cookie

Ми використовуємо файли cookie для покращення вашого досвіду перегляду. Натиснувши «Прийняти все», ви погоджуєтеся на використання файлів cookie.

avatar

ሰኞ መርሃ ግብር / ማኅበረ ጽዮን

ሰኞ መርሃ ግብር / ማኅበረ ጽዮን: ✍የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተከርስቲያን ያከበረቻቸው ቅዱሳን ታሪክ ✍ የቤተክርስትያኗን ትክክለኛ አስተምህሮዋን የያዙ መዝሙራት ✍ አጭርና ተከታታይ ትምህርቶች ✍ ለመናፍቃን ጥያቄዎች መልስ ✍ ወቅታዊ መረጃዎችና ሌሎችንም የሚያገኙበት ቻናል ➾ሀሳብ አስተያየት ካላችሁ @Hailegebereal19አድርሱን

Більше
Рекламні дописи
1 610
Підписники
Немає даних24 години
-27 днів
-1130 днів

Триває завантаження даних...

Приріст підписників

Триває завантаження даних...

ድነኀል ወይስ አልዳንክም? ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ በአንድ መጽሐፋቸዉ እንዲህ ይላሉ። አንድ ወጣት ልጅ እንዲህ ብሎ ጠይቆኛል “አንድ ሰው ድነኀል ወይስ አልዳንኽም?” ብሎ ቢጠይቀኝ መልሴ ምንድ ነው? መጀመሪያ ይሄ ሰዉ እዉነተኛ ኦርቶዶክስ እንዳልሆነ ማወቅ አለብህ። በእርግጠኝነት ይሄ ሰዉ ፕሮቴስታንት ነዉ ወይንም ቢያንስ በፕሮቴስታንታዊ ባህል ውስጥ ነዉ የሚኖረዉ፣ ባህሉም የፕሮቴስታንት ነው። ከዚህ በፊት የተቀበልካቸዉን ምስጢራትንና ጥምቀትን እንደ ምንም ቆጥሮ፣ በሃይማኖትህ ላይ ጥርጥር ለመሙላት በመሞከር፣ ባለፈዉ የሕይወት ዘመንህ ሁሉ አሕዛብ እንደነበርክ አድርጎ እንደ ገና እመንና ዳን ሊልህ ነው። ይሄ ሰዉ በፍጹም ኦርቶዶክስ ሊሆን አይችልም አነጋገሩም ይገልጠዋል። ለማንኛዉም እንዲህ ብለህ ልትመልስለት ትችላለህ “በጥምቀት ከአዳም የውርስ ኀጢአት ድኜያለሁ፤ ይሄ ድኅነት የሚገኛዉ በደመ ክርስቶስ የቤዛነትንና የድኅነት ኀይል ነው። ነገር ግን የመጨረሻዉ ድኅነት በስጋ ስንለይ የሚገኝ ነው። አሁንም በውጊያ ላይ ነን “መጋዳላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ከአለቆችና ከስልጣናት ጋር ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳዊያን ሰራዊት ጋር እንጂ።” (ኤፌ. 6፥12)። ይሄንን ውጊያ ድል ስናደርግና ስናሸንፍ ድኅነትን እናገኛለን…” በስጋ እስካለን ድረስ “ድል ነስተናል፤ ድኅነትን አግኝተናል” ልንል አንችልም። ስለዚህ ቅድስት ቤተክርስቲያን የቅዱሳንን ልደት አታከብርም ወይም የተጠመቁበትን ዕለት፤ ይልቁንም ከዚህ ዓለም የተለዩበትን ወይንም መስዋዕት የሆኑበትን ቀን ታከብራለች እንጂ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላልና “ዋነኞቻችሁን አስቡ፣ የኑሮአቸዉንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸዉ ምሰሉአቸዉ።” (ዕብ. 13፥7)። ስለዚህ በቅዳሴ ላይ የቅዱሳንን መታሰቢያ እናደርጋለን፤ በእምነት ፍጹማን የሆኑትንና ሕይወታቸውን በእምነት የፈጸሙትን፣ በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳንን ሁሉ እናስባለን። ይሄም የታላቁ አባ መቃርስን ከዚህ ዓለም መለየት እንዳስታውስ ያደርገኛል። ነፍሱ ከስጋው ተለይታ ስትሄድ “መቃርስ አንተ ድነኸል” እያሉ አጋንንት ነፍሱን አሳደዷት፤ ነገር ግን ገነት እስከሚገባ ድረስ “በጌታ ጸጋ ድኜያለኹ” አላላቸዉም ነበር…! አባታችን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት ነገረ ድኅነትን አስመልክቶ ለፕሮቴስታንቶች መልስ ከሰጡበት “Salvation in the Orthodox Concept” ከተሰኘው መጽሐፍ ላይ የተወሰደ ነዉ።
Показати все...
