ch
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

前往频道在 Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

显示更多
610
订阅者
-124 小时
-37 天
-1130 天
帖子存档
🌼 "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼           🌼 #መስከረም ፲፪ (12) ቀን። 🌼 እንኳን #በኤፌሶን_አገር በ_431 ዓ.ም (ሦስተኛው ጉባኤ) ሁለት መቶ ኤጲስ ቆጶሳት  በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት #በቅዱስ_አባ_ቄርሎስ ሊቀ መንበርነት ንስጥሮስ ለማውገዝ ለተሰበሰቡበት ቀን ለመታሰቢያ በዓል፣ #ለሊቀ_መላእክት_ለቅዱስ_ሚካኤል እግዚአብሔር ወደ አሞፅ ልጅ ወደ #ነቢዩ_ቅዱስ_ኢሳይያስ_ለንጉሡ_ሕዝቅያስ ከደዌው እንዳዳነው በዕድሜው ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እንደተጨመረለት ንገረው ብሎ ለተላከበት ለወራዊ መታሰብያ በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከሰማዕት #ቅዱስ_አፍላሆስ ከመታሰቢያውና ከሥጋው ፍልሰት፣ ከእስክድርያ አገር ከሆኑ ከባልንጀሮቹ ሰማዕታትም ከመታሰቢያቸው፣ #ከሰማዕታት_ከቅዱሳን_ከሉዩራስና_ባሌኒኮስ፣ #ከቅዱስ_ኢያቄምና_ከቅድስት_ሐናም ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                      ✝️ ✝️ ✝️ 🌼 በዚችም ቀን ደግሞ #በኤፌሶን_ከተማ #የቅዱሳን_የሁለት_መቶ_ኤጲስቆጶሳት_ስብሰባ ሆነ ይህም ለታላላቆች ጉባኤያት ሦስተኛ ነው። 🌼 ስብሰባቸውም የተደረገው የታላቁ ቴዎዶስዮስ ልጅ አርቃድዮስ የወለደው ታናሹ ቴዎዶስዮስ በነገሠ በሃያ ዓመት ነው። የስብሰባቸውም ምክንያት የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት በሆነ በንስጡር ነው። እርሱ ስቶ እንዲህ ብሏልና "እመቤታችን ድንግል ማርያም አምላክን በሥጋ አልወለደችውም እርሷ ዕሩቅ ሰውን ወልዳ ከዚህ በኋላ በውስጡ የእግዚአብሔር ልጅ አደረበት ከሥጋ ጋር በመዋሐድ አንድ አልሆነም በፈቃድ አደረበት እንጂ። ስለዚህም ክርስቶስ ሁለት ጠባይ ሁለት ባህርይ አሉት" የተረገመ የ*ከ*ሐ*ዲ ንስጡር የከፋች ሃይማኖቱ ይቺ ናት። 🌼 ስለ እርሱም የተሰበሰቡ እሊህ አባቶች ከእርሱ ጋር ተከራከሩ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው አምላክ እንደሆነ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ በአበሠራት ጊዜ ከተናገረው ቃል ምስክር አመጡ። እንዲህ የሚል "እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው ከአንቺ የሚወለደውም ጽኑዕ ከሀሊ ነው የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል"። ዳግመኛም "እነሆ ድንግል በድንግልና ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች" ብሎ በትንቢቱ ከተናገረው ከኢሳይያስ ቃል ሁለተኛም "ከእሴይ ዘር ይተካል ከእርሱም ለአሕዛብ ተስፋቸው ይሆናል"። 🌼 ዳግመኛም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ ገሠጸው መከረው ስለዚህም እንዲህ ሲል አስረዳው "ክብር ይግባውና የክርስቶስ የመለኮቱና የትስብእቱ ባሕርያት በመዋሐድ አንድ ከሆኑ በኋላ አይለያዩም አንድ ባሕርይ በመሆን ጸንተው ይኖራሉ እንዲህም አምነን ሰው የሆነ እግዚአብሔር ቃል አንዲት ባሕርይ ነው እንላለን"። 🌼 ከ*ሀ*ዲ ንስጥሮስ ግን ከክፉ ሐሳቡ አልተመለሰም ከሹመቱም ሽረው እንደሚአሳድዱትም ነገሩት። እርሱ ግን የጉባኤውን አንድነት አልሰማም ስለዚህም ከሹመቱ ሽረው ረግመው ከቤተ ክርስቲያን ለይተው አሳደዱት ወደ ላይኛውም ግብጽ ሒዶ በዚያ ምላሱ ተጎልጒሎ እንደ ውሻ እያለከለከ በክፉ አሟሟት ሞተ። 🌼 እሊህም ሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት አባቶች ሃይማኖትን አጸኑዋት በዚህም ጉባኤ ውስጥ እንዲህ ብለው ጻፉ "እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእርሷ ሰው የሆነውን የእግዚአብሔርን አካላዊ ቃል በሥጋ ወለደችው"። 🌼 ከዚህም በኋላ ሥርዓትን ሠርተው ሕግንም አግገው በእጆቻቸው ጽፈው ለምእመናን ሰጡ። እኛም የሕይወትንና የድኅነትን መንገድ ይመራን ዘንድ እግዚአብሔርን እንለምነው። ለእርሱም ክብር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።                           ✝️ ✝️ ✝️ 🌼 በዚች ቀን #የመላእክት_አለቃ_የቅዱስ_ሚካኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው። 🌼 በዚችም ቀን ክብር ይግባውና እግዚአብሔር ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢይ ኢሳይያስ ላከው ይቅርም ብሎት ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስ ሒዶ እግዚአብሔር ይቅር እንዳለውና ከደዌው እንዳዳነው በዕድሜውም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እንደ ጨመረለት ይነግረው ዘንድ አዘዘው። ንጉሱም ሚስት አግብቶ ምናሴን እስከወለደው ድረስ እንዲሁ ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን። ምንጭ፦ የመስከረም 12 ስንክሳር።                                                       ✝️ ✝️ ✝️ 🌼 "#ሰላም_ለምቅወምከ_ዘልዑል_ማዕረጋ። እምቅዋመ አእላፍ እንግልጋ። #ሚካኤል_መንፈስ ዘንበለ ሥጋ። ታድኅን ዘተመንደበ ለማዕበለ ባሕር እምጹጋ ወለእለ በበድው ትባልሕ በጸጋ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመስከረም_12።                        ✝️ ✝️ ✝️ 🌼 #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦"ሐለዩ ወነበቡ ከንቶ። ወነበቡ ዓመፃ ውስተ አርያም። ወአንበሩ ውስተ ሰማይ አፉሆሙ"። መዝ 72፥8-9። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 13፥424-44።                          ✝️ ✝️ ✝️ 🌼 #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዐውዶሙ። ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ። ጠዐሙ ወታእሙሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር"። መዝ 33፥7-8። የሚነበቡት መልዕክታት 1ቆሮ 5፥3-11፣ ይሁ 1፥9-20 እና የሐዋ ሥራ 20፥28-31። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 18፥15-19። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ የቅዱስ ቄርሎስ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ሚካኤል ወራዊ በዓልና የኤፌሶን ጉባኤ የተሰበሰቡ የ200 ኤጲስቆጶሳት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

