ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ
Kanalga Telegram’da o‘tish
ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።
Ko'proq ko'rsatish608
Obunachilar
-124 soatlar
-37 kun
-1130 kun
Postlar arxiv
ሐዋርያው ቅዱስ በርተሎሜዎስ
ሐዋርያው ቅዱስ በርተሎሜዎስ ስሙ በሐዲስ ኪዳን ላይ የተገለጠው በሐዋርያት ዝርዝር ላይ ብቻ ሲሆን ታሪኩ ተጽፎ አይገኝም፡፡ ጌታን ከተከተለ በኋላ የወንጌልን ትምህርት በአረብ አገር፣ በሕንድና በአርመንያና በአካባቢዋ አስተምሯል፡፡ የአርመንን መንበር ያቋቋመው በርተሎሜዎስ ነው፡፡
ይህም ሐዋርያ ሒዶ ያስተምር ዘንድ እልዋህ በሚባል አገር ዕጣው ወጣ ። እርሱም ከጴጥሮስ ጋር በአንድነት ሔደ የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አስተማሩ ልባቸውንም የሚያስደነግጥ ድንቆች ተአምራትን በፊታቸው ከአደረጉ በኋላ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መለሷቸው።
ከዚህም በኋላ ወደ ከተማው ውስጥ ገብቶ ያስተምር ዘንድ ምክንያት አደረገ ቅዱስ ጴጥሮስም እንደ ባሪያ ሸጠው። ባለ ጸጋ ለሆነ መኰንንም በወይን አትክልት ውስጥ የሚያገለግል ሆነ ድንቅ ተአምርን በማድረግ የተቆረጡ የወይን ቅርንጫፎች በሠራተኞች እጅ ላይ ሳሉ አፈሩ። የአገረ ገዥውም ልጅ በሞተ ጊዜ ከሞት አሥነሣው የሀገር ሰዎችም ሁሉ አመኑ እግዚአብሔርንም ወደ ማወቅ ተመለሱ።
ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በርበር ወደሚባል አገር ሔዶ ያስተምር ዘንድ ሐዋርያ በርተሎሜዎስን አዘዘው እንዲረዳውም ሐዋርያ እንድርያስን ከደቀ መዝሙሩ ጋር ላከለት ። የዚያች አገር ሰዎች ግን እጅግ የከፉ ስለሆኑ በፊታቸው ድንቆች ተአምራቶችን እያደረጉላቸው ሐዋርያትን አልተቀበሏቸውም።
ጌታችንም ሰውን ከሚበሉ አገር አንዱን ገጸ ከልብ ይታዘዝላቸው ዘንድ በሚያዙት ሁሉ ትእዛዛቸውን እንዳይተላለፍ አዘዘው።
ሐዋርያትም ወደዚያች አገር ሁለተኛ ይዘውት ገቡ የሀገር ሰዎችም ሐዋርያትን ይበሏቸው ዘንድ ነጣቂዎች የሆኑ አራዊትን አወጡ። ያን ጊዜም ያ ገጸ ከልብ በአራዊቱ ላይ ተነሥቶ እየነጠቀ በላቸው ይህንንም ገጸ ከልብ ከመፍራት የተነሣ ከሰዎች በድንጋጤ የሞቱ ብዙዎች ናቸው።
የሀገር ሰዎች ሁሉም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ከሐዋርያትም እግር በታች ሰገዱ የሚሉአቸውን ሁሉ የሚያደርጉ ታዛዦች ሆኑ። ሐዋርያትም ቤተ ክርስቲያን ሠርተውላቸው ካህናትንም ሹመውላቸው ከእነርሱም ዘንድ ወጥተው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ሔዱ።
ሐዋርያ በርቶሎሜዎስም እግዚአብሔርን የማያውቁ ሰዎች ወደሚኖሩት በባሕር ዳርቻ ወዳሉ አገሮች ሔዶ የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰበከላቸው በፊታቸውም ተአምራትን አደረገ ሁሉም የጌታችን በሆነች በቀናች ሃይማኖት አመኑ።
ሐዋርያ በርቶሎሜዎስም ከዝሙት ርቀው ንጹሐን እንዲሆኑ ሰዎችን የሚያዝዝ ሆነ። ንጉሥ አግሪጳም ስለርሱ በሰማ ጊዜ በከበረ ሐዋርያ በርቶሎሜዎስ ላይ እጅግ ተቆጣ።
መስከረም 1 ቀን አሸዋ በተሞላ ከረጢት ውስጥ ከተውት ከነሕይወቱ ባህር ውስጥ ወረወሩት፡፡ በዚያም ዐረፈ፡፡ በነጋታው ምእመናን ከባህር አውጥተው ቀበሩት፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
+9
✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨✨
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
በትላንትናው ዕለት የፃድቁ የአባታችን የአቡነ ሀብተማርያም በዓለ ዕረፍት በደብራችን ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ አልፏል ለአመቱ በሠላም ያድርሰን እያልን ከሚዲያና ዕቅበተ ዕምነት ክፍል የምስል ማህደር በጥቂቱ ይህን ይመስላል።
ሕዳር 27/፳፯/በዚችም ቀን በንሑር ከሚባል አገር ቅዱስ ጢሞቴዎስ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሁልጊዜ በጾም በጸሎት ተጠምዶ የሚኖር ነው ስሟ ሞራ የምትባል የአጎቱ ልጅ የሆነች በሥራዋ ሁሉ ደስ የምታሰኘው መልካም ሚስትም ነበረችው። እንደዚህም በፍቅርና በስምምነት ሲኖር ከከሀዲ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ዘንድ የጣዖታት ቤቶች ይከፈቱ ዘንድ አብያተ ክርስቲያናት እንዲዘጉ ትእዛዝ ወጣ። ቅዱስ ጢሞቴዎስም ስለ ክርስቶስ ፍቅር ደሙን ያፈስ ዘንድ ይህን ዘመን ይጠብቀው ነበርና እጅግ ደስ አለው ለሚስቱም ሊሠራው ያሰበውን ነገራት እርሷም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን አለች። ከዚህም በኋላ መንገዱን ያቀናለት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ጌታችንም በዚያች ሌሊት በሕልሙ ተገልጾለት ወዳጄ ጢሞቴዎስ ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን እነሆ ከጻድቃኖቼ ቁጥር ውስጥ ቆጥሬሃለሁ አሁንም ተነሣ ሚስትህንም ይዘህ ወደ ብህንሳ ከተማ ሒዳችሁ ጣዖታትን በሚያመልኩ ሁሉ ሕዝብ ፊት በስሜ ታመኑ አለው። በነቃ ጊዜም ለሚስቱ ነገራት እርሷም ይህንኑ የሚመስል ሕልሟን ነገረችው። ከዚህም በኋላ ተነሥተው በአንድነት ሔዱ ያለ ርኅራኄም ገረፏቸው ሚስቱም በዚህ ሥቃይ ምስክርነቷን ፈጸመች። እርሱን ግን ከእሥር ቤት አውጥተው ወደ በንሑር ከተማ ወስደው ቅድስት ራሱን ቆረጡ ያን ጊዜ ንውጽውጽታ ሆነ አየርም መላእክትን ተመላች አማንያን ሰዎችም መጥተው ሥጋውን ወስደው በመልካም አገናነዝ ገንዘው ቀበሩት። የመከራውም ዘመን በአለፈ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ሠሩለት ሰኔ ሃያ ሰባት ቀንም አከበርዋት ሥጋውንም በውስጥዋ አኖሩ። ወስብሐት ለእግዚአብሔር ምንጭ:- መጽሐፈ ስንክሳር
