en
Feedback

Don't get caught by a cheater! Telemetrio finds and tags such channels 👉 If you want to see the tag, subscribe

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

✟...ገድለ ቅዱስን...✟

Open in Telegram

" ዝምታ ሃይማኖትን ትጠብቃለች ምግባርም ወደ ሰማያት ታወጣለች "

Show more
1 027
Subscribers
No data24 hours
No data7 days
-1330 days
Posts Archive
+በመጨረሻ ግን አባቱ በምልክት ለይቶት አለቀሰ:: "ልጄ! አንተ ለእኔ አባቴ ነህ" ብሎታል:: አበው መነኮሳትም ተሰብስበው እጅ ነስተውታል:: በ7 ዓመቱ የመነነው አባ ዘካርያስ በ52 ዓመቱ በዚህች ቀን ዐርፎ በክብር ተቀብሯል:: =>አምላከ አፈ ወርቅ ዮሐንስ የድንግል እመ ብርሃንን ፍቅሯንና ውዳሴዋን ይግለጽልን:: ከአባቶቻችን ክብርና በረከትንም ያሳትፈን:: =>ጥቅምት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ 2.አባ ዘካርያስ ገዳማዊ 3.አባ ማርዳሪ ጻድቅ 4.ቅዱስ አብጥማዎስ ሰማዕት =>ወርኀዊ በዓላት 1.እግዚአብሔር አብ 2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት 3."99ኙ" ነገደ መላዕክት 4.ቅዱስ አስከናፍር 5."13ቱ" ግኁሳን አባቶች 6.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ 7.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ =>+"+ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም:: መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያናሩታል:: በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል:: መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ:: +"+ (ማቴ. 5:13-16) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ ጥቅምት ፲፫ (13) ❖ ✞✞✞ እንኩዋን ለዓለም ሁሉ መምሕር "ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ" እና ለአባ "ዘካርያስ ገዳማዊ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞ +"+ ዮሐንስ አፈ ወርቅ +"+ =>ለቤተ ክርስቲያን የብርሃን ምሰሶ ስለሆነላት ስለ ታላቁ ሐዋርያዊ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? እንደ እኔ ያለ ኃጥእ: ለባሴ ሥጋና ገባሬ ንስሃ ስለሱ ሊናገር አይቻለውምና:: አባቶቻችን እንደ ነገሩን ስለ አፈ ወርቅ ለመናገር "አፈ ወርቅ" መሆን ያስፈልጋል:: እስኪ በቅዱሱ አባት ምልጃ ጥቂት ልሞክር:: +ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ማን ነው? =>ነገዱ ከሶርያ: የተወለደው በ347 ዓ/ም በእስክንድርያ ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ:: እነርሱ ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው:: ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምሕርትና በጥበብ አደገ:: ገና በሕጻንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና) ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል:: +ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም አንዱ ይሔው ነው:: በዘመናዊም ሆነ በመንፈሳዊ ትምሕርት ይህ ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በ15 ዓመቱ ነበር:: በ2 ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኩዋን በሕይወተ ሥጋ እያለ ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው:: +ቅዱሱ ገና በ16 ዓመቱ ሃብት: ንብረት: ውበት: ክብርና እውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ ጋር በርሃ ገባ:: ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበርሃ ሲኖር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ወደ እርሱ መጡ:: ሊቀ ሐዋርያት የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ ስልጣን ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት:: +ከዚህች እለት በሁዋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ ምስጢራት ሆነ:: ብሉይ ከሐዲስ: ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራዕየ ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጉዋሜ ተነተናቸው:: በተለይ ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው:: ቅዱስ ሕሊናው ሳይታክት: ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት: መልዕክታትና ትርጉዋሜያት ቢቆጠሩ አሥር ሺህ ሞሉ:: በእውነት ለዚህ አንክሮ ይገባል! የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሰራ እድሜው ገና ለጋ: ማዕርጉም ዲቁና ነበር:: +ከዚህ በሁዋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ:: በቅድስናው ወደውታልና የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት:: አፈ ወርቅ ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኩዋን የሚያወራ ኮሽ የሚል የለም:: ከጣዕመ ትምሕርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር:: ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት ተሰብስበው ያደንቁት ነበር:: አንዴም እመቤታችን በሕዝብ መካከል "አፈ ወርቅ" ብላ ጠርታዋለች:: ለዛም ነው "አፈ ወርቅ" የሚባለው:: ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልዐከ ሞትን ገስፆ 10 ዓመት አቁሞታል:: +ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም:: በርሱ ዘንድ ንጉሥና ደሃ ነዳይ እኩል ነው:: ለሞት ያበቃውም ይሔው ነበር:: ምክንያቱም የወቅቱ ንግስት አውዶክስያ ያንዲት ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ "አልመልስም" በማለቷ መክሮ አወገዛት:: እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ 2 ጊዜ አጋዘችው:: በተሰደደበት ሃገር ፍሬ አፍርቶ: አስተምሮና አሳምኖ በ407 ዓ/ም አርፏል:: ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት እንደናፈቁት በ60 ዓመቱ አጡት:: በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ:: =>ከዕረፍቱ አስቀድሞ አንድ ቀን የዘመኑ ደግ ንጉሥ አርቃድዮስ ግብር አገባ:: (ግብዣ አዘጋጀ) በዚያች ሌሊት ደግሞ ቅዱሱ ሊቅ ታጥቆ ሲጸልይ ሳለ: አባ ማርዳሪ የሚባል ጻድቅ ደግሞ ከሰማይ 12ቱ ሊቃነ መላእክት (እነ ቅዱስ ሚካኤል) ከሰማይ በግርማ ሲወርዱ ተመለከተ:: +ደንግጦ "ወዴት ናችሁ ጌቶቼ" ቢላቸው "ቁስጥንጥንያ: ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንሔዳለን:: እርሱ እመቤታችንን እንደሚያመሰግናት ጌታ ነግሮናልና" አሉት:: "እባካችሁ እኔም የአፈ ወርቅ ምስጋናው እንገለጥልኝ መርቁኝ" አላቸው:: ሊቃነ መላእክቱም መርቀውት ጐዳናቸውን ቀጠሉ:: +በማግስቱ በቤተ መንግስት ውስጥ ሊቃውንቱ: መሳፍንቱ: ዻዻሳቱ: ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ከድግሱ በሉ:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ግን በመንበሩ ተቀምጦ ነበር እንጂ አልበላም:: ድግሱ ሲጠናቀቅ ንጉሡ አርቃድዮስ ሊቁን "ጥያቄ አለኝ" ብሎ በጉባኤ መካከል ጠየቀው:: +"ምነው ወንጌላዊ ማቴዎስ 'ኢያዕመራ ዮሴፍ እስከ አመ ወለደት ወለደ ዘበኩራ-የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም' ማለቱ (ማቴ. 1:25) ስለ ምን ነው?" ቢለው ቅዱሱ ተነስቶ: በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይተረጉምለት ጀመር:: +"ድንግል ማርያም ንጹሕ ብርሌን ትመስላለች:: ብርሌ የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ቢያስገቡበት ቀለሙ አብሮ ይቀያየራል:: እመቤታችንም ጌታን ጸንሳለችና ሕብረ መለኮቱ ሲለዋወጥ መልኩዋ አብሮ ሲለዋወጥ እያየ ዮሴፍ ይደነግጥ ነበር:: +'እርሷ ማን ናት? በማሕጸኗ ያለውስ ማን ነው?' እያለ ይጨነቅ ነበር:: ጌታን ከወለደች በሁዋላ ግን አንድ ሕብረ መልክ ሆናለችና:: አስቀድሞ ማን እንደ ነበረች አላወቀም:: +አሁን ግን ልጇ አምላክ ዘበአማን: እርሷም ወላዲተ አምላክ መሆኗን አወቀ ማለት ነው" እያለ ሲተረጉም ሰምተው ሁሉም ሲያደንቁ በዚያ የነበረች ስዕለ አድኅኖ "አፈ ወርቅ! ልሳነ ወርቅ! አፈ በረከት!" ስትል ተናገረች:: +ያን ጊዜ አርቃድዮስ የወርቅ ልሳን በሊቁና በስዕሏ ላይ አደረገ:: አፈ ወርቅ ግን ባጭር ታጥቆ "እሰግድ ለኪ! እሰግድ ለኪ! ወእዌድሰኪ . . ." ብሎ ዛሬ በተአምረ ማርያም የምናውቀውን ምስጋና ሰተት አድርጐ አደረሰላት:: ይህንን ምስጋናም ሊቃነ መላእክቱ ሰምተው እያደነቁ ወደ ሰማይ ወጥተዋል:: =>ቅዱሱ ሲጠራ እንዲሕ ነው:- ¤ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ¤አፈ በረከት ¤አፈ መዐር (ማር) ¤አፈ ሶከር (ስኩዋር) ¤አፈ አፈው (ሽቱ) ¤ልሳነ ወርቅ ¤የዓለም ሁሉ መምሕር ¤ርዕሰ ሊቃውንት ¤ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ) ¤ሐዲስ ዳንኤል ¤ሊቀ ዻዻሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው) ¤መምሕር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ ¤ጥዑመ ቃል - - - +"+ አባ ዘካርያስ ገዳማዊ +"+ =>ይህ ታላቅ ጻድቅ ባለ ጥዑም ዜና ነው:: ወላጆቹ እሱንና አንዲት ሴትን ከወለዱ በሁዋላ አባቱ መንኖ ገዳም ገባ:: ከዘመናት በሁዋላ ረሃብ በሃገሩ ሲገባ እናቱ ወስዳ ለአባቱ ሰጠችው:: ይህን ጊዜ ዕድሜው 7 ዓመት ነበር:: +በገዳም ከአባቱ ጋር ሲኖር ከመልኩ ማማር የተነሳ አባቶች መነኮሳት "ይህ ልጅ ይህን መልክ ይዞ እንዴት መናኝ መሆን ይችላል!" ሲሉ ሰማ:: በሌሊትም ተነስቶ በሕጻን አንደበቱ "ጌታየ! መልኬ ካንተ ፍቅር ከሚለየኝ መልኬን አጠፋዋለሁ" አለ:: ከገዳሙም ጠፋ:: +አባትም በጣም አዘነ:: ከ40 ቀናት በሁዋላ ግን ሊያዩት የሚያሰቅቅ: አካሉ ሁሉ የቆሳሰለ አንድ ነዳይ ሕጻን መጥቶ ወደ ገዳሙ ተጠጋ:: ይህ ሕጻን በጾም: በጸሎትና በትሕትና ተጠምዶ ለ45 ዓመታት አገለገለ:: +በነዚህ ዓመታት ሁሉ ይህ አካሉ የተለወጠ ሕጻን ቅዱስ ዘካርያስ መሆኑን ያወቀ የለም:: እንዲህ የቆሰለውም አሲድነት ካለው የጉድጉዋድ ውሃ ውስጥ ሰጥሞ ለ40 ቀናት በመጸለዩ ነው::

=>አምላከ ዳዊት ፍቅሩን: አምላከ ማቴዎስ አገልግሎቱን: አምላከ ድሜጥሮስ ንጽሕናውን ያሳድርብን:: ጸጋ በረከታቸውን ደግሞ ያትረፍርፍልን::=>ጥቅምት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ (የነገሠበት) 2.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ 3.ቅዱስ ድሜጥሮስ ሊቅ 4.ቅድስት ልዕልተ ወይን 5.ቅዱስ ሳሙኤል ነቢይ 6.ጻድቃን ዼጥሮስ ወዻውሎስ =>ወርሐዊ በዓላት 1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት 2.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ) 3.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ 4.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት) 5.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ 6.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ =>+"+ ከሕዝቤም የተመረጠውን ከፍ ከፍ አደረግሁ:: ባሪያየን ዳዊትን አገኘሁት:: ቅዱስ ዘይትም ቀባሁት:: እጄም ትረዳዋለች:: ክንዴም ታጸናዋለች:: ጠላት በእርሱ ላይ አይጠቀምም:: የዓመጻ ልጅም መከራ አይጨምርበትም:: ጠላቶቹን ከፊቱ አጠፋለሁ:: የሚጠሉትንም አዋርዳቸዋለሁ:: +"+ (መዝ. 88:20) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ ጥቅምት ፲፪ (12) ❖ ✞✞✞ እንኩዋን ለልበ አምላክ "ቅዱስ ዳዊት": ለቅዱስ "ማቴዎስ ሐዋርያ" እና ለቅዱስ "ድሜጥሮስ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞ +*" ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ "*+ =>ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- "እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ: አይጸጸትም::" (መዝ. 131:11) አሁን በእግዚአብሔር መጸጸት ኑሮበት አይደለም:: ቅዱስ ዳዊት የማያጸጽት ፍጹም ወዳጅ መሆኑን ሲገልጥ ነው እንጂ:: ጌታ ቅዱስ ዳዊትን "እንደ ልቤ የሆነ: ፈቃዴን የሚፈጽም: ባሪያየን ዳዊትን አገኘሁት" (መዝ. 88:19) ብሎ ሲናገር ሰምተን እጅግ አደነቅን:: +እንደ አምላክ ልብ ሆኖ መገኘት ምን ይረቅ?! ምንስ ይደንቅ?! ለዚህ አንክሮ ይገባል !! ጌታ ይቀጥልና ደግሞ "ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ" (መዝ. 88:35) ይላል:: *" አቤት አባታችን ዳዊት!!! . . . ክብር: የክብር ክብር: ውዳሴና ስግደትም ላንተ በጸጋ ይገባል "* እንላለን:: +ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ዳዊት 7 ሃብታት ሲኖሩት:- 1.ሃብተ ትንቢት 2.ሃብተ መንግስት 3.ሃብተ ክህነት 4.ሃብተ በገና (መዝሙር) 5.ሃብተ ፈውስ 6.ሃብተ መዊዕ (ድል መንሳት) 7.ሃብተ ኃይል ተብለው ይታወቃሉ:: +በ7ቱ ስሞቹም:- 1.ጻድቅ 2.የዋህ 3.ንጹሕ 4.ብእሴ እግዚአብሔር 5.ነቢየ ጽድቅ 6.መዘምር እና 7.ልበ አምላክ ተብሎ ይጠራል:: +ይህች ቀን ለእሥራኤል የነገሠባት ቀን ናት:: እግዚአብሔር ሳዖልን ከናቀው በሁዋላ ከእሴይ ልጆች መካከል "እንደ ልቤ የሆነውን ቀብተህ አንግስልኝ" ቢለው በዚህች ቀን ነቢዩ ሳሙኤል ቤተ ልሔም ገብቷል:: +በዚያም ከኤልያብ እስከ አሚናዳብ: 7ቱን የእሴይን ልጆች ቢፈትን አልሆነም:: በቅዱስ ሚካኤል ጠቁዋሚነት ግን ከእረኝነቱ ዳዊት ተጠራ:: ገና ከርቀት ሲመጣ የዘይት ቀርኑ ቦግ ብሎ ተከፈተ:: +በቅዱስ ዳዊት ራስ ላይም እንደ እሳት ፈላ:: በአምላክ ምርጫም በ12 ዓመቱ ንጉሥ ተባለ:: የቅዱሱ ዜና ብዙ ነውና ለታሕሳስ 23 ይቆየን:: በቸር ቢያደርሰን በዚያው ቀን ከክብሩ እንካፈላለንና:: +"+ ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ +"+ =>ቅዱሱ በቀዳሚ ስሙ "ሌዊ": በቀዳሚ ግብሩ ደግሞ "ቀራጩ" ይባል ነበር:: ወንጌል እንደሚል ጌታችን የጠራው ከሚቀርጥበት ቦታ ሲሆን (ማቴ. 9:9) ከ12ቱ ሐዋርያት ደምሮ (ማቴ. 10:1) ስሙን "ማቴዎስ" ብሎታል:: ትርጉሙም "ኅሩይ" (ምርጥ) እንደ ማለት ነው:: +ጌታችንን በዘመነ ሥጋዌው በፍጹም ምናኔ ከማገልገሉ ባለፈ ከዋለበት እየዋለ: ካደረበት እያደረ: የእጁን ተአምራት ተመልክቷል:: የቃሉንም ትምሕርት ሰምቷል:: በጌታ ሕማማት ጊዜ ምንም በፍርሃት ከተበተኑት አንዱ እሱ ቢሆን አመሻሽ ላይ ወደ ማርቆስ እናት ቤት (ጽርሐ ጽዮን) ሒዶ ወንድሞቹን ሐዋርያትን ተቀላቅሏል:: +የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነስቶ ትንሳኤውን ሲገልጥም ቅዱስ ማቴዎስ ነበረ:: ለ40 ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓትን ተምሮ በጌታ ዕርገት ጊዜ ሊቀ ዽዽስናን ተሹሟል:: በ50ኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜም ጸጋውንና 71 ልሳናትን ተቀብሎ በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ወንጌልን ሰብኩዋል:: +ሐዋርያት ወንጌልን ለዓለም ለማዳረስ እጣ በተጣጣሉ ጊዜ ለቅዱስ ማቴዎስ ምድረ ፍልስጥኤም ደረሰችው:: ሃገረ ስብከቱን ካዳረሰ በሁዋላም ወደ ሌሎች ሃገራት ተጉዞ ሰብኩዋል:: +ለምሳሌ በገድለ ሐዋርያት ላይ በኢትዮዽያ: በፋርስና በባቢሎን አካባቢ ማስተማሩን ይገልጻል:: የሚገርመው ደግሞ ለዚህ ማረጋገጫ የሚሆን ነገር ሃገራችን ውስጥ መኖሩ ነው:: +ወደ አክሱምና አካባቢዋ ቅዱሳት መካናትን ለመሳለም በሔድንበት ወቅት በጻድቃነ ዴጌ/ዶጌ ገዳም ውስጥ (አክሱም አካባቢ የሚገኝ የ3ሺ ስውራን ቦታ ነው) የቅዱስ ማቴዎስን በትረ መስቀል መመልከት ችለናል:: አባቶችም ቅዱስ ማቴዎስ በዘመነ ስብከቱ አክሱም አካባቢ መጥቶ እንደ ነበር ነግረውናል:: +ቅዱሱ ሐዋርያ በአይሁድ: በአሕዛብና በአረሚ መካከል እየተመላለሰ አስተምሮ በርካታ ተአምራትን ሠርቷል:: የጣዖት ካህናትንና ነገሥታትን ጨምሮ እልፍ አእላፍ ነፍሳትን ወደ ክርስትና መልሷል:: +ስለዚህ ፈንታም እጅግ ብዙ መከራዎች ተፈራርቀውበታል:: ጌታችንም በየጊዜው እየተገለጸ ያጽናናው ነበር:: በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የመጀመሪያውን ወንጌል በምድረ ፍልስጥኤም ሲጽፍ: ዘመኑም ጌታ ባረገ በ8ኛው ዓመት (ማለት በ43 ዓ/ም) አካባቢ ነው:: +ወንጌሉ 28 ምዕራፎች ሲኖሩት በጌታ የዘር ሐረግ ጀምሮ የጌታችንን ትምሕርቱንና ተአምራቱን በሰፊው ያትታል:: በመጨረሻም ከምሴተ ሐሙስ እስከ ትንሳኤ ድረስ አትቶ ይጠናቀቃል:: +ቅዱስ ማቴዎስ ከ12ቱ ሐዋርያት በአንድ ነገሩ ይለያል:: ከ5ቱ ዓለማት አንዱን (ብሔረ ብጹዓንን) ያስተምር ዘንድ ተመርጧል:: ዘወትር እሑድ በደመና እየተነጠቀ ኃጢአት ወደ ሌለበት ዓለም ገብቶ ብጹዓንን ያስተምር ነበር:: "ሰላም ለማቴዎስ በደመና ሰማይ ዘተነጥቀ: ኅሩያነ ይርዓይ ዘብሔረ ብጹዓን ደቂቀ::" እንዲል:: +በዚያም ዘወትር ጌታችንን ያየው ነበር:: ቅዱስ ማቴዎስ እንዲህ ከተመላለሰ በሁዋላ በፍጻሜው ለጊዜው ባልለየናት አንዲት ሃገር ውስጥ አረማውያን አስረው አሰቃይተውታል:: በዚህች ቀንም ገድለውታል:: +"+ ቅዱስ ድሜጥሮስ +"+ =>ቅዱስ ድሜጥሮስ በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የተወለደ: በመንፈሳዊ ለዛ ከአጐቱ ደማስቆስ ጋር ያደገ የዘመኑ ደግ ሰው ነበር:: በዘመኑ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት ያለቁበት በመሆኑ ቤተሰቦቹ የአጎቱን ልጅ ልዕልተ ወይንን እንዲያገባ ግድ አሉት:: +ቅዱስ ድሜጥሮስ የነርሱን ፈቃድ ለመፈፀም ጋብቻውን በተክሊል ፈፀመ:: የፈጣሪውን ፈቃድ ለመፈፀም ደግሞ ከቅድስት እናታችን ልዕልተ ወይን ጋር ተስማምተው ለ48 ዓመታት በአንድ አልጋ ላይ እየተኙ: አንድ ምንጣፍና ልብስ እየተጋሩ በድንግልና ኑረዋል:: ቅዱስ ሚካኤልም ስለ ክብራቸው ከመካከላቸው ሆኖ ቀኝ ክንፉን ለርሱ: ግራ ክንፉን ለርሱዋ ያለብሳቸው ነበር:: +ከ48 ዓመታት በሁዋላ ቅ. ድሜጥሮስ የግብፅ 12ኛ ሊቀ ዻዻስ ሆኖ ተሹሞ ምስጢር በዝቶለት ባሕረ- ሐሳብን ጽፎ ሠርቷል:: ሰይጣን በሰዎች አድሮ ቅዱሱን ሚስት አለው በሚል ቤተ ክርስቲያን ላይ ሁከት በመፈጠሩ ቅዱስ ድሜጥሮስ በመልዐኩ ትእዛዝ ሕዝቡን ሰብስቦ: እሳት አስነድዶ: ከቅድስት ልዕልተ ወይን ጋር እሳቱ ውስጥ ገብተው ለረዥም ሰዓት ጸልየዋል:: +ሕዝቡም ይሕን ተአምር አይተው: የቅዱሳኑን ንጽሕና ተረድተው: ማረን ብለው በፍቅር ተለያዩ:: መጋቢት 12 ቀን ድንግልናው ተገልጧል:: +ቅዱስ ድሜጥሮስና እናታችን ልዕልተ ወይን ተረፈ ዘመናቸውን በቅድስና አሳልፈዋል:: በተለይ ሊቀ ዻዻሳቱ ድሜጥሮስ ብዙ ድርሳናትን ደርሷል:: እነ አርጌንስ (Origen) ና ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ (Clement of Alexandria) የመሰሉ መናፍቃንንም አውግዟል:: +ከጣዕመ ስብከቱም የተነሳ አርጅቶ እንኩዋ ምዕመናን እየተበሰቡ ይማሩ ነበር:: በአልጋ ተሸክመውም ይባርካቸው ነበር:: ቅዱሱ በ107 ዓመቱ ያረፈው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ አካባቢ በዚህች ቀን ነው::

