fa
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

رفتن به کانال در Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

نمایش بیشتر
608
مشترکین
-124 ساعت
-47 روز
-1230 روز
آرشیو پست ها
የሊቀ መልዓኩ የቅዱስ ሚካኤልን አመታዊ ክብረ በዓል እንዲህ ባለሁኔታ ተከብሮ አልፏል ለአመቱ በሰላም ያድርሰን እያልን ከሚዲያና ዕቅበተ ዕምነት ክፍል የምስል ማህደር በጥቂቱ ይህን ይመስላል።

በዚያንም ጊዜ የኖባ ንጉሥ ጊዮርጊስ ለኢትዮጵያ አገር ጳጳስን ይሾምላቸው ዘንድ የልመና ደብዳቤ ወደ አባ ፊላታዎስ ጻፈ ይህ ቅዱስ ፊላታዎስም ልመናውን ተቀብሎ ከአስቄጥስ ገዳም ስሙ ዳንኤል የሚባል አንድ ጻድቅ መነኰስ አስመጣ እርሱን ጵጵስና ሹሞ ወደ ኢትዮጵያ አገር ላከው ወደ እነሱም በደረሰ ጊዜ የኢትዮጵያ ሰዎች በታላቅ ደስታ ተቀበሉት ። በዚህም አባት ፊላታዎስ ዘመን ብዙ ተአምራት ተገልጠዋል በሰላምም አረፈ። #ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሊቀ መላእክት #ቅዱስ_ሚካኤል እና በቅዱሳን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። (#ስንክሳር_ዘወርኀ_ኅዳር_12 እና #ዲያቆን_ዮርዳኖስ_አበበ)

በባሕሩም አካባቢ በጎቹን አሰማርቶ የሚጠብቅ አንድ ሰው ነበረና ሣጥኑን በውኃ ላይ ተንሳፎ አየው እርሱም ከባሕሩ አውጥቶ ወደ ቤቱ ወሰደው ይህንም ሣጥን እንዴት እንደሚከፍተው ያስብ ጀመረ ይህንም ሲያስብ ወደ ባሕሩ ይሔድ ዘንድ #ጌታችን በልቡናው ኃሳብ አሳደረበት ወዲያውኑም ተነሥቶ ወደ ባሕሩ ሔደና አንድ ዓሣ የሚያጠምድ ሰው አገኘ ። ዓሣ አጥማጁንም መረብህን በኔ ስም ጣል ለሚያዘውም ዓሣ ዋጋውን እሰጥሃለሁ አለው አጥማጁም እንዳለው አደረገ ያን ጊዜም ታላቅ ዓሣ ተያዘ ዋጋውንም ሰጥቶ ዓሣውን ተቀበለ ዓሣውንም ይዞ ወደቤቱ ሔደ ለራትም ይጠብሰው ዘንድ አረደው በሆዱም ውስጥ መክፈቻ አገኘ ። በልቡም ይህ መክፈቻ ይህን ሣጥን ይከፍተው ይሆን አለ በሣጥኑ ቀዳዳም በአስገባው ጊዜ ፈጥኖ ተከፈተ በውስጡም ይህን ታናሽ ብላቴና አገኘ ። ልጅ የለውም ነበርና ታላቅ ደስታ ደስ አለው #ጌታችንንም አመሰገነው። ሕፃኑንም በመልካም አስተዳደግ አሳደገው ሕፃኑም አድጎ ጐልማሳ ሆነ ። ከብዙ ዘመናትም በኋላ ያ ባለ ጸጋ ተነሥቶ ወደዚያ አገር ሔደ በመሸም ጊዜ ወደ በግ ጠባቂው ደጅ ደረሰ በግ ጠባቂውን እስከ ነገ የምናድርበት ማደሪያ በአንተ ዘንድ እናገኛለን ኪራዩንም እሰጥሃለሁ አለው በግ አርቢውም እንዳልክ ይሁንና እደር አለው ባለጸጋውም በዚያ አደረ ። ራት በሚቀርብም ጊዜ ሕፃኑን ባሕራን ብሎ ጠራው ባለጸጋውም ሰምቶ ልጅህ ነውን ብሎ ጠየቀው በግ ጠባቂውም አዎን ታናሽ ሕፃን ሆኖ ሳለ ከባሕር አግኝቼዋለሁና #እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጄ ነው አለው ባለጸጋውም በምን ዘመን አገኘኸው አለው እርሱም ከሃያ ዓመት በፊት ብሎ መለሰለት ። ያን ጊዜም እርሱ ወደ ባሕር የጣለው መሆኑን አውቆ እጅግ አዘነ ። በማግሥቱም ጎዳናውን ሊጓዝ በተነሣ ጊዜ ሰይጣናዊ ምክንያት አመካኝቶ በግ ጠባቂውን እንዲህ አለው ዕገሊት ወደምትባል አገር በቤቴ የረሳሁት ጉዳይ ስለ አለ እንድልከው ልጅህን ትሰጠኝ ዘንድ እሻለሁ እኔም የድካም ዋጋውን ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሃለሁ አለው ። የብላቴናውም አባት ስለ ገንዘቡ ደስ ብሎት ልጁ ባሕራንን ሰጠው እንዲህም ብሎ አዘዘው ልጄ ባሕራን ይህ የከበረ ሰው ስለ ጉዳዩ ወደ ቤቱ ይልክህ ዘንድ ና ወደ ቤትህም በሰላም ትመለሳለህ ። ባሕራንም አባቴ ሆይ እሽ በጎ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ ። ያን ጊዜም ባለጸጋው ወደ መጋቢው እንዲህ ብሎ ደብዳቤ ጻፈ ይችን ደብዳቤ በምታነባት ጊዜ ደብዳቤዋን ይዞ የመጣውን ገድለህ በጉድጓድ ውስጥ ጣለው ማንም አይወቅ በመካከላቸውም የሚተዋወቁበትን ምልክት ጽፎ አሸጋት ። ለባሕራንም ሰጠው ለመንገዱም የሚሆነውን ስንቅ ሰጠው ባሕራንም ተነሥቶ ጉዞውን ጀመረ ሲጓዝም ሰንብቶ የአንዲት ቀን ጐዞ ሲቀረው እነሆ የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ አንተ ጐልማሳ የያዝኸው ምንድነው አለው ወደ ዕገሌ አገር ወደ ቤቱ ለማድረስ ከአንድ ባለጸጋ የተጻፈች መልእክት ናት አለው ያቺን ደብዳቤ አሳየኝ አለው እርሱም ስለ ፈራ ሠጠው ። በዚያን ጊዜም የከበረው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ያቺን የሞት መልእክት ደመሰሳት በእርሷ ፈንታም በንፍሐት ለውጦ እንዲህ ብሎ ጻፈ ይቺን ደብዳቤ ይዞ ለመጣ ባሕራን ለሚባል ሰው ይቺ ደብዳቤ ደርሳ በምትነበብበት ጊዜ ልጄ እገሊትን አጋቡት በውስጥና በውጭ ያለ ንብረቴንና ጥሪቴን ወንዶችና ሴቶች ባሮቼን ጠቅላላ ንብረቴንም አውርሼዋለሁና የፈለገውንም ሊያደርግ ሥልጣን ሰጥቼዋለሁና እኔን አትጠብቁኝ ። እኔ ብዙ እዘገያለሁ የኔ ሹም ዕገሌ ሆይ በእኔና በአንተ መካከል ይቺ ምልክት እነኋት ከዚህ በኋላ አሽጐ ለባሕራን ሰጠውና ወደ ባለጸጋው ቤት ሒደህ ይቺን ደብዳቤ ለሹሙ ሰጠው በጎዳናም እኔ እንደ ተገናኘሁህ አትንገረው እንዳይገድልህም ይህን የሞት ደብዳቤ ለውጬልሃለሁ አለው ። ባሕራንም እሺ ጌታዬ ያዘዝኽኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ ። ባሕራንም ወደ ባለጸጋው ቤት በደረሰ ጊዜ ያቺን ደብዳቤ ለሹሙ ሰጠው በአነበባትም ጊዜ በመካከላቸው ያለውን ምልክት አገኘ አስተውሎም አርግጠኛ እንደሆነ አወቀ ። ከዚህም በኋላ ለባሕራን ሠርግ አዘጋጅቶ እንደሚገባ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በተክሊል የባለጸጋውን ልጅ አጋቡት ። አርባ ቀን ያህልም ደስታና ሐሴት እያደረጉ ኖሩ ። ከዚህ በኋላ ባለጸጋው ከሔደበት መመለሻው ጊዜ ሁኖ በደስታ የሆነውን የመሰንቆና የእንዚራ ድምፅ ሰምቶ ይህ የምሰማው ምንድነው ብሎ ጠየቀ እነርሱም ስሙ ባሕራን ለተባለ የአንተን ደብዳቤ ላመጣ ጐልማሳ ሰው ልጅህ ዕገሊትን አጋቡት እነሆ ለአርባ ቀናት በሠርግ ላይ ነው ። ገንዘብህንና ጥሪትህን ሁሉ ወንዶችና ሴቶች ባሮችህን አንተ እንዳዘዝክ ሰጥተውታል አሉት ። ይህንንም በሰማ ጊዜ ደንግጦ ከፈረሱ ላይ ወደቀ በድንገትም ሞተ ። ባሕራንም በጎ ሥራዎችን የሚሠራ ሆነ የተገለጸለትና ከመገደል ያዳነው የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ሊገድለው የሚሻውን የባለጸጋውን ጥሪቱን ሁሉ ያወረሰውም እርሱ እንደ ሆነ ተረዳ የዚህንም የከበረ መልአክ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን መታሰቢያ በየወሩ ያደርግ ጀመረ ቤተ ክርስቲያንም ሠራለት የቅዱስ ሚካኤልንም ሥዕሉን አሥሎ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ አደረገው