uk
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

Відкрити в Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

Показати більше
637
Підписники
-124 години
-47 днів
-1230 день
Архів дописів
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤ ❤ እንኳን #ለዐቢይ_ጾም_ሦስተኛ_ሳምንት_ለምኵራብ እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የምኵራብ_መዝሙር፦ ሃሌ ሉያ ፭ "#ቦአ_ኢየሱስ_ምኵራበ_አይሁድ ወመሀረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እምሥዋዕት #አነ_ውእቱ_እግዚአ_ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት #እግዚእ_ውእቱ_ለሰንበት_ወልደ_እጓለ_እምሕያው ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ #ቤትየሰ_ቤተ_ጸሎት_ይሰመይ_ቦአ_ምኵራቦሙ ወገሠፆሙ ያርምሙ አንበሩ ምህሮቶ ሞገሰ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሳአ አፋሁ"። ትርጉም፦ #ኢየሱስ_ወደ_አይሁድ_ምኵራብ_ገባ ሃይማኖት ቃል አስተማረ ከመስዋዕት ምጽዋትን አላቸው፤ #የሰንበት_ጌታዎ_የምሕረት_አባትዋ_እኔ_ነኝ አላቸው፤ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታዋ ነውና የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ ቤቴ የጸሎት ቤት ነው (ይባላል)  ምኵራባቸው ገባ ዝም ይሉ ዘንድም ገሠጻቸው። ጽምጹና ቃሉን ሞገስ (መውደድ) የነገሩትን የአፉን ለዛ አደነቁ። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በጾመ_ድጓው_ላይ።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #ምኩራብ፦ የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሣምንት ምኩራብ ይባላል። ❤ ምኵራብ ፦ የአይሁድ መቅደስ ቤተ ጸሎት ታላቅ አዳራሽ ነበር። ❤ በዚህ ሣምንት ጌታ በመዋዕለ ስብከቱ፡ በምኩራብ ገብቶ ማስተማሩ ይነገራል ማቴ 4፥23፣ ማር 1÷21፣ ሉቃ 4÷15። ❤ ክርስቶስ ለማስተማር በገባ ጊዜ አይሁድ ቤተ ጸሎቱን እንደ ስያሜው ሳይሆን መሸጫና መለዋወጫ መገበያያ አድርገውት ስለአገኛቸው ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ መሸጫ መለዋወጫ አደረጋችሁት ብሎ ሰዎችንና እንስሳትን በጅራፍ እየገረፈ ገበታቸውን እየገለበጠ አባሮአቸዋል ስለዚህ ይህ ሳምንት ለታሪኩ መታሰቢያ ምኩራብ ተብሉአል ማቴ 21፥12-13፣ ማር 11፥15-18፣ ሉቃ 19÷45-47 ዮሐ 2÷14-16። ❤ ቅዱሳን ሐዋርያትም እንደ ጌታችን ለጸሎትና ለትምህርተ ወንጌል ወደ ምኩራብ ይወጡ ነበር፡፡ የሐዋ ሥራ 3፥1፣ የሐዋ ሥራ 13፥5፣ የሐዋ ሥራ14፥1፣ የሐዋ 17-1፣ የሐዋ.10-17፣ የሐዋ ሥራ 18-4፣ የሐዋ ሥራ 19፥8። 1. ምኩራብ ፦ ለአምልኮና ለትምህርት ለሕብረተሰቡም ጠቅሞአል። 2. ምኩራብ በአለቆች ይመራ ነበር ማር 5፥ 22፣ የሐዋ ሥራ 3÷14-15፣ የሐዋ18፥8። 3 በየሳምንቱ ሕዝቡ ሁሉ በምኩራብ ይሰበሰቡ ነበር፡፡ ሉቃ 4÷16፣ የሐዋ ሥራ 15 21፡፡ 4 ወንዶችና ሴቶች ለየብቻቸው ይቀመጡ ነበር። 5 የእግዚአብሔር ቃል ሲነበብ አንባቢው እንዲሰማ በተዘጋጀው ከፍተኛ ቦታ ይቆም ነበር። የክብር ወንበሮች ከዚህ ቦታ ፊት ለፊት ነበሩ ማቴ 23÷6፣ ሉቃ 4፥20። ምንጭ፦ ከአምኃ ሥላሴ ፌስቡክ ፔጅ የተወሰደ።                                                                                 ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "እስከ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ። ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ። ወቀጻዕክዋ ለጾም ለነፍስየ። መዝ 68፥9-10። የሚነበቡት መልዕክታት ቈላ 2፥16-ፍ.ም፣ ያዕ 2፥14-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 10፥1-9። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 2፥12-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም የጾም ወራትና ዕለተ ሰንበት (ምኵራብ) ለሁላችንም ይሁንልን።                    

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #የካቲት ፳፪ (22) ቀን። ❤ እንኳን የፋርስ ንጉሥ ልጅ በጸሎቱ ከነበረባት ጋኔን ለፈወሳት #ለኤጲስቆጶስ_ለአባ_ማሩና ለዕረፍቱ በዓል መታሰቢያና በከሀዲ በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን #በፋርስ_አገር_ለተገደሉ_ሰማዕታት ለሥጋቸው ለፈለሰበት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በዚች ቀን በተጨማሪ ከሚታሰቡ፦ ከከበረ #ከአባ_ቡላና_ከሦስት_መቶ_ሰማንያ ሰማዕታት ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ማሩና፦ ኤጲስቆጶስ ማሩናንም ስለ ድንቆች ተአምራቶቹ ስለ ትሩፋቱና ስለ ጽድቁ የአኖርዮስና የአርቃድዎስ አባት ታላቁ ቴዎዶስዮስ ንጉሥ ላከው ከእርሱም ጋር እጅ መንሻ በመካከላቸው ስለ አለው ፍቅር ተላከ። ወደ ሳቦር ወደ ፋርስ ንጉሥም በደረሰ ጊዜ ታላቅ ክብርንም አከበረው በቤተ መንግሥቱም እልፍኝ ውስጥ አኖረው። ❤ ይህ ቅዱስም የንጉሡ ልጅ ጋኔን አድሮበት እንደታመመች በሰማ ጊዜ የከበረ አባ ማሩና ብላቴናዪቱን ጠርቶ በፊቱ አቁሞ በላይዋ ጸለየ ጋኔኑም ከእርሷ ወጥቶ ዳነች ንጉሡም ልጁ እንደ ዳነች አይቶ እጅግ ደስ አለው የአባ ማሩናንም ፍቅርና አክብሮት ጨመረ። ከዚህም በኋላ አባ ማሩና በፋርስ አገር በሰማዕትነት