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ ጥቅምት ፲፩ (11) ❖ ✞✞✞ እንኩዋን ለአባ "ያዕቆብ ስዱድ" እና ለእናታችን "ቅድስት ዺላግያ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞ +"+ አባ ያዕቆብ ስዱድ +"+ =>"ዻዻስ" ማለት "አባት - መሪ - እረኛ" ማለት ነው:: በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ በሐዲስ ኪዳን የመንፈሳዊ ስልጣን ደረጃዎች በጥቅሉ 3 ናቸው:: እነሱም ዲቁና: ቅስና: ዽዽስና ሲሆኑ በሥራቸው ወደ 9 ያህል ክፍሎች አላቸው:: ከእነዚህም ከፍተኛው ስልጣን ዽዽስና ነው:: +ዽዽስና ማለት የክርስቶስን መንጋ እንደ ባለቤቱ አድርጐ መጠበቅ ማለት ነው:: ሥልጣኑ በምድር "ሸክም: ዕዳ" ሲሆን በሰማይ ግን "ክብር" ነው:: ማንም በሥጋው ላይ ካልጨከነ በቀር ዽዽስናን አይመኝም:: +ቅዱስ ዻውሎስ "ሠናየ ግብረ ፈተወ - ማንም ዽዽስናን ቢመኝ መልካም ሥራን ተመኘ" (1ጢሞ. 3:1) ማለቱን ይዞ "ሹሙኝ" ማለት ወደ ማይጠፋ እሳት የሚያስጥል ከባድ ውሳኔ ነው:: ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን የሚጠየቅ በራሱ ኃጢአት ሲሆን አንድ ካህን ደግሞ ስለ ልጆቹ ይጠየቃል:: የከፋው ግን የዻዻሱ ነው:: +አንድ ዻዻስ ቢጾም ቢጸልይም እንኩዋ ለድኅነቱ በቂ አይደለም:: ምክንያቱም በመንበሩ ላይ ያስቀመጠው መንጋውን እንጂ ራሱን እንዲያድን አይደለምና:: ጌታ እንዳለ መልካም እረኛ "ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግኢሁ - መልካሙ እረኛ ስለ በጐቹ ቤዛ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው::" (ዮሐ. 10) ስለዚህም ክህነት ( ዽዽስና) ሐዋርያዊ አገልግሎት ከባድም ኃላፊነት ነው:: +አባቶቻችን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሐዋርያውያን ታላላቅ የዽዽስና መንበሮችን መሥርተው: ትምሕርቱን ከነ ወንበሩ አስተላልፈዋል:: ከእነዚህ መንበረ ዽዽስናዎች 4ቱ የበላይ ናቸው:: እነዚህም የቅዱስ ዼጥሮሱ የሮም: የቅዱስ ዮሐንሱ የአንጾኪያ: የቅዱስ ማርቆሱ የእስክንድርያና የቅዱስ ዻውሎሱ የኤፌሶን መናብርት ናቸው:: +እነዚህ መንበሮችም ከክርስቶስ ዕርገት እስከ 443 (451) ዓ/ም: ጉባኤ ኬልቄዶን ድረስ በአንድነት ቆይተው ተለያይተዋል:: ከእነዚህ መናብርት መካከል የእስክንድርያው (የግብጹ) እና የአንጾኪያው (የሶርያው) ዛሬም ድረስ በተዋሕዶ እምነት የጸኑ ናቸው:: +የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት እንደ መሆኗ ሐዋርያትን መስለው: ሐዋርያትን አህለው የተነሱ አበው ዻዻሳትን በየጊዜው በበዓላት ታስባለች: ታከብራለች:: +በተለይ ደግሞ የእስክንድርያና የአንጾኪያ በርካታ አባቶችን እናከብራለን:: እነርሱ ለቀናች ሃይማኖትና ለመንጋው ሲሉ ብዙ መከራን በአኮቴት ተቀብለዋልና:: ከእነዚህም መካከል አንዱ አባ ያዕቆብ ሲባሉ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ የአንጾኪያ መንበር ፓትርያርክ ነበሩ:: +ቅዱሱ በገዳማዊ ሕይወት የተመሠከረላቸው: በትምሕርት የበሰሉና ለመንጋው የሚራሩ በመሆናቸው በምዕመናን ይወደዱ ነበር:: ነገር ግን ተረፈ አርዮሳውያንና መለካውያን ከነገሥታቱ ጋር አብረው ብዙ አሰቃዩዋቸው:: በመጨረሻም ከመንበራቸው አፈናቅለው ወደ በርሃ አሳድደዋቸዋል:: ከስደት በሁዋላም አባ ያዕቆብ በዚህች ቀን ዐርፈዋል:: +"+ ቅድስት ዺላግያ ገዳማዊት +"+ =>ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚል እግዚአብሔር የኃጥኡን መመለስ እንጂ ሞቱን አይፈልግም:: በጠፋው በግ መገኘት ደስ ይለዋል:: በእግርህ ሒድ እንኩዋ አይለውም:: ይልቁኑ በትከሻው ተሸክሞ ከጐረቤቶቹ ጋር ደስ ይለዋል እንጂ:: +ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ቅዱሳን አንዳንዶቹ ጭንቅ ከሆነ የኃጢአት ሕይወት የተመለሱ ናቸው:: ግን ድንቅ በሆነ ንስሃቸው "ቅዱሳን" ከመባል ደርሰዋል:: ከእነዚህም አንዷ ቅድስት ዺላግያ ናት:: =>ይህቺ ቅድስት እናት በልጅነቷ በመልኩዋ ምክንያት ስሕተት ያገኛት ናት:: አምላክ የፈጠረውን መልክና ገላ እንዴት መጠቀም እንዳለብን እየተማርን አይደለምና በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረውን ገላችን ለዲያብሎስ ሰጥተነዋል:: +ይህቺ እናትም ችግሯ ይኼው ነበር:: ስለ ገጽታዋና ገላዋ የነበራት የተሳሳተ አመለካከት መጀመሪያ ወደ ትውዝፍት (ምንዝር ጌጥ): ቀጥሎም ወደ ዝሙት ከተታት:: ለዘመናትም የሰይጣን ወጥመድ ሆና ኑራለች:: +ፈጣሪ ግን ለሁላችንም የመዳን ቀን ጥሪ አለውና እሷንም ጠራት:: ምናልባትም በዘመኗ የብዙ ሰባክያንን ትምሕርት ሰምታለች:: አንዱም ግን ወደ ልቧ አልገባም:: +ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ያላደረበት አስተማሪ በጥሩ አማርኛ ልባችን ደስ ያሰኝ ይሆናል እንጂ ሊለውጠን አይችልም:: +በዘመኑም የሚታየው ትልቁ ችግር ይኼው ይመስለኛል:: እግዚአብሔር የሾማቸው አባቶቻችን ተቀምጠው ወጣቶች መድረኩን የሙጥኝ ብለነዋል:: +ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ዺላግያ አንድ ቀን የሰማችው የደጉ ዻዻስ ትምሕርት ግን ፈጽሞ ዘልቆ ተሰማት:: ተጸጸተች: አለቀሰች:: ወደ ዻዻሱ ሔዳ "ማረኝ" አለች: ንስሃ ሰጣት:: እርሷም ንብረቷን ሁሉ መጽውታ በርሃ ገባች:: +አንገቷን ደፍታ በጾምና በጸሎት ሰይጣንን ድል ነሳችው:: ከሃገሯ ሶርያ ወደ ቀራንዮ ደርሳ ተመልሳ ለ30 ዓመታት ዘጋች:: ተባሕትዎዋን ስትፈጽም በጸጋ እግዚአብሔር ተአምራትን ሠርታ: ለኃጥአን መንገድ ጧፍ ሆና አብርታ በዚህች ቀን ዐርፋለች:: =>አምላከ ቅዱሳን የሚያስተውለውን የንስሃ አእምሮን ያድለን:: ከወዳጆቹ በረከትም አያርቀን:: =>ጥቅምት 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ አባ ያዕቆብ (ስደተኛው ሊቀ ዻዻሳት) 2.ቅድስት ዺላግያ ገዳማዊት 3.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት 4.ቅዱስ አርማሚ ሰማዕት =>ወርሐዊ በዓላት 1.ቅዱስ ያሬድ ካህን 2.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት 3.ብፁዐን ኢያቄምና ሐና 4.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ =>+"+ መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበርሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል:: ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ 'የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ' ይላቸዋል:: እላችሁአለሁ: እንዲሁ ንስሃ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሃ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል:: +"+ (ሉቃ. 15:3-7) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ ጥቅምት ፲ (10) ❖ ✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱሳን ሰማዕታት "ባኮስ ወሰርጊስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞ +"+ ቅዱሳን ባኮስ ወሰርጊስ +"+ =>ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው:: ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ: ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል:: ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው:: +ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል:: የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው:: "አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም: ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው:: +እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ! በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ:: ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም:: +እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ: የሚረግሟችሁን መርቁ: ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ" ብሎናልና:: (ማቴ. 5:44) ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል:: +በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል:: የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና:: ¤እስኪ ለዛሬ ደግሞ በአጭሩ የቅዱሳን ባኮስና ሰርጊስን ዜና እንካፈል:: +እነዚህ ቅዱሳን የዘመነ ሰማዕታት ፍሬዎች ናቸው:: ባኮስ እና ሰርጊስ (ሰርግዮስ) ከልጅነት ጀምሮ ባልንጀሮች ናቸው:: በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን በሮም ግዛት ሥር መክስምያኖስና ዲዮቅልጢያኖስ እስከ ነገሡበት ዘመን ድረስ በአንጻሩም ቢሆን ሰላም ነበር:: +ታዲያ በዚህ የሰላም ጊዜ 2ቱ ቅዱሳን ሥራ አልፈቱም:: ጾምን: ጸሎትንና በጐ ምግባራትን ሁሉ ይከተሉ ነበር:: ለመከራ ዘመን ስንቅ የሚሆነን በሰላሙ ዘመን የተያዘ ስንቅ ነውና:: +በዚያው አንጻር ደግሞ ሠርቶ መብላት ይገባልና ሥራ ሲፈልጉ መክስምያኖስ ሠራዊት መሰብሰብ ጀመረ:: እነርሱም ከሠራዊቱ ዘንድ ተቆጥረው የምድራዊ ንጉሥ ጭፍሮች ሆኑ:: በእርግጥ በዘመናችን ለክርስትና አይመቹም ከሚባልላቸው ሥራዎች አንዱ ውትድርና ነው:: +ነገር ግን ብዙ ቅዱሳንን ስትመለከቷቸው ሙያቸው ይሔው ነበር:: ቅዱሳን ባኮስና ሰርጊስ ጊዜው የሰላምም ይሁን የጦርነት ይጾማሉ: ይጸልያሉ: ይመጸውታሉ:: እንዲህ እንዲህ እያሉም ዘመናት አለፉ:: +ከቆይታ በሁዋላ ግን ሰይጣን ያደረበት ንጉሡ መክስምያኖስ ጣዖት አመለከ:: አዋጅም አውጥቶ ክርስቲያኖችን ያሰቃይ: ይገድልም ያዘ:: ቅዱሳኑ ይህንን ሲሰሙ አዘኑ:: +ቁጭ ብለውም ተወያዩ:: በልባቸው ፍቅረ ክርስቶስ ይነድ ነበርና ወጣትነታቸው: መልካቸው: ተወዳጅነታቸው ሁሉ ሊያታልላቸው አልቻለም:: እንደ አንድ ልብ መካሪ: እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ስለ ሃይማኖት ሊሰው ወሰኑ:: +በማግስቱም ንጉሡ ወደ ሾመው የቅርብ አለቃቸው ቀረቡና "የምንነግርህ ነገር አለን" አሉት:: "እሺ" ሲላቸው በወገባቸው ያለውን የክብር መታጠቀያና የክብር ልብሳቸውን በፊቱ ወረወሩለትና "እኛ የክርስቶስ ጭፍሮች ነንና ከዚህ በሁዋላ ላንተ: ለጣዖት አምላኪው አንታዘዝም" አሉት:: +መኮንኑ ነዶታልና አስገረፋቸው: አሳሰራቸው:: በረሃብና በጥም: በብዙ መክፈልተ ኩነኔም አሰቃያቸው:: እነርሱ ግን ጽኑዓን ነበሩና አልቻሏቸውም:: ጥቅምት 4 ቀን በሆነ ጊዜ ግን 2ቱን ለያዩዋቸው:: ቅዱስ ባኮስን ለብቻው ወስደው ትልቅ ድንጋይ በአንገቱ ላይ አሠሩበትና ባሕር ውስጥ አሰጠሙት:: +ነፍሱም ከስጋው ስትለይ ባሕር ወደ ዳር አስወጣችው:: በአካባባቢውም "ባባ" እና "ማማ" የሚባሉ ባሕታውያን ነበሩና እግዚአብሔር እንዲገንዙት አዘዛቸው:: ሲሔዱም ቅዱስ ሥጋውን አንበሳና ተኩላ ሲጠብቁት አግኝተው: በታላቅ ዝማሬ ገንዘው: በራሳቸው ተሸክመው ወስደው: በበዓታቸው ውስጥ ቀበሩት:: +ቅዱስ ሰርጊስን ደግሞ ለ6 ቀናት ካሠሩት በሁዋላ በዚህች ቀን እጁንና እግሩን በእንጨት ላይ ቸንክረው: በእንስሳት ጭራ ላይ አስረው ሲጐትቱት ውለዋል:: አንገቱን በሰየፉት ጊዜም አንዲት ወጣት ደሙን ተቀብላ በረከትን አግኝታለች:: የመከራ ዘመን ካለፈ በሁዋላም ለቅዱሳኑ ቤተ ክርስቲያን ታንጾ በዚህች ቀን ተቀድሷል:: ተአምራትም ታይተዋል:: =>አምላከ ሰማዕታት ጽንዓት: ትእግስታቸውን አሳድሮ ከበረከታቸው ይክፈለን:: =>ጥቅምት 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱሳን ባኮስና ሰርጊስ (ሰማዕታት) 2.ቅዱስ ዮሐንስ መስተጋድል 3.አባ አውማንዮስ ሊቀ ዻዻሳት =>ወርሐዊ በዓላት 1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ 2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ 3.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ 4.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ) 5.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት 6.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ 7.ቅዱስ እፀ መስቀል =>+"+ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ: ወይስ ጭንቀት: ወይስ ስደት: ወይስ ራብ: ወይስ ራቁትነት: ወይስ ፍርሃት: ወይስ ሰይፍ ነውን? 'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን:: እንደሚታረዱ በጐች ተቈጠርን' ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው:: በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን:: +"+ (ሮሜ. 8:35-38) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

