የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን🙏
Open in Telegram
የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና የጠበቁ የነፍስ ስንቅ የምናገኝበት፦ ✍️"ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም" ፩ኛ ቆሮ. ፰፥፪ #ለተጨማሪ፦👇✞👇 https://www.youtube.com/EOTC2921 https://www.facebook.com/eotc2921 https://www.tiktok.com/@eotc2921 https://www.instagram.com/eotc2921
Show more4 374
Subscribers
No data24 hours
No data7 days
No data30 days
Posts Archive
4 374
#ስላሴን_አመስግኑ
*************
ስላሴን አመስግኑ /2/
የምድር ፍጥረታት ዘምሩ እልል በሉ
አ.ዝ----------------------------//
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
ምስጋና ይገባል ከምንም በፊት
ዓለማትን ሁሉ ለፈጠረ ጌታ
ምስጋና ይድረሰው ከጠዋት እስከማታ
አ.ዝ----------------------------//
ኪሩቤል ሱራፌል የሚያመሰግኑት
መላእክት በሰማይ ስሉስ ቅዱስ ያሉት
እኛም የአዳም ልጆች እንዘምራለን
በሰማይ በምድር እንጠራሃለን
አ.ዝ-----------------------//
ብራብ በሥላሴ እጠግባለሁኝ
ብጠማም በአምላኬ እረካለሁኝ
ስላሴ አምባዬ ክብሬ ናቸውና
ሁሌም ይመሩኛል በህይወት ጎዳና
#እሰይ_እሰይ
===========
እሰይ እሰይ ተወለደ
እሰይ እሰይ ተጠመቀ
ከሰማየ ሰማያት ወረደ
ከድንግል ማርያም ተወለደ/4/
አዝ--------------//
እሱ ባይወለድ እሰይ እሰይ
ቸሩ አምላካችን እሰይ እሰይ
እርሱ ባይጠመቅ እሰይ እሰይ
መደኃኒታችን እሰይ እሰይ
መች ትገኝ ነበር እሰይ እሰይ
ገነት ርስታችን እሰይ እሰይ
አዝ--------------//
ብርሃን ወጣላቸው እሰይ እሰይ
በእውነት ወገኖቹ እሰይ እሰይ
በጨለማው ጉዞ እሰይ እሰይ
እንዳይሰላቹ እሰይ እሰይ
አዝ--------------//
እንደ ጠል ወረደ እሰይ እሰይ
ከሰማይ ወደኛ እሰይ እሰይ
ወገኖቹን ሊያድን እሰይ እሰይ
ከክፉ ቁራኛ እሰይ እሰይ
አዝ--------------//
እግዚአብሔር አብ ላከ እሰይ እሰይ
እንድያ ልጁን እሰይ እሰይ
እርሱ ወዷልና እሰይ እሰይ
እንዲሁ አለሙን እሰይ እሰይ
#አጥምቆ_በማይ
==========
አጥምቆ በማይ(3×)
እኧ ዮሀንስ እኧ(3×) እጥምቆ በማይ(2×)
#ሃሌ_ሃሌ_ሉያ
ሃሌ ሃሌ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ /2/
ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ /2/
ሃሌ ሃሌ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ/2/
አምላክ ሆይ ሕዝቦችህ ዳኑ በጥምቀትህ
አምላክ ሆይ ሕዝቦችህ ዳኑ በጥምቀትህ/2/
#በእደ_ዮሐንስ
በእደ ዮሐንስ ተጠምቀ ኢየሱስ ናዝራዊ/2/
ኧኸ ሠማያዊ /5/ ኢየሱስ ናዝራዊ/2/
#ሖረ_ኢየሱስ
ሖረ ኢየሱስ ሖረ ኢየሱስ/2/
እምገሊላ /3/ ኀበ ዮሐንስ/2/
ሔደ ኢየሱስ ሔደ ኢየሱስ/2/
ከገሊላ /3/ ወደ ዮሐንስ/2/
#ወረደ_ወልድ
ወረደ ወልድ/3/
እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት/2/
#ዮሐንስኒ
ዮሐንስኒ ያጠምቅ/2/
በሄኖን/4/ በማዕዶተ ዮርዳኖስ
ዮሐንስ ሲያስተምር ያጠምቅ
በጫካ በሜዳ ያጠምቅ
የበግ ፀጉር ለበሶ ያጠምቅ
ሆኖ ምድረ በዳ ያጠምቅ
አምላኩን የሚወድ ያጠምቅ
ብዙ ሰው እያለ ያጠምቅ
ጌታውን ለማጥመቅ ያጠምቅ
ዮሐንስ ታደለ ያጠምቅ
ተራራው ዝቅ ይበል ያጠምቅ
ጎባጣውም ይቅና ያጠምቅ
ብሎ ያስተማረው ያጠምቅ
ዮሐንስ ነውና ያጠምቅ
ከሐጢያት ተለዩ ያጠምቅ
በውሀ ተጠመቁ ያጠምቅ
መንግስተ ሠማያት ያጠምቅ
እንዳለች እወቁ ያጠምቅ
#እሰይ_እሰይ
===========
እሰይ እሰይ ተወለደ
እሰይ እሰይ ተጠመቀ
ከሰማየ ሰማያት ወረደ
ከድንግል ማርያም ተወለደ/4/
አዝ--------------//
እሱ ባይወለድ እሰይ እሰይ
ቸሩ አምላካችን እሰይ እሰይ
እርሱ ባይጠመቅ እሰይ እሰይ
መደኃኒታችን እሰይ እሰይ
መች ትገኝ ነበር እሰይ እሰይ
ገነት ርስታችን እሰይ እሰይ
አዝ--------------//
ብርሃን ወጣላቸው እሰይ እሰይ
በእውነት ወገኖቹ እሰይ እሰይ
በጨለማው ጉዞ እሰይ እሰይ
እንዳይሰላቹ እሰይ እሰይ
አዝ--------------//
እንደ ጠል ወረደ እሰይ እሰይ
ከሰማይ ወደኛ እሰይ እሰይ
ወገኖቹን ሊያድን እሰይ እሰይ
ከክፉ ቁራኛ እሰይ እሰይ
አዝ--------------//
እግዚአብሔር አብ ላከ እሰይ እሰይ
እንድያ ልጁን እሰይ እሰይ
እርሱ ወዷልና እሰይ እሰይ
እንዲሁ አለሙን እሰይ እሰይ
#ክርስቶስ_ተወልደ
ክርስቶስ ተወልደ እሰይ ክርስቶስ ተጠምቀ በማይ/2/
ወለደነ ዳግመ እምማይ/2/ ዳግመ ዳግመ ወለደነ ዳግመ እምማይ/2/
#የጥምቀት_ወረብ
#ይትባረክ
ይትባረክ እግዚአብሄር
አምላከ/2/ እስራኤል
ዘገብረ አቢየ ወመንክረ
ባይቲቱ እግዚአብሄር
#ጥምቀተ_ባሕር
ጥምቀተ ባሕር ዮርዳኖስ ነያ /2/
ሀሌ ሉያ /4/
ጌታችን ሲጠመቅ ባሕር ምን አለች
አልችለውም ብላ ወደ ኋላ ሸሸች
ብርሃነ መለኮት በወንዙ ሲሞላ
ዮርዳኖስም ሸሸ ሄደ ወደ ኋላ
አብ በመጣ ጊዜ ደመናውን ጭኖ
መንፈስ ቅዱስ ታየ በርግብ አምሳል ሆኖ
ለልጁ ምስክር ሊሆን ፈለገና
ቃሉን ተናገረ ሆኖ በደመና
ጌታችን ሲጠመቅ በ30 ዓመት
ባሕር ኮበለለች ግዑዟ ፍጥረት
ሰማይ ተከፈተ ሆነልን ፀአዳ
ምሥጢረ ሥላሴ ታወቀ ተረዳ
እልል በይ ዮርዳኖስ የጥምቀት መገኛ
የጽድቅ መሰላል የድኅነታችን መገኛ
ቀላያት አብርህት ብዙዎች እያሉ
እንደምን ተመረጥሽ ዮርዳኖስ ከሁሉ
#ሰው_ሆይ_ደስ
ሰው ሆይ ደስ ይበለን በአምላካችን
ከሃጢአት ባርነት ነፃ ባወጣን
ተነሱ እናመስግን ውለታው ብዙ ነው
ምን ይከፈለዋል ተመስገን ብቻ ነው
በሃጢአት በሽታ ወድቄ ሳለሁኝ
መድሃኒት ከርስቶስ ከውድቀቴ አነሳኝ
ስጦታው ብዙ ነው ለእኔ የሰጠኝ
ተመስገን ብቻ ነው አምላክ ለአንተ ያለኝ
አዝ.....
እንደ በርጠሚዎስ ዕውር የነበርኩኝ
ዛሬ ግን በአምላኬ ደህነት አገኘሁኝ
ሕጉ ለመንገዴ ብርሃን ሆኖኛል
የእርሱ ስለሆንኩኝ ሰላሙም ሰጥቶኛል
አዝ.....
በድንቅ አጠራርህ በፍቅር የጠራኸኝ
ከአጋንንት እስራት ነፃ የወጣኸኝ
አልፋና ኦሜጋ ዘላለም የምትኖር
ኤልሻዳይ የሆንከው አማኑኤል ተመስገን
አዝ......
የዕዳ ደብዳቤዬን ጌታዬ የቀደደው
የማዳንህን ሥራ በዓይኔ አይቻለሁ
ቸርነቱ አያልቅም ድንቅ የሆነ ጌታ
ስሙን እናወድስ እንዘምር በእልልታ
አዝ...