❤ ፍሬምናጦስም ወደ እስክንድሪያ ለመሄድ አስቦ ሳለ እንደተኛ እመቤታችን ድንግል ማርያም ተገልጣለት "ዲቁናና ቅስናን መቀበል ይገባሃል፣ ለጵጵስና ተዘጋጅ፣ እግዚአብሔር ይህችን ከፍ ያለችውን ማዕረግ ሰጥተሃልና የልጄ ወዳጅ ሆይ በጸሎትህና በልመናህ በስብከትህም የኢትዮጵያ ሰዎች ሁሉ ይድናሉ፣ በእጅህ ጥምቀትንና ሥጋ ወደሙን ይቀበላሉ" አለችው፡፡ ጌታችንም እንዲሁ ተገልጦለት "ወደ ሊቀ ጳጳሳት ወደ አትናቴዎስ ሄደህ ከፍ ያችውን ማዕረግ ተቀብለህ የኢትዮጵያን ሰዎች አጥምቅልኝ፣ ነቢዩ ዳዊት ስለ እነርሱ "ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች" ብሎ ተናግሯልና" አለው፡፡ ከዚህም በኋላ አቡነ ሰላማ ቅዱሳኑን ነገሥታት አብርሃንና አጽብሓን አግኝቶ ከእነርሱም ጋር ተማክሮ ወደ እስክንድሪያ ሄዶ በቅዱስ አትናቴዎስ እጅ በአገራችን ላይ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ታኅሳስ 18 ቀን ተሾመ፡፡ ስሙንም ሰላማ ከሣቴ ብርሃን አለው፡፡ ሰላማ ማለት እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስታርቅ ማለት ነው፡፡ ከሣቴ ብርሃን ማለትም ሃይማኖትን ገልጦ የሚያስተምር ማለት ነው፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስም ከሾመው በኋላ ታቦትና በጣም ብዙ ንዋያተ ቅድሳትንና መገልገያ ዕቃዎችን ሰጥቶ መርቆ በሰላም ወደ ኢትዮጵያ ላከው...፡፡ አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #አቡነ_ኢየሱስ_ሞዐ፦ አገራቸው ጎንደር ክፍለ ሀገር ስማዳ ወረዳ ሲና ዳኅና በሚባል ቦታ ነሐሴ 26 ቀን ተፀንሰው ግንቦት 26 ቀን 1210 ዓ.ም ከአባታቸው ከቅዱስ ዘክርስቶስና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ክብራ ተወለዱ፡፡ የተወለዱትም በቅዱስ ነአኲቶ ለአብ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡
❤ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የቆብ አባት ሲሆኑ ታላቁን ሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገዳም የቆረቆሩ ደገኛ አባት ናቸው፡፡ ዕድሜያቸው 30 ዓመት እስከሚደርስ ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ትምህርተ ሃይማኖትንና ግብረ ገብን ሲማሩ ከቆዩ በኋላ በ1240 ዓ.ም ይህንን ዓለም በመተው ወደ ደብረ ዳሞ ገዳም ገቡ፡፡ በደብረ ዳሞ ገዳም መነኰሳቱን እየረዱ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እያጠኑ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እየገለበጡ ለሰባት ዓመታት ከቆዩ በኋላ የደብረ ዳሞ 3ኛ አበ ምኔት ከሆኑት ከአባ ዮሐኒ እጅ ምንኩስናን በ1247 ዓ.ም ተቀበሉ፡፡
❤ አንድ ቀን ሌሊት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደርሳቸው መጥቶ "የስምህ መክበርያ ወደሆነው ሐይቅ ወደ ተባለው ሥፍራ ሂድ" አላቸው፡፡ አባታችንም "ቦታውን እንዴት ዐውቀዋለሁ?" በማለት መልአኩን ቢጠይቁት "ተነሥ! ጉዞህን ጀምር ቦታውን እኔ አሳይሃለሁ" አላቸው፡፡ አባ ኢየሱስ ሞዐ በመልአኩ እንደታዘዙት ከበዓታቸው ተነሥተው ተከተሉት፡፡ የብዙ ወራት መንገድ የሆነውን ጐዳናም በስድስት ሰዓት አደረሳቸው፡፡ በዚያን ወቅት ከሐይቅ ገዳም በስተ ሰሜን ወደነበረው የቅዱሳን ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ደረሱ፡፡ ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ከመግባታቸው በፊት ለ6 ወራት ያህል በቅዱሳን በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን አገልግለዋል፡፡ ያገለግሉበት በነበረው ቤተ ክርስቲያን ቀን ቀን ሕዝቡን ሲያስተምሩ በመዋል ሲመሽ ወደ ሐይቁ በመግባት ሲጸልዩ ያድሩ ነበር፡፡ በሐይቅ እስጢፋኖስና በዙርያው ለነበሩ አበው ማታ ማታ አንድ ብርሃን ወደ ሐይቁ ሲገባ ጠዋት ጠዋትም ሲወጣ ይታያቸው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን በገዳሙ አባቶች ልመናና በልዑል እግዚአብሔር ትዕዛዝ ወደ ሐይቅ ገዳም ገብተው አበምኔት ሆኑ፡፡
❤ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከደሴ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ሲሆን የመሠረቱት ካልዕ ሰላማ የተባሉ ግብፃዊ ጻድቅ ናቸው፡፡ ሐይቅን አባ ሰላማ ካልዕና ዐፄ ድል ነአድ በ862 ዓ.ም ነው የቆረቆሩት። ገዳሙን ካቀኑት በኋላ "የማንን ታቦት እናስገባ?" ብለው ሲያስቡ ቶራ የምትባል እንስሳ ጭነት ተጭና ከመካከላቸው ተገኘች፤ ጭነቱን አውርደው ቢያዩት በሐር ጨርቅ የተጠቀለለ የቅዱስ እስጢፋኖስንና የቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለት ታቦት አገኙ፡፡ በላዩም ላይ "ይህንን ታቦት በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የተሰወሩ ቅዱሳን ከእግዚአብሔር ታዘው የላኩት ነው" የሚል ጽሑፍ አገኙ፡፡ ይህ ከሆነ ከ400 ዘመን በኋላ ነው አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ወደዚህ ቦታ የመጡት፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ለ52 ዓመት ቀን ቀን መንፈሳዊ ሥራቸውን እየሠሩ ሌሊት ሌሊት ሐይቁ ውስጥ ቆመው ሲጸልዩ ያድራሉ፡፡
❤ አባ ኢየሱስ ሞዐ በሐይቅ እስጢፋኖስ በአበ ምኔትነት በቆዩባቸው 45 ዓመታት ከየገዳማቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመገልበጥና በማሰባሰብ የመጀመርያው ዘመናዊ የቤተ ክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ በዚሁ ገዳም ውስጥ የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ቋሚ ትምህርት ቤት በማቋቋም 800 መነኮሳትን በትምህርተ ሃይማኖት አሠልጥነው በንቡረ ዕድነት ማዕረግ ሾመው በመላ ሀገራችን እንዲሠማሩ አድርገዋቸዋል፡፡ ከእነዚህም ተማሪዎቻቸው መካከል አቡነ ተክለ ሃይማኖት (ደብረ ሊባኖስ)፣ አቡነ ኂሩተ አምላክ (ጣና ሐይቅ ዳጋ እስጢፋኖስ)፣ አቡነ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ቦረና)፣ አባ በጸሎተ ሚካኤል (ቦረና)፣ አቡነ ገብረ እንድርያስ (ቦረና)፣ አቡነ ሕዝቅያስ (ቦረና)፣ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ዳውንት)፣ አቡነ አሮን (መቄት)፣ አቡነ ተክለ ኢየሱስ ሞዐ (ሐይቅ)፣ አቡነ አላኒቆስ (ትግራይ)፣ አቡነ በግዑ (ሐይቅ)፣ አቡነ ሠረቀ ብርሃን (ሐይቅ)፣ አቡነ ብስጣውሮስ (ሐይቅ)፣ አቡነ ዮሴፍ (ላስታ) ዋና ዋናዎቹና በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ጻደቁን ንጉሥ ዐፄ ይኩኖ አምላክንም በትምህርተ ሃይማኖት አንጸውና ኮትኩተው ያሳደጉት ጻድቁ አባታችን ናቸው፡፡