✞✞✞ ቸሩ አምላክ እንዲህ ለመንጋው የሚራሩ እረኞችን አይንሳን:: ከሐዋርያው: ከሰማዕቱና ከደጉ ፓትርያርክም ጸጋ በረከትን ይክፈለን::✞✞✞ ጥቅምት 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ 2.ቅዱስ እስጢፋኖስ ካልዕ (ሰማዕት) 3.ቅዱስ አትናስዮስ ብጹዕ 4.ቅዱስ ስምዖን ሰማዕት 5.ቅዱስ ሊዋርዮስ ሊቀ ዻዻሳት 6.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ 7.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቀ ዻዻሳት 8.አቡነ መዝገበ ሥላሴ ጻድቅ (ኢትዮዽያዊ) 9.አፄ ዳዊት ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ (ግማደ መስቀሉን ያመጡ) በ 09 የሚከበሩ ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት 1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት) 2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ /ኢትዮዽያዊ/ 3."318ቱ" ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ) 4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን 5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮዽያዊ) 6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት) ✞✞✞+ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ:: የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ:: እንዲሁም ጐበዞች ሆይ! ለሽማግሌዎች ተገዙ:: ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ:: እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና:: ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል:: ✞✞✞ (1ዼጥ. 5:3) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ✞✞✞ ጥቅምት 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞✞✞ +" ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ "+ ✞✞✞ ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ ከኢትዮዽያ እስከ ሕንድና ባርቶስ በደረሰች ስብከቱ እጅግ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ሠርቷል:: 'አሐደ እምተአምራቲሁ' እንዲሉ አበው ከእነዚህ ዛሬ አንዱን እንመለከታለን:: +ቅዱስ ቶማስ ጐና ወደምትባል የሕንድ አውራጃ መግቢያ ፈሊጥ ቢያጣ ጌታ ወርዶ አበኒስ ለሚባል ነጋዴ ባሪያ አድርጐ ይሸጠዋል:: በመጀመሪያ በንጉሡ ሠርግ ቤት ውስጥ ተአምራትን አሳይቶ ሕዝቡን ከነ ሙሽሮቹና ንጉሣቸው አሳምኗል:: +ቀጥሎ ግን ጎንዶፎር ለሚባል ሌላ ንጉሥ 'ቤተ መንግስት ሥራ' ተብሎ ይላካል:: ሐዋርያውም ንጉሡን "የማንጽበትን ወርቅና ብር ስጠኝ" ብሎት ይሰጠዋል:: ንጉሡ ዘወር ሲል ግን "ወእሁብ ዘንጉሥ ለንጉሥ-የምድራዊው ንጉሥ ለሰማያዊው ንጉሥ እሰጣለሁ" እያለ ገንዘቡን ሁሉ ለነዳያን በተነው:: +ገንዘቡ ሲያልቅበት "ንጉሥ ሆይ! መሠረቱ ታንጿልና ለግድግዳው ላክልኝ" ይለዋል:: ሲልክለት ይመጸውተዋል:: አሁንም "ንጉሥ ሆይ! ለጣሪያው ላክልኝ" ይለውና ይመጸውተዋል:: መጽሐፍ እንደሚል ምጽዋት ለሐዋርያው ልማዱ ነውና:: +በመጨረሻ ግን ንጉሡ ሲመጣ ባዶ መሬት ላይ ነዳያን ገንዘቡን ሲበሉት አገኘ:: ተበሳጭቶም ቅዱስ ቶማስን ይገድለው ዘንድ አሠረው:: በዚያች ሌሊት ግን የንጉሡ ወንድም ጋዶን ሙቶ ሐዘን በሆነ ጊዜ ሐዋርያው አስነሳው:: +ጋዶንም ለቅዱሱ ሰግዶ በሰማይ ለንጉሥ ጐንዶፎር ትልቅ ቤት ታንጾ ማየቱን ተናገረ:: ንጉሡና ሠራዊቱም በፊቱ ሰግደው አመኑ:: አጥምቋቸውም ሔዷል:: +" ቅዱስ እስጢፋኖስ ካልዕ "+ +በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳን ሊቀ ዲያቆናቱ ቅድሚያውን ሲይዝ ዛሬ የምናከብረው ቅዱስ ደግሞ 'ካልዕ እስጢፋኖስ' (ሁለተኛው) ይባላል:: 2ቱም 'ቀዳሜ ሰማዕት' ይባላሉ:: ዋናው በሐዋርያት ዘመን ቀድሞ እንደተሰዋ ሁሉ ሁለተኛው በዘመነ ዲዮቅልጢያኖስ ርጉም ቀድሞ ተሰይፏል:: +ቅዱሱ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ ሲሆን በአንጾኪያ ቤተ መንግስት ውስጥ ከነበሩ ልዑላንና የጦር መሪዋችም አንዱ ነበር:: በዝምድና ደረጃም የታላቁ ቅዱስ ፋሲለደስ የእህቱ ልጅ ነው:: በቤተ ፋሲለደስ ከማደጉ የተነሳም የእርሱ ልጅ እንደ ሆነ በገድሉ ተጠቅሷል:: +ቅዱስ እስጢፋኖስ ካልዕ ማለት መልክ ከደም ግባት የተባበረለት: ጾምና ጸሎትን የሚወድ: የነዳያን አጉራሽ: ኃያል የጦር ሰውና ተወዳጅ ክርስቲያን ነው:: ያ ክፉ አውሬ በዓለም በሚገኙ ምዕመናን ሁሉ ላይ ሞትና ስቃይን ሲያውጅ በአካባቢው የነበረ ይኼው ቅዱስ ነው:: +በቦታው ከነበሩ ብዙ ሺህ ሰዎች ንጉሡን ደፍሮ የተናገረው አንድም አልነበረም:: ቅዱስ እስጢፋኖስ ግን ለክርስቶስ ቀና:: ከሕዝቡ መካከልም እየሮጠ አልፎ በንጉሡ ፊት አዋጅ የሚያነበውን ወታደር ቀማውና በአደባባይ ያችን የክህደት ደብዳቤ ቦጫጭቆ ጣላት:: +ንጉሡንም "ሰነፍ" ሲል ገሠጸው:: እጅግ የተቆጣው ንጉሡ ግን ቅዱሱን በሰይፍ ሰንዝሮ ከ2 ከፈለው:: አካሉ መሬት ላይ ሲወድቅ ራሱ ግን በዓየር ላይ ሁና ለ3 ቀናት ትንቢትን ተናገረች:: ለዚያ አስጨናቂ የመከራ ዘመንም በር ከፋቹ ቅዱስ እስጢፋኖስ ካልዕ ሆነ:: +" ቅዱስ አትናስዮስ ብጹዕ "+ +ይህ ቅዱስ አባት ደግሞ ባለ አስደናቂ ታሪክ ነው:: ዜና ሕይወቱ ሲሰማ ጣዕመ ነፍስን ያድላል:: ተወልዶ ባደገባት ሶርያ በመናኝነቱ የሚታወቀው ቅዱስ አትናስዮስ ሕይወቱ በጽሙና የተሞላ ነበር:: በገዳም ገብቶም በዓት ለይቶ ሰውነቱን ለእግዚአብሔር ሲያስገዛት ዘመናት አልፈዋል:: +በዘመኑ የአንጾኪያ ፓትርያርክ አርፎ ነበርና ለመንበሯ የሚገባውን ሰው ፍለጋ በየበርሃው ዞሩ:: ነገር ግን ከቅዱሱ አትናስዮስ የተሻለ ሰው አላገኙም:: እርሱ መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ: ለመንጋውም የሚራራ በጐ እረኛ ነውና ይዘውት ወደ ከተማ መጡ:: +በሃገራቸው ባሕል መሠረት ሊቀ ዻዻሳት የሚሾመው የሁሉም አሕጉረ ስብከት ዻዻሳት ባሉበት ነውና ጠበቁ:: ሁሉ ተገኝቶ በሶርያ የሰልቅ ዻዻስ የነበረው አባ እልመፍርያን ግን ዘገየ:: ለ50 ቀናት ጠብቀው አባ አትናስዮስን 'ፓትርያርክ ዘአንጾኪያ' ብለው ሹመውት ተለያዩ:: +በ51ኛው ቀን አባ እልመፍርያን ሲደርስ በዓለ ሲመቱ መጠናቀቁን ሲነግሩት ተቆጣ:: "እኔ በሌለሁበት የተሾመው አይሠራምና አትናስዮስን ፓትርያርክ ብሎ የሚጠራ ሁሉ የተወገዘ ይሁን" ብሎ ወደ ሰልቅ ተመለሰ:: ቅዱስ አትናስዮስ ይህንን ነገር ሲሰማ ፈጽሞ አዘነ:: +ከቀድሞውም አስገድደውት እንጂ እርሱ ሹመቱን ፈልጐ አልመጣም:: ልክ በዘመኑ እንደምንመለከተው ቅዱሱ መልሶ ማውገዝ ይችላል:: ለዚያውም በሥልጣን ይበልጠዋል:: ቅዱሱ ግን ለግል ክብሩ ሲል ቤተ ክርስቲያንና ምዕመናን ሲከፈሉ ማየትን አልወደደም:: +ደቀ መዝሙሩን ጠራውና "ልጄ! እሺ በለኝ: ነፍሴ ትመርቅሃለች:: እኔ ለ1 ዓመት መንገድ ስለምወጣ አንተ በእኔ ፈንታ እዘዝ: እሠር: ፍታ:: ሕዝቡ ከጠየቁህ ወደ ገዳም ሔዷል በላቸው" ብሎት ከመንበረ ዽዽስናው ወጣ:: እጅግ የነተበ የበርሃ ልብሱን ለብሶ: ለ1 ቀን በእግሩ ተጉዞ ሰልቅ ውስጥ ደረሰ:: +ወደ አባ እልመፍርያን ዘንድ ገብቶም በፊቱ ሰገደ:: "አባቴ! ነዳይ ነኝና አስጠጋኝ?" ብሎ ለመነው:: አባ እልመፍርያንም ከመነኮሳቱ ጋር እንዲኖር ፈቀደለት:: +ቅዱስ አትናስዮስ ፓትርያርክ ሲሆን ወገቡን ታጥቆ ያገለግል ገባ:: ውሃ ይቀዳል: ዳቦ ይጋግራል: ቤቶችን ይጠርጋል: መጸዳጃ ቤቶችን ያጸዳል: የመነኮሳቱን እግር ያጥባል:: በዚህ ሁሉ ላበቱ እየተንጠፈጠፈ በሰውነቱ ላይ ይወርድ ነበር:: +አባቶች ትጋቱንና ትሕትናውን ሲያዩ ለዲቁና አጩት:: ዻዻሱም ጠርቶ "ዲቁና ልሹምሕ" ቢለው ፓትርያርኩ ቅዱስ አትናስዮስ አለቀሰ:: "ምነው?" ቢለው "አባቴ! በነውር ተይዞብኝ ነው እንጂ ዲቁናስ አለኝ" አለው:: አሁንም ለ7 ወራት በዲቁና አገልግሎት ቆይቶ ቅስና ተሾም ቢሉት እንደ ቀደመው እያለቀሰ መለሰላቸው:: +ልክ በዓመቱ ግን ለአንዲት ሃገረ ስብከት ዻዻስ ያደርጉት ዘንድ በዕለተ እሑድ ተሰበሰቡ:: ቅዱስ አትናስዮስ እንዲተውት እያለቀሰ ለመናቸው:: "ለሹመቱ ትገባለህ" ብለው ግድ ሲሉት ግን "ምሥጢር ልንገራችሁ" ብሎ "ፓትርያርኩ አትናስዮስ ይሏችኋል እኮ እኔ ነኝ" አላቸው:: +የሰማውን ነገር ማመን ያቃተው አባ እልመፍርያን ደንግጦ በግንባሩ መሬት ላይ ወደቀ:: እየተንከባለለም አለቀሰ:: "ወየው ለእኔ! ጌታየን አትናስዮስን እንደ አገልጋይ ላዘዝኩ" እያለም ተማለለ:: በአካባቢው የነበሩ ዻዻሳት: ካህናት: መነኮሳትና ምዕመናንም ከቅዱስ አትናስዮስ የትህትና ሥራ የተነሳ ፈጽመው አደነቁ:: +መንበረ ዽዽስና አምጥተው እየዘመሩ ተሸክመውት ዞሩ:: ቅዳሴንም ቀድሶ ሥጋውን ደሙን አቀብሏቸው ታላቅ ደስታ ሆነ:: በማግስቱም ቅዱሱን ባማረች በቅሎ ላይ አስቀምጠው: አባ እልመፍርያን በእግሩ (በራሱ ፈቃድ) እየተጓዘ በታላቅ ዝማሬ አንጾኪያ ደረሱ:: +በዚያም ታላቅ የአንድነት በዓል ተከበረ:: ታላቁ እረኛ ቅዱስ አትናስዮስ እነሆ በዚህ መንገድ ቤተ ክርስቲያንን ከ2 ከመከፈል ታደጋት:: ቅዱሱ ሲጋደል ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል::

