የዘር ሐሳቦች/ Yezer Hasaboch
رفتن به کانال در Telegram
990
مشترکین
اطلاعاتی وجود ندارد24 ساعت
-17 روز
-430 روز
آرشیو پست ها
“ወንድም ዘሪሁን ግርማ (የወንጌላውያን ሚዲያ ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት) ለንባብ ያበቃው መፅሃፍ በሚዲያ ኢንዱስሪው ዘርፍ እጅግ ጠቃሚ መልክተኛ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ለምሳሌ: “ሚዲያ እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” ሙያዊና ታሪካዊ ፋይዳውን ሲዳስስ፦
ይህ መፅሃፍ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚዲያ ጉዞ ላይ የታየውን ሰፊ የታሪክ፣ የስነ-መለኮት እና የህግ እውቀት ክፍተት ለመሙላት በቁርጠኝነት የተነሳ ድንቅና አቅኚ ስራ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ደራሲው ዘሪሁን ግርማ፣ ከ70 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የክርስቲያን ሚዲያ ታሪክ—ከቀዳሚው የብስራተ ወንጌል ሬዲዮ (RVOG) ምሥረታና ስደት ጀምሮ፣ በህትመት ውጤቶች፣ በድምፅና ምስል ካሴቶች፣ በሳተላይት ቴሌቪዥንና በዘመናዊው የማህበራዊ ሚዲያ አብዮት ውስጥ ያለፈበትን ውጣ ውረድ በጥልቀትና በስልት ሰንዶ አቅርቦታል። ስራው በቃል ብቻ ተበታትኖ የነበረውን የታሪክ አሻራ በፅሁፍ መልክ ለትውልድ ማቆየት መቻሉ፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ሃይማኖታዊ ይዘቶች ላይ የሚታየውን የማህበራዊ ሚዲያ ትርምስምስና መፍትሔዎች በግልፅ ማስቀመጡ መፅሃፉን አንዴ ተነቦ የሚቀመጥ ሳይሆን፣ ዘመን የሚመረምርበት እውነተኛ የጥናት መነሻ ያደርገዋል።
በተለይም መፅሃፉ ከታሪክ ዳሰሳ ባለፈ፣ ሚዲያን በስነ-መለኮታዊ መነፅር (Theology of Media) በመመርመር እግዚአብሔርን ቀዳሚው የተግባቦት ጀማሪ አድርጎ ማቅረቡና የወንጌልን አደራ ከቴክኖሎጂ ጋር ማስተሳሰሩ እጅግ የሚደነቅ ጠንካራ ጎኑ ነው። በዲጂታል እቅበተ እምነት (Digital Apologetics) ዙሪያ የቀረቡት የሥነ-ምግባር መመሪያዎች፣ የቅጂ መብት ጥበቃ፣ የስህተት እርምት ባህል እና የምስክርነትና ተአምራት አቀራረብ መመሪያዎች በዘርፉ ላይ ላሉ የሚዲያ ባለሙያዎችና መሪዎች ተቋማዊና ሙያዊ ብስለትን የሚለግሱ ፍንትው ያሉ መብራቶች ናቸው። በአጠቃላይ፣ ይህ መፅሃፍ የቤተ ክርስቲያንን ሚዲያ ከስሜታዊነትና ከግለሰብ ተፅዕኖ አውጥቶ፣ ወደ ተደራጀ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት ወዳለውና በህጋዊ ማዕቀፍ የሚመራ ተቋማዊ ራዕይ ለማሸጋገር የሚረዳ የማይተካ መመሪያ መፅሐፍ ስለሆነ ወንጌል አማኞች ሁሉ ቢያነቡት ይታነፁበታል።"
ደረጀ ታፈሰ / መጋቢ
