የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን
Открыть в Telegram
1 411
Подписчики
+224 часа
+257 дней
+8530 дней
Архив постов
1 411
የግብርና ምርቶችን ጥራትና የዜጎቻችንን ጤንነት ለማስጠበቅ ልክ እንደወታደር የሚሰራው የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን!
***
የአገራችን የግብርና ምርትና ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ቢሆንም ወደ ውጪ የሚላኩና ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ አብዛኛዎቹ የግብርና ምርቶችና ግብዓቶች በተቀመጡ የጥራት መስፈርቶች ሲመዘኑ አብዛኞቹ የጥራት ችግር የሚስተዋልባቸው ሲሆን ይህም በሰው፣ በእንስሳትና አካባቢ ጤና እንዲሁም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እያደረሱ ያለው ጉዳት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ለዚህም አንዱና ዋነኛው ምክንያት በግብርና ቴክኖሎጂን፣ በግብርና ምርት፣ በግብርና ግብዓትና በግብርና አገልግሎት ላይ በአገሪቱ ያለው የቁጥጥር(ሬጉላቶሪ) ሥርዓት እና አገልግሎት አሰጣጡ በተበታተና ባልተቀናጀ መልኩ ሲመራ ስለነበር እና ጠንካራ፣ በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን የሆነ፣ አቅሙ የጎለበተና ለተገልጋዩ በሬጉላቶሪው መስክ ዋስትና የሚሰጥ ተቋም ሳይገነባ በመቆየቱ ነው፡፡
የኢፌድሪ መንግስት የሬጉላቶሪው ሥርዓት የተዳከመና መሆኑን በመገንዘብና ለሕዝብ የገባውን ፈጣን የኢኮኖሚያዊ እድገት የማረጋገጥ ግብ ለማሳካት የሬጉላቶሪውን ሥርዓት የሚመራ ተቋም ማደራጀት አስፈላጊነቱ ላይ ጠንካራ አቋም በመያዝ ተበታትነው የነበሩ አደረጃጀቶችን በማሳባሰብና አዳዲስ የሬጉላቶሪ አሰራሮችን በማካተት የግብርና ቴክኖሎጂ፣ ግብዓት፣ ምርትና አገልግሎትን ብቃት፣ ጥራት፣ ፍቱንነት፣ ጤንነትና ደኅንነት የማረጋገጥ ርዕይ ሰንቆ በኢ/ፌ/ዲ/ሪ/ የፌዴራል መንግስት የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 45 ንኡስ አንቀጽ 1 መሠረት “የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን”ን አቋቁሟል፡፡
የግብርና ቴክኖሎጂ፣ ግብዓት፣ ምርትና አገልግሎት ብቃትን፣ ጥራት፣ ፍቱንነት፣ ጤንነትና ደህንነት በማረጋገጥ የመንግስትን በጀትና ሌሎች ሀብቶችን በአግባቡ በመጠቀም ጊዜና ወጪ የሚቆጥቡና በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ የአካባቢ ደህንነትን ያገናዘበ፣ የዘመነ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ ተገልጋዮችን ጭምር በሬጉላቶሪ አገልግሎት ማሳተፍ የሚችል የግብርና ሬጉላቶሪ የአሠራር ስርዓት በመገንባትና የግብርና ምርቶች የጥራት ጉድለት የሚያስከትሏቸው የጤና ችግሮች በማስወገድ አገራዊ ምርት ተጠቃሚነትን በማሻሻል፣ ለውጭ ንግድ የሚቀርበው፣ የግብርና ምርትና ግብዓት ጥራትና ደህንነት ሊረጋገጥ በሚችል ቴክኖሎጂ የተደገፈ ግልጽና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ እንዲሆን በማድረግ የገበያ መዳረሻን ማስፋትና የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት አቅምን ማሳደግ የተቋሙ ዋነኛ ተልዕኮዎች ናቸው።
ባለሥልጣን መ/ቤቱ የእንስሳት እና የእጽዋት ሪጉላቶሪ በሚል ሁለት ዓብይት ዘርፎች ያሉት ሲሆን የግብርና ግብዓት ወይም ምርት ከውጭ ሀገር ለሚያስገቡ ወይም ለውጪ ሀገር ገበያ ለሚያቀርቡ፤ በእንስሳት መድኃኒትና መኖ ማምረትና ንግድ ተቋማት ውስጥ ለሚሰማሩ ባለሙያዎች፤ የእንስሳት እና የእፅዋት ግብዓት ምርት ማምረቻ፤ማዘጋጃ ማቀናበሪያ፣ ማከማቻ ጅምላ መሸጫ ቦታዎችን በመስፈርት እና በወጡ የግብርና ስታንዳርዶች፣ በአገር ውስጥ ከአንድ ክልል በላይ ለሚደረግ የግብርና ግብዓት እና የግብርና ምርትን ማምረት የግብይት ተግባር ሲኖር የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መስጠት፣ መመዝገብ፣ ማደስና ማገድና መሰረዝ ተግባራትን ያከናውናል፡፡ ከውጭ የሚገባና በሀገር ውስጥ የሚበለፅግ የግብርና ቴክኖሎጂ ብቃትን ፈትሾ በመመዝገብ በአመልካች ሲጠየቅም መርምሮ የአዳቃዮች ባለቤትነት መብት ጥበቃ የመስጠትና የማስተዳደር ኃላፊነትም ተሰጥቶታል፡፡
በስራ ላይ ያሉትንና ከግብርና ግብዓት እና የግብርና ምርትን ጥራት ፍቱንነት ደህንነትና ጤንነት ጋር ተያያዥ የሆኑ የግብርና ስታንዳርዶችን ተግባራዊ በማድረግ እንደአስፈላጊነቱም የማሻሻል፤ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር አዳዲስ ስታንዳርዶችን የማውጣት፤ የግብርና አገልግሎት አሰጣጥን እንዲሁም የግብርና ግብዓትና ምርት አመራረትና ግብይት የአገሪቱንና እንደአስፈላጊነቱም የአለም አቀፍ የጥራት፤ የኳራንቲን ደህንነትን ስታንዳርዶች አሟልተው እየተከናወኑ መሆኑን በመስክና በላቦራቶሪ ምርመራ በማረጋገጥ የመቆጣጠርና ተቀባይነት ያለው የእዕዋት ወይም የእንስሳት ጤና ሰርተፊኬት የመስጠት፤ በውጭ ሀገር ተመርተው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡና ቁጥጥር የሚደረግበት የግብርና ግብዓት እና ምርት በተመለከተ በወጡ የህግ ማዕቀፎች ጥራት ጤንነትና ደህንነት መስፈርቶችን ማሟላታቸውን የማረጋገጥ፤ የቅድመ የማስገቢያ ፈቃድ እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላ የመልቀቂያም ፈቃድ የመስጠት፤ መስፈርቱን ካላሟሉ የማገድ ወይም እንዲታከም ወይም እርምት እንዲደረግበት ወይም አስፈላጊም ከሆነ እንዲወገድ ወይም ወደመጣበት ሀገር እንዲመለስ ማድረግ፤ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ቀጠናዊ የሬጉላቶሪ እና የኳራንቲን ቁጥጥር መርሆዎችና ስምምነቶች እንዲተገበሩ ማድረግ፤ የእፅዋት ኳራንቲን ተባይና በሽታ እንዲሁም ድንበር ተሸጋሪ የእንስሳት በሽታ ቅኝት፣ አሰሳ እና የስጋት ትንተና የማካሄድ፤ የእፅዋትና እንስሳት ኳራንቲን ግልጋሎት የሚሰጥ የቅድመና ድህረ መግባት ኳራንቲን እና የዘር-ድህረ ጥራት ቁጥጥር ጣቢያዎች የማቋቋምና የማደራጀት፤ የእፅዋትና እንስሳት ተባይና የበሽታ ስርጭት ጥናት በማድረግ አገራዊ የኳራንታይን ተባይና በሽታ መዘርዝር የማዘጋጀት፤ ህይወት ያለው ደቂቀ ዘ-አካላት ወይም እንስሳት ወይም እፅዋት ከውጭ ሀገር ሲገባ መርምሮ የመግቢያ ፈቃድ የመስጠት፤ የሀገር ውስጥ ብዝሀ ሕይወት ከውጭ በሚገቡ ባዕድ ወራሪ ዝርያዎች ጥፋት እንዳይደርስበት ቁጥጥርና ክትትል አድርጎ አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ለሀገር ውስጥ ብዝሀ ሕይወት የአርክቦት ፈቃድ የመስጠት ተግባራትንም ያከናውናል፡፡
