ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ
Відкрити в Telegram
ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።
Показати більше610
Підписники
-124 години
-37 днів
-1130 днів
Архів дописів
❤ ያን ጊዜም ቅዱስ አቦሊ ተነሣ እንዲህ ብሎ ጸለየ "ስለ ቅዱስ ስምህ መከራን እቀበል ዘንድ የመረጥከኝ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በእኒህ በሞቱ ሰዎች ላይ ኃይልህን ግለጥ። እኒህ ሰዎች ሁሉ እንዲአምኑ ያለ አንተም ሌላ አምላክ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ከሞት አንሣቸው። ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን"።
❤ ከዚህም በኋላ የተገፈፈ ቆዳውን ወስዶ በሞቱት ሰዎች ላይም ዘረጋውና "በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከሞት ተነሡ" አለ። ወዲያውም ሁሉም ድነው ተነሡ በዚያ ያሉ ሕዝብም ይህን ድንቅ ሥራ በአዩ ጊዜ "የክርስቲያን አምላክ የቅዱስ አቦሊም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ነው እኛም እናምንበታለን ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለምና" እያሉ ጮኹ።
❤ ባለ ጸጋው አብስኪሮንም መጥቶ ለቅዱስ አቦሊ እንዲህ እያለ ሰገደ "ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ዛሬ አወቅሁ እኔም አምንበታለሁ። ከቤተሰቦቹም ሁሉ ጋር አመኑ መኰንኑም" ዐፈረ።
❤ ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ አቦሊ ተገለጠለት እንዲህም ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠው። "በመከራ ውስጥ ያለ ሰው በስምህ ርዳታ ቢለምን እኔ እሰማዋለሁ ልመናውን ፍላጎቱንም እፈጽምለታለሁ። በስምህ ቤተ ክርስቲያን ለሠራም እኔ በሰማያት ብርሃናዊ ማደሪያ ቤት እሠራለታለሁ የገድልህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውን ወይም የሚሰማውን እኔ በኪሩቤል ክንፎች ላይ ስሙን እጽፉለሁ በአብርሃም በይስሐቅና በያዕቆብ እቅፍም አሳርፈዋለሁ ተድላ ደስታ ካለባት ከገነት ፍሬዎችም እመግበዋለሁ። ብዙ ኃጢአትን ሠርቶ የበደለውንም በስምህ ወደኔ እየለመነ ንስሐ ቢገባ በደሉን ሁሉ ይቅር እለዋለሁ። ከጻድቃንም ጋርም እቈጥረዋለሁ ሰላሜም ካንተ ጋራ ይሁን" ይህንንም ብሎ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ።
❤ መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ የከበረች ራሱን ቆረጡት የሕይወት አክሊልንም ተቀበለ። ሥጋውም ከምስር ከተማ ውጭ ሕንቅ በሚባል ገዳም ይኖራል ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ ቅዱስ አቦሊ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የነሐሴ 1 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወእነግር ስምዐከ በቅድመ ነገሥት ወኢይትኃፈር። ወአነብብ ትእዛዘከ ዘአፍቀርኩ ጥቀ። ወአነሥእ እደውየ ኀበ ትእዛዝከ ዘአፍቀርኩ"። መዝ 118፥46-47 ወይም 131፥13-14 ። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ጢሞ 5፥1-11፣ 1ኛ ዮሐ 5፥1-6፣ የሐዋ ሥራ 5፥26-34። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 19፥38-ፍ.ም ወይም ሉቃ 1፥39፥47። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ወይም የዮሐንስ አፈወርቅ ቅዳሴ ነው። መልካም የፆም ጊዜና በዓል ለሁላችን ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ የተባረከው #የነሐሴ_ወር_የቀኑ_ሰዓት_ዐሥራ_ሦስት ነው ከዚህም በኋላ ይጎድላል።
❤ #ነሐሴ ፩ (1) ቀን።
❤ እንኳን #ጌታችንን_ለገነዙ ለአምላካዊ ምሥጢር አገልጋዮች ለሆኑ ለተገባቸው ለከበሩ #ለቅዱስ_ዮሴፍና_ለቅዱስ_ኒቆዲሞስ_ለመታሰቢያ በዐላቸውና ለታላቁ ሰማዕት ለቅዱስ ዮስጦስ ልጅ #ለቅዱስ_አቦሊ_ለዕረፍት_በዐል_በሰላም_አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ አምላክን ከወለደች ከእመቤታች ከድንግል ማርያም እናት #ከቅድስት_ሐና ከመታሰቢያዋ፣ #ከፋኑኤል_ልጅ_ከነቢይት_ሐና ከመታሰቢያዋና #ከንግሥት_ሶፍያ_ልጆች #ከቅዱሳን_ደናግል ከመታሰቢያቸው ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅዱሳን_ዮሴፍና_ኒቆዲሞስ፦ በፈቃዱ መከራ ተቀብሎ ስለ ደኅንነታችን በሞተ ጊዜ የደኅንነታችንንም ምሥጢር በፈጸመ ጊዜ የሕያው እግዚአብሔርን ልጅ የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ እነርሱ ከመስቀል ላይ አውርደዋልና። የአይሁድም መገርመም ከጲላጦስ ዘንድ የመድኃኒታችንን ሥጋ እስከ ለመኑ ድረስ አላስፈራቸውም።
❤ ጲላጦስም በፈቀደላቸው ጊዜ የእጆቹንና የእግሮቹን ችንካሮች ነቅለው ከመስቀል አውርደው በትክሻቸው ተሸከሙት ሲገንዙትም እንዲህ የሚል ቃል ከበድኑ ሰሙ። "ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ አቤቱ ይቅር በለን። ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት በዮርዳኖስ የተጠመቀ በእንጨት መስቀልም የተሰቀለ አቤቱ ይቅር በለን። ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ የተነሣ በክብር ወደ ሰማያት ያረገ በአባቱም ቀኝ የተቀመጠ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ የሚመጣ አቤቱ ይቅር በለን። ለአብ ምስጋና ይገባል ለወልድ ምስጋና ይገባል ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን አሜን ይሁን ይሁን። ልዩ ሦስት ሕያው እግዚአብሔር ይቅር በለን"።
