cookie

Sizning foydalanuvchi tajribangizni yaxshilash uchun cookie-lardan foydalanamiz. Barchasini qabul qiling», bosing, cookie-lardan foydalanilishiga rozilik bildirishingiz talab qilinadi.

avatar

የማርያም ልጆች ®

በቦሌ ኆኅተ ብርሃን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰ/ት/ቤት ስር የተካተተ የአከባቢው ወጣቶች የዓርብ ጉባኤ ተማሪዎች መማማሪያ ትክክለኛ ገጽ ። ትምህርቶች ፣ መዝሙር እና የተለያዩ ሃይማኖት ቀመስ ጽሑፎችን ከዚህ ያገኛሉ ለጥያቄ እና አስተያየት @kimi_king

Ko'proq ko'rsatish
Reklama postlari
361
Obunachilar
Ma'lumot yo'q24 soatlar
+37 kunlar
+230 kunlar

Ma'lumot yuklanmoqda...

Obunachilar o'sish tezligi

Ma'lumot yuklanmoqda...

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ ግንቦት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት +"+ ቅዱስ አርሳኒ +"+ =>ቅድስት ሃይማኖት እዚህ ዛሬ እኛ ጋር የደረሰችው በበርካታ ሰማዕታትና ጻድቃን ደም ነው:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግድግዳዎቿ እንጨትና ድንጋይ እንዳይመስሏችሁ:: አጽመ ቅዱሳን ነው እንጂ:: +ቅዱሳን ልዑለ ባሕርይ ክርስቶስን እንደ እኔ እና እንደ ዘመኑ ትውልድ በከንፈራቸው የሚሸነግሉ አልነበሩም:: እነርሱ በፍጹም ልባቸው ስለ ፍቅሩ ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጡ እንጂ:: በቅድስናቸው ከተመሰከረላቸው ቀደምት ቅዱሳን አንዱ ደግም ቅዱስ አርሳንዮስ ነው:: +ቅዱሱ የተወለደው በ345 ዓ/ም ሮም ውስጥ ነው:: በወጣትነቱ ይሕ ቀረህ የማይሉት የጥበብና የፍልስፍና ሰው ነበር:: በተለይ በትልቁ የሮም ቄሳር ቴዎዶስዮስ ዘመን በቤተ መንግስት አካባቢ የተከበረና የንጉሡ ልጆች መምሕር ነበር:: አኖሬዎስና አርቃዴዎስን ቀጥቶ ያሳደጋቸውም እርሱ ነበር:: +በድንግልና እስከ 40 ዓመቱ ድረስ ሮም ውስጥ ቆየ:: ከዚህ በኋላ ግን ስለ ሰማያዊ ነገሮች ሲያስብ መልዐኩ በሕልም ወደ ግብፅ ሒድ አለው:: በመጀመሪያ ወደ እስክንድርያ ቀጥሎ ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሒዶ መነኮሰ:: በቆይታ ግን ብሕትውና ምርጫው ሆነ:: +ቅዱስ አርሳኒ በእነዚሕ ነገሮቹ ይታወቃል:- 1.በምንም ምክንያት ከማንም ጋር አያወራም:: (ለ60 ዓመታት በአርምሞ ኑሯል) 2.በቤተ መቅደሱ ግድግዳ ተጠግቶ እንባውን ሲያፈስ የርሱን አካል አርሶ በመሬት ላይ ሲፈስ ይታይ ነበር:: ከእንባው ብዛት ቅንድቦቹ ተላልጠው አልቀው ነበር:: 3.በርካታ ድርሳናትን ደርሷል:: ብዙዎቹ ዛሬም ግብጽ ውስጥ አሉ:: 4.ሸንጎበቱን ወደ ደረቱ አዘንብሎ ስለሚቆም ማንንም ቀና ብሎ አያይም ነበር:: 5.ለጸሎት አመሻሽ 11:00 አካባቢ ላይ ይቆምና ጸሎቱን የሚጨርስ ፀሐይ ግንባሩን ስትመታው ነው:: 6.ሁል ጊዜ ራሱን "አንተ ሰነፍ (ሐካይ) እያለ ይገስጽ ነበር:: 7.በገዳማውያን ታሪክ የርሱን ያሕል በቁመቱ ረዥም አልተገኘም ይባላል:: የራሱ ጸጉር በጀርባው የወረደ ሲሆን ጽሕሙን በስዕሉ ላይ እንደምታዩት ነጭና እስከ መታጠቂያው የወረደ ነበር:: +እነዚህ ግን በጣም ጥቂቶቹ ናቸው:: +ቅዱስ አርሳንዮስ አካሉ በተጋድሎ ደቆ: ለ60 ዓመታት በግሩም መንፈሳዊነት ኑሮ በ100 ዓመቱ በዚሕች ዕለት ዐርፏል:: ❖አምላካችን እግዚአብሔር ከታላቁ የቅድስና ሰው አርሳኒ በረከት አይለየን:: =>ግንቦት 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ አርሳንዮስ - አርሳኒ (ጠቢብ ገዳማዊ) =>ወርኀዊ በዓላት 1.እግዚአብሔር አብ 2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላዕክት 3."99ኙ" ነገደ መላዕክት 4.ቅዱስ አስከናፍር 5."13ቱ" ግኁሳን አባቶች 6.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ =>+"+ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል:: ደግሞ ተገርቷል:: ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም:: የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው:: በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን:: በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን:: ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ:: ወንድሞቼ ሆይ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም:: +"+ (ያዕ. 3:7-11) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>> https://t.me/zikirekdusn
Hammasini ko'rsatish...
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ)