በሕማም፣ በመከራና መሥዋዕት በመሆን ፍቅራችን ይፈተናል ፍቅርን የሚያውቅ ሰው ለእግዚአብሔር እና ለሌሎች ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል፡፡ ሰው በመጀመሪያ መሥዋዕት ለማድረግ መልመድ ያለበት ከእርሱ ውጪ በሆኑ ነገሮች ማለትም ገንዘቡን፣ ጊዜውን እና ሀብቱን በመለገስ ነው፤ መስጠት ከማግኘት አንድ ነውና፡፡ ለሰዎች ደስታ እንደራሱ የሚጨነቅ እርሱ ፍቅርን ያውቃል፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ይኖራል፡፡ መሥዋዕትነት መክፈል ካልቻልን ግን ፍቅር አልገባንም ማለት ነው፤ አምላካችን እግዚአብሔርን ማፍቀር ካልቻልን ደግሞ ድኅነተ ሥጋንም ሆነ ድኅነተ ነፍስን ማግኘት አንችልም፡፡ ፍቅር የሚፈተነው በሕማም በመከራና መሥዋዕት በመሆን ነው፤ መሥዋዕት መሆን የማይችል ሰው የማይወድ ወይም የማያፈቅር ሰው ነው፡፡ የሚወድ ሰው ከሆነ ግን ለመውደድ ማንኛውም ነገር መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል፡፡ የአባቶች ሁሉ አባት የተባለው አብርሃም ለእግዚአብሔር ካለው ፍቅር የተነሣ ወገኖቹንና የአባቱን ቤት ትቶ በመውጣት በአንድነት በድንኳን ውስጥ ኖሯል፤ ይሁን እንጂ አብርሃም ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር ያሳየው አንድ ልጁን በመሠዊያው ላይ ባስተኛው ጊዜ ነበር፡፡ እርሱ በልጁ ዙሪያ እንጨቶች ሰብስቦ ካቀጣጠለ በኋላ መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርበው ቢላዋ የያዘ እጁን ቃጥቶ ነበር፡፡ ነቢዩ ዳንኤል እግዚአብሔርን በወደደ ጊዜ ወደ ተራቡ አናብስት ይወረወር ዘንድ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል፡፡ ሦስቱ ወጣቶች እንዲሁ ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ያረጋገጡት በእቶኔ እሳት ውስጥ በመወርወር የከፈሉት መሥዋዕትነት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ፍቅር የገለጠው እንዲህ በማለት ነው፤ ‹‹አዎን፤ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቆጥራለሁ፤….›› (ፊል. ፫፥፰-፱) አባታችን ያዕቆብ ከራሔል ጋር በፍቅር በወደቀ ጊዜ ስለ እርሷ ብዙ መሥዋዕትነት ከፍሏል፡፡ እርሱ ራሔልን ለማግኘት ለሃያ ዓመታት ያህል በቀን ሀሩንና በሌሊት ቁር መድከም ነበረበት፡፡ ይሁን እንጂ ለእርሷ ከፍተኛ ፍቅር ስለ ነበረው እነዚህ ዓመታት ለእርሱ እንደ ጥቂት ቀናት ነበር ያለፈለት፡፡ እኛም ለሰው ዘር በሙሉ ሲል በመስቀል ላይ መሥዋዕት ሆኖ ለቀረበው ለኢየሱስ ክርስቶስ የምናቀርበው መሥዋዕት በዚህ ምድር የሚገጥመን ችግር በወጣት፤ የሚደርስብንን መከራ እና ሥቃይ በትዕግስት በማለፍ ነው፡፡ ‹‹ነገር ግን በዚያ መሥዋዕት በየዓመቱ የኃጢአት መታሰቢያ አለ፤ የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና›› እንደተባለውም ጌታችን ኢየሱስ መሥዋዕት ሆኖ ካዳነን በኋላ እኛም የምናቀርበው ለእርሱ መባ እና ምጽዋዕት ኃጢአታችንን ያስተሰርይልናል፡፡ ይህም በቤተክርስቲያን ለመዘከርም ሆነ ወርኃዊ እና ዓመታዊ በዓል ለማክበር ስንሄድ እግዚአብሔር የምናቀርበው ስጦታ ነው፤ ሆኖም ግን በእምነት እና በበጎ ምግባር ያልተደገፈ ማንኛውም ስጦታ በእርሱ ዘንድ ዋጋ አይኖረውም፡፡ ሁሉን የሚያይ አምላካችን ልባችንን እና ኵላሊታችንን ይመረምራልና የውስጣችንን ክፋት ስለሚያውቅ የምናቀርበውን መሥዋዕት አይቀበለውም፤ ቅድስት ቤተክርስቲያንን በድፍረት በመርገጣችንም በኋላኛው ዓለም ይቀጣናል፡፡ (ዕብ. ፲፥፫-፬) አባቶቻችን ሰማዕታትን ካህናት ለእግዚአብሔር ካላቸው ፍቅር የተነሣ ደማቸውን፣ ሕይወታቸውን እና መደላደላቸውን መሥዋዕት አድርገው አቅርበዋል፡፡ እነርሱ ለእግዚአብሔር የተለየ ፍቅር ስለነበራቸውና ሥቃይን ስለተለማመዱት ፈጽሞ ፈርተው አያውቅም ነበር፡፡ እኛም እንደ አባቶቻችን ለእምነታችንም ሆነ ለሃይማኖታችን ሰማዕት መሆን ባንችል እንኳን በዚህ በምድራዊ ሕይወታችን ማንኛውም ዓይነት ችግር እና መከራ ሲገጥመን ባለመማረር ሥቃዩንም ተቋቁመን ፈተናችንን ማለፍ ይጠበቅብናል፤ ከራሳችን አልፎ ለሌሎች መዳን ምክንያትም ልንሆን እንችላለን፡፡ ያን ጊዜም በሰላም፣ በፍቀር እና በአንድነት እንኖራለን፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር በሰላም እና በፍቅር አንድንኖር ፍቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡ ምንጭ፤ ‹‹መንፈሳዊ ቃላትና ጥቅማቸው- ክፍል አንድ፤›› በግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ፤ ትርጉም አያሌው ዘኢየሱስ @kallefiretube
Показати все...
