ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ
Відкрити в Telegram
ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።
Показати більше609
Підписники
-124 години
-37 днів
-1130 днів
Архів дописів
⓷ ልደትና ጥምቀት ረቡዕና ዐርብ ሲውሉ እህል በነግህ (በጧት) መቀመስ ስላለበት የእርሱ ቅያሪ (ተውላጥ) እንዲሆን ነው::
❖ ጾመ ገሃድን የሠሩት አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ሲሆኑ ያጸኑት ደግሞ ቅዱሳን ሊቃውንት ናቸው፤ አጿጿሙም ጥምቀት ከማክሰኞ እስከ ቅዳሜ ከዋለ በዋዜማው "እስከ ይሠርቅ ኮከብ" እንዲሉ አበው እስከ ምሽት 1 ሰዓት ድረስ ይጾማል::
❖ በዓለ ጥምቀት እሑድ ሲሆን ዐርብን አዘክሮ በዕለተ ቅዳሜ ደግሞ ከጥሉላት ተከልክሎ መዋል ይገባል፤ በመሳሳይ ሰኞ ቢውል ዐርብን አዘክሮ ቅዳሜና እሑድን ከጥሉላት (ከሚያገድፉ ምግቦች) ሁሉ ተከልክሎ መዋል ይገባል::
❖ ከ7ቱ አጽዋማት አንዱ ነውና የተለየ ግለሰባዊ ችግር እስከሌለ ድረስ ሊጾም ግድ ይላል፤ ችግር ካለ ደግሞ ከንስሃ አባት ጋር ሊመክሩ ይገባል::
አርኬ
✍️ሰላም እብል ለጾም ዕለት ዋሕድ። ዘስሙ ገሀድ። መምህራነ ሥርዓት አቀሙ ለዘይመጽእ ትውልድ። እመባልዕት ጥሉላት ወእምነ ቅሡም ማዕድ። አንስት ይትሀረማ ወይጹሙ ዕድ።
አባ ታውብንስጦስ ዘሲሐት
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ በዚችም እለት አባ ታውብንጦስ አረፈ ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ አባቱአና በሚባል በሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ቤት አደገ እርሱም የምንኩስናን ልብስ አለበሰው።
❖ መንፈሳዊ እውቀትንና ኃይል እንደተሰጠው አይቶ ከእስክንድርያ አገር ውጪ ስሙ ጤናዲራን በሚባል ቦታ ኤጲስቆጶስነት ሹሞ የገዳም አበመኔት አደረገው በእርሱ ስር ያሉ መነኵሳትም ሰባት መቶ ናቸው።
❖ ከዚህም በኋላ ከእርሱ ጋር ላሉ መነኰሳት አለቃ የሆነ ኤጲስቆጶስ ታውብንጦስ ከከሀዲ ንጉስ ዲዮቅልጥያኖስ ስለሆነው ሁከት በሰማ ጊዜ ሸሽቶ ወደ ደብረ ሲሐት ገዳም ሒዶ እግዚአብሔርን ከምትፈራ ከአንዲት ድንግል ዘንድ ተቀመጠ፤ በእርሷ ቤትም ብዙ ዘመናት ኖረ በመጀመሪያ ወደርሷ በገባ ጊዜ ግን ንጉሱን ስለመፍራት ጣዖትን ስታመልክ አገኛትና የክብር ባለቤት ጌታችን ክርስቶስን ወደ ማመን መለሳት።
❖ ከዚያም ተርኑጥና መርኑስ ወደሚባሉ ገዳማት ሔደ የአብያተ ክርስቲያናትን ወሬ ይሰማ ዘንድ ፈልጎ በፆመወ በጸሎት ሌሊትም በመትጋት እያገለገለ በአንዲት ገዳም ውስጥ ሁለት ሶስት ቀን ተሰውሮ ያድር ነበር።
❖ የመንፈስ ቅዱስም ፀጋ በላዩ እንዳደረ እግዚአብሔርም በእጆቹ ድንቆች ተአምራቶችን እንዳደረገ ከወንበዴዎችና ከዓመፀኞች ብዙዎችን መነኰሳትን አድርጎ ለክርስቶስ ወደ መገዛት እስከ መለሳቸው ድረስ መነኰሳቱ ሁሉም መሰከሩለት።
❖ ከዚህም በኋላ ፈጽሞ በአረጀ ጊዜ የሚሞትበትን ቀን አወቀ ልጆቹንም የክርስቶስ በሆነች በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ ትእዛዙንም እንዲጠብቁ አስተማራቸው ወዲያውኑ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✍️ሰላም ለታውብንጦስ ኀበ ደብረ ሲሐት ዘሖረ። ከመ ለጣዖት ኢይስግድ ዘበእደ ሰብእ ተገብረ። ውስተ ቤተ ድንግል አሐቲ ከመ ፈላሲ ኀደረ። እስከ ሜጠ ዐማፄ ወፈያተ መሀረ። በኃይለ አምላኩ ዘገብረ መንክረ።
በዚችም ዕለት የሰማዕት ለጠምያኒ የኪናርያና የንግሥት በጥሪቃ መታሰቢያቸው ነው። በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን።
አምላከ ቅዱሳን ፍቅሩን ምሥጢሩን ይግለጥልን፤ ከጾመ ገሃድ በረከትም አይለየን::
አርኬ
✍️ ሰላም ለክሙ ጽዕድዋን አርጋብ። እምነ ቢረሌ ወሐሊብ። ካህናት ኄራን ፍቁራኒሁ ለአብ። እስእለክሙ በማየ ዮርዳኖስ ምኀፃብ። ከመ ታንጽሑኒ ለብእሲ ስዑብ
ጾመ ገሃድ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ በዚች ዕለት ምእመናን እስከ ምሽት እንዲጾሙት ያዘዙበት ምክንያቱ ይህ ነው፤ የልደትና የጥምቀት በዓል በረብዕ ወይም በዓርብ ቀን ቢሆን በበዓለ ኃምሳ የሚበላውን የጥሉላት መብል በጥዋት በመብላት ምእመናን ሁሉ በአሉን እንዲአከብሩ የከበሩ አባቶቻችን ሐዋርያት አዝዘዋል እሊህ ሁለቱ የእግዚአብሔር ታላላቅ በዓሎቹ ናቸውና።
❖ እኛ በዚህ በኃላፊው አለም ተድላ ደስታ ደስ የሚለን ለሌሎች እንዳይመስላቸው እንደ አይሁድና እንደ አረማውያን በዓል በመብልና በመጠጥ ብቻ እንዳናደርግ ስለዚህ ከልደትና ከጥምቀት በአል በዋዜማ ያሉትን ሁለቱን እለታት እንድንፆም አዘዙን የልደትና የጥምቀት በዓል በረቡዕና በዓርብ ላይ በሚሆን ጊዜ በረቡዕና በዓርብ ፈንታ እንድንጾማቸው ይገባልና በዚህም ሁለት ሥራ ይፈጸምልናል የጾም ሥራና የበዓል ማክበር ሥራ ነው፤ እንዲሁም በግብጻውያን አብያተ ክርስቲያን የተሠራ ነው።
❖ በይረሙን በእሑድ ወይም በአይሁድ ሰንበት ቀን ቢሆን ይህም ጌታ የተገለጸበት ጥር ዐሥር ቀን ነው በዋዜማው ዐርብ እስከ ምሽቱ ይጹሙ አስቀድመን እንደተናገርን ጥሉላት አይብሉ የልደትና የጥምቀት በዓልም ሰኞ ቀን ቢሆን በሰንበት ቀን ይጾሙ ዘንድ አይቻልም ነገር ግን ጥሉላትን ከመብላት ይጠበቁ።
❖ በጥምቀትም እለት ከእኩለ ሌሊት በፊት ተነስተው በውኃው ላይ ይጸልዩና ይጠመቁ ሕፃናትም በሚጠመቁ ጊዜ በውኃ እንዳይገድፉ ካህናቱም ከመንጋቱ በፊት ቀድሰው ቁርባኑን ያሳርጉ እጅግም ማልደው በጥዋት ከቤተ ክርስቲያን ይውጡ በከበረ ሥርዓታቸው ጌቶቻችን ሐዋርያት እንዳዘዙ።
❖ የመለካውያን ወገኖች ግን የልደትና የጥምቀት ዋዜማ በቅዳሜ ቀን ወይም በእሁድ ቀን ቢሆን በሶስት ሰአት ይቀድሳሉ ከወደዱም የተባረከ ኅብስት ተመግበው ውኃ ይጠጣሉ ከዚህም በኋላ ካህናቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁነው በየሰአቱ በመጸለይ ለበዓሉ የሚገባውን የነቢያትን ትንቢቶች ያነባሉ በዚያም ቀን በምሽት ይኸውም ጥር ዓሥር ነው።
❖ በውኃው ላይ ይጸጸልያሉ ይህም አባቶቻችን ሐዋርያት እብዳዘዙት፤ እርሳቸው ርሳቸው የኤጲፋንያን በዓል እንዲአከብሩ አዘዋል ይኸውም መድኀኃኒታችን የተገለጠበት ካኑን በሚባል በሮም ሁለተኛ ወር በሰባት ይህም ጥር ዓሥዐሥራ አንድ ቀን ነው።
❖ መለካውያን ግን የከበሩ አባቶች የቤተ ክርስቲያን መምህራን ያዘዙትን ይተላለፋሉ በልደትና በጥምቀት በዓል ዓርብም ረቡዕም ቢሆን አስቀድመው በርሱ ፈንታ ሳይጾጾሙ በጥዋት ተነሥሥተው ይበላሉና።
❖ እኛንም ከበደላችን ያነጻን ዘንድ በዮረዳኖስም ወንዝ እንደ ገለጸ የጌትነቱን ክብር በልቡናችን ይገልጥልን ዘንድ የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው ጌትነት ክብር ስግደት ለእርሱ ይገባልና።ከቸር አባቱ ጋር ይቅር ባይ ከሆነ መንፈስ ቅዱስም ጋር ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን።
📌 በተጨማሪ
❖ ቅድስት ቤተክርስቲያን በአዋጅ ምዕመናን እንዲጾሟቸው የሠራቻቸው 7 አጽዋማት አሏት::
❓ጾም ማለት
❖ መከልከል ነው፤ የምንከለከለው ደግሞ ከኃጢአትና ከክፋት ሲሆን አንድም ሰውነትን ወደዚያ ከሚወስዱ መባልዕት መከልከልን ይመለከታል::
📌 7ቱ አጽዋማት
1. ዓቢይ ጾም
2. ጾመ ፍልሠታ
3. ጾመ ሐዋርያት
4. ጾመ ነቢያት
5. ጾመ ድኅነት
6. ጾመ ነነዌ እና
7. ጾመ ገሃድ ይሰኛሉ::
❖ በእነዚህ አጽዋማት ከዓቢይ ጾም በቀር እስከ 9 ሰዓት ድረስ መጾም ይገባል፤ ዓቢይ ጾም ግን የተለየ ሥርዓት አለውና ይቆየን፤ ስለ ጾም ሲነሳ አስቀድሞ የሚመጣው ጥያቄ አስፈላጊነቱ ነው::
❓ሃይማኖት ለምን ያስፈልጋል ብሎ መጠየቁ ይቀላል፤ ምክንያቱም ከሃይማኖታዊ ትዕዛዛት ትልቁ በመሆኑ እርሱን መቃወም ሃይማኖትንና ትዕዛዙን እግዚአብሔርን መቃወም ነውና::
❖ እኛ ሃገር ላይ የተለመደች ክፉ ልማድ አለች፤ የከበደችንን ነገር "አያስፈልግም" በሚል እንከራከራለን፤ ደግሞ ጾምን ለመሻር ጥቅስ የሚጠቅሱ ወገኖች በጣም ይገርሙኛል::
❖ ኃጢአትን ለመሥራት ጾምንም ለመሻር ጥቅስን መጥቀስ አያስፈልግም፤ እኛ ግን ከፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ
📖ማቴ 4፥2
❖ አበው ቅዱሳን ጾመው
📖ዘዳ 9፥19
📖ነገ 19፥8
📖ሐዋ 13፥3
📖ቆሮ 4፥11 አሳይተውናልና እንደ አቅማችን እንጾማለን::
❓ገሃድ ማለት
❖ ገሃድ የሚለው ቃል በቁሙ "መገለጥን መታየትን ይፋ መሆንን" የሚያመለክት ሲሆን በምሥጢሩ ግን "የማይታይ አምላክ መታየቱን የማይዳሰሰው መዳሰሱን" ያመለክታል፤ ወይም በሌላ ልሳን ወልደ እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም በተዋሕዶ ሰው ከሆነ በሁዋላ ለ30 ዓመታት ራሱን ሳይገልጥ ቆይቶ ነበርና በ30 ዓመቱ ራሱን ለእሥራኤል በዚህ ሰሞን መግለጡን ልብ የምንልበት በዓል ነው::
❖ መድኃኒታችን ሁሉን ነገር የሚሠራው በጊዜው ነውና ከሥጋዌው በሁዋላ ለ30 ዓመታት ከስደት መልስ ደግሞ ለ25 ዓመታት የሰውነቱን ምሥጢር በይፋ ሳይገልጥ ቆይቷል፤ ያም ሆኖ የሰውነቱን ምሥጢር እርሱ የባሕርይ አባቱና ቅዱስ መንፈሱ ለድንግል ማርያም ገልጠውላት ታውቀው ነበር፤ እርሷ ግን መዝገበ ምሥጢር ናትና ሁሉን ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር::
📖ሉቃ 2፥52
❖ መድኃኒታችን ከሥጋዌው (ሰው ከሆነባት) ደቂቃ ጀምሮ መግቦቱን አላቁዋረጠም፤ ምንም በግዕዘ ሕጻናት ቢኖርም እርሱ በዘባነ ኪሩብ የሚሠለስ ቸር ጌታ ነውና መግቦናል፤ እንደ እሥራኤል ባህል 30 ዓመት በሞላው ጊዜ ግን ሥግው አምላክ መሆኑን ገለጠ፤ የተገለጠውም በጥምቀቱ ሲሆን በዕለቱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ልጅነቱን አስመስክሯል፤ በባሪያው በዮሐንስ እጅም ተጠምቆ ሥርዓተ ጥምቀትን ሠርቶልናል::
❖ የእዳ ደብዳቤአችን ቀዶ ልጅነታችንን መልሶልናል፤ ይህ ሁሉ የተደረገ ለእኛ ነውና በዓለ ኤዺፋንያን (እለተ አስተርእዮቱን) በድምቀት እናከብራለን፤ ነገር ግን ልክ በቅርብ ጊዜ እያየነው እንደሚገኘው በዘፈንና ከአምልኮ ባፈነገጠ መንገድ እንዳይሆን ቤተክርስቲያን አበክራ ታሳስባለች::
❖ የመድኃኒታችንን የማዳን ሥራ ከማዘከርና ለእርሱ ከመገዛት ይልቅ ራስን ዘፈን በሚመስል መዝሙር መቃኘቱና ለልብስ ፋሽን መጨነቁ የሚጠቅም አይደለም፤ በዓላት በሚዲያ ታዩ ተመዘገቡ ብለን ከመዝናናት ትውፊታችንን እያጠፉ ያሉ ድርጊቶቻችን ብንታዘባቸውና ብናርማቸው ይመረጣል፤ ስኬታችን ሁሉም ክርስቲያን ለእግዚአብሔር መንግስት መብቃቱ እንጂ በዓል አከባበራችን ዝነኛ መሆኑ አይደለም::
❖ ጉዳዩ መለኮታዊ እንጂ ፓለቲካዊ አይደለምና ጥንቃቄን ይሻል፤ ዛሬ ለታቦተ እግዚአብሔር ክብርን የማይሰጥና ተጋፊ ትውልድን እየፈጠርን ነው፤ ካህናትን አለመስማትና ታቦታትን አግቶ አላስገባም ማለት በክርስትና ትርጉሙ ከሰይጣን መወዳጀት ነው፤ ስለዚህም በዓል አከከባበራችንን እንታዘብ ደግሞም እናርመው::
📌 ጾመ ገሃድ
⓵ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጥሙና እያሰብን በጾም እንድናመልከው።
⓶ በዓል አከባበራችን እንደ አሕዛብ በተድላ ሥጋ በመብልና በመጠጥ ብቻ እንዳይሆንና ሰውነታችንን በጾም እንድንገራው::
✝ ✝ ✝
❤ #ሶርያዊው_ሰማዕቱ_ቅዱስ_ጳውሎስ፦ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ የሶርያ ሰዎችና በእስክንድርያ ከተማ የሚኖሩ ነጋዴዎች ናቸው ከዚህም በኋላ በእስሙናይን ከተማ የሚኖሩ ሆኑ። ወላጆቹም ሲሞቱ ብዙ ገንዘብ ተውለት ከዚህም በኋላ ከሀድያን ነገሥታትና መኳንንት በክርስቶስ የሚያምኑ ምእመናንን እንደሚያሠቃዩአቸውና እንደሚገድሏቸው ሰማ በዚያንም ጊዜ ተነሥቶ ገንዘቡን ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች በተነ። ከዚያም በኋላ የወደደውን መንገድ ይመራው ዘንድ ወደ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየ ጌታችንም
መልአኩን ሱርያን ላከ እርሱም በክብር ባለቤት ክርስቶስ ስም የሚደርስበትን ሥቃይ ሁሉ ነገረው "እነሆ ከአንተ ጋር እንድኖር እንዳጸናህም እግዚአብሔር አዞኛልና አትፍራ" አለው።
❤ በዚያንም ጊዜ ተነሥቶ ወደ እንዴናው ከተማ ሔደ በመኰንኑም ፊት ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኰንኑም ልብሱን አራቁተው ይገርፋት ዘንድ አዘዘ። ይህንንም አደረጉበት ከዚህም በኋላ በጐኖቹ ውስጥ መብራቶችን አስገብተው ለበለቡት እሳት ግን አልነካችውም መኰንኑም ለጣዖት እንዲሰግድ ብዙ ገንዘብ አመጣት የተመሰገነ ጳውሎስም "ወላጆቼ ሲሞቱ ዐሥራ ሰባት የወርቅ መክሊት ትተውልኝ ነበር። ስለ ክብር ባለቤት ክርስቶስ ፍቅር ትቼ ለድኆች መጸወትኩት ወደዚህ ወደተናቀ ገንዘብህ እንዴት እመለሳለሁ" አለው።
❤ መኰንኑም ሰምቶ ብረቶችን በእሳት አግለው በአፉና በጆሮዎቹ እንዲጨምሩ አዘዘ ይህንንም አደረጉበት ሱርያል መልአክም ወርዶ ዳሠሠውና አዳነው ሁለተኛም እባቦችን በላዩ ሰደዱ አልነኩም ምላሱንም ቆረጡ ጌታችንም አዳነው። መኰንኑም ወደ እስክንድርያ ከተማ በሚሔድ ጊዜ ከእርሱ ጋር ወሰደው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመርከብ ውስጥ ተገለጠለትና አጽናናው የዚህም ቅዱስ ኤሲም የሚባል ወዳጅ አለው እኅቱ ቴክላም። በጌታችንም ሥጋው ከሥጋቸው ነፍሱ ከነፍሱሳቸው ጋር እንደሚሆን ነገረው ያን ጊዜ እሊህ ቅዱሳን በእስክንድርያ ከተማ በእስር ቤት ነበሩ የከበረ ጳውሎስም ወደርሳቸው በደረሰ ጊዜ እርስበርሳቸው ተሳሳሙ በመገናኘታቸውም ነፍሳቸው ደስ ብሏት እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
❤ መኰንኑም ወደ እንዴናው ከተማ በሚመለስ ጊዜ የቅዱስ ጳውሎስን ራስ ቆርጠው ሥጋውን ከጥልቅ ባሕር ወረወሩ የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ ምእመናንም ሥጋውን በሥውር ወስደው በአማሩ ልብሶች ገነዙት በእርሱም ዘንድ አኖሩት ከእርሱም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ በቅዱስ ጳውሎስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት 9 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለጳውሎስ_ቅሡፈ_ዘባን_በተጠብጥቦ። ወበመኃትወ ነድ ውዑየ ገቦ። #ሱርያል_መልአክ እንዘ ይሜግቦ። በድሮ ፈጺሞ ወሃይማኖቶ ዐቂቦ። ዘምስለ ኤሲ ወቴክላ ተወፈየ ዐስቦ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_ 9።
ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta):
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #የካቲት ፱ (9) ቀን።
❤ እንኳን #ለከበረ_በሶርያ_አገር ላሉ መነኰሳት አባት ለሆነ እንደ ኢያሱ ፀሓይን ገዝቶ ላቆመ፣ ዝናብንም በጸሎቱ ላዘነበ፤ ሳይቀመጥ ሃምሣ አራት ዓመት ቁሞ ለኖረ #ለታላቁ_አባት_ለአባ_በርሱማ ለዕረፍት በዓልና ለከበረ ለሶሪያዊ ከሃድያን ይዘው ምላሱን በመቁረጥ፣ በእሳት በማቃጠል፣ የብረት ችንካሮችን በእሳት አግለው በአፉና በጆሮዎቹ ለቸነከሩበትና በመጨረሻውም አንገቱን ለሰየፉት #ለቅዱስ_ጳውሎስ ለዕረፍቱ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ #ከከበረ_ሰማዕት_ከቅዱስ_ጴጥሮስ ከመታሰቢያው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_በርሱማ_ዘሶርያ፦ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ሳሚሳጥ ከሚባል አገር ሰዎች ውስጥ ናቸው አንድ በዋሻ ውስጥ የሚኖር ሰው በእርሱ ላይ ትንቢትን ተናገረ ከመወለዱ አስቀድሞ ለአባቱ እንዲህ አለው "የትሩፋቱ ዜና በሶርያ አገር ሁሉ የሚሰማ ጣዕም ያለው ፍሬ ከአንተ ይወጣል ከእርሱ የሚሆነውንም አሰረዳው"። ተወልዶም አድጎ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ በደረሰ ጊዜ ወላጆቹን ሸሽቶ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ደርሶ በዚያ ስሙ አብርሃም ከሚባል ሰው ዘንድ ተቀመጠ እርሱም ወላጆቹን ስለፈራ ኪዚያ ገዳም ሰደደውና ሒዶ በአለት ውስጥ ኖረ በዚያም ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ ወሬውም በሶርያ አገሮች ሁሉ በተሰማ ጊዜ ብዙዎች ደቀ መዛሙርት ወደርሱ ተሰበሰቡ የዚያ ቦታ ውኃ ግን እጅግ መራራ ነበር በላዩ በጸለየ ጊዜ ተለውጦ ጣፋጭ ሆነ። እግዚአብሔርም በእጆቹ ድንቅች ተአምራቶችን አደረገ ከእርሳቸውም በአንዲት ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ከበአቱ ርቆ ሳለ የፀሓይ መግቢያ ሰዓት ተቃረበ የክብር ባለቤት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነው ወደ በአቱም እስቲደርስ ያን ጊዜ ፀሓይን አቆመለት።
❤ በሌላም ጊዜም እንዲህ ሆነ ረዓም የምትባል አገር ነበረች ሰዎቿም ከሀዲዎች ናቸው በላያቸውም ዝናብ ተከለከለ በተጨነቁም ጊዜ ወደ ከበረ አባ በርሱማ መጥተው ለመኑት እርሱም ገሠጻቸው እንዲህም አላቸው "ከክህደታቸሁ ተመልሳችሁ በእግዚአብሔር ብታምኑ እርሱ ብዙ ዝናብን ያወንብላችኋል" እነርሱም "እናምንበታለን አሉት"። በዚያን ጊዜ ጌታችንን ለመነውና ብዙ ዝናብ ዘነበላቸው የአገሩ ሰዎችም ሁሉ በጌታችን አመኑ። እዲሁም ሰዎቿ ከሀድያን የሆኑ ሌላ አገር ነበረች እነርሱንም ገሥጾ መክሮ አስተምሮ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መለሳቸው የጣዖቶቻቸውንም ቤቶች አፈረሰ።
❤ ይህም ቅዱስ ለራሱ ቦታ አዘጋጅቶ በዚያ ሳይቀመጥ ሃምሣ አራት ዓመት ቁሞ ኖረ ከመትጋት የተነሣ ሲደክመው ከናሱ ግድግዳ ላይ ተደግፎ ያሸልባል በየሰባት ቀንም ይጾማል። የከበረ አባ ስምዖን ዘዓምድ ሊያየው ወዶ ወደርሱ ላከ የትሩፋቱንና የቅድስናውን ዜና ከብዙዎች ሰዎች ሰምቶ ነበርና እርሱም ወደ አባ ስምዖን መጥቶ እርስበርሳቸው በረከትን ተቀባበሉ ከዚያም በኋላ ወደ ገዳሙ ተመለሰ። በሶርያም አገርም አስተማረ በፊታቸው ተአምራትን በአደረገ ጊዜ በትምህርቱ ብዙዎች አመኑ። ዳግመኛም ወደ ታናሹ ቴዎዶስዮስ ንጉሥ ሒዶ በቀናች ሃይማኖት አጸናው ንጉሡም ብዙ ገንዘብን ሰጠው እርሱ ምንም ምን አልወሰደም በአንጾኪያም አገር በኤጲስቆጶሳቱ ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዲኖረው ንጉሥ ጻፈለትና ኀቲም ቀለበትን ሰጠው።
❤ በከሀዲው ንስጥሮስ ምክንያት ሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት በኤፊሶን ከተማ በተሰበሰቡ ጊዜ ከእሳቸው ጋር ይህ ቅዱስ አለ። ከእርሳቸውም ጋር ንስጡርን አወገዘው ዳግመኛም በአንጾኪያ አገር ያሉ መኳንንት መሳፍንትን ሹማምንት ሁሉም ይታዘዙለት ዘንድ ንጉሥ ደብዳቤን ጻፈለት እርሱም በጎ ሥራ እንዲሠሩ በሃይማኖት እንዲጸኑ የሚያዝዝ ደብዳቤ በመጻፍ በንጉሥ ኀቲም ቀለበት እያተመ ለአገሮች ሁሉ የሚልክ ሆነ። ክፋዎች ሰዎችም ጠሉት በንጉሥም ዘንድ ነገር ሠሩበት እንዲህም አሉት" እሆ አባ በርሱማ እንደ ዓለም ሰው ሁኖ ይበላል ይጠጣል መልካም ልብስንም ይለብሳል" ንጉሥም ስለ አባ በርሱማ የተነገረውን ያረጋግጥ ዘንድ ከባለሟሎቹ አንዱን ላከ። የንጉሡም ባለሟል ወደ አባ በርሱማ በደረሰ ጊዜ በእርሱ ላይ ከተነገረው ምንም ምን ያገኘው የለም ከዚህም በኋላ ወደ ንጉሥ ወሰደው ንጉሥም ቀድሞ ከሚያውቀው ከመንፈሳዊ ሥራው ልውጥ ሁኖ ያገኘው ነገር የለም ንጉሡም ታላቅ ክብርን አከበረው ወደ ቦታውም መለሰው።
❤ መናፍቁ ንጉሥ መርቅያንም የኬልቄዶንን ጉባኤ በሰበሰበ ጊዜ የንጉሥ አማካሪዎች አባ በርሱማን እንዳያስመጣ ንጉሡን መከሩት እንደማይፈራና እንደ ማያፍር በሰው ፊትም እንደማያዳላ ተከራክሮ ረትቶ እንደሚሳፍራቸውም ስለሚያውቁ ነው። አንዱ ክርስቶስ ወደ ሁለት የከፋፈሉበት ይህ ጉባኤ በተፈጸመ ጊዜ የከበረ አባ በርሱማ ተጣላቸው ነቀፋቸው ቃላቸውንም በመሻር አወገዛቸው እርሱም ወደ ንጉሥ ወንጅለው በጽሑፍ ከሰሱት ንጉሡም ልኮ ወደርሱ አስቀረበው ግን በላዩ ስለ አደረ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ ሊቃወመው አልቻለም በሊቁ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ላይ ስለ አደረገው ክፋት ንግሥቲቱን ረገማት ከጥቃት ቀንም በቀር አልኖረችም በክፉ አሟሟትም ሞተች። ከዚህም በኋላ መናፍቃን የሚቃወሙት ሆነ ምእመናን እንዳይታዘዙለት ወደ ሀገሮች ሁሉ ጽፈው የሚልኩ ሆኑ እነርሱ ግን አልተቀበሏቸውም እርሱ መታዘዛቸውንም አልተዉም። ዳግመኛም በጐዳና ሸምቀው ይገድሉት ዘንድ ሁለት መቶ መናፍቃን ሰዎች ከመናፍቃን ኤጲስቆጶሳት ጋር ተስማምተው ወደ እርሳቸው እንዲመጣና በአንድነት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደ ሚሔዱ ሁነው ላኩበት መጥቶም አብሮ በተጓዘ ጊዜ ደንጊያዎችን አንሥተው ጣሉበት ደንጊያዎታቸውም ወደ ራሳቸው የሚመለሱ ሆኑ በፍርሃትም ከእርሱ ሸሹ።
❤ እግዚአብሔርም ከዚህ ዓለም እሥረኛነት ሊአወጣው በወደደ ጊዜ መልአኩን ወደርሱ ልኮ ከአራት ቀን በኋላ ከዓለም እንሚፈልስ ነገረው በዚያንም ጊዜ በዙሪያው ወዳሉ አገሮች ምእመናንን ያጽናናቸው ዘንድ ረድኡን ላከው እርሱም ሲዞር የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራስ ወደምትኖርበት ቦታ ደረሰና የከበረች የቅዱስ ዮሐንስን ራስ እጅ ነሣት ስለ ከሀዲው ስለ ንጉሥ መርቅያን በማልቀስ ለመነ። እንዲህ የሚልም ቃል ከመጥምቁ ዮሐንስ ራስ ወጣ " አባ በርሱማ ወደ እግዚአብሔር ስለ ከሰሰው ያ መርቅያን ሙቷልና አትፍራ"። የከበረ አባ በርሱማ ረድኡን ባረከው የካቲት9 በሰላ አረፈ። ከበአቱም ደጃፍ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ ታየ። ምእመናንም ሁሉ ከሩቅ አይተው ወደርሱ መጡ አርፎም አገኙት። ከሥጋውም ተባረኩ በላዩም አለቀሱ ከእርሱም ስለመለየታቸው እጅግ አዘኑ እደሚገባውም እየዘመሩና እያመሰገኑ ገንዘው በመቃብር አኖሩት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ በርሱማ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ትኑር አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት9 ስንክሳር።
❤ ይህም የከበረ አባት ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ ድርሳናትን ደርሶል ከእርሳቸውም ስለ አካላዊ ቃል ሰው መሆንና ከኃጢአት በቀር በሥራው ሁሉ አንድ ባሕርይ ስለ መሆኑ የደረሰው አለ። ዳግመኛም እግዚአብሔር የሚወደውን ስለ መሥራት የደረሳቸው ተግሣጻትና ትምህርቶች አሉ ስለ ቤተ ክርስቲያንም ሕግ ሠላሳ ስምንት መመሪያዎችን ሠርቷል እሊህም በሁሉ አብያተ ክርስቲያን ይገኛሉ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ አቡሊዲስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት6 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_እብል_ዕርገተ_ሥጋሁ_እምባሕር። እንዘ ዕብን ክቡድ ውስተ እገሪሁ እሡር። #አቡሊዲስ_ሊቅ ዘበትውልዱ ማእምር። ያምጽእ ሊተ በረከተ እምነ ገሪዛን ደብር። ከመ ንዋየ ክቡር ወብዕል ያመጽእ ሐመር"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_6።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦"ከርቤ ወቀንዓት ወሰሊሆት አእምነ አልባሲከ። እምክቡዳነ አቅርንት ዘእምኔሆሙ አስተፌሥሐከ። አዋልደ ንሥት ለክብር"። መዝ 44፥8-9። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 1፥15-18፣ ያዕ 4፥1-10 እና የሐዋ ሥራ 27፥39-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 26፥6-17። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የማርያም እንተ ዕፍረት የዕረፍት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta):
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #የካቲት ፮ (6) ቀን።