ስለሞቱ የከበሩ ሰማዕታት ሥጋቸውን ስለ መሰብሰብ ከንጉሥ ዘንድ ፈለገ ንጉሡም የሰማዕታትን ሥጋቸውን ይሰብስቡ ዘንድ አዘዘ ያች ቤተ ክርስቲያንም በዚች ዕለት ከበረች። ዳግመኛም በታላቋ ከተማ ውስጥ በከበረ አባ ማሩና ስም ያማረች ቤተ ክርስቲያንን ሠሩ እርሷም ማረፊያ የተባለች ናት። ❤ ከዚህም በኋላ ይህ አባት ወደ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ተመልሶ በሮሜ አገር ሁለት ዓመት ተቀመጠ የእነዚያ ሰማዕታት ቤተ ክርስቲያን በከበረችበት በዚች በየካቲት22 ዕለት ዐረፈ ከቤተ ክርስቲያኒቱም ክብር ጋር በዓሉንና መታሰቢያውን የሚከብሩበት ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የአባ ማሩና በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት 22 ስንክሳር።                              ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለማሩና_ሠናየ_ተልእኮ_ቀሲስ። ወዓዲ ካዕበ ኤጲቆጶስ። ቤተ ሰማዕታት ሐኒፆ በአገረ ፋርስ። በዕለተ ቀደሳ #በስመ_ኢየሱስ_ክርስቶስ። ተጸውዐ ዮም ለመርዓ ሐዳስ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_22።                  

❤ በመነኰሱም ጊዜ በብዙ ተጋድሎ ተጠመዱ ይልቁንም አባ ዘካርያስ በዚያም ወራት አረጋውያን አባ አብርሃምና አባ ገዐርጊ ነበሩ ወደ እርሳቸው እየመጡ በሥራቸው ሁሉ ያረጋጉዋቸውና ያጸኑዋቸው ነበር። የአገረ ስሐ ኤጲስቆጶስም በዐረፈ ጊዜ ሕዝቡ አባ ዘካርያስን አሰቡት እርሱንም ይሾሙላቸው ዘንድ ስለ አባ ዘካርያስ እየለመኑ ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ የመልእክትን ደብዳቤ ጻፈ። ሊቀ ጳጳሳቱም ወደ አስቄጥስ ገዳም ልኮ አባ ዘካርያስን ወደ እርሱ አስመጣው በአገረ ስሐ ላይም ኤጲስቆጶስነት ሾመው ሊቀ ጳጳሳቱም እጁን በላዩ በጫነ ጊዜ የእግዚአብሔርን ኃይል አየ በላዩ ወርዷልና ፊቱም በብርሃን ተጋረደ። ❤ ወደ መንበረ ሢመቱም በደረሰ ጊዜ ሕዝቡ በታላቅ ደስታ ተቀበሉት በዕለተ ሆሣዕና የእስራኤል ሕዝብ መድኃኒታችንን እንደተቀበሉት።ከዚህም፡በኋላ፡በትምህርቱና በድርሰቶቹ ቤተ ክርስቲያን ብርሃን ሆነች ቃሉም እጅግ ጣዕም ያለው እርሱም የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ የተመላ ነው። በመንበረ ሢመቱም አርባ ዘመን ኖረ እግዚአብሔርንም አገልግሎ የካቲት21 በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን። ምንጭ፦ የካቲት21 ስንክሳር።                              ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለኪ_ለብርሃን_ሕይወት_መፆሩ። አምሳለ ተቅዋም ዘወርቅ ጠበብተ እስራኤል ዘገብሩ። #ማርያም_ክብርት_ለእግዚአብሔር በክብሩ። ረስዪ ትሕትና አእጋርየ ይሑሩ። ትዕቢትሰ ለአምላክ ፀሩ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_21።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት። ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ"። መዝ44፥8-9። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 1፥46-57።                          ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ኪያከ ተወከሉ ወኢተኃፍሩ። አንሰ ዕፄ ወአኮ ሰብእ። ምኑን በኀበ ሰብእ ወትሑት በውስተ ሕዝብ"። መዝ 21፥5-6። የሚነበቡት መልዕክታት ፊል 1፥10-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 5፥5-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ  13፥1-7። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 22፥24-31። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታች የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ወራዊ፣ የቅዱስ አናሲሞስ የዕረፍት በዓልና የጾም ወራት። ለሁላችንም ይሁንልን።                   

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #የካቲት ፳፩ (21) ቀን። ❤ እንኳን አምላክን ለወለደች #ለእመቤታች_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም ለወራዊ በዓልዋ መታሰቢያ፣ ለከበረ ለሐዋርያው #ለቅዱስ_ጳውሎስ ደቀ መዝሙር ለሆነ #ለቅዱስ_አናሲሞስ ሰማዕትነት ለተቀበለበት ለዕረፍቱ በዓል፣ ለእስክድርያ ኃምሳ ሰባተኛ ሊቀ ጳጳሳት #ለአባ_ገብርኤል ለዕረፍት በዓልና ለአገረ ስሐ ኤጲስቆጶስ ለከበረ አባት #ለአባ_ዘካርያስ ለዕረፍት በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከከበሩ #ከአባ_አካክዮስና ከኢትዮጵያ አገር ጳጳስ #ከአባ_ገብርኤል ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ በዚች ቀን አምላክን ለወለደች #ለእመቤታችን_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም የበዓልዋ መታሰቢያ ነው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በአማላጅነቷና በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_አናሲሞስ፦ ይህም ቅዱስ አስቀድሞ ከሮሜ ሰዎች ወገን የሚሆን ስሙ ፊልሞና ለሚባል ለሮሜ ሰው አገልጋይ ሆኖ ነበር ይህም ፊልሞና በሮሜ በአስተማረ ጊዜ በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት በጌታችን አመነ ይህ ፊልሞናም ከዚያ ከሮሜ አገር ወደ አስባንያ ሔደ። ይህንንም አገልጋዩን አናሲሞስን ከእርሱ ጋር ወሰደው ሰይጣን ግን