ከእርሱም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ ባሕራንም ቅስና ተሹሞ እስከ ዕለተ ሞቱ በዚያች ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግል ሁኖ ኖረ በዚህ በከበረ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ከእናቱና ከአባቱ ከልጆቹም ጋራ የዘላለም ሕይወትን ወረሰ ። ✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞ #ጻድቁ_በእደ_ማርያም በዚችም ቀን የኢትዮጵያ ንጉሥ የጻድቁ በእደ ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው ። በዕደ ማርያም" ማለት "በማርያም እጅ" እንደ ማለት ነው:: እኒህ ሰው የኢትዮዽያ ንጉሥ ሲሆኑ የነገሡትም በ1460 ዓ/ም ነው:: ደጉ አባታቸው አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ሲያርፉ በመንግስቱ ተተክተው ሃገራችንን አስተዳድረዋል:: ድርሰት ደርሰዋል:: አብያተ መቅደስ አንጸዋል:: በተለይ ለቅኔ ትምሕርት ማበብ ልዩ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ይነገራል:: ልክ በነገሡ በ10 ዓመታቸው ግን መንግስተ ምድር በቃኝ ብለው በምናኔ በርሃ ገብተዋል:: በዙፋናቸውም አፄ እስክንድር ተተክተዋል:: ጻድቁ ንጉሥ ግን ቅዱስ ሚካኤልን ይወዱት ነበርና በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: ✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞ #ቅዱስ_አባት_ፊላታዎስ በዚችም ቀን ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስልሳ ሦስተኛ የሆነ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ፊላታዎስ አረፈ። በሹመቱ ወራትም የኢትዮጵያ ንጉሥ ወደ ኖባ ንጉሥ ወደ ጊዮርጊስ እንዲህ ብሎ የመልእክት ደብዳቤ ጻፈ ወንድሜ ሆይ ከሊቀ ጳጳሳት ቆዝሞስ ጊዜ ጀምሮ ለረጅም ጊዜ ጳጳስ ስለ ሌለን እኛ በታላቅ ችግር ውስጥ እንዳለን ዕወቅ ። ይህም የሆነው ተንኰለኛው ሚናስ በተንኰልና በሐሰት ነገር የከበረ ጳጳሳችንን ጴጥሮስን ከሹመቱ ወንበር እንዲሰደድ ስለ አደረገው ነው። ስለዚህ አምስት ሊቃነ ጳጳሳት እስቲአልፉ ለሀገራችን ጳጳስ አልተላከልንም ። አሁንም ስለ #እግዚአብሔር ብለህ ስለ ቀናች ሃይማኖትም በድካም ከእኛ ጋር አንድ በመሆን ስለእኛ ወደ ግብጽ ሊቀ ጳጰሳት ወደ ቅዱስ ፊላታዎስ ጳጳስ ይልክልን ዘንድ ከራስህ ደብዳቤ እንድትጽፍለት እለምንሃለሁ የሚል ነበር ።

ቅዱሳን ክቡራን: #ኅዳር_12 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ኅዳር ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ #ቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው፣ #ቅዱስ_ሚካኤል_ኢያሱን እንደ የተረዳበት ቀን ነው፣ #ለቅዱሳኑ_ዱራታኦስ_እና_ቴዎብስታ #ቅዱስ_ሚካኤል ተዓምር ያደረገበት ነው፣ #የባህራን_ቀሲስ መታሰቢያ ነው፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ #የጻድቁ_በእደ_ማርያም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ የሊቀ ጳጳሳት #ቅዱስ_አባት_ፊላታዎስ እረፍቱ ነው። ✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞ #ቅዱስ_ሚካኤል_ሊቀ_መላዕክት ኅዳር ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን ለሰው ወገን የሚያዝንና የሚራራ በ #እግዚአብሔር ጌትነት ዙፋን ፊት ሁልጊዜ በመቆም ለፍጥረቱ ሁሉ የሚማልድ የመላእክት አለቃ በሰማያትም ለሚኖሩ ኃይሎች ሁሉ አለቃቸው ለሆነ ለ #ቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። ✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞ #ኢያሱ_ወልደ_ነዌ ዳግመኛ በዚህች ዕለት #ቅዱስ_ሚካኤል ኢያሱን የተረዳበት ቀን ነው። ይህም በንጉሥ ጭፍራ አምሳል በታላቅ ክብር ሁኖ የነዌ ልጅ ኢያሱ ያየው ነው ከእኛ ሰዎች ወገን ነህን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ አለው። እኔስ የ #እግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ አሁንም ወዳንተ መጥቻለሁ አለው ። ኢያሱም ወደ ምድር በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደለትና በእኔ በባሪያህ ዘንድ ምን አቁሞሃል አለው ። የ #እግዚአብሔር የሠራዊቱም አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ኢያሱን የቆምክባት ምድር የከበረች ቦታ ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው ቅዱስ ኢያሱም እንዳለው አደረገ ። #እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ አለው በውስጧ ያለውን ንጉሧን ከኃያላኑና ከአርበኞቹ ጋር በእጃችሁ ኢያሪኮን እነሆ አስገባታለሁ ። ይህም የከበረ መልአክ ከቅዱሳን ሰማዕታት ጋር በመሆን ገድላቸውን እስከ ሚፈጽሙ የሚያጸናቸውና የሚያስታግሣቸው ነው ። ስለዚህም ስለ ልዕልናውና ስለ አማላጅነቱ በየወሩ በዐሥራ ሁለት ቀን ለመታሰቢያው በዓል ተሠራለት እርሱ ስለ እኛ የምድሩን ፍሬ ይባርክልን ዘንድ ዝናሙንም በጊዜው እንዲአወርድልን የወንዙንም ውኃ እንዲመላልን ነፋሱንም የምሕረት ነፋስ እንዲአደርግልን ሁሉንም የተስተካከለ እንዲአደርግልን ወደ #እግዚአብሔር በጸሎት ይማልድልናልና። ✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞ #ቅዱሳን_ዱራታኦስና_ቴዎብስታ ቅዱሳኑ ዱራታኦስ እና ቴዎብስታ የቅዱስ ሚካኤል ወዳጆች ናቸውና በዚህች ዕለት ይታሰባሉ። እንዲህም ሆነ የ #እግዚአብሔር ወዳጅ የሆነ ስሙ ዱራታዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ የሚስቱም ስም ቴዎብስታ ነው እነርሱም ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የ ቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ነበር ከዚህም በኋላ በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ ለዚህም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉት አጡ ዱራታዎስም ሽጦ ለበዓሉ መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ የእርሱን ልብስና የሚስቱን ልብስ ይዞ ወጥቶ ሔደ ። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በታላቅ መኰንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገለጠለት ወደ ባለ በጎች ሒዶ በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ እንዲወስድ ሁለተኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ሒዶ አንድ ዓሣ እንዲወስድ ግን መልአኩ ወደ ቤቱ ሳይደርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ ወደ ባለ ሥንዴም እንዲሔድና የሚሻውን እንዲሁ በርሱ ዋስትና እንዲወስድ አዘዘው ዱራታዎስም ቅዱስ ሚካኤል እንዳዘዘው አደረገ ። ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ በረከትን ሁሉ ቤቱ ተመልቶ አገኘው ። እጅግም አደነቀ የዚህንም የከበረ መልአክ የበዓሉን መታሰቢያ እንዳስለመደ አደረገ ። የተራቡ ድኆችን ሁሉንም ጠርቶ መገባቸውና ወደየቤታቸው አሰናበታቸው። ከዚህም በኃላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቅዱስ ሚካኤል ሁለተኛ ተገለጠላቸው ። ዱራታዎስንም የዓሣውን ሆድ እንዲሠነጥቅ አዘዘው ። በሠነጠቀውም ጊዜ ሦስት መቶ የወርቅ ዲናር በዓሣው ሆድ ተገኘ ። ቅዱስ ሚካኤልም ዱራታዎስንና ቴዎብስታን እንዲህ አላቸው ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ ለባለ ዓሣውና ለባለ ሥንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ #እግዚአብሔር አስቧችኋልና በጎ ሥራችሁን መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን አስቦ በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ ። በኋላኛውም መንግሥተ ሰማያትን አዘጋጅቶላችኋል ። እነርሱም ሲሰሙ ስለዚህ ነገር ደነገጡ። እርሱም ከመከራችሁ ሁሉ ያዳንኳችሁ የመላእክት አለቃ እኔ ሚካኤል ነኝ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን ወደ #እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁ እኔ ነኝ አሁንም በዚህ ዓለም ከበጎ ነገር እንድታጡ አላደርጋችሁም አላቸው ። ይህንንም ብሎ ወደ ሰማያት ወጣ ። እነርሱም ሰገዱለት ተአምራቱም የማይቁጠር ብዙ ነው ። #ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበረ መልአክ ጸሎትና አማላጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን። ✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞ #ቅዱስ_ባህራን_ቀሲስ ዳግመኛም በዚህች እለት የባህራን ቀሲስ መታሰቢያ ነው። የዚህ የከበረ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ተአምራቱ ብዙዎች ናቸው ። ከእነርሱም አንዱ ይህ ነው ። #እግዚአብሔርን የሚፈራ አንድ ሰው ነበረ አርሱም የከበረ የሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ በየወሩ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ይልቁንም በሰኔና በኅዳር ወር አብልጦ ያከብር ነበር ። በጐረቤቱም ርኅራኄ የሌለው አንድ ባለጠጋ ሰው ነበረ ። ይህን #እግዚአብሔርን የሚፈራውን ሰው የከበረ መልአክ የሚካአልን በዓል በሚያደርግበት ጊዜ ይጠላውና ያቃልለው ነበር ለድኆች ስለ መራራቱም ይዘባበትበት ነበረ ። የሕይወቱ ዘመንም ተፈጽሞ የሚሞትበትና ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ድካምም የሚያርፍበት ጊዜ ሲቀርብ የክብር መልአክ ቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ታደርግ ዘንድ ምጽዋት ሰጭም ትሆን ዘንድ ሚስቱን አዘዛት ። ከዚህም በኋላ አረፈና ገንዘው ቀበሩት ሚስቱም ፀንሳ ነበረች የመውለጃዋ ጊዜም ደርሶ ምጥ ያዛት በታላቅ ጭንቀት ውስጥ ሳለችም እንዲህ ብላ ጸለየች የ #እግዚአብሔር መልአኩ ሆይ ራራልኝ በእርሱ ዘንድ ባለሟልነት አለህና በ #እግዚአብሔር ዘንድ ስለ እኔ ለምንልኝ ። ይህንንም በአለች ጊዜ በቤቷ ውስጥ ብርሃን በራ ከችግርም ዳነች መልኩ ውብ የሆነ ወንድ ልጅንም ወለደች የ #እግዚአብሔርም መልእክተኛ ቅዱስ ሚካኤል ከሰማይ ወርዶ ሕፃኑን እንዲህ ብሎ ባረከው ርኅራኄ የሌለውን የዚህን ባለጸጋ ገንዘብና ሀብት ጥሪቱንም ሁሉ ይህ ሕፃን እንዲወርስ #እግዚአብሔር አዝዟል ባለጸጋውም በቤቱ በዐልጋው ላይ ሳለ #ጌታ ጆሮውን ከፍቶለት ይህን ነገር ከመልአኩ ሰማ ። ይህንንም በሰማ ጊዜ ታላቅ ኀዘን ደረሰበት ሕፃኑንም የሚገድልበትን ምክንያት ይፈልግ ጀመረ ነገር ግን ክብር ይግባውና #ጌታ ይጠብቀው ነበር ። ከዚህም በኋላ ያ ባለጸጋ ምክንያት አዘጋጅቶ የሚያገለግለኝ ልጅ ይሆነኝ ዘንድ ልጅሽን ስጪኝ እኔም እየመገብኩና እያለበስኩ አሳድገዋለሁ ለአንቺም ሃያ ወቄት ወርቅ እሰጥሻለሁ አላት ። ይህንንም ነገር ከባለጸጋው በሰማች ጊዜ ስለችግሯ እጅግ ደስ አላት ልጅዋንም ሰጠችው እርሱም ሃያውን ወቄት ወርቅ ሰጣት ልጅዋንም ወሰደው የምሻው ተፈጸመልኝ ብሎ ደስ አለው ። ከዚህም በኋላ በልጁ ቁመት ልክ ሣጥን አሠርቶ ሕፃኑን በሣጥኑ ውስጥ አስገብቶ ዘጋበት እስከ ባሕርም ተሸክመው ወስደው በባሕር ጣሉት ክብር ይግባውና በ #ጌታችን ፈቃድ ያ ሣጥን ሳይሠጥም ከዚያች አገር የሃያ ቀን መንገድ ያህል ርቃ ወደምትገኝ ወደ አንዲት አገር ወደብ እስከሚደርስ በባሕሩ ላይ ተንሳፈፈ ።

√ የዩቲዩብ ገጻችንን https://youtube.com/@FinoteBirhanzkidistarsema?feature=shared √ ፌስቡክ ገጻች https://www.facebook.com/finotebirhanz
+3
√ የዩቲዩብ ገጻችንን https://youtube.com/@FinoteBirhanzkidistarsema?feature=shared √ ፌስቡክ ገጻች https://www.facebook.com/finotebirhanzekidistarsema √ የቴሌግራም ገጻችንን https://t.me @Z_FINOTE_BIRHAN √ የኢንስታግራም ገጻችን https://www.instagram.com/ FINOTE BIRHAN Z KIDIST ARSEMA √ የቲክ ቶክ ገጻችንን tiktok.com/@finotebirhanzkidstarsema ✨✨✨ፎሎ በማድረግ ቤተሰብ ይሁኑ ✨✨✨