❤ ይህንንም በሰሙ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖታቸው ጸናች። ዮሴፍም በፍታ ኒቆዲሞስም ሽቶዎችን አምጥተው ጌታችንን ገነዙት በአዲስ መቃብር ውስጥም ቀበሩት።
❤ ይህ ዮሴፍም ለሰማዕታት መጀመሪያ ለእስጢፋኖስ ዘመድ ለሆነው ለቀለዮጳ ወንድሙ ለኒቆዲሞስ ዘመዱ ነው ኒቆዲሞስም የአይሁድ አለቃ ፈሪሳዊ ነበር እርሱም ወደ ጌታ ኢየሱስ አስቀድሞ በሌሊት የሔደና ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣ ያመነ ነበር። ጌታችንም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንደማይችል የነገረው ነው።
❤ ይህ ኒቆዲሞስም የጌታችንን ቃል በሚአቃልሉ ጊዜ አይሁድን ይገሥጻቸው ነበር። ከተነሣ በኋላም በኢማሁስ መንገድ ሲሔድ ጌታችን ኢየሱስ የተገናኛቸው እሊህ ኒቆዲሞስና ቀለዮጳ ናቸው። እነርሱም ሳያውቁት በእርሱ ላይ የሆነውን ሁሉ ነገሩት። እርሱም ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ነቢያት ትንቢት እንደ ተናገሩ አስተማራቸው።
❤ ከዘህም በኋላ እርሱ መሆኑን ባወቁት ጊዜ ተሠወራቸው እነርሱም ተመልሰው ለደቀ መዛሙርቱ ነገሩ። ክብር ይግባውና የጌታችንን ሥጋ ስለ ቀበረ ሊገድሉት ፈልገው አይሁድ ዮሴፍን በወህኒ ቤት አሠሩት። የወህኒ ቤቱም በር በሊቃነ ካህናቱና በጲላጦስ ማኅተም ተቆልፎ ሳለ ጌታችን በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጦ ዮሴፍ ወደ አለበት ገባ ከእርሱ ጋርም እልፍ አእላፋት መላእክት ነበሩ። ሱራፌልም በዙሪያው ቁመው በፊቱ ያጥናሉ በቀኝ በኩል ተሰቅሎ የነበረ ወንበዴውም ብሩህ ልብስ ለብሶ በቀኝ ቁሞአል ባለሟልነትን በልዑል ፊት አግኝቶአልና ስለ ኃጢአተኞች ይማልድ ነበር።
❤ የወህኒ ቤት ጠባቂዎችም በአዩ ጊዜ ደነገጡ ፈርተውም መንቀጥቀጥ ያዛቸው ጌታችንም ዮሴፍን ጠርቶ እንዲህ አለው "ከአይሁድ ግርማ የተነሣ አትፍራ ከማሠሪያህ ልፈታሕ እኔ መጣሁ አንተ መከራዬን የተሳተፍከኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ አኔ ጌታህና የዓለሙ ሁሉ ጌታ እንደሆንሁ ፈጽመህ ታውቅ ዘንድ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን የተወጋ ጐኔንም እይ"።
❤ ከዚያም ዮሴፍን ነጥቆ ወደ አገሩ አርማትያስ ወሰደው። የወህኒ ቤቱ ጠባቂዎችም ሔደው ጌታችን ያደረገውን ሁሉ ዮሴፍንም ይዞ ከእርሱ ጋር እንደወሰደው ለካህናት አለቆች ነገሩ። የካህናት አለቆችም በሔዱ ጊዜ የወህኒ ቤቱ በር ተቆልፎ አገኙ እሽጉም አልተለወጠም ነበር። እሊህ ቅዱሳንም ከሐዋርያት ጋር ወንጌልን እየሰበኩ ኖሩ ብዙ መከራም አገኛቸው። ከዚህም በኋላ በሰላም ዐረፉ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
❤ የዮስጦስ ልጅ ሰማዕቱ ቅዱስ አቦሊ፦ ይህም ቅዱስ አቦሊ ከመንግሥት ልጆች ውስጥ ነበር ዐላውያንን ወግቶ በተመለሰ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስን ክብር ይግባውና ክርስቶስን ክዶ አገኘው። ያም አቦሊና አባቱ ዮስጦስ ሌሎችም የመንግሥት ልጆች ሁሉ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስን ሊያጠፉትና መንግሥትን ከእርሱ ሊወስዱ ችሎታ ሲኖራቸው የማታልፍ ሰማያዊት መንግሥትን አሰቡ።
❤ ከዚህም በኋላ ቅዱስ አቦሊ ወደ ንጉሡ ቀርቦ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም አብዝቶ አባበለው። እንዲሁም አባቱ ዮስጦስንና የከበረች እናቱ ታውክልያን አባበላቸው እነርሱ ግን አልሰሙትም ልባቸው በመድኅን ክርስቶስ ፍቅር ተነድፏልና። ንጉሡም እነርሱን በዚያ ማሠቃየትን ፈራ ስለዚህም ከመልእክት ደብዳቤ ጋር ወደግብጽ ስሙ ኄርሜኔዎስ ወደሚባል የእስክንድርያ ገዥ ላካቸው በመልእክቱም እንዲህ አለው "ዮስጦስና ሚስቱ ታውክልያ ልጃቸው አቦሊም ወደአንተ በሚደርሱ ጊዜ አባብላቸው አለዚያም እየአንዳንዳቸውን ለያያቸው"።
❤ በዚያችም ሌሊት ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዮስጦስና ለሚስቱ ታውክልያ ለልጃቸው አቦሊም ተገልጦላቸው አጽናናቸው ከእነርሱም የሚሆነውን ነገራቸው የጸና ቃል ኪዳንም ሰጣቸው።
ወደ መኰንኑ ኄርሜኔዎስም በደረሱ ጊዜ ስለእነርሱ እጅግ አደነቀ እነርሱ መንግሥታቸውን ትተዋልና ክፋ ነገርንም ሊናገራቸው አልደፈረም ከምክራቸው ይመለሱ ዘንድ በለሰለሰ ቃል ሸነገላቸው እንጂ ነገር ግን አልሰሙትም።
❤ ከዚህም በኋላ በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ ለእየብቻቸው ለያያቸው ቅዱስ ዮስጦስን ወደ እንዴናው ከተማ ሚስቱን ታውክሊያን ፃ ወደ ሚባል አገር ልጃቸው አቦሊንም ብስጣ ወደ ሚባል አገር ሰደዳቸው ለእያንዳንዳቸውም የሚአገለግላቸው አንዳንድ አገልጋይ ሰጣቸው። ቅዱስ አቦሊም ወደ ሀገር ብስጣ በደረሰ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመኰንኑ ፉት ታመነ። መኰንኑም ጽኑ ሥቃይን በእሳት ቃጠሎና በመንኰራኵር አሰቃየው ሕዋሳቱንም ቆራርጦ ለአንበሶች ጣለው ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስም ከሥቃዩ ሁሉ አድኖ ያለ ጉዳት በጤና አነሣው።
❤ ብዙዎች ሰዎችም ስቃዩንና ዳግመኛ መዳኑን በአዩ ጊዜ እጅግ አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም አምነው ሰማዕታት ሆኑ። መኰንኑ ግን እጅግ ተቆጥቶ የቅዱስ አቦሊን ቆዳውን እንዲገፍፉትና ጨውና መጻጻን በማቅ አምጥጠው ቍስሉን እንዲያሹ አዘዘ ይህንንም ሁሉ አደረጉበት።
ለሚነሡ ልጆቻችሁም አስተምሯቸው።
