cookie

Мы используем файлы cookie для улучшения сервиса. Нажав кнопку «Принять все», вы соглашаетесь с использованием cookies.

avatar

Getahun ayano.blogpost's

አጫጭር ትምህርት አዘል መልዕክቶች የሚቀርቡበት ቻናል ።

Больше
Рекламные посты
214
Подписчики
Нет данных24 часа
Нет данных7 дней
+130 дней

Загрузка данных...

Прирост подписчиков

Загрузка данных...

ስቻለሁ የምለው አንዳች ነገር የለኝም፤ ኅሊናዬ ከሚያዘኝ ውጪ መሆን ትክክልም ሆነ አግባብ አይደለም። እነሆ፤ እዚሁ ቆሜያለሁ፤ ከዚህ ውጪ ምንም ላደርግም አይቻለኝም። እግዚአብሔር ሆይ እርዳኝ። አሜን።» ማርቲን ሉተር
Показать все...
..... 👣 እግረ መንገዴን ፸፬ 👣.... “በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እንዲረዳኝም ወደ አምላኬ ጮኽሁ፤ እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ ጩገርግጥምከፊቱ ደረሰ፤ ወደ ጆሮውም ገባ።” — መዝሙር 18፥6 (አዲሱ መ.ት) ጭንቀት ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ በሚታይበት ጊዜ የሚከሰት የትላንት ስጋት እና የነገ ፍርሃት ተዳብለው የሚውልዱት ነው ። ትላንት ይደገም ይሆን የሚል ስጋት አንዳንድ ሰዎችን በጭንቀት ተኮራምተው እንዲቀመጡ ያደርጋቸዋል ። ባልተጀመረ እና ባላለቀ ዛሬ ገና ጎህ ሳይቀድ ያለፈው ትላንት ዛሬም ይቀጥል ይሆን ብሎ መስጋት ርግጥም ለጭንቅ ይዳርጋል ።" ትላንት ይደገም ይሆን? "ብሎ የሚሰጋ ልብ ጭንቀት በተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚያኖር ነውና ከመኖር ይልቅ ሞትን ይመርጣል ። ዛሬን ካለፈው ትላንት ለይቶ ማየት የማይችል ሰው ሁሌም በድግግሞሽ ሕይወት ስለሚኖር በጭንቀት ይበከነከናል። እንዲህ ባለ ጭንቀት ውስጥ ያለ ሰው ትላንት ይደገማል የሚል ስጋቱ ነገን እንዲፈራ ያደርጋዋል ። ጭንቀት ዛሬ በተከሰተውም ነገር መርበትበት ነው ። ድንገት የሚከሰት ነገር ከመሆኑ የተነሳ ከቁጥጥር በላይ ሆኖ ለጭንቅ ይዳርጋል ። ለነገሩ የዛሬው ድንገተኛ ክስተት ነው ነገን ይቀጥል ይሆን የሚል ፍራቻ ውስጥ የሚዶለን። ጭንቀት ከልክ በላይ የመወጠር አባዜ ነው ። ሰው ከልኩ ወይም ከመጠኑ በላይ ሆኖ ራሱን ከፍ ባለ ሁኔታ ሊያይ በሚሻበት ጊዜ ማሰብ ከሚገባው በላይ ማሰብ ይጀመራል ። የዚህም ሁናቴ ውጤቱ ጭንቀት ይሆናል ። በጭንቀት የሚመጣ ምንም ዓይነተ አውንታዊ ነገር የለም ። ሰው በጭንቅቱ ብዛት ሊያጎድለው የሚችለው እንጂ ሊጨምረው የሚችለው ነገር የለም ። እንደ ዶ/ር ዊሊያም ባርክሌይ ገለጣ "በአሁን ወቅት ጭንቀት በዓለም ውስጥ በየጊዜው በጣም እየበዛና እየተስፋፋ የመጣ ይመስለላል።"እንደ አንድ የጤና ተቋም ሪፖርት፣ "የጭንቀት መዛባቶች በአሜሪካን የተለመዱ የአእምሮ ሕመም እየሆኑ ነው።" ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጭንቀት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ባሉት መካከል እንኳን እየጨመረ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉት ትላልቅ የመጻሕፍት መሸጫ ተቋማት ውስጥ ባርነስ እና ኖብል የሚባለው መደብር ከሁለት ዓመታት በፊት እንዳስታወቀው፣ ስለ ጭንቀት የተጻፉ መጻሕፍት ሽያጭ በ25 በመቶ ጨምሯል። ይህ ሁሉ በቅርብ የተከሰተውና እያለፍንበት ያለው ወረርሽ ከመምጣቱ በፊት ነው። ባለፈው ዓመት ጭንቀት ይበልጥ መጨመሩ ምንም ጥርጥር የለውም።" ይለናል ። ጭንቀት ውስጣዊ ማንነታችን ጠፍሮ በመያዝ ከአንድ ሥፍራ እንዳንራመድ የሚያደርግ ክፉኛ በሽታ ነው ። ወስጣዊ ማንነታችን ወይም ልባችን የውጫዊ ማንነታችን መሪ ነው ። ልብ በተጎዳበት አካል ጤነኛ አይሆንም ። የልብ ጤንነት የአካላዊ ጤንነት ማረጋገጫ ነው ። ምስጥ የዛፍን ውስጣዊ አካል አንድባንድ እየገዘገዘች የኋላኋላ ምን ትልቅ ቢሆን እንደምትጥለው ሁሉ ጭንቀትም የሰው የሕይወት ምንጭ የሆነውን ልብ ተቆጣጥሮ ቀስበቀስ ላልተገባ ውጤት ይዳርገናል ። በጭንቅ ጊዜ ማንኛውም ሰው ሰሚ ፍለጋ ብዙ ይኳትናል ። ለውስጣችን ጭንቀት የሌሎች ሰዎች እኛን መስማት ፈውስን የሚቸር ባይሆነን እንኳ የተወሰነ አህል ጋብ ሊያደርጉልን ይችላሉ ። ለጭንቀት በሽታ ዘላቂ መፈትሔ የሚሰጥ ሐኪም በየተኛውም ዓለም ሊገኝ አይችልም ። ወቅታዊ መድኃኒት የሚሆን ማስታገሻ ይሰጥ ይሆናል እንጂ ። ጭንቀት ማስታገሻ ሳይሆን ትክክለኛ መድኃኒት ይፈልጋል ። ለጭንቀት ትክክለኛው መድኃኒት ከእግዚአብሔር በቀር የትም ሆነ ማንም ጋር የለምና ዘማሪው “በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ ይለናል ። በተጨነቅን ጊዜ ማን ጋር ነው የምንሄደው? ፣ ማንንስ ነው የምንጣራው? ሰው ዘንድ ብንሄድ ከእኛ በባሰ ጭንቀት ውስጥ እየዳኸ ነው ። ዘማሪው በጨነቀው ጊዜ ሊጠራው የሚገባውን አካል አውቋል ። በጭንቀት ወቅት ከተጨነቅንበት ነገር በላይ የሚያስጨንቀን ነገር " ከጭንቅ ነጻ ሊያወጣን የሚችል አካል ከየት እናገኝ ይሆን? " የሚል ነው ። በጭንቅ ወቅት ከጭንቅ ነጻ ከሚያወጡን ነገሮች ውስጥ ቀዳሚው ከጭንቅ የሚያወጣንን አካል ማወቃችን ሲሆን ቀጣዩ ግን ያንን አካል መጣራት እና ጭንቀትን ማዋየት ነው ። ዘማሪው “በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እንዳለው በጭንቅ ጊዜ እግዚአብሔርን ልንጠራው ይገባናል ።" እንዲረዳኝም ወደ አምላኬ ጮኽሁ፤" እንዲል በጭንቅ ወቅት እግዚአብሔርን መጣራት ከዛን መጮኽ አለብን ። የጭንቅ ፣ የጣር ድምጻችንን የሚሰማ የሚረዳን የሚያስጨንቀንን ሁሉ ሊሸከም የሚችል አምላክ ነውና ሐዋሪያው ጴጥሮስ “እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።”1ኛ ጴጥ,5፥7 (አ. መ.ት) ብሎ ከተበልን ። የሚያስጨንቀንን የምንጥልበት ፤ ስለእኛ የሚያስብ አምላክ እግዚአብሔር አለና በዚህ ሐሴት እናደርጋለን። በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እንዲረዳኝም ወደ አምላኬ ጮኽሁ፤ እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ ጩኸቴም ከፊቱ ደረሰ፤ ወደ ጆሮውም ገባ።” — መዝሙር 18፥6 (አዲሱ መ.ት) ✍️ ጌታሁን አያኖ
Показать все...
