925
مشترکین
+224 ساعت
+27 روز
+830 روز
آرشیو پست ها
ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም
የክልሉን የገቢ አቅም በማሳደግ ሁለንተናዊ ልማት ዕውን ለማድረግና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት የላቀ ቁርጠኝነትና ዝግጅት አለው፦ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)
፨፨፨፨፨///፨፨፨፨፨
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) በ2018 በጀት ዓመት የመንግስት የፋይናንስ ስርዓትን በማጠናከር ክልሉ የጀመራቸውን ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎች ለማጎልበት መታቀዱን አሳወቁ።
ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የፋይናንስ ሴክተር የንቅናቄ መድረክ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የክልሉ መንግስት ከዕዳ የሆነ ክልል፣ዞን፣ልዩ ወረዳና ወረዳ ለመፍጠር ቁርጠኛ አቋም መያዙን አመልክተዋል።
ክልሉ ያደሩ እዳዎችን በመመለስ ረገድ አበረታች የሚባሉ ስራዎች መስራቱንም ገልጸው፣የቀሩ እዳዎችን በአጠረ ጊዜ ለመመለስም የእያንዳንዱ ሰው ጥረት ወሳኝ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ክልሉን ከዕዳ ለማውጣትም ሆነ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ይበልጥ ለማፋጠን ፍትሀዊ፣ግልጽ፣ አሳታፊና የሀብት ብክነትን የሚቀንስ የፋይናንስ ስርዓት መከተል አስፈላጊ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው አሳስበዋል።
ክቡር ፕሬዚዳንቱ በክልሉ ማዕከላት እየተካሄዱ የሚገኙ የተቋማት ግንባታ ሂደትን፣ተቋማቱ ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥም እንዴት እየተሰሩና የቅርብ አመራር እየተሰጠባቸውም እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ዶክተር እንዳሻው በክልሉ የተሰበሰበው ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም አሳውቀው፣በስኬት እየተካሄዱ የሚገኙ የአንድ ወረዳ አንድ ፕሮጀክት ጠንካራ አፈጻጸሞችና የህብረተሰብ ተሳትፎንም በመድረኩ ገልጸዋል።
የፋይናንስ ስርዓቱን ለማጠናከርና ማነቆዎችን ለመፍታትም የውስጥ ኦዲትና ቁጥጥር ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉም መመሪያ ሰጥተዋል።
ከቁጥቁጥ ስራ መላቀቅ ይገባል ያሉት ክቡር ፕሬዚዳንቱ ከተሞች የገቢ አቅማቸውን አሟጠው በመሰብሰብ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ማገዝ እንደሚገባቸውም አመላክተዋል።
በአጠቃላይም የክልሉን የገቢ አቅም በማሳደግ ሁለንተናዊ ልማት ዕውን ለማድረግና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት የላቀ ቁርጠኝነትና ዝግጅት እንዳለውም ክቡር ርዕሰ መስተዳደሩ በመድረኩ አረጋግጠዋል።
መረጃው የማ/ክ/መ/ኮ/ቢሮ ነው!!
ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም
ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት ሌብነትን ለመቀነስ እየተሰራ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
፨፨፨፨፨///፨፨፨፨፨
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልከ ብዙና ዋነኛ ሀገራዊ ፈተና የሆነውን ሌብነት ዘመናዊ አሰራር በመዘርጋት ለመቀነስ እየተሰራ ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መንግሥት በተሰኘው አዲሱ መጽሐፋቸው ዙሪያ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ሌብነት ሰዎች ስልጣናቸውን በመጠቀም በነጻ መስጠት ያለባቸውን አገልግሎት ለሃብት ማከማቻነት ሲጠቀሙበት ነው ብለዋል፡፡
ይህም አነስተኛ ዝርፊያ መሆኑን ጠቅሰው፥ የመንግስት ሰራተኞች የተሰጣቸውን አደራ ወደ ጎን በመተው ለሚሰጡት አገልግሎት ሲያስከፍሉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሰዎች ያላቸውን የትኛውንም ሙያ እንደመሳሪያ በመጠቀም አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት ሲሞክሩ ይስተዋላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህም አነስተኛ ሙስና እንደሆነ ተናግረዋል።
የመደመር መንግስት ይህን አይነቱን ሌብነት በአረም መልኩ እንደሚመለከተው ጠቅሰው፥ አረምን ለይቶ ማወቁ ለመንቀል ቀላል ቢያደርገውም ብዛቱ እና ከማሳው ጋር መመሳሰሉ ስራውን አታካች ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ይህ አይነቱ ሌብነት ብዙ እና ለልየታ አዳጋች ቢሆንም ከተለየ ለመንቀል ቀላል መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላው የሌብነት ዓይነት ከባድ ዝርፊያ መሆኑን በመጥቀስ በግለሰቦችና ቡድኖች መካከል በቅንጅት የሚሰራ ነው ብለዋል፡፡
ይህም አንዳንዶች ስልጣን ይዘው፣ አንዳንዶች ሚዲያ ይዘውና ሌሎች ደግሞ የጦር መሳሪያ ይዘው የሚፈጽሙት የተቀናጀ ዝርፊያ መሆኑን አብራርተዋል።
መንግስታት ከባዱን ዝርፊያ ቢመለከቱ እንኳን ለመንቀል ያስቸግራቸዋል ነው ያሉት፡፡
መሰል ዝርፊያዎች እንደ ዋርካ የሚታዩ ሆኖም ግን በቀላሉ ለመንቀል የሚያዳግቱ ሲሆን በሀገር ደረጃ ካደጉ የመንግስትን ፖሊሲና አቅጣጫ የሚወስኑ እንደሆነ ገልጸዋል።
መንግስትም በአቻነት ስሜት የሚያያቸው ይሆናሉ ብለዋል፡፡
ይህም በተለያዩ ሀገራት እንደሚታይ አንስተው፥ በኢትዮጵያም ከለውጡ በፊት በግልጽ ሲታይ እንደነበር አስታውሰዋል።
ባለስልጣናት ከባለሃብቶች ጋር ተመሳጥረው ህግ ሲያወጡና ያሻቸውን ሲዘርፉ የነበሩበት ሁኔታ ነበር ነው ያሉት፡፡
ከለውጡ በኋላ በተሰራው ስራ መሰል ዝርፊያ አለመኖሩን ተናግረዋል።
የመደመር መንግስት በስፋት የሚስተዋለውን አነስተኛ ዝርፊያ ለመንቀል ስርዓት ዘርግቶ ለማስወገድ በስፋት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ጨምሮ ሞባይል ባንኪንግና ዘመናዊ ግብይቶች መፈጠራቸው ችግሩን ይቀርፋል ነው ያሉት፡፡
ኤፍ ኤም ሲ
“ብዙ መንግሥታት ካልደፈሩት እና የመደመር ትውልድ ደፍሮ ካነሣቸው ሐሳቦች አንዱ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የቀይ ባሕር ጉዳይ ነው” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
#EBC
ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም
ፖለቲካ በጥላቻና ስሜት ሳይሆን በሃሳብ የበላይነት መመራት አለበት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
፨፨፨፨፨///፨፨፨፨፨
የፖለቲካ ገበያው በግል ጥላቻና ስሜት ሳይሆን በሃሳብ የበላይነት ሊመራ ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መንግስት በተሰኘው አዲሱ መጽሐፋቸው ዙሪያ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ መጽሐፉ ከዚህ ቀደም በንድፍ ሃሳብ የተነሱ ሃሳቦችን ተቋማዊ ወይም መንግስታዊ ቅርጽ እንዲይዙ ያስችላል፡፡
ቀደምት የኢትዮጵያ መንግስታት የመንግስታቸውን ቅርጽ፣ እሳቤ፣ የሚከወንበትን መንገድ፣ ሊያሳካው የሚፈልገውን ግብና ውጤት በዚህ ደረጃ በሰነድ ሰንደው አስቀምጠው እንደማያውቁ አንስተዋል፡፡
