cookie

Sizning foydalanuvchi tajribangizni yaxshilash uchun cookie-lardan foydalanamiz. Barchasini qabul qiling», bosing, cookie-lardan foydalanilishiga rozilik bildirishingiz talab qilinadi.

avatar

የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት

ይህ የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ልሳን ነው።

Ko'proq ko'rsatish
Reklama postlari
7 353
Obunachilar
+224 soatlar
+367 kunlar
+13830 kunlar

Ma'lumot yuklanmoqda...

Obunachilar o'sish tezligi

Ma'lumot yuklanmoqda...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ግንቦት ፳፩ ቀን ፳፱፲ወ፮ ዓ/ም ባደረገው የጠዋቱ የግንቦት ርክበ ካህናት የቅዱስ  ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ሰባት አበው ሊቃነ ጳጳሳትን በመወያያ አጀንዳ አርቃቂነት ሰየመ። በዚሁም መሰረት በመወያያ አጀንዳ አርቃቂነት የተሰየሙት ሰባት አበው ሊቃነ ጳጳሳት  ሕገ ቤተ ክርስቲያን በሚያዘው መሰረት ከቋሚ ሲኖዶስ ለምልአተ ጉባኤ እንዲቀርቡ የተመሩ እና ተጨማሪ የሚባሉ አጀንዳዎችን በመቅረጽ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የማስጸደቅ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴነት የተመረጡት አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚከተሉት ናቸው። 1.ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ 2.ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ 3.ብፁዕ አቡነ ማርቆስ 4. ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ 5. ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል 6. ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ 7. ብፁዕ አቡነ ገብርኤል
Hammasini ko'rsatish...
#አባታችን አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ መክፈቻ ላይ ያስተላለፉት መልእክት!!! +++++++++++++++++++++++ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ¶ብፁዕ አቡነ አብርሃም - የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሰሜን ጎጃምና የባሕር ዳር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ¶ብፁዕ አቡነ ሄኖክ - የዐዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ¶ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት! እግዚአብሔር አምላካችን በቤተ ክርስቲያን ላይ በየጊዜው የሚደርሰውን ፈተና በማስቻል ለዚኽ ሲኖዶሳዊ ምልአተ ጉባኤ እንኳን በሰላም አደረሰን!!! ‹‹አስተብቊዓክሙ አኃዊነ በስሙ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ትበሉ ኵልክሙ አሐደ ቃለ ወአሐደ ነገረ ወትኩኑ ፍጹማነ ወኢትትፋለጡ ወሀልዉ በአሐዱ ምክር ወበአሐዱ ልብ፤  ወንድሞች ሆይ ኹላችኁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ፣ በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብም የተባበራችኁ እንድትኾኑ እንጂ መለያየት በመኻከላችኁ እንዳይኾን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ›› (፩ኛ ቆሮ. ፩፥፲)፡፡  ቅዱስ ጳውሎስ ይኽንን መልእክት ለቆሮንቶስ ሰዎች ለመጻፍ ሲያስብ አንድ ዐቢይ ምክንያት