በዚህ ቻናል ዲ/ዮርዳኖስ የሚያስተምራቸው ወቅታዊ እና የነገረ ቅዱሳን (ዝክረ ቅዱሳን ትምህርቶችን ከእርሱ በመቀበል እናስተላልፋለን):: "ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖ ❖ ግንቦት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት +°✝ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ✝°+ =>ለቤተ ክርስቲያን የብርሃን ምሰሶ ስለሆነላት ስለ ታላቁ ሐዋርያዊ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? እንደ እኔ ያለ ኃጥእ: ለባሴ ሥጋና ገባሬ ንስሃ ስለሱ ሊናገር አይቻለውምና:: አባቶቻችን እንደ ነገሩን ስለ አፈ ወርቅ ለመናገር አፈ ወርቅ መሆን ያስፈልጋል:: ግን እስኪ በቅዱሱ አባት ምልጃ ጥቂት ልሞክር:: << ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ማን ነው? >> +ነገዱ ከሶርያ: የተወለደው በ347 ዓ/ም በእስክንድርያ ሲሆን አባቱ አስፋኒዶስ እናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ:: እነርሱ ደግ ቢሆኑ ይህንን እንቁ ልጅ እግዚአብሔር ሰጣቸው:: ዮሐንስ ለክርስቲያን እንደሚገባ በትምሕርትና በጥበብ አደገ:: ገና በሕጻንነቱ ወደ ግሪክ ሔዶ የዘመኑን ሳይንስ (ፍልስፍና) ከአፉ እስከ ገደፉ ተምሮ ተመልሷል:: +ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን ለየት ከሚያደርጉት ነገሮችም አንዱ ይሔው ነው:: በዘመናዊም ሆነ በመንፈሳዊ ትምሕርት ይህ ቀረህ የማይሉት ሊቅ የሆነው ገና በ15 ዓመቱ ነበር:: በ2 ወገን የተሳለ ሰይፍ በመሆኑ ስንኳን በሕይወተ ሥጋ እያለ ዛሬም ለንፉቃን ትልቅ የራስ ምታት ነው:: +ቅዱሱ ገና በ16 ዓመቱ ሃብት: ንብረት: ውበት: ክብርና እውቀት የሞላለት ቢሆንም ያለውን ሁሉ ለነዳያን ሰጥቶ መጻሕፍትን ብቻ ሰብስቦ ከባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ ጋር በርሃ ገባ:: ሰውነቱን በጾምና በጸሎት እየቀጣ በበርሃ ሲኖር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ዼጥሮስ ወደ እርሱ መጡ:: ሊቀ ሐዋርያት የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ ስልጣን ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ወንጌሉን ሰጥተው ተሰወሩት:: +ከዚህች እለት በኋላ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ባሕረ ምስጢራት ሆነ:: ብሉይ ከሐዲስ: ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ራዕየ ዮሐንስ ድረስ በአንድምታ ትርጉዋሜ ተነተናቸው:: በተለይ ሐዲስ ኪዳንን እየመላለሰ አመሰጠረው:: ቅዱስ ሕሊናው ሳይታክት: ንጹሕ እጆቹ ሳይዝሉ የጻፋቸው ድርሳናት: መልዕክታትና ትርጉዋሜያት ቢቆጠሩ አሥር ሺህ ሞሉ:: በእውነት ለዚህ አንክሮ ይገባል! የሚገርመው ይህን ሁሉ ሲሰራ እድሜው ገና ለጋ: ማዕርጉም ዲቁና ነበር:: +ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ቅስና ተሹሞ በስብከተ ወንጌል ብዙ ቦታዎችን አዳረሰ:: በቅድስናው ወደውታልና የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት:: አፈ ወርቅ ሲናገርም ሆነ ሲያስተምር እንኳን የሚያወራ ኮሽ የሚል የለም:: ከጣዕመ ትምሕርቱ የተነሳ ሕዝቡ በተደሞ ይሰሙት ነበር:: +ሲያስተምር ምድራዊው ሰው ይቅርና ልዑላኑ መላእክት ተሰብስበው ያደንቁት ነበር:: አንዴም እመቤታችን በሕዝብ መካከል " አፈ-ወርቅ" ብላ ጠርታዋለች:: ለዛም ነው አፈ-ወርቅ የሚባለው:: ቅዱሱ በሥልጣነ ቃሉ መልዐከ ሞትን ገስፆ 10 ዓመት አቁሞታል:: +ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ለሰው ፊት አያደላም:: በርሱ ዘንድ ንጉሥና ደሃ ነዳይ እኩል ነው:: ለሞት ያበቃውም ይሔው ነበር:: ምክንያቱም የወቅቱ ንግስት አውዶክስያ ያንዲት ድሃ መበለትን መሬት ቀምታ አልመልስም በማለቷ መክሮ አወገዛት:: እርሷ ግን ከኃጥአንና መናፍቃን ጋር መክራ 2 ጊዜ አጋዘችው:: +በተሰደደበት ፍሬ አፍርቶ: አስተምሮና አሳምኖ በ407 ዓ/ ም አርፏል:: ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ሳይጠግቡት እንደናፈቁት በ60 ዓመቱ አጡት:: በወቅቱ ታላቅ ሐዘንና ለቅሶ ተደረገ:: +አንድ ቀን የዘመኑ ደግ ንጉሥ አርቃድዮስ ግብር አገባ (ግብዣ አዘጋጀ):: በዚያች ሌሊት ደግሞ ቅዱሱ ሊቅ ታጥቆ ሲጸልይ ሳለ: አባ ማርዳሪ የሚባል ጻድቅ ደግሞ ከሰማይ 12ቱ ሊቃነ መላእክት (እነ ቅዱስ ሚካኤል) በግርማ ሲወርዱ ተመለከተ:: +ደንግጦ "ወዴት ናችሁ ጌቶቼ" ቢላቸው "ቁስጥንጥንያ: ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንሔዳለን:: እርሱ እመቤታችንን እንደሚያመሰግናት ጌታ ነግሮናልና" አሉት:: "እባካችሁ እኔም የአፈ ወርቅ ምስጋናው እንገለጥልኝ መርቁኝ" አላቸው:: ሊቃነ መላእክቱም መርቀውት ጐዳናቸውን ቀጠሉ:: +በማግስቱ በቤተ መንግስት ውስጥ ሊቃውንቱ: መሳፍንቱ: ዻዻሳቱ: ሕዝቡ ሁሉ ተሰብስበው ከድግሱ በሉ:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ግን በመንበሩ ተቀምጦ ነበር እንጂ አልበላም:: ድግሱ ሲጠናቀቅ ንጉሡ አርቃድዮስ ሊቁን "ጥያቄ አለኝ" ብሎ በጉባኤ መካከል ጠየቀው:: +"ምነው ወንጌላዊ ማቴዎስ 'ኢያዕመራ ዮሴፍ እስከ አመ ወለደት ወለደ ዘበኩራ-የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም' ማለቱ (ማቴ. 1:25) ስለ ምን ነው?" ቢለው ቅዱሱ ተነስቶ: በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይተረጉምለት ጀመር:: +"ድንግል ማርያም ንጹሕ ብርሌን ትመስላለች:: ብርሌ የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ቢያስገቡበት ቀለሙ አብሮ ይቀያየራል:: እመቤታችንም ጌታን ጸንሳለችና ሕብረ መለኮቱ ሲለዋወጥ መልኳ አብሮ ሲለዋወጥ እያየ ዮሴፍ ይደነግጥ ነበር:: +'እርሷ ማን ናት? በማሕጸኗ ያለውስ ማን ነው' እያለ ይጨነቅ ነበር:: ጌታን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ሕብረ መልክ ሆናለችና:: አስቀድሞ ማን እንደ ነበረች አላወቀም:: +አሁን ግን እርሷም ወላዲተ አምላክ: ልጇም አምላክ ዘበአማን መሆኗን አወቀ ማለት ነው" እያለ ሲተረጉም ሰምተው ሁሉም ሲያደንቁ: በዚያ የነበረች ስዕለ አድኅኖ "አፈ ወርቅ! ልሳነ ወርቅ! አፈ በረከት!" ስትል ተናገረች:: +ያን ጊዜ አርቃድዮስ የወርቅ ልሳን በሊቁና በስዕሏ ላይ አደረገ:: አፈ ወርቅ ግን ባጭር ታጥቆ "እሰግድ ለኪ! እሰግድ ለኪ! ወእዌድሰኪ . . ." ብሎ ዛሬ በተአምረ ማርያም የምናውቀውን ምስጋና ሰተት አድርጐ አደረሰላት:: ይህንን ምስጋናም ሊቃነ መላእክቱ ሰምተው እያደነቁ ወደ ሰማይ ወጥተዋል:: +ሊቁ ባረፈ በ35 ዓመቱ: በትንሹ ቴዎዶስዮስ ዘመን: ሥጋው ፈልሷል:: ወደ ቁስጥንጥንያ ሲደርስም ከናፍቆት የተነሳ ታላቅ ዝማሬና እንባ ተደርጓል:: አፈ ወርቅም ቀና ብሎ ሕዝቡን ባርኳል:: ✔ቅዱሱ ሲጠራ እንዲሕ ነው:- *ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ *አፈ በረከት *አፈ መዐር (ማር) *አፈ ሶከር (ስኳር) *አፈ አፈው (ሽቱ) *ልሳነ ወርቅ *የዓለም ሁሉ መምሕር *ርዕሰ ሊቃውንት *ዓምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ) *ሐዲስ ዳንኤል *ሊቀ ዻዻሳት ዘበርትዕ (እውነተኛው) *መምሕር ወመገስጽ ዘኢያደሉ ለገጽ *ጥዑመ ቃል - - - +እግዚአብሔር ከቅዱሱ በረከት አብዝቶ: አብዝቶ: አብዝቶ ይክፈለን:: +ዳግመኛ በዚህ ቀን ታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥጋቸው ፈልሷል:: ይሕ የተደረገው ጻድቁ ከረፉ ከ56 ዓመታት በኋላ ነው:: በዕለቱም ድንቅ ድንቅ ተአምራት ተፈጽመዋል:: +እናታችን ርሕርሕቷ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ደግሞ በዚሕ ቀን ስሟን ለጠራና መታሠቢያዋን ላደረገ የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብላለች:: ❖ቸር አምላካቸው ከሁለቱም ብሩሃን ቅዱሳኑ ክብር ያድለን::
Hammasini ko'rsatish...
❖ግንቦት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ (የዓለም ሁሉ መምሕር) 2አቡነ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ (ፍልሠታቸው) 3.ቅድስት እናታችን ክርስቶስ ሠምራ (ቃል ኪዳን የተቀበለችበት) 4.አባ አብርሃም ዘደብረ ሊባኖስ 5.ቅዱስ ዕንባቆም ነቢይ 6.እስክንድር ንጉሠ ኢትዮዽያ 7.ቅዱስ መስቀል (የተአምር በዓሉ) 8.አባታችን ያሬድ (የማቱሳላ አባት) 9.ቅዱስ ሚናስ ዲያቆን❖ወርኃዊ በዓላት 1፡ ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት2፡ ቅዱስ ድሜጥሮስ 3፡ ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ 4፡ ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድሌዎስ 5፡ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ 6፡ ቅዱስ ላሊበላ 7፡ ቅድስት መስቀል ክብራ ++"+ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም:: መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያናሩታል:: በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል:: መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ:: +"+ (ማቴ. 5:13-16) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>> https://t.me/zikirekdusn
Hammasini ko'rsatish...
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ)

