cookie

We use cookies to improve your browsing experience. By clicking «Accept all», you agree to the use of cookies.

avatar

የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች

"ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን" 2ኛ ቆሮ. 2:14 YouTube https://www.youtube.com/@Min22111 Telegram Group https://t.me/D_n_henok_hiyla

Show more
Advertising posts
6 120
Subscribers
+1224 hours
+1127 days
+29430 days

Data loading in progress...

Subscriber growth rate

Data loading in progress...

‘ለእግዚአብሔር የሚሳነው የለምና’ ብሎ ሲነግራትም ሌላ ጥያቄ እንኳን ልትጨምር አልወደደችም፡፡ የእምነት ኃያልነት የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ሰምቶ ጥያቄ የሚያስጠይቅ አልነበረምና ለከሃሊነቱ ተረታች፡፡ የናዝሬት ገሊላዋ ድንግል ማርያም የሚሳነው ነገር ለሌለው አምላክ ተማርካ እጅዋን ብቻ ሳይሆን ራስዋን ሠጠች፡፡ ‘እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ’ የሚሉ ከአልማዝ የከበሩ ቃላትን ክፉ ከማይናገሩ ፣ ማንንም ሰው በንግግር አስቀይመው ከማያውቁ ንጹሐን ከንፈሮችዋ አፈሰሰች፡፡ ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ የብርሃን እናት ገጽ 208 ለሐምሌ ሥላሴ ዝክር የተለጠፈ https://t.me/hinokhayla https://t.me/hinokhayla
Show all...
የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች

"ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን" 2ኛ ቆሮ. 2:14 YouTube

https://www.youtube.com/@Min22111

Telegram Group

https://t.me/D_n_henok_hiyla

10
‘ወልድ ከአብ ተወለደ ፣ መንፈስ ቅዱስ ከአብ ወጣ’ የሚለውን ትምህርት ያለ መቀዳደም እንዴት ልንረዳው እንችላለን? ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ የተገኙ ናቸው፡፡ በመውለድና በማስረፅ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ወልድ ሠረፀ ፣ መንፈስ ቅዱስ ተወለደ ለምን አልተባለም? ወልድ ከአብ መወለዱ እንዴት ነው? ከተወለደ በኋላስ ከአብ ጋር አንድ መሆኑ እንዴት ነው? የሚሉ ብዙ ጥያቄዎች ይከተላሉ፡፡ የአብን ልብነት ፣ የወልድን ቃልነትና የመንፈስ ቅዱስን እስትንፋስነት መረዳት ግን እነዚህን ጥያቄዎች ይመልሳል፡፡ እግዚአብሔር አብ ወልድን ላከ ሲባል ነቢዩ ‘ቃሉን ላከ ፤ ፈወሳቸውም’ እንዳለ ሰው በቃሉ ቢጣራ ቃሉ የእርሱ የበታች እንደማይባል ወልድም ከአብ የተገኘ ከአብ የማያንስ የሚሠራ ቃል ነው ማለት ነው፡፡ መዝ. ፻፯፥፳ ጌታችን ‘እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና’ ሲል በልቡ በአብ ፈቃድ እንጂ በራሱ ፈቃድ ብቻ እንዳልመጣ ተናግሮአል፡፡ ‘የላከኝም ከእኔ ጋር ነው ፤ ብቻዬን አይተወኝም’ በማለት ደግሞ ከአብ ቢላክም አብ ከእርሱ ጋር በህልውና እንዳልተለየ ያሳያል፡፡ ዮሐ. ፰፥፵፪ ፣ ፱፥፳፱ ‘ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም’ እንደሚል ወልድም ከአባቱ ሳያንስ የልቡን የአብን ፈቃድ የሚፈፅም ‘እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ’ የሚል የአብ ቃሉ ነው፡፡ ኢሳ. ፶፭፥፲፩ ፤ ዮሐ. ፲፯፥፬መዝ. ፷፩፥፬ ሰው በልቡ ከሚያስበው ውጪ በቃሉ ሊናገር እንደማይችል ሁሉ ቃል ወልድም በልቡ አብ ካሰበው በቀር ምንም አያደርግም፡፡ [እዚህ ላይ ነቢዩ ዳዊት ‘በአፋቸው ይባርካሉ ፤ በልባቸው ይረግማሉ’ እንዳለ በአፉ ሌላ ነገር እየተናገረ በልቡ ሌላ የሚያስብ ሰው ነፍሱን ባልተቀደሰ ሦስትነት (unholy trinity) እያስጨነቃት ነውና ልቡ ያሰበውን ብቻ በታማኝነት እስካልተናገረ ድረስ ልብና ቃል ያልተስማሙባት ነፍሱ ለቅድስት ሥላሴ አንድነትና ሦስት ምሳሌ አትሆንም፡፡] እነዚህ ጥቅሶች ይህንን ያሳያሉ፦ ‘እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና። አብ ወልድን ይወድዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል’ ዮሐ. ፭፥፲፱-፴ የዚህ ቃል ትርጓሜ በልቤ በአብ ካሰብሁት በቀር በቃልነቴ ብቻ አንዳች አላደርግም፡፡ ወልድ ከአብ ጋር በህልውና አንድ ነውና አብ ወልድ የማያውቀው አንዳች ነገር አያደርግም ፤ ወልድ በህልውና ከአብ ጋር አንድ ሆኖ ያየውን ያደርጋል እንጂ ማለት ነው፡፡ ‘እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ’ ሲልም ከልቤ ከአብ ካሰብሁት በቀር ፣ በህልውና አንድ ሆኜ ከሰማሁት በቀር ከአብ የተለየ ፍርድ የለኝም ማለት ሲሆን ‘ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም’ ማለት ደግሞ የወልድና መንፈስ ቅዱስ ልባቸው አብ ታይቶ በማንም ላይ ፍርድ አይሰጥም ፤ በእርሱ ልብነት እያሰበ ታይቶ መፍረድን ለቃሉ ለወልድ ሠጠው እንጂ ማለት ነው፡፡ ዮሐ. ፭፥፲፱-፴ ልባችን ድምፅ ባያወጣም ያለማቋረጥ እያሰበ ቃልን በውስጡ ያመላልሳል ፤ በቃል ስንናገርም ድምፅ አውጥተን እያሰብን (thinking outloud) ነው፡፡ በቃል የምንናገረው ነገር ከልባችን ስለተገኘ በህልውና አንዱ ከሌላው እንደማይቀዳደም እንዲሁ በአብና በወልድ ዘንድ መቀዳደም የለም፡፡ ‘ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ ናቸው እንጂ ከአብ በኋላ አይደሉም ፤ ፀሐይ ከብርሃንዋና ከሙቀትዋ እንደማትቀድም እንዲሁ አብ ከመንፈስ ቅዱስና ከወልድ አይቀድምም’ (St. Gregory of Nazianzus, The Five Theological Orations, On the Son 1:3 178) አሳብ ከልብ ያለማቋረጥ እንደሚፈልቅ ፣ የወልድ ከአብ መወለድም እንደ ሥጋዊ ልደት አንድ ጊዜ ሆኖ በመለያየት የሚያበቃ ሳይሆን መለያየት የሌለበት የማይፈጸም ልደት ነው፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ስለዚህ ጉዳይ ‘ኢይትፈለጥ እምኔሁ ወኢየኃልቅ ልደቱ እምኔሁ’ ‘ከእርሱ አይለይም ፤ ከአብ የተወለደው ልደቱ አይፈጸምም’ ሲል እንዳብራራው ‘ልደቱ ተመትሮ የለውም’ ፡፡ (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ፤ ሃይማኖተ አበው ንባቡና ትርጓሜው ፤ ፲፫፥፲፰ ፣፳፬) ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ መገኘታቸውን ለመግለፅ በቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ወልድን ‘ከአብ ተወለደ’ ፤ መንፈስ ቅዱስን ከአብ ሠረፀ (ወጣ) እንላለን፡፡ በመወለድና በመስረፅ መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት ለሚሻ ሰው አሁንም ቀላሉ መንገድ ወደ ራሳችን ነፍስ መመለስ ሲሆን በመውለድና በማስረፅ መካከል ያለው ልዩነት በመናገርና በመተንፈስ መካከል ያለው ልዩነት ነው፡፡ አንድ ሰው ተናገረ ማለት ተነፈሰ ማለት አይደለም ፤ ተነፈሰ ማለትም ተናገረ ማለት አይደለም፡፡ እየተነፈሰ ይናገራል ፤ እየተናገረ ይተነፍሳል፡፡ እግዚአብሔርም በቃሉ ይናገራል በእስትንፋሱ መንፈስ ቅዱስ ህያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ የተገኙ ቢሆኑም መንፈስ ቅዱስን እንደ ወልድ ‘ከአብ ተወለደ’ አንልም፡፡ ቃላት የሚያመጡትን የዶግማ ተፋልሶ የሚገነዘቡት ጓደኛሞቹ ባስልዮስና ጎርጎርዮስ እንዳሉት መንፈስ ቅዱስን ተወለደ ብንል ኖሮ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለው ግንኙነት ‘ወንድማማችነት’ ይሆንና የህልውና አንድነትን የሚያዛባ ይሆን ነበር፡፡ ከአብ የሠረፀው መንፈስ ቅዱስን ከወልድም ሠርፆአል ብለው የሚያስተምሩ ሰዎችም መንፈስ ቅዱስን የአብ የልጅ ልጅ እያደረጉት ነው፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ እንዲህ ይላል ፦ ‘መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳት መጻሕፍት ከአብ የተወለደ ተብሎ አልተጠራም፡፡ ይህም ለእግዚአብሔር ወልድ ወንድም ስለሚያሰኘው ነው፡ ፡ መንፈስ ቅዱስን ከወልድ የተገኘም አንለውም፡፡ ይህን ብንልም እግዚአብሔር አብን አያት ማሰኘት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ወልድን የአብ ልጅ ስንል መንፈስ ቅዱስን ከአብ የሚወጣ መንፈስ እንለዋለን’ ከልባችን ሃሳብ እንዴት እንደሚወለድና ወደ ቃልነት እንደሚለወጥ ማብራራት አንችልም፡፡ የወልድን ከአብ መወለድና የመንፈስ ቅዱስን መሥረፅም እንዲህ ነው ብለን በቀላሉ መግለፅ አንችልም፡፡ በሕሊናችን ያለው የተከማቸ የሃሳብ እውቀትና ትውስታ በዚህች ቅፅበት በውስጣችን ወደሚመላለስ ቃልነት አለዚያም ወደ ድምፅ ተለውጦ በሌሎች ወደሚሰማ ንግግር የሚለወጥበት ሒደት እንዴት ያለ ነው? ‘መመርመር ከተቻለን የሥጋዊውን ነገር ምሥጢር እስቲ እንመርምር? ይህም ሃሳብ ከልብ የሚወለደው እንዴት ነው? የሚለውን ነው፡፡ የፍጡራንን አፈጣጠር እናውቅ ዘንድ ከተቻለንስ ከአንደበት የቃል መወለድ ምን እንደሚመስል እስቲ እንመርምር፡፡ በእኛው ውስጥ ያሉ እነዚህን ነገሮች መርምሮ ማወቅ ካልተቻለን ሕሊናት ሁሉ የማይመረምሩት ፍጡር ያይደለ የፈጣሪን ምሥጢር እንዴት ልናውቅ ይቻለናል?’ ይላል ቅዱስ ጎርጎርዮስ ‘ወዳእሙ እመሰ ክህልነ ንኅሥሥ ከመ ናእምር ምሥጢሮ ለሥጋዊ ዘውእቱ ልደተ ሕሊና እምልብ እፎ ውእቱ አው ንክህል ናእምር ፍጥረተ ፍጡራን፡፡ ወልደተ ቃል እምልሳን ምንተ ይመስል፡ ለእመ ኢይትከሃለነ ናእምር እሎንተ እለ ሀለዉ ውስቴትነ እፎኑመ ነአምር ምሥጢሮ ለፈጣሪ ለዘኢተፈጥረ ዘይትሌዓል ኵሎ ሕሊናተ’ ሃይማኖተ አበው ንባቡና ትርጓሜው ፤ ዘጎርጎርዮስ ፲፫፥፲፮
Show all...
ቅዱስ ገብርኤል ለድንግሊቱ ‘መንፈስ ቅዱስ ይጸልልሻል ፤ የልዑል ኃይልም ያድርብሻል ፤ ከአንቺ የሚወለደው የልዑል ልጅ ይባላል’ አላት፡፡ መልአኩ ለድንግሊቱ እግዚአብሔር አብን ‘ልዑል’ ፣ እግዚአብሔር ወልድን የልዑል ኃይል ፣ የልዑል ልጅ ፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን መንፈስ ቅዱስ ብሎ በመጥራት ያለ ወንድ ዘር የምትፀንሰው በሥላሴ ሥራ መሆኑን ነገራት፡፡ የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ብዙዎች የሚያምኑት ነገር ግን ገና ሲነሣ ይከብዳል ብለው የሚሸሹት ርእሰ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ምሥራቃዊ ጸሐፊ ‘የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ለሰብአዊው አስተሳሰብ [ለመሸከም የሚከብድ] መስቀል ነው’ ብሎ እንደገለጠው ነገረ ሥላሴ ለብዙዎች ለማሰብ ራሱ የሚከብድ የሕሊና መስቀል ሆኖ ይታያል፡: ( Vladimir Lossky, The Orthodox Way, Bishop Kallistos Ware, SVS, 1999) ምሥጢረ ሥላሴን አስፍቶ አምልቶ በማስተማር ወደር ያልተገኘለትና በዚህም ምክንያት በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በተጠራበት ስም ነባቤ መለኮት ብላ የሰየመችው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙም ምሥጢረ ሥላሴን የመሰሉ ጥልቅ የነገረ መለኮት ትምህርቶች ላይ መራቀቅ ለሁሉ እንደማይቀልል ሲያስረዳ ፦ ‘ወዳጆቼ ነገረ መለኮትን ማራቀቅ ለሁሉም ሰው የሚሆን ነገር አይደለም ፤ (Philosophising God is not for everyone) ርእሰ ጉዳዩ በቀላሉ የምታገኘው ወይም ለምድራዊ አስተሳሰብ የሚሆን አይደለም ፤ ለሁሉም አድማጭ ፤ ለሁሉም ጊዜ ፤ ለሁሉም ጉዳይ የሚሆንም አይደለም፡፡ በሆኑ ቦታዎች ከሆኑ ሰዎች ጋር በገደብ የሚነሣ ርእስ ነው’ (St. Gregory of Nazianzus, The Five Theological Orations, 27.3) ቅዱስ ጎርጎርዮስ ይህን ይበል እንጂ የረቀቀ ነገር ለመረዳት የሚቸገሩ ምእመናንንም የተወሳሰበውን ቋንቋ ለሊቃውንቱ ተወት አድርገው በእውቀታቸው ውስንነት ልክ ምሥጢረ ሥላሴን ሊረዱ እንደሚገባ ካስተማረ በኋላ ሊቃውንቱም ምእመናኑም የሚድኑት አንዱን እምነት በማመናቸው እንጂ በእውቀታቸውና በመራቀቃቸው ልክ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡ (St. Gregory of Nazianzus, Oration on the Moderation in debate, 32.21. 24-25 216) የእግዚአብሔር አንድነት እንጂ የእግዚአብሔር ሦስትነት በብሉይ ኪዳን የተሠወረ ትምህርተ መለኮት ነበረ፡፡ ይህ ማለት እግዚአብሔር ‘ቀስ በቀስ ሦስት ሆነ’ የሚል የትምህርተ መለኮት እመርታ (dogmatic progression) ሳይሆን ለሰው ልጆች ቀስ በቀስ የተገለጠ በቅድምና የነበረ እውነታ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህን ትምህርት ለእስራኤል ከመነገር የሰወረው የሦስትነቱ ነገር ለመረዳት የሚችሉት መንፈሳዊ ጫንቃ ስላልነበራቸውና ሦስት አማልክት አድርገው ወደ መረዳት ስሕተት እንዳይገቡ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሦስትነቱን በግልጥ አይናገር እንጂ በብሉይ ኪዳንም አብን አባት ፣ ወልድን ጥበብ ፣ መንፈስ ቅዱስን የእግዚአብሔር መንፈስ እያሉ የሚጠሩ እጅግ ብዙ ቃላት በብሉያት መጻሕፍት ይገኛሉ፡፡ ሥላሴን በፀሐይ መስለው ካስተማሩ ሊቃውንት አንዱ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙም ‘ወደ ፀሐይ ለመመልከት ዓይናችንን ቀስ በቀስ እንገልጣለን እንጂ በአንድ ጊዜ የገለጥን እንደሆነ ዓይናችን ይጎዳል ፤ እግዚአብሔርም ሦስትነቱን በአንድ ጊዜ ለሰው ልጅ ቢገልጥ ኖሮ የሰው ልጅ ዓይነ ልቡና ይጎዳ ነበር’ (St. Gregory Nazianzen, Oration XXXI (Theological Orations) 26, pg 36:161, NPNF, 2nd ser., Vol. 7, p.326) እንዳለ ምሥጢረ ሥላሴ ቀስ በቀስ ፍንትው ያለ አምላካዊ ምሥጢር ነው፡፡ ፀሐይን በራስዋ ብርሃንነት ካልሆነ በቀር ልናያት እንደማንችልም እግዚአብሔርንም በእርሱ ምሥጢር ገላጭነት ካልሆነ በቀር ልንረዳው አንችልም፡፡ ‘በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን’ እንዳለ ነቢዩ፡፡ መዝ. ፴፮፥፱ ወዳጄ ምሥጢረ ሥላሴን ለመረዳት ትፈልግ እንደሆንህ ብዙ መጻሕፍትን ማገላበጥና መመራመርህን ቆም አድርገህ አንድ መጽሐፍ እንድትገልጥ ልጠቁምህ፡፡ መጽሐፉ እስከዛሬ ያላነበብኸው ነገር ግን አብሮህ የኖረ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህች ምሥጢረ ሥላሴ የተጻፈባት መጽሐፍ የገዛ ነፍስህ ናት፡፡ የሰው ነፍስ ከሌሎች ሁሉ የተሻለች የምሥጢረ ሥላሴ ምሳሌ ናት፡፡ እግዚአብሔር ‘ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር’ ብሎ ሲፈጥረው ‘ምሳሌያችን’ ተብላ የተጠራችው ነፍስ ነበረች፡፡ አንድ ሰው ነፍስ ስላለው ሦስት ነገሮች ያከናውናል ፤ በልቡ ያስባል ፣ በቃሉ ይናገራል ፣ በእስትንፋሱ ይኖራል፡፡ ልብህ ካሰበው ነገር በቀር በቃልህ ምንም ልትናገር አትችልም፡፡ ቃልህና ልብህም ያለ እስትንፋስህ ሕይወት የላቸውም፡፡ ሦስት ነገሮች ቢኖሩህም አንድ ሰው ነህ እንጂ ሦስት ሰው አትባልም፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድም ሦስት ኩነታት አሉ፡፡ ‘እግዚአብሔር አብ በራሱ መሠረትነት ለራሱ ለባዊ ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ እውቀት ይሆናል ፤ እግዚአብሔር ወልድም በአብ መሠረትነት ለራሱ ቃል ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ይሆናል፤ መንፈስ ቅዱስም በአብ መሠረትነት ለራሱ ሕያው ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወት ይሆናል’ (መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ፤ ኰኵሐ ሃይማኖት ገጽ ፻፵፩) የእግዚአብሔርን ልብ አብ እንለዋለን የእግዚአብሔርን ቃል ወልድ እንለዋለን ፤ የእግዚአብሔርን እስትንፋስ መንፈስ ቅዱስ እንለዋለን፡፡ በእርሱ ዘንድ ሦስት ሁኔታዎች (ኵነታት) ቢኖሩም ሦስት አምላክ አይደለም በህልውና አንድ ናቸውና አንድ አምላክ እንላለን