+ ትሞታለህና ቤትህን አስተካክል + ንጉሥ ሕዝቅያስ በጠና ታምሞ ተኝቶአል::  ነቢዩ ኢሳይያስ ሊጠይቀው መጣ:: ሆኖም እንደ ልማዱ እግዚአብሔር ይማርህ አላለውም:: ለጆሮ የሚከብድ  ቃል ጥሎበት ወጣ:: "ትሞታለህና ቤትህን አስተካክል!" ነቢዩ ይህንን ብሎት ከወጣ በኁላ ሕዝቅያስ ወደ ግድግዳው ዞሮ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ:: አምላኩ በንግግር ብዛት የሚሰማ አምላክ አይደለምና ፊቱን ወደ መቅደሱ አቅጣጫ አዙሮ አለቀሰ::  ከጥቂት ደቂቃ በኁዋላ ነቢዩ ኢሳይያስ ሌላ መልእክት ይዞ ተመለሰ:: እግዚአብሔር እንዲህ ይላል :- ጸሎትህን ሰምቻለሁ ዕንባህን አይቻለሁ በዕድሜህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ" (ኢሳ 38:5) ሕዝቅያስ ቤትህን አስተካክል ከተባለ በኁዋላ ፊቱን አዙሮ ከማልቀስ በቀር ምንም አላደረገም:: ሕዝቅያስ ሆይ ከአልጋህ ሳትወርድ ያስተካከልከው ቤት ምን ዓይነት ቤት ነው? ለባሪያዎችህ መመሪያ ሳትሠጥ የምታስተካክለው ቤትስ እንዴት ያለ ነው? በደቂቃዎች ውስጥ ትሞታለህ ከተባልክ በኁዋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ያስጨመረልህ ምን ዓይነት ማስተካከያ አድርገህ ነው? ለእኛም ንገረንና ዕድሜ እናስጨምር:: ሕዝቅያስ ከአልጋው ሳይነሣ ያስተካከለው ቤቱ ልቡ ነበር:: ልብህን ካስተካከልህ ቤትህ ይስተካከላል:: እግዚአብሔር እንደሆን ትሞታለህ ቢልህም መሞትህን አይፈልግም:: እርሱ ካንተ ጋር ጸብ የለውም:: "በውኑ ኃጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን?" ይላል መሐሪው (ሕዝ 18:23) እርሱ ትሞታለህ የሚልህ መኖርህን ፈልጎ ነው:: አንዴ ብያለሁ ብሎ አይጨክንብህም:: በንስሓ ተመለስ እንጂ ምሬሃለሁ ለማለት ይቸኩላል:: አሁን ትሞታለህ ብዬው አሁን ትድናለህ ብለው ይንቀኛል ሳይል ተመልሶ ይምርሃል:: ኃጢአትህንም ወደ ጥልቁ ይጥለዋል:: በጎ እንድትሠራም ዕድሜ ይጨምርልሃል:: አንተ ብቻ ተመለስና አሁኑኑ ንስሓ ግባ:: ከበደል አልጋ ጋር ያጣበቀህን ፈተናም ድል መንሻው ጊዜ አሁን ነው:: ሕዝቅያስ በደቂቃ ዕንባ ምሕረት አግኝቶ ዕድሜ ካስጨመረ በዐቢይ ጾም ሙሉ የሚያለቅስ ምን ያህል ዕድሜ ያገኝ ይሆን? ወዳጄ አንተም ተነሣና በዚህ ወር ቤትህን አስተካክል:: እንደ ሕዝቅያስ ፈጣሪህ ይጠብቅሃል:: የተቀየምከውን ይቅር በል  የበደልከውን ካስ የሚበቀልህን የማይተኛ ጠላትህን ዲያቢሎስ ተበቀለው:: የዐቢይ ጾም የወንጌል ምንባብ ስለ ዲያቢሎስ ፈተና ሦስቱ ወንጌላት የተናገሩትን ስናስተውል ሦስት ዓይነት ጥቅሶች እናገኛለን:: አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። (ሉቃ 4:2) በምድረ በዳም ከሰይጣን እየተፈተነ አርባ ቀን ሰነበተ (ማር 1:13) የሚሉት ቃላት ጌታችን ዐርባውንም ቀን መፈተኑን ያሳያሉ:: አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ። ፈታኝም ቀርቦ እንዲህ አለው (ማቴ 4:2) የሚለው ደግሞ ከጾሙ በኁዋላ የቀረቡለትን ሦስት ፈተናዎች የሚያሳይ ነው:: ሦስተኛው ጥቅስ ደግሞ ከተፈተነ በኁዋላ ያለው ሲሆን ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ። (ሉቃ 4:13) ይላል:: ዲያቢሎስ ፈተናውን ቢጨርስም የሚተወው ለጊዜው እንጂ መፈተኑን አያቆምም::  የዲያቢሎስ ፈተና ስልቱ ይቀያየራል እንጂ ይቀጥላል:: ዐቢይ ጾም ዲያቢሎስ ድል የተደረገበት የጦር ዐውድማ ነው:: በዚህ ወራት ድል ያላደረግነውን ፈተና በሌላ ጊዜ አናደርገውም:: ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል እንደሚባለው በዐቢይ ጾም የተኛ ክርስቲያን መቼም አይነቃም:: ከነስሙ ሁዳዴ (ሰፊ እርሻዬ) የምንለው ይህ ጾም ለነፍሳችን ብዙ ዘር የምንዘራበት አጋንንት መድረሻ የሚያጡበት ጾም ነው:: በዐቢይ ጾም ያልተገራ አንደበት መቼም አይገራም:: በዐቢይ ጾም ያልተፈወሰ ቂም መቼም አይፈወስም:: ጌታችን በወንጌል አንዴ ወደ እሳት አንዴ ወደ ውኃ የሚጥል ጋኔን ያለበትን ልጅ ሲፈውስ "ይህ ዓይነቱ ጋኔን ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም" ብሎ ነበር:: ሀገራችንን አንዴ ወደ እሳት አንዴ ወደ ውኃ የሚጥላት የጥላቻ ጋኔንም ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም:: ወዳጄ ከቁስልህ የምትፈወስበት ወር እንደደረሰ ዕወቅ:: አንተስ ብትሆን ልትላቀቀው እየፈለግህ ያቃተህ ክፉ ልማድ የለብህም:: እንደ ቅዱስ ጳውሎስ "የምፈልገውን መልካም ነገር አላደርግም የማልፈልገውን ክፉ ነገር ግን አደርጋለሁ:: ምንኛ ጎስቋላ ለዚህ ለሞት ከተሠጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?" ብለህ ምርር እንድትል ያደረገህ ኃጢአት የለም? እንግዲያውስ እወቀው:: ይህ ዓይነቱ ወገን ያለ ጾምና ጸሎት አይወጣም:: ይህ ጾም ቁስል የሚሽርበት ጾም ነው:: ይህ ጾም ሸክም ማራገፊያ ጾም ነው:: እንደ ሕዝቅያስ በዚህ ወር ቤትህን በንስሓ አስተካክል:: ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ የካቲት 15 2012 ዓ ም ዝዋይ ኢትዮጵያ
Показати все...
