ru
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

Открыть в Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

Больше
613
Подписчики
+124 часа
-17 дней
-1030 дней
Архив постов
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤             ❤ #ሐምሌ ፲፯  (17) ቀን። ❤ እንኳን  ለየዋሁ ነቢይ #ለቅዱስ_ዮናስ ከዓሣ ዐንበሪ ሆድ ውስጥ ለወጣበት ቀን መታሰቢያ በዓልና #ለቅድስት_አውፎምያ_ሰማዕትነት_ለተቀበለችበት ለዕረፍቷ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከቅዱሳን_ኤስድሮስና ከሰማዕቱ #ቤዱል፣ #ከዘካርያስና_ከአውልያን_ከዐይነ_ፀሐይ ከመታሰቢያቸው ከቅዱስ ሰማዕት #ከዮስጦስም ዐፅሙ ከተገኘበት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅድስት_አውፎምያ፦ ይቺም ቅድስት በርሴፎስ የሚባል ከዲዮቅልጥያኖስ መኳንንቶች አንዱ አሠቃያት። የታሠሩ ሰማዕታት በሚያልፉ ጊዜ በአንገታቸው የሚከብዱ ሰንሰለቶች ነበሩ። እንደ ውሾችም ይጎትቷቸው ነበር። ግፋቸውንም ባየች ጊዜ ይቺ ቅድስት አለቀሰች ልቡናዋም ክብር ይግባውና በክርስቶስ ፍቅር ተቃጠለ ዲዮቅልጥያኖስንና የረከሱ አማልክቶቹንም ረገመች። ያንንም መኰንን እንዲህ ብላ ዘለፈችው። "ርኅራኄ የሌለህ ልብህ እንደ ደንጊያ የሆነ ለእኒህ ቅዱሳን ሰዎች አትራራምን ፈጣሪያቸውስ እንዲያጠፋህ አትፈራንምን"። ❤ መኰንኑም ሰምቶ ወደርሱ ያቀርቡአት ዘንድ አዘዘ። ስለ ሃይማኖቷም ጠየቃት እርሷም ክርስቲያን እንደሆነች በፊቱ አመነች። በየአይነቱ በሆነ ሥቃይ በግርፋትና በስቅላት ታላቅ ሥቃይን አሠቃያት። ❤ ከዚህ በኋላ በእሳት ምድጃ ውስጥ ጨመሩዋት ነገር ግን ከሥቃዩ የተነሣ ምንም ጉዳት አልደረሰባትም። በዚያን ጊዜሜ በእሳቱ መካከል ቆማ ጸለየች ፊቷንና መላ ሥጋዋንም በመስቀል ምልክት አማተባ ነፍሷን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት አውፎምያ በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 17 ስንክሳር።                             ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ዕብል_ለአውፎምያ_ኅሪት። ክበደ ሰናስል ነጺራ በክሣደ ሰማዕት። ወሶበ ነደ ልባ በአምላካዊ ቅንዓት። መቅሠፍት ኢያፍርሃ ወኢያደንገፃ ስቅለት። ወለኪፎታ ኢክህለ እሳት"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_17።                                ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወአይቴ እጎይይ እምቅድመ ገጽከ። እመኒ ዐረጉ ውስተ ሰማይ ህየኒ አንተ። ወእመኒ ወረድኩ ውስተ ቀላይ ህየኒ ሀሎከ"። መዝ 138፥7-8። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 2፥1-12፣ 1ኛ ጴጥ 2፥1-11 እና የሐዋ ሥራ 26፥1-11። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 12፥38-43። የሚቀደሰው ቅዳሴ የወልደ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ ጻድቁ ከበዓታቸው ጣና ዘጌ ተነስተው አቡነ ሐራ ድንግልን እየሄዱ ይጎበኟቸው እንደነበር በአቡነ ሐራ ድንግል ገድል ላይ ተጽፏል። አቡነ በትረ ማርያም ከበዓታቸው ወጥተው ወደ ሌላ ቦታ የሚሔዱት ለምነው ለነዳያን የሚሰጡትን ለመሰብሰብ ሲፈልጉና ገዳማትን ተሳልመው የቅዱሳንንም በረከት ለመቀበል ሲፈልጉ ብቻ ነበር። ቅዱሳንን ጎብኝተው ወደ ገዳማቸው ዘጌ የሚመለሱትም ለነዳያን የሚሰጡትን ከሰበሰቡ በኋላ ነው። ለነዳያን የሚሰጡትን ገንዘብ የሚሰበስቡትም እንደባርያ እየተሸጡ ለፈረስ ሳር በማጨድና የመንገደኞችን ዕቃ በመሸከም የሚከፈላቸውን ገንዘብ በማጠራቀም ነበር። "ላጡ ለድኆች የሚሆን ምግብ ለማግኘት ሲሉ ለፈረስና ለበቅሎ ሣር ያጭዱ ዘንድ ባሪያ ሆነው የተሸጡበት ጊዜ አለ። ከባለጸጋ ቤት ቁራሽ እንጀራን ተቀብለው ለድኆች ይሰጡ ዘንድ በባለጸጋው ደጅ ከድኆች ጋር ተቀምጠው የሚለምኑበት ጊዜም ነበር። በመንገድ የሚያልፉ ሰዎችን ዕቃቸውን ይሸከሙ ዘንድ በመንገድ የሚቆሙበት ጊዜም ነበር" በማለት ገድለ አቡነ ሐራ ድንግል የአቡነ በትረ ማርያምን የትሩፋት ሥራ ይነግረናል። ❤ አቡነ በትረ ማርያም ድንቅ ድንቅ ተኣምራትን በማድረግ ይታወቃሉ። ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አባታችን ከመነኰሳት ልጆቻቸው ጋር በገዳማቸው ሳሉ በህርመት የሚኖሩ መሆናቸውን የሰማ አንድ መነኵሴ ከሩቅ መጣና እንደገዳሙ ሥርዐት በእንግዳ ቤት ተቀመጠ። መነኰሳቱም የጸሎተ ማዕድ አድርሰው እንደመነኰሳቱ መቁነኑን ለእንግዳው ሰው አደሉት። መነኵሴው ግን መቁነኑን ሳይበላው ደብቆ ይዞ በአኩፋዳው ውስጥ ከተተው። በልቡም "እነዚህ መነኰሳት የሚመገቡት ይኸንን ነው" ብዬ "ለሀገሬ ሰዎች ማሳየት አለብኝ" ብሎ አሰበ። ወዲያም በአኩፋዳው የደበቀውን መቁነን ሰውሮ ይዞ ለመሔድ ሲነሣ ቡራኬ ሊቀበልና ሊሰናበት ከአቡነ በትረ ማርያም ፊት ቆመ። አባታችንም ሰውዬው ደብቆ የያዘውን መቁነን በመንፈስ ቅዱስ ዐወቁበትና "…ይኸ እንግዳ እኛ የሰጠነው እንደሆነ ክብራችንን ከገዳሙ ውጭ አውጥቶ ሊገልጽ አይገባም፣ ይኽንን ይበላሉ እያለ ሊገልጽብን ነው" አሉ። ዳግመኛም የየራሱ የሆነው ይባረክለት የገዳሙ መቁነን የሆነው ግን ከይሲ ይሁን" በማለት እንደተናገሩ ወዲያው ከአኩፋዳው ውስጥ ሰባት ክንድ የሚሆን እባብ ራሱን ከአኩፋዳው ውስጥ ብቅ አደረገ። በዚኸም ጊዜ እንግዳው ሰውዬ እጅግ ደንግጦ ከአባታችን እግር ሥር ወድቆ "በድያለሁ፣ ኀጢአት ሠርቻለሁ፣ ይቅር በሉኝ" እያለ የሠራውን ሁሉ እየተናዘዘ ይቅርታ ያደርጉለት ዘንድ ለመናቸው። አቡነ በትረ ማርያምም "እግዚአብሔር ይቅር ይበልህ ዳግመኛ እንዳትበድል" አሉትና ወደመጣበት መለሱት። ❤ አቡነ በትረ ማርያም መልካሙን ተጋድሏቸውን ፈጽመው ሩጫቸውን ጨርሰው የዕረፍታቸው ጊዜ ሲደርስ የክብር ባለቤት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እልፍ አእላፋት ቅዱሳን መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ ተገለጠላቸውና "ወዳጄ በትረ ማርያም ሆይ! በዚኽች ዕለት ከኀዘን ወደ ደስታ፣ ከሕመም ወደ ሕይወት ልወስድህ ነፍስህንም አሳርፋት ዘንድ መጣሁ፤ ቦታህን እንደ ኢየሩሳሌም አደረግሁልህ፤ በስምህ ቤተ ክርስቲያን የሠራ፣ ዕጣን የሰጠውን መብዓ ያቀረበውን፣ ሥጋህ የተቀበረበትን ዐፅምህ ያረፈበትን ገዳመ ዘጌን የተሳለመውን፣ ወንዱ በ40 ቀን ሴቷ በ80 ቀን ጥምቀተ ክርስትና የተቀበለውን፣ በቦታህ ቅዱስ ሥጋዬን ክቡር ደሜን የተቀበለውን፣ በስምህ ገድልህን የጻፈውን፣ ዐይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን ልብ ያላሰበውን እንደ አንተ ላሉት አባቴ ያዘጋጀውን አወርሰዋለሁ። በገዳመ ዘጌ ላይ መብረቅና ነጎድጓድ፣ በምድር የሚሳቡ በመርዛቸው ሰውን የሚጎዱ እባቦች፣ በእግራቸው የሚሽከረከሩ አራዊቶች ሁሉ በዘጌ የሚኖረውንና በአንተ ያመነውን አይጣሉ (አይጉዱ)፣ በገዳሙ የሚኖሩ መነኰሳትና ምእመናን እንደ መላእክት ኃጢአት የሌለባቸው ይሁኑ፣ ደምህ ከፈሰሰበት ከገዳመ ዘጌ መቃብርህ ላይ አፈር ቆንጥሮ የተቀባ ከሕማሙ ይፈወስ፣ መቃብርህን እጅ የነሣ የእኔን መቃብር እጅ እንደነሣ ይሁንልህ" በማለት አስደናቂ የምሕረት ቃልኪዳን ከገባላቸው በኋላ ዐሥራ ኹለት የክብር አክሊላትን ካቀዳጃቸው በኋላ ጌታችን በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ። ❤ አባታችንም ከዚህ በኋላ መነኰሳት ልጆቻቸውን ሰብስበው የዕረፍታቸው ጊዜ መድረሱን ነግረዋቸው በመጨረሻው ዘመን ወደ ገዳሙ ክፉ ሰዎች ይመጣሉና ከእነርሱ ጋር አትጨመሩ… እያሉ ከመከሯቸውና ካስተማሯቸው በኋላ ረዳታቸውን አቡነ በርተሎሜዎስን በእርሳቸው ቦታ ከሾሙላቸው በኋላ በዕለተ ዐርብ ከቀኑ በሦስት ሰዓት በ89 ዓመታቸው ሐምሌ 17 ቀን በክብር ዐርፈው በዚያው በመሐል ዘጌ ተቀበሩ። ቅድስት ነፍሳቸውን ቅዱሳን መላእክት በምስጋና በማኅሌት ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አስገቧት። ጻድቁ ከዘጌ ጊዮርጊስ በስተ ምስራቅ አቅጣጫ በተቀበሩበት ቦታ ላይ ሌላ ቤተ ክርስቲያን የታነጸበት ሲሆን ከመካነ መቃብራቸው ላይ እየተወሰደ ለምእመናን የሚሰጠው እምነት በዘመናችንም ብዙ ድንቅ ድንቅ ተኣምራት እያደረገ ይገኛል። ከአባታችን ከአቡነ በትረ ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከት ያሳትፈን በጸሎታቸውም ይማረ አሜን። ምንጭ፦ በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን መጽሐፍ።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤             ❤ #ሐምሌ ፲፯  (17) ቀን። ❤ እንኳን  ለኢትዮጵያዊው ጻድቅ የረገጡት የጸለዩበት መሬትና ድንጋይ ሁሉ እምነት ሆኖ ብዙ ድውያንን ይፈውስ ለነበሩት፤ #በትራቸውም_በቆሙበት ቦታ ሁሉ በተኣምራት ከጎኑ #የወይን_ዘለላ_ፍሬ እያፈራ ይለቀም ለነበሩ ለታላቁ አባት #አቡነ_በትረ_ማርያም_ዘዘጌ ለዕረፍታቸው በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_አቡነ_በትረ_ማርያም_ዘዘጌ፦ በጣና ሐይቅ ደሴት ውስጥ ካሉት 37 ደሴቶች ውስጥ በአጠቃላይ 30 ያህል ጥንታዊ ገዳማት ይገኛሉ። ከእነዚኽም ውስጥ ሰባቱ በዘጌ ባሕረገብ መሬት ላይ የሚገኙ ናቸው። ከእነርሱም ውስጥ ዋነኛውና ቀደምቱ የመሐል ዘጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም ነው። ይኽንንም ገዳም በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት በ1264 ዓ.ም የመሠረቱት አቡነ በትረ ማርያም ናቸው። አቡነ በትረ ማርያምና ስድስቱ ወንድሞቻቸው ሰባቱ ከዋክብት ተብለው ይጠራሉ። እነዚህም ሰባቱ ከዋክብት ቅዱሳን እየራሳቸው ከገደሟቸው ጥንታውያን ገዳማት ውስጥ አቡነ በትረ ማርያም (መሐል ዘጌ ቅዱስ ጊዮርጊስን) ፣አቡነ ኂሩተ አምላክ (ዳጋ እስጢፋኖስን)፣ አቡነ ያሳይ (ማንዳባ መድኀኔዓለምን)፣ አቡነ ዘካርያስ (ደብረ ገሊላን)፣ አቡነ አፍቅረነ እግዚእ (ጒጒቤንና ጣና ቂርቆስን)፣ አቡነ ታዴዎስ (ደብረ ማርያምን) እና አቡነ ዘዮሐንስ (ክብራን ገብርኤልን) ገዳማትን ገድመዋል። ❤ የጻድቁን ገድል በአጭሩ ከገዳሙ ታሪክ ጋር አንድላይ ገዳመ ዘጌ ያሳተመው መጽሔት እንደሚገልጠው አቡነ በትረ ማርያም የትውልድ ቦታቸው ሸዋ ሙገር ነው። አባታቸው ቅዱስ ተክለ ማርያም እናታቸው ቅድስት ኢላርያ ይባላሉ። ወላጆቻቸውም በሕገ እግዚአብሔር ጸንተው የሚኖሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው። ነገር ግን እንደ ቅዱስ ኢያቄምና እንደ ቅድስት ሐና ልጅ ስላልነበራቸው የተባረከ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔርን ዘወትር በጾም በጸሎት ይለምኑት ነበር። ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ተኝተው ሳለ ቅድስት ኢላርያ ራእይ ተመለከተች። ቅዱስ ተክለ ማርያምም ተመሳሳይ ራእይ ተመልክቶ ኹለቱም ስላዩት ራእይ ተነጋግረው "የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን" አሉ። ❤ እግዚአብሔርም መልአኩን ልኮ ምዕመናንን ስቦ በወንጌል ጎዳና የሚመራ የተመረጠ ልጅ እንደሚወልዱ ነገራቸው። መልአኩም በነገራቸው መሠረት አቡነ በትረ ማርያም ነሐሴ 16 ቀን ተፀንሰው ግንቦት 21 ቀን ተወለዱ። የተወለዱትም አምላክን የወለደች ክብርት እመቤታችን በደብረ ምጥማቅ ለክርስቲያኑም ለእስላሙም በምትገለጥበት ዓመታዊ በዓል ላይ ስለሆነ አንድም ይረዳናል ምርኩዛችን ይሆናል ብለው ወላጆቻቸው ስማቸውን በትረ ማርያም አሏቸው። ❤ አቡነ በትረ ማርያም ሰባት ዓመት በሆናቸው ጊዜ ወላጆቻቸው ሃይማኖትን እንዲማሩ ወደ ደብረ ኤዎስጣቴዎስ አባታችንም ገዳም ላኳቸው። ትምህርታቸውን እየተማሩ ገዳማውያን አባቶችን ዕንጨት በመስበር በመቅዳትና ውኃ በሚያስፈልጋቸው ሁሉ እየተራዱ ብሉይንና ሐዲስን ተምረው አጠናቀቁ። በኋላም አስኬማ መላእክትን ከአቡነ ዜና ማርቆስ ተቀብለው ከጳጳሱም ዘንድ ሔደው ሥልጣነ ክህነትንና ቁምስናን ከተቀበሉ በኋላ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ የከበረች ወንጌልን ሰበኩ። ❤ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን ከሥዕለ ማርያም ፊት ቆመው ሲጸልዩ ክብርት እመቤታችን ተገልጣላቸው ሕሙማንን የሚፈውሱበት ጽዋ ሰጠቻቸው። በአንድ ወቅት የረኀብ ዘመን ሆኖ ሳለ አቡነ በትረ ማርያም ግን ለመንፈሳዊ ወንድማቸው የረኀቡን ዘመን ማሳለፊያ እንዲሆነው ብለው ጌታችን በተሸጠበት ዋጋ በሠላሳ ብር ተሸጠው በጉልበታቸው ሠርተው በማገልገል ለወንድማቸው የረኀብ ዘመን ማሳለፊያ ሆነዋል። በተሸጡበትም ቦታ በጉልበታቸው እያገለገሉ ሳለ የመኰንኑ ልጅ በጽኑ ሕመም ታማ ለሞት ስትደርስ አባታችን እመቤታችን በሰጠቻቸው ጽዋ ውኃ አድርገው ጸልየው አጥምቀው አድነዋታል። ❤ ከዚኸም በኋላ አቡነ በትረ ማርያም ከሸዋ ወደ ዳሞት (ጎጃም) አውራጃ ተሻግረው በጣዖት ያመልኩ የነበሩ ሰዎችን አስተምረው አጥምቀው በወንጌል ሕግ እንዲኖሩ በማድረግ ሐዋርያዊ አገልግሎት ፈጽመዋል። በጎጃም ካስተማሩ በኋላ ወደ ቤጌምድር ሔደው በዚያም በተጋድሎ እየኖሩ የከበረች ወንጌልን ሰበኩ። አባታችን የረገጡትና የጸለዩበት መሬትና ድንጋይ ሁሉ እምነት ሆኖ ብዙ ድውያንን ይፈውስ ነበር። በትራቸውም በቆሙበት ቦታ ሁሉ በተኣምራት ከጎኑ የወይን ዘለላ ፍሬ እያፈራ ይለቀም ነበር። በዚያም አካባቢ ጠበል አፍልቀው ብዙ ሕሙማንን እየፈወሱ ዜና ተአምራቸው በየቦታው ሲናገር ውዳሴ ከንቱን ሸሽተው ክብራቸው እንዳይታወቅ ወደ ምድረ ደንቢያ ሔዱ። ❤ አቡነ በትረ ማርያም በምድረ ደንቢያም ለስድስት ዓመት ምንም እህል ሳይቀምሱ በተጋድሎ እየኖሩ ወንጌልን እየሰበኩ ብዙ ሕሙማንን ፈወሱ። ከዚኸም በኋላ ከስድስት ወንድሞቻቸው ጋር ተገናኝተው በእግዚአብሔር ተእዛዝ ወደ ጣና መጡ። ሰባቱም ከዋክብት አንድ ላይ የጣናን ባሕር በእግራቸው ጫማ እየጠቀጠቁ ተሻግረው ዳጋ ደሴት ደረሱ። ከእነዚህ ሰባት ከዋክብት በፊት "አትማረኝ" እያሉ ይጸልዩ የነበሩት አባት ቀድመው ወደ ደሴቱ እንደገቡ ታሪካቸው ያስረዳል። አቡነ በትረ ማርያምም በዳጋ ደሴት ምንም ሳይቀምሱ የዐቢይ ጾምን ከጸሙ በኋላ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ተገልጦላቸው ዕጣ ክፍላቸው የሆነችውን ዛሬ ላይ ቤተ መቅደሳቸው የታነጸበትን ደሴት አሳያቸውና "የእስራኤልን ልጆች በሙሴ በትር የኤርትራን ባሕር እንዳሻገርኳቸው አንተንም በያዝካት በትር አሻግርሃለሁ" ካላቸው በኋላ በበትራቸው ባሕሩን ተሻግረው ዘጌ ምድር ደረሱ። በዚያም በአት አበጅተው በጸሎት ተወስነው በተጋድሎ ጸንተው ሲኖሩ ከእግራቸው ሥር ሕሙማንን የሚፈውስ ሙት የሚያስነሣ ዐይነ ሥዉራንን የሚያበራ፣ አጋንንትን የሚያወጣ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተኣምራት የሚያደርግ ፈዋሽ ጠበል ፈለቀ። ከየቦታው የሚመጡ ሕሙማንም በዚኽ ጠበል በአባታችን እጅ እየተጠመቁ የተፈወሱት በርካቶች ናቸው። ❤ አቡነ በትረ ማርያም በዘጌ ምድር እየተዘዋወሩ ሲያገለግሉ አሁን አዝዋ ማርያም ከምትባለው ቦታ የሥዕል ቤት አድርገው ሲጸልዩ ከንጉሥ ዓምደ ጽዮን የተላኩ መልእክተኞች መጥተው "አባታችን ወዴት ናቸው?" ብለው ሲጠይቁ በቦታው የነበሩ መነኰሳት "እዛ ናቸው" በማለት ስላመለከቱ ቦታዋ በዚያው አዝዋ ተባለች። አባታችን ከዘጌ አናት ተራራ ላይ አራራት ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ ሆነው በአራቱም ማዕዘን እየባረኩ የታቦተ ማርያምንና የታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት ይዘው "ለኖኅ የሰጠኸውን ቃልኪዳን አትርሳብኝ" በማለት እየባረኩ ይጸልዩ ነበር። ከዚኽም በኋላ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ በነጭ ፈረስ ላይ ሆኖ ተገለጠላቸውና እየመራቸው ጣና ባሕርን ተሻግረው መሐል ዘጌ አደረሳቸው። ❤ ከዚያም "እዚሁ ቦታ ላይ ቤተ ክርስቲያኔን ሥራ" ብሎ በፈረሱ ድንጋዩን ረግጦ እንደሰም አቅልጦ እንደጭቃ ረግጦ የፈረሱን ኮቴ ምስል አስቀመጠላቸው። አቡነ በትረ ማርያም የመሐል ዘጌን ቤተ ክርስቲያን ሲያንጹ ሳንቃዎቹ (መዝጊያዎቹ) በመንፈስ ቅዱስ ኀይል በነፋስ ተጭነው የመጡ ናቸው። ጻድቁም የመሐል ዘጌ ቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተ ክርስቲያን ሠርተው የጸሎት ልብሳቸውን እርሱም 25 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን ከብረት ሰንሰለት የተሠራው ቀሚሳቸውን ለብሰው ወደ ጣና ሐይቅ እየገቡ ጸሎት እያደረጉ ለ23 ዓመታት በእንዲህ ዓይቱ ጽኑ ተጋድሎ ኖረዋል።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤             ❤ #ሐምሌ ፲፮ (16) ቀን። ❤ እንኳን #ለቅዱስ_አባት_ወንጌሉ_ዘወርቅ ለተባለ ልክ እንደ ገብረ ክርስቶስ በእናት አባቱ ቤት እንደ ነዳይ ሆኖ ለተጋደለ #ለአባ_ዮሐንስ_ለዕረፍት_በዐል በሰላም አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ወንጌሉ_ዘወርቅ_የተባለው_ቅዱስ_አባት_አባ_ዮሐንስ፦ ይህም ቅዱስ ከሮሜ አገር ነበር አባቱም አጥራብዮስ የሚባል ባለጠጋ ነው። የእናቱም ስም ብዱራ ይባላል። እንዲማርም ለመምህር ሰጡት ቅዱሳት መጻሕፍትንም ተማረ። ❤ ከዚህም በኋላ ገበታው የወርቅ የሆነ ወንጌልን ያሠራለት ዘንድ አባቱን ለመነው አባቱም እንደፈለገው አሠራለት ሁል ጊዜም ያነበው ነበር። በሚያነብ ጊዜም አባቱና እናቱ ደስ ይላቸው ነበር። ❤ በዚያም ወራት ወደ ኢየሩሳሌም የሚጓዝ መነኵሴ ወደ እነርሱ መጣ በእነርሱም ዘንድ አደረ ከቅዱስ ዮሐንስም ጋራ ተነጋግሮ የምንኵስናን ሥራ አመሰገለት ይህን ዓለም እስከ ናቀና እንደ እርሱ መነኰስ ይሆን ዘንድ እስከ ወደደ ድረስ ልቡን ማረከው። ያን ጊዜም ያ መነኰስ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ ሁለተኛም ተመልሶ እንደ ልማዱ በእነርሱ ዘንድ አደረ። ቅዱስ ዮሐንስም መነኵሴው ወደ ገዳም ይወስደው ዘንድ ፈለገ መነኵሴውም "አባትህን እፈራዋለሁ ልወስድህ አይቻለኝም" አለው። ቅዱስ ዮሐንስም ከእርሱ ጋራ እንዲወስደውና ነፍሱን እንዲያድን አማለው። ❤ ከዚህም በኋላ በስውር ወሰደው በመርከብም ተጭነው ያ መነኰስ ወደሚኖርበት ገዳም ደረሱ የገዳሙም አበ ምኔት የወጣቱን ዮሐንስን መልኩን አይቶ አደነቀ። ቅዱስ ዮሐንስም የምንኵስናን ልብስ ያለብሰው ዘንድ አበ ምኔቱን ለመነው አበ ምኔቱም "ልጄ ሆይ የምንኵስና ሕግ እጅግ ጭንቅ ናት እኮ" አለው። አብዝቶም በለመነውና ግድ ባለው ጊዜ ራሱን ላጭቶ አመነኰሰው። ❤ ከዚህም በኋላ ከጾም ከትጋትና ከኀዘን የተነሣ ሥጋው ደርቆ አጥንቶቹ እስከ ሚታዩ ድረስ በብዙ ተጋድሎ ተጸመደ። አም ምኔቱም "ልጄ ሆይ ለሰውነትህ እዘን ድካምህንም ቀንስ መነኰሳቱም ሁሉ እንደሚሠሩት ሥራ" እያለ ያጽናናውና ይመክረው ነበር። ❤ በዚህ ተጋድሎም ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜ "ከእነርሱ በረከትን ትቀበል ዘንድ ከመሞትህ በፊት ወደ አባትህና እናትህ ሒድ" የሚል ራእይ አየ። ይህንንም ራእይ በሦስት ሌሊቶች ውስጥ አየ ለአበ ምኔቱም እንዴት እንዳየ ነገረው አበ ምኔቱም "ይህ ራእይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለ ሆነ ልትሔድ ይገባሃል" አለው። ❤ ከገዳሙም በወጣ ጊዜ አንድ ምስኪን ሰው ጨርቅ ለብሶ አገኘ። የእርሱንም ልብስ ሰጥቶት ጨርቁን ወሰደ። ወደ አባቱ ቤትም በደረሰ ጊዜ በትንሽ ጎጆ ውስጥ በአባቱ ደጅ በጾም በጸሎትና በስግደት እየተጋደለ ባሮች ከአባቱ ማዕድ የሚጥሉለትን ፍርፋሪ እየተመገበ ሰባት ዓመት ኖረ። እናቱም በአንጻሩ ስታልፍ የሚከረፋ ሽታው ያስጨንቃት ነበር። ❤ ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ "ከሰባት ቀን በኋላ ከዚህ ዓለም ትወጣለህ" ብሎ ነገረው። ያን ጊዜም ወደ እናቱ ልኮ ልምናውን ልትሰማ ወደ እርሱ መጣች ልጅዋም እንደሆነ ፈጥኖ አልነገራትም ነገር ግን በዚያች በታናሽ ማደሪያ ውስጥ በላዩ ባለ ጨርቅ እንድትቀብረው የለበሰውንም ጨርቅ እንዳትለውጥ አማላት። ከዚህም በኋላ ያንን የወርቅ ወንጌል ሰጣት። እንዲህም አላት "ይህን መጽሐፍ አንብቡ እኔንም አስቡኝ"። ❤ አባቱም በመጣ ጊዜ ያንን የወርቅ ወንጌል አሳየችው ለልጁ ያሠራለት ወንጌል እንደሆነ አወቀ። አባቱና እናቱም ወደ እርሱ ሔደው ስለ ልጃቸው ጠየቁት እርሱም "ከዚህ ጨርቅና ከዚህ ትንሽ ማደሪያዬ ውስጥ በቀር በሌላ እንዳትቀብሩኝ ማሉልኝ" አላቸው። በአማላቸውም ጊዜ እርሱ ልጃቸው እንደሆነ ገራቸው ያን ጊዜም ጮኹ መሪር ልቅሶንም አለቀሱ የሮሜ ከተማ ሽማግሎዎችና ሕዝቡ ሁሉ ተሰበሰቡ ሰባቱ ቀንም ሲፈጸም ቅዱስ ዮሐንስ ሐምሌ 16 ቀን ዐረፈ። ❤ እናቱም መሐላዋን ረስታ አስቀድማ ለሠርጉ ያዘጋጀቻቸውን ያማሩ ልብሶች አውጥታ ገነዘች። በዚያችም ጊዜ ታመመች አባቱ ግን መሐላውን አስታውሶ እነዚያን ያማሩ ልብሶች አስወገደ በጨርቆቹም ገነዙት በዚያ በትንሹ ማድሪያም ውስጥ ቀበሩት ከሥጋውም በሽተኞች የሚፈወሱበት ታላቅ ድኅነት ተገኘ። ❤ ከዚህም በኋላ በስሙ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ሥጋውን በውስጧ አኖሩ ከእርሱም ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 16 ስንክሳር።                             ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለዮሐንስ_ዘወንጌል_ወርቅ_ንዋዩ። ዘአግበረ ሎቱ አቡሁ እምነ ዕበዩ። ወበተጋድሎ ማሰነ ወተወለጠ ራእዩ። እስከ ሰእኑ ጠይቆተ ገጹ ኪያሁ ዘአርእዩ። ወእስከ ሰአልዎ ያውሕድ እምብዙኅ ሥቃዩ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሐምሌ 16።                          ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ከመ ነኪር ኮንክዎሙ ለአኃውየ። ወነግድ ለደቂቀ አቡየ ወእምየ። እስመ ቅንዓተ ቤትከ በልዐኒ"። መዝ 68፥8-9። የሚነበቡት መልዕክታት ፊል 4፥8-15፣ ያዕ 2፥1-10 እና የሐዋ ሥራ 14፥21-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማር 8፥34-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የአቡነ ዳንኤል ዘቦረና የዕረፍት በዓልና የአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ የልደት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #ሐምሌ ፲፮ (16) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ ዐሥራ ሁለት ክንፈ ጸጋ ለተሰጣቸው ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ሐዋርያ_ክርስቶስ ለልደታቸው መታሰቢያ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                         ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ሐዋርያ_ክርስቶስ፦ እኒህ ታላቅ ጻድቅ በኢትዮጵያ ሸዋ ክፍለ ሀገር ልዩ ስሙ መርሐ ቤቴ በሚባል አካባቢ በሕግ ተወስነው ከሚኖሩ ደግነታቸው ከሚታወቁ የእመቤታችን ፍቅር ከበዛላቸው ዝክሯን ከሚዘክሩላት ቅዱሳን ቤተሰብ ከአባታቸው ከንዋየ ጽዮንና ከእናታቸው ፍቅርተ ኪሮስ ከተባሉ ደጋግ ክርስቲያኖች የተገኙ ናቸው። ❤ ቅዱስ ንዋየ ጽዮን እና ቅድስት ፍቅርተ ኪሮስ በደግነት ተግባራቸው ጸንተው በመገኘታቸው ከዕለታት አንድ ቀን የእመቤታችንን ዝክር ዘክረው እንግዶችን በሚያስተናግዱበት ወቅት ንጽሕተ ንጹሐን ቅድስት ቅዱሳን እመቤታችን ድንግል ማርያም በቤታቸው በእንግድነት ተገኘች። እነርሱም በኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል ሥርዓት በቤታቸው አስገብተው ምንጣፍ አንጥፈው፣ እግሯን አጥበው፣ በክብር አስተናግደው ሲሸኟት የጻድቁን የልደት ብሥራት ከእመቤታችን አንደበት ተነገራቸው። ❤ በዚህ ሁኔታ በዓመቱ ሐምሌ ፲፮ (16) ጻድቁ ተወልደው ዕድሜያቸው ፲፰ (18) ዓመት እስኪሞላ ድረስ ቤተሰባቸውን ሲረዱ ትምህርት ሲማሩ ቆይተው የምናኔን ሕይወት ጀመሩ። ❤ በአየለነ (በተለምዶ እየላ) ቅዱስ ሚካኤልና በሰሜን ደብረ በንኰል የምናኔ ሕይወታቸውን እያካሄዱ ሳለ ምንኲስናቸውም በደብረ በንኰል ተፈጸሞ በፈቃደ እግዚአብሔር በእመቤታችን አመልካችነትና በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ወደ ታላቁ የገድልና የትሩፋት ቦታቸው ተከዜ መጡ። በገዳሙም በታላቅ ተጋድሎ ገዳማዊ የምናኔ ኑሮአቸውን አጠናክረው በመቀበል በርካታ መናንያን መነኰሳትን ሲያስተዳድሩ ቆይተው ከፈጣሪ ጋር በግልጽ እስመነጋገር ድረስ ለከዊነ እሳት ደረጃ የደረሱ አባት ናቸው። ❤ ጻድቁ ጌታችን ስለ ሰው ልጆቾ ድኅነት የተቀበላቸውን ሕማማተ መስቀል እያሰቡ ከእሾህ እየወደቁ ደማቸውን እያፈሰሱ፣ በብዙ እያነቡ በቀራንዮ የተከፈለውን ውለታ እያዘከሩ በገድል በትሩፋት ሲኖሩ የዓለም መድኃኒት መድኃኔዓለም ተገልጦላቸው ቃል ኪዳን ሰጥቷቸዋል። "እንዘ ለጸልዮ ትተግህ ለኑኃ ሌሊት ኲላ፤ ወእንዘ ትሰግድ በአሜከላ፤ ለምድረ ተከዜ እማዕከላ መሠጠከ አምላከ ቡላ" እንዲል። (መልክዐ አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ) ተከዜን ገዳማቸውንም አስባርከው፤ "ገዳምከ ትኩን ምዕራፈ ቅዱሳን አምሳሊሃ ለብሔረ ብፁዓን፤ ስሟም ምዕራፈ ቅዱሳን ትባልልህ የብሔረ ብጹዓን አምሳል ናት"፤ "ኢይትቀበር ውስቴታ ዓለማዊ ዘእንበለ ብእሲ ገዳማዊ፤ በውስጧም ገዳማዊ ውጪ አይቀበርባትም" በማለት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል። ❤ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም እጅ ታቦተ ኪዳነ ምሕረትን የተቀበሉ ሲሆን ግንቦት ፲፮ (16) ከልዑል እግዚአብሔር ዐሥራ ሁለት ክንፈ ጸጋ ተሰጥተዋቸው እንደነ ቅዱስ ነአኲቶ ለአብ፣ ቅዱስ ያሬድ ዐይነ ሞትን ሳያዩ ተሠውረዋል። መባርቅትን የሚያዙ፣ አጋንንትን የሚያሳድዱ ታላቁ ጻድቅ አባት ዛሬም ከገዳሙ አርድእት ጋር ከሚወጣው ጋር እየወጡ ከሚወርደውም ጋር እየወረዱ የሚረዱ በቅርብም በሩቅም ሆነው በቃል ኪዳናቸው ለተማጸናቸው በአማላጅነታቸው ለታመነባቸው የሚረዱ ናቸው። ከአቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ ተከዜ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ሐዋርያ ክርስቶስ አንድነት ገዳማ ከታተመው መጽሔት ላይ የተወሰደ።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤              ❤ #ሐምሌ ፲፮ (16) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ ዕድሜ ልካቸውን እናትና አባታቸውን እንኳን ባለመናገር #ዘረኝነትን_ከሀገራችን_ላጠፉ ለታለቁ አባት ለአባታችን #ለአቡነ_ዳንኤል_ዘቦረና_ለዕረፍት_በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ዳንኤል_ዘቦረና፦ እኚህ ጻድቅ አባት አንድ ትልቅ ግብር አላቸው፤ ይኸውም ዕድሜ ልካቸውን እናትና አባታቸውን እንኳን ባለመናገር ዘረኝነትን ከሀገራችን ያጠፋ ታላቅ ጻድቅ አባት ናቸው። ግድ ብለው አጥብቀው ሲይዟቸው "እናቴ አክሱም አለች፤ አባቴም ልጇ ነው" በማለት ዘረኝነትን በዘመናቸው አጥፍተዋል። ❤ ቦረና ሳይንት ባለው ገዳማቸው ውስጥ የሚገኘውን ባለ ሦስት ዓምድ ገድላቸውን ደርቡሾች ከጠባቂው በትንሽ ገንዘብ ገዝተው ወስደውታል። እርሱም በመቅሰፍት ተመቶ ሞቷል። ጻድቁ በሀገራችን ከ 250 በላይ አብያተ ክርስቲናትን አሠርተዋል። መካነ መቃብራቸው በጋስጫ ይገኛል"። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳንና ቅዱሳን በዓላት።