🌼 "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼            🌼 #መስከረም ፲፩ (11) ቀን። 🌼 እንኳን ለኢትዮጵያዊው ጻድቅ ለታላቁ አባት #ለአቡነ_አናንያ የዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                         ✝️ ✝️ ✝️ 🌼  #አቡነ_አናንያ፦ የተባሉት ታላቅ ጻድቅ ከቤተ ኤዎስጣቴዎስ የተገኙ ሲሆን በዐፄ ይስሐቅና ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን የኖሩ ሲሆን ገድል ተጽፎላቸዋል፡፡ ( cf. Kinefe-Rigb, JES 13, vol.2, item no. 15) ገዳማቸው ኤርትራ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ገድልም ተጽፎላቸዋል፡፡ 🌼 ስለጻድቁ የተጻፈ ዝርዝር መረጃ ለጊዜው ባናገኝም ከገዳማቸው የተገኘው ማስታወሻ እንደሚናገረው ጻድቁ የተወለዱት ኤርትራ ሠራየ ውስጥ ልዩ ስሙ "ማይ ልሓም" በሚባል ቦታ ነው፡፡ ወላጆቻቸውም ፈሪሃ እግዚአብሔር የነበራቸው ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ 🌼 የአቡነ አናንያ የምንኵስና ትውልዳቸው ከአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ አባ በኪሞስን ያመነኵሳሉ፣ አባ ኪሞስ አባ ጳውሎስን፣ አባ ጳውሎስ ደግሞ አቡነ አናንያን ያመነኵሳሉ፡፡ ጻድቁ በጾም ጸሎት በገዳማዊ ሕይወታቸው የጸኑ መንፈሳዊ ተጋዳይ ሲሆኑ ለፍጥረቱ ሁሉ የሚራሩ ሩኅሩኅ በመሆናቸው በዚህ ይታወቃሉ፡፡ 🌼 ጻድቁ አቡነ አናንያ አቡነ አናንያ በተወለዱበት ቦታ ላይ ታላቅ ገዳም ያላቸው ሲሆን የአባታቸው የአባ ጳውሎስና የእርሳቸው ዐፅም አንድ ላይ በገዳማቸው ውስጥ በክብር ዐርፎ ይገኛል፡፡ 🌼 ከመቃብራቸውም ብዙ አስገራሚ ተኣምራት ተገልጠው ታይተዋል፡፡ በገዳማቸው ያለው ፈዋሽ ጠበልም እስከአሁን ድረስ ብዙ ተኣምራት እያደረገ ይገኛል፡፡ የጻድቁ ዕረፍታቸው መስከረም 11 ነው፡፡ ከአቡነ አናንያ እግዚአብሔር ረድኤት በረከትን ያሳትፈን፣ በጸሎታቸው ይማረን!፡፡ 🌼 አቡነ አናንያ የሚባሉ ሌላም የሸዋ ተወላጅ ጻድቅ መኖራቸውን ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ጽፈዋል፡፡ ይኽም ጻድቅ የትውልድ ሀገራቸው ሸዋ ተጉለት ልዩ ስሙ በረከት መንደር አቡዬ ገዳም ተወለዱ፡፡ ይኽም ጻድቅ ዋልድባን ከመሠረቱት 800 ቀደምት አበው ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው። ምንጭ፦ ከገድላት አንደበት።

🌼 ከዚህም በኋላ መጽሩስ መኰንን ከአማካሪዎቹ ጋር ተማከረ እንዲህም አላቸው "ስሙ ፋሲለደስ ስለሚባል ስለዚህ ሰው ምን ላድርግ እርሱን ያላሠቃየሁበት የሥቃይ መሣሪያ ምንም የቀረ የለም ከሐሳቡም አልተመለሰም" እነርሱም እንዲህ ብለው መከሩት "ራሱን በሰይፍ ቆርጠህ ከእርሱ ተገላገል እነሆ የዚች አገር ሰዎች በእርሱ ምክንያት አልቀዋልና"። 🌼 በዚያንም ጊዜ የቅዱስ ፋሲለደስን ራስ በሰይፍ እንዲቆርጡ መኰንኑ አዘዘና ቆረጡት የድል አክሊልን ተቀበለ ንቆ ሰለ ተዋት ምድራዊት መንግሥት ፈንታም ሰማያዊት መንግሥት አገኘ። ከሥጋውም ድንቆች የሆኑ ታላላቅ ተአምራት ተገለጡ ከእርሱም ጋር ሰማዕት ሁነው የሞቱ ሁሉም ቊጥራቸው ሃያ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ዘጠና ሦስት ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ ቅዱስ ፋሲለደስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ 🌼 #ቅዱስ_ቆርኔሌዎስ፦ ይህም ቅዱስ የጭፍራ አለቃ የሆነ ትሩፋቱና ገድሉም ያማረ ጻድቅ፤ በቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት ዘመን እግዚብሔርን ያገለገለ ነው። 🌼 የእግዚአብሔር መልአክም ተገልጦለት ሐዋርያ ጴጥሮስን ይጠሩት ዘንድ ሰዎችን እንዲልክ ጴጥሮስም ወደርሱ እንዲመጣ ሊሠራው የሚገባውን ከእርሱ ከጴጥሮስ እንዲሰማ አዘዘው። 🌼 ጴጥሮስም ወደርሱ በደረሰ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል አስተማረው ለርሱና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ ከሁሉ ቤተሰቡ ጋር አምኖ ተጠመቀ። ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ ለእስክንድርያ አገር ቅስና ሾመው ወደርሷ በደረሰ ጊዜ የጣዖታትን አምልኮ ተመልታ አገኛትና አስተማራቸው ብዙዎችንም ወደቀናች ሃይማኖት መልሶ አጠመቃቸው መኰንኑ ድሜጥሮስም አምኖ ከወገኖቹ ጋር በእርሱ እጅ ተጠመቀ። 🌼 የኑሮውን ዘመንና ሐዋርያዊ ተጋድሎውን አድርሶ በሰላም አረፈ እርሱም ከአሕዛብ አስቀድሞ ያመነ የመጀመሪያ አማኒ ነው።                              ✝ ✝ ✝ 🌼 #ቅድስት_ታዖድራ፦ ይችንም ቅድስት ሌላ ሰው አስገድዶ ከባሏ ወስዶ ከባሏ ጋር ያላትን አንድነት አበላሸ ያን ጊዜም ታላቅ ኀዘን በማዘን ተጸጸተች መሪር ልቅሶንም አለቀሰች የወንዶችንም ልብስ ለብሳ ወንድ መሰላ ከእስክንድርያ በሥውር ወጣች ስሟንም ቴዎድሮስ ብላ ሰየመችና ወደ ወንዶች ገዳም ገባች የምንኲስና ልብስንና የመላእክትን አስኬማ ለበሰች። የሚያዩዋት ሁሉ እርሷ እንደ ጃንደረባ የሆነች ወንድ ትመስላቸው ነበር እርሷ ግን በረኃብ፣ በጽምዕ ሌሊት በመትጋት ቀን በመቆም ጸንታ በመጋደል ላይ ታገሠች እንዲህም በመጋደል ተጠምዳ ብዙ ዘመን ኖረች። 🌼 በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ አንድ ሰው ከአንዲት ብላቴና ጋር አመነዘረ እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅን ወለደች ወላጆቿም "ድንግልናሽን ያጠፋው ማነው" ብለው ጠየቋት እርሷም "በገዳም ውስጥ የሚኖር አባ ቴዎድሮስ እርሱ ደፍሮኝ ከእርሱ ፀነስኩ" ብላ በዚች ቅድስት ታኦድራ ላይ በሐሰት ተናገረች። 🌼 ወላጆቿም በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ ሕፃኑንም ወደዚያ ገዳም አበ ምኔት ወሰዱት እንዲህም አሉት "ይህ ሕፃን የልጅህ የመነኵሴው የቴዎድሮስ ልጅ ነው"። ያን ጊዜም አበ ምኔቱ ይቺን ቅድስት ታኦድራን ጠራትና እንዲህ አላት "ይህን ክፉ ሥራ ለምን ሠራህ በመነኰሳቱም ሁሉ ላይ ኀፍረትንና ጒስቁልናን አመጣህ" እርሷ ሴት መሆኗን አላወቀምና እርሷም አባቴ ሆይ "በድያለሁና ይቅር በለኝ" አለችው። 🌼 አበ ምኔቱም ተቆጥቶ ከገዳሙ አስወጥቶ አባረራት በበረሀ ውስጥ ሰባት ዓመት ኖረች ያም ሕፃን ከእርሷ ጋር ሁኖ ከሰይጣናት በሚመጡባት በብዙ መከራዎች ብዙ መከራዎች ላይ ታገሠች ብዙ ሥቃያትንም ፈጽሞ አሠቃዩዋት። 🌼 ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ተቀብለው ወደ ገዳም አስገቡአት ጥቂት ቀንም ኖረች መልካም ተጋድሎዋንም ፈጽማ በሰላም አረፈች ነፍሷንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጥታ የዘላለም ሕይወትን አገኘች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ታኦድራ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ 🌼 #ሰማዕቷ_ቅድስት_በነፍዝዝ፦ የስሟ ትርጓሜ ጣፋጭ የሆነ ማለት ነው።  ይቺም ቅድስት በእድሜዋ ፈጽማ የሸመገለች ነበረች በፋርስ ንጉሥ በሳቦር ዘመንም መከራ ተቀበለች ከዘጠኝ መቶ ክርስቲያን ጋር ማርከው ወስደው አሠሩዋት የሠራዊቱም አለቃ ታላቅ ሥቃይን አሠቃይቶ ከዚያ በኋላ ራሷን በሰይፍ ቆረጠ። 🌼 ራሷንም ከአስቆረጣት በኋላ ከአንገቷ የፈሰሰው ደም እስከ ራቀ ድረስ ወደ ላይ ወጣ ከዚያ የተቀመጡ ጠላቶችም ኃይላቸው ደከመ። የፀሐይ ብርሃንም ጨለመ በዚያም ቦታ ደግሞ ጣፋጭ የሆነ መዐዛ ተመላ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት በነፍዝዝ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                               ✝ ✝ ✝ 🌼#የእስና_አገር_ሰዎች_ሦስቱ_ቅዱሳን_ሰማዕታት #ገበሬዎች_ሱርስ_አጤኬዎስ_መስተሐድራ፦ አርያኖስም ከሀገሪቱ በስተደቡብ ምንም ሳያስቀር ወታደሮቹ እስከ ደከሙ ድረስ ሰይፋቸውንም ወደ አፎቱ መልሰው ነበር የአገር ሰዎችን ጨርሶ ገድሎ ሲመለስ እሊህ ሦስቱ ገበሬዎች ከዱር ሲመለሱ በከተማ መካከል በተገናኙት ጊዜ "እኛ ክርስቲያኖች ነን" ብለው በግልጥ ጮኹ አርያኖስም ሰምቶ ወታደሮቹን "እሊህን ገበሬዎች ትገድሏቸው ዘንድ ይገባል" አላቸው። 🌼 ወታደሮቹም "እኛ ደክመናል ሰይፎቻችንንም ወደ አፎታቸው አስገብተናል" አሉት እሊህ ቅዱሳንም ሰምተው "እነሆ መቆፈሪያዎች ከእኛ ጋራ አሉ" በእነርሱ ግደሉን አሉ ከዚያም አንገታቸውን በደንጊያ ላይ አድርገውላቸው ቆረጡአቸው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የመስከረም 11 ስንክሳር።                             ✝ ✝ ✝ 🌼 "#ሰላም_ለፋሲለደስ_እምነ ክሣዱ ዘአንጠብጠበ። ደመ ቀይሐ ወጸዓድዒደ ሐሊበ። ምስለ አዝማዲሁ ወሰብኡ እስመ ለሞት ተውህበ። በከመ ኮኖሙ ዲበ ምድር አበ። ዘበሰማያት ተሠይመ አቡሆሙ ካዕበ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የመስከረም 11።                              ✝ ✝ ✝ 🌼 #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ተንሥኡ ላዕሌየ ሰማዕተ ዐመፃ። ወዘኢየአመር ነበቡ ላዕሌየ። ፈደዩኒ እኪት ህየንተ ሠናይት"። መዝ 34፥3-4። የሚነበበው ወንጌል 16፥24-ፍ.ም።