❤ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ መጥተው በሐይቁ ዳር ቆመው ሳለ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ በእግሩ በውኃው ላይ እየሄደ እያሳያቸው ተከትለውት እንዲሄዱ ነገራቸው። አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ሐይቁን በእግራቸው ጠቅጥቀው ተራምደው ተሻግረው አቡነ ኢየሱስ ሞዐን አገኟቸው፡፡ እርሳቸውም አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ እርሳቸው እየመጡ እንደሆነ በመንፈስ ዐውቀው ነበርና ሲያገኟቸው በጣም ተደስተው ከተቀበሏቸው በኋላ አመነኵሰዋቸዋል፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ እጅግ በጣም ብዙ መነኰሳትን አፍርተዋል፡፡ የመጀመሪያው መነኩሴ አባ እንጦንስ ነው፡፡ እንጦንስ መቃርስን፣ መቃርስ ጳኵሚስን፣ ጳጉሚስ ቴዎድሮስን፣ አቡነ አረጋዊንና 8ቱን ቅዱሳን አመነኰሱ፡፡ አቡነ አረጋዊም ወደ ኢትዮጵያ በ460 ዓ.ም መጥተው ክርስቶስ ቤዛን፣ አባ ክርስቶስ ቤዛም መስቀለ ሞዐን፣ መስቀለ ሞዐም አባ ዮሐኒን፣ አባ ዮሐኒም አባ ኢየሱስ ሞዐን፣ አባ ኢየሱም ሞዐም አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አመነኰሱ፡፡ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ምን ያህል ቀደምትና ባለ ታሪክ አባት እንደሆኑ ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡
❤ በዮዲት ጉዲት እጅጉን ተጐድታ የነበረችው አገራችን ዳግም የወንጌሉ ብርሃን እንዲበራባት ሊቃውንት፣ እንዳይታጡባት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳይቆነጻጸሉ፣ መነኰሳት አባቶች ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ወርደው ገዳማትን እንዲያስፋፉ ያደረጉት አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለአገራችን ትልቅ ባለውለታ ናቸው፡፡ በተለይም በሐይቅ እስጢፋኖስ ያፈሯቸውን 800 ሊቃውንት በመላዋ ኢትዮጵያ በመሰማራታቸው ዛሬ የምናያቸውን አብዛኛዎቹን ገዳማትና ቅዱሳት መጻሕፍት አቆይተውልናል፡፡ አባታችን ለ45 ዓመታት ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳምን በአበ ምኔትነት እያስተዳደሩ ከቆዩ በኋላ ኅዳር 26 ቀን 1292 ዓ.ም በዕለተ እሑድ ዐርፈዋል፡፡ ከአባታችከኢየሱስ
ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta):
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ኅዳር ፳፮ (26) ቀን።
❤ እንኳን #ለኢትዮጵያውያኑ_ጻድቃን ታላቁን ገዳም ሐይቅ እስጢፍኖስ ለመሰረቱት #ለአቡነ+ኢየሱስ_ሞዐና ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ሀብተ_ማርያም_ለዕረፍታቸው_በዓል፣ ለኢትዮጵያ የመጀመርያው ሊቀ ጳጳስ ለነበሩት #ለአቡነ_ሰላማ_ከሣቴ_ብርሃን ለልደት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #ስለ_አባታችን_አቡነ_ሀብተ_ማርያም_ዕረፍት፦ ... ከዚህም በኋላ ዕለተ ሞቱ በደረሰ ጊዜ ለሞቱ ምክንያት የሚሆን ቸነፈር ያዘው፤ መድኃኔዓለም አምላካችን በዐቢይ ምስጋና ወደ እርሱ መጥቶ "ሰላም ለአንተ ይሁን ወዳጄ ሀብተ ማርያም ሆይ ዛሬ ግን ወደ አንተ የመጣሁት ከድካም ወደ ዕረፍት እወስድህ ዘንድ ነው ሰባት የጽድቅ የክብር አክሊሎችን አዘጋጅቼለሃለሁ አንደኛው ስለ ንጹሕ ድንግልናህ፣ ሁለተኛው ዓለምንና በውስጡ ያለውን ንቀህ በመኖርህ፣ ሦስተኛው ስለ ፍጹም ምንኵስናህ፣ አራተኛው ዘወትር አራቱ ወንጌላትን በማንበብህ በመጸለይህ ስለ እኔ ምክንያት፣ አምስተኛው በረኃብህ፣ ስድስተኛው በጾም ስለ ተጋደልክ፣ ሰባተኛው በልብህ ቂምና ጥላቻን ትዕቢትን ትምክህትን ባለማሳደርህና በልብህ ውስጥ ባለማስቀመጥህ፣ ስለ ንጹሕ ተልዕኮ ክነትህ ስለ ምዑዝ ዕጣንህና ስለ ንጹሕ መሥዋዕትህ ነው፤ እኒህ ሰባት አክሊላትም እያንዳንዳቸው ባለ ዐሥራ አምስት ኅብርና ጌጥ ያላቸው ናቸው። አህጉረ ገነትም በውስጧ አምስት መቶ የወርቅ አምዶች ያለው ትገባበት ዘንድ አንተና እንዳንተ ላሉ ወዳጆችህ የሚገቡበት ቤት እሰጥሃለሁ በምሰጥህም ቤት መታሰቢያህን ያደረገ በጸሎቶህ የተማፀነ ይገባል የወርቅ ጫማን፤ የእሳት መስቀልን የብርሃን ልብስን ድብቅ መናን እሰጥሃለሁ" አለው።
❤ መድኃኔዓለምም ይህንን ቃል ኪዳን ሲሰጠው ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት በየሥርዓታቸው መጥተው ቆሙ፣ "ወዳጃችን አባ ሀብተ ማርያም ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን ዛሬስ በዝማሬና በማኅሌት ከፀሐይና ከጨረቃ ከከዋክብትም ሰባት እጅ ወደ ምታበራ ወደ ሰማያዊት ሀገር እንወስድህ ዘንድ ደስ ይበልህ" አሉት፤ ቅዱስ አባታችን አቡነ ሀብተ ማርያም "ለእግዚአብሔር በሰማያት ምስጋና ይሁን በምድርም የሰውን ልጅ ለወደደውና ላፈቀረው" ብሎ አመሰገነ። ይህንንም ባለ ጊዜ አምላክ በሦስትነቱ ተገልጾ ታየው፤ "ከዮሐንስ መጥምቅ ጎን ለጎን ቀጥላ ያለችውንና ከፀሐይ እልፍ እጅ የበለጠ የምታበራውን አገር እንድሰጥህ እንሆ በማይሻር ቃሌ ማልኩልህ" አለው፣
❤ "እውነት እውነት እልሃለሁ መታሰቢያህም ያደረገ ስምህንም የጠራ ለቤተ ክርስቲያንህም ዕጣን የሰጠ ወይም ዘቢብ የሰጠ ወይን መብራት የሰጠ ከአንተ ጋር ይኖራል አራቱ ወንጌልንም ታነብ ስለ ነበር ለእያንዳንዷም የወንጌል ቃል ፍሬህን አንድ ሺህ አንድ ሺህ አደረኩልህ ይህ ቃል ኪዳን ለአመኑ ልጆችህና መታሰቢያህን ለሚያደርጉ ሁሉ ማየ ጸሎቱን ለሚጠመቁ ለሚያነቡ ለሚያስነብቡ ይህን ቃለ ኪዳን ሰጥቻለሁ" አለው።