በዚህ ቻናል ዲ/ዮርዳኖስ የሚያስተምራቸው ወቅታዊ እና የነገረ ቅዱሳን (ዝክረ ቅዱሳን ትምህርቶችን ከእርሱ በመቀበል እናስተላልፋለን):: "ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/

††† እንኳን ለታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ††† ††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ††† ††† ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ††† ††† ቅዱስ ያሬድ:- ከእግዚአብሔር ያገኘነው አባታችን : ክብራችን : ሞገሳችን ነውና በምን እንመስለዋለን? *አንደበቱ ጣፋጭ (ጥዑም):: *ልቡናው የቅድስና ማሕደር:: *ሕሊናው የምሥጢራት ሠረገላ ነው:: *እስከ አርያም ተነጥቆ የማይፈጸም ምሥጢርን የተመገበ ማን እንደርሱ! ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ እንደሚሉት:- "ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ : ሙሉ አካሏ ነው::" ††† የሊቁ ዜና ሕይወት በጥቂቱ ††† ††† ቅዱስ ያሬድ የተወለደው በ505 ዓ/ም አክሱም አካባቢ ሲሆን እናቱ ክርስቲና (ታኡክልያ) አባቱ ደግሞ ይስሐቅ (አብድዩ) ይባላሉ:: ሊቁ በሕጻንነቱ ምሥጢር (ትምሕርት) አልገባው ብሎ ይቸገር ነበር:: ትምሕርት እንቢ ያለው ሰነፍ ስለ ነበር አይደለም:: በጥበበ እግዚአብሔር እንጂ:: ምን ትምሕርት ባይገባው ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር:: ልቡናው ደግሞ በእመቤታችንና በልጇ ፍቅር የታሠረ ነበር:: አንድ ቀን ግን መምሕሩ የነገሩት ቀለም አልያዝሕ አለው:: ሲፈትኑትም ባለመመለሱ ተገረፈ:: ዱላው በጣም ስለ ተሰማው ቅዱሱ ከመምሕሩ ኮብልሎ ማይ ኪራሕ አካባቢ ሲደርስ ደክሞት አርፎ እግዚአብሔር ትጋትንና ተስፋ አለመቁረጥን ከትል አስተማረው:: ትሏ ስድስት ጊዜ ወድቃ በሰባተኛው ፍሬዋን ስትበላት ተመልክቷልና:: ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ መምሕሩ ተመልሶ : ይቅርታ ጠይቆ ትምሕርት ጀመረ:: ሊቁም ትጋትንና ጸሎትን ከሰጊድ ጋር አበዛ:: እግዚአብሔር ደግሞ በድንግል እናቱ አማካኝነት የምሥጢር ጽዋን አጠጣው:: ካህኑ ያሬድ እንዲያ አልገባህ ያለው ምስጢር ተገልጦለት በጥቂት ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ወሰነ:: በምሥጢር ባሕርም ይዋኝ ጀመር:: ያን ጊዜ ሰማያዊ ዜማ አልተገለጠም ነበርና በጸሎት ላይ ሳለ ተደሞ መጣበት:: ሦስት መላእክት በሦስት ወፎች አምሳል መጥተው አነጋገሩት:: ድንገትም ነጥቀው ወደ ሰማያት : ወደ ልዑላኑ መላእክት ዘንድ አደረሱት:: ሊቁ በሰማያት ልዩ ምሥጢር : ልዩ ምስጋናና ልዩ ዜማን አዳመጠ:: ይሕንን ምስጋና ብዙ ቅዱሳን ቢሰሙትም ቅዱስ ያሬድ ግን ይዞት እንዲወርድ ተፈቀደለት:: ሊቁ ወደ ምድር ተመልሶ በታላቅ ተመስጦ አክሱም ጽዮን ውስጥ በሃሌታ አመሰገነ:: ሕዝቡና ንጉሡም ከጣዕሙ የተነሳ አደነቁ:: ቅዱስ ያሬድ ለተወሰነ ጊዜ በአክሱምና ደብረ ዳሞ ሲያገለግል ቆይቶ : ከመሬት ክንድ ከስንዝር ከፍ ብሎ ለእመቤታችን አንቀጸ ብርሃንን ደርሶላት ከሃገሩ ወጣ:: ††† ቅዱስ ያሬድ በቀሪ የሕይወቱ ዘመናት:- 1. አምስት ያሕል መጻሕፍትን ጽፏል:: 2. በጣና ቂርቆስ : በዙር አባና በሌሎችም ቦታዎች ወንበር ዘርግቶ ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርቷል:: 3.በሰሜን ተራሮች አካባቢ በትጋሃ መላእክትና በተባሕትዎ ኑሯል:: ††† በ576 (571) ዓ/ም በተወለደ በ71 ዓመቱ በዚህች ቀን ተሰውሯል:: ††† አባቶቻችን:- *ጥዑመ ልሳን *ንሕብ *ሊቀ ሊቃውንት *የሱራፌል አምሳያ *የቤተ ክርስቲያን እንዚራ *ካህነ ስብሐት *መዘምር ዘበድርሳን *ማኅሌታይ *ልዑለ ስብከት እያሉ ይጠሩታል:: ††† የቅዱሱ ጸሎትና በረከት ሃገራችንን ከክፉው ሁሉ ይጠብቅልን:: ††† ግንቦት 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 1.ቅዱስ ያሬድ ካህን ወማኅሌታይ 2.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ 3.ቅዱሳን ክርስቲናና ይስሐቅ (የቅዱስ ያሬድ ወላጆች) 4.ቅድስት ታውክልያ እናታችን (ንግሥናን ንቃ ሰማዕት የሆነች) 5.ቅድስት ኤፎምያ ሰማዕት 6.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት 7.ቅድስት አናሲማ ገዳማዊት 8.አባ በፍኑትዮስ ገዳማዊ 9.አባ አሴር ሰማዕት (ኢትዮዽያዊ) 10.አባ በኪሞስ ጻድቅ ††† ወርሐዊ በዓላት 1.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት 2.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት 3.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና ††† "እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ:: እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ:: በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደሆነ አላውቅም:: እግዚአብሔር ያውቃል:: ወደ ገነት ተነጠቀ:: ሰውም ሊናገር የማይገባውን: የማይነገረውን ቃል ሰማ::" ††† (2ቆሮ. 12:2-5) ††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር ††† https://t.me/zikirekdus
Hammasini ko'rsatish...
ዝክረ ቅዱሳን ዘናዝሬት

በዚህ ቻናል ዲ/ዮርዳኖስ የሚያስተምራቸው ወቅታዊ እና የነገረ ቅዱሳን (ዝክረ ቅዱሳን ትምህርቶችን ከእርሱ በመቀበል እናስተላልፋለን):: "ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/ ጥያቄ እና አስተያየት ካላቹ

