ አናሲሞስም ወደ ፊልሞና ወደ ጌታው በደረሰ ጊዜ በማመኑና በመጸጸቱ ደስ አለው ሐዋርያው እንዳዘዘውም አደረገለት እጅግም ወደደው ብዙ ገንዘብም ሰጠው እርሱ ግን ምንም ምን አልወሰደም" እኔ በክርስትና ባለጸጋ ሁኜአለሁ" አለ እንጂ። ከዚህም በኋላ ሸኙትና ወደ ሮሜ አገር ተመለሰ በሰማዕትነት እስከ ሚሞትበት ጊዜ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስን የሚያገለግለ ሆነ። ይህም ቅዱስ ካህን ሆኖ ተሾመ ሐዋርያትም በሥርዓት መጽሐፋቸው በአንቀጽ ሰባ ሰባት፣ ሰማንያ አንድ፣ በኅምሳ ሦስትና በኅምሳ ሰባት በምስጋና አስታውሰውታል "እንደ ታማኝ ካህን ነው" አሉ። ❤ ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የምስክርነት ዕረፍት በኋላ የንጉሥ ጭፍራ አለቃ ይህን ቅዱስ ይዞ ወደ አንዲት ደሴት ሰደደው የዚያችን ደሴት ሰዎች ሃይማኖትን እያስተማራቸው ኖረ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው። ከብዙ ቀኖችም በኋላ የንጉሥ የጭፍራ አለቃ ወደዚያች ደረሰ የከበረ አናሲሞስንም ሕያው ሁኖ የክቡር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት ለሰዎች ሲያስተምራቸው አገኘው ጽኑ ግርፋትምንም ገረፈው ጭኖቹን እንዲሰብሩ አዘዘ ምስክርነቱንም የካቲት21 ፈጸመ። የሰማዕትነት አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አናሲሞስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ትኑር  ለዘላለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የእስክንድርያ_ሊቀ_ጳጳስ_አባ_ገብርኤል፦ ይህም አባት በታናሽነቱ በአስቄጥስ ገዳም መነኰሰ በጾም በጸሎት በስግደት ተጠምዶ ኖረ በውስጡም ትሕትና ፍቅር ቅንነት አለው። በአንዲት  ዕለት ስሙ መክሲሞስ ወደ ሚባል አረጋዊ ቤት ገባ እርሱም "ልጄ ከሰው ለምን ትሸሻለህ አንተ ግን በወንዶችና በብዙ ሴቶች መካከል ትኖር ዘንድ አለህ"አለው። እርሱ ግን የሽማግሌውን የቃሉን ትርጓሜ አላስተዋለም ከጠላትም ወጥመድ ያድነው ዘንድ ሁል ጊዜ በማልቀስ እግዚአብሔርን የሚለምን ሆነ። ❤ ከእርሱም አስቀድሞ የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል በዐረፈ ጊዜ ይህን አባት ይዘው ያለ ውዴታው ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት አረጋዊ አባ መክሲሞስ ትንቢት እንደ ተናገረለት በተሾመ ጊዜ በአስቄጥስ ገዳም ተቀምጦ የቀድሞውን ተጋድሎውንና አገልግሎቱን ቸለል አላለም ስለ አብያተ ክርስቲያንም ጉዳይ ወደ እስክንድርያና ወደ ምስር ይሔድ ዘንድ ግድ በአሉት ጊዜ ይሔዳል ፈጥኖም ወደ አስቄጥስ ገዳም ይመለሳል። ❤ እርሱም በዕድሜው ጐልማሳ ስለሆነ እንስሳዊት ፍትወት ትነሣሣበት ነበር እርሱም ያጠፋት ዘንድ ለጾም ለጸሎት ለስግደትም መትጋትን ያበዛል ሊያበርዳትም ባልተቻለው ጊዜ ለአንድ አረጋዊ ተናዘዘለት እርሱም እንዲህ አለው "ይህች እንስሳዊት ፍትወት ከጾምና ከጸሎት ከስግደትም ጋር ያለ ትሕትና ሥራ አትጠፋም በበለጠ ግን ትሕትና መድኃኒትቷ ነውና"። ይህንንም በሰማ ጊዜ የጉድፍ መጐተቻ ከብረት ሠራ አጭር የሆነ የቆሸሸ ልብስ በመልበስ በሌሊት ተነሥቶ የመኰሳቱን መንደር እየዞረ ቆሻሻውን ጠርጎ ተሸክሞ ወስዶ ከራቀ ቦታ ይጥለዋል። ይህንንም ሥራ እየሠራ ሁለት ዓመት ያህል ኖረ እግዚአብሔርም ንጽሕናውንና የልቡን ትሑትነት ተመልክቶ የባሕርይ የሆነውን ፍትወት አራቀለት። ይህም አባት በገድል እንደተጠመደ ሁኖ መንጋዎቹ በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ እያስተማራቸውና እየገሠጻቸው እየመከራቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመት ኑሮ የካቲት21 በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ገብርኤል በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ዘካርያስ፦ ይህም አባት የጸሐፊዎች ወገን ነው አባቱ ግን ጸሐፊነቱን ትቶ ቅስና ተሾመ ስሙም ዮሐንስ ነው። ልጁ ዘካርያስም በአደገ ጊዜ ትምህቶችን ሁሉ ጽሕፈትንም የጽርእና የሮማውያንን ጥበብ የቤተ ክርስቲያንንም ሕግ ተማረ የንጉሥም የጭፍራ አለቃ ወሰደውና በንጉሡ ቤት ጸሐፊነት ሾመው። በጽሕፈቱም የአገረ ስሐ መኰንን የሆነው ስሙ አብጥልማዎስ የሚባል ወዳጅ ሆነው እርሱም ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደው ይመነኵሱ ዘንድ ተስማሙ። በዚያንም ጊዜ ከአስቄጥስ ገዳም ከአባ ዮሐንስ ደብር አንድ መነኰስ ወደነርሱ መጣ አብረውትም ይሔዱ ዘንድ ተስማሙ መኳንንቶችም ይህን በሰሙ ጊዜ መሔድን ከለከሉዋቸው። ከጥቂት ቀኖች በኋላ "ለእግዚአብሔር የተሰላችሁትን ስለት ለምን አትፈጽሙም" የሚላቸውን ራእይ አዩ በዚያንም ጊዜ በሥውር ወጡ እነርሱ ግን  መንገዱን አያውቁትም ነበር አንድ መነኰስም ተገለጠላቸውና ወደ አስቄጥስ ወደ አባ ዮሐንስ ገዳም መርቶ አደረሳቸው። መኳንንቱም መሔዳቸውን በሰሙ ጊዜ ከንጉሥ ዘንድ ደብዳቤ ተቀብለው በላክ ከገዳም ሊአሰወጡአቸው ተስማሙ የክቡር ባለቤት ጌታችንም ምክራቸውን በተነ።

አገልጋዮች በቅዳሴና ለሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎት ሰዓት ሞባይል ስልክ ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ መከልከሉን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስታወቀ። ሀገረ ስብከቱ የዐቢይ ጾምን አስመልክቶ አገልግሎቱ እንዴት መከናወን እንዳለበት  ከሁሉም ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎችና ሰባክያነ ወንጌል እንዲሁም ቄሰ ገበዞች ጋር ባደረገው ውይይትና ስምምነት መነሻነት  የተለያዩ መመሪያዎች  መተላለፋቸው ተገልጿል። ከመመሪያዎች አንዱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚከናወኑ  የጸሎተ ቅዳሴና ሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች የእጅ ሞባይል ስልክ ይዞ መግባት በጥብቅ  የተከለከተለ መሆኑን ለሁሉም  ገዳማትና አድባራት በተላከው የመመሪያ ደብዳቤ  ለማወቅ ተችሏል። በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት መሠረት ቅዳሴ የሁሉም ጸሎታት ማጠናቀቂያ ፣ ቀራንዮ ላይ ምንገኝበት፣ የበጉ ሠርግ ላይ የምንታደምበት፣የጌታችንን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በአንድነት ለሓጢአት ሥርየት፣ ለነፍስ ሕይወት፣ ለሃይማኖት ጽንዐትና ለመንግሥተ ሰማያት መውረሻ ይሆነን ዘንድ የምቀበልበት  ታላቅ የጸሎት ሰዓት ነው። በመሆኑም አላስፈላጊ የእጅ ስልክ አጠቃቀም ጎልጎታን ከሚያስረሱ ፣በረከትን ከሚያሳጡና  ጸጋን ከሚያስወስዱ ድርጊቶች መካከል አንዱ በመሆኑ እንደተከለከለም  ተገልጿል። ይህንን መመሪያም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሰበካ ጉባኤያት ጥብቅ ክትትል በማድረግ እንዲያስፈጽሙ  መታዘዛቸውን በተጻፈ ደብዳቤ ለማወቅ ተችሏል።

"ጾም ከመላእክት ጋር አንድ ማዕድ መቀመጥ ነው"                     ቅዱስ አትናቴዎስ                            ✨✨✨ ሠናይ ዕለት✨✨✨

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ  አሜን"። ❤             ❤ #የካቲት ፳ (20) ቀን። ❤ እንኳን #መኰንን_አርያኖስን_ለሚያጫውተው ለበገና ደርዳሪው #ለቅዱስ_ፊልሞንና ለጓደኛው #ለአናጉንስጢስ_ለቅዱስ_አስቃሎን ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓልና ለእስክድርያ አገር ሃያ አንደኛ ሊቀ ጳጳስ #ከሐዋርያው_ቅዱስ_አትናቴዎስ በኋላ ለተሹመት #ለአባ_ጴጥሮስ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከማታሰቡ፦ ከከበሩ #ከቅዱሳን_ባስልዮስ_ከቴዎድሮስና #ከጢሞቴዎስ_በእስክድርያ አገር በሰማዕትነት ከዐረፉ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                        ✝ ✝ ✝ ❤ በገና ደርዳሪው #ቅዱስ_ፊልሞን ጓደኛው #ለአናጉንስጢስ_ለቅዱስ_አስቃሎን ፦ በአንዲትም ዕለት አርያኖስ አናጉንስጢስ አስቃሎንን ጠርቶ "ለአጵሎን ሠዋ" አለው አስቃሎንም ወደ ፊልሞን ሒዶ "በእኔ ፈንታ ብትሠዋ አራት የወርቅ ዲናር እስጥሃለሁ" አለው  ፊልሞንም "ልብስህን ስጠኝና ተሸፋፍኜ በአንተ ፈንታ እሠዋለሁ" አለው። በገባም ጊዜ አውቀውት "ምን ሆንክ" አሉት ፊልሞንም "በክርስቶስ የማን ክርስቲያን ነኝ"አላቸው። አርያኖስም "በሕይወት እንድትኖር ለአማልክት ሰዋ" አለው። "ፊልሞንም በክርስቶስ ስም ከመሞት በቀር ሕይወት