ru
Feedback
ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

ፍኖተ ብርሃን ዘ ቅድስት አርሴማ

Открыть в Telegram

ይህ በግራር ደ/አባይ ቅድስት አርሴማ ቤ/ክ ፍኖተ ብርሀን ሰንበት ት/ቤት የተዘጋጀ :- ለምዕመናን : ትምህርትን , ዝማሬዎችን , ኪናዊ ዝግጅቶችን, የቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ዜናዎችንና በአላትን(ንግስ, ልዮ ልዮ የሰርክ ጉባኤያት ..ወዘተ) በምን መልኩ እንደተከበሩ ለምዕመናን ተዘጋጅቶ የሚተላለፍበት ገፅ ነው።

Больше
610
Подписчики
-124 часа
-37 дней
-1130 дней
Архив постов
❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤               ❤ #ሐምሌ ፭ (5) ቀን። ❤ እንኳን #ለብርሃናተ_ዓለም_ለቅዱስ_ጴጥሮስ፣ #ቅዱስ_ጳውሎስ_በጫካኙ ንጉሥ በኔሮን ቄሳር እጅ ሰማትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው መታሰቢያ ዓመታዊ በዓል፣ #ለመላእክት_አለቃ_ለቅዱስ_ሳቁኤል_ለበዓሉ መታሰቢያ፣ #ለሰባ_ሁለቱ_አርድእት_ለመታሰቢያቸው_በዓላቸው፣ #ለአባታችን_ለአቡነ_ገብረ_መንፈስ_ቅዱስ_ዓመታዊ የመታሰቢያ በዓላቸውና ለሐዋርያት (ለሰኔ) ፆም ፍቺ እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን። በተጨማሪ፡በዚች ከሚታሰቡ፦ በጋዛ ሰማዕት ከሆነ #ከይስሐቅና_ከደብረ_ዓሣ_ጻድቃንም ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                                                            ✝ ✝ ✝ ❤ #የሐዋርያት_አለቃ_ቅዱስ_ጴጥሮስ፦ ይህም ጴጥሮስ ከቤተ ሳይዳ የነበረ ዓሣ አጥማጅም ነበረ ጌታችንም ከተጠመቀባት ዕለት ማግስት አግኝቶ መረጠው ከእርሱ አስቀድሞም ወንድሙ እንድርያስን አግኝቶ መረጠው። መድኀኒታችንንም እስከ መከራው ጊዜ ሲያገለግለው ኖሩ ፍጹም ሃይማኖት ለጌታውም ቅንዓትና ፍቅር ነበረው። ስለዚህም በሐዋርያት ሁሉ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው። ❤ ጌታችን ም ሰዎች ማን እንደሆነ ማንም እንደሚሉት ስለ ራሱ በጠየቃቸው ጊዜ ሌሎች "ኤርምያስ ይሉሃል ወይም ኤልያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል" አሉት። ቅዱስ ጴጥሮስ ግን "የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህ" አለ። ጌታችንም "የሃይማኖት አለት የቤተ ክርስቲያንም መሠረት ነህ" ብሎ ብፅዕና ሰጠው "የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻ ቁልፍ ሰጥቼሃለሁ" አለው። ❤ አጽናኝ የሆነ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ ከተበቀለ በኋላ ተናገሪዎች ከሆኑ በዚህ ዓለም ተኲላዎች መካከል ገባ በውስጣቸውም ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰበከ ቊጥር የሌላቸው ብዙዎች አሕዛብንም መልሶ የዋሆች ምእመናን አደረጋቸው። ጌታችንም የማይቈጠሩ ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶችን በእጆቹ አደረገ ጥቅም ያላቸው ሦስት መልእክቶችንም ጽፎ ለምእመናን ላከቸው። ለማርቆስም ወንጌሉን ተርጒሞ አጽፎታል። ❤ ከዚህም በኋላ ወደ ሮሜ ከተማ ገባ የከተማው መኳንንት ወደሚሰበሰቡበት ወደታላቁ የጨዋታ ቦታም ሔዶ በታላቅ ድምፅ እንዲህ ብሎ ተናገረ "የሚራሩ ብፁዓን ናቸው ለርሳቸውም ይራሩላቸዋልና" የዚህንም ተከታታይ ቃሎች ተናገረ። በዚያም ከዚያ የነበሩ አራት የደንጊያ ምሰሶዎችም በሚያስፈራ ድምፅ "አሜን" አሉ የተሰበሰቡትም ይህን ቃል በሰሙ ጊዜ ደነገጡ። ከሰባ ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያደረበት አንድ ሰው ነበረ ከእነዚያ ድንጋዮች ቃልን ስለ ሰማ ያን ጊዜ ጋኔኑ ጣለው ከእርሱም ወጥቶ ሔደ። መኳንንቱም ፈርተዋልና ስለዚህ ነገር እያደነቁ ወደ ቤታቸው ገቡ። ❤ ከከተማ መኳንንቶችም ቀውስጦስ የሚባል አንዱ ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ ስሟ አክሮስያ የምትባል ሚስቱ ዓለምን ስለ መተው ለድኆችም ስመራራትና የመሳሰለውን ቃል ቅዱስ ጴጥሮስ እንዴት እንዳስተማረ ነገራት። እርሷም በሰማች ጊዜ በልቧ ነቃታ "ይህ ገገር መልካምና ድንቅ ነው" አለች። ቅዱስ ጴጥሮስ ያስተማረውንም ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በአንድነት ተስማሙ ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በአንድነት ተስማሙ ከዚህም በኋላ ገንዘባቸውን ሁሉ ለድኆች ሰጡ ከዕለት ራት በቀር ምንም አላስቀሩም። ❤ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ንጉሡ ስለ መንግሥት ሥራ ከርሱ ጋራ ለመማከር በቶሎ እንዲደርስ ወደርሱ መልክትን ላከ። ቀውስጦስም ይህ በሰማ ጊዜ ገንዘብ ስላልነበረው ፈርቶ ደነገጠ ተጨነቀም። ምክንያትም አመካኝቶ ይሰወር ዘንድ ከሚስቱ ጋራ ተማከረ። እርሷ ግን "ምክንያት አታድር ነገር ግን ወደ ንጉሥ ሒድ የቅዱስ ጴጥሮስ አምላክን ጎዳናህን ያቅናልህ" አለች። እርሱም ነገሯን ተቀብሎ ወደ ንጉሡ ሔደ በመንገድም ከእግዚአብሔር የታዘዘ ብዙ በረከትን አገኘ ወደ ንጉሡም ደረሰ ንጉም በደስታና በክብር ተቀበለው። ❤ ከሦስት ዓመት በኋላም ወደ ቤቱ በተመለሰ ጊዜ ሁለቱ ልጆቹ የተመረዘ ውሃ ጠጥተው እነሆ ሞተው ነበር ሚስቱም ለእርሱ መንገርን ፈራች ብዙ ምሳሌዎችን ከመሰለችለት በኋላ ነገረችው። በሰማ ጊዜ እጅግ አዝኖ አለቀሰ። ሚስቱም እንዲህ አለችው "ጌታዬ ሆይ ልባችን የሚጽናናበትን እርሱ ያደርግልናል የቅዱስ ጴጥሮስ ፈጣሪ እግዚአብሔርን እንለምነው"። ሊጸልዩም በጀመሩ ጊዜ ቀወስጦስና አክሮስያ "የደቀ መዝሙሬ የጴጥሮስ ቃል ስለሰማችሁና ስለተቀበላችሁት ስለዚህ ልጆቻችሁን በሕይወታቸው እሰጣቸዋለሁ" የሚል ቃልን ከሰማይ ሰሙ ያን ጊዜም ልጆቻቸው ድነው ተነሱ ቀውስጦስና ሚስቱም ደስ አላቸው የተመሰገነ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት። ❤ እሊህም ከሞት የተነሱ ልጆች ለቅዱስ ጴጥሮስ ቀደ መዝሙሮቹ ሆኑ የአንዱ ስሙ ቀሌምንጦስ ነው እርሱም ቅዱስ ጴጥሮስ ያየውንና ጌታች በሥጋ ወደ ሰማይ በሚያርግ ጊዜ የገለጠለትን ምስጢር ሁሉ የነገረው ነው ሰዎች ሊያዪአቸው የማይገባቸውን መጻሕፍትን አስረከበው። ይህንም ቀሌምጦስን ሊቀ ከጵጵስና ወንድሙንም ዲቁና ሾማቸው። ❤ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ቅዱስ ጴጥሮስ አምላክን የወለደች የንጽሕት ድንግል እመቤታችን ማርያም ክብራን በምሳሌ አየ። በቀስት አምሳል ደመናን አይቷልና በላዪዋም የብርሃን ድንኳን ነበር በድንኳን ውስጥም አምላክን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያም ተቀምጣለች። በእጆቻቸው ውስጥ የነበልባል ጦሮችና ሰይፈችን ያያዙ መላክትና የመላእክት አለቆች በዙሪያዋ ነበር። እንዲህም እያሉ ያመሰግኗት ነበር። "ከእርሷ የደኅንነት ፍሬ የተገኘ የሰመረች የወይን ተክል አንቺ ነሽ ማኅፀንስሽም የእግዚአብሔር በግ የተሸከመ ንጽሕት አዳራሽ አንቺ ነሽ"። ❤ ሁለተኛም እንዲህ ይሏት ነበር " የብርሃን እናቱ ሆይ የምሕረት መገኛ ሆይ ደስ ይበልሽ የአማልክት አምላክ የፍጥረት ሁሉ ጌታ የሆነ የመድኅን ዙፋን ሆይ ደስ ይበልሽ ክብርና ምስጋናን የተመላሽ የፍጥረት ሁሉ እመቤት ደስ ይበልሽ"። መላእክት ምስጋናዋንና ሰላምታዋን ባደረሱ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእርስዋ ተገልጦ ከእርሷ በቀር ማንም ሊያውቀው የማይቻል ነገርን ነገራት ወዲያውኑም ምድር ተናገወች ሊነገር የማይቻል ምሥጢራትንም ገለጠላት። ❤ ከዚህም በኋላ መድኀኒታችን ለአገሩ ሁሉ ቅዱስ ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ ቅዱስ ጴሮስን አዘዘው ቅዱስ ጴጥሮስም መጥቶ ሔደ ኢዮጴም ወደምትባል የባሕር ዳርቻና ልድያ ወደምትባል አገር ደረሰ። በአንዲት ዕለትም በኢዮጴ ሳለ ብርሕት ደመና ዞረችው። እነሆም ሰፊ መጋረጃ ወደርሱ ወረደች በውስጧም የእንስሳት የምድረ በዳ አውሬዎችና የሰማይ አዕዋፍ አምሳል ነበር። "ጴጥሮስ ሆይ ተነሥና አርደህ ብላ" የሚል ቃልም ከሰማይ ጠራው። ቅዱስ ጴጥሮስም "አቤቱ አይገባኝም እርኲስ ነገር አልበላም ወደ አፌም ከቶ አልገባም" አለ። ያም ቃል ዳግመኛ ጠራውና እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገው አንተ ርኲስ ነው አትበል" አለው ያም ቃል ሦስት ጊዜ መላልሶ እንዲህ ነገረው። በየንግግሩም ወደ እሪያዎች፣ ወደ አራዊትና ወደ አእዎፍ ሥዕሎች ጣት ያመለክተው ነበር። ❤ ከዚህም በኋላ ያቺ መጋረጃ ወደ ሰማይ ተመለሰች። ቅዱስ ጴጥሮስም ስለ አየው ራእይ አደነቀ ይህም ራእይ ወደ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር የሚመለሱ አሕዛብን ስለመቀበል እንደሆነ አስተዋለ። ለወንድሞቹ ሐዋርያትም አሕዛብ የእግዚአብሔር ቃል እንደተቀበሉ የመቶ አለቃ ቆርኔሎስንም ከወገኖቹ ጋር እንዳጠመቀው ነገራቸው።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤             ❤ #ሐምሌ ፬ (4) ቀን። ❤ እንኳን #ለዐሥራ_ሁለቱ_ደቂቅ_ነቢያት ለመታሰቢያ በዓላቸውና ከእነርሱ አንዱ ለሆነው ለሴዴቅያስ ልጅ ለጎዶልያ ልጅ ለኩሲ ልጅ #ለነቢዩ_ለቅዱስ_ሶፎንያስ_ለዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከቅዱሳን_አቡቂርና_ዮሐንስ ከሥጋቸው ፍልሰት እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ነቢዩ_ቅዱስ_ሶፎንያስ፦ እርሱም በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ዘመን ትንቢት ተናገረ። እንዲህም አለ "እግዚአብሔር ከዚህ ዓለም ፈጽመው ይጠፋሉ አለ ከብቶችም ሰዎችም ያልቃሉ። የባሕር አሳዎች በሰማይ የሚበሩ አእዋፍም ያልቃሉ"። ❤ ዳግመኛም ስለሞአብ እንዲህ አለ "ስለዚህ ሞአብ እንደ ሰዶም ትሆናለች የሞአብ ልጆች እንደ ገሞራ ልጆች ይሆናሉ ደማስቆም እንደ እህል ታልቃለች"። እርሱም እንደ ተነበየው እነዚያ አገሮች በናቡከደነፆር ምርኮ ይጠፋሉና። ❤ ዳግመኛም ስለ ፋርስ ስለ ነነዌ ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ "የፋርስን ሰዎች አጠፋቸዋለሁ ነነዌም ፍርስራሽና ውኃ እንደሌለባት ምድረ አደርጋታለሁ መንጋዎችም በመካከሏ ይሠማሩባታል"። ይቺ ከተማ በመቄዶናዊው እስክንድር እጅ ጠፍታለች። ❤ ዳግመኛ ስለ ክርስቶስ መምጣት እንዲህ ተናገረ "ያን ጊዜም ሁሉ የእግዚአብሔር ስም ይጠራ ዘንድ በአንድ ሕግም ይገዙልኛ ዘንድ የአሕዛብን ሁሉ አንደበት ወደ ሕግ እመልሳለሁ"። ደግሞም እንዲህ አለ "ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ መሥዋቴን ያመጡልኛል"። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በነቢዩ ቅዱስ ሶፎንያስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱ ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላዓለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ ዳግመኛም በዚች ቀን ስለ ክርስቶስ ትንቢታቸውን እንደ ፈሳሽ ውኃ ያጎረፉ #የዐሥራ_ሁለቱ_ደቂቀ_ነቢያት መታሰቢያቸው ነው። በረከታቸው ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የቅዱሳን_አቡቂርና_ዮሐንስ_የሥጋ_ፍልሰት፦ ይህም እንዲህ ነው እሊህ ቅዱሳን የካቲት ስድስት ቀን ሰማዕት ሆኑው በሞቱ ጊዜ ምዕመናን ሥጋቸውን ተሸክመው ወስደው በእስክንድርያ በስተሰሜን ባለች በቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሥውር አኖሩዋቸው እስከ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቄርሎስ ዘመንም በዚያ ኖሩ። ❤ እግዚአብሔር መልአክም ለቅዱስ ቄርሎስ ተገለጸለት ወደ ወንጌላዊ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያንም ሔዶ የቅዱሳን የአቡቂርና የዮሐንስን ሥጋቸውን አውጥቶ እንዲሸከም አዘዘው። እርሱም ተነሥቶ ሔደ ከእርሱም ጋራ ቡዙ ሕዝቦች ነበሩ በደረሱም ጊዜ ጸለዩ ምድሩንም ሲቆፍሩ ሥጋቸው በውስጡ ያለበት ቦታ ተገለጠላቸው በባሕር ዳርቻ ወደ አለች ወደ ሌላዪቱም ወደ ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ክብር የቅዱሳኑን ሥጋ ተሸክመው አድርሰው በዚያ አኖሩ። በዚያም ቤተ ክርስቲያን ሠሩላቸው በዚች ቀን ታላቅ በዓል አደረጉ ከሥጋዎቻቸው ድንቆች ተአምራት ተገለጡ። ❤ አረማውያንም ተሰበሰቡ ይህን ድንቅ ተአምር በአዩ ጊዜ ጣዖቶቻቸው ትተው ክርስቲያን ሆኑ። በዚያችም ጣዖት ቤት አሸዋ በላይዋ ተከመረባት ታላቅ ኮረብታም ሆነ። የቅዱሳንም ሥጋቸው ታአምራትንና ለበሽተኞች ታላቅ ፈውስን ያደርናጋል። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አቡቂርና በዮሐንስ በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 4 ስንክሳር።                               ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለከ_ሶፎንያስ_ክቡር። ዘተነበይከ በእንተ ይሁዳ ኅልቀተ ኃጥአን እምድር። እንዘ ትብል ከመዝ እንበለ ሠናይ ምግባር። ኢያድኅን ወኢይትቤዘው ብሩር። አመ ምጽአተ እግዚእ ዕለተ ፍዳ ዘድምፃ መሪር"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_4።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "እግዚአ ሰማዕነ በዕዘኒነ። ወአበዊነሂ ዜነዉነ። ግብረ ዘገበርከ በመዋዕሊሆሙ በመዋዕለ ትካት"። መዝ 43፥1። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 11፥32-ፍ.ም፣ 2ኛ ጴጥ 1፥19-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 10፥37-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 21፥33-46። የሚቀደሰው ቅዳሴ ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የነቢዩ የቅዱስ ሶፎንያስ የዕረፍት በዓል፤ የዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት መታሰቢያ በዓልና የሐዋርያት ጾም የመጨረሻ የጾም ቀን። ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤             ❤ #ሐምሌ ፫ (3) ቀን። ❤ እንኳን #ለእስክንድርያ_ሃያ_አራተኛ_ሊቀ_ጳጳስ ለአምደ ሃይማኖት መናፍቁ ንስጥሮስ በጉባኤ ኤፌሶን ተከራክሮ ረቶ ላወገዘው ለታላቁ #ለአቡነ_ቄርሎስ_ለዕረፍት መታሰቢያ በዓልና ከእርሱ በፊት ለነበረው ሊቀ ጳጳሳት ዮናክንዲኖስ ደቀ መዝሙሩ ለነበረው ለሮሜ ሊቀ ጳሳት ለቅዱስ አባት #ለአባ_ክልስቲያኖስ_ለዕረፍት መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #አባ_ቄርሎስ፦ ይህም አባት ለእስክንድርያ (ለግብጽ) ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃያ አራተኛ ነው። ይህም ቅዱስ የእናቱ ወንድም በሆነው በአባ ቴዎፍሎስ ዘንድ አደገ፤ ጥቂት ከፍ ባለ ጊዜም ወደ አስቄጥስ ወደ መቃርስ ገዳም ላከው በዚያም አምላካውያን የሆኑ መጻሕፍትን ተማረ እግዚአብሔርም መጽሐፍትን አንድ ጊዜ አንብቦ እስከሚአጸናው ድረስ ዕውቀትንና ማስተዋልን ሰጠው። ❤ ከዚህም በኋላ ደግሞ ያስተምረው ዘንድ ለአባ ሰራብዮን ሰጠው ከእርሱም ዘንድ ያለውን ትምህርትን በፈጸመ ጊዜ ወደ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎፍሎስ መለሰው። እርሱም እጅግ ደስ ተሰኘበት እግዚአብሔርንም አመሰገነው። ❤ ከዚህም በኋላ ሁል ጊዜ መጻሕፍትን እንዲያነብና ሕዝቡን እንዲያስተምር ለሊቀ ጵጵስና ሥራ ውስጥ ሾመው። ከትምህርቱም ጣዕም የተነሣ ዝም ይል ዘንድ ማንም አይወድም ነበር። ❤ አባ ቴዎፍሎስ በዐረፈ በኋላ በእስክንድርያ ከተማ ላይ ይህን አባ ቄርሎስነ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት በዘመኑም በትምህርቱ ቤተ ክርስቲያን በራች። ይኸው አባት ቄርሎስ የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት የነበረው ንስጥሮስ በካደ ጊዜ በንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘመን የሁለት መቶ ኤጲስቆጶሳት ጉባኤ ማኅበርን በኤፌሶን ከተማ ሰበሰበ። ይህ አባት ቄርሎስን መረጠው ሊቀ ጉባኤ አደረጉት ንስጥሮስንም ተከራከረው ስህተቱንም ገለጠለት ከስህተቱም ባልተመለሰ ጊዜ አውግዘው ከመንበረ ሲመት አሳደዱት። ❤ ይህም አባት ቄርሎስ አሥራ ሁለት አንቀጾችን ደረሰ። በውስጣቸውም የቀናች ሃይማኖትን ገለጠ። ከዚህም በኋላ ግን ብዙዎች ድንሳናትን ተግሳጻትንና መልእክቶችን ደረሰ። እሊህም በሁሉ ቦታ በመምእመናን እጆች ይገኛሉ። ❤ ይህም አባት ቄርሎስ እግዚአብሔር ቃል ከትሥብእቱ ጋራ ከተዋሐደ በኋላ በሥራ ሁሉ በምንም በምን የማይለያይ አንድ አካል አንድ ባሕሪይ እንደሆነ አስረዳ። ይህም አባት ቄርሎስ ሃይማኖታቸው ከቀና ከሦስት መቶ አሥራ ስምንት አባቶ ሃይማኖት ወጥተው ክርስቶስ ወደ ሁለት የሚከፍሉት መናፍቃንን ሁሉንም አውግዞ ለያቸው። ❤ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ መንበር ላይ ሠላሳ ሁለት ዓመት ኖረ መልካም የሆነ ሥራውም ፈጽሞ ሐምሌ 3 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ቄርሎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላዓለሙ አሜን።                              ✝ ✝ ✝ ❤ #የሮሜ_ሊቀ_ጳጳሳት_ቅዱስ_አባት_አባ #ክልስቲያኖስ፦ ይህ አባ ዮናክንዲዮስ በሚያርፍበት ጊዜ በእርሱ ፈንታ አባ ክልስቲያኖስን ሊቀ ጵጵስና እንዲሾሙት አዘዘ እርሱንም አባ ክልስቲያኖስን "በሮሜ አገር ነጣቂ ተኩላዎች አሉና ልጄ ሆይ ተጠበቅ" ብሎ አዘዘ። ❤ ከዚህም በኋላ አባ ዮናክንዲዮስ በዐረፈ ጊዜ ይህን አባት ክልስቲያኖስን በእርሱ ፈንታ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት። በዚያ ወራት ደግ ንጉሥ አኖርዮስ ነበር ከእርሱም በኋላ አመጸኛ ሉልያኖስ ነገሠ እርሱም ክርስቲያኖስን ከመንበሩ አሳድዶ መናፍቁን ንስጥሮስን ሊቀ ጵጵስና ሾመው። የከተማ ሰዎች ግን አባረሩት እንጂ አልተቀበሉትም በከሀዲው ንጉሥም ልብ በክርስቲያስ ላይ ቂም ነበረ ሊገድለውም ይሻ ነበር። እርሱ አባ ክልስቲያኖስ ግን በሮሜ ከተማ የሚገኙ ገዳማት በንዱ ገብቶ ኖረ እግዚአብሔርም ብዙ ድንቆችንና ተአምራቶችን በእጆቹ ያደርግ ነበር። ❤ ከዚህም በኋላ ከሀዲው ንጉሥ ወደ ጦርነት ሆደ የእግዚአብሔር መልአክ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሩፋኤልን ለክልስቲያኖስ ተገለጠለት ወደ አንጾክያ ከተማ ወደ ሊቀ ጳጳሳት ድምትርያኖስ ይሔድ ዘንድ አዘዘው "በዚያም ኑር" አለው። "ንጉሡ ከጦርነት እንደተመለሰ ይገድልህ ዘንድ በልቡ አስባልና"። ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ ከዚያ ገዳም ወጣ ከእርሱም ጋራም ሁለት መነኰሳት ነበሩ ወደ አንጾኪያ ከተማ ወደርሶ ቅዱስ ድምትርያኖስ አገኘው ከአመጸኛው ንጉሥም የደረሰበትን ሁሉ ነገረው እርሱም በአንጾኪያ ከተማ የሚገኙ ገዳማት በአንዱ ገዳም አኖረው። ❤ ከዚህ በኋላ ቅዱሳን ሊቃ ጳጳሳት አግናጥዮስና ዮናክንዲዮስ በሌሊት ዕራይ ለንጉሡ ተገለጡለት ከእርሳቸውም ጋራ የነበረው አንዱ እጅግ የሚያስፈራና ግሩም ነበር። እርሱም ንጉሡን እንዲህ አለው "ሊቀ ጳጳሳቱን ክልስቲያኖስን አገሩን ለምን አስተውከው እነሆ እግዚአብሔር ነፍስህን ከአንተ ይወስዳል በጠላቶችህም እጅ ትሞታለህ"። ንጉሥም ጌታዬ "ምን ላድርግ" አለው እነዚያም ሁለትም አባቶች "በእግዚአብሔር ልጅ ሕማም በመቀበሉ ታምናለህን" ብለው መለሱለት "እኔ አምናለሁ" አላቸው "ዳግመኛም መልእክትን ልከህ ልጃችን ክልስቲያኖስ ወደ መንበሩ መልሰው" አሉት። ❤ ከእንቅልፉም በነቃ ጊዜ መልክትን ጽፌ ወደ ድምትራያኖስ እንዲህ ብሎ ላከ "ስለ ሊቀ ጳጳሳት ክልስቲያኖስ በእኔ ላይ አትዘን ወደ መንበረ ሲመቱ ይመልሱት ዘንድ ሊቀ ጳጳሳት ክልስቲያኖስ ያለበትን በመላእክተኞቼ ታመላክታቸውና ታደርሳቸው ዘንድ እለምንሀለሁ"። መልአክተኞችም በሔዱ ጊዜ አገኙትና መለሱት ሕዝቡም በታላቅ ክብርና በብዙ ደስታ ተቀበሉት በዚያም ወራት ንጉሡ ከጦርነት በደና ተመለሰ ቤተ ክርስቲያንም በዕረፍትና በሰላም ኖረች። ❤ የንስጥሮስም ክህደቱ በተገለጠ ጊዜ በእርሱ ምንክያት አንድነት ያላቸው ማኅበር ተሰበሰቡ ይህ አባት ክልስቲያኖስ በደዌውና በእርጅናው ምክንያት ወደ ጉባኤው መምጣት አልተቻላቸውም ነገር ግን ንስጥሮስን ከሚያወግዝ ደብዳቤ ጋር ሁለት ቀሳውስትን ላከ። ❤ ክብር ይግባውና ጌታችንም ከዚህ ኃላፊ ዓለም ድካም ሊያሳርፈው በፈቀደ ጊዜ ዮናክንዲዮስና አትናስዮስ ተገለጡለት እንዲህም አሉት "ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕይወት ጠርተሀልና አንተ ወደ እኛ ስለምትመጣ አስጠንቅቃቸው" አሉት። ከእንቅልፉ ነቅቶ ወገኖቹን ጠራቸው እንዲህም አላቸው "ተኩላዎች ወደዚች ከተማ ይገቡ ዘንድ አላቸውና ተጠንቀቁ"። ❤ ይህንም ከተናገረ በኋላ ዳግመኛ እንዲህ አለ "እንነሳና እንሂድ እነሆ ቅዱሳን ይሹኛልና ሁለቱ ሌሎች ናቸው በዚችም ሰዓት በዚች ዓለም በአንድነት እንወጣለን እነርሱም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ቄርሎስና የፃን አገር ኤጲስቆጶስ ሉቅያስ ናቸው" ይህንንም ብሎ ሐምሌ 3 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን አባቶቻችን ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 3 ሰንክሳር።                                                       ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "እነግሮሙ ስመከ ለአኃውየ። ወበማዕከለ ማኅበር እሴብሓከ። እለ ትፈርህዎ ለእግዚአብሔር ሰብሕዎ"። መዝ 21፥22-23። የሚነበቡት መልዕክታት ቲቶ 3፥18-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 3፥15-ፍ.ም የሐዋ ሥራ 20፥28-31። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 18፥15-21። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ቄርሎስ ቅዳሴ ነው። መልካም የቅዱስ ቄርሎስ በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ ከዚህ በኋላ በላ መርፌው ቀዳዳው ጠባብ የሆነውነ መርፌ በአቀረበለት ጊዜ "ኃይልህ ግለጥ" ብሎ ወደ ጌታችን ጸለየ እጁንም ዘርግቶ በአለ ገመሉን ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አንተ ከገመልህ ጋር በመርፎ ቀዳዳ ውስጥ ግባና እለፍ" አለው ገብቶም አለፈ "ሕዝቡም የፈጣሪያች የክርስቶስ ኃይል ይረዱ ዘንድ ዳግመኛ ገብተህ እለፍ" አለው። ባለ ገመሉም በመርፎው ቀዳዳ ሦስት ጊዜ ከገመሉ ጋር አልፎ ሆደ። ❤ ሕዝቡም አይተው "ከቅዱሳን ሐዋርያት አምላክ ከህያው እግዚአብሔር ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለም" እያሉ ጽምጻቸውን ከፍ አድርገው ተናገሩ። ያም ጎልማሳ ባለጸጋ መጥቶ ከሐዋርያው እግር በታች ወድቆ ሰገደና ኃጥያቴን ሁሉ ይቅ በለኝ ገንዘቤንም ሁሉ ወስደህ ለድኆችና ለምስኪኖች አከፍፍልልኝ" አለው። እንደ ለመነውም አደረገለት የሃይማኖትንም ሕግ አተምሮ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቀው ሥጋውንና ደሙ አቀበለው ሁሉንም በቀናች ሃይማኖት አጸናቸው። ❤ ከዚህ በኋላ ከዚያ ወጣ በሰላምም ሸኙት በቡዙ አገሮችም ውስጥ ገብቶ ሰበከ ከአይሁድና ከአረማውያን መከራ ደረሰበት ከዚህም በኋላ ሐምሌ 2 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ይሁን እኛንም በሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱ ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላዓለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 1 ስንክሳር።                               ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለታዴዎስ_ምንዳቤ_ሕንቀት_ዘተወክፈ። እንበይነ ጥሪቱ ወብዕሉ አመ ባዕለ ዘለፈ። ለትውልድ ደኀሪ እስከ ተአምሩ ተጽሕፈ። ሰቀለ ብእሲተ በነፋስ ዘትዜሙ ዘልፈ። ወበስቊረተ መርፍዕ ካዕበ ገመለ አኅለፈ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሐምሌ_2።                            ✝️ ✝️ ✝️ ❤ የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ "ውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ። ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ። ወወስተ ፀሓይ ሤመ ጽላሎቶ"። መዝ 18፥4-5። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 13፥24-33።                            ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ሐወጸካ ለምድር ወአርወይካ። ወአብዛኅኮ ለብዕላ። ፈለገ እግዚአብሔር ምሉዕ ማያት"። መዝ 64፥9። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 9፥1-13፣ ይሁ 1፥17-ፍ.ም እና የሐዋ ሥራ 5፥17-33። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 19፥16-30። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱሳን ሐዋርያት ቅዳሴ ነው። መልካም የሐዋርያው የቅዱስ ታዴዎስ የዕረፍት በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤              ❤ #ሐምሌ ፪ (2) ቀን። ❤ እንኳን #ከዐሥራ_ሁለቱ_ሐዋርያት ለአንዱ ግመልን በመርፌ ቀዳዳ ላሳለፈ #ለሐዋርያው_ለቅዱስ_ታዴዎስ ለዕረፍቱ በዓል መታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                            ✝ ✝ ✝ ❤ #ሐዋርያው_ቅዱስ_ታዴዎስ፦ ይህንንም ሐዋርያ ከዐሥራ ሁለት ጋራ ጌታችን አስቀድሞ መረጠው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ በላቸው በወረደ ጊዜ ወደ አገሮች ወጥቶ የወንጌልን ትምህርት አስማረ ከአይሁድና ከአረማውያን ብዙዎቹን ወደ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር መልሶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው። ❤ አንድ ቀንም ወደ ሶርያ ከተማ ሲጓዝ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልአኩ በሚአምር ጎልማሳ አምሳል ለእርሱ ተገልጦ "ወዳጄ ታዴዎስ ቸር አለህን አትፍራ እኔ ከእንተ ጋራ እኖራለሁና" አለው። ሰላምታም ሰጥቶት ከእርሱ ዘንድ ዐረገ። ❤ ወደ ከተማውም በቀረበ ጊዜ ከእርሱ ጋራ አባት ጴጥሮስ ነበረ ማሳ የሚያርስ ሽማግሌ ሰውን አዩ ሐዋርያትም ሰላምታ ሰጡትና "ሽማግሌ ሆይ የምንበላው እንጀራ ስጠን" አሉት። እርሱም "ከዚህ የለም ግን አመጣላችኋለሁ እናንተም ከበሮቹ ዘንድ ተቀመጡ" አላቸው። እነርሱም " እንዳልክ ይሁን" አሉት። ❤ ያሽማግሌም ከሔደ በኋላ ሐዋርያ "ከበሮች ጋር ያለ ሥራ በከንቱ መቀመጥ ለኔ ኀፍረት ነው ያሽማግሌ ለእኛ በጎ ሊሠራ ሒዷልና" አለ። ይህንኔም ብሎ ተነሥቶ እርፋን ይዞ በበሮቹ ላይ ድምፅ አሰማና ያርስ ጀመረ በዚያም ከርሱ ጋራ የሥንዴ ዘር ነበርና ያን ጊዜ ዘሩንና ማሳውን ባርኮ የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእርሻው ላይ ዘራ ሠላሳ ትልሞችኖም አረሰ። ❤ የተዘራው ዘርም ወዲያውኑ በቀለና አደገ እሸትም ሆነ ያ ሽማግሌም በተመለሰ ጊዜ ሐዋርያት ያደረጉትን ተመልክቶ ደነገጠ። ከእግራቸውም በታች ወድቆ ሰገደ "እናንተ ከሰማይ የወረዳችሁ አማልክት ናችሁን" አላቸው እነርሱም "እኛ የቸሩ አምላክ ባሮቹ ነን እንጂ አማልክት አይደለንም" አሉት ደግሞ እንዲህ አላቸው "ስለ አደረጋችሁልኝ በጎ ሥራ በምትሔዱባት ቦታ ሁሉ ልከተላችሁን"። "ይህን ልታደርግ አይገባም ነገር ግን በሮቹን ለጌታቸው ወስደህ መልስ ቤትህንም አዘጋጅልን የምንበላውንም ታዘጋጅልን ዘንድ ለሚስትህ ንገራት። እኛም ወዚች ከተማ ልንገባና እግዚአብሔር እስከ ጠራን ድረስ በውጧ ለመኖር እንሻለን" አሉት። ❤ ከዚህም በኋላ ያ ሰው ከዚያ እርሻ እሸት ቆርጦ ተሸከመ በሮቹንም እየነዳ ሔደ የከተማው ሰዎችም የተሸከመውን እሸት አይተው "አሁን የእርሻ ወቅት አይደለምን ይህን ከወዴት አገኘህ" አሉት ቃልንም አልመለሰላቸውም። በሮቹንም ለጌታቸው መለሰ ወደ ቤቱም ሔዶ ለሐዋርያት ቦታን አዘጋጀ ራትንም እንድታዘጋጅላቸው ለሚስቱ ነገራት። ❤ ወሬውም ወደ ከተማው መኳንንት ደረሰ "በክፉ አሟሟት እንዳትሞት ይህን እሸት ከወዴት እንዳገኘህ ንገረን" ብለው ወደርሱ ላኩ። ይህንም በሰማ ጊዜ "ከእኔ ጋራ ሕይወት ሳለ ሞትን አልፈራም" አለ ይህንንም ብሎ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ነገራቸው። "ሒደህ ወደእኛ አምጣቸው" አሉት እርሱም "ጥቂት ቆዩ እነርሱ ወደእኔ ቤት ይመጣሉ በመጡም ጊዜ በዐይኖቻቸችሁ ታይዋቸዋላችሁ" አላቸው። ❤ ሰይጣንም የከተማ መኳንንቱን ልቡና ለውጦ አከፋ "እኒህ አይሁድ ከሰቀሉት ከናዝሬቱ ኢየሱስ ዐሥራ ሁለት ወገኖች ውስጥ ከሆኑ ወዮልን እንድንገድላቸውም ተዘጋጁ" አሉ። እኩሌቶቹም "ልገድላቸው አንችልም አምላካቸው ኢየሱስ የሚሹትን ሁሉ እንደሚያደርግላቸው ሰምተናልና ነገር ግን አመንዝራ ሴት ወስደን በከተማ መግቢያ በር ራቁቷን እናስቀምጣት በአዩዋትም ጊዜ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ ወደ ከተማችንም አይገቡም" አሉ። ❤ እንዲሁም አደረጉ ሴትዮዋንም አራቁተው በከተማው መግቢያ በር ላይ አስቀመጧት። ሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስም በአያት ጊዜ "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ወደ ከተማው ገብተን በከበረ ስምህ እስክንሰብክ ድረስ በራሷ ጠጉር በአየር ላይ ይሰቅላት ዘንድ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ላክልን" አለ። በዚያን ጊዜም ተሰቀለች የከተማዋ ሰዎችም አዩዋት ያቺ ሴትም በከተማው መኳንንቶ "አቤቱ ፍረድልኝ እያለች ጮኸች" ነገር ግን የሐዋርያትን ቃል ወደ መቀበል አልተመለሱም ሰይጣን የሰዎችን ልብ አጽንቷልና። ❤ ከዚህም በኋላ ወዲያውኑ ተነሥተው ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ ያንጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወረደና የከተማው ሰዎችን ልቡና የማረኩ መናፍስት ርኩሳንን አስወጥቶ ሰደዳቸው ሰዎቹም የሐዋርያትን ትምህርት ተቀበሉ። ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ያን ጊዜም ሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስ ያቺን በአየር ላይ የተሰቀለትውን ሴት አወረዳት። ❤ ከዚህም በኋላም ኤጲስቆጶሳትን ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስም ስም አጠመቃቸው ያቺንም ተሰቅላ የነበረች ሴት ለቤተ ክርስቲያን የምትላላክ ዲያቆናዊት አደረጋት። ❤ በሐዋርያትም እጆች ብዙ ድንቅና ተአምር ተደረገ እውሮች አየ፣ ሀንካሶችም በትክክል ሔዱ፣ ዲዳዋች ተናገሩ፣ ደንቆሮዎች ሰሙ ለምጻሞች ነጹ፣ አጋንትም ከሰው እየወጡ ተሰደዱ የከተማው ሰዎችም ሁሉ በጌታችን ስኪያምኑ ሙታን ተነሱ። ❤ ሰይጣንም የከተማው ሰዎች ሁሉም በጌታችን እንዳመኑ በአየ ጊዜ ተቆጣ በአንድ ገንዘብ በሚወድ ጎልማሳ ባለጸጋ ልቡ አድሮ በሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስ ላይ አነሳሳው ወደእርሱም ሰገደለትና እንዲህ አለው "የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆይ እኔ ብዙ ገንዘብ አለኝ እድን ዘንድ ምን ላድርግ" አለው። ሐዋርያውም ጎልማሳውን "ፈጣሪህ እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡህ በፍጹም ኃይልህ ውደደው፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ አታመንዝር፣ በአንተ ሊያደርጉብህ የማትሻው በሌላው ላይ አታድርግ፣ ደግሞም ገንዘብህ ሸጠህ ለድኆችና ለምስኪኖች ስጥ በሰማያትም ለዘላለዓለም የሚኖር ድልብ ታገኛለህ" አለው። ይህንንም በሰማ ጊዜ ቊጣን ተመልቶ ሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስ ይገድለው ዘንድ አነቀው የእግዚአብሔርም ኃይል ከዚህ ሐዋርያ ጋር ባይኖር ኖሮ ከመታነቁ ጽናት የተነሳ አይኖቹ ተመዘው በወጡ ነበር። ❤ አባት ቅዱስ ጴጥሮስም "የክርስቶስን ሐዋርያ እንዴት ደፍረህ ታንቃለህ" አለው። ያን ጊዜም ተወው። ሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስም "ጌታችን እንደአንተ ላለው ሀብታም ባለፀጋ ወደ መንግሥተ ሰማይ ከሚገባ ገመል በመርፎ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል" ብሎ በእውነት ተናገረ አለው። ጎልማሳ "ባለፀጋም ይህ ነገር ትክክል አይደለም እንዴት ሊሆን ይችላል" አለ። ❤ በዚያ ጊዜም በዚያ ጎዳና ሊያልፍ ባለ ገመል መጣ ሐዋርያው ቅዱስ ታዴዎስም ጠርቶ አስቆመውና መርፌ ከሚሸጥ ዘንድ መርፌን ፈለገ መርፌ የሚሸጠው ግን ሐዋርያው ሊረዳው ፈልጎ ቀዳዳው ሰፊ የሆነ መርፌ አመጣለት ሐዋርያው እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ ነገር ግን በዚች አገር የእግዚአብሔር ክብር ይገለጥ ዘንድ ቀዳዳው ጠባብ የሆነ መርፌ አምጣል" አለው።

❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን" ❤                ❤ #ሐምሌ ፩ (1) ቀን። ❤ እንኳን ሰማዕት ለሆነች ሰውነቷን ለእግዚአብሔር ለሰጠች #ለቅድስት_ድንግልና_ለመስጋድልት_ለቅፍሮንያ_ለዕረፍቷ_መታሰቢያ_በዓልና #ለቅዱሳን_መስተጋድላን #ብዮክና_ብንያሚን_ለዕረፍታቸው_መታሰቢያ_በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከሮሜ_ሊቀ_ጳጳሳት_ከክልዮስና #ከበርተሎሜዎስ #ከጻድቁ_ከገብረ_መድኅንም_ከዕረፍታቸው መታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ ሰውነቷን ለእግዚአብሔር የሰጠች #ቅድስት_ድንግልና_መስተጋድል_ቅፍሮንያ፦ እርሷም በደናግል ገዳም ቊጥራቸው ሃምሳ ለሆኑ ለደናግሉ እመ ምኔት እኅት ነበረች። የእመ ምኔትዋም ስሟ ኦርያና ነው። ይህችንም ቅድስት በፈሪሀ እግዚአብሔር አሳደገቻት። በትሩፋት ሥራ ተጋዳሊት እስከሆነችም ድረስ አምላካውያን የሆኑ መጻሕፍትን አስተማረቻት። ❤ ከዚህም በኋላ ፍጹም ገድልን ጀመረች በየሁለት ቀኑ ትጾም ነበር ብዙ ጸሎታትንም ትጸልይ ነበር። ያቺም እመ ምኔት ሥራዋ ያማረ በሃይማኖቷም የጸናች ነበረች። በበጎ ሥራ ሁሉ እንዲጸኑ ወገኖቿን ታስተምራቸው ነበር። ❤ ከዚህም በኋላ ሰዎች ሁሉ ጣዖታትን እንዲያመልኩ ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ በአዘዘ ጊዜ ብዙዎች ክርስቲያኖችን ይዘው አሠቃዩአቸው ሰማዕታትም ሆኑ። እሊያ ደናግልም ይህን በሰሙ ጊዜ ሁሉም ከገዳም ወጥተው ሸሽተው ተሠወሩ። እመ ምኔቷ ግን ከዚች ቅድስት ቅፍሮንያ ጋራ ብቻዋን ቀረች። ❤ በማግሥቱም የንጉሡ መልክተኖች ወደ ዚያ ገዳም በመጡ ጊዜ እመ ምኔቷን አግኝተው ያዟት ሌሎችንም ደናግል ፈለጓቸው ግን አላገኟቸውም። ቅድስት ቅፍሮንያን "በእርሷ ፈንታ እኔን ውሰዱኝ ይቺንም አሮጊት ተውዋት" አለቻቸው። እነርሱም ያዟት በብረት ሰንሰለትም አሠሩዋት መኰንኑ ወደአለበትም ከተማ ወሰዱዋት እመ ምኔቷም እያለቀሰች ተከተለቻቸው። ❤ ወደ መኰንኑም በአደረሷት ጊዜ ለአማልክት ሠዊ አላት ብዙ ቃል ኪዳንም ገባላት እርስዋ ግን ቃል ኪዳኖቹን አቃለለች ትእዛዙንም አልተቀበለችም እንዲደበድቧትም አዘዘና በበትሮች