cookie

Ми використовуємо файли cookie для покращення вашого досвіду перегляду. Натиснувши «Прийняти все», ви погоджуєтеся на використання файлів cookie.

avatar

✞ገድለ ቅዱሳን✞

✝✞ከኢ/ኦ/ተዋህዶ ቤ/ክ ላይ የተገኙ የየዕለቱ የቅዱሳን አባቶቻችን እና የቅዱሳት እናቶቻችን ገድል ይነገርበታል✝

Більше
Рекламні дописи
16 141Підписники
+224 години
+97 днів
-8030 днів

Триває завантаження даних...

Приріст підписників

Триває завантаження даних...

✞✝✞ ሚያዝያ 18 ✞✝✞ ✞✝✞ እንኩዋን ለጻድቅና ሰማዕት "አባ ዼጥሮስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✝✞ *+" ጻድቅና ሰማዕት አባ ዼጥሮስ "+* =>ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው:: ሰው ለፈጣሪው ሰውነቱን ሊያስገዛ: ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል:: ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው:: +ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል:: የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው:: "አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም: ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግስተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው:: +እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ! በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ:: ክርስትና ግን መሞትን እንጂ መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም:: +እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ: የሚረግሟችሁን መርቁ: ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ" ብሎናልና:: (ማቴ. 5:44) ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ ይመጣል:: +በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል ይገባናል:: የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን እንድንጸና ነውና:: ❖ቅዱስ አባ ጴጥሮስም ከዘመነ ሰማዕታት ፍሬዎች አንዱ ነው፡፡ በዚያ የመከራ ዘመን (3ኛው መቶ ክ/ዘ) ግብፅና ሶርያ በብዙ መከራ ውስጥ ሳሉ በርካታ ቅዱሳን ተሰውተዋል፡፡ በተለይ በግብፅ ደግሞ ብዙ ንጹሐን አበውና ቅዱሳት አንስት መከራውን ታግሠው ለክብር በቅተዋል፡፡ ❖ከእነዚሁ አንዱ የሆነው አባ ጴጥሮስ ገና ከልጅነቱ ጣዕመ ክርስትናን የተማረው ከአሳዳጊው (ከአክስቱ) ነበር፡፡ በፍፁም ልቡ የሚወደው ወንድም እና ባልንጀራም ነበረው፡፡ ስሙ ደግሞ አባ ብሶይ ይሰኛል፡፡ ሁለቱም በበጎ ምግባር ተኮትኩተው ፡ ዓለምንም ንቀው በርሃ ገብተው ፡ በጾም በጸሎት ተወስነው ብዙጊዜ ኑረዋል፡፡ ❖በመከራው ዘመን ደግሞ ክርስቶስን ስላመለኩ ብቻ ተከሰው ታስረዋል፡፡ ተገርፈው ተደብድበዋል፡፡ ጭንቅ ስቃይንም በትእግስት አሳልፈዋል፡፡ በፍጻሜውም አባ ጴጥሮስ በዚህች ቀን ተሰውቶ ለክብር አክሊል በቅቷል፡፡ ወዳጁና ወንድሙ ቅዱስ ብሶይም በክብር ገንዞ ቀብሮታል፡፡ =>አምላከ ሰማዕታት ከጸናች ገድላቸው ፡ ከበዛች ትእግስታቸው ፡ ከፍጹም በረከታቸው ያሳትፈን፡፡ =>ሚያዝያ 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ አውሳብዮስ ሰማዕት 2.አባ ዼጥሮስ ሰማዕት 3.ሰማዕታተ ጠርሴስ =>ወርሐዊ በዓላት 1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ 2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን) 3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ 4.ማር ያዕቆብ ግብፃዊ =>+"+ በድካም: አብዝቼ በመገረፍ: አብዝቼ በመታሠር: አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ:: በድካምና በጥረት: ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት: በራብና በጥም: ብዙ ጊዜም በመጦም: በብርድና በራቁትነት ነበርሁ . . . የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው:: +"+ (2ቆሮ 11:23) <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Показати все...