❤ ይህንንም ካለው በኋላ ጌታችን አፋን ሦስት ጊዜ ሳመው፤ ያን ጊዜም ከመድኃኔዓለም ጣዕም ፍቅር የተነሣ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፤ ጌታችንም ተቀብሎ አቀፋት ከእርሱም ጋር ወደ ሰማይ አሳረጋት ያን ጊዜም በቅዱሳን ሠራዊተ መላእክት ዘንድ ታላቅ እልልታና ብዙ ደስታ ሆነ በሰማያዊ መላእክት በምድራዊያን ስውራን ቅዱሳን ዘንድ ታላቅ ደስታ ሆነ በሐሳበ ዕብራውያን በናኢብሮስ ታስሪን ወርህ 22 ቀን በኢትዮጵያ ኅዳር26 ቀን በሰማዕታተ ናግራን በዓል በ6ሺ 9መቶ 99 ዓመተ ኩነኔ በኋላ 1ሺ 499 ዓ.ም በሆነ ዘመን ዕለት የአባታችን የአቡነ ሀብተ ማርያም ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፤ ያን ጊዜም ከአባታችን ከአቡነ ሀብተ ማርያም የሕይወት መንፈሳቸው ከወጣች በኋላ ካህናት በመልካም ልብስ ገንዘው በዝማሬ በማኅሌት ከቅዱስ አባታችን ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት አጽም ጋር በጻድቁ መቃብር ቀበሩት። ከአባታችን አቡነ ሀብተ ማርያም ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸውም ይማረን።
ምንጭ፦ ገድለ አቡነ ሀብተ ማርያም 18፥18-27።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #አቡነ_ሰላማ_ከሣቴ_ብርሃን፡- ቅዱስ አባታችን አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በኋላ በ245 ዓ.ም በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ኅዳር 26 ቀን ሲወለዱ ታላቅ ብርሃን ከሰማይ ወርዶ ለ7 ቀናት አብርቷል፡፡ ቅዱሳን መላእክትም ወደ ምድር ወርደው ጻደቁ በመወለዳቸው ታላቅ ደስታን አድርገዋል፡፡ አባታችን በተወለዱ ጊዜ "ለአብ ስግለት ለወልድ ስግደት ለመንፈስ ቅዱስ ስግደት ይገባል፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን ለአወጡኝ ቅድመ ዓለም ለነበሩ ዛሬም ላሉ ዓለምን አሳልፈው ለሚኖሩ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል" ብለው ዳግመኛም "አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ" ብለው ፈጣሪያቸውን በአንድነት በሦስትነት አመስግነዋል፡፡ ቅዱስ አባታችን በሌላኛው ስማቸው ፍሬምናጦስ እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ በ40 ቀናቸው ጌታ በተጠመቀበት በዮርዳኖስ ያጠመቋቸውና ስመ ክርስትና የሰጧቸው ሊቀ ጳጳስ "ይህ ሕፃን ለኢትዮጵያውን ሁሉ ብርሃን ይሆንላቸዋል" በማለት ትንቢት ተናግረዋል፡፡
❤ አቡነ ሰላማ በሊቀ ጳጳሱ በቅዱስ አትናቴዎስ በሚገባ ተምረው ካደጉ በኋላ በ257 ዓ.ም ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ስሙ ሜርጵዮስ ከሚባል ከአንድ ነጋዴ ጋር መጡ፡፡ ከእነሱም ጋር አድስዮስ የሚባል ልጅ ነበር፡፡ ወደ ሀገራችንም ሊመጡ የቻሉት እንዴት ነው? ቢሉ መጀመሪያ ለሰባት ወር በአንድ ሌላ አገር ኖረው ወደ ኢየሩሳሌም ሊመለሱ ሲሉ የበረሃ ሽፍቶች ሜርጵዮስንና ሌሎች መንገደኞችን ገደሏቸውና ሁለቱን ልጆች ማርከው ወስደው ስሙ አልአሜዳ ለሚባል ለአክሱም ንጉሥ ሰጡት፡፡ እርሱም አድስዮስን የቤተክርስቲያን የአልባሳትና የዕቃ ቤት ጠባቂ አድርጎ ሲሾመው ፍሬምናጦስን ደግሞ የቤተ ክርስቲያንና የሕግ ጠባቂ አደረገው-የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓቷንና አገልግሎቷን ጠንቅቆ ያውቅ ነበርና፡፡ እርሱም በአክሱምም በተጋድሎና በትጋት ኖረ፡፡ ቅዳሜና እሁድ የዛፍ ቅጠሎችን ከመመገብ በቀር ሌላ ምግብ አይቀምስም ነበር፡፡ በየቀኑም አምስት ሺህ ስግደትን ይሰግድ ነበር፡፡ በእርሱም የተጋድሎ ዘመን ደጋግ የሆኑ ነገሥታት አብርሃና አጽብሓ ነገሡ፡፡ እነርሱም ሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍሬምናጦስን በጣም ይወዱት ነበር፡፡
❤ አንድ ቀን ፍሬምናጦስ የአክሱሙን ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ሚናስን "ግዝረትና እምነት በእናንተ ዘንድ አለ ነገር ግን ጥምቀትና ሥጋ ወደሙ መቀበል በእናንተ ዘንድ የለም" አለው፡፡ ቅዱስ ሚናስም "ግዝረትንስ አባቶቻችን ሌዋውያን አመጡ፣ በክርስቶስ ማመንን ሕንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት ጃንደረባ አመጣልን፡፡ ስለ ጥምቀትና ሥጋ ወደሙ ሐዋርያ ወደ እኛ አልተላከም ነገር ግን ያልከውን ሁሉ የሚያደርግልን የሚባርከንና የሚቀድሰን ጳጳስን ታመጣልን ዘንድ ሊቀ ጳጳሱ ወዳለበት ወደ እስክንድሪያ አገር አንተ ሂድ" አለው፡፡ ጥምቀትስ በጃንደረባው በኩል አገራችን ገብቶ ነበር ነገር ግን ገና ስላልተጠናከና ብዙ ሕዝብም አልተጠመቀም ነበርና አባታችን ፍሬምናጦስ አጠናክሮ ያልተጠመቀውን ሁሉ አጥምቆአል፡፡
እንዳልተባባረ አስረዱት።
❤ ከዚያንም ጊዜ ንጉሥ መልክተኞችን ልኮ ቅዱስ መርቆሬዎስን ወደርሱ አስመጣው በመዘግየቱም አድንቅ "ለአማልክት ዕጣን ለማድረግ ከእኔ ጋር ያልወጣህ የእኔን ፍቅር እንዴት ተውህ" አለው። በዚያንም ጊዜ ትጥቁንና ልብሱን ወረወረለትና ንጉሡን እንዲህ አለው "እኔ ክብር ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም ለረከሱ ጣዖታትም አልሰግድም"። ንጉሥ ዳኬዎስም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ እርጥብ በሆኑ የሽመል በትሮች እንዲደበድቡት አዘዘ። ሁለተኛም ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ ይገርፋት ዘንድ አዘዘ ንጉሡ እንዳዘዘ ይህን ሁሉ አደረጉበት።
❤ በዚያንም ጊዜ የአገር ሰዎች ስለ ቅዱስ መርቆሬዎስ እንዳይነሡበት ፈርቶ የቀጰዶቅያና የእስያ ክፍል ወደ ሆነች ወደ ቂሣርያ በብረት ማሠርያ አሥሮ ላከው። በዚያም እንዲአሠቃዩት አዘዘ ከአሠቃዩትም በኋላ ንጉሥ ዳኬዎስ እንዳዘዘው ራሱን በሰይፍ ቆረጡትና ተጋድሎውን ፈጽሞ በመግሥተ ሰማያት የሕይወት አክሊልን ተቀበለ። የማይጠፋ ሰማያዊ አክሊልንም ተቀዳጅቶ ወደ ዘላለም ሕይወት ከገባ በኋላ በዓለሙ ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ታነፁለት እግዚአብሔርም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራትን በውስጣቸው ገለጠ።