መጽሐፉ ዋና ሃሳብ በንድፍ ሃሳብና በፍልስፍና ትውልድ እንዴት እንደሚገነባ ያሳየው መደመር ተቋማዊ ወይም መንግስታዊ ቅርጽ እንዲይዝ ለማስቻል እንደሆነ አብራርተዋል።
ከዓለም ጋር የት ተላለፍን፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስብራቶቻችን የት ጀመሩ የሚለውን መጽሐፉ ይተነትናል ብለዋል፡፡
ኋላ ለመቅረታችን ምክንያት የሆኑ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው፤ በእኛና በዓለም መካከል የተፈጠረውን ክፍተት እንዴት ልናጠበው እንችላለን፤ ምን አይነት መደመራዊ አካሄዶችን ብንከተልስ ሊጠብ ይችላል የሚለውን ያብራራል ነው ያሉት፡፡
በመጽሐፉ ከተለመደው የመቅዳት አካሄድ በመላቀቅ መደመራዊ ፈጠራ፣ ፍጥነትና የዝላይ መንገዶችን መከተል ይገባል የሚለውን እንደሚዳስስም ጠቅሰዋል፡፡
መጽሐፉ ሃሳቡን ሲያብራራ ከቀደምት መንግስታት ሃሳቦች ጋር ራሱን እንደሚያወዳድርና በንጽጽር የተመረጡ ሃሳቦች ለምን ጥቅም ላይ እንደዋሉ እንደሚያስረዳ ጠቁመዋል፡፡
መደመርን ፍልስፍናው አድርጎ የሚመራ መንግስት ምን አይነት ባህሪያት እንዳሉት እና ስለሚከተለው ስትራቴጂና የሚያስመዘግበውን ውጤት በዝርዝር ያስቀምጣልም ነው ያሉት፡፡
በሀገር ውስጥና በውጪ ስለሚኖረው ግንኙነት እንዲሁም የተሻገረና የዘመነ ገጠርና ከተማ እንዴት መፍጠር እንደሚቻል እንደሚያስረዳ አንስተዋል፡፡
በመደመር በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም እና ሌሎች ሃብቶች ያሉ እምቅ እድሎችን ለሀገር ጥቅም እንዴት ማዋል እንደሚቻል እንደሚተነትንም ተናግረዋል፡፡
መጽሐፉ ለስኬቶቻችን ወሳኝ ጉዳዮችን ያነሳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በተለይም የፖለቲካ ስክነት ለኢኮኖሚ ስምረትና ለተቋም መሳለጥ ያለውን ሚና በማብራራት ተግዳሮቶችን በሚገባው ልክ እንደሚያስረዳ አመልክተዋል፡፡
ፖለቲካ እንደሸቀጥ የሚሸቀጥበት ሥርዓት ከሃሳብ የራቀ መሆኑን እንደሚያስረዳ ጠቁመው÷ ሊከሰት የሚችልን አደጋና ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ላይ የራሱ እይታ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
እንደ ሀገር ሀገራዊ ትርክት መፍጠር እስካልተቻለ ድረስ ኢትዮጵያን በምንፈልገው ልክ አስቀምጠን ጥቅማችንን ለማስከበር ያለውን ፈተና እና መውጫ መንገዶችን እንደሚያሳይም ጠቅሰዋል፡፡
ፖለቲካ በግል ጥላቻና ስሜት ሳይሆን በሃሳብ የበላይነት መመራት እንዳለበት አጽንኦት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ሀገራዊ፣ የወል እና አሰባሳቢ ትርክት መገንባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ኤፍ ኤም ሲ
ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም
በጉራጌ ዞን ገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ "ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ" እያከናወናቸው ያሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ስራዎች 95 በመቶ መድረሳቸው ተገለፀ።
፨፨፨፨፨///፨፨፨፨፨
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከመንግስት ጎን በመሠለፍ የዜጎች የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ከነዚህ ስራዎች መካከል በመሃል አምባ ከተማና በዙሪያው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሳደግ አፅንኦት ሠጥቶ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።
የገ/ጉ/ወ/ወረዳ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጠይብ አስፍር መንግስት የባለሃብቱን፣ የህብረተሰቡን እና ረጂ ድርጅቶችን አቅም በመጠቀም የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋኑን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እየተሰራ ባለው ስራ አበረታች ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ተፈፃሚ እያደረገ ያለው የንፁህ መጠጥ ውሃ ስራ አሁናዊ ያለበትን ደረጃ አስመልክተዉ እንዳሉት ከፍተኛ በጀት በመመደብ ወደ ተግባር መግባቱን አስታውቀዋል።
