cookie

We use cookies to improve your browsing experience. By clicking «Accept all», you agree to the use of cookies.

avatar

መንፈሳዊ ጉባኤ

ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ነውርም የለብሽም። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 4 : 7 @Menfesawi_Gubae ጥያቄ ካላችሁ ከታች ባለው አድራሻ መጠየቅ ትችላላችሁ። @HenokAsrat3

Show more
Advertising posts
3 060
Subscribers
-224 hours
-17 days
-930 days

Data loading in progress...

Subscriber growth rate

Data loading in progress...

መንፈሳዊ ጉባኤ: Henok: 💦💦የሚገርም ፍቅር💦💦💦 ♥የጌታችን ሕማማት በሊቃውንት♥ : ☞በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕሙማነ ሥጋን በተአምራት ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት በማዳኑ፣ ዕዉራነ ሥጋን በተአምራት ዕዉራነ ነፍስን በትምህርት በማብራቱ፣ ልሙጻነ ሥጋን በተአምራት ልሙጻነ ነፍስን በትምህርት በማንጻቱ፣ አጋንንትን በማውጣቱ፣ ሙታንን በማንሣቱና ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው የአብ የባሕርይ ልጅ መኾኑን በማስተማሩ አይሁድ ከፍተኛ ቅንአት ዐድሮባቸው ጌታን ይዘው የካህናት አለቃ ቀያፋ ወዳለበት ይዘውት በመኼድ የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ሸንጎውም ኹሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሐሰት ምስክር ቢፈልጉም ምንም ዐይነት በደል ሊያገኙበት አልቻሉም ነበር፤ በኋላም ሊቀ ካህናቱ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የኾንኽ እንደ ኾነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልኻለኊ” ብሎ ሲጠይቀው፤ ጌታም “አንተ አልኽ፤ ነገር ግን እላችኋለኊ፤ ከእንግዲኽ ወዲኽ የሰው ልጅ በኀይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችኊ” በማለት ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው በአብ ቀኝ ያለው የአብ የባሕርይ ልጅ የኾነው ርሱን በኀይል ቀኝ በሰማይ ደመና ማለት፡- ዓለምን በማሳለፍ ኀይል ባለው ዕሪና በባሕርይ ክብሩ መጥቶ ታዩታላችኊ በማለት ተናገረው (ማቴ 26፡63-64)፡፡ ያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ በንዴት ልብሱን ቀደደ፤ በዘሌ 21፡10 ላይ “በራሱም ላይ የቅባት ዘይት የፈሰሰበት የክህነትም ልብስ ይለብስ ዘንድ የተቀደሰ ከወንድሞቹ የበለጠው ካህን ራሱን አይግለጥ ልብሱንም አይቅደድ” በማለት እንዳዘዘው በኦሪት ሥርዐት ካህን በሐዘን ምክንያት ልብሱን ከቀደደና ፊቱን ከነጨ ከሹመቱ የሚሻር ነውና በዚኽም የሊቀ ካህናቱ ኦሪታዊ ክህነት ማለፉን አጠይቋል፡፡ ከዚያ በኋላ ጌታን “ሞት ይገባዋል” በማለት በደረቅ ግንባር ላይ ዐይንን በፈጠረ በርሱ ፊት ላይ ምራቃቸውን ተፉበት፡- ጌታ በኢሳይያስ ዐድሮ በምዕ ፶፥፮ ላይ “ወኢይትሀከዩ ወሪቀ ውስተ ገጽየ ወኢሜጥኩ ገጽየ እምኀፍረተ ምራቅ” (ዠርባዬን ለገራፊዎች ጕንጬንም ለጠጕር ነጪዎች ሰጠኊ ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስኹም) ያለው ትንቢት ሊደርስ ሊፈጸም ምራቃቸውን ተፍተውበታል፡፡ አንድም አዳምን ዲያብሎስ በገጸ ልቡናው ምራቀ ምክሩን እየተፋ ሲኦል አውርዶት ነበርና ለርሱ ካሳ ሊኾን ንጹሐ ባሕርይ አምላክ ተተፍቶበታል፡፡ ከዚያም ራሱን በዘንግ መቱት “ወኲሉ ርእስ ለሕማም” (ራስ ኹሉ ለሕመም ኾኗል) ብሎ ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት ይደርስ ይፈጸም ዘንድ የሕይወት ራስ ርሱን በዘንግ መቱት (ኢሳ ፩፥፭)፤ አንድም ዲያብሎስ የአዳምን ርእሰ ልቡናውን በበትረ ምክሩ እየመታ ሲኦል አውርዶት ነበርና ካሳ ሊኾን ነበር፤ ከዚያም ፊቱን በሻሽ ሸፍነው “መኑ ውእቱ ክርስቶስ ዘጸፍዐከ” (ክርስቶስ በጥፊ የመታኽ ማነው? ንገረን እስቲ ዕወቀን) እያሉ ዘብተውበታል፤ ይኸውም መተርጒማን እንዳመሰጠሩት አዳምና ሔዋን የአምላክነትን ዕውቀት ዕንወቅ ብለው ሲኦል ወርደው ነበርና ልቡና ያሰበውን ኩላሊት ያመላለሰውን ኹሉን የሚያውቅ ርሱ ላይ በዚኽ ቃል መዘበታቸው ለአዳምና ለሔዋን ሊክስላቸው ነው፡፡ ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት የሚያድሩ ቊጥራቸው ከ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት የኾኑት ኤልሳቤጥ፣ ቤርዜሊ፣ መልቴዳ በዕለተ ዐርብ በዐይናቸው ያዩትን የጌታን ሕማማት በተናገሩበት ድርሳን ላይ ይኽነን ሲገልጹ፡- “ወሶበ ዘበጥዎ አፉሁ ለእግዚእ ኢየሱስ ሐሙ ከናፍሪሁ ወአስናኒሁ፤ ወውሒዘ ደም ብዙኅ እምአፉሁ…” (ጌታችን ኢየሱስን አፉን በመቱት ጊዜ ከንፈሮቹ ጥርሶቹም ታመሙ፤ ከጌታችንም ከኢየሱስ አፍ ብዙ ደም ፈሰሰ፤ አሕዛብን በሚያጠፋበት ስለቱ (ሥልጣኑ) በኹለት ፊት የኾነ የተሳለ ሰይፍ ከአንደበቱ የሚወጣ ሲኾን (ወደ እኔ ኑ፣ ከእኔ ኺዱ የሚልበት ሥልጣን ገንዘቡ ሲኾን) (ማቴ ፳፭፥፴፩-፵፮)፤ ዳግመኛ አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን ፊቱን ፳ ጊዜ በጡጫ መቱት ይኸውም እግዚአብሔር አብን መንፈስ ቅዱስንም በመልክ የሚመስል በባሕርይ የሚተካከል ነው (ዮሐ 10፡30)፤ በጌትነት ክብር በደብረ ታቦር በተገለጸ ጊዜ ተለውጦ እንደ ፀሓይ ያበራ መልኩ ፊቱ ነው (ማቴ ፲፯፥፪)፤ ርሱ የማይጠልቅ ፀሓይ የማይጠፋ ፋና ነውና፤ በወዳጆቹም ላይ ዘወትር የሚያበራ ፀሓይ ነውና (ራእ ፳፪፥፭)፤ ሰነፎች አይሁድም ከምድር ነገሥታት ይልቅ የሚያስፈራ ፊቱን ሲመቱት የጌታችን የኢየሱስ የፊቱ ግርማ ሦስት ጊዜ ወደ ምድር የኋሊት የጣላቸው መኾኑን አላሰቡትም) በማለት በቅንአት የሰከሩ የዝንጉኣን የአይሁድን ነገር አስምረዋል፡፡ ዓለምን ለማዳን ሲል አካላዊ ቃል ክርስቶስ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም በቅዳሴው ላይ ሲተነትናቸው፡- “በይእቲ ሌሊት እንተ ባቲ ረፈቀ ምስለ አርዳኢሁ መጠወ ነፍሶ ለሞት በፈቃደ አቡሁ ወበሥምረተ ርእሱ…” (ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ በተመጠባት በዚያች ሌሊት በአባቱ ፈቃድ በራሱም ፈቃድ ሰውነቱን ለሞት ሰጠ፤ ኹሉን የያዘውን ያዙት ኹሉን የሚገዛውን አሰሩት የሕያው የአምላክን ልጅ አሰሩት፤ በቊጣ ጐተቱት በፍቅር ተከተላቸው፤ በሚሸልተው ፊት እንደማይናገር እንደ የዋህ በግ በኋላቸው እየተከተላቸው ወሰዱት፤ ሊቃነ መላእክት በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ከፊቱ የሚቆሙለትን በዐደባባይ አቆሙት ኀጢአትን ይቅር የሚለውን ኃጥእ አሉት፤ በመኳንንት በሚፈርደው በርሱ ፈረዱበት፤ ለሱራፌል ዘውድ የሚያቀዳጃቸውን የእሾኽ ዘውድ አቀዳጁት፤ ለኪሩቤል የግርማ ልብስ የሚያለብሳቸውን ለመዘበት ቀይ ግምጃ አለበሱት ኪሩቤል በእሳት ክንፍ ተሸፍነው በፊቱ የሚሰወሩለትን ርሱን (ኢሳ ፮፥፪፤ ራእ ፭፥፭-፲፬)፤ ክፉ ባሪያ እጁን አጽንቶ ፊቱን ጸፋው (ዮሐ ፲፰፥፳፪) የመላእክት ሰራዊት በፍጹም መደንገጥ ለሚሰግዱለት እየዘበቱበት በፊቱ ተንበረከኩ (ፊልጵ ፪፥፲) ይኽን ያኽል ትሕትና እንደ ምን ያለ ትሕትና ነው?፤ ይኽን ያኽል ዝምታ እንደ ምን ያለ ዝምታ ነው?፤ ይኽን ያኽል ቸርነት እንደ ምን ያለ ቸርነት ነው?፤ ይኽን ያኽል ሰውን ማፍቀር እንደ ምን ያለ ፍቅር ነው?፤ ኀያል ወልድን ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው እስከ ሞትም አደረሰው፤ በደል የሌለበትን እንደ በደለኛ ሰቀሉት፤ ሕይወት የሠራውን ከበደለኞች ጋራ ቈጠሩት፤ አዳምን የፈጠሩ እጆች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ ወዮ፤ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ ወዮ፤ በአዳም ላይ የሕይወት መንፈስን እፍ ያለ አፍ ከሐሞት ጋራ የተቀላቀለ የኾመጠጠ መጻጻን ጠጣ ወዮ፤ የወልድ መከራውን የሚናገር ምን አፍ ነው? ምን ከንፈር ነው? ምን አንደበት ነው? የፍቁር የጌታ ሕማማት በተነገረ ጊዜ ልብ ይለያል ኅሊናም ይመታል ነፍስም ትንቀጠቀጣለች ሥጋም ይደክማል፤ የማይሞተው ሞተ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ) በማለት ሕማማቱን በስፋት አስተምሮታል፡፡ ወንጌላውያንም እንደጻፉት ጌታችንን አይሁድ ኀሙስ ማታ ከያዙት በኋላ “ወወሰድዎ ለእግዚእ ኢየሱስ እምኀበ ቀያፋ ኀበ ዐውድ ወጎሕ ውእቱ” ይላል በማለዳ ከቀያፋ ወደ ገዢው ግቢ ወደ ፍርድ ዐደባባይ አስረው በማለዳ ወደ ጲላጦስ ዘንድ ወስደውታል (ማቴ ፳፯፥፲፩፤ ማር ፲፭፥፩፤ ሉቃ ፳፫፥፩፤ዮሐ ፲፰፥፳፰) ይኸውም አዳምን ከመልአከ ገሀነም ፊት አስረው ወስደው አቁመውት ነበርና ለካሣ ሊኾን ነበር፡፡ .