❤ እንኳን #ጌታችንን_ሽቱ_ለቀባችው_ለማርያም_እንተ ዕፍረት ለዕለፍቷ መታሰቢያ በዓል፣ ለዓለሙ ሁሉ መምህር ለሆነ ለሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት ለከበረ አባት #ለአባ_አቡሊዲስ ሥጋው ከባሕር ለወጣበት በዓልና #ለከበሩ_ቅዱሳን_አቡቂርና_ዮሐንስ ለሦስቱ ደናግላን #ለቅድሳት_ቴዎድራ_ቴዎፍና_ቴዎዶክስያና ለእናታቸው #ለቅድስት_አትናስያ ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። ከእነዚህ ቅዱሳን እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #ማርያም እንተ ዕፍረት፦ ይችም ቅድስት አስቀድማ ኑሮዋን በዝሙት ያሳለፈች ኃጢኣተኛ ነበረች። እርሷም ጐልማሶችን ወደርሷ ትማርካቸው ዘንድ በየራሱ በሆነ ሽልማትና ጌጥ ትሸለም ነበር። በአንዲትም ዕለት እንደ ልማድዋ ተሸልማ አጊጣ ሽቱም ተቀብታ ፊቷን በመስታዋት ተመለከተች የጉንጯ ቅላትና ደም ግባቷ፡የዓይኗም ወገግታና ጥራት ማማሩን አይታ እያደነቀች አንድ ሰዓት ያህል ቆየች ከዚህም በኋላ በጎ ኀሳብ በላይዋ መጣ ሞትንና የዚህን ዓለም ማለፍ አሰበች። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስም ኃጢኣተኞችን እንደ ሚቀበልና ኃጢአትንም እንደሚያአስተሰርይ ሰምታ በዝሙት የሰበሰበችውን ሦስት መቶ ወቄት ወርቅ አላት ያን ይዛ ኼዳለች።
❤ ዲያብሎስም ታመልጠኛለች ይኽነን ጊዜ ላስታት ብሎ ቀድሞ ከምታውቀው አንዱን መስሎ፡በመልከ፡መልካም ወጣት አምሳል ከመንገድ ላይ ቆይቷት "ወዴት ትኼጃለሽ" አላት፤ ዝም አለችው፤ "አንቺ ባትነግሪኝ እኔ እነግርሽ የለም፤ እንግዳ ወንድ መጥቶብሽ ለርሱ የምትቀቢው ሽቶ ልትገዢ ትኼጃለሽ" አላት፤ "አዎን" አለችው፤ ይኽም አይደለም "ፍቅሩ ያላለቀበት ወንድ መጥቶብሽ ለርሱ የምትቀቢው ሽቱ ልትገዢ ትኼጃለሽ" አላት፤ "አዎን" አለችው። ይኽም አይደለም "በጥቂት ገንዘብ ብዙ ገንዘብ የሚሸጥ ነጋዴ መጥቶብሽ ለርሱ የምትቀቢው ሽቱ ልትገዢ ትኼጃለሽ" አላት፤ "አዎን" አለችው። ኹሉንም "አዎን አዎን ትያለሽ ማናቸው ነው ትክክል" አላት፤ ርሷም ተገልጾላት "እንግዳ ወንድ መጥቶብሽ አልከኝ፤ ከዚኽ ዓለም ልዩ የሚኾን ጌታ መጥቷል፤ ፍቅሩ ያላለቀበት ወንድ መጥቶብሽ ላልከኝ የሰው ፍቅር አገብሮት ሊሞት መጥቷል፤ በጥቂት ገንዘብ ብዙ ገንዘብ የሚሸጥ ነጋዴ መጥቶብሽ ላልከኝ "አዎን በጥቂት ትሩፋት ብዙ ክብር የሚሰጥ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቷልና ለርሱ የምቀባው ሽቱ ልገዛ እኼዳለኊ"ብላ ስሙን ብትጠራበት እንደ ትቢያ በኖ እንደ ጢስ ተንኖ ጠፍቶላታል፤ ከዚኽ በኋላ ሃድኖክ የሚባል ባለጸጋ ነጋዴ አለ፤ ኼዳ "ለነገሥታት የሚገባ ሽቱ አምጣ" ብላ ሦስት መቶ ወቄት ወርቅ ሰጠችው፤ በአገራቸው "ሐሰት የለምና ይኽን ያኽልስ የሚያወጣ የለለኝም" አላት፤ ርሱ የማያውቀው እናቱ የምታውቀው ዳዊት ሰሎሞን ተቀብተውለት የተረፈ ነበርና ከእንዲኽ ያለ ቦታ አለና ሽጥላት ብላው ሽጦላት አምጥታ ቀብታዋለች፤ ይኽም ብቻም አይደለም ጌታ ከእናቱ ጋር ግብጽ በተሰደደበት ጊዜ ሰሎሜም ፈያታዊ ዘየማንም ይዘውት ሳለ ከልብሱ ላይ ወዛ ቢያጥቡት ሰፈፈ ይኽም በዕቃ አኑረውት ነበርና ያም ተጨምሮበታል፤ በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ ዋጋው እጅግ የበዛውን ይኽነን ሽቱ የመላው የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ ርሱ ቀርባ በማዕድም ተቀምጦ ሳለ በራሱ ላይ አፍስሳዋለች፤ ጌታችንም ለደቀ መዛሙርቱ "ይኽነን ሽቱ በሰውነቴ ላይ አፍስሳ ለመቃብሬ አደረገች፤ እውነት እላችኋለኊ ይኽ ወንጌል በዓለም ኹሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት ርሷ ያደረገችው ደግሞ ለርሷ መታሰቢያ እንዲኾን ይነገራል" ብሏታልና። ምንጭ፦ የየካቲት6 ስንክሳርና መጽሐፈ ተአምኆ ቅዱሳን ንባብና ትርጓሜው መጋቢ ሐዲስ ሮዳስ ከጻፈው።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅዱስ_ዮሐንስ_ቅዱስ_አቡቂር #ሦስቱ_ደናግልም_ልጆቿና_እናታቸው_ቅድስት_አትናስያና፡- የእሊህም ስማቸው ቴዎድራ ትርጓሜው "የእግዚአብሔር ስጦታ" ነው ሁለተኛወ ቴዎፍና ትርጓሜውም "የእግዚአብሔር ሃይማኖት" ሦስተኛይቱም ቴዎዶክስያ ትርጓሜውም "የእግዚአብሔር ምስጋና" የእናታቸውም የአትናስያ ትርጓሜው "ሕይወት የሆነ" ነው፡፡ ይህም የከበረ ቅዱስ አቡቂር ከታናሽነቱ ጀምሮ በገድል ተጠምዶ የሚኖር መነኰስ ነው፡፡ የከበረ ቅዱስ ዮሐንስ ግን በንጉሥ ሠራዊት ውስጥ ወታደር ነበር፡፡ የእነርሱም አገራቸው እስክንድርያ ሲሆን የሚኖሩት ግን አንጾኪያ ነው፡፡በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም ፊት ቁመው ከእሊህ ደናግል ከእናታቸው ከአትናስያም ጋር በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ። እርሱም ከወዴት እንደሆኑ ጠየቀ ከእስክንድርያ አገር እንደሆኑ በተረዳ ጊዜ ወደዚያ ይወስዷቸው ዘንድ አዘዘ፡፡
❤ ወደ እስክንድርያ በደረሱ ጊዜ ዳግመኛ በመኰንኑ ፊት ቁመው በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ መኰንኑም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ማሠቃየትንም በደከመው ጊዜ ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ፡፡ አትናስያም ደናግል ልጆቿን በከበረ ስሙ ምስክር ሁነው ከሞቱ ለሰማያዊው ሙሽራ ለክርስቶስ እነርሱም ሙሽሮቹ እንደሚሆኑ በማስረዳት ታጽናናቸው ታስታግሣቸው ነበር፡፡ እንዲሁም ቅዱስ አቡቂር በከበረች ሐዋርያዊት በቅድስት ቴክላ ላይ የደረሰውን መከራና ያገኘችውን ክብር ይገልጥላቸውና ያጽናናቸው ነበር፡፡ ወታደሮችም ባለ ሰይፍ በማከታተል አንዲቱን ከአንዲቱ በኋላ የሚያቀርቡ ሆኑ ከዚህም እናታቸውን የከበሩ፣ ቅዱስ አቡቂርንና ቅዱስ ዮሐንስን ቆረጡ። መኰንኑም ሥጋቸውን ለአራዊትና ለአዕዋፍ ይጥሉ ዘንድ አዘዘ፡፡ ምእመናንም ሥጋቸውን በሥውር ወሰዱ በክብር ገነዙአቸው የመከራው ዘመን እስቲያልፍ በሣጥን አድርገው ሠወሩአቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶላቸው ቅዱስ ሥጋቸውን በውስጧ አኖሩ፡፡ ከእርሳቸውም ታላላቅ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጠ። በረከታቸው ከእኛ ጋራ ትኑር ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_አቡሊዲስ፦ ይህም የከበረ በእውቀቱም ፍጹም የሆነ ሰው ነው ከአባት አውክዮስም በኋላ ለሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት ይሆን ዘንድ መንፈስ ቅዱስ መረጠው ይህም የእስክንድር ሊቀ ጳጳሳት አባ ከላድያኑ በተሾመባት በመጀመሪያ ዓመት ነው ሕዝቡንም ከአረማውያን ጠባይ የሚጠብቃቸው የምያስተምራቸውና በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት የሚያጸናቸው ሆነ።
❤ በከሀዲውም ንጉሥ በከላድያኖስ ዘንድ ዜናው ተሰማ ይህንንም የከበረ አቡሊዲስን ይዞ በብዙ ግርፋትና ድብደባ አሠቃየው ማሠቃየቱንም በሰለቸው ጊዜ በእግሮቹ ውስጥ ታላቅ ድንጊያ አሥሮ ከጥልቅ ባሕር የካቲት አምስት ቀን አሰጠመው። ማግሥትም ሲሆን የካቲት ስድስት በዛሬዋ ቀን የዚህ አባት ሥጋው በውኃ ላይ ተንሳፎ ተገኘ ደንጊያውም በእግሮቹ ውስጥ እንደታሠረ ነበር አንድ ምእመን ሰው ወስዶ በርሱ ዘንድ አኖረው በከበሩ ልብሶችም ገንዞ ሠወረው ወሬውም በሮሜ አገሮች ሁሉ ተሰማ ንጉሡም ሊአቃጥለው ፈልጎት ነበር ግን አላገኘውም ያ ሰው ሠውሮታልና።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ጴጥሮስ_የተባለ_አባ_ብሶይ፦ እርሱም ከላይኛው ግብጽ አክሚም ከሚባል ከተማ ነው። በጐልማሳነቱም ጊዜ የክፉ ሥራዎችን የሚሠራ ሁኖ ነበር በመብላትና በመጠጣትም ይደሰት ነበር። እግዚአብሔርም የነፍሱን ድኅነት ሽፍ ጽኑ ደዌ አምጣበትና ለመሞት ተቃረበ። ነፍሱንም በተመሥጦ አውጥተው የሥቃይ ቦታዎችንም ጥልቅ የሆነች ጒድጓድንም አሳዩት። በዚያም ብሩህ ልብስ የለበሱ ሰዎች አሉ በእጆቻቸውም የሰው በድን ነበር አራት ክፍል አድርገው ለያዩትና "የሰውን ገንዘብ የሚሰርቀውን ሁሉ እንዲህ ያድርጉበታል" አሉት። ይህንንም ነገር በሰማ ጊዜ ጮኸ ከልቡም አዝኖ አለቀሰ ከዚህም በኋላ ነፍሱ ተመለሰች ዐይኖቹንም ወደ ሰማይ አቅንቶ "ጌታዬና ፈጣሪዬ ከዚህ ደዌ ከአዳንከኝ እኔ ስለ ኃጢአቴ ንስሐ በመግባት በፍጹም ልቡናዬ አመልክሃለሁ ከእንግዲህም ከቶ ለዘላለሙ የሴት ፊት አላይም" አለ።
❤ በዚያንም ጊዜ ከደዌው አዳነውና ተነሥቶ ብንዋይ ወደሚባል ገዳም ሔደ መንኰሳቱም ከፈተኑት በኋላ የምንኵስናን ልብስ አለበሱት በግብጽ አገር ሁሉ እስከሚሰማ ታላቅ ተጋድሎን በጾም፣ በጸሎት፣ በመስገድም ተጋደለ። ከሁሉ በላይም ከፍ ከፍ አለ ለመነኰሳትም ትምርት የሚሆኑ የሚጠቅሙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሰ አንድ ጊዜም እንጀራ ሳይቀምስ ውኃ ሳይጠጣ አንድ ወር ጾመ እንዲህም እየተጋደለ ሠላሳ ስምንት ዓመት ያህል ኖረ።
❤ መላዋንም ሌሊት በጸሎትና በስግደት በመትጋት ቁሞ ያድራል ሰዎች የሚሠሩት ሁሉ ጻድቅም ቢሆን ኃጢአተኛም ቢሆን በፊቱ ግልጥ ሆነ ከዚህም በኋላ ጥቂት ታመመና የካቲት 5 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ብሶይ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_አክርጵስ፦ ይህም አባት የእስክንድር አገር ሊቀ ጳጳሳት ዐሥረኛ ነው። እግዚአብሔርን የሚፈራ ንጹሕ ቅዱስ ነው። በእስክንድርያ አገርም ቄስ ሁኖ የሚያገለግል ነበር ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ከላድያኖስ በዐረፈ ጊዜ የእስክንድር አገር ሕዝቡና ኤጲስቆጶሳት መረጡት በወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ወንበር ላይ ጵጵስና ሾሙት።
❤ ከዚህም በኋላ እንደ ሐዋርያት መልካም ጒዞን ተጓዘ የእግዚአብሔርን ሃይማኖት ሕይወት የሆነ ሕጉንም እያስተማረ ቅዱሳት መጻሕፍትንም እያነበበላቸውና እያስተማራቸው መንጋዎቹን ይጠብቃቸው ነበር ሁል ጊዜም ይመለከታቸዋል አንድ የብር አላድን ወይም አንድ የወርቅ ዲናርን ጥሪት አላኖረም ከዕለት ምግቡ ከቁርና ከሐሩር ሥጋውን ከሚሸፍንበት ልብስ በቀር ምንም አላከማቸም።
❤ በዚህ ተጋድሎ ዐሥራ ሁለት ዓመት ኑሮ ጌታችንንም አገልግሎ የካቲት5 በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ አክርጵዮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት 5 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለብሶይ_ጴጥሮስሃ_ዘተሰምየ። ኵነኔ ሰራቂ በሕልሙ ሶበ ነጸረ ወርእየ። ኀዲጎ ዘትካት ምግባሮ እኩይየ። እንዘ ይፈዲ ብፅዓቶ በከመ ውእቱ ጸለየ። በመዋዕለ ጾሙ ኢጥዕመ ኅብስተ ወማየ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_5።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ኵሉ ማዕበልከ ወሞገድከ እንተ ላዕሌየ ኃለፈ። ዓልተ ይኤዝዝ እግዚአብሔር ሣህሎ ወሌሊተ ይነግር። እምኀቤየ ብፅዐተ ሕይወትየ ለእግዚአብሔር"። መዝ 41፥7-8። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 5፥1-6፣ ይሁ 1፥20-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 14፥21-24። የሚበበው ወንጌል ማቴ 16፥1-5። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም የጾም፣ የጸሎት፣ የምህላ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta):
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አሜን"። ❤
❤ #የካቲት ፭ (5) ቀን።
❤ እንኳን አስቀድሞ ራሱን በኃጢአት አስገዝቶ ለነበረ ለጽኑዕ ተጋዳይ #ለአባ_ዕብሎይ ለዕረፍት በዓል፣ ለተጋዳይ ለሆነ #አባት_ጴጥሮስ_ለተባለው አስቀድሞ በድሎት ብቻ ይኖር ለነበረውና በኋላም ነፍሱ ተነጥቃ ሲኦልን አይቶ ከተመለሰ በኋላ በታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ ሠላሳ ስምንት ዓመት ለኖረው #ለአባ_ብሶይ ለዕረፍት በዓል፣ መነሳንሱ የወርቅ ለሆነ ለጻድቅ #አባ_ኖብ ለዕረፍት በዓልና ለእስክድርያ አገር ዐሥረኛ ሊቀ ጳጳሳት ለከበረ አባት #ለአባ_አክርጵዮስ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ በአስቄጥስ ገዳም በሰማዕትነት ከሞቱ #ከአርባ_ዘጠኝ_መነኰሳት፣ ከሮሜ ሊቀ ጳጳሳት #ከአባ_አቡሊዲስ_ከቡላ_ከአሞኒ_ከዕብሎይ_እናት_ከአበያ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ዕብሎይ፦ ይህይ የበጎች አርቢ ራሱን ለሰይጣን በማስገዛት ከኃጢአት ሥራ ምንም የቀረው የለም ያመነዝራል፣ ይሰርቃል፣ ይቀማል፣ ይድላል በዚህም የሰይጣንን ሥራ እየፈጸመ አርባ ዓመት ያህል ኖረ። በአንዲትም ዕለት ከቀኑ እኩሌታ ከበጎቹ ጋር በዱር ውስጥ ሳለ እነሆ የመውለጃዋ ጊዜ የደረሰ ያረገዘች ሴትን አየ ሰይጣንም በልቡ ክፉ ሐሳብን ጨመረ እንዲህም አለ "የተረፈችኝ ኃጢአት አንዲት አለች እርሷም ያረገዘች ሴት ሆዷን ሠንጥቄ በእናቱ ሆድ ሕፃኑ የማተኛበትን አይ ዘንድ ነው"። ያን ጊዜ ተወርውሮ ሔዶ በራስዋ ጠጒር ይዞ ከምድር ላይ ጣላት ሾተልም አንሥቶ ሆዷን ሠነጠቀ ሕፃኑንም በማሕፀኗ ውስጥ እንዴት ሁኖ እንደተኛ አየው እርሷም በጻዕር ተጨንቃ አስቀድማ ሞተች ሕፃኑ ግን በጻዕር እየተሠቃየ ብዙ ቆይቶ ሞተ።