✞✞✞ እንኩዋን ለታላቁ ነቢይና ሰማዕት "ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞ +*" ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ "*+ =>ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6) *የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል! እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር:: *ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ በስተእርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው:: *ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው:: *የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል:: *ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ:: *እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት:: *ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ:: *ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በኋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25 (23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም:: *ከዚህ በኋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጀን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና:: *ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና:: *ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ: ለንስሃም በርካቶችን አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው:: *"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው:: *በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ. 1:6) *ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በኋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት ደብረ ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: ቅዱሳን ሐዋርያትበኋላ በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት:: *ከዚሕ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለ15 ዓመታት ስትሰብክ ኑራ በዚህች ቀን ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች:: =>" አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ/ የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች" 1.ነቢይ 2.ሐዋርያ 3.ሰማዕት 4.ጻድቅ 5.ካሕን 6.ባሕታዊ/ገዳማዊ 7.መጥምቀ መለኮት 8.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ) 9.ድንግል 10.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ) 11.ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ) 12.መምሕር ወመገሥጽ 13.ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ) ❖ጌታችን መድኃኔ ዓለም የመጥምቁ ዮሐንስን ምትረት አስቦ ይቅር ይበለን:: ጸጋውን: በረከቱንና ክብሩንም ያሳድርብን:: ❖ሚያዝያ 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት= 1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት (ጸዐተ ነፍሱ) 2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ (ከ318ቱ ሊቃውንት) 3.ቅዱስ አጋቦስ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት) 4.ቅድስት እለእስክንድርያ ሰማዕት 5.አቡነ አቢብ ጻድቅ ወርኃዊ በዓላት 1 ቅዱስ ሚናስ 2 .ቅዱስ ማርቂርቆስ ለእሙ ኢየሉጣ 3 ቅድስት ዕንባ መሪና 4 ቅድስት ክርስጢና 5 ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ++"+ ጌታ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ . . . ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችሁአለሁ ከነቢይም የሚበልጠውን . . . እውነት እላቹሃለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም. . . ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ:: ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይሕ ነው :: የሚሰማ ጀሮ ያለው ይስማ:: +"+ (ማቴ. 11:7-15) ❖ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ❖
Показати все...