🌼 "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼            🌼 #መስከረም ፲፩ (11) ቀን። 🌼 እንኳን #ለአንጾኪያ_ነገሥታት_አባታቸው፤ መካሪያቸው ለሆነ በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን ለነበረው፤ ጌታችን ከሞት እያስነሣው በጽኑ ሥቃይና ተጋድሎ ሲጋደል ለኖረው ለታላቁ ሰማዕት #ለቅዱስ_ፋሲለደስ፣ #በቅዱሳን_አባቶቻችን_ሐዋርያት ዘመን እግዚአብሔርን ያገለገለ #የጭፍራ_አለቃ (፻አለቃ) ለሆነ ትሩፋቱና ገድሉም ላማረ ለጻድቁ ሰው #ለቅዱስ_ቆርኔሌዎስ ለዕረፍታቸው በዓል፣ ለእስክድርያ አገር በንጉሥ ዘይኑን ዘመን ለነበረች #ለቅድስት ታዖድራ ለዕረፍቷ በዓል እግዚአብሔር አምላክ ሰላም አደረሰን፡፡ በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ የስሟ ትርጓሜ ጣፋጭ ከሆነ ከከበረች #ከሰማዕቷ_ከቅድስት_በነፍዝዝ ከዕረፍት በዓል፣ #ስማቸው_ሱርስ_አጤኬዎስና_መስተሐድራ ከሚባሉ ሦስት ገበሬዎች ከእስና አገር ሰዎች በሰማዕትነት ከዐረፉ፣ #ከቅዱሳን_ከባስልዮስ ሰማዕትና #ከኢየሩሳሌም_ኤጲስቆጶስ_ከቴዎድሮስ ከሰማዕት አለቃ #ከቀውስጦስም ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                       ✝ ✝ ✝ 🌼 #ለአንጾኪያ_ነገሥታት_አባታቸውና_መካሪያቸው የሆነው #ሰማዕቱ_ቅዱስ_ፋሲለደስ፦ እርሱም ለሮም ንጉሥ የሠራዊት አለቃ ነው መንግሥቱም ሁለመናዋ በእርሱ ምክር የጸናች ናት። ብዙዎችም ወንዶችና ሴቶች የቤት ውልዶች አገልጋዮች አሉት። 🌼 ዝምድናውም እንዲህ ነው ስሙ ኑማርያኖስ የተባለ የሮም ንጉሥ ለቴዎድሮስ በናድሌዎስ እናቱ የሆነች የቅዱስ ፋሲለደስን እኅት አግብቶ ዮስጦስን፣ ገላውዴዎስን፣ አባዲርን ወለደችለት እሊህም ለቅዱስ ፋሲለደስ የእኅቱ ልጆች ናቸው። የቅዱስ ፋሲለደስም ሚስት ለቅዱስ ፊቅጦር እናት እኅት ናት ከእርሷም ስማቸው አውሳብዮስና መቃርስ የተባሉ ሁለት ልጆችን ወለደ። 🌼 በዚያም ወራት የቊዝና የፋርስ ሰዎች የሮምን ሰዎች ሊወጓቸው በላያቸው ተነሡ ያን ጊዜ የንጉሥ ልጅ ዮስጦስን የፋሲለደስ ልጅ አውሳብዮስን ከጦር ሠራዊቶቻቸው ጋር ለውጊያ ላኳቸው። ንጉሡ ኑማርዮስም ሌሎች ጠላቶች በተነሡበት በኩል ለጦርነት ሒዶ በውጊያው ውስጥ ሞተ የሮም መንግሥትም የሚጠብቃትና የሚመራት የሌላት ሆነች። 🌼 እንዲህም ሆነ በዚያ ወራት ስለ ጦርነት ለመደራጀት የሮም ሰዎች ከሀገሩ ሁሉ አርበኞች የሆኑ ሰዎችን ሰበሰቡ ከውስጣቸውም ከላይኛው ግብጽ ስሙ አግሪጳዳ የሚባል የፍየሎች እረኛ የሆነ አንድ ሰው አለ። እርሱንም መኳንንቱ ወስደው በመንግሥት ፈረሶች ላይ ባልደራስ አድርገው ሾሙት እርሱም በጠባዩና በሥራው ሁሉ ኃይለኛና ብርቱ ነበር። 🌼 ከንጉሥ ኑማርያኖስ ሴቶች ልጆች አንዲቱ ወደርሱ በመስኮት ተመለከተች ወደደችውም መልምላም ወስዳ አገባችው ስሙንም ዲዮቅልጥያኖስ ብላ ሰይማ አነገሠችው። ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ሰማይና ምድርን የፈጠረ እግዚአብሔርን ትቶ ጣዖታትን አመለከ ቅዱስ ፋሲለደስም ሰምቶ እጅግ አዘነ የመንግሥትንም አገልግሎት ተወ። 🌼 ከዚህም በኋላ የንጉሥ ኑማርያኖስ ልጅ ዮስጦስና የፋሲለደስ ልጅ አውሳብዮስ ጠላቶቻቸውን ድል አድርገው የጠላቶቻቸውንም አገሮች አጥፍተው ደስ ብሏቸው ተመለሱ። ነገር ግን የነገሠው ዲዮቅልጥያኖስ የክብር ባለቤት ክርስቶስን ክዶ አምልኮ ጣዖትን አቁሞ አገኙት እጅግም አዘኑ ተቆጥተውም ተነሡ ሰይፎቻቸውን መዝዘው ዲዮቅልጥያኖስን ገድለው የንጉሥ ኑማርያኖስን ልጅ ዮስጦስን ሊያነግሡ ወደዱ ፋሲለደስም ከዚህ ሥራ ከለከላቸው። 🌼 ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስ ዘመዶቹን፣ ሠራዊቱን፣ አገልጋዮቹንም ሁሉ ሰበሰባቸውና በክብር ባለቤት በክርስቶስ ስም ደሙን ሊያፈስ እንደፈለገ አስረዳቸው ሁሉም እንዲህ ብለው መለሱለት "አንተ በምትሞትበት ሞት እኛ ከአንተ ጋር እንሞታለን" በዚህም ምክር በአንድነት ተሰማሙ። 🌼 ከዚህም በኋላ በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ፊት ቁመው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ ከእርሳቸውም ግርማ የተነሣ ታላቅ ፍርሃትን ፈራ እነርሱ የመንግሥት ልጆች ናቸውና። 🌼 የቅዱስ ፊቅጦር አባት ኅርማኖስም ወደ ግብጽ አገር ይልካቸው ዘንድ በዚያም እንዲያሠቃዩዋቸው መከረው ሁሉንም እየአንዳንዳቸውን ለብቻቸው አድርጎ ላካቸው አባዲርንና እኀቱ ኢራኒን ወደ አንዲት አገር፣ አውሳብዮስንና ወንድሙ መቃርስን ወደሌላ ቦታ፣ ገላውዴዎስንም እንዲሁ አደረጉ። በናድሌዎስ ቴዎድሮስም እሼ በሚባል ዕንጨት ላይ በመቶ ሃምሳ ሦስት ችንካር ተቸንክሮ ገድሉን ፈጸመ። 🌼 ቅዱስ ፋሲለደስን ግን አምስት ከተማዎች ወዳሉበት ወደ አፍሪካ ምድር ወደ መኰንኑ ወደ መጽሩስ ላከው መጽሩስም በአየው ጊዜ መንግሥቱን ክብሩን ስለ ተወ እጅግ አደነቀ። ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስም መልአኩን ልኮ በመንፈስ ወደ ሰማይ አውጥቶ በብርሃን ያጌጠ መንፈሳዊ ማደሪያን አሳየው ነፍሱም እጅግ ደስ አላት ከዚህም በኋላ ወደነበረበት መለሰው። ባሮቹን ግን ነፃ ያወጣቸው አሉ የቀሩትም ከእርሱ ጋር የሰማዕትነት አክሊልን የተቀበሉ ሰባት ሺህ ሠላሳ ሦስት የሚሆኑ አሉ። 🌼 ቅዱስ ፋሲለደስንም ታላቅ ስቃይን አሰቃዩት በመንኰራኲርና በተሣሉ የብረት ዘንጎች ሥጋውን ሰነጣጥቀውት ሞተ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ያለ ጥፋት ከሞት አድኖ አስነሣው አሕዛብም ሁሉ ይህን ድንቅ ተአምር በአዩ ጊዜ አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አመኑ መኰንኑንም ረገሙት ጣዖቶቹንም ሰደቡ በእነርሱ ላይም ተቆጥቶ ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጧቸው ዘንድ ወታደሮቹን አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ ቊጥራቸውም ዐሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ወንዶች ሠላሳ ሰባት ሴቶች ናቸው። 🌼 ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስን ሥጋው ሁሉ ቀልጦ እንደ ውኃ እስከሚሆን በብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት መኰንኑም በተራራ ላይ ጥልቅ ጒድጓድ ቆፍረው በዚያ እንዲቀብሩት አዘዘ እንዲሁም አደረጉ። ያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ፋሲለደስን ከሞት ደግሞ አስነሣው ወደ መኰንኑም መጥቶ እንዲህ ብሎ ጮኸ "መኰንን መጽሩስ ሆይ እፈር ከሀዲ ንጉሥህም የረከሱ ጣዖቶችህም ይፈሩ እነሆ ክብር ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ጉዳት ከሞት ጤነኛ አድርጎ አስነሥቶኛልና"። ሕዝቡም ይህን ተአምር በአዩ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት ሞቱ ቁጥራቸውም ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ሆነ። 🌼 ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስን በውስጧ መጋዝ ካላት መንኰራኲር ላይ አውጥቶ ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው ዳግመኛም በብረት ዐልጋ ላይ በሆዱ አስተኝተው ከበታቹ እሳትን አነደዱ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለት ከዚያ ስቃይም ውስጥ አንስቶ ያለ ጉዳት ጤነኛ አደረገው እንዲህም ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠው "ፋሲለደስ ሆይ ዕውቅ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ ወይም ለድኆች በስምህ ምጽዋትን ለሚሰጥ ወይም ለተራቈተ ልብስን ወይም በመታሰቢያህ ቀን ለቤተ ክርስቲያን መባ ለሚሰጥ በብዙም ቢሆን በጥቂት መታሰቢያህን ለሚያደርጉ ሁሉ እኔ በደላቸውን ሁሉ እተውላቸዋለሁ መኖሪያቸውንም በመንግሥተ ሰማያት ከአንተ ጋራ አደርጋለሁ"። ጌታችንም ይህን ካለው በኋላ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ ቅዱስ ፋሲለደስም በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኘ።