❤ አባ ዕብሎይ (በግ አርቢው የሠራውን ይህን ታላቅ ኃጢአት ተመልክቶ ደነገጠ እጅግም አዘነ መራራ ልቅሶንም። በማልቀስ "ታላቅ ኃጢአትን ሠርቻለሁና ወዮልኝ" አለ። በጎቹ እንደተበተኑ ትቷቸው በእጁ የያዛትን መጠበቂያ በትሩን ብቻ ይዞ አስቄጥስ ገዳም እስከሚደርስ እያለቀሰ ተጓዘ፡፡ ወደ አረጋውያን መነኰሳት አልገባም ይልቁንም ዐሥር ምዕራፍ ያህል ርቆ ከበረሃው ውስጥ ገባ፡፡ ከዱር አራዊት ጋር በጫካ ያድራል እንጂ በቤት ውስጥም አያድርም ነበር፡፡ከአራዊት ጋር የሚኗር ሆነ እንጂ ከዕፅዋትም ፍሬ በየጥቂቱ ይመገብ ነበር። ከዕንባ እየጮኸ አላቋረጠም፡ "አቤቱ በደልኩ ክፉ ሥራንም ሠራሁ ይቅር በለኝ እኔ ኃጢአተኛ የሆንኩ ክፉ ባሪያ ነኝና አንተም ቸር አምላክ ይቅር ባይ አባት ነህና የማይበድል ባሪያ የማይምር ጌታ የለምና አቤቱ ይቅር በለኝ…" እያለ፡፡ እንዲህም እየተደለ አርባ ዓመት ኖረ፡፡ ከሌሊት ቁርና ከቀን ፀሐይ ሐሩርና የተነሣ ሥጋው ደርቆ ጠቆረ፡፡ከዚህም በኋላ እንዲህ የሚል ቃል ሰማ "ስለ ሴቲቱ ደም ጌታ ይቅር ብሎሃልና ጽና በርታ"፡፡ ይህንንም ያለው እንዳይታክትና ዳግመኛ ወደ በኃጢአት ውስጥ እንዳይወድቅ ነው፡፡ ይህንም በሰማ ጊዜ ከሦስት ቀን ብቻ በቀር ያቺን ዓመት እስከሚፈጽም መሪር ልቅሶ እያለቀሰ ተጋድሎውን ጨመረ የእግዚአብሔር መልአክ ከእርሱ ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ርቆ ለሚገኝ ከቶ ሰውን ሳያይ በዚያች በርሀ ለሰባ ዓመት ዘግተው የኖረውን አንድ ገዳማዊ "አንተ ካለህበት ቦታ ወደ ውጭ ሂድና አንድ ሽማግሌ ታገኛለህ፣ ኃጢአቱን ካመነልህ አጽናናው፣ ኃጢአትህ ሁሉ ስለ ሕፃኑም መገደል ተሠርዮልሃል በለው" በማለት አዘዘው።
❤ በዚያም ጊዜ ያ ገዳማዊ ሒዶ አገኘው እርስበርሳቸው ሰላምታ ተሰጣጡ። እርሱ ዕብሎይ ግን ያለማቋረጥ ያለቅስ ነበር ገዳማዊውም "የሠራኸውን ንገረኝ በምን ምክንያት ወደዚህ ወጣህ" አለው።እርሱም ሁሉንም ነገረው ያረገዘችውንም ሴት ሆድዋን እንደሠነጠቀ ነገው ገዳማዊውም "ኃጢአትህ ሁሉ ተሠርዮልሃል፣ አባቴ ሆይ ደስ ይበልህ ነገ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ አንተ መጥቶ የክርስቶስን ሥጋና ደም ያቀብልሃል" አለው፡፡ የቀዳሚት ሰንበት ዕለትም በነጋ ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሁኖ የማያውቅ ጣፋጭ ሽታ ሸተተ ለአባ ዕብሎይ ገዳማዊውን "ከፍርሀት የተነሳ ነፍሴ ከሥጋዋ ልትለይ ደረሰች" አለው። ይህንንም ባለ ጊዜ በመነኰስ አምሳል መልአኩን አየው እርሱም ተቸገርኩ እግዚአብሔር አዳነኝ፡፡ ነፍሴ ሆይ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሽ። እግዚአብሔር ረዳትሽ ነውና። ነፍሴን ከሞት አድኗታልና። ዐይኖቼንም ከእንባ እግሮቼንም በዳጥ ከመሰናከል። በሕያዋን አገር እግዚአብሔር አገለግለው ዘንድ" እያለ ይዘምር ነበር። የበጎች ጠባቂ የነበረው አባ ዕብሎይም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ በምድር ላይ ወድቆ እንደ በድን ሆነ መልአኩም በሰው አምሳል እጁን ዘርግቶ አነሣው ልቡም ጸንቶ በመልአክ እጅ ከሰማይ የወረደለትን ሥጋውንና ደሙን ተቀበለ መልአኩም ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡
❤ አባ ዕብሎይም ቊርባኑን በተቀበለ ጊዜ ሰውነቱ ሁሉ እንደ በረድ ፀዓዳ እንደ ፋናም ብሩህ ሆኖ በዚያችም ዕለት ሁለቱም ደስ እያላቸው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ እስከ ማታ ግን፡ የቀድሞ ጸሎቱን አላቋለጠም እንዲህም እያለ "እኔ ክፉ ባሪያ በየሰባቱ ሰባ ጊዜ በደልኩ ቸር ጌታ ይቅር በለኝ የማይበድል ባሪያ የማይምር ጌታ የለምና"። በዚያችም ዕለት እስከ ሌሊቱ እኩሌታ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አደሩ እርሷም እሑድ ናት። በዚያች ጊዜ ከፊተኛው የሚበልጥ የሽቱ መዓዛ ሸተተ ገዳማዊውም "ወንድሜ ዕብሎይ ና በውኃ ታጠብ ደስ ይበልህም በዚህች ሰዓት ከተቀበልከው መከራ ታርፋለህና" አለው፡፡በዚያንም ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለሁለቱም ቊርባኑን አቀበላቸው፡፡ አባ ዕብሎይም ዐረፈና መላእክት ነፍሱን ተሸክመው እስከ አርያም በረሩ፡፡
❤ ያ ገዳማዊ "እኔ ሽማግሌም ነኝ ሥጋውን መሸከም አልችልም የምቆፍርበትም የሌለኝ ምን አደርጋለሁ" ብሎ የሚያስብ ሆነ በዚያንም ጊዜ ሁለት፡ አንበሶች መጥተው ለሥጋ ሰገዱ መቃብራቸውን ቆፍረው ሥጋውን እንደ ሰው ተሸክመው ወስደው፡ ቀበሩት፡፡ገዳማዊውንም እጅ ነሱት እርሱም ባረካቸውና በሰላም ሄዱ፡፡ ከዚህም በኋላ ያ ገዳማዊ "የሚቀብረኝ አገኝ ይሆን" ብሎ አሰበ ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ "አትዘን ሥጋህን እኔ አስቀብራለሁ ያለ ሦስት ቀንም አልቀረህም ወደአንተም ሦስት ሰዎች እልካለሁ የበግ ጠባቂው የአባ ዕብሎይን ገድል ንገራቸው እነርሱም ለሌሎች ይንገሩ ከእግዚአብሔርም ምሕረት ተስፋ እንዳይቆርጡ በኃጢአት ለወደቁ አለኝታ ይሆን ዘንድ። በማግስቱም ሦስት ሰዎች መጡ እርሱም የበግ ጠባቂውን የአባ ዕብሎይን ተጋድሎ ነገራቸው እነርሱም እጅግ አድንቀው ጻፉት ከገዳማዊው ዘንድ ሦስት ቀን ተቀመጡ ከዚያም በኋላ ገዳማዊው ተነሥቶ ጸለየ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ፡፡ እነዚያም ሁለቱ አንበሶች መጡ መቃብርንም ቆፍረው እንደ፡ሰው ወስደው ቀበሩትና እነዚያ ሦስት ሰዎች ጋር ተጓዙ ወደ፡ አስቄጥስ ወደ አባ መቃርስ ገዳም እስከሚአደርሷቸው መርተው ወሰዱአቸው ሰዎችም የሆነውን ሁሉ ለመነኰሳት ነገሩአቸው፡፡ እነርሱ እጅግ አደነቁ የበግ አርቢው የአባ ዕብሎይ ገድል ጻፉ ሁል ጊዜም እሑድ እሑድ የሚያነቡት ሆነ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦የየካቲት 5 ስንክሳር።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #የካቲት ፭ (5) ቀን።
❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊያኑ_ጻድቃን_ለአቡነ_አሞኒ ለልደታቸው በዓልና ለልጃቸው #ለአቡነ_ዮሐኒም ለመታሰቢያቸው በዓላቸው እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #አቡነ_አሞኒ፦ አባታችን የካቲት 5 ቀን አክሱም ውስጥ ሲወለዱ ሰይጣናት የወላጆታቸውን ቤት ከበው በማየታቸው እንደተወለዱ በእጃቸው ቢያመለክቱ በአንድ ጊዜ 60ሰይጣናት ተሸንፈው እንጢስ በነው ጠፍተዋል። አሞኒ ማለት አሸናፊ ማለት ነው። አባ አሞኒ የራስ ፀጉራቸው ልብስ መጎናጸፊያ ሆኖቸው የኖሩ ታላቅና ቀደምት አባት ናቸው። በደመና ተጭነው ኢየሩሳሌም ደብረ ዘይት ድረስ በመሄድ ከአባ ዕብሎይ ጋር ተገናኝተው ብዙ ምሥጢርን፡ አውርተዋል። አባ ዮሐኒንያ ሳደጉት አስተምረው ያሳደጓቸው አባ አሞኒ ናቸው፡፡ የእናቱን ጡት ፈጽሞ ጠብቶ የማያውቀውን የመንፈስ ቅዱስ ልጃቸውን አባ ዮሐኒን እሳቸው እያጫወቱት የታዘዘ አሞራ በክንፎቹ እያለበሰው ቶራ (ሰሳ) እያጠባችው ነው ያደገው፡፡
❤ አባ አሞኒ ልጃቸው አባ ዮሐኒ አድጎ 12ዓመት ሲሆነው ከዚህም በኋላ ዲቁና ሊያሾሙትና አክሱም ጽዮን ወስደው ሊያስባርኩት ቤተ ካህናት ከተባለው ቦታ ይዘውት ሲሄዱ ልዩ ስሙ ሲሂታ ከሚባለው ቦታ ሲደርሱ ከወገባቸው በላይ እራቁታቸውን የሆኑ እንስራ የተሸከሙ ዐሥር ሴቶች አገኙ፡፡ አባ ዮሐኒም አባታቸውን "አባቴ እነዚህ ደረታቸው ላይ ቀንድ ያላቸው ጽጉራቸው የረዘመ ምንድናቸው? እንደእኛ የሆኑ መስህታን የሚባሉት እነዚህ ናቸውን?" አሏቸው፡፡ አባ አሞኒም"አይደሉም፡ልጄ፡ዝም፡ብለህ፡ሂድ" አሏቸው፡፡በኋላ ግን ትዝ ሲላቸው "በዱር እንስሳት ያሳደኩት ልጄ ወንድና ሴት ለይቶ ሲያውቅ በዚያው ሊሳሳት አይደልምን?" ብለው በማሰብ ዲቁናና ክህነቱ ይቅርበት ብለው ተመልሰው ወደ በዓታቸው ይዘውት ገቡ፡፡ ከዚህም በኋላ አባ አበይዶ ወደ አባ አሞኒ መጣና እሳቸውን ከአባ ዮሐኒ ጋር እያገለገሏቸው ተቀመጡ፡፡ ዮሐኒ እየጻፈ አበይዶ የሚጻፍበትን ቆዳ እያዘጋጁ ሦስቱም በአንድነት በተጋድሎ መቀመጥ ጀመሩ፡፡
❤ አባ ዮሐኒ ሃያ ዓመት አባ አሞኒ ደግሞ አርባ ዓመት በሆናቸው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለአባ አሞኒ ተገለጠላቸውና "አሞኒ ሆይ ከእንግዲህስ እግዚአብሔር ወደኔ ና ብሎሃል" አላቸው። እሳቸውም ልጆቻቸውን አባ ዮሐኒንና አባ አበይዶን ጠርተው "በሉ እንግዲህ እኔ ወደ እግዚአብሔር መሄዴ ነውና ጸልዩልኝ" አሏቸው፡፡ ከማረፋቸውም በፊት አባ ዮሐኒን ለብቻቸው ጠርተው "አንተ አባ ዮሐኒ ካሁን በፊት ሲሂታ ላይ ያየሃቸው ሴቶች ናቸው፣ አዳምንም ከገነት ያስወጡ ናቸው፡፡ ወደፊትም እንደ እነርሱ ያለ የደረሰብህ እንደሆነ ካለህበት ገደል ተወርውረህ ውደቅመ በባሕር ውስጥ ጥለቅ" ብለው ነግረዋቸው ዕለት ኅዳር 5 ቀን በሰላም ዐረፉና ወደ ጠራቸው እግዚአብሔር ሄዱ፡፡ ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አሜን"። ❤
❤ #የካቲት ፬ (4) ቀን።
❤ እንኳን #ከሰባ_ሁለቱ_አርድእት አንዱ ለሆነው በአይሁድ እጅ በድንጋይ ተወግሮ ሰማዕትነት ለተቀበለው #ለሐዋርያው_ለከበረ_ቅዱስ_አጋቦስ ለዕረፍቱ በዓልና በምግባር ፍጹም ለሆነ ተጋድሎውም ለበዛ ለታላቁ አባት #ለአባ_ዘካርያስ_ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን፡፡ በተጨማሪ በዚች ቀን ከምትታሰበው፦ ስለ #ኢየሱስ_ክርስቶስ አምላክነትና #ስለሐዋርያው_ቅዱስ_አጋቦስ እውነተኛነት መስክራ #በሰማዕትነት_ከዐረፈችው_ሴት ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #ሐዋርያው_ቅዱስ_አጋቦስ፦ ይህም ቅዱስ ጌታችን ከመረጣቸውና የከበረች ወንጌልን ይሰብኩ ዘንድ፡ወደ ዓለም ከላካቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ ነው፡፡በጽርሐ ጽዮንም አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሐዋርያት ጋር ስጦታውን ተቀብሏል፡፡ ከዚህም፡በኋላ፡እግዚአብሔር የትንቢትን ሀብት ሰጠው፡፡ ስለ እርሱ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደተነገረ የቅዱስ ጳውሎስን መታጠቂያ አንሥቶ ራሱ እግሮቹን አሠረባትና "የዚህችን መታጠቂያ ባለቤት በኢየሩሳሌም አይሁድ እንዲህ ያስሩታል" ብሎ ትንቢትን ተናገረ፣ትነቢቱም ተፈጸመች፡፡