❤ ከዚህም በኃላ የአራዊትን ጠባይ ከእነርሱ ያርቅ ዘንድ እግዚአብሔርን ለመኑት ክብር ይግባውና ጌታችንም ይህን የአራዊት ጠባይ አራቀላቸው። ሰዎች የሚመገቡትንም የሚመገቡ የዋሆች ሆኑ። አባቶቻችን ሐዋርያትም ብዙ ተአምራትን አደረጉ በሽተኞችን ሁሉ ፈወሱ ከዚህም በኃላ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ግሪክ አገር ተመለሰ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁንእኛንም በአባቶቻችን ሐዋርያት ቅዱስ እንድርያስና በቅዱስ ማትያስ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእርሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ከአባ መርቆሬዎስና ከአባ ማትያስ ከሁሉም ኤጲስ ቆጶሳት ከክርስቲያን ወገኖችም ሁሉ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #ብልጽግናን_ንቆ_የተወ_አባ_ጳውሎስ፡- ይህም ቅዱስ ባለ ጸጋ ነበር። ደግ የሆነች ሚስትና የተባረኩ ልጆችንም ነበሩት፡፡ መነኰስ ሊሆን ወደደ ሚስቱንና ልጆቹንም ጠርቶ "እነሆ ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ ፍቅር እሸጣችሁ ዘንድ ወደድኩ" አላቸው እነርሱም "አሳዳሪያቸን ነህና የወደድከውን አድርግ" አሉት።
❤ ከዚያም በኋላ ገንዘቡን ሁሉ ወስዶ ለድኆችና ለችግረኞች በተነ ሚስቱንም ወደ ደናግል ገዳም ወሰዳት አመ ምኔቱንም ጠራትና እንዲህ አላት "ለገዳምሽ አገልጋይ ትሆን ዘንድ ሚስቴን ልሸጥልሽ አወዳለሁ" እርሷም "እሺ" አለችው የመሸጫዋንም ደብዳቤ ጻፈ የሺያጭዋን ዋጋ ተቀብሎ ለድኆች ሰጠ ልጆቹንም ወደ አበ ምኔቱ ወስዶ እንደ እናታቸው ሸጣቸው ለአበ ምኔቱም አሳልፎ ሰጣቸው።
❤ ከዚህም በኋላ ወደ ሌላ ቦታ ሔደ ራሱንም ለገዳሙ አለቃ ሸጠ አለቃውንም "ወደ ቤተ ክርስቲያን ልገባ እሻለሁ" አለው፡፡ በገባም ጊዜ በሩን በላዩ ዘጋ። እጆቹን ዘርግቶ ቆመ በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብሎ ጮኸ "አቤቱ በፍጹም ልቡናዬ ወዳንተ እንደ መጣሁ፣ አንተ ታውቃለህ" ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ "ሀሳብህን ሁሉ አወቅሁ በፍጹም ልቤም ተቀበልሁህ"
❤ ከዚህም በኋላ ከመነኵሶ አስጨናቂ የሆኑ የገዳሙን ሥራዎች ሁሉ እንደ ባሪያ እየሠራ ኖረ ራሱንም ከሁሉ እጅግ አዋረደ ነገር ግን ስለ መዋረዱ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ አደረገው። ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ ከዚህም በኋላ ሐምሌ 30 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ጳውሎስ ጸሎት ይማሰን ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #ሰማዕታት_ቅዱሳን_መርቆሬዎስና_ኤፍሬም፡- እሊህም ከአክሚም ከተማ የመጡ የሚዋደዱ በመንፈስ ቅዱስ ወንድማማቾች በሥጋም ዘመዳሞች ነበሩ መንፈሳዊ ስምምነትንም ተስማምተው በላይኛው ግብጽ ካሉ ገዳማት በአንዱ ገዳም መነኰሱ፡፡ በጾም በጸሎትና በስግደት በታላቅ እየተጋደሉ በገዳሙ ውስት ሃያ ዓመት ዓመት ያህል ኖሩ፡፡
❤ ከዚህም በኋላ ጠላት ሰይጣን በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ከአርዮሳውያን ችግርን በአመጣ ጊዜ አርዮሳውያኑ በአርዮሳዊ ንጉሥ ትእዛዝ መሥዋዕት ሊሠው ወደ ኦርቶዶክሳዊ ቤተ ክርስቲያን ሊሠዉ ወደ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገቡ፡፡ እኒህ ቅዱሳንም አምላካዊ ቅንአትን ቀንተው ወደ ቤተ ክርስቲያን ገቡና አርዮሳውያን ያኖሩትን መሥዋዕት በተነኑት። እንዲህም አሏቸው "በሥሉስ ቅዱስ ስም ያልተጠመቀ መሥዋዕትን ያሳርግ ዘንድ አይገባውም"።
❤ ያን ጊዜም አርዮሳውያን ይዘው ደበደቧቸው ታላቅ ግርፋትንም ገረፏቸው ዐጥንቶቻቸውም እስኪሰበሩ ድረስ በምድር ላይ ጥለው ረገጧቸው ነፍሶቻቸውንም በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጡ የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበሉ ምእመናንም መጥተው ሥጋቸውን ወሰዱ በአማሩ ልብሶችም ገንዘው በመልካም ቦታ አኖርዋቸው ከእነርሱም ለበሽተኞች ታላቅ ፈውስ ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን መርቆሬዎስ ኤፍሬም ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
❤ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በረከቷ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ጳውሎስ በሁሉም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት እንዲሁም በሁላችን በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ ይደር ለዘላለሙ አሜን። በሐምሌ ወር የሚነገበብ ንባብ ደረሰ ተፈጸ። እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 30 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ዕብል_ለቤትከ_ቅዳሴሃ። ድኅረ ፈጸመ በቊስጥንጥንያ ሕንፄሃ። ሱርያል ገሀደ ተአምሪከ አሜሃ። እምዘይት ማኅቶት ዘሥዕልከ ተቀቢዖ ሶቤሃ። ዐይነ ዕውረሰ በቅጽበት በርህ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_30።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ይቤ ወመጽአ መንፈስ አውሎ። ወተለዓለ ማዕበል። የዐርጉ እስከ ሰማይ"። መዝ 106፥25-26። የሚነበበው ወንጌል ማር 6፥47-53።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "እምውኂዝ እምሰጠት ነፍስነ። እምሰጠት ነፍስነ እማየ ሀከክ። ይትባረክ እግዚአብሔር አምላክነ ዘኢያግብአነ ውስተ መሥገርተ ማዕገቶሙ"። መዝ 123፥4-5። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 2፥1-9፣ 2ኛ ጴጥ 1፥12-17፣ የሐዋ ሥራ 3፥1-10። የሚነበበው ወንጌል ማር 4፥35-41። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሐዋርያት ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ሐምሌ ፴ (30) ቀን።