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤         ❤ #ኅዳር ፲፩ (11) ቀን። ❤ እንኳን #አምላክ_ለወለደች_ለእመቤታች #ለቅድስት_ድንግል_ማርያም_እናት ለሆነች ለተመሰገነነች #ለቅድስት_ሐና ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከሁለተኛው #ከአርኬላዖስ_ሰማዕት፣ #ከአበምኔት_ኤልሳዕ፣ #ከመነኰስ_ጳኵሚስና_ከሰማዕቱ_ሚናስ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                            ✝️ ✝️ ✝️ ❤  #ቅድስት_ሐና፦ ይችም ቅድስት ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት ልጁ ናት። ለማጣትም ሦስት ልጆች አሉት የታላቂቱም ስሟ ማርያም ናት ሁለተኛዋም ስሟ ሶፍያ ሦስተኛዪቱም ስሟ ሐና ናት ታላቂቱ ማርያምም ለባል ተድራ አዋላጅ የሆነች ሰሎሜን ወለደቻት እርሷም መድኃኒታችንን ከወለደችበት ጊዜ ጀምሮ በስደቷም ወራት ከአረጋዊ ዮሴፍ ጋር እመቤታችንን ድንግል ማርያምን ያገለገለቻት ናት። ሶፍያም ለባል ተድራ ለመጥምቁ ዮሐንስ እናቱ የሆነች ቅድስት ኤልሳቤጥ ወለደቻት። ❤ ይችንም ቅድስት ሐናን ከይሁዳ ነገድ ለሆነ ጻድቅ ስሙ ኢያቆም ለሚባል አጋቧትና እመቤታችንን ቅድስት ድንግል ማርያምን ወለደቻት እሊህም ሰሎሜና ኤልሳቤጥ ለቅድስት ሐና የእኅትማማች ልጆች ናቸው። ❤ የዚችንም የቅድስት ሐናን በሥውር የምትሠራውን ገድሏንና ትሩፋቷን እንዳናስታውሰው አናውቀውም ግን ከሴቶች ሁሉ እንደምትበልጥና እንደምትከብር እናውቃለን እንረዳለን እርሷ አምላክን በሥጋ ለወለደችው ወላጅዋ ትሆን ዘንድ የተገባት ሁናለችና ከሴች ሁሉ የሚበልጥና የሚበዛ ትሩፋትና ተጋድሎ ባይኖራት ይህ ታላቅ ጸጋ ባልተገባት ነበር። ❤ ይህችም ጻድቅት ሐና መካን በመሆንዋ ልጅን ይሰጣት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ዘወትር በጸሎት ትማልድ ነበር እግዚአብሔርም በእርሷ ለዓለም ሁሉ ድኅነት የተደረገባትን ይቺን የተባረከችና የከበረች ልጅን ሰጣት እርሷም አምላክን የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት። ስለዚህም ይህን ታላቅ ጸጋ ስለሰጣት የበዓሏን መታሰቢያ በደስታ ልናከብር ይገባል። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በቅድስት ሐና በጸሎቷ የሚኝ በረከቷም ከእኛ ጋር ይሁን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የኅዳር 11 ስንክሳር።                              ✝️  ✝️ ✝️ ❤ "#ሰለም_ለኪ_ለጸሎተ_ኵሉ_ምዕራጋ። ከመ አስካለ ወይን ዲበ ሐረጋ። #ሐና_ብፅዕት ተፈሥሒ እንበለ ንትጋ። እስመ ረከብኪ ሞገሰ ወአድማዕኪ ጸጋ። እምሔውተ አምላክ ትኩኒ በሥጋ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የኅዳር+11።                            ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳት። ያበድሮን እግዚአብሔር ለአናቅጸ ጽዮን። እምኲሉ ተዒይኒሁ ለያዕቆብ"። መዝ 86፥1-2። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 3፥23-ፍ.ም።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "አዋልደ ንግሥት ለክብርከ። ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት"። መዝ 44፥9። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ጢሞ 5፥5-11፣ 1ኛ ጴጥ 3፥5-7 እና የሐዋ ሥራ 16፥14-19። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 18፥1-9። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የቅድስት ሐና የዕረፍት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።

ሕዳር 10 /፲/ አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ኅዳር ዐሥር በዚች ቀን ቅዱሳት ንጹሐት መነኰሳይያት ደናግል እናታቸው ሶፍያም በሰማዕትነት አረፉ። እሊህም ቅዱሳት ከተለያዩ
ሕዳር 10 /፲/
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ኅዳር ዐሥር በዚች ቀን ቅዱሳት ንጹሐት መነኰሳይያት ደናግል እናታቸው ሶፍያም በሰማዕትነት አረፉ። እሊህም ቅዱሳት ከተለያዩ አገሮችና ቦታዎች ሲሆኑ መለኮታዊ ፍቅር በአንድነት ሰበሰባቸው የምንኲስናንም ልብስ ለበሱ ይኸውም የመላእክት ልብስ ነው። በሮሜ አገር ካሉ ገዳማትም በአንዱ የሚኖሩ ሆኑ ቅድስት ሶፍያም በእነርሱ ላይ እመ ምኔት ሆነች። እርሷም ጸጋንና ዕውቀትን የተመላች ናት፤ የቅዱሳን መነኰሳትን ገድል በማንበብ እየጾሙ እየጸለዩ በምድር ላይ እንደ መላእክት እስከ ሆኑ ድረስ መንፈሳዊ ዕድገትን አሳደገቻቸው ከእነርሱም በአንድ ገዳም ውስጥ ሰባ ዓመት ያህል የኖሩ አሉ ከውስጣቸውም ልጅ እግሮች የሆኑ አሉ። ከሀዲ ንጉሥ ዑልያኖስም ከፋርስ ንጉሥ ከሳቦር ጋር ሊዋጋ በሮሀ ሀገር በኩል በሚያልፍ ጊዜ እርሱ ሳቦር ሊወጋው ወደርሱ እንደሚመጣ ሰምቷልና አልፎ ሲሔድም በውስጡ እሊህ ደናግል ያሉበትን ገዳም አይቶ ይህ ምንድን ነው ብሎ ጠየቀ ሰዎችም ይህ የደናግሎች ገዳም ነው አሉት። በዚያንም ጊዜ ወደዚያ ገዳም ገብተው ደናግሎችን እንዲገድሏቸው በገዳሙ ውስጥም ያለ ገንዘባቸውን ሁሉ እንዲዘርፉ ወታደሮቹን አዘዘ ወታደሮችም ገብተው እሊያን ደናግል በሰይፍ ገደሏቸው ገዳሙንም አጠፉ የገዳሙን ገንዘብ ሁሉንም ዘረፉ ። ከሀዲውን ንጉሥ ግን ስለ መንጋዎቹ በቀል እግዚአብሔር ተበቀለው ይህም እንዲህ ነው ያጠፋው ዘንድ ሰማዕት መርቆሬዎስን አዘዘው መርቆሬዎስም በአካለ ነፍስ ሒዶ በጦር ወጋውና በክፉ አሟሟት ሙቶ ወደ ዘላለም ሥቃይ ሔደ። እሊህ ቅዱሳት ደናግል ግን ወደ ዘላለም ተድላ ደስታ ገቡ። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር

ኅዳር ፱ /9/ በዚች ዕለት ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ አንደኛ የእስክንድርያ አገር ሊቃ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ይስሐቅ አረፈ። ወላጆቹ ይህን ቅዱስ በወለዱት ጊዜ በታላቅ ደስታ ደስ ተሰኙበት። ያጠም
ኅዳር ፱ /9/
በዚች ዕለት ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ አንደኛ የእስክንድርያ አገር ሊቃ ጳጳሳት ቅዱስ አባት ይስሐቅ አረፈ። ወላጆቹ ይህን ቅዱስ በወለዱት ጊዜ በታላቅ ደስታ ደስ ተሰኙበት።  ያጠምቀው ዘንድ ወደ ኤጲስቆጶስ በአቀረቡት ጊዜ ሲያጠምቀው በሕፃኑ ራስ ላይ የብርሃን መስቀልን አየ። እንዲህም ብሎ ትንቢት ተናገረለት ይህ ሕፃን በእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ላይ ይሾማል እርሱ ለእግዚአብሔር የተመረጠ መሣሪያ ይሆናልና። የቤተ ክርስቲያንን ትምህርትና ጽሕፈትን አስተማሩት ወላጆቹንም ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ በአበምኔቱ በአባ ዘካርያስም ዘንድ መንኩሶ በገድል ተጠመደ። በአንዲትም ዕለት አንድ ጻድቅ ሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አየው በእርሱም ላይ ይስሐቅ በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ይሾም ዘንድ አለው ብሎ ትንቢት ተናገረ። ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስ ጸሐፊ የሚሆነውና የሚረዳው ብልህ ሰው ፈለገ ስለ አባ ይስሐቅም ነገሩት እሱንም አስመጣው ይጽፍለትም ዘንድ ደብዳቤ ሰጠው እርሱ ግን አባ ይስሐቅ እያወቀ ጽሕፈቱን አበላሽ ሊቀ ጳጳሳቱ እንዲተወውና ወደ አስቄጥስ ገዳም እንዲመለስ ነበር የዚህን ዓለም ክብር ይጠላልና። ሊቀ ጳጳሳቱም እንዲተወውና እንዲአሰናብተው አውቆ ማበላሸቱን በአወቀ ጊዜ በጥሩ ጽፈሃል  እንድትሔድም እኔ አልተውህም አለው ከወራትም በኋላ አባ ይስሐቅ ወደ አስቄጥስ ገዳም ተመለሰ አባ ዮሐንስም የሚያርፍበት ቀን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔርን በራእይ ከአንተ በኋላ ለዚች ሹመት የሚጠቅም ረዳትህ ይስሐቅ ነው አለው። አባ ዮሐንስ በአረፈ ጊዜ ይህን ቅዱስ አባት ይስሐቅን ይዘው በእስክንድርያ አገር ላይ ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ :- መጽሐፈ ስንክሳር