ሰላምታ ሰጥተዋቸው ወደ ፊልጶስ ሀገር ሔዱ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በጌቶቻችን ሐዋርያት በቅዱሳን ጴጥሮስና ጳውሎስ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 15 ስንክሳር።                              ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ዕብል_ሕሊናክሙ_ቅዱሰ። ዘኢያኅዘነ መንፈሰ። #ጴጥሮስ_ወጳውሎስ ወእደ እግርክሙ ጌሠ። ጽንዐ ኃይልክሙ ሰቀለ ንጉሠ። ወዕበይክሙ አሰገደ አፍራሰ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_15።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወኢያስጠሚኒ ዐውሎ ማይ። ወኢየኀጠኒ ቀላይ። ወኢያብቅዉ አፉሆሙ ዐዘቃተ ላዕልየ"። መዝ 68፥15። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 10፥6-15።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "መኑ ይትዔረዮ ለእግዚአብሔር በደመናት። ወመኑ ይመስሎ ለእግዚአብሔር እምደቂቀ አማልክት። እግዚአብሔር ስቡሕ በምክረ ቅዱሳን"። መዝ 88፥6-7። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 1፥18-26፣ ያዕ 5፥12-17 እና የሐዋ ሥራ 9፥22-30። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 4፥17-21። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱሳን ሐዋርያት ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤              ❤ #ሐምሌ ፲፭ (15) ቀን። ❤ እንኳን ለአባቶቻችን #ለቅዱሳን_ሐዋርያት #ለጴጥሮስና_ጳውሎስ_በንጉሥ_ጰራግሞስ_ላይ ተአምራትን ላአደረጉበትና #ዐሥር_ሺህ_ሁለት_መቶ ምዕመናንን በአንድ ጊዜ ላሳመኑበት ለመታሰቢያ በዓላቸው በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከአርባ_አምስት_ሰማዕታት ጋር #ከአባ_ሐርዮንና ተአምራትን ከሚያደርግ ከመስተጋድል #ከመነኰስ_ከፍሬምናጦስ ከመታሰቢያቸው፣ በምስር ስንክሳር እንደ ተጻፈው #ከሕፃኑ_ከቅዱስ_ቂርቆስ ከሰማዕትነት ከመታሰቢያ በዓል እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                               ✝ ✝ ✝ ❤ በዚችም ቀን አባቶቻችን #ቅዱሳን_ሐዋርያት_ጴጥሮስና_ጳውሎስ በንጉሥ ጰራግሞስ ላይ ተአምር አደረጉ። አምላክን ከወለደች ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍልሰት በኋላ ደመና ነጥቆ ወሰዳቸውና በቤተ መንግሥት አወረዳቸው ንጉሥ ጰራግሞስም በአያቸው ጊዜ ደንግጦ "እናንተ ምንድን ናችሁ" አላቸው። እርሱም "መንግሥታትን ሁሉ የሚያጠፋ የሚሰሙትን ማዳን የሚችል የሕያው እግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሮች ነን" አሉት። ንጉሡም "ነገራቸው ትክክል መሆኑን እንዴት ማወቅ እችላለሁ" አላቸው። ❤ ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ያደረገላቸውን ድንቆችና ተአምራትን ነገሩት። "የቀኝ ዐይኗን ወፍ ያወጣት አንድ ልጅ አለችኝ እርሷን ካዳናችኋት በአምላካችሁ አምላለሁ" አላቸው "ልጅህን ወደእኛ አምጣ" አሉትና ልጁን ወደ እነርሱ አመጣት። ሐዋርያትም ወደ እግዚአብሔር ጸልየው እጆቻቸውን በአይኗ አኖሩ። ያን ጊዜም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ዳነች። ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ አይተው ከሐዋርያት እግር በታች ሰገዱ ክብር ይግባውና በጌታችን አመኑ። ❤ ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና በጌታችን እንዳዘዛቸው ወደ አገረ ፊሊጶስ ሔዱ። ሰይጣንም በእንዶር ንጉሥ ተመስሎ አጋንንት በጭፍራ አምሳል አስከትሎ ወደ ንጉሥ ጰራግሞስ መጣ "በሥራያቸው አገርን ሳያጠፉ እኒህን ሁለቱን ሥራየኞች ፈጥነህ የማታጠፋቸው ለምንድነው" አለው። ❤ ንጉሥ ጰራግሞስ ልቡ ወደ ክህደት ተመለሰ። ሐዋርያትም ያመጧቸው ዘንድ ዐሥር ሺህ ጭፍሮችንና ሁለት መቶ ፈረሰኞችን ላከ ጭፍሮችም ሔደው ከተማዋን ከበቧት የከተማው ሰዎች ደንግጠው ለሐዋርያት ነገሩዋቸው። ሐዋርያትም ከከተማው ወጥተው በጭፍሮቹ ፊት ቁመው ርዳታን ይልክላቸው ዘንድ ወደ ጌታችን ጸለዩ። ❤ ያንጊዜም የጭፍሮቹ ፈረሶች ወደ ሐዋርያት ተመለሱ እግሮቻቸውንም አስተካክለው ተንበርክከው ሰገዱ እንደሚያለቅስም በቃጪን ድምጽ ጮኩ። ከፈረሶችም አንዱ ድምፁን ከፍ ከፍ አድርጎ እንዲህ ብሎ እንደ ሰው ተናገረ "እናንት ሰነፎች የጰራግሞስ ጭፍሮች ክብር ይግባውና የክርስቶስን ጭፍሮች ጴጥሮስንና ጳውሎስን ለምን ትፈልጓቸዋላቸሁ ሥራየኞችስ ለምን ትሏቸዋላችሁ እነርሱ ግን ሥራይንና የሰይጣንን ሥራ ሁሉ ሊያጠፉ መጥተዋል። ክብር ይግባውና ከንጉሣቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በነጫጭ ፈረሶች ተቀምጠው አታዩአቸውምን ለክብር ንጉሥ ለክርስቶስ ጭፍሮቹ ትሆኑ ዘንድ ስሞቻችሁም በሕይወት መጽሐፍ ይጻፍ ዘንድ ስለ እናንተ ይለምናሉ። እኛ እንኳ እንስሳ ስንሆን ለአምላካችው እንሰግዳለ"ን ፈረሱም ይህንን ተናግሮ ዝም አለ። ❤ ከዚህም በኋላ እንዲህ የሚል ቃል ተሰማ "ሐዋርያቶቼ ሆይ ሐዲሶች አትክልቶችን ቸለል አትበሏቸው"። ያን ጊዜም ሕዝቡ ሁሉ ዐይኖቻቸውን ቀና አድርገው በታላቅ ክብር ወደ ሰማይ ሲዐርግ ጌታችንን አዩት እነዚያም ዐሥር ሺህ ሁለት መቶ ጭፍሮች ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ለሐዋርያትም ተገዙላቸው። ❤ ሐዋርያትም የምድራዊ ንጉሥ ጭፍራ መሆንን እንዲተዉ ፈረሶቹንና የጦር መሣሪያውንም እንዲመልሱለት ክብር ይግባውና በክርስቶስ በግልጥ እንዲአምኑ አዘዟቸው። እነዚያ ጭፍሮቹም ወደ ንጉሣቸው ጰራግሞስ ሔደው በፊቱ ቆሙ "ታመጧቸው ዘንድ የላክኋችሁ እነዚያ ሁለት ባለ ሥራዮት ወዴት አሉ" አላቸው። "የልጅህን ዐይኗን በማዳን በጎ በሠሩልህ ፈንታ ለምን በክፋት ትፈልጋቸዋለህ" አሉት። ከዚህም ጥሩራቸውንና ትጥቃቸውን ፈትተው "ገንዘብህን ውሰድ እኛ ግን ከአንተ የተሻለ ንጉሥ አግኝተናል ይኸውም የቅዱሳን ጴጥሮስና የጳውሎስ አምላክ ነው" ብለው ከፊቱ ጣሉለት። በሰማ ጊዜም ደነገጠ ተቆጥቶም እስከሚገድላቸው ድረስ በወህኒ ቤት ይጨምሯቸው ዘንደ አዘዘ። ❤ ከዚህ በኋላም ራሱ ይይዛቸው ዘንድ ተዘጋጀ የጦር መሣሪያውንም አዘጋጀ ወደ ፊልጶስ አገር ሔደው እስከ መሠረቷ ያጠፏት ዘንድ ሃያ ሺህ አራት መቶ እግረኞች ጭፍሮችን አዘዛቸው። ቅድስ ጴጥሮስም በመንፈስ ቅዱስ አውቆ ቅዱስ ጳውሎስን እንዲህ አለው። "ወንድሜ ሆይ አገርን እንዳያጠፋ ሳይወጣ ወደ ጰራግሞስ ተነሥ እንሒድ" አለው ከዚህም በኋላ ጸሎትን ጸለዩ ወጥተውም በደመና ተጫኑ በቤተ መንግሥት መካከልም አወረዳቸውና በጰራግሞስ ፊት ቆሙ እንዲህም አሉት "እነሆ እኛ በፊትህ ነን ስለ እኛ አገርን አታጥፋ"። ያን ጊዜም ጭፍሮች እንዲመለሱ አዘዘ። ❤ ሐዋርያትንም እንዲህ አላቸው "አገሩን ሁሉ በሥራይ የምታጠፉ ሥራየኞች አናንተ ናችሁን" እነርሱም "ይህ ሥራ ለእኛ አይገባም" አሉት። ሁለተኛም "ኃጢአታችሁ ነው ወደዚህ ያመጣችሁ" አላቸው። ችንካር ያላቸው ሁለት የራስ ቁሮችን ከብረት እንዲሠሩ አቃቂርንም እንዲመሉአቸው በእሳትም አግለው በሐዋርያት ራስ ላይ እንዲደፉአቸው አዘዘ እንዲሁም አደረጉባቸው። ያን ጊዜም ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ ጸለየ "አቤቱ ፈጣሪዬ ሆይ የጌትነትህን ኃይል በጰራግሞስ ላይ ግለጽ"። ያን ጊዜም ጰራግሞስ ከወገኖቹ ሁሉ ጋር በነፋስ ውስጥ ተዘቅዝቆ ተሰቀለ። በዚያን ጊዜም "ጌቶቼ ሆይ ይቅር በሉኝ ከዚህ ፆዕርም አድኑኝ" እያለ ጮኸ "የእንዶር ንጉሥ አስቶኛልና የተረገመ ይሁን በእናንተም ላይ ክፉ የሚናገር ሁሉ የተረገመ ይሁን" አለ። ቅዱስ ጴጥሮስም "የታሠሩትን ጭፍሮች ይፈቷቸው ዘንድ እስከምታዝ ከዚህ ስቅላት አትወርድም" አለው እርሱም ወደ ልጁ ወደ ሎይ ተጣርቶ ትፈታቸው ዘንድ አዘዛት እርሷም አንዳዘዛት ፈታቻችው። ❤ ቅዱስ ጴጥሮስም ዳግምኛ አለው "አሁንም ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም በምድር ላይም እንደእኔ ያለ ርኩስ የለም ብለህ ካልጻፍህ አትወርድም ይህችንም በከተማው መካከል ያነቧት ዘንድ ታዝዛለህ"። ንጉሡም ወረቀትንና ቀለምን ታቀብለው ዘንድ ወደ ልጁ ተጣራ እርሷ ብቻዋን ከስቅላት ቀርታ ነበርና ባመጣችለትም ጊዜ ቊልቊል ተሰቅሎ እያለ ጻፈ በከተማውም መካከል ያነቧት ዘንድ ላካት። ❤ ያን ገዜም ጰራግሞስንና ወገኖቹን አወረዷቸው ወደ ሐዋርያትም መጥተው ከእግራቸው በታች ሰገዱላቸው ንጉሡም "ጌቶቼ ይቅር በሉኝ እኔ በአምላካችሁ አምናለሁ" አለ ሕዝቡም ሁሉ ሕያው በሆነ አምላካችሁ እናምናለን እያሉ ከሐዋርያት እግር በታች ወድቀዉ ሰገዱ። ❤ እነርሱም ሃይማኖትን አስተምረው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው ጭፍሮችንም አጠመቋቸው። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን አንድ ሆኑ። ቤተ ክርስቲያንንም ሠሩላቸው ከአዋቂዎቻቸውም ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾሙላቸው። ነገረ ምሥጢርንም እያስገነዘቡአቸው በእነርሱ ዘንድ ኖሩ። ሃይማኖታቸውንም ይጸና ዘንድ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሰጧቸው። እንዲህም አሏቸው "በሃይማኖታችሁ ጽኑ እኛ ካስተማርናችሁ ትምህርት አትናወጹ ወደ እናንተም እንመለሳለን"። ከዚህም በኋላ

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤             ❤ #ሐምሌ ፲፭ (15) ቀን። ❤ እንኳን #ውዳሴ_ማርያውና ከ 14 ሺህ በላይ ድረሳናትንና ተግሣጻትን ለደረሰው ለታላቁ ሊቅ #ለአፈ_በረከት_ለቅዱስ_ኤፍሬም_ሶርያዊ_ለዕረፍት በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                                 ✝ ✝ ✝ ❤ #ሶርያው_ሊቅ_አፈ_በረከት_ቅዱስ_ኤፍሬም፦ ይህም ቅዱስ ከዋክብት የሚያመልኩ ሰዎች አገር ነው አባቱ ክብር ይግባውና የክርስቶስን አምልኮት የሚጠላ የጣዖት ካህር ነበር። በዚያን ጊዜም የእግዚአብሔር ቸርነት ቀሰቀሳቸውና አነሳስታ የንጽቢን ጳጳስ ወደ ሆነው ወደ አባ ያዕቆብ ወሰደችው እርሱም የቤተ ክርስቲያን ትምህት አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቀው በእርሱ ዘንድ በጾምና በጸሎት ያለማቋረጥ እየተጋደለ ለብዙ ዘመናት ኖረ። ❤ የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ አደረበት አሕዛብን ተከራክሮ ይረታቸው ነበር። ኒቅያ በሚባል ከተማ የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶች ኤጲስቆጶሳት ጉባኤ በተደረገ ጊዜ ይህ ቅዱስ ኤፍሬም ከመምህሩ ከአባ ያዕቆብ ጋር ወደ ቅዱሳን ጉባኤ ሔደ። ከሀዲው አርዮስንም አውግዘው ከለዩት በኋላ ይህ ቅዱስ ኤፍሬም በዚያች ሌሊት ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ አየ ከዚህ ራዕይ የተነሳ አደነቀ ይገልጽለትም ዘንድ ወደ ጌታ ጸለየ "ይህ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ባስልዮስ ነው" የሚል ቃል ከሰማይ ወደርሱ መጣ። ❤ ቅዱስ ኤፍሬምም ያየው ዘንድ ወዶ ወደ ቂሣርያ አገር ተጓዘ በደረሰም ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በማዕዘኑ በኩል ቆመ ቅዱስ ባስልዮስም ወንጌልን ሊያነብ በወጣ ጊዜ ዋጋው ብዙ የሆነ ከወርቅ የተሠራ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ አየው። ሦስት ምልክቶችን እስኪያይ ድረስ ተጠራጠረ ምልክቶችም እኒህ ናቸው። ነጭ ርግብ መጥታ በራሱ ላይ አረፈች። ሁለተኛም በልብሱ ላይ የሚያርፉ ተዋሐስያን ይቃጠሉና ይረግፉ ነበር። ሦስተኛም ከአፉ የእሳት ነበልባል ወጥቶ በምዕመናን ላይ ያድር ነበር። ❤ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ባስልዮስ ቅዱስ ኤፍሬምን በስሙ ጠራውና እርስ በእርሳቸው ሰላምታ ተለዋወጡ። በአስተርጓሚ ይነጋገሩ ጀመር። የየራሳቸውን ቋንቋ ይገልጽላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንዲጸልይ ቅዱስ ኤፍሬም ቅዱስ ባስልዮስ ለመነው። በጸለየም ጊዜ ተገልጾላቸው ያለ አስተርጓሚ ተነጋገሩ። ❤ ከዚህ በኋላም ቅዱስ ኤፍሬምን ዲቁና ሾመው ከጥቂት ወራት በኋላ ቅስና ሾመው ከእርሱም ብዙ ትሩፋቶች ተገለጡ በመንፈሳዊ ተጋድሎ ሁሉ ተጋደለ። ❤ አንዲት በወገን የከበረች ባለ ጸጋ ሴት ነበረች እርሷንም ለካህን ለማስመርመር ታፍር ነበር ከታናሽነቷ ጀምራ የሠራችው ኃጢያቷን ሁሉ ጽፍ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ አመጣች። "አባቴ ሆይ በዚህ ክርታስ ውስጥ ያሉት ኃጢያቶቼ ይደመሰሱ ዘንድ ተናገር ብላ ለመነችው እርሱ እንዳልሽው ይሁንልሽ" አላት። እርሷ ክርታሱን በገለጠች ጊዜ ከአንዲት ኃጢያቷ በቀር ኃጢያቷ ሁሉ ተደምስሶ አገኘች ያችም ኃጢአት አስጨናቂና ታላቅ ኃጢአት ነበርች። ❤ በአገኘቻትም ጊዜ ያቺን የቀረች ኃጢአቷን ያጠፋላት ዘንድ አልቅሳ ለመነችው እርሱም "ወደ ቅዱስ ኤፍሬም ሒጂ እርሱ ይቺን የቀረች ኃጢአትሽ ያስተሠርይልሻል" አላት። ወዲያውም ወደ ቅዱስ ኤፍሬም ሒዳ እርሷ የሆነውን ሁሉ ነገረችው። እርሱም እንዲህ አላት "ፈጥነሽ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ሒጂ ግን ሙቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱት ታገኚዋለሽ ሳትጠራጠሪም ይቺን ክርታስ በላዩ ጣይ ይደመስስልሻል። ❤ ያቺም ሴት ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ተመለሰች ሙቶ ተሾክመው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዱትም አገኘችው። ያንንም ክርታስ በአስክሬኑ ላይ ጣለችው ወዲያውኑ ተደመሰሰላት። ❤ ይህም ቅዱስ ኤፍሬም ብዙ ተአምራቶችን አድርጓል በዘመኑ ዲዳን የሚባል አንድ ከሃዲ ተነሳ ይህም አባት ኤፍሬም ተከራክሮ ረታው። ❤ እጅግም ብዙ የሆኑ ዐሥራ አራት ሺህ ድርሳናትና ተግሣጻትን ደረሰ ከእርሳቸውም ውስጥ አምላክ የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያው ውዳሴዋ ነው። "አቤቱ የፀጋህን ማዕበል ግታልኝ" እስከሚል ደረስ ድርሳናት ደርሷል። ❤ መልካም የሆነ ገድሉንም በፈጸመ ጊዜ ወደ ወደደው ወደ እግዚአብሔር ሐምሌ 15 ቀን ሔደ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በብፁዕ ቅዱስ ኤፍሬም ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 15 ስንክሳር።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤              ❤ #ሐምሌ ፲፬ (14) ቀን። ❤ እንኳን ልክ እንደ #ቅዱስ_ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ሊሰቃይ ሲሔድ #ጌታችን_ለኢየሱስ_ክርስቶስ ተገልጾ ለመለሰው #ለቅዱስ_አብሮኮሮንዮስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓልና ለመነኰሳት አለቃ #ለታላቁ_አባት_አባ_መቃርስ_ለመታሰቢያ_በዓሉ በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ #ከሰማዕቱ_አሞንዮስ_ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #ሰማዕቱ_ቅዱስ_አብሮኮሮንዮስ፦ የዚህም ቅዱስ ትውልዱ ከኢየሩሳሌም ነው የአባቱ ስም ክርስቶፎሮስ ነው ትርጓሜውም ክርስቶስን የለበሰ ማለት ነው ክርስቲያንም ነበረ የእናቱም ስም ቴዎዶስያ ነው እርሷ ግን ጣዖትን ታመልክ ነበረች። ❤ አባቱም በዐረፈ ጊዜ እናቱ ወሰደችው ከእርሱም ጋራ ብዙ ገንዘብ ይዛ ወደ አንጾኪያ ከተማ ሔደች ልጅዋንም በእስክንድርያ ከተማ ገዥ አድርጎ ይሾመው ዘንድ ለዲዮቅልጥያኖስ እጅ መንሻ ሰጠችው እርሱም ሾመው የሹመት ደብዳቤውንም ጽፎ ክርስቲያኖችን እንዲአሠቃዩ አዘዘው። ❤ ከአንጾኪያም ከተማ ወጥቶ ጥቂት እንደ ተጓዘ ወደእርሱ የሚያስፈራ ቃል ከሰማይ መጣ በስሙ ጠርቶ እንዲህ አለው "ከሀዲው ዲዮቅልጥየኖስ እንዳዘዘህ ብታደርግ አንተ በክፉ አሟሟት ትሞታለህ። እርሱም "ራስህን ትገልጥልኝ ዘንድ ጌታዬ ሆይ እለምህሃለሁ" አለው ወዲያውኑም የብርሃን መስቀል ታየው ዳግመኛም "በኢየሩሳሌም የተሰቀልኩ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ነኝ" የሚለውን ቃል ሰማ። ❤ ይህንንም ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ፈራ ተመልሶም ከአንጥረኛ ዘንድ የወርቅ መስቀል አሠራ ከዚያም በኋላ ወደ እስክንድርያ ከተማ ተጓዘ በጒዞውም ውስጥ ሊገድሉት ዐመፀኞች አረማውያን ተነሡበት እርሱም በእነርሱ ላይ በርትቶ ክብር ይግባውና በጌታ ክርስቶስ መስቀል ድል አደረጋቸው። እናቱም "በጦርነት ላይ ለረዱህና ላዳኑህ አማልክት መሥዋዕትን ሠዋ" አለችው እርሱም እንዲህ አላት "እኔስ አዳኝ በሆነ በመስቀሉ ኃይል ላዳነኝ ክብር ይግባውና ለእግዚአብሔር እሠዋለሁ"። ይህንንም በሰማች ጊዜ ልጅዋ አብሮኮሮንዮስ ክርስቲያን እንደሆነ ወደ ዐመፀኛው ዲዮቅልጥያኖስ ልካ ነገረችው። ዲዮቅልጥያኖስም ጭፍራ ልኮ ወደ ቂሣርያ ከተማ አስወሰደው የቂሣርያውንም ገዥ ስለ ርሱ እንዲመረምርና እንዲአሠቃየው አዘዘው። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ በአቀረቡት ጊዜ በፊቱ ቁሞ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ ለመሞት እስቲደርስም ጽኑዕ ግርፋትን ገረፈው ከዚህም በኋላ አሠረው። በዚያችም ሌሊት ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ብርሃን ውስጥ ታየው ከእርሱም ጋራ ብርሃናውያን መላእክት ነበሩ ከማሠሪያውም ፈታውና በመለኮታዊ እጁ ዳሰሰው ከቍስሎቹም ሁሉ አዳነው። ❤ በማግሥቱም መኰንኑ ስለ ቅዱሱ ዜና ሙቶ እንደሆነ ወይም አልሞተ እንደሆነ ጠየቀ ለእርሱ የሞተ መስሎት ነበረና። ቅዱሱም በመጣ ጊዜ ጤነኛ ሁኖ አየውና መኰንኑ አደነቀ በዚያ የነበሩ ሕዝቡም አይተው እጅግ አደነቁ እንዲህም እያሉ ጮኹ "እኛ በግልጥ ክርስቲያን ነን በቅዱስ አብሮኮሮንዮስ አምላክ እናምናለን"። ከእነርሱም ጋራ ሁለት መኳንንትና ዐሥራ ሁለት ሴቶች እናቱ ቴዎዶስያም ነበሩ መኰንኑም ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጧቸው አዘዘ። እነርሱም ቆረጡአቸው። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ሐምሌ ስድስት ቀን ተቀበሉ። ❤ ቅዱስ አብሮኮሮንዩስን ግን ምን እንደሚያደርግበት እስቲአስብ ድረስ ሦስት ቀን አሠረው ከዚህም በኋላ አውጥቶ እንዲህ አለው "ልብህ እንዲመለስ ነፍስህንም እንድታድን ለአማልክትም እንድትሠዋ እነሆ በአንተ ላይ ሦስት ቀናት ታገሥኩ"። ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት "መኰንን ሆይ የለም ልቤ ወደ ስሕተት አይመለስም ክብር ይግባውና ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ አውቄ ተረድቼአለሁ ጣዖታቱም ሁሉ ከዕንጨትና ከደንጊያ በሰው እጅ የተሠሩ ፍጡራን ናቸው እንጂ አማልክት አይደሉም አይጐዱም አይጠቅሙም"። ❤ መኰንኑም ሰምቶ እጅግ ተቆጣ ጐኖቹንም በሰይፍ እንዲሰነጣጥቁ አዘዘ አርኬላዎስ የሚባል ባለ ሰይፍም የቅዱሱን ጐኖቹን ሊሠነጥቅ እጁን ዘረጋ ያን ጊዜም እጁ ደረቀች ወድቆም ሞተ። መኰንኑም ተቆጥቶ በምድር ጥለው ይገርፉት ዘንድ አዘዘ እንደ አዘዘም ገረፉት በሰይፍም ጐኖቹን ሠንጥቀው በቍስሉ ውስጥ መጻጻ ጨመሩ እስከ ወህኒ ቤትም ድረስ በእግሩ ጐተቱት በዚያም ሁለት ቀኖች ኖረ ከዚህም በኋላ አውጥቶ እሳትን በተመላች ጕድጓድ ውስጥ ጣለው ክብር ይግባውና ጌታችንም አዳነው ምንም ምን አልነካውም። ❤ ብዙ ከማሠቃየቱም የተነሣ መኰንኑ በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጡት በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ ቅዱስ አብሮኮሮንዮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                            ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለአብሮኮሮንዮስ_በኢየሩሳሌም ዘተወልደ። እምለባሴ ክርስቶስ አቡሁ በአርዑተ ወንጌል ዘተጸምደ። በትእዛዘ ንጉሥ ሠዊዐ ሶበ ለጣዖት ፈቀደ። ቃል ዘይከልኦ እምሰማይ ወረደ ወበቊስላቲሁ አንበረ መለኮት እደ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_14።