✞✞✞ እንኩዋን ለአበው ቅዱሳን "አባ አጋቶን ወአባ መጥራ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞ +"+ አባ አጋቶን ባሕታዊ +"+ =>ይህንን ቅዱስ የማያውቅ የቤተ ክርስቲያን ሰው ይኖራል ብየ አልገምትም:: እርሱ ታላቅ ጻድቅ: ገዳማዊና የእግዚአብሔር ሰው ሲሆን አንደበቱን ከክፋት ይከለክል ዘንድ ለ30 ዓመታት ድንጋይ ጐርሶ ኖሯል:: +ይህንን ቅዱስ ሊቃውንት ሲገልጹት: "ክምረ ክምር ጽድቁ እስከ አስተርአየ" ይሉታል:: ትእግስቱ: ደግነቱ: አርምሞው: ትሩፋቱ ከመነገር በላይ ነው:: በነበረበት በ4ኛው መቶ ክ/ዘመንም እንደ ኮከብ ያበራ ታላቅ አባት ነው:: +ታላቁ ገዳማዊ ሰው አባ አጋቶን የታላቁ መቃርዮስ ቅዱስ ልጅ ነው:: ገዳመ አስቄጥስ እልፍ አእላፍ ቅዱሳንን ስታፈራ ይህ አባት ቅድሚያውን ይይዛል:: ምንም በብዛት የሚታወቀው በአርምሞው (በዝምታው) ቢሆንም ባለ ብዙ ትሩፋት አባት ነው:: +የሚገርመው የቀደሙ አባቶቻችን የፈለገውን ያህል መናኝ ቢሆኑም የሰው ጥገኛ መሆንን አይፈልጉም:: "ሊሠራ የማይወድ አይብላ" የሚለውን መለኮታዊ ትዕዛዝ መሠረት አድርገው ከተጋድሎ በተረፈቻቸው ሰዓት ሥራ ይሠራሉ:: +አንዳንዶቹ እንደሚመስላቸው ምናኔ ሥራ መፍታት አይደለምና ሰሌን: ዕንቅብ: ሠፌድ የመሳሰለውን ይሠፋሉ:: ታላቁ አባ አጋቶንም በአንደበቱ ድንጋይ ጐርሶ: በእግሮቹ ቀጥ ብሎ ቆሞ እንቅቦችን ይሠፋ ነበር:: +ለነገሩስ ዛሬ ዛሬ እንኩዋን ወንዶቹ ሴቶችም ብንሆን ይህንን ሙያ እየረሳነው ነው:: ቅዱሱ ግን ይሰፋና ወደ ገበያ ይወጣል:: በጠየቁት ዋጋ ሽጦት አንዲት ቂጣ (ዻኩሲማ) ይገዛል:: የተረፈውን ገንዘብ ግን እዚያው ለነዳያን አካፍሎት ይመጣል እንጂ ወደ ገዳሙ አይመልሰውም:: +ታዲያ አንድ ቀን እንደልማዱ የሠፋቸውን 5 እንቅቦች ተሸክሞ ወደ ገበያ ሲሔድ መንገድ ላይ አንድ ነዳይ (የኔ ቢጤ) ወድቆ ያገኛል:: እንደ ደረሰም ስመ እግዚአብሔር ጠርቶ ይለምነዋል:: አባ አጋቶን ከእንቅቦቹ ውጪ ምንም ነገር አልነበረውምና "እንቅቡን እንካ" አለው:: +ነዳዩ ግን ወይ የሚበላ: ካልሆነም ገንዘብ እንደሚፈልግ ይነግረዋል:: ወዲያው ደግሞ "የምትሠጠኝ ነገር ከሌለህ ለምን ወደ ገበያ ተሸክመህ አትወስደኝም?" አለው:: የነዳዩ አካል እጅግ የቆሳሰለ በመሆኑ እንኩዋን ሊሸከሙት ሊያዩትም የሚከብድ ነበር:: +ጻድቁ ግን ደስ እያለው: ያለማመንታት አንስቶ ተሸከመው:: ከረጅም መንገድ በሁዋላም ከገበያ በመድረሳቸው አውርዶ ከጐኑ አስቀመጠው:: ያ ነዳይ አላፊ አግዳሚውን ሁሉ ቢለምንም የሚዘከረው አጣ:: አባ አጋቶን አንዷን እንቅብ ሲሸጥ "ስጠኝ?" ይለዋል:: ጻድቁም ይሠጠዋል:: +እንዲህ "ስጠኝ" እያለ የ5ቱንም እንቅቦች ዋጋ ያ ነዳይ ወሰደበት:: አባ አጋቶን ግን ምንም ቂጣ ባይገዛ: በሆነው ነገር አልተከፋምና ሊሔድ ሲነሳ ነዳዩ "ወደ ቦታየ ተሸክመህ መልሰኝ" አለው:: አባቶቻችን ትእግስታቸው ጥግ (ዳር) የለውምና ጐንበስ ብሎ በፍቅር አንስቶት አዘለውና ሔደ:: +ካነሳበት ቦታ ላይ ሲደርሱ ይወርድለት ዘንድ ጻድቁ ቆመ:: ነዳዩ ግን አልወርድም አለ:: መቼም እኛ ብንሆን ብለን እናስበውና . . . ምን እንደምናደርግ ይታወቃል:: ጻድቁ ግን ዝም ብሎ ቆመለት:: +ትንሽ ቆይቶ ግን ስለ ለቀቀው ሊያየው ዞር ቢል መሬት ላይ የለም:: ቀና ሲል ግን ያየውን ነገር ማመን አልቻለም:: ደንግጦ በግንባሩ ተደፋ:: ነዳይ መስሎ እንዲያ ሲፈትነው የነበረው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ነበር:: +ክንፎቹን ዘርግቶ: በብርሃን ተከቦ: በግርማ ታየው:: ከወደቀበትም አነሳው:: "ወዳጄ አጋቶን! ፍሬህ: ትእግስትህ: ደግነትህ ግሩም ነውና ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎት ተሰወረው:: ጻድቁም በደስታ ወደ በዓቱ ሔደ:: አባ አጋቶን ተረፈ ዘመኑን በአርምሞ ኑሮ ዐርፏል:: +"+ ቅዱስ መጥራ አረጋዊ +"+ =>ቅዱሱ የ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ክርስቲያን ሲሆን በትውልድ ግብጻዊ ነው:: ከልጅነት እስከ እውቀት: ከእውቀት እስከ ሽበት ክርስቶስን ሲያመልክ ኑሯል:: ዘመኑ ክርስቲያኖች ስለ ሃይማኖታቸው ከባዱን ዋጋ (ሕይወታቸውን) የሚከፍሉበት ነበር:: +በወቅቱ ብርቱ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ቢበዙም ብርቱ መንፈሳዊያን ተዋጊ ክርስቲያኖች ነበሩና ውጊያው ተመጣጣኝ ነበር:: ዛሬ ደግሞ ሁሉም በዛለበት ዘመን ላይ ተገኝተናል:: +ቅዱስ መጥራ ካረጀ በሁዋላ ነገሥታቱ "ክርስቶስን ካዱ" እያሉ መጡ:: ቅዱሱ ወሬውን ሲሰማ እጅግ ተገረመ:: ምክንያቱም መድኃኔ ዓለምን መካድ ፈጽሞ የሚታሰብ ነገር አይደለምና:: ቅዱሱ አረጋዊ ስለ 2 ነገር ሰማዕትነትን ፈለገ:: +አንደኛ በክርስቶስ ስም መሞት የክብር ክብርን ያስገኛልና ከዚሁ ለመሳተፍ ነው:: ሁለተኛው ግን ለወጣቶች አብነት (ምሳሌ) ለመሆን ነበር:: መልካም መሪ ባለበት ዘንድ ብዙ ፍሬዎች አይጠፉምና:: ቅዱስ መጥራ እንዳሰበው ወደ መኮንኑ ሒዶ በአሕዛብ ፊት ክርስቶስን ሰበከ:: ስለዚህ ፈንታም ብዙ አሰቃይተው በዚህች ቀን ከተከታዮቹ ጋር ገድለውታል:: =>አምላከ ቅዱሳን ትእግስታቸውን ያሳድርብን:: ከአባቶቻችንም በረከትን ይክፈለን:: =>ጥቅምት 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.አባ አጋቶን ባሕታዊ 2.ቅዱስ መጥራ አረጋዊ (ሰማዕት) 3.ቅድስት ሶስናና ልጆቿ (ሰማዕታት) 4.አባ ሖር 5.ቅድስት በላግያ ሰማዕት =>ወርሐዊ በዓላት 1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት 2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ) 3.አባ ብሶይ (ቢሾይ) 4.አቡነ ኪሮስ 5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን 6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት) =>+"+ ጸሎቴን በፊትህ እንደ እጣን ተቀበልልኝ:: እጅ መንሳቴም እንደ ሠርክ መስዋዕት ትሁን:: አቤቱ ለአፌ ጠባቂ አኑር:: የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ:: ልቤን ወደ ክፉ ነገር አትመልሰው:: ለኃጢአት ምክንያት እንዳልሠጥ:: ከምርጦቻቸውም ጋር አልተባበር:: ጻድቅ በምሕረት ይገሥጸኝ: ይዝለፈኝም:: +"+ (መዝ. 140:2) ✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለታላቁ ገዳማዊ "ቅዱስ አባ ባውላ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞ +"+ አባ ባውላ መስተጋድል +"+ =>ቅዱሱን የመሰሉ አባቶች "መስተጋድላን" ይባላሉ በግዕዙ:: ለሃይማኖታቸው እስከ ደም ጠብታና እስከ መጨረሻዋ ህቅታ ድረስ መጋደላቸውን የሚያሳይ ነው:: መጋደል ጐዳናው ብዙ ዓይነት ነው:: +ከራሱ ጋር የሚጋደል አለ:: ከዓለም ጋር የሚጋደልም አለ:: የቅዱሳኑ ተጋድሎ ግን በዋነኝነት ከ2 አካላት ጋር ነው:: በመጀመሪያ ፍትወታት እኩያትን (ኃጣውዕን) ከሚያመጡ አጋንንት ጋር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ "ሃይማኖቸታችሁን ካዱ: ለጣዖትም ስገዱ" ከሚሉ ከሃድያን ጋር የሚደረግ ትግል ነው:: +በተለይ 2ኛው እስከ ሞት የሚያደርስ ውሳኔን ይጠይቃል:: ታላቁ አባ ባውላ ገዳማዊ ጻድቅ እንደ መሆኑ ትግሉ የነበረው ከአጋንንት ጋር ነው:: የዚህን ቅዱስ ሕይወት ለመረዳት ግን አንድ ነገርን ልብ እንድትሉልኝ እፈልጋለሁ:: +ያለንበት ዘመን ክርስትና በራድ (ቀዝቃዛ) በመሆኑ የቀደሙ አባቶች የጸና ተጋድሎ አንዳንዴ ግራ ሲያጋባን ተመልክቻለሁ:: ቅዱሳኑ ሁሌም አንድ ነገርን እያሰቡ ይኖራሉ:: ይኼውም በዘመኑ በርካቶቻችን የረሳነው: ወይም ማስታወስ የማንፈልገው ነገር ይመስላል:: +ሰማያዊው አምላክ ከዙፋኑ ወርዶ በተዋሐደው ሥጋ በቃል ሊገለጽ የማይችል መከራን ስለ እኛ ተቀብሏል:: ክርስትና ማለት ቀራንዮን በልብ ውስጥ መሳል ነው:: ፍቅረ መስቀሉን: የጌታንም ውለታ የሚያስብ ማንኛውም ሰው: የትኛውም ዓይነት መከራ ቢመጣበት አይታወክም:: +ቅዱሳኑም የፍቅራቸውና የትእግስታቸው ምሥጢር ይኼው ነው:: ጌታ "የሚወደኝ ቢኖር የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ" (ማቴ. 16:24) እንዳለው: ቅዱሳኑ ይህንን ቃል በቃል ሲፈጽሙት እነሆ እንመለከታለን:: +ታላቁ አባ ባውላ የተወለደው በላይኛው ግብጽ አካባቢ ሲሆን ዘመኑም 4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ከክርስቲያን ወላጆቹ መንፈሳዊ ነገሮችን ተምሮ በወጣትነቱ መንኗል:: ያ ዘመን እልፍ አእላፍ ቅዱሳን የነበሩበት ነውና ወደ ጠመው አካባቢ ሔዶ ምናኔን ተምሯል:: +ሥርዓተ ገዳምን ማለትም:- አገልግሎትን: ፍቅርን: ተጋድሎንና የመሳሰሉትን ከተማረ በሁዋላም ደቀ መዝሙሩን አባ ሕዝቅኤልን አስከትሎ ለዋናው የተጋድሎ ሕይወት ወደ በርሃ ወጣ:: አባ ባውላ ዘወትር በፍቅረ ክርስቶስ ይመሰጥ ነበርና የተጋድሎ ምርጫው ልዩ ሆነ:: +አንድ ቀንም እንዲህ ሲል አሰበ:- "ጌታ ሆይ! አንተ ለእኛ ለኃጥአን ኃፍረተ መስቀልን ታግሠህ: ሞትን ከሞትክልን እኛ ደግሞ ስለ ንጹሑ አምላክ ስንል እልፍ ሞትን መታገስ አለብን::" +ይህንን ብሎ ከወትሮው በተለየ መንገድ ሊጋደል ጀመረ:: በዚህ እጅግ የጸና ተጋድሎው ምክንያትም 7 ጊዜ ሙቶ 7 ጊዜ ተነሳ:: 1.እግሩን ከረዥም ዛፍ ላይ አስሮ: ወደ ታች ተዘቅዝቆ ይጸልይ ጀመረ:: እህልም: እንቅልፍም: ዕረፍትም አልነበረውምና ደሙ በአፍ: በአፍንጫው ፈሶ አለቀ:: እንዲህ በሆነ በ40ኛው ቀንም ሞተ:: መልአከ እግዚአብሔር መጥቶ ከሞት አስነሳው:: 2.ጥልቅ ባሕር ውስጥ ሰጥሞ እንዳስለመደ ይጸልይ ጀመረ:: ከባሕሩ ሳይወጣ: ከቆመ ሳያርፍ: ከዘረጋም ሳያጥፍ ለ40 ቀናት ጸለየ:: በዚያው ሳለም ለ2ኛ ጊዜ ሞተ:: ቅዱስ መልአክ መጥቶ ከሞት አስነሳው:: 3.እርሱ በሚኖርበት ጠመው አካባቢ ረዥም ተራራ ነበርና ወደዚያ ወጣ:: ከተራራው ጫፍ ሆኖ ወደ ታች ተመለከተ:: የተጠራረቡ ድንጋዮች በየመንገዱ ተሰልፈው ነበር:: በዚያች ቅጽበት የጌታ ኅማማት ከፊቱ ቢደቀንበት ከላይ ወደ ታች ተወርውሮ ሔደ:: በየመንገዱ ያሉት ጥርብ ድንጋዮች ቢቀበሉት አካሉ እየተነተፈና እየተቆራረጠ በየመንገዱ ቀረ:: በዚህም ሞተ:: አሁንም ፈጣሪው ከሞት አስነሳው:: 4.አንድ ቀን ደግሞ (ዕለቱ ዓርብ ነበር) የጌታን ኅማማት እያሰበ የሚያደርገው ጠፋው:: ከቆመበት አካባቢ ትልቅ ዛፍ ነበርና ወደዚያ ወጥቶ ሲመለከት ከመሬት ላይ የተነጠፈ ትልቅ ድንጋይ አየ:: ከላይ ወደ ታች ሲወድቅና ድንጋዩ ላይ ሲያርፍ ለሁለት ተከፍሎ ሞተ:: አሁንም በፈጣሪ ትዕዛዝ ተነሳ:: 5.በሌላ ቀን ደግሞ በዕለተ ዓርብ ጭንቅላቱን ከእግሩ ጋር አሥሮ ይጸልይ ገባ:: ያለ ምንም እህል: ውሃና እንቅልፍ ለ40 ቀናት ቆይቶ ሞተ:: እንደገናም ተነሳ:: 6.እጅግ ሊመለከቱት እንኩዋ በሚከብድ የጉድጉዋድ ውሃ ውስጥ ገብቶ ለ40 ቀናት እጆቹን ዘርግቶ ቢጸልይ ከጭንቁ ብዛት ነፍሱ ከሥጋው ተለየች:: 7.አንድ ቀንም እንደዚሁ የጌታን ሕማማት እያሰበ ወደ ጽኑ ቆላ ወረደ:: በአካባቢው ከአሸዋ በቀር ምንም አልነበረምና ቆሞ ሲጸልይ አሸዋው ውጦ ደፈነውና ለ7ኛ ጊዜ ሞተ:: በዚህ ጊዜ ግን ሊያስነሳው የመጣው እንደ ወትሮው ቅዱስ መልአክ ሳይሆን ራሱ የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ ነበር:: +ጌታችን አባ ባውላን ከሞተበት አስነስቶ:- "ወዳጄ ባውላ! ስለ እኔ ፍቅር እጅግ ተሰቃየህ" አለው:: ቅዱሱ ግን "ጌታየ ሆይ! የእኔ መከራ በአንተ መከራ ሲታሰብ ኢምንት ነውና እባክህ ስለ ስምህ ሌሎች መከራዎችን እንድቀበል ፍቀድልኝ? ገና ሕማምህን አስቤ አልረካሁምና" አለው:: +ጌታ ግን "የለም! መከራው ይበቃሃል:: መጥቼ እስክወስድህ ድረስ ከአባ ብሶይ ጋር ቆይ" ብሎት: ባርኮት ዐረገ:: አባ ባውላም እንደ ታዘዘው በአባ ብሶይ ገዳም ከቅዱስ ብሶይ ጋር ቆይቶ በዚህች ቀን ዐርፏል:: +ይህቺውም ዕረፍቱ ለ8ኛ ጊዜ ሆና ተቆጥራለች:: የቅዱሱን ዜና የጻፈው ደቀ መዝሙሩ አባ ሕዝቅኤል ሲሆን ያሰፈረው እንባው እንደ ዥረት እየወረደ ነው:: አባቶቻችን ሊቃውንትስ ታላቁን ጻድቅ ሲያመሰግኑት እንዲህ አይደለምን! "ውስተ ገድል ጽኑዕ ዘአልቦ ምምዐ: ወደቀ ስብአ: ወተንሳእከ ስብአ::" =>አምላከ አባ ባውላ በጻድቁ ላይ ያሳደረውን ፍቅሩን ያሳድርብን:: ከበረከቱም ያድለን:: =>ጥቅምት 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.አባ ባውላ መስተጋድል 2.አባ ሕዝቅኤል ጻድቅ 3.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት 4.ቅዱስ ሐናሲ ሰማዕት =>ወርሐዊ በዓላት 1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ) 2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ 3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ) 4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት 5.አባ ባውላ ገዳማዊ 6.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ 7.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ) =>+"+ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ:: መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ:: ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል:: ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል:: ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ: ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? +"+ (ማቴ. 16:24) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