የለም" አለው። አርያኖስም "ጥምቀትን ሳታገኝ ፈጥኜ እገድልሃለሁ ተስፋህን ታጣለህ" አለው። ፊልሞንም ሰምቶ የክርስትና ጥምቀትን ያድለው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ በዚያንም ጊዜ ከሰማይ ብሩህ ደመና መጥቶ አጠመቀው። አርያኖስም አፍሮ ቢመለስ ብሎ ሦስት ወታደሮች እንዲጸፋት አዘዘ ፊልሞንም "የእግዚአብሔር መላእክት ስለ እኔ ደስ ሲላቸው አያለሁና ከዚህ የከፋ ቢጻፋኝም አልፍርም" አለ። አርያኖስም ባላ ባለው ግንድ ላይ ሰቅለው በፍላፃዎች ይነድፉት ዘንድ አዘዘ ግን ምንም የነካው የለም ፍላፃውም እንዳልካው ለአርያኖስ ነገሩት ዳግመኛም እርሱ እንደ ቆመ ይነድፉት ዘንድ አዘዘ አንዲትም ፍላፃ ተመልሳ፡ የአርያኖስን ዐይን ነድፋ ዐሳወረችው በዚያን ጊዜ ከተሰቀለበት አውርደው ከአናጉንስጢስ አስቃሎን ጋር ራሱን እንዲቆርጡ አዘዘ ገድላቸውን፡ ፈጽመው የሰማዕትነት አክሊል የካቲት20 ተቀበሉ። ❤ መኰንኑም በፍላፃው ሕመም በተሠቃየ ጊዜ ከቅዱሳን ደም ወስዶ ከዐይኑ ውስጥ እንዲጨምር ሰዎች መከሩት ይህንንም ሲያደርግ ዳነ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም አመነ እሥረኞችንም ሁሉ ፈታቸው እርሱም መጋቢት ስምንት ቀን በዲዮቅልጥያኖስ እጅ በሰማዕትነት ዐረፈ። የሰማዕታትም በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን አሜን።                                                       ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ጴጥሮስ፦ የእስክድርያ ሃያ አንደኛ ሊቀ ጳጳስ ነው። ይህንንም ቅዱስ ከሐዋርያዊ አትናቴዎስ በኋላ በሹመቱ ወንበር በተቀበጠ ጊዜ ከንጉሥ ዳርዮስ ከከሀዲ አርዮስ ወገኖች ብዙ መከራ ደርሶበታል። ሊገሉትም በፈለጉ ጊዜ ሸሽቶ ሁለት ዓመት ያህል ተሠወረ አርዮሳውያንም ሉቅዮስ የተባለ ከሀዲውን ሰው በእርሱ ፈንታ በወንበሩ ላይ አስቀምጠው ሁለት ዓመት ኖረ። ከዚያም በኋላ ሃይማኖታቸው የቀና ምዕመናን ሁሉም ተነሥተው አርዮሳዊ ሉቅዮስን አሳደዱትና ይህን አባት ጴጥሮስን ወደ መንበረ ሢመቱ መለሱት አርዮሳውያንንም በመጣላት እያወገዛቸው እያሳደዳቸው ሰባት ዓመት ኖረ። ከዚህም በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም የካቲት20 ዐርፎ ወደ ዘላለም ዕረፍት ሔደ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ጴጥሮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት 20 ስንክሳር።                                                       ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_እብል_ለባስልዮስ_ብፁዕ። #ወቴዎድሮስ_ካዕለ#ወጢሞቴዎስ_ሣልስ ቅኑታነ ኃይል ወጽንዕ። ውስተ ቤተ መረዓ አምሳለ እሡራን ሰብእ። ዘተጸዋዕክሙ ኅቡረ ለስምዕ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_20።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦"ተገኃሥ እምእኩይ ወግበር ሠናይ። ኅሥሣ ለሰላም ወዴግና። እስመ አዕይንቲሁ ለእግዚአብሔር ኀበ ጻድቃኑ"። መዝ 33፥14-15። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ጢሞ 3፥1-13፣ 1ኛ ጴጥ 5፥1-11 እና የሐዋ ሥራ 9፥23-32።  የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥1-17። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም በዓልና የጾም ወራት። ለሁላችንም ይሁንልን።    

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #የካቲት ፳ (20) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያውያን_ጻድቅ ውኃ ከዓለት ድንጋይ ላይ እያፈለቁ አሕዛብን ሁሉ እያስተማሩ ያጠምቁ ለነበረ፤ ኅብስትም ከሰማይ እየወረደላቸው ሕዝቡን ያቆርቡ ለነበረ ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ክፍለ_ማርያም_ዘድባጋ ከዚህ ዓለም እንደነ #ቅዱሳን_ሄኖክና_ኤልያስ ከሞት ለተሰወሩበት በዓልና #ለአባ_ገብረ_መርዓዊ_ዘአግዶ_ገዳም ለመታሰቢያ በዓላቸው እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ለአቡነ_ክፍለ_ማርያም_ዘድባጋ፦ ትውልዳቸው እንደርታ ሲሆን በ14 ዓመታቸው መንኵሰው፡ መንነው በቅተው ሲኖሩ በአንድ ወቅት ወደ አክሱም ሄዱና ወላጆቻቸው ካሉበት ደረሱ። ከቅዳሴ በኋላ መክፈልት ቆርሰው ሲያድሉ ወላጅ እናታቸው ከስተውና ጠቁረው ስላዩአቸው ለእናታቸው አዳልተው በብዙ ሰጧቸው። እናትየው ግን ጻድቁ የሰሩትን አያወቁም ነበር። ጻድቁ ከብቃታቸው የተነሳ መና ከሰማይ አየወረደላቸው ከዓለትም ላይ ውኃ እያፈለቁ ይጠጡ ነበር። አድሎ ስላደረጉ ግን በዚህ ድርጊታቸው እግዚአብሔር ተቆጥቷቸው የሰጣቸውን ይህን ጸጋውን ነሳቸው። አቡነ ክፍለ ማርያምም ይህን ባወቁ ጊዜ "ወዮልኝ ወዮታ አለብኝ" ብለው ከሰው ሳይገናኙ ዋሻ ገብተው ድፍን 11ዓመት በለቅሶና በዋይታ እግዚአብሔርን ለምነው ነው ይቅር ተብለው የቀደመ ጸጋቸውና ክብራቸው የተመለሰላቸው። ❤ ከዛ በኋላ ውኃ ከደረቅ ጭንጫ ላይ እያፈለቁ አሕዛብን ሁሉ እያስተማሩ ያጠምቁ ጀመር። ኅብስትም ከሰማይ እየወረደላቸው ሕዝቡን ያቆርቡ ጀመር። ጻድቁ በመጨረሻ በየካቲት 20 ቀን እንደነ ሄኖክና ኤልያስ ዐርገዋል እንጂ በምድር ሞት አልቀመሱም። ትልቅና አስደናቂ ገድላቸው በአክሱም ይገኛል። ከአቡነ ክፍለ ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።

"ሆዳችሁ ጠግቦ ከምታቀርቡት አንድ መቶ ጸሎትና ተራራ ከሚያርድ ድምጻችሁ ይልቅ በጾም ውስጥ ሆናችሁ የምታቀርቡት አንድ ጸሎት ተሰሚነት አለው። ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ✨✨✨ሠናይ ዕለት✨✨✨

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #የካቲት ፲፱ (19) ቀን። ❤ እንኳን #ለተጋዳይ_መነኰስ ለሆኑት በዝሙት ላለመውደቅና ገሃነመ እሳትን በማሰብ እግራቸውን የሚነድ እሳት ውስጥ በመጨመር ዘማዊቷንም ሴት ለንስሓና ለጽድቅ ላበቋት ለታላቁ አባት #ለአባ_መርትያኖስ_ሥጋቸው_ከአቴና_አገር_ወደ_አንጾኪያ_ለፈለሰበት_በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                             ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #አባ_መርትያኖስ፦ እርሱም ሽንግላ በኃጢአት ልትጥለው በወደደች ጊዜ ከአመንዝራ ሴት ከተፈተነ በኋላ እርሱ ግን መንኵሳ በገድል እስከ ተጸመደች ድረስ ስቦ ወደ ንስሓ መልሷታል። ከዚህም በኋላ መኖሪያውን ትቶላት ከአገር ወደ አገር የሚዞር ሆነ ከአቴና አገርም ደርሶ በዚያ ጥቂት ቀን ኖረ ጥቂትም ታመመና በሰላም አረፈ ዜናው በግንቦት ሃያ አንድ ቀን እንደተጻፈ። ❤ የከበረ ቴዎድሮስም ለአንጾኪያ አገር በከሀዲው የፋርስ ንጉሥ ዘመን ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ይህ አባት የካህናት አለቆችንና ምእመናንን ልኮ ሥጋውን ከአቴና አፍልሰው ወደ አንጾኪያ ከተማ አመጡት በምስጋናም እየዘመሩ አክብረው ተቀበሉት ሊቀ ጳጳሳቱም ተሳለመው በሣጥንም አድርጐ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖረው። በዚችም ዕለት የካቲት19 በዓልን አደረገለት። ለእግዚአብሔር ምስና ይሁን እኛንም በአባ መርትያኖስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት19 ስንክሳር።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ "#ሰላም_ለፍልሰተ_ሥጋከ ኀበ አንጾኪያ እምአቴና። #በእደ_ቴዎድሮስ አብ ዘሥርግው በጵጵስና። #መርትያኖስ_ተወከፍ ዘመሥዋዕተ ቃል ጼና። በከናፍረ ልብ ወበአፈ ኅቡእ ሕሊና። ሶበ ለሥጋከ እኤምኅ ሣፁና"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲ_19።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "እስመ ብከ እምድኅን እምንሱት። ወበአምላኪየ እትዐደዋ ለዕረፍት። ለአምላኪየሰ ንጹሕ ፍኖቱ"። መዝ 17፥19-20።  የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 7፥22-ፍ.ም፣ ያዕ 4፥1-11 እና የሐዋ ሥራ 16፥16-22። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 13፥10-18። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም በዐልና የጾም ወራት። ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #የካቲት ፲፱ (19) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ በአባ ጰንጠሌዎን እጅ ምንኵስና ለተቀበሉ ለታላቁ አባት #ለአቡነ_አባለ_ክርስቶስ ለልደታቸው በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_አባለ_ክርስቶስ፦ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አቡነ አባለ ክርስቶስ ዘደብረ መድኃኒት ጻድቁ አቡነ አባለ ክርስቶስ ከአባታቸው ቅዱስ አቃርዮስ እና ከእናታቸው ቅድስት ታውክልያ በ8ኛው ክፍለ ዘመን በየካቲት 19 910 ዓ.ም በአክሱም ከተማ የተወለዱ ጻድቅ ሲሆኑ ከሰውነታቸው ማሀል ዲካባ፣ ማርትያስ፣ ክስብኤል የሚሉ ኅቡአን የሥላሴ አስማት ተጽፎውላቸው የተወለዱ ጻድቅ ናቸው። ❤ በዚሁ መሰረት ከጻድቁ አቡነ ጰንጠሌዎን በሠላሳ ሁለት ዓመታቸው ምንኲስናን ከተቀብሉ በኋላ ጽላትን ለ24 ዓመታት ያህል እያጠኑ ከቆዩ እንደ ሌሎቹ ቅዱሳን ዛሬ ገደማቸው በሚገኝበት እና አፅማቸው ካረፈበት ገዳማቸው ተጋድሎን በመፈጸም ከፈጣሪያቸው በታሕሳስ 19 ቀን ቃልኪዳን ተቀብለው በ 332 ዕድሜያቸው ያረፉ ኢትዮጵያዊው ጻድቅ ናቸው። ❤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸው ቃል ኪዳን "ዝክርህን የዘከረ ስምህን የጠራ እስከ 24 ትውልድ ምሬልሀለሁ" አላቸው። "ስምህን በመጥራት የተራቡ ያበላ የተጠሙ ያጠጣ የታረዙትን ያለበሰ ለቤተ ክርስቲያንህ የተለያዩ ምፅዋት የሰጠ እስከ 28 ትውልድ አድነዋለሁ" አላቸው። ማየ ጸሎትህም፣ ፀበልህ፣ የተጠመቁ፣ የታጠቡ እስከ 27 ትውልድ አድነዋለሁ" አላቸው። ገዳምህን ለመሳለም፣ ለመሳም፣ አስበው ያልተሳካላቸው 26 ትውልድ አድነዋለሁ" አላቸው። ቤተ ክርስተያንህን የሰራ በመንግስተ ሰማያት እስከ 33 ትውልድ የብርሃን ማደርያ እሰራለታለሁ አላቸው። ዝክርህን፣ መታሰብያህን፣ ሊያደርግ ብሎ ያሰበ ነገር ግን በተለያየ ምክንያት ሳይሳካለት የቀረ እሰከ 25 ትውልድ አድነዋለሁ" አላቸው። ❤ "በገዳምህ በየዓመቱ እና በየወሩ ቅዱስ ቊረባን የተቀበለ እስከ 35 ትውልድ አድነዋለሁ" አላቸው:: መፅሓፍህን የፃፈ፣ ያነበበ፣ የተረጎመ፣ የሰማ እስከ 28 ትውልድ አድነዋለሁ" አላቸው። "ይህች የምታርፍባት የነበርክ ድንጋይ የመካናት ማህፀን ፈትታ ልጅነት ትሰጣለች" አላቸው። ሰውነታቸው በተለያዩ ሕመሞች፣ በሽታዎች የተያዙ አለቱን ቤተክርስቲያኑን በምትፈለፍልባት የነበርክ በትርህ ታሽቶው ይደናሉ" በማለት በማይሻር ቃሉ ይሀንን ቃል ኪዳንገበቶላቸው በክብር ወደ ሰማያት አረገ። ❤ ገዳሙ የምገኘው ከአክሱም ወደ ማሕበረ ጻድቃን ዴጔ 17 ኪሎሜትር ተጉዘው ማሕበረ ጻድቃን ዴጔ ከተማ ላይ እንደደረሱ ወደ ግራ በመንገጠል 25 ኪ.ሜ እንደተጓዙ ጠላዕ በምትባል ትንሽ ከተማ ቀበሌ ሲደርሱገዳሙ አስደናቂ በሆነ አቀማመጥ ከሚያስደንቅ ሸለቆ ከአለት ተፈልፍሎ የተሰራ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ባለ ቃል ኪዳንገዳሙ ያገኙታል። በገዳሙ በየዓመቱ ታሕሳስ 19 ቀን የጻድቁ በዓለ ዕረፍት ፥ የካቲት 19 ቀን የጻድቁ በዓለ ልደታቸው ዓበይት በዓላት ብዙ ምእመናን በተሰበሰቡበት በታላቅ ድምቀት ይከበራል። ጻድቁ ገድለኛ እና ታአምረኛ በመሆናቸው በእሳቸው እጅ ከአለት ተፈልፍሎ የተሠራ ቤተ መቅደስ፣ቅኔ ማህሌት፣ ምቋም ሰዓታት እና ቤተ አንድነት በገዳሙ ውስጥ ይገኛል። ያርፉባት የነበረች ድንጋይ እብነ ሕይወት ተብላ እንድትጠራ እና የመካናት ማህፀን ፈትታ ልጅ እንድ ትሰጥ ቃል ኪዳንየተሰጣት ድንጋይ እና ቤተ መቅደሱን የሚፈለፍሉባት የነበረች በትረ ትእምርት ለምስክር ያህል እስከ አሁን ብዙ ህሙማን እና መካናት እየተፈወሱ በገዳሙ ውስጥ ይገኛሉ። ❤ በገዳሙ ካሉ ቅርሳቅርሶች ከ1000 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው መዛግብተ እክል፣ ጎተራዎች፣ ሰፍየዶች፣ ከሸክላ የተሰሩ ፅዋዎች እና ጋኖች በአስገራሚ ሁኔታ እስከ አሁን በገዳሙ ውስጥ ተጠብቀው ይገኛሉ። እንዲሁም በገዳሙ ውስጥ የሚገኙሁለት ዓይነት ጠበል ማለትም መጀመርያ ወደ ገዳሙ ሲገቡ በመስቀላቸው ባርከው ከዐለት ያፈለቁት ማየ ጸሎት እና በዕረፍታቸው ቀን ከመቃብራቸው ከቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚመነጭ ማየ ጸሎት ብዙ ህሙማን እየተፈወሱበት የሚገኝ ታሪካዊ ገዳም ነው። ከአባታችን ከአቡነ አባለ ክርስቶስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን!።

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #የካቲት ፲፰ (18) ቀን። ❤ እንኳን #ከሰባ_ሁለቱ_አርድእት ለአንዱ ለጌታችን ወንድም ለተባለ #ለሐዋርያው_ለቅዱስ_ያዕቆብ ለዓመታዊ ለመታሰቢያ በዓሉና ለታማኝ ለከበረ አባት ለአንጾክያ አገር ሊቀ ጳጳስ ከአርዮሳውያን ብዙ ስደትና እንግልት ለደረሰበት #ለአባ_መላልዮስ ለዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን፡፡                                                          ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ወልደ_ዮሴፍ፦ ይኸውም ቅዱስ የጌታችን ወንድም የተባለውና የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ የነበረው ነው፡፡ እርሱም የጠራቢው የዮሴፍ፡ልጅ ሲሆን ከአራቱ ልጆቹ ትንሹ መጨሻው ነው፡፡የቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ እናቱ በልጅነቱ ስለሞተችበትና የብርሃን እናቱ የሆነች ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን ዮሴፍ አረጋዊ በ83 ዓመቱ ጠባቂ ይሆናት ዘንድ ወደቤቱ ሲወስዳት ድንግል ማርያም ቅዱስ ያዕቆብን የሙት ልጅ ሆኖ አግኝታው ከተወደደ ልጇ ከጌታች ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብራ ተንከባክባ አሳድጋዋለች፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ያዕቆብ ድንግልና ንጹሕ ሆኖ ከጌታችን ጋር እየተጫወተ አብሮ አድጓል፡፡ ❤ ከጌታችን ዕርገት በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ አድርገው ሾመውታል፡፡ ብዙዎችንም አስተምሮ ወደ ቀናች ሃይማኖት መልሷቸዋል፡፡ ሕዝቡም የታመሙትን ድውያንን ሁሉ እያመጡለት ይፈውሳቸው ነበር፡፡ ከኢየሩሳሌምም ውጭ እየሄደ ያላመኑትንም አስተምሮ እያጠመቀ ቤተ ክርስቲያን ይሠራላቸው ነበር፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ በጾም በጸሎት ሆኖ በመቆም ብዛት እግሮቹ አብጠው ነበር፡፡ ❤ አንድ ቀን አይሁድ ተሰብስበው መጥተው ጌታችን የማን ልጅ እንደሆነ ይነግራቸው ዘንድ ወደ ቅዱስ ያዕቆብ መጡ፡፡እነርሱም ወደ ቅዱስ ያዕቆብ የመጡት ጌታችን የዮሴፍ ልጅ እንደሆነና የእርሱም የሥጋ ወንድም እንደሆነ እንደሚነግራቸው አስበው ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ያዕቆብ ከፍ ካለው ከሦስተኛው መደብ ላይ ወጥቶ ጌታችን የራሱ የያዕቆብና የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ መሆኑን መሰከረባቸው፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ፍጹም አምላክ መሆኑን፣ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና ከአብም ጋር፡ ትክክል እንደሆነ መሰከረባቸው፡፡ ይህንንም በሰሙ ጊዜ አይሁድ እጅግ ተናደው በጽኑ ግርፋት ካሠቃዩት በኋላ ራሱን ቀጥቅጠው ስለገደሉት ሰማዕትነቱን፡ ሐምሌ 18 ቀን በድል ፈጽሟል፡፡ ከሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ረድኤት በረከትን ያሳትፈን። በጸሎቱ ይማረን!። ምንጭ፦ ገድለ ሐዋርያትና መዝገበ ቅዱሳን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_መላልዮስ፦ ይህም ቅዱስ አዋቂና አስተዋይ ነበረ ነው፡፡ በታናሹ ቈስጠንጢኖስም ዘመነ መንግሥት በአንጾኪያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ፡፡ ከተሾመም እስከ ሠላሳ ቀን ኖረ፡፡ ከዚያም በኋላ አርዮሳውያንን አወገዛቸው። በአንጾኪያ ካለች ቤተ ክርስቲያንም፡ አሳደዳቸው። ንጉሡም በሰማ ጊዜ ከመንበረ ሢመቱ ሊቀ ጳጳሱን አሳደደው እርሱ አርዮሳዊ ነውና። ❤ የአንጾኪያ አገር ታላላቆችና ኤጲስጶሳት ካህናቱም ተሰብስበው ስለ ሊቀ ጳጳሳቱን ይመልስላቸው ዘንድ የልመና ደብዳቤ፡ ጽፈው ለንጉሡ ላኩ፡፡ ንጉሡም ልመናቸውን ተቀብሎ መለሰላቸው፡፡ ይህም አባት በተመለሰ ጊዜ አርዮሳውያንን ወደ ማውገዙ ተመለሰ በቃላቸው የሚያምኑትንም ስሕተታቸውንና ስድባቸውን ግልጽ እያደረገ ወልድ ከአብ ባሕርይ እንደ ተወለደ በመለኮቱም ትክክል እንደሆነ በሁሉ የሚሰብክ የሚያስተምር ሆነ። ዳግመኛ አርዮሳውያን ተነሡ የንጉሡን ልብ ወደእርሳቸው እስከ መለሱ ድረስ ይህን አባት እየወነጀሉ ወደ ንጉሥ ጻፉ ዳግመኛም ልኮ ከፊተኛው ወደሚርቅ አገር አሳደደው። ወደ ተሰደደበት አገር በደረሰ ጊዜ መልእክቶቹን ጽፎ በመላክ ከወገኖቹ ጋር እንደ ሆነ ከእርሳቸውም ሥውር የሆነውን የመጻሕፍትን ቃል ይተረጒምላቸው ነበር፡፡ በአንጾኪያ ላሉ መንጋዎቹም ይደርሳቸውል አዋቂዎች የሆኑ ኤጲስቆጶሳትንና ቀሳውስትን ልዩ በሆነች ሦስትነት ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ አባቶቻችን ያስተማሩዋት የቀናች ሃይማኖትን እንዲህም እያደረገ እስከ ዐረፈበት ቀን ድረስ በተሰደደበት ብዙ ዘመናት ኖረ። ❤ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም አመስግኖታል፡፡ የምስጋና ድርሰቶችንም ደረሰለት፡፡ ስለቀናች ሃይማኖትም ብዙ መከራ ስለደረሰበት ክብሩ ግርማው ከከበሩ ሐዋርያት ክብር እንደማይጎድል ተናገረ፡፡ የአባ መላልዮስ ዕረፍቱ የካቲት18 ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱ ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የካቲት 18 ስንክሳር።                              ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለመላልዮስ_ዘእሙን_ነገሩ። አርዮሳውያን ሕዝብ እለ አውጽእዎ እማኅደሩ። #አፈ_ወርቅ_ዮሐንስ_በከመ_ወደሶ በዕለተ ተዝካሩ። እንበይነ ስደቱ ወእንበይነ ብዙኅ ኅሣሩ። እምሐዋርያት ይቤ ኢየሐጽጽ ክብሩ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_18።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ይዘግቡ ወኢየአምሩ ለዘይስተጋብዑ። ወይእዜኒ መኑ ተስፋየ አኮኑ እግዚአብሔር። ወትግሥትየኒ እምኀቤከ ውእቱ"። መዝ 38፥6-7። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 6፥19-22።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ። ውስተ ኵሉ ምድር ወጽአ ነገሮሙ። ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ"። መዝ 18፥3-4። የሚነበቡት መልዕክታት ገላ 1፥15-ፍ.ም፣ ያዕ 1፥1-12 እና የሐዋ ሥራ 21፥17-27። የሚነበበው ወንጌል ማቴ13፥53-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም የቅዱስ ያዕቆብ የዕረፍት  በዓል። በሁላችንም ይሁንልን።

📢📢📢እንኳን ለአብይ ፆም በሰላም አደረሳችሁ📢📢📢 እንደሚታወቀው በየዓመቱ የአብይ ፆምን አስመልክቶ ከዘወረደ እስከ ኒቆዲሞስ የሚቆይና ከሰኞ እስከ አርብ በየሳምንቱ ከጠዋቱ 11:30 ሰዓት⏰ የሚደረገው የጸሎት መርሐግብር ማክሰኞ 18/06/2017 ዓ.ም ስለሚጀምር የምትችሉ ሁላችሁም ተጠራርታችሁ ተገኝታችሁ የፆሙ የበረከቱ ተካፋይ እንድትሆኑ በአምላከ ቅድስት አርሴማ ስም እናሳስባለን 🙏                                                         መልካም ፆም                                                       ትምህርት ክፍል

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤ ❤ እንኳን #ለዐቢይ_ጾም_ለመጀመርያ_ሳምንት #ለዘወረደ (ለጾመ ሕርቃል) እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #የዚህ_ሳምንት_የዘወረደ_መዝሙር፦ ሃሌ ሉያ  "#ተቀነዩ_ለእግዚአብሔር_በፍርሃት_ወተሐሠዩ_ሎቱ በረዓድ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ ባኡ ቅድሜሁ በተጋንዮ ወውስተ አዕፃዲሁ በስብሐት እመንዎ፤ እ፣ #ንጹም_ጾም_ወናፍቅር_ቢጸነ_ወንትፋቀር_በበይናቲነ፤ እ፣ አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ እስመ ሰንበትሰ በእንተ ሰብእ ተፈጥረት፤ እ፣ ምሕረተ ወፍትሐ አሐሊ ለከ እዜምር ወእሌቡ ፍኖተ ንጹሐ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ አባግዐ መርዔቱ። ትርጉም፦ #ለእግዚአብሔር_በፍርሃት_ተገዙ፣ ለእርሱም መገዛት ደስ ይበላችሁ። #እግዚአብሔር ቸር ምሕረቱም ለዘላለም፣ እውነቱም ለልጅ  ልጅ ነውና። እኛስ ሕዝቡ የማሰማሪያው በጎች  ነን፤ ወደ ደጁ በመገዛት፣ ወደ አደባባዮችም በምስጋና ግቡ፤ #ጾምን _እንጹም፤ #ጓደኞቻችንን_እናፍቅር_እርስ_በርሳችንም_እንፋቀር። ሰንበት ስለሰው ተሠርታለችና ሰንበትን እናክብር። እውነትንም እንሥራ፤ አቤቱ ምሕረትንና ፍርድን እቀኝልሃለሁ፤ እዘምራለሁ፤ ንጹሕ መንገድንም አስተውላለሁ። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በጾመ_ድጓው ላይ።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ዘወረደ፦ የ0ቢይ ጾም የመጀመሪያው እሁድ (ሳምንት) ዘወረደ ይባላል። ❤ ጌታችን እኛን ለማዳን ከሰማይ መውረዱን የሚነገርበት ሳምንት በመሆኑ ዘወረደ ተብሏል። ❤ ከሰማይ ወረደ ማለት እርሱ የሌለበት ኖሮ ካለበት ወደዚህ መጣ ማለት አይደለም እርሱስ ጽርሐ አርያም ምጥቀቱ በርባኖስ ጥልቀቱ ፥ አድማስ ናጌብ ስፋቱ ተብሎ የማይነገርበት በዓለም ሙሉዕ ነውና ዓለማትን ቢወስን እንጂ ዓለማት እርሱን አይወስኑትም ።   ❤ የፀሐይ ብርሃን ከክበቡ ሳይለይ ከ0ይናችን ብሌን ጋር እንደሚዋሓድ ወልደም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በምልዓቱ መወሰን ሳይኖርበት በሥጋ ማርያም መገለጹን ሰው መሆኑን ያስረዳል :: ❤ ከሰማይ ወረደ ሲባል ስንሰማ "ሰማይ" ያለው ዕበዩን፣ ክብሩን ፣ ልዕልናውን ፣ ጌትነቱን፣ መንግሥቱን ፣ ርቀቱን .... ነው :: ስለዚህ ከሰማይ ወረደ ማለት የባሪያውን መልክ ይዞ ሰው መሆኑን ለመግለጽ ነው። ፊል 2፥6-8 ❤  ሰው ሆኖ መፈጠር ታላቅ ክብር ነው ለአምላክ ግን ሰው መሆኑ ተዋርዶ ነውና ይልቁንም እኛን ለማዳን በለበሰው ሥጋ መራብ መጠማቱ ፣ መገረፍ መታመሙ ... እንኳን ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ይቅርና ከመላእክት እንኳን ያነሰበት ነው መላእክት በባህሪያቸው መራብ መጠማት፣ መታመም የለባቸውምና " ከመላእክት እንኳን አሳነስከው" ያለውም ስለዚህ ነው ። መዝ 8፥5፣ ዕብ 2፥7 ❤ ይህ ማለት ግን ወልድ ሰው መሆኑ አምላክነቱን አጥቶ በዚህም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አነሰ ማለት አይደለም ጌታችንም "አብ ይበልጠኛል" ያለው በለበሰው ሥጋ ባገኘው መራብ መጠማት አነሰ ለማለት ነው አብ እና መንፈስ ቅዱስ ሰው ሆነው መራብ መጠማት ... ያላገኛቸው መሆኑን ለመግለጽ ነው። ዮሐ.14፥28 ❤ ቅዱስ ያሬድ ጾመ ድጓውን ሲጀምር  ሃሌ ሃሌ ሉያ "ዘወረደ እም ላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኩሉ ዘየሃዩ በቃሉ"። ትርጉም፦ ከሰማየ ሰማያት የወረደ አይሁድ የሰቀሉት ሁሉን በቃሉ እንደሚያድን አይሁድ ያላወቁት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።  በማለት ሰው ሆኖ በአይሁድ ተዋርዶ ያገኘው መሆኑን የዚህን ሳምንት ጠቅላላ ሀሣብ ይገልጻል። ምንጭ፦ ከአምኃ ሥላሴ (መኩሪያ ተስፋዬ) ፔጅ የተወሰደ።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዐቢይ_ጾም የመጀመሪያው ሌላ ስሙ #ጾመ_ሕርቃል፦ ሕርቃል ማን ነው? ለምንስ በስሙ ተሰየመ? በ614 ዓ.