❤ እንኳን #ለሊቀ_መላእክት_ለቅዱስ_ሱርያል (እስራልዩ) ቤተ ክርስቲያኑ ለከበረችበት (ለቅዳሴ ቤቱ) በዐል፣ #ለሐዋርያው_ቅዱስ_እንድርያስ አስገራሚ ተአምር በማድረግ #ሐዋርያው_ቅዱስ_ማትያስን ከእስር አስፈትቶ ሰውን ከሚበሉ ሰዎች እጅ ላዳነበት፣ ክብርንና ብልጽግናን ንቆ ለተወ ራሱን ስለ ጽድቅ ለሸጠ #ለቅዱስ_ጳውሎስ_ለዕረፍት በዐል፣ ለቅዱሳን ለገሊላ ሰዎች #ለመርቆሬዎስና_ለኤፍሬም ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ ከእስክድርያው ሊቀ ጳጳሳት #ከአባ_ጢሞቴዎስ ከምስር በአስቄጥስ ወደ አለወደ አባ መቃረስ ገዳም ከሥጋው ፍልሰት፣ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትን በረከት ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ በዚችም ቀን #የእስራልዩ_ቤተ ክርስቲያን የከበረችበት ነው ይኸውም #ቅዱስ_ሱርያል መልአክ ነው። የቅዱስ ሱርያል አማላጅነቱና ረድኤቱ ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ በዚችም ቀን #ሐዋርያው_ቅዱስ_እንድርያስ ተአምራትን አደረገ። እንድርያስ በጽርዕ አገር እያለ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ተገልጦ እንዲህ አለው "ማትያስን ከእሥር ቤት ታወጣው ዘንድ ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች አገር ሒድ የዚያች አገር ሰዎች ከሦስት ቀን በኃላ ሊበሉት ያወጡታልና"። እንድርያስም ጌታችንን እንዲህ አለው "የቀረው ሦስት ቀን ከሆነ እንዴት እደርሳለሁ ነገር ግን ፈጥኖ የሚያወጣውን ከመላእክት አንድ ላክ እንጂ"።
❤ ጌታችንም ለእንድርያስ እንዲህ ብሎ መለሰለት "ስማ ሀገሪቱን ወደዚህ ነዪ ከልዃት በውስጧ ከሚኖሩ ሁሉ ጋር ትመጣለች አንተና ደቀ መዘሙሮችህ ግን ጠዋት በሆነ ጊዜ ተነሥታችሁ ወደ ባሕር ሒዱ የተዘጋጀ መርከብንም ታገኛላችሁ እርሱም ያደርስሃል" ይህንንም ብሎ ከእርሱ ዘንድ በክብር ዐረገ። በነጋ ጊዜም እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ተነሥቶ ወደ ወደብ ደረሰ ጥሩ መርከብንም አየ ጌታችንንም በሊቀ ሐመር አምሳል አየው ጌታችን እንደሆነ አላወቀም "ሊቀ ሐመር ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን" አለው ጌታም "የእግዚእብሔር ሰላም ይደርብህ" አለው እንድርያስም ደግሞ "በዚህ መርከብ ወዴት ትሔዳለህ" አለው "ሰውን ወደ ሚበሉ ሰዎች አገር እሔዳለሁ" አለው እንድርያስም ሊቀ ሐመሩን "ወንድሜ ሆይ ከአንተ ጋር ትጭነኝ ዘንድ እለምንሃለሁ" አለው ሊቀ ሐመሩም "እሺ" ብሎ ወደ መርከቡ አወጣቸው። በባሕሩ ላይም ሲጎዙ ጌታችን እንድርያስን እንዲህ ብሎ ጠየቀው "ጌታህ ምን ኃይል አደረገ" እንድርያስም ጌታችን ከአደረጋቸው ተአምራቶች ይነግረው ጀመረ ጌታችን እንደሆነ አላወቀም ነበርና።
❤ ከዚህም በኋላ ሊቀ ሐመሩ እነደሚአንቀላፋ ሰው ሆነ ያንጊዜም እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ተኛ በዚያን ጊዜም ጌታችን እንድርያስንና ሁለቱን አርድእቱን ይሸክሙአቸው ዘንድ መላእክትን አዘዛቸውና ወስደው በባሕሩ ዳርቻ አኖሩዋቸው። እንድርያስም ከእነቅልፍ በነቃ ጊዜ መረከብን አላገኘም እጅግም አደገቀ ለደቀ መዛሙርቱም እንድህ አላቸው "ልጆቼ ሆይ በመርከብ ውስጥ ከጌታችን ጋር ነበርን ግን አላወቅንም"።
❤ ከዚህም በኋላ እንድርያስ ተነስቶ ጸለየ ክብር ይግባውና ጌታችንም በመልካም ጎልማሳ አምሳል ተገለጸለት እንዲህም አለው "ወዳጄ እንድርያስ አትፍራ እኔ ይህን አድርጌአለሁና አንተ በሦስት ቀን አልደርስም ብለህ ነበር ስለዚህ በፍጥረት ሁሉ ላይ ኃይል እንዳለኝ የሚሳነኝምእንደሌለ ታውቅ ዘንድ እንግዲህም ወደ ከተማው ገብተህ ማትያስን ከእሥር ቤት አውጣው ከእርሱ ጋር ያሉትንም ሁሉ"።
❤ ከዚህም በኋላ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተነሥቶ ወደ ከተማ ገባ ማትያስ ወዳለበትም እስር ቤት ሔደ። በደረሰም ጊዜ የወሀኒ ቤቱ ደጀ ራስዋ ተከፈተች በገባ ጊዜም ማትያስን ተቀምጦ ሲዘምር አገኘው እርስ በርሳቸውም ሰላምታ ተሳጣጡ እንድርያስም ማትያስን "ከሁለት ቀን በኋላ አውጥተው እንደ እንስሳ አርደው ይበሉኛል አልክ አንተ በጌታችን ዘንድ ያየናትን ያቺን ምሥጢር ረሰሃትን በምንናገርበት ጊዜ ሰማይና ምድርን ይናወጣሉ" አለው። ማትያስም "ወንድሜ ሆይ እንሆ ይህን አወቅሁ ነገር ግን በዚች ከተማ ውስጥ ሥራዬን እንድፈጽም የጌታችን ፍቃድ እንደ ሆነ እኔ እናገራለሁ እርሱ ራሱ "እንሆ እኔ እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እንኳችኋለሁ" ብሏልና ወደ ዚህም እሥር ቤት በጨመሩኝ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችንን ጠራሁት እርሱም ሃያ ሰባት ቀን ሲፈጸም ወንድምህ እንድርያስን ወዳንተ እልከዋለሁ እርሱም ከእሥር ቤት ያወጣሃል ከአንተ ጋራ ያሉትን ሁሉ ያወጣችዋል ብሎ ገለጠልኝ እንሆም ደርሰሃል የምትሠራውን አስተውል" አለው።
❤ እንድርያስም ወደ እስረኞች በተመለከተ ጊዜ እንደ እንስሳ ሣር ሲበሉ አይቶ አዘነ አለቀሰም ሰይጣንንም ከሠራዊቱ ጋር አሠረው ከዚህ በኃላ አንድርያስና ማትያስ ተነሥተው ወደ እግዚአብሔር ማለዱ እጆቻቸውንም በእሥረኞች ሁሉ ላይ ጫኑ አእምሮአቸውም ተመለሰ ከከተማው ውጭ ወጥተው በዚያ በአንድነት እንድቀመጡ አዘዙአቸው።
