ar
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

الذهاب إلى القناة على Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

إظهار المزيد
613
المشتركون
+124 ساعات
-17 أيام
-1030 أيام
أرشيف المشاركات
                          ✝ ✝ ✝ ❤ #ለእግዚአብሔር_ልጅ_ምሳሌው_የሆነ #ካህኑ_ቅዱስ_መልከጼዴቅ፦ መልከጼዴቅም ዐሥራ አምስት ዓመት በሆነው ጊዜ ከአዳም ሥጋ ጋር እንዲልከውና በምድር መካከል እንዲያኖረው እግዚአብሔር ኖኅን አዘዘው እርሷም ቀራንዮ ናት። የዓለም መድኃኒት ክርስቶስም መጥቶ በዚያ እንደሚሠዋ አዳምንም ከልጆቹ ሁሉ ጋር እንደሚያድነው አመለከተው። ❤ ከዚህም በኋላ በአባቱ በኖኅ ትእዛዝ ሤም መልከጼዴቅን በሥውር ወሰደው የእግዚብሔርም መልአክ እየመራቸው ሔደው ወደ ቀራንዮ ተራራም አደረሳቸው መልከጼዴቅም ክህነትን ተሾመ። ዐሥራ ሁለት ደንጊያዎችንም ወስዶ መሠዊያ ሠራ ከሰማይ የወረደለትንም ኅብስትና ወይን መሠዊያ በሠራቸው ደንጊያዎች ላይ መሥዋዕትን አሳረገ። ❤ ምግቡንም መላእክት ያመጡለታል ልብሱም ዳባ ነው በአባታችን አዳም ሥጋ ዘንድ ሲያገለግል ኖረ። አብርሃምም ከጦርነት ነገሥታትን ድል አድርጎ በተመለሰ ጊዜ ኅብስትንና ወይንን አቀረበለት አብርሃምም ከገንዘቡ ሁሉ ከዐሥር አንድ ሰጠው እርሱ ካህንም ንጉሥም ሁኖ ተሹሟልና። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በካህኑ ቅዱስ መልከጼዴቅ በአማላጅነቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_ሰራጵዮን፦ ይህም ቅዱስ ሰንዱን ከሚባል አገር ነው። ከታናሽነቱ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ትርጓሜያቸውንም ተማረ የዚህንም ዓለም ገንዘብ ሁሉ ትቶ ወደ አረሚ አገር ሔደ ራሱንም በሃያ ብር ሸጦ ማገልገል ጀመረ የሽያጩንም ዋጋ ጠበቀው። እንጀራ ሳይበላ ውኃ ሳይጠጣ ከስሕተታቸው ይመልሳቸው ዘንድ ሁል ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር። ❤ ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት በሆነ በክርስቶስ አሳመናቸው ሕግንና ሥርዓትንም ሁሉ አስተማራቸው ከዚህም በኋላ ስለርሳቸው ራሱን ባሪያ አድርጎ እንደሸጠ እንጂ እርሱ ባሪያ እንዳልሆነ ነገራቸው ሽያጩንም ለድኆች እንዲሰጡት ሰጣቸው። ❤ ከዚህም በኋላ መንካያውያን ወደሚባሉ ሕዝቦች ሒዶ ለነርሱም ራሱን ሸጠ የክብር ባለቤት ወደሆነ ክርስቶስ እምነት እስከመለሳቸው ድረስ ተገዛላቸው። ከዚህም በኋላ ደግሞ ወደ ሮሜ አገር ሒዶ በሰላም እስከ አረፈ ድረስ በጾምና በጸሎት እየተጋደለ ኖረ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጳጒሜን 3 ስንክሳር።                                                          ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "መሐለ እግዚአብሔር ወኢይኔስሕ። አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከጼዴቅ። እግዚአብሔር በየማንከ"። መዝ109፥4-5። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 17፥20-31።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "እግዚአብሔር ገሃደይ መጽእ። ወአምላክነሂ ኢያረምም። እሳት ይነድድ ቅድሜሁ"። መዝ 49፥2-3። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 7፥1-7፣ ይሁ 1፥11-17 እና የሐዋ ሥራ 5፥16-26። የሚነበው ወንጌል ማቴ 25፥31­46። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ነው። መልካም የመልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል በዓል ለሁላችን ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤                  ❤ #ጳጒሜን ፫ (3) ቀን። ❤ እንኳን #ለሊቀ_መላእክት_ለቅዱስ_ሩፋኤል ለተሾመበት፣ #ቅዱስ_ጦቢትን_ዐይኑን_ለአበራለትና ልጁ #ቅዱስ_ጦብያን_ለረዳበት፣ የራጉኤልን ልጅ #ሣራን_ተቆራኝቷት_የነበረው_አስማንድዮስ_ጋኔን ላወጣላት በዓል (ታሪክ በጽሐፈ ጦብት ላይ ያንብቡ)ና #ለሊቀ_ካህን_ለኢየሱስ_ክርስቶስ ምሳሌ ለሆነ #ለካህኑ_ቅዱስ_መልከፄዴቅ ለመታሰቢያ በዓሉ በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ ሰንዱን ከሚባል አገር #ከቅዱስ_ሰራጵዮን ዕረፍት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                                                                     ✝ ✝ ✝ ❤ #ሊቀ_መላእክት_ቅዱስ_ሩፋኤል፦ እርሱም ከመላእክት አለቆች ሦስተኛ የሆነ ነው። ደግሞም ከእስክንድርያ ውጭ በደሴት የታነፀች ቤተ ክርስቲያኑ በከበረ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን በውስጧ ተአምር የተገለጸባት የከበረችበት ነው። ❤ ይህም እንዲህ ነው ሀብታም ሴት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ መጥታ ሳለ ከእርሷ ጋርም ብዙ ሰው ነበረ። ከባሏም የወረሰችው ብዙ ገንዘብ አላት በሊቀ ጳጳሳቱ ቤት አንጻር ያለውን ኮረብታ አስቆፈረችው በጥቅምት ወር ዐሥራ ስምንት ቀን እንደጻፍን የወርቅ መዝገብ ተገለጠ። በዚያም ወርቅ ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትን አነፀ ከእርሳቸውም አንዲቱ የመላእክት አለቃ በሆነ በከበረ መልአክ ሩፋኤል በስሙ የታነፀች ይህች ናት። ሥራዋንም በፈጸመ ጊዜ እንደዛሬው በዚች ቀን አከበራት። ❤ ብዙ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጸች ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና። የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው። ወደ ክብር ባለቤት እግዚአብሔርም በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮኹ ያን ጊዜ ይህ የከበረ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በጦሩ ወግቶ እንዲህ አለው "እግዚአብሔር አዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጽ ጸጥ ብለህ ቁም"። አንበሪውም ጸጥ ብሎ ቆመ አልታወከም በውስጧም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆነ። ❤ ይቺም ቤተ ክርስቲያን እስላሞች እስከተነሡበት ዘመን ኖረች ከዚህም በኋላ ሁለተኛ ያ አንበሪ ተናወጸ ደሴቲቱም በላይዋ ከሚኖሩ ብዙ ሕዝብ ጋራ ሠጠመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የመልአክ ቅዱስ ሩፋኤል በረከቱ ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ዳግመኛም_የቊስጥንጥንያ_ሊቀ_ጳጳሳት #አባ_ዮሐንስ_ጻድቅ_ለሆነ_ንጉሥ_አኖሬዎስ_ተናገረው፦ እንዲህም አለው "ንጉሥ ሆይ እኛ ወዳንተ ልንመጣ በመርከብ እንደተሳፈርን ዕወቅ በጒዞ ላይ ሳለንም በቀዳሚት ሰንበት ቀን በደሴት ውስጥ ታናሽ ቤተ ክርስቲያን አየን ወደ ወደቡም ደርሰን በዕለተ እሑድ ሥጋውን ደሙን እንቀበል ዘንድ ወደርሷ ሔድን። ❤ ለዚያች ቤተ ክርስቲያንም በጐኗ ታናሽ ገዳም አገኘን በውስጧም ወንድሞች መነኰሳት አሉ በክብር ባለቤት ጌታችንም ፈቃድ ወደ ርሳቸው ደረስን። መነኰሳቱንም "በቀደሙ አባቶች ዘመን የተጻፈ አሮጌ መጽሐፍ በእናንተ ዘንድ እንዳለ እጽናናበት ዘንድ እርሱን ሰጡኝ" አልኳቸው። ❤ እንዲህም ብለው መለሱልኝ "እኛ ትርጓሜያቸውን የማናውቀው መጻሕፍቶች በዕቃ ቤት አሉ"። እኔም "አያቸው ዘንድ ወደዚህ አምጡልኝ" አልኳቸው። በአመጡአቸውም ጊዜ መረመርኳቸው ጌታችንም በደቀ መዛሙርቱ ፊት ያደረጋቸውን ኃይሎችና ድንቆች ተአምራቶችን ስለ ሰማይና ምድርም ጥንተ ተፈጥሮ አገኘሁ። ❤ ሁለተኛም ስመረምር ስለ ሰባቱ ሊቃነ መላእክት ሹመትና መዐርግ አባቶቻችን ንጹሐን ሐዋርያት የጻፉትን አገኘሁ ይኸውም ጌታችን በደብረ ዘይት ከእሳቸው ጋራ እያለ የመለኮቱን ምሥጢር በገለጠላቸው ጊዜ። ሐዋርያትም እንዲህ ብለው እንደለመኑት "ጌታችንና ፈጣሪያችን ሆይ የከበረ የሩፋኤልን ክብሩን ታስረዳን ዘንድ እንለምንሃለን በየትኛው ዕለት በየትኛው ወር ሾምከው"። ከባልንጀሮቹ የመላእክት አለቆችም ትክክል ነውን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ዘንድ በዓለም ውስጥ ስለርሱ እንድናስተምር እርሱም በመከራቸው ጊዜ ይረዳቸው ዘንድ በአማላጅነቱም በአንተ ዘንድ ይቅርታን ያገኙ ዘንድ። ❤ ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዘዘና ከሦስተኛው ሰማይ ሦስቱ የመላእክት አለቆች ሚካኤል፣ ገብርኤልና ሩፋኤል መጡ በታላቅ ደስታም ለክብር ባለቤት ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰገዱ። ጌታችንም ሩፋኤልን እንዲህ አለው "የክብርህን ገናናነት የባልንጀሮችህንም ልዕልናቸውን እንዲያውቁ ለሐዋርያት ንገራቸው"። ያን ጊዜም ለጌታችን ሰገደ ይነግራቸውም ዘንድ ጀመረ እንዲህም አላቸው "ደገኛው የመላእክት አለቃ ሚካኤል ለሁሉም መላእክት አለቃቸው ነው ስሙም ይቅር ባይ ይባላል"። ❤ "ሁለተኛም የመላእክት አለቃ ገብርኤል የስሙ ትርጓሜ አገልጋይም ጌታም የሆነ የዓለሙ ሁሉ እመቤት የሆነች አምላክን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያምን ያበሠራት ነው"። "የእኔም ስሜ ሩፋኤል ነው ይህም ደስ የሚያሰኝ ቸር መሐሪ ቅን የዋህ ማለት ነው እኔም ኃጢአተኞችን በእግዚአብሔር ዘንድ አልከሳቸውም ከኃጢአታቸው በንስሓ እስኪመለሱ ስለ ቅንነቴ በእነርሱ ላይ እታገሣለሁ እንጂ። በሃያ ሦስቱ የመላእክት ነገድ ሠራዊት ላይ እግዚአብሔር የሾመኝ እኔ ሩፋኤል ነኝ እግዚአብሔር አብን ይቅር ባይ ልጁን አጽናኝና አዳኝ የሆነ መንፈስ ቅዱስን እናመሰግነው ዘንድ። ❤ በደብረ ጽዮን በሚደረገው የሺህ ዓመት ተድላ ደስታ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክብር ጽዋን በሚሰጣቸው ጊዜ ለቅዱሳኖቹ በጎ ነገርን እንድሰጣቸው እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ። ደግሞም በዚች ቀን ከዕፀ ሕይወት ዐጽቅ ወስጄ ለተመረጡ ክርስቲያኖች በእጄ እንድሰጣቸው እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ። የሰማያት መዛግብትም ከእጄ በታች ተጠብቀው የሚኖሩ እኔ ሩፋኤል ነኝ። እኔም እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ እከፍታቸዋለሁ እዘጋቸዋለሁም። ❤ በምድር ሰው ለባልንጀራው ስለ ስሜ በጎ ነገር ቢያደርግ እኔ በመከራው በችግሩ ረዳዋለሁ ወይም የሹመቴን ነገር የሚጽፍ ወይም ከቅዱሳን ጋራ ስሜን የሚያስብ ወይም በስሜ ለቊርባን የሚሆነውን የሚሰጥ ወይም በበዓሌ ቀን ምጽዋትን የሚሰጥ ይኸውም እግዚአብሔር በሊቃነ መላእክት ክብር የሾመኝና ያከበረኝ ጳጕሚን ሦስት ቀን ነው። ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እስከማስገባው በብርሃን ሠረገላ እኔ እሸከመዋለሁ በምድር ላይ ከቶ እንደርሱ ያለ የማይገኝ መዐዛው እጅግ ጣፋጭ በሆነ ሽቱ ነፍሶቻቸው እርሱን በማሽተት ደስ እንዲላቸው አደርጋለሁ። ❤ ሐዋርያት ሆይ በእግዚአብሔር ፊት እስከምትቆሙ እጠብቃችሁ ዘንድ ከእኔ ርዳታን ሹ። የዚህ የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሩፋኤል ተአምራቶቹ ብዙ ናቸው ስለእኛ ይማልድ ዘንድ የበዓሉን መታሰቢያ ልናደርግ ይገባናል። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል አማላጅነት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                         

🌿🌿🌿🌿  የዕለቱን ወንጌል እናንብብ! 🌿🌿🌿🌿          ዕለተ ሰኑይ! ጷጉሜን 2 ቀን 2018 ዓ.ም          የሉቃስ ወንጌል ም 10 ቁ 1 - 12 —————————————————————————— ¹ ከዚህም በኋላ ጌታ ሌሎቹን ሰብዓ ሾመ፥ ሁለት ሁለትም አድርጎ እርሱ ሊሄድበት ወዳለው ከተማና ስፍራ ሁሉ በፊቱ ላካቸው። ² አላቸውም፦ መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት። ³ ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ። ⁴ ኮረጆም ከረጢትም ጫማም አትያዙ፤ በመንገድም ለማንም እጅ አትንሡ። ⁵ ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ፦ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ። ⁶ በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል። ⁷ በዚያም ቤት ከእነርሱ ዘንድ ካለው እየበላችሁና እየጠጣችሁ ተቀመጡ፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና። ከቤት ወደ ቤት አትተላለፉ። ⁸ ወደምትገቡባትም ከተማ ሁሉ ቢቀበሉአችሁ፥ ያቀረቡላችሁን ብሉ፤ ⁹ በእርስዋም ያሉትን ድውዮችን ፈውሱና፦ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀረበች በሉአቸው። ¹⁰ ነገር ግን ወደምትገቡባት ከተማ ሁሉ ባይቀበሉአችሁ፥ ወደ አደባባይዋ ወጥታችሁ፦ ¹¹ ከከተማችሁ የተጣበቀብንን ትቢያ እንኳን እናራግፍላችኋለን፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ግን ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ይህን እወቁ በሉ።

❤ "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤                  ❤ #ጳጒሜን ፪ (2) ቀን። ❤ እንኳን #ከሰባ_ሁለቱ_አርድእት አንዱ ለሆነው ሐዋርያው #ቅዱስ_ጳውሎስ_መልእክት_ለጻፈለት ለከበረ #ለሐዋርያው_ለቅዱስ_ቲቶ ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #ሐዋርያው_ቅዱስ_ቲቶ፦ የዚህም ቅዱስ ትውልዱ ቀርጤስ ከሚባል አገር ነው። እርሱም ለዮናናውያን ወገን ለሆነ ለአገረ ገዥው እኅት ልጅዋ ነው። ከታናሽነቱም የዮናናውያንን ትምህርትና ፍልስፍና ተምሮ እጅግ አዋቂ ሆነ በጠባዩም ቅን ሥራው ያማረ ለድኆችና ለችግረኞች መራራት የሚወድ ነው። ከሌሊቶችም በአንዲቱ "ቲቶ ሆይ ስለ ነፍስህ ድህነት ተጋደል ይህ ዓለም አይጠቅምህምና" የሚለውን በሕልሙ አየ። ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ደነገጠ ምን እንደሚሠራም አላወቀም። ❤ ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት በተሰማ ጊዜ ብዙዎች ሰዎችም ተአምራቱን እርስበርሳቸው ተነጋገሩ የአክራጥስ መኰንንም ሰምቶ አደነቀ ዕውነት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ወይም የሥራይ እንደሆነ ሊያውቅ ሽቶ የሚልከው ብልህ ሰው ፈለገ የእኅቱንም ልጅ ቲቶንን መረጠው ከእርሱ የሚሻል የለምና። ሲልከውም ታላቅና ጥልቅ የሆነ ምርመራ እንዲመረምር አዘዘው። ❤ ቲቶም ከይሁዳ ምድር በደረሰ ጊዜ የመድኃኒታችንን ድንቆች የሆኑ ተአምራቶቹን አየ ሕይወትነት ያላቸው ትምህርቶቹንም ሰማ። ከዮናናውያንም በትምህርታቸውና በሥራቸው መካከል ታላቅ የሆነ መራራቅን አግኝቶ የዮናናውያን ሃይማኖታቸው የቀናች እንዳልሆነች ለይቶ ዐወቀ። ❤ ከዚህም በኋላ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ አመነ፤ ደቀ መዝሙሩም ሁኖ ተከተለው። ወደ እናቱ ወንድም ወደ አገረ ገዥውም መልእክትን ላከ የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምረውና የሚሠራው ዕውነት እንደሆነ ነገረው። ❤ ጌታችንም ከሰባ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ውስጥ የተቆጠረ አደረገው ከዕርገቱም በኋላ ከሐዋርያት ጋር የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ተቀብሎ ከእሳቸው ጋር በሀገሮች ሁሉ ዙሮ አስተማረ። ጌታችንም ጳውሎስን ጠርቶ ሐዋርያው በአደረገው ጊዜ ያን ጊዜ ሐዋርያ ጳውሎስን ተከተለው በብዙ አገሮችም ወንጌልን ሰበከ። የከበረ ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜ ከተማ ምስክር ሆኖ ከሞተ በኋላ ቅዱስ ቲቶ ወደ ሀገረ አክራጥስ ተመለሰ ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው በዙሪያቸው ላሉ አገሮችም እንዲሁ አደረገ። ❤ ከዚህም በኋላ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ፈጽሞ ወደ ወደደው እግዚአብሔር ጳጒሜን 2 ቀን ሔደ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ቅዱስ ቲቶ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር። ምክር ሠናይት ለኵሉ ዘይገብራ። ወስብሐቲሁኒ ይነብር ለዓለም"። መዝ 110፥10። የሚነበቡት መልዕክታት ቲቶ 1፥1-11፣ 2ኛ ጴጥ 3፥7-14 እና የሐዋ ሥራ 4፥31-36። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 10፥1-12። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱሳን ሐዋርያት ቅዳሴ ነው። መልካም የሐዋርያው የቅዱስ ቲቶ የዕረፍት በዓልና የጾም፣ የጸሎትና የምሕላ ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።

🌿🌿🌿🌿  የዕለቱን ወንጌል እናንብብ! 🌿🌿🌿🌿          ዕለተ ሰንበተ ክርስቲያን! ጳጉሜን 1 ቀን  2018 ዓ.ም          የሉቃስ ወንጌል ም 17 ቁ 11 - ፍጻሜው —————————————————————————— ¹¹ ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ። ¹² ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት አሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤ ¹³ እነርሱም እየጮኹ፦ ኢየሱስ ሆይ፥ አቤቱ፥ ማረን አሉ። ¹⁴ አይቶም፦ ሂዱ፥ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው። ¹⁵ እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፥ ¹⁶ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። ¹⁷ ኢየሱስም መልሶ፦ አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ¹⁸ ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ። ¹⁹ እርሱንም፦ ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ²⁰ ፈሪሳውያንም፦ የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤ ²¹ ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም፦ እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው። ²² ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ፦ ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ልታዩ የምትመኙበት ወራት ይመጣል አታዩትምም። ²³ እነርሱም፦ እነሆ በዚህ፥ ወይም፦ እነሆ በዚያ ይሉአችኋል፤ አትሂዱ አትከተሉአቸውም። ²⁴ መብረቅ በርቆ ከሰማይ በታች ካለ ከአንድ አገር ከሰማይ በታች ወዳለው ወደ ሌላ አገር እንደሚያበራ፥ የሰው ልጅ በቀኑ እንዲህ ይሆናል። ²⁵ አስቀድሞ ግን ብዙ መከራ እንዲቀበል ከዚህም ትውልድ እንዲጣል ይገባዋል። ²⁶ በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመን ደግሞ እንዲሁ ይሆናል። ²⁷ ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር፥ የጥፋት ውኃም መጣ ሁሉንም አጠፋ። ²⁸ እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደ ሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ ²⁹ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ። ³⁰ የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል። ³¹ በዚያም ቀን በሰገነት ያለ በቤቱ ያለውን ዕቃ ሊወስድ አይውረድ፥ እንዲሁም በእርሻ ያለ ወደ ኋላው አይመለስ። ³² የሎጥን ሚስት አስቡአት። ³³ ነፍሱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም የሚያጠፋ ሁሉ በሕይወት ይጠብቃታል። ³⁴ እላችኋለሁ፥ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል። ³⁵ ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች ሁለተኛይቱም ትቀራለች። ³⁶ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል። ³⁷ መልሰውም፦ ጌታ ሆይ፥ ወዴት ነው? አሉት። እርሱም፦ ሥጋ ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ አላቸው።

❤ "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤ ❤ እንኳን #የጌታችን_የአምላካች_የመድኃኒት #የኢየሱስ_ክርስቶስ_ዳግም_ምጽአት_ስለ_ዓለም_መጨረሻ፣ #ስለ_ምሥጢረ_ትንሣኤ ለሚነገርበት ለዓመቱ የመጨረሻ #ዕለተ_ሰንበት (እሑድ) እግዚአብሔር አምላክ በሰላም በጤና አደረሰን።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #በዚህ_ሳምንት_መዝሙር፦ ሃሌ ሉያ በ፪ "ከመ እንተ መብረቅ ዘይወጽእ እምጽባሕ ወያስተርኢ እስከ ዓረብ ከማሁ #ምጽአቱ_ለወልደ_እግዚአብሔር ምስለ ኃይል ሰማያት በንጥረ መባርቅት (ከማሁ) ምስለ አዕላፍ መላእክት ወኵሎሙ ሊቃነ መላክት (ከማሁ) አክሊለ አክሊላት ዲበ ርእሶሙ ለካህናት"። ትርጉም፦ መብረቅ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እንዲታይ ከመላእክት አለቆች ሁሉ ጋር ከሰማያት ኃይል ጋር በመብረቆች ብልጭታ በካህናት ራስ ላይ አክሊልን የሚቀዳጅ #የወልደ_እጓለ_እመሕያው_የክርስቶስ ምጽአት እንዚሁ ነው። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በድጓው_ላይ።                            ✝ ✝ ✝ ❤  #የኢትዮጵያ_ኦርቶዶክስ_ተዋሕዶ_ቤተ_ክርስቲያን #ስለ_ዳግም_ ምጽአትና_ስለ_ዓለም_መጨረሻ፣ ስለ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንም ሁልጊዜ የምታስተምር ቢሆንም በተለይ በዐቢይ ጾም ውስጥ "ደብረ ዘይት" በሚለው ዕለት ሰንበትና በዓመቱ መጨረሻም በወርኃ ጳጒሜን ስለ ዳግም ምጽአትና ስለ ዓለም ፍጻሜ ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ነገረ ምጽአቱንና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን የሚመለከቱ ጥቅሶችን እያነበበችና ምዕመናንን እያስጠነቀቀች በየጊዜም ትኵረት ሰጥታ ታስተምራለች። በእነዚህ ወቅቶች በቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው መዝሙር፣ ቅዳሴና ትምህርቱም ሁሉ ይህንኑ የተመለከተ ነው።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #የዚህ_ሳምንት_የዕለቱ_ምስባክ፦ "እግዚአብሔር ገሃደይ መጽእ። ወአምላክነሂ ኢያረምም። እሳት ይነድድ ቅድሜሁ"። መዝ 49፥2-3። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ ፥1-10፣ 2ኛ ጴጥ 3፥10-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 9፥1-10። የሚነበው ወንጌል ሉቃ 17፥11­-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ነው። መልካም የጾምና የጸሎት ጊዜና የዓመቱ የመጫረሻ ዕለተ ሰንበት ለሁላችንንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤        ❤ #የተባረከ_የጳጒሜን_ወር_ባተ።             ❤ #ጳጒሜን ፩ (1) ቀን። ❤ እንኳን #ለወንጌላዊው_ለቅዱስ_ዮሐንስ ረድእ #ለሐዋርያውና_ለሰማዕቱ_ለከበረ_ቅዱስ_ዑቲኮስ ለዕረፍት በዓል፣ #ለአባ_ሖር_ወንድም ለሰማዕቱ #ለቀሲስ_ቅዱስ_አባ_ብሶይ_ለዕረፍት በዓል አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከከበሩ #ከአባ_ጳኩሚስና_ከአባ_ሰራብዮን ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #በዚች_ቀን_መጥምቀ_መለኮት_ቅዱስ_ዮሐንስ ሄሮድስን የወንድምህን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ማግባት የለብህም ብሎ ይገስጸው ስለነበር በሳምንቱ በልደቱ ቀን መስከረም 2 እስኪገለው በዛሬው ዕለት ወደ እስር ቤት ያስገባበት ነው።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የሐዋርያው_የቅዱስ_ዮሐንስ_ረድእ_ቅዱስ_ዑቲኮስ፦ ይህም ቅዱስ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስን ሲያገለግለውና ሲታዘዘው ኖረ። ከዚያም ከሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ጋራ ሔደ እርሱም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲሰብክ አዘዘው በአረማውያንና በዮናናውያንም መካከል ሰበከ። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ወደማወቅ ብዙዎችን መለሳቸው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው። ❤ የጣዖታት ቤቶችን አፍርሶ አብያተ ክርስቲያናትን ሠራ። ከሀድያንም ብዙ መከራ ደረሰበት መታሠርና ብዙ ቀኖች ግርፋቶችን በመቀበል የእግዚአብሔርም መልአክ ወደ እሥር ቤት ከምግብ ጋር መጥቶ ይመግበዋል። ❤ ከዚህም በኋላ ከእሳት ውስጥ ጣሉት እሳቱም ከቶ አልነካውም ሁለተኛም ለአንበሶች ጣሉት እነርሱም እንደ በጎች ሆኑለት። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ ቊስጥንጥንያ አገር ሔደ ሲሔድም የእግዚአብሔር መልአክ ይመራውና ያጸናናው ነበር ተጋድሎውንም ፈጽሞ በበጎ ሽምግልና ጳጉሜን 1 ቀን ወደ እግዚአብሔር ሔደ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሐዋርያው ቅዱስ ዑቱኮስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                                                   ✝ ✝ ✝ ❤ #የአባ_ሖር_ወንድም_ቀሲስ_ቅዱስ_ብሶይ፦ ይህም ቅዱስ ከአንጾኪያ አገር ክብር ካላቸው ወገኖች ውስጥ ነው ስለ ዕውቀቱና ስለ ሃይማኖቱ ጽናት ቅስና ተሾመ። ❤ ወንድሙ አባ ሖርና እናቱ ወደ ግብጽ አገር ሒደው በሰማዕትነት ከሞቱ በኋላ እርሱም ተነሥቶ ወደ እስክንድርያ ሥጋቸውን ያይ ዘንድ ሔደ። ገንዘቡን ሁሉ ለድኆች ሰጠ ከሦስት እንጀራና ከሚመረጐዛት ከአንዲት የሰኔል በትር በቀር ምንም አልያዘም ነበር። ✝ ወደ እስክንድርያ አገርም በደረሰ ጊዜ የዘመዶቹ በድን ወዳለበት ሰዎች መርተው አደረሱት የእናቱንና የወንድሙንም ሥጋ በአየ ጊዜ ከእርሳቸው ስለ መለየቱ መሪር ልቅሶን አለቀሰ። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ መነኰንኑ ሒዶ በፊቱ ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ። ለመኰንኑም የአባ ሖር ወንድም እንደሆነ ነገሩት መኰንኑም ታላቅ የደንጊያ ምሰሶ በሆዱ ላይ እንዲአቆሙበት አዘዘ ይህንንም በአደረጉበት ጊዜ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጠ። ❤ ከዚህም በኋላ ደግሞ ሥጋውን ከወንድሙና ከእናቱ ሥጋ ደግሞ ቊጥራቸው ሰማንያ ስምንት ከሆነ ከሌሎች ሰማዕታት ሥጋ ጋር በአንድነት ያቃጥሉ ዘንድ መኰንኑ አዘዘ ወደ እሳት በጨመሩአቸውም ጊዜ ከቶ እሳቱ አልነካቸውም። ❤ ምዕመናን ሰዎችም መጥተው የከበሩ የአባ ሖርና የወንድሙ የአባ ብሶይን የእናታቸውንም ሥጋ ወሰዱ። አገርዋ ዲብቅያ የሚባል የቅድስት ዳሞንንም ሥጋ አገሩ በረሞን ከሚባል የቅዱስ ቢማኮስም ሥጋ ጡልያ ከሚባል አገር የመጣ የውርሱኑፋን ሥጋም አብስላሲ ወደሚባል አገር እስከሚያደርሷቸው በመርከብ ጫኗቸው። የስደቱ ወራት እስከሚፈጸም አክብረው ወስደው በመልካም ቦታ አኖሩዋቸው። ❤ ከዚህም በኋላ አብያተ ክርስቲያን ተሠርቶላቸው ሥጋቸውን በውስጣቸው አኖሩ ከእርሳቸውም ተአምራት ተገለጡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆኑ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጳጕሜን 1 ስንክሳር።                               ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለዑቲኮስ_ዘተሰምየ_ሱታፎ። ለወንጌላዊ ዮሐንስ ለንጹሐ መላእክት ዘተዐጽፎ። መኰንን ዕልው አመ ውስተ እሳት ገደፎ። ካዕበኒ እምህየ ለአናብስት አኅለፎ። በአናብስት ስእኑ ይግሥሥዎ ወእሳት ይልክፎ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የጳጒሜን_1።                             

