አንድ ሰው አዲስ ልማድን ለማዳበር የሚያልፍባቸው ስድስት ደረጃዎች።
የስነልቦና ባለሞያ ቢኒ ግርማቸው
አንድ ሰው መጥፎ ልማዱን ለማጥፋት ወይም ወደ አዲስ ጥሩ ልማድ ሲገባ የሚያልፍባቸው ስድስት ደረጃዎች እንዳሉ የስነ-ልቦና ባለሙያዎች
ያስቀምጣሉ። ሰውየውም ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላኛው ደረጃ ለመሸጋገር ወራት አልፎ ተርፎም ዓመታት ሊፈጅበት እንደሚችል መረዳት ተገቢ ነው።
ይህን መረዳት በሂደቱ ላይ የበለጠ ትእግስት ለመግዛት ብሎም በተስፋ መቁረጥ ሂደቱን እንዳናቆም ወሳኝ ሚና አለው።
ደረጃዎች ከሚያስፈልጋቸው
የጊዜ መጠን እና ልፋት ውጭ አንድን ደረጃ አልፎ ወደመጨረሻው ለመሄድ መሞከር ተስፋ መቁረጥ ስለሚያስከትል ደረጃዎችን መረዳት በጣም
ተገቢ ነው። እነዚህ ደረጃዎች እንደሚከተሉት ተቀምጠዋል።
ደረጃ1: ለመለወጥ ከማሰብ እና ከመቁረጥ በፊት (Precontemplation)
በዚህ ደረጃ ግለሰቡ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ምንም ዓይነት አዎንታዊ ለውጦችን የማድረግ እቅድ አይኖረውም። ይህ ምናልባት ችግሮች
እንዳሉበት ባለማመን፣ መጥፎ ልምዱ በቀላሉ መፈታት እንደማይችል ባለማመን ወይም በርካታ ያልተሳኩ የለውጥ ሙከራዎች በፊት በማድረጉ ተስፋ
በመቁረጥ ሊሆን ይችላል።
ለምሳሌ፣ አንድ ሰው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ መጀመር እንደሚያስፈልገው ሊገነዘብ ይችላል፣ ነገር ግን በፊት ሞክሮ ስላልተሳካለት ያንን ለማድረግ
ተነሳሽነቱ አይኖረውም
ደረጃ 2: ስለመለወጥ ማሰብ እና መቁረጥ (Contemplation)
በዚህ ደረጃ፣ ግለሰቡ እራሱን በመለውጥ የሚያገኛቸውን ጥቅሞች በውል ማገናዘብ ይጀምራል። እራሱንም መቀየር እንዳለበት መቀበል ይጀምራል፣
ነገር ግን የሚያስፈልገውን ጥረት እና ልፋት በማሰብ ከራሱ ጋር ብዙ ጊዜ ይታገላል። ስለሆነም ግለሰቡ በዚህ ደረጃ ውስጥ ለወራት ወይም ዓመታት
ሊቆይ ይችላል።
ለምሳሌ፣ አንድ ግለሰብ በተደጋጋሚ የአካላዊ እንቅስቃሴ ጥቅሞችን በቁም ነገር ማጤን ይጀምራል፣ ነገር ግን ስለሚጠይቀው ጊዜ እና
ልፋት አያሰበ ከራሱ ጋር ለረጅም ጊዜ ይታገላል። ግለሰቡ ወደሚቀጥለው ደረጃ ሊያልፍ የሚችለው እራሱን ስለመለወጥ ያለው ሃሳብ ወደ እምነት
ሲቀየር ነው።
ለምሳሌ “የአካል እንቅስቃሴ ለማንኛውም ሰው ጥሩ ነገር ነው” ከሚለው ጥቅል ሃሳቡ ወደ “የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ያሉብኝን
ችግሮች ለመቅረፍ፣ ማንነቴን ለማጎልበት አማራጭ የሌለው ነገር ነው” ወደሚል እምነት መሸጋገር መቻል አለበት።
ደረጃ 3: ዝግጅት (Preparation)
በዚህ ደረጃ ሰውየው እቅድ ማውጣት ይጀምራል። ይህ ደረጃ አጭር ነው፣ ለጥቂት ሳምንታት ብቻ ይቆያል።
ለምሳሌ፣ ለመለወጥ እንቅስቃሴው
የሚያስፈልጋቸውን ግብአት ያሰባስባሉ፣ ድጋፍ ሊሰጧቸው ከሚችሉ ሰዎች ጋር ቀጠሮ በመያዝ ስለ ዕቅዳቸው ይወያያሉ፣ ወዘተ።
ደረጃ 4: እርምጃ (Action)
ይህ ደረጃ አብዛኛውን ጊዜ ለበርካታ ወራት ይቆያል። ለምሳሌ፣ ሰውዬው ወደ ጂምናዚየም በመደበኛነት መሄድ እና የአመጋገብ ለውጦችን ማድረግ
ይጀምራል.