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን ኅብረት ፕሬዚዳንት
"ይህ “ሚዲያና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን” የሚለው መጽሐፍ ከዚህ በኋላ በዝርዝር ጥናትና ንባብ ለሚሰሩ መሰል ጥናቶች ከፍተኛ ጠቀሚታ እንዳለው ተገንዝቤያለሁ፡፡ በተለይም ይህ ዘመነ ሶሾል ሚዲያ በሌሎቹ ብዙኃነ መገናኛዎች ላይ ተጽእኖ አሳድሮ ነባሮቹን ከማቀጨጩ አስቀድሞ እንደነዚህ ዓይነት ዐይን ከፋች ሥራዎች በኅትመት መልክ ለትውልዱና ለታሪክ እንዲቆዩ ለማድረግ ድርብ ድርብርብ ኃላፊነትን እንደመወጣት ቆጥሬዋለሁ፡፡
ደራሲው ዘሪሁን ግርማ ከሰነዶች፣ ከግለሰብ ምስክሮችና እየኖረበት ካለው “ከራሱ” ዘመን ጋር ታሪክንና ነባር እውነታዎችን እያጣቀሰና እየሸረበ ያቀረበው የጥናት ውጤት ምናልባትም በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚችል ሥራ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት በዚህ ርዕሰ ገዳይ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው የተሰሩ ሥራዎች እስከዛሬ ለንባብ ስለ መብቃታቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ስለሆነም መጽሐፉ አንዴ ተነቦ ሼልፍ ላይ የሚቀመጥ ሳይሆን ተደጋግሞ እየተነበበ ዘመን የሚመረመርበት ስራ ስለሆነ ደራሲውን እንኳን ደስ ያለህ፡ እንኳንም ጻፍክልን እያልኩ አድናቆቴን እለግሰዋለሁ፡፡"
ጌታቸው በለጠ (ደራሲ፣ ጋዜጠኛ፣ የሚዲያ ሰው፣ የቀድሞ የደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት)
የአገልግሎት ጉዞው አርባ አመት ሊሞላው የተቃረበው፣ አገልግሎቱን በወሊሶ መካነየሱስ ቀጥሎም፣ በአዲስ አበባ መካነ የሱስ ያገለገለውና የመጽሐፍ ቅዱስ ሰራዊት ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆነው፣ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራሱን የአገልግሎት በጎ አሻራ ያሳረፈ የእግዚአብሔር ሰው ቶማስ ምትኩ ዛሬ ከእርሱ ከአገልግሎቱና ከህይወቱ የተማርኳቸውን አምስት ነገሮች ማንሳት ወደድኩ። በአገልግሎቱ በስም ቀደም ብዬ ባውቀውም፣ በግል የዛሬ ከአስራ ሁለት አመት ወዲህ አውቀዋለሁ።
ከእርሱ ጋር ያገለገሉ ወይም በቅርበት የሚያውቁት ከዚህ በታች የማነሳውን ሐሳብ ይጋሩኛል ብዬ አምናለሁ። አምስቱን ነገሮች ከዚህ በታች እነሆ፤
መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምርበት መንገድ፦
መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምርበትና እና የሚረዳበት መንገድ እጅግ በጣም ይገርመኛል። ጉባኤ ላይ ከማገልገሉ በፊት ምን ያህል ተዘጋጅቶ እንደሚያገለግል በአገልግሎቱ ያስታውቃል። የዛሬ ሁለት አመት በፊት አምቦ በሃገር አቀፍ የብርሃነ ክርስቶስ የአገልጋዮች ስልጠና ላይ የሐዋሪያት ስራ መጽሐፍን በጥልቀት ተንትኖ ለሶስት ቀናት አስተምሮናል። የቃለ እግዚአብሔር መረዳቱ፣ ዝንጅቱ እና የሚያስተምርበት መንገድ በብዙ የተማርኩበት ነው። ለእግዚአብሔር ቃል ያለው ፍቅርና አክብሮቱ አስተማሪ ነው።
