ሰዋስው ☘☘☘☘
الذهاب إلى القناة على Telegram
በሰዋስወ ብርሀን ቅዱስ ዻውሎስ ገዳም እና ለተለያዩ ቤተክርስቲያን ለክብረ በአላት ማውጫ ። በተጨማሪም-ዋዜማ ሥርዓተ ማኅሌት - መዝሙራት ስንክሳር - የየእለቱን ምስባክ ቅኔያት ጥያቄዎች እንዲሁም የወቅታዊ ነገር መወያያ በተጨማሪም @eotcww ብለው ይቀላቀሉን ለወዳጅ ዘመድዎ share#Share#Share# ያድርጉ።
إظهار المزيد1 161
المشتركون
لا توجد بيانات24 ساعات
لا توجد بيانات7 أيام
لا توجد بيانات30 أيام
أرشيف المشاركات
1 161
+ + +
❤ የዕለቱ ምስባክ፦ "ወትሠይመኒ ውስተ ርእሰ ሕዝብ። ሕዝብ ዘኢየአምር ተቀንየ ሊተ። ውስተ ምስማዐ ዕዝን ተሠጥዉኒ"። መዝ 17፥43-44። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ቆሮ 12፥10-17፣ 1ኛ ዮሐ 5፥14-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 15፥1-13። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 15፥1-11። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።
https://t.me/Eotcw
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ ነሐሴ ፭ (5) ቀን።
❤ እንኳን እህቱን ቅድስት ማርያን ከዘማዊነት ሕይወት ወደ ጽድቅ ሕይወት ለመራት ለታላቁ ተጋዳይ ለሌለው ለአባ አብርሃም ለዕረፍት በዓል፣ ለከበረ ተጋዳይ ወታደር ለቅዱስ ዮሐንስ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከአባ አብርሃም እህት ከቅድስት ማርያ ከመታሰቢያዋ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
+ + +
❤ "ሰላም ለካልዕ አብርሃም ዘመጽለወ ሥጋሁ በጾም"። ትርጉም፦ ሥጋው በጾም የጠወለገ ለኾነ ለኹለተኛው አብርሃም ሰላምታ ይገባል። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ፡፡
+ + +
❤ አባ አብርሃም፦ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ባለጸጎች ናቸው በተግሣጽና ፈሪሃ እግዚአብሔርን በማስተማር አሳደጉት ። በአደገ ጊዜም ያለ ፈቃዱ አጋቡት እግዚአብሔርም ወደሚፈቅደው ይመራው ዘንድ ሲለምን ኖረ። በሰባተኛውም ቀን በዐልጋው ላይ ሳለ የእግዚአብሔር ቸርነት አነሳሥቶት ከጫጉላ ቤቱ ወጣ ብርሃን እየመራው ሒዶ ባዶ ቤት አግኝቶ በውስጡ ገብቶ ኖረ ምግቡን ከሚቀበልባት ከጥቂት መስኮት በቀር መዝጊያ ሠርቶ ደጁን ዘጋ።
❤ ዓለምን ከተወ በዓሥረኛው ዓመት አባትና እናቱ ብዙ ጥሪት ትተውለት ሞቱ እርሱ ግን ለድኆችና ለችግረኞች በትኖ በጾምና በጸሎት ተወስኖ እየተጋደለ ኖረ ከአንድ ዐጽፍና ሰሌን በቀር ምንም ምን ጥሪት አላኖረም እንዲህም ሆኖ ዐሥር ዓመት ተጋደለ።
❤ እግዚአብሔርም ትዕግሥቱን አየ በአንዲት አገርም አረማውያን ነበሩ ከታናሾቻቸው እስከ ታላላቆቻቸው ወደ ሃይማኖት ሊመልሳቸው የሚችል የሌለ። በአንዲት ቀንም አባ አብርሃምን ጳጳሱ አሰበው ብርታቱንና ብልህነቱንም አይቶ ቄስ እንዲሆንና እነዚያን አረማውያን እንዲመልሳቸው አስገደደው በግድ አስጨንቆም ቅስና ሾመው ። ወደዚያም ቦታ ደርሶ ቤተ ክርስቲያን ሠራ እነዚያን አረማውያን እርሱን ፈጣሪያቸውን ወደ ማወቅ ይመልሳቸው ዘንድ በውስጧ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።
❤ በአነዲት ቀንም ወደ ጣዖቶቻቸው ቤት ገባ ያን ጊዜ ጣዖታቱን ከመቀመጫቸው ጣላቸው የአገር ሰዎችም በአዩ ጊዜ ቁጣን ተመልተው አብዝተው ደበደቡትና ከአገር አበረሩት በጥዋትም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲጸልይ አገኙት። ሁለተኛም በገመድ አሥረው ወደ ከተማው ውጭ ጐትተው በላዩም አፈር ቆልለው እንዳይሞት ጥቂት መተንፈሻ ትተው አልፈው ከዚያ ሔዱ። በእግዚአብሔርም ኃያል ተነሥቶ ሔደ ስለ መመለሳቸውም ሲጸልይ አገኙት በእንዲህ ያለ ሥራም እየተጋደለ ዐሥር ዓመት ኖረ።
❤ የክብር ባለቤት እግዚአብሔርም ትዕግሥቱን አይቶ ወደ ቀናች ሃይማኖት ልባቸውን መለሰ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ከታናናሾች እስከ ታላላቆች ድረስ ሁሉንም አጠመቃቸው የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖትም ጸኑ።
❤ ከዚህም በኋላ በሃይማኖታቸው መጽናታቸውን ባየ ጊዜ ከንቱ ውዳሴ እንዳያመጣበት ፈርቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ አገሪቱንም በመስቀል ምልክት አማተበባትና ማንም ሳያውቅ ወጥቶ ወደ ሌላ አገር ሔደ ።
❤ ሰይጣንም በሚያስፈራው በብዙ ሥራ ይፈታተነው ነበር ቅዱሱም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኃይል አሸነፈው። ጽኑ በሆነ ተጋድሎም ኖረ ያለ ዕንባም ሰዓት አላለፈችውም በጥርሶቹም አልሳቀም በከንፈሮቹም ፈገግ አላለም ስጋውን ቅባት አልነካውም ስጋውንና ደሙን ከሚቀበልበት ጊዜ በቀር ፊቱንና እግሩን አልታጠበም ።
❤ እናትና አባቱ በስድስት ዓመቷ ትተዋት የሞቱ እኅት ነበረችው ስሟም ማርያ ይባላል ዘመዶቿም ወደ አብርሃም አምጥተዋት ፈሪሀ እግዚአብሔር ሃያ ዓመት ሆናት ድረስ ትሕትናንም እያስተማራት በእርሱ ዘንድ አደገች።
❤ ከዚህም በኋላ ሰይጣን ቀንቶባት ከአንድ መነኩሴ ጋር አፋቀራት ድንግልናዋንም አጠፉች ልብሷንና አስኬማዋን ለውጣ ወደ ሌላ አገር ሔደች። አባ አብርሃምም በዚያች ሌሊት ታላቅ ከይሲ ርግቢቱን ሲውጣትና ጥቂት ቆይቶ ከእግሩ በታች ሲተፋት ራእይን አየ። በማግሥቱም ማርያ ከቦታዋ ታጣች አባ አብረሃምም ደነገጠ ወደ እግዚአብሔርም ከብዙ ዕንባ ጋር ጸለየ እርሷን ያገናኘው ዘንድ። ከጥቂት ወራትም በኋላ እኅቱ ያለችበትን አባ አብርሃም ሰማ ሰዎችም እንዳያውቁት የምንኵስናውን ልብስ ለውጦ ፊቱንም ተከናንቦ የወታደር ልብስ ለብሶ በፈረስ ተቀምጦ ወዳአለችበት አገር ሔደ ከዚያም ደርሶ ማርያ ወዳለችበት ገባ የመሸተኛንም ልብስ ለብሳ በአያት ጊዜ እጅግ አዘነ ነገር ግን እንዳትሸሸው እንድታውቀው አልሆነም።