እንዳለው ከመልእክቱ ይዘት መረዳት ይቻላል፤ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አንድነትንና ሰላምን ፍቅርንና መተባበርን ከምትሰብከው ወንጌለ መንግሥተ እግዚአብሔር ወጥተው ብዙ ርቀት ኼደዋል፤ አንድነቱ፣ ኅብረቱ መረዳዳቱ መተጋገዙና መተባበሩ ከመኻከላቸው ጠፍቷል፤ ሌላው ቀርቶ ቅዱስ ቊርባንን ለመቀበል በሚሰበሰቡበት ጊዜ እንኳ የሀብታምና የድሀ የሚል ክፍፍል ተፈጥሮ ቤተ ክርስቲያኗን አደጋ ላይ ጥሏል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይኽንን እና ይኽንን የመሳሰለ ፈተና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሥር እየሰደደ መምጣቱን በእጅጉ አሳስቦታል፤ ይኽ የሰላምና የአንድነት ጠንቅ የኾነው የመለያየት አዝማሚያ በጣም ሰፍቶ ቤተ ክርስቲያንን ከማፍረሱ በፊት በትምህርት በምክርና በተግሣጽ ማረም እንዳለበት ቅዱስ ጳውሎስ ተገንዝቧል፤ ርሱ ራሱም በአካል በመኻከላቸው ተገኝቶ ሊያስተካክላቸው ፈቃደኛ ነበረ፤ ነገር ግን ርሱ በዚኽ ጊዜ በሮም ውስጥ እስር ቤት ላይ ስለነበረ አልቻለም፤ የነበረው አማራጭ በጽሑፍ ማስተማርና መምከር ነውና፤ ይኽንን መልእክት ጽፎላቸዋል፡፡  ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት! ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዘላቂው የቤተ ክርስቲያን ፈተና ሲነግረን ‹‹ወበዓለምሰ ሀለወክሙ ትርከቡ ሕማመ፤ በዓለም ሳላችኁ መከራ አለባችኁ›› እንዳለው ቤተ ክርስቲያን ከፈተና ተለይታ አታውቅም፤ ፈተናውም ከተወሰነ አቅጣጫ ብቻ የሚመጣ ሳይኾን ከብዙ አቅጣጫ ይከባታል፤ የቤተ ክርስቲያን መከራ ከውጭ ብቻም አይደለም ከውስጥም እንጂ፤ ከባዕድ ብቻም አይደለም ከወዳጅም እንጂ፣ የወዳጅ ፈታኝ እንደሚብስም ታውቆ ያደረ ነገር ነው፤ ባዕዳውያን አይሁድ ጌታን ይዘው የገደሉ የውስጥ ሰው የኾነው ይሁዳ  በሰጣቸው ምልክት ነው፡፡ ከዚኽ አንጻር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአኹኑ ጊዜ በከባድ ፈተና ውስጥ እያለፈች ትገኛለች፤ እንደተነገረው የውጭው ፈተና ባይቀርላትም ከርሱ በላይ ግን በውስጧ የሚነሡ ፈተናዎች ተልእኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ እንቅፋት ኾነውባታል፤ ከጥንት ዠምሮ የነበረ፣ በእግዚአብሔር ቃል የተቃኘ፣ የጸሊአ ሢመትና የጸሊአ ንዋይ መንፈሳዊ ባህሏ ተዘንግቷል፤ በምትኩም ፍቅረ ሢመትና ፍቅረ ንዋይ ነግሧል፤ መለያየትና መነቃቀፍ እየሰፉ መጥተዋል፣ ሃይማኖታችንንና ባህላችንን የማይወክሉ ኃይለ ቃላት፣ ኃላፊነት በጎደለው አገላለጽ እየተሰነዘሩ በጎቻችንን አስበርግገዋል፤ ድርጊቶቹ በበጎቻችን ዘንድ የነበረንን ተሰሚነትና ተደማጭነት ሊቀንሱብን እየተንደረደሩ ነው፡፡ እነዚኽና እነዚኽ የመሳሰሉ ክሥተቶች በውስጣችን ሥር በሰደዱ ቁጥር ጉዳትን እያስከተሉ ነው፤ ሰዎች ከኦርቶዶክሳዊ ቀኖና እና ሥርዐት ባፈነገጠ መልኩ ራስን በራስ የመሾም አባዜ እየተለማመዱ ነው፤ እሽቅድምድሙም በዚኽ ዙሪያ አይሏል፤ በአጠቃላይ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን የፈተነ መለያየት በቤተ ክርስቲያናችንም ብቅ ጥልቅ እያለ እየፈተነን ነው፤ የፈተናው መንሥኤ ውጫዊ ሳንካ ባይጠፋበትም የውስጣችን ሰዎች ለርሱ ምቹ ኾነው መገኘታቸው አልቀረም፤ በመኾኑም ቤተ ክርስቲያናችን በዚኽ ፈተና የማይናቅ ጉዳት እየደረሰባት ነው፤ ከኹሉ በላይ ደግሞ ሰላሟና አንድነቷ ጥያቄ ላይ ወድቋል፡፡ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት! በሀብተ መንፈስ ቅዱስ ወልደን፣ በሀብተ ክህነት ሹመን፣ በመዐርገ ምንኩስና አልቀን በቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ያስቀመጥናቸው ሰዎች በውኑ "እርስ በርስዋ የምትለያይ ቤት…" የሚለውን አምላካዊ አስተምህሮ እንዴት ዘነጉት? ወይስ ድሮውንም ሳያውቁት ነው ኃላፊነቱ የተሰጣቸው? ወይስ ደግሞ ኾን ብለው ቃሉን ቸል ብለውታል? ኹሉም ውሉደ ክህነት ለዚኽ መልስ መስጠት ይጠበቅበታል፤ በመልካም አስተዳደርና በቂም በቀል እያሳበቡ ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ብሎም ለማፍረስ መሮጥ በማናቸውም መመዘኛ ሚዛን አይደፋም፤ ውሃም አያነሣም፡፡ ችግር ሲኖር በመወያየት በጥበብና በሕግ ማረም እንጂ የጋራ ችግርን ለተወሰነ አካል በመለጠፍና ርሱን ብቻ ተጠያቂ በማድረግ ንጹህ መኾን አይቻልም፤ ኹሉም ጓዳው ቢፈተሽ ከዚኽ የተለየ ነገር አይገኝም፤ አንድነትንና ሰላምን ግቡ ያደረገ ግምገማን መገምገም፣ መወያየትና መመካከር፣ ሕግንና ሥርዐትን ማእከል አድርጎ መሥራት ተመራጭ መፍትሔ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት አስከፊ በደል ተፈጽሟል አኹንም አልቆመም፤ ይኹን እንጂ በደል ዛሬ ብቻ የተዠመረ አድርገን አናስብ፤ ይብዛም ይነስ በደል ፊትም ነበረ፤ ዛሬም አለ፤ ነገም የተለየ ነገር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በደልን በካሣና በዕርቅ በይቅርታና በምሕረት መዝጋት፣ ተመሳሳይ በደል እንዳይፈጸም አስተማማኝ የኾነ ተቋማዊ ሥርዐትን ማበጀት መልካም ፈሊጥ ይኾናል፤ በደልንና ጥፋትን ምክንያት አድርገን እስከ ዘለቄታው መለያየትን መምረጥ ግን ራስን በራስ መጉዳት ይኾናል፤  ስለዚኽ ይኽ ቅዱስ ጉባኤ በዚኽ ዙሪያ በስፋትና በጥልቀት በመወያየት ሁሉንም ሊያስማማ በሚችል መልኩ ወደ ሰላምና ዕርቅ ሊያደርስ የሚችል ሥራ መሥራት ይኖርበታል፡፡   ብፀዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት! የማኅበረ ሰባችን ችግር በቤተ ክርስቲያን ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ በሀገር ደረጃ እየቀጠለ ያለው አለመግባባትም ለጠቅላላ ማኅበረ ሰባችን ፈተና ከኾነ ውሎ አድሯል፤ የቤተ ክርስቲያናችን ፈተና ምንጭ ከኾኑትም አንዱና ዕድል ሰጪ ይኽ ሀገራዊ አለመግባባት ነው፤ በዚኽ አለመግባባት ምክንያት ገዳማውያን መነኮሳት፤ መምህራን ካህናት ምእመናን አብያተ ክርስቲያናት ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በሰላም ወጥቶ መግባትም አጠራጣሪ ሆኗል፤ ይኽንን ችግር ለመፍታት የሚደረግ ጥረትም ጎልቶ አይታይም፡፡
Hammasini ko'rsatish...
በመኾኑም ይኽ ክሥተት እውን ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት የማንችል ሰዎች ነን ወይ? ለኛስ ከኛ የበለጠ ማን ይመጣልናል? የሚለውን ጥያቄ ልናነሣ ግድ ነው፤ ስለዚኽ ለሀገር ሕልውናና ድኅነት የሚበጅ ነገር እንዲመጣ ቤተ ክርስቲያን ባላት ሃይማኖታዊና ሰብአዊ ኃላፊነት ጠንክራ መሥራት ይጠበቅባታል፤ ከዚኽ በተረፈ ይኽ ዐቢይ ጉባኤ ወሳኝና ወቅታዊ እንዲኹም ሐዋርያዊና ቀኖናዊ በኾኑ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚበጁ ነገሮችን በማየት ጠቃሚ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ በዚኽ አጋጣሚ ለማሳሰብ እንወዳለን። በመጨረሻም ዓመታዊው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በእግዚአብሔር ፈቃድ የተጀመረ መኾኑን በመንፈስ ቅዱስ ስም እናበስራለን ፡፡ መልካም ጉባኤ ያደርግልን! እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!! ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!! አሜን፡፡ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ዐዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ +++++++++++++
Hammasini ko'rsatish...
03:12
Video unavailableShow in Telegram
Video from Menkir
Hammasini ko'rsatish...
Hammasini ko'rsatish...
የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሚዲያ ሰ/ት/ቤቶች ከ500 ሺህ ነድያን ጋር በበዓለ ትንሣኤ