❤ ከተአምራቱም አንዲቱ ዑልያኖስ በነገሠ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ካደ በዚያንም ወራት ቅዱስ ባስልዮስ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ነበረ ተአምራቱ በተጻፈበት መጽሐፍ እንደተጻፈ ምእመናን በጽኑዕ ሥቃይ ዑልያኖስ ባሠቃየ ጊዜ መክሮ አስተምሮ ከስሕተቱ ይመልሰው ዘንድ ቅዱስ ባስልዮስ ወደርሱ መጣ።
❤ ዑልያኖስም ቅዱስ ባስልዮስን በአየው ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችንን ሰደበ ቅዱስ ባስልዮስንም አሠረው በዚያ በእስር ቤትም የቅዱስ መርቆሬዎስን ሥዕል አይቶ በፊቱ ቅዱስ ባስልዮስ ጸለየ ሥዕሉም ከቦታው ታጣ። ያን ጊዜ ወደ ዑልያኖሰሰ ሒዷልና በጦርም ወግቶ ገደለውና ወዲያውኑ ወደቦታው ተመለሰ ከጦሩም አንደበት ደም ይንጠፈጠፍ ነበር። ቅዱስ ባስልዮስም ከሀዲ ዑልያኖስን እንደገደለው አውቆ እንዲህ ብሎ ተናገረ "የክርስቶስ ምስክር ሆይ የእውነት ፀር የሆነ ዑልያኖስን ገደልከውን?" ያን ጊዜ አዎን እንደሚል ሥዕሉ ራሱን ዘንበለሰ አደረገ ቅዱስ ባስልዮስም ደስ ብሎት እግዚአብሔር አመሰገነ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ መርቆሬዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ ገድለ መርቆሬዎስና የኅዳር 25 ስንክሳር።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ልሳነ ከለባቲከ ላዕለ ጸላእቱ። አስተርአየ ፍናዊከ እግዚኦ። ፍናዊሁ ለአምላክነ ለንጉሥ ዘውስተ መቅደስ"። መዝ 67፥23-24 ወይም መዝ 88፥14-15። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 10፥17-32 ወይም ማቴ 20፥20-24።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ቅረብ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ። ወኢይትኀፈር ገጽክሙ። ዝንቱ ነዳይ ጸርሐ ወእግዚአብሔር ስምዖ"። መዝ 33፥5-6 የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 12፥25-ፍ.ም፣ ያዕ 3፥4-13 እና የሐዋ ሥራ 21፥27-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 8፥22-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም የሰማዕቱ የቅዱስ መርቆሬዎስ የዕረፍት በዓልና፣ ዕለተ ሰንበትና የነቢያት (የገና) የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።
ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta):
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ኅዳር ፳፭ (25) ቀን።
❤ እንኳን #ለታላቁ_ሰማዕት_ለቅዱስ_መርቆሬዎስ (ፒሉፓዴር) በንጉሥ ዳኬዎስ እጅ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ መታሰቢያ ዓመታዊ በዓል እግዚአብሔር አምላከ በሰላምና ጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከእስላሞች ወገን ከነበረ #ቅዱስ-መርቆሬዎስ ተአምር አድርጎ ከመለሰው #ከቅዱስ_ዮሐንስ፣ #ከአቃርዎስና_ከሮማኖስ ከመታሰቢያቸወ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #ቅዱስ_መርቆሬዎስ፦ መርቆሬዎስ ማለት የአብ ወዳጅ ማለት ነው። በሁለተኛ ትርጓሜ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ማለት ነው። ይህም ቅዱስ አስሊጥ ከምትባል አገር ነው እርሷም የአባቱና የአያቱ አገር ናት እርሱ ግን ተወልዶ ያደገው በሮሜ ከተማ ነው።
❤ የአባቱና የአያቱ ሥራቸው አውሬ ማደን ነበር በአንዲት ዕለትም እንደልማዳቸው ለማደን ወጡ ከገጸ ከለባት ወገንም ሁለት ወንዶች ተገናኙአቸውና የቅዱስ መርቆሬዎስን አያት ስዲሮስ በሉት። ሁለተኛም አባቱን አሮስን ሊበሉት ፈለጉ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክም ከለከላቸው "ከእርሱ የሚወጣ መልካም ፍሬ ስለ አለ አትንኩት" አላቸው።
❤ ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ዙሪያቸውን በእሳት ከበባቸው በተቸገሩ ጊዜም ወደ ቅዱስ መርቆሬዎስ አባት አሮስ መጥተው ሰገዱለት በዚያንም ጊዜ እግዚአብሔር ፍጥረታቸውን ወደገራምነት ለወጠውና እንደ በጎች የዋሆች ሆኑ አብረውትም ወደ መንደር ገቡ።
❤ ከዚህም በኋላ ቅዱስ መርቆሬዎስ በተወለደ ጊዜ ስሙን ፒሉፓዴር ብለው ጠሩት የውሻ መልክ ያላቸው በእነርሱ ዘንድ ብዙ ዘመናት የሚኖሩ ሆኑ ከዚህም በኋላ ክርስቲያኖች ሆኑ የቅዱስ መርቆሬዎስ ወላጆች አስቀድሞ አረማውያን ነበሩና የክርስትና ጥምቀትንም ጸጋ በተቀበሩ ጊዜ የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት ኖኅ ብለው ሰየሙት እናቱንም ታቦት አሏት ፒሉፓዴርንም መርቆሬዎስ ብለው ሰየሙት። የውሻ መልክ ያላቸው ግን የእግዚአብሔር መልአክ በተገለጸላቸው ጊዜ እንደ ነገራቸው ለቅዱስ መርቆሬዎስ አባት የሚታዘዙና የሚያገለግሉ ሆኑ።
❤ ንጉሡም የኖኅንና የውሻ መልክ ያላቸውን ዜና በሰማ ጊዜ ወደርሱ አስቀረባቸው በዚያንም ጊዜ እግዚአብሔር በንጉሡ ፊት የቀድሞ ፍጥረታቸውን መልሶላቸው የንጉሡ ያቀረባቸውን ሁሉንም አራዊት አጠፏቸው። ንጉሡም ይህን በአየ ጊዜ እጅግ ፈራ የአራዊትንም ተፈጥሮአቸውን ያርቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንዲማልድ የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት ለመነው። እርሱም በለመነ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ተፈጥሮአቸውን መልሶላቸው ገራሞች ሆኑ።
❤ ከዚህም በኋላ የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት ንጉሡ ወስዶ ገዥና የሠራዊት አለቃ አድርጎ ሾመው የውሻ አርያ ያላቸውም ይታዘዙለት ነበር ከእርሳቸውም የተነሣ ሁሉም ይፈሩ ነበር። ከዚህም በኋላ የቅዱስ መርቆሬዎስን አባት የሾመውን ንጉሥ ይወጋ ዘንድ ከሀዲ ንጉሥ ተነሣ ንጉሡም ከጦር አባት ወደ ጦርነት ላከው። ከሀዲው ንጉሥ ግን እነዚያን የውሻ አርያ ያላቸውን አባብለውና ሸንግለው ወደርሱ የመጧቸው ዘንድ ወታደሮችን ላከ በአመጧቸውም ጊዜ ሃይማኖታቸውን ይለውጡ ዘንድ አብዝቶ ሸነገላቸው ባልሰሙትም ጊዜ ሊአሠቃያቸው ጀመረ አንዱ አምልጦ ሸሽቶ ወደ ጌታው ሔደ ሁለተኛውም በሰማዕትነት ሞተ።