❤ ከዚህም በኋላ ለሚያገለግላት አሽከር ከማርያ ጋር የሚደሰትበት መብልና መጠጥ እንዲያዘጋጅ የወርቅ ዲናር ሰጠው ለርካሽ ሥራ እንደሚፈልጓት ሰዎች ይመስላት ዘንድ። ከራት በኋላም ወደ ውስጠኛው ቤት አስገባት በሩንም ዘጋ እጇንም ይዞ ራሱን ገለጠላት በአወቀችውም ጊዜ ደንግጣ እንደ በድን ሆነች "ልጄ ሆይ አይዞሽ ከእግዚአብሔር በቀር ከኃጢአት ንጹሕ የሆነ የለም ነገር ግን ወደ ንስሐ ተመለሺ ወደቦታሽም ገብተሽ የቀድሞ ሥርዓትሽን ያዢ" አላት እርሷም እሺ አለች።
❤ በነጋም ጊዜም ወስዶ በፈረሱ አስቀመጣትና ደስ እያለው ተመለሰ እኅቱን ከሰይጣን እጅ ማርኳልና ወደቦታውም በደረሰ ጊዜ የቤቷን ደጅ ዘግቶላት ማቅ በመልበስ እየተጸጸተች የተጋድሎንም ሥራ እየተማረች በብርታቷና በተጋድሎዋ ያዩ ሁሉ እስቲአደንቁ ጸንታ ኖረች ።
❤ እግዚአብሔርም በዚህ ቅዱስ ሰው እጆች ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ አጋንንትን በማስወጣት በሽተኞችን በማዳን ከአንዲት ዓመትም በኋላ የማርያን ንስሓዋን አይቶ በሰባ ዘመኑ የተመሰገነ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ነሐሴ 5 ቀን ዐረፈ።
❤ ማርያ እኅቱም ከለቅሶ ጋር ትርኅምትን በማብዛት ቀንና ሌሊት እየተጋደለች ሌሎች አምስት ዓመታትን ኖረች ከዚያም በኋላ ዐረፈች ያዩዋትም በፊቷ ውስጥ ሰለአለው ብርሃን እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ አብርሃም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
❤ ተጋዳይ ወታደር የሆነ ቅዱስ ዮሐንስ፦ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ክርስቲያኖች ናቸው እርሱም በከሀዲ በዑልያኖስ ሠራዊት ውስጥ ወታደር ሆነ። ንጉሡም ከባልንጀሮቹ ወታደሮች ጋራ ላከው የክርስቲያን ወገኖችንም በሚኖሩበት ቦታ ሁሉ እንዲአሠቃዩአቸው አዘዛቸው።
❤ እርሱም ለባልንጀሮች ጭፍሮች ክርስቲያኖችን እጅግ እንደሚጠላቸውና እንደሚጣላቸው ይገልጽላቸዋል በጭልታም ገብቶ በጎ ነገርን የሚሹትን ሁሉ ይሰጣቸዋል ያጽናናቸዋልም። ሁል ጊዜም ይጸልያል ይጾማል ይመጸውታልም የቅዱሳንንም አኗኗር ኖረ ምስጉን እግዚአብሔርንም አገልግሎ በሰላምዐአረፈ። ለእርሱም ለጌታ ምስጋና ይሁን። የቅዱሳንም በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 5 ስንክሳር።
+ + +
❤ "ሰላም ለአብርሃም ዘተሰደ ወተዘብጠ፡ እምሕርትምና ወካሕድ አረማውያን እስከ ሜጠ። ወነፍሰ እኅቱ ጼዊዎ እምአፈ ከይሲ መሠጠ። እስመ ኢጸግብ እምተጋድሎ እስከ ዕድሜሁ ሰለጠ። መዋዕለ ዓመታት ፸ ኮነ ኅዳጠ"። ትርጉም፦ አረማውያን ከጥፋትና ከክሕደት እስኪ መልስ ድረስ ተደብድቦ የተሰደደ ለኾነ ለአብርሃም ሰላምታ ይገባል፤ የእኅቱን ሰውነት ከከይሲ አፍ ማርኮ ነጠቀ፤ እድሜውን እስኪጨርስ ድረስ ተጋድሎን አልጠገበምና፤ ሰባዎቹ ዓመታት ጥቂትን ኾኑበት። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የነሐሴ 5።
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ ነሐሴ ፭ (5) ቀን።
❤ እንኳን ለኢትዮያዊው ጻድቅ በኤርትራ አገር በሐማሴን አውራጃ ከአስመራ ከተማ በስተምሥራቅ 25ኪ.ሜ ርቀት የሚገኝ አስደናቂ ገዳም ዘደብረ ቢዘን ለመሰረቱት እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላቸው ድውያንን ይፈውሱ ለነበሩት ለአንዳዴ ባሕር ለአባታችን ለአቡነ ፊልጶስ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን።
+ + +
❤ አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ቢዘን፦ እንደ ነቢዩ ኤርምያስ በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ የተመረጡና እንደተወለዱ ነው ሰማንያ አንዱን የብሉይ መጻሕፍትን አጠናቀው ያወቁት ናቸው፡፡ በ12 ዓመታቸውም ለመመንኰስና ገዳም ለመግባት ወስነው ወላጅ እናታቸውን "አሰናብቺኝ" በማለት ጠይቀዋል፡፡ ቅድስት እናታቸውም መርቀው ሸኟቸውና ትግራይ ውስጥ ወደሚገኘውና ደብረ ጸራቢ ወደሚባለው ገዳም ገቡ፡፡ የገዳሙ አስተዳዳሪ አቡነ በኪሞስም የምንኵስና ቀንበሩና ሸክሙ እጅግ ከባድ መሆኑን በመንገር ወደ እናታቸው እንዲመለሱ ቢመክሯቸውም አቡነ ፊልጶስ ግን ለምንኵስና የታጩ ሙሽራ መሆናቸውን ነገሯቸው፡፡ ከብዙ ፈተናም በኋላ አመነኰሷቸው፡፡
❤ በገዳሙም እንጨት እየለቀሙና እየፈለጡ፣ ውኃ እየቀዱ፣ የክርስቶስን ሕማሙን ሞቱን እያሰቡ በጾምና ጸሎት ሲጋደሉ ከኖሩ በኋላ ጌታችን ተገልጦላቸው ወደ ሽሬ እንዲሄዱ ነገራቸውና ሽሬ አደያቦ ወደሚባለው ስፍራ ሄዱ፡፡ ብዙ አስደናቂ ተአምራት እያደረጉ ወንጌልን በሀገሩ ዞረው ሰበኩ፡፡ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላቸው ድውያንን ይፈውሱ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ደብረ ቢዘን እንዲሄዱ ተነግሯቸው የእርሳቸውን በረከት ለመቀበል ከመጡ 16 ደጋግ መነኰሳት ጋር ወደ ደብረ ቢዘን ሄዱ፡፡ ይኸውም በኤርትራ ክፍለ ሀገር በሐማሴን አውራጃ ከአሥመራ ከተማ በስተምሥራቅ 25 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው አስደናቂው ገዳም ነው፡፡
❤ ጻድቁ የሐይቅ እስጢፋኖስን ባሕር በተአምራት ያቃጠሉት አባት ናቸው፡፡ በንጉሡ በዐፄ ዳዊት ዘመን ሰንበትን አንድ ብቻ ናት እያሉ በአንደኛዋ ሰንበት ሥራ ሲሠሩ ጻድቁ አቡነ ፊልጶስ ይህን ሰምተው አንዲት ሰንበት የሚሉትን ሁሉ ተቃወሟቸው፡፡ ከግብፅ የመጡት ጳጳስም ቀደም ብሎ ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አሁንም ከአቡነ ፊልጶስ ጋር ንጉሡ ዐፄ ዳዊት አከራክረዋቸው ጳጳሱም በክርክሩ ተረቱ፡፡ ክፉዎችም በአቡነ ፊሊጶስ ላይ በክፋት ተነሱባቸው፡፡ በአቁማዳ ጠቅልለው ሐይቅ ባሕር ውስጥ ጣሏቸው፡፡ በዚህም ጊዜ እሳቸው የተጣሉበት ባሕር በእሳት ተቃጥሎ ጽድቃቸውን መስክሮላቸዋል፡፡