Show all...
የያዘውን በትር ከእጁ ተቀብለው ራሱን መቱት፤ ነገር ግን የሾኽ አክሊልን በመቀዳጀቱ በምድራችን ላይ የበቀሉትን አሜከላና እሾኽ ርግማንን አጠፋልን፤ ራሱንም በዘንግ በመመታቱ የታላቁን እ ባብ ሰባቱን ራሶቹን ዐሥሩን ቀንዶቹን አጠፋልን) በማለት አስተምረዋል፡፡ ክብር ይግባውና ንጹሐ ባሕርይ ጌታችንን አይሁድ መስቀሉን አሸክመው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ከወሰዱት በኋላ ኹለት ወንበዴዎችን በቀኝና በግራ ጌታችንን በመኻከል አድርገው ሰቅለውታል (ማቴ ፳፯፥፴፰፤ ማር ፲፭፥፳፯፤ ሉቃ ፳፪፥፴፫፤ ዮሐ ፲፱፥፲፰)፡፡ ክፉዎች አይሁድ ይኽነን ያደረጉበት ምክንያት በክፋት ነው ይኸውም በቀኝ የሚመጡ ሰዎች በቀኝ የተሰቀለውን ወንበዴ አይተው ይኽ ምንድነው? ብለው ሲጠይቁ ወንበዴ ነው ይሏቸዋል፤ ከዚያም ጌታን ይኽስ ምንድነው? ብለው ሲጠይቁ ይኽስ ከርሱ ልዩ ነውን አንድ ነው እንጂ ብለው ሰዎችን ለማሳሳት፤ በግራ የሚመጡ ሰዎች በግራ የተሰቀለውን ወንበዴ አይተው ይኽ ምንድነው? ብለው ሲጠይቁ ወንበዴ ነው ይሏቸዋል፤ ከዚያም ጌታን ይኽስ ምንድነው? ብለው ሲጠይቁ ይኽስ ከርሱ ልዩ ነውን አንድ ነው እንጂ ብለው ሰዎችን ለማሳሳት፤ ዳግመኛም አነገሥንኽ ብለውታልና ቀኛዝማች ግራዝማች ሾምንልኽ ለማለት ለመዘበት ነው በተጨማሪም ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕ ፶፫፥፲፪ ላይ “ከዐመፀኞችም ጋር ተቈጥሯልና” የሚለው ትንቢቱን ሊፈጽም ሲኾን ምስጢሩ ግን በዕለተ ምጽአት እኛን ኃጥኣንን በግራ ጻድቃንን በቀኝ ታቆማለኽ ሲያሰኛቸው ነበር (ማቴ ፳፭፥፴፫፤ ራእ ፩፥፯)፡፡ ቊጥራቸው ከ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት ውስጥ የኸኑት ኤልሳቤጥ፣ መልቴዳና በርዜዳ ስለዚኽ ነገር ሲገልጹ “ወሰቀልዎ ለእግዚእ ኢየሱስ ዲበ ዕፀ መስቀል እንዘ ገጹ መንገለ ምሥራቅ ወእዴሁ ዘየማን መንገለ ደቡብ ወእዴሁ ዘፀጋም መንገለ ሰሜን…” (ጌታችን ኢየሱስንም በዕንጨት መስቀል ላይ ሰቀሉት፤ ፊቱን ወደ ምሥራቅ ቀኝ እጁን ወደ ደቡብ፤ ግራ እጁን ወደ ሰሜን አድርገው ሰቀሉት…ከርሱም ጋር ኹለቱን ወንበዴዎች አንዱን በቀኝ አንዱን በግራው በመኻከላቸው ጌታችን ኢየሱስን አድርገው ሰቀሉ፤ ሕዝቡም ርሱም እንደነርሱ ወንበዴ ነው ይሉት ዘንድ ሰቀሉት፤ ርሱ ግን ወድዶ ከወንበዴዎች ጋር በዕንጨት መስቀል ተሰቀለ፤ ልዑላን መላእክት ፈርተው በፊቱ ራሳቸውን ዝቅ ዝቅ የሚያደርጉለት ርሱ በሚሰቅሉት ፊት ራሱን ዝቅ አደረገ (ፊልጵ ፪፥፲፤ ራእ ፬፥፲-፲፩)፤ በከሃሊነቱ ሰማይና ምድርን ያጸና ከግርማውም የተነሣ ሰማያትና ምድር የሚንቀጠቀጡለትን ርሱን ደካማ ዕንጨት ተሸከመው (ምሳ ፴፥፬፤ ኢሳ ፵፪፥፭)፤ ርሱ ግን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ከራሱ ያስታርቀን ዘንድ ከሰማይ ዝቅ ብሎ ከምድር ከፍ ብሎ በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ፤ ርሱም ስለእኛ በሥጋው በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ፤ ከኀጢአታችን ይለየን ዘንድ በቸርነቱ ያድነን ዘንድ ተሰቀለ (፩ጴጥ ፪፥፳፬)፤ ርሱ ግን ሰማያትን ይቀድስ ዘንድ በአየር ያሉ አጋንንትን ያወርዳቸው ዘንድ በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ፤ ሙሴ አርዌ ብርትን በገዳም እንደ ሰቀለው ርሱም በዕንጨት ላይ ተሰቀለ ፤ በርሱ ያመነ ኹሉ ይድናል እንጂ እንዳይጐዳ የክብር ባለቤት ርሱ ግን ስለ እኛ በዕንጨት ላይ ተሰቀለ (ዮሐ ፫፥፲፬-፲፭)፤ አውቀውስ ቢኾን የክብር ባለቤት ጌታን ባልሰቀሉት ነበር (፩ቆሮ ፪፥፰)፤ ሰማይ ዙፋኑ ሲኾን ምድርም በእግሮቹ የተረገጠች ስትኾን ስለኛ በዕንጨት ተሰቀለ (ኢሳ ፷፮፥፩)፤ ርሱ ግን ተጠብቆለት ስላለ ስለ ደስታው የመስቀልን መከራ ንቆ አቃልሎ ተቀበለ ኀፍረትንም ናቃት፤ ለተሰቀለው ለርሱ የማይሰግድ ቢኖር የተለየ የተወገዘ ይኹን (ፊልጵ ፪፥፰-፲፩)፤ ርሱ ግን ስለ ዓለሙ ደኅንነት በማእዝነ ምድር ወደ ላይ ወደ ታች ወደ ግራ ወደ ቀኝ ኾኖ እንደ መጋረጃ በዕንጨት ላይ ተሰቀለ፤ እኛን ከጻድቃን ጋራ አንድ ያደርገን ዘንድ ርሱ ከበደለኞች ጋር ተቈጠረ) በማለት በስፋት የነገረ ስቅለቱን ምስጢር አስተምረዋል፡፡ በመስቀል ሲሰቀልም በቀኙ የተሰቀለው ጥጦስ በግራ የተሰቀለው ዳክርስ ይባላል፤ በቀኝ የተሰቀለው ጥጦስ ፀሓይ ስትጨልም፣ ጨረቃ ደም ስትኾን፣ ከዋክብት ከብርሃናቸው ሲራቈቱ፣ ድንጋዮች ሲሠነጠቁ፣ መቃብራት ሲከፈቱ፣ ሙታን ሲነሡ፣ የምኩራቡ መጋረጃ ወደ ኹለት ወደ ሦስት ሲቀደድ ሰባቱ ተአምራት ሲደረጉ አይቶ አምላክነቱን ተረድቶ ወደ ርሱ ሲለምን በግራ የተሰቀለው ወንበዴ ሰምቶ “አንተስ ክርስቶስ አይደለኽምን? ራስኽንም እኛንም አድን” ይል ዠመር (ሉቃ ፳፫፥፴፱)፡፡ ያን ጊዜ በቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ጌታችን ለቤዛ ዓለም የተሰቀለ እውነተኛ የባሕርይ አምላክነቱን ስለተረዳ በግራ የተሰቀለውን “አንተ እንደዚኽ ባለ ፍርድ ሳለኽ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይኽ ግን ምንም ክፋት አላደረገም” ብሎ ከገሠጸው በኋላ ኀጢአት ሳይኖርበት የተሰቀለውን ንጹሐ ባሕርይ አምላኩን “ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ” (ጌታ ሆይ በመንግሥትኽ በመጣኽ ጊዜ አስበኝ) እያለ ሲለምነው ጌታችንም “እውነት እልኻለኊ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኾናለኽ” ብሎት ደመ ማኅተሙን ሰጥቶታልና ሊቁ አባ ጊዮርጊስ በዚኽ መጽሐፉ ላይ፡- “ምስጋና ለአንተ ይገባል፤ የሞትን ፃዕረኝነት (ችንካር) ትሽር ዘንድ ክፋትን የሠራኽ ሳትኾን (ሳትሠራ) በኹለት ሽፍቶች (ወንበዶች) መኻከል የተቸነከርኽ እውነተኛ ኢየሱስ ምስጋና ለአንተ ይገባል” በማለት ንጹሐ ባሕርይ አምላኩን አመስግኗል (ሉቃ ፳፫፥፴፱-፵፫)፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ . . . .
Show all...