✍️YouTube 👇

https://www.youtube.com/channel/UC83L...

✍️ FaceBook 👇

https://www.facebook.com/EOTC.GSSU

✍️Telegram 👇

https://t.me/EOTCNSSU

✍️Website👇

https://eotc-gssu.org/a/

✍️Twitter👇

https://twitter.com/tibeb_felege

“በእምነት ትንሣኤ፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር ትንሣኤ፣ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ትንሣኤ፣ በፍቅር ትንሣኤ፣ በሰላም ትንሣኤ፣ በይቅርታ ትንሣኤ፣ በመከባበር ትንሣኤ፣ በአንድነት ትንሣኤ፣ በመተሳሰብ ትንሣኤ ወዘተ በመሳሰሉ ሃይማኖታዊና ግብረ ገባዊነት ጸንተን መኖር ከቻልን የፊተኛው ትንሣኤ ማለት እሱ ነው፡፡ “    ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ #ቃለ_በረከት_ዘብፁዕ_ወቅዱስ_አቡነ_ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወስድስቱ ዓመተ ምሕረት፡፡ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤ በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ፡- የትንሣኤ ሙታን በኲር በመሆን ቀድሞ የተነሣው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ስድስት ዓመተ ምሕረት በዓለ ትንሣኤ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ! “ወይእዜኒ ክርስቶስ ቀደመ ተንሥኦ እምኲሎሙ ሰብእ ሙታን@ አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኲር ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል” (1 ቆሮ 05.!) በዛሬው ዕለት በከፍተኛ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የሚከበረው የጌታችን ትንሣኤ ለሰው ልጅ ያለው መንፈሳዊ ትርጉም እጅግ የላቀ ነው፤ እግዚአብሔር ፍጥረታትን በሙሉ በተለይም የሰው ልጅን ሲፈጥር በፍጹም ፍቅር ነው፡፡ ለዚህም የሰው በአርአያ እግዚአብሔር መፈጠር በቂ ማስረጃ ነው፤ ሰው በበደሉ ምክንያት ለሞት ቢዳረግም የእግዚአብሔር ፍጹም ፍቅር ጨርሶ አልተለየውም፤ እግዚአብሔር አንድ ቀን ሞትን ከሰው ጫንቃ አሽቀንጥሮ እንደሚጥል በየጊዜው ይገልጽ ነበረ፤ ያም በራሱ ልዩ ጥበብ እንደሚከናወን አረጋግጦ ለሰው ልጅ ተስፋውን አሳውቆ ነበር፤ ያም ልዩ ጥበብ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ዕውቀትና ጥበብ ድንበር የለውምና ከፍጥረተ ዓለም በፊት ሳይቀር የሰው ድኅነት በኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንደሚፈጸም በእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ነገር ነበረ፤ ጊዜው ሲደርስም በህላዌና በክዋኔ ከእርሱ ጋር አንድ የሆነ እግዚአብሐር ወልድ የሰውን ሰውነት ተዋሕዶ ሰውን የማዳን ስራውን አንድ ብሎ ጀመረ፡፡ ሰዎች በኃጢአትና በዲያብሎስ በደዌና በሞት ላይ ሥልጣን ያለው አዳኝ እሱ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ የማዳን ስራውን በመዋዕለ ሥጋዌው በስፋት አከናወነ፡፡ ልዩ ልዩ ደዌና በሽታ የሚያሠቃያቸውን ፈወሰ፤ ኃጢአተኞችን በይቅርታ ተቀበለ፤ ኃጢአታቸውንም ደመሰሰ፤ አጋንንትንም በትእዛዝ አስወጣ፤ ወደ ጥልቁም አሰመጣቸው፤ ዲያብሎስንም ድል ነሥቶ አባረረ፤ ሙታንንም አነሣ፤ በባሕር ላይ በእግሩ ተራመደ፤ ነፋሳትን ገሠጸ፤ በአምስት እንጀራ ከአምስት ሺሕ ሕዝብ በላይ መገበ፤ ውሀውንም ወደ ጠጅ ለወጠ፡፡ ሰውን ሁሉ በፍቅርና በይቅርታ ይቀበልና ያገለግል ነበር እንጂ በአንዱ ስንኳ የመጨከንና የማግለል መንፈስ አላሳየም፤ ይህ ሁሉ ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፍቅር ማሳያ ነበረ፡፡ በፍጥረት ሁሉ ላይ መለኮታዊ ሥልጣን እንዳለውም ማረጋገጫ ነበረ፤ መልእክቱም ዓለም መዳኛዋና አዳኝዋ እሱ መሆኑን አውቃ በአእምሮ እንድትከተለውና የድኅነቱ ተቋዳሽ እንድትሆን ማስቻል ነው፡፡ የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት! በእግዚአብሔር አሠራር ኃጢአት ያለ ቤዛነት አይሰረይም፤ በመሆኑም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ፍጹም ኃጢአተኛ ሆኖ ስለተገኘ ቤዛ ሆኖ የሚያድነው ያስፈልገው ነበር፤ ቤዛ መሆን የሚችለው አካል ደግሞ ራሱ ፍጹም ንጹህ መሆን ነበረበት፡፡ ከዚህም አንጻር በእግዚአብሔር ፊት ለሱ የሚመጥን ንጹህ ኣካል ከፍጡራን ወገን አልተገኘምና እሱ ራሱ ሰው ሆኖ የሰው ቤዛ ለመሆን በሥጋ ተገለጠ፤ በዚህም መሠረት የሰው ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ በመሰቀል ንጹህ ደሙን አፈሰሰ፤ በዚህ ደም ምክንያት የሰው ኃጢአት በሥርየት ተዘጋ፤ ለዚህም ነው ቅዱስ መጽሐፍ “ያለ ደም ሥርየት ወይም ይቅርታ የለም” ብሎ የሚነግረን፡፡ ከዚህ ደም መፍሰስ በኋላ ወደ ሲኦል ወርዶ በዚያ የነበሩ የኃጢአት ግዞተኞችን በሙሉ ፈትቶ ወደ ቀደመ ስፍራቸው ወደ ገነት መለሰ፤ ከስቅለተ ክርስቶስ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ያለው የሰው ኃጢአት በሙሉ በክርስቶስ ደም ይደመሰሳል፡፡ ሆኖም ይህ ሥርየት የሚገኘው በእምነት መሆኑን ቅዱስ መጽሐፍ አበክሮ ይነግረናል፣ በክርስቶስ አምኖ በደሙ የነጻ ሁሉ ክርስቶስ በተነሣው ዓይነት ትንሣኤ ይነሣል፡፡ የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት! የጌታችንን ትንሣኤ ስናከብር የኛንም ትንሣኤ በማሰብ ሊሆን ይገባል፤ ትልቁ ነገርም የኛን ትንሣኤ ማሰቡ ላይ ነው፤ ምክንያቱም የክርስቶስ ትንሣኤ ለኛ ተብሎ የተደረገ በመሆኑ ነው፡፡ የሱ ትንሣኤ ለኛ ትንሣኤ በኲር ነው፤ ማሳያና ማረጋገጫም ነው፤ እግዚአብሔር በየዕለቱ የሚፈልገው የኛን ትንሣኤ ማየት ነው፤ የኛ ትንሣኤ በአንድ ቀን በቅፅበት የሚሆን አይደለም፤ ትንሣኤያችን አምነን ስንጠመቅ ተጀምሮ ከመቃብር ስንነሣ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዛሬም እያንዳንዱ ሰው በትንሣኤ ሕይወት እንዲመላለስ ይጠራል፤ ምክንያቱም የኋለኛው ትንሣኤ የሚገኘው በፊተኛው ትንሣኤ እንደሆነ እግዚአብሔር በመጽሓፉ ነግሮናልና ነው፤ በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕ ነው፤ በሱ ላይ ሞት ሥልጣን የለውምና ነው፤ ለሰው ልጆች ተጠብቆልን ያለው ተስፋ ይህ ነው፡፡ ተስፋውን እውን ማድረግ የሚቻለውም በኛ ሃይማኖታዊና ተግባራዊ ተሳትፎ እንደዚሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ ደም ነው፤ የነገውን ትንሣኤ ተሳታፊ ለመሆን ዛሬ መነሣት ግድ ይላል፤ ይህም የሚቻል እንጂ የማይቻል አይደለም፡፡ በእምነት ትንሣኤ፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር ትንሣኤ፣ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ትንሣኤ፣ በፍቅር ትንሣኤ፣ በሰላም ትንሣኤ፣ በይቅርታ ትንሣኤ፣ በመከባበር ትንሣኤ፣ በአንድነት ትንሣኤ፣ በመተሳሰብ ትንሣኤ ወዘተ በመሳሰሉ ሃይማኖታዊና ግብረ ገባዊነት ጸንተን መኖር ከቻልን የፊተኛው ትንሣኤ ማለት እሱ ነው፡፡ ዛሬ እግዚአብሔር እያንዳንዳችን ይህንን ትንሣኤ እውን አድርገን ስንኖርና ስንመላለስ ማየት ይፈልጋል፡፡ በአንጻሩም ክሕደትን፣ ከሕገ ተፈጥሮ ያፈነገጠ ጸያፍ ተግባርን፣ ጥላቻን፣ ጦርነትን፣ መለያየትን፣ ራስን ብቻ መውደድን፣ መጨካከንን፣ ግብረ ኃጢአትን፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር ገንዘብ አለማድረግን፣ ፈጣሪን አለማመንን የተጸየፈ ምእመንን ማየት ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ኃጣውእ አፅራረ ትንሣኤ ናቸውና ነው፤ ኃጣውእ በምድርም በሰማይም የሰው ጠላቶች ናቸው፤ በምድር ለሥጋዊና መንፈሳዊ በሽታ ይዳርጉናል፡፡ በተለይም በእግዚአብሔር ፊት እጅግ አስጸያፊ የሆነው የነውረ ኃጢአት ርኲሰትና በጋብቻ ያልታሰረ ሩካቤ ሥጋ ትውልድን እንደ ቅጠል እያረገፈው እንደሆነ፣ ምንም ዓይነት ፈውስ ላልተገኘለት የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ ዋነኛ መተላፊያም ይህ ነውረ ኃጢአት እንደሆነ ተደጋግሞ ተነግሮአል፡፡ ይሁንና አሁንም ጥንቃቄ በጎደለው ድርጊት ስሕተቱ በመቀጠሉ በጦርነት ከሚያልቀው ሕዝብ ባልተናነሰ በዚህ ገዳይ በሽታ ብዙ ወገን እያለቀ ነውና እባካችሁ ሕዝበ እግዚአብሔር አንድ ለአንድ በመተሣሰርና በተቀደሰ የጋብቻ ሕይወት በመወሰን ትንሣኤያችንን እናብስር፡፡
Hammasini ko'rsatish...
በመጨረሻም በዓለ ትንሣኤ የእግዚብሔር ፍቅር መገለጫና የተስፋችን ማሳያ መሆኑን በመገንዘብ ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰው ልጆች ደኅንነት በአንድነት በመቆም ለተራቡት፣ ለተጠሙት፣ ለታረዙት፣ ለታመሙትና ለታሰሩትም ሁሉ ካለን ከፍለን በመስጠት ከኛ ጋራ በመንፈስና በሞራል በዓለ ትንሣኤውን እንዲያሳልፉ እናደርግ ዘንድ መንፈሳዊ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን። በድጋሚ በዓሉን የሰላም የዕርቅ የይቅርታ የትንሣኤ ኅሊና ወልቡና ያድርግልን፤   እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!! ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!! አሜን። አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
Hammasini ko'rsatish...