❤ ዛሬም ድረስ በሐይቅ እስጢፋኖስ ባሕር ዳርቻ ላይ የተቃጠለው ድንጋይ ምልክቱ በግልጽ ይታያል፡፡ በወቅቱ የንጉሡ ሚስት በዋናተኛ አስፈልጋ ከሐይቁ ውስጥ አስወጣቻቸው፡፡ እግራቸውንም አጥባቸው ስትጨርስ የእግራቸውን እጣቢ ጠጣችው፡፡ ወዲያውም "ከማኅፀንሽ ፍሬ ታላቅ ጻድቅ ልጅ ይወጣል" ብለው ትንቢት ነገሯት፡፡ በትንቢታቸውም መሠረት ታላቁ ጻድቅ ንጉሥ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ተወልዱ፡፡ በወቅቱ በተፈጠረው አለመግባባትና ክፉዎችም በባሕር ውስጥ ስለጣሏቸው ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም አቡነ ፊልጶስን ከልብ ይቅርታ ጠይቀው ወዲያው ታርቀዋል፡፡ በዘመናቸውም ርኃብ ስለነተሳ ጻድቁን ከገዳማቸው አስጠርተው "ምን ባደርግ ይሻለኛል?" ብለው አማክረዋቸዋል፡፡ አቡነ ፊልጶስም "የጌታችንን መስቀል ያስመጡ" ብለው መከሯቸው፡፡
❤ ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም በአቡን ፊልጶስ ምክር መሰረት ከኢየሩሳሌም፣ ከቍስጥንጥንያና ከእስክንድርያ መንግሥታት ጋር ተጻጽፈው ዐሥሩን ታላላቅ ቅዱሳን ይዘው ሄደው መስቀሉን መስከረም 10 ቀን አምጥተውታል፡፡ ቅዱስ መስቀሉን ያመጡት ዓሥሩ ቅዱሳንም የደብረ ቢዘኑ አቡነ ፊልጶስ ፣ የጣና ደሴቱ አቡነ ኂሩተ አምላክ፣ የጣና ደሴቱ አቡነ እንድርያስ፣ አቡነ በትረ ማርያም፣ አቡነ ዮሐንስ፣ አቡነ ታዴዎስ፣ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ፣ አቡነ ዘካርያስ፣ አቡነ ያሳይና አቡነ ቶማስ ናቸው፡፡ አቡነ ፊሊጶስ ዘደብረ ቢዘን በታላቅ ተጋድሎ ኖረው ከጌታችን ዘንድ ታላቅ ቃልኪዳን ከተቀበሉ በኋላ ነሐሴ 5 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል። ከአባታችን አቡነ ፊሊጶስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱስ ከሚለው መጽሐፍ።
+ + +
❤ "ሰላም ለፊልጶስ እንተ ክህለ ያዕዱ። ለዘጸውዖ ብእሲ ለውኂዘ ክረምት እምነ ሞገዱ። ወእምኔሁ አብ እለ መንፈስ ተወልዱ። እንዘ ይዜንው ኃይሎ ወምግባረ ጽድቁ ይንዕዱ። ስሙዓቲሁ ወጽአ ለዓለም በዐውዱ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የነሐሴ5።
❤ በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።
https://t.me/Eotcw
1 161
ጻዲቁ ዮሴፍ እጅግ ከባድ የሆነ ውጪያዊ ውጊያ ከጲጥፋራ ሚስት ቢገጥመውም አልወደቀም።
እርሱ ኃጢአትን በልቡ ውስጥ ስላልተቀበለው ፈተናውንም አልተቀበለውም። ስለሆነም ጥቃቱን ሊቋቋም ችሏል።
እያስተዋልን
ዲያብሎስ አሳቦችን ያቀርብልሃል እንጅ ተቀብለህ ተግባራዊ እንድታደርጋቸው አያስገድድህም።
እናም ለስህተት ሌላ ሰው ተጠያቂ አታድርግ መጀመሪያ እራስን ይቅርታ ጠይቀህ ከዛም በነገሮች የተረበሹትን ይቅርታ መጠየቅ በመቀጠል አምላክህን ይቅርታ መጠየቅ
መልካም የፍልሰታ ፆም
1 161
ፍልሰታ
×
|
መቼም ቢሆን የልጅነት ዘመኔን ከሚያስታውሱኝ የቤተክርስቲያን ወቅቶች መካከል የፍልሰታ የፆም ወቅት አንዱ ነው። በዚሕ የፆም ወቅት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀዳደደ ነጠላ አጣፍቼ ወደ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ለማስቀደስ የሄድኩት።
ሕንፃ ቤተክርስቲያኑን ከራሴ ቁመት ጋር አነፃጽሬ የተገረምኩት። ትልቀቱ ግዝፈቱ የገረመኝ። የቤተክርስቲያኑ ግንብ ላይ ያሉት ጠጠሮች ። የቆሙት አስራ ሁለቱ የቤተክርስቲያን ምሰሶዎች….. ብቻ ሁሉንም ማወቅ የቻልኩት በዛን የልጅነቴ ጊዜዬ ነው ፡፡
ነጠላዬን አላስተካከልኩም
"ወዴት ነው የምትሄደው? "
" ስንት ሰዓት ነው የምትመጣው? " አልተባልኩም። ብቻ ነጠላዬን አጣፍቼ ወደ ቤተክርስቲያን ራሴን ችዬ ከሰፈሬ ልጆች ጋር የሄድኩት በፍልሰታ የፆም ወቅት ነው፡፡
ቤተክርስቲያኑ እንደኔ ያሉትን ብዙ ሕፃናት የማስተናገድ አቅም ነበረው። ብዙ ነን። በጣም ብዙ።
አንዱ ዣንጥላ ይዞ ይሯሯጣል ….
አንዳንዱ ሹሌ ይጫወታል…..
ሌላው ምንጣፍ ይጎትታል….. በዘረጋነው ምንጣፍ ላይ ተርታውን ዓውደ ምሕረቱ ላይ እንተኛ ነበር፡፡ (ካደኩ በኋላ ነው እንዲያ የምንተኛው የአተኛኘት ዓይነት አስመራ ድርድር መባሉን ያወኩት)። የደብሩ ዲያቆናት ከመቅደሱ ወደ ቤተልሔም ለአገልግሎት ሲፋጠኑ ….ውር ውር ሲሉ የልጅነት አዕምሮዬ ላይ ተከትቦ ቀርቷል። መቅደስ ውስጥ የጉልላቱን ርቀት እያየሁ ይደንቀኝ ነበር። መንግስተ ሰማያት ማለት ያ ይመስለኝ ነበር ። ያኔ ነው የመቅደሱ ፍቅር የጣለኝ፡፡
ካሕናቱ ፍሕሙን በጧፍ ሲያቀጣጥሉ ። የዕጣኑ መዓዛ በንፋስ እተገፋ ያለንበት ድረስ መጥቶ ሲያውደን። የቤተክርስቲያኑ ጠባቂ ንቦች አንዳንድ ጊዜ ለመደበቅ የማይመች ቦታ ሲነድፉን በእብጠቱ ጓደኞቻችን እየሳቁ ያስኮርፉን ነበረ ። ከንፈራችን አፍንጫችን ቅንድባችን የተነደፈ ዕለት የሚኖረው እብጠት እኛኑ ራሱ ያስገርመን ነበረ። ደሞ በ
ሌላ ጊዜ እንዳይነድፉን በነጠላችን ስንሸፋፈን ትዝ ይለኛል፡፡
በቃ ደስ የሚል ትዝታ አለ አይደለ ….ፍልሰታ ለእኔ እንደዛ
የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች ሁላችንንም ሰብስበው አዳራሽ ውስጥ ቁርባን እስኪጀመር ድረስ አስገብተው የሚነግሩን መፅሃፍ ቅዱሳዊ ታሪኮች። መሳጭ የሆኑት የእነ አብርሃም ታሪክ አጣፍጠው የሚነግሩን የተረት አባቶች ። ያኔ አዳራሹ መቀመጫ ወንበር አልነበረውምና ምንጣፍ ተነጥፎልን ነበር የምንቀመጠው። ብዙዎቻችን ለመቀመጥ እንጋፋለን ።
ሥርዓተ ቅዳሴ ሲጀመር ይሰማናል።
"አሐዱ አብ ቅዱስ ..." ሲባል ሁላችንም እንድንነሳ ይደረጋል። አቤት የነበረ ፍቅር። ቶሎ ለመነሳት ያለን እሽቅድድም። ለመነሳት አንዱን ስንደገፍ…. ሌላኛው እኛን ሲደገፈን…. የነበረው መልካምነት ደስ ይል ነበር። የሰንበት ትምህርት ቤቱ መድረክ ለልጅነታችን አዕምሮ ይገዝፍብን ነበር። እየተቀባበሉ የሚያቀርቡልን መነባንብ ….. የምድብ ማቴዎስ የሕጻናት ክፍል ተማሪዎች እየተቀባበሉ የሚዘምሩልን መዝሙር…. አዝማቹ ሲጠፋቸው ለማረም ስንሞክር የምነፈጥረው ረብሻና ጩኽት። አቤት እንዴት ደስ ይል ነበር። አዳራሽ በተራ ነበር የምንገባው…… ዛሬ ወንዶች ከገቡ ነገ ደግሞ ሴቶች ይገባሉ፡፡ በዛ ድራማና መነባንብ ተስበን ብዙዎቻችንን ሰንበት ትምህርት ቤት አባል ሆነን ቀርተናል።
ጥሬ የሚለቅሙት ነጫጭ እርግቦች አውደ ምህረቱ ላይ የተበተነላቸውን የድፎ ዳቦ ፍርፋሪ….. የእንጀራ ቁራሽ…. የጥሬ ብትን ሲመገቡ ቆመን እናያቸው ነበር።
ስንት ነበሩ ርግቦቹ?