🔥 ✣ #_አርባዕቱ_እንስሳ  ✢ #ህዳር_8 በዓላቸው       መንፈሳውያን አመስጋኞችና መዘምራን የምትሆኑ                አራቱ እንስሳት ስለ አኛ ለምኑ   🍂አርባዕቱ እንስሳ መንፈሳውያን ሰባሕያን ወመዘምራን                       ሰዐሉ በእንቲአነ       ( አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመጽሐፈ ሰዓታት )                       #_ኪሩቤል                           🔥 ገጸ ሰብዕ                           🔥  ገጸ አንበሳ      #_ሱራፌል           💥 ገጸ ላህም           💥  ገጸ ንስር 👉 ገጸ ሰብዕ ፦ ስለ ሰው ልጆች ይለምናል       ገጸ አንበሳ ፦ ስለ አራዊት ይለምናል       ገጸ ላህም ፦ ስለ እንስሳት ይለምናል       ገጸ ንሥር ፦ ስለ አዕዋፍ ይለምናል ( ሥንክሳር ኅዳር 8 ፥ ቁጥር 17 ) 🔥 ቅዱስ ጄሮም እንዲህ አለ ፦      አርባዕቱ እንስሳት የድኅነታችን ምሥጢር የሆኑትን አራት ደረጀዋች ያስረዳሉ ።      ገጸ ሰብእ ፦ ሥጋዌውን ( ቃል ስጋ መሆኑን )          ገጸ አንበሳ ፦ ትንሣኤውን         ገጸ ላህም ፦ ንጹሕ መሥዋዕት ( ቤዛ ) መሆኑን         ገጸ ንሥር ፦ ዕርገቱን 🔥  አርባዕቱ አንስሳት                  የጳጳሳት                  የቀሳውስት                  የዲያቆናት                 የምዕመናን    ( የቤተ ክርስቲያን አምድ እኚህ ናቸውና )    🔥 የእግዚአብሔርን ባሕርያት ያመለክታሉ።             ገጸ ሰብእ ፦ ጥበቡንና ዕውቀቱን                   ገጸ አንበሳ ፦ ግርማውንና ኃይሉን                    ገጸ ላህም ፦ ትዕግስቱን ፈታሒነቱን                     ገጸ ንሥር ፦ ክብሩን ልዕልናውን 🔥አንድም አርባዕቱ እንስሳት በአራቱ ወንጌላውያን ይመሰላሉ።      🔥 “አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሉአቸው፥ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዓይኖች ሞልተውባቸዋል፤ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም።”    ( ራእይ 4፥8 )   🔥 #አርባዕቱ_እንስሳት      #በእመቤታችን_ድንግል_ማርያም_ይመሰላሉ።    እነሱ መንበሩን ለመሸከም እንደተመረጡ ፤  ሰማይና ምድር የማይችሉትን አምላክ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኗ ተሸክማዋለችና ።   ወርኃዊ መታሰቢያ በዓላቸው  በ 8 ነው. 🙏 በረከት ረድኤታቸው አይለየን 🙏

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤       ❤ #ኅዳር ፰ (8) ቀን። ❤ እንኳን #የቅድስት_ሥላሴ_መንበር_ለሚሸከሙ ሥጋ ለሌላቸው #ለአርባዕቱ_እንስሳ_ለኪሩቤል ለመታሰቢያ ዓመታዊ በዓላቸው፣ ለመላእክት አለቃ #ለቅዱስ_አፍኒን_ለተሸመበት_በዓል፣ #ለአቡነ_አምደ_ሚካኤል ዘወሎ ለልደታቸው በዓል፣ #ለታላቁ_አባት_ለአቡነ ኪሮስ ለቅዳሴ ቤታቸው  መታሰቢያና ለበዓላቸው ለአረማዊ መኰንን ልጅ ለነበረ #ለአባ_ቅፍሮንያ_ለዕረፍትበዓል በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከሊቀ ጳጳሳት #ከአባ_ዮሐንስ ከመታሰቢያው፣ #ከንጉሥ_ቈስጠንጢኖስ መስቀል ከተገለጠለትና ከሰማዕት #ከቅዱስ-ኤስድሮስ ማኅበር ከሆኑ #ከመቶ_ሰማንያ ሁለት ከመታሰቢያቸው ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                           ✝ ✝ ✝ ❤ #በዚች_ቀን_ሥጋ_የሌላቸው_የአርባዕቱ_እንስሳ በዓላቸው ሆነ። እሊህም መንበሩን የሚሸከሙ የእግዚአብሔር ሠረገላዎቹ ናቸው ስለ እርሳቸውም ወንጌልን የጻፈ ዮሐንስ እንዲህ ሲል እንደመሰከረ "በዚያ ዙፋን ፊት በረድ የሚመስል ባሕር አለ በዙፋኑም ዙሪያ አራት እንስሶች አሉ በፊትም በኋላም ዐይንን የተመሉ ናቸው። የፊተኛው አንበሳ ይመስላል ሁለተኛውም ላም ይመስላል ሦስተኛውም የሰው መልክ ይመስላል አራተኛውም የሚበር አሞራ ይመስላል። የእሊህም የአራቱ እንስሶች እያንዳንዱ ክንፋቸው ስድስት ስድስት ነው ሁለንተናቸውም ዐይኖችን የተመሉ ናቸው የነበረ የሚኖር የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ጽዑዕ ክቡር ልዩ ነው እያሉ በመዓልትና በሌሊት ዕረፍት የላቸውም። ❤ ሁለተኛውም ስለእርሳቸው ኢሳይያስ እንዲህ አለ "ከዚህም በኋላ ንጉሡ ኦዝያን በሞተ ጊዜ አሸናፊ እግዚአብሔርን ሰፊ በሆነና ከፍ ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ብርሃኑም ቤቱን መልቶ ሱራፌልም በዙሪያው ቁመው አየሁት። የአንዱም የአንዱም ክንፋቸው ስድስት ነው በሁለቱ ክንፋቸው ፊታቸወን በሁለቱ ክንፋቸው እግሮቻቸውን ይሸፍናሉ በሁለቱ ክንፎቻቸው ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ይበራሉ። አንዱም አንዱም ከአንዱ ጋር ፍጹም አሸናፊ የሆንክ እግዚአብሔር ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብለህ የምትመሰገነው ምስጋናህ በምድርና በሰማይ የመላ ነው እያሉ ያመሰግናሉ"። ❤ ነቢዩ ዳዊትም "በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ" አለ ሁለተኛም "በኪሩቤል ላይ የተቀመጠ እርሱ ምድርን አናወጻት" አለ። ❤ ሕዝቅኤልም እንዲህ አለ "ከወደ ሰሜን እነሆ ጥቅል ነፋስ ሲመጣ አየሁ ታላቅ ደመና አለ በዙሪያውም ብርሃን አለ ከእርሱም እሳት ቦግ ብሎ ይወጣል። በደመናውም መካከል ባለ በእሳቱ ውስጥ እንደ አራት ራስ አሞራ መልክ የሚመስል አለ በመካከሉም እንደ አራቱ ኪሩቤል መልክ ያለ አለ። መልካቸውም እንዲህ ነው በውስጣቸው የሰው መልክ አላቸው የአንዱም የአንዱ ፊት አራት ነው ክንፉም አራት