ደረጃ 4 አንድ ሰው ለለውጥ ያለው ፍላጎት ለቤተሰብ እና ለጓደኞቹ የሚስተዋልበት ደረጃ ነው። ለሚያዩት ሰዎች ድንገት ለውጡን የጀመረ ሊመስል
ይችላል፣ ነገር ግን ይህ ደረጃ ለሰዎች መታየት የሚጀምርበት ስለሆነ ነው እንጂ ሰውየው ለውጡን የጀመረው ከ ደረጃ 1-3 ጀምሮ ነው።
ደረጃ 5: የለውጥ እርምጃውን ማስቀጠል (Maintenance)
በዚህ ደረጃ ላይ ግለሰቡ ለውጦቹን እንዴት ማቆየት እንደሚችል ማሰብ ይጀምራል። እናም የአኗኗር ዘይቤዎችን ማስተካከል ይጀምራል። ለምሳሌ
ከመጠጥ ሱስ ለመላቀቅ እየሰራ ያለ ሰው ወደመጠጥ የሚገፋፉትን ጉዋደኞች እንዴት መራቅ እንዳለበት ዘዴዎችን ይነድፋል። በአጠቃላይ አዲሱን
ልምዱን የሚያስቀጥል እርምጃዎችን ሁሉ ይወስዳል።
ግለሰቡ እዚህ ደረጃ ላይ ንቁ ተሳትፎ ካላደረገ፣ አዲሱ ልምዱቹን ማስቀጠል ይከብደዋል።
እዚህ ደረጃ ላይ ለብዙ ወራቶች ምን አልባትም ለአንድ ዓመት የቆዩ ሰዎች ወደ ሚቀጥለው ደረጃ (ደረጃ 6) መሸጋገር ይችላሉ።
ደረጃ 6: ከድሮ ልማዳቸው ሙሉ በሙሉ መላቀቅ (Termination)
ይህ ደረጃ ለአዲሱ ልምድ ሙሉ በሙሉ ቁርጠኝነት የተንጸባረቀበት ደረጃ ነው፣ እናም ወደ ቀድሞ ወደነበሩበት ልምድ ፈጽሞ አይመለሱም። አዲሱን
ልምዳቸውንም ብዙ ግፊት ማድረግ ሳይኖርባቸው በቀላሉ ያደርጋሉ።. ለምሳሌ አንድ ሰው ሲጋራ ማጨሱን ቢያቆምም እንኳ "አንድ ብቻ" ሲጋራ
በዓመት ውስጥ የማጨስ መገፋፋትን ፈተና መቋቋም ይከብደዋል። እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ግን ልክ አጭሶ እንደማያውቅ ሰው ድጋሜ ለማጨስ
ፈተና አይገጥማቸውም
ሌሎችም ሼር ያድርጉ
@BiniGirmachew
@BiniGirmachew
@BiniGirmachew