=>ወርሐዊ በዓላት 1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም 2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን 3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል 4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ 5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ 6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ 7.ቅድስት ሰሎሜ 8.አባ አርከ ሥሉስ 9.አባ ጽጌ ድንግል 10.ቅድስት አርሴማ ድንግል =>+"+ ምንም እንኩዋ በለስም ባታፈራ: በወይን ሐረግም ፍሬ ባይገኝ: የወይራ ሥራ ቢጐድል: እርሾችም መብልን ባይሰጡ: በጐች ከበረቱ ቢጠፉ: ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ: እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል:: በመድኃኒቴ አምላክ ሐሴት አደርጋለሁ:: +"+ (ዕን. 3:17) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

✝✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ ጥቅምት ፮ (6) ❖ ✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱስ "ዲዮናስዮስ ሐዋርያዊ" ወአባ "ዸንጠሌዎን" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞ +"+ ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሐዋርያዊ ሊቅ +"+ =>በዘመነ ሐዋርያት ከነበሩና አስደናቂ ታሪክ ከነበራቸው ቅዱሳን አንዱ ይህ አባት ነው:: ቅዱስ ዲዮናስዮስ በትውልዱ አረሚ (ግሪካዊ) የሆነ ፈላስፋ: ከነ አሪስቶትል ሲያያዝ የመጣውን ፍልስፍና ጨርሶ በማጥናቱ ርዕሰ ሊቃውንት (የፈላስፎች አለቃ) የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር:: +በግሪክ አቴና (ATHENS) ለነበሩ ፈላስፎችም ሁሉ የበላይ ሲሆን በአርዮስፋጐስ (ሐዋ. 17) ታላቁ ሰው እርሱ ነበር:: ይህ ሁሉ ሲሆን ግን እድሜው ገና ወጣት ነበር:: ቅዱስ ዲዮናስዮስ ፈላስፋ ስለ ሆነ ቅሉ ይመራመር ነበር:: +ይልቁኑ ስለ እውነተኛው አምላክ ያስብ ነበር:: በግሪክ ምድር ከሚመለኩ 250 አማልክት መካከል ቁም ነገር አልተገኘምና:: ነገር ግን አንድ ቀን ዓለም በተፈጠረች በ5,534 ዓመት: መጋቢት 27 ቀን: በዕለተ ዓርብ: 6 ሰዓት ላይ ምድር ተናወጠች:: ፀሐይ ጨለመች: ጨረቃ ደም ሆነች: ከዋክብትም ረገፉ:: +በዚህ የተደናገጡ የአቴና (ATHENS) ነዋሪዎችና ፈላስፎች ወደ ዲዮናስዮስ ተሰብስበው "መምሕራችን የተፈጠረውን ነገር መርምረህ አስረዳን" አሉት:: +ዲዮናስዮስም ባለው ጥበብ ባሕሩን: የብሱን: ፀሐይ: ጨረቃን: ከዋክብትን መረመራቸው:: "ወረከቦሙ ኅዱዓነ" እንዲል በቀደመ ቦታቸው አገኛቸው:: ግራ ቢገባው እንቅልፍ ከዐይኑ ተከለከለ:: +ከዚያም ወደ ቤተ መዛግብቱ ገብቶ መጻሕፍትን ሲያገላብጥ "አርስጣላባ" የሚባል ግዙፍ መጽሐፍ አግኝቶ ቢገልጠው "እልመክኑን" የሚል ጽሑፍ አገኘ:: ወደ ውጪ ወጥቶ በሕዝቡና ጠቢባኑ ፊት ልብሱን ቀድዶ አለቀሰ:: +እነርሱም ደንግጠው "ምነው መምሕራችን? ምን ሆንህ?" ቢሉት "የማይታየው አምላክ ቢወርድ በምቀኝነት ገደሉት የሚል ጽሑፍ አገኘሁ" አላቸው:: "እልመክኑን" ማለት "የማይታይ አምላክ" ማለት ነውና:: "ዘኢያስተርኢ ኅቡዕ እስመ አስተርአየ ለነ: እሳት በላኢ አምላክነ" እንዲል:: +ከዚህ በሁዋላ ደቀ መዛሙርቱን (ተማሮቹን) ጠርቶ (ኡሲፎስና ኡርያኖስ ይባላሉ) "እልመክኑን" የሚለውን ስም "ከቤተ ጣዖቱ በር ላይ ለጥፉት" ብሏቸው ለጠፉት:: በእንዲህ ያለ መንገድ 14 ዓመታት አልፈው ቅዱስ ዻውሎስ ወንጌልን እየሰበከ አቴና ደረሰ:: ዘመኑም በ48 ዓ/ም ነበር:: +ወደ ከተማዋ ሲገባ በጣዖት ቤቱ በር ላይ የተለጠፈውን ጽሑፍ ተመለከተና ያስተምራቸው ያዘ:: ትምሕርቱን የሰሙ ጠቢባኑና ሕዝቡ ሐዋርያውን ይዘው ወደ ዲዮናስዮስ ፊት አቀረቡት:: "ምንድን ነው በደሉ?" ቢላቸው "አዲስ አምላክን ሲያስተምር አግኝተነዋል" አሉት:: +ቅዱስ ዻውሎስም "እኔ አዲስ አምላክን የምሰብክላችሁ አይደለሁም:: ይልቁኑ ከቀድሞም የፈጠራችሁ: ቀጥሎም የሞተላችሁ: እናንተም "እልመክኑን" ብላችሁ ሳታውቁት ታመልኩት የነበረውን ጌታ እንጂ:: እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው አላቸው:: +ዲዮናስዮስም ቅዱስ ዻውሎስን "ለዚህ ምን ምልክት አለህ?" ቢለው "የዛሬ 14 ዓመት: መጋቢት 27 ቀን: በዕለተ ዓርብ 6 ሰዓት ላይ ታላላቅ ተአምራት የተደረጉ አይደለምን! እነዚህ ሁሉ የተደረጉት በስቅለቱ ጊዜ ነው" ሲል መለሰለት:: +ዲዮናስዮስም ፈጥኖ በክርስቶስ አመነ:: የአካባቢው ጠቢባንና ሕዝቡም አምነው ከመሪያቸው ጋር ተጠመቁ:: ቅዱስ ዻውሎስም ቅዱስ ዲዮናስዮስን አስተምሮ የአቴና የመጀመሪያው ዻዻስ አደረገው:: ቅዱሱም ክርስቲያኖችን ያበዛ: መንጋውንም ያጸና ዘንድ ብዙ ተጋ:: +በተለይ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩ ታዋቂ ደራስያን አንዱ ሆነ:: በርካታ ድርሰቶችንም በመንፈስ ቅዱስ ደረሰ:: ዛሬ ድረስ እንኩዋ ሃይማኖተ አበው ውስጥ የሚገኘው ድርሰቱ (ዘዲዮናስዮስ) ጣዕሙ ልዩ ነው:: ቅዱሱ ለብዙ ዘመናት ለወንጌል አገልግሎት ተግቶ: በዚህች ቀን የአካባቢው አገረ ገዥ አንገቱን አስቆርጦት ሰማዕት ሆኗል:: +የሚገርመው ግን ሲገድሉት በቦታው ሰው ስላልነበረ ቅዱሱ ተነስቶ: ተቆርጣ የወደቀች ራሱን አነሳት:: በጐኑ አቅፎም ደቀ መዛሙርቱ እስካሉበት ሒዶ በፊታቸው ዘንበል አለ:: ምዕመናንም እያለቀሱና እየዘመሩ ከአርድእቱ ኡሲፎስና ኡርያኖስ ጋር ቀብረውታል:: እነርሱም አብረውት ተሰይፈዋልና:: +"+ አባ ዸንጠሌዎን ዘጾማዕት +"+ =>ታላቁ ጻድቅ: ሰባኬ ወንጌልና ገዳማዊ አባ ዸንጠሌዎን የተስዓቱ (ዘጠኙ) ቅዱሳን መሪ (አባት) ናቸው:: ጻድቁ ሃገረ ሙላዳቸው ሮም ቢሆንም ገድላቸውን የፈጸሙት በኢትዮዽያ ነው:: +ወላጆቻቸው በሮም ቤተ መንግስት የቀኝ መንበር ያላቸው ክቡራን ቢሆኑም ልጃቸውን ይማር ብለው ወደ ገዳም ከተቷቸው:: በገዳም ትምሕርቱን ከጠነቀቁ በሁዋላ በዚያው ጠፍተው ወደ ግብጽ ወረዱ:: በዚያም መነኮሱ:: +እድሜአቸው እየገፋ ሲሔድ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት 8ቱን ቅዱሳን ሰብስበው: በአቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል) መሪነት ወደ ሃገራችን መጡ:: በ470ዎቹ አካባቢ የነበረው ንጉሥ አልዓሜዳም በክብር ተቀብሎ አክሱም ውስጥ "ቤተ - ቀጢን" የሚባል ቦታን ሰጣቸው:: +ዘጠኙ ቅዱሳን በአንድነት: ቀን ቀን ወንጌልን ሲያስተምሩ ውለው ሌሊት ሲጸልዩና መጻሕፍትን ሲተረጉሙ ያድሩ ነበር:: ነገር ግን ለየብቻቸው መኖራቸውን መንፈስ ቅዱስ ስለ ወደደ ሁሉም በየራሳቸው ገዳማትን መሠረቱ:: +አባ ዸንጠሌዎንም ከአክሱም ከተማ በላይ ከደብረ ቆናጽል ጐን ወደ ሚገኝና 'ጾማዕት' ወደ ሚባል ረዥም ተራራ ወጡ:: ቦታው ዛሬ "እንዳባ ዸንጠሌዎን" ይባላል:: በዚያም አስቀድመው ለወንጌል አገልግሎት እየተጉ ድውያንን ፈወሱ:: +ሙታንን አስነሱ: አጋንንትን አሳደዱ:: ብዙ ተአምራትንም አደረጉ:: እንዲያውም አንድ ቀን ወይራውን በጧት ተክለው: በሠርክ ትልቅ ዛፍ ሆነላቸው:: ከዚያ ዘንጥፈው እሳቱን በቀሚሳቸው ላይ አፍመው ማዕጠንት አሳርገዋል:: +የሚገርመው ያ ዛፍ ዛሬም ድረስ ለምስክርነት ቁሟል:: እኛም ሳይገባን ሔደን በዓይናችን አይተነዋል:: አምላከ ቅዱሳን ግሩም ነው !!! በመጨረሻ ዘመናቸው ግን ጻድቁ 5 ክንድ ርዝመት ባላት ጾማዕት (በዓት) ውስጥ ገብተው ቆሙ:: ለ45 ዓመታት ሳይቀመጡና ሳይተኙ በእንባ ቢጸልዩ ቅንድባቸው ተላጠ:: አካላቸውም በአጥንቱ ብቻ ቀረ:: +በ6ኛው ክ/ዘመንም በዚህች ዕለት የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም መጥቶ "ወዳጄ! ስምህን የጠራ: መታሰቢያህን በእምነት ያደረገውንም ሁሉ እምርልሃለሁ" አላቸው:: ያን ጊዜ አጥንቶቻቸው ተወዛወዙና ነፍሳቸው በክብር ዐረገች:: ከዚህ አስቀድሞም ንጉሡን አፄ ካሌብን አባት ሆነው ያመነኮሱት እርሳቸው ናቸው:: =>አምላከ አበው የወጡ ወገኖቻችንን ሁሉ በሰላም ይመልስልን:: ከክብረ ቅዱሳንም አይለየን:: =>ጥቅምት 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሐዋርያዊ 2.አባ ዸንጠሌዎን ዘጾማዕት 3.ቅዱስ ዕንባቆም ነቢይ (ዕን. ከ1 - 3 ያንብቡ) 4.ቅድስት ሐና ነቢይት (የሳሙኤል እናት - 1ሳሙ. ከ1 - 2ን ያንብቡ) 5.ቅዱሳን ኡሲፎርና ኡርያኖስ (ሰማዕታት) 6.አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ኢትዮዽያዊ (ፍልሠቱ) 7.ቅዱስ ሄኖስ ነቢይ