https://t.me/+Jmm8mYFhFpFkNTM0

††† እንኳን ለቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ††† ††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ††† ††† ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ††† ††† አናንያ : አዛርያና ሚሳኤልን እንዲያው በቀድሞው አጠራር ሠለስቱ ደቂቅ (ሦስቱ ሕጻናት) እንላቸዋለን እንጂ ለእኛስ በእድሜም : በጸጋም : በትሩፋትም አባቶቻችን ናቸው:: ቅዱሳኑ የወቅቱ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጆች ናቸው:: ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ ሕዝቡን ሲማርክ አብረው ተማርከው ባቢሎን ወርደዋል:: ንጉሡ ከምርኮ ወጣቶች ለቤተ መንግስት ሲመርጥ ሦስቱ ቅዱሳንና ዳንኤል ተመርጠው የምቾት ሕይወት ተዘጋጅቶላቸው ነበር:: ነገር ግን በምግብና በአምልኮ ከአሕዛብ ጋር መተባበርን አልፈለጉምና ምርጫቸው ጾምና ጸሎት ከቆሎ ጋር ሆነ:: ምንም እንኳ በቤተ መንግስት ውስጥ ቢኖሩ : ምንም የነገሥታት ልጆች ቢሆኑ ለእነርሱ ከእግዚአብሔር ፍቅር የተሻለ አልነበረምና በጥሬ ቆሎ ተወስነው ኖሩ:: አምላካቸው ከሃሊ ነውና በውበትም ሆነ በጥበብ በባቢሎን ምድር ከነርሱ የሚደርስ አልተገኘም:: ንጉሡም በባቢሎንና በአውራጃዋ ላይ ሾማቸው:: ስማቸውንም በአማልክቱ ስም ሲድራቅ : ሚሳቅና አብደናጐ አላቸው:: ከነገር ሁሉ በኋላ አሕዛብ ቀንተውባቸዋልና የክፋት አዋጅን አሳወጁ:: ናቡከደነጾር 60 ክንድ ቁመት ያለውን የወርቅ ምስል አቁሞ "ስገዱ" ቢላቸው አይሆንም በማለታቸው ተቃጥለው እንዲሞቱ እሳት ተፈረደባቸው:: ነበልባሉ ከጉድጓዱ ወደ ላይ 49 ክንድ ቢነድም ቅንጣት ያህል ፍርሃት አልጎበኛቸውም:: ወደ እሳቱም ሲጥሏቸው መልዐከ አድኅኖ ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ አዳናቸው:: ከሆነው ነገር የተነሳ አሕዛብ አፈሩ:: ናቡከደነጾር ግን ከዙፋኑ ተነስቶ የቅዱሳኑን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ:: ከዚያች ቀን በኋላ አናንያ : አዛርያና ሚሳኤል በአት አጽንተው : በጾምና በጸሎት ተወስነው ኑረዋል:: ነፍሳቸው ከሥጋቸው ስትለይ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆኗል:: ቅዱስ ዳንኤልና ናቡከደነጾር ተሯሩጠው ቢሄዱ ሦስቱም በአንድነት ዐርፈው ተገኝተዋል:: ንጉሡ በእጅጉ ይወዳቸው ነበርና በወርቅ በተለበጠ ሳጥን ቀብሯቸዋል:: ስሞት ከመካከላቸው ቅበሩኝ በማለቱ ዛሬ ድረስ ለበቁ አባቶች የአራቱ መቃብር ባቢሎን ውስጥ ይታያል:: ቅዱሳን አናንያ : አዛርያና ሚሳኤል (ሲድራቅ : ሚሳቅና አብደናጐ) ያረፉት ግንቦት 10 ቀን ሲሆን ዘመኑም ከክርስቶስ 500 ዓመት በፊት ነው:: ††† አምላካቸው ከእሳት ባወጣቸው ቀንም:- "ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ:: ስቡሕኒ ውዕቱ ወልዑልኒ ውዕቱ ለዓለም::" የሚለውን ምስጋና ፈጣሪ ገልጾላቸው ደርሰውታል:: (በእሳቱ ውስጥ ሆነው ተናግረውታል:: ) ድርሰታቸው 2 ወገን ሲሆን ባለ ስድስት አንቀጹ ምስጋናቸው ከ600 ዓመት በኋላ ክርስቶስ እንደሚወለድ የሚያሳይ ነው:: ሌላኛውና 33 አንቀጾች ያሉት ምስጋናቸው ደግሞ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ለ33 ዓመታት እንደሚመላለስ ያጠይቃል:: ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ካረፉ ከ900 ዓመታት በኋላ (ማለትም ከክርስቶስ ልደት በ400 ዓመታት) ታላቁ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ቤተ ክርስቲያንን አንጾላቸው ነበርና አጽማቸውን ሊያገኝ ተመኘ:: ወዳጁን ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ጠርቶ "አባ! አጽመ ቅዱሳንን ባቢሎን ወርደህ አምጣልኝ?" አለው:: ቅዱሱ ሐጺር ዮሐንስም በደመና ተጭኖ ባቢሎን ገባ:: በቅዱሳኑ መቃብር ፊትም ሰግዶ አለቀሰ:: ሠለስቱ ደቂቅም "ወዳጃችን! ምን ሆንክ?" አሉት:: ቅዱሱም መልሶ "ወደ ግብጽ እንሒድ:: አባ ቴዎፍሎስ ይፈልጋቹሃል" አላቸው:: እነሱም "ለቅዱሱ ቴዎፍሎስ እንዲህ በለው:: እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ:: ግን አጽማችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ባቢሎንን አይለቅም:: ለክብርህ ግን እንመጣለን::" "ለምልክትም ይሆን ዘንድ መብራት ሳታበራ በሌሊት ጠብቀን በለው" ብለው ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ባርከው ሸኙት:: ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርም መጥቶ መልእክቱን አደረሰ:: በዕለተ ቅዳሴ ቤታቸው ቅዱሳን:- ቴዎፍሎስ : ቄርሎስ : ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርና ሌሎችም ከምዕመናን ጋር በጨለማ ሳሉ ቤተ ክርስቲያኑ ቦግ ብሎ በራ:: እጅግ የሚደነቅ ብርሃንም ከበባቸው:: በብርሃኑ መካከል ሠለስቱ ደቂቅ ሲያልፉ በጐ መዓዛ ሸተተ:: ሕዝቡም በደስታና በዝማሬ የቅዱሳኑን ቅዳሴ ቤት አክብሯል:: ††† በረከታቸው ይደርብን:: ††† ግንቦት 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 1.ሠለስቱ ደቂቅ ቅዱሳን (አናንያ : አዛርያና ሚሳኤል) 2.ቅዱስ አብርሃም ጸራቢ (ሰማዕት) 3.አባ ሚካኤል ገዳማዊ 4.አባ ይስሐቅ ግብጻዊ ††† ወርሐዊ በዓላት 1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ 2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ 3.ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጻድቅ ንጉሥ 4.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ 5.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ) 6.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት 7.ቅዱስ ዕፀ መስቀል ††† "ናቡከደነፆርም መልሶ:- መልአኩን የላከ : ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን : የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን : በእርሱ የታመኑትን ባርያዎቹን ያዳነ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ::" ††† (ዳን. 3:28) ††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Hammasini ko'rsatish...
††† እንኳን ለእናታችን ቅድስት እሌኒ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ††† ††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ††† ††† እሌኒ ንግሥት ††† ††† ቅድስት እሌኒ የታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ እናቱና እግዚአብሔር ለበጐ አገልግሎት የጠራት ቡርክት ሴት (ንግሥት) ናት:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- የቅድስቲቱ ሃገረ ሙላዷ ሮሃ (ሶርያ) አካባቢ ነው:: ነገዷ ከእሥራኤል ዝርዋን እንደሆነም ይነገራል:: ጣልያኖች "Helena" : በእንግሊዝኛው "Helen" ይሏታል:: እኛ ደግሞ "እሌኒ" እንላታለን:: ትርጓሜው "ጥሩ ምንጭ" : አንድም "ውብና ደግ ሴት" ማለት ነው:: ቅድስት እሌኒ በመልካም ክርስትና አድጋ እንደ ቤተ ክርስቲያን መተርጉማን ተርቢኖስ የሚባል ነጋዴ አግብታ ነበር:: ወቅቱም ዘመነ ሰማዕታት ነበር:: በማይሆን ነገር ጠርጥሮ ባሕር ላይ ጥሏት ንጉሥ ቁንስጣ አግኝቷታል:: እርሱም የበራንጥያ (የኋላዋ ቁስጥንጥንያ) ንጉሥ ነበር:: ቅድስት እሌኒ ከቁንስጣ የተባረከ ልጅን ወለደች:: ቆስጠንጢኖስ አለችው:: በልቡናው ፍቅርን : ርሕራሄን : መልካምነትን እየዘራች አሳደገችው:: ቅዱሱ አባቱ በሞተ ጊዜ ተተክቶ ነገሠ:: ቅድስት እሌኒንም ንግሥት አደረጋት:: ያንን የአርባ ዓመት ግፍ በአዋጅ አስቀርቶ ለክርስቲያኖች ነፃነትን : ክብርን በይፋ ሰጠ:: አንድ : ሁለት ብለን የማንቆጥረውን ውለታ ለምዕመናን ዋለ:: ከነዚህ መልካም ምግባራቱ ጀርባ ታዲያ ቅድስት እናቱ ነበረች:: ቅድስት እሌኒ ጾምን : ጸሎትን ከማዘውተሯ ባሻገር አጽመ ሰማዕታትን ትሰበስብ : አብያተ ክርስቲያንን ታሳንጽ : ለነዳያንም ትራራ ነበር:: በኢየሩሳሌምና አካባቢው ብቻ ከሰማንያ በላይ አብያተ መቃድስ አሳንጻለች:: እነዚህንም በወርቅና በእንቁ ለብጣቸዋለች:: በዘመኗ መጨረሻም የጌታችንን ቅዱስ ዕፀ መስቀል ከተቀበረበት አውጥታ ለዓለም በረከትን አስገኝታለች:: እናታችን ቅድስት እሌኒ እንዲህ በቅድስና ተመላልሳ በሰማንያ ዓመቷ በ330ዎቹ አካባቢ ዐርፋለች:: ቤተ ክርስቲያናችንም ስለ ቅድስናዋና ውለታዋ በዓል ሠርታ : ታቦት ቀርፃ ስታከብራት ትኖራለች:: ††† ከቅድስት እናታችን ምልጃና በረከት አምላካችን ያድለን:: ††† ግንቦት 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 1.ቅድስት እሌኒ ንግሥት 2.ቅዱስ ስልዋኖስ ††† ወርኀዊ በዓላት 1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት) 2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮጵያዊ) 3.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ) 4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን 5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ) 6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት) ††† "ነገር ግን ለበጐ ነገር ጥበበኞች : ለክፉትም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ:: የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል:: የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን::" ††† (ሮሜ. ፲፮፥፲፱) ††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር ††† https://t.me/zikirekdusn
Hammasini ko'rsatish...
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ)