#ውስተ_ማኅፀነ_ድንግል
ውስተ ማኅፀነ ድንግል ኀደረ ማኅፀነ
ድንግል/2/
ሰማይ ወምድር ዘኢያገምሮ ሰማይ ወምድር በማይ ተጠመቀ
ትርጉም፡-
ሰማይና ምድር የሟይችሉት አምላክ
በእመቤታችን ማኅፀን አደረ በውኃም
ተጠመቀ
.
.
.
@EOTC2921
@Ethio_Orthodox1
4 374
☞✞ #ቅዱስ_ሚክያስ_ነቢይ ✞☜
✞ ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::
✞ ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27)
✞ ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ:: ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል:: "እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር:: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ::" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)
✞ የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::
✞ ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)
✞ ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: (ማቴ. 13:16, 1ዼጥ. 1:10) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::
✞ ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት 15ቱ አበው ነቢያት: 4ቱ ዐበይት ነቢያት: 12ቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በ4 ይከፈላሉ::
☞✞ #15ቱ_አበው_ነቢያት ማለት:-
*ቅዱስ አዳም አባታችን
*ሴት
*ሔኖስ
*ቃይናን
*መላልኤል
*ያሬድ
*ኄኖክ
*ማቱሳላ
*ላሜሕ
*ኖኅ
*አብርሃም
*ይስሐቅ
*ያዕቆብ
*ሙሴና
*ሳሙኤል ናቸው::
☞✞ #4ቱ_ዐበይት_ነቢያት
*ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
*ቅዱስ ኤርምያስ
*ቅዱስ ሕዝቅኤልና
*ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::
☞✞ #12ቱ_ደቂቀ_ነቢያት
*ቅዱስ ሆሴዕ
*አሞጽ
*ሚክያስ
*ዮናስ
*ናሆም
*አብድዩ
*ሶፎንያስ
*ሐጌ
*ኢዩኤል
*ዕንባቆም
*ዘካርያስና
*ሚልክያስ ናቸው::
☞✞ #ካልአን_ነቢያት ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስና
*ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው::
☞✞ #ነቢያት_በከተማም ይከፈላሉ፦
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል)ና
*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ::
☞✞ #በዘመን_አከፋፈል ደግሞ:-
*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)
*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት):
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::
✞ ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::
☞✞ ቅዱስ ሚክያስ ቁጥሩ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ.ል. ክርስቶስ በ800 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው:: አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ 14 ምዕራፍ: ሲያንስ 1 ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::
✞ ሚክያስ ትውልዱ ከነገደ ብንያም ሲሆን አባቱ ሞራት (ሞሬት) ይባላል:: ሚክያስ ማለት "መኑ ከመ አምላክ-እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው!" ማለት ነው:: አንድም "መልአከ እግዚአብሔር" ማለት ነው:: የአባቶቻችን ሁሉ ስማቸው እግዚአብሔርን የሚሰብክ ነው::
✞ ቅዱሱ ነቢይ ልጅ እያለ መላእክት ያነጋግሩት ነበር:: በዚህ ምክንያት ከሰው አይቀርብም:: ትክ ብለው ሲያዩት በፊቱ ላይ ብርሃን ቦግ ቦግ እያለ ይታይ ነበር:: በወጣትነት ዘመኑ እግዚአብሔር ለትንቢት ሲጠራው በእሺታ ታዘዘ:: በ3ቱ ነገሥታት (በኢዮአታም: አካዝና ሕዝቅያስ) ዘመንም ትንቢቶችን ተናግሯል:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን: ነገሥታቱን አስተምሮ ገስጿል::
✞ አንድ ቀን በቤተ ልሔም ሲያልፍ የዳዊት ከተማ ፈት ሁና: ዳዋ በቅሎባት ቢመለከት አዘነ:: ወዲያውም ትንቢት ተናገረላት::"ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ: ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ: እስመ እምኔኪ ይወጽዕ ንጉሥ::"
(አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም: የይሁዳ ነገሥታት ከነገሡባቸው ከተሞች ከቶ አታንሺም:: ወገኖቼን እሥራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ካንቺ ዘንድ ይወጣልና) አለ::
✞ ይኸውም አልቀረ ለጊዜው ከሚጠት በሁዋላ ደጉ ዘሩባቤል ነግሦባታል:: በፍጻሜው ግን የባሕርይ ንጉሠ ነገሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ተወልዶባታል::
✞ ቅዱስ ሚክያስ ወገኖቹን ሲያስተምርና ሲመራ ኑሮ: 7 ምዕራፎች ያሉትን ሐረገ ትንቢት ተናግሮ: በመልካም ሽምግልና በንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን ዐርፏል:: ወገኖቹም ቀብረውታል:: ጌታም በክብረ ነቢያት ከልሎታል::
✞ አምላከ አበው ቅዱሳን ለተፋቅሮ ይበለን: ከበረከታቸውም ይክፈለን
✞ ጥር 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ
2.ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ
3.አባ እንድራኒቆስ ሊቀ ዻዻሳት
4.አባ ብንያሚን ሊቀ ዻዻሳት
✞ ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
☞✞ ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መስዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጐች: ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? . . . ሰው ሆይ! መልካሙን ነግሮሃል:: እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ: ምሕረትንም ትወድ ዘንድ: ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሔድ ዘንድ አይደለምን? ✞✞✞ (ሚክ. 6:6)
-----፡✞ወስብሐት ለእግዚአብሔር✞፡------
4 374
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን። ✞✞✞
☞✞ #እንኩዋን_ለቅዱሳን_አበው__አባ_መቃርስ__እና__ቅዱስ_ሚክያስ_ነቢይ_ዓመታዊ_በዓል_በሰላም_አደረሳችሁ ✞☜
☞✞ #ታላቁ_ቅዱስ_መቃርስ ✞☜
✞ ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (ቅዱስ መቃሬ) "ጽድቅ እንደ መቃርስ" የተባለለት የመነኮሳት ሁሉ አለቃ: ከ80 ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ: በግብፅ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ: ከ50,000 በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው::
✞ በ4ኛው መቶ ክ/ዘ አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብፅ ወደ እስያ በርሃ ከጉዋደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል:: በዚያ ለ2 ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በሁዋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነ ንጉሳቸው አጥምቀዋል::
✞ በተሰደዱባት ሃገርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ስም አጠራሩ ይክበርና) እመቤታችንን: ቅዱሳን ሐዋርያትን: አዕላፍ መላእክትን: በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን: ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን: ማርቆስን: ዼጥሮስን: ዻውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል:: በቅዱስ አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::
✞ ታላቁ ቅዱስ መቃርስና ባልንጀራው መቃርዮስ ከ2 ዓመታት ስደትና መከራ በሁዋላ ስደት በወጡባት ዕለት መልዐኩ ኪሩብ በክንፉ ተሽክሞ ወደ ግብፅ መልሷቸዋል:: በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከ50,000 በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል::
✞ ቅዱስ መቃርስ ካረፈ በሁዋላ ከክቡር ሥጋው ብዙ ተአምራት ይታዩ ነበርና የሃገሩ (የሳስዊር) ሰዎች ሊወስዱት ፈለጉ:: ሳስዊር ማለት ቅዱሱ ተወልዶ ያደገባት ወላጆቹ (አብርሃምና ሣራ ይባላሉ) የኖሩባት ቦታ ናት:: የምትገኘውም ግብጽ ውስጥ ነው::
✞ በምድረ ግብጽ: በተለይም በገዳመ አስቄጥስ የአባ መቃርስን ያህል ክቡርና ተወዳጅ የለምና የሃገሩ ሰዎች የነበራቸው አማራጭ መስረቅ ነበር:: መሥረቅ ኃጢአት ቢሆንም እነሱ ግን ስለ ፍቅር: አንድም ለበረከት አደረጉት::