ይኽ የጌታችን ትሕትና ብዙዎችን አስደንቋል፤ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንትም በቅዳሴያቸው ላይ “በይእቲ ሌሊት አኀዝዎ ወጸቢሖ ረበናተ አይሁድ ወሊቃነ ካህናት ምስለ ጲላጦስ መስፍን ወነበሩ ዐውደ ለኰ ንኖቱ…” (በዚያች ሌ ሊት ያዙት. በነጋም ጊዜ የአይሁድ መምህሮችና የካህናት አለቆች ከገዢው ከጲላጦስ ጋራ ሊፈርዱበት በዐደባባይ ተቀመጡ፤ እንደ ሌባ የኋሊት አሰሩት እንደ የዋህ በግ በፍቅር ተከተላቸው፤ ሊፈርዱበት በዐደባባይ ተቀመጡ፤ የመላእክት ሰራዊት በመፍራት የሚቆሙለትን በፊታቸው አቆሙት፤ ክፉ ባሪያ ርሱን ያልበደለውን ፊቱን በጥፊ ይመታው ዘንድ እጁን አጸና፤ የመላእክት አለቆች በፍጹም ድንጋፄ ለሚሰግዱለት ለርሱ በትዕቢት ይሰግዱ ዘንድ አጐነበሱለት) በማለት ዐርብ ጠዋት አይሁድ ጌታን ወደ ፍርድ ዐደባባይ እንዴት እንዳቀረቡት በስፋት አስተምረዋል፡፡ ጌታ ከመወለዱ አንድ ሺሕ ዓመት አስቀድሞ ጌታችን በንጉሥ ዳዊት ዐድሮ በመዝ ፳፩፥፲፰ ላይ “ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” በማለት ያናገረው ትንቢት ሊደርስ ሊፈጸም ጭፍሮች ጌታን ከሰቀሉት በኋላ ልብሶቹን ወስደው ለእያንዳንዱ ጭፍራ አንድ ክፍል ኾኖ በአራት ሲከፋፍሉት ከላይ ዠምሮ ወጥ ኾኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ ያልነበረው እጀ ጠባቡን ደግሞ በመውሰድ ርስ በርሳቸው ለማን እንዲኾን በርሱ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው ተባባለዋል፤ ይኽቺውም ቀሚሱ ሰብአ ሰገል ያመጡለት ሲያድግ የምታድግ ዐሥራ ኹለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የነበረችው ሴት የተፈወሰችበት ገባሪተ ተአምራት ነበረች (ማቴ ፪፥፲፩፤ ፱፥፳)፡፡ አይሁድ ይኽነን ማድረጋቸው ለጊዜው “ኹለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል” (ማቴ ፭፥፵) በማለት ኹለት ልብስ አታኑሩ በማለት የሚያስተምረው የርሱ ልብስ ለአራት ቤት ጭፍራ በቃ ለማለት ለመዘበት ሲኾን ፍጻሜው ግን ልብስ የወንጌል ምሳሌ አራት ዕጣ መጣጣላቸው ወንጌል አራት ወገን ኹና ለመጻፏ፤ አለመቅደዳቸው በምስጢር አንድ የመኾኗ፤ አንድም አራቱ ኹሉ ባንዲቱ ዕጣ መጣጣላቸው ወንጌል አራት ክፍል ስትኾን አንድ ሕግ ለመኾኗ ምሳሌ፤ አንድም “አንቅደድ” ማለታቸው ትስብእቱን ከመለኮቱ ሳንለይ እንመን ሲያሰኛቸው ነው በማለት መተርጒማነ ሐዲስ ያመሰጥራሉ (ማቴ ፳፯፥፴፭፤ ማር ፲፭፥፳፬፤ ሉቃ ፳፫፥፴፬፤ ዮሐ ፲፱፥፳፫)፡፡ ቊጥራቸው ከ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት የሚኾን ኤልሳቤጥ፣ መልቴዳ፣ በርዜዳ የሚባሉት በጻፉት የጌታን ሕማማቱን በሚናገረው መጽሐፍ ላይ ይኽነን ሲገልጹ “ወእምዝ አዕተቱ አልባሲሁ ወአልበስዎ ሜላተ ልብስ…” (ከዚያም ልብሶቹን ገፍፈው የመንግሥት ልብስ የሚኾን ነጭ ሐር የካህናት ልብስ የሚኾን ቀይ ሐር ሕብራቸው ቀይና ጥቁር የሚኾን ልብስ አለበሱት፤ የአጣቢ ሳሙና ማንጻት የማይቻለው እንደ መብረቅ የሚያንጸባርቅ እንደ በረድ የኾነ ነጭ ልብስ የሚለብስ ሲኾን፤ ለኪሩቤል የመብረቅ ልብስን ለሱራፌል ግርማ ያለው ልብስን የሚያለብሳቸው ርሱን እንደዚኽ በምድር በመዘባበት ቀይ ሐርና ነጭ ልብስ አለበሱት) በማለት አስተምረዋል፡፡ ልዑል አምላክ ዘመኑ ሲፈጸም ስለሚቀበላቸው ሕማማተ መስቀል አስቀድሞ በነቢዩ ዳዊት ዐድሮ በመዝ ፳፩፥፲፮ ላይ “ብዙ ውሾች ከብበውኛልና የክፋተኞች ጉባኤም ያዙኝ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ፤ ዐጥንቶቼ ኹሉ ተቈጠሩ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም” በማለት ውሻ ከአፉ ያወጣውን መልሶ ለምግብነት እንዲፈልገው፤ አይሁድም ኦሪትን እለፊ ካላት በኋላ ሲሠሯት በመገኘታቸው በውሻ መስሎ ትንቢት ያናገረባቸው ሲኾን፤ ዳግመኛም ከ፯፻ ዓመት አስቀድሞ በነቢዩ በኢሳይያስም ዐድሮ በምዕ ፶፥፮ ላይ “ዠርባዬን ለግርፋት ጕንጬንም ለጥፊ ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስኹም” በማለት ያናገረው ትንቢት ሊደርስ ሊፈጸም ጌታችንን አይሁድ ገርፈውታል፡፡ አንድም ንጹሐ ባሕርይ ጌታችን መገረፉ ዲያብሎስ የአዳምን ዘባነ ልቡና እየገረፈ ወደ ሲኦል አውርዶት ነበርና ለርሱ ሊክስለት ሲኾን ዳግመኛም በጌታ ላይ አይሁድ የግፍ ድርብ አድርገውበታል በሀገራቸው የሚሰቀል አይገረፍም ነበር በተጨማሪም በኦሪት ልምድ ከአርባ አትርፎ መግረፍ የተከለከለ ሲኾን እነርሱ ግን ፴፱ ጊዜ ከገረፉ በኋላ ቊጥር ተሳሳትን እያሉ ሥጋው ዐልቆ ዐጥንቱ እንደ በረድ ነጭ እስከሚኾን ድረስ ፮ሺሕ ከ፮፻፷፮ ግርፋትን ገርፈው እንደ ብራና ወደዚያና ወደዚኽ ወጥረው ሲሰቅሉት ዐጥንቱ ታይቶ የሚቈጠር ኹኗል፡፡ ቊጥራቸው ከ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት የሚኾን ኤልሳቤጥ፣ መልቴዳ፣ በርዜዳ የሚባሉት በጻፉት የጌታን ሕማማቱን በሚናገረው መጽሐፍ ላይ ይኽነኑ ሲያብራሩ “ወእምድኅረ አሠርዎ ቀሠፍዎ ለእግዚእ ኢየሱስ ጲላጦስ ወአርባዕቱ ሐራ በሐብል ወበአስዋጥ መጠነ ፷፻ ወ፮፻፷፮ … ” (ጌታችን ኢየሱስንም ካሠሩት በኋላ አራት ቤት ጭፍሮችና ጲላጦስ በገመድና ባለንጋ ፮ሺሕ ከ፮፻፷፮ ጊዜ ገረፉት፤ ዐምስት እልፍ ነው የሚሉም አሉ፤ የግርፋቱን ቊጥር እያሳሳቱ ገርፈውታልና፤ የሚሞት እንዳይገረፍ የማይሞት እንዲገረፍ እያወቁ፤ በግፍ ገርፈው በግፍ ገደሉት የተገረፈባቸውም አለንጋና ገመድ በደም ታለሉ፤ ከግርፋቱም ጽናት የተነሣ ሥጋው ኹሉ ዐለቀ፤ ሺሕ ከ፮፻ ከሚኾኑ ቊስሎቹም ወገን ዐጥንቶች ታዩ፤ ጥቁርና ሰማይ የሚመስሉ ቊስሎቹ ግን ሺሕ አንድ መቶ ከዘጠና ናቸው፤ የማይገረፍ አምላክ በዚኽ ሥጋ ተገረፈ፤ ጲላጦስ እጁን ከታጠበ በኋላ ጌታችንን የገረፈው በዦሮ ለሚሰማው በዐይን ለሚያየው ሰው ዕጹብ ድንቅ ነው፤ በመገረፉም አይሁድን ደስ አሰኛቸው፤ ጌታችን ኢየሱስ ግን በመገረፉ ሰው ኹሉ ከተገረፈባት ኀጢአት ፍዳ አዳነን፤ ስለ ልጆቹና ስለ አዳም መገረፍን መታሠርን ከፍሏልና) በማለት ለኹላችን ካሳ ስለተገረፈው ግርፋት አስተምረዋል፡፡ በነቢዩ ኢሳይያስ ላይ ጌታ ዐድሮ በምዕ ፶፥፮ ላይ “ዠርባዬን ለግርፋት ጕንጬንም ለጥፊ ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስኹም” ብሎ ያናገረው ሊደርስ ሊፈጸም ክብር ይግባውና በአምላካችን ፊት ላይ አይሁድ ምራቃቸውን ተፍተውበታል፤ ዳግመኛም ዲያብሎስ ምራቀ ምክሩን እየተፋ ወደ ሲኦል ላወረደው ለአዳም ሊክስለት የማኅበረ አይሁድን ምራቅ ክብር ይግባውና አምላካችን በትዕግሥት ተቀብሎታል፡፡ ይኽ ለካሳ አምላካችን ስለፈጸመው የድኅነት ምስጢር ቅዱሳት ደናግል ሲያብራሩ “አስተቀጸልዎ ከመዝ ለርእሰ ሕይወት አክሊለ ሦክ…” (የሕይወት መገኛ ርሱን የእሾኽ አክሊልን አቀዳጁት፤ መላእክትን የብርሃን ራስ ቁር የሚያቀዳጃቸው የነገሥታት ገዢ የሚኾን ርሱን የሾኽ አክሊል አቀዳጁት፤ በሾኽ አክሊልም ከራሱ ክፍል ያቆሰሉት ሺሕ ናቸው፤ ከራሱም ቊስሎች ደም እንደ ውሃ በዝቶ ፈሰሰ፤ ፊቱም ደምን ለበሰ ሰውነቱም በደም ተጠመቀ፤ የጽዮን ልጆች እናቱ ያቀዳጀችውን አክሊል ተቀዳጅቶ አዩት፤ ተድላ ደስታ የሚያደርግበትና የሙሽርነቱ ቀን ነውና፤ በቀኝ እጁ ዘንግ አስያዙት፤ ሲያሽሟጥጡ በፊቱ እየወደቁ እጅ ነሡለት፤ የመላእክት ሰራዊት እየደነገፁ የሚሰግዱለትን የአይሁድ ንጉሥ ቸር ውለኻል አሉት፤ ሥልጣናትና ሊቃናት እየፈሩ ለሚሰግዱለት ለርሱ በትዕቢት እጅ ነሡት፤ ዐምስት የሚኾኑ መዘባበቻቸውን ከጨረሱ በኋላ በምራቁ ኹለተኛ ዐይኖችን በሚፈጥር በርሱ ፊት ላይ ምራቃቸውን ተፉበት፤ ዳግመኛም ፊቱን በጥፊ መቱት፤ ኪሩቤል ፊቱን ከማየት የተነሣ በእሳት አክናፍ የሚሰወሩት ያልበደላቸውን ርሱን አይሁድ በጥፊ መቱት፤ ፊቱ እንደ መንፈስ ቅዱስና እንደ አባቱ ሲኾን በተዋሐደው ሥጋ ፊቱን ጸፉት ከፊቱ ግርማ የተነሣ ፍጥረቱ ኹሉ የሚርዱለት የሚንቀጠቀጡለት የፈጣሪያቸውን ፊቱን ጸፉት፤ መዠመሪያ በመመታቱና የሾኽ አክሊል በመቀዳጀቱ ራሱ የቈሰለ ከመኾኑም በላይ
Show all...