❤ እኒያ ሐዋርያትም የሚሆነውን ያዩ ዘንድ ወጥተው በሀገሩ ጎዳና ዳር ተቀመጡ የከተማው ሰዎችም እነደ ልማዳቸው የሚበሉትን ከእሥረኞቹ ውስጥ ሊአመጡ መጡ የእሥር ቤቱን ደጅ ክፍት ሆኖ አገኙ እሥረኞችም አልነበሩም ደነግጠውም "በእኛ የደረሰብን ምንድነው ወዮልን" አሉ ያን ጊዜም ሰይጣን በሰው መስሎ ሐዋርያት ይህን እንዳደረጉ ነገራቸው የአሉበትንም አመለከታቸው የከተማው ሰዎችም በመቀዳደም ሮጡ እንድርያስንና ማትያስንም ይዘው በከተማው ጥጋጥግ አስጎተቱአቸው በሌሊትም በእሥር ቤት ያሳድሩአቸው ነበር ሦስት ቀናትም እንዲህ አደረጉባቸው ደማቸውም እንደ ውኃ ፈሰሰ።
❤ ከዚህም በኋላ ሰለ ከተማዋ ሰዎች ድኀነት ወደ እግዚአብሔር ጸለዪ ጸሎታቸውንም በፈጸሙ ጊዜ በላዩ ምስል ወደአለበት የዕብነ በረድ ምሶሶ ቀርበው በመስቀልመ ምልክት አመተቡት እንዲህም አሉት "አንተ ምሶሶ ፍራ ከበታችህም እንደ ጥፋት ውኃ ያለ ብዙ ውኃን በዚች ከተማ ላይና በውስጧ የሚኖሩ ሁሉ ላይ አውጣ" ያን ጊዜም ከምሶሶው ሥር ብዙ ውኃ መነጨ የከተማው ሰዎችንም ያሠጥማቸው ዘንድ ገነፈለ ሰዎችም ከከተማው ወጥተው ሊሸሹ ወድደው ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ያዙ ውኃውም በዝቶ ከበባቸው ማምለጥም አልቻላቸውም ውኃውም እስከ እስከ አንገታቸው ደረሰ ያን ጊዜም አለቀሱ እንዲህም አሉ "ወዮልን ይህ ሁሉ በእኛ ላይ የመጣው በእነዚህ በተመረጡ ሰዎች በእግዚአብሔር አገልጋዮች ምክንያት ነው እኛም በአምላካቸው እናምናለን"።
❤ ቅዱስ እንድርያስም "የዕብነ በረደ ምሰሶ እንግዲህስ በቃህ እነሆ የጥፋት ጊዜ አለፈ" ያን ጊዜም ውኃው ተገታ ውኃውም እንደተገታ የከተማው ሰው አይተው ወደ ሐዋርያት ሔዱ ስለዚያች ከተማ ሰዎች ድኅነትም ቁመው እጆቻቸውን ዘርግተው ወደ እግዚአብሔር ሲጸልዩ አገኙአቸው ሐዋርያትን "ይቅር በሉን" ብለው ለመኑአቸው። ሐዋርያትም "በሕያው እግዚአብሔር እመኑ እንጂ አትፍሩ" አሏቸው ሐዋርያትም ሁለተኛ ጸለዩ በውኃ ስጥመት የሞቱትንም ሙታን አስነሡአቸው በዚያም ውኃ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው። ሥጋውንና ደሙንም አቀበሏቸው ቤተ ክርስቲያንንም ሠሩላቸው። ሕግንና ሥርዓትንም ሁሉ አስተምረው በቀናች ሃይማኖት አጸኑአቸው እንዲህም አሏቸው ያዘዝናችሁን ጠብቁ ከእናንተ በኃላ
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ሐምሌ ፳፰ (28) ቀን።
❤ እንኳን ክርስቶስ ለሚወዱ #ለቅዱስ_እንድራኒቆስና #ሚስቱ_ቅድስት_አትናስያ_ለመታሰቢያ_በዐላቸው በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከከቅዱሳን አባቶቻችን #አብርሃም_ከይስሐቅና_ከያዕቆብ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅዱስ_እንድራኒቆስና_ሚስቱ_ቅድስት_አትናስያ፦ እነርሱም ከአንጾኪያ ከተማ ነበሩ። በወርቅና በብርም የከበሩ ባለጸጎች ነበሩ ከገንዘባቸውም ለድኆችና ለችግረኞች ይሰጡ ነበር።
❤ ከዚህም በኃላ አንድ ወንድ ልጅና አንዲት ሴት ልጅን ወለዱ ወንዱን ዮሐንስ ሴቲቱንም ማርያም ብለው ሰየሟቸው ልጆችም አደጉ እንዱራኒቅስና ሚስቱም እንግዳ በመቀበል ለድኆችና ለምስኪኖች በመመጽወት በጎ ሥራን አበዙ እነርሱም መገናኘትን ትተው ሰውነታቸውን በንጽሕና ጠበቁ።
❤ ልጆቻቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆናቸው ጊዜ የሆድ ዝማ በሽታ ታመው በአንዲት ቀንም ሞቱ እንዲራኒቆስም አይቶ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥዕል ፊት ራሱን ጥሎ እንዲህ ብሎ አለቀሰ "ከእናቴ ማሕፀን ራቁቴን ወጣሁ ወደ እግዚአብሔርም ራቁቴን እሔዳለሁ እርሱም ሰጠ እርሱም ወሰደ የእግዚአብሔር የጌትነቱ ስም የተባረከ ይሁን ለዘላለሙ አሜን"። እናታቸውም ለሞት እስከምትደርስ እጅግ አዘነች ልጆቿ ወደ ተቀበሩበት ወደ ዐፀደ ቤተ ክርስቲያን ሔደች ከኀዘንዋም ብዛት የተነሳ አንቀላፋች በእንቅልፏም ውስጥ "በልጆችሽ ሞተ አታልቅሺ እነርሱ ግን በሰማያት ደስ እያላቸው ናቸው" እያለ በመነኰስ አምሳል ሲነግራት አየች። ይህንንም ሰምታ ሒዳ ለባሏ ነገረችው።
❤ ከዚህም በኃላ ይህን ዓለም ይተዉ ዘንድ ተስማሙ ገንዘባቸውንም ሁሉ ምንም ሳያስቀሩ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጡ በሌሊትም ወጥተው ወደ እስክንድርያ ከተማ ደረሱ ሚስቱንም በዚያ ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ በአባ ዳንኤል ዘንድ መነኰሰ። ከዚያም ተመልሶ ሚስቱ አትናስያን ወደ ሴቶች ደናግል ገዳም ወሰዳት በዚያም ተዋት።
❤ ከዐሥራ ሁለት ዓመትም በኋላ እንድራኒቆስ ከቅዱሳት መካናት ይባረክ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሔድ አባ ዳንኤልን ለመነው ፈቀደለትም በመድኃኒታችንም ቸርነት ሚስቱ አትናስያ በወንድ አምሳል በጉዞ ላይ ተገናኘችው ሚስቱ እንደሆነችም አለወቀም እርሷ ግን አወቀችው ነገር ግን ሚስቱ እንደሆነች አልገለጠችለትም።
❤ ወደ ቅዱሳት መካናትም በደረሱ ጊዜ ሥራቸውን ፈጽመው ወደ አባ ዳንኤል በአንድነት ተመለሱ። አባ ዳንኤልም ሚስቱ እንደሆነች በመንፈስ ቅዱስ አውቆ እንድራኒቆስን "ባልንጀራ ካደረግኸው ከዚህ መነኰስ ጋራ በአንድ ቦታ ኑሩ እርሱ ቅዱስ ነውና" አለው። ዐሥራ ሁለት ዓመትም በአንድነት ኖሩ ማንም የአወቀ አልነበረም።
❤ አባ ዳንኤልም ይጎበኛቸውና ስለ ነፍሳቸው ጥቅም ያስተምራቸው ነበር። ከዚህም በኃላ አትናስያ በታመመች ጊዜ ለእንድራኒቆስ "አባታችንን አባ ዳንኤልን ጥራልኝ" አለችው ሒዶም ለአባ ዳንኤል እንዲህ ብሎ ነገረው "ባልንጀራዬ ታሞ ለመሞት ተቃርቧልና ትጎበኘው ዘንድ ና"። በደረሰም ጊዜ በታላቅ ሕመም ላይ አገኛት እርሷም "ታቆርበኝ ዘንድ እሻለሁ" አለችው ያን ጊዜም ተፋጠነና ሥጋውንና ደሙን አቀበላት ከዚህም በኋላ አረፈች በሚገንዟትም ጊዜ ሴት እንደሆነች አገኙ ዳግመኛም ታሪኳንና ለባሏ ያወራቻቸውን ምልክቶች አገኙ።