❤ ከዚህም በኋላ ሕይወት በሆነ በወንጌልን ትህምርት ሊያስተምር ከሐዋርያት ወጣ፡፡ እያስተማረና ቀና የሆነ የእግዚአብሔርን መንገድ እየመራ ብዙ አገሮችም ዞረ ከአይሁድና ከዮናናውያንም ብዙዎችን የክብር ባለቤት ወደሆነ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅን ሃይማኖት አስገባቸው፡፡ በከበረች በክርስትና ጥምቀትም አነፃቸው (አጠመቃቸው)፡፡ ቅናትን የተሞሉ አይሁድም ብቻውን በኢየሩሳሌም ድንገት ያዙትና ታላቅ ግርፋትን ገረፉት ከዚያም በአንገቱም ገመድ አስገብተው እስከ ከተማ ውጭ ጐትተው በዚያም ነፍሱን እስካለፈች ድረስ በድንጋይ ወገሩት፡፡ በዚያም ጊዜ ከሰማይ ብርሃን ወርዶ በሥጋው ላይ እንደምሰሶ ተተከለ ወደ ሰማይ ደርሶ አሕዛብ ሁሉ ወደርሱ ሲመለከቱ ነበር። እግዚአብሔርም የአንዲቱን አይሁዳዊት ሴት ልቡናዋን ገለጠላት፡፡ እርሷም በውስጥዋ ሽንገላ፣ ቅናትና ጠብ የሌለባት ናት የኦሪትንም ሕግ የምትጠብቅ መልካም ሴት ነበረች፡፡ እርሷም ይህንን ብርሃን አይታ "ይህ ሰው እውነተኛ የእግዚአብሔር ሰው ነው" አለች፡፡ ያን ጊዜም በላይዋ ብርሃን ወረደ፡፡ ከዚህም በኋላ ጮኻ "እኔ በቅዱስ አጋቦስ ፈጣሪ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነ በጌታ ኢየሱስ የማምን ክርስቲያን ነኝ"። እግዚአብሔርንም ከፍ ከፍ እያደረገች እግዚአብሔርን ስታመሰግነው በደንጊያ ወግሩዋት ነፍሷንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠች፡፡ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛን በሐዋርያው በቅዱስ አጋቦስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትሁን ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ዘካርያስ፦ እርሱንም ነፍሱ ከሥጋው በምትለይ ጊዜ አባ ሙሴ "ወንድሜ ሆይ! ምን ታያለህ?" አለው፡፡እርሱም "ለእኔስ ዝምታ ይሻለኛል" አለ ነፍሱም ስትወጣ አባ ኤስድሮስ ሰማይ ተከፍቶ አየ "ልጄ ዘካርያስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያት በር ተከፍቶልሃልና ደስ ይበልህ" አለው፡፡ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ዐረፈ። በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን አሜን። ምንጭ፦የየካቲት4 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለአጋቦስ_እምአርድእተ_ክርስቶስ ዋሕድ። ከመ ወገርዎ በአዕባን ወቀተልዎ አይሁድ። ተተከለ ብርሃን በአምሳለ ዓምድ። መልዕልተ ሥጋሁ ቅድመ ጉቡአን በዓውድ። እስከ አይሁዳዊት ተመይጠት ወአምነት በወልድ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_4።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ኵሉ ማዕበልከ ወሞገድከ እንተ ላዕሌየ ኃለፈ። ዓልተ ይኤዝዝ እግዚአብሔር ሣህሎ ወሌሊተ ይነግር። እምኀቤየ ብፅዐተ ሕይወትየ ለእግዚአብሔር"። መዝ 41፥7-8። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 5፥1-6፣ ይሁ 1፥20-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 14፥21-24። የሚበበው ወንጌል ማቴ 16፥1-5። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም የጾም፣ የጸሎት፣ የምህላ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
ጾመ ነነዌ
ጾመ ሰብአ ነነዌ (የነነዌ ሰዎች ጾም) የምትጾመው ለሦስት ቀናት ነው ጾሙ የሚጀመርበት ዕለትም ልክ እንደ ዐቢይ ጾም ሰኞን አይለቅም ጾሙ የሚጀመርበት ቀን ደግሞ ሲወርድ ወይም ወደ ኋላ ሲመጣ እስከ ጥር ፲፯ ቀን ድረስ ነው ሲወጣ ወይም ወደ ፊት ሲገፉ ደግሞ እስከ የካቲት ፳፩ ድረስ ነው በእነዚህ ፴፭ ቀናት/ዕለታት/ ስትመላለስ ትኖራለች ከተጠቀሱት ዕለታት አይወርድም፤ አይወጣም ማለት ነው በዚህም ቀመር መሠረት የ፳፻፲፯ ዓ.ም ጾመ ነነዌ የካቲት ሦስት ጀምሮ በአምስት ያበቃል፡፡
ጾመ ነነዌን የጾሙት በነነዌ የሚኖሩ ሰዎች በአምላካችን እግዚአብሔር ትእዛዝ እና በነቢዩ ዮናስ ነጋሪነት ነው የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ በኃጢአታቸው ምክንያት ሊያጠፋቸው ሲል ቸርነትና ምሕረቱ የማያልቅበት አምላካችም ነቢዩ ዮናስ መክሮ ዘክሮ እንዲመልሳቸውና ንስሐ እንዲገቡ ወደ ነነዌ ሕዝብ እንዲሄድ አዘዘው፡፡ (ዮናስ. ፬፥፲፩)
እግዚአብሔርም “ሄደህ በነነዌ ላይ ስበክ” ባለው ጊዜ “አንተ መሐሪ ነህ፤ ልትጠፉ ነው ብዬ ተናግሬ ብትምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ” ብሎ ላለመታዘዝ እስራኤልን ለቆ በመርከብ ወደ ተርሴስ ሸሸ እግዚአብሔር ግን ታላቅ ነፋስን አስነሥቶ መርከቧ በማዕበል እንድትመታ አደረገ ከዮናስ ጋር በመርከቧ ተሳፍረው የነበሩት ነጋድያንም ያላቸውን ሀብት ወደ ባሕሩ መጣል ሲጀምሩ ነቢዩ ዮናስ “በእኔ ምክንያት የመጣ ስለሆነ ንብረታችሁን ሳይሆን እኔን ወደ ባሕር ጣሉኝ” ብሎ ተማጸናቸው እነርሱም “የሰው ደም በእጃችን እንይሆንብን አይሆንም” ብለው ዕጣ ተጣጣሉ፤ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወጣ ነጋድያኑም ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት ወዲያው የእግዚአብሔርን የማዳን መልእክት ዮናስ እንዲያደርስ፣ የታዘዘ ታላቅ ዓሣ አንበሪ ዮናስን በአፉ ተቀብሎ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አሳድሮ ነነዌ አደረሰው፡፡
ዮናስም ከእግዚአብሔር መኮብለል አለመቻሉን ሲረዳና ነነዌ መሬት ላይ መድረሱ ሲነገረው ለነነዌ ሰዎች “ንስሐ ግቡ” ብሎ መስበክ ጀመረ፤ (ዮናስ ፩ እና ፪) መጀመሪያ ከተልእኮው ቢያፈገፍግም “ዮናስም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ፤ ጮኾም፦ በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ” እንደተባለው ነቢዩ ዮናስ የኋላ ኋላ ወደ ነነዌ ሄዶ የእግዚአብሔርን መልእክት ዐውጇል። (ዮናስ ፴፫፥፬) በዚያን ጊዜ የነበሩት ሰዎችም እንዲህ አደረጉ “የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም ዐዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ” (ቁጥ.፭) እንዲል፡፡
መጽሐፉ የነነዌ ሰዎች ንስሐ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር እንደማራቸው ይገልጻል (ዮናስ ፫) ነቢዩ ዮናስም ውሸታም ላለመባል መኮብለሉ ስሕተት መሆኑን አምላካችን ቅልን ምሳሌ በማድረግ አስረዳው (ዮናስ ፬) ነቢየ ሐሰት እንዳይባልም ለቅጣት የመጣው እሳት እንደ ደመና ሆኖ ታይቶአል የታላላቅ ዛፎች ቅጠል እስኪጠወልግ ድረስ የእሳቱ ወላፈን ነክቷቸው ለሕዝቡ አሳይቷቸዋል፡፡ በንስሐ በጾምና ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀው ከጥፋትና መዓት ድነዋል።
እኛንም ካለንበት መከራ፣ ችግርና ሥቃይ እንዲያወጣን፣ በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት እንዲያኖረን እንደ ነነዌ ሰዎች ንስሐ እንግባ፤ በጸሎት፣ በጾምና በበጎ ምግባር ተወስነን በሃይማኖት እንጽና!
አምላካችን እግዚአብሔር ቸርነቱን ያብዛልን አሜን!
ጾመ ነነዌ
ተአምራቶችን አደረገ ከዚህም በኋላ አባ ሉክያኖስ ዐረፈ።
❤ የኬልቄዶንን ጉባኤ በሰበሰበ በከሀዲው መርቅያኖስም ዘመን ወደ አገሮችም ሁሉ መልእክተኞችን ላከ ከእርሳቸውም ጋር አንዱን ክርስቶስን ወደ ሁለት ባሕርይ የምትከፍል የረከሰች የሃይማኖቱ ደብዳቤ አለች። ከንጉሥ መልእክተኞች ሦስቱ ወደ ደብረ ዝጋግ በደረሱ ጊዜ ያንን ደብዳቤ ለአባ ለንጊኖስ ሰጡት በዚህ "ጽሑፍ እንድታምኑ በውስጡም እንድትፈርሙ ንጉሥ መርቅያኖስ አዝዞአል" አሉት። አባ ለንጊኖስም "ከቅዱሳን አባቶቼ ጋር ሳልማከር እኔ ምንም ምን መሥራት አልችልም እንድንማከርም እናንተም ከእኔ ጋር ኑ" አላቸውና የቅዱሳን በድኖች ወደ አሉበት ዋሻ ውስጥ አስገባቸውና "የከበራችሁ አባቶቼ ሆይ እናንተ ዐርፈን ተኝተናል አትበሉ እነሆ አንዱን ክርስቶስን ሁለት ባሕርይ የሚያደርግ በውስጡ የተጻፈበትን ይህን ደብዳቤ አምጥተዋልና በቃሉ አምን ዘንድ በውስጡም እፈርም ዘንድ ታዙኛላችሁን ወይም አታዙኝም የምሠራውንም ካልነገራችሁኝ ሕያው እግዚአብሔር ዐፅማቻችሁን ከዚህ ቦታ አወጣለሁ" አላቸው።
❤ ያን ጊዜ ሰዎች ሁሉም እየሰሙ ከአስከሬናቸው "የአባቶቻችንን የሐዋርያትንና የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱን የቀናች ሃይማኖትን አትተው ይህንንም የረከሰ ደብዳቤ አትከተል ከአስከሬናችን ቦታ አርቀው እንጂ" የሚል ቃል ወጣ የንጉሥ መልክተኞችም ይህን ነገር ሰምተው እጅግ አደነቁ በላያቸውም ታላቅ ፍርሀት አደረባቸው ወደ ንጉሡም አልተመለሱም ራሳቸውን ተላጭተው መነኰሱ እንጂ እስከ ዐረፉም ድረስ ብዙ ዘመን እየተጋደሉ ኖሩ። የከበረ አባ ለንጊዮስ ያማረ ተጋድሎውን ጨርሶ እግዚአብሔርንም አገልግሎ የካቲት 2 ቀን በሰላም ዐረፈ የሕይወት አክሊልንም ተቀበለ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ለጊዮኖስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የካቲት 2 ስንክሳር።
❤ ከዚህም በኋላ አባ እንጦኒ አባ ጳውሊን "አባቴ ሆይ ይህ አስኬማ በምድር ላይ ይበዛ እንደሆነ ወይም አለመብዛቱን ትነግረኝ ዘንድ እሻለሁ" አለው። የከበረ ጳውሊም ወደ ሰማይ ተመለከተና ፈገግ አለ። ከዚህም በኋላ አዘነ ጩኾም አለቀሰ አባ እንጦንዮስም "ፈገግ ስትል በአየውህ ጊዜ ደስ አለኝ በአዘንክም ጊዜ አዘንኩ" አለው። የከበረ ጳውሊም እንዲህ ብሎ መለሰለት "እሊህ ተራሮችና በረሐዎች እግዚአብሔር ከሁሉ አገሮች መርጦ ለሚሰበስባቸው ንጹሐን ርግቦች ማደሪያዎች ይሆናሉ"።
❤ "ዳግመኛም ይህ ስም ያልፋል ስማቸውም መነኰሳት ይባላሉ እነርሱም ብዙ ዘመናት ደስ ይላቸዋል እግዚአብሔርም ከቁጣው ቀን አስቀድሞ ከዚያ ያፈልሳቸዋል። ከእነርሱም በኋላ ሰምተው ለመምህሮቻቸው የማይታዘዙ ትውልድ ይነሣሉ ስለ ነፍሳቸውም ድኅነት በቀንና በሌሊት የማይተጉና የማይጸልዩ ናቸው። ያን ጊዜ እግዚአብሔር ተቆጥቶ ይፈርዳል የማያስተውሉ ሕግ የሌላቸው አረማውያንም ተነሥተው ገዳማቱንና አድባራቱን ያጠፋሉ ብዙ ዘመናትም ምድረ በዳ ይሆናሉ የቅዱሳን መታሰቢያቸው አይጠፋም እግዚአብሔርም በሌሎች ሰዎች ልቡና ይቅርታውን ያሳድርባቸዋል እነርሱም ወደ ገዳማቱና ወደ አድባራቱ በመሔድ በውስጣቸው ዳግመኛ ይኖራሉ ሰይጣንም ወደ ገዳማት ሔዶ በመካከላቸው ጸብን ይዘራል እነርሱም የእግዚአብሔርን ፍቅር ገንዘብ በማድረግ ጨክነው አልታገሡባትምና ምንኵስናቸውን አስኬማቸውን ትተው ወደ ዓለም ይወርዳሉ "በትዕግሥታችሁ ነፍሳችሁን ገንዘብ ታደርጓታላችሁ" የሚለውን ጽሑፍ አላስተዋሉምና"።
❤ እንጦንዮስም "የከበርክ አባቴ ጳውሊ ሆይ ፊትህን አይ ዘንድ የታደልኩባት ሰዓት የተባረከች ናት" አለ። የከበረ አባ ጳውሊም "አሁን ወደ ማደሪያህ ሒድ ቈስጠንጢኖስ ለሊቀ ጳጳሳት አትናቴዎስ የሰጠውን ልብስ እርሱም አንተን ያለበሳትን ያቺን ከአንተ ጋር ይዘሃት ና ሥጋዬን በርሷ ትገንዝ ዘንድ" ብሎ ተናገረው የተሠወረውን በማወቁ እጅግ አደነቀ የተነበየለትንም ትንቢት ሁሉ አመነ። ዳግመኛም እንዲህ አለው "በሰው ሁሉ ላይ እንደተሠራ ከዓለም የምወጣበት ጊዜዬ ቀርቧልና ፈጥነህ ሒድና ተመለስ እርሱም ከአባ ጳውሊ ዘንድ ወጥቶ ወደ በዓቱ እስኪደርስ የሁለት ቀን ጎዳና ተጓዘ ያቺንም ልብስ ይዞ ተመለሰ በመንገድም እየተጓዘ ሳለ በአየር ውስጥ አባ ቡላን የመላእክትንም ማኅበር አየ "ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን" ይሉ ነበር።
❤ ሁለተኛም "እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ የመረጠህ ሰላምታ ፍቅር አንድነት ይገባሃል የእግዚአብሔር ሰው አንተ ጳውሊ የተመሰገንክ ነህ እንግዲህስ በሰማያዊ መንግሥት ከመላእክት ጋር ደስ ይበልህ የጨለማውን ዓለም ትተህ የብርሃን ሀገርን አግኝተሃልና ወደ ዘላለማዊ ተድላ ደስታ ይወስዱሃልና የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆንክ አንተ ገዳማዊ ጳውሎስ በትውልድህ የከበርክና የተመሰገንክ ነህ" እንዲህ እያሉ ተሠወሩ።
❤ የከበረ እንጦኒም "ይህች ወደ ሰማይ የሚያሳርጓት የአባቴ የጳውሊ ነፍስ ናት" አለ ወደ በዓቱም በገባ ጊዜ እንደ ሰገደ ሁኖ እጆቹም በመስቀል ምልክት ተዘርግተው አገኘው አንሥቶም ሸፈነው "አባቴ ሆይ በሰማያዊ ማደሪያህ ሁነህ አስበኝ" ብሎ በላዩ አለቀሰ።
❤ ከዚህም በኋላ ተነሥቶ በዚያች ልብስ ሥጋውን ገነዘና በላዩ የቤተ ክርስቲያንን የጸሎት ሥርዓት ፈጸመ አደረሰም ከዚህም ቀጥሎ ከእርሱ ጋር የተማከርኩት ነገር የለም ምን ላድርግ ብሎ አሰበ በዚያንም ጊዜ አንበሶች መጡ እጅ ነሡትም ቀድሞ እንደሚያውቁትም ዘንበል ብለው የእግሩን ትቢያ ላሱ መቃብሩን በየት ቦታ እንቆፍርለት እንደሚሉ አመለከቱት እርሱም ምልክታቸውን አውቆ በቁመቱ ልክ ለክቶ ሰጣቸው አንዱ በራስጌ አንዱ በግርጌ ሁነው ቆፈሩ በአደረሱም ጊዜ "በቃችሁ" ብሎ አመለከታቸው እሊህ አንበሶችም ወጥተው ሰገዱለት። እርሱም ባረካቸውና ወደ ቦታቸው ሔዱ የከበረ እንጦኒ ወደ መቃብር አስገብቶ ዘጋው። ከሰኔል ቅጠልም የተሠራች ዐጽፉን ወሰደ የአባቱን ገንዘብ እንደሚወርስ ልጅ ነውና ወደ እስክንድርያም ሔደ፡፡ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አትናቴዎስም ገብቶ ከከበረ አባ ጳውሊ የሆነውን ሁሉ ነገረውና ያቺን ከሰኔል የተሠራች ዐጽፍ ሰጠው።