በአጠቃላይ በግብርና ዘርፍ የተጠናከረ ሪጉላቶሪ ስርዓት በመዘርጋት እና በመተግበር በአለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ በሰው፤ በእንስሳትና በእፅዋት ጤና እንዲሁም በአካባቢ ላይ ጎጂ ተፅዕኖ እንዲቀንስ ወይም እንዲወገድ የማስቻል ዓላማን ይዞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ባለሥልጣን መ/ቤቱ የቁጥጥር ሥራ እጅግ ውስብስብ በመሆኑና በዘርፉ ላይ በርካታ ችግሮች በመኖራቸው የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የተጣለበትን አገራዊ ተልዕኮ ለመወጣት የግብርና ቴክኖሎጂ፣ ግብዓት፣ ምርትና አገልግሎትን ብቃት፣ ጥራት፣ ፍቱንነት፣ ጤንነትና ደኅንነት በማረጋገጥ የግብርና ምርቶችን ጥራትና የዜጎቻችንን ጤንነት ለማስጠበቅ ተቋማዊ አቅሙን በማሳደግ፣ አሰራሮችን በማዘመንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀቴ ልክ እንደወታደር እየሰራ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የአዲሱ መስሪያ ቤት አድራሻ
ቂርቆሰ ክ/ከተማ ወረዳ 6 የቤት ቁጥር 252/2 ከአፍሪካ ህብረት ፊት ለፊት ዮቴክ ህንፃ ላይ ነው፡፡
ለበለጠ መረጃ
ስልክ፡- 011 553 45 20
ዌብሳይት፡- www.eaa.gov.et
ፌስቡክ፡- የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን/
Ethiopian Agricultural Authority
ቴሌግራም፡- የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን
ነፃ ጥሪ፡- 8083
ፖ.ሳ.ቁ፡- 31303
1 411
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን አግባባዊ የእንስሳት መድኃኒት አያያዝና አጠቃቀምን ለማጎልበት በሚያደርገው ጥረት የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ፤
*
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ለተውጣጡ የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች በአዳማ ከተማ ሂል ሳይድ ሆቴል ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የእንስሳት ሪጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሐሚድ ጀማል ጥራቱ፣ ደኅንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ የእንስሳት መድኃኒት ለእንስሳት ኃብቱ እድገት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ አግባባዊ የእንስሳት መድኃኒት አያያዝና አጠቃቀም ለማጎልበት ባለሥልጣን መ/ቤቱ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነና ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓቶችን እየዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ሐሚድ አክለውም የእንስሳት መድኃኒት አያያዝና አጠቃቀም ጉድለት በዘርፉ ላይ ትልቅ አደጋ መደቀኑን እና በአገር ላይ ከሚያደርሰው ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ባሻገር በሰው ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን አግባባዊ የእንስሳት መድኃኒት አያያዝና አጠቃቀምን በማጎልበት የአገሪቱን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚያደርገው ጥረት የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከአግባባዊ የእንስሳት መድኃኒት አያያዝና አጠቃቀም ጋር የተያያዙ በባለሥልጣኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ያሉ የሕግ ድንጋጌዎችና የሚያስከትሉት የሕግ ተጠያቂነት፣ አግባባዊ የእንስሳት መድኃኒት አያያዝና አጠቃቀም ለማጎልበትና እና ለቁጥጥር ሥራ በሚረዱ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በባለሥልጣን መ/ቤቱ ባለሙያዎች የሥልጠና ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ደኅንነቱ፣ ፈዋሽነቱና ጥራቱ የተጠበቀ የእንስሳት መድኃኒት አያያዝና አጠቃቀምን ማሻሻል የእንስሳት ኃብት ልማትን በማሳደግ በአገሪቱ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የእንስሳት ጤና አጠባበቅ መርኃ ግብር በተሻለ ሆኔታ ውጤታማ በማድረግ በእንስሳትና በእንስሳት ውጤቶች በዓለምአቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኝት እንዲሁም የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑ በሥልጠና ሰነዶቹ ተመላክቷል፡፡ በተጨማሪም በእንስሳት መድኃኒት ላይ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራት እስከ 10 ዓመት ጽኑ እስራት የሚደርስ የሕግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ተገልጿል፡፡
አግባባዊ የእንስሳት መድኃኒት አያያዝና አጠቃቀምን ለማስፈን የሚደረጉ አበረታች ተግባራትን ያደነቁት የሥልጠናው ተሳታፊዎች ሥለሕጉ እና ሥለችግሩ ግዝፈት ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠርና ከክልሎች ብሎም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ ከመሥራት አኳያ ባለሥልጣኑ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ መሰል የግንዛቤ ማጎልበቻ ሥልጠናዎች እስከታች ላለው የእንስሳት ጤና ባለሙያና ለጸጥታና አስተዳደር አካላት ተደራሽ ሊሆን እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡
የአገሪቱን የግብርና ዘርፍ ለማሳደግ በዋነኛነት በእንስሳት መድኃኒት አያያዝና አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን መቅረፍ መሰረታዊ ነው ያሉት የባለሥልጣኑ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ገመዳ ቢነገዴ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ ግንዛቤዎችን ከመፍጠር ባለፈ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮና ተቀናጅቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ገመዳ አክለውም አግባባዊ የእንስሳት መድኃኒት አያያዝና አጠቃቀምን ማጎልበት ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ባለመሆኑና ችግሩም አገሪቱ በግብርናው ዘርፍ የምታገኘውን ኢኮኖሚዊ ተጠቃሚነት ከማሳጣቱም ባለፈ የሕብረተሰቡን ጤና የሚያቃውስ በመሆኑ የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች የእንስሳት መድኃኒት ጥራት፣ ደኅንነትና ፈዋሽነትን ለማስጠበቅ ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
@የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፤
የፌስቡክ ገጻችን ይቀላቀሉ፡- https://www.facebook.com/EthiopianAgriculturalAuthority
1 411
እንኳን አደረሳችሁ!