ለትምህርት እና ለስራ ያለው ምልከታ
እኔ በግሌ በጥቂቱ አውቀው የነበረና ከሚያውቁት ደግሞ በብዙ የሰማሁት ሰዎች አገልጋዮች ጭምር እንዲማሩ አልፎም ሰዎች ሰራተኛ እንዲሆኑ የሰራው ስራ ልዩ ምሳሌ ነው። በገንዘቡ ጭምር አገልጋዮችን ከፍሎ አስተምሯል። ስለ ስራ የተለያዩ ስልጠናዎችን ጭምር በማዘጋጀት በርካታ ሰዎች በስራቸው ስኬታማ እንዲሆኑና ሰራተኛ እንዲሆኑ ሰርቷል።
ለቀደሙ አባቶች ያለው ስፍራ
ከእግዚአብሔር ሰው ቶማስ ምትኩ ጋር ባሳለፍኩት ጊዜያት ለበርካታ አባቶች ያለውን አክብሮት በቃልም በተግባርም ሲያሳይ አይቻለሁ። ለበርካታ አባቶች በገንዘብም በሚያስፈልጋቸው አብሮ ሲቆም እንዲሁም ሲያከብራቸውና አይቻለሁ። እኔ ራሴ ብዙ ለቀደሙ አባቶች በገንዘብ ጭምር አይቻለሁ።
የቤተ ክርስቲያን የራሷ መሬት እንዲኖራት ያለው አቋሙ
ቤተ ክርስቲያን በመሬት አቅጣጫ እንድትነቃና የራስዋ ርስት እንዲኖራት በማሰብ ቤተ ክርስቲያናቸው ቀድማ የተለያዩ መሬቶችን እንድትገዛ የሄደበት ርቀት ይገርማል። በርካታ መሬቶችን ገዝቶ የቤተ ክርስቲያኒቱ ርስት እንዲሆን ሰርቷል። ይህም እጅግ ልንማርበት የሚገባ ምሳሌ ነው።
ለጋስነትና አካፋይነት
ማንም ሰው ሲያካፍል ከራሱ እየተቆረሰ ነው። በብዙ በማካፈል ከበርካታ ቤተ ክርስቲያናት አገልጋዮችና ግለሰቦች ጭምር በብዙ መስጠት ይታወቃል። አንድ ቀን አንድ ጥያቄ ጠየኩት "ቤተ ክርስቲያን ከመቀበል ይልቅ መስጠት ላይ እንዴት ማተኮር ትችላለች" ጠየኩት ሲመልስልኝም "እንደ እግዚአብሔር ቃል የሆነውን ጤናማ የሆነ መስጠት ካስተማርን ሰዎችን ባለጠጋ እንዲሆኑ እናደርጋለን።" አለኝና "ለመባረክ መስጠትን መልመድ አለብን።" ብሎኛል። የልገሳ ህይወቱ በርካቶች የተካፈሉት እና ምሳሌ የሚሆን አገልጋይ አካፋይ መሆኑን ማሳያ ነው ብዬ አምናለሁ።
ይህ ጽሑፍ ከአክብሮት እና ከፍቅር የተጻፈ ሲሆን፣ ከላይ የእግዚአብሔር ሰው ቶማስ ምትኩ የተማርኳቸውና እኔም ቢኖሩኝ ብዬ የምመኛቸው ናቸው። የእግዚአብሔር ሰው ቶሚ አንተን ለቤተ ክርስቲያን በረከት አድርጎ ስለ ሰጠኝ እግዚአብሔር ይመስገን፣ ስላገለገልከንም እናመሰግናለን።
ዘሪሁን ግርማ
ሰዎች እንዲሰሙን እንፈልጋለን፣ እኛ ግን ሰዎችን እንሰማለንን?፣ ሰዎች እንዲወዱን እንፈልጋለን፣ እኛስ ሰዎችን እንወዳለን?፣ ሰዎች እንዲያከብሩን እንፈልጋለን፣ ሰዎችን ለማክበር ዝግጁ ነንን? የእኛ ነገር እንዲቀድም እንፈልጋለን፣ እኛስ ሰዎችን እናስቀድማለን?፣ ታናናሾቻችን እንዲታዘዙን እንጠብቃለን፣ እኛ ለታላላቆቻችን ታዛዥ ነን? ያልዘራነው ያጨደ፣ ያልተጋበትን የወረሰ፣ ያላሸነፈውን የገዛ ማነው? ያልዘራነውን የምንጠብቅ ሞኝ እንዳንሆን፣ እኛ እንዲደረግልን የምንፈልግ ለሌሎች እናድርግ።
..