እመቤታችን በአበው ቀደምት የተመሰለላት ምሳሌ እና እመቤታችን በቅዱሳን ነቢያት የተነገረላት ትንቢትና እመቤታችን በሊቃውንት ትርጓሜ ወላዲተ አምላክ በዘመነ አበው/በሕገ ልቦና ሀ)  የያዕቆብ መሰላል:: (ዘፍ ፳፰÷፲-፳) "ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ወጥቶ ወደ ካራን ሄደ ።ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ ፀሐይም ጠልቃ ነበርና ከዚያ አረፈ በዚያም ስፍራ ድንጋይ አነሳ ከራሱም በታች ተንተርሶ በዚሀ ስፋራ ተኛ፡፡ ሕልምም አለመ እንሆ መሠላል በምድር ላይ ተተክሎ ራሱም ወደ ሰማይ ደረሶ እነሆም እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር " " ዘፍ ፳፰፥፫-፳ 👉ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ በራዕይ ያያት ወሠላል :-  የእመቤታችን 👉የተንተራሰዉ ድንጋይ ትንቢተ ነቢያት:- እመቤታችን በትንቢተ ነቢያት ፀንታ ለመግኘቷ ምሳሌ ነዉ፡፡ 👉 ያዕቆብ መሠላል ከምድር እስከ ሰማይ ደርሶ ማየቱ :-በሰዉና በእግዚአብሔር መካከል የነበረዉ ጥላቻ ተወግዶ ምድራዊያን ሠዎችና ሰማያዊያን መላዕክት እግዚአብሔር ወልድ ስጋዋን ለመዋሐድ የወረደና ያደረባት የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ነዉ፡፡ የያዕቆብ❤️ ምሰጢር፡ ዘፍ ፳፱÷፩-፲፩ ያዕቆብ ከወንድሙ ከኤሳዉ ጋር ተጣልቶ ወደ አጎቱ ወደ ላባ በሚሄድበት ወቅት መንገድ ላይ መንጋቸዉን እየጠበቁ ከዉኃዉ አፍ ላይ የተገጠመዉን ድንጋይ የሚያነሳላቸው አጥተዉ በችግር ላይ የነበሩት እረኞችን እንደ አገኘና ራሔል ከመጣች በኋላ ያን ታላቅ ድንጋይ ከጉድጓድ ዉኃ አፍ ላይ አንስቶ በጎቻቸውን እንደ አስጠላቸዉ ቅዱስ መፅሐፍ ይናገራል። ዘፍ ፳፱÷፩-፲፩ ምስጢራዊ ምሳሌዉ። ውኃ - የማየ ሕይወት ድንጋይ- መርገም አባግዕ በጎች -የምዕመናን ኖሎት(እረኞች)- የነቢያት ራሔል - የእመቤታችን ያዕቆብ- የክርስቶስ 👉እረኞች በላቻቸውን ለማስካት ድንጋርን ማንሳት አለመቻላቸዉ ነቢያትም በትምህርታቸው በተጋድሏቸዉ መርገምን አርቀው ማየ ህይወት ለማጠጣት አልቻሉም። 👉እረኞች ራሔል እስክትመጣ ድረስ እንደጠበቁ ሁሉ ነቢያትም በትንቢታቸዉ የእመቤታችንን መምጣት ይጠባበቁ ነበር። 👉ራሔል በመጣች ጊዜ ብዙ እረኞች ማንሳት ያልቻሉትን ድንጋይ ያዕቆብ ብቻዉን አንስቶ በጎቹ እንዲከጡ አደረገ። 👉 እመቤታችን ከተወለደች በኋላም ክርስቶስ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ነቢያት በተጋድሎአቸዉ ሊያርቁት ያልቻሉትን መርገም በፍቃዱ በተቀበለዉ ፀዋትወ መከራ አራቀዉ:: አባግዕ ምእመናንም ከማየ ህይውት አጠጣ  (ዮሐ ፬÷፯)
Показати все...
ሰው በግእዝ ሰብእ ይባላል። ይህንን አንዳንድ ሰዎች "ሰብዐ-ሰባት አደረገ" ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ዘር ውስጠዘ ነው ይላሉ። ይኽውም ከሰባቱ ባሕርያት የተገኘ ማለት ሲሆን ሰባቱ ባሕርያት የተባሉትም አራቱ ባሕርያተ ሥጋ ማለትም ባሕርየ እሳት፣ ባሕርየ ማይ፣ ባሕርየ መሬት፣ ባሕርየ ነፋስ እና ሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ ለባዊነት፣ ነባቢነት እና ሕያውነት የተገኘ ነው ይላሉ። ይህ ግን የተሳሳተ አነጋገር ነው። ሰው ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋና ከአንዲት ባሕርየ ነፍስ ተገኘ ይባላል እንጂ ሦስት ባሕርያተ ነፍስ የሚባል የለም። ሰብእ የሚለው ዘር ውስጠ ዘ "ተሰብአ-ሰው ሆነ" ከሚለው ግሥ ይወጣል እንጂ "ሰብዐ-ሰባት አደረገ" ከሚለው አይወጣም። ለባዊነት፣ ሕያውነትና ነባቢነት የነፍስ ግብራተ ባሕርይዎች (መሆኖች) ናቸው እንጂ ባሕርይዎች አይደሉም። ወይም የነፍስን ግብራተ ባሕርያት ከተናገርን የእያንዳንዱን ባሕርያተ ሥጋ ግብራትም ጠቅሰን መቁጠር ነው። የእያንዳንዱን አንድ ብለን ከቆጠርን ደግሞ የነፍስንም አንድ ብሎ መቁጠር ይገባል። በእርግጥ ግብረ ባሕርይን ባሕርይ ብለው የሚገልጹ መጻሕፍት ሊኖሩ ይችላሉ። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ሰው በጠቅላላው ከሰባቱ ባሕርያት የተገኘ ከሚባል ይልቅ የእያንዳንዱን ግብረ ባሕርይ ቆጥሮ ፲፭ ቢል የቀና ይሆን ነበር። ይኽውም       ፩) የመሬት ግብራተ ባሕርይ                  -ደረቅነት                  -ጥቁርነት                  -ርጥብነት       ፪) የውሃ ግብራተ ባሕርይ                  -ብሩህነት                  -ርጥብነት                  -ቀዝቃዛነት       ፫) የነፋስ ግብራተ ባሕርይ                  -ሞቃትነት                  -ቀዝቃዛነት                  -ጥቁርነት       ፬) የእሳት ግብራተ ባሕርይ                  -ብሩህነት                  -ሞቃትነት                  -ደረቅነት ናቸው። የነፍስን ግብራተ ባሕርይ ባሕርይ ብለን ቆጥረን ሦስት ካልን የሥጋን ግብራተ ባሕርይም ቆጥረን ፲፪ ማለት ግድ ይለናል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ሰው ከ፲፭ቱ ባሕርያት ተገኘ ያሰኛል። የአራቱን ባሕርያተ ሥጋ ባሕርይን ቆጥረን አራት ብለን ከቆጠርን ደግሞ የነፍስን አንድ ብለን መቁጠር ግድ ይለናል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ከአምስቱ ባሕርያት ተገኘ ያሰኛል እንጂ ከሰባቱ አያሰኝም። ፍርድ:- አንዳንድ መጻሕፍት ላይ ለምሳሌ አክሲማሮስ አንድምታ ላይ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋና ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ ሲል ይገኛል። ይህን ጊዜ ሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ ያላቸው ግብራተ ባሕርይ እንደሆኑ ልብ ማድረግ ይገባል። አራቱ ባሕርያተ ሥጋ ሲል ግን ግብራተ ባሕርይን አይቶ ሳይሆን ባሕርይን ራሱን አይቶ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። ግብራተ ባሕርይን ሳይመለከት ቀጥታ ባሕርይን ተመልክቶ በሚታተት ሐተታ ግን ትክክለኛው ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋና ከአንዲት ባሕርየ ነፍስ የሚለው መሆኑን መረዳት ይገባል። ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ላይ "አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እም ገነት" ከሚለው የታተተው በዚህ መንገድ ነው።@kallefiretube
Показати все...