ነው። እግራቸውም የቀና ነው ከእግራቸውም ክንፍ አላቸው ሰኰናቸው ግን እንደ ላም ሰኰና ነው ከሱም እሳት ቦግ ይላል እንደጋለ ብረት ፍንጣሪም ይበራል"። ❤ ወንጌላዊ ዮሐንስም ዳግመኛ እንዲህ አለ "በዚያው ዙፋን ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ የእንስሶቹንም የእነዚያ አለቆችንም ቃል ሰማሁ ቊጥራቸውም እልፍ አለቆች ያሉአቸው ብዙ የብዙ ብዙ ነው። ለዚያ ለተገደለው በግ ኃይልን ባለጸግነትን ጥበብን ጽናትን መንግሥትን ክብርን ጌትነትን ምስጋናን ገንዘብ ሊያደርግ ይገባል ብለው በታላቅ ቃል ተናገሩ። በሰማይና በምድር ከምድር በታች በባሕር ውስጥ በእነዚያም ውስጥ የተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ጌትነት ክብር ኃይል በረከት በዙፋኑ ለተቀመጠው ለሱ ለበጉም ለዘላለሙ ይገባል" አሉ "በእውነት ይገባል"። እሊህም አራቱ እንስሶች "አሜን" ይላሉ። እሊያም አለቆች ይሰግዳሉ"። ❤ ስለ ልዕናቸውና ስለ ክብራቸው ለእሊህ አርባዕቱ እንስሳ ከብሉይና ከሐዲስ ብዙ መጻሕፍት መስክረዋል መሐሪና ይቅር ባይ እግዚአብሔርም ስለ ሁሉ የሰው ፍጥረት ይለምኑት ዘንድ ቀራቢዎቹ አደረጋቸው። ዳግመኛም እንዲህ ተባለ "ገጸ ሰብእ ስለሰው ፍጥረት ይለምናል ገጸ አንበሳ ስለ አራዊት ይለምናል ገጸ ላሕም ስለ እንስሳ ይለምናል ገጸ ንስርም ስለ አዕዋፍ ይለምናል" ከሰማይ ሠራዊት ሁሉ እነርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ በባለሟልነት እጅግ የቀረቡ ናቸውና። ❤ ስለዚህም በዓለሙ ሁሉ በስማቸው አብያተ ክርስቲያን እንዲታነፁ በዚችም ቀን መታሰቢያቸው እንዲደረግ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙ እነርሱ  ስለ ሰው ወገን በእግዚአብሔር ዘንድ ይማልዳሉና። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ኪሩቤል አማላጅነት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #ሊቀ_መላእክት_ቅዱስ_አፍኒን፦ ይህም ከሱራፌልና ከኪሩቤል ጋር የልዑልን የጌቱነቱን ዙፋን የሚጠብቅ ነው ስለርሱ ሄኖክ እንዲህ አለ "ያንን ቤት ሱራፌልና አፍኒን ዙሪያውን እየዞሩ ይጠብቁታል" እነርሱም የልዑልን የጌትነቱን ዙፋን ሲጠብቁ የማያንቀላፉ ናቸው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በመልአኩ ቅዱስ አፍኒን አማላጅነት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ቅፍሮንያ፦ ይህ አባት የአረማዊ መኰንን ልጅ ነው። ከዕታትም በአንዲቱ ስሙ መርቆሬዎስ የሚባል መነኰስ ከአባ ጳኲሚስ ገዳም ወደ አገሩ መጣ እርሱ ክርስቲያን እንደሚሆን በእርሱ ላይ ትንቢት ተናገረ። ከጥቂት ወራትም በኋላ ገዳማትን ሊአጠፋ ምርኮንም ሊማርክ ሠራዊቱን ሰብስቦ ወደ ግብጽ አገር ዘመተ ወደ አባ ጳኲሚስም ገዳም በደረሰ ጊዜ አበ ምኔቱ ወደርሱ ወጥቶ "እኔ ነኝ" አለው ቅፍሮንያም ሰምቶ አበ ምኔቱን ለብቻው አግልሎ እንዲአጠምቀውና የምንኲስናንም ልብስ እንዲአለብሰው ለመነው አበ ምኔቱም "እሺ በጎ" አለው። ❤ ከዚህም በኋላ ሠራዊቱ ወደ አገራቸው በተመለሱ ጊዜ ብቻቸውን ቀረ በዚያንም ጊዜ ተጋድሎውንም በመጾምና በመጸለይ ጀመረ። ሰይጣንም በእርሱ ላይ ቀንቶ ነገረ ሠሪ አስነሣበት በመኳንንቱም ዘንድ ወነጀለው እነርሱም "አገራችንን ያጠፋ የመኰንን ልጅ ከዚህ አለ" ብለው ገዳሙን ከበቡ እግዚአብሔር ሠወረው በአጡትም ጊዜ ነገረ ሠሪውን ገደሉት። ❤ ይህም ቅዱስ በገድል ተጠምዶ ኖረ በየሰባት ቀንም ይጾማል ያለ መራራ አደንጓሬ አይመገብም። በዚያም ወራት የምድር አውሬ እንስሶቻቸውን እየገደለ በገዳሙ ላይ ጥፋትን አደረሰ አባ ቅፍሮንያም ወደርሱ መጥቶ እንደ በግ ይዞ አሠረው ዐሥር ዓመትም ቆይቶ ሞተ። ❤ ቅድስ ቅፍሮንያም የእግዚአብሔር መልአክ እየመራው ወደ ኢየሩሳሌም ሔደ በአንዲትም ቀን ደረሰ በዚያም ታላቅ ምሥጢርን አየ ከከበሩ ቦታዎችም ተባርኮ ወደ መኖሪያው ተመልሶ በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የኅዳር 8 ስንክሳር።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "እግዚአብሔር ነግሠ ደንገፁ አሕዛብ። ዘይነብር ዲበ ኪሩቤል አድለቅለቃ ለምድር። እግዚአብሔር ዐቢይ በጽዮን"።  መዝ98፥1-2። የሚነበበው ወንጌል ማር16፥14-ፍ.ም                

                              ✝ ✝ ✝ 🌹 #ሐዲስ_ቅዱስ_መርቆሬዎስና_ወንድሙ_ቅዱስ_ዮሐንስ፡- እነዚህም ቅዱሳን የደጋግ ክርስቲያን ልጆች ናቸው፡፡ የታላቁ ስም ሙናሂ ነበር ሲመነኩስ ግን መርቆሬዎስ ተባለ፡፡ የታናሹም ስም አቡፈረዥ ነበር እርሱም ሲመነኩስ ዮሐንስ ተባለ፡፡ ሁለቱም ወንድማማቾች ወደ ሊቀ ሠራዊት ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም ገብተው ጽኑ የሆነ ተጋድሎአቸውን ጀመሩ፡፡ ለመነኰሳቱ ሁሉ የሚላላኩና የሚያገለግሉ ሆኑ፡፡ ጣዕም ካላቸው ምግቦችና መጠጦች እንዲሁም ከእንቅልፍ እርቀው በታላቅ ተጋድሎ ኖሩ፡፡ የሚመገቡትም በሦስት ቀን አንድ ጊዜ ሆነ፡፡ የግብፅንና የሌላውንም ጽሕፈት ተምረው መጻሕፍትን መረመሩ፡፡ እነዚህም ወንድማማቾች አንድ ቀን አብረው ሳሉ የታዘዘ መልአክ ተገለጠላቸውና ወደ ምስክርነት አደባባይ ሄደው ስለጌታችን ስለ ስሙ እንዲመሰክሩና ሰማዕትነታቸውን እንዲፈጽሙ ነገራቸው፡፡ 🌹 እነርሱም እንደታዘዙት በከሃዲው መኰንን ፊት ሄደው ስለ ጌታችን ክብር መሰከሩ፡፡ መኰንኑም የተለያዩ ጽኑ ሥቃዮችን አሠቃያቸው፡፡ ከብዙ ሥቃይም በኋላ በወህኒ ቤት ተጥለው ሳለ ሌላ መኰንን ተሹሞ እርሱም ሊተዋቸው በወደደ ጊዜ የአገሩ ሰዎች "እነርሱን ካልገደልካቸው በንጉሡ ዘንድ እንከስሃለን" አሉት፡፡ ይህም መኰንን ሕዝቡን ከመፍራቱ የተነሣ ፈቃዳቸውን ይፈጽምላቸው ዘንድ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ ሕዝቡም ኅዳር 7 ቀን ሐዲስ የተባለ የቅዱስ መርቆሬዎስንና የወንድሙ የቅዱስ ዮሐንስን ራስ በሰይፍ ከቆረጧቸው በኋላ የሰማዕትነት ፍጻሜአቸው ሆነ፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ 🌹 #ቅድስት_ዘኖብያ እና ልጇ ቅዱስ ዘኖቢስ፡- እነዚህም ቅዱሳን ተበይስ ከምትብል አገር ከታላላቅ ወገኖች የተገኙ ሰማዕታት ናቸው፡፡ እነርሱም ክርስቲያኖች እንደሆኑ በከሃዲው ንጉሥ ዘንድ ዜናቸው ተሰማ፡፡ ንጉሡም ወደ እርሱ ካስመጣቸው በኋላ እምነታቸውን መረመራቸው፡፡ እነርሱም "አገራችን ተበይስ ነው የምናመልከውም የክብርን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው" አሉት፡፡ ✝ ከዚህም በኋላ ንጉሡ እናትና ልጅን "ለአማልክት ሠው" አላቸው፡፡ ቅዱሳኑም "እኛስ ለእውነተኛው አምላክ ለክርስቶስ እንሠዋለን እንጂ ለረከሱ ጣዖታት አንሠዋም" አሉት፡፡ ንጉሡም በዚህ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ቅድስት