በዚህ ቻናል ዲ/ዮርዳኖስ የሚያስተምራቸው ወቅታዊ እና የነገረ ቅዱሳን (ዝክረ ቅዱሳን ትምህርቶችን ከእርሱ በመቀበል እናስተላልፋለን):: "ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/

††† እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ በዓለ ዕርገት እና ለጻድቁ አባ ዳንኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ††† ††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ††† ††† ዕርገተ እግዚእ ††† ††† ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓለ ዕርገትን 2 ጊዜ ታከብራለች:: አንዱ "ጥንተ በዓል" : ሁለተኛው ደግሞ "የቀመር በዓል" ይሠኛል:: ጥንተ በዓል ማለት ጌታችን በትክክል ያረገበትን ቀን ያመለክታል:: የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በኪነ ጥበቡ (በሕማሙ : በሞቱ) ዓለምን አድኖ: 40 ቀን ለሐዋርያቱ መጽሐፈ ኪዳንን: ትምሕርተ ኅቡዓትን አስተምሯቸዋል:: በ40ኛው ቀን 120ውን ቤተሰብ ይዟቸው ወደ ቢታንያ ወጣ:: በዚያም እስከ ሊቀ ዽዽስና ድረስ ሾሟቸው : ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡም አዟቸው የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ጠብቁ ብሏቸዋል:: እየባረካቸው በተዋሐደው ሥጋ ወደ ሰማያዊ ዙፋኑ አርጓል:: ሰማያት: ምድር: ደመናት: ነፋሳት: መባርቅትና መላእክት: ፍጥረት በሙሉ አመስግኗል:: አይሁድ መናፍቃን ዕርገቱን ምትሐት ነው እንዳይሉ: ጌታችን ትንሳኤውን አማናዊ እንደሆነ ለማስረዳት በ40ኛው ቀን ዐረገ:: አንድም ራስ ባለበት ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊኖሩ ይገባልና ጌታችን ዕርገቱን በገሃድ አደረገው:: "ዐርገ እግዚእ ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን ንጹሐን" እንዲል:: ††† ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ:: ወእግዚእነ በቃለ ቀርን:: ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ:: ††† (መዝ. 46:6) ††† ታላቁ አባ ዳንኤል ††† ††† ይህ ቅዱስ አባት ስም አጠራሩ ክቡር ነው:: በሁሉ ነገሩ የተቀደሰ የገዳማውያን መብራትም ነው:: ከተረፈ ንጹሕ ሕይወቱ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን አይቷልና:: አባ ዳንኤል በትውልድ ግብጻዊ ሲሆን ዓለምን ንቆ (መንኖ) ገዳም የገባው ገና በወጣትነቱ ነው:: ጊዜውም ዘመነ ጻድቃን (በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን) ነበር:: በገዳመ አስቄጥስ እና በደብረ ሲሐት ይታወቃል:: ታላቋ መካነ ቅዱሳን ገዳመ ሲሐት ዛሬም ድረስ በስሙ የምትጠራ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ እጅግ ለብዙ ዘመናት በውስጧ ተጋድሎ ፍሬ ስላፈራባት : ደቀ መዛሙርትን በቅድስና ስለ ወለደባት ነው:: ስለዚህም ዛሬም ድረስ "አባ ዳንኤል ዘደብረ ሲሐት" ተብሎ ሲጠራ ይኖራል:: ሌላኛው ስሙ ደግሞ "ዘገዳመ አስቄጥስ" ይሰኛል:: ገዳመ አስቄጥስ የታላቁ ቅዱስ መቃርስ ርስት ሲሆን በዓለም በስፋትም : ብዙ ቅዱሳንን በማፍራትም አንደኛ የሆነ ገዳም ነው:: በዚህ ገዳም ላይ አበ ምኔት ሆኖ የሚሾሙ አበው ሁሌም የብቃት መዓርግ ላይ የደረሱ ሲሆኑ ክብራቸው ከፓትርያርክ በላይ ነው:: አባ ዳንኤልም ከብዙ የቅድስና ዓመታት በኋላ በአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ እልፍ አእላፍ መነኮሳትን በጽድቅ መንገድ መርቷል:: ቅዱሱ ከትጋቱ የተነሳ ለምግብና ለእንቅልፍ ጊዜ አልነበረውም:: ቀን ቀን መነኮሳቱን ሲናዝዝ : ድውያንን ሲፈውስ : ሥርዓተ ገዳምን ሲቆጣጠር ይውላል:: ልክ ሲመሽ ጭው ወዳለውና ስውራን ወደ ሚገኙበት በርሃ ይወጣል:: +በዚያም ሙሉውን ሌሊት የተሰወሩ አባቶችን ሲፈልግ ያድር ነበር:: በዚህም ምክንያት የብዙ ስውራንን ገድል የጻፈ ሲሆን ባረፉ ጊዜም ገንዞ በመቅበር በረከታቸውን ተሳትፏል:: ታላቅ ሙያንም ፈጽሟል:: እርሱ ገንዞ ቀብሮ : ዜናቸውን ከጻፈላቸው ሥውራን ቅዱሳንም እንደ አብነት እሥራኤላዊቷን ቅድስት ዓመተ ክርስቶስን (ለ38 ዓመት ራቁቷን በሥውር የኖረች) እና ቅድስት በጥሪቃ ንግሥትን (መንግስቷን ትታ በሥውር የኖረች ናት) መጥቀስ እንችላለን:: ከዚህ ባለፈም አባ ዳንኤል በሰው ዘንድ የተናቁትንም ማክበርን ያውቅበታል:: ለምሳሌ በሴቶች ገዳም እብድ ናት ተብላ በበር የተጣለችውን ቅድስት አናሲማን : በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ዻዻሳቱ ሳይቀር "እብድ ነው" ብለው የናቁትን ቅዱስ ምሕርካን: እብድ ሳይሆኑ ራሳቸውን የሠወሩ ቅዱሳን መሆናቸውን ገልጧል:: አባ ዳንኤል ሐዋርያዊም ነበር:: በጊዜው ጦማረ ልዮን የሚባል የኑፋቄ ደብዳቤ ይላክ ነበርና ለዚህ ኬልቄዶናዊ ኑፋቄ በትጋት ምላሽ ይሰጥ ነበር:: አንድ ቀንም በንጉሥ ትዕዛዝ ኑፋቄው በእርሱ ገዳም ሊነበብ ሲል ቅዱሱ ከወታደሩ ቀምቶ ስለ ቀደደው ለሞት እስኪደርስ ደብድበውታል:: ጻድቁ አባ ዳንኤል አንዴ አውሎጊስ የሚባልድሃ ድንጋይ ጠርቦ እንግዳ ሲቀበል ተመልክቶ "ጌታ ሆይ! ይህንን ደግ ሰው ለምን ድሃ አደረከው?" ሲል በፈጣሪ ሥራ ገባ:: ጌታም እንደ ወትሮው በገሃድ ተገልጦ "በነፍስህ ትዋሰዋለህ?" አለው:: "አዎ ጌታየ" ስላለው ጌታችን ለአውሎጊስ ሃብትን ሰጠው:: ግን ወዲያው የጦር አለቃና ጨካኝ ሰው ሆነ:: ጻድቁ ወሬውን ሰምቶ ሊጠይቅ ቢሔድ የአውሎጊስ ወታደሮች ደበደቡት:: ጌታችንም አባ ዳንኤልን ወደ ፍርድ ዙፋኑ አቅርቦ "ወዳጄን መልስልኝ" አለው:: እመ ብርሃን ግን ቀርባ የልጇን እግር ሳመች:: "ልጄ ሆይ ማር!" አለችው:: ጌታም "እሺ" ብሎ ጻድቁን ወደ በአቱ: አውሎጊስን ወደ ቀደመ ግብሩ መለሳቸው:: የአባ ዳንኤል ድንቁ ብዙ ነው:: ሌላው ቢቀር ሽፍታ አባ ዳንኤልን መስሎ ወደ ደናግል ገዳም ሊዘርፍ : በማታለል ገባ:: ደናግሉም ጻድቁ መስሏቸው እግሩን አጥበው ዐይነ ስውሯን ቢቀቧት ዐይኗ በርቷል:: ሽፍታውም ደንግጦ ንስሃ ገብቷል:: አባ ዳንኤል ግን ተጋድሎውን ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል:: ††† በተረፈው ግን ከቅድስና ሕይወቱ ባሻገር:- 1.በገዳመ አስቄጥስ (ግብጽ) አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ ባሳየው ትጋት:: 2.በሃይማኖት ጠበቃነቱ በደረሰበት ድብደባና ስደት:: 3.ብዙ የበርሃ ቅዱሳንን በየበአታቸው እየዞረ በመቅበሩ:: 4.የብዙ ስውራን ቅዱሳንን ዜና ሕይወት በመሰብሰቡ:: 5.በየጊዜው በእግዚአብሔር ኃይል ይፈጽማቸው በነበሩ ተአምራት:: እና 6.ለድንግል እመቤታችን ማርያም በነበረው ልዩ ፍቅር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታከብረዋለች:: ††† ቸር አምላክ ክርስቶስ ከዕርገቱና ከጻድቁ በረከት አይለየን:: ††† ግንቦት 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 1.ቅዱሳን የጌታ ቤተሰብ (120ው) 2.ቅዱስ አባ ዳንኤል ጻድቅ 3.ቅዱስ ዮሐንስ ሰማዕት 4.ቅዱስ መክሲሞስ መስተጋድል 5.አቡነ ዮሐኒ ዘደብረ ዳሞ (አቡነ ተክለ ሃይማኖትንና አቡነ ኢየሱስ ሞዐን ለምንኩስና ያበቁ) ††† ወርሐዊ በዓላት 1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት 2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ) 3.አባ ብሶይ (ቢሾይ) 4.አቡነ ኪሮስ 5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን 6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት) ††† "እስከ ቢታንያም አወጣቸው:: እጆቹንም አንስቶ ባረካቸው:: ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ:: ወደ ሰማይም ዐረገ:: እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ:: ዘወትርም እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እየባረኩ በመቅደስ ኖሩ::" ††† (ሉቃ. 24:50-53) ††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Hammasini ko'rsatish...