❤ ከጦር ሜዳ የቅዱስ መርቆሬዎስ አባት በመለሰ ጊዜ ሚስቱንና ልጁን ፈለጋቸው ግን አላገኛቸውም ንጉሡ የሱ ወገኖች ድል እንደሆኑ በሰማ ጊዜ የቅዱስ መርቆሬዎስ አባት መኰንኑ የሞተ መስሎት ነበርና የቅዱስ መርቆሬዎስን እናት ወስዶ ሊአገባት ፈለገ ከንጉሥ ወታደሮችም አንዱ ንጉሡ ያሰበውን በጽሞና ነገራት። እርሷም ይህንኑ ወታደር ከአገር ውስጥ በሥውር ያወጣት ዘንድ ለመነችውና ከልጇ ከብፁዕ መርቆሬዎስ ጋር ወጥታ ወደ ሌላ አገር ሔደች። ንጉሡም ከእርሱ የሆነውን የመኰንኑም የመርቆሬዎስን አባት ሚስቱን ለማግባት ማሰቡን እንዳይነግሩት አዘዘ የውሻ መልክኮች ያላቸው ከእርሱ ጋር እንዳሉ የተቆጣም እንደሆነ እንደሚአመጣቸውና አገሮችን ያጠፋሉ ብሎ ይጠራጠራልና ስለዚህ እጅግ ይፈራዋል።
❤ ከዚህም በኋላ ደግሞ በንጉሡ ላይ ጦርነት ተነሣ የቅዱስ መርቆሬዎስም አባት ወደ ጦርነት ወጣ በእግዚአብሔርም ፈቃድ ይዘው ማረኩት ወደ ሮሜውም ንጉሥ አቀረቡት ንጉሡም ክርስቲያን ነበርና የተማረከው መኰንን ክርስቲያን መሆኑን በአወቀ ጊዜ አልገደለውም በክብር አኖረው እንጂ እጅግም ወደደውና ከጥቂት ቀኖች በኋላ በመርዶሳውያን አገሮች ሁሉ ላይ ገዥ አድርጎ ሾመው።
❤ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ ሚስቱና ልጁ መርቆሬዎስ ወዳሉበት አገር ደረሰ ሚስቱም በቤተ ክርስቲያን ደጃፍ በአየችው ጊዜ ባሏ እንደሆነ አወቀችው እርሱ ግን አላወቃትም በአንዲትም ዕለት እርሱና ጭፍሮቹ ከእንግዳ ማረፊያ ቤት በወጡ ጊዜ ልጅዋን መርቆሬዎስን ወስዳ ያማሩ ልብሶችን አልብሳ ሒዶ ከመኰንኑ ፈረስ ላይ እንዲቀመጥ አዘዘችው እርሱም አባቱ ነው በተቀመጠም ጊዜም ጭፍሮች ይዘው ወደ መኰንኑ ፊት አቀረቡት መኰንኑም ልጁ እንደሆነ አላወቀምና በእርሱ ላይ ተቆጣ።
❤ የመርቆሬዎስ እናት መጥታ "ጌታዬ ሆይ እኛ መጻተኞች ነን አንተም መጻተኛ እንደሆንክ በአወቅሁ ጊዜ ልጅህ ሁኖ ልጄ ከአንተ ጋር እንዲሆን አሰብኩ" አለችው። እርሱም ጠየቃት እንዴት እንደተሰደደችም መረመራት እርሷም ሚስቱ እንደሆች ነገረችው በዚያንም ጊዜ አወቃት ልጁን መርቆሬዎስንም አወቀው አጅግም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔር አመሰገኑት ያንንም የእንግዳ ማረፊያ ቤት ቤተ ክርስቲያን አደረጉት እግዚአብሔርም እያመሰገኑ በአንድነት ኖሩ።
❤ ከዚህም በኋላ አባቱና እናቱ በሞቱ ጊዜ ንጉሡ ቅዱስ መርቆሬዎስን ወስዶ በአባቱ ፈንታ በመርዶሳውያን አገር ላይ ሾመው ቅዱስ መርቆሬዎስም መኰንንነትን በተሾመ ጊዜ ያ ገጸ ከልቡ ከርሱ ጋር ነበር ወደ ጦርነትም አብሮት የሚወጣ ሆነ። ለመዋጋትም በሚሻ ጊዜ የቀድሞ የአራዊት የሆነ ተፈጥሮውን እግዚአብሔር ይመልስለት ነበር ማንም ሊቋቋመው የሚችል የለም። ለቅዱስ መርቆሬዎስም ታላቅ የድል አድራጊነት ኃይል ተሰጠው ዜናውም በሁሉ ቦታ ተሰማ ከቤተ መንግሥት ሰዎችም ከፍ ከፍ አለ።
❤ እንዲህም ሆነ ያን ጊዜ በዚያን ወራት በሮሜ አገር ጣዖትን የሚያመልክ ዳኬዎስ የሚባል ንጉሥ አለ። ጠላቶቹም የበርበር ሰዎች ተነሡበት እርሱም ከእርሳቸው ጋር ሊዋጋ ሠራዊቱን ሰብስቦ ወጣ እነርሱ ግን እንደ ባሕር አሸዋ ብዙ ነበሩ ብዛታቸውንም በአየ ጊዜ ደንግጦ እጅግ ፈራ ቅዱስ መርቆሬዎስም "እግዚአብሔር ያጠፋቸው ዘንድ በእጃችንም አሳልፎ ሊሰጣቸው አለውና አትፍራ" አለው።
❤ ከዚህም በኋላ ቅዱስ መርቆሬዎስ የእግዚአብሔርን መልአክ በውጊያው ውስጥ አየው የተሳለ ሰይፍም በእጁ ውስጥ አለ ያቺንም ሰይፍ ሰጠውና እንዲህ አለው "ጠላቶችህን ድል በአደረግህ ጊዜ ፈጣሪህ እግዚአብሔር አስበው"። ጠላቶቹንም ድል አድርጎ በሰላም ተመለሰ መልአኩም ዳግመኛ ተገልጦለት "ለምን ፈጣሪህን የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ረሳህ" አለው።ጦርነቱም ከተፈጸመ በኋላ ንጉሥ ዳኬዎስ ለጣዖታቱ ዕጣን በማሳረግ በዓልን ሊያደርግ ወደደ ቅዱስ መርቆሬዎስም ለበዓል ማክበር አብሮት አልወጣም ወደ ቤቱ ሔደ እንጂ ሰዎችም ቅዱስ መርቆሬዎስ እንዳልመጣና ዕጣንን በማሳረግም
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለክሙ_ካህናተ_ሕጉ_ወትእዛዙ። ለእግዚአብሔር ቃል ዘጶደሬ ሥጋ ዐራዙ። እምነቅዓ አፉክሙ ሐሤት ዘኢይነጽፍ ውኂዙ። ኪያየ ኅዙነ ወትኩዘ ልብ ናዝዙ። በወክንፍክሙ ብርሃናዊ ዐውድየ ሐውዙ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የኅዳር_24።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወአስተዮሙ ከመ ዘእምቀላይ ብዙኅ። ወአውኃዘ ማየ ከመ ዘእምአፍላግ። ወአውጽአ ማየ እምዕብን"። መዝ 77፥15-16። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 4፥10-27።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ባርክዎ ለእግዚአብሔር ኵልክሙ መላእክቲሁ። ጽኑዓን ወኃያላን እለ ትገብሩ ቃሎ። ወእለ ትሰምዑ ቃለ ነገሩ"። መዝ 102፥20። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ጢሞ 5፥17-ፍ.ም፣ ያዕ 5፥17-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 22፥18-21 ወይም 12፥6-12። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 13፥37-43። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ወይም የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ቅዳሴ ነው። መልካም የሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ፣ የአቡነ ተክለሃይማኖት በዓል፤ የአቡነ ዜና ማርቆስ የልደት በዓል የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።
ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta):
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤
❤ #ኅዳር ፳፬ (24) ቀን።