ዘኖብያንና ልጇን ቅዱስ ዘኖቢስን ጽኑ በሆነ ሥቃይ አሠቃያቸው፡፡ ልብሳቸውን ገፈው በራሳቸው ጸጉር ተቅለው እየደበደቡ እንዲያሠቃዩአቸው አደረገ፡፡ ቅዱሳኑም ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜ ማሰሪያው በተአምራት ተፈታላቸው፡፡ የብርሃን ልብሶችንም ለብሰው ሕዝቡ ሁሉ አዩአቸው፡፡ ይህንንም ባዩ ጊዜ "የእነዚህ ቀዱሳን አምላካቸው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይክበር ይመስገን እኛም በአምላካቸው አምነናል" እያሉ ጮኹ፡፡ ንጉሡም በታላቅ ቁጣ ሆኖ እናትና ልጅን እርስ በእርስ እንዲተያዩ አድርጎ በሁለት መስቀሎች ላይ እርቃናቸውን ሰቀላቸው፡፡ በዚያን ጊዜም ደመና መጥታ ሸፈነቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ብዙዎች በጌታችን አመኑ፡፡ 🌹 ዳግመኛም ንጉሡ ቅድስት ዘኖብያንና ልጇን ቅዱስ ዘኖቢስን በብረት ወንበሮች ላይ አስሮ በማስቀመጥ ከሥር በሚነድ እሳት አቃጠላቸው፡፡ ጌታችንም ከዚህ ሥቃይ አዳናቸው፡፡ በወንበሩም ላይ ሆነው በእሳት እየተቃጠሉ ሳለ ሕዝቡን ያስተምሩ ጀመር፡፡ ንጉሡም ይህንን ባየጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ቁመቱና ጎኑ ሃያ ሃያ ክንድ የሆነ ጉድጓድ ቆፍረው በውስጡም እሳትን እንዲያነዱበትና ቅዱሳኑን ከዚያ እንጨምሯቸው አደረገ፡፡ ነገር ግን አሁንም ቅድስት ዘኖብያንና ልጇን ቅዱስ ዘኖቢስን ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜ እሳቱ ፈጥኖ ጠፋ፡፡ ንጉሡም ከዚህ በኋላ ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ በሰይፍ አንገታቸውን ቆርጠው እንገድሏቸውና እስከ ነገ ድረስ በድናቸውን ጠብቀው በእሳት እንዲያቃጥሉአቸው በነፋስም ውስጥ እንዲበትኑአቸው አዘዘ፡፡ ቅዱሳኑንም በገደሏቸው ጊዜ ነጎድጓድ መብረቅ ንውጽውጽታ ሆነ፣ ዝናብም ዘነበ፡፡ በዚህም ታላቅ ንውጽውጽታ ምክንያት 54 ሰዎች ሞቱ፡፡ በሌሊትም ምእመናን መጥተው የቅሱሳኑን ሥጋ በሥውር ወስደው ቀበሯቸው፡፡ በማግሥቱም ንጉሡ በድናቸውን በፈለገ የሆነውን ሁሉ ተረዳ፡፡ የሆነውን ሁሉ ባስተዋለ ጊዜ ዐይነ ልቡናው በራለትና በጌታችን አምኖ ንስሓ ገብቶ ተጠመቀ፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ 🌹 #ሰማዕቱ_አባ_ናህርው፡- ይኸውም ቅዱስ ከግብጽ አገር ከፍዩም መንደር የተገኘ ታላቅ ሰማዕት ነው፡፡ ይኸውም ቅዱስ ፈሪሃ እግዚአብሔር በእጅጉ ያደረበት ደገኛ ክርስቲያን ነው፡፡ በእስክንድርያ አገር በከሃዲያን መኳንንት የሚሠቃዩትንና የሚሞቱትን የክርስቲያኖቹን ዜና በሰማ ጊዜ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይሁንና ስለ ጌታችን ስለ ስሙ ሰማዕት ይሆን ዘንድ ተመኘ፣ የሰማዕትነት ክብርንም ይቀዳጅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ እግዚአብሔር ጸሎቱን ሰማውና በራእይ ተገልጦለት "ወደ አንጾኪያ አገር ሂድ በዚያ በሰማዕትነት ትሞት ዘንድ አለህ" አለው፡፡  🌹 አባ ናህርው ከዚህ በኋላ ወደዚያ እንዴት መድረስ እችላለሁ ብሎ ሲያስብ እግዚአብሔር ቅዱስ ሚካኤልን ላከለትና መልአኩ ይህንን ቅዱስ በክንፎቹ ተሸክሞ ወደ አንጾኪያ አገር አደረሰው፡፡ አንጾኪያ አገር ላይ ያለው ንጉሥ ደግሞ እጅግ ጨካኝ የሆነው የክርስቲያኖችን ደም በዓለም ዙሪያ ያፈስ የነበረው ዲዮቅልጥያኖስ ነበር፡፡ እናም አባ ናህርው በከሃዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ፊት በደረሰ ጊዜ የእግዚአብሔር ክብር መሰከረ፡፡ ንጉሡም ስሙንና አገሩን ጠየቀው፡፡ እርሱም ከግብጽ አገር እንደሆነ አስረዳው፡፡ ንጉሡም ቃሉን ከሰማ በኋላ ለጣዖታቱ ቢሠዋለት ብዙ ገንዘብና ሥልጣን እንደሚሰጠው ቃል ገባለት፡፡ ነገር ግን አባ ናህርው በጌታችን ታመነ፡፡ ንጉሡም "ትእዛዜን አልሰማም ካልክ አሠቃይቼ ለሞት እዳርግሃለሁ" እያለ በተደጋጋሚ ቢናገረውም አባ ናህርው ግን ከሥቃዩ የተነሣ አልፈራም፡፡ 🌹 ከዚህም በኋላ ንጉሡ ቅዱስ አባ ናህርውን በብዙ ዓይነት ሥቃዮች እንዲያሠቃዩት አደረገው፡፡ በእሳት ውስጥ ቢጨምሩት ረድኤተ እግዚአብሔር ጠብቆት ምንም ሳይቃጠል ቀረ፡፡ ዳግመኛም ለተራቡ አንበሶች ቢሰጡት አንበሶቹም ምንም ሳይነኩት ቀሩ፡፡ በሌላም ጊዜ በትልቅ ወጪት አድርገው በእሳት ቀቀሉት ነገር ግን አሁንም ምንም አልሆነም፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሡ ዲዮቅልጥያኖስ አባ ናህርውን ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ በዚህች ዕለት አንገቱን በሰይፍ አስቆረጠውና የቅዱስ አባታችን የሰማዕትነት ፍጻሜአቸው ሆነ፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።  ምንጭ፦ የኅዳር 7 ስንክሳርና መዝገበ ቅዱሳን።                                                        ✝ ✝ ✝ 🌹 #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኒሁ። አምላከ እስራኤል ውእቱ ይሁብ ኃይለ ወፅንዐ ለሕዝቡ። ወይትባረክ እግዚአብሔር"። መዝ67፥35 የሚነበበው ወንጌል ዮሐ1 4፥1-15።

🌹 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌹           🌹 #ኅዳር ፯ (7) ቀን። 🌹 እንኳን #ለሰማዕታት_አለቃ_ለታላቁ_መስተጋድል #ለቅዱስ_ጊዮርጊስ_በልዳ_አገር (በዓለም ላይ) #ቤተ_ክርስቲያን_ለከበረችበት፤ ጌታችን በውስጧ ላደረገው ድንቅ ተአምር፣ ሰባ ነገሥታት #ከደሃይቱ_መበለት ቤት አስረውት ሳለ #ልጇን_ለፈወሰበት፤ ታስሮ የነበረበትን ደረቅ ምሰሶ ከሃገሪቱ ቅጽር በላይ እንዲታይ #ላለመለመበት፤ #ዲዳ_ደንቆሮ_ዕውርና_አንካሳ የነበረው ልጇን #ለፈወሰበት_ለዓመታዊ_መታሰቢያ_በዓል #ከእስክድርያ_አገር ለሆነ ሰማዕትነት ለተቀበለ #ለቅዱስ_ጊዮርጊስ_ለዕረፍቱ_በዓል፣ ከግብፅ አገር ከፍዩም መንደር ሰማዕትነት ለተቀበለ #ለአባ_ናህርው ለዕረፍት በዓል ከገምኑዲ አውራጃ ከአገረ ተመይ ለሆነ ኤጲስቆጶስ #ለአባ_ሚናስ_ለዕረፍቱ_በዓል መታሰቢያ፣ ተበይስ ከምትባል አገር ከታላላቆች ወገን ለሆኑ ሰማዕትነት ለተቀበሉ #ለቅዱሳን_ዘኖቢስና_ለእናቱ_ዘኖብያና_ለዕረፍታቸው በዓልና #ለቅዱሳን_ሐዲስ_መርቆሬዎስና #ለወንድሙ_ቅዱስ_ዮሐንስ_ለዕረፍታቸው_በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                                                                                ✝ ✝ ✝ 🌹 በዚችም ቀን #የልዳ_አገር_የሆነ_የሰማዕታት_አለቃ_የታላቁ_መስተጋድል_የቅዱስ_ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት ነው ዳግመኛም ጌታችን በውስጧ ላደረገው ድንቅ ተአምር መታሰቢያ ሆነ። 