❤ እንድራኒቆስም በአነበበ ጊዜ እርሷ ሚስቱ እንደሆነች አወቀ ደንግጦም ልቡ ተሠወረ ፊቱንም እየጻፈ ጮኸ ያለቅስ ጀመረ። ከጥቂት ቀን በኋላም ታመመ አረጋውያንም መጥተው በረከቱን ተቀበሉ ሥጋውንና ደሙንም ተቀበሉ በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ እንድራኒቆስ በሚስቱ አትናስያ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 28 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰአሉ_ለነ_አብርሃም_ይስሐቅ_ወያዕቆብ አበወ ሕዝብ ወአሕዛብ ወዘመሐይምናን መክብብ ሰአሉ ለነ አስተምሕሩ ለነ"። ትርጉም፦ የምዕመናን ሹሞች የአሕዛብና የሕዝብ አባቶች #አብርሃም_ይስሐቅ_ያዕቆብ ፈጽማችሁ ለምኑልን፡፡ #ሊቁ_አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ_በሰዓታት_ላይ፡፡
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለእንድራኒቆስ_ለምኔተ_አስቄጥስ ዘሐወጻ። እንዘ ይዘሩ ብዕሎ ዘኢኮነ ብዕለ ዐመፃ። #ወለአትናስያ_ሰላም ለነቢር ዘተባየፃ። ከመ ይእቲ ብእሲቱ እንበለ ይጠይቅ ገጻ። እስመ አዕፅምቲሃ በጽምእ ከመ ሣዕር ነቅጻ። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_28።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወአንተሰ ብእሲ ዘከመ ነፍስየ። ማእምርየ ወዐውቅየ። ዘኅቡረ አስተጠዓምከ ሊተ መባልዕተ"። መዝ 54፥13-14። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ 7፥1-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 3፥1-8 እና የሐዋ ሥራ 7፥1-9። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 19፥1-13። የሚቀደሰው ቅዳሴ የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የአቡነ ፊሊጶስ የዕረፍት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ሐምሌ ፳፯ (27) ቀን።
❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊቷ_ጻድቅ ለታላቁ ለጻድቅ ንጉሥ #ለቅዱስ_ላሊበላ_ባለቤት (ሚስት) #ለቅድስት_መስቀል_ክብራ_ለዕረፍቷ_በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #ቅድስት_መስቀል_ክብራ፡- የትውልድ ሀገሯ ትግራይ ሽሬ አካባቢ ነው፡፡ ይኽችም ቅድስት የታላቁ ጻጽቅ ንጉሥ የቅዱስ ላሊበላ ባለቤት ስትሆን ሁለቱን ያጋባቸው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ላሊበላን ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶ የሚያንጻቸውውን የሕንጻ ዲዛኖችና ሌሎችንም ብዙ ምሥጢራትን ካሳየውና ወደ ምድር ከመለሰው በኃላ ድጋሚ ተገልጦለት "...እንደ አንተ የተመረጠች ናት እንደ ልብህም ትሆናለች፣ ሥራዋም ከሥራህ አያንስም እርሷ የተመረጠች የእግዚአብሔር አገልጋይ ናትና" በማለት መልአኩ የቅድስት መስቀል ክብራን ንጽሕናና ቅድስና መስክሮላታል፡፡
❤ ቅድስት መስቀል ክብራ ከቅዱስ ላሊበላ ይትባረክን የወለደች ሲሆን በ23 ዓመት ውስጥ ቅዱስ ላሊበላ 11 እጅግ አስደናቂ የሆኑ ፍልፍል ቤተ መቅደሶቹን ከመላእክት ጋር ሲያንጽ ብታየው ልቧ በመንፈሳዊ ተመስጦ ተመልቶ እርሷም እግዚአብሔር ፈቅዶላት አስደናቂውን የአባ ሊባኖስን ቤተመቅደስ ራሷ እንዳነጸችው መጽሐፈ ገድሏና ገድለ ቅዱስ ላሊበላ ያስረዳል፡፡ ከዚህም በኋላ ቅድስት መስቀል ክብራን መንና ትግራይ ገባች። ወደ ትግራይ እየመራ የወሰዳት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ መልአኩ እርሷን በትግራይ ቅዱስ ሚካኤል እንዲጠብቃት ከተዋት በኃላ ቅዱስ ላሊበላን ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ መንግሥተ ሰማያት አውጥቶታል፡፡
❤ ቅድስት መስቀል ክብራም በትግራይ ሆና መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እየጠበቃት ከሰው ተለይታ በታላቅ ተጋድሎ ኖረች፡፡ በቀን እልፍ እልፍ እየሰገደች በታላቅ ተጋድሎ ስትኖር ጌታችን ተገልጦ ክብሯ ከ 36ቱ ቅዱሳት አንስት ጋር እኩል መሆኑን ነግሯታል፡፡ ይኽችም ቅድስት ብዙ ሐዋርያዊ አገልግሎት ፈጽማለች፡፡ ለምሳሌ በመስቀል ጦርነት ጊዜ እስላሞች ከባሕር ማዶ እየፈለሱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በፍቅር እየተቀበለችና እያስተናገደች ሃይማኖትንና ሕገ እግዚአብሔርን እያስተማረች ወደ ክርስትና እንደገቡና እንዲጠመቁ አድርጋለች፡፡
❤ ቅድስት መስቀል ክብራም በትግራይ ክልል ሽሬ አውራጃ መደባይ ታብር በተባለው ቦታ ላይ በስማ የተሰራ ትልቅ ገዳም አላት። እጅግ ውብ በሆኑ ሰንሰላታማ ትላላልቅ ድንጋዮች መካከል የሚገኝ አስደናቂና ጥንታዊ ገዳም ነው። ገዳሙ ከሽሬ ከተማ በእግር የ 7 ሰዓት መንገድ ያስኬዳል። የቅድስት መስቀል ክብራ ረድኤት በረከቷ ይደርብን፣ በጸሎቷ እግዚአብሔር አምላክ ይማረን፡፡ ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳንና ቅዱሳት በዐላት።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ሐምሌ ፳፮ (26) ቀን።
❤ እንኳን #ለእመቤታች_ድንግል_ማርያም_እጮኛዋ (ጠባቂ) ድካሟን ለመሳተፍ ክብር ይግባውና ለጌታችንም አሳዳጊው ለመሆን ለተገባው #ለአረጋዊው_ለጻድቁ_ለቅዱስ_ዮሴፍ_ለዕረፍት በዐል፣ #ለኢትዮጵያው_ለመጀመርያው_ሊቀ_ጳጳስ #ለአቡነ_ሰላማ_ከሣቴ_ብርሃን (ፍሬምናጦስ) ለዕረፍት በዐልና #ለእስክድርያው_ሊቀ_ጳጳስ በጉባኤ ቁስጥንጥንያ ከሃዲያን (መናፍቃንን) መቅዶንዮስን፣ ሰባልዮስና አቡሊናርዮስንም ተከራክሮ ለረታቸው #ለአቡነ_ጢሞቴዎስ_ለዕረፍት_በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ #ከአባ_ሮዲስ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