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ ጥቅምት ፭ (5) ❖ ✞✞✞ እንኩዋን ለጻድቁ "አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ" እና "ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞ +"+ አቡነ ገብረ ሕይወት +"+ =>ጻድቁ የተወለዱት ግብፅ (ንሒሳ አካባቢ) ሲሆን አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ:: አባታችን ገብረ ሕይወት የጻድቃን አለቃ: የቅዱሳን የበላይ: ተጋድሎአቸውና ድንቅ ተአምራቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ቅዱስ ሰው ናቸው:: +የጻድቁን ክብር መናገር የሚችል ምን አነደበት ይኖራል? እንደ ምንስ ባለ ብራና ይጻፋል? ዜናቸውንስ ለመስማት የታደለ እንደ ምን ዓይነት ሰው ይሆን? +አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለ562 ዓመታት በዚህች ዓለም ሲኖሩ እህል ያልቀመሱ (ምግባቸው ምስጋና ነውና): ልብስ ያልለበሱ (ጠጉር አካላቸውን ይሸፍን ነበርና): ሐዋርያዊ ሆነው ከግብፅ እስከ ኢትዮዽያ ብዙ ነፍሳትን ያዳኑ አባት: ሃገራችንን አስምረው: አስራት እንድትሆናቸውም ተቀብለው ምድረ ከብድ አካባቢ አርፈዋል:: +ጻድቁ ገብረ መንፈስ ቅዱስም: ገብረ ሕይወትም ይባላሉ:: በ562 ዓመታት ሕይወታቸው እንደ ሐዋርያት ከምድረ ግብጸ እስከ ኢትዮዽያ ወንጌልን ሰብከዋል:: በዚህም በሚሊየን (አእላፍ) ለሚቆጠሩ ነፍሳት የድኅነት ምክንያት ሆነዋል:: +ጻድቁ እንደ ሰማዕታትም ከከሃዲ ሰዎች ብዙ መከራን ተቀብለዋል:: እንደ ባሕታውያን ለብዙ መቶ ዓመታት ሰው ሳያዩ ቆይተዋል:: ለየት የሚለው ግን የጽድቅ ሕይወታቸው ነው:: ከእልፍ አዕላፍ አጋንንት ጋር ተዋግተው ድል ማድረግ ችለዋልና:: +የንሒሳው ኮከብ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለኢትዮዽያ ልዩ ፍቀር አላቸው:: ስለ ሃገሪቱና ሕዝቧ ፍቅር ሲሉ ለ100 ዓመታት በደብረ ዝቁዋላ መከራን ተቀብለዋል:: ምሕረትን ሲለምኑ ሥጋቸው አልቆ በአጥንታቸው ቁመው ነበርና ሃገራችን አሥራት ሆና ተሰጠቻቸው:: +ስለዚህም ነው በሃገሪቱ ውስጥ ከ2,000 በላይ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳማትና አድባራት ዛሬም ድረስ ያሉት:: በ8ኛው ክ/ዘመን አካባቢ የተወለዱት አባታችን ያረፉት በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ ነው:: ፍጥረታትን ሁሉ አዘው መጋቢት 5 ቀን ሲያርፉ ግሩማን መላእክት ገንዘው አካላቸውን ሠውረዋል:: +ሥላሴን የተሸከመ አካላቸው በጐልጐታ ተቀብሯል የሚሉም አሉ:: "ሰላም ለመቃብሪከ ዘኢተከሥተ ለባዕድ: ከመ መቃብሩ ለሙሴ ወልደ ዮካብድ: ዜና መቃብሪከሰ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸማድ: ቦ ዘይቤ በኢየሩሳሌም አጸድ: ወቦ ዘይቤ ኀለወ በከብድ::" እንዲል:: +የጻድቁ በዓል ጥቅምት 5 ቀን የሚከበረው ብዙ ጊዜ መጋቢት 5 ዐቢይ ጾም ውስጥ ስለሚውል ተውላጥ (ቅያሪ) ሆኖ ነው:: +"+ ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ +"+ =>ይህ ቅዱስ አባት ስም አጠራሩ የከበረ: ሽምግልናውም ያማረ ነው:: ብዙዎቻችን የምናውቀው በበዓለ መስቀል ስሙ ተደጋግሞ ሲጠራ ነው:: ግን ይህ ታላቅ ሰው ለቅድስት እሌኒ መካነ መስቀሉን አሳያት ከሚል አረፍተ ነገር የዘለለ ታሪኩ ሲነገርለት ብዙ ጊዜ አንሰማምና እስኪ በዕለተ ዕረፍቱ ስለ ቅዱሱ ጥቂት እንበል:: +ቅዱስ ኪራኮስ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን እናቱ ቅድስት ሐና ትባላለች:: በእጅጉ የተባረከች ሴት ናት:: ምንም በነገዳቸው አይሁድ ቢሆኑም የዘመኑ የአይሁድ ክፋት አልገዛቸውም:: የተባረከች እናቱ ታሪክ እያስጠናች ከማሳደጉዋ ባለፈ አስቀድማ ኦሪቱን: ነቢያቱን እንዲያውቅ አደረገች:: +አስከትላም ሕገ ክርስትናን እንዲረዳ አደረገችው:: የታሪክና የመጻሕፍት ምሑሩ ቅዱስ ኪራኮስ ከእናቱ ጋር ሆኖ እግዚአብሔርን እያገለገለ: ክርስቶስን እያመለከ ቆየ:: በዚህ ጊዜ ግን እድሜው እየገፋ ነበር:: +ሠለስቱ ምዕት (318ቱ ሊቃውንት) ጉባኤያቸውን ከፈጸሙ በሁዋላ ቅድስት እሌኒም መስቀሉን ፍለጋ ስትወጣ ትልቁ ፈተናዋ የተቀበረበትን ቦታ ማወቅ አለመቻሏ ነበር:: እንዲያውም አማራጭ ስታጣ በአካባቢው የነበሩ አይሁድን ምሥጢር እንዲያወጡ ቀጥታቸው ነበር:: በሁዋላ ግን ኪራኮስ ስለሚባል ደግ ታሪክ አዋቂ ሰው ሰምታ ተገናኙ:: +ቅዱስ ኪራኮስም አባቶቹ አይሁድ ናቸውና አካባቢውን ያውቀው ነበር:: ችግሩ ቆሻሻው ተራራ በመሆኑ ከ3ቱ የትኛው እንደ ሆነ አለመታወቁ ነበር:: ቅዱሱ ግን ለዚህም መፍትሔ ነበረውና "ደመራ ደምረሽ: በእሳት አቃጥለሽ: እጣን ጨምሪበትና ይገለጥልሻል" አላት:: +ቅድስት እሌኒም የተባለችውን በትክክል ፈጽማ የመድኅን ክርስቶስን ቅዱስ ዕጸ መስቀል አገኘች:: ቅድስት እሌኒ ወደ ሃገሯ ከተመለሰች በሁዋላም ቅዱስ ኪራኮስ በኢየሩሳሌም አካባቢ ዻዻስ ሆኖ ተሾመ:: +አረጋዊው ቅዱስ የሚገርም እረኛ ነውና የባዘኑትን ሲፈልግ: በቤቱ ያሉትንም ሲያጸና ብዙ ደከመ:: በቅርቡ ያሉትን በአፉ: የራቁትን ደግሞ በጦማር (በመልእክት) አስተማረ:: በወቅቱ በአካባቢው ኤልያኖስ የሚሉት ከሃዲ ንጉሥ ነበርና በቅዱስ ኪራኮስ ላይ ተቆጣ:: +ወደ እርሱ አስጠርቶ በአደባባይ: ቅዱስ ቃሉን ይጽፍበት የነበረው ቀኝ እጁን አስቆረጠው:: ቅዱስ ኪራኮስ ግን እጁ መሬት ላይ ወድቃ: ደሙ እየተንጠፈጠፈ ተናገረ:- "አንተ ልብ የሌለህ ንጉሥ! እጄን ቆርጠህ ከክርስቶስ ፍቅር ልትለየኝ አትችልም" አለው:: +በዚህ የተበሳጨ ንጉሡ እሳት አስነድዶ: አልጋውን አግሎ ቅዱሱን ጠበሰው:: ኪራኮስ ግን በእሳቱ ላይ ሳለ ወደ እሥራኤል ፈጣሪ በእብራይስጥኛ ጸለየ:: በማግስቱ እናቱን ቅድስት ሐናን አምጥተው የነደደ እሳት ውስጥ ጣሏት:: +ለ3 ሰዓት ያህል በእሳት ውስጥ ስትጸልይ ቆይታ በጦር ወግተው ገደሏት:: ቅዱስ ኪራኮስንም ለአራዊት ሰጡት:: አራዊቱ ሰገዱለት:: በሌሎች ዓይነት ስቃዮችም ፈተኑት: ግን እንቢ አላቸው:: በመጨረሻው በዚህ ቀን ገድለውት የክብርን አክሊል ተቀዳጅቷል:: =>አምላከ ቅዱሳን በእነርሱ ላይ የበዛች ፍቅሩን ለእኛም ያድለን:: ፍሬ ትሩፋት: ፍሬ ክብር እንድናፈራም ይርዳን:: ክብራቸውንም አያጉድልብን:: =>ጥቅምት 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ 2.ቅዱስ ኪራኮስ አረጋዊ (ዻዻስ ወሰማዕት) 3.ቅድስት ሐና ሰማዕት (እናቱ) 4.ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ (ከ12ቱ ሐዋርያት) 5.አባ ዻውሎስ ሰማዕት (አርዮሳውያን አንቀው የገደሉት አባት) =>ወርሐዊ በዓላት 1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት 2.ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም 3.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ 4.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ 5.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ) =>+"+ ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት: እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ:: በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና:: +"+ (ገላ. 6:14) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

✝️✝️✝️††† እንኳን ለታላቁ ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐጺር ዓመታዊ የፍልሠት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ††† ††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ††† †††✝️✝️ ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐጺር †††✝️✝️ ††† በቤተ ክርስቲያን ያሉ አበው ሊቃውንት እንደሚሉት ከቅዱሳን በቁመቱ የአባ #አርሳኒን ያክል ረዥም አልነበረም:: እርሱ እንደ ዝግባ ቀጥ ያለ ነበር:: በዚያው ልክ ደግሞ የቅዱስ ዮሐንስን (ዛሬ የምናከብረውን) ያህል አጭር አልነበረም:: በዚህ ምክንያት ይሔው ለዘለዓለም " #ዮሐንስ_ሐጺር- አጭሩ አባ ዮሐንስ" ሲባል ይኖራል:: ሊቃውንትም ቁመቱንና ቅድስናውን በንጽጽር ሲገልጡ:- "ሰላም ሰላም ዕብሎ በሕቁ: ለዮሐንስ ሐጺር ዘነዊኅ ሒሩተ ጽድቁ" ይላሉ:: "ቁመቱ እጅግ ያጠረ: ጽድቁ ግን ከሰማይ የደረሰ ቅዱስ ዮሐንስን ሰላም ሰላም እንለዋለን" እንደ ማለት ነው:: ቅዱሱ የተወለደው በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በምድረ ግብጽ ነው:: ወላጆቹ ምንም ከሥጋዊ ሃብት ድሆች ቢሆኑም ባለ መልካም ክርስትና ነበሩና በጐውን ሕይወት አስተምረውታል:: ወደ ምናኔ የገባው ገና በ18 ዓመቱ ሲሆን የታላቁ አባ ባይሞይ ደቀ መዝሙር ሆኖ ተጋድሎንና ትሕርምትን ተምሯል:: ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር በወቅቱ ከነበሩ ቅዱሳን ከቁመቱ ባሻገር በትሕትናው: በትእግስቱና በመታዘዙ ይታወቅ ነበር:: አባ ባይሞይ ይጠራውና ያለ ምንም ምክንያት ደብድቦ ያባርረው ነበር:: እርሱ ግን "ምን አጠፋሁ?" ብሎ እንኩዋ ሳይጠይቅ "አባቴ ሆይ! ማረኝ?" እያለ ከእግሩ ሥር ይወድቅ ነበር:: ለብዙ ጊዜ በተመሳሳይ ሲደበድበው: እርሱም እርሱው ተደብድቦ: እርሱው ይቅርታን ሲጠይቅ ኖረ:: አንድ ቀን ግን እንደ ልማዱ ሊገርፈው ሲሔድ 7ቱ ሊቃነ መላእክት ከበውት አይቶ ደንግጦ ተመልሷል:: #አባ_ባይሞይ ይሕንን ሁሉ የሚያደርገው ጠልቶት ወይ ክፉ ሆኖ አይደለም:: አንድ ሰው የሌላኛውን ግፍ መቀበል ካልቻለ ሰይጣንን ድል አይነሳም የሚል ትምሕርት ስለ ነበረ ነው እንጂ:: አንድ ቀን ቅዱስ ዮሐንስ ወደ መምሕሩ ቀርቦ "አባቴ ጅብ ካገኘሁ ምን ላድርግ?" ሲል ጠየቀው:: (የአካባቢው ጅብ መናጢ ነበር) አባ ባይሞይ ግን "ይዘህልኝ አምጣው" አለው:: ትዕዛዝ ነውና ቅዱሱ ወደ በርሃ ወርዶ: ጅብ አልምዶ ይዞለት መጥቷል:: ሌላ ቀን ደግሞ አባ ባይሞይ ቅዱስ ዮሐንስን ጠራውና ተፈልጦ የወደቀ ደረቅ እንጨት ሠጠው:: "ምን ላድርገው አባ?" አለው:: "ትከለውና እንዲያፈራ አድርገው:: ከዚያ አምጥተህ አብላኝ" ሲል መለሰለት:: ይህ ነገር ከተፈጥሮ ሥርዓት ውጪ መሆኑን እያወቀ ቅዱስ ዮሐንስ "እሺ" ብሎ ወስዶ ተከለው:: ከዚያም ለ2 ዓመታት ሳይታክት ውሃ አጠጣው:: ውሃውን የሚያመጣበት ቦታ ደግሞ 10 ኪሎ ሜትር ያህል ከገዳሙ ይርቅ ነበር:: ቅዱሱ ላቡን እያፈሰሰ አሁንም ማጠጣቱን ቀጠለ:: በ3ኛው ዓመት ግን ለምልሞ አበበ: ደግሞም አፈራ:: ካፈራው በኩረ ሎሚም ወስዶ ለመምሕሩ "አባቴ! እንካ ብላ" ብሎ ሰጠው:: አባ ባይሞይ ግን ማመን አልቻለም:: እጅግ አደነቀ: አለቀሰም:: ወዲያው ያን ፍሬ ታቅፎ ወስዶ ለገዳሙ መነኮሳት አላቸው:- "ንሱ ብሉ: በረከትንም አግኙ:: ይህ የዛፍ ሳይሆን የመታዘዝ ፍሬ ነው::" ቅዱስ ዮሐንስ አባ ባይሞይ ቢታመም ለ12 ዓመት አስታሞታል:: መምሕሩ ከማረፉ በፊትም መነኮሳቱን ሰብስቦ የቅዱስ ዮሐንስን እጅ አስጨበጣቸው:: "ይህ የያዛችሁት እጅ የሰው ሳይሆን የመልአክ እጅ ነው" ብሏቸው ዐርፏል:: ቅዱስ ዮሐንስም ከዓመታት ቆይታ በሁዋላ የገዳሙ አበ ምኔት ሆኖ አገልግሏል:: ብዙ ነፍሳትንም ለቅድስና ማርኩዋል:: #መላእክት ንጽሕናው ደስ ስለሚያሰኛቸው አብረውት ይውሉ ነበር:: ሲተኛም በተራ በተራ ክንፋቸውን ያለብሱት ነበር:: ምጽዋትን በጣም ስለሚወድ ሰፌድ እየሰፋ ይሸጥና ገንዘቡን ለነዳያን ያን ያካፍል ነበር:: አንድ ቀን እንደ ልማዱ ወደ ገበያ ወጥቶ ሳለ ተደሞ (ተመስጦ) መጣበት:: ሰማያት ተከፍተው: ቅዱሳን #ሊቃነ_መላእክት #ሚካኤል እና #ገብርኤል በግርማ በጌታ ፊት ቆመው ተመለከተ:: "እጹብ: እጹብ" እያለ ሲያደንቅ አንድ ገዢ መጥቶ "ባለ እንቅብ ዋጋው ስንት ነው?" ቢለው "እኁየ ሚካኤልኑ የዓቢ ወሚመ ገብርኤል - ከሚካኤልና ከገብርኤል ማን ይበልጣል?" ብሎታል:: ገዢውም ደንግጦ "እብድ መነኩሴ" ብሎት ሔዷል:: ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ወደ #ባቢሎን (የአሁኗ ኢራቅ) ሒዶ ከተመለሰ በሁዋላ በበርበሮች ምክንያት ከአስቄጥስ ወደ #ቁልዝም ተሰዷል:: በዚያም በአባ እንጦንስ በዓት ውስጥ ዐርፏል:: ለ400 ዓመታት በዚያው ቆይቷል:: በ825 ዓ/ም ግን በአባ #ዮሐንስ_ፓትርያርክ ዘመን ክቡር ሥጋው ወደ #ገዳመ_አስቄጥስ ተመልሷል:: ቅዱሱ ያረፈው ጥቅምት 20 ቀን ሲሆን ዛሬ ሥጋው የፈለሠበት ነው:: በዚህ ዕለትም የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርና የታላቁ #ቅዱስ_መቃርስ ሥጋ በተገናኙ ጊዜ ግሩም ተአምር ተደርጉዋል:: ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሲገባም ታላቅ የብርሃን ጐርፍ ሲፈስ ታይቷል:: ሰማያዊ መዓዛም አካባቢውን ሞልቶታል:: ከዻዻሳቱ አንዱ እባረካለሁ ብሎ የቅዱስ ዮሐንስን ሥጋ ቢገልጠው አካባቢው ተናወጠ:: መባርቅትም (መብረቆች) ተብለጨለጩ:: ደንግጠው ቶሎ ቢያለብሱት ጸጥታ ሆኗል:: በዚህ ሁሉ ደስ ያላቸው አበው ቅዱሱን በዝማሬ ሲያወድሱት ውለዋል:: ††† አምላከ ቅዱሳን የሐጺር ቅዱስ ዮሐንስን መታዘዙን: ትሕትናውን: ትእግስቱንና ቅንነቱን ያድለን:: በበረከቱም ይባርከን:: ††† ነሐሴ 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 1.ቅዱስ አባ ዮሐንስ ሐጺር (ፍልሠቱ) 2.ቅዱስ አትናቴዎስ ሰማዕት 3.ቅዱሳን ገርሲሞስና ቴዎዶጦስ (ሰማዕታት) 4.አባ ባስልዮስ ጻድቅ (ዘትግራይ) ††† ወርኀዊ በዓላት 1.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት 2.ቅድስት አርሴማ ድንግል 3.ቅዱስ ዼጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት 4.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ 5.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮዽያዊት 6.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት) ††† "እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ 'የማንጠቅም ባሪያዎች ነን: ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል' በሉ::" ††† (ሉቃ. 17:10) †††✝️✝️ ወስብሐት ለእግዚአብሔር✝️✝️ †††

ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ): : ✝️††† እንኩዋን ለታላላቁ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት: ቅድስት ክርስቶስ ሠምራና ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✝††† ††† ✝ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ ††† *ልደት* =>መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው:: እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል:: +በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል: ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በሁዋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል:: +ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የጸነሱት መጋቢት 24 ቀን በ1206 ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታሕሳስ24 ቀን በ1207 ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል:: *ዕድገት* =>የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል:: ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት: ሐዲሳትን) ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ዻዻስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል:: *መጠራት* =>አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮስ ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አእላፍ መላእክት እያመሰገኑ በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ:: +የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:: "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: ከዚህ በሁዋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በሁዋላ ሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ:: *አገልግሎት* =>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዻዻሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮዽያ 2 መልክ ነበራት:: +1ኛ ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል:: +2ኛው ደግሞ በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር:: +ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን (ጠንቁዋዮችን) አጥፍተዋል:: *ገዳማዊ ሕይወት* =>ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮዽያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል:: +እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ12 ዓመታት: በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26 ዓመታት አገልግለዋል:: +በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በሁዋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል:: *ስድስት ክንፍ* =>ኢትዮዽያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮዽያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር:: +የወቅቱ ሊቀ ዻዻሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በሁዋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር:: +ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:- -በቤተ መቅደስ ብስራቱን -በቤተ ልሔም ልደቱን -በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን -በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን -በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር:: +የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ:: በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ ተክልየን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው:: +በዚያም:- -የብርሃን ዐይን ተቀብለው -6 ክንፍ አብቅለው -የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው -ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው -ከ24ቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው -ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው -"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል:: *ተአምራት* =>የተክልየ ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው:: *ሙት አንስተዋል *ድውያንን ፈውሰዋል *አጋንንትን አሳደዋል *እሳትን ጨብጠዋል *በክንፍ በረዋል *ደመናን ዙፋን አድርገዋል:: +ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕጻናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና:: *ዕረፍት* =>ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው መከራን በብዙ ተቀብለው: እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው ነሐሴ 24 ቀን በ1306 ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10 ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል:: ††† ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ††† =>እጅግ የከበረችና የተመሰገነች እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን እናመሰግናታለን:: እርሷ በሁሉ ጐዳና ፍጹምነትን ያሳየች ኢትዮዽያዊት እናት ናት:: ገና ከልጅነት የነበራት የትሕትናና የመታዘዝ ሕይወት እጅግ ልዩ ነበር:: እናታችን ቅድስናን ያገኘችው ገና በትዳር ውስጥ እያለች ነው:: +ከተባረከ ትዳሯ 12 ልጆችን አፍርታ: ምጽዋትን የዕለት ተግባሯ አድርጋ ኑራለች:: በዚህ ደግነቷም ሙት እስከ ማንሳት ደርሳለች:: አብያተ ክርስቲያናትን አንጻ አንድ ልጇን (ዳግማዊ ቂርቆስን) አዝላ ምናኔ ወጥታልች:: +በደብረ ሊባኖስ ውስጥ የቆየችው ቅድስት እናት ተጋድሎዋን የፈጸመችው ግን ጣና ሐይቅ ውስጥ ነው:: በተለይ ለ22 ዓመታት ሐይቁ ውስጥ አካሏ አልቆ: አሣ በሰውነቷ ውስጥ እስከሚያልፍ ድረስ ተጋድላለች:: በቀኝና በግራ 12 ጦሮችን ተክላም ጸልያለች:: +ብዙ ኃጥአንን አማልዳ: 12 ክንፎችን አብቅላ: ከፍ ከፍ ብላለች:: ከርሕራሔዋ ብዛት የተነሳ ሰይጣንን እንኩዋ ለማስታረቅ ሞክራለች:: ጌታም ከሲዖል ነፍሳትን እንድታወጣ ፈቅዶላታል:: ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ያረፈችው በዚህ ዕለት ሲሆን አጽሟ ዛሬ በራሷ ገዳም (ጣና ዳር) ይገኛል:: +" ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ "+ =>ቅዱስ ቶማስ "መርዓስ" በምትባል ሃገር የፈለቀ የንጋት ኮከብ: ጻድቅ: ገዳማዊ: ዻዻስ: ሐዋርያ: ሰማዕትና ሊቅ ነው:: የዚህን ቅዱስ ተጋድሎ እንደ እኔ ያለው ሰው አይቻለውም:: የእርሱ ሕይወት ክርስትና ምን እንደ ሆነ ያሳያል::

††† እንኳን ለሰላሳ ሺ ግብጻውያን ሰማዕታት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ††† ††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ††† ††† ሠለስቱ እልፍ ሰማዕታት ††† ††† ዘመነ ሰማዕታት አርባ ሰባት ሚሊየን ክርስቲያኖችን በአርባ ዓመታት ከበላ በኋላ በ305 (312) ዓ/ም ቢጠናቀቅም ስለ ሃይማኖት መሞት ግን እስከ ምጽዓት ድረስ ይቀጥላል:: ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ከሚቀርቡ ፈተናዎች ሁሉ እጅግ ከባዱ ይሔው ሰማዕትነት ነውና ሊቀበለው ያለው (ያደለው) ይቀበለዋል:: ቤተ ክርስቲያን በባሕር ላይ ያለች መርከብ ናትና ዘወትር በፈተና ውስጥ መኖሯ የሚጠበቅ ነው:: ዘመነ ሰማዕታትን ተከትሎ የመጣው የመናፍቃን ዘመን ሲሆን ለመቶ ሃምሳ ዓመታት ያህል መናፍቃን እንደ አሸን ፈልተዋል:: በዚያው ልክ ከዋክብት ቅዱሳን ሊቃውንት ነበሩና በየጊዜው ጉባኤያትን እየሠሩ: መናፍቃንን አሳፍረዋል:: ምዕመናንንም አጽንተዋል:: በ451 ዓ/ም የተፈጸመው ድርጊት ግን ዛሬም ድረስ ጠባሳው የሚለቅ አልሃነም:: ንጉሡ መርቅያንና ጳጳሱ ልዮን የንስጥሮስን ትምሕርት አለባብሰው ሊያስተምሩ ሲሞክሩ ግጭት በመፈጠሩ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሁለት ተከፈለች:: በጉባኤው የነበሩ ስድስት መቶ ሰላሳ ስድስት ጳጳሳት ስቃይና ሞትን ፈርተው በኑፋቄ መጽሐፍ ላይ በመፈረማቸው "መለካውያን" (ከእግዚአብሔር ይልቅ ለንጉሥ የሚታዘዙ) ተባሉ:: ጉባኤውም "ጉባኤ ከለባት" (የውሾች ስብሰባ): "ጉባኤ አብዳን" (የሰነፎች ጉባኤ) ተብሏል:: የወቅቱ የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ግን "በኑፋቄው ላይ አልፈርምም::" ከማለቱ አልፎ መናፍቃኑን አወገዛቸው:: በዚህ ምክንያት ጽሕሙን ነጭተው: ጥርሱንም አርግፈው: ወደ ጋግራ ደሴት ከሰባት ደቀ መዛሙርቱ ጋር አሳደዱት:: በዚያም ለሦስት ዓመታት ቆይቶ በ454 ዓ/ም ዐረፈ:: እግዚአብሔር ፈርዶባቸው ንጉሡ መርቅያን እና ንግሥቲቱ ብርክልያ (ክፉ ሴት ናት) ድንገት ሞቱ:: ፈተናው ግን በዚህ አላበቃም:: በዙፋኑ የተተካው ሌላኛው ጨካኝ ልዮን ነበር:: መንፈሳዊውን አርበኛ አባ ዲዮስቆሮስን በሞት ያጡት የግብጽ ክርስቲያኖች ደቀ መዝሙሩን "አባ ጢሞቴዎስን እንሾማለን::" ቢሉ ንጉሡ ከለከለ:: የሚሾመው መለካዊ ነው ብሎ አብሩታርዮስ የሚባል መናፍቅ ጳጳስ በላያቸው ላይ ሾመባቸው:: ይህንን መታገስ ለሕዝቡና ለካህናቱ ከባድ ነበር:: ተኩላ እንኳን በበጐች ላይ በይፋ ተሹሞ: ተደብቆም ቢሆን እየነጠቀ መብላት ልማዱ ነው:: መናፍቁ ጳጳስ በተለያየ መንገድ ሕዝቡን ለመሳብ ሞክሮ ነበር:: ለምሳሌ አውጣኪን (የክርስቶስን ሰው መሆን ምትሐት የሚል 'የቱሳሔ' አስተማሪ መናፍቅ ነው::) አወገዘው:: እነሱ ግን ተረድተውታልና ቦታ አልሰጡትም:: ምክንያቱም አውጣኪ ከቀድሞም የተወገዘ መናፍቅ ነውና:: የሚገርመው ከሕዝቡ አንድስ እንኳ ከመናፍቁ ጳጳስ የሚባረክ አልነበረም:: ሥጋውን ደሙንም ከእውነተኛ ካህናት በድብቅ ይቀበሉ ነበር:: አንድ ቀን ግን መናፍቁ ጳጳስ አብሩታርዮስ ተገድሎ ተገኘ:: (መልአክ ቀሥፎት ነው የሚሉ አሉ:: እስካሁን ድረስ የገዳዩ ማንነት አልታወቀም::) ግብጻውያን ክርስቲያኖች ግን የእርሱን ሞት ሲሰሙ ደጉን እረኛ አባ ጢሞቴዎስን ሾሙ:: ችግሩ የመጣው ከዚህ በኋላ ነው:: የመናፍቁ ተከታዮች ለንጉሡ ልዮን "አንተን ንቀው: የሾምከውን ገደሉ:: ሌላ ጳጳስም ሾሙ::" ብለው መልዕክት ላኩለት:: በዚህ የተበሳጨው ልዮን ኦርቶዶክሳውያንን ባገኛችሁበት ሁሉ ግደሉ የሚል አዋጅ አወጣ:: ይህን አዋጅ ተከትሎ ሰላሳ ሺ ሰዎች በእስክንድርያ ከተማ ተጨፈጨፉ:: ገዳዮቹ ወንድ: ሴት: ሕፃን: ሽማግሌ ሳይመርጡ የክርስቲያኖችን ደም አፈሰሱ:: ለሦስት ቀናትም ግድያው ቀጥሎ እንደ ነበር ይነገራል:: ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት "ወኀጥኡ ዘይቀብሮሙ" እንዳለ ቀባሪም አጡ:: ገዳዮቹ ቀጥለውም አባ ጢሞቴዎስን አስረው አጋዙት:: ለአሥር ዓመታትም አሰቃዩት:: ከእነዚህ ዓመታት በኋላ ግን ንጉሡ ተጸጽቶ አባ ጢሞቴዎስን ወደ መንበሩ መልሶታል:: ወገኖቻችን የግብጽ ክርስቲያኖች እንኳን ያኔ ዛሬም በጽናታቸው አብነት ልናርጋቸው የሚገቡ ናቸው:: ††† አምላከ ሰማዕታት በቸርነቱ ይጠብቀን:: ከበረከታቸውም ያድለን:: ††† ነሐሴ 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 1.ሰላሳ ሺ የእስክንድርያ (ግብጽ) ሰማዕታት 2.ቅዱስ ድምያኖስ ሰማዕት ††† ወርኀዊ በዓላት 1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት 2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት 3.ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ሰሎሞን (ንጉሠ እሥራኤል) 4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ 5.ቅዱስ ዳንኤል ነቢይ 6.አባ ሳሙኤል 7.አባ ስምዖን 8.አባ ገብርኤል ††† "በጐንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብጹዓን ናችሁ:: ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ: አትናወጡም:: ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስን በልባችሁ ቀድሱት:: በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ:: ነገር ግን በየውሃነትና በፍርሃት ይሁን::" ††† (፩ጴጥ. ፫፥፲፫-፲፮) ††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

††† እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ሚክያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ††† †††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ††† ††† ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ ††† ††† ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ:: ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ:: ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል:: "እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም) የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል:: ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ::" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36) ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ::" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: (ማቴ. 13:16, 1ጴጥ. 1:10) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ:: ††† ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት ¤አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት: ¤አራቱ ዐበይት ነቢያት: ¤አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና ¤ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ:: ††† አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት ማለት:- *ቅዱስ አዳም አባታችን *ሴት *ሔኖስ *ቃይናን *መላልኤል *ያሬድ *ኄኖክ *ማቱሳላ *ላሜሕ *ኖኅ *አብርሃም *ይስሐቅ *ያዕቆብ *ሙሴና *ሳሙኤል ናቸው:: ††† አራቱ ዐበይት ነቢያት *ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል *ቅዱስ ኤርምያስ *ቅዱስ ሕዝቅኤልና *ቅዱስ ዳንኤል ናቸው:: ††† አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት *ቅዱስ ሆሴዕ *አሞጽ *ሚክያስ *ዮናስ *ናሆም *አብድዩ *ሶፎንያስ *ሐጌ *ኢዩኤል *ዕንባቆም *ዘካርያስና *ሚልክያስ ናቸው:: ††† ካልአን ነቢያት ደግሞ:- *እነ ኢያሱ *ሶምሶን *ዮፍታሔ *ጌዴዎን *ዳዊት *ሰሎሞን *ኤልያስና *ኤልሳዕ . . . ሌሎችም ናቸው:: ††† ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ:: *የይሁዳ (ኢየሩሳሌም): *የሰማርያ (እሥራኤል)ና *የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ:: ††† በዘመን አከፋፈል ደግሞ:- *ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት): *ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት) *ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት) *ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ:: ††† ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ:: ቅዱስ ሚክያስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ.ል. ክርስቶስ በ800 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው:: አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ አሥራ አራት ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል:: ሚክያስ አባቱ ሞራት (ሞሬት) ይባላል:: ሚክያስ ማለት "መኑ ከመ አምላክ - እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው!" ማለት ነው:: አንድም "መልአከ እግዚአብሔር" ማለት ነው:: የአባቶቻችን ሁሉ ስማቸው እግዚአብሔርን የሚሰብክ ነው:: ቅዱሱ ነቢይ ገና ልጅ እያለ መላእክት ያነጋግሩት ነበር:: በዚህ ምክንያት ከሰው አይቀርብም:: ትክ ብለው ሲያዩት በፊቱ ላይ ብርሃን ቦግ ቦግ እያለ ይታይ ነበር:: በወጣትነት ዘመኑ እግዚአብሔር ለትንቢት ሲጠራው በእሺታ ታዘዘ:: በሦስቱ ነገሥታት (በኢዮአታም: አካዝና ሕዝቅያስ) ዘመንም ትንቢቶችን ተናግሯል:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን: ነገሥታቱን አስተምሮ ገስጿል:: አንድ ቀን በቤተ ልሔም ሲያልፍ የዳዊት ከተማ ፈት ሁና: ዳዋ በቅሎባት ቢመለከት አዘነ:: ወዲያውም ትንቢት ተናገረላት:: "ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ: ኢትቴሐቲ እምነገሥተ ይሁዳ: እስመ እምኔኪ ይወጽዕ ንጉሥ: ዘይርዕዮሙ ለሕዝብየ እሥራኤል::" "አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተ ልሔም: የይሁዳ ነገሥታት ከነገሡባቸው ከተሞች ከቶ አታንሺም:: ወገኖቼን እሥራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ (መስፍን) ካንቺ ዘንድ ይወጣልና::" አለ:: ይኸውም አልቀረ ለጊዜው ከሚጠት በኋላ ደጉ ዘሩባቤል ነግሦባታል:: በፍጻሜው ግን የባሕርይ ንጉሠ ነግሥት ኢየሱስክርስቶስ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ተወልዶባታል:: ቅዱስ ሚክያስ ወገኖቹን ሲያስተምርና ሲመራ ኑሮ: ሰባት ምዕራፎች ያሉትን ሐረገ ትንቢት ተናግሮ: በመልካም ሽምግልና: በንጉሡ ሕዝቅያስ ዘመን ዐርፏል:: ወገኖቹ ቀብረውታል:: ጌታም በክብረ ነቢያት ከልሎታል:: ††† ቸር አምላከ ነቢያት የነቢያቱን መከራ አስቦ ከመከራ: በእንባቸውም ከእንባ ይሰውረን:: ከተረፈ በረከታቸውም አያጉድለን:: ††† ነሐሴ 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 1.ቅዱስ ሚክያስ ነቢይ ††† ወርኀዊ በዓላት 1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት 2.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ 3.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ) 4.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት 5.አባ ጳውሊ የዋህ ††† "ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መስዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን? እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጐች: ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? . . . ሰው ሆይ! መልካሙን ነግሮሃል:: እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ: ምሕረትንም ትወድ ዘንድ: ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሔድ ዘንድ አይደለምን?" ††† (ሚክ. ፮፥፮) ††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