✞ ወደ ሳስዊርም ወስደው: ቤተ ክርስቲያን በቅዱሱ ስም አንጸው በክብር አኖሩት:: በዚያም ለመቶዎች ዓመታት ተቀመጠ:: በ7ኛው መቶ ክ/ዘመን ግን ተንባላት (እስላሞች) መጥተው ቤተ ክርስቲያኑን አጠቁ:: በዚህ ጊዜም ሕዝቡ የጻድቁን አጽም ይዘው ሸሹ:: በሌላ ቦታም እንደ ገና በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በዚያ አኖሩት::
✞ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመንፈሳዊ አባታቸውን ሥጋ ያጡት የገዳመ አስቄጥስ ቅዱሳን ያዝኑ ይጸልዩ ነበርና ልመናቸውን ፈጣሪ ሰማ:: አባ ሚካኤል ሊቀ ዻዻሳት በነበረበት ዘመን: ከገዳሙ ለሌላ ተግባር ወደ ሳስዊር የተላኩ አበው ከታላቁ አባት ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ሰውነታቸው ታወከ::
✞ ይዘው ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉ ሊሳካላቸው አልቻለም:: ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ደወል ደውሎ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ ነበርና:: ሕዝቡና ሃገረ ገዢው የሆነውን ሲሰሙ "የቅዱሱን ሥጋ ብትነኩ እንገላቹሃለን" ብለው ሰይፍ: ዱላ: ጐመድና ጦር ይዘው መጡባቸው::
✞ መነኮሳቱ ግን ባዷቸውን ሊመለሱ አልፈቀዱምና ሌሊቱን ሲያለቅሱና ሲጸልዩ አደሩ:: መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜም ታላቁ መቃርስ በግርማ ወርዶ መኮንኑን "ለምን ወደ ልጆቼ እንዳልሔድ ትከለክለኛለህ?" ሲል በራዕይ ተቆጣው:: በዚህ ምክንያትም መነኮሳቱ የቅዱሱን ሥጋ ተቀበሉ::
✞ ሕዝቡም በዝማሬና በማሕኅሌት: ከብዙ እንባ ጋር ሸኟቸው:: ታላቁ መቃሬ ወደ ገዳሙ ሲደርስም ታላቅ ደስታ ተደረገ:: ቅዱሳን ልጆቹ ከመንፈሳዊ አባታቸው ተባርከው በክብር አኑረውታል::
✞ ይህቺ ዕለት ቅዳሴ ቤቱ ስትሆን የተቀደሰችውም በ7ኛው መቶ ክ/ዘ በአባ ብንያሚን እጀ ነው::
4 374
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን ✞✞✞
✞✞✞ #ጥር_7_ሥሉስ_ቅዱስ✞✞✞
✞ ምሥጢራት በእምነት ለማይኖር: በትሕትናም ለማይቀርብ የሚገለጡ አይደሉም::
✞ እግዚአብሔር አንድም ነው: ሦስትም ነው:: ጊዜ ሣይሠፈር ዘመንም ሳይቆጠር እግዚአብሔር በስም: በአካል: በግብር
ሦስትነቱ: በባሕርይ: በሕልውና: በመለኮትና በሥልጣን አንድነቱ የጸና አምላክ ነው::
✞ ከዓለም መፈጠር በፊት ስለ ነበረው ነገር የሚያውቅ ራሱ ሥላሴ ብቻ ነው:: ዓለምን ከፈጠረ በኋላም ምሥጢረ ሥላሴ (መለኮት) ብለን የምንማረው ትምሕርት እንድንና እንጠቀም ዘንድ እርሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ ነው::
✞ ይኼውም በየጊዜው እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ የገለጠው ምሥጢር ነው:: ከዚህ አልፈን
በሥጋዊ አዕምሯችን ጌታን 'እንመርምርሕ' ብንለው ግን ፍጻሜአችን ሞት: ማደሪያችንም ገሃነመ እሳት መሆኑ አይቀርም::
✞ እግዚአብሔር በአንድነቱና ሦስትነቱ ሳለ ይህንን ዓለም ፈጠረ:: እግዚአብሔር ዓለምን ለምን ፈጠረ ቢሉ:- ስሙን ቀድሰን ክብሩን እንድንወርስ ነው:: ከዚህ የተረፈውን ምክንያት ግን ራሱ ባለቤቱ ያውቃል::
✞ በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት): በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት) የሌለበት የዘለዓለም አምላክ: የፍጥረታት ሁሉ
ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው:: አብ: ወልድ: መንፈስ ቅዱስ በስም: በአካል: በግብር ሦስትነት በባሕርይ: በሕልውናና በፈቃድ
አንድነት የጸኑ ናቸው:: በዚህ ጊዜ ተገኙ: በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም:: መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ
ናቸውና::
✞ ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት "ቅድስት ሥላሴ" እንላቸዋለን:: የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም:: የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል:: በቤቱም መጥተው ያድራሉ::
✞ ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም:: አባታችን
ቅዱስ አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል::
✞ አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ: እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ ሥላሴን በድንኳናቸው አስተናገዱ:: አብርሃም
እግራቸውን አጠበ:: (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው:: (ድንቅ
አባት!) ምሳቸውንም አቀረበላቸው:: እንደሚበሉ ሆኑለት:: በዚያው ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት::
✞ ሥላሴን ያስተናገደች ድንኳን (ሐይመት) የድንግል እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት:: በድንግል ላይ አብ
ለአጽንኦ: መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ: ወልድ በተለየ አካሉ ለሥጋዌ በእርሷ ላይ አርፈዋል / አድረዋልና::
✞ በዓለ ሥላሴ በዚህ ቀን የሚከበረው ስለ 2 ምክንያቶች ነው:: ቀዳሚው ሕንጻ ሰናዖርን ማፍረሳቸው ሲሆን 2ኛው
ደግሞ ቅዳሴ ቤታቸው ነው::
✞" #ሕንጻ_ሰናዖር "✞
✞ ሰናዖር ከሺዎች ዓመታት በፊት በአሁኗ ኢራቅ አካባቢ እንደ ነበረ የሚነገርለት ግዛት ሲሆን ስሙ ለሃገሪቱም:
ለንጉሡም በተመሳሳይ ያገለግል ነበር:: ከናምሩድ ክፋት በኋላ ሰናዖርና ወገኖቹ ከሰይጣን ተወዳጁ::
✞ ከጥፋት ውሃ (ከኖኅ ዕረፍት) በኋላ በሥፍራው በአንድነት ይኖሩ ነበርና እርስ በርሳቸው "ኑ ሳንበተን ስማችን የሚጠራበትን ሕንጻ እንሥራ:: በዚያውም አባቶቻችን በውሃ ያጠፋ እግዚአብሔርን እንውጋው" ተባባሉ::
✞ ቀጥለውም ሰማይ ጠቀስ ፎቅን ገነቡ:: ከሕንጻው መርዘም የተነሳ በጸሐይ አብስለው በልተዋል ይባላል:: ቀጥለውም ጦር እያነሱ ፈጣሪን ሊወጉ ወርውረዋል::
✞ መቼም የእነዚህን ሰዎች ክፋትና ቂልነት ስንሰማ ይገርመን ይሆናል:: ግንኮ ዛሬ ሰለጠንኩ በሚለው ዓለም እየተሠራ ያለው ከዚህ የከፋ ነው:: ቸርነቱ ቢጠብቀን እንጂ እንደ ክፋታችንስ ጠፊ ነበርን::
✞ ርሕሩሐን ሥላሴ ግን የሰናዖር ሰዎች የሠሩትን አይተው: ማጥፋት ሲችሉ አላደረጉትም:: የባሪያቸውን የኖኅን ቃል
ኪዳን አስበዋልና:: ይልቁኑ "ንዑ ንረድ ወንክአው ነገሮሙ ለከለዳውያን-ቁዋንቁዋቸው እንደባልቀው" አሉ እንጂ::
✞ ከለዳውያን ልሳናቸው ተደበላልቆ 71 ቋንቋዎች ተፈጠሩ:: እነርሱም ስምምነት አጥተው ተበተኑ:: ሥላሴም ያን ሕንጻ
በነፋስ ትቢያ እንዲሆን በተኑት:: ስለዚህም እስከ ዛሬ ሥፍራው 'ባቢሎን (ዝሩት)' ሲባል ይኖራል::
✞" #ቅዳሴ_ቤት "✞
✞ ልክ የዛሬ 323 ዓመት: አድያም ሰገድ ኢያሱ በኢትዮዽያ በነገሡ በ10ኛው ዓመት: (ማለትም በ1684 ዓ/ም) በጐንደር ከተማ ንግሥተ አድባራት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን
ተሰርታ ተጠናቃለች::
✞ ጥር 7 ቀንም ሊቁ ክፍለ ዮሐንስን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን: ሠራዊት: መሣፍንትና ሊቃውንት ባሉበት ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሯል:: በዕለቱም ታላቅ ሐሴት ተደርጓል:: ኢያሱ አድያም ሰገድ ኃያል: ደግ: ጥበበኛ: አስተዋይ: መናኝ
ንጉሥ ነውና::
✞ ቤተ ሥላሴን አስጊጿታልና ከዚህ ቀን ጀምሮ ጥር ሥላሴ በድምቀት የሚከበር ሆኗል:: ነገር ግን በተሠራች በ16 ዓመቷ ደጉ ኢያሱ ከተገደለ በኋላ ቤተ ክርስቲያኑ በአደጋ ፈርሷል:: ዛሬ የምናየው በ1708 ዓ/ም በልጁ በአፄ
ዳዊት ሣልሳዊ የታነጸውን ነው፡፡
#ጥር_7__ቅድስት_ሥላሴ
☞✞ በዚህች ቀን ቅድስት ሥላሴ በኃጢያት የተገነባውን የሰናኦር ግንብ ያፈረሱበት አንድነታቸውንና ሶስትነታቸውን በግልጽ ያሳዩበት ቀን ነው፤ (ዘፍጥረት 11÷1) እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። እግዚአብሔርም አለ። "ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።" እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፤ ከተማይቱንም መሥራት ተዉ። ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ ይላል።
☞✞ “እግዚአብሔርም አለ” አንድነታቸውን ሲያጠይቅ ኑ እንውረድ ሶስትነታቸውን፤ ሥላሴ በስም አአካል በግብር ሶስት ናቸው፤ የስም ሶስትነታቸው እንደምን ነው ቢሉ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው፤ የግብር ሶስትነታቸውስ እንደምን ነው ቢሉ አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ፤ የአካል ሶስትነታቸውስ እንዴት ነው ቢሉ ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው ለወልድም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ አለው፤ ለመሆኑ የሥላሴ ገጽ አካል ፊት እንደ ሰው ነውን ቢሉ አዎን እንደ ሰው ነው ነገር ግን የሰው ውሱን ጠባብ ፈራሽና በስባሽ ነው የሥላሴ ግን እንዲህ አይደለም በሰማይና በምድር በአየርና በእመቅ የመላ ረቂቅ ህያው ባህርይ ነው ኢሳ 66÷1። የሥላሴ አንድነታቸው በመለኮት በፈቃድ በስልጣን በምክር ወዘተ በመሳሰሉት ነው።
🙏ከበዓሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን🙏
4 374
#የሕይወትን_መዝገብ
የሕይወትን መዝገብ ቃሉን ያስነበቡህ፣
የተዋህዶ አርበኞች ቀዱሳን ዋኖችህ፣
የድካም ዋጋቸው የዕምነታቸው ፍሬ፣
ያማረ ነውና ምስላቸው ዛሬ።
#አዝ
.