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ እንኳን አደረሳችሁ ❖ ❖ ግንቦት 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✝✞✝ ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ✝✞✝ =>በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት ቀጥሎ የቅዱስ አትናቴዎስን ያሕል ስለ ሃይማኖት የተዋጋ ቅዱስ ፈልጐ ማግኘት አይቻልም:: ❖ቅዱስ አትናቴዎስ ማን ነው? +ቅዱስ አትናቴዎስ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት በዘመነ ሰማዕታት መጠናቀቂያ በ300 አካባቢ(296) እስክንድርያ ግብፅ ውስጥ ነው የተወለደው:: ወላጆቹ አረማውያን በመሆናቸው ክርስትናን አልተማረም ነበር:: +ሕጻን እያለ ለጭዋታ ከቤቱ ሲወጣ የክርስቲያን ልጆች ሃይማኖታዊ ጨዋታ ሲጫወቱ ተመለከተ:: ሊቀላቀላቸው ቢፈልግም ክርስቲያን ባለመሆኑ ከለከሉት:: አትናቴዎስም ክርስቲያን ልሁንና አጫውቱኝ ብሏቸው እሺ ስላሉት ሕጻናቱ ዕጣ ተጣጣሉ:: +ላንዱ ቄስ: ላንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው ለአትናቴዎስ ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕጻናት ይሰግዱለት ጀመር:: በአጋጣሚ ሕጻናቱ ይሕንን ሁሉ ሲያደርጉ የወቅቱ ፓትርያርክ ቅዱስ እለ እስክንድሮስ በመገረም ያያቸው ነበርና ለሕጻኑ አትናቴዎስ ትንቢት ተናገረለት:: +ከዚያም የአትናቴዎስ አባቱ ሲሞት ሊቀ ዻዻሳቱ ከእናቱ ወስዶ አጥምቆ: የሚገባውን መንፈሳዊ ትምሕርት ሁሉ በልቡናው ላይ ቀረጸበት:: ከዚሕ በኋላ ዲቁናን ሹሞ አስተምር አለው:: ምንም ሕጻን ቢሆንም ከሊቅነቱ: ከአመላለሱና ከአንደበቱ ጣፋጭነት የተነሳ የሰማው ሁሉ ይደነቅ ነበር:: ጸጋ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ አድራለችና:: +ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ዲቁና በተሾመ ወራት አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ 318ቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ ጸሐፊ አድርገው ሾሙት:: በጊዜውም በዕድሜ የስንት ጊዜ ትልቁ የሚሆነውን አርዮስን ተከራክሮ ምላሽ አሳጣው:: ✝ቅዱስ አትናቴዎስ ከሊቃውንቱ ጋር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ: እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ መሠከረ:: ጸሎተ ሃይማኖትንም ያረቀቀው እርሱ ነው:: +ከዚሕ በኋላ የእስክንድርያ (የግብፅ) 20ኛ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ:: ቤተ ክርስቲያንን በመልካም እረኝነት ለ48 ዓመታት ሲመግብ ብዙ መከራዎችን ተቀበለ:: ለ5 ጊዜ ከመንበሩ አፈናቅለው ወደ በርሃ ሲያግዙት በስደት ከ15 ዓመታት በላይ አሳልፏል:: +በተሰደደባቸው ቦታዎች መከራን እየተቀበለ ያላመኑትን አሳምኗል:: በጎቹ እንዳይባዝኑበት ደግሞ በጦማር (በደብዳቤ) ይጠብቃቸው ነበር:: ዛሬ በሃይማኖተ አበው የምናገኘው ቃለ ሃይማኖት በዚሕ ዘመን የተጻፈ ነው:: +በወቅቱ የነበረው ንጉሥ (ትንሹ ቆስጠንጢኖስ) የአባቱን (ታላቁ ቆስጠንጢኖስን) ዕረፍት ተከትሎ ነገሠ:: +ወዲያውም አርዮሳዊ መናፍቅ ሆነ:: ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችንም ያሳድድ ገባ:: ከአበው ቅዱሳን መካከል ግን የዚህ መከራ ቀዳሚው ገፈት ቀማሽ ታላቁ ሊቅ ቅዱስ አንትናቴዎስ ነበር:: +በተለይ አንድ ጊዜ ንጉሡ ቅዱሱን ወደ በርሃ አግዞ: መናፍቅ ዻዻስ በግብጽ ሹሞ: ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ ሲያስገድል: ቅዱሱን ለ6 ዓመታት አሰቃየው:: የወገኖቹ (የልጆቹን) ስቃይ የሰማው ቅዱስ አትናቴዎስ ግን በድፍረት ወደ ቤተ መንግስት ገብቶ ተናገረው:: +2 አማራጭን አቅርቦ "ወይ ግደለኝና እንደ አባቶቼ ሰማዕት ልሁን: ካልሆነ ግን ወደ መንጐቼ (ምዕመናን) መልሰኝ" አለው:: መናፍቁ ንጉሥም ቢገድለው ብጥብጥ እንደሚነሳ ስለሚያውቅ በስልት ሊያጠፋው ወሰነ:: +ቀዛፊ: መቅዘፊያ: ምግብና ውሃ በሌላት ጀልባ ውስጥ ከቶም ሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ጣለው:: ድንገት ግን ከሰማይ ጌታችን መላእክቱን አስከትሎ ወረደ:: +ሚካኤልና ገብርኤል ባሕሩን እየቀዘፍ: ሌሎች መላእክት እየመገቡት በዚህች ቀን እስክንድርያ (ግብጽ) አድርሰውት ተሠውረዋል:: ሕዝቡም በታላቅ ሐሴት እየዘመሩ አባታቸውን ተቀብለውታል:: +ሐዋርያዊው ቅዱስ ስለ ኦርቶዶክስ ተዋግቶ: ብዙ ስቃይንም ተቀብሎ በ373 ዓ/ም አካባቢ አርፏል:: ቤተ ክስርቲያን ☞"ሊቀ ሊቃውንት: ☞ርዕሰ ሊቃውንት: ☞የቤተ ክርስቲያን (የምዕመናን) ሐኪም (Doctor of the Church): ☞ሐዋርያዊ" ብላ ታከብረዋለች:: =>አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሊቁ በረከት አይለየን:: በምልጃውም ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን:: =>ግንቦት 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ 2.የባሕታውያን አለቃ ታላቁ አባ ሲኖዳ (ጽንሰቱ) 3.ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ (ሃብቱን: ንብረቱን: ልብሱን ሳይቀር መጽውቶ ራቁቱን የተገኘ ደግ ሰው ነው) 4.አባ ሐርስዮስ ገዳማዊ =>ወርሐዊ በዓላት 1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ) 2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ 3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ) 4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት 5.አባ ባውላ ገዳማዊ 6.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ) =>+"+ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዐን ናቸው:: መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና:: ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ:: ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ:: ሐሴትም አድርጉ:: ከእናንተ በፊት የነበሩ ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና:: +"+ (ማቴ. 5:10) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>> https://t.me/zikirekdusn
Hammasini ko'rsatish...
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ)