አናሲሞስን አሳተው ልቡንም ለወጠውና የጌታውን ገንዘብ ሰረቀው ጌታውም እንደሚቆጣው አውቆ ሸሽቶ ወደ ሮሜ ተመልሶ ሔደና በዚያ ተቀመጠ። በእግዚአብሔርም ፈቃድ ወደ ከበረ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ሔደ ትምህርቱንም ሰምቶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ ለቅዱስ ጳውሎስም ደቀ መዝሙሩ ሆነ። ነገር ግን የጌታውን ገንዘብ በመስረቁ በአናሲሞስ ልብ ጽኑ ኀዘን አደረ ለሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የሠራውን ሁሉ ነገረው ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም "አትፍራ ልብህም አይዘን" አለው ወደ ጌታው ወደ ፊልሞናም መልክትን ጻፈለት ይቺም ስለ አናሲሞስ የጻፋት ከመልእክቶቹ አንዲቱ ናት። በመልክቱም እንዲህ አለው "እኔ በእሥራቴ ጊዜ ስለወለድኩት ልጄ እማልድሃለሁ ይኸውም አናሲሞስ ነው። የቀድሞው ሥራው አልጠቀመህም ነበር ዛሬ ግን ላንተም ለእኔም እጅግ የሚጠቅም ሁኗልና አሁንም ወዳንተ ልኬዋለሁና ልጄ እንደመሆንህ ተቀበለው። የበደለህ በደልም ቢኖር ወይም የሚከፍልህ ቢኖር በኔ ላይ አድርገው"። ❤ ይህ የከበረ አናሲሞስም ወደ ፊልሞና ወደ ጌታው በደረሰ ጊዜ በማመኑና በመጸጸቱ ደስ አለው ሐዋርያው እንዳዘዘውም አደረገለት እጅግም ወደደው ብዙ ገንዘብም ሰጠው እርሱ ግን ምንም ምን አልወሰደም" እኔ በክርስትና ባለጸጋ ሁኜአለሁ" አለ እንጂ። ከዚህም በኋላ ሸኙትና ወደ ሮሜ አገር ተመለሰ በሰማዕትነት እስከ ሚሞትበት ጊዜ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስን የሚያገለግለ ሆነ። ይህም ቅዱስ ካህን ሆኖ ተሾመ ሐዋርያትም በሥርዓት መጽሐፋቸው በአንቀጽ ሰባ ሰባት፣ ሰማንያ አንድ፣ በኅምሳ ሦስትና በኅምሳ ሰባት በምስጋና አስታውሰውታል "እንደ ታማኝ ካህን ነው" አሉ። ❤ ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የምስክርነት ዕረፍት በኋላ የንጉሥ ጭፍራ አለቃ ይህን ቅዱስ ይዞ ወደ አንዲት ደሴት ሰደደው የዚያችን ደሴት ሰዎች ሃይማኖትን እያስተማራቸው ኖረ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው። ከብዙ ቀኖችም በኋላ የንጉሥ የጭፍራ አለቃ ወደዚያች ደረሰ የከበረ አናሲሞስንም ሕያው ሁኖ የክቡር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሃይማኖት ለሰዎች ሲያስተምራቸው አገኘው ጽኑ ግርፋትምንም ገረፈው ጭኖቹን እንዲሰብሩ አዘዘ ምስክርነቱንም የካቲት21 ፈጸመ። የሰማዕትነት አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አናሲሞስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ትኑር  ለዘላለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የእስክንድርያ_ሊቀ_ጳጳስ_አባ_ገብርኤል፦ ይህም አባት በታናሽነቱ በአስቄጥስ ገዳም መነኰሰ በጾም በጸሎት በስግደት ተጠምዶ ኖረ በውስጡም ትሕትና ፍቅር ቅንነት አለው። በአንዲት  ዕለት ስሙ መክሲሞስ ወደ ሚባል አረጋዊ ቤት ገባ እርሱም "ልጄ ከሰው ለምን ትሸሻለህ አንተ ግን በወንዶችና በብዙ ሴቶች መካከል ትኖር ዘንድ አለህ"አለው። እርሱ ግን የሽማግሌውን የቃሉን ትርጓሜ አላስተዋለም ከጠላትም ወጥመድ ያድነው ዘንድ ሁል ጊዜ በማልቀስ እግዚአብሔርን የሚለምን ሆነ። ❤ ከእርሱም አስቀድሞ የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል በዐረፈ ጊዜ ይህን አባት ይዘው ያለ ውዴታው ሊቀ ጳጳሳት አድርገው ሾሙት አረጋዊ አባ መክሲሞስ ትንቢት እንደ ተናገረለት በተሾመ ጊዜ በአስቄጥስ ገዳም ተቀምጦ የቀድሞውን ተጋድሎውንና አገልግሎቱን ቸለል አላለም ስለ አብያተ ክርስቲያንም ጉዳይ ወደ እስክንድርያና ወደ ምስር ይሔድ ዘንድ ግድ በአሉት ጊዜ ይሔዳል ፈጥኖም ወደ አስቄጥስ ገዳም ይመለሳል። ❤ እርሱም በዕድሜው ጐልማሳ ስለሆነ እንስሳዊት ፍትወት ትነሣሣበት ነበር እርሱም ያጠፋት ዘንድ ለጾም ለጸሎት ለስግደትም መትጋትን ያበዛል ሊያበርዳትም ባልተቻለው ጊዜ ለአንድ አረጋዊ ተናዘዘለት እርሱም እንዲህ አለው "ይህች እንስሳዊት ፍትወት ከጾምና ከጸሎት ከስግደትም ጋር ያለ ትሕትና ሥራ አትጠፋም በበለጠ ግን ትሕትና መድኃኒትቷ ነውና"። ይህንንም በሰማ ጊዜ የጉድፍ መጐተቻ ከብረት ሠራ አጭር የሆነ የቆሸሸ ልብስ በመልበስ በሌሊት ተነሥቶ የመኰሳቱን መንደር እየዞረ ቆሻሻውን ጠርጎ ተሸክሞ ወስዶ ከራቀ ቦታ ይጥለዋል። ይህንንም ሥራ እየሠራ ሁለት ዓመት ያህል ኖረ እግዚአብሔርም ንጽሕናውንና የልቡን ትሑትነት ተመልክቶ የባሕርይ የሆነውን ፍትወት አራቀለት። ይህም አባት በገድል እንደተጠመደ ሁኖ መንጋዎቹ በቀናች ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ እያስተማራቸውና እየገሠጻቸው እየመከራቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመት ኑሮ የካቲት21 በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ገብርኤል በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ዘካርያስ፦ ይህም አባት የጸሐፊዎች ወገን ነው አባቱ ግን ጸሐፊነቱን ትቶ ቅስና ተሾመ ስሙም ዮሐንስ ነው። ልጁ ዘካርያስም በአደገ ጊዜ ትምህቶችን ሁሉ ጽሕፈትንም የጽርእና የሮማውያንን ጥበብ የቤተ ክርስቲያንንም ሕግ ተማረ የንጉሥም የጭፍራ አለቃ ወሰደውና በንጉሡ ቤት ጸሐፊነት ሾመው። በጽሕፈቱም የአገረ ስሐ መኰንን የሆነው ስሙ አብጥልማዎስ የሚባል ወዳጅ ሆነው እርሱም ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደው ይመነኵሱ ዘንድ ተስማሙ። በዚያንም ጊዜ ከአስቄጥስ ገዳም ከአባ ዮሐንስ ደብር አንድ መነኰስ ወደነርሱ መጣ አብረውትም ይሔዱ ዘንድ ተስማሙ መኳንንቶችም ይህን በሰሙ ጊዜ መሔድን ከለከሉዋቸው። ከጥቂት ቀኖች በኋላ "ለእግዚአብሔር የተሰላችሁትን ስለት ለምን አትፈጽሙም" የሚላቸውን ራእይ አዩ በዚያንም ጊዜ በሥውር ወጡ እነርሱ ግን  መንገዱን አያውቁትም ነበር አንድ መነኰስም ተገለጠላቸውና ወደ አስቄጥስ ወደ አባ ዮሐንስ ገዳም መርቶ አደረሳቸው። መኳንንቱም መሔዳቸውን በሰሙ ጊዜ ከንጉሥ ዘንድ ደብዳቤ ተቀብለው በላክ ከገዳም ሊአሰወጡአቸው ተስማሙ የክቡር ባለቤት ጌታችንም ምክራቸውን በተነ።