🌿🌿🌿🌿  የዕለቱን ወንጌል እናንብብ! 🌿🌿🌿🌿          ዕለተ ቀዳሚት ሰንበት! ነሐሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም          የሉቃስ ወንጌል ም 24 ቁ 13 - 33 —————————————————————————— ¹³ እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ ¹⁴ ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ¹⁵ ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤ ¹⁶ ነገር ግን እንዳያውቁት ዓይናቸው ተይዞ ነበር። ¹⁷ እርሱም፦ እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ፥ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩአቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው? አላቸው። ¹⁸ ቀለዮጳ የሚባልም አንዱ መልሶ፦ አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? አለው። ¹⁹ እርሱም፦ ይህ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፤ ²⁰ እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። ²¹ እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው። ²² ደግሞም ከእኛ ውስጥ ማልደው ከመቃብሩ ዘንድ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ ²³ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ፦ ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ ደግሞ አየን ሲሉ መጥተው ነበር። ²⁴ ከእኛም ጋር ከነበሩት ወደ መቃብር ሄደው ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፥ እርሱን ግን አላዩትም። ²⁵ እርሱም፦ እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ ²⁶ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው። ²⁷ ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው። ²⁸ ወደሚሄዱበትም መንደር ቀረቡ፥ እርሱም ሩቅ የሚሄድ መሰላቸው። ²⁹ እነርሱ፦ ከእኛ ጋር እደር፥ ማታ ቀርቦአልና ቀኑም ሊመሽ ጀምሮአል ብለው ግድ አሉት፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ። ³⁰ ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጦ ሳለ እንጀራውን አንሥቶ ባረከው፥ ቈርሶም ሰጣቸው፤ ³¹ ዓይናቸውም ተከፈተ፥ አወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። ³² እርስ በርሳቸውም፦ በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን? ተባባሉ።

ተኙ" ያን ጊዜም ወደ መቃብራቸው ተመለሱ። እሊህ ሦስቱ አባቶችም የካህናት አለቆችና እኛ ወደ አለንበት ከቅርጺቱ ሥዕል ጋር መጥተው ወቀሷቸው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነም ነገሩአቸው። ❤ ከዚህም በኋላ ጌታችን አባቶችን "ወደቦታችሁ ሒዱ" አላቸው ወዲያው ተመለሱ ቅርጺቱንም "ወደቦታሽ ተመለሽ" አላት እርሷም ወደ ቀደመው አኗኗርዋ ተመለሰች "ይህንንም አይተው የካህናት አለቆች አላመኑም ሌላም ብዙ አለ ብነግርህ መወሰን አትችልም ነገር ግን ለብልህ ጥቂት ቃል ትበቃዋለች ለሰነፍ ግን ቢነግሩት በቁም ነገር ላይ አይታመንም"። ❤ ከዚህም በኋላ ጌታችን ማነጋገሩን ገታ ራሱንም እንደሚያንቀላፋ አደረገ እንድርያስም አንቀላፋ እንድርያስንና ደቀ መዛሙርቱን እንዲሸከሙአቸውና ሊገቡበት ወደሚሹት አገር በውጭ እንዲአኖሩዋቸው መላእክትን አዘዛቸው። ❤ ከዚህም በኋላ እንድርያስ በነቃ ጊዜ ዐይኖቹን ገለጠ የከተማውንም በር ተመለከተ በየብስም ላይ እንዳለ አውቆ ደነገጠ አደነቀም። ደቀ መዛሙርቱንም አነቃቸውና እንዲህ አላቸው "ጌታችንን በባሕር ላይ ሳለን ያላወቅነው ምን አደረገብን ሲፈትነን መልኩን ለውጦ እንደ ሰው ሁኖ ታይቶናልና"። ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉት "እኛም በጌትነቱ ዙፋን ላይ ሁኖ የመላእክት ሠራዊት ሁሉ በዙሪያው ሁነው ጌታችንን አየነው አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብንም ቅዱሳንን ሁሉ አየናቸው ንጉሥ ዳዊትም በመሰንቆ ይዘምር ነበር። እናንተንም ዐሥራ ሁለት ሐዋርያት በፊቱ ቁማችሁ ዐሥራ ሁለቱንም የመላእክት አለቆች በፊታችሁ ሌሎች መላእክት በኋላችሁ ሁነው አየናችሁ። እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስንም መላእክትን እንዲህ ብሎ ሲያዛቸው ሰማነው የሚሉአችሁን ሁሉ ሐዋርያትን ስሟቸው"። ❤ እንድርያስም በሰማ ጊዜ እጅግ ደስ አለው ይህን ድንቅ ምሥጢር ያዩ ዘንድ ደቀ መዛሙርቱ የሚገባቸው ሆነዋልና። ከዚህም በኋላ እንድርያስ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶ እንዲህ ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ከእኛ ከባሮችህ ሩቅ እንዳልሆንክ አወቅሁ። ነገር ግን በመርከብ ላይ እኔ እንደማስተምረው ሰው መስለኸኝ በድፍረት ተናግሬሃለሁና ጌታዬ ይቅር በለኝ"። ❤ በዚያንም ጊዜ የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእንድርያስ ዳግመኛ ተገለጠለት እንዲህም አለው። "አዎን እኔ ነኝ በሊቀ ሐመር አምሳል በባሕር ውስጥ የተገለጥኩልህና መርከቡን የቀዘፍኩልህ። አትፍራ አትደንግጥ እኔ ከአንተ ጋራ እኖራለሁ ይህንንም ብሎ ወደ ሰማያት በክብር ዐረገ እንድርያስም መንገዱን ሄደ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጌቶቻችን ሐዋርያት በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ❤ #በነሐሴ_ወር_የሚበብ_ንባብ_በእግዚአብሔር ቸርነት ደረሰ ተፈጸመ። ክብር ጌትነት ገንዘቡ ለሆነ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።                                                               ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ። ውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ"። መዝ 18፥3-4። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 10፥1-ፍ.ም።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "መንክር ተላህያ ለባሕር። መንክርሰ እግዚአብሔር በአርያሙ። ስምዐ ዚአከ እሙን፡ፈድፋደ"። መዝ 92፥4-5 ወይም መዝ 100፥6-7። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 11፥32-ፍ.ም፣ ይሁ 1፥17-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 1፥12-15። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 24፥13-33 ወይም ማር 1፥1-9። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱሳን ሐዋርያት ቅዳሴ ነው። መልካም የነቢዩ ቅዱስ ሚልክያስ የዕረፍት በዓልና የሐዋርያው ቅዱስ እንድርያስ የመታሰቢያ ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #ነሐሴ ፴ (30) ቀን። ❤ እንኳን #ከዐሥራ_ሁለቱ_ደቂቀ_ነቢያት አንዱ ለሆነው ለታላቁ ነቢይ #ለቅዱስ_ሚልክያስ_ለዕረፍት በዓል፣ #ጌታችን በባሕር ውስጥ በሊቀ ሐመር አምሳል ለሐዋርያው #ቅዱስ_እንድርያስ_ለተገለጠለትና ድንቅ ተአምር ላደረገበት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ ከሀገረ ፈርማ ኤጲስቆጶስ #ከአባ_ሙሴ_ዕረፍት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #ነቢዩ_ቅዱስ_ሚልክያስ፦ ይህም ነቢይ የእስራኤል ልጆች ከተሰደዱበት ከባቢሎን ሀገር በተመለሱ ጊዜ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፋቸው ገሥጿቸዋል። ❤ ሁለተኛም ነቋር ስለሆነ መሥዋዕት ስለ አሥራትና በኵራት ገሥጿቸዋል። በዚህ ነቢይ አንደበት እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሯልና "ርኅራኄ አድርጋችሁ ምጽዋትን መጽውቱ፣ ዐሥራቴንና በኵራቴንም አስገቡና እስቲ ፈትኑኝ እኔ ከሰማይ ዝናሙን ባላወርድላችሁ በረከትንም አስቲበቃችሁ ባልጨምርላችሁ የምድራችሁንም ፍሬ ነቀዝና