👍 1👏 1
Repost from Nolawi ኖላዊ
Фото недоступноПоказать в Telegram
Фото недоступноПоказать в Telegram
............ ዝክረ መጽሐፍ.......... ከታተመ ዐራት ዓመታት ያስቆጠረውን ‹‹የፍጥረቴ ሩጫ›› የተሰኘውን የኃይል ከበደ ሥራ በፖስተር ስሜ በጎነት ተደርጎልኝ በዚህ ዓመት ነበር በእጄ ገብቶ የማንበብ ዕድሉን ያገኘኹት ። መጽሐፍን በስጦታ የሚያበረክቱ ሰዎች ለኔ  የጸሐፊውን አህል ዋጋ አላቸው ። ጸሐፊው የከተባቸውን ጦማሮች  መድረስ ወዳለበት ሰው ሁሉ እንዲደርስ የሚደክሙ ናቸውና ምስጋና ይገባቸዋል ። ለኔ ሁሌም የሚያንጽ መጽሐፍትን የሚደርሱ  እና የተጻፈውን የሚሸጡም ሆነ የሚሰጡ ሰዎች ጀግናዎቼ ናቸው ። እና ምን ልል ነው ጋሽ ስሜ   ይህን መጽሐፍ እንዳነብ ፥ አንብቤም ትልቅን ቁም ነገር እንዳገኝ ስለረዱኝ እጅግ አድርጌ ላመስግንዎት እወዳለሁ ። በአንደ የምጽሐፍ ምረቃ ላይ አቶሚናስ ብሩክ " በማይሮጡ እግሮቹ የሚሮጡ ማኅበረሰቦችን ፈጠረ ፣ እኛ በእግሮቻችን ወደ አልባሌ ቦታ ስንሮጥ እሱ ግን በተቀመጠበት ተደራሽ መጽሐፍትን ጻፈልን " ያሉለት ኃይል ከበደ  የግጥም ፣ የወግ ፣ የአጫጭር ልቦለዶች  ፣ መልእክቶች እና የትርጉም ሥራዎቹን ትቶልን ወደጌታ እቅፍ ከሄደ ዓመታት ቢቆጠሩን   የተለያዩ ሥራዎቹን እንዲህ ባለ መልክ ተሰባጥረው መቅረባቸው ዛሬም በአሳቦቹ ሕያው ሆኖ እንዲሞግተን ሆኗልና የዝግጅት ክፍሉ ሊመሰገን ይገባዋል ። ከመጽሐፉ የተወሰደ " በሚላን ካቴድራል ሦስት በሮች ላይ በሚገኙ ውብ ቅስቶች ላይ ሦስት ጽሑፎች ይነበባሉ ። በአንደኛው ቅስት ላይ የጽጌረዳ አበባ ጉንጉን ተቀርጾበት ፣ ከስሩ "አስደሳች ነገሮች ሁሉ የቅጽበት ናቸው ። " የሚል ጽሑፍ ይነበባል ። በሁለተኛው ቅስት ላይ የመስቀል ቅርጽ ተበጸጅቶበት ከስሩ "የሚያውኩ ነገሮች ሁሉ የቅጽበት ናቸው "ይላል ። ወደጠባቡ ኮሪደር በሚየስገባው በትልቁና በዋናው ማእከላዊ መግቢያ ስር ደግሞ "ዋናው ነገር የዘላለም የሆነው ብቻ ነው "የሚል ጽሑፍ ይነበባል ። እነዚህን ሦስት እውነታዎች ብናስታውል ተራ ነገሮች አያውኩንም ፤ በሚያልፍ ደስታ አንወሰድም ፣ ለዘላቂውና ለዘላለሙ እንኖራለን ። " ገጽ 236 ባረካታ አስተማሪ ፣ ሞጋች እና ምክር ለጋሽ በሆኑ አሳባች ታጭቆ ቀርቧልና እባካችሁ ፈለግፈለግ አድርጉና አንብቡት ። ✍️ ጌታሁን አያኖ
Показать все...