ተቀጸል ጽጌ በዓል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጬጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በተገኙበት ተከብሯል። በየዓመቱ መስከረም ፲ ቀን በጥን
+6
ተቀጸል ጽጌ በዓል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጬጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በተገኙበት ተከብሯል። በየዓመቱ መስከረም ፲ ቀን በጥንት ጊዜ ወርኃ ክረምቱ አለፈ  የጽጌ ዘመን መጣ ይህን ያደረገ እግዚአብሕር ይመስገን ሲሉ ተቀጸል ጽጌን መስከረም ፳፭ ቀን በታላቅ የምስጋና ማዕድ በቤተ ክርስቲያንንና ነገሥታቱ አብያተ መንግሥት ይከበር ነበር። በኋላ አጼ ዳዊት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ግማደ መስቀል ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ መስከረም  ፲ ቀን በመግባቱ  ምክንያት መስቀል ከሁሉም  ነገር በላይ ነውና የተቀጸል ጽጌ በዓል በወደ ዚሁ ቀን በመሳብ አንድ ላይ ማክበሩ እንደቀጠለ ሊቃውንት ይናገራሉ። የተቀጸል ጽጌ በዓል ከ፲፱፻፹፯ ዓ/ም ወዲህ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፭ኛው የቤተ ክርስቲያናችን ፓትርያርክ አማካኝነት  በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እስካሁን በተለያዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብራት እየተከበረ እዚህ ደርሷል። EOTC TV