*
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ለክርስትና እምነት ተከታይ የባለሥልጣን መ/ቤታችን አመራሮችና ሠራተኞች እንዲሁም ለመላ ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ2015 ዓ.ም የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ይላል!
በዓሉ የሰላም፣ የጤናና የመተሳሰብ እንዲሆንም ይመኛል!
#መልካም_የከተራና_የጥምቀት_በዓል!
@የኢትዮጵያ_ግብርና_ባለሥልጣን
1 411
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የእንስሳት ሪጉላቶሪ ዘርፍ የአገልግሎት ክፍያ የጥናት ሰነድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ፤
****
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን በደንብ ቁጥር 509/2014 አንቀጽ 30 መሠረት ባለስልጣኑ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሰረት የአገልግሎት ክፍያዎችን የመሰብሰብ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይሄን ተግባራዊ ለማድረግ በባለሥልጣኑ የእንስሳት ሬጉላቶሪ ዘርፍ የአገልግሎት ክፍያ ጥናት ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የግብርና ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ኤክስኪዩቲቭ ሆቴል የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባለሥልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ ባለስልጣን መ/ቤቱ በሕግ ከተሰጠው የቁጥጥር ተግባራት በተጓዳኝ ለቁጥጥር ሥራ አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችንና ወደፊት በአዲስ መልክ ለተገልጋዮች ለሚሰጣቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች የተቀለጠፈና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ የወጪ መጋራት መርህን ታሳቢ ያደረገ፣ ተመጣጣኝና የተገልጋዎችን የመክፈል አቅም ያገናዘበ፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ብሎም ግልጽና ወጥነት ያለው የክፍያ አሰራር ሥርዓት በሁሉም የእንስሳት ሬጉላቶሪ ዘርፍ ተግባራዊ ማድረግ አንዱ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም እየተሰራባቸው የሚገኙ ነባር የአገልግሎት ክፍያ ተመኖች በጣም የቆዩና ያልተከለሱ ስለሆኑ የሥራ ዘርፉ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያወጣው ወጪና የሚሰበስበው ክፍያ ያልተመጣጠነ እንዲሁም ከወቅቱ የገንዘብ የመግዛት አቅም ጋር ያልተገናዘበ በመሆኑ ነባር የአገልግሎት ክፍያ ደንብና መመሪያዎችን መከለስና ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ድሪባ በባለስልጣን መ/ቤቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የክፍያ አሰራሮችን በጥልቀት በመመርመርና በመፈተሽ፣ ሌሎች ከባለስልጣን መ/ቤቱ ጋር ተመሳሳይ የቁጥጥር ስራዎችን የሚሰሩ ተቋማት ልምድና ተሞክሮ እንደ ግብዓት በመጠቀም የወጪ መጋራት መርህን ታሳቢ ያደረገ፣ ተመጣጣኝና የተገልጋዎችን የመክፈል አቅም ያገናዘበ፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ የአገልግሎት ክፍያ ጥናት ሰነድ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ድሪባ አክለውም የምክክር መድረኩ ዋነኛ ዓላማም ይህን በባለሥልጣን መ/ቤቱ የተዘጋጀውን የእንስሳት ሪጉላቶሪ ዘርፍ የአገልግሎት ክፍያ የጥናት ሰነድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግና የተለያዩ ምክረ ኃሳቦችንና ግብዓቶችን በመቀበል ደንቡ ከመጽደቁ በፊት የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ነው ብለዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ በባለሥልጣን መ/ቤቱ የተዘጋጀው የእንስሳት ሪጉላቶሪ ዘርፍ የአገልግሎት ክፍያ ጥናት ሰነድ በሚመለከታቸው አካላት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በባለሥልጣን መ/ቤቱ ባዘጋጀው የእንስሳት ሪጉላቶሪ ዘርፍ የአገልግሎት ክፍያ የጥናት ሰነድ ላይ የምክክር መድረክ በማዘጋጀቱ አመስግነው የአገልግሎት ክፍያ መኖር እንዳለበት ብናምንም ተመኑ በዘርፉ ያለውን ኤክስፖርትና ኤምፖርት ላይ ተጽዕኖ እንዳይኖረውና በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን እንዳያቀጭጭ ሊታሰብበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በጥናት ሰነዱ ሊታዩና ሊስተካከሉ ይገባል ያሏቸውን ሌሎች ጥያቄዎችና አስተያየቶችም አንስተዋል፡፡
ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ የሰጡት በባለሥልጣን መ/ቤቱ የእንስሳት ሪጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሐሚድ ጀማል የአገልግሎት ክፍያ ጥናት ሰነድ ማዘጋጀት ያስፈለገው ዘርፉን ለማቀጨጭ ሳይሆን ግልጽና ወጥነት ያለው የክፍያ አሰራር ስርዓት በሁሉም የእንስሳት ሬጉላቶሪ ዘርፍ ተግባራዊ በማድረግ የዘርፉን ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግና በዘርፉ የተሰማሩ አካላትንም ሆነ አገሪቱን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ግብርናን ለማዘመን ባለሥልጣኑ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ማዘመን ይጠይቃል ያሉት ዶ/ር ሐሚድ ከባለድርሻ አካላት የተነሱ አስተያየቶችን ታሳቢ በማድረግ የአገልግሎት ክፍያ ጥናት ሰነዱ እንደሚፈተሸ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ሐሚድ አክለውም እንደባለሥልጣን መ/ቤት የባለድርሻ አካላትን ኃሳብ ለማዳመጥ፣ በቅንነት ለማገልገልና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና ዘርፉን ለማላቅ ሁሌም ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
እንደአገር የእንስሳት ኃብቱ ቢኖረንም የቁጥጥር ሥርዓቱን ማጠናከርና ማዘመን እስካልቻልን ድረስ በዘርፉ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት አንችልም ያሉት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የእንስሳት ሪጉላቶሪ ዘርፍ የአገልግሎት ክፍያ የጥናት ሰነድ ዘርፉን ለማዘመንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ድሪባ አክለውም በምክክር መድረኩ ላይ የተነሱ ኃሳቦችን በመውሰድ ባለሥልጣኑ በትኩረት እንደሚመለከታቸውና ዘርፉን ወደፊት ለማራመድ ባለድርሻ አካላትም በግልጽነት ከባለሥልጣኑ ጋር ተቀራርበውና ተባብረው እንዲሰሩ በማሳሰብ የምክክር መድረኩ ተጠናቋል፡፡
@የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፤
የፌስቡክ ገጻችን ይቀላቀሉ፡- https://www.facebook.com/EthiopianAgriculturalAuthority
1 411
ዶ/ር ደሴ፦ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ከ2009 ዓ.ም ከተቋቋመ ጀምሮ እስከ አሁን የሰራቸው ሥራዎች ስንመለከት በዋነኛነት ተቋማትን ማቋቋም ሲሆን ወደ 35 የሚደርሱ ጅምላ እና 5 አስመጪ የቅድመ ፈቃድ ተቋማትን ማቋቋም ተችሏል፡፡ ነገር ግን ሕግና መመሪያውን ተከትሎ በአግባቡ ካለመስራትና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ጥቂት ተቋማት ብቻ አብረውን እየሰሩ ይገኛሉ ማለት ነው፡፡ በእነዚህ ተቋማት ላይም የኢንስፔክሽን ሥራዎችን እንሰራለን፤ በዚህም መሰረት 9 የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ 1 እገዳና 7 ተቋማትን ላይ የመሰረዝ እርምጃ ወስደናል፡፡ እንዲሁም 12 ተቋማት በራሳቸው ፈቃድ፣ ከገበያው ጋር ባለመወዳደር እና ሌላ ዘርፍ ላይ በመሰማራት የሙያ ፈቃዳቸውን የመለሱ ሲሆን እኛም የሥራ ስረዛ ደብዳቤ ሰጥተናቸዋል፡፡ በመኖ ተቋማት በኩልም 13 የመኖ ማቀነባበሪያዎች፣ 3 ጅምላ አከፋፋዮች በባለስልጣኑ በኩል የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት አውጥተው የሚሰሩ ሲሆን እነዚህ ተቋማትም ማሟላት ያለባቸውን መስፈርት እንዲያሟሉ የተለያዩ ሥራዎችን ሰርተናል፡፡ ነገር ግን ቁጥጥር ከማድረግ አንፃር እየተሰራ አይደለም፤ ምክንያቱም የመኖ ቁጥጥር ባለሙያ ባለመኖሩ ሲሆን ይህ ችግር በቀጣይ ይስተካከላል ብለን እናስባለን፡፡ ሌላው የችርቻሮ ተቋማትን በ16 ከተማ አስተዳደርና በ46 ወረዳዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት መመሪያና ሕጉን ጠብቀው እየሰሩ ነው ወይ የሚለውን ክትትልና ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ባደረግነው ክትትልና ድጋፍም ክፍተት የተገኘባቸውን ሕግና መመሪያውን የጠበቀ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከሚመለከተው አካል ጋር ተባብረን እንሰራለን፡፡ እንዲሁም የእንስሳት መድኃኒትና መኖ ባለሙያዎችን በመድኃኒትና መኖ አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ በሰጠነው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የተገኘው ውጤት ምንድን ነው የሚለውን በዳሰሳ ጥናት ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ በተጨማሪም የጥራት ችግር ያለባቸውን መድኃኒቶችንና መኖዎችን ከባለስልጣን መ/ቤቱና ከሌሎች ባለድርሻ አካለት ጋር በመሆን ህግና መመሪያውን ተከትለው እንዲሰበሰቡና ምርመራ እንዲደረግባቸው እናደርጋለን፡፡
ሕ/ግ፦ አገልግሎት አሰጣጣችሁን ከብልሹ አሰራርና ኪራይ ሰብሳቢነት የጸዳ ለማድረግ የምታከናውኗቸው ተግባራት ምንድን ናቸው? በስራችሁ ላይስ ቅሬታዎች ሲኖሩ የምታስተናግዱባቸውና የምትፈቱባቸው መንገዶች ካሉ ቢገልፁልን?