በዚህ ቻናል ዲ/ዮርዳኖስ የሚያስተምራቸው ወቅታዊ እና የነገረ ቅዱሳን (ዝክረ ቅዱሳን ትምህርቶችን ከእርሱ በመቀበል እናስተላልፋለን):: "ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ❖ ግንቦት 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት +"+ አባ መቃርስ ካልዕ +"+ +ይህ ቅዱስ "መቃርዮስ: መቃርስ: መቃሬም" ይባላል:: ትርጉሙ በ3ቱም መንገድ አይለወጥም:: ምክንያቱም ሥርወ ቃሉ በዮናኒ ልሳን "ብጹዕ: ንዑድ: ክቡር" ማለት ነውና:: +ከስሙ ቀጥሎ "ካልዕ-2ኛው": አንዳንዴ ደግሞ "እስክንድርያዊ" እየተባለ ይጠራል:: "ካልዕ-2ኛው" የሚባለው ከቀዳሚው (ታላቁ መቃርስ) ለመለየት ሲሆን "እስክንድርያ" ደግሞ ተወልዶ ያደገባት ሃገር ናት:: +አባ መቃርስ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ ገዳማዊ: ጻድቅና ትሩፈ-ምግባር ነው:: በዓለም ለ40 ዓመት ሲኖር እንደ ሕጉ ፈጣሪውን ደስ ያሰኘ ሰው ነው:: ጻድቃን እንደ ከዋክብት በበዙበት በዚያ ዘመን የታላቁ መቃርስን ዜና ሰምቷልና ይህቺን ክፉ ዓለም ከነግሳንግሷ ንቋት በርሃ ገብቷል:: +እንደሚገባ ሥርዓተ ገዳምን ጠብቆ: ለአበው ታዞ: በጾም: በጸሎት: በትሕትናና በስግደት ተጠምዶ ቢያገኘው ፈጣሪ አከበረው:: በዚያ ጊዜም ለታላቁ ገዳመ አስቄጥስ መናንያን አበ ምኔት ሊሆን መረጡት:: +እርሱም እረኝነትን ያውቃልና በጐቹን (መነኮሳትን) ከተኩላ (ሰይጣናት) ይጠብቅ ዘንድ ብዙ ተጋ:: ከብቃቱ የተነሳም ሳያስታጉል: ሳይበላ: ሳይጠጣና ሳይቀመጥ እስከ 40 ቀን ይጸልይ ነበር:: ሲጸልይ ደግሞ በልቡ እየተቃጠለ በፍቅረ ክርስቶስ ነበርና አጋንንት ይርዱለት ነበር:: +እርሱ ጸሎት ሲጀምርም በገዳሙ ዙሪያ ያሉ አጋንንት እየጮሁ ይሸሹ ነበር:: ከተጋድሎው ጽናትና ከትሕትናው ብዛት የተነሳ ያዩት ትዕቢተኞች ሁሉ ይገሠጹ ነበር:: በዘመኑም ብዙ ተአምራትን ሠርቷል:: +አንድ ቀን በበዓቱ ሳለ ጅብ መጥታ ተማጸነችው:: አብሯት ወደ ዋሻዋ ቢሔድ ልጆቿ በሙሉ ዓይነ ሥውራን ሆነው አገኛቸው:: እርሱም ወደ መሬት ምራቁን እትፍ ብሎ በጭቃ ለውሶ ቢቀባቸው የሁሉም ዐይናቸው በርቷል:: +ስለ ውለታውም ጅቢቱ የበግ ቆዳ እየጐተተች አምጥታ ሰጥታዋለች:: (ከሰው ልጅ በቀር እንስሳት ውለታን አይረሱምና) ቅዱስ መቃርስም ለወትሮው ባዶው መሬት (አፈር) ላይ ይተኛ የነበረው ከዚያ ቀን በኋላ በአጐዛው ላይ የሚተኛ ሁኗል:: +በሃገሩ እስክንድርያም ለ2 ዓመታት ዝናብ በመጥፋቱ ሕዝቡ ተጨንቆ ነበርና "ናልን" ሲሉ መልዕክት ላኩበት:: እርሱ መጥቶ ሲጸልይም መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ ጣለ:: ዝናቡም ያለ ማቆም ለ2 ቀናት በመዝነቡ ሕዝቡ ፈርተው "አባታችን ስለ ኃጢአታችን እንዳንጠፋ ለምንልን?" አሉት:: እርሱም በጸሎቱ (በፈጣሪው ኃይል) እንደ ወደዱት ዝናቡን አቁሞላቸዋል:: +የአባ መቃርስን ዜና ሕይወትና ተአምራት ተናግሬ አልፈጽመውም:: ግን አንዲት ብቻ ላክል:: ሁሌ ሳስበው ስለሚገርመኝም ነው:: +ብዙዎቻችን የጌታችን ሥጋና ደም አንቀበልም:: ለምን ያከበርነውና የፈራነው አስመስለን ኃጢአትን ለመጥገብ ቦታን ( አጋጣሚን) ስለምንፈልግ:: በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዶቻችን መለኮት የተዋሐደውን የጌታ ሥጋና ደም እንደ ተርታ ነገር (ያለ ጥንቃቄ) ስንቀበል ይታያል:: 2ቱም ግን ስሕተት ነው:: +ፈርተን (ፍርሃቱ ጤነኛ ባይሆንም) ስለ ራቅን በፍርድ ቀን ማምለጥ አንችልም:: "ሥጋየን ያልበላ: ደሜንም ያልጠጣ የዘለዓለም ሕይወት የለውም" ይለናልና:: (ዮሐ. 6:52) +በድፍረት ለምንቀበልም ሥጋው እሳት ሁኖ እንዳይበላን: ደሙም ባሕር ሆኖ እንዳያሰጥመን ልናከብረው ይገባናል:: "ሳይገባው ከጌታ ሥጋና ደም የተቀበለ የጌታ ሥጋ ዕዳ አለበት" ይለናልና:: (1ቆሮ. 11:27) << ታዲያ የሚሻለው ለሁላችንም ንስሃ ገብቶ: በፍርሃት ሆኖ መቅረቡ ነው:: >> +ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና አባ መቃርስ ወደ በርሃ እንደ ገባ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎ ነበር:: ቅዱሱ ይህንን እያሰበ ለ60 ዓመታት ምራቁን ሳይተፋ ኑሯል:: ለዚያ አይደል አበው "ብታከብሩት ያከብራቹሃል" ያሉት:: +ሊቃውንቱም ይህንን ሲያደንቁ:- "ኢታስተማስልዎ ለቁርባን ከመ ሕብስት ዕራቆ:: አኮኑ ሥጋ መለኮት ዘይትላጸቆ:: መቃርዮስ አብ ዕበየ ቁርባን ለአጠይቆ:: ድኅረ ተወክፈ በአሚን እንበለ ያብዕ ናፍቆ:: መጠነ ዓመታት ስሳ ኢተፍአ ምራቆ::" ብለዋል:: +ቅዱስ መቃርስም በ100 ዓመቱ በ5ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በዚህች ቀን ዐርፏል:: ❖ጌታችን ከክብሩ: ከበረከቱ አይለየን:: =>ግንቦት 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ አባ መቃርስ ገዳማዊ 2.እናታችን ቅድስት ሰሎሜ ኢትዮዽያዊት 3.አባ ይስሐቅ ጻድቅ 4.ቅድስት ዲላጊና 4 ሴት ልጆቿ (ሰማዕታት) 5.ቅዱስ ዳናስዮስ ሰማዕት 6.ቅዱስ በንደላዖስ ሰማዕት (የታላቁ ኤስድሮስ አባት) 7.አባ አሞን ጻድቅ (ዽዽስናን አልፈልግም ብሎ የሸሸ አባት) =>ወርኀዊ በዓላት 1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም 2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን 3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል 4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ 5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ 6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ 7.ቅድስት ሰሎሜ 8.አባ አርከ ሥሉስ 9.አባ ጽጌ ድንግል 10.ቅድስት አርሴማ ድንግል =>+"+ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው:: እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ:: ሥጋዬ እውነተኛ መብል: ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና:: ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል:: እኔም በርሱ እኖራለሁ:: +"+ (ዮሐ. 6:53-56) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>> https://t.me/zikirekdusn
Hammasini ko'rsatish...
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ)