ም ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በመውረር ጥቃት አደረሰ፡፡ በዚህ ወቅት በኢየሩሳሌም ንግሥት ዕሌኒ በሠራችው ቤተመቅደስ ውስጥ ሲገባ ንግሥቷ በክብር አስቀምጣው የነበረው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ፀሐይ ሲያበራ አገኘው፡፡ ❤ ቢነካው አቃጠለው ዲያቆናቱን አሸክሞ ሌላውን ንዋየ ቅድሳት ዘርፎ 60ሺ የሚደርሱትን አቁስሎ ገድሎ 3ሺ የሚሆኑትን ማርኮ ከተማዋንም አቃጥሎ ወደ ፋርስ ባቢሎን ይመለሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ከጦርነቱ ያመለጡ በየዋሻው በየጉራንጉሩ ገብተው የተሸሸጉ ተሰብስበው ከ14 ዓመት በኋላ በ628 ጩኸታቸውንና የደረሰባቸውን በደል ለክርስቲየኑ የሮም ንጉሥ ሕርቃል ይነግሩታል፡፡ ❤ እርሱም "ሐዋርያት ሰውን የገደለ  ዕድሜውን በሙሉ ይጹም ስላሉ እንዴት ላድርገው?" አላቸው እኛ "የአንተን ዕድሜ ተከፋፍለን እንጾማለን" ብለው አንድ አንድ ሳምንት ደርሷቸው ጾሙን በሚገባ ጾመውታል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና የተማረኩ ክርስቲያኖችን ለመመለስ ሕርቃል ጦር መዝዞ በኪርዮስ ላይ ተነሳበት ድል ለሕርቃል ሆነና መስቀሉን ያለበትን አጥቶ ሲቸገር መስቀሉን ሲቀብርና ዲያቆናቱን ሲያስገድል በመስኮት ሆና ያየችው ከኢየሩሳሌም የተማረከች አንዲት ብላቴና አሳይታው አውጥቶ በልብሰ መንግሥቱ ጠቅልሎ ወደ ቊስጥንጥንያ ተመለሰ፡፡ ❤ የተማረኩት በሙሉ ነጻ ወጡ ይህን ለማሰብ ለማስታወስ በተጨማሪም በኃጢአት ላይ ድል እንድናገኝ መንፈሳዊ ጦር በውስጣችን እንዲበዛልን መስቀልህ ከምርኮ እንደተመለሰ እኛንም ከኃጢአት ምርኮ መልሰን ለሕርቃል ድል መንሳትንና በጠላቶቹ ላይ ኃይልን እንደሰጠኸው ለእኛም በኃጢአት ላይ ድል መንሳት መንፈሳዊ ኃይልን ስጠን እያልን እንጾመዋለን፡፡ ❤ በጌታ ጾም ላይ እንዲጾም የሆነበት ምክንያት ጾሙ የጌታ ጾም በሚጾምበት ወቅት ላይ ስለተጾመ ቤተክርስቲያናችን አብራ ደንግጋዋለች፡፡ እዚህ ላይ በዚያን ጊዜ ለሕርቃል ሕዝቡ ሱባኤ ይዞለታል፡፡ ❤ ዛሬም እኛ ለቤተክርስቲያን ያደረግነውን በማሰብ እግዚአብሔር አምላክ ለሕርቃል የሰጠውን በጠላቶቹ ላይ ድል መንሳትን ለእኛም እንዲሰጠን የምንጠይቅበት ስለሆነ የመጀመሪያውን ሳምንት በሕርቃል ሰይመን ጾሙን እንጾማለን፡፡ ❤ የእኛ ጠላት የጨለማ ገዥ የሆነው ዲያቢሎስ ነውና እሱን ደግሞ በጾም እንደምናሸንፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡ ምንጭ፦ የመጋቢት 10 ስንክሳር እና ከፌስቡክ ከማኅበረ ጎዶልያስ ዘ ዑራኤል የተወሰደ።                                 ✝ ✝ ✝ ❤ #የዘወረደ_አራራይ_ዜማ፦ ሃሌሉያ "#መሐረነ ንጉሠ ስብሐት #ተሣሀለነ_እግዚአ_ለሰንበት አቡሃ ለምሕረት #ወሀበነ_ጾመ ለንስሐ በዘይሰረይ ኃጢአት። ትርጉም፦ #የምስጋና_አምላክ ማረን የምሕረት አባት #የሰንበት_ጌታ_ይቅር_በለን #ጾምን_ለንስሐ_ስጠን  ኃጢአታችን ይሰረይ ዘንድ፡፡ #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በጾመ_ድጓው_ላይ።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት። ወተኀሠዩ ሎቱ በረዓድ። አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐዕ እግዚአብሔር"። መዝ 2፥11-12። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 13፥7-16፣ ያዕ 4፥6-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 25፥13-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 3፥10-25። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም የቅበላ በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #የካቲት ፲፬ (14) ቀን። ❤ እንኳን #ለታላቁ_አባት ሃይማኖታቸው ለቀና ምዕመናን መምህራቸው ለሆነ ለአንጾክያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ለከበረ አባት #ለአባ_ሳዊሮስ ለዕረፍቱ በዓል፣ ለእስክንድርያ ለኃምሳኛ ሊቀ ጳጳስ በጸሎቱ አንድ ሙት ላስነሳ ለከበረ አባት #ለአባ_ያዕቆብና ሰባ አምስተኛ ሊቀ ጳጳሳት ለከበረ አባት #ለአባ_ቄርሎስ ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከቅዱሳን_ከዳርዮስ፣ #ከጳውሎስ_ከአኩደራስና_ከሊድና ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                                               ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ሳዊሮስ_ዘአንጾኪያ፦ የዚህ ቅዱስ ዘመዶቹ ከሮሜ አገር ናቸው አባቱም ስሙ ሳዊሮስ የሚባል ኤጲስቆጶስ ነው። እርሱም ስለ ንስጥሮስ በኤፌሶን ከተማ ጉባኤ በሆነ ጊዜ ከሁለት መቶ አባቶች ኤጲስቆጶሳት ጋር መጣ በዚያም እንዲህ የሚለውን ራእይ አየ "ከአንተ የሚወለድ ልጅህ ስሙም እንደ ስምህ ሳዊሮስ ተብሎ የሚጠራ እርሱ ለቀናች ሃይማኖትን" ያጸናታል። ❤ ይህም ኤጲስቆጶስ በዐረፈ  ጊዜ ልጁን ሳዊሮስ ብለው ጠሩት ከቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆነውን ጥበብን ሁሉ ተማረ። ከመምህሩም ወጥቶ ወደ አንድ ቦታ ሲጓዝ በዋሻ ራሱን እሥረኛ አድርጎ የሚኖር ጻድቅ ሰው ተገናኘው በእርሱም ደስ ብሎት "የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሃይማኖታቸው ለቀና ምዕመናን መምህራቸው የሆንክ ሳዊሮስ ሆይ መምጣትህ መልካም ነው" አለው። ሳዊሮስም ከቶ ሳያውቀው በስሙ በጠራው ጊዜ የሚደረግለትንም ከመሆኑ አስቀድሞ በመናገሩ አደነቀ። ❤ ከዚህም በኋላ ሳዊሮስ ትሩፋት በመሥራት አደገ መልካም ስም አጠራሩና ዜናው ተሰማ በአባ ሮማኖስ ገዳም መንኵሶ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ በትሩፋትም ሥራ እጅግ የተጠመደ ሆነ የከበረ ወንጌል "በተራራ ላይ የተሠራች መንደር መሠወር አትችልም" እንዳለ ዜናው በሁሉ ዘንድ ተሰማ። የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳትም በዐረፈ ጊዜ አዋቂዎች ኤጲስቆጶሳት ይህን የከበረ ሳዊሮስን ይሾሙት ዘንድ ተስማምተው ያለ ውዴታው ወስደው በአንጾኪያ አገር ላይ ጵጵስና ሾሙት በሹመቱም እስከ ዓለም ዳርቻ ያለች ቤተ ክርስቲያን ብርሃን ሆነላት በአገሮች ሁሉ ወዳሉ መናፍቃን ከሀድያን ትምህርቱ በሚደርስ ጊዜ ሁለት አፍ እንዳለው ስለታም ሰይፍ ሥራቸውን ይበጥሳልና። ❤ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ አማኒ ንጉሥ ሙቶ በርሱ ፈንታ ስሙ ዮስጥያኖስ የሚባል መናፍቅ ነገሠ ንግሥቲቱ ሚስት ግን ሃይማኖቷ የቀና ነው ስማ ቴዎድራ ይባላል። ንጉሡም የኬልቄዶን ወደ ሆነች ወደረከሰች ሃይማኖቱ ይህን የከበረ አባት ያስገባው ዘንድ ያስፈራራው ነበር እርሱ ግን ፈርቶ አይትዘዝለትም ቊጣውንም የሚፈራ መስሎት በእርሱ ላይ አብዝቶ ተቆጣ ቊጣውንም ባልፈራ ጊዜ በሥው፡ ሊያስገድለው መከረ ንግሥቲቱም አውቃ ከንጉሡ ፊት ይሸሽ ዘንድ ሊቀ ጳጳሱን መከረችው እርሱም በሥውር ወጥቶ ገለል አለ። እግዚአብሔር የዚህን አባት ሞት አልፈቀደምና ስለ ምእመናንም ጥቅም ጠበቀው። በአንድ ተራ መነኵሴ አምሳል ሁኖ፡ በቦታዎችና በገዳማት የሚዘዋወርና ምእመናንን የሚያጠናክራቸው ሆነ ስካ በሚባል አገር ስሙ ዶርታኦስ ከሚባል ደግ ምእመን ባለ ጸጋ ሰው ዘንድ ተምጦ ሳለ ጌታችን በእጆቹ ብዙ ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ ስካ በተባለ አገር እስከ ዐረፈ ድረስ በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ ሁሉንም ያስተምራቸው ነበር ከዚህም በኋላ ወደ ዝጋግ ገዳም አፈለሱት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ሳዊሮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ቄርሎስ፦ ይህም አባት ፍዩም ከምትባል አገር ነው። በእርሷም ቅስና ተሹሞ ኖረ ከዚህም በኋላ ከዚያ፡ ለቆ ከምስር ከተማ ውጭ ወደ ሆነች የኢትዮጵያውያን የጒድጓድ ውኃ ወዳለበት ወደ ቅዱስ ፊቅጦር ገዳም ደረሰ በውስጡም ታላቅ ተጋድሎን እነተጋደለ ብዙ ዘመናትን ኖረ። ❤ የዕውቀቱና የቅድስናው ዜና በተሰማ ጊዜ ያለ ውዴታው ይዘው በእስክድርያ አገር ሊቀ ጵጵስና ሾሙት መንጋውንም በበጎ አጠባበቅ ጠበቀ በቊርባንና በጸሎት ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊሠሩት የሚገባቸውን ለካህናት ሦርዓትን ሠራ። በሹመቱም ሰባት ዓመት ከዘጠኝ ወር ከሃያ ሰባት ቀን ኑሮ የካቲት14 በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #አባ_ያዕቆብ፦ ይህም አባት እልመቱዝ ለተባለ የግብጽ ንጉሥ በነገሠ በ17 ዓመት ተሾመ እርሱም ለመኰንኑ ለወልደ ኀሮን ረሽድ ወንድም የሆነ ነው፡ በዚህም አባት ዘመን የአስቄጥስ ገዳማት ታድሰው መነኰሳቱ ወደሳቸው ተመለሱ። ❤ አፎን በሚባል አገር ስሙ መቃርስ የሚባል ሰው ነበር ወደዚህ አባት ወደ ያዕቆብ መጥቶ ወደቤቱ በመሔድ ቤቱን ይባርክለት ዘንድ ለመነው እርሱም አብሮት ሔደ ታሞ የነበረ ልጁም ሞተ ወደ አባ ያዕቆብ አቅርቦ እንዲህ ብሎ ለመነው "ከርሱ በቀር ልጅ የለኝምና አባቴ ሆይ ራራልኝ እርሱም እነሆ ሞተ ስርሱ፡ ወደ እግዚአብሔር ትማልድ ዘንድ እለምንሃለው" አለው። አባ ያዕቆብም "እንደ እምነትህ ይሁንልህ አትፍራ" አለው። ሕፃኑንም ከአባቱ ተቀብሎ ታቀፈውና በላዩ ጸለየ በመስቀል ምልክትም አማተበበት ስለርሱም ወደ እግዚአብሔር ለመነ ጌታችንም ልመናውን ተቀበለው የሕፃኑ ነፍስ ተመልሳ ዐይኖቹን ገለጠ ከሞትም ድኖ ተነሣ አባቱንም "ልጅህን ውሰድ የሞተ አይደለም ያንቀላፋ ሁን ነው እንጂ" አለው። የሕፃኑም አባት ይህን ድንቅ ሥራ በአየ ጊዜ እጅግ ፈራ የገንዘቡንም እኩሌታ ለምጽዋት ብሎ ሰጠው እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ልኮ ሃይማኖታቸው ለቀና ምእመናን ሁሉ ወደርሷ በመጡ ጊዜ መጠጊያ ይሆን ዘንድ ቤተ ክርስቲያንን ሠራበት። ❤ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ዲዮናስዮስም ወደ ምስር በመጣ ጊዜ ከአባ ያዕቆብ ጋር ተቀምጦ ወደ አገሩ ተመለሰ። ይህ አባት ያዕቆብ በሹመቱ ዐሥር ዓመት ከስምት ወር፡ ከሦስት ቀን ኑሮ የካቲት14 በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ያዕቆብ በጸሎቱ ይማረን በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት 14 ስንክሳር።                              ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለያዕቆብ_ለእግዚአብሔር_ቅዱሱ። ዘአድባረ ገዳም ኵሉ በመዋዕሊሁ ተሐደሱ። እስከ አቡሁ ገነየ ለብዕለ ጸጋሁ ወዕበየ ሞገሱ። በግሠተ እዱ ወበጽላሎታ ለእርሱ። ውስተ በድነ ሕፃን ገብአት ዘወጽአት መንፈሱ። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_14።                                                           ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "አሕፃከ ስሑል ኃያል። አሕዛብ ይወድቁ ታሕቴከ። ውስተ ልቦሙ ለጸላዕተ ንጉሥ"። መዝ 44፥5። የሚነበቡት መልዕክታት ቲቶ 1፥7-12፣ 1ኛ ዮሐ 2፥20-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 20፥28-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 18፥15-23። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ቄርሎስ ቅዳሴ ነው። መልካም የአቡነ ሳዊሮስ የዕረፍት በዓልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።

❖ አንድ መጻተኛ ሰውም አረጋዊ አባ ገላስዮስን ሊጎበኝ በገባ ጊዜ ያንን መጽሐፍ አየውና አማረው በጭልታም ከዚያ ሰርቆት ወጣ ወደ ከተማ ውስጥም በገባ ጊዜ ሊሸጠው ወደደ አንድ ሰውም ዋጋው ምን ያህል ነው አለው እርሱም ዐሥራ ሰባት የወርቅ ዲናር ስጠኝ አለው። ❖ ያ የሚገዛውም ሰው ያልከውን እሰጥሃለሁ ነገር ግን ለወዳጄ እስካሳየው ታገሠኝ አለው ያሳየውም ዘንድ ሰጠው የሚገዛው ሰው ግን ወደ አባ ገላስዮስ ወሰደውና ተመልከትልኝ መልካም ከሆነ እገዛዋለሁ አለው አባ ገላስዮስም ያመጣውን ሰው ከአንተ ምን ያህል ፈለገ አለው ዐሥራ ሰባት የወርቅ ዲናር አለው ቅዱስ ገላስዮስም መጽሐፉ መልካም ነው ዋጋውም ቀላል ነው ግዛው ብሎ መለሰለት። ❖ ወደ ሌባውም በተመለሰ ጊዜ አባ ገላስዮስ የነገረውን ሠውሮ ለአባ ገላስዮስ አሳየሁት እርሱም ዋጋው በዝቷል አለኝ አለው ሌባውም ያ ሽማግሌ ሌላ የተናገረህ ነገር የለምን አለው አዎን የለም አለው። ❖ ሌባውም እንግዲህ እኔ አልሸጠውም ብሎ ወደ አባ ገላስዮስ ሒዶ ከእግሩ በታች ወድቆ ለመነው ሰይጣን አስቶኛልና ይቅር በለኝ መጽሐፍህንም ውሰድ አለው የከበረ ገላስዮስም እኔ መጽሐፉን መውሰድ አልሻም አለው። ❖ ሌባውም በፊቱ እያለቀሰና እየሰገደ ብዙ ለመነው በብዙ ድካምም መጽሐፉን ተቀበለው ማንም ያወቀ የለም፤ እግዚአብሔርም ትንቢት የመናገርን ሀብት ሰጥቶት ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ። ❖ በአንዲትም ዕለት ለገዳሙ መነኰሳት ዓሣ አመጡ ባለ ወጡ ዓሣውን አብስሎ በቤት ውስጥ አኑሮ አንዱን ብላቴና ጠባቂ አድርጎ ወደ ሥራው ሔደ ብላቴናውም ከዚያ ዓሣ በላ፤ ባለ ወጡ በመጣ ጊዜ ተበልቶ አገኘውና በብላቴናው ላይ ተቆጥቶ አረጋውያን አባቶች ሳይባርኩት እንዴት ደፍረህ በላህ አለው የቊጣ መንፈስም በልቡ አደረና ብላቴናውን ረገጠው ወዲያውኑ ሞተ እንደሞተም አይቶ ደነገጠ ታላቅ ፍርሀትንም ፈራ ሒዶ ለአባ ገላስዮስ የሆነውን ሁሉ ነገረው እርሱም ወስደህ ከቤተ መቅደሱ ፊት አስተኛው አለው ሰውየውም እንዳዘዘው አደረገ። ❖ ወደ ማታ ጊዜም አረጋውያን መነኰሳት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሰብስበው የማታውን ጸሎት አድርሰው ወጡ አረጋዊ አባ ገላስዮስም በወጣ ጊዜ የሞተው ብላቴና ተነሥቶ በኋላው ተከተለው ከመነኰሳትም ማንም አላወቀም እርሱም የገደለውን ባለ ወጥ ለማንም እንዳይናገር አዘዘው። ❖ የተመሰገነ አባ ገላስዮስም ያማረ ትሩፋቱንና ተጋድሎውን ፈጽሞ አድርሶ እግዚአብሔርንም አገልግሎ ይህንንም በጎ መታሰቢያ ትቶ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም የሚለይበት ሲደርስ በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።                   አርኬ ✍️ሰላም ለገላስዮስ ለሐውዘ ዓለም ዘገደፎ። ምንዳቤ ገዳም በተሳትፎ። መንፈሶ አኒኆ ወትዕግሥቶ አዝሊፎ። ለብእሲ ሰራቂ ኢተሀበለ ይዝልፎ። እንዘ በእዴሁ እኁዘ ይሬኢ መጽሐፎ። በዚችም ዕለት የዶርቃስ መታሰቢያዋ ነው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይገባል አሜን።   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥     አቡነ ሠርጸ ጴጥሮስ ❖ አቡነ ሠርፀ ጴጥሮስ የትውልድ ሀገራቸው ሸዋ ደብረ ጽላልሽ ሲሆን በሕፃንነታቸው ወደ ወሎ ሄደው ሐይቅ እስጢፋኖስ ገብተው ብዙ ተጋድለዋል፤ ከተጋድሎአቸውም በኋላ በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ እጅ መነኮሱ፤ በገዳሙ ብዙ ካገለገሉ በኋላ በመልአክ ትእዛዝ ወደ ጎጃም ሲሄዱ ዓባይን የተሻገሩት አጽፋቸውን አንጥፈው እርሱን እንደ ጀልባ ተጠቅመው ነው፤ ጻድቁ ታላቋን ተድባበ ማርያምን ለ41 ዓመት አጥነዋል፡፡ ❖ የንጉሡ ልጅ ሞቶ ሊቀብሩት ሲወስዱት የአቡነ ሠርጸ ጴጥሮስ ጥላቸው ቢያርፍበት ከሞት አፈፍ ብሎ ተነሥቶ ድኖ ‹‹አምላከ አቡነ ሠርጸ ጴጥሮስ›› ብሎ ፈጣሪውን አመስግኗል፤ ጻድቁ ሲያርፉም መቋሚያቸው አፍ አውጥታ ተናግራለች፤ ርዕደተ መቃብራቸው ሲፈጸምም እንባ አፍስሳ አልቅሳላቸዋልች፡፡ ❖ ይህች ተአምረኛ መቋሚያቸው ዛሬም ጎጃም ውስጥ መካነ መቃብራቸው ባለበት በደብረ ወርቅ ገዳም ትገኛለች፤ ጻድቁ ደብረ ወርቅ ገዳምን እንደ መሶብ አንሥተው አስባርከዋታል፤ አቡነ ሠርፀ ጴጥሮስ የካቲት 12 ቀን ያረፉ ሲሆን ዐፅማቸውም በታላቋ ደብረ ወርቅ ይገኛል፡፡ ❖ ከሰማይ የወረደላቸው የወርቅ መስቀላቸውም በዚያው ይገኛል፤ ጸበላቸው እጅግ ፈዋሽና ኃይለኛ ከመሆኑም በላይ በሰውነት ውስጥ የሚገኝ በሽታንና አጋንንትን የሚያስወጣበት መንገድ ለየት ያለው፡፡ የአቡነ ሠርጸ ጴጥሮስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ በጸሎታቸው ይማረን

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል    ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥ ❖ በዚች ዕለት የከበረ ሚካኤልን እግዚአብሔር ወደ ረዓይታዊ ወደ ሶምሶን ላከው የፍልስዔም ሰዎች ሊገድሉት በጠላትነት በተነሡበት ጊዜ ድል እስከ አደረጋቸውና እስከ ገደላቸው ድረስ ረዳው ኃይልንም ሰጥቶ በአህያ መንጋጋ ከእርሳቸው አንድ ሺህ ሰዎችን ገደለ፤ ተጠምቶም ለሞት በተቃረበ ጊዜ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ተገለጠለትና አጸናው እግዚአብሔር ከአህያ መንጋጋ አጥንት ውኃን አፈለቀለትና ጠጥቶ ዳነ። ❖ ዳግመኛም ከሚስቱ ጋር ተስማምተው ዐይኖቹን አሳወሩ የራሱንም ጠጉር ላጩ አሠሩትም ከዚህም በኋላ ለጣዖቶቻቸው በዓልን በአዘጋጁ ጊዜ ሶምሶንን ወደ ጣዖቶቻቸው ቤት ወሰዱት በዚያም ሦስት ሽህ ያህል ሰዎች ተሰብስበው ነበር የከበረ ሚካኤልም ተገለጠለትና ኃይልን መላው የዚያንም ቤት ምሰሶዎች ነቀላቸው ቤቱም በላያቸው ወድቆ ከእርሱ ጋር ሁሉንም ገደላቸው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበረ መልአክ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።                    አርኬ ✍️ሰላም እብል ሠናይተከ ተአዛዜ። ለትፍሥሕተ ሰብእ ወለኑዛዜ። ሚካኤል ኢይበል አድኅኖተከ ምእዜ። ረሲ ደኀሪትየ እምግብረ ኃጢኣት አግዓዜ። እንተ ተቀነይኩ የአክል እምይእዜ።   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥   ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥ ❖ በ1929 ዓ.