ዶ/ር ደሴ፦ ተቋማችን አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለኪራይ ሰብሳቢነትና ለብልሹ አሰራር ተጋላጪነቱ በጣም ደካማ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል የሚከናወኑ ሥራዎች የሉም ማለት አይደለም፤ ለአብነትም በኢንስፔክሽን ወቅት ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ባለሙያዎች በአንድ ላይ እንዲሰሩ ከማድረግ ባለፈ ተቋማቱ ትንሽ በመሆናቸው መረጃዎችን በቀላሉ በተለያዩ መንገዶች በመሰብሰብ ለብልሹ አሰራር የሚያጋልጥ ሥርዓት እንዳይኖር በትኩረት ነው የምንሰራው፡፡ በቀጣይ ግን ተቋማቱ እየሰፉ ስለሚሄዱና ሥራውም ተጋላጭ ስለሆነ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል የሚያስፈልግ በመሆኑ ከሚመለከተው የባለሥልጣን መ/ቤቱ የሥራ ክፍል ጋር በመሆን በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራ ይሆናል፡፡
ሕ/ግ፦ የ2015 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀማችሁ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ደሴ፦ የ2015 እቅድ አፈፃፀማችን በእቅዳችን መሰረት ተቋማቱን የእድሳት እንስፔክሽን አካሂደናል፡፡ በዚህም መሰረት ማሳደስ ያለባቸው እንዲያሳድሱ ከማድረግ ባለፈ ሕግና መመሪያውን ጠብቀው ላልሰሩ 3 ድርጅቶች የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ 1 ድርጅት ላይ እገዳና ሌላ 1 ድርጅት ላይ ደግሞ የመሰረዝ እርምጃ ወስደናል፡፡ ከዚህ ባለፈ ሕገ-ወጥ የእንስሳት መድኃኒትን ሥርጭትን መከላከልና መቆጣጠር እንዲቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ በተለያዩ ከተማዎችና አስተዳደሮች ላይ በመገኘት ሕግና መመሪያውን ጠብቆ ከመስራትና ከማሰራት አኳያ ግንዛቤን የመፍጠር ስራ ሰርተናል፡፡
ሕ/ግ፦ ሥራችሁን ስታከናውኑ ያጋጠማችሁ ችግር ካለ?
ዶ/ር ደሴ፦ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ተነሳሽነት ያለው መስራት የሚችል ባለሙያ አለ፤ ነገር ግን በሚፈለገው ደረጃ አላሰራነውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ባለሙያው ተንቀሳቅሶ የሚሰራበት የትራንስፖርት አቅርቦትና በጀት አለመኖሩ እንዲሁም ማግኘት ያለበትን ጥቅማጥቅም ባለማግኘቱ በሁሉም አካባቢዎች ላይ ተደራሽ ሆኖ ከመስራት አኳያ ክፍተት አለ፡፡ በተጨማሪም በቂ የሰው ኃይል አለመኖሩና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ባለስልጣን መ/ቤቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በሙሉ በክልል ደረጃ እንዲሰጥ አለመደረጉ ቀልጣፋና ምቹ አሰራርን ለመዘርጋት እንቅፋት እየሆነ መጥቷል፡፡
ሕ/ግ፦ በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
ዶ/ር ደሴ፦ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ከመስፋቱ ጋር ተያይዞ ጥሩ የሆነ አገራዊ ተቋም በመፍጠር ለውጥን በማምጣት የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችንም በተጠናከረ ሆኔታ በማደራጀት በመደገፍ የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት ይችላል የሚል ከፍተኛ እምነት አለን፡፡ እኛም የባለሥልጣኑን አገልግሎቶች ለማኅበረሰቡ በቀላሉ ተደራሽ ከማድረግ አልፈን የግብርናውን ዘርፍ በማሳደግ የውጭ ምንዛሪያችንን በሚፈለገው ሆኔታ የምንጨምርበትን አቅም መፍጠር ስለምንችል ተናበንና ተቀናጅተን እንስራ የሚል መልዕክቴን በዚሁ አጋጣሚ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡
ሕ/ግ፦ ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!
ዶ/ር ደሴ፦ እኔም አመሰግናለሁ!
@የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፤
የፌስቡክ ገጻችን ይቀላቀሉ፡- https://www.facebook.com/EthiopianAgriculturalAuthority
1 411
«ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሕገ-ወጥ የእንስሳት መድኃኒትና መኖ ሥርጭትን ለመቀነስ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል!»
ዶ/ር ደሴ ደበብ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ
****
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን በግብርና ዘርፉ የተጠናከረ ሬጉላቶሪ ሥርዓት በመዘርጋትና በመተግበር በዓለምአቀፍ እና በአገርአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ በሰው፣ በእንስሳትና በእጽዋት ጤና እንዲሁም በአካባቢ ላይ ጎጂ ተጽዕኖ እንዲቀንስ ወይም እንዲወገድ የማስቻል ዓላማ ይዞ በደንብ ቁጥር 509/2015 የተቋቋመ የፌደራል መ/ቤት ነው፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ባለሥልጣን መ/ቤቱ ይሄን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የከፈታቸውን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የሥራ እንቅስቃሴ በመዳሰስ በየ2 ወሩ በሚያዘጋጀው የውስጥ ዜና መጽሔት የሚያቀርብ ሲሆን በዚህ ወር እትምም የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ከዶ/ር ደሴ ደበብ ጋር በእንስሳት መድኃኒትና መኖ ላይ እየተሰሩ ያሉ የቁጥጥር ሥራዎችንና አጠቃላይ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱን የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ቆይታ አድርገን ለአንባቢያን በሚመች መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ፡፡
ሕ/ግ፦ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ዋና ተግባራትና የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ምንድን ናቸው?
ዶ/ር ደሴ፦ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የተቋቋመው በ2009 ዓ.ም ሲሆን የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማም የዋና መ/ቤቱን ራዕይና ተልዕኮ ለማሳካት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ባለስልጣን መ/ቤቱ ሲቋቋም አንደኛው ዓላማው የእንስሳት መድኃኒትና መኖ የቁጥጥር ሥራዎች ሥርዓት በማስያዝ ሕጋዊ ሰንሰለታቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ጥራቱ፣ ደኅንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ የእንስሳት መድኃኒት እና ጥራቱ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ የእንስሳት መኖ ለማኅበረሰቡ እንዲቀርብ ማድረግና አገሪቱ ካላት እንስሳት ኃብት ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሕገ-ወጥ የእንስሳት መድኃኒትና መኖ ሥርጭትን በመቀነስ በመከታተልና በመቆጣጠር በኩል የራሱን ሚና የሚወጣ መ/ቤት በመሆኑ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱም ይህንን የባለስልጣኑን ኃላፊነትና ተግባር መሰረት አድርጎ የሚሰራ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ 35 ለሚሆኑ የእንስሳት መድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች የጅምላ ተቋማት ከባለሥልጣን መ/ቤቱ የሚመለከተው ክፍል ጋር በመሆን ምዝገባና ፈቃድ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በአስመጭ በኩልም 5 ተቋማት የቅድመ ፍቃድ እንዲያወጡ ማድረግ ችለናል፡፡ መኖን በተመለከተ በማቀነባበርና ጅምላ በማከፋፈል ለተሰማሩ እንዲሁም ወደ ዘርፉ ለሚገቡ ተቋማት አስፈላጊ ክትትልና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ አከናውነናል፡፡
ሕ/ግ፦ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በሚወጡና በሚገቡ የእንስሳት መድኃኒት፣ መኖና የላቦራቶሪ መገልገያ መሳሪያዎች እንዲሁም በእንስሳት መድኃኒትና መኖ አስመጭና ጅምላ አከፋፋይ ተቋማት ላይ የኢንስፔክሽንና የቁጥጥር ሥራ የምታደርጉት በምን አግባብ ነው?