..... 👣 እግረ መንገዴን ፸፪ 👣.... “የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።” — መዝሙር 94፥19 (አ.መ.ት) የውስጥ ጭንቀት አንድ ቦታ ጠፍሮ የሚያቆራምድ የማይታይ ወኅኒ ነው ። ሰው በሚታየው ዓለም ቅብዝብዝ ሆኖ በመታወክ የሚራኮተው በውስጡ ጭንቀት መብዛት ነው። ውጫዊ ነገር መሠረቱ ውስጣዊ ነው። ውስጥ ሰላም ሲሆን ውጭም ሰላም ይሆናል ። የውጭ ገጽ የውስጥ ማንነት ነጸብራቅ ነው ። ውስጥ በጭንቅ እና በመከራ ሲዳክር ጉልበት በርክ ብርክ ይላል ፤ እግር ጸንቶ መቆሞ ይሳነዋል ፤ እጅ የሚይዝ የሚጨብጠው ይጠፋዋል ፤ ዓይን ደህናውን ከማየት ይቦዛል ፤ ቀቢጸ ተስፋነት ልብ ላይ ይነግሣል ፤ እምነት ይሸረሸራል ፤ ፍቅርም ትቀዘቅዛለች ፤ ሽሽት የያዘው እግርም ይሸሸግበት ዋሻ እና ይጠለልበት ጥላ እስኪያገኝ እግር ወደመራው ሁሉ ይነጉዳል ። ልብ በሀዘን ሲዝል ፈገግታ ከፊት ሸረር ይላል ። ጭንቀት እና ሀዘን የልብ ዝለት ምንጮች ናቸው ። ሰው በጭንቅ ፣ በመከራ እንዲሁም በሀዘን ጥላ ወስጥ የታወከ እንደሆነ አባሪ ወዳጅ ይሻል ። እንዲህ ላለ ሰው አብሮት ጭንቁን የሚጋራ ፣ ሀዘኑን የሚያስተዛዝን አጽናጽ ወዳጅ ማግኘት ዳግመኛ የመኖር እድል የማግኘት አህል ሆኖ ሊቆጥር ይችላል ።እንዲህ ባለ ሁናቴ እያሳለፈ መዝሙረኛው በመዝሙሩ “ስድብ ልቤን ጐድቶታል፤ ተስፋዬም ተሟጦአል፤ አስተዛዛኝ ፈለግሁ፤ አላገኘሁምም፤ አጽናኝም ፈለግሁ፤ አንድም አልነበረም።”{መዝ 69፥20 (አ. መ.ት) ይለናል ። ልብ በስድብ ተጎድቶ ፤ ተስፋ ተሟጦ ፤ አስተዛዛኝ የሚሆን አጽናኝ ፈልጎ አለማግኘት እጅጉን መሪር ነው ። ልብን ከጎዳው መከራም ሆነ ስድብ በላይ ልብ የሚያዝነው የሚስተዛዝነው አጽናኝ ወዳጅ ማጣቱ ነው። አጽናኝ ፈልጎ አለማግነት ልብን በብቸኛንት ስሜት እንዲሰቃይ ያደርገዋል ። ለሰው ልጅ ከባዱና ሊቋቋመው የሚይችለው ነገር ቢኖር ብቸኝነት ነው ። ብቸኝነት ጭው ካለ በረሃ ይልቅ የከፋ ድምጽ አለው ። ብቸኝነት ሰሚ እና ተመልካች ማጣት ነው ። ብችነት ህመም ነው ። ፈውሱ አብሮ የሚያስተዛዝን አጽናኝ ማግኘት ነው። ለሰው ልጅ ከሞት የሚከፋው አጽናኝ ማጣት ነው ። አጽናኝ ማጣት አሳቢ ፣ ተሟጋች ፣ ወዳጅ ማጣት ነው። ሰው በድሉ ጊዜ ደስታውን ከሚጋሩለት ሰዎች ይልቅ ሀዘኑን የሚያስተዛዝኑለትን ይፈልጋል ። ድልና ደስታን ለመጋራት የቅርብ ሰው መሆን አይጠይቅም ፤ አላፊ አጋዳሚም ይህን ያደርጋልና። የሚያጽናና ሰው ለመሆን ግን የቅርብ ሰው መሆን ይጠይቃል ። ከመቼውም ጊዜ በላይ ሁሉም በየፊናው ለራሱ ነገር በሚሮጥበት ዓለም ዛሬም የቅርብ ሆኖ የሚያጽናናቸው ያጡ በብቸኛነት ስቃይ የሚታመሙ ሰዎች እልፍ ናቸው ። "መገኘት ከችሎታ ይበልጣል! ይላሉ። "ፈረንጆች። ለአንድ መንገድ ላይ የመኪና አደጋ ለደረሰበት ሰው ትልቁ ከሚያክመው ሀኪም በላይ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ አብሮት በመሆን ያስታመመው ሰው ነው ። ሰው በሀዘን ታምሞ በሚማቅቅበት ጊዜ አብሮ በመሆን አስተዛዛኝ የሚያጽናና ሰው መሆን ትልቅነት ነው ። ሀኪም ለጥቂት ጊዜ ህክምናውን ሊያደርግ ይችላል ። አስተማሚ ቁስሉ እስኪያሽረው አብሮት ለመሆን ጊዜ የሚሰጥ ነው ። ጊዜ እና ሁኔታ ሳይገድበው በየሠርኩ በማጽናናቱ ብዛት አብሮን በሚሆን እግዚአብሔር ባንታመን ብቸንነት ቀስቱን ገትሮ ፤ ነፍሳችንን በጨለማ ለመንደፍ፣ ፍላጻውን በአውታሩ ላይ በደገነብን ነበር?! ሰው ሊያጽናና ቢሻ የሚያጽናናውን ሰው ይመርጣል። ሰው ሳይመርጥ የታመነውን ነፍስ ሁሉ እንደመከራው በዛት በማጽናናቱ ደስ የሚስኝ እግዚአብሔር ምስጋና ይግባው። “እንደ ገና ከፀሓይ በታች የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ አስተዋልሁም፤ የተገፉትን ሰዎች እንባ ተመለከትሁ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ ኀይል በሚገፏቸው ሰዎች እጅ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም።” — መክብብ 4፥1 (አዲሱ መ.ት) ጠቢቡ ከጸሐይ በታች ያየው እና ያስተዋለው ግፍ የተገፉት ሰዎች እንባ መመልከቱና የሚያጽናናቸውን ማጣታቸው ነው ። በብዙ መገፋት የሚያልፉ ሰዎች አጽናኝ ማጠታቸው ትልቁ ግፍ ነው ። ዛሬም ባደጉም ሆነ ባላደጉ አገራት በመገፋት እና መጨቆን የሚያልፉ ፤ ስለምኑም የማያውቁ ንጹሓን ሰዎች እንባቸውን የሚመለከት ተመልክቶም የሚያጽናናቸው ሰዎች ይፈልጋሉ ። ኃይል በሚገፏቸው ሰዎች እጅ በመሆኑ ፍትሕ ይጎደላል ፤ፍረደ ገምድል ያይላል። ይህም ሀዘናቸውን ያበዛዋል ። ለግፉኣን መጽናናትን የሚቸረው የፍትሕ መስፍን ነው ። ከዚህ በተቃሪኒ በሀዘን ጊዜ ሊያጽናኑ የሚችሉ ሰዎች ቢኖሩ እንኳ ቃላቸው የሚያጽናና ሳይሆን እንደ ጭንቁር የሚበላ ሀዘነን የሚያብስ ነው ። ሊያስተዛዝኑ ሄደው ሀዘንን መሪር ሀዘን እንዲሆን የሚያደርጉ አስጨናቂ አስዛዛኞችም አሉ ። ጻድቁ ኢዮብ ውጭውም ሆነ ውስጡ በሀዘን በተሰበረበት የኅመም ወቅት ሊያጽናኑት የመጡትን ወዳጆቹን ““. እናንተ ሁላችሁ የምታስጨንቁ አጽናኞች ናችሁ።"