🌼 ሌላው የገዳሙ ታሪክ ሲወሳ አብሮ የሚነሣው የአቡነ ክርስቶደሉ ታሪክ ነው። አቡነ ክርስቶደሉ የዐፄ ሱስንዮስ ጳጳስ ሲሆኑ ያስመጡዋቸውም ከኢየሩሳሌም ነው። ጳጳሱ መንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው ትንቢት በመናገር ዴንሳ ውስጥ ግንብ በተባለ ቦታ ሲኖሩ ዕለተ ሞታቸው ደረሰ። አንድ ቀን ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ "ዕረፍቴ ደርሷልና እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ስብሐተ እግዚአብሔር ከማይታጎልበት ገዳም ጎንጂ ውሰዱና ቅበሩኝ" ብለው በዙሪያቸው ለሚገኙ ሰዎች ይናገራሉ። ሰዎችም "አባታችን አሁን የፀሓይ መግቢያ ሰዓት ነውኮ" ቢሏቸው ጻድቁም "ፀሓይን ገዝቻታለሁ" ብለው ተናገሩ። በቃላቸውም ግዝት መሠረት ፀሓይ ባለችበት ቆመች። እርሳቸውም ዐርፈው ሰዎቹ ይዘዋቸውና አስከሬናቸው ጎንጂ ደርሶ ከተቀበሩ በኋላ ኀዘንተኛው ወደ ዴንሳ እስኪመለስ ድረስ ፀሓይ ብርሃኗ አልጠፋም ነበር። ከዴንሳ እስከ ጎንጂ የአንድ ቀን መንገድ ያህል ያስኬዳል። 🌼 በአሁኑ ወቅት የኢየሩሳሌሙ ጳጳስ የአቡነ ክርስቶደሉ መቃብር ደዌ ያለባቸውን ሰዎች እየፈወሰ በደብረ ጥበብ ጎንጂ ቴዎድሮስ ገዳም ውስጥ ይገኛል። ዐፄ ቴዎድሮስ በንግሥና ዘመናቸው ምንም እንኳን ያን ያህል የተረጋጋ መቀመጫ ባይኖራቸውም በአንጻሩ ይባባ(ጎጃም) ውስጥና ደብረታቦር (በጌምድር) መቀመጫቸው ነበሩ። ንጉሡ ከይባባ ይልቅ ደብረ ታቦርን ይመርጡ ነበርና በአንድ ወቅት ጎጃም የሚገኘውን ጎንጅ (ደብረ ጥበብ) የሰማዕቱ የቅዱስ ቴዎድሮስ ጽላት መኖሩን ያውቁ ስለነበር ጽላቱን ወደ ደብረ ታቦር ለመውሰድ አሉላ የሚባል ሰው ልከው ነበር፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ስላልነበር አሉላና ጭፍሮቹ ጽላቱን ይዘው ዓባይ ወንዝ እንደደረሱ አሉላን ከነበቅሎው ጭፍሮችን ጨምሮ ዓባይ ወሰዳቸው። 🌼 የሰማዕቱ ጽላትም ተመልሶ ወደ ጎንጅ ቴዎድሮስ ቤተ ክርስቲያን ይገባል። ወሬው በሀገሩ ኹሉ ተወርቶ ከተሰማ ከወራት በኋላ ከእነማይ (ከጎጃም) ጽላቱ እንደተሰረቀና የደረሰበትም ለጊዜው እንደጠፋ አንዱ የእነማይ ባለቅኔ፦  የጎንጁ ቴዎድሮስ የአሉላው ገዳይ እንዲህ ወደ እነማይ ብቅ አትልም ወይ ሲል እንደተቀኘ በታሪክ ይነገራል። ምንጭ፦ ዝክረ ቅዱሳን በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን።

