fa
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

رفتن به کانال در Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

نمایش بیشتر
613
مشترکین
+124 ساعت
-17 روز
-1030 روز
آرشیو پست ها
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #ሐምሌ ፳፭ (25) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጽያዊ_ጻድቅ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት ለአጎት ልጅ ለታላቁ አባት ከበሬ ጋር ተጠምደው በማረስ ሰማዕትነት ለተቀበሉት ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ሕፃን_ሞዐ ለዕረፍታቸው በዐል በሰላም አደረሰን።                          ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ሕፃን_ሞዐ፡- በአባታቸው አርከሌድስ እናታቸው ትቤ ጽዮን ይባላሉ፡፡ የተወለዱት ጥር25 ነው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ እና ከእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር የሥጋ ዝምድና አላቸው፡፡ ይኸውም አባታቸው አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ወንድማማቾቸ ናቸው፡፡ አርከሌድስና ጸጋ ዘአብ ሌሎች ሌሎች አራት ወንድሞች አሏቸው፡፡ ❤ እነርሱም እንድርያስ፣ ዘርዐ አብርሃም፣ ቀሲስ ዮናስ እና ቀሲስ ዮሐንስ ናቸው፡፡ አርከሌድስ ሕፃን ሞዐን ይወልዳል፣ ጸጋ ዘአብ ተክለ ሃይማኖትን ይወልዳል፣ እንድርያስ ሳሙኤል ዘወገግን፣ዘርዐ አብርሃም ታላቁ አኖሬዎዮስን፣ ቀሲስ ዮናስ ገላውዲዮስንና የፈጠጋሩን ማትያስን፣ እና ቀሲስ ዮሐንስ ዜና ማርቆስን ይወልዳሉ፡፡ እነዚህ የከበሩ ቅዱሳን አባቶቻችን በእናታቸውም ወገን ቢሆን እንዲሁ በዝምድና የተቆራኙ ናቸው፡፡ አቡነ ሕፃን ሞዐ በሌላኛው ስማቸው ሕፃን ዘደብረ በግዕ ተብለውም ይጠራሉ፡፡ ይኸውም የደብረ በግዕን ገዳም የመሠረቱት እርሳቸው ስለሆኑ ነው፡፡ ❤ ከአራባ ሰባቱ የአገራችን ቀደምት ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ በመንዝና በተጉለት የሚገኙ ታላላቅ ገዳማትን አብዛኞቹን የመሠረቷቸው አቡነ ሕፃን ሞዐ ናቸው፡፡ ጻድቁ በክፉዎች ወሬና ሴራ ምክንያት ከበሬ ጋር ተጠምደው ሰማዕትነት የተቀበሉ አባት ናቸው፡፡ ከበሬ ጋር ሲታረሱ ውለው በእጅጉ ከደከማቸ  በኋላ በኃይል የተነፈሱባት ምድሪቱ ዛሬም ድረስ ልክ እንደሰው የሚሞቅ ትንፋሽ ታወጣለች፡፡ ያም በጻድቁ እስትንፋስ አምሳል ከመሬት ውስጥ የሚወጣው እስትንፋስ ለአስም በሽታ መድኃኒት ሆኖ ብዙዎችን እየፈወ ነው፡፡ ገዳማቸው ከደብረ ብርሃን ከተማ በእግር የሁለት ሰዓት መንገድ ርቀት ይገኛል፡፡ ይኸውም ከወንይዬ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አጠገብ ነው፡፡ ጻድቁ ጥር 25 ቀን ልደታቸው፣ ጥቅምት 25 ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ዕለት ሲሆን ሐምሌ25 ደግሞ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ምንጭ፦ ከገድላት አንደበት።

❤ ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጸለትና የደዌውን ምክንያት አስረዳው ያንን መርዝ ያደረጉበትንም ስማቸውን ገለጠለት። በዚያ ወራትም የግብጽ ንጉሥ አብዶ አልዓዚዝ ወደ እስክንድርያ ከተማ መጣ ይህ አባት ሊቀ ጳጳሳት ስምዖንም ሊቀበለው ወጣ ንጉሡም በሊቀ ጳጳሳቱ ፊት ላይ የደዌ ምልክት አይቶ መሳፍንቶቹን "መልኩ እንዲህ እስኪለወጥ ድረስ ሊቀ ጳጳሳቱ ምን ደረሰበት" ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም ክፉዎች ካህናት በእርሱ ላይ እንዳደረጉበት መርዝንም እንዳ በሉት ነገሩት ንጉሡም ተቆጣ ካህናቱንና መሠርያኑንም በእሳት እንዲአቃጥሏቸው አዘዘ ያን ጊዜም ይህ አባት ከንጉሡ እግር በታች ወድቆ ይምራቸው ዘንድ እያለቀሰ ለመነው ንጉሡም አይደለም "እንደሚገባቸው ያቃጥሏቸው እንጂ" አለው። ይህም አባት "ስለእኔ አንተ ከአቃጠልካቸው ለእኔ ክህነትና ሊቀ ጵጵስና አይገባኝም" አለው። ንጉሡም ሰምቶ ከየዋህነቱና ከርኅራኄው የተነሣ አደነቀ እነዚያን ካህናትና መሠርዮች ከእስክንድርያ እንዲያሳድዷቸው አዘዘ። ❤ ንጉሡም ይህን አባት እጅግ ወደደው አከበረውም እንደወደደም አብያተ ክርስቲያናትን ገዳማትን ይሠራ ዘንድ ፈቀደለት። እርሱም በምስር ሰሜን አልዋህ በሚባል አገር አብያተ ክርስቲያን ሠራ በሹመቱም ዘመን ሌሎች ብዙዎችን ሠራ። ❤ ካደረጋቸው ተአምራቶቹ ሌላው ይህ ነው ሚናስ የሚባል አንድ ቄስ ነበረ ሙቶ ከተገነዘ በኋላ በዚህ አባት ጸሎት ተነሣ። የመነሣቱ ምክንያትም እንዲህ ነበር ይህ አባት ስምዖን በመላው አብያተ ክርስቲያናት ንብረት ንዋየ ቅድሳትና አልባሳት ላይ መጋቢ አድርጎ ይጠብቅ ዘንድ ቄሱን ሾመው። ሁልጊዜም "የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ በቤትህ ውስጥ አታኑር" እያለ ያዝዘው ነበር። ከዚህም በኋላ ድንገተኛ ደዌ አገኘውና አንደበቱና ጒረሮው ተጣጋ። ሊቀ ጳጳሳቱም ሰምቶ እጅግ አዘነ ስለ አቢያተ ክርስቲያናትም ንብረት ያንን ቄስ ከሞት ያድነው ዘንድ በዚያች ሌሊት እግዚአብሔርን እየለመነ መላዋን ሌሊት ለጸሎት ተጋ። መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ያ ቄስ ለመሞት እንደተቃረበ ይህ አባት ሰምዖን ሰማ ስለ አቢያተ ክርስቲያናት ነብረት ይጠይቃት ዘንድ አዝዞ ወደ ቄሱ ሚስት ረዳቱን ላከ። ❤ ወደ ቄሱ ቤትም በቀረበ ጊዜ ሰዎች እያለቀሱለት ጩኸታቸውን ሰማ በገባ ጊዜም ሙቶ ልብሰ ተክህኖ መጐናጸፊያ ሲያለብሱት በዐልጋ ላይም ሲያስተኙት ብዙዎችም በዙሪያው ሲያለቅሱ አገኛቸው ያም ረዳቱ የቄሱን በድን ሊሳለም ዘንበል አለ። ያን ጊዜም ያ የሞተው ቄስ ተነሥቶ አቀፈውና "የክቡር አባ ስምዖን ፈጣሪ እግዚአብሔር ሕያው ነው" አለው። ረዳቱም "በርታ አትፍራ" አለው። ቄሱም በጌታው በአባ ስምዖን ጸሎት አዎ በእውነት ጸናሁ እግዚአብሔር ሕይወትን ሰጥቶ ከሞት አስነሥቶኛልና አለ። ❤ ያን ጊዜም ያ ረዳት ስለ መሞቱ ደንግጠው የነበሩትን ካህናት እነሆ ቄሱ ከሞት ተነሥቷል ብሎ ጠራቸው። ካህናቱና ሕዝቡም ወደርሱ በቀረቡ ጊዜ ቄሱ እንዲህ አላቸው "እኔ ሙቼ እንደነበረ ዕወቁ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ዙፋን ፊት አቆሙኝ ከአባት ሐዋርያ ማርቆስ እስከ አባ ይስሐቅ ያሉትን ሁሉንም የጳጳሳት አለቆች ክብር ይግባውና በክርስቶስ ዙፋን ፊት ቁመው አየኋቸው እኔንም ከወንድማችን ከሊቀ ጳጳሳት ስምዖን የአብያተ ክርስቲያናትን ንብረት ለምን ሸሸግህ ብለው ገሠጹኝ"። ያን ጊዜም ጌታ ክርስቶስ "ይቺን ነፍስ በውጭ ወዳለ ጨለማ ውሰዱአት" ብሎ አዘዘ። ሊወስዱኝም በጐተቱኝ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ዙፋን ፊት የጳጳሳት አለቆች ሰገዱ እንዲህ እያሉም ማለዱ "ይህን ሰው አንድ ጊዜ ማረው ንብረታቸውን ስለሚጠብቅላቸው አብያተ ክርስቲያናት ብሎ ወንድማችን ስምዖን ስለ እርሱ እነሆ ቁሞ ይጸልያልና"። ጌታችንም ልመናቸውን ተቀብሎ ነፍሴን ወደ ሥጋዬ መለሰ እንዲህም አለኝ "እነሆ ስለ ምርጦቼና ስለ ወንድማቸው ስለ ሊቀ ጳጳሳት ስምዖን ማርኩህ አንተም የአብያተ ክርስቲያናትንም ንብረት ግለጥለት። አለዚያ ግን ወደዚህ እመልስሃለሁ የእነዚህንም ልመናቸውን ስለአንተ ሁለተኛ አልቀበልም"። ❤ በዚያ የነበሩም ሰዎች ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ አደነቁ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገኑት ኀዘናቸውም ወደ ደስታ ተለወጠ ይህም ቄስ ተአምር ለሁሉ እየተናገረ ብዙ ዘመናት ኖረ። ❤ ይህም አባት ስምዖን በበዐቱ ውስጥ በገድል የተጸመደ ሁኖ ኖረ መንጋዎቹንም ያስተምራቸው፣ ይገሥጻቸውና በቀናች ሃይማኖትም ያጸናቸው ነበር። ከዚህም በኋላ ሐምሌ 24 ቀን በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ስምዖን ጸሎት ይማረን በርከቱም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 24 ስንክሳር።                            ✝️ ✝️ ✝️ ✝ "#ሰላም_ለኖብ_እንተ_ሠረፀ_እምከርሣ። ለታሕተ ምድር ንሒሳ። መኰንን ዕልው ጽጉበ ኃጢአት ወአበሳ። ያውዕያ ለሥጋሁ በፍልሐተ ተይ ወፒሳ። እምፍቅረ ክርስቶስ ኢክህለ ለነፍሱ ያግኅሣ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_24።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ማእምርየ ወዐውቅየ። ዘኅቡረ አስተጠዓምከ ሊተ መባልዕተ። ወነሐውር ቤተ እግዚአብሔር በአሐዱ ልብ"። መዝ 54፥13-14። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ቆሮ 7፥8-11፣ 1ኛ ጴጥ 5፥1-6 እና የሐዋ ሥራ 26፥35-ፍ.ም የሚነበበው ወንጌል ማቴ 19፥16-22። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የአባ ኖብ የዕፍት በዐል ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ሐምሌ ፳፬ (24) ቀን። ❤ እንኳን #ከደቡብዊ_ግብጽ ከታችኛው ምድር አውራጃ ከንሒሳ ከተማ ለሆነ #ለቅዱስ_ለአባ_ኖብ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕፍቱ በዓል፣ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ሁለተኛ ለሆነ #ለእስክንድርያ_ሊቀ_ጳጳሳት ለቅዱስ አባት #ለአባ_ስምዖን_ለዕረፍት እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከአንድ_መቶ_ዘጠና_ሽህ_ሰማንያ አራት #ከአባ_ኖብ_ማኅበር_ከሰማዕታት ከሌሎች ማኅበሮቻቸው ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                                ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_አባ_ኖብ፦ይህም ቅዱስ ከደቡባዊ ግብጽ ከታችኛው ምድር አውራጃ ከንሒሳ ከተማ ነው። ወላጆቹ ቅዱሳን ንጹሐንና የሚራሩ ነበሩ። ይህንንም ቅዱስ ኖብን በወለዱት ጊዜ ዐሥራ ሁለት ዓመት እስኪሆነው ፈሪሀ እግዚአብሔርን እያስተማሩ አሳደጉት። ቤተ ክርስቲያንን የመጻሕፍትን ቃል መስማትንና መማርን የሚወድ ሆነ። ❤ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የክርስቲያን ወገኖችን ዲዮቅልጥያኖስ በአሠቃያቸው ጊዜ ይህ ቅዱስ ደሙን ስለ ጌታችን ሊአፈስ አሰበ ያን ጊዜም ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ ቄሱንም ምእመናንን እንዲህ እያለ ሲያስተምራቸውና ሲያበረታቸው "ጣዖታትን ከምታመልኩ ክብር ይግባውና ስለ መድኃኒታችን ስለ ክርስቶስ ነፍሳችሁን ለሞት አሳልፋችሁ ብትሰጡ ለእናንተ መልካም ነው" ሲላቸው ሰማው። ይህም ቅዱስ እያዘነና እየተከዘ ወደ ቤቱ ተመለሰ አባቱም የተወለትን ወርቁንና ብሩን ልብሶችን ሁሉ ተመልክቶ እንዲህ አለ ሁሉ ነገር የዚህ ዓለም ፍላጎቱም ሁሉ እንደ ሚያልፍ እነሆ ተጽፏል። ከዚህም በኋላ ገንዘቡን ሁሉ ወስዶ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጠ። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ ሀገረ ገምኑዲ ሔደ በእግሩም ሲጓዝ በባሕሩ ዳርቻ ሉስዮስ የሚባለውን መኰንን አገኘው በፊቱም ቁሞ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመነ። መኰንኑም ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለት በእርሱ ላይም የሚደርሰውን ሁሉ ነግሮት አጽናናው። ❤ ከዚህም በኋላ መኰንኑ ወደ ሰሜን አገር ሲጓዝ የከበረ ኖብን ከእርሱ ጋራ በመርከብ ወሰደው በመርከቡም ምሰሶ ላይ ዘቅዝቆ ሰቀለው መኰንኑም ሊበላና ሊጠጣ ተቀመጠ በመኰንኑም እጅ የነበረው ጽዋ ወዲያውኑ እንደ ደንጊያ ሆነ የወታደሮቹም ዐይኖቻቸው ታወሩ የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ወርዶ አባ ኖብን ፈትቶ ከተሰቀለበት አወረደው በአፍንጫውና በአፉ የወረደውንም ደሙን አሻሸለት። ❤ ከዚህ በኋላም መልካም ነፋስ ነፍሶ መርከቢቱ ተጓዘች። ወደ አትሪብ ከተማም ደረሱ ወታደሮችም ይህን ድንቅ ተአምር አይተው ትጥቃቸውን ፈተው በመኰንኑ ፊት ጣሉ። ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመኑ ሰማዕታትም ሆነው ራሳቸውን ቆረጡአቸው የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ። መኰንኑም በአትሪብ ከተማ ቅዱስ አባ ኖብን ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው በብረት ዐልጋ ላይም አስተኝተው ከበታቹ እሳትን አነደዱ በጸለየ ጊዜም እግዚአብሔር ከእሳት አዳነው። ❤ ከዚህም በኋላ በመጋዝ መገዙት ሕዋሳቱንም ቆራረጡ የእግዚአብሔር መልአክም ወርዶ አዳነው ያለ ጉዳትም በጤና አስነሣው። ከዚህም በኋላ ወደ እስክንድርያ ከተማ ወሰዱት በዚያም ብዙ አሠቃዩት በላዩም እባቦችን ሰደዱ ግን አልቀረቡትም ከእባቦችም አንዱ ሒዶ በመኰንኑ አንገት ተጠመጠመ ያስጥሉትም ዘንድ ሟርተኞቹን አዘዛቸው ግን አልተቻላቸውም ከዚህም በኋላ ያድነው ዘንድ ቅዱስ አባ ኖብን ለመነው ቅዱሱም ከይሲውን ትቶት ከአንገቱ እንዲወርድ አዘዘው። ❤ መኰንኑም ሁለተኛ በእሳት እንዲአቃጥሉት ሟርተኞችንና ሥራየኞችን አዘዛቸው እሳቱም ምንም አልነካውም። አቅፋሐስ ከሚባል አገርም ዮልዮስ መጣ ከእርሱም እንደ ተረዳ ገድሉን ጻፈ። መኰንኑም ማሠቃየቱን በሰለቸ ጊዜ አንገቱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። ❤ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ተገልጾለት አጽናናው እንዲህ ብሎም ቃል ኪዳን ሰጠው "ሥጋህ በሚኖርበት ቦታ ከእርሱ ታላቅ ፈውስ ይሆናል እንዲሁም በመከራው ጊዜ ስምህን በመጥራት ከእግዚአብሔር ርዳታ ለሚሻ ሁሉ ድኅነት ይደረግለታል። መታሰቢያህንም ለሚያደርግ ሁሉ የተራበ ለሚያጠግብ፣ የተጠማም ለሚያጠጣ፣ ለቤተ ክርስቲያንም በስምህ መባ ለሚሰጠው፣ የገድልህንም መጽሐፍ ለሚጽፍ ኃጢአቱን ይቅር እለዋለሁ መንግሥተ ሰማያትንም አወርሰዋለሁ"። ❤ ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡ ተጋድሎውንም ፈጸመ ሥጋውንም ቅዱስ ዮልዮሰ አንሥቶ ከሁለት አገልጋዮቹ ጋራ ንሒሳ ወደ ሚባል አገሩ ላከው። የመከራውም ወራት በተፈጸመ ጊዜ አብያተ ክርስቲያናትን ሠሩለት በውስጣቸውም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ አባ ኖብ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ስምዖን፦ ይህም ቅዱስ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ሁለተኛ የሆነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ነው። አገሩም ከምሥራቅ አገር ሰዎች ወገን ነው። ወላጆቹም ከእስክንድርያ በስተምዕራብ ወዳለች በውስጧም የቅዱስ ሳዊሮስ ሥጋ ወደ አለባት ገዳም አመጠትና በዚያ መንኵሶ ጽሕፈትን ተማረ የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍት ሁሉ አጠና ቅስናም ተሾመ። ❤ ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳት ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር መረጠው። በተሾመ ጊዜም መንፈሳዊ መምህሩ የሊቀ ጵጵስናውን ሥራ አስተማረው በጾምና በጸሎት እየተጋደለ ኖረ። እንጀራና ጨውም አይበላም ነበር ነገር ግን በእሳት ያላበሰሉትን ጎመን ከተልባ ጋራ ይበላ ነበር። እንዲህም አድርጎ ደማዊት ነፍሱን ለነባቢት ነፍሱ አስገዛ። ❤ እግዚአብሔርም ታላላቅ የሆኑ ብዙዎች ድንቆችንና ተአምራትን በእጆቹ ላይ አደረገ ከእነዚህም ከእስክንድርያ ካህናት ክፉዎች ሰዎች ቀኑበት ወደመተተኞችም ሒደው ብዙ ገንዘብ ሰጧቸው የሚገድል መርዝንም አዘጋጁለት እሊህ ክፉዎችም ያን መርዝ ወስደው ከሚጠጣው መጠጥ ጋራ በብርሌው ውስጥ ደባለቁት ጠጥቶም ይባርካቸው ዘንድ እንዲጠጣ እየለመኑት ለሊቀ ጳጳሳቱ ሰጡት እርሱም ቅዱስ ቍርባንን ከተቀበለ በኋላ ያንን መርዝ ጠጣው ከክፉም ነገር ምንም ምን አልደረሰበትም ሁለተኛም ሦስተኛም ሰጥተውት ምንም ምን አልጎዳውም ከመዳኑም የተነሣ አደነቁ። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ ገበያ ሒደው ሁለት አዲስ በለስን ገዙ በውስጡም የሚገድል መርዝን አደረጉ ቅዱስ ቍርባንን ከመቀበሉ በፊት በጾም ሳለ ይሰጡት ዘንድ ተስማሙ መሠርያኖች ይህን በለስ ከቍርባን በፊት ቢበላ ሆዱ ይሠነጠቃል ብለዋቸው ነበርና። ያን ጊዜም ወደርሱ በተንኮል ሒደው ከዚያ በለስ ይበላ ዘንድ ሊቀ ጳጳሳቱን ለመኑት አብዝተውም አስገደዱት ከቅዱስ ቍርባን በፊት ሳይፈቅድ በእጁ ውስጥ አደረጉለትና በላ ነገር ግን መሠርያኖች እንዳሉአቸው አልሆነም ሆዱም አልተሠነጠቀም ነገር ግን አርባ ቀን ታመመ።

ሀገርም ያለንስሓ የሕፃናትና የጎልማሶች ሞት አይሁን፣ እስከ ዘለዓለምም ድረስ ጸሎት ከእርሷ አይቋረጥ" አለው፡፡ ❤ ጌታችንም ለአባ ዘዮሐንስ ይህን ከተናገረው በኋላ ቡራኬ ሰጥቶት ከቅዱሳን መላእክት ጋር ወደቀደመ ቦታው ዐረገ፡፡ ጻድቁ በ 105 ዓመታቸው ሐምሌ 24 ቀን በክብር ዐርፈዋል፡፡ ከአባታችን አቡነ ዘዮሐንስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸውም ይማረን!። ምንጭ፦ ገድለ አቡነ ዘዮሐንስ።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ሄላ_ድንግል፦ ባሕታዊ አቡነ ሄላ ድንግል የትውልድ ሀገራቸው ባሕርዳር ነው። በብሕትውናቸው እጅግ የታወቁ ወንጌልን ዞረው ሲያስተምሩ ሕይወታቸው ያለፈ ታላቅ አባት ናቸው። እጅግ ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትንም በማድረግ ይታወቃሉ። ዓባይ በክረምት ሞልቶ ለመሻገር አስቸጋሪ ሆኖ ቢያገኙት በቅዱስ መስቀላቸው ባርከው ለሁለት ከፍለውት ተሻግረዋል። ወንዙ ሳይቀር ቆሞ ያሳለፋቸው ባሕታዊው አቡነ ሄላ ድንግል ወንጌልን ሲሰብኩ፣ ሕሙማንን ሲፈውሱ ኖረው በመጨረሻ ከዚህ ዓለም ድካም ሐምሌ 24 ቀን ዐርፈው ጎጃም ደብረ ጽላሎ ተቀብረዋል።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ጊዮርጊስ_ዘመንበረ_ኢትዮጵያ፦ እኚህ ጻድቅ ሀገራቸው ጎጃም ሲሆን የአባታቸውና የእናታቸው ሀገር ግን ሰሜን ጎንደር ናቸው። ሲወለዱ መልአክ መጥቶ ወስዶ 24ቱ ካህናሀ ሰማይን አሳይቶ ቅዱስ ያሬድም ሲዘምር ጥዑም ዜማውን አሰምቷቸውል። የቅዱስ ያሬድም ፍቅር በዚያው ልባቸው ተቀርጾ ቀረ። ❤ ጻድቁ ዋሸራ ገዳም ሁሉንም ተምረው ጨርሰው በ25 ዓመታቸው ከመነኰሱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅዱስ ያሬድ ስም ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል። ታቦቱንም አስገብተው በዚያው እያገለገሉ ሲኖሩ "እንደ ኤልያስና እንደ አንተ ሞትን እንዳላይ ለምንልኝ..." እያሉ ቅዱስ ያሬድን ዘወትር ሲማፀኑት ቅዱስ ያሬድም አንድ ቀን ከእነ አቡነ አረጋዊ፣ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘርዐ ቡሩክ ዘግሽ ጋር በመሆን ተገልጦላቸው "አይዞህ ፈጣሪዬ ያልከውን ያደርግልሃል" ብሏቸዋል። ❤ አስደናቂውን ባለ ሦስት ዓምድ የሆነውን የቅዱስ ያሬድንም ገድል የጻፋት እሳቸው ነበሩ ነገር ግን ቅዱስ ገድሉን ደርቡሾች ከወሰዱት በኋላ የት እንደደረሰ አይታወቅም። ቅዱስ ገድሉም 382 ገጽ ያሉት ሲሆን 69 አስደናቂ ሥዕላት ነበሩት፣ በ132 ሐረጎችም ያሸበረቀ ነበር። ጻድቁ ቅዱስ ያሬድን "እንደ አንተ እንዳልሞት ጸልይልኝ" ብለው በለመኑት መሠረት ራሱ ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት ቦታ በሰሜን ተራራ ምድረ ጸለምት ተሰውረዋል። በስማቸው የተሠራው ቤተ ክርስቲያን ጎንደር ይገኛል። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳና ቅዱሳን በዓላት።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #ሐምሌ_፳፬ (24) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያውያን_ጻድቃን ለአባቶቻችን ጣና ደሴት ላይ የሚገኘውን ክብራን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምን ለመሰረቱት #ለአቡነ_ዘዮሐንስ_ዘክብራን የዕረፍት በዓል፣ #ለአባ_ተክለ_አዶናይ_ዘደብረ ሊባኖሱና #ለአቡነ_ተወልደ_መድኅን_ለዕረፍታቸው በዓል፣ #ለባሕታዊ_አባ_ሄላ_ድንግል_ለበዐላቸው መታሰቢያና #ለአቡነ_ጊዮርጊስ_ዘመንበረ_ኢትዮጵያ ለበዐላቸው መታሰቢያ በሰላም አደረሰን።                          ✝ ✝ ✝ ❤ #አቡነ_ዘዮሐንስ_ዘክብራን፦ ይኸውም አባቱ ዘካርያስና እናቱ ሶፍያ እግዚአብሔርን በማመን የተመሰገኑ ምግባር ሃይማኖታቸው የቀና ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የሀገር ሰዎችም መክረው ዘካርያስን በእነርሱ ላይ ጌታና ገዥ አደረጉት፡፡ እርሱም በጥሩ አገዛዝ በፍቅር ገዛቸው፡፡ እነርሱም እንደ አሽከሮች ሆኑት፣ እርሱም እስከ አማራ ጠረፍ ድረስ ለሸዋ ሰዎች እንደ ቸር እረኛ ሆናቸው፡፡ ዘካርያስና ሚስቱ ሶፍያም በጎ ሥራን ሁሉ አላቋጡም፡፡ ምጽዋትን መስጠትን፣ ከገንዘባቸውም ከፍለው ለእግዚአብሔር አሥራት መስጠትን አላቋረጡም፡፡ የተቸገሩትን፣ የተራቡትንና የተጠሙትን ሁሉ ያበላሉ፣ ያጠጣሉ፡፡ ይህንንም ሲሄዱም ሲመለሱም ሁልጊዜ ያደርጋሉ፡፡ ❤ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስንና የቅድስት ድንግል ማርያምን፣ የጻድቃንና የሰማዕታን መታሰቢያም ያድርጋሉ፡፡ ልጅም አልነበራቸውምና ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ይማፀኑ ነበር፡፡ ሶፍያም ጠዋት ማታ እንዲህ እያለች ትጸልይ ነበር፡- "መካን ለነበረች ለሐና ልጅ እንደሰጠኻት፣ ለአብርሃም ሚስት ለሣራም፣ ለጸጋ ዘአብ ሚስት እግዚእ ኀረያም እንደሰጠኻቸው አቤቱ እንደ እነርሱ አንተን ደስ የሚያሰኝህን ልጅ ስጠኝ" እያለች እመቤታችንንም እየተማፀነች ታለቅስ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም መጥምቁ ዮሐንስን የመሰለ ልጅ "አባ ዘዮሐንስ" የተባለ ቅዱስ ልጅ ሰጣቸው፡፡ እሱም በሸዋ፣ በመራቤቴ እስከ አማራ ጠረፍ ድረስ የሚያበራ መብራት ሆነ"፡፡ በኋላም በጣና ሐይቅ ላይ የሚገኘውን "ክብራን ቅዱስ ገብርኤል ገዳምን" የመሠረቱት እኚህ አባ ዘዮሐንስ የተባሉ ጻዲቅ ናቸው፡፡ ❤ ቀጥሎ ደግሞ ታሪካቸውንና የተሰጣቸውን አስደናቂ ቃልኪዳን እንመለከት፡- ለአባ ዘዮሐንስ በጌታ ዘንድ ታዘው ነቢዩ ኤልያስና ዮሐንስ በእኩለ ሌሊት ተገልጠውላቸው አስኬማና ቆብ ሰጥተዋቸዋል፡፡ እመቤታችንም ተገልጣላቸው ወደ ደብረሊ ሊባኖስ ሄደው እንዲመነኵሱ ነግራቸው ኤልያስና ዮሐንስ እየመሩ ከቦታው አድርሰዋቸዋል፡፡ ሰባት ዓመትም በዚያ ሲያገለግሉ ኖሩ፡፡ ስግታቸውም ሁልጊዜ ስምንት ሺህ ነበር፡፡ ጌታም በደብሊባኖስ ሲያጥኑ ተገልጦላቸው ስምህ "ዘዮሐንስ ይሁን" ብሎ ትልቅ ቃልኪዳን ተጥቷቸዋል፡፡ ደመናም ተሸክማ ወስዳ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም አድርሳቸው በዚያም ከቆዩ በኋላ ደመናዋ መልሳ ወደ ሸዋ አምጥታቸዋለች፡፡ በትግራይ ለራሳቸው መጠለያ ሲሠሩ የጌታ ፈቃድ አልነበረምና ከባድ የሆድ ሕመም መጣባቸው፡፡ ደመናዋም ደራ ሮቢት አደረሰቻቸው፡፡ በዚያም እንደደረሱ ገብርኤልና መስቀል ክብራ በሚባሉ እግዚአብሔርን በሚወዱ ደጋግ ባለትዳሮች ቤት ዕረፍት አደረጉ፤ ለሰባት ቀናትም በዚያ ቆዩ፡፡ ከዚያም መልአኩ ተገልጦ ወደ ደሴቷ እንዲሄዱና እርሷም ዕጣ ክፍላቸው እንደሆነች ነገራቸው፡፡ ❤ አባ ዘዮሐንስም በደሴቷ ላይ በጾም በጸሎት ጸንተው ተቀመጡ፣ ትሎችም ሰውነታቸውን እንዲመገቡ ያድርጉ ነበር፡፡ ገብርኤልና መስቀል ክብራ የተባሉትም ደጋግ ባለትዳሮች የሚያስፈልጋቸውን ይወሰዱላቸው ነበርና ባገኙዋቸው ጊዜ ትሎቹን ከሰውነታቸው ላይ ሲያራግፉላቸው "ተዋቸው እኔን ሊመገቡ ተፈቅዶላቸዋል" አሏቸው፡፡ አባታችን አንድ ቀን የሰው ድምፅ ሰምተው ወደ ውጭ ወጥተው ሲመለከቱ የአካባቢው ሰዎች አንድ ማድጋ ወተት፣ አንድ በግና አንድ ከብት ለዘንዶ ሲገብሩ አይተው ያንን ዘንዶ በሥላሴ ስም በመስቀል ምልክት አማትበው ከሰዎቹ ፊት ገደሉት፡፡ ይህን የሰማውና ሰዎቹን እንዲገብሩ የላካቸው ጃን ቹሐይ የተባለው ጣኦት አምላኪ የአገሩ ሹም "የማመልከውን ዘንዶ እንዴት ትገድላለህ?" በማለት እንዲታሰሩ አደረጋቸው፡፡ ንጉሥ ዐምደ ፅዮንም ይህን ሲሰማ ሠራዊቱን ልኮ ያንን ጣኦት አምላኪ የአገሩን ሹም ገድለው አባ ዘዮሐንስ እንዲፈቷቸው አደረገ፡፡ ❤ አባ ዘዮሐንስም ወንጌልን እያስተማሩ፣ ሙትን እያስነሱና ታላላቅ ተአምራትን እያደረጉ በደሴቷ ላይ ተወስነው ተቀመጡ፡፡ በደመናም ተጭነው ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው ታቦተ ቅዱስ ገብርኤልን አምጥተው በደሴቷ ላይ ክብራን ገብርኤል ገዳምን መሠረቱ፡፡ ደመናም ደሴቷ ላይ ስታደርሳቸው ኤልያስና ዮሐንስ በቀኝ በግራው እየተራዱአቸው እርሳቸው ሠራዒ ቄስ ሆነው ቀደሱ፡፡ ደሴቷንም መጀመሪያ እንደመጡ ባሳረፈቻቸው ደገኛ ሴት ስም ሰየሟት፡፡ ለሴቶች መነኰሳት ከዚያው አጠገብ የሚገኘውን እንጦንስ ገዳምን አድርገው ክብራን ገብርኤልን ለወንዶች ብቻ አደረጓት፡፡ ❤ አንድ ቀን አባ ዘዮሐንስ በደብረ ሊባኖስ መሥዋዕት ለማቅረብ እያጠነ ሳለ ለስም አጠራሩ ክብርና ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሌላ ሀገር የመጣ እንግዳ ሰው መስሎ ታየውና "ሰላም ለአንተ ይሁን" አለው፡፡ አባታችን ዘዮሐንስም "ወንድሜ ሆይ! የእግዚአብሔር ፍቅር አንድነት ከአንተ ጋር ይሁን" አለው፡፡ "አንተ እንግዳ ሰው ከየት ሀገር የመጣህ ነህ? ከዚህ በፊት አላውቅህም" አለው፡፡ ጌታችንም ከልቡናው ፍግግ አለና "ከእናትህ ማኅፀን ሳትወጣ እኔ አውቅሃለሁ" አለው፡፡ ይህንንም ብሎ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ ያደረገለትን ከመወለዱም አስቀድሞ የሆነውን ሁሉ፣ ከተወለደም በኋላ እስከዚያ ቀን ድረስ ያደረገለትን፣ አባቱንም በአመፀኛው በጎዶልያ እጅ ከመሞት እንዳዳነው፣ እናቱንም ዕቁባቱ ሊያደርጋት እንደነበረ ምሥጢሩንም ሁሉ ነገረው፡፡ ይህንንም ብሎ ዳግመኛ ተነጋገረው፡- "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ዘዮሐንስ ይሁን፣ አንተ የዓለሙ ሁሉ ደስታ ነህና የሚያለቅሱም በአንተ ደስ ይላቸዋል" አለው፡፡ "በደመናም ተጭነው ኢየሩሳሌም ደርሰው ታቦተ ቅዱስ ገብርኤልን አምጥተው ክብራን ገብርኤል አስገብተው በዚያም ሲኖሩ በጣም አርጅተው ነበርና ራሳቸውን ወደ ምድር አጎንብሰው ይሄዱ ነበር፡፡ ❤ ከዚህም በኋላ ሐምሌ 10 ቀን ለዓርብ አጥቢያ ሲጸልዩና በግንባራቸው ወደ ምድር ሲሰግዱ ለስም አጠራሩ ስግደት የሚገባው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክረስቶስ ቅዱሳን ሚካኤልንና ገብርኤልን አስከትሎ መጥቶ "ወዳጄ አባ ዘዮሐንስ ሆይ! ከድካም ወደ ዕረፍት፣ ከበሽታ ወደ ሕይወት፣ ከዚህ ዓለም ዐይን ወዳላየውና ጆሮ ወዳልሰማው ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት አሳርፍህ ዘንድ ወደ አንተ መጣሁ" አለው፡፡ ይህንንም ብሎ ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ ከእርሱ በረከት እንደማይጠፋ ቃልኪዳን ሰጠው፡፡ "ገድልህን የሚጽፍ ወይም የሚያነብ እኔን እንደመሰለ እንደ መልከጼዴቅ ካህን በእኔ ዘንድ የተመረጠና የተወደደ ይሆናል፣ በበዓልህ ማኅሌት የቆመ የመላእክት ባልንጀራ ይሆናል፣ እነዚህን ልጆችህንም የመላእክት አምሳያ አደርጋቸዋለሁ" አለው፡፡ "ይህችን ደሴት እንደ ኢየሩሳሌም ሀገሬ፣ እንደ ደብረ ዘይትና ለባሪያዬ ለሙሴ ሕግን እንደ ሰጠሁባት እንደ ደብረ ሲና አድርጌያታለሁ፣ በረከቴም ከእርሷ አይታጣም፣ እኔም ከእርሷ አልለይም ይልቁንም በተጠመቅሁባት ቀን ከዚህች ገዳምህ አልለይም፣ የዚህች ደሴትና የሀገሬ የኢየሩሳሌም መክፈቻ በአንድ ላይ አንድ ይሁን" አለው፡፡ "ከዚህች

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #ሐምሌ ፳፫ (23) ቀን። ❤ እንኳን #ለታላቋ_ሰማዕት ሰይጣንን በራሱ ጠጉር ይዛ ለደበደበችው በእግሮቿም ለረገጠችው #ለቅድስት_መሪና ለዕረፍት በዓል፣ ከቀጰዶቅያ አገር ለሆነ በመስቀል ላይ ጌታችንን ከሞተ በኋላ የቀኝ ጎኑን ለወጋው #ለቅዱስ_ለንጊኖስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ #ከአብጥልማዎስ ከመታሰቢያው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                         ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #ሰማዕቷ_ቅድስት_መሪና፦ የዚችም ቅድስት የአባቷ ስም ዳኬዎስ ነበር እርሱም በአንጾኪያ ሀገር ለጣዖታት ካህናት አለቃ ነበር ያን ጊዜ ንጉሡም ከሀዲው ዳኬዎስ ነበር። አምስት ዓመትም በሆናት ጊዜ እናቷ ሞተች አባቷም ከከተማ ውጭ ለምትኖር ሞግዚት ሰጣት እርሷም ክርስቲያናዊት ነበረች የክርስቶስ የሆነ የሃይማኖት ትምህርትን ሁሉ አስተማረቻት። ዐሥራ አምስት ዓመትም በሆናት ጊዜ አባቷ ሞተ።  ❤ ከዚህም በኋላ ሰዎች የሰማዕታትን ተጋድሏቸውንና መከራቸውን ሲናገሩ ሰምታ የጌታ ክርስቶስ ፍቅር በልቧ አደረ በሰማዕትነት መሞትንም ፈልጋ ሔደች።  በዚያን ጊዜም ከሀዲ መኰንን ወደዚያች አገር ደረሰ እርሷንም አይቶ ወደርሱ አስመጣትና "ከወዴት ነሽ" አላት "ክብር ይግባውና ከጌታ ኢየሱስ ሰዎች ወገን ነኝ ስሜም መሪና ነው" አለችው። ደም ግባቷንና ላሕይዋንም አይቶ መታገሥ ተሳነው እሺ ትለው ዘንድ በብዙ ነገር አባበላት። እርሷ ግን ረገመችው የረከሱ አማልክቶቹንም ረገመች።  ❤ ያን ጊዜም በብረት ዘንጎች ይደበድቧት ዘንድ ደሟ እንደ ውኃ እስኪፈስ ሕዋሳቷን ይቆራርጡ ዘንድ አዘዘ። ያን ጊዜም ወደ ጌታ እግዚአብሔር ጸለየች የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም መጥቶ አዳናት። ሁለተኛም ወደ ወህኒ ቤት ያስገቧት ዘንድ አዘዘ ጌታችንም ወደ ሰማይ አውጥቶ የቅዱሳን ሰማዕታትንና የጻድቃንን ማደሪያዎች አሳይቶ ወደ ቦታዋ መለሳት።  በማግሥቱም ሥጋዋን በመጋዝ እንዲሠነጥቁ ጐኖቿንም እንዲሰነጣጥቁና በእሥር ቤት እንዲጥሏት አዘዘ ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ አዳናት። ❤ በወህኒ ቤቱ ውስጥም ቁማ ስትጸልይ እጅግ የሚያስፈራ ታላቅ ዘንዶ ወደ ርሷ መጣ በአየችውም ጊዜ ደነገጠች ሰውነቷ ሁሉ ተንቀጠቀጠ መናገርም ተሳናት። ያን ጊዜም እጆቿ በመስቀል ምልክት አምሳል እንደተዘረጉ በልቧም ስትጸልይ ወደርሷ ቀርቦ ዋጣት። ያን ጊዜም ሆዱ ተሠንጥቆ ያለ ጉዳት ወጣች እግዚአብሔርንም አመሰገነችው።  ❤ ሁለተኛም በጥቁር ሰው አምሳል ሰይጣንን አየችው እጆቹም በጉልበቶቹ ላይ ተጨብጠው ነበር። ፊቷንም በመስቀል ምልክት አማትባ በራሱ ጠጉር ይዛ ደበደበችው። በእግሮቿም ረገጠችው ያን ጊዜም ክብር ይግባውና የጌታ ክርስቶስ ዕፀ መስቀል ተገለጠላት በላዩም ነጭ ርግብ ተቀምጣ እንዲህ ብላ አነጋገረቻት "መሪና ሆይ የመንፈስ ቅዱስን የጸጋ አረቦን ተቀብለሻልና ደስ ይበልሽ"።  ❤ በማግሥቱም መኰንኑ ልብሷን አራቁተው ዘቅዝቀው ሰቅለው እንዲአቃጥሏት ደግሞም ውኃ ከአፈሉበት ጋን ውስጥ እንዲጨምሩዋት አዘዘ። በውስጡም ሁና ስትጸልይ ከሰማይ ርግብ መጣ በአፉም ውስጥ የወርቅ አክሊል ነበር ማሠሪያዋንም ፈትቶ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሦስት ጊዜ አጠመቃት እግዚአብሔርንም እያመሰገነች ከውኃው ውስጥ ወጣች።  ❤ መኰንኑም እንደ ዳነች በአየ ጊዜ ራሷን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። ወደ ሰማዕትነቱ ቦታም በደረሰች ጊዜ ነፍሷን በፍቅር ይቀበል ዘንድ ወደ ጌታችን ጸለየች። ክብር ይግባውና ጌታችንም ተገለጠላት ስሟን ለሚጠራ መታሰቢያዋንም ለሚያደርግ ገድሏንም ለሚጽፍ ወይም ለሚያነበውና ለሚሰማው ኃጢአቱን እንዲአስተሠርይለት ለርሷም ርሱን እንዲሰጣት ቃል ኪዳን ሰጣት።  ❤ ከዚህም በኋላ ራሷን በሰይፍ ቆረጡ ከእርሷም ብዙ ተአምር ተገለጠ ዕውራን አይተዋልና፣ ሐንካሶች በትክክል ሔደዋልና፣ ደንቆሮዎችም ሰምተዋልና፣ ዲዳዎችም ተናግረዋልና ቁጥር የሌላቸው ብዙ ሰዎችም ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቷ በቅድስት መሪና ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።                          ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #ወታደሩ_ሰማዕት_ቅዱስ_ለንጊኖስ፦ ይህም ቅዱስ ከጲላጦስ ጭፍሮች ውስጥ ነበር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ደኅንነት መከራ እንዲቀበል የፈቀደበት ሰዓት በደረሰ ጊዜ በእርሱ ላይ የፈለጉትን ያደርጉ ዘንድ ለዐመፀኞች ፈቅዶላቸው ነበር። ይህም ለንጊኖስ ጌታን ይሰቅሉት ዘንድ ጲላጦስ ከአዘዛቸው ወታደሮች ውስጥ ነበር።  ❤ በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ ጌታችንን የቀኝ ጐኑን ወጋው ከጐኑም ደምና ውኃ ፈሰሰ። ይህንንም አይቶ እጅግ አደነቀ ከዚህም በፊት ፀሐይ እንጨለመ፣ ጨረቃ ደም እንደሆነ፣ ዐለቱም እንደተሠነጠቀ፣ ሙታንም እንደተነሡ አይቶ ነበር።  ❤ ጌታችንም በተነሣ ጊዜ ስለ ትንሣኤው የሆነውን ሰምቶ ይህን ምሥጢር ይገልጽለት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ሐዋርያው ጴጥሮስንም ላከለት እርሱም ነቢያት ስለ ጌታችን፣ ስለ መከራው፣ ስለ መሰቀሉ፣ ስለ መሞቱ፣ ስለ መነሣቱ፣ ስለ ዕርገቱም ትንቢት እንደተናገሩ ነገረው። እርሱም ከቅድስት ድንግል በሥጋ ተወልዶ ዓለምን ለማዳን የመጣ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደሆነ አስረዳው።  ❤ ያን ጊዜም በቅዱስ ጴጥሮስ ቃል አመነ የምድራዊ ንጉሥ አገልግሎትንም ትቶ ወደ ቀጰዶቅያ ሔደ በውስጧም ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንደ ሐዋርያት ሰበከ። አይሁድም በጠላትነት ተነሡበት በመሳፍንትም ዘንድ ከሰሱት በላዩም የሐሰት ምስክር አስነሡበት ስለዚህም ሐምሌ 23 ቀን ራሱን በሰይፍ አስቆረጡት የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ ቅዱስ ለንጊኖስ በጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 23 ስንክሳር።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ "#ሰላም_ለለንጊኖስ ዘኂሩተ አምላክ ቀጸበቶ። ለጴጥሮስ ረድእ ከመ ይትወከፍ ትምህርቶ። ከመ ኢያሐስብ ቦቱ ዘኲናለ እዱ ርግዘቶ። በኃጢውኢሁ ለዘኢፈቀደ ሞቶ። ምሕረቶ እሴብሕ ወዓዲ ትዕግሥቶ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_23።                          ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ኢይቀሥፍ ወትረ ወኢይትመዓዕ ዘልፈ። አኮ በከመ ኃጢአትነ ዘገብረ ለነ። ወኢፈደየነ በከመ አበሳነ"። መዝ 102፥9-10 ። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ቆሮ 9፥5-ፍ.ም፣ ያዕ 2፥14-20 እና የሐዋ ሥራ 16፥13-16። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 19፥31-38። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ የዮሐንስ አፈወርቅ ወይም እግዚእነ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ሐምሌ_፳፫ (23) ቀን። ❤ እንኳን ለመናገሻ ገነተ ጽጌ #ቅዱስ_ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን (አራዳ ጊዮርጊስ) ለቅዳሴ ቤቱ ዓመታዊ በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የበዓሉ_አንገርጋሪ_ግእዝ_ዜማ፦ ሃሌ ሉያ "ተቀደሲ ወንሥኢ ኃይለ ኦ #ቤተ_እግዚአብሔር እስመ ናሁ ንጉሥኪ በጽሐ ዘያበርግህ ለኪ በኃይሉ ለዛቲ ቤት ሣረራ አብ ቀዲሙ ለዛቲ ቤት ሐነፃ ወልድ ለዛቲ ቤት ወፈጸማ መንፈስ ቅዱስ"። ትርጉም፦ #ቤተ_እግዚአብሔር ሆይ ተቀደሺ ኃይልንም ልበሺ ንጉሥሽ እያበራ ወደ አንቺ ደርሷልና፡፡ ይእቺን ቤት አስቀድሞ አብ ሠራት ወልድ አነፃት መንፈስቅዱስ ፈፀማት፡፡ #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በድጓው_ላይ።                             ✝ ✝ ✝ ❤ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ በአደዋ ጦርነት ጊዜ ለረዳቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ከድሉ ከተመለሱ በኋላ በአዲስ አበባ መሐል ከተማ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ቤተክርስቲያን አሠሩ ስሟንም ገነተ ጽጌ ብለው ሰየሟት የባረኳትም ሊቀ ጳጳሱ ግብፃዊው አቡነ ማቴዎስ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት የቅዱስ ጊዮርጊስ ልመናው አማላጅነቱ ከእኛ ጋር ይሁን አሜን!!! ተኣምረ ጊዮርጊስ ተአምር17 ላይ።                                                            ✝ ✝ ✝ ❤ #የበዓሉ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወንሰግድ ውስተ መካነ ኀበ ቆመ እግረ እግዚእነ። ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ። አንተ ወታቦተ መቅደስከ"። መዝ131፥7-8 ወይም መዝ90፥13። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 12፥23-30።                                     ✝ ✝ ✝ ❤ #የበዓሉ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል። እግዚአብሔር ውስተ ማዕከላ ኢትተሐወክ። ወይረድኣ እግዚአብሔር ፍጽመ"። መዝ 45፥4-5 ወይም መዝ 121፥2-3። የሚነበቡት መልዕክታት ኤፊ 2፥13-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 2፥4-11 እና የሐዋ ሥራ 1፥12-15። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 16፥13-20። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም የአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የቅዳሴ ቤት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።                   

❤ መኰንኑም በሰማ ጊዜ ወደርሱ አስቀርቦ ጠየቀው እርሱ ግን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስን እንደሚያመልከው በመኰንኑ ፊት ታመነ ቅዱስ ጳውሎስ "ከፈጣሪዬ ከክርስቶስ ማን ይለየኛል እንዳለ ከታናሽነቴ ጀምሮ በፍጹም ልቡናዬ አመልከዋሁ ለእርሱም እሰግዳለሁ" አለው። መኰንኑም እጆቹንና እግሮቹን አሥረው በወህኒ ቤት ውስጥ እንዲጥሉት አዘዘ እንዲሁም አደረጉበት። በማግሥቱም መኰንኑ አቅርቦ እንዲህ አለው "በምን ኃይል የንጉሥን ትእዛዝ ደፍረህ ትተላለፋለህ ሰዎችንም አማልክትን ከማምለክ በምን ኃይል ትመልሳቸዋለህ" ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት። "በእውነት ሰዎች ሁሉ ክብር ይግባውና ወደጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት እንዲገቡ እኔ እሻለሁ አንተም ስሕተትህን ትተህ ክብር ይግባውና ኢየሱስ ክርስቶስን ብታመልከው የረከሱ አማልክትንም ማምለክ ብትተው የዘለዓለም መንግሥትን በወረስህ ነበር"። ይህንንም በሰማ ጊዜ መኰንኑ እጅግ ተቆጣ ደሙ እንደ ውኃ እስኪፈስ ድረስም ይገርፉት ዘንድ አዘዘ እርሱም እግዚአብሔርን ፈጽሞ ያመሰግነው ጀመረ። ❤ ከወታደሮችም አንዱ አዘነለትና በጆሮው አሾከሾከ "እኔ ስለአንተ አዝናለሁ ጉልምስናህንም ላድን እወዳለሁ አንተ ለአማልክትም እንደምትሠዋ ለመኰንኑ አንዲት ቃልን ብቻ ተናገር እኔም እዋስሃለሁ" አለው። ቅዱሱም ሰይጣን ከኋላዬ ሒድ ብሎ ገሠጸው። መኰንኑም ጭካኔውን አይቶ ሥጋው እስከ ሚቆራረጥ ደሙም እንደ ውኃ በምድር ላይ እስኪፈስ ድረስ ሥቃዩን እጥፍ ድርብ አደረገበት። ❤ ከዚህም በኋላ በውኃ እንዲዘፍቁት በእግሩም እንዲጐትቱትና በወህኒ ቤት እንዲጥሉት አዘዘ በዚያም ነፍሱን አሳለፈ ገድሉንም ፈጸመ። የምታምን ሀብታም ሴት መጥታ ለወታደሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥታ የቅዱሱን ሥጋ ወሰደች በአማሩ ልብሶችም ገነዘችው የወርቅ ሣጥንም አሠርታ በውስጡ አኖረችው። ሥዕሉንም አሣለች በፊቱም ሁልጊዜ የሚያበራ ፋና አኖረች። ለዚችም ሴት ቅዱሱ ያደረገላት የድካም ዋጋዋ ሰኔ አንድ ቀን ተጽፎ አለ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ለውንትዮስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ፦ 22 ስንክሳር።                                ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለከ_ለጠራብሎስ_ማኅቶት። ለውንትዮስ ፈጻሚ ሥቃይ ስምዕ በበፆታ። እንዘ ትገብር ለበድንከ ዐራዘ ወርቅ ትርሲታ። ነጺረከ ዘንተ ብዙኅ አፍቅሮታ። ውስተ ቤተ ሞቅሕ ሮጽከ ታድኅኖ ለምታ። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_22።                              ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "እስመ ለመላእክቲሁ ይኤዝዞሙ በእንቲአከ። ከመ ይዕቀቡከ በኲሉ ፍናዊከ። ወበእደዊሆ ሙ ያነሥኡከ"። መዝ 90፥11-12 ወይም መዝ 62፥6 ወይም 62፥6። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 5፥4-12።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ወኢይትኀበር ውስተ ማኅበሮሙ ዘደም። ወኢይዜከር አስሚቲሆሙ በአፉየ። እግዚአብሔር መክፈልተ ርስትየ ወጽዋዕየ"። መዝ 15፥4-5። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ቆሮ 12፥1-11፣ 1ኛ ጴጥ 1፥6-10 እና የሐዋ ሥራ 5፥26-34። የሚነበበው ወንጌል ማር 13፥14-21። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ባስልዮስ ወይም የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ። መልካም የቅዱስ ዑራኤል በዓልና የአቡነ ጴጥሮስ የዕረፍት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #ሐምሌ ፳፪ (22) ቀን። ❤ እንኳን #ለሊቀ_መላእክት_ለቅዱስ_ዑራኤል #ለቅዱስ_ዕዝራ_ሱቱኤል የዕውቀት ፅዋ ላጠጣበት ፤ #ለቅዳሴ_ቤቱ_ዓመታዊ_በዐል፣ ለፋሲለደስ ልጅ #ለቅዱስ_መቃርስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዐል መታሰቢያ፣ #ለቅዱስ_ለውንትዮስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦# ከቅዱስ_መርካሎስ_ከመታሰቢያው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #ሊቀ_መላእክት_ቅዱስ_ዑራኤል፦ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ "በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ 7 መላእክትን አየሁ" ራዕ 8፥2 እንዳለ ሊቃነ መላእክት በቁጥር 7 ናቸው፡፡ እነርሱም፡- ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ቅዱስ ራጉኤል፣ ቅዱስ ዑራኤል፣ ቅዱስ ፋኑኤል እና ቅዱስ አፍኒን ናቸው፡፡ "ዑራኤል" የሚለው ስም "ዑር" እና "ኤል" ከሚሉ ሁለት ቃላት የተመሠረተ ስም ነው፡፡ "ዑራኤል" ማለት ትርጉሙ "የብርሃን ጌታ፣ የአምላክ ብርሃን" ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ዑራኤል ከ7ቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ በመብረቅና በነጎድጓድ ላይ የተሾመ መልአክ ነው፡፡ በመሆኑም መጽሐፈ ሄኖክ እንደሚገልጸው መባርቅት ለጥጋብና ለበረከት እንዲበርቁ ነጎድጓድም ለሰላም እንዲሆን ያሰማራል፡፡ ምሥጢረ ሰማይንና ሰማያዊውን ዕውቀት ሁሉ ለሄኖክ የገለጸለት መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ የፀሐይን፣ የጨረቃን፣ የከዋክብትንና የሰማይ ሠራዊትን ብርሃንን የሚመራው ይኸው ገናና መልአክ ነው፡፡ መጽሐፈ ሄኖክ 28፥13፡፡ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሆኖ በተሰቀለ ጊዜ ክቡር ደሙን በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ በብርሃነ መነሳንስ በዓለም ላይ የረጨው ይኸው ገናና መልአክ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ ❤ ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል ጽዋ ጥበብን አጠጥቶ ሰማያዊውን ምሥጢር የገለጠለት መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ ዕውቀት ተሠውሮበት ለነበረው ለኢትዮጵያዊው ሊቅ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በእመቤታችን ትእዛዝ ጽዋ ጥበብን አጠጥቶ ሰማያዊውን ምሥጢር የገለጠለት ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ "ዑራኤል የተባለ መልአክ ሊረዳኝ መጣ"፡፡ መጽሐፈ ዕዝራ 2፥1፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር የሕይወትና የይቅርታ ዝናም በምድራችን ላይ ያዘንብ ዘንድ እንዲሁም የእርሻችንን አዝመራ በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ ለምግብነት እንዲበቃ ከፈጣሪ ዘንድ ምሕረትን የሚለምን መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ ❤ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም በመልአኩ አማላጂነት እጅግ ብዙ ድርሰቶችን የደረሱት መልአኩ ጽዋ ሕይወትን ካጠጣቸው በኋላ ነው፡፡ በመጀመሪያም አባ ጊዮርጊስ የተወለዱት በቅዱስ ዑራኤል አብሳሪነት ነው፡፡ በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ የተመሠረቱ አብዛኞቹ ቅዱሳት ገዳማት በቅዱስ ዑራኤል መሪነት ነው፡፡ ድርሳኑ ላይ የማይጠቅሳቸው የሀገራችን የከበሩ ቅዱሳት ገዳማትና ቅዱሳን ነገሥታት የሉም፡፡ ❤ የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክን ከልጇ ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስትሰደድ መንገድ እየመራ ወደ ግብጽ እና ወደ አገራችንን ኢትዮጵያ ያመጣቸው ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ እመቤታችንን ከተወደደ ልጇ ጋር በደመና ጭኖ መላ ኢትዮጵያን ካስጎበኛት በኋላ ቅድስት አገራችንን ለእመቤታችን የዐሥራት አገር እንድትሆን ያደረገው መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል በዓመት 3 ዓበይት በዓላት አሉት፡፡ ጥር 22 በዓለ ሲመቱ ነው፡፡ መጋቢት 27 የጌታችንን ክቡር የሆነ ወርቀ ደሙን ለዓለም የረጨበት ነው፡፡ ሐምሌ 22 ቀን ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበትና ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል የዕውቀትን ጽዋ ያጠጣበት ዕለት ነው፡፡                               ✝ ✝ ✝ ❤ #ሰማዕቱ_ቅዱስ_መቃርስ፦ ይህም ሰማዕት የጭፍሮች አለቃ የሆነ የፋሲለደስ ልጅ ነው። ይህንንም ቅዱስ አማልክትን እርሱ እንደማያመልክ በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ዘንድ ወነጀሉት ንጉሥም ወደ እስክንድርያ ወስደው በዚያም እንዲአሠቃዩት አዘዘ። እርሱም ወላጆቹን በተሰናበታቸው ጊዜ ለድኆችና ለችግረኞች እንዲአስቡ አደራ አላቸው። ከዚህም በኋላ ወጥቶ ሔደ ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስም ተገልጾለት አጽናናው የሚደርስበትንም ነገረው። ወደ እስክንድርያ ከተማም በደረሰ ጊዜ በመኰንን ኅርማኖስ ፊት ቆመ መኰንኑም የጭፍሮች አለቃ የፋሲለደስ ልጅ እንደሆነ አውቆ ብዙ አባበለው ለመነውም እርሱ ግን አልሰማውም ከመልካም ምክሩም አልተመለሰም። ❤ ከዚህም በኋላ ሰውነቱ እስከምትቀልጥ ድረስ ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው በሥቃይም ውስጥ እያለ ጌታችን የቅዱሳንን ማደሪያዎችንና የአባቱንና የወንድሙን ማደሪያ አሳየው። ከዚህም በኋላ መኰንኑ ወደ ኒቅዮስ ሀገር ሰደደው በዚያም ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት ምላሱንና ክንዱን ቆረጡት በጎኖቹም ውስጥ በእሳት ያጋሉአቸውን የብረት ችንካሮች ጨመሩ ጌታችንም አዳነው ያለ ጉዳትም በጤና አስነሣው። ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በእጆቹ ላይ ታላላቅ ድንቆችንና ተአምራቶችን አደረገ ከእነርሱም ብዙ ሰዎች የሞተ ሰው ተሸክመው ሊቀብሩ ሲሔዱ አየ። ሁሉም እያዩት ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ማለደ። ስለዚያም ምውት ተነሥቶ ያየውን ይነግራቸው ዘንድ ለመነ። ወዲያውኑም ያ ምውት ተነሥቶ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አምላክና የሁሉ ጌታ እንደሆነ ተናገረ። ይህንንም ድንቅ ተአምር አይተው ብዙ አሕዛብ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ መኰንኑም ተቆጥቶ ያመኑትን ራሳቸውን አስቆረጠ ሰማዕታትም ሆነው የሰማዕታትን አክሊል ተቀበሉ። ❤ በዚያም የእንዴናው ገዥ አርያኖስ ነበረ በተመለሰ ጊዜም ቅዱስ መቃርስን ከእርሱ ጋራ ወሰደው ወደ ሀገረ ሰጥኑፍም በደረሰ ጊዜ መርከቢቱ ቆመች የማትንቀሳቀስም ሆነች እነሆ ጌታችንም ለእርሱ ተገልጦ ተጋድሎውን በዚያ እንደሚፈጽም ነገረው። ❤ ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡ። የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማይ ተቀበለ። ቈስጠንጢኖስም በነገሠ ጊዜ የጣዖታትን ቤቶች እንዲዘጉ አብያተ ክርስቲያናትንም እንዲከፍቱ አዘዘ። ያን ጊዜም ስሙ አውሎጊዮስ የሚባል ምእመን መኰንን አብያተ ክርስቲያናትን ሊሠራ ጀመረ። ቅዱስ መቃርስም ተገለጠለትና ሥጋው ያለበትን ነገረው። መኰንኑም ወደ አመለከተው ቦታ ሔዶ የቅዱስ መቃርዮስን ሥጋ አገኘ ከዚያም ወሰደው ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶ ሥጋውን በውስጥዋ አኖረ። ከእርሱም ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ ቅዱስ ፋሲለደስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #ሰማዕቱ_ቅዱስ_ለውንትዮስ፦ ይህም ቅዱስ ክርስቲያን ከሀድያን ከሆኑ ሠራዊት ጋር ይኖር ነበር ሀገሩም ጠራብሎስ ነው መልኩም ያማረ በገድሉም ፍጹም የሆነ ነበር። አምላክ ያስጻፋቸው መጻሕፍትንም ያነብ ነበር። ይልቁንም የዳዊትን መዝሙር ሁልጊዜ ያነብ ነበር። ባልንጀሮቹ ለሆኑ ወታደሮችም ያስተምራቸው ይመክራቸውም ነበር። እግዚአብሔርንም እንዲፈሩ ያስገነዝባቸው ነበር። የማይጠቅሙ የረከሱ የአማልክትንም ሸክም ከትከሻችሁ ጣሉ ይላቸው ነበር። ከስሕተትም ተመልሰው ክብር ይግባውና በጌታችን ያመኑ አሉ። ከእነርሱም ወደ መኰንኑ ሒደው "ለውንትዮስ አማልክትን አቃለላቸው ሰማይና ምድርን በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ የፈጠረ ክርስቶስ ነው ይላል" ብለው የከሰሱት አሉ።