አንድ ጨቅላ ሕጻን ልጅ እየሮጠ ወደ ተሰበሰቡት እርግቦች መሰስ ብሎ ሲሄድ እየተበታተኑ ወደ የአቅጣጫው ሲሄዱ። በየዛፎቹ ላይ ሲንጠላጠሉ። እናቶች ሕፃኑን ልጅ ይዘውት ሲሄዱ። የተበታተኑት እርግቦች መልሰው ሲሰበሰቡ። ከሕ
ንፃ ቤተክርስቲያኑ መስኮት ላይ ….. ከደውሉ ላይ…… ከዛፎች ላይ ….ድጋሚ ተሰብስበው ጥሬ ሲለቅሙ ያለው ድባብ መቼም የማይረሳ ትዝታ ነው፡፡
ሕፃንነት ነውና ጊቢው ዙርያ እንሮጣለን…. አንዱን ጓደኛችንን እናባራለን፡፡
በሌላ ቀን ደሞ
ካህናቶች ወደ ቤተልሔም ወርደው መሶበ ወርቅ ዲያቆኑ ተሸክሞ ሲመለስ የዲያቆኑን ቃጭል ተከትሎ የሚደወለው ትልቁ ደወል ። ሕዝበ ክርስቲያኑ መሬት ወድቆ ሲሳለም።
"እምነ በሃ ቅድስት ቤተክርስቲያን አረፋቲሃ "ሲሉ። ሁለቱ ድምፅ ማጉዎች ሲያስገመግሙ ሲያስተጋቡ ።
"ሃሌ ሉያ እመቦ ብዕሲ ምዕመናን ዘቦአ ቤተክርስቲያን " ሲባል እንረጋጋለን። ወላጆች ልጆቻቸው እንዳይቀሰፉ በማለት በእጆቻቸው ይጣራሉ፡፡
በፍልሰታ ፆም የማላየው የዣንጥላ አይነት የለም። ጥቁር ቢጫ አረንጓዴ ቀይ...
የማልመለከተው የሰው ዓይነት የለም አጭር ወፍራም ሽማግል ወጣት ቀጫጫውን ...ወዘተ
ያላየሁት መቀመጫ ዱካ በርጩማ ያላየሁት ምንጣፍ የለም። ከቤተክርሰቲያኑ ዋናው በር በስተግራ የመባዕ መሸጫውን….. ክርስትና ቤቱን ….. የሰንበት ትምህርት ቤቱ አዳራሽን ይዞ….. የደብሩ አስተዳደር ያለበትን…. የአባታችን የአባ ክፍለ ዮሐንስ ዘወልደማርም መኖሪያ ቤት በሙሉ መጠለያ ስምንትን ጨምሮ እስከ ቤተልሔሙ ድረስ[ከቤተልሄም በመለስ] ሴቶች ይቆማሉ።
ጥንታዊያን የተሰኙ ዲያቆናት መሪጌታዎች መነኮሳት ቀሳውስት የቤተልሔሙን አጸድ ይመርጣሉ። ወጣቶችም አይጠፉም ። መጠለያዎቹ ግጥም ብለው ይሞላሉ ። ደወሉም ላይ የሚወጣ አይጠፋም። በቤት መኪና …. በላዳ ታክሲ ጭምር መጥተው የሚያስቀድሱም አሉ። ብቻ ሁሉም እግሩ በመራውና ይመቸኛል ባለው ቦታ ለማስቀደስ ይቆማል ።
"ሥመር እግዚኦ ከመ ታድኅነነ " ሲባል ሁሉም ቀጥ ብሎ ይቆማል ። የቤተክርስቲያኑ በሮች በጥበቃዎቹ ይዘጋል። እጆች ይዘረጋሉ።
"አሐዱ" ሲባል ጥበቃው እየተራመደ ከሆነ ይቆማል። አንዳንዱ ያለቅሳል ሌላው በፍርሃትና በተመስጦ በጌታ ፊት ሲቆም። የሚነደው ፍሕም ላይ የገባው ዕጣን ያለከልካይ ብቻውን ሲንቦለቦል። የካህናቱ ዜማ እንደ ንፁሕ ምንጭ ውሃ ኩልል ሲፈስ። የእጣኑ መዓዛ ጅረት ሆኖ ቤተክርስቲያኑን ሲዞር ለተመለከተው የሰማይ ሥርዓት በምድር እንደተሰራ የሚያመላክት አንዳች ኃይል አለው ፡፡
ሕፃናት ጃንጥላዎቻቸውን ዘርግተው የቤተክርስቲያኑን ግንብ ተደግፈው ይቀመጣሉ፡፡ በጊቢው ውስጥ የተገኙት ምዕመናን "ስግዱ ለእግዚአብሔር በፍርሃት" የሚለውን የዲያቆኑ ትዕዛዝ ተከትለው "ቅድሜከ እግዚኦ ንሰግድ" እያሉ በሕብረት ይሰግዳሉ።
ሁለት አንድ አይነት የሆኑ የካሕናት ዜማዎች ከቤተመቅደሱ አናት ላይ ይፈሳሉ። በልጅነቴ የሰማሁት ቅዳሴ ማርያም ዛሬምድረስ ይታወሰኛል። የእመብርሃን…. የወላዲተ አምላክ ቅዳሴ እኮ ነው ።
አኮቴተ ቊርባን ዘእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘደረሰ በመንፈስ ቅዱስ አባ ሕርያቆስ ኤጲስ ቆጶስ ዘሀገረ ብህንሳ ። ሁላችንም ይህን የቅዳሴ አንቀጽ የሰማነው በልጅነታችን አእምሮ ነው። "
"...ጎሥዐ ልብየ ቃለ ሠናየ ወአነ አየድሕ ቅዳሴሃ ለማርያም አኮ በአብዝኆ አላ በአውሕዶ" የቀዳስያኑ ድምጽ ባለ ግርማ ሞገስ ነበር (አሁንም ነው ድረስ ነው) ። ፍሬ ቅዳሴውን እየተቀባበሉት ሲደግሙት። አንድ ቀን በግዕዝ። በሌላኛው ቀን ደሞ በአማርኛ ንባቡን ሲዘልቁት። ዛሬም በአዕምሮዬ ትዝታ ሆኖ ቀርቷል፡፡
"ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራዊን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለም በንፅሕና በቅድስና በቤተመቅደስ ኖርሸ እንጂ….."
"ድንግል ሆይ ምድራዊ መጠጥ የጠጣሽ አይደለሽም ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥ ነው እንጂ ….. "
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ ነሐሴ ፬ (4) ቀን።
❤ እንኳን ከዳዊት ዘር ለሆነ ለአካዝ ልጅ ንስሃ በመግባቱ በእድሜ ላይ 15 ዓመት ለተጨመረለት ለንጉሥ ቅዱስ ሕዝቅያስና እንደ በግ የጸጉር ልብስ ለብሶ በበረሃ ለሚኖር ሰማዕቱ መርምኅናምን ላሳመነና እህቱን ሣራንም ከለምፅዋ ላነፃት ለአባታችን አባ ማቴዎስ ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከከበሩ ዳዊትና ወንድሞቹና ከግብጽ ደቡብ ስንካር ከሚባል አገር በሰማዕትነት ከዐረፈ ከቅዱስ ፊልጶስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
+ + +
❤ "ሰላም ለሕዝቅያስ ንጉሥ ዘፈወሶ እግዚአብሔር እምደዌሁ በቃለ ኢሳይያስ ወአግብኦ በእንቲኣሁ ለፀሓይ ድኅረ፤ ወአድኀኖ እምእደ ሰናክሬም ዘተዐየሮ በሐዋርያቲሁ"። ትርጉም፦ እግዚአብሔር ከደዌው የፈወሰው፤ በኢሳይያስ ቃልም ፀሓይ ወደ ኋላ እንዲመለስለት ያደረገው ለሚኾን በመልእክተኞቹም ከተገዳደረው ከሰናክሬም እጅ ላዳነው፤ ለሕዝቅያስ ሰላምታ ይገባል። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።
+ + +
❤ ቅዱስ ንጉሥ ሕዝቅያስ፦ ይህ ንጉሥ ከዳዊት ዘር የአካዝ ልጅ ነው። ከጻድቁ ንጉሥ ከዳዊት በኋላ እንደ ሕዝቅያስ ያለ በእስራኤል ውስጥ አልተሾመም ከዚህ ጻድቅ ንጉሥ በቀር ሁሉም ጣዖትን አምልከዋልና መሠዊያም ሠርተዋልና።
❤ እርሱም በነገሠ ጊዜ ጣዖታትን ሰበረ መሠዊያቸውንም አፈረሰ ከነሐስ የተሠራውንም እባብ ቆራረጠ የእስራኤል ልጆች አምልከውት ነበርና እግዚአብሔርም ዘመነ መንግሥቱን እጅግ አሳመለት በጎ ነገርንም ሁሉ ሰጠው።
❤ ሕዝቅያስም በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዘመን የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ኢየሩሳሌምን ከበባት ይህም ሰናክሬም በዘመኑ እንደርሱ ያለ የሌለ ኃይለኛ ብርቱ የምድር ነገሥታት ሁሉ የፈሩትና የታዘዙለት ነው። ሕዝቅያስም ከእርሱ ግርማ የተነሣ ፈርቶ አገሩን እንዳያጠፋ ብዙ ወርቅና ብር እጅ መንሻ ላከለት ሰናክሬምም ደስ ብሎት ምንም ምን አልተቀበለም በእርሱ ላይና በልዑል እግዚአብሔር ላይ ተቆጥቶ "እግዚአብሔር ከእኔ እጅ ሊያድናችሁ አይችልም " በማለት የስድብ ቃል ላከ እንጂ።
❤ ሁለተኛም በልዑል ስም ላይ ስድብና ቊጣ የተጻፈበትን ደብዳቤ ላከ ሕዝቅያስም በሰማ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ አለቀሰ ልብሱንም ቀዶ ማቅ ለበሰ እንዲህም ብሎ ጸለየ "አቤቱ የእስራኤል አምላክ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ አንተም ብቻህን ዓለም መንግሥታት ላይ ንጉሥ የሆንክ አንተም ሰማይና ምድርን የፈጠርህ ልመናዬን አድምጥ። ዐይኖችህን ገልጠህ ተመልከት ሕያው እግዚአብሔር አንተን እያቃለለ ሰናክሬም የላከውን ቃሉን ስማ"።
❤ ከዚህም በኋላ ንጉሥ ሕዝቅያስ የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬም የተናገረውን እንዲነግሩትና ስለርሱና ስለ ሕዝቡ ይጸልይ ዘንድ ወደ ኢሳይያስ መልእክተኞችን ላከ። ኢሳይያስም ከእግዚአብሔር ቃልን ተቀብሎ እንዲህ ብሎ መለሰለት "ልብህን አጽና አትፍራ በዓለሙ ሁሉ እንደርሱ ያለ ያልተማ ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሥራ በሰናክሬም ላይ ሊሠራ እግዚአብሔር አለውና"።
❤ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር የላከው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ ከፋርስ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሰዎችን ገደለ የለኪሶም ሰዎች ሲነጋ በተነሡ ጊዜ የሞቱትን ሰዎች ሬሳ ሁሉ አገኙ የተረፉትም ከንጉሣቸው ጋራ ሸሽተው ነነዌ አገር ገቡ። ሰናክሬምም ሊጸልይ ወደ ጣዖቱ ቤት በገባ ጊዜ ልጆቹ አድራማሌክና ሶርሶር በሰይፍ መትተው ገደሉት። ሕዝቅያስም ከሰናክሬም እጅ ድኖ የተመሰገነ እግዚአብሔርን አመሰገነው።
❤ በዚያም ወራት ሕዝቅያስ ታመመ ለሞትም ደረሰ የአሞፅ ልጅ ኢሳይያስም ወደርሱ መጥቶ "እግዚአብሔር እንዲህ አለ ትሞታለህ እንጂ አትድንም ቤትህን ሥራ" አለው። ሕዝቅያስም ፊቱን ወደግድግዳው መልሶ ወደ እግዚአብሔር ለመነ እያመሰገነውም እንዲህ አለ "አቤቱ በቀና ልቡና በዕውነት ሥራ በፊትህ ጸንቼ እንደኖርኩ ፈቃድህንም እንደፈጸምሁ አስብ" ብሎ ሕዝቅያስ ፈጽሞ ጽኑዕ ልቅሶን አለቀሰ።
❤ ኢሳይያስም ወደ መካከለኛው ዐፀድ ደረሰ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው "ሒደህ ለወገኖቼ ንጉሥ ለሕዝቅያስ ያባትህ የዳዊት ፈጣሪ እግዚአብሔር እንዲህ አለ በለው። ጸሎትህን ሰማሁ ዕንባህንም አየሁ እነሆ እኔ አድንሃለሁ እስከ ሦስት ቀንም ወደ እግዚአብሔር ቤት ትመጣለህ። በዘመኖችህም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት ጨምሬልሃለሁ ከፋርስ ንጉሥ እጅም አድንሃለሁ ይቺንም አገር ስለ እኔና ስለ ባላሟሌ ዳዊት አጽንቼ እጠብቃታለሁ"።
❤ ሕዝቅያስም ኢሳይያስን እንዲህ አለው "እግዚአብሔር እንደሚያድነኝ እስከ ሦስት ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት ለመውጣቴ ምልክት ምንድ ነው"። ኢሳይያስም እንዲህ አለው "የተናገረውን ቃል ያደርግ ዘንድ ከእግዚአብሔር የተገኘ ምልክቱ ይህ ነው አነሆ ጥላው ወደ ዐሥረኛው እርከን ይወርዳል። ወደ ዐሥረኛው እርከን ቢመለስ ምልክቱ ይህ ነው"። ሕዝያስም "እንዲህ አይደለም የጥላው ወደ ዐሥረኛ እርከ መመለስ ቀላል ነው። መመለስስ ከሆነ ፀሐይ ወደ ዐሥረኛው እርከን ይመለስ" አለ። ኢሳያስም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ ፀሐይም ዐሥሩን እርከን ተመለሰ።