ዘሪሁን ግርማ
#የትኩረት_ናፋቂነት_ሱስ (በሽታ)
The great Comeback የተባለለት የ Chris Rock "Selective Outrage" በተሰኘው ስታንድአፕ ኮመዲ ስራ ላይ ካነሳቸው ከብዙ ሐሳቦች አንደኛው የትኩረት ናፋቂነትን አስመልክቶ ነው። በኮሚዲ ስራው ሲናገር " በአሜሪካ ትልቁ ሱስ ትኩረት የመፈለግ ሱስ (the addiction of attention) ነው" ይለናል። ይህ መልዕክት አሁን ያለውን ትውልድ ቅልብጭ አድርጎ ያሳያል።
ትኩረትን መፈለግ የሰው ልጆች ሁሉ ጤናማ ፍላጎት ነው። ነገር ግን ትኩረህን በመፈለግ ውጥረት ሱስ መያዝ ግን ጤናማ ያልሆነ ነው። ትኩረት ናፋቂነት ከሚዲያ አንጻር ሲታይ ደግሞ ብዙ ትውልድ የተያዘበት ወጥመድ ነው። ሰዎች በአካል ከሚሰጡን ቦታ ይልቅ በማህበራዊ ሚዲያዎች ፎቶአችን ላይ በሚያደርጉት react ላይክና ኮሜንት የበለጠ እስረኛ እያደረገን ይገኛል። በማህበራዊ ሚዲያ የሰዎችን ትኩረት የመፈለግ ከልክ ያለፈ ፍላጎት (ሱስ) ውስጥ ተጠምዷል።
ማህበራዊ ሚዲያዎች ከመጡ በኃላ የሰዎች ህይወት ከሚዲያ በሚያገኘው አድናቆት ፍለጋ ወጥመድ ውስጥ ገብተናል። የትኩረት ናፋቂነት የአድናቆት የኮሜንት እስረኞች ሆነናል። ትኩረት ናፋቂነት ሰዎች በሚዲያ "ዜና" ለመሆን ባልተገባ መንገድ ሚዲያን ሲጠቀሙ እናያለን።
በማህበራዊ ሚዲያ ዓለም "ቫይራል" (Viral) መሆን ማለት አንድ ይዘት (ቪዲዮ፣ ፎቶ፣ ጽሁፍ ወይም ድምፅ) በአጭር ጊዜ ውስጥ በበርካታ ሰዎች ዘንድ በፍጥነት መሰራጨት፣ መታየት እና መጋራት (Share) መደረግ ማለት ነው።
ቃሉ "ቫይረስ" ከሚለው የተወሰደ ሲሆን፣ አንድ ቫይረስ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው በፍጥነት እንደሚዛመተው ሁሉ፣ ይዘቱም ከተጠቃሚ ወደ ተጠቃሚ በከፍተኛ ፍጥነት ስለሚሰራጭ ነው ይህ ስም የተሰጠው።
በሚዲያ በተገቢው በምንሰራቸው መልዕክት ሻይራል መሆን በራሱ ችግር የለውም እንደውም ሁላችንም የምንፈልገው ነው። ለቫይራል እና ለትኩረት ብለህ የስነ ምግባር መርሆዎችን መጣስ እንዲሁም ማንነታችንን የምንለካው በምናገኘው ላይክ ኮሜንት እና ሼር ከሆነ ለትኩረት ናፋቂነት ተጋላጭ መሆናችን አይቀርም።
ሰው የሰሩትን ምግብ ሲወዱለት፣ የወለዱትን ልጅ ሲስሙለት ደስ ይለዋል። ሰዎች የምናጋራቸውን መልዕክቶች ሰዎች አይተው ቢባረኩ ደስተኞች ነው። ነገር ግን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በምናገኘው አድናቆት ወይም አለመደነቅ ህይወታችን አይለካም። ህይወት ያለችው ሚዲያ ላይ አይደለችምና።
ስነ ልቦናችን ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያችን ላይ በብዛት ላይክ ስላደረጉን እንደተወደድን የምናስብ፣ ላይክ ካልተደረገ ተቀባነት እንዳጣን እንዲሰማን የሚያደርግ ወጥመድ ውስጥ እየገባን ነው። ከዚህም የተነሳ ብዙዎች "አጀንዳ" በመፍጠር "ከአየሩ" ላይ ላለመጥፋት ያለ የሌለ ነገር በሚዲያው በመንዛት የሰዎችን አይታ በማብዛት ትኩረትን የመግዛት ሱስ ውስጥ ይዘፈቃሉ። ከልክ ያለፈ ትኩረት ናፋቂነት ሱስ ብቻ ሳይሆን በሽታም ነው።
በዚህ ዘመን ብዙ ወጣቶች በዚህ በሽታ ተጠቂ ናቸው። ራሳቸውን የሚቀበሉት ሰዎች በሚሰጧቸው ኮሜንት ላይ፣ ማንነታቸውን የገነቡት በሰዎች ላይክ ብዛት ላይ ነው። እነዚያን ነገሮች ሲያጡ ለባዶነት ይጋለጣሉ፣ አትኩሮትን ላለማጣት ያልተገቡ ነገሮችን በቀላሉ በማድረግ ወጥመድ ውስጥ ይመላለሳሉ።
ብዙ ወጣቶች ከዚህ በሽታ ራሳቸውን ማስመለጥ አለባቸው።
ዘሪሁን ግርማ
https://t.me/theideaofs
#ነገ_ዛሬ_ለተዘጋጁላት_ናት!!