.
. ☞ @EOTC2921
☞ @Ethio_Orthodox1
4 374
✞✞✞ #ጻድቅ_ኖኅ ✞✞✞
††† የዚህን ታላቅ ቅዱስ ሰው ክብር የሚያውቅና የሚያከብረው ሁሉ ንዑድ ነው:: አባታችን ኖኅ ዛሬ በዓለም የሚመላለሰው ሰው ሁሉ አባት ነው:: ደግ ጻድቅና ነቢይ ሰው ነው::
ከአባታችን አዳም 10ኛው ጻድቅ ሲሆን ከ15ቱ አበው ነቢያትም አንዱ ነው:: ከአባቱ ከላሜሕ ተወልዶ: በደብር ቅዱስ አድጐ: ንጽሐ መላእክትን ገንዘብ አድርጐ: ለ500 ዓመታት በድንግልና ኑሯል::
በእነዚህ ጊዜያትም አጽመ አዳምን እየጠበቀና መስዋዕትን ለልዑል አምላክ እየሰዋ ያመልክ ነበር:: የሴት ልጆች ከቃየን ልጆች ጋር ተባብረው ዓለም በረከሰች ጊዜም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆኖ ተገኝቷል:: ከሚስቱ (እናታችን) ሐይከል (አምዛራ) ጋር 3 ጊዜ አብሮ አድሮ ሴም: ካምና ያፌትን ወልዷል::
የጥፋት ውኃ በመጣ ጊዜም የእመቤታችን ምሳሌ በሆነች መርከብ ድኗል:: ከመርከብ ወጥቶም ከጌታ ጋር በቀስተ ደመና ምስክርነት ቃል ኪዳን ተጋብቷል:: ከዚያም ዓለምን ለ3 ልጆቹ አካፍሎ ለ350 ዓመታት በበጐ አምልኮ ኑሯል:: በዚህች ቀንም ዕድሜን ጠግቦ በ950 ዓመቱ ዐርፏል::
††† የአባታችን በረከት ይደርብን።
††† ጥር 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.በዓለ ግዝረቱ ለክርስቶስ
2.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
3.ቅዱስ ኖኅ ጻድቅ
4.ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
5.አባ ሙሴ ገዳማዊ
6.አባ ወርክያኖስ
††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
4.ቅድስት ሰሎሜ
5.አባ አርከ ሥሉስ
6.አባ ጽጌ ድንግል
7.ቅድስት አርሴማ ድንግል
††† "እውነት እውነት እላቹሃለሁ:: በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል:: ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል::" †††
(ዮሐ. ፲፬፥፲፪)
††† "ለእስራኤል ሁሉ ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌ በኮሬብ ያዘዝኩትን: የባሪያየን የሙሴን ሕግ አስቡ:: እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላቹሃለሁ:: መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች: የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል::" ††† (ሚል. ፬፥፬)
††† "እግዚአብሔርም:- 'የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ:: ከሰው እስከ እንስሳ: እስከ ተንቀሳቃሽም: እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቼአለሁና' አለ:: ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ::
የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው:: ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ: ፍጹምም ሰው ነበር:: ኖኅ አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ::" †††
(ዘፍ. ፮፥፯)
-----:✞ወስብሐት ለእግዚአብሔር✞:----
4 374
✞✞✞ #ታላቁ_ቅዱስ_ኤልያስ ✞✞✞
††† ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ቀጥላ ቅዱስ ኤልያስን ታከብራለች:: "ርዕሰ ነቢያት - የነቢያት ራስም" ትለዋለች:: እርሱ ሰማይን የለጐመ: እሳትን ያዘነመ: ፍጥረትንም በቃሉ ያዘዘ አባት ነውና::
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ቅዱሱ ትውልዱ (ነገዱ) ኢዮርብዓም ነጥሎ ከወሰዳቸው እሥራኤል (10ሩ ነገድ) ሲሆን አባቱ ኢያስኑዩ : እናቱ ደግሞ ቶና (ቶናህ) ይባላሉ:: በጐ አምልኮ ነበራቸውና እግዚአብሔር ማሕጸነ ቶናህን ቀድሶ ይህንን ቅዱስ ፍሬ ፈጠረ::
ቅዱስ ኤልያስ በተወለደ ቀን በቤታቸው ብርሃን ተሞልቶ ታይቷል:: ብርሃን የለበሱ 4 ሰዎች (መላእክት) መጥተውም በእሳት ሰፋድል (መጐናጸፊያ) ሲጠቀልሉት ወላጆቹ በማየታቸው ደንግጠው ለነቢያትና ለካህናት ነገሯቸው::
ካህናቱ ግን ነገሩ ቢረቅባቸው "ምን ዓይነት ፍጥረት ይሆን? በእሥራኤል ይነግሥ ይሆን! ወይስ ነቢይ ይሆን?" ብለውም አድንቀዋል:: ቅዱስ ኤልያስ ከልጅነቱ ጀምሮ ኮስታራ: ቁም ነገረኛ: ንጽሕናንም የሚወድ እሥራኤላዊ ነው::
ወቅቱ (ከክርስቶስ ልደት 900 ዓመት በፊት) ሕዝቡና ነገሥታቱ የከፉበት: እግዚአብሔር ተክዶ ጣዖት የሚመለክበት ነበር:ድሮ በኢሎፍላውያን እጅ የነበሩት ጣዖታት (ዳጐንና ቤል) በዚያ ዘመን ወደ እሥራኤል ገብተው ነበር::
ቅዱስ ኤልያስ ግን በዚህ ክፉ ትውልድ መካከል ሆኖም ሥርዓተ ኦሪትን የጠነቀቀ: የንጽሕናና የአምልኮ ሰው ነበር::
በዚያ ወራትም እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው:: እርሱም "እሺ" ብሎ ታዝዞ የእግዚአብሔርን የጸጋ ጥሪ ተቀበለ:: ቅዱሱ ብዙ ጊዜ ለጉዳይ ካልሆነ ከሰው ጋር መዋል: ማደርን አይወድምና መኖሪያውን በተራሮችና በዱር አደረገ::
በተለይ ደብረ ቀርሜሎስ ለእርሱ ቤቱ ነበር:: በዚህ ሕይወቱም ከመልከ ጼዴቅ ቀጥሎ:-
1.ለድንግልና (ድንግል ነበርና)
2.ለብሕትውና (ብቸኛ ነበርና)
3.ለምንኩስና (ተሐራሚ ነበርና) በብሉይ ኪዳን መሠረትን የጣለ ነቢይ ይባላል::
መቼም በብሉይ ኪዳን የቅዱስ ኤልያስን: በዘመነ ክርስቶስ የመጥምቁ ዮሐንስን: በዘመነ ሊቃውንት ደግሞ የአፈ ወርቅ ዮሐንስን ያህል ደፋርና መገሥጽ አስተማሪ አልነበረም:: በጊዜው ደግሞ አክአብና ኤልዛቤል የሚባሉ ክፉ ባልና ሚስት በእሥራኤል ላይ ነግሠው ሕዝቡን ጣዖት አስመለኩት::
ይባስ ብለው ደግሞ በወይኑ እርሻ አማካኝነት ኢይዝራኤላዊው ናቡቴን በሐሰት ምስክር ደሙን አፈሰሱት:: ናቡቴም "የአባቶቼን ርስት አልሸጥም: አልለውጥም" በማለቱ እንደ ሰማዕት ይቆጠራል::
ኤልያስ ግን ይህንን ሲሰማ ወደ አክአብና ኤልዛቤል ቀርቦ "የናቡቴ ደም በእናንተ ላይ አይቀርም:: የአንቺንም ደም ውሻ ይልሰዋል" አላቸው:: በዚህ ምክንያትም ኤልዛቤል ልትገድለው ብትፈልገውም እርሱ የእግዚአብሔር ነውና አላገኘችውም::