መሰክ እንዳይበሉት እከለክላለሁ"። ❤ ዳግመኛም ከክብር ባለቤት መድኃኒታችን ክርስቶስ አስቀድሞ መጥምቁ ዮሐንስ ስለ መምጣቱ ስለ ነቢዩ ኤልያስም ተናገረ። ደግሞ ስለ አይሁድ የሥርዓተ ክህነት ፍጻሜ ተናገረ በአሕዛብም አገር ውስጥ ለእግዚአብሔር የሚቀበላቸውን መሥዋዕት የሚያሳርጉ ዕውነተኞች ንጹሐን ካህናት እንዳሉ ገለጠላቸው። ❤ በበጎ ተጋድሎውም እግዚአብሔርን ከአገለገለ በኋላ ከዚህ ዓለም በመፍለስ በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በነቢዩ ቅዱስ ሚልክያስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                                                               ✝ ✝ ✝ ❤ #ጌታችን በባሕር ውስጥ ለሐዋርያ #ቅዱስ_እንድርያስ_በሊቀ_ሐመር አምሳል ተገልጦ #ድንቅ_ተአምር_እዳደረገለት፦ "እንድርያስም ጌታችንን በመርከብህ አሳፍረን ነገር ግን የምንከፍልህ የመርከብ ዋጋ የለንም" አለው። በሊቀ ሐመር የተመሰለ ጌታችንም "ስለምን የላችሁም" አለው። እንድርያስም "በከረጢታችን ወርቅን፣ ብርን እንዳንይዝ ስለአዘዘን ነው" አለው። ጌታችንም "እንዲህ ከሆነ ወደ መርከቤ ወጥታችሁ ተሳፈሩ" አላቸው ያንጊዜም ወደ መርከብ ወጥተው ተሳፈሩ። ❤ ከዚህም በኋላ ጌታችን እንድርያስንና ደቀ መዛሙርቱን "ከባሕሩ ማዕበል የተነሣ መታገሥ እንድትችሉ ተነሥታችሁ እንጀራ ብሉ" አለ። አንድርያስም አድንቆ እንዲህ አለው "በመንግሥተ ሰማያት የሕይወት እንጀራ እግዚአብሔር ይስጥህ"። ደቀ መዛሙርቱ ግን በባሕር ላይ ጉዞ ስለአልለመዱ ከባሕሩ ማዕበል ፍርሀት የተነሣ መብላት መነጋገርም ተሳናቸው ። ❤ ጌታችንም እንድርያስን "ደቀ መዛሙርትህን ወደ ምድር እንዲወርዱ እዘዛቸው ሲፈሩ አያቸዋለሁና ይህ ካልሆነ እንዳይፈሩ አንተ የኢየሱስ ደቀ መዝሙሩ ከሆንክ ጣዕም ባለው ቃል አስተምራቸው እነሆ ከየብስ ርቀናልና" አለው። ጌታችንም መርከቡን መቅዘፍ ጀመረ እንድርያስም ማስተማርና ማጽናናት ያዘ በልቡም ጸለየ ያን ጊዜም ከባድ እንቅልፍን አንቀላፉ ስለተኙለትም እንድርያስ ደስ አለው። ❤ እንድርያስም ወደ ጌታችን ተመልሶ እንዲህ አለው "ዐሥራ አራት ጊዜ በባሕር ላይ ጒዞ አድርጌአለሁ እንዳንተ የሚቀዝፍ አላገኘሁም"። ጌታም መልሶ እንዲህ አለው "እኛስ በባሕር ላይ ስንጓዝ ሁል ጊዜ እንቸገራለን። ነገር ግን አንተ የክብር ባለቤት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንደሆንክ ባሕር ስለአወቀችህ ማዕበሏን በአንተ ላይ አላነሣችም" እንድርያስም በታላቅ ቃል እንዲህ ብሎ ጮኸ። "የክብር ባለቤት ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግንሃለሁ ከሚያከብርህ ሰው ጋር ተገናኝቼ ተነጋግሬአለሁና"። ❤ ከዚህም በኋላ ጌታችን እንድርያስን እንዲህ አለው "አንተ የክርስቶስ ደቀ መዝሙሩ ነህና ንገረኝ። አይሁድ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ስለምን አላመኑም የሠራውን ብዙ ድንቅ ተአምርን ሰምተናልና" አለው። እንድርያስም እንዲህ አለው "አዎን ወንድሜ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ገልጦልናል አንካሶችንም በትክክል እንዲሔዱ አድርጓልና፣ ደንቆሮዎችንም አሰምቷልና፣ ዲዳዎችንም አናግሮአልና፣ ለምጻሞችንም አንጽቷልና፣ ውኃውንም ወይን አድርጓልና፣ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣን አንሥቶ ያዘ ሕዝቡንም በመስክ ሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ ሣሩም እንጀራ እስቲለብስ ድረስ በልተው ጠገቡ የተረፈውንም በብዙ ቅርጫቶች አነሣን ይህም ሁሉ ሲሆን አላመኑም"። ❤ ጌታ ኢየሱስም እንዲህ አለው "ይህን ያደረገ በግልጥ ነው ወይስ በሥውር"። እንድርያስም እንዲህ አለው "ይህንስ በግልጥ ነው ያደረገ በሥውር ያደረገውም አለ ግን የምትፈትነኝ መሰለኝ" ጌታችንም እንዲህ አለው "ወንድሜ ሆይ ልቤን ደስ ስለሚላት ነውና ንገረኝ"። እንድርያስም እንዲህ አለው "ልጄ ሆይ በጎ ሥራህን ሀሉ እግዚአብሔር ይፈጽምልህ አሁንም ስማ ጌታችን ያደረገውን ተአምር እኛ ዐሥራ ሁለታችን ሐዋርያቶቹ ከእርሱ ጋራ ስንጓዝ ከሊቃነ ካህናትና ከሕዝቡ ብዙዎች አሉ። ወደ ምኵራብም ደረስን ጌታችንም እንዲህ አለ "በሰማይ ባሉ በኪሩቤልና በሱራፌል አምሳል በምድር ላይ ሰው የሠራትን ይቺን የተቀረጸች ሥዕል ታያላችሁን"። ❤ ከዚህም በኋላ ወደሥዕሊቱ ተመልሶ "ብልህ ሰው የተጠበበብሽ የሰማያውያን መልክን ያደረግሽ አንቺን እላለሁ ከቦታሽ ተነቅለሽ ውረጂ የካህናት አለቆችንም ውቀሻቸው እኔም ዕሩቅ ብእሲ ወይም እግዚአብሔር እንደሆንኩ መስክሪ" አላት። ወዲያውኑ ከቦታዋ ተነቅላ ወረደች እንደሰውም በመናገር እንዲህ አለች "እናንተ የደነቆራችሁ አይሁድ የራሳችሁ መደንቆር ያልበቃችሁ ሌሎችንም ለማደንቆር የምትሹ ለድኅነታችሁ ሰው የሆነ እግዚአብሔርን እንዴት ዕሩቅ ብእሲ ትሉታላችሁ አስቀድሞ ሰውን የፈጠረው በንፍሐት ልጅነትንም የሰጠው ይህ ነው። አብርሃምን የተናገረው፣ ይስሐቅንም ከመታረድ ያዳነው፣ ያዕቆብንም ወደ አገሩ ያስገባው ይህ ነው ለሚፈሩት በረከትን የሚሰጥ ለማይታዘዙለት ቅጣትን የሚያዘጋጅ ይህ ነው ። ❤ እውነት እነግራችኋላሁ እናንተ ስለምትክዱት ሕጉንና ሥርዓቱንም ትለውጣላችሁና ስለዚህ እነሆ መስዋዕታችሁ ይሻራል ምኵራቦቻችሁም በዋሕድ ወልደ እግዚአብሔር ስም አብያተ ክርስቲያናት ይሆናሉ"። ይህንንና የሚመስለውን ተናግራ ዝም አለች። እኛም የካህናት አለቆችን መልሰን እንዲህ አልናቸው "እነሆ ቅርጺቱ ሥዕል ተናግራ ወቀሰቻችሁ ታምኑ ዘንድ ይገባችኋል"። የካህናት አለቆችና አይሁድም እንዲህ አሉን "ይህ የሚያናግረው በሥራይ ነው አብርሃምን በወዴት አገኘው ከሞተ ዘመኑ ብዙ ነውና"። ❤ ጌታ ኢየሱስም ወደ ቅርጺቱ መለስ ብሎ እንዲህ አላት "አብርሃምን እንዳነጋገርኩት አላመኑምና ሔደሽ እንዲህ በይው። አስቀድሞ አዳምን የፈጠረው፣ አንተንም ወዳጁ ያደረገህ፣ አንተ ልጆችህ ይስሐቅና ያዕቆብን ይዘህ ተነሥ ከመቃብርም ወጥተህ ወደዚህ ኑ የካህናት አለቆችን ትወቅሱአቸው ዘንድ እኔ የማውቃችሁና የተነጋገርኳችሁ መሆኔን አስረዷቸው"። ቅርጺቱም ሥዕል ይህን ሰምታ እያየናት ሔደች ወደ አብርሃምም መቃብር ደርሳ በውጭ ቁማ ጠራቻቸው። ወዲያውኑ ከሦስቱ አርእስተ አበው ጋር ዐሥራ ሁለቱ ወጡ ከእኛ ውስጥ "ወደ ማን ነው የተላክሽ" አሏት። ቅርጺቱም እንዲህ ብላ መለሰች ወደ "ሦስቱ የአባቶች አለቆች ነው እናንተ ግን እስከ ትንሣኤ ሙታን ድረስ

❤ "በስመ አብ ወወልደ  ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #ነሐሴ ፴ (30) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊቷ_ጻድቅ ጌታችን በዕለተ አርብ የጠጣው መራራ ሐሞት በማሰብ #በቅል_ውስጥ_የሚገኘውን_መራራ_ፍሬ_ከኮሶ ጋር #በአንድነት_ደርጣ (አዋህዳ) ትመመገብ ለነበረች ለታላቋ እናት #ለቅድስት_ዜና_ማርያም_ለዕረፍቷ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #ጻድቋ_ቅድስት_ዜና_ማርያም፦ ከአባቷ ከቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ከእናቷ ከቅድስት አመተ ማርያም በ11 መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት በምድ ነጋሲ በጎጃም ምድር ግንቦት 30 ቀን የተወለደች ሲሆን ለአቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ በንፅህ ድንግልና በምድረ ሂንፍራንስ ጣራ ገዳም አካባቢ በሚገኘው በአቡነ እንድርያስ ዋሻ ለ25 ዓመት በጾም በፀሎት ምንም አይነት የላመ የጣፈጠ እህል ሳትቀምስ በቅል ውስጥ የሚገኘውን መራራ ፍሬ ከኮሶ ጋር