ዶ/ር ደሴ፦ መግቢና መውጫ ኬላን በተመለከተ እንደኛቅርንጫፍ ጽ/ቤት አንድ ማለትም የመተማ መውጫና መግቢያ ኬላ ብቻ ነው ያለን፡፡ ኬላው 3 ባለሙያዎች ማለትም 2 የመድኃኒትና 1 የመኖ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ያሉት ሲሆን እስከ 2012 ዓ.ም አሻፋር የሚባል አንድ አስመጪ ተቋም የነበረ ሲሆን በኮቪድና በአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ ምክንያት ስራውን ማከናወን አልቻለም፡፡ በዚህም መሰረት ምንም አይነት የቁጥጥር ስራ አልተከናወነም ማለት ነው።
ሕ/ግ፦ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ሕገ-ወጥ የእንስሳት መድኃኒትና መኖ ንግድ በብዛት የሚታይባቸውን አካባቢዎች ከመለየትና የተለዩትን አካባቢዎች ላይም ትኩረት ሰጥቶ ከመሥራት አንጻር የተሰሩ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?
ዶ/ር ደሴ፦ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሕገ-ወጥን በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ የዳሰሳ ጥናት መስራት ነው፡፡ በዚህም መሰረት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በሕገ-ወጥ የእንስሳት መድኃኒትና መኖ ንግድና ሥርጭት ዙሪያ 2 ጊዜ በአማረኛና በእንግሊዘኛ የዳሰሳ ጥናት አካሂዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከዋና መ/ቤቱ ጋር በመሆን ሕገ-ወጥ የእንስሳት መድኃኒትና መኖ ንግድ ሥርጭት ዙሪያ የመጣ ለውጥ ምንድን ነው? የሚለውን በጋራ ተንትነን ውጤቱን ለሚመለከተው አካል ልከናል፡፡ ሁለት ጊዜ ባደረግነው ጥናት ላይ ስንገመግም ከመጀመሪያው በተሻለ ሕገ-ወጥ የእንስሳት መድኃኒትና መኖ ንግድና ሥርጭት የቀነሰበት ሆኔታ እንዳለ ለማስተዋል ችለናል፡፡
ሕ/ግ፦ ሕገ-ወጥ የእንስሳት መድኃኒትና መኖ ንግድና ሥርጭትን ለመከላከል በተፈጠሩ የሕዝብ ንቅናቄ መድረኮች ላይ የተቋቋሙ ግብረ ኃይሎችን እና የመተማ መግቢያና መውጫ ኬላ ቅርንጫፍን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የሚገኙ የሚመለከታቸውን አካላት ከመደገፍና ከመከታተል አንጻር የምታደርጉት የክትትልና ድጋፍ ሥርዓታችሁ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ደሴ፦ ሕገ-ወጥን ከምንከላከልባቸው መንገዶች መከላከል አንደኛው እንደተጠቀሰው የሕዝብ ንቅናቄ መድረክ ማዘጋጀት ነው፡፡ በዚህም መሰረት ሕገ-ወጥ የእንስሳት መድኃኒትና መኖ አቅርቦት የሚያስከትለው ችግር ምንድን ነው የሚለውን እንደቅርንጫፍ ጽ/ቤት እስካሁን 6 ጊዜ የሕዝብ ንቅናቄ መድረኮችን በመተማ፣ በጃዊ፣ በኮምቦልቻና በባቲ በማካሄድ ግንዛቤን ፈጥረናል፡፡ ከዚህ ባለፈ 4 የግብረ ኃይል ኮሚቴ አቋቁመን ከእነዚህ ኮሚቴዎች ጋርም በተለያዩ የግንኙነት አማራጮች በየጊዜው እየተገናኘን መረጃዎችን እየተለዋወጥን የምንሰራ ሲሆን የበጀት እጥረት ካልገጠመን በቀር በዓመት አንድ ጊዜ በአካል በመገኘት ክትትልና ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ኮሚቴዎች የሚጠበቅባቸውን ሥራዎች በተለያዩ ምክንያቶች እያከናወኑ አይደለም፡፡ የሰራተኛ መቀያየር፣ ሕጋዊ እውቅና አለመሰጠት፣ የበጀት እጥረትና የትራንስፖርት ችግር ለሥራቸው መሳካት እንቅፋት እንደሆነባቸው በመግለጽ የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ አይደለም፡፡ ነገር ግን በእኛ በኩል ዓመታዊ እቅድ በመስጠትና ግንዛቤ በመፍጠር ሥራቸውን እንዲሰሩ ድጋፍና ክትትል እያደረግን እንገኛለን፡፡
ሕ/ግ፦ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ከተመሰረተ ጀምሮ እስከ አሁን የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ቢገልጹልን
1 411
የእፅዋት ጤናና ምርት ጥራት ቁጥጥር የሥራ ክፍል ጥራቱና ደኅንነቱ የተረጋገጠ የእፅዋት ምርት አቅርቦትን ለማሳደግ ከወትሮው በተሻለ ተግቶ እንደሚሰራ አስታወቀ፤
****
በኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የእፅዋት ጤናና ምርት ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ሁለት አበይት ጉዳዮችን እንግቦ የሚሰራ ነው ያሉት የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር አቶ ገብረ ኪዳን አስረሳኸኝ ይህም የእፅዋት ኳራንቲንና የጸረ-ተባይ ማዳበሪያ የመመዝገብና የመቆጣጠር ሥራ ነው ብለዋል፡፡ በእነዚህ ተግባራት ላይ አገሪቱ ወደ ውጪ የምትልካቸውን የግብርና ምርቶች ጥራታቸው ደኅንነታቸው የተረጋገጡና የተቀባይ አገራት መስፈርት ያሟሉ መሆኑን በማረጋገጥ ሰርተፍኬት በማዘጋጀት ምርቶቹ ወደ ውጪ እንዲላኩ የሚያደርግ ሲሆን በተመሳሳይ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን የተለያዩ የውጪ የግብርና ምርቶች የመግቢያ መስፈርቶችን ያሟሉ መሆኑን በማረጋገጥ እንዲገቡ ሲደረግ መስፈርቱን ላላሟሉት ደግሞ ወደ መጡበት አገር ተመልሰው እንዲላኩ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