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ  አሜን"። ❤             ❤ #የካቲት ፳ (20) ቀን። ❤ እንኳን #መኰንን_አርያኖስን_ለሚያጫውተው ለበገና ደርዳሪው #ለቅዱስ_ፊልሞንና ለጓደኛው #ለአናጉንስጢስ_ለቅዱስ_አስቃሎን ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓልና ለእስክድርያ አገር ሃያ አንደኛ ሊቀ ጳጳስ #ከሐዋርያው_ቅዱስ_አትናቴዎስ በኋላ ለተሹመት #ለአባ_ጴጥሮስ ለዕረፍት በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከማታሰቡ፦ ከከበሩ #ከቅዱሳን_ባስልዮስ_ከቴዎድሮስና #ከጢሞቴዎስ_በእስክድርያ አገር በሰማዕትነት ከዐረፉ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                        ✝ ✝ ✝ ❤ በገና ደርዳሪው #ቅዱስ_ፊልሞን ጓደኛው #ለአናጉንስጢስ_ለቅዱስ_አስቃሎን ፦ በአንዲትም ዕለት አርያኖስ አናጉንስጢስ አስቃሎንን ጠርቶ "ለአጵሎን ሠዋ" አለው አስቃሎንም ወደ ፊልሞን ሒዶ "በእኔ ፈንታ ብትሠዋ አራት የወርቅ ዲናር እስጥሃለሁ" አለው  ፊልሞንም "ልብስህን ስጠኝና ተሸፋፍኜ በአንተ ፈንታ እሠዋለሁ" አለው። በገባም ጊዜ አውቀውት "ምን ሆንክ" አሉት ፊልሞንም "በክርስቶስ የማን ክርስቲያን ነኝ"አላቸው። አርያኖስም "በሕይወት እንድትኖር ለአማልክት ሰዋ" አለው። "ፊልሞንም በክርስቶስ ስም ከመሞት በቀር ሕይወት የለም" አለው። አርያኖስም "ጥምቀትን ሳታገኝ ፈጥኜ እገድልሃለሁ ተስፋህን ታጣለህ" አለው። ፊልሞንም ሰምቶ የክርስትና ጥምቀትን ያድለው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ በዚያንም ጊዜ ከሰማይ ብሩህ ደመና መጥቶ አጠመቀው። አርያኖስም አፍሮ ቢመለስ ብሎ ሦስት ወታደሮች እንዲጸፋት አዘዘ ፊልሞንም "የእግዚአብሔር መላእክት ስለ እኔ ደስ ሲላቸው አያለሁና ከዚህ የከፋ ቢጻፋኝም አልፍርም" አለ። አርያኖስም ባላ ባለው ግንድ ላይ ሰቅለው በፍላፃዎች ይነድፉት ዘንድ አዘዘ ግን ምንም የነካው የለም ፍላፃውም እንዳልካው ለአርያኖስ ነገሩት ዳግመኛም እርሱ እንደ ቆመ ይነድፉት ዘንድ አዘዘ አንዲትም ፍላፃ ተመልሳ፡ የአርያኖስን ዐይን ነድፋ ዐሳወረችው በዚያን ጊዜ ከተሰቀለበት አውርደው ከአናጉንስጢስ አስቃሎን ጋር ራሱን እንዲቆርጡ አዘዘ ገድላቸውን፡ ፈጽመው የሰማዕትነት አክሊል የካቲት20 ተቀበሉ። ❤ መኰንኑም በፍላፃው ሕመም በተሠቃየ ጊዜ ከቅዱሳን ደም ወስዶ ከዐይኑ ውስጥ እንዲጨምር ሰዎች መከሩት ይህንንም ሲያደርግ ዳነ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም አመነ እሥረኞችንም ሁሉ ፈታቸው እርሱም መጋቢት ስምንት ቀን በዲዮቅልጥያኖስ እጅ በሰማዕትነት ዐረፈ። የሰማዕታትም በረከታቸው ከእኛ ጋር ትኑር ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን አሜን።                                                       ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ጴጥሮስ፦ የእስክድርያ ሃያ አንደኛ ሊቀ ጳጳስ ነው። ይህንንም ቅዱስ ከሐዋርያዊ አትናቴዎስ በኋላ በሹመቱ ወንበር በተቀበጠ ጊዜ ከንጉሥ ዳርዮስ ከከሀዲ አርዮስ ወገኖች ብዙ መከራ ደርሶበታል። ሊገሉትም በፈለጉ ጊዜ ሸሽቶ ሁለት ዓመት ያህል ተሠወረ አርዮሳውያንም ሉቅዮስ የተባለ ከሀዲውን ሰው በእርሱ ፈንታ በወንበሩ ላይ አስቀምጠው ሁለት ዓመት ኖረ። ከዚያም በኋላ ሃይማኖታቸው የቀና ምዕመናን ሁሉም ተነሥተው አርዮሳዊ ሉቅዮስን አሳደዱትና ይህን አባት ጴጥሮስን ወደ መንበረ ሢመቱ መለሱት አርዮሳውያንንም በመጣላት እያወገዛቸው እያሳደዳቸው ሰባት ዓመት ኖረ። ከዚህም በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም የካቲት20 ዐርፎ ወደ ዘላለም ዕረፍት ሔደ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ጴጥሮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት 20 ስንክሳር።                                                       ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_እብል_ለባስልዮስ_ብፁዕ። #ወቴዎድሮስ_ካዕለ#ወጢሞቴዎስ_ሣልስ ቅኑታነ ኃይል ወጽንዕ። ውስተ ቤተ መረዓ አምሳለ እሡራን ሰብእ። ዘተጸዋዕክሙ ኅቡረ ለስምዕ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_20።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦"ተገኃሥ እምእኩይ ወግበር ሠናይ። ኅሥሣ ለሰላም ወዴግና። እስመ አዕይንቲሁ ለእግዚአብሔር ኀበ ጻድቃኑ"። መዝ 33፥14-15። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ጢሞ 3፥1-13፣ 1ኛ ጴጥ 5፥1-11 እና የሐዋ ሥራ 9፥23-32።  የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥1-17። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም በዓልና የጾም ወራት። ለሁላችንም ይሁንልን።                  