👍 2 1
አስታውስ ደካማነትህን አስታውስ፦ ያን ጊዜ በጣም ጠንቃቃ ትሆናለህ፣ ሊጎዱህ በሚችሉ በትምክህትና በውዳሴ ከንቱም አትሸነፍም። የተሰጠህን በፍቅር የተሞላ የእግዚአብሔርን ቸርነት አስታውስ፦ ይህም በምስጋና የተሞላ ሕይወት እንድትመራ ያደርግሃል። በእግዚአብሔር ፍቅርና ሥራ ላይ ስትታመን ፍጹም የሆነ እምነት በልብህ እያደገ ይመጣል። ከእግዚአብሔር ጋር ያሳለፍከው ጊዜ ደግሞ በእምነት እንድትኖር ያበረታታሃል። የሰዎችን ፍቅርና ካንተ ጋር ያሳለፉትን መልካም ጊዜ አስታውስ፦ የሰዎችን ቀናነት ትጠራጠር ዘንድ ወይም ያደረጉብህን ክፉ ነገር ታስብ ዘንድ ይገባሃልን? የቀደመ ፍቅራቸው ስለ እነርሱ ይማልዳል ያንተንም ቁጣ ያበርዳል። ሞት እንዳለ አስታውስ፦ እንዲሁ በዓለም ያለ ፈተናም እንደሚያልፍ። “ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።” መክብብ 1፡14 ማለትን ትረዳለህ። በእግዚአብሔር ፊት መቆምህንና እርሱም እንደሚመለከትህ አስታውስ፦ ያኔ ኃጢአት አትሰራም እግዚአብሔርን ታየዋለህና። ስለ አንተ የፈሰሰውን የክርስቶስን ክቡር ደም አስታውስ፦ በዚህም ሕይወትህ ያለውን ዋጋ በእርግጥ ታውቃለህ፤ በዓይኖችህ ፊት የከበረ ይሆናል፣ ስለዚህም በከንቱ በመኖር አታጠፋውም “በዋጋ ተገዝታችኋልና” 1ኛ ቆሮ. 6፥20 እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ። በወላጆችህ እምነት በተጠመቅህባት ቦታ ለእግዚአብሔር የገባኸውን ቃል አስታውስ፦ ዲያብሎስን፣ ሥራዎቹን ሁሉ፣ ሐሳቦቹንና ጥበቡን፣ ኃይሉንም ትክድ ዘንድ ኃይል ታገኛለሕና። በዚህ ዓለም እንግዳ መሆንህንና ወደ ሰማያዊው ቤትህ እንደምትመለስ ዘወትር አስታውስ፦ ያን ጊዜ በዚህ ዓለምና በደስታው ተስፋ ማድረግን ትተዋለህ። በጠባቡ በር መጓዝ ወደ መንግስተ ሰማያት እንደሚያደርስህ አስታውስ፦ ሰፊው ደጅ ፊት ለፊትህ ተከፍቶ ብታየው፣ አልፈኸው ሂድ ከእሱም ራቅ፣ በእርሱ የሄዱ እንዳሉ አልቀዋልና። ዘላለማዊውን ሕይወትህን አስታውስ፦ ሁልጊዜም ስለዚህ ትጋ። የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህንና እርሱን መምሰል እንዳለብህ አስታውስ፦ እውነተኞች ከሆኑት ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር አካሄድህን አስተካክል። የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ መሆንህን አስታውስ፦ በውስጥህ ያለውንም ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝን። ዘወትርም ቅዱስ የእግዚአብሔር ማደሪያ ሁን። @kallefiretube
Показати все...