ጥራታቸው፣ ደኅንነታቸው የተረጋገጠ የእፅዋት ምርቶች በዚህ 5 ወር ውስጥ 788000 ቶን ምርት ወደ ውጪ ለመላክ ታቅዶ 463532 .4 ቶን ለመላክ የተቻለ ሲሆን አፈፃፀሙም 67 በመቶ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ገብረ ኪዳን ወደ ውጪ ለሚወጣ የእፅዋት ምርት የጤንነት ማረጋገጫ ሠርተፍኬት በዚህ አምስት ወር ውስጥ ለ21291 ሰርተፍኬት መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡ ጨምረውም በአፈጻጸሙ ወቅት የተስተዋሉ ችግሮችን በመለየት በቀጣይ ጥራቱ ደህንነቱ የተረጋገጠ የእፅዋት ምርት አቅርቦትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን አዳዲስ እና መጤ ተባዮች ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በአዋጅ ቁጥር 6/74/2002 በደነገገው መሰረት በተለየ ሁኔታ የተባይ ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች፣ ሰብሎችና ተባዮች ላይ የተባይ ቅኝት እና ስጋት ትንተና በማካሄድ በሱማሌ ክልል አንድ ኳራንቲን ተባይ ተገኝቶ ሪፖርት መደረጉን በመግለፅ በገቢ እፅዋት፣ የእፅዋት ውጤቶችና ሌሎች ቁጥጥር የሚደረግባቸው ቁሳቁሶችና የግብርና ግብዓቶች ላይ የመግቢያ መስፈርቶችን አሟልተው ለተገኙ 896 የቅድመ ማስገቢያ ፍቃድ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁለት ድርጅቶች ምርታችዉን ወደ ዉጪ ሀገር እንዲልኩ የሚያግዛቸዉ የተባይ ስጋት ትንተና መረጃ ተጠናከሮ ለMarket access ወደ ህንድ ሀገር ተልኳል ያሉ ሲሆን በተጨማሪም የወጪ እና ገቢ የእፅዋት ዝርያዎች እንቅስቃሴ በማጤን እና በመተንተን የተባይ ተገላጭነታቸውን አስቀድሞ ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ መሰራቱን በመግለፅ የዕፅዋት ብዝሀ ሕይወት ሃብትን ከውጭ ከሚገቡ ባዕድና ወራሪ ዝርያዎች ጥፋት ለመጠበቅ ናሙና ከውጭ ምርምር እና ለተለያዩ አገልግሎት ከውጭ በሚገቡ የዕፅዋት ዝርያዎች በቁጥጥር ሥርዓት እንዲያልፉ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
@የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፤
የፌስቡክ ገጻችን ይቀላቀሉ፡- https://www.facebook.com/EthiopianAgriculturalAuthority
1 411
መልካም ገና!
*
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ለክርስትና እምነት ተከታይ የባለሥልጣን መ/ቤታችን አመራሮችና ሠራተኞች እንዲሁም ለመላ ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ2015 ዓ.ም የጌታችንና የመድኃኒታችን የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ይላል!
በዓሉ የሰላም፣ የጤናና የመተሳሰብ እንዲሆንም ይመኛል!
#መልካም_ገና
@የኢትዮጵያ_ግብርና_ባለሥልጣን
1 411
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የሥጋ ምርት ከ41 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኜቱን ገለጸ፤
*
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት አንዱ ከኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ የውጭ አገራት የሚላክ ሥጋና ተረፈ ስጋ ምርት አመራረት፣ አያያዝ እና አጓጓዝን በቅርብ በመከታተል እና የኢንስፔክሽን አገልግሎት በመስጠት የሚላከው ሥጋና ተረፈ ሥጋ ጤንነቱ፣ ደኅንነቱና ጥራቱ የተጠበቀ የአገራችንን እና የተቀባይ አገሮችን መስፈርቶች ያሟላ ስለመሆኑ የጤና ማረጋገጫ ሰርተፊኬት በመስጠት የአገሪቱን የሥጋና ተረፈ ሥጋ ምርት ኤክስፖርት ማሳደግ መሆኑን የገለጹት በባለሥልጣኑ የኤክስፖርት ቄራ ኢንስፔክሽንና ሰርተፊኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር አያሌው ሹመት ባለሥልጣን መ/ቤቱ በ2015 በጀት ዓመት 28 ሺህ ቶን የሥጋ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ 150 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኜት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ባለፋት አምስት ወራትም 5 ሺህ 900 ቶን የሥጋ ምርት ወደ ውጭ አገር በመላክ 41 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኜቱን የገለጹት ዶ/ር አያሌው የሥጋ ምርቱ በስፋት ከተላከባቸው አገራት መካከል ዱባይ፣ ሳዑዲ አረቢያና ኩዌት ይገኙበታል ብለዋል።
የሥጋ ምርቱ ጥራቱን ጠብቆ በብዛት ለገበያ እንዲቀርብ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በበጀት ዓመቱ በ11 ኤክስፖርት ቄራዎች የስጋ ምርት ተቀባይ አገራትን እና ዓለምአቀፍ የምግብ ደኅንነት ስርዓት መስፈርቶችን አሟልተው የሚሰሩ መሆናቸውን ኦዲት በማድረግ የምግብ ደኅንነት የአሰራር ሥርዓቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ታቅዶ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም በቻይና፣ ኢንዶኔዥያ፣ እንዲሁም በአውሮፓ አገራት ገብያውን ሰብሮ ለመግባት የሚያስችሉ ሥራዎች በባለሥልጣኑ እየተከናወኑ መሆኑንም አብራርተዋል።
ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት፣ የእንሰሳት ኮንተሮባንድን በመከላከል፣ ሥራ ያቆሙ ቄራዎችን በቅርበት ችግራቸውን በመፈተሸ፣ በማገዝና በማብቃት ሥራ የሚጀምሩበት ሁኔታን በማመቻቸት እና ሌሎች በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመፍታት አሁን አገሪቱ ባላት አቅም በየዓመቱ ከ200 ሺህ ቶን የሥጋ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚቻል የተናገሩት ዶ/ር አያሌው ይህንንም እውን ለማድረግ ባለሥልጣኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
ከዚህ በተጓዳኝም በአገር ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የሥጋ ፍላጎት ለማሟላት ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንና በተለይም በአገር አቀፍ ደረጃ አሁን የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ይህን ክፍተት በመሙላት ረገድ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሚሆንም አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 70 ነጥብ 2 ሚሊየን የቀንድ ከብት 42 ነጥብ 9 ሚሊየን የበግ፣ 8 ሚሊየን የግመል እንዲሁም 52 ሚሊየን አካባቢ የፍየል ኃብት እንዳላት መረጃዎች ያመላክታሉ።
@የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፤