🌹 ይህም እንዲህ ነው በውስጧ ድንቆች ተአምራት እንደሚሠሩ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስም በሰማ ጊዜ ሊአፈርሳት አሰበ ስሙ አውህዮስ የሚባለውንም መኰንን ከብዙ ሠራዊት ጋር ላከው ያም መኰንን በደረሰ ጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል ወዳለበት አዳራሽ በትዕቢት ሆኖ ገባ በሥዕሉም ፊት በብርጭቆ መቅረዝ መብራት ነበረ በቤተ ክርስቲዪኒቱና በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ እየዘበተ በእጁ በያዘው በትር የመብራቱን መቅረዝ መትቶ ሰበረው የመቅረዙም ስባሪ ወደ ከሀዲው ራስ ደረሶ መታው ራሱንም ታመመ ፍርሃትና እንቅጥቅጥም መጣበት ወድቆም ተዘረረ ባልጀሮቹም ወደ አገሩ ሊወስዱት ተሸከሙት በክፉ አሟሟትም ተጎሳቊሎ ሞተ ወስደውም ከባሕር ጣሉት ወገኖቹም ወደ አገራቸው አፍረው ተመለሱ። 🌹 ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ በልዳ አገር ያለች ነቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተ ክርስቲያን ያፈርሳት ዘንድ ራሱ ተነሥቶ ሔደ በዚያንም ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መታው ሰባት ዓመት ያህልም ዐይኖቹ ታውረው አእምሮውንም አጥቶ ቁራሽ እንጀራም እየለመነ ኑሮ ሞተ። 🌹 ክብር ይግባውና ጌታችንም የቤተ መንግሥቱን ሰዎች አስነሣበት እርሱን አስወግደው ጻድቅ ሰው ቈስጠንጢኖስን በእግዚአብሔር ፈቃድ አነገሡት እርሱም በአዋጅ የጣዖታትን ቤቶች ዘግቶ አብያተ ክርስቲያናትን ከፈተ ለክርስቲያን ወገኖችም በሁሉ ዓለም ተድላ ደስታ ሆነ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የኅዳር 7 ስንክሳር።                                                 ✝ ✝ ✝ 🌹 #ሰማዕቱ_ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ዘእስክንድርያ፡- አባቱ በእስክንድርያ አገር በንግድ ሥራ ይተዳደር የነበረ ሲሆን ልጅ ስላልነበረው በልዳው ኮከብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ወደተሠራች አንዲት ቤተ ክርስቲያን ሄዶ በቅዳሴ ቤቱ ክብረ በዓል ቀን ልጅ እንዲሰጠው ሰማዕቱን በስዕለት ጠየቀው፡፡ ስዕለቱም ተሰምቶለት ልጅ ሲወልድ ስሙን በሰማዕቱ ስም ጊዮርጊስ ብሎ ጠራው፡፡ ሚስቱም የእስክንድርያው አስተዳዳሪ የአርማንዮስ እኅት ናት፡፡ ጊዮርጊስ ከተወለደ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ እናትና አባቱ ስለሞቱ አስተዳዳሪ አጎቱ ወስዶ አሳደገው፡፡ አጎቱም ጣዖትን የሚያመልክ ነው፡፡ ነገር ግን ጊዮርጊስ እስከ 20 ዓመቱ ድረስ በሃይማኖቱም እጅግ ጠንካራ ሆነ፡፡ በጾም በጸሎት እየተጋ ነዳያንን አብዝቶ ይመግብ ነበር፡፡ የጽድቅ ሥራውንም ሰው አያውቅበትም ነበር፡፡ 🌹 የአስተዳዳሪው ብቸኛ ሴት ልጅ ልዩ ልዩ የተዋቡ ቦታዎችን ትጎበኝ ዘንድ ከቤት ወጥታ ወደ ደብረ ቁስቋም ስትደርስ የቤተ ክርስቲያንን የቅዳሴ ዝማሬ ሰምታ ልቧ እጅግ ደስ ተሰኘ፡፡ የአክስቷ ልጅ የሆነ ጊዮርጊስንም መነኮሳቱ ስለሚያሰሙት ዝማሬ ጠየቀችው፡፡ እርሱም ምንነቱን ካስረዳት በኋላ በዚያውም የሃይማኖትን ነገር በደንብ አስተማራት፡፡ ልጅቱም ወደ ከሃዲው አስተዳዳሪው አባቷ ዘንድ ቀርባ ስለ ጌታችን ክብር ትመሰክር ጀመር፡፡ አባቷም ሊሸነግላት ቢሞክር ነገሩን እንዳልሰማችው ሲያውቅ ብቸኛና አንድያ ልጁን አንገቷን በሰይፍ አስቆረጠው፡፡ ከዚህም በኋላ ልጅህን አስተምሮ ያሳታት የእኅትህ ልጅ የሆነው ጊዮርጊስ ነው" ብለው ለመኰንኑ ነገሩት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስንም ይዞ ጽኑ ሥቃይን ካሠቃየው በኋላ ኅዳር 7 ቀን አንገቱን በሰይፍ ቆረጠውና ሰማዕትነቱን በድል ፈጸመ፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                               ✝ ✝ ✝ 🌹 #አቡነ_ሚናስ_ዘሀገረ_ተመይ፡- ተመይ የምትባለው አገር ኤጲስ ቆጶስ የሆነው የአቡነ ሚናስ ወላጆቹ የመነኮሳትን ሥራ የሚሠሩ ደጋጎች ነበሩ፡፡ የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት እያስተማሩ አሳደጉት፡፡ ሲያድግም ያለፈቃዱ ሚስት አጋቡት፡፡ ወደ ጫጉላ ቤትም በገባ ጊዜ ድንግልናቸውን ይጠብቁ ዘንድ ከሚስቱ ጋር ተማክሮ ሁለቱም በንጽሕናና በድንግልና ሆነው በአንድነት ሊኖሩ ተስማሙ፡፡ ሌሊቱንም ሁሉ ለጸሎት ቆመው ያድሩ ነበር፡፡ እርሱም በዓለም እየኖሩ የምንኩስናን ሥራ ከመሥራት ይልቅ መንኩሶ ገዳም መግባት እንደሚሻል ለሚስቱ ሲነግራት ሸኝታ አሰናበተችው፡፡ አቡነ ሚናስም ወደ አቡነ እንጦንስ ገዳም ገባ ነገር ግን በንጉሡ ትእዛዝ ቤተሰቦቹ ቢያስፈልጉትም ጌታችን ሰውሮታል ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሄደ፡፡ 🌹 በዚያም ሁለቱ ብርሃን ከዋክብት አባ አብርሃምንና አባ ገዐርጊን በማገልገል ልጅ ሆናቸው፡፡ ተጋድሎአቸውንና ትምህርታቸውን በሚገባ ከተማረ በኋላ እርሱም በተጋድሎው አባ አብርሃምና አባ ገዐርጊ እስኪያደንቁትና እስኪገረሙበት ድረስ ከፍ ከፍ አለ፡፡ ከዚህም በኋላ ኤጲስ ቆጶስነት ይሾም ዘንድ ጌታችን መርጦት ለሊቀ ጳጳሳቱ እንዲሾመው ነገረው፡፡ ሊቀ ጳጳሳቱም ጠርተው ሲያስመጡት እምቢ ቢላቸውም የእግዚአብሔር ትእዛዝ መሆኑን ነግረውት ተመይ በሚባል አገር ላይ ሾሙት፡፡ አቡነ ሚናስ ከዚህም በኋላ ሀብተ ፈውስም ተሰጥቶት ብዙ ድውያንን የሚያድናቸው ሆነ፡፡ ሁለተኛም የተሰወረውን የማወቅ ሀብት ተሰጠውና በሰው ልቡና የታሰበውን የሚያውቅ ሆነ፡፡ አቡነ ሚናስ ለአራት ታላላቅ አባቶች አባት ሆኖ እጁን በላያቸው ላይ ጭኖ ሾሟቸዋል፡፡ እነርሱም ለእስክንድርያ አገር ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት አባ እለእስክንድሮስ፣ አባ ቆዝሞስ፣ አባ ቴዎድሮስና አባ ሚካኤል ናቸው፡፡ አባታችን በመጨረሻም ከዚህ ዓለም ድካም የሚያርፍበትን ጊዜ ዐውቆ ካህናቱንና ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ በቀናች ሃይማኖት ጸንተው እንዲኖሩ ከመከሯቸው በኋላ ኅዳር 7 ቀን በሰላም ዐረፉ፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

📌 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ  ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!! ⚪️ የፍኖተ ብርሃን ሰንበት ት/ቤት   ኪነ -ጥበብ ክፍል  ኹለተኛ ዙር  የስነ ስዕል ስልጠና ሊጀምር ስለሆነ  ሥልጠናውን መካፈል የምትፈልጉ ተማሪዎች እስከ (11/3/17)ከታች ባለው   user መመዝገብ ምትችሉ መሆኑን ከወዲሁ እናሳውቃለን። ። ። @samuelgezahegn1 የፍኖተ ብርሃን ሰ/ት ቤት  ኪነ ጥበብ ክፍል