በዚህ ቻናል ዲ/ዮርዳኖስ የሚያስተምራቸው ወቅታዊ እና የነገረ ቅዱሳን (ዝክረ ቅዱሳን ትምህርቶችን ከእርሱ በመቀበል እናስተላልፋለን):: "ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/

††† እንኳን ለነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ኤርምያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ††† ††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ††† ††† ቅዱስ ኤርምያስ ††† ††† ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤርምያስ ከዐበይት ነቢያት አንዱ ሲሆን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስድስት መቶ አካባቢ የነበረ ነቢይ ነው:: አባቱ ኬልቅዩ ይባላል:: ከካህናተ እስራኤል አንዱ ነበር:: እግዚአብሔር ኤርምያስን የጠራው ገና በሕፃንነቱ ነበር:: "ከእናትህ ማኅጸን ሳትወጣ መርጬሃለሁ: ቀድሼሃለሁ" ሲልም በገሃድ መስክሮለታል:: (ኤር. 1:5) ከቅዱሳን ነቢያት እንደ ኤርምያስ የተሰቃየና ያለቀሰ የለም:: ከሰባ ዘመናት በላይ ስለ ወገኖቹ አልቅሷልና ሊቃውንት "ነቢየ ብካይ" (ባለ እንባው ነቢይ) ይሉታል:: ዘመኑ ዘመነ-ኃጢአት (ዘመነ ዐጸባ) ነበር:: እሥራኤላውያን ከመሪዎቻቸው ከነ ሴዴቅያስ ጋር በክፋት ተባብረውም ነበርና ኤርምያስን አልሰሙትም:: ይልቁኑ ክፉ ቦታ ውስጥ አስረው አሰቃዩት:: እግዚአብሔር ግን በኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ አማካኝነት ከመከራው አዳነው:: የተሰበከላቸውን የንስሐ ጥሪ አልሰሙምና ስልምናሦር የሚባል የአሕዛብ ንጉሥ መጥቶ አሥሩን ነገድ ማርኮ በ722 አሦር (ነነዌ) አወረዳቸው:: በኋላ ደግሞ በኃይለኝነቱ የታወቀው የባቢሎን ንጉሥ ይማርካቸው ዘንድ ወደ ሁለቱ ነገድ ኢየሩሳሌም ደረሰ:: ኤርምያስ ወደ ከተማዋ ዳር ወጥቶ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አለቀሰ:: ከቤተ መቅደስ ንዋያት እኩሉን ለምድር አደራ ሰጣትና ሸሸገችው:: ነቢዩ የተናገረው አይቀርምና ንጉሡ ናቡከደነጾር እኩሉን ገድሎ: እኩሉንም ማርኮ: ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ: የአሕዛብ መዘባበቻ አድርጐ በ586 ባቢሎን አወረዳቸው:: ቅዱስ ኤርምያስን ግን ትሩፋን (ከመከራው የተረፉት) ይዘውት ወደ ግብጽ ወረዱ እንጂ አልተማረከም:: በዚያም ተአምራትን አድርጐ አራዊትን አጥፍቷቸዋል:: ትንሽ ቆይቶ ግን እውነተኛ አባት : ነቢይ : መምሕርም ነውና ወደ ሕዝቡ (ወደ ባቢሎን) ወረደ:: በዚያም ትንቢትን እየተናገረ : ሕዝቡን ከሰባ ዓመታት በኋላ ወደ ሐገራቸው እንደሚመለሱ እያስተማራቸው በባቢሎን ቆይቷል:: ያለ በደሉም በመከራቸው ተካፋይ ሆኗል:: ሰባው ዘመን ሲፈጸም እግዚአብሔር እንደ ቃል ኪዳኑ በኤርምያስ መሪነት እሥራኤል ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ:: አሁንም ግን ክፋታቸውን ይተው ዘንድ ፈቃደኞች አልነበሩምና ኤርምያስ ገሠጻቸው:: በዚህ ተበሳጭተው ሊወግሩት ሲሉ ጸጋ በዝቶለት : ምሥጢርም ሰፍቶለት ስለ ነገረ ሥጋዌ (ስለ ክርስቶስ የማዳን ሥራ) አምልቶና አጉልቶ ትንቢት ተናገረ:: አንዴ ልቡናቸው ታውሮ ኤርምያስ ነው ብለው ድንጋዩን በድንጋይ ሲወግሩት ውለዋል:: ዘግይቶ ግን ኤርምያስ ራሱን ገለጠላቸው:: ስለ እነርሱ ሲል ሰባ ዘመን ያለቀሰውንና ምትክ የሌለውን አባታቸውን ወግረው ገደሉት:: ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኤርምያስ ሃምሳ ሁለት ምዕራፎች ያሉት ሐረገ ትንቢት ተናግሯል / ጽፏል:: ዜና ሕይወቱ ከራሱ የትንቢት መጽሐፍ በተጨማሪ በተረፈ ኤርምያስ : በመጽሐፈ ባሮክ : በገድለ ኤርምያስ : በዜና ብጹዐን : በመጽሐፈ ስንክሳርም ተጽፏል:: ††† ቸር እግዚአብሔር በኤርምያስ ምልጃ ሃገራችንን ከጥፋት: ሕዝቦቿን ከስደትና ከመቅሰፍት ይሰውርልን:: ††† ግንቦት 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 1.ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ (ከታላላቆቹ ነቢያት አንዱ) ††† ወርኀዊ በዓላት 1.ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት 2.ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ 3.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ 4.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮጵያዊ 5.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ ††† "ኢየሩሳሌም ሆይ ነቢያትን የምትገድል : ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትወግር : ዶሮ ጫጩቶቿን ከክንፎቿ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም:: እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላቹሃል:: እላችሁአለሁና : በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ እንግዲህ ወዲህ አታዩኝም::" (ማቴ. ፳፫፥፴፯-፴፱) ††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር ††† https://t.me/zikirekdusn
Hammasini ko'rsatish...
ዝክረ ቅዱሳን ማኅበረ ቅዱስ ዳዊት - ዘብሔረ ጎንደር (ዲ/ዮርዳኖስ አበበ)

በዚህ ቻናል ዲ/ዮርዳኖስ የሚያስተምራቸው ወቅታዊ እና የነገረ ቅዱሳን (ዝክረ ቅዱሳን ትምህርቶችን ከእርሱ በመቀበል እናስተላልፋለን):: "ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/