ደበደቧት። ዳግመኛም ልብሷን ገፍፈው ሥጋዋን ግልጥ እንዲያደርጉ አዘዘ እመ ምኔቷ ኦርያናም "አንተ ከሀዲ ይችን ታናሽ ብላቴና እንዳጎስቈልሃት እግዚአብሔር ያጎሳቊልህ ዘንድ አለው" ብላ ጮኸች። ❤ መኰንኑም እጅግ ተቈጥቶ ይህችን ቅድስት ቅፍሮንያን አሥረው በመንኰራኵር ውስጥ እንዲአሠቃዩዋት በብረት መጋዝም እንዲሠነጥቋት አዘዘ ሁሉንም አደረጉ። ይህንም ሁሉ ፈጸሙባት እርሷም ርዳታን ሽታ ወደ እግዚአብሔር ጮኸች ወዲያውኑ ከሕመሟ ሁሉ ድና ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባት ሆነች። ❤ ከዚህ በኋላ ደግሞ ምላሷንና ሕዋሳቷን ሁሉ ቆረጡ ጥርሶቿንም ሰበሩ ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ሕማም አስነሣት። መኰንኑም እርሷን ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘና ቆረጧት በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጀች። ❤ አንድ ባለ ጸጋ ምእመን ሰውም መጥቶ የቅድስት ቅፍሮንያን ሥጋ ወሰደ በአማሩ የሐር ልብሶችም ገንዞ በወርቅ ሣጥን አኖራት ከሥጋዋም ብዙ ድንቅ ተአምር ተገለጠ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስት ቅፍሮንያ ጸሎት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።                             ✝ ✝ ✝ ❤ #ቅዱሳን_መስተጋድላን_ብዮክና_ብንያሚን፦ እሊህም ቅዱሳን በግብጽ ደቡብ በቴዎዳ አውራጃ ቱና በሚባል አገር የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ነበሩ። እነርሱም ወንድማማች ነበሩ። አባታቸውም የቤተ ክርስቲያን ሹም የሆነ ደግና የዋህ ሰው ነበር እሊህም ሁለቱ ልጆች በእግዚአብሔር ጸጋና በቅድስና ፍጹማን ነበሩ። ❤ እግዚአብሔርም በእጆቻቸው ተአምራትን ያደርግ ነበር በሽተኞችን ሁሉ ይፈውሱ ነበር እነርሱም ከቤተ ክርስቲያኑ የጉድጓድ ውኃ ቀድተው በሽተኞችን ያጥቧቸዋል ወዲያውም ከበሽታቸው ይድኑ ነበር። ❤ አባታቸውም የዕረፍቱ ቀን በቀረበ ጊዜ በዚያን ሰዓት ቀሲስ ብንያሚን ቊርባን ያሳርግ ዘንድ የቅዳሴ ልብስ ለብሶ በቤተ መቅደስ ነበረ መልክተኞችም መጥተው አባቱ ለመሞት እንደ ተቃረበ እርሱንም እንደሚፈልገው ነገሩት። ብንያሚንም "የቊርባኑን ሥርዓት ሳልፈጽም ልብሰ ተክህኖውን አላወልቅም ከመሞቱ በፊት እንደየው እግዚአብሔር ከፈቀደ ይቆየኛል ካልሆነም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን" አለ። አባቱም ሁለተኛና ሦስተኛ ጊዜ ላከ አባ ብንያሚን ግን የቊርባኑን ሥርዓት ከፈጸመ በኋላ ወደ አባቱ ሔደ ሙቶም አገኘው ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ንዋየ ቅዱሳትም እጅግ አዘነ እነርሱ በእርሱ ዘንድ እየኖሩ ዕቃዎችን ያኖረበትን ቦታ አላመለከታቸው ነበርና። ❤ ወንድሙ ብዮክም አባታቸው ስለ አስቀመጠው ንዋየ ቅዱሳት ወደ አስቆጥስ ገዳም ወደ ቅዱሳን አረጋውያን ሒዶ እንዲጠይቅ መከረው። አባ ብያሚንም በሔደ ጊዜ የአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት አባ ዳንኤልን አገኘው አባ ዳንኤልም ስርሱ የመጣበትን ሥራ ሁሉ ነገረው ነገር ግን ወደ አንድ ጻድቅ ሰው እንዲሔድ አዘዘው እርሱ ንዋየ ቅዱሳቱ ያለበትን እንደሚያስረዳው ነገረው። በሔደም ጊዜ እንደ አመለከተው ያንን ጻድቅ ሰው አገኘው። እርሱም ገልጾ አስረዳው በተመለሰም ጊዜ እንዳስረዳው አገኘው። ❤ ከዚህም በኋላ በመልካም ገድል ሁሉ ከወንድሙ ጋራ ተጠምዶ ኖረ። ለሕሙማን ነፍሳቸው ሳትወጣ ያቀብሏቸው ዘንድ ከቅዱስ ቊርባን ከፍለው በሣጥን የሚኖር ሥርዓት ነበራቸው ሰይጣንም ከይሲን አነሣሣውና ሣጥኑን ቀድዶ ከዚያ ከቅዱስ ቊርባኑ በላ። ❤ ብዮክና ብንያሚንም ይህን ባወቁ ጊዜ እጅግ አዘኑ ከይሲውንም ገደሉት ከዚህም በኋላ የተቀደሰውን ቊርባን ስለ በላ ከይሲውን ይበሉት ዘንድ ተማከሩ ፈቃዱም ከሆነ እንዲያስረዳቸው እግዚአብሔርን ለመኑት የእግዚአብሔር መልአክም ተገለጸላቸውና ያን ከይሲ ይበሉት ዘንድ አዘዛቸው እነርሱም በሉት። ከበሉትም በኋላ ዐረፉ። ❤ እግዚአብሔርም ሥራቸውንና ገድላቸውን ለአንዲት ድንግል ሴት ገለጸ እርሷም የእሊህን ቅዱሳን ገድል ለሕዝብ ተናገረች። እርሱም የአማረች ቤተ ክርስቲያንን ሠርተው ሥጋቸውን በውስጧ አኖሩ ከሥጋቸውም ብዙ ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ብዮክና ብንያሚን በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሐምሌ 1 ስንክሳር።                            ✝ ✝ ✝ ❤ "#ሰላም_ለቅፍሮንያ_አስናኒሃ_ዘሰበሩ። ወመለያልያቲሃ ዘመተሩ። ወዘንተ ኲሎ እንዘ ይገብሩ። ኢክህሉ በጽንዖሙ ለዲዮቅልጥያኖስ ማኅበሩ። ከመ ይምጥዋ ለክርስቶስ እምፍቅሩ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሐምሌ 1።                           ✝ ✝ ✝ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ለስሒት መኑ ይሌብዋ። እምኅቡዓትየ አንጽሐኒ። ወእምነኪር መሐኮ ለገብርከ። መዝ 18፥12። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ጢሞ 5፥1-18፣ 1ኛ ጴጥ 3፥1-7 እና የሐዋ ሥራ 9፥36-ፍ.ም። የሚበበው ወንጌል ዮሐ 20፥19-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ኤጲፋንዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።

ክረምቱን በአብነት 🎤ከአቀባይ መምህር ተቀድቶ በትውልድ አእምሮ ላይ የተቀመጠ እውነት መጥፋት አይችልም። 🎤የአብነት ትምህርት  ጠንክረው ከተማሩት ተኖ የሚጠፋ፦"የድምጫ ትምህርት የገቦ አዝርዕት"አይደለም።ልጆቻችንን ጠንክረን ብናስተምራቸው ቢያንስ ቢያንስ ለመካሪ አያስቸግሩም። 🎤ሴት ልጆቻችሁንም ወደ አብነት ትምህርት ላኳቸው። "አርፈሽ ተቀመጭ አንቺ አትቀድሺ"?የምትሉ ወላጆች ትክክል አይደላችሁም። የቅዳሴም የማኅሌቱም ዋነኛዋ ሴት አይደለችም እንዴ? ሴቶች በዕውቀት በእምነት ሲጸኑ ያን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን በብዙ የአገልጋይ ፍሬ ትሞላለች። እግዚአብሔርም በነቢዩ አድሮ "ሴቶች ልጆቼ ቍርባኔን ያመጡልኛል።"ሶፎ.፫፥፲እንዳለ። 🎤ሴቶችም ወንዶችም ልጆቻችን፦ፊደል ቆጥረው፣ውዳሴ ማርያም አጥንተው፣ ዳዊት ደግመው፣የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ አውቀው፣ትምህርተ ሃይማኖት ተምረው፣ሥነ ምግባርን ተላብሰው፣ከመቅደሱ ሥር ዕጣን አሽተው፣ጸበል ጠጥተው፣እምነት ተቀቦተው..ቢያድጉ ጉዳቱ ምንድን ላይ ነው? 🎤እንኳን ከእግዚአብሔር ለተቀበልነው ለአብነት ለሌላውስ ተምህርትስ ቢሆን ይጠቅማል ብለን ገንዘብ ውጥተን ጊዜ በጅተን ደክመን የለም ወይ? 🎤መርጌቶች፣ካህናት፣ዲያቆናት፣ሰባክያን፣የከፍተኛ የአብነት ደቀ መዛሙርት የክረምት ሥራችን በአብነት ትምህርት በኩል ትውልድ መተካት ላይ መሆን አለበት። አጥቢያዎች፣መንደሮች ሁሉ በየአቅራቢያው ትምህርት ሊሰጥባቸው ይገባል። ወላጆች፣ሰበካ ጉባኤያት፣ወጣቶች፣ማኅበራት፣ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ማኅበረ ካህናት፣ሰንበቴዎች..