በዚህ ብስጭትም ይመስላል አንድ ሺህ ነቢያትን ሰብስባ "ፍጇቸው" አለች:: 900ው ሲታረዱ አንድ መቶውን ግን ቅዱስ አብድዩ በዋሻ ውስጥ ደብቆ እየመገበ አተረፋቸው:: በእሥራኤል ውስጥ ግን ዓመጻና ኃጢአት እየተስፋፋ ሔደ:: የእግዚአብሔርን ስጦታ እየተመገበ ሕዝቡ ለቤል (ለበዓል) ሰገደ::
ይህን ጊዜ ግን ቅዱስ ኤልያስ እንዲህ አለ:-
"ሕያው እግዚአብሔር አምላከ ኃይል: ዘቆምኩ ቅድሜሁ: ከመ ኢይረድ ጠል በእላ መዋዕል ዘእንበለ በቃለ አፉየ" ብሎ ዝናም ከሰማይ እንዳይወርድ ከለከለ:: ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ሰማይ ዝናም ለዘር : ጠል ለመከር ከመስጠት ተከለከለ::
ሕዝቡ በኃጢአቱ ምክንያት ተጐዳ:: እርሱን ቁራ ይመግበው: ምንጭ ፈልቆለት ይጠጣ ነበር:: ይሔው ቢቀርበት ጸለየ:: እግዚአብሔርም ከፈለገ ኮራት ወደ ሰራፕታ እንዲወርድ አዘዘው:: በዚያም የነቢዩ ዮናስ እናት እንጐቻ ጋግራ ብታበላው ቤቷ በበረከት ተሞላ::
ልጇ ሕጻኑ ዮናስ ቢሞትም በጸሎቱ አስነሳላት:: ቀጥሎም 7 ጊዜ በትጋት ጸልዮ ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት የዘጋውን ሰማይ ከፍቶታል:: ሕዝቡም ዕለቱኑ ከበረከቱ ቀምሰዋል::
ከዚያ አስቀድሞ ግን ከኤልዛቤል 850 ነቢያተ ሐሰትና ካህናተ ጣዖት ጋር ተወዳድሮ አሸንፏቸዋል:: መስዋዕት ሰውተው የእርሱን ብቻ እሳት ከሰማይ ወርዳ በልታለታለችና ሕዝቡ 850ውን ሐሰተኛ ነቢያት በወንዝ ዳር በሰይፍ መትተዋቸዋል::
ይሕንን የሰማች ኤልዛቤልም ትገድለው ዘንድ አሳደደችው:: "አቤቱ ከአባቶቼ አልበልጥምና ውሰደኝ! ብቻየን ቀርቻለሁና" ብሎ ቢጸልይ እግዚአብሔር ለጣዖት ያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎችን እንዳተረፈ: እርሱንም ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደሚወስደው ብሥራትን ነገረው::
ደክሞት ተኝቶ ሳለም ቅዱስ መልአክ (ሚካኤል) ቀስቅሶ ታየው:: እንጐቻ ባገልግል: ውኃ በመንቀል አቅርቦ "ብላ! ጠጣ!" አለው:: በላ: ጠጣ: ተኛ:: እንደ ገና ቀስቅሶ አበላው:: በ3ኛው ግን "ብላዕ እስከ ትጸግብ እስመ ርሑቅ ፍኖትከ - ጐዳናህ ሩቅ ነውና እስክትጠግብ ብላ" አለው::
ኤልያስም ለ40 ቀናት ያለ ምግብ ተጉዟል:: ከዚያ በኋላም ምድራዊ ሕብስትን አልተመገበም:: እግዚአብሔር አክአብና ኤልዛቤልን ከተበቀላቸው በኋላም ቅዱስ ኤልያስ በክፋተኞች ላይ 2 ጊዜ እሳትን አዝንሟል::
የሚያርግበት ጊዜ ሲደርስም ደቀ መዝሙሩን ኤልሳዕን "የምትሻውን ለምነኝ" ቢለው "እጥፍ መንፈስህን" አለው:: ሦስት ጊዜ ሊያስመልሰው ሞከረ:: ቅዱስ ኤልሳዕ ግን በብርታት ተከተለው:: ዮርዳኖስን ከፍለው ከተሻገሩ በኋላ ግን ቅዱስ ኤልያስን ሠረገላ እሳት ወርዶ ነጠቀው:: ለኤልሳዕም እኩሉን ግምጃውን ጣለለት::
ዛሬ ቅዱስ ኤልያስ በብሔረ ሕያዋን ያለ ሲሆን በዘመነ ሐሳዌ መሲሕ መጥቶ በሰማዕትነት ከቅዱስ ሄኖክ ጋር ያርፋል:: (ራዕይ) ለተጨማሪ ንባብ ( ከ1ነገ. 17-2ነገ. 2 / እና ዕርገተ ኤልያስን ያንብቡ:: ) ✞ነቢዩ ኤልያስ በእውነት ታላቅ ነው!
🙏አምላከ ኤልያስ ለሃገራችንና ለሕዝቧ ርሕራሔውን ይላክልን::🙏
4 374
✞✞✞ #እንኳን_ለታላቁ_ቅዱስ_ባስልዮስ_ዘቂሣርያ__ለታላቁ_ነቢይ_ቅዱስ_ኤልያስ_እና_ለጻድቁ_ቅዱስ_ኖኅ_ዓመታዊ_በዓል_በሰላም_አደረሳችሁ_አደረሰን። ✞✞✞
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
✞✞✞ #ቅዱስ_ባስልዮስ_ዘቂሣርያ ✞✞✞
††† ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ባስልዮስ "አርእስተ ሊቃውንት" ከሚባሉ አባቶች አንዱ ነው:: አባቱ ኤስድሮስ (ባስልዮስ የሚሉም አሉ): እናቱ ደግሞ ኤሚሊያ ይባላሉ:: ባል እና ሚስት ከተቀደሰ ትዳራቸው 5 ወንድና አንዲት ሴት ልጅን አፍርተዋል:: የሚገርመው ሴቷ (ቅድስት ማቅሪና) ገዳማዊት ስትሆን 5ቱም ወንዶች ጳጳሳት መሆናቸው ነው::
የሁሉ የበላይ የሆነው ግን ቅዱስ ባስልዮስ ነው:: አባቶቻችን እንዳስተማሩን ቅዱሱ ሊቅ ከ318ቱ ሊቃውንት አንዱ ነው:: ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊንም ያስተማረው እርሱ ነው:: ነገር ግን ቅርብ ጊዜ ከድረ ገጾች (websites) እየገለበጡ የሚጽፉ አንዳንድ ወንድሞች ይህንን የሚያፋልስ ነገር ጽፈው ተመልክተናል::
ቅዱስ ባስልዮስ ገዳማዊ ጻድቅ: ባለ ብዙ ምሥጢር ሊቅ: የብዙ ምዕመናን አባት: የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት: ባለ ብዙ ተአምራትና ከከዊነ እሳት (ከፍጹምነት) የደረሰ አባት ነው:: ለመጀመሪያ ጊዜ የነዳያንን ሆስፒታል በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ያስገነባ እርሱ ነው::
እጅግ ብዙ ድርሰቶች አሉት:: መጽሐፈ ቅዳሴውንም ዛሬ በምናውቀው መንገድ ያሰናሰለው እርሱ ነው:: ለምዕመናን የሚጠቅሙ ብዙ ሥርዓቶችን ሠርቶ: የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ተርጉሟል:: ታዲያ ይህ ሊቅ: ቅዱስና ጻድቅ ሰው ብዙ ድንቆችን ሠርቷል::
በዘመኑ እዚያው ቂሣርያ ውስጥ አንድ አገልጋይ (በዘመኑ አጠራር ባሪያ) ነበር:: የሚሠራው ደግሞ በሃገረ ገዥው ግቢ ውስጥ ነው:: ለሥራ ሲገባ የሰውየውን አንዲት ብቸኛ ልጅ ተመለከታት:: ቆንጆ ነበረችና በፍትወት ተለከፈ:: ጧት ማታ ሥራው እሷን ማየት ሆነ::
እንዳይጠይቃት ደረጃው አይመጥንምና ከባድ ፍርድ ይጠብቀዋል:: ነገሮች ከአቅሙ በላይ ሲሆኑበት በቀደመ ስሕተቱ ላይ ሌላ ከባድ ስሕተትን ጨመረ:: ወደ ጠንቅዋይ (መተተኛ) ቤት ሒዶ ሥራይ እንዲደረግለት ጠየቀ:: መተተኛው ግን "ይህንን ማድረግ የሚችል ሰይጣን ብቻ ስለሆነ ካልፈራህ ወደ እርሱ ልላክህ" አለው::
ያ ከንቱ ሰው "እሺ" አለ:: መተተኛው ቀጠለ "በል! ሌሊት 6 ሰዓት ሲሆን ወደ አሕዛብ መቃብር ሒድና ግራ እጅህን ወደ ላይ ዘርጋ:: ከዛ ይመጣልሃል" ብሎ ላከው:: አገልጋዩም የተባለውን ሲያደርግ ከአጋንንት አንዱ መጥቶ: ነጥቆ ወደ ጥልቁ: የሰይጣኖች አለቃ ወደ ሚገኝበት ወሰደው::
ጋኔኑ ሰውየውን አለው:- "አንተ የፈለከው እንዲፈጸም መጀመሪያ ክርስትናህን ካድ:: በክርታስም ላይ ክህደትህን ጽፈህ በፊርማህ ስጠኝ" አለው:: ያ ልቡ የታወረ ሰው እንደተባለው መጽሐፈ ክህደቱን ለሰይጣን ሰጠ:: ወዲያው ያ ያመጣው ወደ ቤቱ መለሰው::
በማግስቱ ጠዋት በሃገረ ገዥው ቤት ታላቅ ግርግር ሆነ:: አንዲት ልጃቸው "ያን አገልጋይ ካላጋባችሁኝ ራሴን አጠፋለሁ" አለች:: ቢለምኗትም ልትሰማ አልቻለችም:: ወላጆቿ ግራ ስለተጋቡ ከምትሞት ብለው እያዘኑ ልጃቸውን ከአጋንንት ጋር ለተዛመደ ሰው ሰጡ::