መንፈሳዊ ጉባኤ: Henok: ❖ ❖ ❖ ጸሎተ ሐሙስ ❖ ❖ ❖ ጸሎተ ሐሙስ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ስያሜ ያለው ነው፡፡ ይህም ምክንያቱ በዕለቱ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ የተገለጠበት ስለሆነ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ይህን በሚዘክር ሁኔታ ታስበዋለች፡፡        ❖ በዚህ ዕለት ምን ተፈጸመ? ❖ √ በዚች ዕለት በአልአዛር ቤት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጡ፡፡ ከኅብስቱ ከፍሎ አማናዊ ሥጋ፤ ከወይኑ ከፍሎ አማናዊ ደም አድርጎ ባርኮ ቀድሶ አክብሮ እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው እንዲህም አለ /ማቴ 26፥26/ በዚህ እለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕብስቱን ቆርሶ ይህ አማናዊ ሥጋዬ ነው ወይኑን ባርኮ ይህ ለሐዲስ ኪዳን ሥርየት የሚፈሰው ደሜ ነው ብሎ ለደቀመዛሙርቱ ሥርዓተ ቁርባንን በተግባር ያስተማረበት ነው፡፡ ይህ ዕለት በቃል ያስተማረውን ትምህርት በተግባር እንዴት መፈጸም እንዳለበት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ ሌላው በዚህ ዕለት የተፈጸመው ተገባር ሕጽበተ እግር ነው፡፡ወንጌሉ እንዲህ ይላል “እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው ሐሳብ ካገባ በኋላ ኢየሱስ ከራት ተነሣ፤ ልብሱንም አኖረ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ የደቀመዛሙርቱን እግር አጠበ፡፡” � /ዮሐ.13፥1-10/ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ሊከላከል ሞከረ፤ ጌታችን እንዲህ አለው “እኔ የማደርገውን አሁን አንተ አታውቅም በኋላ ግን ታስተውለዋለህ አለው” /ዮሐ.13፥10/፡፡ ጴጥሮስ የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም ባለው ጊዜ የጌታችን መልስ ይህ ነበር “ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም” በዚህም ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ደቀ መዛሙርቱን ሥርዓተ ጥምቀት ፈጸመ ሁለተኛ በቃል ያስተማረውን ትኅትና በተግባር ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሮል፡፡ “ከእኔ ተማሩ እኔ የዋሕ በልቤም ትሁት ነኝና” እንዲል /ማቴ. 11፥29/፡፡ ይህንም ሲፈጽም አሳልፎ ሊሰጠው ያለውን የአስቆሮቱን ይሁዳ አላየውም፡፡    √ ሌላው በዚህ ዕለት ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጠው ተናገረ በዚህም ማንነቱን ጭምር ለይቶ ነገራቸው፡፡ እንዲህም ብሎ “እጁን በወጭቱ ያጠለቀው እኔን አሳልፎ የሚሰጥ ነው” በዚህ ዕለትም የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ የተቀበለልን የእኛን ሥጋ የተዋሐደ ፍጹም አምላክ፤ ፍጹም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ነው፤ /ማቴ.26፥36-46፣ ዮሐ.17/     ❖ የዚህ ዕለት ስያሜዎች፦ ❖       ☞  ጸሎተ ሐሙስ ፦ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ይለምን የነበረን ሥጋን የተዋሐደ ፍጹም አምላክ፤ ፍጹም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ነው፤ /ማቴ.26፤36-46፣ ዮሐ.17/ በዚህም ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ እየተባለ ይጠራል፡፡        ☞  ሕጽበተ እግር ፦ ይህ ስያሜ የተሰጠው ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት ነው፡፡ ወንጌሉ እንደሚል “እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው ዐሳብ ካገባ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ከራት ተነሣ፤ ልብሱንም አኖረ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ የደቀመዛሙርቱን እግር አጠበ፡፡”/ማቴ.26፥27/            ☞  የምሥጢር ቀን ፦ በዚች ዕለት በአልአዛር ቤት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጡ፡፡ ከኅብስቱ ከፍሎ አማናዊ ሥጋ፤ ከወይኑ ከፍሎ አማናዊ ደም አድርጎ ባርኮ ቀድሶ አክብሮ እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው እንዲህም አለ /ማቴ 26፥26/ በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕብስቱን ቆርሶ ይህ አማናዊ ሥጋዬ ነው ወይኑን ባርኮ ይህ ለሐዲስ ኪዳን ሥርየት የሚፈሰው ደሜ ነው ብሎ ለደቀመዛሙርቱ ሥርዓተ ቁርባንን በተግባር ያስተማረበት ነው፡፡ ይህ ዕለት በቃል ያስተማረውን ትምህርት በተግባር እንዴት መፈጸም እንዳለበት ያስተማረበት ዕለት በመሆኑ የምሥጢር ቀን ይባላል፡፡       ☞  የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ፦ በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ የሆነውን የሐዲስ ኪዳን መስዋዕት የመሠረተበት ነው፡፡ ቀድሞ የነበረውን መስዋዕተ ኦሪት ሽሮ የሐዲስ ኪዳን ደምና ሥጋውን ፈትቶ ስላቀበላቸው የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡፡ /ሉቃ.22፥20/      ☞  የነጻነት ሐሙስ ፦ በመብል ያጣነውን ክብር በመብል የመለሰበት ዕለት በመሆኑ ጌታችን በሰጠን ሥልጣን ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባርያ ሆኖ መኖር በማብቃቱ የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡፡         ❖ሥርዓተ ጸሎተ ሐሙስ ❖ ☞ በዚህ ዕለት ስግደቱ፣ ጸሎቱ፣ ምንባባቱ እንደተለመደው ይከናወናሉ ለየት ያለው ሥርዓት መንበሩ /ታቦት/ ጥቁር ልብስ ይለብሳል ጸሎተ ዕጣን ይጸለያል ቤተ ክርስቲያኑ በማዕጠንት ይታጠናል፡፡ በዘጠኝ ሰዓት ዲያቆኑ ሁለት ኰስኰስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ ጸሎተ አኮቴት የተባለ የጸሎት ዐይነት ተጸልዮ ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ /በሊቀ ጳጳሱ/ እጅ ተባርኮ የሕጽበተ እግር ሥርዓት ከካህናት እስከ ምእመናን ከወንዶች እስከ ሴቶች በካህኑ አስተናጋጅነት ይከናወናል፡፡ ሥርዓተ ኅጽበቱ የሚከናወነውም በውኃ ብቻ ሳይሆን የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ምስጢሩም ወይራ ጸኑዕ ነው ክርስቶስ ጽኑ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ በተጨማሪ እኛም /የሚያጥበውና የሚታጠበው ክርስቲያን/ መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ነው፡፡ የወይኑ ቅጠል በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ ይሆናቸው ዘንድ መስጠቱን ለማዘከር ነው፡፡ ማቴ 26.26 ይህም ሥርዓት ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለምእመናን ለማሳየት ነው ዮሐ. 13፤14፡፡ በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐፀበ እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ምእመናን ይቀበላሉ፡፡ የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴው የሚከናወነው በተመጠነ ድምፅ ነው፡፡ ደወሉ የጸናጽል ድምጽ ሲሆን በቀስታ ስለሚጮህ ነው፡፡ የድምጽ ማጉያ አይጠቀሙም፡፡ ምክንያቱም ዲያቆኑና ካህኑ ዜማውን በቀስታ የሚሉት ይሁዳ በምስጢር ጌታችንን ማስያዙን ለመጠቆም ሲሆን በሌላ በኩል የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደነበር ለማስታወስ ነው፡፡ በመቀጠል ክቡር ይእቲ፣ ዕጣነ ሞገር ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ ይሰናበታሉ፡፡             ❖  ጉልባን  ❖ ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ በጸሎተ ሐሙስ በቤት ውስጥ ከሚፈጸሙ ተግባራት አንዱ ጉልባን ማዘጋጀት ነው፡፡ ጉልባን እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ በችኮላ መጓዛቸውን የምናስታውስበት ከእስራኤላውያን የመጣ ትውፊታዊ ሥርዓት ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ አብዛኞቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ይህ ሥርዓት ዛሬም በኢትዮጵያውያን ምእመናን ዘንድ ይከበራል፡፡ ጉልባን እስራኤላውያን ከባርነት በወጡ ጊዜ አቡክተው፣ ጋግረው መብላት አለመቻላቸውን ያስታውሰናል፡፡ በወቅቱ ያልቦካውን ሊጥ
Show all...
እየጋገሩ ቂጣ መመገብ፤ ንፍሮ ቀቅለው ስንቅ መያዝ የመንገድ ተግባራቸው ነበርና፡፡ ይህን ታሪክ ለማሰብም በሰሙነ ሕማማት በተለይም በጸሎተ ሐሙስ ቂጣና ጉልባን ይዘጋጃል፡፡ በጸሎተ ሐሙስ የሚዘጋጀው ጉልባንና ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ይኸውም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ዅሉ፣ ጌታችንም በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ ነው፡፡ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ፃማ ወድካም ዓመ ከመ ዮም ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ ለብርሃነ ትንሣኤሁ እግዚአብሔር በፍስሓ ወበሰላም አሜን !!! ያለ ደዌና ያለ ሕማም ያለጥምና ያለ ድካም እግዚአብሔር ለትንሣኤው ብርሃን እንደ ዛሬ ቀን በደስታና በፍቅር በአንድነት ያድርሰን ያድርሳችሁ አሜን !!! የዘመኑን ወረርሽኝ በቸርነቱ ያስታግስልን አሜን!!! ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖ ❖
Show all...