††† እንኳን ለአባ መክሲሞስ ሊቀ ዻዻሳት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ††† ††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ††† ††† አባ መክሲሞስ ሊቀ ዻዻሳት ††† ††† "ዻዻስ" ማለት "አባት - መሪ - እረኛ" ማለት ነው:: በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ በሐዲስ ኪዳን የመንፈሳዊ ስልጣን ደረጃዎች በጥቅሉ 3 ናቸው:: እነሱም *ዲቁና: *ቅስና: *ዽዽስና ሲሆኑ በሥራቸው ወደ 9 ያህል ክፍሎች አላቸው:: ከእነዚህም ከፍተኛው ስልጣን ዽዽስና ነው:: ዽዽስና ማለት የክርስቶስን መንጋ እንደ ባለቤቱ አድርጐ መጠበቅ ማለት ነው:: ሥልጣኑ በምድር "ሸክም" : "ዕዳ" ሲሆን በሰማይ ግን "ክብር" ነው:: ማንም በሥጋው ላይ ካልጨከነ በቀር ዽዽስናን አይመኝም:: ቅዱስ ዻውሎስ "ሠናየ ግብረ ፈተወ - ማንም ዽዽስናን ቢመኝ መልካም ሥራን ተመኘ" (1ጢሞ. 3:1) ማለቱን ይዞ "ሹሙኝ" ማለት ወደ ማይጠፋ እሳት የሚያስጥል ከባድ ውሳኔ ነው:: ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን የሚጠየቅ በራሱ ኃጢአት ሲሆን አንድ ካህን ደግሞ ስለ ልጆቹ ይጠየቃል:: የከፋው ግን የዻዻሱ ነው:: አንድ ዻዻስ ቢጾም ቢጸልይም እንኩዋ ለድኅነቱ በቂ አይደለም:: ምክንያቱም በመንበሩ ላይ ያስቀመጠው መንጋውን እንጂ ራሱን እንዲያድን አይደለምና:: ጌታ እንዳለ መልካም እረኛ "ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግኢሁ - መልካሙ እረኛ ስለ በጐቹ ቤዛ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነው::" (ዮሐ. 10) ስለዚህም ክህነት (ዽዽስና) ሐዋርያዊ አገልግሎት: ከባድም ኃላፊነት ነው:: አባቶቻችን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው ሐዋርያውያን ታላላቅ የዽዽስና መንበሮችን መሥርተው: ትምሕርቱን ከነ ወንበሩ አስተላልፈዋል:: ከእነዚህ መንበረ ዽዽስናዎች 4ቱ የበላይ ናቸው:: ††† እነዚህም:- *የቅዱስ ዼጥሮሱ የሮም: *የቅዱስ ዮሐንሱ የአንጾኪያ: *የቅዱስ ማርቆሱ የእስክንድርያና *የቅዱስ ዻውሎሱ የኤፌሶን መናብርት ናቸው:: እነዚህ መንበሮችም ከክርስቶስ ዕርገት እስከ 443 (451) ዓ/ም {ጉባኤ ኬልቄዶን} ድረስ በአንድነት ቆይተው ተለያይተዋል:: ከእነዚህ መናብርት መካከል የእስክንድርያው (የግብጹ) እና የአንጾኪያው (የሶርያው) ዛሬም ድረስ በተዋሕዶ እምነት የጸኑ ናቸው:: የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት እንደ መሆኗ ሐዋርያትን መስለው: ሐዋርያትን አህለው የተነሱ አበው ዻዻሳትን በየጊዜው በበዓላት ታስባለች: ታከብራለች:: በተለይ ደግሞ የእስክንድርያና የአንጾኪያ በርካታ አባቶችን እናከብራለን:: እነርሱ ለቀናች ሃይማኖትና ለመንጋው ሲሉ ብዙ መከራን በአኮቴት ተቀብለዋልና:: ከእነዚህም መካከል አንዱ አባ መክሲሞስ ነው:: አባ መክሲሞስ የእስክንድርያ (ግብጽ) 15ኛ ፓትርያርክ ሲሆን በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ቤተ ክርስቲያንን ለ15 ዓመታት አገልግሏል:: ቅዱሱ ከልጅነቱ ጀምሮ ምስጢረ ሃይማኖትን የተማረ ሲሆን መናኝ ሰው እንደ ነበርም ይነገርለታል:: በደቀ መዝሙርነትም ለአባ ያሮክላ (13ኛው ሊቀ ዻዻሳት) እና ለአባ ዲዮናስዮስ (14ኛው ሊቀ ዻዻሳት) በትህትና አገልግሏል:: ዲቁናና ቅስና ሹመት ያገኘውም በዚህ ጊዜ ነው:: ፓትርያርክ ሆኖ ከተመረጠ በሁዋላም ምዕመናንን በአፍም : በመጣፍም ብሎ አስተምሯል:: በዚህም መንጋውን ከተኩላ የመጠበቅ ተግባርን ከውኗል:: በተለይ ደግሞ ዓለማቀፍ መናፍቃን የሆኑትን ማኒንና ሳምሳጢን ተዋግቷል:: ትግሉም ተሳክቶ መናፍቃኑ ተወግዘዋል:: ቅዱሱ አባት አባ መክሲሞስ (ማክሲሙስ) ከዚህም የሚበልጥ ብዙ በጐ ሥራ ሠርቶ በበጐ ዕረፍት በዚህች ቀን ዐርፏል:: ††† አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ብሎ ለመንጋው የሚራራ እረኛን ይስጠን:: ከቅዱሱ በረከትንም ይክፈለን:: ††† ሚያዝያ 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት 1.አባ መክሲሞስ ሊቀ ዻዻሳት ††† ወርሐዊ በዓላት 1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል) 2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ 3.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ 4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው) 5.አባ ስምዖን ገዳማዊ 6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ 7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት ††† "ስለዚህ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያንን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ዻዻሳት አድርጎ ለሾመባት: ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ:: ከሄድሁ በሁዋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ እኔ አውቃለሁ:: ስለዚህ 3 ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሰጽ እንዳላቁዋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ::" ††† (ሐዋ. 20:28) ††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✝✝✝
Показати все...