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "እስመ በእንቲአሁ ይቀትሉነ ኵሎ፡አሚረ። ወኮነ ከመ አባግዕ ዘይጠብሑ። ንቃሕ እግዚኦ ለምንት ትነውም"። መዝ 43፥22-23። የሚነበቡት 1ኛ ተሰ 4፥1-13፣ 1ኛ ጴጥ 5፥6-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 14፥19-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 13፥1-10። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤            ❤ #ሐምሌ_፲፫ (13) ቀን። ❤ እንኳን #ለአገረ_ቅፍጥ_ኤጲስቆጶስ ከነቢያት ትንቢትም አንዳንዱን መጽሐፍ በሚነብ ጊዜ ትንቢቱ የሚነበብለት ነቢይም ወደርሱ መጥቶ ንባቡን እስቲፈጽም ይቆይ ለነበረ፤ እጆቹን አንሥቶ በሚጸልይ ጊዜ ጣቶቹ እንደ ፋና ይበሩ ለነበር ለታላቁ አባት #ለአባ_ብስንድዮስ_ለዕረፍቱ_መታሰቢያ በዓልና በግብፅ ደቡብ ከቡና አውራጃ ከጡሕ ከሚባል አገር ለሆነ #ለቅዱስ_አሞን_ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል መታሰቢያ በሰላም አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የአገረ_ቅፍጥ_ኤጲስ_ቆጶስ_አባ_ብስንድዮስ፦ ይህም ቅዱስ ሰው መንኵሶ በታላቅ ገድል ተጠምዶ ቅዱሳት መጻሕፍትንም አጠና ከቅዱሳት መጻሕፍትም ውስጥ የዳዊትን መዝሙርና የነቢያትን መጻሕፍት አጥንቶ ነበር። ከነቢያት ትንቢትም አንዳንዱን መጽሐፍ ያነብ ነበረ። ትንቢቱ የሚነበብለት ነቢይም ወደርሱ መጥቶ ንባቡን እስቲፈጽም ይቆይ ነበር። ❤ ስለርሱ እንዲህ ተባለ እርሱ እጆቹን አንሥቶ በሚጸልይ ጊዜ ጣቶቹ እንደ ፋና ይበሩ ነበር እግዚአብሔርም በእጆቹ ታላላቅ ድንቆችንና ተአምራቶችን አደረገ። እርሱም በዕድሜው ዘመን ሁሉ የሴት ፊት አላየም። ራሱን ወደ ምድር ያዘነብል ነበር እንጂ። በሆድዋ ውስጥ ታላቅ ደዌ የነበረባትም አንዲት ሴት ነበረች ከበዐቱ ደጅ ጠበቀችውና በድንገድ አገኘችው። እርሱም ሮጠ እርሷም ተከትላው ሮጠች ወደ እርሱ መድረስም በተሳናት ጊዜ እግሩ የረገጠቻትን አንዲት እፍኝ አፈር ዘግና በእምነት በላች ከደዌዋም ፈጥና ተፈወሰች። ❤ በአንዲት ዕለትም የሚያበሩ ሦስት ሰዎች አየ እነርሱም "አንተ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ትመግባት ዘንድ አለህ" እያሉ መክፈቻ ቅልፍን ሰጡት። ከዚህ በኋላ ቅፍጥ በሚባል አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ተሾመ የቊርባን ቅዳሴ በሚቀድስ ጊዜም ጌታችንን እጆቹ በመሠዊያው ላይ ሆነው ይመለከተው ነበር። መላእቶቹንም በዙሪያው ቁመው ያያቸው ነበር። ❤ በአንዲት ዕለትም አንድ ቄስ ሊቀድስ ገባ በቅዳሴ እኩሌታ ላይም በመሠዊያው ፊት እያለ ምራቁን ተፋ። ቅዳሴውም በተፈጸመ ጊዜ ይህ አባት ገሰጸው እንዲህ አለ "በሚያስፈራው ወሠዊያው ፊት በምትቆም ጊዜ ከእግዚአብሔር ጌትነት የተነሳ አትፈራምን የተፈኸውስ ምራቅ በመሠዊያው ዙሪያ በቆመ ኪሩብ ክንፈች ላይ እንደረሰ አታውቅምን"። ያን ጊዜም ያንን ቄስ መንቀጥቀጥ ያዘው ተሸክመውም ወደ ቤቱ ወሰዱትና ታሞ ሞተ። ❤ ይህም ቅዱስ አባት አንደበቱ ጣዕም ያለው ነበር በሚያነብ ጊዜ በሚያስተም ጊዜ በሚመክርም ጊዜ አይጠገብም ነበር። የዕረፍቱ ቀን በቀረበ ጊዜ አውቆ ሕዝቡን ጠራቸውና አስተማራቸው መከራቸውም በቀናች ሃይማኖትም ይጸኑ ዘንድ አዘዛቸው። ከዚህም በኋላ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጠ። ❤ ከሥጋውም ብዙ ተአምር ተገለጠ ደቀ መዝመሩ ከመግነዙ ጥቂት ቁራጭ ወስዶ በእምነት በሽቶኞችን ሁሉ ይፈውስ ነበር። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛን በአባ ብስንድዮስ ጸሎቱ ይማረን በረከቱ ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #ሰማዕቱ_ቅዱስ_አሞን፦ ይህም ቅዱስ ከግብጽ ደቡብ ከቡና አውራጃ ጡሕ ከሚባል አገር ነው። ለዚህም ቅዱስ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ተገለጸለት ከእርሱ የሚሆነው ሁሉ ነገረው። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ እንዴናው ከተማ ሒዶ አውግስጦስ የሚባል መኰንን ፊት ክብር ይግባው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ። መኰንኑም በመንኰራኵር ውስጥ በእሳት ላይ በመጣል በእሳት በአጋሉት በብረት አልጋ ላይ በማጋደም ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ በውሽባ ቤት ማንደጃ ውስጥ በመጨመር ጽኑዕ ስቃይም አሰቃዩት። የራሱንም ቆዳ ገፈው በራሱ ላይ የእሳት ፍም አኖሩ እግዚአብሔርም ያጸናው ነበር ያለምንም ጉዳት ጤነኛ አድርጎ ያስነሳው ነበር። ❤ ከዚህም በኋላ ክብር ይግባው እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ በጎልማሳ አምሳል በብርሃን ሠረገላ ላይ ሁኖ ተገለጠለትና አጽናናው እንዲህም አለው "ወዳጄ አሞን እኔ ከአንተ ጋራ እኖራለው ስምህን የሚጠራውን፣ መታሰቢያህን የሚያደርገውን ሁሉ፣ ወይም ገድልህ የሚጽፈውን ሁሉ እኔ በመንግሥቴ ውስጥ አስበዋለሁ ኃጢያቱንም እደመስሳለሁ አገርህም እጠብቃለሁ" ይህንንም ብሎ ሰላምታ ሰጥቶ ከእርሱ ዘንድ አረገ። ❤ ይህም ቅዱስ በሥጋው ሳለ ታላላቅ ታምራቶችንና ድንቆችን አደረገ ወዲያውንም በሠይፍ ራሱን ቆረጡት የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበለ። ቅዱስ ዮልዮስም በዚያ ነበር ሥጋውን ወስዶ በመልካም ልብስ ገነዘው ከሁለት አገልጋዮቹም ጋር ወደ አገሩ ላከው በላይኛው ግብጽም ታላላቅ የሆኑ ድንቆችንና ተአምራቶች እያሳየ እስከ ዛሬ አለ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ሰማዕት በቅዱስ አሞን ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 13 ሰንክሳር።                                                        ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወዘሕጎ ያነብብ መዓልተ ወሌሊተ። ወይከውን ከመ ዕፅ እንተ ትክልት ኀበ ሙኃዘ ማይ። እንተ ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ"። መዝ 1፥2-3። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 8፥18-35፣ 1ኛ ጴጥ 1፥13-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 19፥11-21። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 10፥32-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ኤጲፋንዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችን ይሁንልን።