ከዚህም ውስጥ በመጀመሪያው ምዕራፍ ስራ 54 ሚሊዮን ብር በጀት በመያዝ 3 የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮና ፓምፕ ስራ እንዲሁም በሁሉተኛዉ ምዕራፍ ስራ 52 ሚሊዮን 279 ሺህ 900 መቶ ብር በሆነ ወጪ 2 ባለ 100 ሜትር ኪዮብብ እና ባለ 25 ሜትር ኪዮብ ተገጣጣሚ ታንከር ስራ፣ 10 ቦኖ ግንባታን ጨምሮ 10.017 ኪሎ ሜትር መስመር ዝርጋታ በዋናነት ተጠቃሾች መሆናቸውን ሃላፊው ጠቅሰው አሁን ላይ ስራውን በተቀላጠፈ መልኩ በመተግበር በተያዘለት ጊዜ መሠረት ለማጠናቀቅ አስፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ስለመሆኑ ገልጸው
ቀሪው ስራ የትራንስፎርመር ተከላ እና የማገናኘቱ ስራ እንደሚቀር ሲሆን አጠቃላይ አሁናዊ አፈፃፀሙ 95 በመቶ ላይ መድረሱን ገልፀዋል።
ኢንጂነር ገመቹ ከተማ የፕሮጀክት ማናጀር ናቸው።
እንደሳቸው ገለፃ ፕሮጀክቱ የመሃል አምባ ከተማንና በዙሪያው ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሙሉ በሙሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆን እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
ስራውን ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ያወሱት አስተባባሪው እስከ መጪው ነሃሴ 20/2017 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ አቅደው እየሰሩ ሲሆን ስራው በተቀላጠፈ መልኩ እየሄደ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
በመጨረሻም አቶ ጠይብ አስፍር ባስተላለፉት መልዕክት ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከወረዳው አስተዳደር ጋር በመሆን የህዝባችንን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ እያደረገ ያለው ብርቱ ጥረት ተደናቂ መሆኑን በማንሳት በወረዳው መንግስትና ህዝብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበው ፅህፈት ቤታቸው እያደረገ ያለውን ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ የሚቀጥል ስለመሆኑ አስታውቀዋል።
ዘገባው የገ/ጉ/ወ/ወ/የመ/ኮ/ጉ/ፅ/ቤት ነው።
ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም
በጉራጌ ዞን ገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ ለማህበረሰባችን እሴት ግንባታ በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኘው የክረምት በጎ ፍቃድ በዘሬ ቀበሌ ለወ/ሮ ሎሚናት ሽኩሬ የወረዳው አብይ ኮሚቴ 40 ቆርቆሮ፣ 2 ፓኬት የግድግዳ ሚስማርና 1 ፓኬት የቆርቆሮ ሚስማር በዛሬው እለት ድጋፍ በማድረግ የቤት ግንባታውን አስጀምሯል።
ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም
በጉራጌ ዞን ገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ቦኔ ቀበሌ የመስኖ ቅድመ ዝግጅት የተለያዩ የጎሮ አትክልቶች በመደብ የተዘጋጀ ቀይ ሽንኩርት፣ ቃሪያ ፣ ጎመን በምስል፦
ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም
በጉራጌ ዞን ገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ግብርና ልማት ፅህፈት ቤት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አስታወቀ።
፨፨፨፨፨///፨፨፨፨፨
የገ/ጉ/ወ/ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና ፅ/ቤት ዋና ኃላፊ አቶ ከድር መርጋ በዘንድሮ እርሻ ዘመን የተቀናጀ ግብርና ስራዎች ላይ ግብ ተጥሎ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ አስታውቀዋል።
በ2017 ዓ.ም የመኸር እቅድ አፈፃፀም በተመለከተ 14 ሺህ 909 ሄ/ር መሬት ለማልማት ታቅዶ በተለያዩ ዘርፎች የልየታ ስራ መሠራቱን ጠቅሰዉ ከዚህም ዉስጥ 14ሺህ 14ሄ/ር መሬት የታረሰ ሲሆን 13 ሺህ 189.5 ሄ/ር መሬት መልማቱን ገልፀዋል።