❤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አባትና እናት የሌላቸውን ሕጻናት ሰብስቦ ማሳደግ የቤተ ክርስቲያን አንዱ ዓላማ መሆኑን በተግባር አሳይተዋል። እርሳቸው ባረፉበት ወቅት ከ200 በላይ ሕጻናት የሚያድጉበት የነበረው ያ ገዳም የነገ ተስፋ የሆኑ ልጆችን በመንከባከቡ በኩል የሃይማኖት መሪዎች ያለባቸውን ታላቅ ኃላፊነት የሚያመለክት ነው። የሌላውን እንኳን ብንተው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጥቂቱ ከሚታዩ ሙከራዎች ውጪ ይህ ነው የሚባል ሕጻናትን የመታደግ እንቅስቃሴ ስታደርግ አይታይም። በሀብት ደረጃቸው የናጠጡ የከተማ አብያተ ክርስቲያናት ለዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ጊዜ ያላቸውም አይመስሉም። የድሃ መብዛት የፈጣሪ ጸጋ ይመስል ድህነትንና ድሃውን በእነርሱ ኑሮ ማድመቂያነት የወሰዱት ይመስላል። ሌላውና የዚህ ዘመን የአገራችንና የቤተ ክርስቲያን ሁነኛ ፈተና የሆነውን ዘረኝነትን በተመለከተ የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ  ሕይወት ብዙ አስተማሪነት አለው። የሚያውቋቸው ሰዎች በሙሉ በአንድነት የሚመሰክሩላቸው በወገን፣ በወንዝ፣ በመንደርተኝነትን የማይጠረጠሩ፣ ዘረኝነትን በፍፁም የሚጠየፉ አባት መሆናቸውን ነው። ቤተ ክርስቲያናችንን ጨምድዶ ለያዛት የዘመነ መሳፍንት ዓይነት መንደርተኝነት፣ ጠባብነት እና ጎሰኝነት እንደ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ያለ ሰው ያስፈልጋል። በምድራውያን ባለ ሥልጣኖች ፊት በሃይማኖታዊ ግርማ እንጂ በማጎብደድ መቆም ያልለመደባቸው ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ራሳቸውን አክብረው አባትነትን፣ ሃይማኖተኝነትን፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስከብሩ መሆናቸውን ብዙዎች ይስማሙበታል። የታሪክ ተመራማሪ እንደመሆናቸው ቤተ ክርስቲያን በቤተ መንግሥት መዳፍ ሥር ስትወድቅ ያለውን ጣጣ በመጻሕፍቶቻቸው መጥቀስ ብቻ ሳይሆን እርሳቸውም ያ ነገር እንዳይደገም በሕይወታቸው አብነት ሆነዋል። ❤ በቤተ መንግሥት መዋጥን ብቻ ሳይሆን በዓለማቀፋዊነት (ሉላዊነት) መዋጥ እንዳይመጣ ማንነትን ጠብቆ በዓለም መድረክ መገኘትንም አበክረው ያሳስቡ ነበር። ቤተ ክርስቲያን በምትካፈልባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች በውክልና ከመገኘታቸውም በላይ የዓለም አቃዊነት መርሖ ማንነትን ካለማጣት ጋር እያነጻጸሩ አቅርበዋል። ጠንካራ ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊነትንም ከታሪክ አንጻር የሚያብራሩት እነዚህ አባት የዕውቀት ብርሃን ቀድሞ የተለኮሰባት አፍሪካ እንዴት ባለ መንገድ ወደ ጨለማው እንደገባችና የቅኝ ግዛት ቀንበር እንደተሸከመች ያትታሉ። ከ1983ቱ የመንግሥት ለውጥ አንድ ዓመት ቀድሞ “ምንም ብትሉ ምንም ብትሉ ይህ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው” በሚለው ንግግራቸው አንድነት እና ኢትዮጵያዊነት የገጠመውንና የሚገጥመውን ፈተና በትንቢታዊነት አስረድተዋል። በአንድነት ውስጥ ብዝሕነት በጸጋነት መኖሩን የሚያስተምሩ አባት ነበሩ። ከምንም በላይ ለተተኪው ትውልድ ትልቅ አክብሮት እና ጥንቃቄ በማሳየታቸው ይታወቃሉ። ወጣቶች “የቤተ ክርስቲያን የስስት ልጆች” ከማለታቸውም በላይ በዕውቀት እንዲበለጽጉ በብዙ ደክመዋል። ገና በ50 ዓመታቸው በመኪና አደጋ ከዚህ ዓለም ቢለዩም ትምህርታቸው፣ ዓላማቸው፣ ጽናታቸው፣ ኢትዮጵያዊ አርበኝነታቸው፣ ለአፍሪካዊነት ያላቸው ከበሬታ፣ ለወላጅ አልባ ሕጻናት ያላቸው ደራሽነት እና ለወጣቶች ያላቸው አክብሮት ሁሌም የማይረሱ ያደርጋቸዋል። ከአባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከታቸው ይደርብን። ጸሎታቸውም የአገራችን ኢትዮጵያ ትንሣኤል ያቅርብልን። ምንጭ፦ (ኤፍሬም እሸቴ)፡- እንደጻፈው ከአዲስ ጉዳይ መጽሔት ሐምሌ 2ዐዐ6 ዓ.ም።

❤ እንዲሁም የአቡነ ጴጥሮስን ሥጋ በተመለከተ ማንም እንዳይወስደው በአስቸኳይ ከአ.አ ውጭ ማንም በማያውቀው ቦታ በምሥጢር እንዲቀበር መደረጉ በትንሣኤ መጽሔት ቁ.58 1978 ዓ.ም ላይ የተገለጠ ቢሆንም ነገር ግን አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ቅዱሳን መላእክት የጻድቃንን በድን እያመጡ ወደሚያስቀምጡበትና በውስጡ የሚቀመጥ አስክሬን ወደማይፈርስበት አቡነ መልከ ጼዴቅ ዋሻ ገዳም መላእክት ወስደው እንዳስቀመጡትና በዚያም እንደታየ ይናገራሉ፡፡ ሰሜን ሸዋ ሚዳ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው በአቡነ መልከ ጼዴቅ ዋሻ ውስጥ የቅዳሱኑ አጽም ሳይፈርስና ሳይበሰብስ የአንገት ክራቸው ራሱ ሳይበጠስ እንደዛው እንደነበሩ ስለሚገኝ ቦታውም እጅግ ትልቅ የቃልኪዳን ቦታ ስለሆነ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅም በዚህ በጨረሻው ሀሳብ ይስማማል፡፡ ❤ ሰማያዊ ክብርን የሚያስገኝ አኩሪ ገድል በመፈጸም የቤተክርስቲያን ታላቅ አለኝታ አባትና መሪ የሆኑት የዘመናችንን ታላቅ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስን ትውልዱ የግድ ሊያስባቸውና ሊዘክራቸው ይገባል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (united nations) አቡነ ዼጥሮስን "የሺህ ዓመቱ ምርጥ ሰማዕት" ወይም በፈረንጅኛው አፍ (MARTYR OF THE MILLENIUM) በሚል መጠሪያ ሰይሟቸዋል። ❤ ላልተነገረላቸውና ላልተዘመረላቸው ለእኚህ ብርቅዬ የቤተ ክርስቲያናችን ድንቅ አባት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 12 ቀን 1998 ዓ.ም እኚህን ሰማዕት "አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕተ ጽድቅ ዘኢትዮጵያ" ተብለው እንዲጠሩ ወስኗል፡፡ በስማቸውም መቅደስ እንዲታነጽ ፈቅዶ በመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ መሠረት (ኢሳ 56፡4) ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቁ በተወለዱበት ሥፍራ መታሰቢያ አቁማላቸዋለች፡፡ ግንቦት 1 ቀን 2001 ዓ.ም በስማቸው የተሰየመው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንና መታሰቢያ ሐውልታቸው ሲሠራ የፍቼ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ የእስልምና እምነት ተከታዮችም ጭምር ለግንባታ የሚሆን አሸዋ ከመርዳት አንስቶ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ድንኳን እስከመትከል ተሳትፈዋል፡፡ በገንዘብም በጉልበትም ተባብረዋል፡፡ ጠላት ድል ተደርጎ ሀገራችን ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የአባታችንን እጅግ አኩሪ ታሪክ ሲያዘክራቸው እንዲኖር መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት አሳሳቢነት ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓ.ም በአ.አ መሐል ከተማ ላይ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ ከብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ ምዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ። ❤ #ታላቁ_ብፁዕ_አቡነ_ጎርጎርዮስ_ካልዕ (1933 ዓ.ም_ሐምሌ 22 ቀን1982 ዓ.ም። ❤ “ምንም ብትሉ፣ ምንም ብትሉ፤ ይህ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው!!!!” ❤ ሐምሌ 22 ቀን 1982 ዓ.ም በመኪና አደጋ ሕይወታቸውን ያጡት በ20ኛው መቶ ክ/ዘመን የወንጌልና የታሪክ ብርሃንን በተለይ በወጣቱ ሕይወት ላይ የፈነጠቁት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ (በድሮው የክፍላተ ሀገር አከፋፈል) የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ነበሩ። ከዚህ ዓለም ከተለዩ እነሆ 34 ዓመት ሞላቸው። መታወቂያቸው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስነታቸው እና አባትነታቸው ቢሆንም በጽሑፋቸው፣ በትምህርታቸው እና ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ባላቸው ጽኑዕ ፍቅር ከእምነት ድንበር ባሻገር የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ልቡና ሊገዛ የሚችል ስብዕና የነበራቸው አባት ነበሩ። ❤ ብፁዕነታቸው ሚያዚያ 23 ቀን1982 ዓ.ም፣ ሻሸመኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ያስተማሩት ትምህርት ኢትዮጵያ አገራችን በዚያን ወቅት የነበረችበትን የጦርነት እሳት እና መጻዒውን የሕዝቧን ሁናቴ በቅጡ የሚያመለክት ነበር። ከተናገሯቸው ዐበይት ቃላት መካከል “ምንም ብትሉ ምንም ብትሉ፣ ይህ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው። ቤተ ክርስቲያኒቱ ደህና አድርጋ መሥራታዋለችና” የሚለውን አባባላቸውን ዛሬም ድረስ በቃሌ አስታውሰዋለሁ። “ምንም ብትሉ ምንም ብትሉ” ያሉት በዓይነ ልቡናቸው ማን ምን እያለ ታይቷቸው ይሆን? እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። በተለይም የሃይማኖት አባቶች መንፈሳዊ እና አገራዊ አቋማቸው በሚዋዥቅበት በዚህ ዘመን እጅግ በጣም ባልራቀው ዘመን የነበሩትን የነአቡነ ጎርጎርዮስን ሕይወት መጥቀስ ዙሪያ ገባው ጨለማ እንዳልሆነ ለማሳየት አንድም በእውነት እና በዕውቀት ብርሃን ለመመላስ አንገቱን ቀና ለማድረግ ለሚታትር ማንም ሰውም ጥብዓት ለመስጠት ይጠቅማል። ❤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በጵጵስና ያገለገሉባቸው ዓመታት 10 ዓመታት ብቻ ናቸው። በነዚህ ጥቂት ዓመታት ያበረከቷቸው ተግባራት ግን ዛሬም ሕያው ሆነው ይታያሉ። ከአገር ቤት አገራዊውን ዕውቀት በቅጡ በማደላደል፣ ወደ ውጪውም ዓለም በመሔድም ከዘመናዊው ዓለም የዕውቀት ገበያ በመገብየት ሚዛናዊነቱን የጠበቀ ኅሊና ባለቤት የሆኑት ገና ከማለዳው ነው። የአገሩን ዕውቀት ሲጨብጥ የውጪው፣ የውጪውን ሲይዝ የአገሩ ለሚጎድልበት አገርና ምሁር ጥሩ ማሳያ ናቸው። የአገራቸውን ሳያውቁ የውጪውን ብቻ በማነብነብ ያልተፈተነ መፍትሔ ለአገራቸው ችግር ለመስጠት በመሞከር መክነው የቀሩ ብዙ ትውልዶቻችንን ያጣነው በዚህ ምክንያት ነው። ❤ አገራችን ከአፍሪካዊ ማንነት በአንድ ጊዜ ተነቅላ ፈረንጃዊ ለመሆን ሞክራ በመካከል ደክማ የቀረችው መሠረቷን ሳታጠብቅ በውጪው ላይ ለመንጠላጠል ባደረገችው ሙከራ ነው። ዕብራይስጥ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እና አረብኛ ቋንቋዎችን በቅጡ የሚያውቁት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በዝዋይ ሐመረ ብርሃን በመሠረቱት የቅዱስ ገብርኤል ገዳም የዕውቀት ዓምባ አቋቁመው ኢትዮጵያዊውን ታሪክ ከዓለሙ ጋር እያነጻጸሩ ለደቀመዛሙርቶቻቸው ሲያሰተምሩ ቆይተዋል። ጭው ጭው የሚል የሩቅ አገር ሬዲዮ ድምጽ ከደጃፋቸው የሚሰማው እኒህ አባት ለገዳማውያኑና ለትምህርት ከየከተማው ለሚሰባሰቡት ተማሪዎቻቸው ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን ለተማሪዎቹ ዕውቀትና ሥነ ልቡና በሚመጥን መልኩ ሲያቀርቡ መስማት ያስደንቃል።  ❤ የሃይማኖትና የታሪክ ጥናትና ምርምራቸውን “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” እና “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዓለም መድረክ” በሚሰኙ መጻሕፍቶቻቸው ቅልብጭ አድርገው አቅርበዋል። ለ፤መጻሕፍቱ መርጃነት የተጠቀሙባቸው ዋቤ መጻሕፍት ዝርዝር በሕዳግ በገጽ በገጹ ተጠቅሶ ይታያል። በአዋቂነት ድፍረት ሳይሆን በማስረጃ ጥንቁቅነት የቀረቡ፣ ከወጣት የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች እስከ ካህናት ብሎም ከየዩኒቨርሲቲው ትምህርት የዕረፍት ጊዜውን ወስዶ ከርሳቸው ሊማር ለሚመጣው ዘመናዊ ትውልድ በሚሆን መልኩ የተዘጋጁ የጥናት ሥራዎች ናቸው። ❤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የሃይማኖት አባቶች የሚያሳዩትን የቅምጥል ኑሮ እንደሚቃወሙ በአንድም በሌላም ቢገልጹም "እኛ የመነኰስነው ለፍትፍት አይደለም" የምትለው አባባላቸውን ብዙዎች ያስታውሱታል። መነኮሳት ይህንን መስመር የሚመርጡት እንደማንኛውም ተርታ አማኝ በተቀማጠለ ኑሮ ለመመላለስ ሳይሆን ራስን በሚጎስም መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎት ለመጠመድ መሆኑን አበክረው ይናገራሉ። ለኑሮ የማይመቸውንና ከዝዋይ ሐይቅ በተጎራበተው የቅዱስ ገብርኤል ገዳማቸው ጠንካራ ኑሮን በመቋቋም ገዳሙን ለወላጅ አልባ ሕጻናት ማሳደጊያነት እና ለትምህርት ማዕከልነት የሚመች ሥፍራ ያደረጉት በዚሁ መርሐቸው ነበር። በተለይም በዚህ ዘመን፣ በሃይማኖት አባቶች ላይ የሚታየው የቅምጥል ኑሮ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሕይወት ሲመዘን እጅጉን ጎዶሎ ይሆናል።

❤ ወደ ምሥራቅ አፍሪካው ዜና መዋዕል አዘጋጁ ወደ ፖጃሌ ዘገባ እንመለስና የአቡነ ጴጥሮስን መልካቸውንና ተክለ ቁመናቸውን እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡- "ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም፣ ፊታቸው ዘለግ ያለ፣ መልካቸው ጠየም ያለ፣ ዐዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብሰ ጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡ ለፍርድ የተሰየሙት ዳኞቸ ሦሰት ሲሆኑ እነዚህም ጣሊያኖችና የጦር ሹማምንቶች ናቸው፤ መካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር፡፡ ❤ የቀረበባቸውም ወንጀል "ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራስዎም አምፀዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምፁ አድርገዋል" የሚል ነበር፡፡ ዳኛውም "ካህናቱም ሆኑ የቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የጣሊያንን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?" ሲል ጠየቃቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስም በቆራጥነት የሚከተለውን መለሱ፡- "አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵየዊ ነኝ፡፡ ሓላፊነትም ያለብኝ የቤተ ክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ" አሉ፡፡ "ይህንንም ብለው በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲመለከት ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ የሚከተለውን ሕያው መልእክት አስተላለፉ፡- "አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው፤ እንጂ በጎ ለመሥራት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፡፡ ስለ ውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ፡፡ ነጻነታችሁ ከሚረክስ ሙታችሁ ስማችሁ ቢቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን" ብለው አወገዙ፡፡ ❤ ቀጥሎም ብፁዕነታቸው በፍጥነት ችሎት ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለ እርሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየጸለዩ ሕዝቡን ባረኩ፡፡ ወዲያው የሞታቸው ፍርድ ሲሰማ ሕዝቡ በኢጣሊያ የእጅ ሰላምታ ዓይነት እጁን እንዲያነሳ ታዘዘ፡፡ በዚያን ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ የሞታቸው ሰዓት መድረሱን ዐውቀው ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ፡፡ በዚህን ጊዜ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር፡፡ የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣሊያዊው ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡ ታላቅ ፍርሃም በፊቱ ላይ ይታይ ነበር፡፡ የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ጸልየው በመስቀላቸው ባረኳቸው፡፡ የሀገራቸው በጠላት መወረር፣ የሕዝባቸው መገደልና መታሰር፣ የቤተክርስቲያናቸው መደፈር እስከ ሞት ያደረሳቸው እኒያ እውነተኛ ጳጳስ እንዲገደሉ ሲወሰዱ ጥይት አልፎ ሌላ ሰው እንዳይመታ ግንብ ይፈለግ ጀመር፡፡ ሩቅ ባለመሄድ ከመካነ ፍትሑ ዐሥር ሜትር ርቆ ግንብ ያለው መግደያ ቦታ ተገኘና ወደዚያ ተወሰዱ፡፡ ከገዳዮቹም አንዱ "ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉን?" ሲል ጠየቃቸው፡፡ "ይህ ያንተ ሥራ ነው" ሲሉ ብፁዕነታቸው መለሱ፡፡ ❤ ከመግደያውም ቦታ እንደደረሱ ወንበር ቀረበላቸውና ፊታቸውን ወደ ግንቡ ጀርባቸውን ወደ ሕዝቡ አድርገው እንዲቀመጡ ሆኑ፡፡ ከዚያም በኋላ ስምንት ወታደሮች በስተ ጀመርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተጠንቀቅ ቆሙ፣ ወዲያው አዛዡ "ተኩስ!" በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቱዋቸው፡፡ ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ፡፡ መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ፡፡ ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ፡፡ ከዚያም በኋላ አንድ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው፡፡ ❤ ብፁዕነታቸው የተገደሉበት ቦታ መሐል አዲስ አበባ ላይ ዛሬ መታሰቢያ ሐውልታቸው ቆሞ በሚገኝበት ቦታ ላይ ነው" በማለት የጋዜጣ ወኪልና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛው ፖጃሌ ስለ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ "አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ?" ሲል በወቅቱ አባታችን ሰማዕትነትን ሲቀበሉ በቦታው ላይ በአካል በመገኘት ሁኔታውን ይከታተሉ የነበሩትን ሙሴ ፓይላክን ጠይቋቸው እርሳቸውውም የሚከተለውን ተናረዋል፡- "አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ፡፡ መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት፡፡ ቀጥለውም በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ፡፡ የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ከተቱት፡፡ ወዲያው ወታደሮቸ በሩምታ ተኩሰው ገደሏቸው፡፡ ❤ ይህ እንደሆነ አስገዳዩ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ፡፡ ማታ ከአስገዳዩ ኮሎኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት "በዚህ ቄስ መገደልኮ ሕዝቡ ተደስቷል" አለኝ፡፡ "እንዴት?" ብለው "አላየህም ሲያጨበጭብ?" አለኝ፡፡ "ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጨበጭባል" አልኩት፡፡ "እንዴት?" ቢለኝ እጄን አጨብጭቤ አሳየሁት፡፡ "ከዚህ በኋላ የሆነው ቢሆን እኔ ትልቅ ማስታወሻ አግኝቻለሁ" ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀልና መጽሐፍ ቅዱስ የኪስ ሰዓታቸውንም ጭምር አሳየኝ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ መሐል ለመሐል በጥይት ተበስቷል፡፡ መስቀሉም ልክ በመሐሉ ላይ ጥይት በስቶት ወጥቷል፡፡ የኪስ ሰዓታቸውንም እንዳየሁት እንዲሁ ጥይት በስቶታል" ብለው በወቅቱ የተመለከቱትን መስክረዋል፡፡ ❤ ብፁዕ አባታችን በአደባባይ በሕዝብ ፊት የሰማዕትነት ጽዋቸውን ሲቀበሉ ከሕዝቡ ጋር ሆና ትመለከት የነበረች አንዲት ከድጃ የምትባል እስላም ሴት ማንም ሰው ያላየውን ታላቅ ነገር እርሷ ተመልክታለች፤ ይኸውም አባታችን ሰማዕትነትን ሲቀበሉ የብርሃን አክሊል በራሳቸው ላይ ሲቀዳጁ ተመልክታ በዚያው እርሷም "የእኚህን አባት ሃይማኖት እከተላለሁ" ብላ በመጠመቅ ክርስቲያን ሆናለች፡፡ ❤ የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል በሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ሰማዕቱን አቡነ ጴጥሮስን ገድሎ አስክሬናቸው አደባባይ ላይ ጥሎ ከዋለ በኋላ ቀብራቸው በምሥጢር መፈጸሙን አንዳንዶች ይናገራሉ፡፡ የእኚህን ታላቅ አባት ቀብር በምሥጢር የተፈጸመበት ቦታ ለማግኘት የተለያዩ ምሁራን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የታሪክ ሰነዶችን ሲመረምሩ ቢቆዩም "ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በምሥጢር ቀበሯቸው" ከሚል ከመላምት ያለፈ ነገር ምንም ዓይነት የተረጋገጠ ማስረጃ ሳይገኝ ቀርቷል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ "ፉሪ ለቡ" ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የሰፈሩ ምዕመናን በአካባቢው ተወልደው ካደጉ አረጋውያን ጋር ባደረጉት ማኅበራዊ ግንኙነት ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፋሽስቶች በመኖርያነትና በእስር ቤትነት ይጠቀሙበት በነበረው "ሙኒሳ ጉብታ" ላይ መቀበራቸውን ከወላጆቻቸው ሲሰሙ እንዳደጉ እየተነገረ ይገኛል፡፡