❤ ሊቀ ጳጳሳት አትናቴዎስም የከበረ ጳውሊን ዜና በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለው ያቺንም ዐጽፍ ተቀብሎ በእርሱ ዘንድ አኖራት በየዓመቱም በከበረ በልደት በዓል በጥምቀትም በዓል በመድኃኒታችን ክርስቶስ ትንሣኤ በዓልም ሦስት ጊዜ ይለብሳት ነበር።
✝ ጌታችንም የቅዱስ ጳውሊን የልብሱን ክብር ሊገልጥ ወደደ በዚያችም ወቅት አንድ ወጣት ልጅ ሞተ አባ አትናቴዎስም ያቺን ልብስ በሞተው ላይ አኖራት ወዲያውኑ ተነሣ ይህንንም ያየ ኤጲስቆጶስ አባ ኤስድሮስ ምስክር ሆነ ይችም ተአምር በአገሮች ሁሉ ተሰማች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበረ በአባ ጳውሊ ጸሎት ይማረን በረከቱ ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #ሐዋርያው_ቅዱስ_ቶማስ_ያደረገው_ተአምር፦ ጌታችን ወደ አዘዘው ሊአስተምር በወጣ ጊዜ ከመንገድ ጥቂት ፈቀቅ አለ ድንገትም የሞተ ጐልማሳ አየ መልኩ እጅግ የሚያምር ነበር ሐዋርያውም "አቤቱ ይህን ጥፋት አይ ዘንድ ወደዚህ አመጣኸኝን ነገር ግን ፈቃድህ ይሁን" አለ።
❤ ከዚህም በኋላ ስለሞተው ሰው ጸለየ ያን ጊዜ ታላቅ ከይሲ ከደንጊያዎች ውስጥ ወጥቶ በጅራቱ ምድሩን እየደበደበ መጣ "የክርስቶስ ሐዋርያ ሆይ እኔ ካንተ ጋር ምን አለኝ ሥራዬን ልትዘልፍ መጣህን" ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ ሐዋርያውም "አዎን ሥራህን ተናገር" አለው። ከሲውም እንዲህ አለ "በዚህ ቦታ አንጻር መልከ መልካም ሴት ነበረች እኔ የምወዳት ናት ይህም ጐልማሳ ሲሰማት አየሁት በሰንበት ቀንም ከርሷ ጋር አደረ ስለዚህም ነክሼ በመርዝ ገደልኩት" ሐዋርያውም "መርዝህን ከሱ ትወስድ ዘንድ በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝዤሃለሁ" አለው። ሒዶም ከዚህ ከሞተው መርዙን መጠጠና ወሰደ ወዲያውኑ ተነፍቶ አበጠ ተሠንጥቆም ሞተ የሞተውም ሰው ድኖ ተነሣ። ስለዚች ምልክትም ብዙዎች በክብር ባለቤት ጌታችን አመኑ እርሱም ሃይማኖትን አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው በአባታችን በቅዱስ ቶማስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #የደብረ_ዝጋግ_ገዳም_አበ_ምኔት #አባ_ለንጊኖስ፦ ይህም ቅዱስ ከኪልቅያ አገር ነው በዚያም መነኰሰ መምህሩም ክርስቶስን የሚወድ ሰው ከሚሰጠውም ክብር የሚሸሽ ነበር። በዚያንም ጊዜ የገዳማቸው አበ ምኔት ዐረፈ ይህንንም ስሙ ሉክያኖስ የተባለ አረጋዊ መምህሩን አበ ምኔትነት ሊሾሙት መነኰሳቱ ወደዱ እርሱም ደቀ መዝሙሩን ለንጊኖስን ይዞ በጭልታ ከኪልቅያ ወጥቶ ወደ ሶርያ አገር ሔደ በአንዲት ቤተ ክርስቲያንም ግቢ በአንድነት ተቀመጡ በእጆቻቸውም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶችን ያደርግ ዘንድ ከንቱ ውዳሴና ክብር ሆነባቸው።
❤ አባ ለንጊኖስም በመምህሩ ምክር ወጥቶ ወደ ግብጽ አገር ሔደ ወደ ደብረ ዝጋግ ገዳምም በገባ ጊዜ በደስታ ተቀበሉትና ከእርሳቸው ጋራ ኖረ ከዚያም በኋላ አበ ምኔቱ ዐረፈ ተጋድሎውን ትሩፋቱንና ደግነቱን ስለ አወቁ በደብረ ዝጋግ ገዳም ላይ አባ ለንጊኖስን አበ ምኔት አድርገው ሾሙት። ከጥቂትም ወራት በኋላ መምህሩ አባ ሉክያኖስ መጣ የመርከቦችን ጣሪያዎች እየሠራ በእጆቻቸውም ከሚሠሩት እየተመገቡ በአንድ ልብ በመሆንም በአንድነት ኖሩ እግዚአብሔርም በእጆቻቸው ብዙዎች የሆነ ድንቆች
ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta):
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #የካቲት ፪ (2) ቀን።
❤ እንኳን #ለመላእክት_ወገን_ለሆነ_ለገዳማውያን_ባሕታውያን (መናንያን) ሁሉ አለቃ ለሆነ ለከበረ ለታላቁ አባት #ለአባ_ጳውሊ ለዕረፍት በዓል፣ ለከበረ #ለሐዋርያው_ቅዱስ_ቶማስ አንድ ከይስ ነድፎ የገደለው ሰው ተምራትን በማድረግ ከሞት ላስነሳበትና ከይሲውን በመግደል ብዙዎችን አስተምሮ ላጠመቀበት፣ ከእስክንድርያ ውጭ ለደብረ ዝጋግ ገዳም አበ ምኔት የቅዱሳን ዐፅም ቃል በቃል በማጋገር የሃይማኖት ነገር ለተረዳ ለከበረ አባት #ለአባ_ለንጊኖስ ለዕረፍት በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን። ከእነዚህ ቅዱሳን እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝️ ✝️
❤#ርዕሰ_ገዳማውያን_ባሕታውያን (መናንያን) #አባ_ጳውሊ፦ ይህም ቅዱስ ከእስክንድርያ አገር ጴጥሮስ የሚባል ወንድም አለው አባታቸውም የገንዘቡ ብዛት ሊቈጠር የማይቻል እጅግ ባለጸጋ ነበር በዐረፈም ጊዜ የኀዘናቸው ቀን ሲፈጸም ርስቱንና ገንዘቡን ሊካፈሉ ጀመሩ ጴጥሮስም ታላቁን ክፍል ወደራሱ በመውሰድ የሚያንሰውን ለጳውሊ የሚሰጠው ሆነ። ስለዚህም ጳውሊ አዘነና "ከአባቴ ርስት በትክክል ለምን አትሰጠኝም?" አለው እርሱም "አንተ ወጣት ስለሆንክ ታባክነዋለህ እስከ ምታድግ እኔ እጠብቅልሃለሁ" ብሎ መለሰለት።
❤ ስለዚህም ጳውሊ ተቆጣና እርስ በርሳቸው ተጣሉ ይፈርድላቸውም ዘንድ ወደ ዳኛ ሔዱ እነርሱም ወደ ዳኛ ሲሔዱ ሰዎች ተሸክመውት ወደ ሚቀብሩበት ሲወስዱት ብዙዎችም የተከተሉትን የሞተ ሰውን አገኙ ጳውሊም ከተከተሉት አንዱን ሰው "ዛሬ የሞተው ማን?" ነው ብሎ ጠየቀው። ያም ሰው እንዲህ ብሎ መለሰለት "ልጄ ሆይ ዕወቅ አስተውል ይህ የሞተ ሰው በወርቅ በብር እጅግ ባለጸጋ የሆነ ሁል ጊዜ ደስ የሚለው ነበር አሁንም እነሆ ይህን ሁሉ ትቶ ራቁቱን ወደ መቃብር ወደማይመለስበት መንገድ ይሔዳል በኃጢአት ማዕበል ውስጥ እያለ ሙቷልና። አሁንም ልጄ ሆይ ስለ ነፍሳችን ድኅነት ልንታገል ይገባናል እኛ መቼ እንደምንሞት አናውቅምና ነገር ግን በዚህ ዓለም ውስጥ ገንዘብ ኑሮት ሥልጣንም ኑሮት ሳለ ይህን ሁሉ የተወ የተመሰገነ ነው እርሱ የቅዱሳን ሀገር በሆነች በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ታላቅ ክብርን ይቀበላልና"።
❤ የከበረ ጳውሊም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ከልቡ አዘነ እንዲህም አለ "የዚህ የኃላፊው ዓለም ገንዘብ ምኔ ነው ምን ይጠቅመኛል ከጥቂት ቀኖች በኋላ ትቼው ራቁቴን የምሔድ አይደለሁምን" አለ። ከዚህም በኋላ ወደ ወንድሙ ተመልሶ "ወንድሜ ሆይ ወደ ቤታችን እንመለስ ከእንግዲህ ስለ ገንዘብ ምንም ምን ከአንተ ጋር አልነጋገርም" አለው።
❤ ከዚህም በኋላ ከወንድሙ ሸሽቶ ከሀገሩ ወጣ ከመቃብር ቤት ውስጥም ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት መንገዱን ይመራው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እየጸለየና እየማለደ ኖረ። ወንድሙ ጴጥሮስም በሀገር ውስጥ እየዞረ ሲፈልገው ሰነበተ ግን አላገኘውም ታላቅ ኃዘንንም አዘነ። የተመሰገነ ጳውሊ ግን ሦስት ቀኖች ያህል በዚያች መቃብር ቤት ሲኖር መብልና መጠጥን አላሰበም ፍርሀትና ድንጋፄም አልደረሰበትም አምላካዊ ኃይል ትጠብቀው ነበርና።
❤ በአራተኛዪቱም ዕለት እግዚአብሔር ወደርሱ መልአኩን ላከ ከዚያም ነጥቆ ወሰደው በምሥራቅ በኵል በምትገኝ በረሀ ውስጥ አኖረው በዚያም የውኃ ምንጭ አለ መልአኩም ሰላምታ ሰጥቶት ወደ ሰማይ ዐረገ የከበረ ጳውሊም አራዊት የሚኖሩበትን ጒድጓዶች አግኝቶ ወደ አንዲቱ ፍርኩታ ገባ ልብሱንም ሰኔል ሠርቶ ለበሰ። እንዲህም ብሎ ጸለየ "የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ርኀራኄ ከሌለው ጠላት እጅ ጠብቀኝ አድነኝም ተጋድሎዬን እስከምፈጽም ተጸናኝ ዘንድ ቸርነትህ ወደእኔ ትምጣ የትውልድ ሁሉ ንጉሥ ሆይ ኃይል ጌትነት ክብር ገንዘብህ ነውና ለዘላለሙ"።
❤ በዚያችም ዋሻ ውስጥ ሰማንያ ዓመት ኖረ ከሰውም ከቶ ማንንም አላየም ልብሱም ከሰኔል ቅጠል የተሠራ ነው እግዚአብሔር ወደ ማታ ሁል ጊዜ ወደርሱ ቁራን ይልክለታል ከርሱም ጋራ ግማሽ እንጀራ አለ ያንን ለከበረው ጳውሊ ይሰጠዋል።
❤ የክብር ባለቤት እግዚአብሔርም ቅድስናውንና ጽድቁን ይገልጥ ዘንድ በወደደ ጊዜ መልአኩን ወደ ታለቅ አባት ወደ እንጦንዮስ ላከ ይህም እንጦንዮስ በበረሀ ውስጥ መኖርን የጀመረ እርሱ እንደሆነ በልቡ ያስብ ነበር መልአኩም እንዲህ አለው "እንጦንዮስ ሆይ ከአንተ የሁለት ቀን ጎዳና ርቆ በበረሀ ውስጥ ሰው አለ የዓለም ሰዎች ከሚረግጥባቸው የእግሩ ጫማዎች እንደ አንዲቱ ሊሆኑ የማይገባቸው ስለ ርሱም ጸሎት ዓለም ተጠብቆ የሚኖር ምድርም ፍሬዋን የምትሰጥ ጠል በምድር ላይ የሚወርድ በምድር በሚኖሩ ኃጢአተኞች ሁሉ ላይ ፀሐይ የሚወጣ የሰውም ፍጥረት በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ተጠብቆ የሚኖር"።
❤ አባ እንጦንዮስም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ተነሥቶ ወደ በረሀው መካከል ተጓዘ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ሁኖ ጎዳናውንም እንደሚጠርግለት አምኖ ሲጓዝ የሰውና የአራዊትን ፍለጋ አገኘ ያንንም ፍለጋ ተከትሎ ከቅዱስ ጳውሊ በዓት ደረሰ በሩንም አንኳኳ የከበረ አባ ጳውሊ ግን ከሰይጣን ሥራ እንደሆነ አስቦ ታላቅ ደንጊያ ወስዶ ከመዝጊያው ጀርባ አኖረ አባ እንጦንዮስም "ይሰጠኝ ዘንድ ፈለግሁ አገኝ ዘንድ ለመንኩ ይከፈትልኝም ዘንድ ቡሩን አንኳኳሁ" ብሎ አሰምቶ ተናገረ። በዚያንም ጊዜ ከፈተለትና ገባ እርስ በርሳቸውም በመንፈሳዊ ሰላምታ አጅ ተነሣሥተው በአንድነትም ጸልየው ተቀመጡ።
❤ አባ እንጦንዮስም "አባቴ ሆይ ስምህ ማነው?" አለው አባ ጳውሊም "አንተ ስሜን ካላወቅህ እስከዚች ቦታ ለምን ተጓዝክ" ብሎ መለሰለት በዚያችም ሰዓት እግዚአብሔር የእንጦንዮስን ልቡን ገለጠለትና "ገዳማዊ ጳውሎስን አየው ዘንድ ስለተገባኝ እኔ ብፁዕ ነኝ" አለ ከዚህም በኋላ እርስ በእርሳቸው የእግዚአብሔርን ልዕልናውን ቸርነቱን ይነጋገሩ ጀመር በመሸም ጊዜ ቍራ መጥቶ አንዲት ሙሉ እንጀራ ጣለለት አባ ጳውሊም አባ እንጦኒን "አንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደሆንክ አሁን አወቅሁ እስከ ዛሬ ሰማንያ ዓመት በዚህ በረሀ ስኖር እግዚአብሔር ሁልጊዜ የሚልክልኝ ግማሽ እንጀራ ነበር እነሆ አሁን ምግብህን ላከልህ" አለው።
❤ ከዚህም በኋላ ተነሥተው የማዕድ ጸሎት ጸለዩ በልተውም እግዚአብሔርን አመሰገኑት መላ ሌሊቱንም ሲጸልዩ አደሩ። ነግቶ ፀሐይ በወጣ ጊዜም እርስ በርሳቸው ሰላምታ ተሰጣጡ አባ እንጦኒም "አባቴ ሆይ በዚህ ሁሉ ዘመን ሥጋውንና ደሙን ከወዴት ትቀበላለህ?" አለው የከበረ ጳውሊም "እግዚአብሔር መልአኩን ይልክልኛል በቀዳሚት ሰንበትና በእሑድ ሰንበት በየሳምንቱ ከሥጋውና ከደሙ ያቀብለኛል በዘመኑም ሁሉ እንዲህ ያደርግልኛል" ብሎ መለሰለት።
ማኅበረ ቅዱሳን ( Mahibere Kidusan):
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የ2017 ዓ.ም የጾመ ነነዌ የሰላምና የጸሎት አዋጅ መግለጫ
ሙሉ መልእክት የሚከተለው ነው፡፡
ጥር ፳፱/፳፻፲፯ዓ.ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የተላለፈ የምህላ ሱባዔ፡-
‹‹ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምህላ አስተጋብኡ ሕዝበ ሊቃውንተ ሕዝብ፤ ጾምን ቀድሱ፣ጉባኤውንም አውጁ፤ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ ኣምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ (ኢዩ ፩÷፲፬)
ሁላችንም እንደምናውቀው ያለንበት ዓለም የመከራ ዓለም ነው፣ መከራው በኛ ስሕተትና ክፋት የመጣና እየሆነ ያለ መሆኑም ይታወቃል፤ እኛ የምንፈጽመው ጥቃቅንና ትላልቅ ግብረ ኃጢአት እግዚአብሔርን እንደሚያስቈጣ በቅዱስ መጽሐፍ ተረጋግጦ ያደረ ነው፤ ለዚህም ከነነዌ ነዋሪ ሕዝብ የበለጠ ማስረጃ የለንም፤ የነነዌ ከተማ ነዋሪዎች በፈጸሙት ግብረ ኃጢአት እግዚአብሔርን አስቈጥተዋል፤ ድርጊታቸው እግዚአብሔርን የሚያስቆጣ ቢሆንም እሱ ምሕረቱን ማስቀደም ስለፈለገ በዮናስ በኩል አስጠንቅቆአቸዋል፤ የነነዌ ነዋሪዎችም በዮናስ በኩል የደረሳቸውን የንስሓ ጥሪ ወዲያውኑ ተቀብለው በምህላ፣ በጾም፣ በጸሎት ንስሓ ስለገቡ እግዚአብሔር ፍጹም ይቅርታ አድርጎላቸዋል፤
• የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን ልጆቻችንና ወገኖቻችን !
