ማኅሌተ ጽጌ ዘይሰመይ ስሙ ፡፡
ማኅሌተ ጽጌ ከሁለት የግዕዝ ቃላት ጥምረት የተገኘ ነው፡፡ ማኅሌት ማለት ምስጋና፣ ማወደስ ማለት ሲኾን፤ ጽጌ ማለት ደግሞ አበባ፣ የፍሬ ምልክት፤ ውበት፣ ደም ግባት ያለው ማለት ነው፡፡ ማኅሌተ ጽጌ ተብሎ በአንድነት ሲነገር እና ሲተረጎም ደግሞ የአበባ ምስጋና ማለት ነው፡፡ ይህም ድንግል ማርያም እና የማሕፀኗ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ በጎ መዓዛ ባላቸው አበባዎችና ፍሬዎች እየተመሰሉ በዳዊት መዝሙር መጠን በ150 እንዲሁም እንደ መልክዕ በባለ 5ት መስመር ግጥም ተደርጎ የሚመሰገኑበት ምስጋና ማለት ነው፡፡
ጽጌ የዘመን (የወራት) ስምም ይኾናል፤ ዘመነ (ወርኃ) ጽጌ 40 ቀን ነው ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ነው፡፡ በዚህ ወራት የሚጾመው ጾም ጾመ ጽጌ ሲባል ጾሙም የፈቃድ ጾም ነው፡፡
በሀገራችን ዘመነ ክረምት አልፎ መስከረም 26 ቀን ዘመነ ጽጌ ይጀመራል፡፡ ዘመኑ አበቦች የሚያብቡበት እና ሜዳዎችን እና ተራሮችን የሚስጌጡበት ዘመን ነው፡፡ ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኝ ኹሉ በማኅሌተ ጽጌ እመቤታችንን በአበባ፥ ጌታችን በፍሬ፤ ወይም እመቤታችንን በፍሬ፥ ጌታችንን በአበባ እየተመሰሉ በምሥጢራዊ ግጥም ቀርበዋል፡፡ የማኅሌተ ጽጌ ደራሲ ሊቁ አባ ጽጌ ድንግልም የአበቦችን ነገር ከእመቤታችን ስደት ጋር እያደረገ፣ እጅግ አስደናቂ የሆኑ ታሪኮችን እያጣቀሰ ማኅሌተ ጽጌ (የአበባ ማኅሌት) የተባለውን ጸሎት ደርሷል፡፡
በዘመነ ጽጌ ወቅት ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ ማኅሌት ይቆማል፤ የሚቆመው ቁመትም አባ ጽጌ ድንግል የደረሱት ማኅሌተ ጽጌና ሰቈቃወ ድንግል ነው፡፡
አባ ጽጌ ድንግል ጓደኛቸው አባ ገብረማርያም የጀመሩትን ማኅሌተ ጽጌ አብነት በማድረግ በተለይም በጎንደር ዘመነ መንግሥት በእቴጌ ምንትዋብ ዘመን በጎንደር ደብረ ፀሐይ ቊስቊም ማርያም የማኅሌተ ጽጌ ቁመት መቆም ተጀምሯል፤ ቆይቶ ግን ይህ ማኅሌት ወደ ዘንሥር ዮሐንስ ማእከላ ለጎንደር ተዛውሮ እስከ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ድረስ ሲቆም ቆይቶ በመምህር ተክሌ ጊዜ ወደ መካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም ተዛውሮ በጎንደር አብያተ ክርስቲያናት በብቸኝነት በዚህችው ደብር የጎንደር አድባራት ሊቃውንት በመሰባሰብ ሲቆም ቆይቷል፤ በሌሎች የሃገራችን ክፍሎች አዲስ አበባን ጨምሮ ባሊ አብያተ ክርስቲያናትም የጽጌ ቁመት ተስፋፍቷል፡፡
ከ1999(2000)ዓ.ም. ጀምሮ በጎንደር ደብረ ፀሐይ ቊስቋምና የተወሰኑ የጎንደር አብያተ ክርስቲያናት የማኅሌተ ጽጌ ቁመት ጀምረዋል፤ ነገር ግን ቢጀምሩም ቅሉ አሁንም ግን የጎንደር አድባራት ሊቃውን በዋነኛነት በመካነ ነገሥት ግምጃቤት እየተሰባሰቡ የሚቆሙት የማኅሌተ ጽጌ ቁመት እጅግ በጣም ልብን የሚማርክና ኅሊናን የሚመስጥ በሃገራችን በኢትዮጵያ ደረጃም ተወዳዳሪ የሌለው ነው፡፡
በሌሎች የሃገራችን ክፍሎችና በመዲናችን በአዲስ አበባ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ የአገልጋይ ካህናት እጥረት በሌለባቸው ኹሉ ይቆማል፡፡
ሰቈቃወ ድንግል፤ ማለት እመቤታችን ከልጇ ከመድኀኔዓለም፥ ከአረጋዊ ዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር በስደቷ ወቅት ያየችውን መከራ፥ ልቅሶ፥ ዋይታ የሚዘከርበት የማኅሌተ ጽጌ አርኬ ነው፡፡ የሰቈቃወ ድንግልን ደራሲ በተመለከተ አባ ጽጌ ድንግል ደረሱት የሚሉ አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አባ ገብረ ኢየሱስ ዘገዳመ መጕና ወይም /አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ/ ወይም /አባ አርከ ሥሉስ/ ነው የደረሱት የሚሉም አሉ፡፡
ፎቶዎቹ፤
ቤተ ክርስቲያኖች