ዐይናችሁን ወደ አብነት መልሱ። እየተደራጃችሁ መምህር መቅጠር ካለባችሁ ቅጠሩ፣መደጎም ካለባችሁ ደጉሙ። በተለይም ሰበካ ጉባኤው የትምህርት ኬላዎን አበጅቶ በበቂ ሁኔታ መምህራንን መመደብ እና መከታተል አለበት። 🎤መምህር የማይመድብ ሰበካ ጉባኤ ካለ ምእመናን አጥብቃችሁ ጠይቁት። የሰበካ ጉባኤ ዋነኛ ሥራው ይሄ ነው።ሕንጻ ግንባታዎ፣ልማቶች ከዚህ ባሻገር ናቸው።በምድር ላይ ሁሉም ከሰው በታች ነው። ሰው ግን ከሁሉም አመክንዮ በላይ ነው። 🎤ዘመኑን መዋጀት፣ቀድሞ መገኘት ማለት ትውልድ ላይ መሥራት ነው። ኋለቀር ማለት የነገውን ትውልድ መርሳት ነው። ስለዚህ በተተኪ ትውልድ ላይ እንሥራ ማለት መጻኢ ዘመኑን እንዋጅ ማለት ነው። 🎤የሰንበት ተማሪዎችም ከነጠላ  ዘፈናዊ ዝማሬ ወጥተን ወደ መሠረታዊ የአብነት ትምህርት እና ትምህርተ ሃይማኖት ብናተኩር ጥሩ ነው።ሀምሳ ዝማሬ ከመላስ አንድ ውዳሴ  ማርያም አጥንቶ መቅመስ ይሻላል። 🎤በተለይም በጦርነት ቀጠና ያሉ ሕጻናት ሦስት ዓመት ሙሉ ያለ ትምህርት በመባጀታቸው በነገው ማኅበረ ሰብእ መካከል ትልቅ ክፍተት ነው። ስለዚህ የማያነብ፣የማይጽፍ፣የማይረዳ፣የማይጸልይ ትውልድ እንዳይኖር ጥልቅ እሳቤ ቅን ህሊና፣ትጋት ያለው ተግባር ይጠይቃል። 🎤የማያነብ፣የማይጽፍ፣የማያሰላ ትውልድ ያለበትን ክፍተት አስበችሁታል? በዲጅታል ዓለም፣በ5G ትውልድ፣በAI ዘመን፣በበርችዋል ሥርዓት መካከል ፊደል ሳይቆጥሩ ሂሳብ ሳያሰሉ ተቀምጠው እንዴት ነው ራሳቸውን መምራት እና ዘመኑን መዋጀት የሚችሉት? 🎤ቢያንስ በየገጠሩ ሁሉ ሰላም መጥቶ የትምህርት ዕድሉ እስኪገኝ ድረስ በአብነት ትምህርት ቤት ከየኔታዎቻች ተምረው ማንበብ፣ መጻፍን፣ቁጥር ማስላት መለማመድ አለባቸው። 🎤በሥሁት ትርክት የተጠለፉት ግን ከትናንት እስከ ዛሬ የሀገር እና የቤተ ክርስቲያን መልካም እና ርቱዕ የሆኑ ሀብተ-ትምህርቶችን አይፈልጓቸውም። አለዚያም በጣሊያን ወለድ ድረታ የደብተራ ዕውቀት እያሉ ያጣጥሏቸዋል።ደብተራ የትምህርት ሚንስተር ሁኖ የሠራት፣ የጠበቃት፣ ያቆያትን ሀገር መሆኗን ስለዘነጉት "ድንቡልቡል መሀይምነታቸው"ሊገልጹብን ይሞክራሉ። 🎤በዚህ መንገድ "ዘመናዊ ፊት ኋላ ቀር ልቦች"በማያባራ ትርክትና ትችት እየነዘነዙ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ያናንቋቸዋል ያጠፏቸዋል። 🎤እውነተኛውን መንገድ ከሚያመክኑባቸው ነገሮች አንዱ ትውልዱን ያለ ዕረፍት በሰላም እጦች፣በድረታ ትርክት፣በሥሁት ሥርዓት፣ በመነዝነዝ ማሰላቸት ማፍዘዝ እና ራስ ጠል አድርጎ ከርቱዕ ሀገር በቀል እሳቤው ጋራ ማጣላት ነው። 🎤ከመሠረቱ፣ከጥንቱ፣ከአብነቱ እየለዩ የትውልዱን ህሊናቸውን ብኩን ተግባሩን ትኑን ብኑን ማድረግ ተገቢ አይደለም አልነበረም።በጭፍን ግልበጣ የተዋስነው ያደረሰብንን የማያውቅ የለም ማለት ይቻላል። "ጥንቱን የተውሶ ያውም ጠፋ ተጨርሶ"እንዲሉ። 🎤የባከነ ህሊና እና የተነነ ተግባር ሀገር የለውም፣ሃይማኖት የለውም፣ሥርዓት የለውም፣ሞራል የለውም፣ሰብአዊነት የለውም፣ኪዳን የለውም፣ባህል የለውም፣ ወግ መዕረግ የለውም፣መረጋጋት የለውም፣ዕውቀት የለውም፣ተተኪ ትውልድ የለውም..። 🎤በድርት ስሁት ሀሳባቸው እና ዕቅዳቸው ወደ ጥንተ መሠረታችን እንዳናይ፣ከትምህርት ከመሠረት እንድንፋታ የሚፈልጉ በለ ጊዜዎች በሚያመጡት የመከራ ዜና ጧት መነዝነዝ፣ማታም መነዝነዝ፣ነገም መነዝነዝ፣በቃ ነገር እየፈለጉ መነዝነዝ ዕረፍት ማሳጣት ማባከን ማዋከብ ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። 🎤ስለሆነም በችግር ዘመን ያልሠራነውን ትውልድ በሰላም ዘመን ትክክለኛ ሰው ሁኖ አናገኘውም። 🎤መፍትሄው ከጥፋት በላይ የሆነ፣መሠረተ-ዕውቀት ያለው፣ ራስ በቅ የሆነ፣ሁሉን መመዘን የሚችል፣ በራሱ የማያፍር፣አዲስ ተቸኪ ትውልድ በአብነት ትምህርት በሀገር በቀል ዕውቀት መቅረጽ ነው። 🎤ከመሠረቱ የተፋታ ትውልድ ግን ጽኑዕ ሃይማኖት፣ የተረጋጋ ሀሳብ፣ሀገር በቀል ዕቀት፣መልካም ሰብእና፣ትሁት እና ጠቢብ ሰውነት..አይኖረውም። 🎤ሀገር በቀል ዕውቀት የሌለው ሰው ልቡን የተበላ ሰው ነው።ማሰቢያ ልቡን የተበላ ትውልድ ደግሞ መዳረሻው ጉጻጉጽ ነው።መስተሀልይ ህሊናውን ከአብነት አፋትቶ አንተ እለቅ እኔ ላጥልቅ፣አንተ ጥፋ እኔ ላናፋ የሚል ሰው መዳረሻው ወና ነው። 🎤ተተኪውን ትውልድ ከመሠረቱ እያነጹ መተካት እና ማውጣት ካልተቻለ፦ዛሬ በትቂቱም ቢሆን ጽኑዕ ሃይማኖት፣ መልካም ሰብእና፣ቋሚ ጠቃሚ ሀሳብ፣ቅን ህሊና ያላቸው ሰዎችም ከንዝነዛው ብዛት የተነሣ መሰላቸት መፋዘዝ መደንዘዝ ያገኛቸዋልና መንገድ የሚያሳይ ጠፍቶ ጨርሶ መናድ መውደም ሊመጣ ይችላል። 🎤በሥሁት እሳቤ ከሚፈልቀው ንዝናዜ ብዛት የተነሳ አብነት የሚሆነውን አባት እና የህሊና ዕረፍት ያጣ ምእመን ደግሞ ከአስጨኛቂ ጫጫታዎች ሁሉ ለመራቅ ሲል የሚያደርገው የስደት ሽሽት፣የማስመሰል ኑሮ፣የህሊና መታወክ፣ሀገርንም ቤተ ክርስቲያንንም ይጎዳታል። 🎤የአንዱ ዳፋ ሌላውንም ያዳፋልና የአንዱ ንዝነዛ ወደ ሁሉም ምእመናን ይጋባና አዚም በሚመስል መልኩ ብዙዎቻች ንዝነዛው ሰልችቶን ከርቱዓዊ መንገዱ እንዳንወጣ ወሳኙ ጠጋኙ አብነት ትምህርት ነው። 🎤ሚልዮን ብራናዎች፣የተራቀቁ ቅኔዎች፣የለዘቡ ዜማዎች፣የተቀደሱ ባህሎች፣ተሻገሪ ቀመሮች፣ምሥክር የሚሆኑን ውቅሮች፣የርቱዓዊነት መገለጫዎች፣ትናንታዊ ታሪኮች፣ሀገር በቀል ፍልስፍናዎች፣ጣዕም ያላቸው የአባቶች ጫወታዎች፣...የአብነት ፍሬዎች ናቸው። 🎤አብነት ትምህርታችን የትናንት ማያ፣  የነገ ማስያ፣ የዛሬም መዋያ ነው።በራሳችን ዐይን ወደ ኋላ ማየት እና ለነገም መተንበይ የሚቻለው በአብነት መረዳት ውስጥ ተሁኖ ነው። 🎤ስለሆነም ሁሉም ሕጻናት እና ጊዜ ያለን ወጣቶች በሙሉ ክረምቱን በአብነት ማሳለፍ መቻል አለብን። ያልሰማ እንዳይኖር በየአካባቢያችን እንቀስቅስ።         🎤(ክረምቱን በአብነት)🎤

ተአምኆ ቅዱሳን ወግጻዌ (የቅዱሳን ሰላምታ) Teamho Kidusan Wegtsawe (Yekidusa Selamta) Saints Of The Orthodox Tewahedo Church.: ❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤            ❤ #ሰኔ_፲፭ (15) ቀን። ❤ እንኳን #ለታላቁ_ሰማዕት_ለሰማይ_ጭፍራ ለተባለ #ለቅዱስ_ሚናስ_ቤተ_ ክርስቲያን_መርዩጥ በተባለ አገር #ለከበረችበት_ለቅዳሴ_ቤቱ_በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                         ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የቅዱስ_ሚናስ_ቤተ_ክርስቲያን_ቅዳሴ_ቤት፦ ከዚህ አስቀድሞ የቅዱስ ሚናስ ሥጋ ተሠውሮ ይኖር ነበር ጌታችንም ሊገልጠው በወደደ ጊዜ ምክንያት አደረገ ይኸውም እንዲህ ነው ቅዱስ ሚናስ ሥጋው ተደፍኖ በሚኖርበት ኮረብታ አቅራቢያ በጎችን የሚያረባ አንድ ሰው በጎቹን እየጠበሸ ይኖር ነበር። ከዚያ እረኛ በጎች ውስጥ ደዌ ያለበት አንዱ በግ በዚያ በኮረብታው አጠገብ ባለ የጒድጓድ ውኃ ተጠምቆ ወዲያውኑ ከደዌው ዳነ እረኛውም አይቶ አደነቀ ሌሎችንም ደዌ ያለባቸውን አመጣ በዚያ ውኃም በታጠቡ ጊዜ ሁሉም ዳኑ። ❤ ከዚህም በኋላ ይህ በቦታው ሁሉ ታወቀ ደዌ ያለባቸውም ሁሉ እየመጡ አፈሩን ከውኃው ጋራ አንድ አድርገው ለውሰው በመቀባት ወዲያውኑ ይድኑ ነበሩ ምክንያቱን ግን አላወቁም። በዚያ ውኃና በአፈሩ በሽተኞችን እንደሚያድን የዚያ በግ ጠባቂ ወሬው በሮሙ ንጉሥ ዘንድ ተሰማ ለንሡም የቊስል ደዌ የታመመች ልጅ ነበረችው ወደ በግ ጠባቂውም ላካት እርሱም በጎቹን እንደ አዳናቸው አዳናት። እርሷም በተፈወሰች ጊዜ ከዚያ ቦታ ፈውስ የሚደረግበትን