🌼 "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼           🌼 #መስከረም ፲ (10) ቀን። 🌼 እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ ገበያተኛውን ሕዝብ አስተምረው ሲጨርሱ ድንጋዩን ዳቦ እያደረጉ ሕዝቡን ይመግቡ ለነበሩት ለታላቁ አባት #አቡነ_ግርማ_ሥሉስ_ለዕረፍታቸው_በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                            ✝ ✝ ✝ 🌼 #አቡነ_ግርማ_ሥሉስ፦ አባታቸው ነገደ ኢየሱስ እናታቸው ትኩና ለጽዮን የሚባሉ ሲሆን ትኩና ለጽዮን የዐፄ ሰይፈ አርእድ ልጅ ናት። ስለዚኸም አቡነ ግርማ ሥሉስ ትውልዳቸው ከመንግሥት ወገን ቢሆንም "በዓለም ነግሦ መኖርን አልፈልግም" በማለት የዓለምን ጣዕም ንቀው ገዳም የገቡ ጻድቅ ናቸው። ክቡር ዐፅማቸው ያረፈው በጎንጅ ደብረ ጥበብ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም ነው። ገዳሙ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ጎንጅ ቆለላ ወረዳ ከባሕር ዳር 70 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከጥንታዊቷ የጎንጅ አነስተኛ የገጠር ከተማ ላይ ይገኛል። በጊዜው አወቃቀር የዞኑ ዋና ከተማ ፍኖተ ሰላም ነው። ምንም እንኳን ጎንጂ ቆላላ ለባሕር ዳርና ለአዴት ቅርብ ቢሆንም በአወቃቀር ደረጃ በምዕራብ ጎጃም ዞን ውስጥ ተካትቷል። 🌼 ጎንጅ ቴዎድሮስ ወይም ጎንጅ ደብረ ጥበብ ገዳም ከክርስቶስ ልደት በፊት በ4518 ዓመተ ዓለም በሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ አማካይነት ተመሠረተ። እስከ ልደተ ክርስቶስ ድረስ የኦሪት መሥዋዕት ሲሠዋበት ኖሯል። ደብረ ጥበብ የሚለው ስያሜው ከጠቢቡ ተዋነይ ጠቢብነት ጋር ይያያዛል፤ ይኸውም በአሁኑ አጠራር ጎንጅ ደብረ ጥበብ የተባለበት ምክንያት በገዳሙ ታዋቂ የነበረው የቅኔ ሊቅ ተዋነይ የተባለው ሊቅ መወደስ የተባለውን ቅኔ ከተቀኘ በኋላ በደመና ተጭኖ በተመሳሳይ ሰዓት ጎንደር ከተማ ዕጣነ ሞገር የተባለውን ቅኔ በመቀኘቱ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል። 🌼 ሊቁ ተዋነይ ከዚኸ ዋርካ ሥር ተደግፎ ለ20 ዓመታት ግስ ገስሶበታል፣ የቅኔ ቀመር ቀምሮበታል፣ መወድስ ዘርፎበታል፣ ተፈላስፎበታል። የአካባቢው ሕዝብ በእምነት የሚኖር አስገራሚና የዋህ ሕዝብ ነው፣ የሀገሬው ሰው አዲስ ልብስ ገዝቶ ከመልበሱ በፊት እሑድ ቀን ወደ ቤተ ክርስትያን ወስዶ አስባርኮ ነው የሚለብሰው። 🌼 በገዳሙ ውስጥ 44 ታቦታት የሚገኙ ሲሆን ከእነዚኸ ታቦታት ውስጥ አንዱ የቅዱስ ባስልዮስ ታቦተ ነው። የጎንጅ ደብረ ጥበብ ካህናት ከ44ቱ ታቦታት ቀድመው የሚጠቅሱት ታቦተ ቅዱስ ባስልዮስን ነው። ምክንያቱም ታቦተ ቅዱስ ባስልዮስ በሌላ ቦታ ሳይኖር በጎንጅ ደብረ ጥበብ ብቻ መኖሩን ለማመልከት ነው። ከቤተ ክርስቲያኑ 50 ሜትር ያህል ከቅጽሩ ደግሞ 25 ሜትር ፈቀቅ ብሎ ትልቁ የተዋነይ ዋርካ በሰባት አክናፍ እንደዣንጥላ ተዘርግቶ ይገኛል። በወረዳው ከጎንጅ ደብረ ጥበብ የቅኔ ትምህርት ቤት በተጨማሪ ታዋቂው የቅኔ ትምህርት ቤት ዋሸራ ማርያም በዚኹ ወረዳ ይገኛል። 🌼 ጎንጅ ገዳም የሚገኘው ትልቅ ተራራ ሥር ሲሆን ሰይጣን ከተራራው ጫፍ ላይ ወጥቶ ድንጋዩን ገደሉን እየናደ ሲጥለው ድንጋዩ እየተፈነቀለ ሲወርድ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ሊያፈርስ ሲል ጻድቁ በቃላቸው ድንጋዩን እንዳትንቀሳቀስ ብለው ገዝተው አቁመውታል። በዚያ ትልቅ ገደል ላይ የድንጋዮቹ አቋቋም ላያቸው እጅግ ያስደንቃሉ። 🌼 የገዳሙ አስተዳዳሪ ቄስ መልካም በዜ ስለገዳሙ አመሠራረት በቃለ መጠይቅና በጽሑፍ በሰጡት ማስረጃ መሠረት የደብረ ጥበብ ጎንጅ ቴዎድሮስ ገዳም የኦሪት መሥዋት ሲሠዋበት የኖረ መሆኑ፣ ከዋሸራና ከጽላሎ በፊት በእነ ጠቢቡ ተዋናኝ ቅኔ የተዘረፈበትና አሁንም ያለበት መሆኑ፣ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትና ዕድሜ ጠገብ የብራና የመቃ ላይ ሥዕላትና በርካታ ቅርሶች የሚገኙበት ከመሆኑም በላይ ጻድቁ አቡነ ግርማ ሥሉስ የጸለዩበትና ዐፅማቸው ያረፈበት በመሆኑ ልዩና ታሪካዊ ገዳም ያደርገዋል። 🌼 ጻድቁ አቡነ ግርማ ሥሉስ ለ40 ዓመት ያህል እሙይት በተባለው ወንዝ አካባቢ ሲጸልዩ ከኖሩ በኋላ በራእይ ተነግሯቸው ወደ ጎንጅ ደብረ ጥበብ ቴዎድሮስ ገዳም በሚሔዱበት ጊዜ ድንጋዮች ተከትለዋቸው ሔደዋል። ተከትለዋቸው ከሔዱት ድንጋዮች መካከል አንዱ ግዝት ድንጋይ እየተባለ የሚጠራው በአሁኑ ወቅት ከገዳሙ 200 ሜትር ርቀት ላይ በደቡብ በኩል ይገኛል። ከላይ የተከማቸው ድንጋይ ወደ ገዳሙ ለመውረድ ሲንከባለል ተገዝቶ ቆሞ ላየው ይደንቃል። ድንጋዩ ከከተማው እስከ ገዳሙ ድረስ አልፎ አልፎ ተንጠባጥቦ ይታያል። 🌼 ጻድቁ ወንጌልን ሊያስተምሩ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲዘዋወሩ ዛፎችና ድንጋዮች ሁሉ ይከተሏቸው ነበር። አቡነ ግርማ ሥሉስ ገበያተኛውን ሕዝብ አስተምረው ሲጨርሱ ድንጋዩን ዳቦ እያደረጉ ሕዝቡን ይመግቡ የነበሩ ታላቅ አባት ናቸው። ጻድቁ የተወለዱት በተኣምራት በአካላቸው ላይ ማዕተብ አድርገው፣ በእጃቸው መስቀል ይዘው እና ተገዝረው ነው። ከልጅነታቸው ጀምረው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተምረው ከጨረሱ በኋላ አበምኔትና መምህር በመሆን በገዳሙ ለ40 ዘመን በመምህርነት አገልግለዋል። 🌼 በተጋድሏቸውም ወቅት እሙይት ከተባለው ባሕር ውስጥ ገብተው ሲጸልዩ ያድሩ ነበር። በኋላ ከእሙይት ባሕር ወደገዳማቸው ቦታ ሲመለሱ ድንጋዮች "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ አቡነ ግርማ ሥሉስ" እያሉ ከእሙይት ባሕር እስከ ጎንጂ ድረስ ተከትለዋቸዋል። በኋላም ወደ ገዳሙ ሊወርዱ ሲሉ አብዛኛው ድንጋይ በጻድቁ ቃለ ግዝት ከአፋፍ በላይ ሲቀር፣ ሦስቱ ድንጋዮች ግን አባታችንን "ከወደቁበት እንወድቃለን" ብለው ተከትለዋቸው ሲወርዱ "አይሆንም ተመለሱ" ብለው አዘዟቸው። ድንጋዮቹም ካለበት ቦታ ላይ ቆመው በመቅረታቸው "ግዝት ድንጋዮች" ተብለው እስከዛሬ ድረስ ይጠራሉ። 🌼 ድንጋዮቹ የቆሙበት ቦታ ከታች ቁልቁለታማ ገደል ቢሆንም ምንም ሳይሆኑ በጻድቁ ቃለ ግዝት እንደቆሙ ቀርተዋል። ከአፋፍ በላይ የቀሩት ሌሎቹ ደንጋዮች በአሁኑ ወቅት ከጎንጂ ቆለላ ከተማ ከገበያው መሐል ይገኛሉ። ቦታው ከጊዜ በኋላ ገበያ እንደሚቆምበት የታያቸው አቡነ ግርማ ሥሉስ ከባሕር ውስጥ ወጥተው "ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ አቡነ ግርማ ሥሉስ" እያሉ የተከተሏቸውን ድንጋዮች ባሉበት ቦታ ላይ እንዲቆሙ ጻድቁ በቃላቸው ሲያዟቸው "ከጊዜ በኋላ ከዚኸ ቦታ ላይ ገበያ ይቆማል፣ የደጋውና የቆላው ወገኔ ለገበያ በሚገናኙበት ጊዜ ማረፊያና የሸቀጣሸቀጡ መቀመጫ ትሆናላችሁ" ብለው ስላሏቸው በአሁኑ ወቅት በቍጥር ከ60 በላይ የሚሆኑ ድንጋዮች በገበያው ቦታ ላይ በየቦታው በመደዳ ተሰድረው ለገበያተኛው ሕዝብ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። 🌼 አቡነ ግርማ ሥሉስ የትውልድ ሀገራቸው ጎጃም ሲሆን በተወለዱ ጊዜ ብርሃን ከሰማይ ወርዶላቸዋል። አስቀድመን እንደጠቀስነው የዐፄ ሰይፈ አርእድ የልጅ ልጅ ቢሆኑም ንግሥናን ትተው ዓለምን ንቀው ስለመነኑ መጽሐፍ "መናኔ መንግሥት ወብእሲት" ይላቸዋል። በአሁኑ ወቅት ከደብረ ጥበብ ገዳም ከፍ ብሎ በአቡነ ግርማ ሥሉስ ስም የተሰየመ ጠበል ፈልቆ ሕሙማን በየጊዜው እየተፈወሱበት ይገኛሉ። መስከረም 10 ቀን በገዳማቸው በዓለ ዕረፍታቸው በደማቅ ሁኔታ ይከበራል። ከአባታችን አቡነ ግርማ ሥሉስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከት ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!።

                            ✝ ✝ ✝ 🌼 #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወዘሕጎ ያነብብ መዓልተ ወሌሊተ። ወይከውን ከመ ዕፅ እንተ ትክልት ኀበ ሙኃዘ ማይ። እንተ ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ"። መዝ1፥2-3። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 12፥33-38።                             ✝ ✝ ✝ 🌼 #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኁብርት። ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአፅምዒ እዝነኪ"። መዝ 44፥9-10። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 3፥1-ፍ.ም፣ ያዕ 3፥13-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 1፥12-15። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥46-57 ወይም ማቴ 25፥1-14። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች ማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የፄዴንያ ማርያም በዓልና የመስቀሉ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።                