እኛ ሰዎች ዛሬም በየሰዓቱ ብቻ ሳይሆን በየደቂቃው እግዚአብሔርን የሚያስቆጣ አበሳ እንደምንፈጽም ማወቅ ኣለብን፣
አበሳውና ኃጢኣቱ ሲበዛ እግዚአብሔር እውነተኛ ዳኛ ነውና ወደ ዳኝነት ተግባሩ ይገባል፤ይህ ደግሞ በሰብአ ትካት በሰዶምና በጎሞራ ያስተላለፈውን ዳኝነት ያስታውሰናል፤ አሁን ያለንበት ዘመን ዓመተ ምሕረት በመሆኑ እግዚአብሔር ለጊዜው ቢታገሠንም በኃጢኣታችን የምንጠየቅበት ጊዜ አዘጋጅቶአል፤ ዛሬም ቢሆን የማናስተውለው ሆነን ካልሆነ በስተቀር እግዚአብሔር ተግሣጹን ማስተላለፍ አላቆምም፤ በምድራችን ላይ በምናደርሰው የተዛባ ተግባር በጐርፍ፣ በድርቅ፣ በመሬት መንቀጥቀጥና በአየር መዛባት እየገሠጸን እንደሆነ ማስተዋል አለብን፤
እግዚአብሔር ከጥንቱ ከጠዋቱ ጀምሮ ምድርን እንድንከባከባት፤ እንድናበጃት፣ እንድናጠብቃትና እንድናለማት አዞናል፤ ሆኖም ይህን ትእዛዙን ገሸሽ አድርገን በኬሜካልና በመርዛም ጋዝ ምድርን በመበከል፣ደንዋን በመመጠርና ራቁቷን በማስቀረት በምናደርገው ድርጊት አበሳ እየፈጸምን እንደሆነ ያወቅነው አይመስልም፤ በዚህም ምክንያት በጐርፍ፣ በድርቅ ለሰው ልጆች በማይመች የኣየር ፀባይ ወዘተ . . . ስጋት ውስጥ እየወደቅን ነው፤
በሌላም በኩል በምናወሳስበው የአስተዳደር ርእዮትና መሳሳብ የእግዚአብሔር ገንዘብ የሆነውን ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲጋጭና ያላስፈላጊ አደጋ ላይ እንድወድቅ እያደረግን ነው፤ በዚህም ጠንቅ ሰላም እየደፈረሰ፣ ፍቅርና አንድነት እየላላ የሃይማኖት ክብርና ልዕልና እየተነካ ራሳችንንም እየጐዳን ነው፤በዚህ ሁሉ ተግባራችን እግዚአብሔርን እያሳዘንን ነው፤ ይህ ሊገባንና ሊቈረቁረን ይገባል፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ አላቸው፤ መፍትሔውም የሚገኘው ከእግዚአብሔርና ከእኛ ነው፤ ከእኛ በንስሓ ተመልሰን ከልብ እግዚአብሔርን ይቅርታ መጠየቅና ከክፉ ተግባራችን በእውነት መጸጸት ይጠበቃል፤ እግዚአብሔር ደግሞ ይህንን ዓይነቱ ንስሓ ከኛ መኖሩ ሲመለከት ምሕረትና ይቅርታን ይለግሰናል፤በዚህም መፍትሔና ፈውስ ይገኛል፤ ከዚህ አንጻር በአሁኑ ጊዜ ለሀገራችንና ለዓለማችን ስጋት የሆኑ የጦርነት ክሥተቶች፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የአየር መዛባት፣የድርቅ መከሠት፣የጎርፍ መጥለቅለቅ የሰላም መደፍረስ፣ የሰላማውያን ወገኖች መጎዳት፣ የፍቅርና የአንድነት መላላት ወዘተ. . . . ከምድራችን ተወግደው ፍጹም ምሕረትና ሰላም እናገኝ ዘንድ በኃጢኣታችን ተጸጽተን በምህላ ንስሓ መግባት አለብን፤ ከዚህ አኳያ ከጥንት ጀምሮ በቤተክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዓት መሠረት በየዓመቱ የሚጾመው ጾመ ነነዌ ለዚህ አመቺ ጊዜ ስለሆነ ከየካቲት ፫ ቀን ፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ ለሦስት ቀናት ከልኂቅ እስከ ደቂቅ ሁላችንም ጠዋትና ማታ በየቤተክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት እየተገኘን በንስሓ በዕንባ በጸሎት በምህላ የእግዚአብሔርን ምሕረትና ይቅርታ እንድንጠይቅ፤ እንደዚሁም በሀገራችንና በውጭ ያላችሁ ሊቃውንተ ሕዝብ ቀኖናውን ጠብቃችሁ ይህንን በማስፈጸም ምህላውን በቀኖናው መሠረት እንድታከናውኑ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤
እግዚአብሔር አምላካችን ምሕረቱን ይቅርታውንና ሰላሙን ለሀገራችንና ለዓለማችን ይስጠን፤ ምህላችንንም ይቀበልልን፤
“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ” ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስምወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ጥር ፳፱ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ምንጭ:- EOTC Broadcasting Service Agency
“እግዚአብሔር ታላቅ፥ ምስጋናውም ብዙ ነውና፤ በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነው።”
— 1 ዜና 16፥25
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !!!
በዕለተ ሰንበት 02/06/2017 08:00 ሰዓት ልዩ የምስጋና መርሐግብር ስለተዘጋጀ ሁላችንም እንድንገኝ ላልሰሙትም በማሰማት ከዚህ በፊት ስዕለት የተሳልን ስለቱን በማስገባት እንዲሁም ያጠፋን የበደልን ካለን ይቅርታ በመጠያየቅ እንዲሁም ለቀጣዩ እዲያደርሰን በመሳል በፍቅር፣በይቅርታ፣በአንድነት አገልግሎታችንን አጠናክረን እንድንቀጥል እያልን ሁላችንም ያለን ነጭ ልብስ በመልበስ የሌለን ደሞ ንፁህ በመልበስ እንድንገኝ በቅዱስ እግዚአብሔር ስም እናሳስባለን።
❤ ከዚህም በኋላ የከበረ ሰራብዮንን ወደ አገሩ ከእርሱ ጋር ወስዶ ያሠቃየው ዘንድ ከኀሳቡም ካልተመለሰ ራሱን በሰይፍ ይቆርጥ ዘንድ ኄሬኔዎስ አንዱን መኰንን አዘዘው። መኰንኑም ከርሱ ጋር በመርከብ ወሰደው ሌሊትም በሆነ ጊዜ ወደ አንድ ወደብ ደርሰው በዚያ ተኙ በእግዚአብሔርም ፈቃድ ያቺ መርከብ ወደ ቅዱስ ሰራብዮን አገር ደረሰች በጥዋትም በነቁ ጊዜ የመሔጃቸው አቅጣጫ ተለውጦ አገኙ እጅግም አደነቁ ወደ ሰራብዮንም "እነሆ ይቺ አገርህ ናት" የሚል ቃል ከሰማይ መጣ ከመርከብም አውርደው ታላቅ ሥቃይን አሠቃይተው ጥር27 ቀን ራሱን በሰይፍ ቆረጡት በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ። መኰንኑም ልብሶቹን አውጥቶ ገንዞ ለዘመዶቹ ሰጠው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ በቅዱስ ሰራብዮን በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #ሰማዕቱ_ቅዱስ_ቢፋሞን፦ ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ድንግል የሆነ እግዚአብሔርን የሚወድ ለድኆችና ለችግረኞች የማሚመጸውት ይህንንም ዓለም ንቆ የተወ ነው። አባቱም ከከበሩ ወገኖች የሆነ ስሙ አንስጣስዮስ የእናቱም ስም ሶስና ነው። እነርሱም መመጽወትን የሚወዱ ክርስቲያኖች ናቸው የጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የእመቤታችንን ድንግል ማርያምን የከበሩ ሰማዕታትንም ሁሉ በዓላት ለድኆችና ለምስኪኖች ምጽዋትን በመስጠት ያከብራሉ የሚኖሩትም በምስር አውራጃ አውሲም በሚባል አገር ውስጥ ነው።
❤ እግዚአብሔርም ደግነታቸውን ተመልክቶ መልኩ እጅግ ያማረ ልጅ ቅዱስ ቢፋሞንን ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ገና ሲወልድ ጀምሮ ብዙ ተአምራት አድጎላቸዋልና እጅግ አላቸው፡፡ በሃይማኖት በምግባር ኮትኩተው አሳደጉት፡፡ ዘጠኝ ዓመትም በሆነው ጊዜ ሃይማኖትንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንዲማር ለአንድ መምህር ሰጡት፡፡ ከመምህሩም ዘንድ ጥበብንና ተግሣጽን የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍት ሁሉ አጠና፡፡ ከልጅነቱም ጀምሮ በጾም በጸሎት በስግደት ይጋደል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለቅዱስ ቢፋሞን ገና በልጅነቱ በእጆቹ ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን የማድረግ ጸጋ ሰጠው፡፡ በቁስል ደዌ እጆቹንና እግሮቹን የታመመ አንድ ድኃ ቅዱስ ቢፋሞንን ምጽዋት ቢለምነውና ቅዱሱም በእጆቹ ቢነካው ወዲያው ከደዌው ድኖ ጤነኛ ሆነ፡፡
❤ ሁለተኛም በሌላ ጊዜ በቅዱስ ዳዊት መዝሙር ሲያመሰግን ከዚያ አንድ ጋኔን የሚጥለው ሰው ነበረና "የእግዚአብሔር ቅዱስ ሆይ ተወኝ፣ ከዚህ ቦታ ልጥፋ" ብሎ ጮኸ፡፡ ቅዱስ ቢፋሞን ወደ ጌታችን ጸልዮ ያንን ጋኔን ያደረበትን ሰው አዳነው፡፡ መምህሩም ይህን አይቶ በዚህ ሕፃን ልጅ ያደረውን ጸጋ አደነቀ አከበረውም፡፡ በመምህሩም ዘንድ 8 ዓመት ኖረ፡፡ ጌታችንም ቅድስት እናቱን ድንግል ማርያምንና ቅዱሳኑን እያስከተለ እየመጣ ይገለጥለት ነበር፡፡
❤ ቅዱስ ቢፋሞን በየሰባት ቀን በመጾም ተጋድሎውን ጨመረ፡፡ ከሰንበት በቀር አይበላም ነበር፡፡ ዕድሜው ከፍ ሲል ወላጆቹ ሚስት ሊያጋቡት አሰቡ፡፡ እርሱ ግን "በዚህ እንደጤዛ በሚያልፍ ዓለም ከሴት ጋር መኖር ለእኔ ምኔ ነው? ፍላጎቱም ዓለሙም ሁሉም ያልፋል" አላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ በሰባተኛው ወር አባቱ ሲያርፍ ቅዱስ ቢፋሞን ንብረቱን ሁሉ አውጥቶ ለጦም አዳሪዎች ሰጣቸውና በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተጠመደ ሆነ፡፡ በዚያም ወራት የፋርስ ሰዎች በሮም ሰዎች ላይ ጦርነት አስነሥተው ነበር፡፡ የሮሙ ንጉሥ በጦርነቱ ስለሞተ ሮም ያለንጉሥ ቀረች፡፡ መኳንንቱና የመንግሥት ታላላቅ ሰዎችም ተሰብስበው ከአገሮች ሁሉ ተዋጊዎች የሆኑ አርበኞችን ይሰበስቧቸው ዘንድ በየአገሩ አዘዙ፡፡ ከላይኛው ግብፅ ልበ ደንዳና የሆነ ስሙ አግሪጳዳ የሚባል ሰይጣን በልቡ ያደረበት ፍየል ይጠብቅ የነበረ ኃይለኛ ሰው ተገኘ፡፡ እርሱንም ወደ አንጾኪያ አገር ወስደው የፈረሶች ባልደራስ አድርገው ሾሙት፡፡
❤ በአንዲት ዕለትም ሸንበቆ አንሥቶ ዋሽንት ሠርቶ ሲነፋ በፈረሶቹ ላይ ሰይጣን አደረባቸውና ፈረሶቹም እያሽካኩ ይጨፍሩ ጀመር፡፡ በጦርነት የሞተው ንጉሥ ሴት ልጅም በቤተ መንግሥት አዳራሽ ሆና ሲዘፍንና ዋሽንት ሲነፋ አግሪጳዳን አይታ ወደደችው፡፡ ሰይጣንም በልቧ የዝሙትን ፍላጻ ጨመረባትና ወደ እርሷ አስመጣችውና አገባችው፡፡ ስሙንም ዲዮቅልጥያኖስ ብላ ሰየመችውና አነገሠችው፡፡ ታናሽ እኅቷም በእርሷ ቀንታ መክስምያኖስ የሚባለውን አንዱን መኮንን መልምላ አገባችና ልብሰ መንግሥት አልብሳ አነገሠችው፡፡ መክስምያኖስና ዲዮቅልጥያኖስም በአንጾኪያና በሮም ተስተካከለው ነገሡ፡፡