እንጂ፡፡ ‘በአብ ለባውያን በወልድ ነባብያን በመንፈስ ቅዱስ ሕያዋን ይባላሉ’ እንጂ መለያየት በእነርሱ ዘንድ የለባቸውም፡፡ ስለ እግዚአብሔር አብ ልብነትና ስለ ወልድ ቃልነትና ስለ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ብሏል፡፡ ‘ጎሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ’ ‘ልቤ [አብ] በጎ ቃል [ወልድን] አወጣ’ ‘የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች ፤ በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ ፤ ሠራዊቶቻቸውም በአፉ እስትንፋስ’ ‘የውዴ ቃል በተራሮች ላይ ሲወረወር ይመጣል’ ‘ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ’ ‘ቃልም ሥጋ ሆነ’ ‘በደም የተረጨ ልብስ ተጎናጽፎአል ፤ ስሙም የእግዚአብሐር ቃል ተብሏል’ የሚሉት ቃላት ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡ መዝ. ፵፬፥፩ ፤ ፴፪፥፭ ፤ መኃ. ፪፥፰ ፤ ዮሐ. ፩፥ ፩፣፲፬ ፤ ራእ. ፲፱፥፲፫ ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት እንዳለ ሆኖ የአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ነገር ብዙ ጥያቄዎችን ይወልዳል፡፡ በስም አጠራራችን አብን ማስቀደማችን አብ ይቀድማል ለማለት ባይሆንም በብዙ ሰው ሕሊና ግን እግዚአብሔር አብ ለወልድና መንፈስ ቅዱስ መገኛ መሆኑን ከመቀዳደምና ከመዓርግ ብልጫ ለይቶ ለማሰብ እንዲቸገር ምክንያት ሆኖአል፡፡ አብ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን ላከ ሲባልም የላኪና የተላኪ ተዋረድ አድርጎ የሚያስብም ሰው ብዙ ነው፡፡ ይህን ተከትሎም ብዙ ጥያቄ ይመጣል፡፡
Show all...
ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ከአብ መወለድ እና የመንፈስ ቅዱስም ከአብ መውጣት የሚደነቅ እንጂ ሊነገር የማይችል ረቂቅ ምሥጢር ነው፡: ቅዱስ ዲዮናስዮስም ‘ልደተ ወልድ ወጸአተ መንፈስ ቅዱስ እምአብ ይትነከር ወኢይትነገር’ ‘የወልድ ከአብ መወለድ የመንፈስ ቅዱስ መውጣት ይደነቃል እንጂ አይነገርም’ ብሏል፡፡ሃይማኖተ አበው ንባቡና ትርጓሜው ዘዲዮናስዮስ ፲፥፲፪ ቅዱስ ገብርኤል ግን ለድንግሊቱ በተናገረው የብሥራት ቃል ላይ ከብሉይ ኪዳን ሰዎች ተሠውሮ የነበረውን ምሥጢረ ሥላሴ ለድንግሊቱ በመንገርና በእርስዋ ላይ እንደሚገለጥ በማብሠር ትምህርተ ሥላሴን አስጀመረ፡፡ መዝገበ ምሥጢር ማርያምም መልአኩ የነገራት የእግዚአብሔር ልጅ ነገር እንደ አይሁድ መምህራን እንግዳ አልሆነባትም፡፡ በጥያቄዋም ስለ ድንግልናዋ ጠየቀች እንጂ ልዑል አብ ልጁ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ብሎ የተናገረው ነገር አዲስ አልሆነባትም፡፡ ምሥጢረ ሥላሴ ከዚያ በኋላ በዮርዳኖስ ወንዝ ፣ በታቦር ተራራ በተከሰቱት ተአምራት ግልጥ ሆኖአል፡፡ አባ ጽጌ ድንግል እንዳለ ፡- ‘በላዕሌኪ ወበዮርዳኖስ ወበታቦር ሥልሰ ጊዜያተ፡ ዘአልቦ ተውሳከ ወአልቦ ሕጸተ፡ ለውሉደ ሰብእ ያርኢ ዘሥላሴሁ ገጻተ ጽጌኪ ድንግል ተአምሪሁ ከሠተ፡ ወበጸዳሉ አብርሓ ጽልመተ’ ‘ጭማሬም ጕድለትም በሌለበት ሥራ ምሥጢረ ሥላሴን በዓለም ሊያብራራ ማርያም ሆይ ልጅሽ በክብር የሚጠራ በአንቺ ፣ በዮርዳኖስ ፣ በታቦር ተራራ ሦስትነቱን ገልጦ ተአምራትን ሠራ በብርሃኑም ኃይልም ጨለማን አበራ’ ( አባ ጽጌ ድንግል ፤ ማሕሌተ ጽጌ ፤ ማኅበረ ቅዱሳን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ገጽ ፸፬ ፤ አማርኛው መምህር ኤፍሬም የኔሰው ውብ አድርገው እንደተረጎሙት) በድንግሊቱ ማሕፀን የሆነው ይህ ነው ፤ እግዚአብሔር አብ ድንግሊቱን መለኮትን ለመቀበል እንድትችል አድርጎ አጸናት ፤ ወልድ በማሕፀንዋ አደረ ፤ መንፈስ ቅዱስ ፅንሱን አከናወነ፡፡ ከእርስዋ ሰው የሆነው ሰውን እንፍጠር ብሎ የፈጠረው ቃል ራሱ ነበር፡፡ ቀሌምንጦስ ‘የፈጠረው ቃሉ ነውና በቃሉ ሊያድነው ይገባል’ እንዳለው ነው፡፡ በቃሉ የፈረደበትም እርሱ ነውና እርሱ ሊያድነው ወደደ፡፡ ነቢዩ ሆሴዕ ‘እርሱ ሰብሮናልና እርሱ ይፈውሰናል ፤ እርሱ መትቶናልና እርሱ ይጠግነናል ፤ ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፥ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን’ ብሎ ሰው መሆኑን እስከ ሞቱና ትንሣኤያችንን ስላወጀው ትንሣኤው ሳይቀር እንደተናገረ ሰውን በቃሉ ሊያድን ወረደ፡፡ ከድንግል ማርያም የተወለደው ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ በተለየ አካሉ ነው፡፡ ስለዚህ በሥላሴ ሥራ አንዱን ወልድ ወለደች እንላለን፡፡ ከእርስዋ አብ ወይም መንፈስ ቅዱስ ለምን አልተወለዱም? ለምን ወልድ ሰው ሆነ? የሚለው ጥያቄ ሌላው የሊቃውንትን ትኩረት የሳበ ነው፡፡ መጽሐፈ ሥነ ፍጥረት እንዲህ ይላል ፦ ‘አብና መንፈስ ቅዱስ ሰው ቢሆኑ ኖሮ የባሕርይ ስም የባሕርይ ግብር በተፋለሰ ነበር፡፡ ምክንያቱም የወለደው አብ የተወለደ ፣ የተወለደው ወልድ የወለደ ፣ የሚሠርፀው መንፈስ ቅዱስም የተወለደ በተባለ ነበር፡፡ እንዲህ እንዳይሆን ግን እግዚአብሔር ወልድ በባሕርይ ስሙ ፤ በባሕርይ ክብሩ ለመጠራት በሦስቱ ፈቃድና ሥምረት ሰው ሆኖ ተወለደ’ (መጽሐፈ ሥነ ፍጥረት ፤ ሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ ፤ ኮከበ ጽባሕ ማተሚያ ቤት ፤ አሥመራ ፤ ፲፱፻፷፰ ዓ.