(ኢዮ16፥2 አ.መ.ት) ይላቸዋል ። በሀዘን ላይ ሀዘን የሚጨምሩ አስጨኒቂ አጽናኞች አቅም አጥቶ ቁልቁል እየተመመ ያለን ሰው ከመደገፍ ይልቅ የሚገፍትሩ ናቸው ። የሚያስተዛዝኑ አጽናጾች ናቸው ዳሩ አስጨናቂ አጽናኞች ናቸው ። ቁስልን ከማከም ይልቅ ቁስሉን እየነካኩ የሚያሰቃዩ ባስ ሲልም እንጨት የሚሰዱ ጨካኞች ናቸው ። ከነዚህ ይጠብቀን ። የሚያጽናና ቃል እንደ መድኃኒት በሚፈለግበት ዘመን ሁሉ ከወንድም ይልቅ ከልብ ተጠጋግቶ የሚያጽናና የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ዛሬም አለ ። ለዚህ ነው ዘማሪው “የውስጤ ጭንቀት በበዛ መጠን፣ ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።” መዝ 94፥19 (አ.መ.ት) የሚለን ። ከሰው አጽናኝ ቢገኝ እንኳ ለልብ እንደመከራውና እንደጭንቁ መጠን ነፍስን ደስ የሚያሰኝ ማጽናናትን ሊያጽናና አይችልም ። አንዳንድ በመከራ እና በጭንቅ ጊዜ አብረው በመሆን የሚያጽናኑ ሰዎች ቢኖሩ እንኳ ይታክታቸዋል ። እንደሀዘናችን ፣ እንደመከራችን መጠን ማጽናናትን ከሰው ልናገኝ አንችልም። ሰው ሊደርስ የሚችልበት ልክ አለው ። ሰው መድረስ ከሚችልበት ልክ አልፎ መድረስ አይችልም። እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ነው ። የሚሳነው ነገር የለም። አንዳንድ ጊዜ ሰውን መድረስ ከሚችልበት ልክ በላይ እንጠበቃለን ። ያ ሳይሆንልን ይቀርና እንደገና ልባቸን ያዝናል ። ሰው መድረስ የሚችልበት ልክ አናሳ መሆኑን መገንዘብ ያሻል ። አለበለዚያ ደጋግመው ሰዎች ልባችንን እንዲጎዱት እንፈቅዳለን ። እግዚአብሔር የሚደርስበት ልክ የለውም ፤ እርሱን የሚረቀው ነገር የለም ፤ ከእርሱ ተሰውሮ የሚደበቅ ነገርም ከቶ አይኖርም ። ልብን ኩላሊትን የሚመረምረው እግዚአብሔር ሁሏችንን ያየዋል ፤ ያውቀዋልም ። የተዘጋ በር ከመግባት የማያግደው እግዚአብሔር በሀዘን ፣ በጭንቅ እና በመከራ ቅጠጥቃጤ ለወየበች ነፍስ እንደ መከራዋ መብዛት መጠን በማጽናናቱ ይደግፋታል ። እግዚአብሔር ረድኤቱን በማጽናናቱ ይገልጣልና ዘማሪው በሌላው መዝሙር “ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ረድተኸኛልና፤ አጽናንተኸኛልም።”— መዝ 86፥17 (አ.መ.ት) እያለ ይዘመራል ። አምላካችን የመጽናናት አምላክ ነውና የሰው ልጅ ባዘነ እና በተጨነቀ ጊዜ ሁሉ አጽናኝ ስለሚሻ ከፍቅር በሚመነጭ ማጽናናት እናጽናና ። መጽናናት በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር የሚያጽናና አምላክ ነውና ከሰው ይልቅ ወደእርሱ እንጠጋ ። ✍️ ጌታሁን አያኖ
Показать все...
Repost from Nolawi ኖላዊ
ተፈውሳችኋል “በመገረፉ ቍስል ተፈወሳችሁ ።” 1ጴጥ. 2፡25። ቍስል የመገረፍ ውጤት ነው ። ግርፊያ አደጋ አይደለም ፣ የታቀደ ቅጣት ነው ። ግርፊያ አንድ ጊዜ የሚከናወን አይደለም ፣ የሚደጋገም ልምጥ በትር ነው ። ግርፊያ ጠል መሬትን እንደሚያረሰርስ ሕመም ውስጥ ዘልቆ እንዲሰማ የሚያደርግ ነው ። ግርፊያ ዓላማው መግደል አይደለም ፣ መከራን ማራዘም ነው ። ግርፊያ ሥልጣን ካላቸው አካላት የሚታዘዝ ነው ። ግርፊያ ገራፊው ሲገርፍ ፣ አስገራፊው ደግሞ “ድገም” እያለ የሚያዝዝበት ነው ። ጌታና ሎሌ የተስማሙበት ነው ። ግርፊያ ላይ አራት ወገኖች ይታያሉ፡- የመጀመሪያው የፈረደው ባለሥልጣን ፤ ሁለተኛው አስፈጻሚው ወታደር ፣ ሦስተኛው ተመልካቹ ሕዝብ ፤ አራተኛው ተገራፊው ናቸው ። የፈረደው ሹም ካባ ለብሶ ያዝዛል ፣ ገራፊው እጁን ሰብስቦ ፣ ልብሱን አስቀምጦ ይገርፋል ፣ ሕዝቡ በንጹሑ ስቃይ እንዲፈራ ይደረጋል ። ሕዝብም የሰጡትን የሹም ዳቦ ለመግመጥ ዝግጁ ነውና “አንድ ጥፋት ባይገኝበት እንዲህ አይቀጣም ነበር” እያለ ላሸነፈ ድጋፉን ይሰጣል ። ተገራፊው አካልም ዕርቃኑን በአደባባይ ቆሞ ይገረፋል ። ተገራፊው አካል ንጹሕ ከሆነ በፍርድ መዛባት ያዝናል ፣ ለምን በማይሉ ፍርድ አስፈጻሚዎች ጭካኔ ልቡ ይሰበራል ። በሕዝቡ መነዳትም ይገረማል ። ግርፊያ ክብረ ነክ ነው ። ተገራፊው ልብሱን ይገፉታል ፣ ዕርቃኑን ይቆማል ። “ዓይን ይብላህ” ብለው ይጨክኑበታል ። በ “በለው” ድምፅ መንፈሱን ለማድቀቅ ያነሣሡበታል ፤ ግርፊያው ሲጀምር ቀዩ ገላ ይቀላል ፣ ጥቁሩ ይነጣል ። ሲቀጥል ቆዳው መሳሳት ፣ መሰንጠቅ ይጀምራል ። ከዚያ በኋላ ደም ይዘንባል ። ግርፊያ ሲቆም ቍስሉ ይፋፋማል ። ለሰዓታትና ለሳምንታት ጥዝጣዜው ያሰቃያል ። ልብሰ መንግሥቱን ተገፍፎ ስለ ተገረፈ ንጉሥ አልሰማን ይሆናል ። ብንሰማና ብናይም በዚህች ዓለም እጅግ እናዝንባታለን ። የራሳችን መጨረሻም ያሳዝነናል ። ጨካኝ ንጉሥ ሲዋረድ ብናይ ፡- አንተም ጨካኝ ነበርህ ጨካኝ አዘዘብህ ፣ እንደ ገና ዳቦ እሳት ነደደብህ ፤ እንል ይሆናል ። ክርስቶስ ግን ደግ ሳለ ተገረፈ ። የፈወሳቸው እጆች በጥፊ መቱት ፣ የሠራቸው ክንዶች ጅራፍ አወረዱበት ። በንጽሕናው ተቀጣ ። ሌሎችን በማዳኑ ቆሰለ ። ያ የሮማውያን አለንጋ ጫፉ ላይ ድቡልቡል ብረቶች አሉት ። የተሰባበሩ አጥንቶችም አዘርዝረዋል ። ብረቱ ሥጋውን ሲቀጠቅጥ ፣ ያዘረዘሩት ሹል አጥንቶች አካልን መቅደድ ይጀምራሉ ። ሲደጋገም ሥጋ እየተቦጨቀ ይነሣል ፣ ደም እንደ ጎርፍ ይወርዳል ። በጌታችን ላይ የሆነው ይህ ሁሉ ነው ። አካላቸው በበሽታ ፣ ልቡናቸው በኀዘን የታመመባቸው ብዙዎች ናቸው ። እነርሱን ሊፈውስ ክርስቶስ ተገረፈ ። ወላጆች ልጆቻቸውን የሚገርፉት “እንዳይለመድህ” እያሉ ነው ፣ ጌታ ክርስቶስም “እኛን መውደድ እንዳይለመድህ” ተብሎ ተገረፈ ። እርሱ ጅራፍ የማያስቆመው ፍቅር ነበረውና መውደድን አልተውም ብሎ ተሰቀለ ። ቢጠላን ዓለም እርስዋን መስሏልና በጅራፍ ትለቅቀው ነበር ። እንቢ ብሎ በማፍቀሩ ተሰቀለ ። በመገረፉ ቍስል ተፈወስን ። ቍስል ማንንም የመፈወስ አቅም የለውም ። ወዳጃችን ቢቆስልልን የበለጠ ያመናል ። የአምላክ ልጅ በመቍሰሉ ግን ተፈውሰናል ። የብዙዎች አምላካቸው የሚያቆስል ነው ፣ የእኛ አምላክ ግን ለፍቅር የቆሰለ ነው ። ብዙ በሽታዎች ተራብተውብናል ። የማያቃስት ሰው የለም ። የሥነ ልቡና ስብራት በዝቷል ። ሰው በሰው ተጎድቷል ። እናውቃለን በሚሉ ሰዎች በመጎዳታቸው ብዙዎች ልባቸው ቂም አርግዟል ። ሥጋንም ነፍስንም የሚፈውስ አንድ ቍስል አለ ። እርሱ የጌታችን የመገረፉ ቍስል ነው ። እናቶች ልጆቻቸው ሲታመሙ ይታመማሉ ፣ ግን ልጆቹ አይድኑም ። አንዳንድ ሰው ዓይኑ የታመመ ወገን ሲያይ አብሮ ይታመማል ፣ ጥርሱን ያመመው ሰው ሲያይ ታሞ ያድራል ። የሌላውን ስቃይ ይዘው የሚገቡ ሰዎች አሉ ። ታማሚውን ግን አያሳርፉትም ። እንደውም ሁለት በሽተኛ ይሆናሉ ። በመገረፉ ቍስል የፈወሰን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ነው ። በኑሮ በአገልግሎት የተገረፍን ፣ የቆሰልን ነን ። በመገረፉ ቍስል ግን ተፈውሰናል ። የተገረፈ ብቻ የተገረፈን ያድናል ። ቅምጥሎች ሳይሆኑ የቆሰለው እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ መልስ ይሆነናል ። እርሱ በየዕለቱ አይገረፍልንም ፤ አንድ ጊዜ በሆነው መገረፉ ፈውሳችንን በእምነት እንቀበል ። የፈውስ ዘመን ይሁንልን ! ዕለተ ብርሃን 9 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም.
Показать все...
..... 👣 እግረ መንገዴን ፸፪ 👣.... “እግሮቼ ተሰናከሉ ባልሁ ጊዜ፥ አቤቱ፥ ምሕረትህ ረዳኝ።” (መዝሙር 94¹⁸) እግር መቆሚያ ነው ። እግር የልብን አሳብ ተከትሎ የሚሄድ እና የሚያስሄድ ነው ። ያለ እግር ልብ ካሰበበት አይደርስም ። ያለ እግር ስለ መቆም ፣ ስለመሄድ ፣ ስለ መሮጥ አይታሰብም ። ልብ ያለ እግር የትም አይሄድም ። ልብ ካልሄደበት እግር አይቀድምም ። ሁሌም ልብ በቀደመበት እግር ይነጉዳል። እግር አሳብን ተከትሎ ግብር ይወልዳል ። አንድ ህጻን በወላጆቹ ማደጉ የሚረጋገጠው በእግሩ መቆም ሲጀምር እንደሆነ በማኅበረሰባችን የታወቀ ነው ። ወላጆችም የሚናፍቁት ያንን ጊዜ ነው ። ለዚህ ነው ልጃቸው ከመቀመጥ አልፎ መቆም ሲጀምር "ወፌ ቆመች ፥ አልወደቀች! "እያሉ የሚያጨበጭቡለት መራመድ እና መሮጥ ከመቆም ኋላ የሚመጡ ነገሮች ስለሆኑ ነው ። ልጆችም ይህን እየተባሉ ለጥቂት ቆም ይሉና የመወደቅ አዝማማያ ሲያሳዩ ወላጆች ደገፍ አደርገው ይይዟቸዋል ። ለራሳችን ቆምን እያልን ሌሎችም "ወፌ ቆመች... "ባሉን ሰዓት ለመውደቅ መንገዳገድን የሚያስረሳን ደገፍ አደርጎ የሚይዘን የእግዚአብሔር እጅ ነው ። ሁለተኛው መቆም ግን እንደመጀመሪያው ያለ አይደለም ። ይኸኛው መቆሞ ራስን እንደመቻል ይታሰባል ። ይህን ጊዜ በሁሉም ነገር ብቁ ሆኖ መቆምን የመፈለግ ስሜት ያይላል ። አዎ ራስን በማንኛቸውም ነገር ከቤተሰብ ጥገኝነት ነጻ ለማውጣት የሚደረገውን ጥረት ያሳየናል ። በዚህ ጊዜ ከቤተሰው እጅ ምንም ርዳታ ከመቀበል አልፎ ቤተሰውን ወደመርዳት ደረጃ የደረሰ እንደሆን ለሁለተኛ ጊዜ "ወፌ ቆመች....!"