❤ ሕዝቅያስንም የምድር ነገሥታት ሁሉ ፈሩት እጅ መንሻም አገቡለት የእግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋራ እንዳለ አውቀዋልና። በመንበረ መንግሥቱም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነግሦ ኖረ። እግዚአብሔርን አገልግሎ ነሐሴ 4 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በንጉሥ ቅዱስ ሕዝቅያስ በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
+ + +
❤ በዚችም ቀን እንደ በግ የደጒር ልብስ ለብሶ በበረሃ የሚኖር አባ ማቴዎስ ዐረፈ። እርሱም መርኅናምን ያሳመነው ሣራንም ከለምፅዋ ያነፃት ነው። የአባ ማቴዎስ በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 4 ስንክሳር።
+ + +
❤ "ሰላም ለሕዝቅያስ ዘጸለየ በሕቁ። ዘተወሰከ ዘመኑ ወፈድፈደ እምኊልቁ። እመኒ ሶቤሃ ተዐየርዋ ለድድቁ። በእደ መልአክ ሠራዊት ፋርስ ኀልቁ። ወለመልኮሙ ቀተልዎ ደቁ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የነሐሴ 4።
+ + +
❤ የዕለቱ ምስባክ፦ "እግዚኦ በኃይልከ ይትፌሣሕ ንጉሥ። ወብዙኀ ይትኀሠይ በአድኅኖትከ። ፍትወተ ነፍሱ ወሀብኮ"። መዝ 20፥1-2። የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 12፥16-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 5፥6-12 እና የሐዋ ሥራ 17፥23-28። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 14፥31-35። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት
https://t.me/Eotcw
1 161
ዘነሐሴ ፫
#ምንባባት
፩ቆሮ ም፫ቊ፲-፳፪
፩ ጴጥ ም ፫ቊ ፩-፯
ግብ ሐዋ ም፲፯ቊ፲፫-፲፱
#ምስባክ
መዝ ፵፬ቊ፲፪-፲፫
ወይሰግዳሎቱ አዋልድ ጢሮስ በአምኃ።
ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኲሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር
ኲሉ ክብራ ለወለተ ንጉሠ ሐሴቦን።
#ትርጉም
የጢሮስ ሴቶች ልጆች እጅ መንሻን ይዘው ይሰግዱለታል፣
የምድር ባለጠጎች አሕዛብ ሁሉ በፊትሽ ይማልላሉ፣
ለሐሴቦን ንጉሥ ሴት ልጅ ሁሉ ክብርዋ ነው፣
#ወንጌል
የማርቆስ ወንጌል ም ፲፮ቊ፱-፲፱
#ቅዳሴ
ዘእግዝእትነ(የእመቤታችን ቅዳሴ)
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ ነሐሴ ፫ (3) ቀን።
❤ እንኳን በገድል ለተጠመዱ ስልሳ ክንድ የድንጋይ ምሰሶ ላይ ወጥተው በዚያም ሳይቀመጡ ቆመው እያስተማሩና እየጸለዩ ለ 42 ዓመታት ለተጋደሉ ለታላቁ አባት ለአባ ስምዖን ዘዓምድ ሶርያዊ ለዕረፍት በዓልና ከመንግሥት ወገን ለሆነች ለቅድስት ሶፍያ ዘሮምና ለሦስት ሴት ደናግል ልጆቿ ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን።
+ + +
❤ አባ ስምዖን ዘዓምድ ሶርያዊ፦ ለዚህም ቅዱስ ስድስት ዓመት በሆነው ጊዜ አባቱ የበጎቹ ጠባቂ አደረገው። ወደ ቤተ ክርስቲያንም በመሔድ ሁል ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይሰማ ነበር የእግዚአብሔርም ቸርነት አነሳሥቶት ወደ አንድ ገዳም ሒዶ መነኰሰ ብዙ ዘመናትም በገድል ተጠምዶ ሲጋደልና ሰውነቱን ሲያስጨንቅ ኖረ።
❤ ከዚህም በኋላ ገመዱ ሥጋውን ቆርጦ እስቲገባ ድረስ በወገቡ ላይ ገመድን አሠረ። ሥጋውም ተልቶ ከእርሱ ክፉ ሽታ ይወጣ ነበር ስለ ክፉ ሽታውም መነኰሳቱ አዘኑ ተጸየፉትም ወደ አበ ምኔቱም ተሰብስበው "ይህን መነኰስ ስምዖንን ከእኛ ዘንድ ካላወጣኸው አለዚያ አንተን ትተን ወደሌላ እንሔዳለን" አሉት እርሱም "ምን አደረገ" አላቸው እነርሱም "ጥራውና አንተ ራስህ እይ" አሉት። ጠርቶትም መጥቶ በፊቱ በቆመ ጊዜ ደም ከመግል ጋራ በእግሮቹ ላይ ሲፈስ አየ አበ ምኔቱንም እጅግ አስጨነቀው። ልብሶቹንም ገልጦ በሥጋው ውስጥ የገባውን ያንን ገመድ አየው አበ ምኔቱም በእርሱ ላይ ተቆጥቶ "ይህን ታደርግ ዘንድ እንዴት ደፈርክ" አለው በታላቅ ድካምም ያንን ገመድ ከሥጋው ውስጥ አወጡት ቍስሉም እስከሚድን መድኃኒት እያደረጉለት ኃምሳ ቀኖች ያህል ኖረ።
❤ ከዚህም በኋላ አበ ምኔቱ እንዲህ አለው "ልጄ ስምዖን ሆይ እንግዲህስ ወደ ፈለግኸው ቦታ ሒድ" ከዚያም ወጥቶ ሔደ በደረቅ ጕድጓድ ውስጥም ገብቶ ከእባቦችና ከጊንጦች ጋራ ኖረ።
❤ ከዚህም በኋላ "አገልጋዩ ስምዖንን ለምን ሰደድከው አሁንም ፈልገህ መልሰው በፍርድ ቀን እርሱ ከአንተ ይሻላልና" ብሎ ሲገሥጸው አበ ምኔቱ ራእይን አየ። አባ ስምዖንንም ከገዳሙ ስለመውጣቱ ገሠጸው። በነጋም ጊዜ አበ ምኔቱ ራእይን እንዳየ ስለ አባ ስምዖንም እንደገሠጸው ለመነኰሳቱ ነገራቸው ወንድሞችም ደንግጠው እጅግ አዘኑ "እስከምታገኙትም ሔዳችሁ በቦታው ሁሉ ፈልጉት" አላቸው ሔደውም ፈለጉት ግን አላገኙትም። ከዚህም በኋላ መብራትን አብርተው ወደ ጕድጓድ ውስጥ ገቡ ያለ መብልና መጠጥም ከእባቦችና ከጊንጦች ጋራ ተቀምጦ አዩት።
❤ ገመድም አውረዱለትና ከዚያ አወጡት በፊቱም ሰግደው "በአንተ ላይ ያደረግነውን በደላችንን ይቅር በለን" አሉት "እኔንም ስለ አሳዘንኳችሁ ይቅር በሉኝ" አላቸው። ከዚህም በኋላ ወደ ገዳማቸው ወሰዱት በብዙ ገድልም ተጠምዶ ሲያገለግል ኖረ።
❤ ከዚህም በኋላ ከዚያ ገዳም በሥውር ወጥቶ ወደ አንዲት ዐለት ቋጥኝ ደረሰ። በእርስዋም ላይ ሳያረፍና ሳይተኛ ስልሳ ቀን ቆመ። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ስለ ብዙ ሰዎች ድኅነት እግዚአብሔር እንደ ጠራው ነገረው። ከዚያም ሔዶ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ የሚሆን የድንጋይ ምሰሶ አገኘ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ በሽተኞችንም እየፈወሰ ወደርሱ የሚመጡትንም እያስተማረ ዐሥራ ሁለት ዓመት በድንጋይ ምሰሶው ላይ ቆመ።