ህይወት እጅግ ብርቱ ትግል አለው። ህይወት ለሰነፎች አትሆንም። ድል ያለ ትግል፣ ጽናት ያለ ፈተና አይመጣም። ነገ የሚከናወንላቸው ዛሬ በትጋት ለሚሰሩ ነው። እግዚአብሔር ሰዎችን የሚባርክ አምላክ ነው፣ ሰነፎችን ባርኮ ግን አይታወቅም።
ዛሬ ያለን ስፍራ ትናንት የነበረን ዝግጅት ውጤት ነው፣ ነገ ደግሞ ዛሬ በተዘጋጀነው መጠን የምንሆነው ነው። በተሰማራንበት ስፍራ፣ ባለን ማንኛውም እቅዶች ዙሪያ ራሳችን ላይ በሰራነው መጠን ነው ውጤታማ የምንሆነው። የምንባረከው በተዘጋጀንበት መጠን ነው።
" የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው፤ የምላስ መልስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።' መጽሐፈ ምሳሌ 16:1
ቀኖች ከእግዚአብሔር የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው። እኛ ውጤታማ የምንሆንባቸው በተዘጋጀነው መጠን፣ ነገ ላነበቡ፣ ተግተው ለጸለዩ፣ በእጆቻቸው ስራን የሰሩ፣ ትላልቅ ራዕዮችን አልመው ለሰሩ፣ በልባቸው እንዳለው ተግተው ለተዘጋጁ ነው። የእግዚአብሔር በረከት ለተዘጋጁት ነው። ከላይ እንደ ርዕስ የጠቀሰኩት ጥቅስን የተናገረው ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ነው። ነገ ዛሬን ለተዘጋጁላት ናት።
መልካም አዲስ አመት
ዘሪሁን ግርማ
"ማስረዳት ስለቻልክ አትናገርም፣ ቦክስም ስለ ቻልክ አትሰነዝርም፣ ጠቢብ ሰው ጊዜና ሁኔታዎችን አይቶ ለሁኔታዎች ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ ነው።"
የማስበው እንደ ራሴ ነው!!
"አንድ ዓይነት ማሰብ የምንችል ከሆነ፣ አንዳችንም እያሰብን አይደለም ማለት ነው።"
ዎልተር ሊፕማን (Walter Lippmann)
ከሰዎች መማርን የማምን፣ አሁን ያለንኝ ማንነት ከብዙ ሰዎች ተምሬ የገነባኋቸው ናቸው። ስለዚህ ከሚያስተምረኝ ሁሌም እማራለሁ። እንደዚያም ሆኖ፣ የማስበው እንደራሴ ነው፣ ህይወቴን የምገነባውን አምኜ በደረስኩበት በራሴ ልክ ነው።
በዘር ሐሳቦች መጽሐፌ ላይ "እንደ እኔ ካላሰብክ የእኔ ወገን አይደለህም" የሚል መጣጥፍ አለኝ። ያንን ያልኩት ሰዎች ትክክል የሚሉህ እነርሱ ይህ ነው ትክክል ብለው በነገሩህ መሰረት ስታስብ መሆኑን ለማመልከት ነበር። ሰው ማሰብ ያለበት እንደ ራሱ እንደ እንደ ገባው እንደሆነ በብርቱ አሞናለሁ። ህይወቴን መምራት የምፈልገውም እኔ ባመንኩበት ላይ ነው።
ማኅበረሰብ ሁሌም ትክክል ብሎ ያስቀመጠውን መንገድ የሚከተሉ ሰዎች ብዙም ፈተና የለባቸውም፣ ሐሳብም አያስፈልጋቸውም። ይህ ተገቢ የሆኑ በጋራ የሚያስማሙንን የማኅበረሰብ እሴቶችን ይህ አይጨምርም፣ ነገር ግን ሰው እንደ ራሱ እንዲያስብ ነው የተፈጠረው፣ ማሰብ ያለበትም እንደዚያ ነው።
ሐሳብን፣ የሐሳብን ነጻነትንና የሚገድቡ ሰዎች፣ ከእነርሱ የተለየ እሳቤ ካለህ ትክክል አይደለም ብለው የሚፈርጁ ሰዎች፣ የእነርሱ ሚዛን ትክክል ነው ብሎ ማን እንዳጸደቀላቸው ሁሌም አይገባኝም። ሰው በእግዚአብሔር ሲፈጠር እንዲያስብ ተደርጎ የተፈጠረ ፍጥረት ነው። ስለዚህ ሰው ሐሳቢ ነው።
ሰው ከሰዎች ሁሌም ይማራል፣ ሐሳቡ ግን መገንባት ያለበት በራሱ ነው። የሐሳብ ልዩነት ደግሞ በተፈጥሮ የተሰጠን በረከት ነው። ያለን ትልቁ በረከታችን ሰዉ ሁሉ ማሰብ የሚችልበት የራሱ አቅምን መያዙ ነው።
"ልዩነት ውበት ነው። ሁላችንም አንድ ዓይነት ብናስብ ኖሮ ዓለም እንዴት ሰልቺ ትሆን ነበር?"