እነርሱ ተጋብተው ኑሯቸውን ቀጠሉ:: ወላጆች ግን የአንድ ልጃቸውን ነገር እንዲህ በዋዛ ሊተውት አልወደዱምና ጾሙ: ጸለዩ: ተማለሉ:: በእንዲህ ሁኔታ ብዙ ዓመታት አለፉ:: ወላጆቿ ግን ተስፋ አልቆረጡምና እግዚአብሔር : ሰይጣን የቀማትን ማስተዋል መለሰላት::
አንድ ቀንም ባሏን ጠርታ "ቤተ ክርስቲያን ተሳልመህ: ቆርበህ : ስመ እግዚአብሔር ጠርተህ: አማትበህስ ታውቃለህ?" አለችው:: እርሱም "በጭራሽ አላውቅም" አላት:: "ለምን" ብትለው የሆነውን ነገር ሁሉ ዘርዝሮ ነገራት:: በጣም ከመደንገጧ የተነሳ ምድር ከዳት::
ለረዥም ሰዓት አለቀሰች:: ከሰይጣን ጋር ተጋብታ የኖረች ያህል ስታስበው አንገፈገፋት:: ሰውነቷ ተስፋ ቆረጠ:: ወዲያው ግን በህሊናዋ አንድ ሐሳብ መጣላት:: "ያ ታላቅ የእግዚአብሔር ሰው ከሰይጣን ባርነት ሊገላግለኝ ይቻለዋል" አለች:: ፈጥናም ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ዘንድ ሒዳ ከእግሩ ሥር ወድቃ አለቀሰች::
እርሱም "ልጄ ሆይ! አይዞሽ: በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ቀላል ነው:: ሒጂና ባልሺን አምጪው" አላት:: ሒዳ አመጣችው:: ቅዱሱም ያን ሰው "መዳን ትፈልጋለህ?" አለው:: ሰውየው መልሶ "ያቺን ደብዳቤ መመለስ የሚቻል ቢሆንማ እፈልግ ነበር" አለው:: ቅዱስ ባስልዮስም ሴቷን "ሒጂና ጸልይ: ከ40 ቀን በኋላ ትመጫለሽ" ብሎ አሰናበታት::
በሰይጣን ባርነት የተያዘውን ያን ሰው ግን ወደ ራሱ በዓት ወስዶ አስገባውና በ4 አቅጣጫ በመስቀል አተመው:: ትንሽ ምግብ ሰጥቶት "ከ3 ቀን በኋላ እመጣለሁ" ብሎት ሔደ:: ቅዱሱ ያለ ዕረፍት ይጋደልም ጀመር:: በ3ኛው ቀን መጥቶ "እንዴት ነህ?" አለው:: "አባቴ! አጋንንት አሰቃዩኝ" አለው:: "አይዞህ!" ብሎት ወጣ::
በ6ኛው ቀን መጥቶ "አሁንስ?" አለው:: "አባ! ስቃዩ ቀረልኝ:: ግን ደብዳቤዋን እያሳዩ ያስፈራሩኛል" አለው:: "በርታ" ብሎት ሔደ:: በ9ኛው ቀን ተመልሶ "ደግሞ አሁንሳ?" አለው:: "አባቴ! ምስጋና ለፈጣሪህ! ከአካባቢው እየራቁ ነው" አለው::
እንዲህ በ3: በ3 ቀናት እየተመላለሰ ለ13 ጊዜ ጠየቀው:: በ39ኛው ቀን መጥቶ "ዛሬ ምን አየህ" ቢለው "አባ! አጋንንትን ከእግርህ በታች ስትረግጣቸው አየሁ" አለው:: ቅዱስ ባስልዮስ በ40ኛው ቀን ደወል ደውሎ መነኮሳት: ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ: ያን ሰው ከመሃል አቁሞ: "እግዚኦ በሉ" አላቸው::
ሕዝቡ እግዚኦታውን ሲፈጽሙ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ:: ቀና ሲሉ ያቺ የክህደት ደብዳቤ ሁሉ እያዩአት ከመካከላቸው ወደቀች:: በዚያች ቦታም ታላቅ እልልታና ሐሴት ተደረገ:: ቅዱሱ በጸሎቱ ለ40 ቀናት ከእንቅልፍና ከምግብ ተከልክሎ ያቺን ነፍስ ማረከ::
የሕዝቡንም ሃይማኖት አጸና:: በዚያውም ቅዳሴ ቀድሶ ሕዝቡን አቁርቦ አሰናበታቸው:: ባልና ሚስቱንም ባርኮ በፍቅር ይኖሩ ዘንድ አሰናበታቸው:: ታላቁ ሊቅም ተጋድሎውን ፈጽሞ ጥር 6 ቀን ዐርፏል::
አምላከ ቅዱስ ባስልዮስ እኛንም ከኃጢአት ማሠሪያ ፈትቶ ከአጋንንት ሤራ ይሰውረን:: ከሊቁም በረከትን ያሳትፈን::
4 374
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞
✞ ጥር 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞
+" በዓለ ግዝረት "+
+'በዓል' ማለት በቁሙ 'ክብር: መታሰቢያ' እንደ ማለት
ነው:: የበዓላት ባለቤት ደግሞ ራሱ እግዚአብሔር ነው::
በመጻሕፍተ ኦሪት እንደ ተቀመጠው ጌታ ምርጦቹን
(ሕዝቡን) ስለ በዓላት አዟል:: ከሰንበት ጀምሮ የፋሲካ:
የእሸት: የዳስ . . . ወዘተ በዓላት በብሉይ ኪዳን ይከበሩ ነበር::
+በእርግጥ አሕዛብም ለጥፋታቸው በዓላትን ሲያከብሩ
ኑረዋል:: ዛሬም ቀጥለዋል:: በዓላት በሐዲስ ኪዳንም
ቀጥለዋል:: የቅዱሳን ሐዋርያትና ሊቃውንትን ቀኖናዎች መሠረት
አድርጋ ቤተ ክርስቲያን በዓላትን ታከብራለች::
+እነዚህም ከጊዜ (ወቅት) አንጻር:-
*የሳምንት
*የወር እና
*የዓመት በዓላት ተብለው ሲታወቁ ከተከባሪዎቹ አንጻር
ደግሞ:-
*የጌታ
*የእመቤታችን እና
*የቅዱሳን ተብለው ይከፈላሉ::
+ጌታ "በዓላትን አክብሩ" ያለን ሥራ እንድንፈታ ሳይሆን
ለአምልኮው እንድንተጋና የጽድቅ ተግባራትን እንድንከውን
ነው:: ስለዚህም በበዓላት መልካም ይሠራል እንጂ ተተኝቶ
አይዋልም:: የጌታችን በዓላቱ 18 ሲሆኑ 9ኙ ዐበይት:
9ኙ ደግሞ ንዑሳን ተብለው ይታወቃሉ:: ሁሉም ለእኛ የድኅንት ሥራ
የተፈጸመባቸው ናቸው::
+የጌታ ዐበይት በዓላቱ:-
1.ጽንሰቱ (ትስብእቱ)
2.ልደቱ
3.ጥምቀቱ
4.ዑደተ ሆሳዕናው
5.ስቅለቱ
6.ትንሳኤው
7.ዕርገቱ
8.በዓለ ዸራቅሊጦስ እና
9.በዓለ ደብረ ታቦር ናቸው::
+ንዑሳን በዓላቱ ደግሞ:-
1.ስብከት
2.ብርሃን
3.ኖላዊ ሔር
4.ጌና
5.ግዝረት
6.በዓቱ (በዓለ ስምዖን)
7.ቃና ዘገሊላ
8.ደብረ ዘይት እና
9.በዓለ መስቀል ተብለው ይታወቃሉ::
+ከእነዚህም አንዱ በዓለ ግዝረት ሁሌ በየዓመቱ ጥር 6
ቀን ይከበራል:: መድኃኒታችን ለእኛ ሲል በተዋሐደው ሥጋ
ማርያም
ሕግን ሁሉ ፈጽሟል:: ራሱ ሠራዔ ሕግ እንደ ሆነው ሁሉ
ፈጻሜ ሕግም ተብሏል::
+ለአብርሃም ባዘዘው (ዘፍ. 17:9) መሠረትም በተወለደ
በ8ኛ ቀኑ ተገዝሯል:: ስሙንም ኢየሱስ (መድኃኒት)
ብለውታል:: (ሉቃ. 2:21) ነገር ግን የተገዘረው እንደ
ፍጡር በምላጭ (በስለት) ሳይሆን በኪነ ጥበቡ ነው::
"ማርያም ግዝር" እንዲሉ አበው:: ልደቱ እንደማይመረመር
ሁሉ ግዝረቱም አይመረመርም::
+ለእኛ ሲል ሁሉን የሆነ መድኃኒታችን ክርስቶስ ለፍቅሩና
ለክብሩ ያብቃን:: ከበረከተ በዓለ ግዝረቱም አይለየን::
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
4 374
#ጥር_5_ልደቱ_ለአቡነ_ገብረ_መንፈስ_ቅዱስ
🌾🌾🌾🙏🙏🙏🌾🌾🌾
❤🌿 አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የተወለዱት ታህሳስ 29 በጌታችን ልደት ነው:: ነገር ግን ዕለቱ ትልቅ ሚስጥርየያዘ ነውና አባቶቻችን የጌታ ልደት ዘምረው ጣዕሙ ሳያልቅ ቅዳሴ ይገባሉ:: ስለዚህ የአባታችን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ከሚቀር ልደታቸው ጥር 5 እንዲከበር ስርዓት ሰርተዋል::
❤🌿"እግዚአብሔር ያፈቅሮሙ ለጻድቃን እግዚአብሔር የዐቅቦሙ ለፈላስያን፡፡“ (እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፡፡)“” መዝ.፻፵፭፡፰ (145፡8)