በአንድነት ደርጣ (አዋህዳ) በመዘፍዘፍ ከ3 ቀን በኃላ በመመገብ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ አደባባይ ላይ የቀመሰውን መራራ ሐሞትን በማሰብ ሙሉ ሕይወቶን እየተመገበች ታላቅ ተጋድሎዋን ፈፅማለች፡፡ ከዚህ የተነሳ ሸክላ ማርያም ተብላ ትጠራ የነበረችው ቦታ ስያሜ ተቀይሮ ደሪጣ ዜና ማርያም ዋሻ ተብሎ እስከ አሁን ድረስ በስሞ እየተጠራ ይገኛል፡፡ ❤ ከአቡነ እድርያስ ዋሻ በመቀጠል ከአዲስ አበባ ተነስተን ስንጓዝ አዲስ ዘመን ከተማ በስተቀኝ በኩል ተገንጥለን 15 ኪሜ ያክል የጥርጊያ መንገድ እንደተጓዝን  በስሟ የተሰየመውን ደሪጣ ጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም ገዳም ላይ ቀሪ ሕይወቶን ምንም አይነት ዋሻ ባልነበረበት በከፍተኛ ተራራ ላይ እጅግ አስቸጋሪ ቀዝቃዛ አየር ባለበት ብርዱን፣ ፀሐዩን፣ ቁሩን፣ ረኃቡንና ጥሙን በመቋቋም ራቁቶን በመሆን መራራ ምግቦችን አዋህዳ በመመገብ በጾም በፀሎት በመትጋት አስቸጋሪ የሆነውን ተጋድሎዋን በመፈፀም በዚሁ በተቀደሰ ስፍራ ነሐሴ 30 ቀን በታላቅ ክብር አርፋለች፡፡ ❤ በዚህም ወቅት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያምና ከእልፍ አላፋት ቅዱሳ መላዕክት ጋር እንዲሁም ከሐዋርያት ፣ ከሰማዕታት ፣ ከጻድቃን ፣ ከደናግል ጋር በመሆን ከሰማይ በመውረድ በታላቅ ክብር ዕረፍቷን አክብሮላታል ታላቅ ኪዳንም ገብቶላታል፡፡      ❤ በዚሁ በተቀደሰ ስፍራ ላይ ወይንም በአሁኑ ሰዓት መቃብሯ በሚገኝበት ዋሻ ቤተመቅደስ አካባቢ በተጋድሎዋ ጊዜ ራቁቷን በሆነች ሰዓት መላ ገላዋን የሸፈነላት ፀጉር በእየ ዛፎቹ ላይ እስከ አሁን ድረስ አለ፡፡ ይህም የጸጉር አምሳያ ከገዳሙ በመውሰድ ብዙ ሰዎች በቤታቸው በመታጠን ከአስም እንዲሁም ከተለያዩ በሽታዎች እየተፈወሱና እየዳኑ ሲሆን ታላላቅ ታምራትን እያደረገ ይገኛል፡፡ ❤ በዚህ ገዳም ከሌሎች ገዳማት ለየት የሚያደርገው ታሪክ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ በመውረድ ራሱ የባረከው ልዩ ታሪክ ያለው ጠበል የሚገኝ ሲሆን ይህም ጠበል በቦታው ላይ ሆኖ የተጠመቀ ፣ የጠጣ ፣ አልያም በአለበት ቦታ ሆኖ የተጠቀመ እስከ አሁን ድረስ መካን የሆኑ ሰዎች በፍጥነት ልጅ የሚያገኙ ከመሆናቸው ባሻገር ከማንኛውም ከተለያዩ በሽታዎች በመፈወስ  ታላላቅ ታምራትን እየሰራ ይገኛል፡፡ ❤ በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱስ ላሊበላ በጌታችን በአምላካችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ መሰረት ወደዚሁ ታላቅ ስፍራ በመምጣት የጻድቋ ማረፈያ መታሰቢያ ዋሻ ቤተ መቅደስ በመፈልፈል የሰራላት ሲሆን በመቀጠል አፄ ይስሐቅ በ14ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይህን ገዳም በስሟ በመገደም በዚሁ ዋሻ ውስጥም የጻድቋ የቅድስት ዜና ማርያም መቃብሯ እንዲሁም የመታሰቢያዋ ፅላት የሚገኝ ከመሆኑ አንጻር በአካባቢው ያሉት ሕዝበ ክርስትያን ከካህናት ጋር በመሆን ሥርዓተ አምልኮ በመፈፀም እየተገለገሉበት ይገኛሉ፡፡ ❤ ይህ ዋሻም አስቀድሞ ሦስቱ ቅዱሳን ማለትም አቡነ እንድርያስ ዘጣራ ገዳም ፣አቡነ ተክለኃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ፣ ጻድቋ ቅድስት ዜናማርያም ዘደሪጣ ውስጥ ለውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት በፀጋ እግዚአብሔር ይገናኙበት የነበረ ሲሆን በአሁን ሰዓትም እግዚአብሔር የመረጣቸው ቅዱሳን ይመላለሱበታል፡፡ ❤ ለጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም የተሰጠ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር አምላክ መርጦና ፈቅዶ በጻድቋ አማላጅነት ካለበት ስፍራ ተነስቶ የጻድቋ ደጃን የረገጠ ለ3 ግመል ጭነት ጤፍ ወይም የሦስት አህያ ጤፍ ያህል ነፍሳትን እምርልሻለሁ፤ ከሲዖልም እሳት ነፍሳትን አወጣልሻለሁ የሚል ቃል ኪዳን ለጻድቋ ቅድስት ዜና ማርያም ተሰቶታል። ከእናታችን ቅድስት ዜና ማርያም ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቷም ይማረን!። ምንጭ፦ ማኅበረ ቅድስት ዜማ ማርያም ካዘጋጁት በራሪ ወረቀት የተወረደ።

🌿🌿🌿🌿  የዕለቱን ወንጌል እናንብብ! 🌿🌿🌿🌿          ዕለተ አርብ! ነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም          የማቴዎስ ወንጌል ም 5 ቁ 1 - 17 —————————————————————————— ¹ ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ² አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው እንዲህም አለ፦ ³ በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ⁴ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና። ⁵ የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። ⁶ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። ⁷ የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና። ⁸ ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና። ⁹ የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። ¹⁰ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ¹¹ ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ¹² ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና። ¹³ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። ¹⁴ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። ¹⁵ መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። ¹⁶ መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።

                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "እዜም ወእሌቡ ፍኖተ ንጹሐ። ማእዜ ትመጽእ ኀቤየ። ወአሐውር በየዋሃተ ልብየ ማእከለ ቤትየ"። መዝ 100፥1-2። የሚነበቡ መልዕክታት ገላ 3፥15-21፣ 1 ዮሐ 4፥9-18 እና የሐዋ ሥራ 20፥28-31 የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥1-17። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም የአባ ዮሐንስ ሐጺር የፍልሰት ሥጋ በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ነሐሴ ፳፱ (29) ቀን። ❤ እንኳን #ለታላቁ_ለትሑቱና_ለትዕግስተኛው አባት #ለአባ_ዮሐንስ_ሐጺር _የአባ_እንጦንዮስ በሆነ በቁልዝም ገዳም ከዐረፈ በኋላ ወደ #አስቄጥስ_ገዳም #ለሥጋው_ለፈለሰት_በዓልና ለሰማዕቱ ኤጲስቆጶስ #ቅዱስ_አትናቴዎስ ለሁለቱ አገልጋዮች #ቅዱሳን_ሰማዕታት_ገርሲሞስና_ቴዎዶጦስ ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ ለክብር ባለቤት ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታች ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ለተወለደበት #ለልደቱ_ከበዓለ ወልድ ከወራዊ መታሰቢያ በዓል  እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                    ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ዮሐንስ_ሐጺር_የሥጋው_ፍልሰት፦ ይህም የአባ እንጦንዮስ በሆነ በቊልዝም ገዳም ከዐረፈ በኋላ ነው። ለእስክንድርያ አባ ዮሐንስ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት አርባ ስምንተኛ የሆነ ነው። እርሱም ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ የከበሩ መነኰሳትም እንዲህ አሉት "የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ በዚህ በቤተ ክርስቲያኑ ቢሆን እኛም ሥጋው በአለበት ለፈጣሪያችን እግዚአብሔር እንሰግድ ዘንድ እንሻ ነበር"። ❤ ያን ጊዜ የእግዚአብሔር ቸርነት አነሣሣችውና ስሙ ቆዝሞስ ለሚባል ለአንድ አበ ምኔት መልእክትን ጻፈ ከእርሱም ጋር የቊልዝም አገር የሆነ አረጋዊ አለ በደረሱም ጊዜ በዚያን ሰዓት ሥጋውን መውሰድ አልተቻላቸውም። የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ የኬልቄዶንን ጉባኤ በተቀበሉ መለካውያን ዘንድ ይጠበቅ ስለነበረ ነገር ግን ቦታውን አወቁ ተረዱ ወደ ቦታቸውም ተመልሰው ሃይማኖታቸው የቀና ምእመናን ሰዎችን አገኙ እነርሱም በዚያች አገር የሚኖሩ ናቸው ስለርሱ የመጡበትን ነገሩአቸው። ❤ ከጥቂት ቀኖች በኋላም ከታላላቅ ዐረቦች ወገን ለቊልዝም አገር መኰንን ተሾመ እርሱም ለኤጲስቆጶስ አባ ሚካኤል ወዳጁ ነው ሊቀ ጳጳሳት አባ ዮሐንስም ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ ወደ ኤጲስቆጶሱ መልእክትን ጻፈ፤ በመልእክቱም የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ሥጋ ከከሐድያን መለካውያን እጅ እስከ አፈለሱት ድረስ መልእክተኞች አእሩግ መነኰሳትን ምክንያት ፈልጎ እንዲረዳቸው በማሳሰብ አዘዘው። ❤ ኤጲስቆጶሱም በሰማ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለው ሒዶም ወዳጁ ለሆነ ለመኰንኑ ጸሐፊ ነገረው። ጸሐፊውም ለመኰንኑ ነገረው። እነሆ መኰንኑም ከመነኰሳቱ ጋራ ሔደ ጸሐፊውም "መነኰሳቱ ወደዚያ ቦታ እንዲገቡ ምክንያት እንዴት እናገኛለን" አለ ። መኰንኑም "በልብሶቻቸው ላይ የዓረቦችን ልብሶች ያልብሱአቸውና ከእኔ ጋራ ወደዚያ ቦታ ይምጡ" አለ እንዲሁም እንዳላቸው አደረጉ። ❤ ከዚህም በኋላ መኰንኑ ሔደ ከእርሱም ጋራ ብዙ ፈረሰኞች ሰዎች ብዙ ሕዝብም የአስቄጥስ ገዳም የከበሩ አረጋውያን አሉ ወደቊልዝም ገዳምም ደረሱ። መኰንኑም በዚያ የሚኖራውን የመለካውያን ኤጲስቆጶስ እንዲህ ብሎ አዘዘው "ያንተን ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስወጣቸው በዚች ሌሊት እኔ በውስጧ አድራለሁና" ያ መለካዊም መኰንኑ እንዳዘዘው አደረገ። ❤ መነኰሳቱም እንስሶቻቸውን ከከተማ ውጭ አዘጋጅተው በሌሊት ወደዚያ ገብተው የቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ሥጋ ይዘው ወደ ምስር ደረሱ ከዚያም ወደ አስቄጥስ ገዳም ደረሱ የአባ መቃርስ ገዳም መነኰሳትም መስቀሎችን፣ ወንጌሎችን፣ ማዕጠንቶችንና መብራቶችን በመያዝ እየዘመሩና እያመሰገኑ ተቀበሏቸው ወደ አባት መቃርስ ሥጋም አቀረቡትና ከእርሱ ተባረኩ በላዩም ብዙ ሽቱዎችን ነሰነሱ የቊርባን ቅዳሴንም ቀደሱ የከበረ ወንጌልም በሚነበብ ጊዜ ታላቅ ድንቅ ተአምር ተገለጠ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለመናዋ በሰማያዊ ብርሃን በራች። ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ በጎ መዓዛ ሸተተ ታላቅ ደስታም ሆነ በዚያም ቦታ ሰባት ቀን ኖረ። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ ራሱ ቤተ ክርስቲያን ተሸክመው ወሰዱት ዕብራውያንም "በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ" ነው እያሉ መድኃኒታችንን እንደተቀበሉት ልጆቹ መነኰሳት ተቀበሉትና ወደ ቦታው አኖሩት ከእርሱም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሊቀ ጳጳሳት አባ ማርቆስ በወጣ ጊዜ ወደ አባ ዮሐንስ ሐጺር ቤተ ክርስቲያን ገባ። ከእርሱም ጋር ብዙዎች ኤጲስቆጶሳትና የእስክንድርያ አገር ታላላቆች ከግብጽ አገር ሁሉ አሉ። የአባ ዮሐንስ ሐጺር ሥጋ የተጠቀለለበትን ሰሌን ገልጦ ከእርሱ ተባረከ መሪር ልቅሶንም አለቀሰ ያን ጊዜ ሥጋው ሲገለጥ መብረቅና ነጐድጓድ ሆነ። በቤተ ክርስቲያኑም ውስጥ ያሉት ሁሉም ደንግጠው ወደቁ ሊቀ ጳጳሳቱም ሰሌኑን መልሶ በፍጥነት ሥጋውን ጠቀለለ በሽብሸባ እየዘመሩና እያመሰገኑ እንደቀድሞው ሸፈነው። ❤ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ እንዲህ እያሉ ሊያመሰግኑ ጀመሩ "ፈጣን ደመና ሁነህ የመንፈስ ቅዱስን ዝናም የተሸከምክ ሠለስቱ ደቂቅ ወዳሉበት ወደ ባቢሎን የሔድክ በላይህ በአደረ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወደ እስከንድርያ አገር የተመለስክ ሁለተኛም ወደ ቊልዝም የሔድክ የጣዖታትን ቤቶች አፍርሰህ ሃይማኖትን የሰበክ በሽተኞችን የፈወስክ አጋንንትን ያስወጣህ ወደርስትህም የተመለስክ አንተ የበረከት ማደሪያ ነህና"። ❤ የአባ ዮሐንስ ሐጺር የሥጋው ፍልሰት ከንጹሐን ሰማዕታት ዘመን በአምስት መቶ ሃያ ዓመት ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ዮሐንስ ሐጺር ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ሰማዕቱ_ኤጲስቆጶስ_ቅዱስ_አትናቴዎስ ሁለቱ አገልጋዮች #ቅዱሳን_ሰማዕታት_ገርሲሞስና_ቴዎዶጦስ፦ ይህንንም ቅዱስ አትናቴዎስን የእንጦኒቆስን የጭፍራ አለቃውን ልጅ እርሱ እንዳጠመቃት በንጉሥ ዘንድ ወነጀሉትና ንጉሥ አርስያኖስ ያዘው እርሱም ክርስቲያን እንደሆነ ታመነ ብዙ ሥቃይንም አሠቃየው። ❤ በሃይማኖቱም ጸና እንጂ ሃይማኖቱን ባልካደ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ እንዲሁም እሊህን ሁለቱን አገልጋዮች ገርሲሞስንና ቴዎዶጦስን በግርፋትና በስቅላት ከቀጣቸው በኋላ ራሶቻቸውን በሰይፍ አስቆረጠ ሦስቱም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ። ❤ አማንያን ሰዎችም መጡ ለወታደሮችም ገንዘብ ሰጥተው የቅዱሳኑን ሥጋቸውን ወሰዱ በአማሩ ልብሶችም ገንዘው በሣጥን ውስጥ አኖሩአቸው ከሥጋቸውም ታላላቅ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ ኤጲስቆጶስ ቅዱስ አትናቴዎስ ሁለቱ አገልጋዮች ቅዱሳን ሰማዕታት ገርሲሞስና ቴዎዶጦስ ጸሎት ይማረን። በረከታቸውም ትድረሰን ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 29 ስንክሳር።                             ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለልደትከ_ዘተለዓለ_ዓቅሙ። እምልደተ ጻድቃን ድኀርት ወእለ ቀደሙ። በይቡስ ጌጋይ እስመ አባላትየ ሐሙ። ይትከዐው በአሥራውየ ለምሕረትከ ዝናሙ። ወበአምትንትየ ገቦከ ደሙ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የነሐሴ_29።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ምስሌከ ቀዳማዊ በዕለ ኃይል። ወብርሃኖሙ ለቅዱሳን። ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ"። መዝ109፥3።የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 2፥1-8።