የፌስቡክ ገጻችን ይቀላቀሉ፡- https://www.facebook.com/EthiopianAgriculturalAuthority
1 411
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የእንስሳት መድኃኒትን ጥራት፣ ደኅንነትና ፈዋሽነትን ለማስጠበቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ ተቀራርቦ እንደሚሰራ አስታወቀ፤
****
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ከእንስሳት መድኃኒት አስመጪና ጅምላ አከፋፋይ ባለሀብቶች እና ሥራ አስኪያጆች ጋር የእንስሳት መድኃኒትን ጥራት፣ ደኅንነትና ፈዋሽነትን ማስጠበቅ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ማዕከል መሰብሰቢያ አዳራሽ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ የእንስሳት መድኃኒት ጥራት፣ ደኅንነትና ፈዋሽነትን በማስጠበቅ ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ለዚህም የእንስሳት መድኃኒት አስመጪና ጅምላ አከፋፋይ ባለሀብቶች እና ሥራ አስኪያጆች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ባለሥልጣን መ/ቤቱ የእንስሳት መድኃኒት ከየትኛውም አካባቢ ማለትም ከአውሮፓ ወይም ከሌሎች አካባቢዎች ሲመጣ ባለሥልጣን መ/ቤቱ የአሰራርና ሥርዓቱን በማዘመንና ቁጥጥሩን በማጠናከር የመድኃኒት ጥራት፣ ደኅንነትና ፈዋሽነትን ለማስጠበቅ እንደሚሰራና የእንስሳት መድኃኒት ንግድ ላይ የተሰማሩ የንግድ ድርጅት ባለቤቶች ባለስልጣን መ/ቤቱ የሚዘረጋቸውን አሰራሮችን በማክበር መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ድሪባ አክለውም ወደፊት አገራችን የአለም ንግድ ድርጅት አባል እንደምትሆን በመግለጽ ውድድሩ ከፍተኛ እንደሚሆን እና የእንስሳት ምርቶች እና ውጤቶች የሚላኩበት ሀገር እንደሚሰፋ፤አስገዳጅ ደረጃዎችንም ማሟላት ስለሚጠበቅብን፤ ለዚህ ደግሞ የእንስሳት በሽታዎችን ለመቆጣጠር ጥራት ያለው የእንስሳት መድኃኒት ማቅረብ እንደሚጠበቅና አሰራሮችን በማዘመን መስራት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡ የእንስሳት መድኃኒት እጥረት፣ የዋጋ ንረትና የፈዋሽነት ችግሮች የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን የጠቀሱት አምባሳደር ድሪባ መድረኩ በዋናነት ባለስልጣን መ/ቤቱ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በመቀራረብ የታዩ የአሰራር ክፍተቶችን እንዴት መቅረፍና ማስተካከል እንደሚገባ ወደፊትም እንዴት መቀጠል እንዳለብን ምክክር የሚደረግበት መሆኑን በመግለጽ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ተቀራርቦ በመተጋገዝ ጥራቱ፣ ደኅንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ የእንስሳት መድኃኒት ለማሕበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ በእንስሳት መድኃኒት አስመጪ እና ጅምላ አከፋፋይ ድርጅቶች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ቁጥጥር ምልከታ የተገኙ ክፍተቶች ሪፖርት፣ የእንስሳት መድኃኒት አስመጪ እና ጅምላ አከፋፋይ ድርጅቶች ፈቃድ አሰጣጥ እና የተስተዋሉ ክፍተቶች፣ በእንስሳት መድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች አስመጪ፣ ጅምላ አከፋፋይና ላኪ ድርጅቶች የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት አሠጣጥና ቁጥጥር መመሪያ፣ በአዋጅ ቁጥር 728/2004 እና ደንብ ቁጥር 509 የተወሰኑ አንቀጾች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው በባለሥልጣን መ/ቤቱ የበላይ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን መ/ቤት በደንብ ቁጥር 509/2014 መሠረት ሲቋቋም የእንስሳት መድኃኒት ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነትን ለማረጋገጥ፣ የእንስሳት ጤናን ለመጠበቅና ህገ-ወጥ የእንስሳት መድኃኒት ንግድና ዝውውርን ለመቆጣጠር መሆኑን የገለጹት የባለሥልጣን መ/ቤቱ የእንስሳት ሪጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሀሚድ ጀማል ባለስልጣኑም የንግድ ማህበረሰቡን እንዲጠናከር እንጂ እንዲቀጭጭ የማይፈልግ በመሆኑ በተቋማት ላይ እርምጃ ስንወስድ የባለሥልጣን መ/ቤቱን መመሪያና አዋጅ መሰረት ተደርጎ በኢንስፔክሽን ውጤት መሰረት መሆኑን በመገንዘብ ተቋማት ሕግና ሥርዓትን አክብረው በመስራት ለዘርፉ ማደግ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን በቀጣይ የእንስሳት መድኃኒትን ጥራት፣ ደኅንነትና ፈዋሽነትን ለማስጠበቅ እና ዘርፉን በማዘመን ችግሮችን ለመቅረፍ ከአቢሲኒያ እንስሳት መድኃኒት አስመጪና ጅምላ አከፋፋይ ማኅበር እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ ተቀራርቦ እንደሚሰራ የተገለጸ ሲሆን የእንስሳት መድኃኒት ንግድ ላይ የተሰማሩ የንግድ ድርጅት ባለቤቶች ባለስልጣን መ/ቤቱ የሚዘረጋቸውን አሰራሮችን በማክበር መስራት እንዳለባቸው የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ የምክክር መድረኩ ተጠናቋል፡፡
@የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፤
የፌስቡክ ገጻችን ይቀላቀሉ፡- https://www.facebook.com/EthiopianAgriculturalAuthority
1 411
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት በየ2 ወር የሚያዘጋጀው የውስጥ ዜና መጽሔት የታኅሣሥ ወር እትም በፒዲኤፍ
@የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፤
የፌስቡክ ገጻችን ይቀላቀሉ፡- https://www.facebook.com/EthiopianAgriculturalAuthority