ም. ገጽ. ፻፳፪) ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያም ስለዚሁ ጉዳይ በድርሳኑ ላይ አብራርቶአል፦ ‘ማንም ሰው የአብና የመንፈስ ቅዱስ ስም የወልድ ስም ወደ መሆን ይፋለሳል እንዳይል አብ ሰው ለመሆን በድንግል ማሕፀን ውስጥ ያደረ አይደለም፡፡ ለሦስቱ ቅዱስ ፈቃዳቸው አንድ ነውና ወልድ በአባቱና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሰው ሆነ እንጂ’ ‘ወአኮ አብ ዘኀደረ ውስተ ከርሠ ድንግል ለተሰብኦ ከመኢይበል መኑሂ ይትፋለስ ስመ አብ ወመንፈስ ቅዱስ ለከዊነ ስመ ወልድ አላ ውእቱ ወልድ በፈቃደ አቡሁ ወበሥምረተ መንፈስ ቅዱስ ተሠገወ እስመ አሐቲ ፈቃድ ለሥሉስ ቅዱስ’ (ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ ፤ ሃይማኖተ አበው ንባቡና ትርጓሜው ፤፹፬፥፲፩) እግዚአብሔር አብ ሁልጊዜም አብ ፤ እግዚአብሔር ወልድም ሁልጊዜም ወልድ እንደተባለ ይኖር ዘንድ በሥጋዌውም ከድንግል መወለድ የወልድ ሆነ፡፡ ይህም በአካላት ሦስት በሆኑት በአብ ፣ በወልድ ፤ በመንፈስ ቅዱስ ዘንድ የስምና የግብር ተፋልሶ እንዳይኖር አደረገ፡፡ (‘The Word was incarnated in order that the Hypostatic Attributes of the Three Persons of the Holy Trinity would remain unmovable. It was not intended for the Father to become the Son of the Man, rather than the Word Who has the attribute of being ‘The Son’ in the Trinity ’ Orthodox Teachings, By His Eminence Panteleimon Lampadarios, Port Said 2006, pg 231) ቅዱስ ገብርኤል ለሐዲስ ኪዳንዋ የአብርሃም ድንኳን ለድንግል ማርያም ተገልጦ ‘እንዴት ይሆናል?’ ለሚል ጥያቄዋ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በአንቺ ላይ ይሠራል አላት፡፡ የአብርሃም ታሪክ በዘመን ከእርስዋ የራቀ ታሪክ ነው፡፡ ሆኖም ለድንግል ማርያም እንደ አብርሃምና ሣራ በእርጅናቸው ልጅ ሊወልዱ የተቃረቡትን የኤልሳቤጥና ዘካርያስን ነገር ነገራት፡፡ በቀደመችው የአብርሃም ድንኳን በእርጅና የመውለድ ዜና ተነግሮ ‘በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው አለን?’ በሚል ቃል እንደተጠናቀቀ በዚህችኛዋም የሐዲስ ኪዳን ድንኳን ፊት በእርጅና የመውለድ ዜና ተነብቦ ‘ለእግዚአብሔር የሚሳነው የለም’ በሚል ቃል ተፈጸመ፡፡ ልብ በሉ ፤ በአብርሃም ድንኳን የተነገረው ቃል ‘በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው አለን?’ የሚል ሣራን ለምን ሳቅሽ የሚል ወቀሳ ያዘለ ንግግር ነበር፡፡ ለድንግል ማርያም ግን የተነገረው ጥያቄ ሳይሆን ‘ለእግዚአብሔር የሚሳነው የለምና’ የሚል አስረጂ ቃል ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ሣራ በእርጅና ከባልሽ ትወልጃለሽ ስትባል እንደሳቀችው ድንግል ማርያም ያለ ወንድ ዘር ትወልጃለሽ ስትባል ስላልሳቀች ነው፡፡ ሣራ በተፈጥሮአዊ መንገድ ትፀንሻለሽ መባልዋ ሳቅዋን መቆጣጠር እንዳትችል አደረጋት፡፡ እንግዳ ሲናገር በእንግዳው መሳቅ ከአረጋዊያን የማይጠበቅ ቢሆንም ሣራ ግን የሰማችው ነገር በስተርጅና አሳቃትና በኋላም ‘ኸረ አልሳቅሁም’ ብላ ለመካድ እስከምትሞክርና ከጌታ ጋር ‘ስቀሻል አልሳቅሁም’ የሚል ክርክር እስክትገጥም ድረስ አሳፈራት፡፡ ዘፍ. ፲፰፥፲፭ የልጅ አዋቂዋ ድንግል ማርያም በመልአኩ የተነገራት ጨርሶ ሊታመን የማይችል ነገር ነበር፡፡ ሆኖም ከተፈጥሮ ውጪ በሆነ መንገድ ትወልጃለሽ ስትባል ‘አዬ ጉድ?! የትኛዋ ሴት ያለ ወንድ ዘር ፀንሳ ታውቅና ነው እኔን እንዲህ የምትለኝ?’ ብላ አልሳቀችም፡፡ ድንግሊቱ ልብዋ በፈጣሪ ፍጹም የሚያምን ነውና በዕድሜዋ ልጅ ብትሆንም የሰማዩን እንግዳ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ገብርኤልን እንደ አሮጊትዋ እናትዋ ሣራ እየሳቀች አላስከፋችውም፡፡ እንደ ዘካርያስ ምልክት ጠይቃ አላስቆጣችውም፡፡
Show all...
የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች

"ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን" 2ኛ ቆሮ. 2:14 YouTube

https://www.youtube.com/@Min22111

Telegram Group

https://t.me/D_n_henok_hiyla

+ የአብርሃም ድንኳን + አባታችን አብርሃም በመጽሐፍ ቅዱስ እንግዳን አክብሮ በመቀበል ወደር የሌለው ጻድቅ ሰው ነበር፡፡ ምንም እንኳን ኑሮው የድንኳን ቢሆንም ወደ አብርሃም ቤት ገብቶ ሳይስተናገድ የወጣ ሰው በዘመኑ አልነበረም፡፡ ‘በምድር እንግዳ ተቀባይ የነበረውን አብርሃም እግዚአብሔር በሰማይም ነፍሳትን እንግዳ ተቀባይ አድርጎታል’165 ወደ አብርሃም ቤት በአንድ ቀትር ላይ የመጡት እንግዶች ግን የተለዩ ነበሩ፡፡ ምዕራፉ ሲጀምር እግዚአብሔር ለአብርሃም ተገለጠለት ይልና ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ ይላል፡፡ ሦስቱን እንግዶች ካየ በኋላ የአብርሃም ንግግር የተለመደውን የሰዋስው ሕግ መጠበቅ አቆመ፡፡ ሦስቱን ሰዎች ጠጋ ብሎ አንድን ሰው እንደሚያናግር ንግግሩን ፦ ‘አቤቱ፥ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ባሪያህን አትለፈኝ’ ብሎ በነጠላ ይጀምራል፡፡ ዘፍ. ፲፰፥፪ ‘ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፥ እግራችሁን ታጠቡ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ’ ብሎ በብዙ ይፈጽማል፡፡ ዘፍ. ፲፰፥፬-፭ አብርሃም ብቻ ሳይሆን የዘፍጥረት ጸሐፊ ሙሴም እንደ አብርሃም የሰዋስው ሕግ ጥሶ አንድ ጊዜ ‘እነርሱም እንዲህ አሉት’ ብሎ በብዙ ይጠራቸውና መልሶ ደግሞ ከሦስቱ አንዱም እንዲህ አለ በማለት ፈንታ ‘እርሱም እንዲህ አለው’ ብሎ በነጠላ እንግዶቹን ይጠራል፡፡ ዘፍ.፲፰፥፱፣፲ አብርሃምም ለሚስቱ የሠጣት መመሪያ ሦስት መስፈሪያ ዱቄት እንድታዘጋጅና አንድ አድርጋ እንድትለውሰው መሆኑ ያለ ምክንያት የተቀመጠ አላስፈላጊ ዝርዝር አይመስልም፡፡ ዘፍ. ፲፰፥፮ በአብርሃም ቤት በሦስት ሰዎች አምሳል ራሱን እንግዳ ያደረገውና ከሌሎች የተሠወረ ሦስትነቱን ለወዳጁ ለአብርሃም የገለጠው እግዚአብሔር ነበረ፡፡ በነጠላ የተነገሩት ቃላት አንድነቱን ፣ በብዙ የተነገሩት ደግሞ ሦስትነቱን የሚገልጡ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ‘ስለ አንድነታቸው ማሰብ በጀመርሁበት ቅጽበት ራሴን በሦስትነታቸው ግርማ ተከብቤ አገኘዋለሁ፡፡ ስለ ሦስትነታቸው ለይቼ ባሰብሁኝ ቅጽበትም ራሴን ወደ አንድነታቸው ተመልሼ አገኘዋለሁ’ላለው ከአብርሃም ታሪክ የተሻለ ማሳያ የለም፡፡ ( St. Gregory Nazianzus, On Holy Baptism, Sermon 40) ይህንኑ ታሪክ ከቀጣዩ ምዕራፍ ጋር በማያያዝ ‘በአብርሃም ቤት የተገለጡት ሁለቱ መላእክት ሲሆኑ አንዱ እግዚአብሔር ወልድ ነበር’ የሚሉ ቀደምት አበው ብዙ ናቸው፡፡ የመጻሕፍተ ብሉያት ትርጓሜም ለሥላሴ ከተረጎመ በኋላ ‘አንድም ሠለስቱ ዕደው ያላቸው ሁለቱ መላእክት ናቸው፤ አንዱ ጌታ ነው’ ብሎ በአንድታም ማስቀመጡ ይህ አሳብ በጥንታዊትዋ ቤተ ክርስቲያን የትርጓሜ ስልት ውስጥ ምን ያህል መሠረት ያለው አሳብ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ሆኖም በአብርሃም ቤት የተገለጠውን ምሥጢር ለምሥጢረ ሥላሴ ማብራሪያ አድረገው ያስተማሩ እንደ ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ ፣ እንደ ቅዱስ አምብሮስ ፣ ሊቀ ጳጳስ አውግስጢኖስ ያሉ ቅዱሳን አባቶች አሉ፡፡( The Mystery of the Trinity, Trinitarian Experience and Vision in the Biblical and Patristic Tradition, Boris Bobrinskoy, SVS Press, 1999, pg 140-141) ታሪኩ በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ላይ ያለው ክብደት የላቀ መሆኑን በመገንዘብም አስቀድመው የቤተ አብርሃም መስተንግዶን ታሪክ የሚሥሉ የምሥራቃውያን ሠዓሊያንም ሳይቀሩ ከሦስቱ አንዱን አጉልቶ ከመሣል እኩል አድርጎ ወደ መሣልና የምሥጢረ ሥላሴ ምሳሌያዊ መገለጥ እንደሆነ ጠቅሶ ወደ ማስተማር አዘንብለዋል፡፡ (R.M. Grant, ‘Greek Litrature in the Treatise on the Trinity and Cyril against Julianum, Journal of Theological Study, Vol. 15 1964, 265-299 ; Augstine of Hippo, On Trinity, ii. 20, S.Mckenna, ‘Saint Augstine : The Trinity’ The Fathers of the Church, vol. 46 DC 1963, 7) በአብርሃም ቤት የሥላሴን መገለጥ አስፍታ አምልታ በምታስተምረውና በዓል ሠርታ የምታከብረው የእኛ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አሳብ ግን የእንግዶቹን ነገር ለመላእክት የሚሠጠውን ትርጓሜ እንዲህ ጠንከር ብሎ የሚወቅስ ነው፡፡ ‘ወአንተሰ ክርስቲያናዊ እመን ዘንተ ሃይማኖተ ንጽሕተ፡ ቤተ አብርሃምሂ እለ ቦኡ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እሙንቱ፡ ወሰገደ ሎሙ አብርሃም በአዔርዮ ወለመላእክትሰ ኢይሰግዱ ሎሙ ምስለ እግዚአብሔር በአዔርዮ አሐተ ስግደተ በከመ ሰገደ አብርሃም እንዘ ይብል አጋእዝትየ፡ ወኢነገሩነ ኦሪት ወነቢያት ወንጌል ወሐዋርያት ከመ ይሰግዱ ኵሉ ፍጥረት ለእግዚአብሔር ጸባኦት በአዔርዮ ምስለ መላእክት፡ ዘንተ ዘኢየአምን ወድቀ እመዓርገ ሃይማኖት ወለነሰ ይዕቀበነ በሥላሴሁ ንጽሕት’ ‘አንተ ክርስቲያናዊ ሆይ ይህችን ንጽሕት የሆነች እምነትን እመን፡፡ በአብርሃም ቤትስ የገቡት አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ አብርሃምም አስተካክሎ በአንድነት ሰገደላቸው፡፡ ለመላእክትስ አብርሃም ጌቶቼ እያለ እንደሰገደው ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክለው አንድን ስግደት ሊሰግዱላቸው አይገባም፡፡ ኦሪትና ነቢያት ፣ ወንጌልና ሐዋርያት ፍጥረት ሁሉ ለአሸናፊ እግዚአብሔር ከመላእክቱ አስተካክለው ጋር በአንድነት ሊሰግዱለት እንደሚገባ አልነገሩንም፡፡ ይህን የማያምን ከሃይማኖት መዓርግ ወደቀ ፤ እኛንስ ንጽሕት በሆነች ሦስትነቱ ይጠብቀን’ (መጽሐፈ ሥላሴ ፤ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ገጽ ፹ | ወደ ሰዶም የወረዱትን በተመለከተ መጻሕፍተ ብሉያት አብና መንፈስ ቅዱስ ናቸው ፤ ከአብርሃም ቤት የቀረው ወልድ ነው፡፡ ከቤተ አብርሃም ሰው የሆነ እርሱ ነውና ሲል መጽሐፈ ሥላሴ ደግሞ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ናቸው ፤ የቀረው አብ ነው ይላል) እግዚአብሔር በአብርሃም ድንኳን በሦስትነት በተገለጠበት በዚያ ዕለት ‘የዛሬ ዓመት ወደ ቤትህ እመጣለሁ ፤ ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች’ ብሎት ነበር፡፡ ይህን በጓዳ ሆና የሰማችው አሮጊትዋ ሣራም እንዴት ይሆናል? ብላ ሳቀች፡፡ ‘እግዚአብሔርም ፦ እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ ሣራም ልጅን ታገኛለች’ አለው፡፡ እግዚአብሔር በዓመቱ ወደ አብርሃም ቤት ተመልሶ መጣ የሚል ቃል በዘፍጥረት ላይ አልተጻፈም ፤ አመጣጡ በሥራው ነበርና የይስሐቅ መወለድ የእግዚአብሔር ረድኤት መገለጫ ሆነ፡፡ እግዚአብሔር ወደ አብርሃም ቤት ተመልሶ የመጣበት ትክክለኛው ጊዜ ግን ከድንግል ማርያም ተፀንሶና ተወልዶ ‘የአብርሃም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ’ ተብሎ የተጠራበት ዘመነ ሥጋዌ ነው፡፡ ይህ መሆኑን እንድናውቅ እግዚአብሔር በአብርሃም ቤት በመጣ ጊዜ ‘እንዴት ይሆናል?’ ላለችው ሣራ ‘በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?’ ብሏት እንደነበረ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ድንግል ማርያም መጥቶ ሲያበሥራት ‘እንዴት ይሆናል?’ ላለችው ጥያቄ የሠጣት መልስ መደምደሚያው ‘ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም’ የሚል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሣራን የረታበትን ቃል ድንግሊቱን በገብርኤል ሆኖ ባበሠራት ጊዜ ረትቶበታል፡፡ በመሆኑም በአብርሃም ድንኳን ያደረው እግዚአብሔር ያደረባት የሐዲስ ኪዳንዋ የአብርሃም ድንኳን ድንግል ማርያም ናት፡፡ ዘፍ. ፲፰፥፲፬ ፤ ሉቃ. ፩፥፴፯
Show all...
Photo unavailableShow in Telegram
6👍 2
Photo unavailableShow in Telegram
ሐምሌ 7 የአብርሃሙ ስላሴ እንኳን ለፈጣሪያችን ለቅድስት ሥላሴ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ# በዚች ቀን ልዩ የሆኑት ሶስቱ አካላት (ቅድስት ስላሴ) ወደ አብርሃም ቤት ገቡ ያቀረበላቸዉንም ተመገቡ የይስሐቅንም ልደት አበሰሩት ባረኩት አከበሩትም። baga ayyaana waggaa ummaa keenyaa qulqulleettii silaaseen nagaan geenye. Guyyaa kanaatti adda kan ta'an qamonii sadii (qulqulleetti silaasee) Gara mana abiri'haam seennaan kan isaanif dhiyeeses nyaatan. dhalachuu yisaaqis itti himan hin ebbisaan hin kabaajanis መልካም በዓል ለሁላችንም❤ Ayyaana garii hundaa keenyaaf. https://t.me/hinokhayla https://t.me/hinokhayla
Show all...
12
Photo unavailableShow in Telegram
እንኳን ለዚህ ክብር አበቃህ ውድ ወንድማችን ዘማሪ ክብሮሜ!!!
Show all...
10
ፍቅር ቊስል ነው እውነቱ ይህ ነው ፣ ፍቅር የሚለካው በልባችን ላይ በተወው ቊስል ልክ ነው። እጅግ የምንወዳቸው ሰዎች አሳምመውን ይሆናል። እኛም እጅግ የሚወዱንን ሰዎች አሳምመን ይሆናል። ምክንያቱም ፍቅር የሚታየው በታገስነው ቊስል ውስጥ ነው ፍቅር የሚታወቀው የተለዋወጥናቸውን ቃላት ሳይሆን በምንታገሠው ቊስል ፣ በተሰማን የውስጥ ሕመም ፣ በከፈልነውን መሥዋዕትነትና በተካፈልነውን ብርሃን ነው። ከትንሣኤው በኋላ በሐዋርያቱ ፊት የተገለጠው ክርስቶስ እርሱ የሚወዱት ጌታ እንደሆነ ለማስረዳት ያሳያቸው የትንሣኤው ድል ማብሠሪያ መለከት አይደለም ፣ የፍቅሩ ማስረጃ ቊስሉ ነበር። "ወደ እኔ ኑ ቊስሌን ዳስሱ ፣ እጃችሁንም ስለ እናንተ ፍቀር በቆሰልሁት ቊስል አስገቡ" ነበር ያላቸው። አታስታውሱኝም? አላወቃችሁኝም? እስከ ሞት ድረስ የወደድኳችሁ እኔ ነኝ። ለፍቅሬ ማረስጃ እንዲሆናችሁ ደግሞ ቊስሌን ተመልከቱ! ነው ያላቸው። ፍቅር ቊስል ነው። በእግዚአብሔር መንግሥት ክብርና ምስጋና የምናገኘውም በምድር ሳለን በነበሩ ስኬቶቻችንና ባስገኘናቸው ውጤቶቻችን ሳይሆን በታገሥናቸው መከራዎችና በተሰቃየንባቸው ሕመሞች ልክ ነው። ለዚህም ነው በአበው መጽሐፍ አንድ ቅዱስ አባት ለረጅም ዓመት በሰውነትዋ ላይ ቆስሎ የምትሰቃይን ሴት ሊጠይቁ ሲሔዱ "እዩት ቊስሌን አጎንብሰው ቢያዩት አጥንቴ ይታይዎታል" አለቻቸው። እርሳቸውም ጎንበስ ብለው "ብዙ ዓመት በታገስሽው በቊስልሽ ውስጥ የሚታየኝ አጥንት ሳይሆን ገነት ነው" አሏት። ጸሐፊ: Fr Haralambos Libyos Papadopoulos ተርጓሚ: ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ግንቦት 10 2011 ዓ ም አዲስ አበባ https://t.me/hinokhayla https://t.me/hinokhayla
Show all...
21🥰 6👏 6👍 2
Choose a Different Plan

Your current plan allows analytics for only 5 channels. To get more, please choose a different plan.