ም የካቲት 12 ቀን ከሠላሳ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን አባቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶችና ሕፃናት በሮማዊው የፋሽስት ጦር ደማቸው ፈሷል፤ እነዚህ ወገኖቻችን ደማቸው እንደ ጐርፍ አዲስ አበባ ላይ የፈሰሰው ስለ ሃገር ፍቅር ብቻ አልነበረም፤ ስለ ቀናች ሃይማኖት ተዋሕዶ ጭምር ነው እንጂ፤ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ግጻዌ ላይ ስማቸውን ጽፋ በቅዱስ ዳዊት መዝሙር እንዲህ ታስባቸዋለች። ✍"አቤቱ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ፤ የቅድስናህንም መቅደስ አረከሱ፤ ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጉአት፤ የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች አደረጉ፤ የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት፤ ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውኃ አፈሰሱ፤ የሚቀብራቸውም አጡ" 📖መዝ. 78፥1-3 በረከታቸው ረድኤታቸው ፍቅራቸው ያሳድርብን፤ በጸሎታቸው ይማረን   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥     ሶምሶን ረዓይታዊ  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥ ❖ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን 22ቱን ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ አዳምን ገዢ አደረገው፤ አክሎም በነፍስ ሕያው አድርጐ በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ ነቢይና ካህን አድርጐ ካንዲት ዕፀ በለስ በቀር በፍጥረት ሁሉ ላይ አሰለጠነው:: ❖ አባታችን አዳም ግን ስሕተት አግኝቶት ከገነት ወጣ፤ መከራና ፍዳም አገኘው፤ በሁዋላም ለ100 ዓመት አልቅሶ ንስሃ ገባ፤ ጌታም ንስሃውን ተቀብሎ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ተስፋ ድህነትን ሰጠው:: ❖ ስለዚህም ምክንያት ለ5,500 ዓመታት ትንቢት ሲነገር ሱባኤ ወደ ታች ሲቆጠር ምሳሌም ሲመሰል ኖረ፤ ከደግ ፍጥረት አዳም እስከ ኖኅ ድረስ የሴት ልጆች እግዚአብሔርን በንጽሕና ሁነው በደብር ቅዱስ አመለኩ፤ ትንሽ ቆይተው ግን ስለተቀላቀሉ ከቃየን ልጆች ጋር በማየ ድምሳሴ ጠፉ:: ❖ በጻድቅ ሰው ኖኅ የተጀመረው ትውልድም እግዚአብሔርን ለመዘንጋት ጊዜ አልፈጀበትም፤ ነገር ግን ከሴም ዘር ቅንና ጻድቅ ሰው አብርሃም ተገኘ፤ ከእርሱም ይስሐቅ ከዚያም ያዕቆብ (ደጋጉ) ተገኙ፤ ያዕቆብም "እሥራኤል" ተብሎ በልጆቹ "ሕዝበ እግዚአብሔር" የተባለ ነገድ ተመሠረተ፤ በተስፋይቱ ምድር በከነዓን እንዳይኖሩም ርሃብ ምድረ ግብጽ አወረዳቸው:: ❖ በዚያም ለ215 ዓመታት በጭንቅ የባርነትን ሕይወትን አሳለፉ፤ እግዚአብሔርም ስለ ወዳጁ አብርሃም ሲል እሥራኤልን አሰባቸው፤ የዋሕና ጻድቅ ሰው ሙሴን አስነስቶ እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አዳናቸው፤ ይኸውም በጸናች እጅ በበረታችም ክንድ በ9 መቅሰፍት በ10ኛ ሞተ በኩር በ11ኛ ስጥመት ግብጻውያንን አጥፍቶ ነው፤ በየመንገዱም ጠላቶቻቸውን እየተበቀለላቸው ነው:: ❖ ከዚህ ዘመን ጀምሮም እሥራኤል በመሳፍንትና በካህናት የሚተዳደሩ ሆኑ፤ አስቀድሞ ሙሴ በምስፍና አሮን በክህነት መሯቸው፤ ቀጥሎም በቅዱስ ሙሴ ኢያሱ በአሮን አልዓዛር ተተኩ፤ እንዲህ እንዲህ እያለም ከኃያል ሰው ሶምሶን ረዓይታዊ ደረሱ:: ❖ ይኸውም ከዓለም ፍጥረት 4,200 ዓመታት በሁዋላ መሆኑ ነው፤ በጊዜው እሥራኤል ጣዖትን እያመለኩ እግዚአብሔርን ስላሳዘኑት ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር፤ የአካባቢው መንግስታት እነ አሞን አማሌቅ ኢሎፍሊ ስንኩዋ ያኔ ዛሬም ቢሆን እንደምትመለከቱት ዶሮና ጥሬ ናቸው፤ በጊዜውም የእሥራኤል ኃጢአት ስለ በዛ ኢሎፍላውያን (ፍልስጤማውያን) 40 ዓመት በባርነት ገዟቸው፤ ንስሃ ሲገቡ ደግሞ ልጅ በማጣት ያዘኑ ማኑሄ እና ሚስቱ (እንትኩይ) በቅዱስ ሚካኤል ተበሥረው ኃያሉን ሶምሶንን ወለዱላቸው:: ❖ እርሱም ናዝራዊ (ከእናቱ ማኅጸን ለጌታ የተለየ) ነበርና ፍልስጤማውያንን ቀጥቶ ወገኖቹን እስራኤልን ከባርነት በአምላኩ ኃይል ታደገ፤ ከኃይሉ ብዛት የተነሳም 📖መሣ 14፥5 👉300 ቀበሮዎችን አባሮ ይይዝ 📖መሣ 15፥3 📖መሣ 15፥14 👉በአህያ መንጋጋ ሽህ ሰው ይገድል 📖መሣ 15፥15 👉ጠባቂዎችን ከነ መቃናቸው ተሸክሞ ይወረውር ነበር:: 👉ውሃ ሲጠማውም ከአህያ መንጋጋ ላይ ፈልቆለት ጠጥቷል:: ❖ በፍጻሜው ግን ደሊላ በምትባል ሴት ተታልሎ ምሥጢሩን በመግለጡና ጸጉሩ በመላጨቱ ኃይሉን አጥቷል፤ ጠላቶቹም ዐይኑን አውጥተው መዘባበቻ አድርገውታል፤ በፍጻሜው ግን ኃይሉ እንዲመለስለት ፈጣሪውን ለምኖ አሕዛብ ለጣኦት በዓል እንደተሰበሰቡ የአዳራሹን ምሰሶ አፍርሶ አጥፍቷቸው ዐርፏል:: 📖መሣ 13፥16 ❖ ቅዱስ ሶምሶን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥላ (ምሳሌ) ነው፤ በዘመኑ ሁሉ ቅዱስ ሚካኤል ረድቶታልና በዚህች ቀን መታሠቢያው ይደረግለታል። ረድኤቱ በረከቱ ይደርብን፤ በጸሎቱ ይማረን    ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥     ቅዱስ አባ ገላስዮስ ገዳማዊ ❖ በዚችም ቀን ተጋዳይ የሆነ የከበረ አባት አባ ገላስዮስ አረፈ፤ የዚህ ቅዱስ ወላጆቹ አግዚአብሔርን የሚፈሩ ምእመናን ናቸው ጥበብንና የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተማሩትና ዲቁና ተሾመ። ❖ ከታናሽነቱም ጀምሮ ይህን ዓለም ንቆ ተወ የክብር ባለቤት የሆነ የክርስቶስንም ቀንበር በመሸከም በምንኵስና ሆኖ በትጋት እየጾመ እየጸለየና እየሰገደ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ እግዚአብሔርም መርጦት በአስቄጥስ ገዳም ባሉ መነኰሳት ላይ ቅስና ተሾመ። ❖ ተጋድሎውንና አገልግሎቱን እየፈጸመ ሳለ ለአባ ጳኵሚስ እንደ ተገለጠ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና መነኰሳትን ሰብስቦ ፈሪሀ እግዚአብሔርን የምንኵስናንም ሕግ ያስተምራቸው ዘንድ አዘዘው በዚያንም ጊዜ ብዙዎች መነኰሳትን ሰበሰበ መንፈሳዊ የሆነ የአንድነት ማኅበራዊ ኑሮንም ሠራላቸው እርሱ በመካከላቸው እንደ መምህር አልሆነም ከእርሳቸው እንደሚያንስ አገልጋይ እንጂ። ❖ ይህም አባት የዚህን ዓለም ጥሪት ሁሉ ንቆ የተወ ሆነ እጅግም የዋህና ቸር ሆነ ከብሉይና ከሐዲስ መጻሕፍቶችም የተሰበሰበ አንድ ታላቅ መጽሐፍን አጻፈ ለማጻፊያውም ዋጋ ዐሥራ ስምንት የወርቅ ዲናር አወጣ ከርሱ ሊጠቀሙ በሚፈልጉ ጊዜ መነኰሳቱ እንዲያነቡት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአትሮንስ ላይ አኖረው።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #የካቲት ፲፪ (12) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮያዊው_ጻድቅ አጽፋቸውን አንጥፈው ዓባይ ወንዝ ለተሻገሩት፣ የንጉሡ ልጅ ሞቶ ሊቀበር ሲሂድ ጥላቸው ሲያርፍበት ከሞት ላስነሱት ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ሠርጸ_ጴጥሮስ ለዕረፍታቸው በዓል፣ ለኢትዮጵያኑ ሰማዕታት (#በ1929ዓ.ም #የካቲት_12_ቀን_ከ30,000 በላይ ኢትዮጵያውያን አባቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶችና ሕፃናት በሮማዊው የፋሽስት ጦር ሰማዕትነት ለተቀበሉበት) በዓል በሰላም አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ሠርጸ_ጴጥሮስ፦ የትውልድ አገራቸው ሸዋ ደብረ ጽላልሽ ሲሆን በሕፃንነታቸው ወደ ወሎ ሄደው ሐይቅ እስጢፋኖስ ገብተው ብዙ ተጋድለዋል፡፡ከተጋድሎአቸውም በኋላ በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ እጅ መነኰሱ፡፡ በገዳሙ ብዙ ካገለገሉ በኋላ በመልአክ ትእዛዝ ወደ ጎጃም ሲሄዱ ዓባይን የተሻገሩት አጽፋቸውን አንጥፈው እርሱን እንደ ጀልባ ተጠቅመው ነው፡፡ ጻድቁ ታላቋን ተድባበ ማርያምን ለ41ዓመት አጥነዋል፡፡ ❤ የንጉሡ ልጅ ሞቶ ሊቀብሩት ሲወስዱት የአቡነ ሠርጸ፡ጴጥሮስ ጥላቸው ቢያርፍበት ከሞት አፈፍ ብሎ ተነሥቶ ድኖ "አምላከ አቡነ ሠርጸ ጴጥሮስ" ብሎ ፈጣሪውን አመስግኗል፡፡ ጻድቁ ሲያርፉም መቋሚያቸው አፍ አውጥታ ተናግራለች፤ ርዕደተ መቃብራቸው ሲፈጸምም እንባ አፍስሳ አልቅሳላቸዋልች፡፡ ይህቺ ተአምረኛ መቋሚያቸው ዛሬም ጎጃም ውስጥ መካነ መቃብራቸው ባለበት በደብረ ወርቅ ገዳም ትገኛለች፡፡ ጻድቁ ደብረ ወርቅ ገዳምን እንደ መሶብ አንሥተው አስባርከዋታል፡፡ አቡነ ሠርፀ ጴጥሮስ የካቲት12 ቀን ያረፉ ሲሆን ዐፅማቸውም በታላቋ ደብረ ወርቅ ይገኛል፡፡ ከሰማይ የወረደላቸው የወርቅ መስቀላቸውም በዚያው ይገኛል፡፡ጸበላቸው እጅግ ፈዋሽና ኃይለኛ ከመሆኑም በላይ በሰውነት ውስጥ የሚገኝ በሽታንና አጋንንትን የሚያስወጣበት መንገድ ለየት ያለው፡፡ ከአቡነ ሠርጸ ጴጥሮስ ረድኤት በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸውም ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።