❤ ከዚህም በኋላ ሰይጣን ተገለጠላቸውና እንዲህ አላቸው፡- "በንጉሡ ሴቶች ልጆች ላይ የዝሙትን ፍቅር በልባቸው ላይ አሳድሬ እንዲወዷችሁና እንዲያገቧችሁ ያደረኩት እኔ ነኝ፤ አሁንም ትእዛዜን ከሰማችሁ በምድር የሚኖረውን ሕዝብ ሁሉ በእጃችሁ ውስጥ አደርግላችኋለሁ፤ እናንተም ስገዱልኝ የብርና የወርቅ ምስልም ሠርታችሁ አማልክት በሏቸው፡፡ ስማቸውንም አጵሎን አርዳሚስ ብላችሁ ጥሯቸው፡፡ ሰዎችም ሁሉ ዕጣን እንዲያሳርጉላቸውና እንዲሰግዱላቸው እዘዙ፤ ያልሰገዱላቸውንም ራስ ራሶቻቸውን በሰይፍ ቁረጡ፤ ይህን ካደረጋችሁ መንግሥታችሁን አሰፋላችኋለሁ ካለዚያ ግን መንግሥታችሁ ታልፋለች" አላቸው፡፡ እነዚህም ሁለት ሰነፎች መክስምያኖስና ዲዮቅልጥያኖስም ለሰይጣን ሰገዱለትና "ያዘዝከንን ሁሉ እናደርጋለን ብቻ መንግሥታችንን አጽናልን" አሉት፡፡ በዚህም ጊዜ ኄሬኔዎስንና አርያኖስን በግብጽ አገር ላይ መኳንንት አድርገው ሾሟቸው፡፡ ለጣዖት የማይሰግዱትን ሁሉ እንዲገድሉ አዘዟቸው፡፡ የከበረ ቅዱስ ቢፋሞንም ይህንን ትእዛዝ በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ፡፡ ወዳጁን ቴዎድሮስን ጠራውና በክብር ባለቤት በጌታችን ስም ደማቸው አፍስሰው ሰማዕት ይሆኑ ዘንድ በምክር ተስማሙ፡፡
❤ የቅዱስ ቢፋሞን ዜናው በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነውና ወሬው ከሃዲው ንጉሥ መክስምያኖስ ዘንድ ተሰማ፡፡ መኳንንቶቹም "በምስር አውራጃ በአውሲም ከተማ የሚኖር ስሙ ቢፋሞን የሚባል ሰው አለ፣ እርሱም የነገሥታትን ትእዛዝ የሚተላለፍ አማልክትን የሚረግምና የሚያቃልል ነው" ብለው ለንጉሥ መክስምያኖስ ነገሩት፡፡ በዚህም ጊዜ ንጉሡ ቅዱስ ቢፋሞን ለአማልክት ካልሰገደ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጠው ትእዛዝ ጽፎ ለጨካኙ መኮንን ለአርያኖስ ላከለት፡፡ ደብዳቤውም ከመኮንኑ ዘንድ ሳይደርስ የታዘዘ የእግዚአብሔር መልአክ ለቅዱስ ቢፋሞን ተገልጠለትና በሰማዕትነት እንደሚሞት እናቱና አገልጋዩ ዲዮጋንዮስም አብረውት እንደሚሞቱ ከነገረው በኋላ ሰማዕትነቱን በትዕግስት እንዲፈጽም ነገረው፡፡ የተዘጋጀላቸውንም የክብር አክሊላት አሳየው፡፡ ቅዱስ ቢፋሞን ተነሥቶ ለእናቱ መልአኩ የነገረውን ነገራት፡፡ መልአኩ ለእርሷም ተልጦ ይህንኑ እንደነገራት ለልጇ ነገረችውና ለሰማዕትነት በመመረጣቸው በአንድነት እጅግ አላቸው፡፡ ሲጸልዩ አደሩና በነጋታው ቅዱስ ቢፋሞን ወዳጁን ቴዎድሮስን አስጠራውና ሁሉን ነገረው፡፡ ቀጥሎም "የመከራው ጊዜ ካለፈ በኋላ አንተ በዚህች አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ትሾማለህ ያንጊዜም በስሜ ቤተ ክርስቲያን ትሠራለህ" ብሎ ትንቢት ነገረው፡፡ ወዲያም ሰላምታ ተሰጣጡና ተሳስመው ተለያዩ፡፡
ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta):
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አሜን"። ❤
❤ #ጥር ፳፯ (27) ቀን።
❤ እንኳን #ሳፍራ_ለሚባል_ለመልአክ_ለቅዱስ_ሱርያል ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል፣ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ በሞት ፋንታ ለተሰውረው #ለነቢዩ_ቅዱስ_ኄኖክ ለዕርገቱ መታሰቢያ በዓል፣ ለከበረ ሐዋርያ #ለቅዱስ_ጢሞቴዎስ ከኤፌሶን አገር ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ ለሥጋው ፍልሰት በዓል፣ ከግብጽ ደቡብ ከታችኛዪቱ ምስር አውራጃ በብኑዲ ከምትባል መንደር ለሆነ ለከበረ #ቅዱስ_ሰራብዮን ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል፣ ከታናሽነቱ ድንግል ለሆነ እግዚአብሔርን ለሚወድ ለድኆችና ለችግረኞች ለሚመጸውት ይህንንም ዓለም ንቆ ለተወ በእሳት ተቃጥሎ ሰማዕትነት ለተቀበለ ለከበረ #ቅዱስ_ቢፋሞን ለዕረፍቱ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከቸሩ_መድኃኔዓለም_ከስቅለቱ ከወራዊ መታሰቢያ፣ #ከሰማዕታት_ትውፍሎን_ከዮስና_ከሰርኒስ ከመታሰቢያቸው ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ በዚች ቀን #ሳፍራ_የሚባል_የመልአክ_ሱርያል በዓል ነው እርሱም #ከነቢይ_እዝራ ጋር የኖረ የተሠወረ ምሥጢርንም የገለጠለት ነው እርሱም ስለ ሰው ልጆች ወደ እግዚአብሔር የሚለምን ነው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሱርያል አማላጅነት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ በዚችም ዕለት #የያሬድ_ልጅ_ኄኖክን የመላልኤል ልጅ #የቃይናን_ልጅ_የኄኖስ_ልጅ_የሴት_ልጅ #የአዳም_ልጅ_ኄኖክን_መላእክት ይዘው አሳረጉት ይኸውም በመባርቅትና በነፋሳት ላይ ተጭኖ በመብረር ወደ ሰማይ ወስደው ከረቂቃን መላእክት ጋር አኖሩት የእግዚአብሔርም ትእዛዝ ጸሐፊ ተባለ።
❤ እንዲህም አለ "ከማደሪያው ከሚወጣው ከቅዱሱና ከገናናው በጸናች ኃይሉ ከሠራዊቱ ጋር በሲና ተራራ ከሚገለበጠው ጋር በመነጋገር ተመላለስኩ። ሁሉም ይፈሩ ነበር በውኃ ዳርም ሳለሁ የልመናቸውን መታሰቢያ ጻፍኩ እስከ አንጎላቸሁና ሕልም እንደሚያይ እስከምሆን ይችም በአርሞን ግራና ቀኝ ያለች አገር ናት"። በደብር ቅዱስ ለነበሩ ለኃጢአት ለሚተጉ ለሴት ልጆች ይዘልፋቸው ዘንድ ቃል እንደጠራውና እንዳሳየው ተናገረ።
❤ እንዲህ አለ "በበረድ ደንጊያ ወደ ተሠራ ታላቅ ቤት ቀረብኩ በበረድ ደንጊያ የተሠራ የዚያ ቤት ግድግዳ እንደ ሳንቃ ልዝብ ነው ከዚህ ቤት የሚበልጥም ሌላ ቤት አየሁ ደጃፉም የተከፈተ ነው በእሳት ቅጽርም የተሠራ በክብር ከሁሉ የሚበልጥ ነው። በውስጡም ከፍ ያለ የእግዚአብሔርን ዙፋን አየሁ መልኩም እንደ ውርጭ ነው አጎበሩም እንደሚያበራ ፀሐይ ነው ከዙፋኑም በታች የኪሩቤል ድምፅ ይሰማል። ዳግመኛም ወደ ሰባት ተራራዎች ደረስኩ ሦስቱ በምሥራቅ በኵል ሦስቱ በአዜብ በኵል ናቸው የመካከለኛው ግን ሰማይ ጠቀስ ነው የመላእክትም ጌታ በላዩ አለ"። ሌሎች አራት ገጾች ኪሩቤልን አየ ስለ ክርስቶስም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ "የዘመናት አለቃ ወደ ሆነው የሰው ልጅ ተጠራ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ የነበረ ሆነ" ሁለተኛም "ለጻድቃን የጽድቅ በትር ለአሕዛብም ብርሃን ተስፋ ለሌላቸወሰ አለኝታ ይሆናል" አለ።
❤ በሰማይ ገጽ ስለሚመላለሱ ብርሃናት እንዲህ አለ "አንዱም አንዱ በየወገናቸው በሠለጠኑበትና በተሠየሙበት ጸንተው ይኖራሉ" ስለ ነፋሳትም መውጫዎች እንዲህ ብሎ ተናገረ "ሦስቱ በሰማይ ገጽ ሦስቱ በምድር ገጽ ሦስቱ በግራ ናቸው"። ስለ አዳምም እንዲህ አለ "እነሆ በሬ ከምድር ወጣ ፀዓዳም ሆነ" ስለ ሔዋንም "ሴት እምቦሳ ከርሱ ወጣች" አለ።
❤ ስለ ምኵራብም "ያንን አሮጌ ቤት እስከሚአሳንሰው ድረስ አየሁ አለ ምሰሶዎቹንም ከውስጡ አወጣ"። ስለ ቤተ ክርስቲያንም "ጌንን አሮጌ ቤት እስከሚአሳንሰው ድረስ አየሁ አለ ምሰሶዎቹንም ከውስጡ አወጣ"። ስለ ቤተ ክርስቲያንም "ጌታ አዲስ የበጎች ቤት አምጥቶ እስቲሠራ ድረስ አየሁ ከቀድሞውም ቤት የበለጠ ነው በጎችም ሁሉ በውስጧ ይሠማራሉ" አለ። ስለ ምእመናንም "የእሊህም በጎች ፀጒራቸው ንጹሕ ነጭ ነው የተበተኑትም ከአራዊት ጋራ ይሠማራሉ ሁሉም በአንድነት ተሰብስበው ገራሞች ሁነዋልና"። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ኄኖክ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #የሐዋርያው_ቅዱስ_ጢሞቴዎስ ከኤፌሶን አገር ወደ #ቊስጥንጥንያ_ከተማ_የሥጋው_ፍልሰት፦ ጻድቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስም መንግሥትን በያዘ ጊዜ የከበሩ የሐዋርያትን ሥጋቸውን ከሰማዕታትም ብዙዎችን ከቦታቸው ሁሉ ወደ ቊስጥንጥንያ አፈለሳቸው ስለ ሐዋርያ ጢሞቴዎስም ሥጋ በኤፌሶን አገር እንዳለ ሰምቶ ካህናትንና ምእመናንን ላከ እነርሱም አፍልሰው ወደ ቊስጥንጥንያ አድርሰው በከበሩ ሐዋርያት ቤተ መቅደስ ውስጥ አኖሩት። በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #ሰማዕቱ_ቅዱስ_ሰራብዮን፦ ይህም ቅዱስ ከግብጽ ደቡብ ከታችዪቱ ምስር አውራጃ በብኑዲ ከምትባል መንደር ነው። ቅዱሱም ብዙ የገንዘብ ጥሪት እንስሳትም አሉት አብዝቶ መመጽወትንም የሚወድ ነው ስደትም በሆነ ጊዜ የክርስቲያን ወገኖችን ፈልጎ ያሠቃይ ዘንድ መኰንኑ ኄሬኔዎስ በየአገሩ እንደሚዞር ሰማ ለርሱም ስማቸው ቴዎድሮስና ሁለተኛውም በግ አርቢ ሰርማ የሚባሉ ወዳጆች ነበሩት እነርሱም ተከተሉት ይህም ቅዱስ መኰንኑን ሊገናኘው ከአገሩ ወጣ መኲንኑንም በአገኘው ጊዜ በፊቱ ቁሞ ከወገኖቹ ጋር በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ መኰንኑም ሁሉንም አሠራቸው።
❤ የአገር ሰዎችም በሰሙ ጊዜ ሁሉንም ተሰበሰቡ መኰንኑን ገድለው ቅዱስ ሰራብዮንን ከእጁ ሊወስዱ ሽተው የጦር መሣሪያ በመያዝ ለጦርነት የተሰለፉ ሠራዊት ሁነው ደረሱ ቅዱሱ ግን ከለከላቸው እንዲህም አላቸው "እኔ በጌታዬ ክርስቶስ ስም ደሜን አፈስ ዘንድ በፈቃዴ የመጣሁ አይደለምን" መኰንኑም በመርከብ ተሳፍሮ ከዚያ ሔደ ቅዱሳኑም አብረውት ሔዱ። ወደ እስክንድርያ አገርም በደረሰ ጊዜ የከበረ ሰራብዮንን በመንኰራኵር ውስጥ ጽኑዕ ሥቃይ እንዲአሠቃዩት ወደ እሳት ማንደጃም ይጨምሩት ዘንድ አዘዘ። ከዚህም በኋላ ከነዳጅ ድፍድፍና ቅመማ ቅመም ጋር በወጭት ውስጥ ቀቀሉት የሥጋውንም ሥሮች ቆረጡ በብረት ዐልጋ ላይም አስተኝተው በችንካር ቸነከሩት ይሁን ሁሉ ሥቃይም የሚታገሥ ሆነ የእግዚአብሔርም መልአክ ሥቃዩን ከላዩ ይቀበልለት ነበር።
❤ ከዚህም በኋላ ከእንጨት ላይ ሰቅለው በፍላፃዎች ነደፉት የእግዚአብሔርም መልአክ እርሱን ከተሰቀለበት አውርዶ በእርሱ ፈንታ መኰንኑን አሥሮ ሰቀለው። የከበረ ሰራብዮንም እንዲህ አለው "ሕያው እግዚአብሔርን በክርስቶስ ስም የታሠሩትን ሁሉንም እስከምታወጣቸውና የሞታቸውን ፍጻሜ እስከምታዝዝ አንተ ከእዚህ ከተሰቀልክበት ዕንጨት እንደማትወርድ ዕወቅ"። በዚያንም ጊዜ ሁሉንም አውጥተው ራሷቻቸውን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጧቸው የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ የእሊህም ሰዎች ቊጥራቸው አምስት መቶ አርባ ነፍስ ሆነ።