❤ እንኳን #በእግዚአብሔ_ዙፋን_ዙርያ ለሚቆሙ #የቅድስት_ሥላሴ_ዙፍን ለሚያጥኑ #ለሃያ_አራቱ_ካህናተ_ሰማይ_ቅዱሳን_ለሱራፊል ለበዓላቸው መታሰቢያ፣ #ለናግራ_አገር_ቄስ ለከበረ #ለቅዱስ_አዝቂር፤ እርሱ ጋር አብረው ሰማዕትነት ለተቀበሉ #አርባ_ስምንት_ሰዎች ለዕረፍታቸው በዓል፣ #ለፃን_አገር_ለሆነ_ለአባ_ዮሴፍ_ለዕረፍታቸው እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን በስንክሳሩ ከሚታሰቡ፦ #ከቅዱሳን_ጋይዮስ_ከቃርዮስ ከጽኑዕ መስተጋድልም ከሆነና መልካም ስም አጠራር ዜና ካለው #ከአባ_ዲዮስቆሮስም ከመታሰቢያቸው ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #ሃያ_አራቱ_ካህናተ_ሰማይ_ቅዱሳን_ለሱራፊል፦ እሊህም ሥጋ የሌላቸው ረቂቃን የእውነት ካህናት የሆኑ ከቅዱሳን ሁሉ በላይ የሆኑና ከሰማይ ሠራዊት ሁሉ ከፍ ከፍ ያሉ ናቸው እነርሱም ለእግዚአብሔር ቀራቢዎች በመሆን ለሰው ወገን የሚማልዱ ከእጃቸው ውስጥ ካለ ማዕጠንት ጋር እንደ ዕጣን የቅዱሳንን ጸሎት የሚያቀርቡ ናቸው ያለእነርሱም አቅራቢነት ጽድቅና ምጽዋት ወደ እግዚአብሔር አይቀርብም።
❤ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንዲህ ብሎ እንደ ተናገረ። "በዙፋኑ ዙርያ ሃያ አራት መንበሮች አሉ በእነዚያ መንበሮችም ሃያ አራት አለቆች ተቀምጠዋል ነጭ ልብስ ለብሰዋል በራሳቸውም ላይ የወርቅ አክሊል አለ። ሁለተኛም እንዲህ አለ "ሌላም መልአክ መጥቶ በመሠዊያው ፊት ቁሞ የወርቅ ጽንሐሕ ይዟል በመንበሩ ፊት ባለ በወርቁ መሠዊያ ላይሞ የቅዱሳንን ሁሉ ጸሎት ያሳርግ ዘንድ ብዙ ዕጣንን ሰጡት። የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳኑ ጸሎት ጋር በዚያ መልአክ እጅ ወደ እግዚአብሔር ፊት ዐረገ"።
❤ "የነበረ የሚኖር የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ነው" እያሉ በመዓልትና በሌሊት ዕረፍት የላቸውም። እሊህም እንስሶቹ ለዘላለሙ ሕያው ለሚሆን በዙፋን ላይ ለተቀመጠ ለሱ እንዲህ እያሉ ክብር ምስጋና አቀረቡ።
❤ እሊህ ሃያ አራቱ አለቆች አክሊላቸውን በዙፋኑ ፊት አውርደው ለዘላለሙ ሕያው ለሚሆን በዙፋን ላይ ለተቀመጠ ለእርሱ ሰገዱለት። አክሊላቸውንም ወደ ዙፋኑ ፊት ወስደው "አቤቱ ፈጣሪያችን ኃይልና ምስጋና ክብር ላንተ ይገባል ይሉታል አንተ ሁሉን ፈጥረሃል የተፈጠረውም ሁሉ በአንተ ፈቃድ ይኖራልና"።
❤ እነርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ በባለሟልነት እጅግ የቀረቡ መሆናቸውንና ስለሁላችን የአዳም ልጆች ስለሚለምኑና ስለሚማልዱ ከብሉይና ከሐዲስ የከበሩ መጻሕፍት ምስክር ኑነዋል ስለዚህም የበዓላቸውን መታሰቢያ እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አዘዙ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ በአማላጅነታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #ቄስ_ቅዱስ_አዝቂር፦ ይህም ንጉሥ አዝቂርን ወደ ወህኒ አስገብተው እንዲዘጉበት ጠባቂዎቹንም ከሰው ወገን ማንም እንዳይገባ ብሎ አዘዘ። ቅዱስ አዝቂርም በጸለየ ጊዜ የወህኒ ቤቱ ደጃፍ ተከፈተና ሃምሳ ሰዎች ወደርሱ ገቡ እርሱም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው።
✝ ንጉሥ ሰራብሄልም በሰማ ጊዜ በወህኒ ቤት አውጥተው ወደሌላ አገር እንዲወስዱት አዘዘ በጉዞም ላይ ስሙ ኪርያቅ ከሚባል ሰው ጋር ተገናኘ ቀስሲስ አዝቂርም ኪርያቅን "ኪርያቅ ሆይ ላንተ የምሥራች ይገባል ለሰማዕትነት ይወስድሃልና" አለው። የንጉሥ ሎሌዎችም ሰምተው አሥረው ከእርሱ ጋር ወሰደቱ። ዳግመኛም ሁለት ሰዎች ተገናኙትና "ስለ ክርስቶስ አጥምቀን" አሉት ያን ጊዜም ቅዱስ አዝቂር ጸለየና ከበረሃ ቦታ ውኃ አፍልቆ ከኪርያቅ ጋር አጠመቃቸው።
❤ ከዚህም በኋላ ወደበረሀ ውስጥ በደረሱ ጊዜ ለእርሳቸውም ለእንስሶቻቸውም የሚጠጡት ውኃ አጥተው ወደ እግዚአብሔር እንዲለምንላቸው ቅዱስ አዝቂርን ለመኑት በጸለየም ጊዜ ደመና መጣ በመሐል እጅ በመመታፈን መጠን በገብታ ላይ ዘነበ ሰባት መቶ ያህል ሰዎች ከእንስሶቻቸው ጋር ጠጥተው ረኩ።
❤ ወደ ንጉሡም በአቀረቡት ጊዜ "ወደ አገራችን ያመጣኸው ይህ አዲስ ትምህርት ምንድነው?" አለው ቅዱስ አዝቂርም "ነቢያት በኦሪት ከሰበኩት በቀር ሌላ አዲስ ትምህርት አላመጣሁም" አለ ንጉሡም ይህን ሰምቶ በክርስቲያን ሃይማኖት ላይ ተዘባበተ። ከአይሁድ መምህራንም አንዱ ተነሥቶ እንዲህ አለ "ጌታዬ ሆይ ወደ አገሩ እንዲወስዱትና በዕንጨት ላይ ሰቅለው በሕይወት ሳለ በእሳት እንዲአቃጥሉት እዘዝ" አለው ንጉሡም እንደ አይሁዳዊው ቃል አዘዘ።
❤ ወደ ናግራን አገርም በአደረሱት ጊዜ በዕንጨት ላይ ሰቅለው ከበታቹ እሳትን አነደዱ ቅዱስ አዝቂርም ወደጌታችን ጸለየ በዚያንም ጊዜ ከማሠሪያው ተፈትቶ ከእሳት ውስጥ በደኅና ወጣ አይሁድም በደንጊያ እንውገረው ተባብለው በወገሩት ጊዜ ደንጊያዎች ተመልሰው ከአይሁድ የሚበዙትን ገደሉ። ከተረፉትም ሰይፍን አንሥተው የቅዱስ አዝቂርን ራስ ቆረጡ ምስክርነቱንም ፈጽሞ የሰማዕትነት አክሊል ተቀዳጀ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ በቅዱስ አባት አዝቂር ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ዮሴፍ፦ ለዚህም ቅዱስ ወላጆቹ በሃይማኖት የበለጸጉ ናቸው ነገር ግን ያለርሱ ልጅ አልነበራቸውም የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት መጽሐፍት ማንበብን እያስተማሩ መልካም አስተዳደግን አሳደጉት መልኩም እንደ ያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ያማረ ነበር በአደገም ጊዜ ሞትን የዚህ ዓለም ኀላፊት ማሰብ በልቡ አሰበ ወደ አንድ ገዳም ሆዶ መነኰሰ በጾም በጸሎት በመስገድ ተጋድሎ የተተከለ ሆኖ ጸና በአቱንም ዘግቶ በዕለ እሁድ ከቊርባን ጊዜ በቀ አይወጣም ነበር።
❤ ዜናውም በተሰማ ጊዜ ከእርሱ በረከቱን ይቀበሉ ዘንድ በአገር ዙርያ ያሉ ሰዎች የሚመጡ ሆኑ አባትና እናቱም የልጃቸውን ወሬ በሰሙ ጊዜ እርሱን ያገናኛቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እየለመኑ ነበር ወሬው በሰሙ ጊዜ ስልጃቸው መገኘት እንዲጸልይላቸው ወደ እርሱ ሄዱ እርሱ ልጃቸው እንደሆነ አላወቁምና ሰው ገላል ባለ ጊዜ ልጃቸው መሆኑን እራሱ ገለጸላቸውና ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው።