                           ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "እስመ ዚአየ ውእቱ ኵሉ አራዊተ ዘገዳም። እንስሳ ገዳምኒ ወአልሕምት። ወአአምር ኵሎ አዕዋፈ ሰማይ"። መዝ 49፥10-11። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ጢሞ 4፥14-19፣ ያዕ 3፥5-11 እና የሐዋ ሥራ 14፥19-ፍ.ም የሚነበበው ወንጌል ማር 1፥12-16። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ባስልዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችን ይሁንልን።

ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta): ❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #የካቲት ፲፩ (11) ቀን። ❤ እንኳን #ለተጋዳይ_ለታላቁ አባት በቀንና በሌሊት ሰባት መቶ ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን ከስግደት ጋር እየጸለ ለአርባ ዓመት በገዳም ለኖረውና በኋላም ወደ በረሃ ከአንዲት ታናሽ ዋሻ ውስጥም ገብቶ እየተጋደለ ብቻውን ለኃምሳ ዓመት ለኖረ፤ ሁለት አንበሶች እንደሰው ለሚላኩለት #ለባለ_አንበሳው_ለአባ_አውሎግ ለዕረፍት በዓል፣ ለሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ለከበረ ለአባት #ለአባ_በላትያኖስ በንጉሥ ዳኬዎስ እጅ ለአንድ ዓመት ያህል ተሰቃይቶ ኋላም አንገቱን በመሰየፍ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓልና #ለአባ_ስልዋኖስ ረድእ #ለአባ_በትራ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከኤጲስቆጶስ #ከአባ_አብርሃም_ከመነኰስ_ከአባ_መቃቢስና #ከኮንቲ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ  ረድኤትና በረከት ያሳትፈን።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #ባለ_አንበሳው_አባ_አውሎግ፦ የዚህ ቅዱስ ወላጆች ፍጹም በወርቅና በብርም የበለጸጉ ናቸው። በአንዲትም ዕለት "አውሎግ ያለህን ገንዘብህን ሁሉ ሽጠህ ለድኆች ሰጥተህ መከራ መስቀሉን ተሸክመህ ና ተከተለኝ" የሚለውን የከበረ የወንጌልን ቃል አሰበና ወዲያውኑ ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች በትኖ ወደ አባ አውሎጊን ሔደ እርሱም በደስታ ተቀበለው። ስለ እርሱ እንዲህ የሚለውን ራእይ አይቶ ነበር "እነሆ ወዳንተ ጐልማሳ ይመጣል ተቀበለውና ከሚያገለግሉ መነኰሳት ጋር ቀላቅለው"። እየፈተነውም ሦስት ዓመት ያህል ኖረ ፍጹም የሆነ ቅድስናውንም በአየ ጊዜ የምንኵስናን ልብስ የመላእክትንም አስኬማ አለበሰው። ከሰንበትም እስከ ሰንበት እየጾመ በብዙ ተጋድሎ ኖረ ምግቡም እንጀራና ጨው ነበረ በቀንና በሌሊትም ሰባት መቶ ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን ስግደት ጋር ይጸልያል በዚህም ተጋድሎ አርባ ዓመት ኖረ። ❤ ከዚያም በኋላ ያሰናብተው ዘንድ መምህሩ አባ አውሎጊንን ማለደውና ወደ በረሀ ሔደ ከአንዲት ታናሽ ዋሻ ውስጥም ገብቶ እየተጋደለ ኃምሳ ዓመት ኖረ። ለፍላጎቱም የሚያገለግሉት ሁለት አንበሶችን እግዚአብሔር ሰጠው በአንዲትም ዕለት ታመመ አንሶቹንም "እጠጣ ዘንድ የሞቀ ውኃ እሻለሁ" አላቸው። አንዱ አንበሳም ወደ ተራራ ሒዶ እረኛ አግኝት ወደ አባ አውሎግ አመጣው በአየውም ጊዜ ሰገደለትና "አባቴ ሆይ ምን ትሻለህ" አለው እርሱም "የሞቀ ውኃ ታጠጣኝ ዘንድ እሻለሁ" አለው እንዳለውም አደረገለት ከዚህም በኋላ አንበሳው እረኛውን ወደ ቦታው መለሰው። ያም እረኛ "ለእግሩ ተረከዝ ዓለሙ ሁሉ መጠኑ የማይሆን ጻድቅ ሰው አገኘሁ" ብሎ ለሰው ሁሉ ተናገረ በሰሙ ጊዜም ሰዎች ሁሉ ወደርሱ ተሰበሰቡ፡ በሽተኞችንም ሁሉ አመጡለትና ፈወሳቸው። ❤ በዚያም ወራትም መምህሩ አባ አውሎጊን ጣዖትን የሚያመልኩ የፋርስ ሰዎችን ወደ ቀናች ሃይማኖት ለመመለስ ወደ ፋርስ አገር ሊሔድ ፈለገ ዳግመኛም ልጁ አውሎግን ከእርሱ ጋር ሊወስደው ወደርሱ መልክተኛ ሊልክ ሽቶ ሳለ መንፈስ ቅዱስ አንበሳውን አስገነዘበውና አጽፉንና ወንጌሉን አንሥቶ ተሸከመ። አባ አውሎግንም ጒዞን አመለከተው ተነሥቶም አንበሳውን ተከትሎ ወደ መምህር አውሎጊን ደረሰ እርሱም በደስታ ተቀበለው። ሲጓዝም ከጤግሮስ ወንዝ ደረሱ ውኃውም ተከፍሎላቸው ተሻገሩ ወደ አገሩም ውስጥ በደረሱ ጊዜ አስተማሩአቸው ወደ ቀናች ሃይማኖትም መለሷቸውና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው። ❤ በአንዲትም ዕለት ደግሞ ቅዱሳን በተራቡ ጊዜ ምግባቸውን ይፈልጉላቸው ዘንድ አባ አውሎግ አንበሶችን አዘዘ ሒደውም እንጀራ በአህያ ላይ ጭኖ የሚጓዝ ሽማግሌ አገኙ ሕፃንም ከእንጀራው ጋር አለ። አህያውንም ወደ ቅዱሳን አመጡት ከድንጋጤም የተነሳ ብላቴናው ሞተ ቅዱሳንም ጸልየው ሕፃኑ ድኖ ተነሣ ቅዱሳንም ተመገቡ አንቦሶችም አህያውን ከእንጀራውና ከሕፃኑ ጋር ወደ ሽማግሌው መለሱት። ❤ ከዚህም በኋላ አባ አውሎግ ወደ በዓቱ ተመለሰና ጥቂት ታሞ የካቲት11 በሰላም ዐረፈ። በታላቅ ክብርም ተቀበረ እነዚያ አንበሶችም መቃብሩን እየጠበቁ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኖሩ ከዚያም በኋላ ወደ ዱር ገቡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ አውሎግ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ትኑር አሜን።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_በላትያኖስ፦ ይህም ቅዱስ ብልህና አዋቂ የሆነ ታላቅ ተጋድሎን የሚጋደል ነው በሮሜ አገርም ሊቀ ጵጵስና ተሹሞ በቅዱስ ጴጥሮስ ወንበር ላይ ዐሥራ ሁለት ዓመት በሰላም ኖረ ሕዝቡን የቀናች ሃይማኖትን እያስተማራቸው ሳለ መኰንኑ ፊልጶስ በንጉሥ ቀላውዴዎስ ላይ ተነስቶ በገደለው ጊዜ በርሱ ፈንታ ነገሠ በምእመናን ላይ ታላቅ መከራን አመጣ በዚህ በንጉሥ በዳኬዎስ እጅ ብዙዎች በሰማዕትነት ሞቱ። በዘመኑም ሰባቱ ደቂቅ ከእርሱ ሸሹ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ዓመት ተኝተው ነቁ እርሱም በኤፌሶን ከተማ መስጊድ ሠርቶ በውስጡ ጣዖታትን አኖረ ሰዎችን ሁሉ ለጣዖታት እንዲሠዉ አስገደዳቸው ለጣዖታት ያልሠዉትንም ገደላቸው። ❤ ይህ የከበረ በላትያኖስም የጣዖታት አምልኮን እንደሚቃወም ሕዝቡም በክብር ባለቤት በክርስቶስ ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ እንደሚያስተምር ንጉሥ በሰማ ጊዜ ወደ ሮሜ አገር ልኮ ወደ ኤፊሶን ከተማ አስመጣውና ለጣዖታት እንዲሠዋ ለመነው። እርሱም ግን ቃሉን አልሰማም ተሣለቀበት አማልክቶቹንም ረገመ እንጂ ንጉሥም ተቆጣ አንዲት ዓመት ያህልም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው ማሠቃየቱንም በሰለቸ ጊዜ የካቲት11 ቀን በሰይፍ ራሱን ቆረጠው የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም  በአባ በላትያኖስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ትኑር አሜን።                             + + + ❤ የአባ ስልዋኖስ ረድእ አባ በትራ፦ ይህም ቅዱስ በደብረ ሲና ካለች በዓቱ በነበረ ጊዜ ትርኅምትን ይጠብቅ ነበር በራትም ጊዜ ለሥጋው የሚያሻውን ይመገባል። ፈርኑ በሚባል አገር ላይ ኤጲስቆጶስ በአደረጉት ጊዜ ትርኅምትን በማብዛት ሰውነቱን እጅግ አደከመ ደቀ መዛሙርቱ "አባታችን ሆይ በገዳም በበአትህ በነበርክ ጊዜ ትርኅምትን እንዲህ አላበዛህም ነበር" አሉት ይህም አባት እንዲህ አላቸው "ያን ጊዜ በገዳም በችግር ውስጥ ነበርኩ ዛሬ ግን ከብዙዎች መካከል በአንድነት አለሁ የምሻውም ሁሉ ብዙ አለኝ ነገር ግን ሥጋዬን ቀጥቼ ብገዛው ይሻላል" እንዲህም እየተጋደለ ኖረ ከዚህም በኋላ የካቲት10 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ በትራ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት 11 ስንክሳር።                            ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለበትራ_ረድአ_ስልዋኖስ_ወምእኑ። ኤጲስቆጶሰ ዘኮነ በሀገረ ፈርኑ። ከመ እንግር ጽድቆ ወኂሩቶ እዜኑ። ለአፉየ ወልሳንየ በመጠኑ። ዘይረድአኒ መንፈሰ ይፈኑ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የካቲት_11።

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ - Статистика та аналітика Telegram каналу @finote_media