ማያ አንጀሉ (Maya Angelou)
የሰዎችን ሐሳብ አንድ አይነት የማድረግ አባዜ መጨረሻው ሰዎችን አስገድደን የእኛን ሐሳብ እንዲያስቡ ማስገደድ ነው። ይህ ደግሞ ዘመናዊ ባርነት ነው። የተፈጠርነው እንደ ራሳችን እንድናስብ ነው።
ዘሪሁን ግርማ
ብዙዎቹ የትናንት ድክመትህን የሚያወሩት ዛሬ ያለህበት ስኬት ስለሚያስቀናቸውና፣ በዛሬው ማንነትህ ላይ ምን የሚሉት ነገር ስለሌላቸው ነው። ወደ ፊት ቀጥል!!
"የግማሽ እውነት ልክፍተኞች ነን" ታገል ሰይፉ
ሁላችንም ለዚህ ችግር ተጋላጭ ነን። ለምሳሌ ይህም ሐሳብ ለማስረዳት ያህል እኛ በሆነ ምክንያት "ክፉ" ነው የምንለውን ሰው "መልካም" ጎኑ ሲነገረን አንቀበልም፣ ወይም ክፉነቱ ብቻ እንዲነገር እንፈልጋለን። ሙሉ ለሙሉ ክፉ ሙሉ ለሙሉ መልካም ሰው አይኖርም። ሰው በሆነ መልኩ ክፉ ሊያደርግ ወይም ሊሳሳት ይችላል፣ ያ ማለት ያ ሰው የተሳሳተው ብቻ ሳይሆን በሌላ መልኩ ደግሞ መልካም ጎን ይኖረዋል። ዘሪቱ ከበደ "ስህተቴ እኔ አይደለሁ...ስህተቴ ጋር እዚያ አልቀረውም" የሚል ዘፈን አላት። ሰው ተሳስቶ ከስህተቱ ሊታረም ይችላል። ሰው የሚሳሳት እንጂ ሙሉ ለሙሉ ስህተት አይደለም።
አዕምሮአችን አንድ ጊዜ 'እንዲህ ነው' ብሎ የተቀበለውን ነገር ለመቀየር ይቸገራል። ማለትም የዚያን ነገር ሌላኛውን ጎን ማየትም አይፈልግም። ለእኛ በሆነ ምክንያት መጥፎ የነበሩ ሰዎች፣ ለሌሎች መልካም ሆነው ሊገኙ ይችላሉ። እነዚያ ሰዎች መጥፎ ጎን ብቻ ሳይሆን መልካም ጎን እንዳላቸው መቀበል ይኖርብናል። ሁላችንም ደግሞ ይህ አይነት ማንነት አለን። ለሁሉም ሰው መልካም ሆነን ላንገኝ እንችላለን። ሰው ስለሆንን!!
ሌላው ግማሽ እውነት ማለት የአንድን ታሪክ ሙሉ ጭብጥ ወይም ሙሉ ታሪክ ያለማወቅ ነው። አንዳንድ እውነቶች ሙሉ እውነቶች አይደሉም። የሆነ እውነት የሆነ ጎን ይኖራቸዋል ነገር ሙሉውን ታሪክ ካላገኘነው ግማሽ እውነት ይሆናል። ብዙዎቻችን በግማሽ እውነት ሙሉውን ታሪክ ባለማወቅ ስንሳሳት እንገኛለን። ሙሉውን እውነት ካላገኘን በግማሽ እውነት እንስታለን።
ስለ አንዳንድ ሰዎች የሚኖረን ግማሽ እውነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ማንኛውም ጥላቻ፣ ሙሉ ማንነታቸውን ስንረዳ እንደተሳሳትን ሊገባን ይችላል። ሰው በማንነቱ አንድ ብቻ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ ሙሉውን እውነት ለማግኘት እንሞክር። ከላይ ርዕስ ያደረኩት የታገል ሰይፉ አባባል ነው ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ።
ዘሪሁን ግርማ