🌼 "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼           🌼 #መስከረም ፲ (10) ቀን። 🌼 እንኳን #ለእመቤታች_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም #በፄዴንያ_አገር_በማርታ_ቤት ሥጋ የለበሠች ከምትመስል #ከእመቤታች_ሥዕል ከሠሌዳዋ #ቅባት_እየተንጠፈጠፈ ተአምር ለሠራችበት ቀን መታሰብያ በዓል፣ #አምላክን_ለወለደች_ለእመቤታችን #ለቅድስት_ድንግል_ማርያም_ለተወለደችበት_ለልደቷ በዓል መታሰቢያ (ይህም የአስቄጥስ ገዳም የከበረ አባ መቃርስ በጻፈው መጽሐፈ ግጻዌ ተጽፎል እንዲሁም ደግሞ በላዕላይ ግብጽ በሚገኝ መጽሐፈ ግጻዌ የከበረች ድንግል እመቤታችን የከበረች ሐና በታኅሣሥ ወር በዐሥራ ሰባት እንደፀነሰቻትና መስከም በዐሥር ቀን እንደወለደቻት ተጽፍአል)፣ ለከበረች  ሰማዕትነት ለተቀበለችበት #ለቅድስት_መጥሮንያ_ሰማዕትነት ለተቀበለችበት በዓል ዕረፍት፣ በሰላም አደረሰን። በተጨማሪም በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #የጌታችን_የአምላካችን_የመድኃኒታችን_የኢየሱስ_ክርስቶስ #ቅዱስ_መስቀል_ወደ_አገራችን_ኢትዮጵያ ድንበር ከደረሰበት (ተቀጽል ጽጌ) አፄ መስቀል) ቀን ለመታሰቢያ በዓልና ከከሀዲው #ሆሎፎርኒስ እጅ በጥበቧ እስራኤልን ካዳነቻቸው ከጥበበኛ ከከበረች #ከቅድስት_ዮዲት በዓለ ዕረፍትና #ከቅድስት_አትናስያና_ሦስት_ልጆቿ_ከመታሰቢያቸው በረከትና ረድኤትን ያሳትፈን።                                                       ✝ ✝ ✝ 🌼 #በዚህች_ቀን_ጼዴንያ በምትባል አገር ሥጋ የለበሰች ከምትመስል ሥዕል ከሠሌዳዋ ቅባት እየተንጠፈጠፈ #አምላክን_የወለደች_የእመቤታችን_የድንግል_ማርያም_ተአምር ተገለጠ። ይቺንም ሥዕል የሣላት ወንጌላዊ ሉቃስ ነው ይባላል። ወደ ጼዴንያ አገርም የመጣችበት ምክንያት አንዲት ስሟ ማርታ የሚባል መበለት ሴት ነበረችና ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች ናት። አምላክን የወለደች እምቤታችን ድንግል ማርያምንም እጅግ ትወዳት ነበር። በሚቻላትም ሁሉ ታገለግላታለች። 🌼 በአንዲት ቀንም ስሙ ቴዎድሮስ የሚባል መነኵሴ ከእርሷ ዘንድ እንግድነት አደረ በመልካም አቀባበልም ተቀበለችው በማግሥቱም ስተሸኘው "አባት ሆይ የምትሔደው ወዴት ነው" አለችው። እርሱም "በከበሩ ቦታዎች ውስጥ ልሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም እሔዳለሁ" አላት እርሷም "ከእኔ ገንዘብ ወስደህ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል ግዛልኝና በመመለሻህ ጊዜ አምጣልኝ" አለችው። እርሱም በራሴ ገንዘብ ገዝቼ አመጣልሻለሁ አላት። 🌼 ከዚህም በኋላ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከቅዱሳት መካናት ተባረከና ሥዕሏን ሳይገዛ ወደ ጎዳናው ተመለሰ። ያን ጊዜም "ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ" የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰማ ወደ ገቢያም ተመልሶ ላሕይዋና መልኳ ያማረና የተወደደ የሆነ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል አግኝቶ ገዛት በሐርና በንጹሕ ልብስም ጠቀለላት። በጎዳናውም እየተጓዘ ሳለ ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ወንበዴዎች ተነሡበት ሊሸሽም ወደደ ከዚያቺም ሥዕል "መንገድህን ሒድ የሚል ቃል ወጣ" የተከተለውም ሳይኖር መንገዱን ተጓዘ። ሁለተኛም ነጥቆ ሊበላው አንበሳ ተነሣበት ያን ጊዜም ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረው። 🌼 አባ ቴዎድሮስም ይህን ሁሉ ድንቅ ተአምር ባየ ጊዜ ያቺን ሥዕል ወደ አገሩ ሊወስዳት ወደደ ግዛልኝ ላለችው መበለት ይሰጣት ዘንድ አልፈለገም። ✝ ከዚህም በኋላ በመርከብ ተሳፍሮ በሌላ አቅጣጫ ሲጓዝ ታላቅ ነፋስ ተነሣበት ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያም ወሰደው ከመርከቡም ወርዶ ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ሔደ ማንነቱንም አልገለጠላትም እርሷም አላወቀችውም። በማግሥቱም ተሠውሮ ወጥቶ ወደ አገሩ ሊሔድ በፈለገ ጊዜ የቅጽሩን ደጃፍ አጥቶ ሲያጥመሰምስ ዋለ በመሸ ጊዜም ወደ ማደሪያው ተመለሰ። ያቺም መበለት በአየችው ጊዜ ታደንቃለች እንዲህም ሁኖ እስከ ሦስት ቀን ኖረ በመሸ ጊዜ በሩን ያየዋል ነግቶ መሔድን ሲሻ የበሩ መንገድ ይሠወረዋል። ያቺም መበለት ያዝ አድርጋ "አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን ስትቅበዘበዝ አይሀለሁና ምን ሆነህ ነው" አለችው። 🌼 ከዚህም በኋላ ከዚያች ሥዕል የሆነውን ሁሉ ነገራት ራሱንም ገለጠላት። ያቺንም ሥዕል ሰጣት ተቀብላም የተጠቀለለችበትን ልብስ ፈታች ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች። ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የዚያን መነኩሴ እጆቹንና እግሮቹን ሳመች። 🌼 ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር የምትቀመጥበትን አዘጋጅታ አኖረቻት ማንም እንዳይዳስሳትም የነሐስ መስኮትን ሠራችላት በቀንና በሌሊትም የሚበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች ከመቅረዞችም ውጭ የሐር መጋረጃን ጋረደች። ከሥዕሊቱ በታችም ከሥዕሊቱ እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሠራ ወጭት አኖረች ያም መነኰስ እስከሚሞትበት ቀን ድረስ የእመቤታችንን ድንግል ማርያምን ሥዕል እያገለገለ ኖረ። 🌼 የሀገሩም ሊቀ ጳጳሳት የዚያችን ሥዕል ዜና በሰማ ጊዜ ከኤጲስቆጶሳትና ከካህናት ከሕዝቡም ሁሉ ጋር መጣ በሠሌዳውም ውስጥ በአዩዋት ጊዜ ሥጋ የለበሰች ሁና አገኙዋት ከዚህ ከአምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ ከዚህም ቅባት ቀድተው ለበረከት በተካፈሉ ጊዜ ወዲያውኑ በወጭቱ ውስጥ ይመላል። ወደ ሌላ ቦታም ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜ ንውጽውጽታ ሆኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ በዚያች አገር ትኖራለች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእናቱ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ 🌼 #ሰማዕቷ_ቅድስት_መጥሮንያ፦ ይቺም የከበረች መጥሮንያ ለአንዲት አይሁዳዊት ሴት አገልጋይዋ ናት። ይችም አይሁዳዊት እመቤቷ ከክርስትናዋ አፍልሳ ትክክል ወደ አልሆነ ሃይማኖቷ ልታስገባት ትሻ ነበር ስለዚህም ታጉሳቁላታለች በላይዋም የአገልግሎት ሥራን ታከብድባታለች ። 🌼 ከዚህም በኋላ በአንዲት ቀን አይሁዳዊት እመቤቷን ተከትላ ወደ አይሁድ ምኵራብ ሔደች ተመልሳም ወደ ከበረች ቤተ ክርስቲያን ገብታ ጸለየች። ወደ ቤት በገቡም ጊዜ "ወዴት ሒደሽ ነበር ወደእኛ ምኩራብ ለምን አልገባሽም" ብላ ጠየቀቻት ቅድስት መጥሮንያም "ከእናንተ ምኵራብ እግዚአብሔር ርቋል እኮን እንዴት ወደርሱ እገባለሁ። በውስጧ ልገባባት የሚገባኝ ቦታዬ ግን ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ በከበረ ደሙ የዋጃት ይህች ቤተ ክርስቲያን ናት" ብላ መለሰችላት። እመቤቷም ይህ ነገር በሰማች ጊዜ ተቆጣቻት እጅግም ደብደባ በጨለማ ቤት ውስጥ አሠረቻት ያለ መብልና መጠጥም አራት ቀን ኖረች። 🌼 ከዚህም በኃላ ከእሥር ቤት አውጥታ በጅራፍ ታላቅ ግርፋትን ገርፋ ሁለተኛ ወደ እሥር ቤት መልሳ አሠረቻት በዚያም ዐረፈች። እመቤቷም በድኗን አንሥታ ከቤቷ ደርብ ላይ አውጥታ በውጭ ወደታች ጣለቻት። ወድቃ የሚያዩዋት ሰዎች በገዛ ፈቃድዋ እንደወደቀች አድርገው እንዲናገሩ ብላ ነው ስለ መገደሏ ዳኞች እንዳይመራመርዋት ፈርታለች። 🌼 በዚያንም ጊዜ በዚያች አይሁዳዊት ሴት ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ወረደ ከደርቧ ላይ ስትወርድም በድንገት ወድቃ ሞተች ወደ ዘላለማዊም እሳት ሔደች ይህች የከበረች መጥሮንያ ግን የሰማዕታትን አክሊል ተቀብላ ወደ ዘላለም ሕይወት ሔደች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በቅድስት መጥሮንያ በረከቷም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የመስከረም 10 ስንክሳር።