ይባላል ። ዳሩ ብረት ለበስ አይደለምና "ቆመ "በታበለበት ማግስት የቆመበት እግር ያዳልጠውና ለመቆም መንገዳገድ ይጀምራል። ከመጀመሪያው በተመሳሳይ ደግፎ የሚይዝ እጅ መሻቱ አይቀሬ ነው ። ሰው ምናልባት ብርቱ ሆኖ ከወላጆችም ሆነ ከአሳዳጊዎቹ ጥገኝነት ወይም ርዳታ ነጻ ሊወጣ ይችል ይሆናል። ዳሩ ከእግዚአብሔር ርዳታ ውጩ መሆን አይችልም ። እያደግን ስንሄድ የወላጅ ደጋፊ የነበረ እጅ መጦርን በመሻት እየደከመ ይሄዳል ። ትናንት ደጋፊ የነበሩ እጆች ዛሬ ደጋፊ ይሻሉ። የሰው ልጅ ዛሬ ብርቱ ሊሆን ይችል ይሆናል ። ነገ የሚያበረታውን የሚሻ ድኩም መሆኑ ግን አይካድም ። ብርቱ ተብሎ የቆመ የመሰለው እግር ጊዜ ጠብቆ መሰናከሉ አይቀርምና ። ዘማሪው" እግሮቼ ተሰናከሉ ባልሁ ጊዜ፥ አቤቱ፥ ምሕረትህ ረዳኝ።” (መዝሙር 94¹⁸) ይለናል ። እግሮች የሚሰናከሉበት ፣ ጉልበት የሚከዳበት ጊዜ ይመጣል ያንጊዜ ደግፎ የሚይዘን የሚረዳን እጅ የእግዚአብሔር ምሕረት መሆኑን ማስታወስ እጅግ መታደል ነው ። ያለ እግዚአብሔር ረዳት እና ደጋፊ እጅ ከመንገዳገድ እና ከመሰናከል መትረፍ አይቻልም ። መሰናከል ማለት ለመወደቅ መንተፋተፍ ነው ። ከመሰናከል ኋላ ውድቀት ይጠበቃል ። ብዙ መሰናከሎች ውስጥ አልፈን ያለመውደቃችን ምክንያቱ ቢፈተሽ የእግዚአብሔር ደጋፊ እጅ ነው ። አዎ የእግዚአብሔር ምሕረት ነው ። እግርን ከእግዚአብሔር ቤት የሚያርቁ ፥ ከጸድቅ ጉዳና የሚያሸሹ መሰናከሎች ባየለበት ዓለም ዛሬም በቤቱ ለመኖራችን ከምሕረቱ በቀር ምን የምናቀርበው ምክንያት አለን?! እልፍ መሰናከሎች ሊጥሉን እንደተሰናዱ ሲገባን ተስፋ ቆርጠን ውድቀታችንን እየጠበቅን ባለንበት ሰዓት ከውድቀት የሚታደገን ደጋፊ እጅ የሆነው የእግዚአብሔር ምሕረት ነውና ክብር ለዘላለም ለእርሱ ይሁን ። "እግሮቼ ተሰናከሉ ባልሁ ጊዜ፥ አቤቱ፥ ምሕረትህ ረዳኝ።” (መዝሙር 94¹⁸) ✍️ ጌታሁን አያኖ መስከረም 12/01/2016
Показать все...
2👍 1
ቢዚ - ቢዚ፤ ለሁሉ ጊዜ አለው ወይስ አለን? በንጉሤ ቡልቻ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ውጪ አገር የሚሄድ ጓደኛውን ለመሸኘት ከተሰበሰቡት መካከል የሽኝት ፕሮግራሙን ማጠቃለያ ጸሎት የሚጸልየው ሰው እንዲህ ብሎ ጸልዮአል አሉ፡፡ “ጌታ ሆይ ይህ ወንድማችን በሚሄድበት አገር ቢዚ ከሚባል ጋኔን እንድትጠብቀው እለምንሃለሁ፡፡” “ቢዚ” የሚባል ጋኔን መኖር አለመኖሩን መመራመራችንን ትተን ባተሌነት (ቢዚነት) የውጪ አገር አበሳ መሆኑ ቀርቶ ውስጥ አገርም የሚያስጨንቀን ጉዳይ እንደ ሆነ እንቀበል፡፡ በቀጠሮ ብዛት፣ በእንቅስቃሴ ብዛት፣ በጉዳይ ብዛት፣ በሥራ ብዛት፣ በሥራ ውጣ ውረድ፣ በማኅበራዊ ግንኙነት ብዛት፣ በሽቅብ ቁልቁል ብዛት፣ የአካላችን አውታር እስኪነዝሩ ተወጣጥረናል፤ ነፍሳችን ብን ትን እስክትል እንማስናለን፡፡ ትንፋሽ አጥሮን ስናለከልክ የሚያየን የሌላ ዓለም ፍጡር ቢኖር “ምን ሥራሥር በጥብጠው ቢጠጡ ነው እንዲህ የሚያዛብታቸው፣ የሚያሽከረክራቸው” ብሎ በጠየቀ፡፡ ለመሆኑ ምን እንዲህ ያባትለናል? የየዕለቱ ውጣ ውረድ ነዋ! የጉረሮ መድፈን ጥሪ፣ የማኅበረ ሰብ ቦታችንን የማስጠበቅ ጥሪ፣ የነገ ምን ይሆናል ጭንቀት፣ ሌሎችም ይህን የመሳሰሉ ሁሉ፡፡ የሰው ልጅ የሚሠራውንና የሚውልበትን ሁነኛ ጉዳይ አግኝቶ በሥራ መጠመዱ በረከት እንጂ ርግማን አይደለም፡፡ ጊዜ እንደ ጅረት በሚንፎለፎልበት ልማዱ ቢነጉድ የሥራ ቦይ እየቀደዱ ጥቅም ላይ የሚያውሉት የታደሉ ናቸው “ዘመኑን ዋጁ” በሚለው ምክር አብነት፡፡ እንዲህ የሚያደርጉ በሥራው ከሚገኘው ጥቃሞት በላይ ስብእናቸው ይለማል፣ ርካታና ደስታም ያገኛሉ፡፡ አሁን ያነሣነው “ጋኔኑ ቢዚነት” ግን ከሚያለማው የሚያጠፋው የበለጠ፣ ከሚያረካው የሚያቅበዘብዘው የበዛ፣ ደስታችንን ቦጥቡጦ የሚበላ መልቲ ነው፡፡ ሮጠን ሮጠን ልባችን ሊፈነዳ ሲል ስንቆም የትም እንዳልደረስን ስንረዳ፣ ከበሬታ ፍለጋ ብዙ የአንቱታ ካባ ደርበን ድንገት ካባው የወደቀ ቀን የነፍሳችን ክሳት ሲጋለጥ የዚህ ዐይነት ቢዚነት ፍሬ ይታወቅ ይሆናል፡፡ መድኃኒታችን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት" ተወስኖ ወደዚህ ምድር ስለመጣ ልክ እንደ እኛ በቀን ውስጥ 24 ሰዓት ብቻ ነበረው፡፡ ያደረገውን ሁሉ ያደረገው በዚሁ በባለ 24 ሰዓት ቀን ነበር፡፡ የምድር እድሜው ጥቂት ነበረ፤ የይፋ አገልግሎቱ ደግሞ ከሦስት ዓመታት እጅግም ያልዘለለ አጭር ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ወደ አባቱ መሄጃው ጊዜ ሲደርስ የጸለየው ጸሎት የተዋከበ፣ የተጨነቀ አልነበረም፤ “ምነው አንድ ዐሥር ዓመት ብትጨምርልኝና የጀመርሁትን በጨረስሁ” የሚል የጊዜ ልመና አልነበረበትም፡፡ “የሰጠኸኝን ሥራ በምድርላይ ፈጽሜ አከበርሁህ” የሚል ደልዳላ ዘገባ ነበር፡፡ እንዴት እንደዚህ ስክን ያለ ሕይወትና አገልግሎት አገኘ? እጅግ ብዙ የእርሱን ርዳታ የሚሹ ፍጡራን ባሉበት ዓለም ውስጥ በቀኝና በግራ ሊያዋክቡት የሚችሉ አስባታሊ ተግባራት በነበሩበት ሁኔታ እንደምን ርጋታ አገኘ? መጽሐፉ ላይ እንደ ተጠቆምን ከሆነ መልሱ ውስብስብ አይደለም፡፡ ጌታችን ዋናውን ጉዳይ ከአስቸኳዩ የለየ፣ የሕይወት ጥሪውን አሳምሮ ያወቀ፣ ቆፍጣና የዓላማ ሰው ስለነበረ ነው፡፡ “የሰጠኸኝን ሥራ” አለ እንጂ በሜዳ ያለውን ተግባር ሁሉ አላለም፤ ወይም ዘመድ ወዳጅ የጠየቀኝን ኀላፊነት ሁሉ ወይም የተገኘውን ሥራ ሁሉ ፈጸምሁ አላለም፡፡ የአባቱ ፈቃድ የሕይወት ጥሪው ነበረና ያንኑ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ፈጸመው፡፡ በጸሎቱ ዘገባ በዝርዝር እንደሰፈረው እያንዳንዱ ቅንጣት ተግባር ከነውጤቱ እንደተከናወነ ርግጠኛ ነበር፡፡ በምድር አገልግሎቱ የነካቸው ሰዎች ሁሉ ሕይወታቸው በጥልቅ ተነክቷል፤ የይድረስ ይድረስ በሽታ ሳይጠናወተው የሚሠራውን ሁሉ ወደ ተገቢው ፍጻሜ አደረሰ፡፡ በዓላማ ጽናት፣ በርግጠኛ ርምጃ፣ በታላቅ ማስተዋል ተራመደ፡፡ ስለዚህ ሞቱ የጸጸት አልነበረም የድልና የስኬት እንጂ፡፡ ሕይወቱ አልተጨናገፈም፤ ውጥኑ ባጭር አልቀረም፤ የሰማይ አባቱን ያስከበረ ወርቃማ ፍጻሜ አገኘ፡፡ የሕይወትን ዋና ጥሪ ለመፈጸም ጊዜን በጥበቡ የመጠቀም ጉልህ አርኣያ ሆነ፡፡ ስሙ ይክበር፡፡ ቻርልስ ሁሜል የተባለ አስተዋይ ጸሐፊ “The Tyranny of the Urgent” ብሎ የጻፈውና ቁምላቸው ፈንታሁን የተረጎመው አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፡፡ "ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፣ያልተጠናቀቁ ሥራዎች፣ ምላሽ ያልተሰጣቸው ደብዳቤዎች፣ ያልተጎበኙ ወዳጆች ያልተጻፉ መጣጥፎችና ያልተነበቡ መጻሕፍት ይታዩናል፡፡ በሥራ እየባተልን ቢሆንም የምናገኝበት ደስታ እያደር የመነመነ ነው፡፡ ሆኖም ችግር የሚፈጥርብን ተግቶ መሥራት ሳይሆን ጥርጣሬና መወላወል ናቸው፡፡ ትልቁ አደጋ ለአስቸኳዩ ጉዳይ መላ ለመፈለግ ስንጣደፍ ዋነኛውን ጉዳይ መዘንጋቱ ነው፡፡ ችግሩ ደግሞ ዋነኛው ጉዳይ ዛሬ ወይም በዚህ ሳምንት ይሠራ የሚያሰኝ አጣዳፊነት የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ፈጣን ርምጃ የሚጠይቁን አጣዳፊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በጊዜው በጣም አስፈላጊና ወደ ጎን የማይባሉ ስለሚመስሉን ጉልበታችንን ይመጡታል፡፡ ክርስቲያን ፋታ ወስዶ መንፈሳዊ ሁኔታውን በመፈተሸ፣ የሥራ ኀላፊነት ለመቀበል እንዳይችል ሆኖ በሥራ ከተጠመደ፣ ለአስቸኳዩ ጉዳይ ምላሽ ለመስጠት ሎሌ ያድራል፡፡ በራሱና በሌሎች ዐይን ዋጋ የሚሰጠው የሚመስል ነገር፣ ሌት ተቀን ሠርቶ ማከናወን ቢችልም፣ እግዚአብሔር ያቀደለትን ሥራ ግን ሳያጠናቅቅ ይቀራል" እንግዲያው በባርነት ቀፍድዶ የያዘን “አስቸኳይ” የሚባል አምባ ገነን የፍዳችን አንዱ ዋና ምክንያት መሆኑ ነው፡፡ አስቸኳዩን ከዋናው ጉዳይ እንዴት እንለያለን? የሚለው ጥያቄ ብርቱ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ መልስ ካገኘን የፍልሚያው እምብርት ታወቀ ማለት ነው፡፡ ይረዳን እንደ ሆነ እስቲ መላ ልምታ፡፡ በጎ ትብብራችሁን ስጡኝና ይህን ጥያቄ በጥሞና መልሱልኝ “ለመሞት አንድ ወር ቀርቶሃል የምትሠራውን ሁሉ በነዚህ ሠላሳ ቀናት ጨርስ” ብትባሉ ቀኖቹንና ሌሊቶቹን ምን ታደርጉባቸው ነበር? ብጣሽ ወረቀት አውጡና የምታደርጓቸውን ነገሮች በቅደም ተከተል ጻፉዋቸው፡፡ ልምምዱ ምናልባት ዋና የምትሉትን ዋና ካልሆኑት ለመለየት ይረዳችሁ ይሆናል፡፡ የሕይወታችሁ ዋና ዓላማ ምንድን ነው? የደም ግፊታችሁን እየጨመረ፣ ናላችሁን እያዞረ፣ ተንፋሽ አሳጥቶ የሚያስሮጣችሁን ነገር ሁሉ ከዚህ ዋና ዓላማ አንጻር ፈትሹት፡፡ ወደ ዓላማው የሚፈስ ነባር ወንዝ ነው ወይስ በየመስኩ የፈነዳ መድረሻው ያልታወቀ የውሃ ምንጭ? የክርስቶስ ተከታይ ዋና ዓላማ ምንድን ነው የተባለ እንደሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ ባጭሩና በግልጽ ከተናገረው ከዚህ ጥቅስ የተሻለ መግለጫ አላገኘሁም፡፡ “አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፣ እንግዲያውስ ሁሉ ሞቱ በሕይወትም ያሉትም ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ፡፡” 2ኛ ዎሮ 5፡13 የክርስቶስ ተከታይ ግለ ሰብም ሆነ ማኅበረ ሰብ የሕይወት ዓላማው ንድፍ ተሠርቶለት አልቋል፡፡ የምንሠራው ሁሉ የምናስበው ሁሉ የዚህ ዋና ንድፍ (Master Plan) አካል ካልሆነ ሕገ ወጥ ግንባታ ነው፤ ለፍቶ መና ነው፡፡ እያንዳንዱዋ የእንቅስቃሴ ቅንጣት መፈተሸ ዋጋዋም መተመን አለባት፡፡ መሮጥ ብቻውን ዋጋ ቢስ ነው፤ ሕይወት መሮጫ ግብ ይሻል፤ ግቡም በአንጻሩ የመገስገሻ መስመር አለው፡፡ ሐዋርያው ትንፋሽ ሊሰበስብ ሲቃረብ ሩጫ ጨረስኩ ሳይሆን ‹‹ሩጫውን ጨረስኩ›› ማለቱ የተሰመረ መንገድ፣ የሚደረስበት ግብ መኖሩን ሲያመለክተን ነው፡፡ ይቀጥላል
Показать все...