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ሐምሌ ፳፪ (22) ቀን። ❤ እንኳን #የ20ኛው_ክፍለ_ዘመን_ሰማዕት ለታላቁ ለሆኑት ለእውነተኛ ለኢትዮጲያዊው ጻድቅ #ለብፁዕ_አቡነ_ጴጥሮስ_ሰማዕትነት_ለተቀበሉበት ቀን መታሰቢያ በዓልና ዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል የካህናት ማሰልጠኛን ለመሰረቱት #ለብፁዕ_አቡነ_ጎርጎርዮስ ካልዕ ዕረፍት ቀን መታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                                                      ✝ ✝ ✝ ❤ #ኢትዮጵያዊው_ሰማዕት_ብፁዕ_አቡነ_ጴጥሮስ፦ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ሰማዕት የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ በ1875 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በሰማዕትነት እንደሚሞቱ አስቀድመው መምህራቸው በትንቢት ነግረዋቸው ነበር፡፡ "አለቃ ተጠምቀ" የተባሉ ቅድስናን ከሊቅነት ጋራ አስተባብረው የያዙ የቅኔ መምህራቸው አንድ ቀን አቡነ ጴጥሮስን ጠርተው "ኀይለ ማርያም አንተ ወደፊት ጳጳስ ትሆናለህ፤ በወቅቱም አረመኔ በዚህች ሀገር ይሠለጥናል፡፡ ታዲያ ያኔ አንተ ለነፍስህ ሳትሳቀቅ በሰማዕትነት እለፍ፤ ሰማዕትነት ክፍልህ ነው፣ አደራ" ብለዋቸው ነበር፡፡ ይኸውም ትንቢት ደርሶ አቡነ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ለማረፍ በቅተዋል፡፡ ❤ ብፁዕ አባታችን የጵጵስና ስማቸውን ከማግኘታቸው በፊት መመህር ኀይለ ማርያም ይባሉ ነበር፡፡ በልጅነታቸው ወላጆቻቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ በሃይማኖትና በምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ አድርገዋቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓተ ትምህርት ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ትምህርቶች በሚያስገርም ፍጥነት ከተማሩ በኋላ ወደ ቅኔው አውድማ ጎጃም በመሄድ በሸዋራ የቅኔ ትምህርታቸውን ፈጽመው መምህር ሆነዋል፡፡ የዜማውንም ትምህርት ወደ ጎንደር ሄደው ተምረዋል፡፡ በመቀጠልም ወሎ ቦሩ ሜዳ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጻሕፍትን ምሥጢር ይመግቡ ወደነበሩት ወደ ሊቁ አካለ ወልድ ዘንድ በመሄድ ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትንና ሊቃውንትን በሚገባ አሒዱ፡፡ ❤ ከዚህ በኋላ በ1900 ዓ.ም ወሎ አምሐራ ሳይንት ሄደው በምስካበ ቅዱሳን ገዳም ገብተው ወንበር ዘርግተው ለ9 ዓመታት ቅኔንና መጻሕፍትን አስተማሩ፡፡ በ1910 ዓ.ም ወደ ደብረ ሊባኖስ መጥተው ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸሙ፡፡ ከዚያም መምህርነት ተሹመው ደብረ መንክራት ምሁር ኢየሱስ ገዳም ሄደው ለ6 ዓመታት ካስተማሩ በኋላ በ1916 ዓ.ም እንደገና በዝዋይ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም በመምህርነት ተሹመው ለ3 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በ1919 ዓ.ም ወደ አ.አ በመምጣት የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ መምህርና በቤተ መንግሥት የግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ የንስሓ አባት ሆኑ፡፡ ❤ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በራሷ ተወላጅ ጳጳሳት ልጆቿ እንድትመራ ከ1600 ዓመታት በኋላ ስለተፈቀደላት ከዚህ በኋላ በሃይማኖታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው አምስት ደጋግ አባቶች ሲመረጡ አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የራሷን ጳጳስ ስትሾም አቡነ ጴጥሮስ ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም ጵጵስና ተሾሙ፡፡ ከዚህም በኋላ ብፁዕ አባታችን "አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዐ" ተብለው በያኔው መንዝና ወሎ ሀገረ ስብከት ተሾሙ፡፡ ❤ ብፁዕ አባታችንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንና ቅድስት ሀገራችን በጸሎታቸው፣ ሕዝቡን በትምህርታቸው እየጠበቁ በተጋድሎ እየኖሩ ሳለ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሺስት በ1928 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን አውጆ ሕዝቡን በግፍ ይገድል ቤተ ክርስቲያንን ያቃጥል ጀመር፡፡ በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ካህናትና መነኮሳት ተገደሉ፣ ብርቅዬ የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች ተዘረፉ፡፡ አቡነ ጴጥሮስም ይህንን ግፍ በማየታቸው ከሀገራችን አርበኞች ጋር በመሆን በጸሎታቸው ሊዋጉት ተነሡ፡፡ አባታችን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ማይጨው ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው በመርዝ የተደገፈ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ወደ አ.አ የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሠላሌ አርበኞች በሚገባ አስተምረዋል፡፡ ❤ በደብረ ሊባኖስ ጫካዎች ውስጥ መሽጎ የነበረው የእነ ደጃዝማች አበራ ካሣ አርበኛ ጦር እና በሸንኮራ በኩል መሽጎ የነበረው የእነ ፍቅረ ማርያም አርበኛ ጦር እንደሁም በምዕራብ ይመራ ከነበረው የእነ ደጃዝማች አባ ነፍሶ ጦር ሦስቱም በአንድ ጊዜ ወደ መሐል አ.አ በመግት አ.አ ላይ መሽጎ የነበረውን ፋሽስትን ለመውጋት ታቅዶ የነበረው ዕቅድ በመረጃ ክፍተት ምክንያት ውጤታማ ሳይሆን ቀረ፡፡ በተለያየ ጊዜ መሐል አ.አ እየደረሱ ማለትም በመጀመሪያ የእነ ፍቅረ ማርያም አርበኛ ጦር ለብቻው በኮተቤ አድጎ የካ ሚካኤል ላይ ሲድርስ ተመቶ ተመለሰ፤ ይሄኛው እንዳለቀ ቀጥሎ የእነ አባ ነፍሶ ጦር በባቡር ጣቢያ መጣሁ ቢልም በጠላት ጦር ድካሚ ተመቶ ተመለሰ፤ መጨረሻ ላይ የእነ ደጃዝማች አበራ ካሣ አርበኛ ጦር በእንጦጦ በኩል ቢመጣም እርሱም በጠላት ጦር ተመቶ ተመለሰ፡፡ ❤ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሦስቱም የአርበኞች ጦር በመረጃ ክፍተት ምክንያት እየተመታ ወደመጣበት ሲመለስ አቡነ ጴጥሮስ አብረው ከአርበኛው ጦር ጋር መመለሱን አልፈለጉትም ይልቁንም "ብችል ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በቅርብ ርቀት ሆኖ የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሣ አደርገዋለሁ ካልሆነም ደግሞ እዚሁ እሞታለሁ" በማለት አባታችን ከአርበኞቹ ተነጥለው አ.አ ቀሩ፡፡ ይሁን እንጂ ጠላት በመላዋ ከተማ ያሰማራቸው ባንዳዎች አባታችንን እንዳሰቡት ሊያነቀሳቅሷቸው አልቻሉም ነበር፡፡ በመሆኑም አባታችን "የሀገሬን ሕዝብ ለጠላት እንዳይገዛ በአደባባይ አውግዤ ጠላትን ረግሜ በሰማዕትነት ባልፍ ይሻለኛል" ብለው ራሳቸውን ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት ወሰኑና የፋሺስት ኢጣሊያ እንደራሴ ለሆነው ለራስ ኀይሉ ሄደው እጃቸውን ሰጡት፡፡ እርሱም ብፁዕ አባታችንን ወስዶ ለግራዚያኒ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አሳልፎ ሰጧቸው፡፡ ግራዚያኒም ግማሽ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲገደሉ ወሰነባቸው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በፈቃዳቸው እጃቸውን አሳልፈው ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ በሰማዕትነት እስካለፉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሒደት ኮርየሬ ዴላሴራ የተባለው ጋዜጣ ወኪልና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ፖጃሌ የተባለው ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ ሰኔ 15 ቀን 1936 ዓ.ም በአዲስ አበባ በነበረ ጊዜ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የተሰጠውን ፍርድና የተፈጸመውን የግፍ ግድያ ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ጽፎ ነበር። ❤ "ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ወደ ግራዚያኒ ቀረቡ፡፡ በዚህ ጊዜ አቡነ ቄርሎስ የተባሉት ግብፃዊ ጳጳስ ቀርበው "ለእስክንድርያው መንበረ ፓትርያርክ ምክር ቤት ሳታሰማ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ እንዳች ነገር ማድረግ አይገባህም" ሲሉ ለግራዚያኒ ነገሩት፡፡ አቡነ ቄርሎስ ይህን ማለታቸው በዲፕሎማቲክ ደረጃ ለዓለም ለማሰማትና የአቡነ ጴጥሮስን ሕይወት ለማትረፍ አስበው ነበር፡፡ ነገር ግን ግራዚያኒ የአቡነ ጴጥሮስ የሞት ፍርድ እንኳንስ እስከ ግብጽ ከአ.አ ውጭ እንኳ ከመሰማቱ በፊት በግማሽ ቀን እንዲፈጸም መመሪያ አስተላላፈ፡፡