❤🌿 አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሀገራቸው ንሂሳ ግብጽ ነው፡፡ አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ፡ ይባላሉ፡፡ ልጅ አጥተው 30 ዘመን ሲያዝኑ ኖረዋል፡፡ አንድ ቀን አቅሌሲያ ቤተ እግዚአብሔር ገብታ ከሥዕለ ሥላሴ ሥር ወድቃ ስትማጸን ክብሩ ከሰማይ ከፍታ የሚበጥ ልጅ እንኪ ተቀበይ የሚል ድምጽ ሰማች፡፡ በዚሁ መሰረት አባታችን መጋቢት 29 ተጸንሰው ታህሳስ 29 ተወለዱ፡፡
❤🌿 ዓይን በገለጹ ጊዜ ከሚታይ ነገር ላይ እንዲያርፍ እርሳቸውም በተወለዱ ጊዜ አፈፍ ተነስተው “ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ዘአውጻእከኒ እምጽ ልመት ውስተ ብረሃን” ብለው በማመስገናቸው ኋላም ምድራዊ መብል መጠጥ ሳይመገቡ ሳይጠጡ ለምስጋና ተግተው በመኖራቸው መላዕክትን ይመስላሉ።
❤🌿 ሦስት ዓመት ሲሆናቸው ቅዱስ ገብርኤል ከእመቤታችንና በገነት ካሉ ቅዱሳን ዘንድ አስባርኮ ገዳማውያን ካሉበት አበ ምኔት ወስዶ ከበሩ አኖራቸው፡፡ አባ ዘመደ ብርሃን አሳድጎ አስተምሮ ከመዓርገ ምንኩስና አድርሷቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ “ሀብተ ፈውስ” ተሰቷቸዋል፡፡ በአንድ ቀን እልፍ እውራንንና አንካሳን ፈውሷል፡፡ ኋላ ግን ኤጲስ ቆጶሳቱ ካህናቱ ዝናቸውን ሰምተው እየመጡ የጸሎት ግብር የሚያስፈቷቸው ቢሆን ቅዱስ ገብርኤል በክንፉ ነጥቆ ከጌታ ፊት አቀረባቸው፡፡
❤🌿 በገድልህ በትሩፋትህ ከሞተ ነፍስ ከርደተ ገሃነም የሚድኑ ብዙ ነፍሳት አሉና ከሰው ተለይተህ ወደ ጫካ ግባ፡፡ ኑሮህም ከ60 አናብስተና ከ60 አናምርት ጋር ይሁን አላቸው፡፡ ጌታዬ ምን ተመግበው ይኖራሉ? ብለው ጌታን ጠየቁት፡፡ “ዘኬድከ ጸበለ-እገሪከ ይልህሱ ወበውእቱ ይጸግቡ…” የረገጥከውን ትቢያ ልሰው ያው ምግብ ሆኗቸው ይኖራሉ፡፡ ብሏቸው ውሳጤ ገዳም ገብተው ከአናብስትና አናምርት ጋር ይኖሩ ጀመር።
❤🌿ዳንኤል በአናብስት ጉድጓድ በጣለ ጊዜ አናብርቱ እንደ ድመት ከእግሩ በታች ሆነው እንደተገኙ የረገጡትን ትቢያ ይልሱ ይታዘዟቸውም ነበር፡፡ በዚህ መልኩ መልአኩ 30 ዓመት ከቆዩ በኋላ ጌታ ባንድነት በሦስትነት ተገልጾ “ምን ላድርግልህ ትሻለህ?” አላቸው፡፡ መጀመሪያ ላሉበት መጸለይ ይገባልና የምድረ ጋቦታን ሰዎች ማርልኝ አሉት፡፡ 3000 ኃጥአንን ከሲኦል አውጥቶ ገነት አግብቶላቸዋል።
❤🌿"ሑር ምድረ ኢትዮጵያ ወበህየኒ ሀላዉከ ነፍሳት ዘታወጽኦሙ ወደ ኢትዮጵያ ሂድ” አላቸው፡፡ ቅዱስ ገብርኤል በሰረገላ ነፋስ ጭኖ ምድረ ከብድ አድርሷቸዋል፡፡ ዳግመኛም ወደ ዝቋላ ደብር ቅዱስ ወስዷቸው ከዚያ ሆነው በንጽሐ ልቦና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሃጢአት አይተው ከባሕሩ በራሳቸው ቆመው ይጸልዩ ጀመር፡፡ አርባ ቀን ሲሆናቸው መልአኩ መጥቶ “ዘገብረ ተዝካረከ ወዘጸውዐ ስመከ እምሕር ለከ ብሎሀል” አላቸው፡፡
❤🌿 መላ ኢትዮጵያን ካልማረልኝ አልወጣም ብለው መቶ አመት ሲጸልዩ ኑረዋል፡፡ ከመቶ አመት በዃላ ጌታ “ተንስእ ወጻእ መሐርኩ ለከ ኩሎ ኢትዮጵያ ምሬለሃለሁ ውጣ” ብሏቸው ወጥተዋል። ከዚህ በኋላ ምድረ ከብድ ወርደው ከምድር በላይ ከሰማይ በታች ሆነው ሰባት ዓመት እንደ ትኩል ዓምድ ሆነው ዓይናቸውን ሳይከድኑ ሰባት ዓመት ቆመው ጸልየዋል፡፡
❤🌿 ሰይጣንም በምቀኝነት ተነሳስቶ ቁራን መስሎ መጥቶ አይናቸውን አንቁሮ አሳወራቸው፡፡ ሁለት ሱባኤ ሲፈጽሙ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል መጥተው እፍ ብሏቸው አድነዋቸዋል፡፡ ከዚያ ተነስተው ወደ ዝቋላ ሲሄዱ ሥላሴን በአምሳለ አረጋውያን ከጥላ ስር አርፈው አገኟቸው፡፡ በእግዚአብሔር ዙፋን ተማጽነናል አዝለህ አንድ አንድ ምዕራፍ ሸኘን አሏቸው፡፡ አዝለው ከሸኙአቸው በኋላ በአንድነት በሦስትነት ሆኖ ታያቸው ደንግጠው ወደቁ፡፡
❤🌿አንስተው ዝቋላ ወርደህ ጠላቶችህን ተበቀላቸው አሏቸው፡፡በዘባነ መብረቅ ደርሰው ሰባቱን ሊቃነ መላእክት አጋዥ አርድገው እልፍ አዕላፍ አጋንንትን በማጭድ አጭደዋል፡፡ እንዲህ ለሰሚዕ እፁብ በሆነ ግብር ዓመት በኢትዮጵያ 262 ኖረው በ562 ዓመታቸው በተስፋቸው ያመነውን በኪዳናቸው የተማጸነ ጌታ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ሊምርላቸው ተስፋቸውን ተቀብለው በዕለተ እሁድ ዐርፈዋል።
❤🌿መላእክት በአክናፈ እሳት ኢየሩሳሌም ወስደው በየማነ ምስዋዕ ቀብረዋቸዋል፡፡ ሮሜ 12፡12፣ 15፡30፣ያዕ5፡16፣ መዝ.88፡3፣111፡6 ምሳ 10፡7 ማቴ10፡40-42 ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በቅዱስ ላሊበላ ዘመነ መንግስት መሆኑ ስለሚታወቅ ከ9- 14ኛው ም/ዓ ድ/ል/ክ መሆኑ ነው
4 374
#ጥር_4_የቅዱስ_ዮሐንስ_ወንጌላዊ_ዓመታዊ_በዓል
🌾🌾🌾🙏🙏🙏🌾🌾🌾
❖ የወንጌላዊ ዮሐንስ ድንቅ ታሪክን አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ለዮሐንስ
በደረሰለት ውዳሴ እንዲኽ እጀምራለኊ፡- “ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ኮከበ
ሰመይናከ ፀሓየ ጽድቅ ዘሐፀነከ ውስተ ሕፅኑ ዘአርፈቀከ ኮከበ ሰመይናከ፡፡
በአፉሁ ዘሰዐመከ ወበቅናቱ ዘአቅነተከ ኮከበ ሰመይናከ፡፡ ኅቡአቲሁ ዘአርአየከ
ወንጌለ ጸጋሁ ዘአወፈየከ ኮከበ ሰመይናከ፡፡ ዮሐንስ መኑ ከማከ አስተምህር ለነ ሰአልናከ”
(ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ኮከብን ብለን ጠራንኽ፤ የጽድቅ ፀሓይ ያሳደገኽ
ባጠገቡ (በጉያውም) ያስቀመጠኽ ኮከብን ብለን ጠራንኽ፡፡ በአፉ የሳመኽ
በመታጠቂውም ያስታጠቀኽ ኮከብን ብለን ጠራንኽ፡፡ የተሰወረውን ምስጢር
ያሳየኽ የጸጋውን ወንጌል የሰጠኽ ኮከብን ብለን ጠራንኽ፡፡ ዮሐንስ እንዳንተ ያለ ማን ነው ታማልደን ዘንድ ማለድንኽ)
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በዚኽ ክፍል ላይ ተጋድሎው፣ ሕይወቱ፣ እንደ
ኮከብ የደመቀውን ዮሐንስን አመስግኖታል፤ ይኽ ዮሐንስ ቊጥሩ ከ፲፪ቱ ሐዋርያት መኻከል ኾኖ የዘብዴዎስ እና የሰሎሜ ልጅ ሲኾን በእኛ ትውፊት እናቱን ማርያም ባውፍልያ ይላታል። ጌታችን ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በታንኳ መረባቸውን ሲያበጁ አየ፤ ጠራቸውም እነርሱም ወዲያው ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከትለውታል (ማቴ ፬፥፳፩-፳፪) ጌታም ኹለቱን ወንድማማቾችን ቦአኔርጌስ ብሏቸዋል፤ ትርጓሜውም የነጐድጓድ ልጆች ማለት ነው (ማር ፫፥፲፯)።