❤ አባቱም ፍልጎት ነበር ግን ሳያየው ሞተ እናቱ ግን ወሬውን ሰምታ ከብዙ ዘመናት በኋላ ወደርሱ መጣች በድንጋይ ምሰሶውም ላይ ቁሞ አገኘችው አይታውም አለቀሰች ከድንጋይ ምሰሶውም በታች ተኛች። ቅዱስ ስምዖንም ጌታችን በጎ ነገርን ያደርግላት ዘንድ ስለርሷ ለመነ ያን ጊዜም እንደተኛች ዐረፈችና ከደንጊያው ምሰሶ በታች ቀበሩዋት።
❤ ሰይጣንም በእርሱ ላይ ቀንቶ እግሩን መታው ከእግሩ ትል እየወደቀ በአንዲት እግሩ ብዙ ዓመታት ኖረ። ከዚህም በኋላ የሽፍቶች አለቃ ወደርሱ መጥቶ ንስሐ ገባ ጥቂት ቀኖችም ኑሮ ዐረፈ በጸሎቱም ሕይወትን ወረሰ። ወደርሱ ስለሚመጡ ብዙ ሕዝቦችም የውኃ ጥማት እንዳያስጨንቃቸው ወደ እግዚአብሔር ለምኖ ከድንጋይ ምሰሶው በታች ውኃን አፈለቀላቸው።
❤ ዳግመኛም ወደ ሌላ ምሰሶ ተዛወረ በእርሱም ላይ እየተጋደለ ሠላሳ ዓመት ኖረ። ብዙዎች አረማውያንንና ከሀድያንን ካስተማራቸውና ወደ ፈጠራቸው እግዚአብሔር ከመለሳቸው በኋላ ክብር ይግባውና ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔደ በሰላምም ዐርፎ የዘላለም ሕይወትን ወረሰ።
❤ ከዚህም በኋላ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባ ስምዖን እንዳረፈ በሰማ ጊዜ ካህናትን ዲያቆናትንና የአገሩን መኳንንቶች ከእርሱ ጋራ ይዞ የቅዱስ አባ ስምዖን ሥጋው ወዳለበት ደረሰ በታላቅ ክብርም ተሸክመው እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ እስክንድርያ አድርሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት ከሥጋውም ድንቆችና ተአምራቶች ታላቅ ፈውስም ተገለጡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛን በመስተጋድል በአባ ስምዖን ዘአምድ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
+ + +
❤ ቅድስት ሶፍያ ሦስቱ ደናግል ልጆቿ፦ ለዚችም ቅድስት ብዙ ሀብትና ብዙ ጥሪት ነበራት ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ ፍቅር የክርስቶስን መከራ መስቀል አንሥታ ትሸከም ዘንድ ከሦስት ሴቶች ልጆቿ ጋራ ወደ ሮም ከተማ ሔደች።
❤ ንጉሥ እንድርያሰኖስም ክርስቲያን እንደ ሆነች አውቆ ከልጆቹ ጋራ ወደ አደባባይ አስቀረባትና ስለ ሀገርዋና ስለ ስሟ ጠየቃት እርሷም "የሚቀደመው ስሜ ክርስቲያን ነኝ ወላጆቼ ያውጡልኝ ስም ሶፊያ ነው እኔም በኢጣልያ ባለ ብዙ ወገን ነኝ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ፈቃድም ልጆቼን መሥዋዕት አድርጌ ላቀርብ ወደ አገርህ መጣሁ" አለችው። ከዚህም በኋላ የከዳተኛው ንጉሥ ሥቃዩ እንዳያስፈራቸው ልጆቿን አበረታቻቸው።
❤ ምስክርነታቸውንም ፈጽመው ከሞቱ በኋላ ገንዛ ከሮሜ ከተማ ውጭ ቀበረቻቸው። በሦስተኛውም ቀን መታሰቢያቸውን ታደርግ ዘንድ ልጆቿ ወደ ተቀበሩበት ከብዙዎች ከከተማው ሴቶች ጋራ ሔደች እንዲህ ብላም ጸለየች "አክሊላትን የተቀዳጃችሁ የምታምሩ ፍጹማት የሆናችሁ ልጆቼ ሆይ እኔንም ከእናንተ ጋራ ውሰዱኝ" ይህንንም እንዳለች ወዲያውኑ ዐረፈች ከልጆቿም ጋር ተቀበረች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ሶፍያና በሦስቱ ደናግል ልጆቿ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
+ + +
❤ "ሰላም ለስምዖን እንተ ለሐቌሁ አድንዖ። በኀብለ በቀልት ይቡስ ዘይገምዶ ወይበልዖ። በእንተ ዝንቱ እምደብር ሶበ አበምኔት አውጽኦ። በቃለ ተግሣጽ እግዚአብሔር አውሥኦ። ለገብርየ ስምዖን እንዘ ይብል አግብኦ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የነሐሴ3።
+ + +
❤ የዕለቱ ምስባክ፦ "ወይሰግዳ ሎቱ አዋልደ ጢሮስ በአምኃ። ወለገጽኪ ይትመሀለሉ ኵሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር። ኵሉ ክብራ ለወለተ ንጉሥ፡ሐሴቦን"። መዝ 44፥12-13። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ተሰ 3፥1-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 3፥10-15 እና የሐዋ ሥራ 14፥20-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 18፥9-18። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።
https://t.me/Eotcw
1 161
ነሐሴ ፪
#ምንባባት
፩ጢሞ ም፪ ቊ፰
፩ጴጥ ም፫ ቊ፩-፯
ግብ ሐዋ ም፲፯ቊ ፲፫-፲፱
#ምስባክ
መዝ ፵፬፥፲፬-፲፮
ወይወስዱ ለንጉሥ ደናግለ ድኅሬሃ።
ወቢጻሂ ይወስዱ ለከ።
ወይወስድዎን በትፍሥሕት ወበሐሤት፡፡
#ትርጉም፦
በኋላዋ ቆነጃጅቱን ለንጉሥ ይወስዳሉ
ባልንጀሮችዋንም ወደአንተ ያቀርባሉ
በደስታና በሐሤት ይወስድዋቸዋል፡፡
#ወንጌል፦
የዮሐንስ ወንጌል ም፰ ቊ፩
#ቅዳሴ፦
ዘእግዝእትነ(የእመቤታችን ቅዳሴ)
1 161
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ ነሐሴ ፪ (2) ቀን።
❤ እንኳን በአባ ዮሐንስ ሐጺር ምክር ለንስሐ በቅታ ከዘማነት ለተመለሰች ለቅድስት አትናስያና ከነገሥታት ወገን ለሆነች ለቅድስት ኢዮጰራቅስያ ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከዲያቆናዊት ኢዮኤልያና ዕረፍት፣ ከሰማዕቱ ደሚናና ሰማዕታት ከሆኑ ወንድሞቹ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
+ + +
❤ ቅድስት አትናስያ፦ የዚችም ቅድስት ወላጆቿ ባለጸጎች ነበሩ እነርሱም በሞቱ ጊዜ ቤቷን ለእንግዳ ማደሪያ ታደርግ ዘንድ በጎ ኃሳብ አሰበች ወደርሷም የሚመጡትን እንግዶች ሁሉ ትቀበላቸው ነበር። በገዳም ለሚኖሩ መነኰሳትም የሚያስፈልጓቸውን ትሰጣቸው ነበር ስለ በጎ ሥራዋም ይወዷት ነበር።