†††✝️🌻 እንኳን ለቅዱሳት አንስት ኄራኒ ሰማዕት: ንግሥተ ሳባ እና ንግሥት ዕሌኒ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††✝️🌻 †††✝️🌻 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††✝️🌻 ††† ✝️🌻ቅድስት ኄራኒ ሐዋርያዊት ሰማዕት †††✝️🌻 ††† ይህቺ ቅድስት ወጣት መልክ ከደም ግባት: ምግባር ከሃይማኖት: ስም ከመልካምነት የተባበረላት ሰማዕት ናት:: #ኄራኒ ማለት "ሰላማዊት: የተወደደች" ማለት ነው:: አንድም በጥሬው "ሰላምና ፍቅር" ማለት ነው:: ቅድስት ኄራኒ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን በታናሽ እስያ የንጉሥ #ሉክያኖስ ልጅ ናት:: ከተወለደች ጀምሮ ስለ ክርስትና ሰምታ አታውቅም:: ምክንያቱም አባቷ ጣዖት አምላኪ ከመሆኑ ባለፈ ክርስቲያኖችን ይቀጣ ስለ ነበር ነው:: ልጁን ማንም እንዳያገኛት ሲል ንጉሡ ለቅድስት ኄራኒ ቤተ መንግስት ሠራላት:: ማንም እንዳይገባ በዙሪያው 12 አጥር አጠረበት:: ጣዖቶቹን እንድታጥን አገልጋዮችንም ሾመላት:: ምናልባት አጥር ሰውን ሊከለክለው ይችላል:: #እግዚአብሔር ግን እግዚአብሔር ነውና ምንም አይከለክለውም:: ጌታ ደግሞ ይህቺን ወጣት ለወንጌል አገልግሎት ይፈልጋታል:: አንድ ቀን አባቷ: ልጁ ምሑር እንድትሆንለት አለ የተባለ ሽማግሌ ፈላስፋ ቀጠረላት:: ጥበበ እግዚአብሔር ማለት ይሔ ነው:: አባቷ ይሕ ሽማግሌ ማንን እንደሚያመልክ አልተረዳም:: አረጋዊው እጅግ የተዋጣለት ክርስቲያን ነው:: ግን ማንም አያውቅበትም:: አረጋዊው ቅድስት ኄራኒን ዝም ብሎ ሊሰብካት አልወደደም:: መጀመሪያ በስነ ምግባር አነጻት:: ቀጥሎ ግን "ጌታ ሆይ! ጐዳናህን ምራት" እያለ ይጸልይላት ገባ:: ጌታችን ልመናውን ሰምቶታልና ቅድስቷ አንድ ቀን ግሩም ራዕይን አየች:: እርሷ ለማዕድ ተቀምጣ ሳለ: የምሥራቅና የምዕራብ መስኮቶቿም ተከፍተው ሳሉ: በምሥራቁ መስኮት ነጭ ርግብ በአፏ የወይራ ዝንጣፊ (ቆጽለ ዘይት) ይዛ ገባችና ማዕዷ ላይ አኑራው ሔደች:: እርሷን ተከትሎ ደግሞ ንስር በአፉ አክሊል ይዞ ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ሔደ:: በ3ኛው ግን ቁራ: እባብ በአፉ ይዞ በምዕራቡ መስኮት ገብቶ ማዕዷ ላይ ጥሎት ወጣ:: ቅድስት ኄራኒ ያየችው ራዕይ ቢጨንቃት ሽማግሌ መምሕሯን "ተርጉምልኝ" አለችው:: እርሱም "ልጄ ሆይ! ለዘመናት ስጠብቀው የነበረ ምኞቴን ነው ጌታ ያሳየሽ:: የሕልምሽ ትርጉም እንዲህ ነው:- ነጭ ርግብ የመንፈስ ቅዱስ (የሃይማኖት) ምሳሌ ናት:: የወይራ ዝንጣፊው ደግሞ #ማሕተመ_ጥምቀት( #ሜሮን) ነው:: ቁራ የክፉ ነገሥታት ምሳሌ ሲሆን እባብ የመከራ ምሳሌ ነው:: ንስር ድል የመንሳት ምልክት ሲሆን አክሊል ደግሞ የመንግስተ ሰማያት ምሳሌ ነው:: ልጄ! ክርስቲያን ሆነሽ የሚደርስብሽን ሁሉ ጌታ አሳይቶሻል" ብሎ ተርጉሞላት ተሰናበታት:: እርሷም ወደ ምሥራቅ ዙራ ጸለየች:- "የማላውቅህ አምላክ ሆይ! ወደ እውነትህ ምራኝ" ስትል ለመነች:: በዚያች ሰዓት የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ አጽናናት:: የሚያጠምቃትም እንደሚልክላት ነገራት:: በዚያን ጊዜ አባቷ ገብቶ "ልጄ! ከመሣፍንቱ ላንዱ ልድርሽ ስለሆነ ምን ትያለሽ?" አላት:: "3 ቀን ስጠኝ" አለችውና ሰጣት:: ወደ ጣዖቶቹ ዕለቱኑ ወርዳ "ላግባ ወይስ ይቅርብኝ?" አለቻቸው:: ከቀድሞም በወርቅ የተለበጡ ድንጋዮች ናቸውና ዝም አሉ:: በሙሉ ቀጥቅጣ ሰባብራቸው ተመለሰች:: በዘመኑ #ቅዱሳን_ሐዋርያት(በተለይ እነ #ቅዱስ_ዻውሎስ) በሕይወተ ሥጋ ነበሩና ከቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቤቷ እንደ ተዘጋ ገባ:: ክርስትናን ከጥንቱ እስከ ተፍጻሜቱ አስተምሮ አጠመቃት:: በ3ኛው ቀን አባቷ "ምን መከርሽ?" ቢላት "የእኔ ምክር #መርዓተ_ክርስቶስ(ሰማያዊ ሙሽራ) መሆን ነው" አለችው:: አባቷ ደነገጠ:: እጅግ ስለ ተናደደ ወደ አደባባይ አውጥቶ: አስሮ መሬት ላይ ጣላትና በመቶ የሚቆጠሩ ፈረሶች እንዲረግጧት አደረገ:: በወቅቱ ሰው የሚጠብቀው የአካሏን ቁርጥራጭ ነበር:: ነገር ግን ጌታ ከእርሷ ጋር ነበርና ልብሷ እንኩዋ ጭቃ አልነካም:: አባቷ ንጉሥ ሉክያኖስና ሠራዊቱ ያዩትን ማመን አልቻሉም:: ሁሉም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው "ከክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም" አሉ:: ቅድስት ኄራኒ ምንም ሳትናገር ይህንን ሁሉ ሰው ማረከች:: ወዲያውም ንጉሡ መልእክተኛ ልኮ: የቅዱስ ዻውሎስ ደቀ መዝሙርን አስጠርቶ: ከነ ቤተሰቦቹ ተጠመቀ:: የዚህን ዓለም ክብር ንቆም ንግሥናውን ተወ:: የጸሎት ሰውም ሆነ:: የቅድስት ኄራኒ ተጋድሎ ግን ቀጠለ:: በአካባቢው የነበረ ንጉሥ መጥቶ የአባቷን መንግስት ቀማ:: እርሷንም እጅግ አሰቃያት:: እርሱ አልፎ አርማንዮስ የሚባል ንጉሥ እንዲሁ አሰቃያት:: እርሱም አለፈ:: ከእርሱ ቀጥሎ የመጣው ንጉሥ ብዙ መከራዎችን በእርሷ ላይ አደረሰ:: በጦርም ጐኗን ወግቶ ገደላት:: ከጥቂት ሰዓታት በሁዋላ ግን ልክ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ተነስታ ጠራችው:: በጣም ደንግጦ "አምላክሽ አምላኬ ነው" ሲል አመነ:: ከ30,000 በላይ ሠራዊቱን ይዞም ተጠመቀ:: ቅድስት ኄራኒ በቀረ ሕይወቷ በስብከተ ወንጌል እስያን አድርሳለች:: ጌታ አብርቶላት: እርሷም አብርታ: እልፍ ፍሬን አፍርታ: በዚህች ቀን ዐርፋለች:: የሐዋርያትንም: የሰማዕታትንም አክሊል ተቀዳጅታለች:: †††✝️🌻 ንግሥተ ሳባ †††✝️🌻 ††† ይሕቺ ኢትዮዽያዊት ከ3 ሺ ዘመናት በፊት የነበረች ደግ እናት ናት:: በሥጋዊ ደረጃ ከታንዛንያ እስከ #የመን ያስተዳደረች ስመ ጥር ንግሥት ስትሆን በመንፈሳዊው ደረጃ ደግሞ እግዚአብሔር የቀባውን ሰው ፍለጋ ወደ #ኢየሩሳሌም ተጉዛለች:: ከዚያውም አምልኮተ እግዚአብሔርን ከሥርዓተ ኦሪት ጋር አምጥታለች:: ድንግልናዋን ለታላቁ #ንጉሥ_ሰሎሞን ሰጥታ #ምኒልክን ወልዳለች:: ይህቺ ንግሥት በጌታችን (በፈጣሪ) አንደበትም ተመስግናለች:: (ማቴ. 12:42) በስምም " #ሳባ: #አዜብና #ማክዳ ተብላ ትታወቃለች:: ዛሬ ዕለተ ልደቷ ነው:: ††† ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት ††† ††† ይሕቺ ቅድስት የቅዱስ #ቆስጠንጢኖስ እናቱ: የመስቀሉ ወዳጅ: የቤተ ክርስቲያን ባለውለታ የሆነች ክብርት እናት ናት:: ይህቺም ቅድስት የተወለደቺው በዚሁ ዕለት ነው:: ††† የቅዱሳት እናቶቻችን አምላክ እህት እናቶቻችንን ከክፋትም: ከጥፋትም: ይሠውርልን:: ለሃገርም: ለሃይማኖትም የሚጠቅሙ ሴቶችንም ጌታ አይንሳን:: በረከታቸውም ይደርብን:: ††† ነሐሴ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 1.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል (6ኛ ቀን) 2.ቅድስት ኄራኒ ሐዋርያዊት (ሰማዕት) 3.ቡርክት ንግሥተ ሳባ (ልደቷ) 4.ቅድስት ዕሌኒ ንግሥት (ልደቷ) ††† ወርኀዊ በዓላት 1.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ 2.አበው ጎርጎርዮሳት 3.አቡነ ምዕመነ ድንግል 4.አቡነ አምደ ሥላሴ 5.አባ አሮን ሶርያዊ 6.አባ መርትያኖስ ጻድቅ ††† " #ንግሥተ_አዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስታ ትፈርድበታለች:: የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና:: እነሆም ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ::" ††† (ማቴ. 12:42) ††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ ነሐሴ ፲፰ ❖ ✞✞✞ እንኩዋን ለሊቁ #ቅዱስ_እለእስክንድሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞ +"+ #ቅዱስ_እለእስክንድሮስ_ሊቅ +"+ =>ቅዱሱ ታላቅ የሃይማኖት ጠበቃ ሲሆን ሃገረ ሙላዱ (የተወለደባት) #ግብጽ ናት:: የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን በምግባሩ: በትምሕርቱ ለምዕመናን ጥቅም ሆኗቸዋል:: ቅዱስ እለእስክንድሮስ ገና ልጅ ሳለ ምሥጢረ ክርስትናን ይማር ዘንድ ወደ #ቅዱስ_ዼጥሮስ #ተፍጻሜተ_ሰማዕት ሔዷል:: +ቅዱስ ዼጥሮስ የግብጽ 17ኛ ፓትርያርክና ሊቅ ሲሆን በታሪክ የዘመነ ሰማዕታት መጨረሻ ተብሎ ይታወቃል:: ከዚህ ሰማዕት ሥር የሚማሩ ብዙ አርድእት ቢኖሩም 3ቱ ግን ተጠቃሽ ነበሩ:: 1.ቅዱስ እለእስክንድሮስ (ደጉ) 2.አኪላስ (ውዳሴ ከንቱ ወዳጅ) 3.አርዮስ (የቤተ ክርስቲያን ጠላት) +ከእነዚህም አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሲታትር ነበር:: አኪላስ ደግሞ ሆዱ ዘመዱ: ስለ ምንም የማይጨንቀው ሰው ነበር:: ቅዱስ እለእስክንድሮስ ግን በጾምና በጸሎት እየተጋ መምሕሩን ቅዱስ ዼጥሮስን ለመተካት (ለመምሰል) ይጥር ነበር:: +ወቅቱ ዘመነ ሰማዕታት እንደ መሆኑ ቅዱሱ ከመምሕሩ ጋር ብዙ ነገሮችን አሳልፏል:: አርዮስ ክዶ: ቅዱስ ዼጥሮስ ካወገዘው በሁዋላ እንደ ባልንጀራ ገስጾ ሊመልሰውም ሞክሮ ነበር:: ነገር ግን የአርዮስን ክፋት ከጌታ ዘንድ የተረዳው ቅዱስ ዼጥሮስ ደቀ መዝሙሩን እለእስክንድሮስን ጠርቶ መከረው:: +"እኔ ከሞትኩ በሁዋላ አኪላስ ይተካል:: ከአርዮስ ጋር ስለሚወዳጅ በ6 ወሩ ይቀሠፋል:: አንተ ግን ከአርዮስ መርዝ ተጠበቅ" አለው:: ይህንን ካለው በሁዋላ ወታደሮች የቅዱስ ዼጥሮስን አንገት ቆረጡ:: ይህ የተደረገውም እ.ኤ.አ በ311 ዓ/ም ነው:: +ወዲያውም አኪላስ ተሾመ:: እንደ ተባለውም ከአርዮስ ጋር ስለተወዳጀ በ6 ወሩ ተቀሰፈ:: በዚያው ዓመትም ቅዱስ እለእስክንድሮስ የእስክንድርያ (ግብጽ) 19ኛ ፓትርያርክ (ሊቀ ዻዻሳት) ሆኖ ተሾመ:: +ሊቁ ሲሾም መልካም አጋጣሚ የነበረው ያ የመከራ ዘመን ማለፉ ሲሆን በጣም ከባዱ ግን የአርዮስ ተከታዮች ከተገመተው በላይ መበብዛታቸው ነው:: ቅዱሱ ሊቅ በዽዽስና መንበሩ ለ17 ዓመታት ሲቆይ ዕንቅልፍም ሆነ ዕረፍት አልነበረውም:: +በዚህ እየጾመ: እየጸለየ: ሥጋውን እየጐሰመ ለፈጣሪው ይገዛል:: በዚያ ደግሞ ሕዝቡን ነጋ መሸ ሳይል ያስተምራል:: ምዕመናንን ከአርዮስ የኑፋቄ መርዝ ለመታደግ ባፍም: በመጣፍም (በደብዳቤ) አስተማረ:: +ብርሃን የሆነ ደቀ መዝሙሩ #ቅዱስ_አትናቴዎስ እያገዘው: አርዮስን ከነአበጋዞቹ አሳፈሩት:: ለእያንዳንዷ የኑፋቄ ጥያቄ ተገቢውን መንፈሳዊ ምላሽ ከመስጠቱ ባለፈ አርዮስን ከአንዴም 2: 3ቴ በጉባኤ አውግዞታል:: +ነገሩ ግን በዚህ መቁዋጨት ባለመቻሉ ንጉሡ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጉባኤ ኒቅያ እንዲደረግ አዋጅ ነገረ:: እ.ኤ.አ በ325 ዓ/ም (በእኛ በ318 ዓ/ም) ከመላው ዓለም ለጉዳዩ 2,348 የሚያህሉ ሰዎች ተሰበሰቡ:: ከእነዚህ መካከል 318ቱ ሊቅነትን ከቅድስና የደረቡ: ስለ ቀናች ሃይማኖት ብዙ መከራ ያሳለፉ ነበሩ:: +ይህንን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲመራ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ እለአእስክንድሮስን መረጠ:: ሊቁም አበው ቅዱሳንን አስተባብሮ በሺህ የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉትን አርዮስን ተከራክሮ ረታው:: +በጉባኤው መጨረሻ አርዮስ "አልመለስም" በማለቱ እርሱን አውግዘው: ጸሎተ ሃይማኖትን ሠርተው: 20 ቀኖናወችን አውጥተው: መጽሐፈ ቅዳሴ ደርሰው: አሥራው መጻሕፍትን ወስነው: ቤተ ክርስቲያንን በዓለት ላይ አጽንተው ተለያይተዋል:: የዚህ ሁሉ ፍሬ አበጋዙ ደግሞ ቅዱስ እለእስክንድሮስ ነው:: +እርሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን "#ወልድ_ዋሕድ: #አምላክ: #ወልደ_አምላክ: #የባሕርይ_አምላክ" መሆኑን መስክሮ ክብርን አግኝቷል:: የእምነታችንም መሠረቱ ይሔው ነው:: ክርስቶስን "ፈጣሬ ሰማያት ወምድር: የባሕርይ አምላክ: ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ (ከአባቱ ጋር በመለኮቱ የሚተካከል)" ብለው ካላመኑ እንኩዋን ድኅነት ክርስትናም አይኖርም:: +ከጉባኤ #ኒቅያ በሁዋላ ቅዱስ እለእስክንድሮስ በመልካሙ ጐዳና ሲጋደል: ምዕመናንንም ሲያጸና ኑሯል:: ዘወትር ወንጌልን በፍቅር ያነብ ነበርና ሲጸልይ የብርሃን ምሰሶ ይወርድለት ነበር:: +ስለ ውለታውም #ቤተ_ክርስቲያን በግብጽ ካበሩ 5ቱ #ከዋክብት_ሊቃውንት እንደ አንዱ ታከብረዋለች:: ቅዱሱ ሊቅ በ328 ዓ/ም (በእኛ በ320 ዓ/ም) በዚህች ቀን ዐርፎ በክብር ተቀብሯል:: =>ቸር አምላከ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያንን ከነጣቂ ተኩላ ይጠብቅልን:: ከቅዱሱ ሊቅም በረከትን ይክፈለን:: =>ነሐሴ 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል (3ኛ ቀን) 2.ቅዱስ እለእስክንድሮስ ሊቅ 3.ቅዱስ እንድራኒቆስ ዲያቆን 4.አባ ዘክርስቶስ ዘወሎ (ኢትዮዽያዊ ጻድቅ) =>ወርሐዊ በዓላት 1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ 2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን) 3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ 4.ማር ያዕቆብ ግብፃዊ 5.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት) =>+"+ . . . ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኩአችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ:: +"+ (ይሁዳ. 1:3) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

✟...ገድለ ቅዱስን...✟ - Statistics & analytics of Telegram channel @s3a7m14i22