የልየታ ዘርፉም በብዕር ሰብል፣ ስንዴ፣ ጤፍ እና በገብስ 1 ሺህ 245 ሄ/ር መሬት፣ በጥራጥሬ 2 ሺህ 753ሄ/ር መሬት፣ በቅባት ሰብል 11ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ከ13 ሺህ 189 ሄ/ር በላይ መሬት ወይም 95 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስታውቀዋል።
እንዳጠቃላይ በምርት ዘመኑ ለማልማት ከታቀደው እቅድ ውስጥ የለማው 13 ሺህ 189 ሄ/ር መሬት ሲሆን በዚህም ገብስ 4700 ሄ/ር፣ ስንዴ 3180
ሄ/ር ፣ ባቄላ 1ሺህ 30 ሄ/ር መሬት፣ አተር 1ሺህ 723 ሄ/ር መሬት፣ጤፍ 25 ሄ/ር፣ እና በአትክልት 190 ሄ/ር፣ በድንች 1ሺህ 400 በጠቅላላው 13 ሺህ 189.5 ሄ/ር መሬት በማልማት በተለያዩ ዘር ተሸፈኗል ብለዋል።
በበጀት አመቱ 641 ሄ/ር መኖ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 580ሄ/ር መሬት መልማቱን ያሳወቁት አቶ ከድር መርጋ ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ 12 ሺህ 200 ኩንታል ዳፕ እና 4 ሺህ 144 ኩ/ል ዩሪያ እንዲሁም Biofertilizer 310 ለአተርና ባቄላ እና
አሲዳማ መሬትን በኖራ በማከም ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ 420 ኩ/ል ኖራ አሲዳማ ለሆነ መሬቶች መጠቀም መቻላቸውን ገልፀዋል።
ከወልቂጤ ምርምር ማዕከል በተደረገ ድጋፍ 40 ኩ/ል የስንዴ ምርጥ ዘር ለተመረጡ አርሶ አደሮች በነጻ በመስጠት 37.4 ሄ/ር የስንዴ ክላስተር ማሳ እየለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከፍራፍሬ ምርትና ምርታማነት አንፃር በክላስተር ደረጃ 30 40 30 በሚል ልየታ አርሶ አደሩን በተገኘ አጋጣሚ ግንዛቤ ተስጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሠው 36 ሺህ 772 ቀርቧል ያሉት ኃላፊው 31 ሺህ 665 ፍራፍሬ መተከሉን አውስተዋል።
የአትክልት አቅርቦት እንደ ወረዳ እጥረት በማጋጠሙ የክልሉ ግብርና ቢሮ መንግስት ቁጥራቸው 7 ሺህ 500 የሚሆን የሙዝ ችግኝ፣ አፕል 6000፣ ፖም 500 ችግኝ እና 5000 የአቮካዶ ችግኝ ድጋፍ ማድረጋቸውንና በዞኑ ግብርና መምሪያ በኩል 500 የፖም ችግኝ ድጋፍ መደረጉን በመግለፅ በተቋማትና በክላስተር በአርሶ አደሮች ማሳ መተከሉን አስታውቀዋል።
ከአረንጓዴ አሻራ ተግባራት ጋር በተያያዘ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸዉ 7.5 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል በተያዘዉ ዕቅድ መሠረት 7.57 ሚሊዮን ችግኞች በመትከል አፈፃፀሙን ከዕቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።
በመጨረሻም አቶ ከድር መርጋ ባስተላለፉት መልዕክት ከመኸር ስራ ጋር በተያያዘ ከሌላ ጊዜ በተሻለ መልኩ ተቋሙ እየተነቀሳቀሰ መሆኑን አስታውሠው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝባዋል።
ዜና ሹመት
የጉራጌ ዞን አስተዳደር ልዩ ልዩ ሹመቶች ሰጥቷል።
የጉራጌ ዞን አስተዳደር በዛሬው እለት የተለያዩ ሹመቶችን ሰጥቷል።
በዚህም መሰረት
1, አቶ ሸምሱ አማን:- የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ
2, አቶ ሀዲሞ ሀሰን:- የጉራጌ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት የሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ
3, አቶ ነስሩ ስራኒ:- የጉራጌ ዞን ህብረት ስራ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ
4, ወ/ሮ አርሺያ አህመድ የጉራጌ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት የመ/አስተዳደርና አካባቢ ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ
5, አቶ ኑርአህመድ አለዊ :- የጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የቤቶች ልማት ዘርፍ ኃላፊ አድረገው ሹመት ሰጥተዋል።
የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ለተሿሚዎች መልካም የስራ ዘመን ይመኛል።