❤ እግዚአብሔር ድንቆች ተአምራትን የማድረግ ሀብት ሰጠው ሰይጣን እስከ ቀናበት ድረስ ወደ አገረ ገዢውም ሆዶ ይህ መነኵሴ ዮሴፍ ብዙ ገንዘብ እንዳለው አስመስሎ ነገር ሰራበት መኰንኑም በሰንሰለት ማሰርያዎች አሰረው በማግስቱም ማሰርያዎቹ ከላዩ ወደ ምድር ወድቀው ተገኙ መኰንኑም አይቶ ደነገጠ ለቅድስናውም ተገዥ ሆነ።
❤ ብዙ ከተጋጋደረ በኋላ እግዚአብሔር ከአገለገለ በኋላ በዚች ዕለት በሰላም አረፈ። በክብርም ቀበሩት ከመቃብሩም ቁጥር የሌላቸው ብዙ ተአምራት ተገለጡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ዮሴፍ ጸሎት ይማረን በከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የኅዳር 24 ስንክሳር።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ አሐዱ አምላክ አሜን። ❤
❤ #ኅዳር ፳፫ (23) ቀን።
❤ እንኳን #ከሰባ_ሁለቱ_አርድእት አንዱ ለሆነው በሐዋርያው #በቅዱስ_ጴጥሮስ_እጅ_ለተጠመቀ ለመቶ አለቃ ለነበረው #ለጻድቁ_ቅዱስ_ቆርኔሌዎስና የስሙ ትርጓሜ የእግዚአብሔር አገልጋይ ለሆነ #ለነቢዩ_ቅዱስ_አብድዩ_ለዕረፍታቸው_በዓል በሰላም አደረሰን። ከእነዚህ ቅዱሳን እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #መቶ_አለቃው_ጻድቁ_ቅዱስ_ቆርኔሌዎስ፡- ይህም ቅዱስ የፍልስጤም ክፍል በሆነች በቂሣርያ የመቶ አለቃ ሆኖ የተሾመ ነው፡፡ እርሱም አስቀድሞ ከዋክብትን ሲያመልክ የነበረ ነው፡፡ እንደርሱ ማንም ሊአደርግ የማይቻለውን የሚያመልካቸው አማልክቶቹም ቢሆኑ በሐዋርያት እጅ የሚደረገውን የተአምራታቸውና የስብከታቸውን ዜና በሰማጊዜ ወዲያውኑ ለአማልክት መስገድን አቆመና በጾም በጸሎት ተወስኖ ለድኆችና ለችግረኞች የሚመጸውት ሆነ፡፡ ሁል ጊዜም በጸሎቱም "አቤቱ እውነተኛው አምላክ ሆይ! እኔ አንተን ከማወቅ ጎደሎ ነኝና አንተ ግን የቀናውን መንገድ ምራኝ" እያለ ይለምን ነበር፡፡ ይቅር ባይ ቸር እግዚአብሔርም ቆርኔሌዎስን ይቅር ብሎት ልመናውን ተቀብሎት መልአኩን ላከለት፡፡ እርሱም መልአኩን ባየው ጊዜ ደነገጠ፡፡ መልአኩም "ቆርኔሌዎስ ሆይ! ጸሎት ልመናህ ምጽዋትህ መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጓልና ደስ ይበልህ፡፡ አሁንም በጫማ ሰፊው በስምዖን ቤት የሚኖረውን ስምዖን ጴጥሮስን ይጠሩልህ ዘንድ ሰዎችን በባሕር አቅራቢያ ወዳለች ኢዮጴ ከተማ ላክ" አለው። ቆርኔሌዎስም መልአኩ እንደነገረው ቅዱስ ጴጥሮስን ከስመጣው በኋላ ከእግሩ በታች ሰገደለት፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም አነሣውና "እኔም እንደ አንተ ሰው ነኝ" አለው፡፡ ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ቆርኔሌዎስም ቤት ብዙ ሰዎችን ተሰብስበው አገኘ፡፡ ቆርኔሌዎስም ቅዱስ ጴጥሮስን ያስጠራበትን ምክንያት መልአኩም ተገልጦለት የነገረውን ሁሉ በዝርዝር ከነገረው በኋላ "እግዚአብሔር ያዘዘህን ሁሉ ልንሰማ እነሆ ሁላችን በፊትህ አለን" አለው፡፡ ሐዋ10፥1-31፡፡
❤ ቅዱስ ጴጥሮስም አንደበቱን ገልጦ የጌታችንን ሰው የመሆኑን ምሥጢር መከራ መስቀሉን፣
ሞቱ፣ ትንሣኤውን ፣ዕርገቱንና ዳግመኛም ለፍርድ እንደሚመጣ በግልጽ አስተማራቸው፡፡ ቆርኔሌዎስም በዚህ ጊዜ ከነቤተሰቡ በጌታችን አምኖ ተጠመቀ፡፡ ከዚያ የነበሩ ብዙ አሕዛብም አምነው ተጠመቁ፡፡ ከዚህም በኋላ ቆርኔሌዎስ ይህን ዓለም ለመግዛት የተሾመውን ሹመቱን ትቶ የቅዱስ ጴጥሮስ ተከታይ ሆነ፡፡ ሐዋርያውም ቆርኔሌዎስን እጆቹን ጭኖ በእስክንድርያ አገር ላይ ኤጲስቆጶስነት ሾመው፡፡
❤ ቅዱስ ቆርኔሌዎስም በእስክንድርያ ወንጌልን እየሰበከ ብዙ ጣዖታት የሚያመልኩ ሰዎችን ወደ ቀናች ሃይማኖት መለሳቸው፡፡ እያስተማረ መኰንኑን ዲሜጥሮስን ጨምሮ ብዙዎችን አሕዛብ አጠመቃቸው። በፊታቸውም ብዙ ተአምራትን ያደርግ ነበር፡፡ እግዚአብሔርን ሲያገለግል ኖሮ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፈ፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስና ስንክሳር የኅዳር 23።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅዱስ_አብድዩ፦ ይህም ቅዱስ ከጠፍ በረሀ አቅራቢያ ከአለች ሱሳም ከምትባል አገር ካሉ ሰዎች ወገን ነው። ለነቢይ ቅዱስ ኤልያስ ደቀ መዝሙሩ ሁኖ ብዙ መከራን በእርሱ ላይ መጣውን ታግሦ ከመከራውም በትዕግሥቱ ዳነ።
❤ ይህም ኤልያስን የተለማመጠና ኤልያስም አዝኖለት አብሮት ወደ ንጉሥ አክዓብ የሔደለት ሦስተኛው የሃምሣ አለቃ ነው። ከዚህም በኋላ ምድራዊ ንጉሥን ማገልገልን ትቶ ነቢይን ሆነ የትንቢቱንም ወራት አድርሶ በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በነቢዩ አብድዩ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ ስንክሳር የኅዳር23።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለከ_ብእሴ_ሐዲስ_መርዓ። ቆርኔሌዎስ ዋሕድ እምነ አርድእት ፸ዓ። ኀቤከአ ከመ አስተበቊዐ። ይጠይቅ አርአያከ ወአምሳሊከ ኅቡአ። ኬንያ ሥዕልከ መዊቶ ተንሥአ"።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለአብድዩ_መንፈስ_አእምሮ_ለባሲ። በውሣጤ በዓት ዘኅብአ ነቢያተ እስራኤል ይሴሲ። እንዘ ያጤይቅ ምጽአቶ በከዊነ አምላክ ወብእሲ። ይቤ በአፉሁ እግዚአብሔር ነጋሢ። ለእለ ተኀርዩ መድኃኒተ በጽዮን እሬሲ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የኅዳር_23።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወበኀቤየሰ ፈድፋደ ክቡራን አዕርክቲከ እግዝኦ። ወፈድፋደ ፀንዑ እምቀደምቶሙ። እምኌቆሙ እምኆፃ ይበዝኁ"። መዝ 138፥17-18። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 11፥32-ፍ.ም፣ 2ኛ ጴጥ 1፥19-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 10፥23፥34። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 10፥32-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ቆርኔሌዎስና የነቢዩ የቅዱስ አብድዩ የዕረፍታቸው በዓልና የነቢያት (የገና) የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።