ምክንያት ታውቅ ዘንድ ወደደች። ❤ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ሚናስ በሕልም ተገለጸላትና ሥጋዬ በዚህ ቦታ ተደፍኖ ስለሚኖር እነሆ አስቆፍረሽ ታወጪው ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል" አላት። ከእንቅልፍም በነቃች ጊዜ ቅዱስ ሚናስ እንዳዘዛት አደረገች የከበረ ሥጋውንም አወጣች በዚያም ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ሠራችለት ንጉሡም በዚያ ቦታ ከተማ እንዲሠሩ መኳንንቱንና ሹሞቹን አዘዛቸው ታላቅ ከተማም ተሠራች ስሟም መርዩጥ ተባለች። ❤ እግዚአብሔር ከቅዱስ ሚናስ ሥጋ ቊጥር የሌላቸው ድንቆችንና ተአምራትን ገለጠ። ሊቀ ጳጳሳቱም ከኤጲስቆጶሳቱ መጥቶ ቤተ ክርስቲያኒቱን በዛሬዋ ሰኔ 15 ዕለት አከበራት በዚያቺም ቦታ የሚሠሩ የድንቆችና የተአምሮች ወሬ በቦታው ሁሉ ተሰማ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚናስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ15 ስንክሳር።                          ✝️ ✝️ ✝️ ❤ "#ሰላም_ለቅዳሴ_ቤትከ እንተ ተሐንፀት በመርዩጥ። በትእዛዝ ንጉሥ ሥሉጥ። #ሚናስ ዘአንቃሕከ በድነ ሐራውያ እምጸጥ። አስተዋጺኦሙ ዕደው ዘበበ፪ቱ ቂራጥ። መባአ ለከ ዘነሥኡ በሤጥ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የሰኔ_15።                            ❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤ ❤ እንኳን #ለሐዋርያት_ሰኔ_ጾም_ሁለተኛ_ሳምንት #ስለ_ዕርገቱና_ስለ_ጰራቅሊጦስ ለሚነገርበት ዕለተ ሰንበት እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዚህ_ሳምንት_መዝሙር፦ሃሌ ሉያ በ፫ "#ዐረገ_እግዚአብሔር_በቃለ ቀርን #በይባቤ_ዐርገ ወበቃለ ቀርን ወነበረ በየማነ አቡሁ (ዐርገ) አዝ፣ #ዐርገ_በስብሐት_ውስተ_ሰማያት ተኰነኑ ሎቱ መላእክት (ዐርገ) አዝ፣ ተኰነኑ ሎቱ መላእክት ኵሉ ኃይል ወኵሉ ፍጥረት (ዐርገ) አዝ፣ ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ ለንጉሥነ። ትርጉም፦ እግዚአብሔር በመለከት #ድምፅ_ዐረገ በዕልልታና #በመለከት_ድምፅ ዐረገ፤ በአባቱ ቀኝ ተቀመጠ፤ በክብር በምስጋና በጌትነት #ወደ_ሰማያት_ዐረገ፤ መላእክት ተገዙለት ኃይል ሁሉ ፍጥረት ሁሉ ተገዙለት፤ ለአምላካችንም ዘምሩ፤ አመስግኑ ለንጉሣችን ዘምሩ አመስግኑ። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በድጓው_ላይ።                         ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዚህ_ሳምንት_የዕለቱ_ምስባክ፦ "ኢትግድፈኒ እምቅድመ ገጽከ። ወመንፈስከ ቅዱሰ ኢታውፅእ እምላዕሌየ። ዕሥየኒ ፍሥሓ ወአድኅኖትከ። መዝ 50፥11_12። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 14፥1-27፣ 1ኛ ዮሐ 4፥1-9፣ የሐዋ ሥራ 10፥11-44። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 15፥17-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ። መልካም ዕለተ ሰንበትና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን

❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። ❤             ❤ #ሰኔ ፲፬ (14) ቀን። ❤ እንኳን #ለቅዱሳን_አባ_አክራና_ለዮሐንስ፣ #ለአብጥልማና_ለፊልጶስ_ሰማዕትነት_ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓል በሰላም አደረሰን። ከእነዚህ ቅዱሳን እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።                         ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #ቅዱሳን_አባ አክራ_ዮሐንስ_አብጥለሰማና ፊልጶስ፦ ይህም ቅዱስ አክራ ከግብጽ ደቡብ ይምንሑር ከሚባል አገር ሰዎች ወገን ነው ስሙ ፊልጶስ የሚባል ወንድም ነበረው እነርሱም ባለጸጎች ነበሩ ስማቸው ዮሐንስና አብጥልማ ከሚባል ሁለት ቀሳውስት ጋራ ሰማዕታት ይሆኑ ዘንድ ተስማሙ አራቱም ቀርጥስ ወደሚባል አገር ሔዱ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በመኰንኑ ፊት ታመኑ። መኰንኑም በቀስቶች እንዲነድፏቸው አዘዘ ግን ቀስቶች አልነኳቸውም። ሁለተኛም እሳትን አንድደው በሚነድ የእሳት ምድጃ ውስጥ ይጨምሩአቸው ዘንድ አዘዘ እንዲሁም አደረጉባቸው ጌታም መልአኩን ልኮ አዳናቸው። ❤ ከዚህም በኋላ በፈረስ ጅራት ላይ አሥረው ከቀርጥስ ከተማ እስከ ይምንሑር አገር ድረስ ይጐትቷቸው ዘንድ አዘዘና ይህንንም አደረጉባቸው ግን ምንም ምን ጉዳት አልደረሰባቸውም። ከዚህም በኋላ ራሶቻቸውን በሰይፍ እንዲቆርጧቸው አዘዘ ከይምንሑር ከተማም አውጥተው ራሶቻቸውን ሰኔ 14 ቀን ቆረጡአቸው። ❤ ፃ ከሚባል አገር ሰዎች መጥተው የቅዱስ አባ አክራን ሥጋውን ወሰዱ ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንም ሠርተው ሥጋውን በውስጧ አኖሩ ከእርሱም ታላላቅ ድንቆችና ተአምራት በብዛት ተገለጠ። ❤ እንዲሁም የእነዚያን የሦስቱን ቅዱሳን የፊልጶስን፣ የአብጥልማንና የዮሐንስን ሥጋቸውን ከይምንሑር ከተማ ሰዎች መጥተው ወሰዱ በመልካም ልብሶችም ገንዙአቸው ጥሩ ቤተ ክርስቲያንም ሠርተው ሥጋቸውን በውስጧ አኖሩ ከእነርሳቸውም ቊጥር የሌለው ድንቅ ተአምር ተገለጠ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእሊህ በቅዱሳን ሰማዕታት በአባ አክራና ዮሐንስ፣ አብጥልማና ፊልጶስ በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸው ከእኛ ጋራ ለዘላለም ይኑር አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ14 ስንክሳር።                          ✝️ ✝️ ✝️ ❤ "#ሰላም_ለአብጥልማ_ወፊልጶስ_አብያጽ። ዮሐንስ ወአክራ ዘደቡብ ግብጽ። አመ ቆሙ ለስምዕ በዐውደ መኰንን ስሑጽ። እግዚአብሔር ባልሖሙ እምዘ ይሰርር ሐፅ። ወአድኃኖሙ ካዕበ እምእሳት ብቊፅ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ(አርኬ) #የሰኔ_14።                           ✝️ ✝️ ✝️ ❤ #የዕለቱ_ምስባክ፦ "ወይርአዩ አሕዛብ በቅድመ አይንቲነ። በቀለ ደሞሙ ለአግብርቲከ ዘተክዕወ። ይባእ ቅድሜከ ገዓሮሙ ለሙቁሓን"። መዝ 78፥10-11። የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 12፥7-15፣ 2ኛ ጴጥ 2፥9-14 እና የሐዋ ሥራ 27፥1-7። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 21፥12-14። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱሳን የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ መልካም በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።

ሰኔ ሚካኤል በደብረ አባይ
+9
ሰኔ ሚካኤል በደብረ አባይ