👍 1
+ የሚያምር እግር + በጸሎተ ሐሙስ ልብን የሚሰውር አንድ ነገር ተፈጽሞ አለፈ፡፡ ይህም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር የማጠቡ ነገር ነው፡፡  የሰውን የቆሸሸ እግር እያሸ የሚያጥብ አምላክ ፣ የተማሪዎቹን እግር የሚያጥብ መምህር ፣ የባሪያዎቹን እግር የሚያጸዳ ጌታ ማየት እንዴት ያስጨንቃል? እስቲ ለአንድ አፍታ ወደዚያ ቤት በሕሊናችን ተጉዘን እንግባና ጌታን እግር ሲያጥብ አብረን እንመልከተው፡፡  የአምስተኛው ክፍለ ዘመን ባለቅኔ የቅዱስ ኤፍሬም ተማሪ ሶርያዊው ቄርሎና በመንፈስ ሆኖ ያንን ቤት በዓይነ ሕሊናው እንዲህ ቃኝቶት ነበር ፦ ‘ጌታ ውኃ ቀዳና መታጠቢያውን ተሸከመ፡፡ የማበሻ ጨርቅ ያዘና ታጠቀ፡፡ የደቀ መዛሙርቱን እግር ሊያጥብ ጀመረ፡፡ ሕሊናዬን አንዳች ነገር ሲወጋው ተሰማኝ ዕንባዬም ፈሰሰ፡፡ በፍርሃት ፊቴን ሸፈንኩ ዓይኖቼንም በመሳቀቅ ዞር አደረግሁ፡፡ ሲያጥባቸው ለማየት አቅም የለኝምና ብወጣ ተመኘሁ’ ይላል፡፡ (Hymns of Cyrillona, On The Washing of the feet, Gorgias Press pg 72)እውነትም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር አጎንብሶ ማጠብ ለማሰብ ይከብዳል፡፡        ጌታችን ሐሙስ ዕለት ያደረገውን ነገር መጥምቁ ዮሐንስ ቢያይ ኖሮ ምን ይል ይሆን? ጌታ ሊጠመቅ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ ዮሐንስ ‘አንተ እንዴት ልትጠመቅ ወደ እኔ ትመጣለህ?’ ብሎ አልነበር? መጥምቁ ዮሐንስ ሆይ ና ተመልከት! በአንተ በባሪያው እጅ ሊጠመቅ ሲመጣ ስለ ትሕትናው የተደነቅህበት ጌታ ዛሬ ደግሞ አጥምቁኝ ከማለት አልፎ የባሪያዎቹን እግር ሲያጥብ አጎንብሶ ታየ፡፡ አንተ ‘የጫማውን ጠፍር ተጎንብሼ ልፈታ አይገባኝም’ ያልክለት ጌታ አጎንብሶ የሐዋርያቱን ጫማ ሲፈታና እግራቸውን ሲያጥብ ብታይ ምን ትል ይሆን? በዮርዳኖስ ዳር ‘አንተ እንዴት ልትጠመቅ ወደ እኔ ትመጣለህ?’ ያልከውን ጌታ ቅዱስ ጴጥሮስ ‘አንተ እንዴት የእኔን እግር ታጥባለህ?’ ሲለው ተመልከት! በእርግጥ በዮርዳኖስ ወንዝ ከታየው ትሕትና የበለጠ ትሕትና በዚያች የመታጠቢያ ውኃ ውስጥ ታየ፡፡ ውኃ በተሞላ በአንድ ማስታጠቢያ ውስጥ የፍጡር እግርና የፈጣሪ እጅ አንድ ላይ ሆነው የታዩበትን ያን ቅጽበት እጅግ ታላቅ ትሕትና ተማርንበት፡፡ ፍጡር ፈጣሪውን ሲያጠምቀው ከማየት በላይ ፈጣሪ የፍጡርን እግር ሲያጥብ ማየት ድንጋይ ልባችንን የሚሰብር ቅጽበት ነው፡፡        ከመጥምቁ ዮሐንስ በፊት የነበሩት ነቢያትስ ይህንን ቢያዩ እንዴት ይደነቁ ይሆን? ኢሳይያስ ሆይ ‘ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ሆኖ አየሁት’ ያልክለት ጌታ ዝቅ ባለ መቀመጫ ላይ ቁጭ ብሎ የአሳ አጥማጆችን እግር ሲያጥብ ተመልከተው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ሆይ ‘እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን’ ብለህ የዘመርክለት ጌታ እግር እያጠበ ነው፡፡ የሚገርመው እግር ከማጠቡ በፊትም ውኃ አስቀረበ አይልም ምክንያቱም ውኃውን የቀዳውም እርሱ ራሱ ነበረ፡፡ አብርሃም ለእንግዶቹ እንዳለው ‘ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ’ ብሎ ውኃ አላስቀዳም፡፡(ዘፍ. 18፡4) ራሱ ውኃውን ቀድቶ በመታጠቢያው ሞልቶ የባሪያዎቹን እግር አጠበ፡፡ ለነገሩ በትሕትና የተጠመቀበትን የዮርዳኖስን ወንዝስ ቢሆን በውኃ የሞላው እርሱ አልነበረምን?               ጴጥሮስ ተጨነቀ ፤ ‘ጌታ ሆይ አንተ እንዴት የእኔን እግር ታጥባለህ?’ አለና ተከላከለ፡፡ የጴጥሮስ ጭንቀት ብዙ ነገር ከማሰብ የመነጨ ነው፡፡  ‘ኪሩቤል በፊትህ ግርማ እንዳይቃጠል ፈርተው በፊትህ ሲቆሙ በክንፎቻቸው እግራቸውን ይሸፍናሉ፡፡ ታዲያ እኔ  እጠብልኝ ብዬ እንዴት ደፍሬ እግሬን እሠጥሃለሁ? ሱራፌል የልብስህን ጫፍ የማይነኩህ ጌታ የእኔን እግር እንዴት ታጥባለህ? በባሕር ላይ በአንተ ትእዛዝ የተራመድሁት አይበቃኝም? እንዴት እግርህን ልጠብህ ትለኛለህ? ይህንን ዕዳ እንዴ እሸከመዋለሁ?’ የሚል ጽኑ ጭንቀት ያዘለ ጥያቄ ነበር፡፡ ጌታ ግን ዕውር ባበራባቸው እጆቹ እግር አጠበባቸው፡፡ ሸክላ ሠሪው አጎንብሶ የሸክላውን እግር አጠበ፡፡ ሰውን ከምድር አፈር የፈጠረው አምላክ ትቢያውን በክብር አስቀምጦ እግሩን አጠበው፡፡        ጌታችን ያጠበው ከሰዓታት በኋላ እግሬ አውጪኝ ብለው ጥለውት የሚሸሹትን የደቀ መዛሙርቱን እግሮች ነበረ፡፡ ለአንድ ሰዓት እንኳን አብረውት ሊተጉ የማይችሉትን ተማሪዎቹን እግር አጠበ፡፡ ጥለውት እንደሚሔዱ እያወቀ ‘ንጹሐን ናችሁ’ ብሎ አወደሳቸው፡፡ ‘ወደ አብ እንደሚሔድ አውቆ የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው’ እንደሚል ምድር ላይ በቀረችው ጊዜ ያልከፈለው የፍቅር ዕዳ እንዲኖርበት አልፈለገምና ጊዜውን ለመውደድ ተጠቀመበት፡፡ የሚወዳቸውን ደቀ መዛሙርት እግራቸውን አጥቦ በፍቅር ተሰናበታቸው፡፡        ጌታ ሆይ የእኔንስ እግር የምታጥበው መቼ ነው? በእውነት በምድር ላይ ከእኔ እግር በላይ የቆሸሸ አለ? ያልረገጥሁት የኃጢአት ጭቃ ፣ ያልነካሁት የበደል ቆሻሻ እንደሌለ አታውቅምን? ‘በክፉዎች ምክር የሔደ’ እግሬን የማታጸዳው ለምንድን ነው? (መዝ. 1፡2) ‘የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም’ ብለህ የለምን? እውነት ነው ፤ እግሬን ከኃጢአት ከከለከልክልኝ ሌላውን አካሌን ማዳንህም አይደል? አጥብቀህ ከምትጠላቸው ነገሮች መካከል አንዱ የሆነውን ‘ወደ ክፉ የሚሮጥ እግሬን’ የማታጥብልኝ ለምንድን ነው? (ምሳ. 6፡18) እባክህን እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ፡፡ በእርግጥ የሐዋርያትን የቆሸሸ እግር በውኃ እንዳጠብከው አስበን አደነቅን እንጂ በማግሥቱ ደግሞ የዓለምን ኃጢአት በደምህ አጥበሃል፡፡ ከዳንሁ በኋላ የቆሰልሁትን ፣ ከታጠብኩ በኋላ ያደፍሁትን እኔን በከበረ ሥጋና ደምህ ከኃጢአቴ እድፍ ታጥበኝ ዘንድ ነው ልመናዬ፡፡ በጌታ እጅ የታጠበው የሐዋርያት እግር እንዴት የታደለ ነው? በእሱ ስለታጠበ ዓለምን ዞሮ ወንጌል ለማዳረስ የቻለ እግር ሆነ፡፡ ጌታ ያላጠበው እግር ወንጌል ለዓለም አያደርስም፡፡ ባልታጠበ እግራችን ብንዞር እኛ እንጂ ወንጌል ዓለምን አይዞርም፡፡ ስለዚህ ሐዋርያ ሊሆን የሚሻ ሁሉ ጌታ ሆይ እግሬን እጠብልኝ ብሎ መለመን አለበት፡፡ ወንጌሉም ‘የደቀ መዛሙርቱን እግር ሊያጥብ ጀመረ’ ይላልና ክርስቶስ ደቀ መዝሙሩ ሊሆኑ ለሚወዱ ሁሉ እግራቸውን ማጠቡን አሁንም አያቋርጥም፡፡ ጌታ ያጠበው እግር ምን ይሆናል ካልከኝ ‘የሚያምር እግር ይሆናል’ እልሃለሁ፡፡ ሐዋርያት እግራቸው እጅግ ያምር ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ በእግሩ እብጠት የማይንቀሳቀሰው ቅዱስ ያዕቆብ ሳይቀር እግሩ ያማረ ነበር፡፡ ምክንያቱም ‘መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው?’ ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ሮሜ 10፡15  ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ሚያዝያ 24 2016 ዓ.ም. ኢየሩሳሌም ፤ ፳ኤል @kallefiretube
Показати все...
ጾም የሥጋ ረሀብ አይደለም የነፍስ ምግብ እንጅ አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ጾም የሥጋ ሥቃይ ሰማዕትነት ወይም መስቀል አይደለም፤ ሥጋ ከነፍስ ጋር የሚተባበርበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ከፍ ከፍ የሚልበት እንጂ። ስንጾም የመጾማችን ዕቅድ ሥጋችንን ለማንገላታት አይደለም ጠባዩን_ለመግራት እንጂ። ይህ በመሆኑም አንድ የሚጾም ሰው መንፈሳዊ እንጂ ሥጋዊ ሰው አይሆንም ማለት ነው። ጾም መናኝ ነፍስ ስለሆነ በምናኔ ውስጥ ያለ ባልጀራ ሥጋውን ይዞ ይጓዛል እንጂ ብቻውን አይጓዝም። ጾም ማለት የተራበ ሥጋ ማለት አይደለም የመነነ ሥጋ እንጂ። ጾም የሥጋ ረሀብ አይደለም የሥጋ ልዕልና እና ንጽህና እንጂ ለመብላት የሚናፍቅ የሚራብ ሰውነት ያለበት ሁኔታ ማለትም አይደለም፤ መብላት ዋጋውን የሚያጣበትና ሰውነት ለመብላት ካለው ፍላጎት ራሱን የሚያላቅቅበት ሁኔታ እንጂ። ጾም ነፍስ ከፍ ብላ ሥጋን ከእርስዋ ጋር ከፍ የምታደርግበት ጊዜ ነው። ይህ ጊዜ ሥጋ ጓዙንና ሸክሙን የሚያራግፍበት ጊዜ ስለሆነ እግዚአብሔር ያለ ምንም እገዳ ለመንፈሳዊ ዘላለማዊነት ደስታ የሚሠራበት ጊዜ ይሆናል። ጾም ማለት ነፍስና ሥጋ በኀብረት መንፈሳዊ ተግባር ለማከናውን የሚጠቀሙበት ጊዜ ነው። በጾም ወቅት ነፍስና ሥጋ የነፍስን ሥራ ለመሥራት ይተባበራሉ። ይህም ማለት ለጸሎት ለተመስጦ ለክብርና ከእግዚአብሔር ጋር የሚሆን ሕይወትን ለመጋራት ይተባበራሉ ማለት ነው። @kallefiretube
Показати все...