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #የካቲት ፳ (20) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያውያን_ጻድቅ ውኃ ከዓለት ድንጋይ ላይ እያፈለቁ አሕዛብን ሁሉ እያስተማሩ ያጠምቁ ለነበረ፤ ኅብስትም ከሰማይ እየወረደላቸው ሕዝቡን ያቆርቡ ለነበረ ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ክፍለ_ማርያም_ዘድባጋ ከዚህ ዓለም እንደነ #ቅዱሳን_ሄኖክና_ኤልያስ ከሞት ለተሰወሩበት በዓልና #ለአባ_ገብረ_መርዓዊ_ዘአግዶ_ገዳም ለመታሰቢያ በዓላቸው እግዚአብሔር አምላክ በሰላም አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ለአቡነ_ክፍለ_ማርያም_ዘድባጋ፦ ትውልዳቸው እንደርታ ሲሆን በ14 ዓመታቸው መንኵሰው፡ መንነው በቅተው ሲኖሩ በአንድ ወቅት ወደ አክሱም ሄዱና ወላጆቻቸው ካሉበት ደረሱ። ከቅዳሴ በኋላ መክፈልት ቆርሰው ሲያድሉ ወላጅ እናታቸው ከስተውና ጠቁረው ስላዩአቸው ለእናታቸው አዳልተው በብዙ ሰጧቸው። እናትየው ግን ጻድቁ የሰሩትን አያወቁም ነበር። ጻድቁ ከብቃታቸው የተነሳ መና ከሰማይ አየወረደላቸው ከዓለትም ላይ ውኃ እያፈለቁ ይጠጡ ነበር። አድሎ ስላደረጉ ግን በዚህ ድርጊታቸው እግዚአብሔር ተቆጥቷቸው የሰጣቸውን ይህን ጸጋውን ነሳቸው። አቡነ ክፍለ ማርያምም ይህን ባወቁ ጊዜ "ወዮልኝ ወዮታ አለብኝ" ብለው ከሰው ሳይገናኙ ዋሻ ገብተው ድፍን 11ዓመት በለቅሶና በዋይታ እግዚአብሔርን ለምነው ነው ይቅር ተብለው የቀደመ ጸጋቸውና ክብራቸው የተመለሰላቸው። ❤ ከዛ በኋላ ውኃ ከደረቅ ጭንጫ ላይ እያፈለቁ አሕዛብን ሁሉ እያስተማሩ ያጠምቁ ጀመር። ኅብስትም ከሰማይ እየወረደላቸው ሕዝቡን ያቆርቡ ጀመር። ጻድቁ በመጨረሻ በየካቲት 20 ቀን እንደነ ሄኖክና ኤልያስ ዐርገዋል እንጂ በምድር ሞት አልቀመሱም። ትልቅና አስደናቂ ገድላቸው በአክሱም ይገኛል። ከአቡነ ክፍለ ማርያም እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።              

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #የካቲት ፲፱ (19) ቀን። ❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ በአባ ጰንጠሌዎን እጅ ምንኵስና ለተቀበሉ ለታላቁ አባት #ለአቡነ_አባለ_ክርስቶስ ለልደታቸው በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ስለ_አቡነ_አባለ_ክርስቶስ_ልደት፦ በመንፈስ ቅዱስ የተወለደው ይኸ ጻድቅ አባለ ክርስቶስ የአባቱ ስም አቃርዮስ ሲባል ትውልዱ ከላይኛው ግብጽ ነው፤ የእናቱ ስም ታውክልያ የምትባል ሲሆን ትውልዷ ከሰሜን ኢትዮጵያ በጌ ምድር ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ነው። ከየሀገራቸው ግብጽና ኢትዮጵያ የመጡ እነዚያም ሰዎች ቡሩካን ናቸው። በኢትዮጵያ የነገሥታት ከተማ በኾነችው በአኵሱም ተገናኙ። ጊዜውም በ910 ዓ.ም ነበር። በዚኸም ዘመን አባቱና እናቱ በአኵሱም ሀገር ሳሉ ይኽ ልጅ ተጸነሰ። ❤ ይኸ አባለ ክርስቶስ የተባለ ሕፃን ከእናቱ ከታውክልያ ማኅፀንና ከአባቱ ከአቃርዮስ አብራክ የእግዚአብሔር ፀባዖት ስሞች በሰውነቱ መሐል በዕብራይስጥ ቋንቋ ዲካባ፣ ማርትያስ፣ ክስብኤል ተብሎ ተጽፎበት የካቲት ዐሥራ ዘጠኝ ቀን በመላእክት አለቃ በቅዱስ ገብርኤል በወርኀዊ በዓሉ ዕለት በአኵሱም ከተማ ተወለደ። ❤ አባቱ አቃርዮስና እናቱ ታውክልያ ይኸን ኅቡዕ የመለኮት ስም በልጃቸው ሰውነት ላይ ተጽፎ በአገኙ ጊዜ ትርጒሙ ምን ይሆን እያሉ ፈጽመው አደነቁ። የሕፃን አባለ ክርስቶስ አባትና እናት በሰውነቱ ላይ ያለውን ምልክቱንና ጽሕፈቱን በገበዘ አኵሱም በቤታቸው ውስጥ እያዩ ሳለ የእግዚአብሔር አዶናይ የስሞችን ነገር ምልክቱና ትርጓሜው ምን ይሆን እየተባባሉ ሳለ ያን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በድንገት መጣ። ❤ ይኸ የኀይል መልአክ ቅዱስ ሚካኤልም በአቃርዮስና በታውክልያ ፊት ቆመ። ያን ጊዜም "ክቡራን የእግዚአብሔርባሮች ጻድቃን ሆይ! ሰላም ለእናንተ ይሁን" አላቸው። "እኔ በዚኽ 'አባለ ክርስቶስ' ተብሎ ታላቅ ስምን በሚሠየም ሕፃን በሰውነቱ ላይ የተጻፈውን የእግዚአብሔር ታዖስ የስሞቹን የጽሕፈቱን ነገር እተረጒምላችሁ ዘንድ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ እናንተ መጣሁ፤ ይኸ ጠላትን የሚያስገዛና አጋንንትን የሚያሳድድ ነውና" አላቸው። "ይኸ ሕፃን አባለ ክርስቶስም ከአደገ በኋላ መጀመሪያ በገበዘ አኵሱም ይኖራል። ዳግመኛም የእናቱ የትውልድ ሀገር በጌ ምድር ውስጥ እግዚአብሔርን የምትፈራ የብፅዕትና የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ማደሪያ ወደሆነችው እና እማሙዝ ተብላ ወደተጠራችው ከእናንተ ጋር ይሔዳል። በዚያም በእናቱ ሀገር ዐሥራ አምስት ዓመት ትኖራላችሁ"። ❤ "ከዚያም በኋላ የነገሥታት ከተማ የሙሴ ጽላት ማደሪያ ወደሆነች ወደ ገበዘ አኵሱም ትመለሳላችሁ። በዚኸ በገበዘ አኵሱም ውስጥም ዐሥራ ሰባት ዓመታትን ትኖራላችሁ። ዛሬም በዚኸች በመጋቢት ኻያ ስምንት ቀን ፈጥናቹ አጥምቁት" አላቸው። አባቱ አቃርዮስና እናቱ ታውክልያ ከድልነዓድ በፊትና ከላሊበላውያን ነገሥታት ከዛጔ ነገሥታት በፊት የነበረው ንጉሠ ጽዮን በነገሠ በኻያኛው ዓመት ወደ ገበዘ አኵሱም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሔዱ። ያን ጊዜ ጳጳሱ አባታችን ሉቃስ ያጠምቀው ዘንድ ቀረበ። ❤ በሕፃን አባለ ክርስቶስ በሰውነቱ ላይ ያለውን የትርጓሜው ነገር ተገልጦ ያልታወቀ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፈውን በአየ ጊዜ ደነገጠ፤ ወደቀም፤ ታወከም፤ እንደ ሰከረም ሆነ። ነገር ግን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ፈጥኖ መጥቶ አነሣውና ከድንጋጤው አነቃው። ከድንጋጤውም ካነቃው በኋላ "አንተ የጳጳሳት አለቃ አባ ሉቃስ ይኸን ድንቅ በአየህ ጊዜ ፈጥነህ አጥምቀው" አለው። "ስሙንም አባለ ክርስቶስ" ብለህ አውጣለት፤ ትርጓሜውም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እንደ ቅዱስ ፋኑኤል አጋንንትን የሚያባርር፤ እንደ ጌታው እንደ ክርስቶስ መድኀኔ ዓለም ሕሙማንን የሚያድናቸው፤ በአጋንንት የተያዙትን፤ አጋንንት የሚጥሉዋቸውንና ሕሙማንን የሚፈውሳቸው፣ አጋንንትንም የሚያባርራቸው ነው"። ❤ "ይኸም ሕፃን አባለ ክርስቶስ ከተጠመቀና ከአደገ በኋላ በሕይወት ዘመናቸው እግዚአብሔርን ደስ ለአሰኙት ለማኅበረ ዴጔ ጻድቃን አባቶች አቅራብያ በሆነች ናዕዴር በምትባል በተባረከችና በተቀደሰች ሀገር ይኖራል"። "የደብሩም ስም አልሓትያ ትባላለች። ወደ ደብሩ በሚገባበት ጊዜም አንደበታቸው ድዳ የሆኑ ሰዎችና የእግዚአብሔር ወዳጅ የአምላክ ባሪያ እንደሆነ እንደ ሙሴ አንደበታቸው የተዘጋ በእርስዋ ያገኛል። ወደ ደብሩ በሚገባበት ጊዜም እነዚያ የተባረኩ ሕዝቦች የአንደበታቸው ድዳነት ማሰሪያ ይፈታል። ደብሩም ደብረ አልሓትያ ተብላ ትጠራለች። ❤ "ዛሬም ፈጥነህ አጥምቀው፤ ስሙንም 'አባለ ክርስቶስ' ብለህ አውጣለት" አለው። ይኸም አባት ጳጳሱ አባታችን ሉቃስ በዚያን ጊዜ መጋቢት ኻያ ስምንት ቀን በገበዘ አኵሱም አጠመቀው፣ ቅዱስ ቍርባንም አቈረበው። የተቀደሰች የልደቱ በረከት በኹላችን ሕዝበ ክርስቲያን ላይትሁን ለዘለዓለሙ አሜን። ከአባታችን ከአቡነ አባለ ክርስቶስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ ገድለ አባለ ክርስቶስ።                  

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤             ❤ #የካቲት ፲፱ (19) ቀን። ❤ እንኳን #ለተጋዳይ_መነኰስ ለሆኑት በዝሙት ላለመውደቅና ገሃነመ እሳትን በማሰብ እግራቸውን የሚነድ እሳት ውስጥ በመጨመር ዘማዊቷንም ሴት ለንስሓና ለጽድቅ ላበቋት ለታላቁ አባት #ለአባ_መርትያኖስ_ሥጋቸው_ከአቴና_አገር_ወደ_አንጾኪያ_ለፈለሰበት_በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                         ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #አባ_መርትያኖስ፦ እርሱም ሽንግላ በኃጢአት ልትጥለው በወደደች ጊዜ ከአመንዝራ ሴት ከተፈተነ በኋላ እርሱ ግን መንኵሳ በገድል እስከ ተጸመደች ድረስ ስቦ ወደ ንስሓ መልሷታል። ከዚህም በኋላ መኖሪያውን ትቶላት ከአገር ወደ አገር የሚዞር ሆነ ከአቴና አገርም ደርሶ በዚያ ጥቂት ቀን ኖረ ጥቂትም ታመመና በሰላም አረፈ ዜናው በግንቦት ሃያ አንድ ቀን እንደተጻፈ። ❤ የከበረ ቴዎድሮስም ለአንጾኪያ አገር በከሀዲው የፋርስ ንጉሥ ዘመን ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ይህ አባት የካህናት አለቆችንና ምእመናንን ልኮ ሥጋውን ከአቴና አፍልሰው ወደ አንጾኪያ ከተማ አመጡት በምስጋናም እየዘመሩ አክብረው ተቀበሉት ሊቀ ጳጳሳቱም ተሳለመው በሣጥንም አድርጐ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖረው። በዚችም ዕለት የካቲት19 በዓልን አደረገለት። ለእግዚአብሔር ምስና ይሁን እኛንም በአባ መርትያኖስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት19 ስንክሳር።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ "#ሰላም_ለፍልሰተ_ሥጋከ ኀበ አንጾኪያ እምአቴና። #በእደ_ቴዎድሮስ አብ ዘሥርግው በጵጵስና። #መርትያኖስ_ተወከፍ ዘመሥዋዕተ ቃል ጼና። በከናፍረ ልብ ወበአፈ ኅቡእ ሕሊና። ሶበ ለሥጋከ እኤምኅ ሣፁና"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲ_19።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "እስመ ብከ እምድኅን እምንሱት። ወበአምላኪየ እትዐደዋ ለዕረፍት። ለአምላኪየሰ ንጹሕ ፍኖቱ"። መዝ 17፥19-20።  የሚነበቡት መልዕክታት ሮሜ 7፥22-ፍ.ም፣ ያዕ 4፥1-11 እና የሐዋ ሥራ 16፥16-22። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 13፥10-18። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም በዐልና የጾም ወራት። ለሁላችንም ይሁንልን።                 

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #የካቲት ፲፰ (18) ቀን። ❤ እንኳን #ከሰባ_ሁለቱ_አርድእት ለአንዱ ለጌታችን ወንድም ለተባለ #ለሐዋርያው_ለቅዱስ_ያዕቆብ ለዓመታዊ ለመታሰቢያ በዓሉና ለታማኝ ለከበረ አባት ለአንጾክያ አገር ሊቀ ጳጳስ ከአርዮሳውያን ብዙ ስደትና እንግልት ለደረሰበት #ለአባ_መላልዮስ ለዕረፍቱ  መታሰቢያ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን፡፡                                                          ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱስ_ያዕቆብ_ወልደ_ዮሴፍ፦ ይኸውም ቅዱስ የጌታችን ወንድም የተባለውና የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ የነበረው ነው፡፡ እርሱም የጠራቢው የዮሴፍ፡ልጅ ሲሆን ከአራቱ ልጆቹ ትንሹ መጨሻው ነው፡፡የቅዱስ ያዕቆብ ወላጅ እናቱ በልጅነቱ ስለሞተችበትና የብርሃን እናቱ የሆነች ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን ዮሴፍ አረጋዊ በ83 ዓመቱ ጠባቂ ይሆናት ዘንድ ወደቤቱ ሲወስዳት ድንግል ማርያም ቅዱስ ያዕቆብን የሙት ልጅ ሆኖ አግኝታው ከተወደደ ልጇ ከጌታች ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብራ ተንከባክባ አሳድጋዋለች፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ያዕቆብ ድንግልና ንጹሕ ሆኖ ከጌታችን ጋር እየተጫወተ አብሮ አድጓል፡፡ ❤ ከጌታችን ዕርገት በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ አድርገው ሾመውታል፡፡ ብዙዎችንም አስተምሮ ወደ ቀናች ሃይማኖት መልሷቸዋል፡፡ ሕዝቡም የታመሙትን ድውያንን ሁሉ እያመጡለት ይፈውሳቸው ነበር፡፡ ከኢየሩሳሌምም ውጭ እየሄደ ያላመኑትንም አስተምሮ እያጠመቀ ቤተ ክርስቲያን ይሠራላቸው