✝ ✝ ✝
❤ #የእመቤታችን_ጠባቂ ( እጮኛ) #ጻድቁ_ቅዱስ_ዮሴፍ፦ መልካም ሽምግልና የነበረው የእመቤታችን ድንግል ማርያም እጮኛዋ ድካሟን ለመሳተፍ ክብር ይግባውና ለጌታችንም አሳዳጊው ለመሆኑ የተገባው ነው
❤ እርሱም እምቤታችንን በርሱ ዘንድ ካስጠበቋት ጀምሮ በሁሉ ነገር ያገለግላት ነበር። በመከራዋም ሁሉ አልተለያትም። በወለደችም ጊዜ በቤተ ልሔም ከርሷ ጋራ ነበረ። ወደ ግብጽም በተሰደደች ጊዜ ከእርሷ ጋራ ብዙ መከራ ደረሰበት። ከዚህም ዓለም የሚለይበት ጊዜው በደረሰ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን ጠርቶ ተሰናበታቸው እጆቹንም ዘርግቶ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሐምሌ 26 ቀን ሰጠ። የዘላለምንም ሕይወት ወረሰ።
❤ በዐረፈበትም ጊዜ ጌታችን ወደርሱ መጥቶ እጆቹን በላዩ ጫነ ለሥጋውም መፍረስና መበስበስ እንዳያገኘው ኃይልን ሰጠው በአባቱ በያዕቆብም መቃበር አኖሩት። ዕረፍቱም ክብር ይግባውና ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዊ በዐሥራ ስድስት ዓመት ነው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ቅዱስ ዮሴፍ በጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #አባ_ሰላማ_ከሣቴ_ብርሃን (ፍሬምናጦስ)፦ ዜናውም እንዲህ ነው ስሙ ሜሮጵዮስ የሚባል የጥበበኞች አለቃ አንድ ሰው ወደ ሕንድ አገር ሊአልፍ ወዶ ከጢሮስ አገር መጣ ከእርሱም ጋራ ከዘመዶቹ ወገን የሆኑ ሁለት ብላቴኖች ነበሩ። የአንደኛው ስሙ ፍሬምናጦስ የሁለተኛውም ኤዴስዮስ ይባላል። ሲድራኮስ የሚሉትም አሉ። በኢትዮጵያ በኩል ወዳለው ወደ አፍሪቃ ባሕር ወደብ ደረሱ ልቡ የተመኘችውን የኢትዮጵያን አገር መልካምነቷን ሁሉ ተመለከተ።
❤ ከዚህም በኃላ በድንገት ወንበዴዎች ተነሥተው በመርከብ ከአሉት ሁሉ ጋር ገደሉት እኒህ ሁለት ልጆች ግን ተረፉ። የአገሩ ሰዎችም አገኙዋቸው ወደ ንጉሥም ወስደው አንድ እጅ መነሻ አድርገው እነርሱን ሰጡት ንጉሡም ተቀበላቸው።
❤ ከጥቂት ቀኖች በኃላም ንጉሡ ኤዴስዮስን በፊቱ የሚቆም ጋሻ ዣግሬ አድርጎ ሾመው ፍሬምናጦስን ግን በገንዘቡ ሁሉ ላይ በጅሮንድ አድርጎ ሾመው ይህም ንጉሥ የአብርሀና የአጽብሐ አባታቸው ስሙ አይዛና የተባለው ነበር። እነርሱ ሕፃናት ሳሉም አረፈ። እኒህም አካለ መጠን እስከሚያደርሱ ድረስ የንጉሡን ልጆች እያሳደጉ ኖሩ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ማመንንም አስተማሩዋቸው።
❤ የንጉሡም ልጆች አድገው በነገሡ ጊዜ ኤዴስዮስ ወደ አገሩ ተመለሰ ፍሬምናጦስ ግን ወደ ግብጽ ሔደ ወደ እስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ አትናቴዎስም ደረሰ። የደረሰብትንም ሁሉ ነገረው። ስለ ኢትዮጵያውያንም ሃይማኖት ጳጳስ ሳይኖራቸው ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንዳመኑ ነገረው። አባ አትናቴዎስም በሰማ ጊዜ እጅግ አደነቀ ፍሬምናጦስንም የነጻ ሕዝብ አገር ለሆነችው ለኢትዮጵያ አገር ጳጳስ ይሆን ዘንድ ግድ አለው። ጵጵስነትንም ሾመ ከታላቅ አክብሮት ጋራ ላከው በአብርሀና በአጽብሐ ዘመነ መንግሥትም ወደ ኢትዮጵያ በደረሰ ጊዜ በክብር ተቀበሉት።
❤ በኢትዮጵያም አገሮች ሁሉ የቀናች ሃይማኖትን ሰበከ አስተማረም ክብር ይግባውና ክርስቶስን የጌትነቱን ብርሀን በሁሉ አገሮች ገለጠ ስለዚህም ብርሃንን ገላጭ ሰላማ ተባለ ሁሉንም አስተካክሎ በሰላም አረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን (ፍሬምናጦስ) ጸሎት ይማረን በረከቱ ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለም አሜን።
✝ ✝ ✝
❤ #የእስክንድር_ሊቀ_ጳጳስ_አባ_ጢሞቴዎስ፦ በተሾመ ጊዜም የክርስቶስን መንጋዎች ከአርዮስ ከመቅዶንዮስና ከሰባልዮስ ተኩላዎች ጠበቀ። ይህም አባት በተሾመ በስድስተኛው ዓመት ለክርስቲያን ወገኖች ደግ የሆነ ቴዎዶስዮስ ነገሠ በዚያችም ዓመት ክብር ይግባውና መንፈስ ቅዱስን ስለ ካደው ስለ መቅዶንዮስ በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡ የመቶ ሃምሳ ቅዱሳን ኤጲስቆጶሳት ጉባኤ ተደረገ ይህም አባት ጢሞቴዎስ ሊቀ ጉባኤ ሆኖ መቅዶንዮስንና ሰባልዮስን አቡሊናርዮስንም ተከራከራቸው። ረትቶም አሳፈራቸው። እነሆ የክህደታቸውንና የክርክራቸውንም ነገር የካቲት አንድ ቀን ላይ ጽፈናል።
❤ ከዚህም በኃላ ይህ አባት በሹመቱ ዘመን አብያተ ክርስቲያናትን በማነፅና በሚገባውም ሥራ ሁሉ በእድሳታቸውም አሰበ። ለመጻተኞችም ቤቶችን ሠራላቸው።
❤ መንጋዎቹንም ሁልጊዜ ያስተምራቸው ነበር በመልካም እውቀቱና በትምህርቱ ጣዕም ሁልጊዜም በማስረዳቱ በቀናች ሃይማኖት አጸናቸው። ከአርዮስና ከመቅዶንዮስ ወገኖችም ብዙዎቹን መልሶ ክብር ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሆነች የቀናች ሃይማኖት አስገባቸው።
❤ በወንጌላዊው በቅዱስ ማርቆስ መንበርም ላይ ዘጠኝ ዓመት ተኩል ኖረ ከዚያም በኋላ ሐምሌ 26 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ጢሞቴዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 26 ስንክሳር።
✝ ✝ ✝
❤ "#ሰላም_ለጢሞቴዎስ_ለጴጥሮስ_እኍሁ። ጳጳሰ ሀገር ዘእምቅድሜሁ። በቊስጥንጥንያ ዘኮነ ሊቀ ማኅበሮሙ ለእሊአሁ። ተክዕወ ለምእመናን እምሁከተ ዐለውት ዘሠርሑ። ሰላም ብዙኅ እስከ የኀልፍ ወርኁ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሐምሌ 26።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ዚአከ ውእቱ ሰማያት ወእንቲአከ ይእቲ ምድር። ዓለምኒ በምልዑ ዘአንተ ሣረርከ። ባሕረ ወመስዐ ዘአንተ ፈጠርከ። መዝ 88፥11-12። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 6፥1-15።