በሕማም፣ በመከራና መሥዋዕት በመሆን ፍቅራችን ይፈተናል ፍቅርን የሚያውቅ ሰው ለእግዚአብሔር እና ለሌሎች ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል፡፡ ሰው በመጀመሪያ መሥዋዕት ለማድረግ መልመድ ያለበት ከእርሱ ውጪ በሆኑ ነገሮች ማለትም ገንዘቡን፣ ጊዜውን እና ሀብቱን በመለገስ ነው፤ መስጠት ከማግኘት አንድ ነውና፡፡ ለሰዎች ደስታ እንደራሱ የሚጨነቅ እርሱ ፍቅርን ያውቃል፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ይኖራል፡፡ መሥዋዕትነት መክፈል ካልቻልን ግን ፍቅር አልገባንም ማለት ነው፤ አምላካችን እግዚአብሔርን ማፍቀር ካልቻልን ደግሞ ድኅነተ ሥጋንም ሆነ ድኅነተ ነፍስን ማግኘት አንችልም፡፡ ፍቅር የሚፈተነው በሕማም በመከራና መሥዋዕት በመሆን ነው፤ መሥዋዕት መሆን የማይችል ሰው የማይወድ ወይም የማያፈቅር ሰው ነው፡፡ የሚወድ ሰው ከሆነ ግን ለመውደድ ማንኛውም ነገር መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል፡፡ የአባቶች ሁሉ አባት የተባለው አብርሃም ለእግዚአብሔር ካለው ፍቅር የተነሣ ወገኖቹንና የአባቱን ቤት ትቶ በመውጣት በአንድነት በድንኳን ውስጥ ኖሯል፤ ይሁን እንጂ አብርሃም ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር ያሳየው አንድ ልጁን በመሠዊያው ላይ ባስተኛው ጊዜ ነበር፡፡ እርሱ በልጁ ዙሪያ እንጨቶች ሰብስቦ ካቀጣጠለ በኋላ መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርበው ቢላዋ የያዘ እጁን ቃጥቶ ነበር፡፡ ነቢዩ ዳንኤል እግዚአብሔርን በወደደ ጊዜ ወደ ተራቡ አናብስት ይወረወር ዘንድ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል፡፡ ሦስቱ ወጣቶች እንዲሁ ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ያረጋገጡት በእቶኔ እሳት ውስጥ በመወርወር የከፈሉት መሥዋዕትነት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ፍቅር የገለጠው እንዲህ በማለት ነው፤ ‹‹አዎን፤ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቆጥራለሁ፤….›› (ፊል. ፫፥፰-፱) አባታችን ያዕቆብ ከራሔል ጋር በፍቅር በወደቀ ጊዜ ስለ እርሷ ብዙ መሥዋዕትነት ከፍሏል፡፡ እርሱ ራሔልን ለማግኘት ለሃያ ዓመታት ያህል በቀን ሀሩንና በሌሊት ቁር መድከም ነበረበት፡፡ ይሁን እንጂ ለእርሷ ከፍተኛ ፍቅር ስለ ነበረው እነዚህ ዓመታት ለእርሱ እንደ ጥቂት ቀናት ነበር ያለፈለት፡፡ እኛም ለሰው ዘር በሙሉ ሲል በመስቀል ላይ መሥዋዕት ሆኖ ለቀረበው ለኢየሱስ ክርስቶስ የምናቀርበው መሥዋዕት በዚህ ምድር የሚገጥመን ችግር በወጣት፤ የሚደርስብንን መከራ እና ሥቃይ በትዕግስት በማለፍ ነው፡፡ ‹‹ነገር ግን በዚያ መሥዋዕት በየዓመቱ የኃጢአት መታሰቢያ አለ፤ የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና›› እንደተባለውም ጌታችን ኢየሱስ መሥዋዕት ሆኖ ካዳነን በኋላ እኛም የምናቀርበው ለእርሱ መባ እና ምጽዋዕት ኃጢአታችንን ያስተሰርይልናል፡፡ ይህም በቤተክርስቲያን ለመዘከርም ሆነ ወርኃዊ እና ዓመታዊ በዓል ለማክበር ስንሄድ እግዚአብሔር የምናቀርበው ስጦታ ነው፤ ሆኖም ግን በእምነት እና በበጎ ምግባር ያልተደገፈ ማንኛውም ስጦታ በእርሱ ዘንድ ዋጋ አይኖረውም፡፡ ሁሉን የሚያይ አምላካችን ልባችንን እና ኵላሊታችንን ይመረምራልና የውስጣችንን ክፋት ስለሚያውቅ የምናቀርበውን መሥዋዕት አይቀበለውም፤ ቅድስት ቤተክርስቲያንን በድፍረት በመርገጣችንም በኋላኛው ዓለም ይቀጣናል፡፡ (ዕብ. ፲፥፫-፬) አባቶቻችን ሰማዕታትን ካህናት ለእግዚአብሔር ካላቸው ፍቅር የተነሣ ደማቸውን፣ ሕይወታቸውን እና መደላደላቸውን መሥዋዕት አድርገው አቅርበዋል፡፡ እነርሱ ለእግዚአብሔር የተለየ ፍቅር ስለነበራቸውና ሥቃይን ስለተለማመዱት ፈጽሞ ፈርተው አያውቅም ነበር፡፡ እኛም እንደ አባቶቻችን ለእምነታችንም ሆነ ለሃይማኖታችን ሰማዕት መሆን ባንችል እንኳን በዚህ በምድራዊ ሕይወታችን ማንኛውም ዓይነት ችግር እና መከራ ሲገጥመን ባለመማረር ሥቃዩንም ተቋቁመን ፈተናችንን ማለፍ ይጠበቅብናል፤ ከራሳችን አልፎ ለሌሎች መዳን ምክንያትም ልንሆን እንችላለን፡፡ ያን ጊዜም በሰላም፣ በፍቀር እና በአንድነት እንኖራለን፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር በሰላም እና በፍቅር አንድንኖር ፍቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡ ምንጭ፤ ‹‹መንፈሳዊ ቃላትና ጥቅማቸው- ክፍል አንድ፤›› በግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ፤ ትርጉም አያሌው ዘኢየሱስ @kallefiretube
Показати все...
🙏 1