❤ ከዚህም በኋላ ግብራቸው የከፋ ክፉዎች ሰዎች ወደርሷ ተሰብስበው ኃሳቧን ወደ ኃጢአት ሥራ መለሱትና ኃጢአትን አብዝታ ትሠራ ጀመር። በአስቄጥስ ገዳም በሚኖሩ አረጋውያን ቅዱሳን ዘንድም ወሬዋ ተሰማ ስለእርሷም እጅግ አዘኑ አባ ዮሐንስ ሐጺርንም ጠርተው ስለርሷ የሆነውን ነገሩት አስቀድማም ከእነርሱ ጋራ በጎ ስለ ሠራች ወደ እርስዋ ይሔድ ዘንድ ነፍስዋንም ለማዳን ይወድ ዘንድ ለመኑት።
❤ እርሱም ትእዛዛቸውን ተቀበለ በጸሎታቸውም እንዲረዱት ለመናቸው ያን ጊዜም አባ ዮሐንስ ሐጺር ተነሥቶ ሔደ አትናስያ ወዳለችበት ቦታ ደረሰ ለበረኛዋም "ለእመቤትሽ ስለእኔ ንገሪ" አላት። በነገረቻትም ጊዜ ለረከሰ ሥራ እንደሚፈልጓት ሰዎች ሁሉ የመጣ መሰላትና አጊጣ በዐልጋዋ ላይ ሁና ጠራችው። ወደርሷም ገባ እርሱም እንዲህ እያለ ይዘምር ነበር "በሞት ጥላ ውስጥ ብሔድም እንኳ ክፉን አልፈራውም አንተ ከእኔ ጋራ ነህና"። ከእርሷ ጋራም አስቀመጠችው ያን ጊዜም ራሱን ዘንበል አድርጎ አለቀሰ "ለምን ታለቅሳለህ" አለችው እርሱም "ሰይጣናትን በላይሽ ሲጫወቱ አየኋቸው ክብር ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ለምን አሳዘንሺው የቀድሞ በጎ ሥራሽን ትተሽ ወደ ጥፋት ሥራ ተመልሰሻልና" አላት።
❤ ቃሉንም ሰምታ ደነገጠችና ተንቀጠቀጠች "ምን ይሻለኛል" አለችው "ንስሐ ግቢ" አላት እርሷም "እግዚአብሔር ይቀበለኛልን" አለችው እርሱም "አዎን" አላት እርሷም "ወደምትሔድበት ከአንተ ጋራ ውሰደኝ" አለችው እርሱም "ነዪ ተከተይኝ" አላት። ያን ጊዜም ፈጥና ተነሥታ በኋላው ተከተለችው ከገንዘቧም ምንም ምን አልያዘችም። በመሸም ጊዜ ለማደር ወደ ጫካ ውስጥ ገቡ በዚያም ለእርስዋ ቦታ አዘጋጅቶ "እስኪነጋ በዚህ አረፍ ብለሽ ተኚ እኔም ወደዚያ እሆናለሁ" አላት። ይህንንም ብሎ ከእርሷ ጥቂት ተገልሎ እየጸለየ ብቻውን ተቀመጠ።
❤ በሌሊቱ እኩሌታም ሊጸልይ ተነሣ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ አየ የእግዚአብሔርም መላእክት የከበረች ነፍስን ተሸክመው ሲወጡ አይቶ አደነቀ። በነጋም ጊዜ ወደ ርሷ ሔደ ሙታም አገኛት እጅግም አዘነ ስለ ርሷም ያስረዳው ዘንድ እየሰገደ ወደ እግዚአብሔር ለመነ።
❤ ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ከቤቷ በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር ንስሓዋን ተቀብሎ ኃጢአትሽ ተሠረየልሽ ብሎአታል። ከዚህም በኋላ ሒዶ ለአረጋውያን የሆነውን ሁሉ ነገራቸው እነርሱም እርሱ እንዳያት ማየታቸውን ነገሩት የኃጢአተኛን ወደ ንስሐ መመለሱን እንጂ ሞቱን የማይሻ እግዚአብሔርን አመሰገኑት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አትናስያ በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
+ + +
❤ ድንግሊቱ ቅድስት ኢዮጰራቅስያ፦ የእርስዋም የአባቷ ስም ኢጣጎኖስ ነው የንጉሥም አማካሪ ነበር የእናቷም ስም ኢዮጰራቅስያ ነው እነርሱም ደጎች ነበሩ ጾምና ጸሎትንም ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡ ነበሩ። ይችንም ቅድስት በወለዷት ጊዜ በእናቷ ስም ኢዮጰራቅስያ ብለዉ ጠሩዋት።
❤ ከጥቂት ጊዜ በኋላም አባቷ ዐረፈ ዕድሜዋም ስድስት ዓመት በሆነ ጊዜ እናቷ ወደ ደናግል ገዳም ከእርሷ ጋር ወሰደቻት ይህችም ቅድስት ደናግሉ ሲያገለግሉ አይታ "ስለ ምን እንዲህ ደክማችሁ ትሠራላችሁ" አለቻቸው እነርሱም ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ ነው ብለው መለሱላት ወደ ዲያቆናዊትም ሒዳ ያመነኲሷት ዘንድ ለመነች እነርሱም ለእናቷ ነገሩዋት እናቷም ለዲያቆናዊተዋ ሰጠቻት በደናግሉም ሁሉ ዘንድ አደራ ሰጠቻት ከጥቂትም ቀኖች በኋላ እናቷ ዐረፈችና ቀበሩዋት።
❤ ከዚህም በኋላ ቅድስት ኢዮጰራቅስያ የምንኲስና ልብስን ለበሰች በጾም በጸሎትና በሰጊድ ተጋድሎ ጀመረች በየሰባት ቀንም ትጾም ነበር ሰይጣንም በእርሷ ላይ ቀንቶ ሊፈትናት ጀመረ ወደ ውኃ ውስጥ እርስዋን የሚጥልበት ጊዜ ነበር እንጨትም ስትፈልጥ በምሳር የሚአቊስልበት ጊዜ ነበር። የፈላ ውኃም በላይዋ የሚያፈሰበት ጊዜ ነበር ነገር ግን ምንም ምን የጐዳት የለም።
❤ ለደነግሎችም ስታገለግል ብዙ ዘመናት ኖረች ምንም አትታክትም ነበር በምድርም ላይ አትተኛም መላዋን ሌሊት ቁማ በጸሎት ታድር ነበር እንጂ ከገድሏ ጽናትም የተነሣ ደናግሉ እስከሚያደንቁ ድረስ አርባ ቀን ቁማ ትፈጽም ነበር።
❤ ከዚህም በኋላ ጌታችን በሽተኞችን በማዳን አጋንንትን በማስወጣት የዕውሮችን ዐይን በመግለጥ የአንካሶችንም እግር በማስተካከል ድንቆችንና ተአምራቶችን በእጆቿ ገለጠ። ዲያቆናዊት ኢዮኤልያም ለኢዮጰራቅስያ መጸሐፍትንና የምንኵስናንም ሥርዓት አስተማረቻት በሥራም ሁሉ ትሳተፋት ነበር እጅግም ይፋቀሩ ነበር እርሷም ሰማያዊ ሙሽራ ወደአለበት የመንግሥት አዳራሽ የማያልቅ ተድላ ደስታም ወደአለበት ኢዮጵራቅስያን ሲያወጧት ራእይን አየች።
❤ በነቃችም ጊዜ ለደናግል ነገረቻቸው ወደርሷ ሲሔዱም በትኩሳት በሽታ ታማ አገኟት ስለእነርሱም እንድትጸልይ ለመኑዋት እርሷም ደግሞ በጸሎታቸው እንዲአስቧት ለመነቻቸው ያን ጊዜም ጸሎት አድርጋ መረቀቻቸውና ነሐሴ 2 ቀን በሰላም ዐረፈች በእናቷም መቃብር ውስጥ ቀበሩዋት።
❤ ወዳጅዋ ኢዮኤልያም ወደ መቃብርዋ ሒዳ ጸለየችና በሦስተኛው ቀን ዐረፈች ከእርሷም ጋር ተቀበረች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ደናግል በቅዱሳት ኢዮጰራቅስያና ኢዮኤልያ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 2 ስንክሳር።
+ + +
❤ "ሰላም ለትናስያ ለተሊወ ክርስቶስ ፌማ። በምክረ ዮሐንስ ሐጺር ወአኮ ከማ። ሶበ መነነት ዓለም ወገደፈት ትርሲተ ዘማ። ነፍሳ ወሰዱ መላእክት እንዘ የኀልዩ በዜማ በዕለተ አዕረፈት ዮም እምሕማም ወፃማ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የነሐሴ 2።
❤ በየቀኑ ይህን ቴሌግራም ላይ ማግት ከፈለጉ ከታች ያለውን ሊኩን ይጫኑት።
https://t.me/Eotcw