✝ ✝ ✝
❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ይምጹኡ ተናብልት እምግብፅ። ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር። ነገስተ ምድር ሰብሕዎ ለእግዚአብሔር"። መዝ 67፥31-32። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ጢሞ 6፥3-20፣ 1ኛ ዮሐ 2፥1-12 እና የሐዋ ሥራ 5፥20-34። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 1፥18-25። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን ማርያም ወይም የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የአረጋዊው የቅዱስ ዮሴፍና የአባ ሰላም ከሳቴ ብርሃን የዕረፍት በዓል። ለሁላችንም ይሁንልን።
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ሐምሌ ፳፮ (26) ቀን።
❤ እንኳን #ለኢትዮጵያው_ጻድቅ የጌታችን መከራ በማሰብ ከተወለዱ ጀምሮ ተላጭተውት የማያውቁትን ፀጉራቸውን ከትልቅ ዛፍ ላይ እያሠሩ ይጸልዩ ለነበሩ ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ሳሙኤል_ዘደብረ_ሃሌሉያ ለዕረፍት በዐል በሰላም አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #አቡነ_ሳሙኤል_ዘደብረ_ሃሌሉያ፦ የትውልድ ሀገራቸው ተንቤን ነው፡፡ አባታቸው ይስሐለነ እግዚእ እናታቸው ትቀድሰነ ማርያም ይባላሉ፡፡ አቡነ አቢየ እግዚእ አጎታቸው ናቸው፡፡ እናታቸው እሳቸውን ፀንሳ ሳለ ቡራኬ ለመቀበል ወደ ወንድሟ ስትሄድ አቡነ አቢየ እግዚእ መሬት ላይ ወድቀው ሰግደውላታል፡፡ ደቀ መዛሙርቶቻቸውም "ለዚህች ሴት እንዴት ሰገዱላት?" ብለው ቢጠይቋቸው አቡነ አቢየ እግዚእ ስለ አቡነ ሳሙኤል ክብርና ጽድቅ ትንቢት ነግረዋቸዋል፡፡
❤ አቡነ ሳሙኤል ሲወለዱ እናታቸው ለአቡነ ዐቢየ እግዚእ ሰጠቻቸው፣ እርሳቸውም በሃይማኖት በመግባር ኮትኩተው ሁሉን አስተምረው አሳደጓቸው፡፡ አባታችን የጻድቃንና የሰማዕታትን ታሪክ እያነበቡ ያዝኑና ያለቅሱ ነበር፡፡ እንደ እነርሱ በሆንኩም እያሉ ይመኙ ነበር፡፡ አቡነ አቢየ እግዚእ ሀሳባቸውን በመንፈስ ተረድተውላቸው ነበርና መርቀው ባርከው አሰናበቷቸው፡፡ አቡነ ሳሙኤልም በሕፃንነታቸው መንነው ወደ አቡነ እንጦንዮስ ገዳም ገብተው በ14 ዓመታቸው መነኰሱ፡፡
❤ ከየት እንደመጣ የማይታወቅና መላ አካሉ እንደበረዶ ነጭ የሆነ አንበሳ መጥቶ እየመራቸው አሁን ደብረ ሃሌሉያ እየተባለ ወደሚጠራው ገዳማቸው ሄደው በዓታቸውን አጽንተው ገዳሙን መሠረቱት፡፡ አቡነ ሳሙኤል ዘሀለሎም እየተባሉ ይጠራሉ፡፡
❤ ጻድቁ የጌታችን መከራ በማሰብ ከተወለዱ ጀምሮ ተላጭተውት የማያውቁትን ፀጉራቸውን ከትልቅ ዛፍ ላይ እያሠሩ ይጸልዩ ነበር፡፡ እንዲሁ አድርገው ዛፍ ላይ ራሳቸውን ሰቅለው 40 ቀንና 40 ሌሊት ሲጸልዩ በመጨረሻ የታሠሩበት ፀጉራቸው ተነቅሎ ከመሬት ላይ ወደቁ፡፡ ደማቸውም እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ጌታችንም ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤልን አስከትሎ ተገልጦላቸው እጃቸውን ይዞ አንሥቷቸዋል፡፡ "ምን እንዳደርግልህ ትወዳለህ?" ቢላቸው ስለ ሀገራችን ሰላም ይልቁንም በዚህ በቆረቆሩት ገዳማቸው የሚኖሩትን ልጆቻቸውን እንዲጠብቅላቸው ለመኑት፡፡
❤ ጌታችንም በገዳማቸው ውስጥ በፍጹም ሕማም፣ ደዌና ተስቦ በሽታ እንደማይገባ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ለመንግሥተ ሰማያትም ያልታጨ ሰው በዚህ ገዳም ገብቶ አይቀበርም፡፡ ጻድቁ ከዛፉ ላይ ወድቀው ሳለ ጌታችንን እጨብጣለሁ ብለው የዘረጓት እጃቸው እያበራች ኖራለች፡፡ እንደ መብረቅም እየጮኸች ለገዳሙ እንደ ደወል ታገለግል ነበር፡፡ በመጨረሻም ሊያርፉ ሲሉ ልጆቻቸውን ሰብስበው ባርከዋቸዋል፡፡ ያ አቡነ ሳሙኤል የባረኩበት ቡራኬም በመጽሐፈ ግንዘት ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ዛሬም ድረስ ሰው ሲሞት "ቡራኬ ዘአቡነ ሳሙኤል" ብሎ ካህኑ ይደግማል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ በከተማ አካባቢ ግን እየተደረገ አይደለም፡፡ አቡነ ሳሙኤል ብዙዎችን ያመነኰሱ ሲሆን እንደነ አቡነ ተጠምቀ መድኅን፣ አቡነ ዘኢየሱስ፣ አቡነ ገብረ ክርስቶስ ያሉ ሌሎችንም በርካታ መነኰሳትን አፍርተዋል፡፡
❤ አባታችንን ያመነኰሷቸው አባት አቡነ እንጦንዮስ ሊጠይቋቸው ወደ ደብረ ሃሌሉያ ሄደው ሲመለሱ እንዲላላካቸው አንድ ትንሽ ልጅ ትተውላቸው ተመለሱ፡፡ አቡነ ሳሙኤልም በጥበብ መንፈሳዊ ኮትኩተው አሳደጉት፡፡
❤ አንድ ቀን ምግባቸው የሚሆን የእንጨት ፍሬዎችን ለመልቀም ከበዓታቸው ሲወጡ ልጃቸው እንዳይደክምባቸው በማሰብ በገዳማቸው ትተውት ለመሄድ አሰቡ፡፡ ብቻውን ስለሆነ አስፈሪ አራዊት እንዳያስደነግጡት በማሰብ ጉድጓድ ቆፍረው በዚያ አኑረውት ሄዱ፡፡ ርቀው ሄደው የእንጨቶችን ፍሬ ሲለቅሙ በጫካው እሳት ተስቶ ገዳማቸውንም ሙሉ በሙሉ አቃጠለው፡፡ ጻድቁ ስለ ልጃቸው ወደ ፈጣሪያቸው ጸልየው ካበቁ በኋላ ወደ ገዳማቸው ቢሄዱ የልጃቸው የራስ ፀጉር እንኳን ሳትቃጠል በሰላም አገኝተውታል፡፡ ያ ልጅም በኋላ አቡነ ገብረ መስቀል የተባለው ገድለኛ አባት ነው፡፡ ከአባታችን ከአቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌሉያ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎታቸውም ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።