የዐዲስ ዓመት መልእክት ንጉሤ ቡልቻ በተናጋ ዓለም ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡ በአሸዋ ክምር ላይ እንደሚራመድ ሰው የምንረግጠው ሁሉ እየከዳን ርምጃችን ሁሉ ያረገርጋል፡፡ ፓለቲካው፣ ኢኮኖሚው፣ ማኅበራዊ ሕይወቱ፣ ጤናው ወዘተርፈ በዕንቅብ ላይ እንደሚበጠር እህል ሲወድቅ ሲነሳ ሲርገበገብ የኛንም ነፍስ አብሮ እየናጠ ትንፋሻችን ቁርጥ ቁርጥ ይላል፡፡ የማይናወጥ አምላክ ግን አለ፤ የሚሰራውን አጥርቶ የሚያውቅ ወደ ግቡም የሚገሰግስ የሠራዊት ጌታ ግን አለ፣ እንደኛ ዘመን ያሉ ሌሎች ብዙ ዘመናት ያሳለፈ የታሪክ ባለቤት የዘመናት ንጉሥ ልዑል እግዚአብሔር አለ፡፡ በእርሱ ባሕርይ ውስጥ መናጋት፣ ሥፍራ መልቀቅ፣ መዛነቅ፣ መዛነፍ መለወጥ መለዋወጥ ከቶ የለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ለይ በነበረበት ጊዜ የኖረበት ሥፍራ የተረጋጋ አልነበረም፡፡ በሕዝባዊ ዐመፅ የተናጠ፣ በኢኮኖሚ ድቀት የተጨነቀ፣ በሞራል ዝቅጠት የተበላሸ፣ በኃይማኖት ግብዝነት የቆሸሸ መሬት ላይ ነበር የተመላለሰው እና በዚሁ እሾሃማ ምድር ላይ ሲኖር የሕፃናትን ፀጉር ዳበሰ የአልጋ ቁራኞችን ፈወሰ ለድሆች የምስራች አወጀ ለእውነት ትምህርትና ምግባር ሲል ከግብዞች ጋር ተፋለመ የሰው ልጅችን ልቅሶና ደስታ ተካፈለ ለአባቱ የመዓዛ ሽታ ፣ ለእኛ ቤዛ ሆኖ ራሱን ሰጠ የዘመኑ ክፋት ከፍቅርና ከእውነት፣ ከፅድቅና ከምሕረት አላፈናቀለውም፡፡ እኛ አሁን የምንኖረው እርሱ በረገጠው ምድር ላይ ነው፡፡ እና ይህን ዐዲስ ዓመት ስንቀበል እንድናደርጋቸው ላሳስብ የፈለግሁትን በአጭሩ ላቅርብ፡፡ መጀመሪያ ….. ልቡናችን መስመር እንዳይስት፣ እንዳናብድ ጥንቃቄ እናድርግ፡፡ ከሚዛናዊ አስተሳሰብ የሚያስወጣ፣ የሚያሰክር የሚያስቀባዥር ለፍላፊና ራቁት ዟሪ ወፈፍተኛ የሚያደርግ ወቅት ስለሆነ ልባችንን/መንፈሳችንን እንጠብቅ፡፡ «መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ» ስለተባለ በነገር፣ በአሉባልታ፣ በአምባጓሮ በጭንቀት፣ በግራ ተጋብቶት በመሳሰለው ሁሉ ተጠላልፈን ከእውነተኛ ክርስቶሳዊ ልቡና እንዳንወጣ እንጠንቀቅ፣ ደግሞም «ቃሉ በሙላት ይኑርባችሁ›› ተብለናልና፣ ባዶ አእምሮና መንፈስ ይዘን ገበያ አንዙር፡፡ ሁለተኛ….. በወንጌል ቃል እንጽና፤ በትምህርቱም በብሥራቱም :: ንፁሑን የክርስቶስ ወንጌል የሚበራርዙ፣ ግርዶሽ የሚያደርጉበት የሚያጨልሙት ክፉ ትምህርቶች በዙሪያችን እንዳሉ ግልፅ ነው፡፡ የእምነት ቃል ትምህርት የተባለ፣ የብልፅግና ወንጌል የተባለ ብዙ አረም መልካሙን የወንጌል እርሻ እየወረረ ፍሬውን አንቆ እንዳያጠፋ ብርቱ ተጋድሎ የሚጠይቅ ዘመን ነው፡፡ የክርስቶስን ልዩትነት (uniqueness) የቅዱስ ቃሉን የማይገሠሥ ሥልጣን የመስቀሉን የድነት ዋስትና ወዘተርፈ በግልጥነት ማስተንተን ይገባል፡፡ ሐዋርያቱ በታላቅ ቅንዓት ፣ በፅኑ የእምነት ገድል ያስተላለፉልንን የእውነት ቃል ልክ እንደነሱ የክርስቶስ በጎ ወታደሮች ሆነን ማሻገር ጥሪያችን ነው፡፡ ለወንጌሉ ስንመክት ወንጌሉን ማወጃችንንም አንርሳ፡፡ ሰው የሚድነው ሰምቶ ሲያምን ነውና፡፡ ሦስተኛ …. በጎ እያደረግን እንቀጥል:: ዓመታትን እያፈራረቀ ለአዳም ልጅ ሁሉ ቸርነቱን እያሳየ በጭንቅ ዘመንም መልካም እያደረገ ምሳሌ የሆነንን ጌታ እንከተል፡፡ ጨለማ ለወረሳት አንዲት ነፍስ ፈገግታችንን አንንፈግ፤ የታጠፈ አንጀት እናቃና ፤ የነፍሱን ሸክም የሚያራግፍበት አጥቶ የሚባዝነውን ሰው እናዳምጥ፤ በክፉ ዘመን መልካም እየሰራን በድቅድቅ ጨለማ ብርሃን እንፈንጥቅ፡፡ በመጨረሻ…. የዘመናት ንጉሥ በሆነው ልዑል አምላክ እንታመን ፡፡ «ቀኑ የአንተ ነው፣ ሌሊቱም የአንተ ነው፡፡» የተባለለት እግዚአብሔር ሁሉን በእጆቹ ይዟል፡፡ የታሪክን መዘውር ያሽከረክራል፡፡ «አቤቱ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፣ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው፡፡ እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ …….. አንተ ግን ያው አንተ ነህ፣ ዓመቶችህም ከቶ አይልቁም፣ የባሪያዎችህም ልጆች ይኖራሉ፣ ዘራቸውም ለዘላለም ትፀናለች፡፡›› መዝ.102፣25-28 መልካም ዐዲስ ዓመት ይሁንልን!
Показать все...
Выберите другой тариф

Ваш текущий тарифный план позволяет посмотреть аналитику только 5 каналов. Чтобы получить больше, выберите другой план.