*ደብረ ጽጌ ገዳም፤ የአባ ጽጌ ደንግል ገዳም፤ ማኅሌተ ጽጌ የተደረሰበት፤ ወሎ ወግዲ አጠገብ፤ ኅዳር 6 ይከብራል፡፡
*ጎንደር ደብረ ፀሐይ ማርያም፤ ለበርካታ ዘመናት ማኅሌተ ጽጌ ይቆምባት የነበረች ታላቋ ደብር፡፡
*ጎንደር ዘንሥር ዮሐንስ፤ እስከ አፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመን የጎንደር የ44ቱ ታቦታት ሊቃውንት አየተሰበሰቡ ማኅሌተ ጽጌ ይቆሙበት የነበረ ደብር፡፡
*ጎንደር መካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም፤ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ እስከ አሁን ድረስ የጎንደር የ44ቱ ታቦታት ሊቃውንት አየተሰበሰቡ ማኅሌተ ጽጌ የሚቆሙባት ታላቂቷ ደብር፡፡
መምህራን
✤
መምህር ተክለማርያም ፤ የታለቁ ገዳም የማኅበረ ሥላሴ አበምኔት፤ የግምጃ ቤት ማርያም የሐዲሳት መምምህር፤ የድጓና የአቋቋምም መምህር፤ የጎንደር አድባራት በጋራ በመኾን የማኅሌተ ጽጌን ቁመት በአንድ ላይ ይቆሙበት ከነበረው ዘንሥር ማዕከላ ለጎንደር ዮሐንስ ወደ መካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ያመጡ ታላቁና ይህ ቀረሽ የሚይባሉ ሊቅ
✤፠
መምህር ክፍለ ማርያም ይመር፤ የመጻሕፍት ትርጓሜ ብርሃን፤ የየቀኑን ምሥጢር ከድጓ፣ ከጾመ ድጓ፣ ከዝማሬ መዋሥዕት፣ ከቅዳሴ፣ ከሰዐታት እየተመለከቱና እያውጣጡ ዚቁን ያዘጋጁ፤ ይህ ቀረሽ የማይባሉ የሊቆች ሊቅ፡፡
✤፠
ሊቀ ማዕምራን ወመጋቤ ሐዲስ ወሰንበት ባይነሳኝ፤ የጽጌ ዚቅን (የላይ ቤትን) አቀናብረው ያቀረቡ፤ የመጻሕፍተ ሐዲሳት ዋና ምስክርና የመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም ዋና አስተዳዳሪ፤ የሚያስተምሩት የሚኖሩ፤ ሊቅነትና ከትሕትና የያዙ፤ ከቀደምት ዐበይት ሊቃውንት መካታቻ የሆኑ፤ በቅርቡ ያረፉ፤ ጕባኤ እያሄዱ (እያስተማሩ) የሚያሳይ ፎቶ
✤፠ ሊቀ ማዕምራን ሐዋዝ ጥሩነህ፤ የግምጃ ቤት ማርያም አለቃ፤ ከላይ የተጠቀሱ ሊቃውንት የደረሱትን ዚቅ በእጅ ጽሑፍ ለትውልድ ያቆዩ ብልህ አስተዳዳሪ፡፡
✤፠
መምህር ክፍሌ ወለደ ጻድቅ፤ የጽጌ ዚቅን (ዚቅን) (የታች ቤትን) አቀናብረው ያቀረቡ፤ የደብረ ኃይል ወደብረ ጥበብ በዓታ የአቋቋም ዋና ምስክር የነበሩ፡፡ የአሁንን ዝክረ ቃልን በቀድሞ ስሙ አባጃሌ የተባለውን መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕትመት ያበቁ፡፡
✤
መምህር ላዕከ ጊዮርጊስ ደምሴ፤ የግምጃ ቤት ማርያም የሐዲሳት ምክትል መምህር የነበሩና ዜማ አዋቂ ምሁር፤ በወርኃ ጽጌ የዕለቱን ምሥጢር በተመለከተ ዚቅ እያዘጋጁ ለሊቃውንቱ ያቀርቡ የነበሩ
✣✤✣
መካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም፤ ለሃገራችን ኢትዮጵያና ለኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ባለውለታ የኾነች ጥንታዊት ቤ.ክ.፤ በደርቡሽ ወረራ ጊዜ መመህራን ጕባኤያችንን (ማስተማራችንን የታሪክ መዘክርነታችንን) ለቅቀን አንሔድም በማለት ሰማዕት የኾኑባት፡፡ **የብዙ ሊቃውንተ መፍለቂያ፤ እስከ ዐፄ ኀይለሥላሴ ዘመን ድረስ (ከሠለስቱ ምዕትና ከልደታ አብያተ ክርስቲያናት ጕባኤ ቤት በመቀጠል) በሃገራችን ኢትዮጵያ ብቸኛዋ የታች ቤት የመጻሕፍት /አንድምታ ትርጓሜ/ (የ4ቱ ጕባኤያት) ብቸኛ ማስመስከሪያ፡፡ /በአሁኑ ሰዓት በዋነኛነት በኢትጵያ ደረጃ የመጻሕፍተ ሐዲሳት የታች ቤት ትርጓሜ ዋና ማስመስከሪያ መካነ አእምሮ (university)/፡፡ እዲሁም የላይ ቤት የአቋቋም የዜማ የድርሰት ማዕከልና ዋና አብነት ነች፡፡ በውስጧ ተዓምረኛ የኾነች የእምቤታችን ሥዕል ይገኝባታል፡፡
/በፍኖተ ሕይወት ሰ.ት.ቤት።/
• Facebook 👉
m.facebook.com/FinoteHiwotSundaySchool
• Telegram 👉
t.me/finotehiwott
• Tiktok 👉
tiktok.com/@finotehiwot
• YouTube 👉
m.youtube.com/@finotehiwot1958