ጌታችን ምስጢረ መንግሥትን ለመግለጽ ወደ ታቦር ተራራ ይዞት ወጥቷል፤
በጌቴሴማኒም ምስጢረ ጸሎትን ሲያሳይ ከጌታ ጋር ነበርና "የምስጢር ሐዋርያ"
ይባላል። ጌታችን ይወድደው የነበረው ደቀ መዝሙር ርሱ ነውና "ፍቁረ እግዚእ" (የጌታ ወዳጅ) ሲባል በምሴተ ኀሙስም ምስጢረ ቊርባንን ሲመሠርት ከጐኑ
የተጠቀመጠው ርሱ ዮሐንስ ነበርና ሊቁ፡-
“የጽድቅ ፀሓይ ያሳደገኽ ባጠገቡ ያስቀመጠኽ” ብሎታል፡፡ ጌታችን ሲጠራው የ25 ዓመት ወጣት እንደ ነበር ሄሬኔዎስ የተባለ ደቀ መዝሙሩ ጽፏል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “Pillars of the Church- አዕማደ ቤተ ክርስቲያን” ብሎ ከሚጠራቸው ሐዋርያት አንዱ ዮሐንስ ነው (ገላ 2፥9)፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈ ወርቅና አውግስጢኖስ ስለ ዮሐንስ ሲመሰክሩ፡- “ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን እስከ መስቀል ድረስ የተከተለ ብቸኛ ሐዋርያ ነውና ጌታም ዮሐንስ ካሳየው ፍቅር ከ100 (መቶ) ዕጥፍ በላይ እናቱን እናት አድርጎ ሰጠው፡፡ ምንኛ የታደለ ሐዋርያ ነው?” ይላሉ፡፡ (ዮሐ.19፡20-27)፡፡
ጌታችን በጸሎተ ኀሙስ ለደቀ መዝሙርቱ ትሕትናን ሊያስተምር ከእራት በኋላ ተነሥቶ ልብሱን አኑሮ “ወነሥአ መክፌ ዘለንጽ ወቀነተ ሐቌሁ” ይላል ዘርፍ
ያላት ዝናር አንሥቶ ወገቡን ታጠቀ ሥራ የምታሠራ የምታስጌጥ ስትኾን ኢዮአብ
ወደ ሰልፍ ሲገባ እየለበሳት ይገባ እንደነበረች ያለች ናት፤ ልብሰ መንድያ ይላታል በሺሕ ዘሓ (ድር) የተሠራች ናት፤ “ወወደየ ማየ ውስተ ንብቲራ ወአኀዘ ይሕጽብ እገሪሆሙ ለአርዳኢሁ ወመዝመዘ በውእቱ መክፌ ዘቀነተ” (በመታጠቢያው ውሃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ
ሊያብስ ዠመረ) ይላል፤ ይኽቺ የታጠቀበትን ለዮሐንስ ወንጌላዊ ሰጥቶት ጌታ በታጠቀበት ቢታጠቅ ሕገ ሥጋ ጠፍቶለታል ፍቁረ እግዚእ ያሰኘው ይኽ ነውና
ሊቁ፡- “በመታጠቂውም ያስታጠቀኽ” በማለት አመስግኗል፡፡ “በአፉ የሳመኽ” ማለቱ የሮሙ ንጉሥ ጢባርዮስ ቄሳር የጌታን ነገር አይሁድ በግፍ፣ ጠልተው፣ተመቅኝተው ሰቅለውት እንደሞተ፣ እንደተነሣ፣ እንዳረገ ሰምቶ
የጌታዬን እናት ማን ባመጣልኝ እኔ ቋሚ ለጓሚ፤ ሚስቴ ገረድ ደንገጥር በኾንላት
ብሎ ተመኘ፤ ተመኝቶም አልቀረ “ወለአከ ኢየሩሳሌም ሰራዊተ ወሐራ ወአዋልደ
ብዙኃተ ወኅጽዋነ” ይላል ወደ ኢየሩሳሌም ብዙ ደንገጥሮች፣ ሰራዊትና ጭፍራ እንደዚኹም የሴት ደናግልና ባለሟሎችን በክብር አጅበው ያመጧት ዘንድ ላከ። ጌታም የእናቱን ተድላ ነፍስ እንጂ ተድላ ሥጋን አይሻምና “ወይቤላ ኦ
ወላዲትየ ተንሥኢ ቁሚ ከመ እንሣእኪ ኀበ ዕረፍት ሰማያዊ ከመ ትርአዪ
ዘመንክር ውዳሴ ዚኣየ ዘይትሌዐል እመንግሥተ ኲሉ ዓለም” (እናቴ ሆይ ከዚኽ ዓለም መንግሥት ክብር የሚበልጥና የሚያስደንቅ የጌትነቴን ክብር ታዪ ዘንድ በጎ ዕረፍት ወዳለበት ወደ ሰማይ አሳርግሽ ዘንድ ተነሥተሸ ቁሚ አላት)፤ ከዚያም ወደ ገነት አግብቶ በገነት ላሉ ነፍሳት “ዛቲ ይእቲ መድኀኒትክሙ ኪያሃ ሰብሑ” (መድኀኒታችኊ እነኋት ርሷን አመስግኑ) ብሏቸው አመስግነዋታል፡፡ በርሱም ሐዘን እንዳይጸናበት ዮሐንስ ወንጌላዊን ላከለት፣ ከዚያም ንጉሡን ስለ ጌታችን ሥጋዌ አስተማረው፤ ንጉሡም “ንግረኒ ዘከመ ሰቀልዎ ወእመሰ ትክል ገቢረ ግበር ሊተ ሥዕሎ ዘከመ ርኢከ እንዘ ሀሎ ዲበ ዕፀ መስቀል” (የሚቻልኽም ከኾነ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንዳየኸው ሥዕሉን ሥለኽ አሳየኝ) አለው፤ ዮሐንስም ንጉሥ ሆይ እሺ በርሱ ላይ የተፈጸመውን ኹሉ ሥዬ አሳይኻለኊ አለው፤ ከዚያም ዮሐንስ በዕለተ ዐርብ ጌታን እንደሰቀሉት
አድርጎ ሣለው። “ወሶበ ፈጸመ ብጹዕ ዮሐንስ ሥዕሎ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ አትሐተ ርእሶ ታሕተ ወሰዐመ ሥዕለ ወልደ እግዚአብሔር ወጠግዐ ከናፍረ ሥዕል ምስለ ከናፍረ ብፁዕ ዮሐንስ ጉንዱየ ሰዓተ በይእቲ ዕለት” (ብፁዕ ዮሐንስም የጌታችንን
የኢየሱስ ክርስቶስን ሥዕል ሠርቶ ከፈጸመ በኋላ ራሱን ወደታች ዝቅ አድርጎ
የሕያው እግዚአብሔርን ልጅ ሥዕል ተሳለመ፤ በዚችም ዕለት የዚኽ ሥዕል ከናፍር ከብፁዕ ዮሐንስ ከናፍር ጋር ለብዙ ሰዓት ተያይዞ ቆየ) ይኽም ጽንዐ ፍቅራቸውን ለማጠየቅ ነው፡፡ “ወውእተ ጊዜ ጸርሐ ሥዕለ መድኅን ንጉሥኒ እንዘ ይሰምዕ ወኲሉ አሐዱ አሐዱ እምእለ ይቀውሙ ይሰምዕ አንዘ ይጸርሕ ሥዕል ወይብል ዮሐንስ ዮሐንስ ፍቁርየ” ይላል በዚያን ጊዜ የመድኅን ጌታ ሥዕል ንጉሥና በዚያም የቆሙ ኹሉ እያንዳዳንዳቸው እየሰሙት ወዳጄ ዮሐንስ ዮሐንስ እያለ ድምፅ አሰምቷልና ሊቁ
አባ ጊዮርጊስ ይኽነን ተናገረ፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ በዚኽ መጽሐፉ ላይ፡- “ኅቡአቲሁ ዘአርአየከ ወንጌለ ጸጋሁ ዘአወፈየከ” (የተሰወረውን ምስጢር
ያሳየኽ የጸጋውን ወንጌል የሰጠኽ ኮከብን ብለን ጠራንኽ) በማለት ለዮሐንስ
የተገለጸለትን ሰማያዊ ምስጢር ተናግሯል። ይኸውም ቅዱስ ዮሐንስ ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሐ ልቡና ተሰጥቶት ሰማያዊ የአንድነት የሦስትነት ምስጢር ተገልጾለት፡- “በመዠመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ይኽ
በመዠመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” እያለ ወንጌሉን ሲጽፍ መልአኩ
ከውቅያኖስ አስኳሉ በወጣለት እንቊላል እየቀዳ ውሃውን ሲያፈስስ አየው። ዮሐንስም በአድናቆት ኾኖ “ምን ያደርግልኻል” ብሎ መልአኩን ጠየቀው፤
“ይኽነን ውሃ በዚኽ እየቀዳኊ አፍስሼ ለማድረቅ ነው” አለው፤ ዮሐንስም
“ያልቅልኻልን” አለው፤ መልአኩም “ይኽስ ፍጡር ነው ቁም ነገር የለውም ይፈጸማል፤ አንተስ የማይፈጸመውን ባሕርየ እግዚአብሔርን እፈጽማለኊ ብለኽ ጀምረኽ የለም” አለው፤ ያን ጊዜ ዮሐንስ፡- “ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ” በማለት ወንጌሉን መጻፍ ጀምሯል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ከወንጌል በተጨማሪ ሦስት መልእክታትን ሲጽፍ፤ በ፺፰ ዓ.ም በፍጥሞ ደሴት ሳለ የዓለም ፍጻሜ ነገር ተገልጾለት ራእዩን ከጻፈ በኋላ ጥር 4 እንደተሰወረ ይነገራል፤
🙏የቅዱስ ዮሐንስ በረከት አብዝቶ ይደርብን!!!🙏ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