语音消息00:36

语音消息01:41

语音消息03:16

+1
የሰርግ መዝሙሮች ስብስብ.pdf6.77 KB

🌼 "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። 🌼           🌼 #መስከረም ፱ (9) ቀን። 🌼 እንኳን #በሮሜ_አገር ፍሩምያ በምትባል ከተማ #በመላእክት_አለቃ_በቅዱስ_ሚካኤል በስሙ በተሠራ ቤተ ክርስቲያን #ላደረገው_ተአምር መታሰቢያ በዓል፣ ከኃላፊው #ከዚኽ_ዓለም_መንግሥቱ_መንኖ ተጋድሎውን በዛፍ ላይ ኹኖ ለፈጸመ፤ የደረቀውን ግንድ ላለመለ፣ ለጽጌ፣ ለፍሬ ለአደረሰ ላሳየ እግዚአብሔርን ደስ ላሰኘ #ለንጉሥ_ለቅዱስ_ለአባ_ያሳይ ለዕረፍት በዓልና ለመጺል ለምትባል አገር ኤጲስቆጶስ ለሆነ #ለቅዱስ_አባት_ለአባ_ቢሶራ_ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከቅዱስ_ፋሲለደስ_ጋር_ዐሥራ_አራት_ሺህ_ሰባት መቶ #ሠላሳ_ወንዶችና_ሰባት_ሴቶችም በሰማዕትነት ከዐረፉ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                               ✝ ✝ ✝ 🌼 በዚህች ቀን #በሮም_አገር_ፍሩምያ በምትባል ከተማ ለሆነው ተአምር መታሰቢያ ሆነ። ይህም እንዲህ ነው የሰማይ ሠራዊት አለቃ በሆነ በከበረ መልአክ #በቅዱስ_ሚካኤል_ቤተ_ክርስቲያን ውስጥ በሚታዩ ድንቆችና ተአምራቶች ምክንያት ዮናናውያን ሰዎች ሰይጣናዊ ቅናትን እንደ ቀኑ ከመቅናታቸውም ብዛት የተነሣ በዚያ አካባቢ የሚወርደውን የወንዝ ውኃ በዚያች ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊመልሱትና ከሚጠብቃት መጋቢዋ ጋር በውኃ ስጥመት ሊአጠፉአት ፈልገው መለሱት። 🌼 የሰማያውያን ሠራዊት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ለቤተ ክርስቲያኑ መጋቢ ለናርጢኖስ ተገለጠለት ወደርሱም ቀርቦ "ጽና አትፍራ" አለው ይህንን ብሎ በእጁ ውስጥ ባለ በትር አለቱን መታው አለቱም ተሰንጥቆ እንደ በር ሆነ የዚያ ወንዝ ውኃም በውስጡ አልፎ ሔደ። 🌼 ይህንንም ያዩ ምስጉን እግዚአብሔርን አመሰገኑት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልንም አከበሩት። ከዚያች ቀን እስከ ዛሬ የወንዙን ውኃ በዚያች በተሠነጠቀች አለት ውስጥ አልፎ ሲሔድ ያዩታል ወደ መላእክት አለቃ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ከቶ አይቀርብም። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማለጅነት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።                                                    ✝ ✝ ✝ 🌼 #ንጉሥ_ቅዱስ_አባ_ያሳይ፦ ይህም ቅዱስ ከኃላፊው ከዚኽ ዓለም መንግሥቱ መንኖ ተጋድሎውን በዛፍ ላይ ኹኖ የፈጸመ ነው፤ የደረቀውን ግንድ ከልምላሜ፣ ከጽጌ፣ ከፍሬ አድርሶ ያሳየ፤ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘ በቅዱስ ነው። ከንጉሥ ከቅዱስ (አባ) ያሳይ ያሳይ በጸሎቱ የምትገኝ በረከቱ ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                            ✝ ✝ ✝ 🌼 #የመጺል_አገር_ኤጲስቆጶስ_አባ_ቢሶራ፦ ይህም ቅዱስ በግብጽ አገር እግዚአብሔርን በምትወድ መጺል በምትባል ከተማ ኤጲስቆጶስ ሆነ። ዲዮቅልጥያኖስም ነግሦ ክርስቲያኖችን በሚያሠቃያቸው ጊዜ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ስም ደሙን ያፈስ ዘንድ ይህ አባት ወደደ። 🌼 ሕዝቡንም ሀሉ ሰብስቦ በቤተ መቅደሱ ፊት በዐውደ ምሕረቱ አቆማቸው ሊጠብቁት የሚገባውን ለጽድቅ የሚያበቃቸውን ትእዛዝ ሁሉ አዘዛቸው። ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ስም ደሙን ማፍሰስ እንደሚሻ ነገራቸው ይህንንም በሰሙ ጊዜ ታላቆችም ታናሾችም በላዩ አለቀሱ። "የሙት ልጆች እንሆን ዘንድ የምትተወን ምን ያደርግልሃል እኛስ እንድትሔድ አንለቅህም" አሉት ሊይዙትም ቃጡ ግን አልተቻላቸውም ተውትም እርሱም ወደ ክብር ባለቤት ክርስቶስ አደራ አስጠበቃቸውና ሰላምታ ሰጥቷቸው ከእነርሱ ዘንድ ወጥቶ ተጓዘ። እነርሱም መሪር ልቅሶን እያለቀሱ ሸኙት። 🌼 ስማቸው ቢስኮስ ፊናቢክስ ቴዎድሮስ የሚባሉ ኤጲስቆጶሳት አብረውት ሔድ መኰንኑ ወደ አለበት አገርም ደርሰው የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ። እርሱም መኰንኑ አሠቃያቸው ኤጲስቆጶሳትም እንደሆኑ አውቆ ሥቃያቸውን አበዛ እሊህ አባቶች ግን በታላቅ ትዕግሥት የጸኑ ናቸው። ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ ያጸናቸዋልና። 🌼 ከዚህም በኋላ መኰንኑ ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጧቸው ዘንድ አዘዘ የሕይወት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ። የቅዱስ ቢሶራ ሥጋው ግን ንሲል በሚባል አገር እስከ ዛሬ ይኖራል። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                                                ✝ ✝ ✝ 🌼 "#ሰላም_እብል_ለዓቢይ_መንክሩ። ዘተክሥተ ዮም በውስተ ዳቤሩ። ፈለገ ማይ ይሚጡ እንዘ ይመክሩ። ተሠጥቀ ኰኵሕ እንተ ዐላውያን አንበሩ። #ሶበ_ሚካኤል_ዘበጦ_በበትሩ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የመስከረም_9።                             ✝ ✝ ✝ 🌼 #የዕለቱ ምስባክ፦ "ደምፁ ወተሐምገ ማያቲሆሙ። ወአድለቅለቁ አድባር እምኃይሉ። ፈለገ ዘይውኅዝ ያስተፌሥሕ ሀገረ እግዚአብሔር"። መዝ 45፥3-4። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 8፥35-ፍ.ም፣ ያዕ 1፥2-13 እና የሐዋ ሥራ 20፥16-22። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 7፥24-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ሚካኤል የተአምራት በዓል፣ የንጉሥ ቅዱስ ያሳይ የዕረፍት በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።