ነበር፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ በጾም በጸሎት ሆኖ በመቆም ብዛት እግሮቹ አብጠው ነበር፡፡ ❤ አንድ ቀን አይሁድ ተሰብስበው መጥተው ጌታችን የማን ልጅ እንደሆነ ይነግራቸው ዘንድ ወደ ቅዱስ ያዕቆብ መጡ፡፡እነርሱም ወደ ቅዱስ ያዕቆብ የመጡት ጌታችን የዮሴፍ ልጅ እንደሆነና የእርሱም የሥጋ ወንድም እንደሆነ እንደሚነግራቸው አስበው ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ያዕቆብ ከፍ ካለው ከሦስተኛው መደብ ላይ ወጥቶ ጌታችን የራሱ የያዕቆብና የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ መሆኑን መሰከረባቸው፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ፍጹም አምላክ መሆኑን፣ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና ከአብም ጋር፡ ትክክል እንደሆነ መሰከረባቸው፡፡ ይህንንም በሰሙ ጊዜ አይሁድ እጅግ ተናደው በጽኑ ግርፋት ካሠቃዩት በኋላ ራሱን ቀጥቅጠው ስለገደሉት ሰማዕትነቱን፡ ሐምሌ 18 ቀን በድል ፈጽሟል፡፡ ከሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ረድኤት በረከትን ያሳትፈን። በጸሎቱ ይማረን!። ምንጭ፦ ገድለ ሐዋርያትና መዝገበ ቅዱሳን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_መላልዮስ፦ ይህም ቅዱስ አዋቂና አስተዋይ ነበረ ነው፡፡ በታናሹ ቈስጠንጢኖስም ዘመነ መንግሥት በአንጾኪያ አገር ላይ ሊቀ ጵጵስና ተሾመ፡፡ ከተሾመም እስከ ሠላሳ ቀን ኖረ፡፡ ከዚያም በኋላ አርዮሳውያንን አወገዛቸው። በአንጾኪያ ካለች ቤተ ክርስቲያንም፡ አሳደዳቸው። ንጉሡም በሰማ ጊዜ ከመንበረ ሢመቱ ሊቀ ጳጳሱን አሳደደው እርሱ አርዮሳዊ ነውና። ❤ የአንጾኪያ አገር ታላላቆችና ኤጲስጶሳት ካህናቱም ተሰብስበው ስለ ሊቀ ጳጳሳቱን ይመልስላቸው ዘንድ የልመና ደብዳቤ፡ ጽፈው ለንጉሡ ላኩ፡፡ ንጉሡም ልመናቸውን ተቀብሎ መለሰላቸው፡፡ ይህም አባት በተመለሰ ጊዜ አርዮሳውያንን ወደ ማውገዙ ተመለሰ በቃላቸው የሚያምኑትንም ስሕተታቸውንና ስድባቸውን ግልጽ እያደረገ ወልድ ከአብ ባሕርይ እንደ ተወለደ በመለኮቱም ትክክል እንደሆነ በሁሉ የሚሰብክ የሚያስተምር ሆነ። ዳግመኛ አርዮሳውያን ተነሡ የንጉሡን ልብ ወደእርሳቸው እስከ መለሱ ድረስ ይህን አባት እየወነጀሉ ወደ ንጉሥ ጻፉ ዳግመኛም ልኮ ከፊተኛው ወደሚርቅ አገር አሳደደው። ወደ ተሰደደበት አገር በደረሰ ጊዜ መልእክቶቹን ጽፎ በመላክ ከወገኖቹ ጋር እንደ ሆነ ከእርሳቸውም ሥውር የሆነውን የመጻሕፍትን ቃል ይተረጒምላቸው ነበር፡፡ በአንጾኪያ ላሉ መንጋዎቹም ይደርሳቸውል አዋቂዎች የሆኑ ኤጲስቆጶሳትንና ቀሳውስትን ልዩ በሆነች ሦስትነት ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ አባቶቻችን ያስተማሩዋት የቀናች ሃይማኖትን እንዲህም እያደረገ እስከ ዐረፈበት ቀን ድረስ በተሰደደበት ብዙ ዘመናት ኖረ። ❤ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም አመስግኖታል፡፡ የምስጋና ድርሰቶችንም ደረሰለት፡፡ ስለቀናች ሃይማኖትም ብዙ መከራ ስለደረሰበት ክብሩ ግርማው ከከበሩ ሐዋርያት ክብር እንደማይጎድል ተናገረ፡፡ የአባ መላልዮስ ዕረፍቱ የካቲት18 ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱ ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የካቲት 18 ስንክሳር።                              ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለመላልዮስ_ዘእሙን_ነገሩ። አርዮሳውያን ሕዝብ እለ አውጽእዎ እማኅደሩ። #አፈ_ወርቅ_ዮሐንስ_በከመ_ወደሶ በዕለተ ተዝካሩ። እንበይነ ስደቱ ወእንበይነ ብዙኅ ኅሣሩ። እምሐዋርያት ይቤ ኢየሐጽጽ ክብሩ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_18።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ይዘግቡ ወኢየአምሩ ለዘይስተጋብዑ። ወይእዜኒ መኑ ተስፋየ አኮኑ እግዚአብሔር። ወትግሥትየኒ እምኀቤከ ውእቱ"። መዝ 38፥6-7። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 6፥19-22።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ። ውስተ ኵሉ ምድር ወጽአ ነገሮሙ። ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ"። መዝ 18፥3-4። የሚነበቡት መልዕክታት ገላ 1፥15-ፍ.ም፣ ያዕ 1፥1-12 እና የሐዋ ሥራ 21፥17-27። የሚነበበው ወንጌል ማቴ13፥53-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም የቅዱስ ያዕቆብ የዕረፍት  በዓልና የጾም ወራት። በሁላችንም ይሁንልን።                

❤ "በስመ አብ  ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤           ❤ #የካቲት ፲፯ (17) ቀን። ❤ እንኳን #የእግዚአብሔር_ሰው ለሆነ #ለየዋህ_ለትሑቱ_ለነቢያት_አለቃ_ለቅዱስ_ሙሴ ለዕረፍቱ መታሰቢያ ለበዓል፣ ከላይኛው ግብጽ ከአክሚም መንደር ለሆነ ስለ #እግዚአብሔር_አብ_አባትነት_ስለ_ወልድ_ልጅነት መስክሮ በእስላሞች መኰንን እጅ ሰማዕትነት ለተቀበለ #ለታላቁ_ጻድቅ_ወሰማዕት_ለመነኰስ_አባ_ሚናስ ለዕረፍቱ በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ሊቀ_ነቢያት_ቅዱስ_ሙሴ፦ ይህ ነቢይ ነፍሱን ስለእርሳቸው አሳልፎ እስከ መስጠት ደርሶ ከእግዚአብሔር ወገኖች ጋር የደከመ ነው እርሱም በግብጽ አገር በኤርትራ ባሕርም ድንቆች ተአምራትን ያደረገ ነው። ይህም ስለ ፈርዖን ትእዛዝ ወላጆቹ በግብጽ ወንዝ ውስጥ በጣሉት ጊዜ አውጥታ ላሳደገችው ለፈርዖን ልጅ ለተርሙት ልጅዋ መባልን አልወደደም። እርሱ ፈርዖን የዕብራውያንን ወንዶች ልጆች ይገድሏቸው ዘንድ አዝዞ ነበርና። በአገኘችውም ጊዜ ለርሷ ልጅ ሊሆናት ወስዳ በመልካም አስተዳደግ አሳደገችው። ❤ አርባ ዓመትም በሆነው ጊዜ አንዱን ዕብራዊ የግብጽ ሰው የሆነ ሲያጠቃው አየ ለዕብራዊው ተበቅሎ ግብጻዊውን ገደለው። በማግሥቱ ሁለት ዕብራውያን እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አያቸው ሊያስታርቃቸውና በመካከላቸው ሰላምን ሊአደርግ ወደደ። አንዱ ዐመፀኛም "ትላንት ግብጻዊውን እንደገደልከው ልትገድለኝ ትሻለህን" አለው። ስለዚህም ነገር ሙሴ ፈርቶ ወደ ምድያም አገር ሸሸ በዚያም ሚስት አግብተሸ ሁለት ልጆችን ወለደ በዚያም አርባ ዓመት ኖረ በጳጦስ ቊጥቋጦ ውስጥ እግዚአብሔር ተናገው። ወደ ግብጽ አገርም ሒዶ የእስራኤልን ልጆች ከዚያ እንዲያወጣቸው አዘዘው። ❤ ከዚህም በኋላ ሕዝቡን ከግብጽ አገር አወጣቸው የኤርትራንም ባሕር ከፍሎ በውስጡ አሳለፋቸው የባሕሩንም ውኃ በጠላቶቻቸው በፈርንና በሠራዊቱ ላይ ገልብጦ አሠጠማቸው። ከዚህም በኋላ በምድረ በዳ ውስጥ አርባ ዓመት ሙሉ መና አወረደላቸው ውኃንም ከአለት አፈለቀላቸው ይህን ሁሉ በጎ ሥራ በዚህ በደግ ነቢይ ሙሴ እጅ እግዚአብሔር አደረገላቸው እነርሱ ግን ይዘልፉት ነበር ብዙ ጊዜም በድንጊያ ሊወግሩት ሽተው ነበር። እርሱ ግን በእነርሱ ላይ ልቡን አስፍቶ በመታገሥ ስርሳቸው ወደ እግዚአብሔር ይማልዳል። እነርሱንም አብዝቶ ከመውደዱ የተነሣ እግዚአብሔርን "አቤቱ የዚህን ሕዝብ በደሉን ይቅር ካላክ ከሕይወት መጽሐፍህ ሰርሰዘኝ" አለው። ❤ ሰው ከወዳጁ ጋር እንደሚነጋገር አምስት መቶ ሰብዓ ቃላትን ከእግዚአብሔር ጋር እንደተነጋገረ መጽሐፍ ምስክር ሆነ። የእስራኤል ልጆችም በሚያዩት ጊዜ እንዳይሞቱ ፊቱን እስከ መሸፈን ድረስ በእግዚአብሔር በጌትነቱ ብርሃን ፊቱ በራ። ❤ መቶ ሃያ ዓመት የሆነ ዕድሜውም በተፈጸመለት ጊዜ ለአገልጋዩ ለነዌ ልጅ ለኢያሱ ሕዝቡን እርሱ እንዲጠብቃቸው በእጁ ውስጥ እንዲአስረክበው እግዚአብሔር ሙሴን ለኢያሱ አስረክብ ብሎ አዘዘው። ሙሴም ኢያሱን ጠርቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አዘዘው ሕጉንም እንዲጠብቅ ሕዝብንም ለኢያሱ በእጁ አስረከባቸው ወደ ምድረ ርስት እርሱ እንደ ሚአስገባቸው አረጋገጠላቸው። ❤ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው በምስክር ድንኳን ውስጥ የሚሠራውን ሁሉ ሠርቶ ከአዘጋጀ በኋላ በናባው ተራራ ውስጥ ዐረፈ በዚያም በመላእክት እጅ በሥውር ተቀበረ። የእስራኤል ልጆች ወስደው እንዳያመልኩት እግዚአብሔር የሙሴን ሥጋ ሠወረ። በእስራኤል ልጆች ውስጥ እንደ ሙሴ ያለ ደግ የዋህ ቅን የሆነ ነቢይ እንደማይነሣ መጽሐፍ ምስክር ሆነ። ❤ ሰይጣንም የሙሴን ሥጋ ለእስራኤል ሊገልጠው በወደደ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ በጻፈው መጽሐፍ እንደመሰከረ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ገሠጸው ከዚህም ሥራ ከለከለው። የእስራኤል ልጆች አርባ ቀን አለቀሱለት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በሊቀ ነቢያት በቅዱስ ሙሴ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የመስከረም 8 ስንክሳር።                               ✝ ✝ ✝ ❤ #መነኰስ_አባ_ሚናስ፦ የዚህም ቅዱስ፡ ወላጆቹ ምድርን የሚያርሱ ክርስቲያን ገበሬዎች ናቸው። እርሱም ይህን ዓለም ንቆ ትቶ በአገረ አክሚም በሚገኝ በአንድ ገዳም መነኰሰ ለመብልና ለመጠጥ ሳይገዛ በየሁለት ቀን እየጾመ ብዙ ቀኖችን ኖረ ከዚያም ወጥቶ ወደ እስሙናይን አገር ሒዶ በአንድ ገዳም ውስጥ እያገለገለና እየተጋደለ ከገዳሙ ደጃፍ ሳይወጣ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖረ። ❤ እስላሞችም በግብጽ አገር በነገሡ ጊዜ ለእግዚአብሔር ከርሱ ጋር ለዘላለሙ ህልው የሆነ የባሕርዩ የተወለደ ልጅ የሚሠርፅ መንፈስ ቅዱስም የለውም እንደሚሉ ሰማ ስለዚህም ነገር እጅግ አዘነ። ከአበ ምኔቱም ቡራኬ ተቀበለ ወደ እስሙናይን ከተማ ወጥቶ ሔደ የእስላሞች ሠራዊት አለቃ በሆነ በመኰንኑ ፊት ቁሞ እንዲህ አለው "እናንተ ለእግዚአብሔር ከባሕርዩ የተወለደ ልጅ እንደ ሌለው አድርጋችሁ የምትናገሩ እውነት ነውን?" መኰንኑም "አዎን ልጅ አለው ማለትን ከእግዚአብሔር እናርቃለን" አለ። አባ ሚናስም "ያለ ልጅ ልታምኑ አይገባም እርሱም ያለ ዘር ያለ ሩካቤ የሆነ ነው ከባሕርዩ ተወለደ እንጂ" አለው። መኰንኑም "ልጅ አለው ማለት በሕጋችን ክህደት ነው" አለ። አባ፡ሚናስም እንዲህ አለው "መኰንን ሆይ እወቅ የከበረ ወንጌል በወልድ ያመነ የዘላለም ሕይወት አለው በእግዚአብሔር ልጅ በወልድ ያላመነ ሕይወትን አያይም የእግዚአብሔር ቊጣ በላዩ ይወርዳል እንጂ ብሏልና"። ስለዚህም መኰንኑ እጅግ ተቆጣ ራሱንም በሰይፍ እንዲቆርጡ ሥጋውንም በየቊርጥራጭ ቆራርጠው ከባሕር እንዲጥሉት አዘዘ ምእመናንም ሥጋውን ወስደው በበጎ አገናነዝ ገንዘው ቀበሩት መታሰቢያውንም አደረጉ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የየካቲት17 ስንክሳር።                             ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_እብል_ለሚናስ_ፍጹም። ዘሀገረ አክሚም። ሶበ ይብል አምላክ ወልደ ማርያም ተንባላት በበግማድ ገመድዎ ዮም። ወወረውዎ ውስተ ባሕር መሥጥም"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_17።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "አርአየ ፍናዊሁ ለሙሴ። ወለደቂቀ እስራኤል ሥምረቶ። መሐሪ ወመስተሣህል እግዚአብሔር"። መዝ 102፥7-8። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 11፥23-29፣ ይሁ 1፥7-11 የሐዋ ሥራ 7፥20-44። የሚነበበው ወንጌል  ሉቃ 20፥37-41። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ሙሴ የዕረፍት በዓልና የጾም ወራት ለሁላችንም ይሁንልን።